Aclesia  


ስለክርስቶስ አገልጋዮች እንዴት መናገር እንዳለብን

‹‹በፍጥነት ደግሜ የምጽፍልህ በክፉ ንግግር ላይ አንተ ካልከው ጋር የምስማማ በመሆኔ ምክንያት ነው፡፡ በሐሰት ወሬዎች የመጡ የሚያስለቅሱ አጋጣሚዎች እና ጎጂ የሆኑ ስም ማጥፋቶች በእኔ ፊት ቀርበዋል፡፡ እነዚህ ነገሮች በፍጥነት ተቀባይነት እንዲያገኙና እንዲሰራጩ ያለው ዝግጁነት የሚያስነባ በደል እንደሆነ እና ንስሐ ካልገባንም በቀር ጌታ ጣልቃ ገብቶ እንዲፈርድ የሚገደድበት እንደሆነ በእውነት አምናለሁ፤ ላለፉት ረጅም ጊዜያት ራሴው ካላረጋገጥሁ በቀር አንድን ወሬ አላምንም ነበር፡፡›› /ዘጸ.23፡1 ይህንን ኃላፊነት ይጥልብናል፡፡/

ከውስጡ የተወሰደውን ይህንን መልእክት ለያዘው ደብዳቤ የሚከተለው ምላሽ ተሰጥቶ ነበር፡፡ ኅብረት የሚያድገው የሚያገለግሉ ወንድሞችን መልካም ስም በመጠበቅ ነው፡፡ «በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ የሚተጉ» ብዙዎች እንዲኖሩ እመኛለሁ፡፡ ሁሉም የሚያለግሉ ወንድሞች በፍቅር እንዲያስቡ፣ አንዱ ሌላውን በማድነቅ እንዲጽፉና እንዲናገሩ እና ጎጂ ከሆነው እኔነት በላይ መሆናቸውንና በጌታ ነገር አብዝቶ መያዛቸውን እንዲያሳዩ፣ የመንፈስ ቅዱስ ቃል እና ሥራው ለእርሱ ክብር የሚያውሉ እንዲሆኑ ከጌታና ከቅዱሳን ሐዋርያቱ ይማሩ ዘንድ ከልቤ በይበልጥ እመኛለሁ፡፡ እኛ በዚህ ጉዳይ በሚያሳዝን ሁኔታ ጉድለት እንዳለብን እርግጠኛ ነኝ፤አገልጋዩ በፊታችን የሚታየን እርሱ ሰው እንደመሆኑ ያለው ሰብእና ነው፤ እግዚአብሔር ከራሱ ጋር በሰማይ ካከበረው እና ከተሳዳቢዎችና ከተቺዎች ዓለም መልካም ስሙን ከጠበቀለት ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አገልጋዩ ካለው ግንኙነት አንጻር አናየውም፡፡ ዓይኖቼን በአባቱ ዙፋን ላይ ወደተቀመጠው ወደ እግዚአብሔር ልጅ ሳደርግ አንድ ነገር አያለሁ፤ የእርሱን ስም ንጹሕ ለማድረግ ያለውን የእግዚአብሔርን ቁርጠኛ ውሳኔ፡፡ ‹ስለጽድቅም ወደ አብ ስለምሄድ… ነው› እንዳለ/ዮሐ.16፡9/፡፡ እንዲሁም የማስታረቅ አገልግሎት ሰማያዊ ልዑካን የሆኑት የእርሱ መልእክተኞች ለእርሱ እንዴት የቀረቡና የተወደዱ እንደሆኑ ስናውቅ በግልጽ የማይታይ የሐሰት ክስን በግል በእነርሱ ላይ በማንሳት የአገልግሎታቸው ውጤት ሲደናቀፍ እርሱን የሚያስቆጣው እንደሚሆን እንገነዘባለን፡፡ የእርሱ አገልጋዮች ክብሩ እየሰፋ እንዲሄድ ሲሠሩ፣ የክርስቶስ በመሆናቸው ምክንያት አንዱ ለሌላው ግድ የሚላቸው ሲሆኑ የእርሱን ልቡ ደስ ያሰኘዋል፤ ጠባያቸውን ለመቆጣጠር በሁሉም አጋጣሚዎች አብዝተው የሚጠነቀቁ፣ ሐሜተኞችን፣ ወሬኞችንና ክፉ ተናጋሪዎችን የሚያሳፍሩ ሲሆኑ ደስ ይለዋል፡፡

