የቤተክርስቲያን ማንነት
የቤተክርስቲያን መሠረት
የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻዎች
የቤተክርስቲያን ሥልጣን
በስሙመሰብሰብ
ቤተክርስቲያን[Assembly]
በክርስትና ስም በሚጠራው ዓለምም ሆነ ክርስቲያን ባልሆነው ዓለም «ቤተክርስቲያንን» በተመለከተ ያለው መረዳት መጽሐፍ ቅዱስ ከሚነግረን እውነት ጋር በሚፋለስበት በዚህ ዘመን ስለ ቤተክርስቲያን ያለውን ትክክለኛ ሐሳብ ማወቅ በብዙዎች ዘንድ የሚናፈቅ ሆኗል፡፡ በብዙ የዶክትሪን አስተሳሰቦች እና ሥርዓተ አምልኮዎች የሚለያዩና በተለያዩ ስያሜዎች የሚጠሩ አብያተ ክርስቲያናት በበዙበት በዚህ በያዝንው ክፍለዘመን የቤተክርስቲያንን ትክክለኛ ማንነት ለማወቅ የተጠማውን የሰዎችን ኅሊና የሚያረካ እውነት መገኘት የሚችለው ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ከተጻፈው ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወደ 150 ጊዜ ያህል ተጠቅሶ የሚገኝ በመሆኑ የቤተክርስቲያን ትክክለኛ ገጽታ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በስፋት ይገኛል፤ የመንፈስ ቅዱስን ምስክርነት በውስጥ ጆሮአችን እያዳመጥን ብናነበው ስለ ቤተክርስቲያንም ሆነ ስለሌሎች ታላላቅ መንፈሳውያን ርእሶች የተገለጠ እውነትን እናገኝበታለን፡፡
የቤተክርስቲያን ማንነት
«ቤተክርስቲያን» የሚለው ቃል በግሪክ ቋንቋ «ኤክሌሲያ» ለሚለው ቃል የተሰጠ ትርጉም ሲሆን ኤክሌስያ ማለትም «የተጠራች ጉባዔ» ማለት ነው፡፡ በግእዝም ቤተክርስቲያን የሚለው ቃል የክርስቲያን ቤት የሚል ፊደላዊ ፍቺ ቢኖረውም ዋነኛ ሐሳቡ «የክርስቲያን ወገን» ማለት ስለሆነ ኤክሌስያ የሚሰጠንን ስሜት በተወሰነ ደረጃ ይዟል፤ በብሉይ ኪዳን ዘመን በምድር ላይ የነበረችው በእግዚአብሔር የተመረጠች ጉባዔ ቤተእስራኤል ነበረች፡፡ ይህችም ጉባዔ ማለትም እስራኤል፣ ኤክሌሲያ ተብላ የተጠራችበትን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ እናገኛለን/የሐ.ሥ.7፡38/፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአሕዛብ አገርም በአንድ ምክንያት የሚሰበሰብ ትልቅ ጉባዔ ኤክሌስያ ይባል ነበር/የሐ.ሥ.19፡3/፡፡ እነዚህ በቤተ እስራኤልም ሆነ በቤተ አሕዛብ የነበሩት ጉባዔያት ምድራውያን ሲሆኑ በወንጌል ቃል በኩል ከዚህ ዓለም የተጠሩት ክርስቲያኖች ጉባዔ /ኤክሌስያ/ ግን ሰማያዊ ባሕርይ ያላት ጉባዔ ናት፤ ሐዋርያው ጳውሎስ «... ብዙ ልዩ ልዩ የእግዚአብሔር ጥበብ አሁን በቤተክርስቲያን በኩል በሰማያዊ ስፍራ ውስጥ ላሉት አለቆችና ሥልጣናት ትታወቅ ዘንድ...» /ኤፌ3፡10/ ብሎ ከጻፈው ቃል ውስጥ ይህንን የቤተክርስቲያንን ሰማያዊ ባሕርይ እንረዳለን፡፡ በብሉይ ኪዳን የነበረችው የተጠራች የእግዚአብሔር ጉባዔ በሥጋ ከአብርሃም ዘር የሆኑትን ብቻ ያካተተች ጉባዔ ነበረች፡፡ በአዲስ ኪዳን ያለችው የእግዚአብሔር ጉባዔ (ኤክሌስያ) ግን ከቤተ እስራኤል ብቻ ሳይሆን ከቤተ አሕዛብም የሆኑትን ወገኖች ያቀፈች ጉባዔ ናት፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ «ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆችን ሊያስነሣለት እግዚአብሔር ይችላል» ብሎ «አብርሃም አባት አለን» እያሉ ለሚመኩት ፈሪሳውያን በተናገረው መሠረት /ማቴ.3፡9/ ከቤተ አሕዛብ መካከል በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑ ሁሉ የአብርሃም ልጆች ለመሆን ችለዋል፡፡ ጳውሎስም ክርስቶስ ኢየሱስ በእንጨት ላይ የተሰቀለው አሕዛብን በእርሱ በኩል ወደ አብርሃም በረከት ውስጥ ለማስገባት እንደሆነ ሲናገር «በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፏልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን የመንፈስን ተስፋ በእምነት እንድንቀበል የአብርሃም በረከት ወደ አሕዛብ በእምነት ይደርስላቸው ዘንድ» ብሏል /በገላ.3፡14/፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን የመሠረተው ከቤተ እስራኤልና ከቤተ አሕዛብ በተጠራ አዲስ ሕዝብ ነው፡፡ በመስቀል ላይ የመሞቱም ዓላማ ይህንኑ አዲስ ሕዝብ ይፈጥር ዘንድ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ሲገልጥ «እርሱ ሰላማችን ነውና ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳ በሥጋው ያፈረሰ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው» ይላል/ኤፌ.2፡11-16/፡፡ ከዚህም እንደምንረዳው በአዲስ ኪዳን ሰዎችን የእግዚአብሔር ሕዝብ የሚያደረገው በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ነው እንጂ እስራኤላዊ እና አሕዛባዊ የመሆን ጉዳይ አይደለም፡፡ ስለዚህ የቤተክርስቲያን አባላት ከፀሐይ መውጫ እስከ ፀሐይ መጥለቂያ ድረስ ካሉት ነገዶች ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ በእውነት ያመኑት ሁሉ ናቸው፡፡
በመሆኑም «በአይሁዳዊና በግሪክ ሰው መካከል ልዩነት የለምና፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፤ ለሚጠሩትም ባለጠጋ ነው፤ የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና» /ሮሜ.10፡12/ የሚለው ቃል የገባቸው አማኞች በምድራቸውም ሆነ በሌሎች የውጭ አገሮች ውስጥ ሰዎች በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው መሰብሰባቸውን ይናፍቃሉ፤ እንዲህ ያሉት አማኞች በዓለም ካሉት ነገዶች ሁሉ ሰዎች በክርስቶስ አምነው በስሙ የመሰባሰባቸውን ዜና ሲሰሙ ደስታና መንፈሳዊ ሐሴት ይሞላባቸዋል፡፡ እንደዚሁም በዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ እንደተመዘገበው የምስጋና ቃልም «መጽሐፉን ትወስድ ዘንድ ማኅተሙንም ትፈታ ዘንድ ይገባሃል፤ ታርደሃልና በደምህም ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ሰዎችን ዋጅተህ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው፤ በምድርም ላይ ይነግሣሉ» እያሉ በጉን /ጌታ ኢየሱስን/ ያመሰግኑታል /ራእ.5፡9/፡፡
«ቤተክርስቲያን» የሚለው ቃል ከሕዝብና ከአሕዛብ መካከል እግዚአብሔር የጠራቸውንና የመረጣቸውን የአዲስ ኪዳን አማኞችን ጉባኤን የሚያመለክት ሆኖ ሳለ ክርስቲያኖች ለመንፈሳዊ ጉዳዮች የምንሰበሰብበትን ቦታ ወይም አዳራሽ እንደዚሁም ራሳችን ስም አውጥተን የፈጠርነውን የእምነት ድርጅት እንዲያመለክት አድርገን መጠቀም ከቃሉ ቀጥተኛ ትርጉም ውጭ መሆን ነው፡፡ እግዚአብሔር ቤተክርስቲያኑን የዋጃት በገዛ ደሙ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ሲያስረዳ «... በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ ...» ይላል /የሐ.ሥ.20፡28/፡፡ ቤተክርስቲያን ሕንፃ ወይም ድርጅት ከሆነች ደግሞ ክርስቶስ ለሕንፃ ወይም ለድርጅት ሞቷል ማለት ሊሆን ነው፤ ሆኖም በመጽሐፍ ቅዱስ ቤተክርስቲያን የሚለው ቃል በሚገኝበት በማናቸውም ጥቅስ ውስጥ በምድር ላይ ሰማያዊ ጠባይን ተላብሳ የምትገኘውን የተመረጠች የእግዚአብሔርን ጉባዔ ከማመልከት በቀር በአንድም ስፍራ ሕንፃን ወይም ድርጅትን አያመለክትም፡፡ እንዲህ ሲባል ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን ለማምለክና ቃሉን ለመስማት የሚሰባሰቡበት ቤት እንዲሁም እንደ የአገሩ ሕግ ለመሰብሰብ ሆነ ለሕዝብ መንፈሳዊ አገልግሎትን ለመስጠት የሚያስችላቸውን መንፈሳዊ ድርጅት ማቋቋም አይችሉም ማለት አይደለም፤ ይሁን እንጂ ሕንፃውም «ሕንፃ»፣ ድርጅቱም «ድርጅት» ሊባል ይችላል እንጂ «ቤተክርስቲያን» ሊባል አይችልም፡፡ ለምሳሌ በፊልሞና ቤት ውስጥ ትሰበሰብ ስለነበረችው ቤተክርስቲያን በፊልሞና መልእክት መግቢያ ላይ «በቤትህም ላለች ቤተክርስቲያን» የሚል ቃል እናነባለን /ፊል.2/፡፡ በዚህ ንባብ ውስጥ ቤተክርስቲያን በፊልሞና ቤት ስለተሰበሰበች የፊልሞና መኖሪያ ቤት «ቤተክርስቲያን» ተብላ እንዳልተጠራች እናያለን፤ በዚያ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ለቤተክርስቲያን መሰብሰቢያ ተብሎ ሕንፃ መሥራትም አልተጀመረም ነበር፡፡ ቤተክርስቲያን ትሰበሰብ የነበረው ከአማኞች መካከል ቤታቸውን ለዚህ አገልግሎት በሰጡ ወይም በፈቀዱ ሰዎች ቤት ውስጥ ነበር፡፡ ለምሳሌ የማርቆስ እናት ማርያም በኢየሩሳሌም/የሐ.ሥ.12፡5-12/፣ አቂላና ጵርስቅላ በሮሜ /ሮሜ16፡3-5/፣ ፊልሞና በቈላስይስ /ፊልሞ2፣11፤ ቈላ.4፡9/፣ ንምፉን በሎዶቅያ /ቈላ.4፡15/ ቤታቸውን ለቤተክርስቲያን መሰብሰቢያ እንዲሆን ከፈቀዱት መካከል የሚጠቀሱ /ቅዱሳን/ ሰዎች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ በቤታቸው የምትሰበሰበው የምእመናን ኅብረት ቤተክርስቲያን ተባለች እንጂ የአንዳቸውም መኖሪያ ቤት «ቤተክርስቲያን» ተብሎ አልተጠራም፡
