5. መትጋት
“ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ፥ በዚያም ቀን ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስ ተጨመሩ፤ በሐዋርያትም ትምህርትና በኅብረት እንጀራውንም በመቍረስ በየጸሎቱም ይተጉ ነበር።" (ሐ.ሥ. 2:41-42)
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለመሰብሰብ ሲያስተምር “ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና” ብሏል (ማቴ. 18:20)፡፡ ይህም ቃል እርሱ ከደቀመዛሙርቱ ጋር በአካል እያለ ስለነበራቸው መሰብሰብ ሳይሆን እርሱ በአካል ከእነርሱ ከተለየ በኋላ በስሙ ስለሚያደርጉት መሰብሰብ የተናገረው ነው፡፡ ስሙ የእርሱን ማንነት የሚወክል በመሆኑ የእርሱ የሆኑት ሁሉ እርሱን ብቻ ማዕከል አድርገው መሰብሰባቸውን ያመለክታል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም በእርሱ ስም ማለት እርሱን ምክንያት አድርገው በሚሰባሰቡት ደቀመዛሙርቱ መካከል እንደሚገኝ በተግባር ያረጋገጠው ከሙታን በተነሣ ዕለት ከሳምንቱ ፊተኛው ቀን በመሸ ጊዜ ደጆቹን ዘግተው በተሰበሰቡት ደቀመዛሙርቱ መካከል ቆሞ ሰላም ለእናንተ ይሁን በማለት ነበር (ዮሐ.20፡19)፤ እርሱ ካረገ በኋላም በሚኖሩበት ሰገነት ውስጥ በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት በመትጋት (የሐ.ሥ.1፡13-14) የቀጠለው ይህ የደቀመዛሙርቱ መሰባሰብ በበዓለ ሃምሳ ዕለት መንፈስ ቅዱስ በወረደላቸው ጊዜ መለኮታዊ ዕውቅናን አግኝቷል፡፡ በዚያም ዕለት ጌታ በእነርሱ ላይ ሦስት ሺህ የሚያህሉ አማኞችን ከጨመረ በኋላ በቀጣይ ዘመናቸው በአንድነት እየተሰባሰቡ የሚተጉባቸውን አራት ነገሮች ተነገራቸው፡፡ በዚህ ዘመንም የአምልኮ መልክ ካለው ሥርዓተ ሃይማኖት የተለየንና በመጀመሪያ ላይ ወደነበረው በጌታ በኢየሱስ ስም ወደመሰብሰብ የተመለስን አማኞች በእነዚህ አራት ነገሮች ልንተጋ ይገባናል፡፡
“መትጋት” አንድን ነገር በመደበኛ ሁኔታ ዘወትር በጽናት ማድረግን የሚያመለክት ቃል ነው፡፡ በመሆኑም እነዚህ አራት ነገሮች አማኞች እየተሰባሰቡ በመደበኛ ሁኔታ ሁል ጊዜ የሚፈጽሟቸው መንፈሳዊ ክንዋኔዎች ናቸው፡፡ እነርሱም፡
- በትምህርት መትጋት
- በኅብረት መትጋት
- እንጀራውን በመቁረስ መትጋትና
- በየጸሎቱ መትጋት
ሲሆኑ በዚህ ጽሐፍ ውስጥ እያንዳንዳቸውን በዝርዝር እንመለከታቸዋለን፡፡