አንድ አገልጋይ ሁል ጊዜ ስለ ክርስቶስ ከፍ ማለት በጣም አስረግጦ እየሰበከ ሳለ ሌሎችን ዝቅ አድርጎ ራሱን ከፍ በሚያደርግ ጊዜ በቅዱሳን መካከል በጣም ክፉ ተጽዕኖ ማሳደሩ ግድ ይሆናል፡፡ እንደዚህ አይነት አገልጋዮች በግል ከቅዱሳን ጋር የሚያደርጉት ንግግር በመድረክ ሲያገለግሉ ከአፋቸው ቅዱሳን ከሰሟቸው ከፍ ካሉ የክርስቲያን ነገሮች ጋር ሲቃረኑ ይህ ሁኔታ አፍራሽ ውጤትን እንደሚያመጣ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ምክንያቱም ከፍ ያሉት ነገሮች በዝቅተኛዎቹ ነገሮች እንዲጠፉ ስለሚደረግ እና የአማኞች ኅሊናም የሚያገለግሏቸው ሰዎች በጣም ምድራዊ በሚሆኑ ጊዜ በሰማያዊ ነገሮች ላይ አንዳች እውነታ እንዳላቸውና እንደሌላቸው ጥያቄ ውስጥ ስለሚገቡ ነው፤ ይህ ካልሆነ ግን/ጥያቄው ካልተነሳ/ ይበልጡኑ የከፋ ነው፡፡ ስለሰማያዊ ነገሮች በአደባባይ በሚሰበኩ ስብከቶች እና በግል ክፉና ሐሰተኛ ነገሮችን እያዳመጡና እያወሩ በመያዝ መካከል ያለ ሞራላዊ ልዩነት የክርስቶስን ክቡር ስም ለማክበርና የእርሱን አገልጋዮች መልካም ስም ለመጠበቅ ከፍ ያለ ስሜት ላላቸው ነፍሳት በጣም መሰናክል መሆኑ የማይቀር ነው፡፡

ጌታ ስለ ራሱ አገልጋዮች የሚናገርበት መንገድ ስለመጥምቁ ዮሐንስ በተናገረው ‹‹እርሱ የሚነድና የሚያበራ መብራት ነበረ››/ዮሐ.5፡35/፣ ‹‹ከነቢይ የሚበልጥ ... እውነት እላችኋለሁ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ አልተነሣም›› በሚለው የታወቀ ንግግሩ ውስጥ ይታያል/ማቴ.11፡11/፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ ስለእውነተኛው ብርሃን ምስክር ሆኖ ነበር፤ አሁን ደግሞ ጌታ የእርሱ ምስክር ሆነ፡፡ ጌታ በዘመኑ ለነበረውና በዚያ ጊዜ በእስር ላይ ለነበረው ለዚህ ታላቅ ሰባኪ በሕዝብ ፊት ከሴቶች ከተወለዱት መካከል የሚበልጥ እንደሆነ በመመስከር በደቀመዛሙርቱ አማካኝነት ማረጋገጫ ሰጥቶታል፡፡ ዮሐንስም ‹‹እርሱ ሊልቅ እኔ ላንስ ይገባል›› በማለት ተናግሮ ነበር፤ ያ ብርሃን /ዮሐንስ/ በቀትር በሚያበራበት ወቅት ኢየሱስ ለሕዝቡ ዮሐንስን በተመለከተ ‹‹እርሱ የሚነድና የሚያበራ መብራት ነበረ›› በማለት መናገር ጀመረ፡፡ እርሱ /ጌታ/ እየላቀ የሄደው ዮሐንስን እያስወገደ ሳይሆን የራሱ በሆነ ክብርና ከሰማይ፣ ከምድር ከሲኦልም ሳይቀር ስለ ድንቅ ሥራዎቹ በነበረው ምስክርነት ነበር፡፡