የቤተክርስቲያን መሠረት
ቤተክርስቲያን የሚለው ቃል ትርጉሙ ምን እንደሆነ ከተመለከትን አሁን ደግሞ ቤተክርስቲያን የተመሠረተችበት መሠረት ምን እንደ ሆነ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እናያለን፡፡ ማንኛውንም መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ከመሠረቱ ጀምረን ካላወቅን የሚኖረን መረዳት የተሟላ ካለመሆኑም በላይ ጣልቃ በሚገቡ የሰው ሐሳቦች ምክንያት በተሳሳተ መንገድ ልናስብም እንችላለን፡፡ እያንዳንዱ እውነተኛ አማኝ የቤተክርስቲያን አባል እንደመሆኑ መጠን ትክክለኛ ስፍራውን ያውቅ ዘንድ ይህንን ጽኑ የሆነ የቤተክርስቲያን መሠረት አጥብቆ ሊረዳ ይገባዋል፡፡ የሁላችንንም ትኵረት በእጅጉ የሚስበውን ይህንን የቤተክርስቲያን መሠረት የሚያሳውቀን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ የሚገኘው «ቤተክርስቲያን» የሚለው ቃል በአዲስ ኪዳን ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ተጽፎ በሚገኝበት በማቴ.16፡13-18 ውስጥ ነው፡፡ ይህም ክፍል እንደሚከተለው ይነበባል:-
«ኢየሱስም ወደ ፊልጶስ ቂሳርያ አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን:- የሰውን ልጅ ማን እንደሆነ ይሉታል? ብሎ ጠየቀ፤ እነርሱም:- አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ ሌሎችም ኤልያስ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት፡፡ እርሱም:- እናንተስ እኔን ማን እንደሆንኩ ትላላችሁ? አላቸው፡፡ ስምዖን ጴጥሮስም:- መልሶ አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ፡፡ ኢየሱስም መልሶ:- የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ፡፡ እኔም እልሃለሁ አንተ ጴጥሮስ ነህ በዚህችም ዓለት ላይ ቤተክርስቲያኔን እሠራለሁ የገሃነም ደጆችም አይችሏትም» ይላል፡፡
በዚህ ክፍል ውስጥ እንደተገለጠው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «... በዚህችም አለት ላይ ቤተክርስቲያኔን እሠራለሁ፤ የገሃነም ደጆችም አይችሏትም ...» ብሎ ሲናገር እንሰማዋለን/ቊ.18/፡፡ ጌታችን ይህንን ቃል የተናገረው የ3ቱን ዓመት የማስተማር ዘመኑን እያጠናቀቀ ሳለ ወደ ኢየሩሳሌም ለመጨረሻ ጊዜ ከመውጣቱ በፊት በፊልጶስ ቂሣርያ እያለ እንደነበር የዚህን ንባብ ምዕራፍ ስናጠና እንደርስበታለን/ቊ.21/፡፡ በዚያ ጊዜ ጌታ ኢየሱስ «ቤተክርስቲያኔን እሠራለሁ» ብሎ በትንቢታዊ ቃል መናገሩ በጊዜው ገና ቤተክርስቲያን ተሠርታ እንዳልነበረ ያመለክተናል፡፡ በእርግጥም በደሙ በሚደረግ ቤዛነት ሕዝብን ከነገድ ከቋንቋ ሳይዋጅ ቤተክርስቲያን ልትሠራ እንዴት ትችላላች? ቤተክርስቲያንን በገዛ ደሙ እንደዋጃት የሚያስረዳ ግልጽ ንባብ እናገኛለንና/የሐ.ሥ.20፡28/፡፡ ስለዚህ በክርስቶስ ሞት የኃጢአት ዕዳ ከመከፈሉ በፊት ቤተክርስቲያን እንዳልተሠራች ልንገነዘብ እንችላለን፡፡
አሁን ደግሞ የቤተክርስቲያንን መሠረት በተመለከተ «...በዚህችም አለት ላይ ቤተክርስቲያኔን እሠራለሁ የገሃነም ደጆችም አይችሏትም...» ብሎ ጌታችን በተናገረው ቃል ውስጥ ያሉትን ሁለት ዋና ዋና ኃይለ ቃላትን እንመልከት፡፡
1. በዚህችም ዓለት ላይ
ጌታ ኢየሱስ ቤተክርስቲያኑን የሚሠራበትን መሠረት ሲገልጥ «በዚህችም ዓለት ላይ ቤተክርስቲያንን እሠራለሁ» ብሏል፡፡ ከዚህም ቃል የቤተክርስቲያን መሠረት «ዓለት» እንደሆነ እንረዳለን፡፡ በማቴ7፡24-27 የተመዘገበውን የጌታችንን ምሳሌ ስናነብ ልባም ሰው ቤቱን በዓለት ላይ እንደሚሠራና ያንንም በዓለት ላይ የተመሠረተ ቤት ዝናብ ቢወርድም ጐርፍ ቢመጣም ነፋስ ቢነፍስም ፈጽሞ ሊወድቅ እንደማይችል ያስረዳል፡፡ በተቃራኒው ግን ሰነፍ ሰው የሚሠራው በአሸዋ ላይ የተመሠረተ ቤት ዝናብ ሲወርድ ጐርፍ ሲመጣ ነፋስም ሲነፍስ ታላቅ አወዳደቅ እንደሚወድቅ ይገልጻል፡፡ ከዚህ አንፃር ስንመለከተው ኢየሱስ ክርስቶስ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ «ልባም ሰው» ነው፡፡
«በዚህችም ዓለት ላይ...» የሚለውን ይህንን ቃል የሚያነቡ ሁሉ «ይህች ዓለት ምንድር ናት?» ብለው መጠየቃቸው የማይቀር ነው፡፡ ጌታችን ከዚህ ንባብ ቀደም ብሎ «አንተ ጴጥሮስ ነህ» ካለ በኋላ «በዚህችም ዓለት ላይ ቤተክርስቲያኔን እሠራለሁ» ብሎ መናገሩን በመመልከት በዚህ ንባብ ውስጥ ዓለት የተባለው «ጴጥሮስ ነው» የሚል የተሳሳተ መረዳት መኖሩ ይታወቃል፡፡ ይህም መረዳት ንባቡ የቀረበበትን ሰዋስው በተለይም የቃሉን ጾታ ካለማስተዋል የመጣ ነው፡፡ ጌታችን «አንተ ጴጥሮስ ነህ» የሚለውን ቃል የተናገረው በተባዕታይ ጾታ እንደሆነ ያስተዋለ አንባቢ «በዚህችም ዓለት» የሚለውን ቃል ሲያነብ ዓለቷ ጴጥሮስ ነው ማለት አይችልም፤ ይህ የተባዕታይንና የእንስታይን ጾታ ማደባለቅ ነው፡፡ በዚህ ፈንታ ግን ጌታችን «በዚህች» በሚለው ጠቋሚ ቃል በእንስታይ ጾታ የጠራት ዓለት ምንድናት? ብሎ በመጠየቅ ምላሹን ከዚሁ ንባብ ውስጥ ያፈላልጋል፡፡ በሰው ሐሳብ ሳይጠላለፍ በመንፈስ ቅዱስ በተቃኘ ኅሊና ሆኖ እሰካነበበ ድረስም ምላሹን በዚሁ አንቀጽ ውስጥ በቅርቡ ያገኛል፡፡ «በዚህች» በሚለው የቅርብ አመልካች ቃል የተጠቆመችው የዚህች ዓለት ምንነት ኢየሱስ ቃሉን በሚናገርበት በዚያው ሰዓት የተገለጠ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህም አንባቢው ዓይኖቹን ከፍ አድርጐ ወደ ቊጥር 16 ቢመለከት ጌታችን ስለማንነቱ ለደቀመዛሙርቱ ላቀረበው ጥያቄ ጴጥሮስ የመለሳትን አጭርና ግልጽ መልስ ያገኛል፡፡ እርስዋም «አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ» ብሎ በሥጋና በደም ሳይሆን በሰማያዊ መገለጥ የተናገራት ቃል ናት፡፡
በግሪክ ቋንቋ በዚህ ጥቅስ ውስጥ ጴጥሮስ የሚለው ቃል «petros/ፔትሮስ/» ተብሎ የተጻፈ ሲሆን ዓለት የሚለው ቃል ግን «petra/ፔትራ/» ተብሎ ተጽፏል፤ ይህም በሁለቱ ቃላት መካከል ግልጽ የሆነ የትርጉም ልዩነት እንዳለ ያሳያል፤ «ፔትሮስ» ማለት ከዓለት የተከፈለ ድንጋይ /ጡብ/ ማለት ሲሆን «ፔትራ» ማለት ራሱ ሙሉው ዓለት ነው፡፡ ጌታችንም ቤተክርስቲያኔን በፔትራ /በንጥፍ ዓለት/ ላይ እመሠርታለሁ አለ እንጂ በፔትሮስ /በጡብ/ ላይ እመሠርታለሁ አላለም፤ ስለሆነም የቤተክርስቲያን መሠረት «አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ» የምትለው የእምነት ቃል ናት እንጂ ጴጥሮስ አለመሆኑን አንባቢው ሊያስተውል ይገባል፡፡ ይህችም የእምነት ቃል ስለክርስቶስ የምትናገር ስለሆነ የቤተክርስቲያን መሠረት ራሱ ክርስቶስ ነው ቢባል ትክክል ነው፡፡ በ1ቆሮ.3፡11 ላይ ‹ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና፤ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው› ተብሎ ተጽፏልና፡፡
ይህንን ቃል የሕይወት መመሪያ ያደረገ ክርስቲያን እኔ የምሰበሰብበት መንፈሳዊ ጉባዔ የተመሠረተው በምን ላይ ነው? ብሎ በማስተዋል ሊመረምር ይገባዋል፡፡ በዘመናችን በየስፍራው የሚቋቋሙት ድርጅታዊ ገጽታ ያላቸው አብያተክርስቲያናት የቆሙበትን መሠረት በጥንቃቄ ልንመረምር ያስፈልጋል፡፡ ለቤተክርስቲያን ህልውና መሠረት የሆነውን «ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነው» የሚለውን የእምነት ቃል ወደ ጐን በመተው ወይም ትኩረት በመንፈግ፣ መሠረት ተደርገው ያልተነገሩትን ሌሎች መንፈሳውያን ትምህርቶችና ሥርዓቶች መሠረት ማድረግ አሳዛኙ የክርስቲያኖች ገጽታ እየሆነ መጥቷል፤ ከ4ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የሚታየውን የዓለማዊቷን ቤተክርስቲያን መለያየት ስንመለከት ዋነኛ ምክንያቱ ሥልጣንን፣ ጥቅምን፣ ክብርንና ማዕርግን ማስጠበቅ ቢሆንም ሰበብ የሆኑት መንፈሳዊ ምክንያቶች ግን፣ ክርስቶስ አንድ ባሕርይ ወይስ ሁለት ባሕርይ ነው?፣ ጥምቀተ ህፃናት ልክ ነው ወይስ አይደለም? ሥዕል ያስፈልጋል ወይስ አያስፈልግም? በጌታ እራት ጊዜ ኅብስቱና ወይኑ ወደ ሥጋና ደም ይለወጣል ወይስ አይለወጥም? የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ሲገለጡ እንዴት ነው? በልሳን መናገርና አጠቃቀሙን የምንረዳው እንዴት ነው? የቤተክርስቲያን አስተዳደር በሽማግሌዎች ወይስ በካህናት ይሁን? የሚሉትና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ «ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው» የሚለውን የቤተክርስቲያን መሠረት የማይተኩ ናቸው፡፡ በእነዚህ አርእስተ ጉዳዮች ያሉት እውነተኛ ትምህርቶችም ቢሆኑ ለቤተክርስቲያን እንደ ዋና መሠረት ታይተው ጉባዔ የሚመሠረትባቸው ቤተክርስቲያን የሚከፈልባቸው አዲስ ስም የሚወጣባቸው ምክንያቶች መሆናቸው አሳዛኝ ነው፡፡ ይሁንና ከዚህ አስተሳሰብ ተለይተው መሠረታቸውን በጥልቀት የተመለከቱ በሁሉም ስፍራ የሚገኙት የእውነተኛ ክርስትና ቅሬታዎች ግን ራሳቸውን «ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነው» በሚለው መሠረት ላይ ያገኙታል!!
2. የገሃነም ደጆች አይችሏትም
ልባም ሰው የሠራውንና በጽኑ ዓለት ላይ የተመሠረተን ቤት ዝናብ ወርዶ፣ ጐርፍ ጐርፎ፣ ነፋስ ነፍሶ ቢገፋውም ሊወድቅ እንደማይችል የተረጋገጠ ነው /ማቴ7፡24-25/፡፡ ዝናብ፣ ጐርፍና ነፋስ በክርስቲያኖች ላይ ስለ ወንጌል የሚደርስ ነቀፋን፣ ስደትንና የተለያየ መከራን እንዲሁም የስህተት ትምህርትን ሊያመለክቱ ይችላሉ፡፡ እነዚህም በጽኑ መሠረት በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የተመሠረተችውን የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን ቢገፏትም ሊጥሏት አይችሉም፡፡ ቤተክርስቲያንን በተመለከተ «የገሃነም ደጆች አይችሏትም» የሚል ጽኑ ቃል ከቤተክርስቲያን መሥራች ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ስንሰማ ልባችን በድል ስሜት ይሞላል፡፡
«የገሃነም ደጆችም አይችሏትም» በሚለው ባማርኛው ንባብ ውስጥ «ገሃነም» የሚለው ቃል በሌሎች ቋንቋዎች «ሲኦል» ተብሎ የተተረጐመው ቃል ነው፡፡ አዲስ ኪዳን በተጻፈበት በግሪኩ ቋንቋም ሆነ በእንግሊዝኛው፣ እንዲሁም በግእዙ ሲኦል ተብሎአል፡፡ «ሲኦል» የሚለው ቃል ከሞት ጋር የተያያዘ ትርጉም እንዳለው ግልጽ ነው/1ቆሮ15፡55/፤ ማለትም ሲኦል ኃጢአተኛ የሞት ፍርድን የሚቀበልበት የሥቃይ ስፍራ ነው/ሉቃ.16፡23/፡፡ ስለዚህ ዋነኞቹ የሲኦል ደጆች ሞትና መውጊያው ናቸው ቢባል ትክክል ነው፡፡ የሞትም መውጊያ ኃጢአት እንደሆነ ተጽፏል/1ቆሮ15፡56/፡፡ ቤተክርስቲያንን ግን እነዚህ የገሃነም ደጆች የሆኑት ኃጢአትና ሞት እንደማይችሏት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አረጋግጦ ተናገረ፡፡ የዚህም ምክንያቱ ቤተክርስቲያን የተመሠረተችበት ዓለት ማለትም «ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነው» የሚለው እውነት ጽኑዕ ስለሆነ ነው፤ ይልቁንም ኢየሱስን የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነው ብለው የሚያምኑ ክርስቲያኖች ሞትና መውጊያውን ሊፈሩት አይችሉም፤ ኢየሱስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ መሆኑን በመስቀል ላይ በሞተ በ3ኛው ቀን ከሞት በመነሣት በተግባር አረጋግጧልና/ሮሜ1፡4/፤ መላእክትም «ሕያውን ከሙታን መካከል ስለምን ትፈልጉታላችሁ?» ብለው በማለዳ ወደ ኢየሱስ መቃብር መጥተው ለነበሩ ሴቶች ተናግረዋል/ሉቃ.24፡5/፤ ሴቶቹም «ሕያው ነው የሚሉ የመላእክትን ራእይ አየን» እያሉ መስክረዋል/ሉቃ.24፡23/፤ ጌታችንም በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖ ለደቀመዛሙርቱ ራሱን አሳይቷቸዋል/የሐ.ሥ.1፡3/፡፡ ጴጥሮስም በመልእክቱ ውስጥ ሲጽፍ «በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ» በማለት ይናገራል/1ጴጥ.3፡18/፡፡ ኢየሱስ የሕይወት ምንጭ ስለሆነና ዘላለማዊ ሕይወት ያለው የአብ ልጅ በመሆኑ በዚህ የሕይወት ኃይል ከሙታን ተነሥቷል፡፡ ያ በአብ ያለው ሕይወት በእርሱም ነበር /ዮሐ1፡4/፤ ይህም ሕይወት መለኮታዊ ሕይወት ነው፤ ስለዚህ ፍጻሜ የሌለው ሕይወት ብቻ ሳይሆን ጅማሬም የሌለው ሕይወት ነው፡፡ በአባቱ ያለው ያ ሕይወት የእርሱም ሕይወት የሆነለት ይህ ልጅ /ኢየሱስ/ ለእኛም የሰጠን ሕይወት ያንኑ በአብ ዘንድ ያለውን መለኮታዊ ሕይወት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ሲያስረዳ «ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን፤ ከአብ ዘንድ የነበረውን ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን» ይላል /1ዮሐ.1፡2/፡፡ የእግዚአብሔር ቃል እንደሚነግረንም ሰዎች እርሱን ባመኑ ጊዜ ኢየሱስ ራሱ ወደ እነርሱ ይገባል /ራእ.3፡20/፤ ኢየሱስ ወደ ልባቸውና ወደ ኑሮአቸው የገባ አማኞችም የመለኮታዊ ሕይወት ባለቤት ይሆናሉ፤ በሌላ አነጋገር የሚያገኙት የዘላለም ሕይወት ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ማለት ነው፤ «እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው» ተብሎ እንደተጻፈ /1ዮሐ.5፡20/፡፡
የሞትና የሲኦል መክፈቻ እንዳለው ገልጦ የነገረን ክርስቶስ /ራእ.1፡18/ «የገሃነም/የሲኦል/ ደጆች አይችሏትም» እያለ ቤተክርስቲያንን በተመለከተ የተናገረው ይህ እርግጠኛ ቃል ዲያብሎስ በዙሪያችን ለሚያሰማን የመከራና የሞት ድምፅ ጆሮ እንዳንሰጠው ያደርገናል፡፡ የክርስቶስ ኢየሱስ በመሆናችን ክርስቶስን ከበር ውጪ አውጥታ የሰቀለችውና ታሪኩንም በሞትና በመቃብር ለመደምደም ሙከራ አድርጋ የነበረችው ዓለም ብትጠላንም ሆነ ብታሳድደን እስከሞት ድረስ ታማኞች እንድንሆን የሚያጠነክር አስተማማኝ ዋስትና ከኢየሱስ አግኝተናል፡፡ ድንጉጥና ፈሪ የሆነው ልባችን ከዓለም የሚደርስብንን ነቀፋ ገና ሲሰማ የሞት ፍርሃት ሊያውከው ቢሞክርም «የገሃነም ደጆች አይችሏትም» የሚለውን ድምፅ ባስታወሰ ጊዜ የሞት ፍርሃቱ ሁሉ ከላዩ ይገፈፋል፡፡ ኢየሱስ ሰው የመሆኑ ዓላማ ይህ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ሲገልጥ «እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር ይኸውም ዲያብሎስ ነው በሕይወታቸውም ሁሉ ስለሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ» ይላል /ዕብ.2፡14/፡፡
ስለሆነም ሰይጣን እኛን ሊያስፈራራበት የሚችለው ትልቁ መሣሪያው ሞትና መውጊያው በኢየሱስ የተሰበረ መሆኑን ከልብ በማመን ከሞት ፍርሃት ነጻ ልንሆን ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥ መሠረቷ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ በሆነላት አንዲቷ ቤተክርስቲያን ውስጥ አባል እንደሆኑ እርግጠኛ የሆኑ አማኞች «በዚህችም አለት ላይ ቤተክርስቲያኔን እሠራለሁ የገሃነም ደጆችም አይችሏትም» በሚለው የጌታችን የማረጋገጫ ቃል ስለሚያምኑ በዘመናቸው ሁሉ በሞት ፍርሃት ሊታሠሩ አይችሉም፡፡ ሞት ይይዘው ዘንድ ያልቻለው /የሐ.ሥ.2፡24/ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ በደሙ የዋጃትና ራስ የሆነላት ይቺ የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን የሲኦል ደጆች የሆኑት ሞትና መውጊያው እንዴት አድርገው ሊያናውጧት ይችላሉ? በእርግጥ ፈጽሞ አይችሉም፡፡