እርሱ ወድቆ የነበረውን ደቀመዝሙሩን ጴጥሮስን እስኪመልሰው እና በሰጠው ሥራ ሁሉ በእርሱ ላይ ያለውን አመኔታ በፊታቸው እስኪገልጥ ድረስ ዓለምን አልተወም/አላረገም/ ነበር፤ በበዓለ ሃምሳ ዕለትም የመንግሥተ ሰማያትን መክፈቻዎችን በገሃድ ሰጠው፤ አስከፊ በሆነ መልኩ ቢወድቅም በአስራ ሁለቱ መካካል በነበረው ቀዳሚ ስፍራ ጠበቀው፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ በመውደቁ ምክንያት ሊታመን እንደማይችል ሰው አድርጎ ወደጎን አልጣለውም፡፡ ዳግመኛም ይኸው ጴጥሮስ በአንጾኪያ ጳውሎስ ፊት ለፊት የተቃወመውን ተቃውሞ በመርሳት ስለእርሱ /ስለጳውሎስ/ ሲጽፍ ‹‹የተወደደው ወንድማችን›› ይላል /2ጴ¬ጥ.4፡15/፡፡ ይህም በጌታ አርአያ የተቀረጸ የእውነተኛ አገልጋይ ክርስቲያናዊ ሁኔታ ነው፡፡

በመቀጠልም ጳውሎስ ትልቅ አብነት ነው፤ ስለሌሎች ሰዎች በደግነትና በፍቅር የተናገራቸውን ሁሉንም ነገሮችና አብረውት ስለሚሠሩት አገልጋዮች የሰጠውን ምስክርነት በጊዜ ውስጥ ማስታወስ ሊያቅት ይችላል፤ ሆኖም አንድሰው በሮሜ16፤ በ1ቆሮ.16፤ በቈላ.4 ስለተዘረዘሩት ሰዎች ማሰብ ይችላል፡፡ ነገር ግን ጥቂት ምሳሌዎችን ለመምረጥ ያህል እንደሚከተለው እናያለን፤ እርሱ /ጳውሎስ/ ወጣት ወንድሞች በሆኑት በቲቶና በጢሞቴዎስ ላይ ያለውን መተማመንና ለእነርሱ በግል የተናገረውን ነገር እንዲሁም ለፊልሞና የጻፈውን የትህትና መልእክት አስቡ፡፡ እነዚህ ሁሉ በክርስቶስ የሆነ አባትንና የበሰለ እውነተኛ ክርስቲያንን ያሳያሉ፡፡ ‹‹ስለቲቶ የሚጠይቅ ቢኖር ስለእናንተ አብሮኝ የሚሠራ ባልንጀራዬ ነው፤ ስለወንድሞቻችን የሚጠይቅ ቢኖርም የአብያተ ክርስቲያናት መልእክተኞችና የክርስቶስ ክብር ናቸው፡፡›› በማለት ይመሰክራል /2ቆሮ.8፡23/፡፡ ስለጢሞቴዎስም ‹‹ስለዚህ የምወደውንና የታመነውን በጌታ ልጄ የሆነውን ጢሞቴዎስን ልኬላችኋለሁ›› በማለት ይጽፋል /1ቆሮ.4፡17/፡፡ ዳግመኛም በመልእክቲቱ መጨረሻ ‹‹ጢሞቴዎስም የመጣ እነደሆነ በእናንተ ዘንድ ያለ ፍርሃት እንዲኖር ተጠንቀቁ፤ እንደ እኔ ደግሞ የጌታን ሥራ ይሠራልና፤ እንግዲህ ማንም አይናቀው፡፡ ነገር ግን ከወንድሞቹ ጋር እጠብቀዋለሁና ወደ እኔ ይመጣ ዘንድ በሰላም በጉዞው እርዱት፤ ስለወንድማችን ስለ አጵሎስ ግን ከወንድሞቹ ጋር ወደ እናንተ እንዲሄድ እጅግ አድርጌ ለምኜው ነበር፤ ዛሬም ለመምጣት ከቶ ፈቃድ አልነበረውም፤ ሲመቸው ግን ይመጣል፡፡›› በማለት ይጽፋል፡፡ /1ቆሮ.16፡10-12/ ስለአጵሎስ ሲናገር ‹‹አጵሎስ የተግባር ሰው አይደለም፤ ሁል ጊዜ ነገሮችን ከተለያየ አቅጣጫ የሚያይ ነው፤ እርሱን በመለመኔ አዝናለሁ›› የሚል ቃል አልጨመረም፡፡ አጵሎስ የጌታ አገልጋይ ነው የሚያገለግለውም በጳውሎስ ሥር ሆኖ ሳይሆን በጌታ ሥር ሆኖ ነው፤ ጳውሎስም ይህንን አውቆ እንዲሄድ ወይም እንዲቆይ የመወሰኑን ነጻነት ለእርሱው ይተውለታል፡፡ በአጵሎስ በኩል ፈቃድ ቢኖር ያ የእርሱ ጉዳይ ነበር፤ በጳውሎስ በኩል ግን ትእዛዝም ሆነ የመቆጣት ዝንባሌ አልነበረም፡፡