ስለዚህ ዛሬ ቤተክርስቲያን ልቧን አስፍታ ድምጿን ከፍ አድርጋ፡-
«ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ፤ ሲኦል ሆይ ድል መንሣትህ የታለ፤ የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው፤ የኃጢአት ኃይል ሕግ ነው፤ ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን» /1ቆሮ.15፡55-57/ ብላ መዘመር ትችላለች፡፡
የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻዎች
/ማቴ.16፡18-19/
«እኔም እልሃለሁ፤ አንተም ጴጥሮስ /petros-ፔትሮስ/ ነህ፤ በዚችም አለት /petra-ፔትራ/ ላይ ቤተክርስቲያኔን እሠራለሁ፤ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም፤ የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል» /ማቴ.16፡18-19/፡፡
«እኔም እልሃለሁ፤ አንተም ጴጥሮስ /petros-ፔትሮስ/ ነህ፤ በዚችም አለት /petra-ፔትራ/ ላይ ቤተክርስቲያኔን እሠራለሁ፤ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም፤ የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል» /ማቴ.16፡18-19/፡፡
ቤተክርስቲያኑን «ኢየሱስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነው» በሚለው እውነት ላይ የሚገነባው ራሱ ጌታ ኢየሱስ ሲሆን ይህችም ቤተክርስቲያን «ሁለት ወይም ሦስት» ወይም ከዚያ በላይ ሆነው፣ ከዓለም ተለይተው በሌላ ስም ሳይሆን በራሱ በጌታ በኢየሱስ ስም በሚሰባሰቡና እርሱ ቀደም ሲል በምድር ላይ ይዞት የነበረውን ስፍራ ይዘው በሚገኙ የእውነተኛ አማኞች አንድነት የምትታይ ናት፡፡ ስለሆነም ወደዚህች ባሕርይዋ ሰማያዊ ወደሆነችው፣ ጌታ ኢየሱስም ራስ ወደሆነላት ወደአንዲቱ የክርስቶስ አካል ሰዎች የሚጨመሩት እንዴት ነው የሚለውን ማጤኑ ከላይ ለጴጥሮስ የተነገረውን የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻዎች ጉዳይ ለመረዳት በር ይከፍታል፡፡ በዚህ ረገድም ሰዎች ወደዚያች ኅብረት ብልት ሆነው የሚገቡት በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ሲያብራራ «አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናል» ይለናል /1ቆሮ.12፡12-13/፡፡ ይሁን እንጂ መንፈስ ቅዱስ ሰዎችን ወደዚህች የክርስቶስ አካል የሚጠራው አስቀድሞ ብልት በሆኑ አማኞች በኩል መሆኑም የማይካድ እውነት ነው፡፡ የእነዚህም ሰዎች አገልግሎት ወይም ምስክርነት እጅግ ጠቃሚ ከመሆኑም ባሻገር በተሰባኪዎች ዘላለማዊ ዕጣ ፈንታ ላይ ወሳኝነት አለው፤ ስለዚህም ነገር ሐዋርያው ሲያስረዳ «የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል» ካለ በኋላ «እንግዲህ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለሰባኪስ እንዴት ያምናሉ?» በማለት የሰባክያን አገልግሎት እንደምን ወሳኝ እንደሆነ ይናገራል /ሮሜ10፡13-14/፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መሰበኩ ብቻ ተሰባኪውን የዚያች የእውነተኛይቱ ጉባኤ ብልት እንዲሆን የማያደርገው መሆኑም ሌላው እውነታ ነው፤ የተሰበከለት ሰው ስብከቱን አምኖ መቀበሉና አለመቀበሉ ከስብከት ቀጥሎ ጠቃሚ የሆነ ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ተሰባኪው ስብከቱን አምኖ ቢቀበል መንፈስ ቅዱስ ወደዚያች ጉባኤ ብልት አድርጎ ይጨምረዋል፤ የተሰበከለትን ባያምነው ደግሞ አለማመኑ ኃጢአት ይሆንበታል፤ ብልት ሆኖ ወደ ክርስቶስ አካል አይጨመርም፤ «ባለማመናቸው ጠንቅ ሊገቡ እንዳልተቻላቸው እናያለን» ተብሎ ስለቀደሙት ሕዝበ እስራኤል እንደተነገረ /ዕብ.3፡19/ ያው ወደ ክርስቶስ አካል ብልት ሆኖ እንዲገባ የተጠራበት የምስክርነት ቃል ሰውን እንዳይገባ ያደርገዋል፤ እንደዚሁም ጌታ «እኔም መጥቼ ባልነገርኋችሁስ ኃጢአት ባልሆነባቸውም ነበር፤ አሁን ግን ለኃጢአታቸው ምክንያት የላቸውም» /ዮሐ.15፡22/ ሲል እንደተናገረው ነው፡፡ በተጨማሪም ቃሉ «በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል» ይላልና የሰማነውን ቃል ማመን አሁኑኑ ከፍርድ የዳንን/የተፈታን/ ሰዎች ሲያደርገን አለማመን ደግሞ አሁኑኑ የተፈረደብን/የታሰሩ/ ሰዎች ያደርገናል /ዮሐ.3፡18/፡፡
በተጨማሪም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ወራቱ በጊዜው ለነበሩ ጻፎችና ፈሪሳውያን የተናገረው ሐሳብ ሌላው የተነሣንበትን ምንባብ ለማብራራት የሚያስችለን ሆኖ ይገኛል፤ ጌታችን ለእነዚያ በዘመኑ መጻሕፍትን እናውቃለን መንፈሳዊነትንም ይዘናል ለሚሉ ነገር ግን የመጻሕፍትን ሐሳብ ለሚያጣምሙ ሕዝቡን ደግሞ «ሕግን የማያውቅ ርጉም ነው» /ዮሐ.7፡49/ እያሉ ከእግዚአብሔር እውቀት እንዲገለል አድርገው ለነበሩት ሰዎች «እናንተ ሕግ አዋቂዎች የእውቀትን መክፈቻ ስለወሰዳችሁ ወዮላችሁ፤ ራሳችሁ አልገባችሁም፤ የሚገቡትንም ከለከላችሁ» ሲል ተናገራቸው /ሉቃ.11፡52/፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በማቴዎስ ወንጌልም «እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት ስለምትዘጉ ወዮላችሁ፤ እናንተም አትገቡም፤ የሚገቡትንም ትከለክላላችሁ» ሲል ተናግሯል /ማቴ.23፡13/፡፡
እነዚህ ሰዎች መንግሥተ ሰማያትን የዘጉት እንደምን ነው? ቢባል መልሱ ህጉን ባለማስተማርና በማጣመም ነው የሚል ይሆናል፡፡ ስለሆነም ከላይ የጠቀስናቸው ሁለት ሐሳቦች የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻ ወይም ቁልፍ እግዚአብሔር ኃጥኣንን ወደራሱ የሚጠራበት በሰዎች ያልተጣመመ ትክክለኛ የቃሉ ምስክርነት እንደሆነ ያሳዩናል፡፡ ይህንን ምስክርነት ሰጥቶ ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር የመጥራትን ጥሪ መቀበልም መክፈቻውን መቀበል ነው፤ መስበክና ማስተማርም መክፈቻውን ሥራ ላይ ማዋል ነው፤ ምስክርነቱን ሰዎች ሳይቀበሉ ሲቀሩ የተፈረደባቸው ወይም የተዘጋባቸውና የታሰሩ ይሆናሉ፤ ምስክርነቱን ሲቀበሉ ደግሞ ወደ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ከፍርድ የዳኑና የተፈቱ ይሆናሉ፤ በዚህ መንገድ ሰባኪው ቁልፉን ይጠቀማል፤ ማለትም ያስራል፤ ይፈታል፡፡ ለጴጥሮስም የተባለው ይኸው ነው፡፡
መታሰርና መፈታት
የተሰባኪዎች መታሰርና መፈታት የሰባክያን ቀጥተኛ ውጤት ሳይሆን መክፈቻ የሆነው የእግዚአብሔር ቃል በሰሚዎች ላይ የሚያመጣው ውጤት ነው፡፡ ሰዎቹን ማሰርና መፍታት የጴጥሮስ ቀጥተኛ ድርሻ አይደለም፤ ከጴጥሮስ የሚጠበቀው የተሰጠውን የወንጌል ሰባኪነት ጸጋ ሥራ ላይ ማዋል ነው፤ ልብ እንበል፤ ይህ ሰዎችን «ተፈቱ» ወይም «ታሰሩ» ብሎ በአፍ ከመናገር ወይም ፍርድን ከመግለጥ ወይም ከማወጅ በእጅጉ የተለየ ነው፡፡ የሰዎች መፈታትም ሆነ መታሰር የመክፈቻው ውጤት እንጂ የጴጥሮስ ፍርድ ወይም ፍላጎት አይደለም፤ የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻ የሆነው የእግዚአብሔር ቃል በሰው ልብ ላይ እንዲሠራ ሲደረግ ውጤት አለው፤ ውጤቱም አንዳንዶችን ለእምነት ማብቃቱ ሲሆን አንዳንዶችን ደግሞ በእልከኝነታቸው ምክንያት በክህደት እንዲገለጡ ማድረጉ ነው፤ አንዱ እሳት ሰሙን ሲያቀልጥ ሸክላውን ደግሞ ከፊት ይልቅ ጠንካራ ያደርገዋል፤ የእግዚአብሔር ቃልም በሰዎች ላይ ተመሳሳይ ውጤት ያስከትላል፡፡
ስለሆነም ጴጥሮስ በተሰጠው መክፈቻ ማለትም በወንጌል ቃል ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንዲገቡ ለማድረግ ሲሰብክና ሰዎች አምነው በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ወደ ክርስቶስ አካል ሲገቡ መክፈቻውን ተጠቅሞ በምድር እየፈታ ነበር፤ ሰዎች ምስክርነቱን አንቀበልም ሲሉ ደግሞ «ባለማመናቸው ጠንቅ» ወይም «ቃሉ ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሐደ» /ዕብ.4፡2/ ወደ መንግሥተ ሰማያት እንዳይገቡ ሆነዋልና በምድር የታሰሩ መሆናቸውን እየገለጠ ነበር፡፡ ለምሳሌ ያህልም በበዓለ ሃምሳ ዕለት ጴጥሮስ ሲሰብክ ሦስት ሺህ ያህል ነፍሳት ወደ ቤተክርስቲያን አምነው ሲጨመሩ /ሲፈቱ/ እንመለከታለን፤ እንደዚሁም በሌላ ወቅት ጴጥሮስ የሰበከውን ቃል አምነው ብዙዎች ወደ ሐዋርያት ሲጨመሩ /ሲፈቱ/ በስብከቱ ደስ ያልተሰኙ ሌሎች ደግሞ በሐዋርያት ላይ «እጃቸውን ጭነውባቸው» ወደ ክርስቶስ ጉባኤ ሳይገቡ እንደቀሩ /እንደታሰሩ/ እናነባለን /የሐዋ.ሥ.4፡3-4/፡፡
ስለሆነም የቁልፉን ያዥ ድርሻና የቁልፉን ውጤት መለየት ይኖርብናል፡፡ ቁልፉን በሥራ ላይ ማዋል ማለትም ቃሉን መስበክ ነው፤ ቃሉን መስበክ የጴጥሮስ ድርሻ ነው፤ የሰዎች መታሰርና መፈታት መክፈቻው በሰዎቹ ምላሽ ላይ ተመርኩዞ የሚያመጣው ውጤት ነው፡፡
ሰማይና ምድር
በመቀጠል ደግሞ «በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የምትፈታው ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል» በሚለው አባባል ውስጥ ያለውን የሰማይና የምድር ግንኙነት እንመለከታለን፡፡ ይህም ማለት ጴጥሮስ ወንጌሉን እንደመለኮት ፍርድ ከሰበከ ያለጥርጥር ተሰባኪው ለወንጌሉ የሚሰጠው ምላሽ በሰማይ እውቅናና ክትትል አለው ማለት ነው፡፡ ይህም ምድር ላይ እንደ ሰማይ ፍርድ ለተሠራው ሥራ ሁሉ ሰማያዊ ክትትል፣ እውቅናና ድጋፍ እንዳለ የሚያመለክት ነው፡፡ ስለዚህ አገልጋዩ የሚያገለግለው ብቻውን ሳይሆን መለኮታዊ መገኘትና ክትትል ባለበት ሁኔታ ውስጥ ነው ማለት ነው፡፡ ሰዎች የሰባኪውን ቃል አምነው ሲቀበሉ መቀበላቸው በእግዚአብሔር ዘንድ ወዲያውኑ የታወቀ ሲሆን አለመቀበላቸውም ወዲያውኑ በእግዚአብሔር ፊት ለፍርድ የተዘጋጁና የተፈረደባቸው ከእግዚአብሔር መንግሥትም የተገለሉ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡ ስለዚህ ሰዎች በምድር ላይ ለሚሰሙት የወንጌል ቃል የሚሰጡት ምላሽ በእጅጉ ዘላለማዊ ማንነታቸውን የሚወስን ነው ማለት ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ሰዎች በምድር ላይ በወንጌል ስብከት አምነው ወደ ክርስቶስ አካል ካልተጨመሩ በቀር ዛሬም ሆነ ወደፊት በሰማይ ላይም ያልተጨመሩ ሆነው እንደሚቀሩ የሚያሳይና እንደዚሁም እንደፍርዱ አሠራር የሚሰጠውን ምስክርነት አምነው ወደ ክርስቶስ አካል የተጨመሩት ደግሞ መጨመራቸው በሰማይም ጭምር የተረጋገጠና ይህ መብታቸውና ያገኙትም ስፍራ ሰማያዊ እውቅናና ድጋፍ ያለው መሆኑን ከዚህ ምንባብ መረዳት እንችላለን፡፡ በምድር ሳሉ ቃሉን ያላመኑትና የካዱት ሁሉ በሰማይም የካዱ ሆነው ይታወቃሉ፤ ከሞቱ በኋላ ወደ ክርስቶስ አካል መጨመርም አይችሉም፤ ሰው ነፍሱ ከሥጋው በምትለይበት ወቅት የነበረው ማንነቱን ሰማይ ላይ ሊቀይር ወይም ሊያሻሽል አይችልም፤ በምድር ላይ የነበረውን ማንነቱን ይዞ ወደዘላለም ስፍራው ይሄዳል እንጂ፡፡ ከነኃጢአቱ ከሞተ በሰማይም ኃጢአተኛ ነው፡፡ በምድር ላይ በጌታ በኢየሱስ ቤዛነት ከኃጢአቱ ድኖ በሥጋ ቢሞት ደግሞ ከዚያን በኋላ ማንነቱን ሊያበላሽበት የሚችል ምንም ኃይል የለም፤ ምክንያቱም በምድር ላይ ከኃጢአቱ ሲድን መዳኑ በሰማይም እውቅና አግኝቷልና፡፡ ስለሆነም በዚህ ምድር ስለጌታ ኢየሱስ የሚሰጠውን የቃሉን ምስክርነት አምኖ ራስ ወደሚሆን ወደእርሱ የተጠጋ አማኝ በአካለ ሥጋ እያለም በእጅ ወዳልተሠራችውና ራሱ ጌታ ኢየሱስ ወዳለባት ሰማያዊ መቅደስ በመንፈስ የመግባት በዚያም ሆኖ የመጸለይ መብት አለው /ዕብ.10፡19-20/፤ ከዚህም ባሻገር እንዲህ ያለው አማኝ ነፍሱ ወደ ጌታ ሳትሄድ ከወዲሁ «ወደ ጽዮን ተራራና ወደሕያው እግዚአብሔር ከተማ፣ ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም፣ በደስታም ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት፣ በሰማያትም ወደ ተጻፉ ወደ በኵራት ማኅበር፣ የሁሉም ዳኛ ወደሚሆን ወደ እግዚአብሔር፣ ፍጹማን ወደሆኑት ወደ ጻድቃን መንፈሶች፣ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፣ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደመርጨት ደም» ደርሷል /ዕብ.12፡22-24/፡፡
ስለሆነም ምስክርነቱን በተመለከተ ሰዎች ዛሬ በምድር ላይ የሚወስኑት ውሳኔ ምድራዊ ውሳኔ ብቻ ሳይሆን በሰማይ ላይም በጌታ ፊት የሚታወቅ ውሳኔ መሆኑን አውቀው ሊጠነቀቁ ይገባቸዋል፡፡ በምድር ላይ ካልተሻሻለም ውሳኔው በሰማይ ላይ ሊሻሻል አይችልም፡፡ ወንጌሉን እምቢ አንቀበልም ሲሉም እምቢ ያሉት የሚመሰክረውን ምስክር ብቻ አይደለም፤ ምስክርነቱንና ምስክሩን የላከውን ጌታ ጭምር እንጂ፡፡ በመሆኑም ሰዎች በጊዜው አሁን በምድር ላይ እየተሰጠ ያለውን ምስክርነት ሊቀበሉና ወደ ክርስቶስ ሊከማቹ ይገባል፡፡ እዚህ ላይ አንባቢው ልብ ይበል፡፡
ከዚህ በመቀጠል ደግሞ እንዲህ ያለውን ግልጥና የተባረከውን የጌታ ኢየሱስን ንግግር በማስታከክ የተፈጠሩና ለብዙ ዘመናት የተንሠራፉ በእጅጉ ስህተት የሆኑ አመለካከቶችን በመዘርዘር እንመለከታቸዋለን፡፡ አላማውም ሰዎችን ለመተቸት ሳይሆን የተመሠረቱት የስህተት አተሳሰቦች ከዚህ ምንባብ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው መሆናቸውን ለማሳየት ነው፡፡ ስለሆነም በጥቅሉ ቃሉ የሚከተሉትን አመለካከቶች የሚያሳይ አይደለም፡፡
የቤተክርስቲያን ሥልጣን
በማቴ 18፡15-20 ውስጥ «አክሌሲያ» የሚለው ቃል ለሁለተኛ ጊዜ ተጠቅሶ የሚገኝ ሲሆን በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ይህን ክፍል እናጠናለን፤ በዚህ ስፍራ ላይ ቤተክርስቲያን የተጠቀሰችው ከሥነሥርዓትና በምድር ላይ ካላት የአስተዳደር ሥልጣን ጋር በተያያዘ መልኩ ነው፡፡ ይህም በየስፍራው ወይም በአጥቢያ ደረጃ በተሰበሰበ ጉባኤ የሚታየው የቤተክርስቲያን ገጽታዋ ነው፤ ንባቡም እንደሚከተለው ነው፤ «ወንድምህ ቢበድልህ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው፤ ቢሰማህ ወንድምህን ገንዘብ አደረግኸው፤ ባይሰማህ ግን በሁለት ወይም በሦስት ምስክር አፍ ነገር ሁሉ እንዲጸና ዳግመኛ አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ፤ እነርሱንም ባይሰማ ለቤተክርስቲያን ንገራት፤ ደግሞ ቤተክርስቲያንን ባይሰማት እንደ አረመኔና እነደ ቀራጭ ይሁንልህ፡፡ እውነት እላችኋለሁ፤ በምድር የምታስሩት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የምትፈቱት ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል፡፡ ደግሞ እላችኋለሁ ከእናንተ ሁለቱ በምድር በማናቸውም በሚለምኑት ነገር ሁሉ ቢስማሙ በሰማያት ካለው ከአባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል፡፡ ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና» /ማቴ.18፡15-20/፡፡
እግዚአብሔር በምድር ላይ ራሱን የሚገልጠው በቤተክርስቲያኑ በኩል በመሆኑና ቤተክርስቲያንም በምድር ላይ የእግዚአብሔር መለኮታዊ ፈቃድ የሚገለጥባት ማዕከል በመሆኗ በእርሱ ፊት ተቀባይነት ያለውን ውሳኔ መወሰን እንድትችልም ሥልጣን እንደተሰጣት ከሚያመለክቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባቦች መካከልም ከላይ የተጠቀሰው አንዱና ዋንኛው ነው፡፡ በዚህ ምንባብ ውስጥ ጌታችን ለቤተክርስቲያን የሰጠውን ሥልጣን ለመገንዘብም በቅድሚያ በምንባቡ ውስጥ ያሉትን ሐሳቦች አንድ በአንድ መመልከቱ ጠቀሚ ነው፡፡
ወንድምህ ቢበድልህ ...