ጳውሎስ ጢሞቴዎስን በስድስት መልእክታቱ ውስጥ ከራሱ ጋር አብሮ እየጠቀሰ በመጻፍ በእርሱ እንዲህ ያለ መተማመን ነበረው /2ቆሮ.1፡1፤ ፊልጵ.1፡1፤ ቈላስ.1፡1፤ 1ተሰ.1፡1፤ 2ተሰ.1፡1፤ ፊልሞ.1፡1/፡፡ ለፊልጵስዩስ ሰዎች ሲጽፍ ‹‹ነገር ግን ኑሮአችሁን ሳውቅ እኔ ደግሞ ደስ እንዲለኝ ፈጥኜ ጢሞቴዎስን ልልክላችሁ በጌታ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እንደ እርሱ ያለ ስለኑሮአችሁ በቅንነት የሚጨነቅ ማንም የለኝምና፤ ሁሉም የራሳቸውን ይፈልጋሉና፤ የክርስቶስ ኢየሱስን አይደለም፡፡ ነገር ግን ልጅ ለአባቱ እንደሚያገለግል ከእኔ ጋር ሆኖ በወንጌል እንደአገለገለ መፈተኑን እናንተ ታውቃላችሁ፡፡›› ብሏል /ፊልጵ.2፡19-22/፡፡ ለተሰሎንቄ ሰዎች ሲጽፍ ደግሞ ‹‹ስለ እምነታችሁም እንዲያጸናችሁና እንዲመክራችሁ ወንድማችንን የእግዚአብሔርንም አገልጋይ ከእኛም ጋር አብሮ የሚሠራውን ጢሞቴዎስን ላክነው›› ብሏል /1ተሰ.3፡2/፡፡ ለራሱም ሲጽፍለት ‹‹በእምነት እውነተኛ ልጄ ለሆነ ለጢሞቴዎስ፣ ... ለተወደደው ልጄ ለጢሞቴዎስ›› ይላል /1ጢሞ.1፡2፤ 2ጢሞ.1፡2/፡፡ ስለጌታ አገልጋዮች ስለማሰብ፣ ስለመናገርና ስለመጻፍ መንፈስቅዱስ በአብነቶች በኩል ያስተማረን የጸጋና የፍቅር መንገድ ይህ ነው፡፡ እነርሱ ለእርሱ የተወደዱ ናቸው፤ስለ እነርሱም መልካም ሲነገር መስማትም የተለየ ደስታን ይሰጠዋል፡፡ አንዲት የቤት ሠራተኛ ለእርስዋ መጥፎ ጠባይን ሰዎች ቢሰጡአት ልትጐዳ እንደምትችል ሁሉ እውነተኛ የክርስቶስ አገልጋይም የስም ማጥፋትና የሐሰት ወሬ ሲደርስበት ታማኝነቱ፣ መልካም ጠባዩና አገልግሎቱ ሊጎዳ ወይም ሊጠፋ ይችላል፡፡ ይህ እንዴት የሚያሳዝን ነው! ይህ እንዴት ኢክርስቲያናዊ ነው! የመተማመን ውሃ ያለበት ጕድጓድ ከተመረዘ የሥነ ምግባር ሞት የማይቀር ይሆናል፡፡