ጌታ ኢየሱስ በዚህ ንባብ ውስጥ የገለጸው በዳይ፣ ለተበዳዩ በእምነት ወንድም የሚሆን አማኝ ወይም ክርስቲያን በመሆኑ አንድ አማኝ ከማያምን ሰው የሚደርስበት የበደል ጉዳይ በዚህ ምንባብ የሚታይ አይደለም፤ በመሆኑም ምንባቡ ሙሉ በሙሉ በአማኞች መካከል ስላለ ጉዳይ የሚናገር እንደሆነ መገንዘቡ ጠቃሚ ይሆናል፤ በዚሁ ምዕራፍ ማለትም በማቴ.18፡3 ላይ ጌታ ተመልሰው እንደ ህፃናት ስለሚሆኑ የመንግሥተ ሰማያት ወራሾች ይናገራል፤ በቊ.6 እና 10 ላይም በኢየሱስ ስለሚያምኑ ታናናሾች ይናገራል፡፡ በመሆኑም ከመጀመሪያው ቊጥር ጀምሮ ንባቡ ስለ አማኞች እንጂ ስለ ኢአማንያን የሚናገር አይደለም፡፡ ስለዚህ «ወንድምህ ቢበድልህ ...» እየተባለ መመሪያ የሚቀበለው ሰውም ሆነ የበደለው ወንድም ሁለቱም በክርስቶስ ወንድማማች የሆኑ ሰዎች ናቸው፤ ይህም በደል በግልጥ የተደረገ በደል ሊሆን ይገባዋል፤ በደል ስለመኖሩ እርግጠኝነት በሌለበትና ሳይበድለኝ አይቀርም የሚባልበት ሁኔታም በዚህ አልተካተተም፤ ሁለቱ አማኞች እርስ በእርስ የተበዳደሉ ከሆኑም ጉዳያቸው ከዚህ ምንባብ ሽፋን ውጪ ነው፤ በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ በደልም በዚህ አልተካተተም፤ ይህ አንድ አማኝ በሌላው አማኝ ላይ የሚያደርሰው የግል በደል ነው እንጂ የቤተክርስቲያን ጉዳይም አይደለም፡፡ ስለሆነም ይህ ቃል አንድ አማኝ ያለጥርጥር በሌላው ባልበደለው አማኝ ወንድሙ ላይ በደል ሲያደርስ ማለትም በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የወንድሙን መብት ቢጋፋ፣ አለአግባብ በወንድሙ ላይ ማናቸውንም ጉዳት ቢያደርስና ወንድሙን ቢያሳዝነው ይህንን የተፈጠረውን ችግር ለማስወገድና ፍቅርን ወደነበረበት ለመመለስ እንዲቻል ጌታችን ያስተማረው ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሰው ምንባብ አራት ደረጃዎች አሉት፤ እነርሱ:-
1. አማኙ በደለኛውን ወንድም ለብቻቸው ሆነው ሳሉ እንዲወቅሰው፣
2. ለብቻው ካልሰማው ከእርሱ ጋር አንድ ወይም ሁለት ሰዎችን ይዞ በአንድነት እንዲወቅሱት፣
3. በሁለት ወይም በሦስት ሰዎች ፊት ሊመለስ ካልቻለ ለቤተክርስቲያን እንዲነግራት፣ ቤተክርስቲያን እንድትገሥጸው፣
4. በዚያም የማይመለስ ከሆነ ውሳኔ እንድትሰጥበት የሚናገሩ አራት ደረጃዎች ናቸው፡፡
እነዚህንም አራት እርምጃዎች እንደሚከተለው ከፋፍለን እንመከታቸዋለን፡፡
1. ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው
በዚህ ደረጃ ወደ በዳዩ የሚሄደው ተበዳዩ ነው፤ ይህም በትክክል ጸጋን የሚያመለክት ነው፤ የበደለው የሰው ልጅ ሆኖ ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቀው ዘንድ ኃጢአተኛውን ሊፈልግ የመጣው ጌታ ለተበደለው ደቀመዝሙሩ የሚሰጠው መመሪያም ወደ በዳዩ መሄድን ነው እንጂ በዳዩ ወደ እርሱ እንዲመጣ አይደለም፤ ይህ የጌታ የኢየሱስ መንገድ ነው፡፡ እንደ ዓለም ሥርዓት ከሆነ በዳዩ ወደ ተበዳይ እንዲሄድ ይጠበቅበታል፤ አለም ኩራተኛ ናትና ዕርቅን የምትፈልግበት ዋና ምክንያትም ፍቅርን ለመመለስና በዳዩን ለማቅናት ሳይሆን በደለኛውን ለመቅጣትና ተበዳዩን ለመካስ በመሆኑ ይህንን የምታስፈጽምባቸው መንገዶችም ክርስቲያኖች ከሚከተሉት መንገድ በእጅጉ የራቀ ነው፡፡ እንደጌታ መንገድ ወደበዳዩ የሚሄደው ተበዳዩ ነው፤ ከልቡ ፍቅር የራቀውን በደለኛ የሚፈልገው ተበዳዩ ነው፤ ወደበደለው ወንድሙ የሚሄደውም ካሳ ፈልጎ ሳይሆን የጠፋውን ፍቅር ሊመልስ ወንድሙንም እንደቀድሞው ገንዘቡ ሊያደርገው ነው፡፡ ይህንንም ለማድረግ ለብቻቸው ባሉበት ተበዳይ በዳዩን እንዲወቅሰው ታዟል፤ እዚህ ላይም የጌታ መንገድ ከዓለም መንገድ ይለያል፤ እኛ በተበደልን ጊዜ ስለመበደላችንና ስለበደለን ሰው ለሌላው ወንድም ወይም እህት ማውራት ይቀልለናል፤ ይህ ደግሞ የሻከረውን ፍቅር ፈጽሞ አደጋ ላይ ከሚጥሉ የሥጋ መንገዶች ዋንኛው መሆኑን የሚክድ ማን ነው? የበደለንን ሰው ወደ ጎን በመተው ሌሎች ከእኛ ጋር ሆነው ለእኛ እንዲያዝኑልን ወይም በበደለን ሰው ላይ እንዲፈርዱ የመፈለግ ሐሳብ በራሱ ሥጋዊ ነው፤ ውጤቱም የበደለውን ሰው ከእኛም ሆነ ከሌሎች ማራቅ ነው፤ ይህ ወንድምን ገንዘብ ለማድረግ ከመፈለግ በእጅጉ የራቀ የጥላቻ አካሄድ ነው፤ በመሆኑም በዚህ በመጀመሪያው ደረጃ የበደለንን ሰው መውቀስ ያለብን ለብቻችን በምንሆንበት ቦታ ነው፤ በዚያም ብቻችንን በምንሆንበት ስፍራ ለበደለን ወንድም እንዴትና እንደምን እንደበደለን በፍቅርና በትህትና እናስረዳዋለን፤ ይህ በፍቅር በዳዩ በደሉን እንዲያውቀው የምናደርግበት መንገድም ደብዳቤ በመጻፍ ሳይሆን ፊት ለፊት በመገናኘትና በመነጋገር ነው፤ «ውቀሰው» ተብሎ የተተረጎመው ቃል ትክክለኛ ፍቺም ይኸው ነው፡፡ በዚህ ከተሳካልንና በዳዩ በደሉን ለማመን ከቻለ ጌታ እንዳለው ገንዘብ እናደርገዋለን፤ ሆኖም ግን በዳዩ ይህን መንገድ የማይቀበል ከሆነ አማራጩ መንገድ በሁለተኛ ደረጃ የተጠቀሰውን እርምጃ መውሰድ ነው፡፡
2. አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ
በሁለተኛ ደረጃም ከአማኞች አንድ ወይም ሁለት ከራሱ ጋር በመውሰድ ዳግመኛ ተበዳዩ ወደበዳዩ በመሄድ አብረውት ካሉት ጋር በዳዩ እንደበደለ ለማስረዳት በመጀመሪያ እንዳደረገው በጸጋ ጥረት እንዲደረግ ጌታ አስተምሮናል፡፡ የዚህ ጥረት ዓላማም እንደመጀመሪያው ሁሉ ወንድምን ገንዘብ ለማድረግ ነው፡፡ ሆኖም በዚህም ባይሳካ ወደ ሦስተኛው እርምጃ እንድንገባ ጌታ ፈቅዶልናል፤ ይህም ለቤተክርስቲያን መንገር ነው፡፡
3. ለቤተክርስቲያን ንገራት
የቤተክርስቲያን ጥረትም እንደቀደሙት ሁሉ በጸጋ ነገሮችን ወደነበሩበት የፍቅርና የወንድማማችነት መንፈስ መመለስን ዓላማው ያደረገ ሊሆን ይገባዋል፤ በተጨማሪም የቤተክርስቲያንን ወቀሳ /ምክር እና ተግሣጽ/ ለመስማት የሚመጣው በደለኛ ወንድም በግል የተወቀሰና ወቀሳውን ያልሰማ ከመሆኑም ባሻገር በሁለት ወይም በሦስት ወንድሞችም ሊመለስ አለመቻሉ በደለኛነቱን እርግጠኛ ያደርገዋልና ቤተክርስቲያን የመጨረሻውን ወቀሳ ለመስጠት ሕጋዊ መሠረት ይኖራታል ማለት ነው፡፡ እንደሚታወቀው ሁሉ የመጨረሻ ምክርና ተግሣጽ የሚሰጠውና ይህንንም ተግሣጽ በደለኛው ካልሰማ የመጨረሻውን ውሳኔ መስጠት የሚችለው «ከፍተኛ ባለ ሥልጣን» የሆነ አካል ነው፤ ጌታችንም አካሉ የምትሆን ቤተክርስቲያንን ወቀሳ እንድትሰጥና አስፈላጊውን የመጨረሻ ውሳኔ እንድትወስን መመሪያ ሲሰጥ ቤተክርስቲያንን በምድር ላይ ከፍተኛ ባለሥልጣን ማድረጉን እንረዳለን፡፡ ይህም ወቀሳ ምክር አዘል ተግሣጽ እንደሆነ መረዳት አያዳግትም፡፡ ቤተክርስቲያንም በደለኛውን ለመውቀስ የሚያስችላት የእግዚአብሔር መንፈስና የእግዚአብሔር ቃል አላት፤ ዋናው ዓላማም በደለኛው የእግዚአብሔር ቃልና የእግዚአብሔር መንፈስ የሚለውን ሰምቶ በሁሉ እንዲወቀስና እንዲመከር በደለኝነቱን እንዲያምን በንስሐም ወደጌታ እንዲመለስ ማድረግ ነው እንጂ በደለኛውን መበቀል አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ በግልና በጋራ ተወቅሶ ወደ ቤተክርስቲያን የመጣውና ቤተክርስቲያንም የወቀሰችው ሰው የቤተክርስቲያንን መንፈሳዊ ወቀሳ ባይሰማስ?
4. እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ
ለዚህ የተሰጠው የጌታ መመሪያም፣ «ቤተክርስቲያንን ባይሰማት እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ» የሚል ነው፤ ተበዳዩ አማኝ ከዚህ አልፎ እንዲሄድ አልተፈቀደለትም፤ ንስሐ ሊገባ ባልቻለው በዚያ ሰው ላይ ቤተክርስቲያን በምትወስደው እርምጃ ላይም ግፊት ማድረግ አይኖርበትም፤ ወዳላመኑ ሰዎች ዘንድም ሄዶ «ንስሐ ባልገባው» በደለኛ ላይም ክስ ይመሥርት አልተባለም፤ ሆኖም እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ እንዲቆጥረውና እንዲተወዉ ታዟል፡፡ ሆኖም ቤተክርስቲያን በመቀጠል የምትወስደው እርምጃ አላት፡፡
በምድር የምታስሩት ሁሉ.. በምድር የምትፈቱት ሁሉ..
ቤተክርስቲያን ግን በአማኞች መካከል የሚነሱ በደሎችን እንድትዳኝ ሥልጣን የተሰጣት በመሆኗ በመቀጠል ስለምትወስደው እርምጃ ጌታ ሲናገር «በምድር የምታስሩት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የምትፈቱት ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል» ሲል ተናገረ፤ ይህም ቤተክርስቲያን በአማኞች መካከል የሚነሡ ችግሮችን በበላይነት የመመልከት ሥልጣን እንዳላት የሚያመለክት ነው፤ ከዚህ አኳያም ማሰሩ በትክክል በዳዩን ሰው ከጉባኤ እንዲገለል ማድረግ ሲሆን መፍታቱ ደግሞ በተጸጸተ ጊዜ በዳዩን ሰው ይቅር ብሎ ወደ ኅብረት መቀበል ማለት ነው፡፡ ይህን የማድረግ ሥልጣንም በሥራ ላይ የሚውለው ሁለት ወይም ሦስት እንኳን በሚሆኑ አማኞች መካከል በሚገኘው ጌታ ኢየሱስ ነው፤ በምድር ላይ ንስሐ አንገባም በሚሉትና ልባቸውን በሚያደነድኑ፣ ወንድሞቻቸውንም በሚበድሉ በደለኞች ላይ ቤተክርስቲያን በምድር የምታስተላልፈው ውሳኔም በሰማይ በጌታ ዘንድ እውቅና አለው፤ በዚህ ዓይነት ቤተክርስቲያን በዳዮችን ከመካከሏ እንድታርቅ ሥልጣን ተሰጥቶአታል፡፡ ሐዋርያው ለቆሮንቶስ ሰዎች በቀዳሚ መልእክቱ በምዕራፍ 6 የተናገረለት ጉድለትም ቤተክርስቲያን ይህን በአማኞች መካከል የሚነሱ የግል በደሎችን በተሰጣት ሥልጣን መዳኘት አለመቻሏ እንደነበር ግልጥ ነው፡፡ ስለዚህም ሐዋርያው የሚከተለውን ለማለት ተገዶ ነበር፤ «ከእናንተ አንዱ ከባልንጀራው ሙግት ቢኖረው በቅዱሳን ፊት በመፋረድ ፋንታ በዓመፀኞች ፊት ሊፋረድ ይደፍራልን? ቅዱሳን በዓለም ላይ እንዲፈርዱ አታውቁምን? በዓለምስ ላይ ብትፈርዱ ከሁሉ ይልቅ ትንሽ ስለሚሆን ነገር ልትፈርዱ አትበቁምን? የትዳር ጉዳይ ይቅርና በመላእክት እንኳ እንድንፈርድ አታውቁምን? እንግዲህ ስለ ትዳር ጉዳይ የፍርድ ቤት ቢያስፈልጋችሁ በቤተክርስቲያን የተናቁትን ሰዎች ፈራጆች አድርጋችሁ ታስቀምጣላችሁን? አሳፍራችሁ ዘንድ ይህን እላለሁ፡፡ እንደዚህ ነውን? በወንድሞች መካከል ሽማግሌ ሊሆን የሚችል አንድ አስተዋይ ሰው በእናንተ ዘንድ አይገኝምን? ነገር ግን ወንድም ወንድሙን ይከሳል ይህም በማያምኑ ፊት ይደረጋልን? እንግዲህ ፈጽሞ የእርስ በእርስ ሙግት እንዳለባችሁ በእናንተ ጉድለት ነው፡፡ ብትበደሉ አይሻልምን? ብትታለሉስ አይሻልምን? ነገር ግን እናንተ ትበድላላችሁ ታታልሉማላችሁ ያውም ወንድሞቻችሁን» /ቊ.1-8/፡፡
የቆሮንቶስን አማኞች ጉድለት በመከተል የገዛ ወንድምን ወደማያምኑ ፈራጆች መጎተትና በዚህም የአማኞችን የከበረ ማንነት በዓለም ፊት የማስነወሩ ተግባር ሊወገድ የሚችለውም ቤተክርስቲያን ይህን ሥልጣን ስትጠቀም ነው፤ ቤተክርስቲያንም ከጌታ ያገኘችውን ውበት ጠብቃ መኖር የምትችለው በዚህ ሥልጣን ተጠቅማ ክፉዎችን ከመካከሏ ማራቅ ስትችል ነው፡፡ ምንም እንኳን ከአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ እስከዚህ ዘመን ድረስ ሰይጣን በአማኞች መካከል መለያየትን በመፍጠሩ ምክንያት በአንድ ስፍራ አማኞች እንደ ጌታ ፈቃድ ከመካከላቸው ያገለሉት በደለኛ በሌላው ስፍራ ባሉ አማኞች ነን ባዮች እንደ ሰማዕት ተቈጥሮ ተቀባይነት የሚያገኝበት ሁኔታ በእጅጉ የሚታይ ቢሆንም አሁንም ይህ ሥልጣን ሁለት ወይም ሦስት ሆነው በጌታ ስም በሚሰበሰቡ እውነተኛ አማኞች ዘንድ መኖሩ የሚያጠራጥር አይደለምና እውነተኛ አማኞች ይህን ሥልጣን ተጠቅመው ክፉን ከመካከላቸው እንዲያርቁ አለመግባባቶቻቸውንም ወደማያምኑት ከመውሰድ እንዲታቀቡ፣ በነውር የተገለሉትንም በደፈናው ወደኅብረታቸው ከመቀበልም እንዲጠበቁ ይመከራሉ፡፡
አማኞች ይህን ጌታ የሰጣቸውን ሥልጣን ተጠቅመው አንድን በደለኛ ከመካከላቸው ቢያስወግዱና ቆይቶ ኃጢአቱ የተያዘበት ሰውም ልቡ ተነክቶ ወደ ጌታ ኢየሱስና ወደ ቤተክርስቲያን በንስሐ ቢመለስ አማኞች ኃጢአቱ እንዲሰረይለት በመስማማት የሚጸልዩለት ጸሎት በጌታ ዘንድ ፍጹም ተሰሚነት አለውና ጌታም ይቅር ይለዋል፡፡ ያ ሰው አልመለስም በማለት ቢቀጥል ግን ይህ በደሉ በጌታ ዘንድ እንደተያዘበት ይኖራል፤ ይህም ማለት የጌታ የሆኑት በምድር ተሰብስበው እንደ ጌታ ልብ የሚወስኑት ውሳኔ በጌታ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሆኑን እንድናውቅ ያስረዳናል፤ ቤተክርስቲያንም በዚህ ዓይነት የማሰርና የመፍታት ሥልጣኗን ትተገብራለች፡፡
ሥልጣኑ የቤተክርስቲያን እንጂ የግለሰብ አይደለም
ሆኖም ይህ ሥልጣን አማኞች በኅብረት የተቀበሉት እንጂ በግለሰቦች እጅ የሚገኝ አይደለም፤ ምንባቡም እንደሚያመለክተው ጌታ ይህን ሥልጣን የሰጠው ሁለት ወይም ከዚያ የሚበልጥ ቊጥር ላላቸውና የሚሠሩትን በመስማማት ለሚያደርጉ የአማኞች ኅብረት ነው እንጂ ለአንድ ግለሰብ አይደለም፡፡ ስለሆነም በጥቅሉ በአማኞች መካከል በሚነሡ የግል አለመግባባቶችም ሆነ ሌሎች ጉዳዮችን የተመለከቱ የሥነሥርዓት ወይም የዲሲፕሊን እርምጃዎች ለግለሰብ የተሰጡ አይደሉም፡፡ በማቴ.16 ለጴጥሮስ እንደተባለለት የወንጌል መልእክተኞች በእግዚአብሔር ቃል መክፈቻነት ሰዎችን ያስራሉ ይፈታሉ፤ ይሁን እንጂ አንባቢው በማቴ.16 ስለማሰርና ስለመፍታት የተነገረው በማቴ.18 ከተነገረው ፈጽሞ የሚለይ መሆኑን ሊረዳ ይገባዋል፡፡ በማቴ.16 ላይ የተነገረው ማሰርና መፍታት ጌታ በራሱ አለትነት ላይ ወደሚገነባት ቤተክርስቲያኑ አማኞች ሕያዋን ድንጋዮች ሆነው እንዲገቡ ከሚያስችለውና በመክፈቻነቱ ከተገለጠው ከወንጌል ቃል ወይም ምስክርነት ጋር በተያያዘ መልኩ ሲሆን በማቴ.18 የተነገረው ማሰርና መፍታት ግን የተገለጠው ወንድማቸውን በሚበድሉ አማኞች ላይ ከሚወሰደው እርምጃ ጋር በተያያዘ መልኩ ነው፡፡