ቤተክርስቲያን ያለችበትን ሁኔታ በተመለከተ ልንጠብቅ የምንችለው ማናቸውም መመለስ /ፈውስ/ መጀመር ያለበት እዚህ ስፍራና በዚሁ ነገር መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ‹‹በመካላችሁ የሚደክሙትን ... ታውቁ ዘንድ ስለሥራቸውም ከመጠን ይልቅ ታከብሯቸው ዘንድ ...›› ይላል /1ተሰ.5፡12-13/፡፡ በጌታ ሥራ የሚደክም እያንዳንዱ አገልጋይ አብሮት ስለሚደክመው አገልጋይ በቸርነትና በፍቅር ያስብ፤ እርሱን እያደነቀው መልካም የሆነ ነገርን ይናገር ይጻፍ፡፡ በዚህም የእርስ በእርስ አንድነት ከምንጩ እያደገ ይመጣል፤ ይህም የአንድነት ምንጭ የቃሉ አገልግሎት ነው፡፡ ስህተቶችን በማወጅ፣ ታላላቅ ክሶችን በማንሳት፣ መሠረት የሌላቸውንና መርዛማ ወሬዎችን በመቀበልና በማሰራጨት ፈንታ እያንዳንዱ ሰው ብዙ ኃጢአቶችን የሚሸፍን የፍቅር መሸፈኛ ሊይዝ ይገባዋል፤ የጌታን አገልጋዮች በተመለከተ ክፉ ወሬን መቀበል የለበትም፤ በተቃራኒው ግን የሐሰት ወሬ የያዙትንና ክፉ የሚናገሩትን በመቃወም መግታት እና የከበረው የክርስቲያን ፍቅር እንዲኖር መሥራት፣ ለወንድሞቹም መልካም ስም ጥንቃቄ ማድረግ ይገባዋል፡፡ በዚህም በቤተክርስቲያን ውስጥ በአገልግሎት ላይ የሚታይ የጸጋ መታደስ፣ የሥነምግባርም መመለስ በቶሎ ይመጣል፡፡