በማቴ.18 ላይ ለቤተክርስቲያን የተሰጣት ሥልጣን በአማኞች መካከል በሚነሡ ጉዳዮች ላይ ያተኰረ ቢሆንም ቤተክርስቲያን በዚሁ ሥልጣን ከዚህ ውጪም ባሉ ጉዳዮች ላይ ክፉን ከመካከሏ ማስወገድ የምትችል መሆኗን የሚገልጡ በርካታ ምንባቦች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ በቆሮንቶስ ዝሙት የፈጸመውን ሰው «ክፉን ከመካከላችሁ አውጡት» /1ቆሮ.5፡13/ በሚለው የተቀደሰ ሐሳብ እርሱን ከጉባኤ ማግለሉ ማሰር ሲሆን በተጸጸተ ጊዜ ደግሞ «ከልክ በሚበዛ ቅጣት እንዳይዋጥ ይልቅ ተመልሳችሁ ይቅር ማለትና ማጽናናት ይገባችኋል» /2ቆሮ.2፡7/ በሚለው ቃል መሠረት እርሱን በፍቅር መቀበል መፍታት ነው፡፡ ሐዋርያውም በዚያ ሰው ላይ እንዲህ ያለ እርምጃ እንዲወሰድበት ሐሳብ ሲያቀርብ «እናንተና መንፈሴም ከጌታችን ከኢየሱስ ኃይል ጋር ተሰብስበን» /1ቆሮ.5፡4/ ማለቱና «ይቅር የምትሉትን እኔ ደግሞ ይቅር እለዋለሁ» በማለት ከእነርሱ ጋር በመስማማት ይቅር ማለቱ /2ቆሮ.2፡9/ ከኃጢአትም ሆነ ከሌሎች የዲሲፕሊን እርምጃዎች ጋር የተያያዘ ለግለሰብ የተሰጠ መብትና ሥልጣን እንደሌለና ለዚህ ዓይነቱ ተግባርና ሥልጣንም ቤተክርስቲያን ብቸኛ ባለሥልጣንና የክርስቶስ እንደራሴ እንደሆነች ያሳያል፡፡ ስለሆነም ማቴ.18ን በተመለከተ ቤተክርስቲያን በሥነምግባር ጉድለት ኃጢአቱን የያዘችበት ሰው ኃጢአቱ የሚያዝበትም ሆነ ይቅር የሚባልለት አማኞች በጌታ ዙሪያ ተሰብስበው በሚስማሙበት ውሳኔ መሠረት እንጂ እንደምድራዊ አሠራር በክርስቶስ መንጋ ላይ ራሳቸውን ባለሥልጣናትና ገዢዎች ያደረጉ ግለሰቦች በሚወስዱት እርምጃ በኩል አይደለም፡፡ አማኞች ተስማምተው በደለኛውን በደለኛ እንደሆነ ወስነው ከማህበር ሲያገሉት ወይም የተገለለውን መጸጸቱን አይተው በፍቅር ሲቀበሉት ጌታ በውሳኔአቸው ይተባበራል፡፡ ቤተክርስቲያንም ውሳኔዋን ለጌታ በጸሎት ታስታውቃለች /ማቴ.18፡19/፡፡
የቤተክርስቲያንን ውሳኔ የሚያጸናውና ተግባራዊ የሚያደርገው «በሰማይና በምድር ሥልጣን ሁሉ» የተሰጠውና /ማቴ.28፡18/ በስሙ በሚሰበሰቡት መካከል የሚገኘው ጌታ ኢየሱስ ነው /ማቴ.18፡20/፡፡ ቤተክርስቲያን ለውሳኔዋ የሚያበቃትንም መለኮታዊ ድጋፍና አግባብነት ያለው ውሳኔ እንድትወስን የሚረዳትን ምሪት የምታገኘው ከእርሱ በመካከሏ ከሚገኘው ጌታ ብቻ ነው፤ በመካከሏ ለመገኘቱ ደግሞ መስፈርቱ በስሙ መሰብሰቧ ብቻ ነው፤ ከሁለት እስካልወረደ ድረስ የአማኞች ቊጥር ማነስም ቤተክርስቲያንን ይህን ሥልጣን ከመገልገል አያግዳትም፤ ሥልጣኑን የሚሰጣትም ያው ስትሰበሰብ በመካከሏ የሚገኘው ጌታ ኢየሱስ ብቻ ነው፡፡ የዚህ ሥልጣን አጠቃምም የተቀደሱ መነሻ ሐሳቦች አሉት፤ ይኸውም ጌታን ለማክበር፣ የጉባኤን ንጽህና ለመጠበቅና አጥፊዎችን አቅንቶ ገንዘብ ለማድረግ ሲባል ብቻ ነው፤ እነዚህን መርሆዎች ግብ ባላደረገ መልኩ ሥልጣኑን እንድንሠራበት ጌታ አይፈቅድልንም፡፡
የቤተክርስቲያንን ውሳኔ የሚያጸናውና ተግባራዊ የሚያደርገው «በሰማይና በምድር ሥልጣን ሁሉ» የተሰጠውና /ማቴ.28፡18/ በስሙ በሚሰበሰቡት መካከል የሚገኘው ጌታ ኢየሱስ ነው /ማቴ.18፡20/፡፡ ቤተክርስቲያን ለውሳኔዋ የሚያበቃትንም መለኮታዊ ድጋፍና አግባብነት ያለው ውሳኔ እንድትወስን የሚረዳትን ምሪት የምታገኘው ከእርሱ በመካከሏ ከሚገኘው ጌታ ብቻ ነው፤ በመካከሏ ለመገኘቱ ደግሞ መስፈርቱ በስሙ መሰብሰቧ ብቻ ነው፤ ከሁለት እስካልወረደ ድረስ የአማኞች ቊጥር ማነስም ቤተክርስቲያንን ይህን ሥልጣን ከመገልገል አያግዳትም፤ ሥልጣኑን የሚሰጣትም ያው ስትሰበሰብ በመካከሏ የሚገኘው ጌታ ኢየሱስ ብቻ ነው፡፡ የዚህ ሥልጣን አጠቃምም የተቀደሱ መነሻ ሐሳቦች አሉት፤ ይኸውም ጌታን ለማክበር፣ የጉባኤን ንጽህና ለመጠበቅና አጥፊዎችን አቅንቶ ገንዘብ ለማድረግ ሲባል ብቻ ነው፤ እነዚህን መርሆዎች ግብ ባላደረገ መልኩ ሥልጣኑን እንድንሠራበት ጌታ አይፈቅድልንም፡፡
ሁለት ወይም ሦስት
ከማቴ.18 ምንባብ የምንማረው ተጨማሪ ጉዳይ ጌታ በአንድ ስፍራ ላይ በስሙ ሁለት ወይም ሦስት ሆነው የተሰበሰቡትን ቤተክርስቲያኑ አድርጎ እንደቈጠረ የሚገልጠውን እውነታ ነው፤ የትም ይሰብሰቡ የት ስፍራው ከግምት ሳይገባ እርሱን የስብሰባቸው ማዕከል አድርገው ከእርሱም ለመስማትና የእርሱንም ልብ ደስ ለማሰኘት በቆረጡ በጥቂቶች መካከል ለመገኘት ጌታ ቃል ገብቶአልና፤ ይህ ምንኛ የተባረከ ተስፋችን ነው! በይበልጥም የመጽሐፍ ቅዱስ ክርስትና ዛሬ እንደገና ሲነገር በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ከማጣቱ የተነሣ ከክፉ በመሸሽ እንደ እግዚአብሔር ቃል በጌታ ስም የሚሰባሰቡ አማኞች ቊጥር ከዘመነ ሐዋርያት ይልቅ አናሳ በሆነበት እንዲህ ባለው ዘመን ይህ እውነት ምንኛ ልብን ያሳርፋል!
በስሙመሰብሰብ
በብሉይ ኪዳን ለአምልኮም ሆነ ለጸሎት ባጠቃላይ እግዚአብሔርን ለመገናኘት ሰዎች በምድር ላይ እንዲሰበሰቡበት የታዘዘው ስፍራ እግዚአብሔር ስሙን ያኖርበት ዘንድ የመረጠው ስፍራ እንደነበረ ይታወቃል /ዘዳግ.12፡11/፤ በአዲስ ኪዳን ደግሞ የእርሱ የሆኑት ሁሉ እንዲሰበሰቡበት እግዚአብሔር የመረጠው የልጁን ስም ነው፡፡ በልጁ ስም መሰብሰብ ማለትም የዚያ ስብሰባ ማዕከል፣ ባለቤት፣ ጠሪና መሪ እርሱ ጌታ ኢየሱስ ነው ማለት ነው፤ ይሁን እንጂ «ማን ተብለን እንጠራ» ከማለት ተነሥቶ ለራስ የተለየ ስያሜን ከወሰዱ በኋላ «የምንሰባሰበው በጌታ ስም ነው» ማለት ራስን ማሳት ከመሆኑም ባሻገር ምንም እንኳን የጌታ ስም በዚያ ስብሰባ ላይ ቢጠራም እንዲህ ያለው አድራጎት በስሙ ከመሰብሰብ ፈጽሞ የራቀ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ በጌታ ስም ነው ከተባለስ ሌላ ስም ወደመውሰድ መሄዱ ለምን አስፈለገ? ላዳነን ጌታ ልንመሰክርና እርሱንም ልናመልክ ከተሰበሰብን በስሙ ከመሰብሰብ የበለጠስ ምን የከበረ ነገር ይገኛል? ለእውነተኛ አማኞችስ ከዚህ የበለጠ አንድነትን ሊሰጣቸው የሚችል ምን መሰብሰቢያ አለ?