በስኮትላንድ ውስጥ በጌታ ሥራ ላይ ስለነበረ ስለአንድ የተባረከ አገልጋይ እናት የተባለ ነገር አለ፤ ማንኛውም ሰው ስለአንድ ጎረቤት ወይም ወዳጅ ክፉ ወሬን ይዞ ከመጣ ‹ባርኔጣዬን አወርድና ስለእርሱ ይህንን ነገር ወደነገርከኝ ሰው እንሂድ፤ ስለጉዳዩም እናያለን፤ እውነት እንደሆነም እናጣራለን› ብላ ትናገር ነበር፡፡ በዚህ የታመነ አካሄድዋም ክፉ ተናጋሪዎችን ሁሉ ፍርሃት ውስጥ ያስገባች ሲሆን ከዚያ በኋላም በስም ማጥፋት ወሬዎቻቸው አልተቸገረችም፡፡ የልጅዋም ሕይወት በእናቱ የእውነተኝነት ክብር የተቃኘ ነበር፤ በእግዚአብሔር ጸጋ የክርስትናን እውነት ባወቀ ጊዜም ታላቅ የሆነ የቤተክርስቲያን ክንዋኔዎችን የፈጸመ ብቻ ሳይሆን የማይነገር ብዛት ያላቸውን ነፍሳት ወደ መዳን ያደረሰ የታላቅ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ዋነኛ ሰው ሆነ፡፡ ልክ እውነትን እንደምትወደው እንደዚህች እናትና እውነትን እንደሚናገረው ልጅዋ፣ በውስጣችን ያለ እውነት በሌሎች ላይ ተጽዕኖ ማድረግ የሚችል ይሁን፤ ይህም የሥነምግባር ለውጥን ያመጣል፡፡ በማገልገል የሚደክሙቱ ከእርስ በእርስ መካሰስ፣ የዚህን ወይም የዚያን ሁኔታ አስመልክቶ ራስን በማጽደቅ ከማልቀስም ነጻ ሆነው ሐሳባቸው፣ ጊዜያቸው፣ ቋንቋቸው ሁሉ በክርስቶስና በመልካም ነገር ሙሉ በሙሉ እንዲያዝ የተዘጋጀ ሊሆን ይገባል፡፡ የሚከስሰው የተከሰሰውን በማግኘት ፈውስን /መፍትሔን/ የማምጣት ሥራ ቢሠራ የጌታን ሥራ በሚሠሩ መካከል ያሉ ሁሉም ክፉ ተናጋሪዎች ሊጠፉ ይችላሉ፡፡ ይህ ግን ነገሩ በአደባባይ እንዳይገለጥ ከመፍራት ችግሩ ውጫዊ በሆነ መልኩ ብቻ እንዲያቆም ያደርግ ይሆናል፡፡ መሠረታዊው ፈውስ ውስጣዊ መሆን አለበት፤ በመንፈስም ሊሆን ይገባል፡፡ ተግባራዊ የሆነ ጽድቅ፣ ለወንድሞች ያለን ተግባራዊ ፍቅር፣ እና እነዚህን ነገሮች የሚያስገኘው ፍቅር ከእግዚአብሔር የመወለዳችን መለኮታዊ ማረጋገጫዎች ናቸው፡፡ /1ዮሐ.3/

በዚህ ርእስ ላይ ቃልን የመጻፍ አስፈላጊነትን ማሰብ አሳዛኝ ነው፤ ነገር ግን በዚህ መልካም ባልሆነና አጥፊ በሆነ ጠባይ ሁላችንም ይነስም ይብዛ በደለኞች አይደለንምን? እናቴ በጌታ ቀን ከሰአት በኋላ በቤተሰብ ክልል ውስጥ ድምፅዋን አሰምታ በምታነበው ጊዜ ስሰማው የነበረውን ርእሱ ‹‹Dyer’s Golden Chain /የወርቃማ ሰንሰለት ቀለም/›› የተባለ አንድ አሮጌ የቀድሞ ፕሮቴስታንት መጽሐፍን አስታውሳለሁ፤ ያኔ ምንም እንኳ ልጅ ብሆንም /እርስዋ በሞተች ጊዜ 13 ዓመቴ ነበር/፣ እናም በውስጡ ያለውን ትምህርት መውሰድ ባልችልም በውስጡ በሕይወቴ ሁሉ የነካኝና ወሳኝ ምልክትን የሰጠኝ አንድ ነጠላ አገላለጽ ነበር፡፡ ይኸውም ጸሐፊው ስለ ‹‹ቤተክርስቲያን መልአክ›› ሲናገር በመጽሐፉ ውስጥ ‹‹አገልጋዮች መላእክት ተብለው የተጠሩት ባላቸው ክብር ምክንያት ነው፣ ነገር ግን መላእክት በወደቁ ጊዜ አጋንንት ሆኑ›› ያለው ቃል ነው/1ዮሐ.3፡8-10/፡፡ ‹‹ስለዚህ ውሸትን አስወግዳችሁ እርስ በእርሳችን ብልቶች ሆነናልና እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ፤... ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ፡፡ ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ፡፡ መራርነትና ንዴት ቊጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ፡፡ እርስ በእርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፤ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ /ኤፌ.4፡25-32/፡፡


Amharic Bible-|- The Holy Bible [King James Version]