Aclesia  


የክርስቲያኖች ማንነት

አማኞች ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲመስሉ የእግዚአብሔር ውሳኔ ነው፡፡ ጳውሎስ ስለዚህ ጉዳይ ሲጽፍ «ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ወስኗልና» ብሏል/ሮሜ.8፡29/፡፡ በመሆኑም አማኞች ስለማንነታቸው ለሚጠይቋቸው ሰዎች ኢየሱስ ስለማንነቱ በተጠየቀ ጊዜ የሰጠውን ዓይነት መልስ ሊመልሱ ይገባቸዋል፡፡

ጌታ ኢየሱስ በዓመፀኞች ተይዞ በጲላጦስ የፍርድ ወንበር ፊት በቀረበ ጊዜ ስለማንነቱ ተጠይቆ የሰጠው መልስ ለዚህ አብነታችን ነው፡፡ በዮሐ.18፡33-38 ያለውን ስናነብ ጲላጦስ ኢየሱስን «የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን?» ብሎ በጠየቀው ጊዜ ኢየሱስ መልሶ «አንተ ይህን የምትለው ከራስህ ነውን ወይስ ሌሎች ስለ እኔ ነገሩህን?» ሲለው እንመለከታለን፤ ከዚህም የምንረዳው በራሱ በጲላጦስም ሆነ በሌሎች ሰዎች ዘንድ ስለ ኢየሱስ ማንነት የሚባል ነገር እንደነበረ ነው፤ ይኸውም «ኢየሱስ የአይሁድ ንጉሥ ነው» የሚል ነበር፡፡ እንዲህም ሲሉ እርሱ በዚያ ጊዜ በምድር በአይሁድ ላይ መንግሥትን የሚመሠርት የአይሁዳውያን ንጉሥ እንደሆነ ያስቡ ነበር፡፡ በቊ.35 ላይ እንደምናነበው ጲላጦስ «እኔ አይሁዳዊ ነኝን? ወገኖችህና የካህናት አለቆች ለእኔ አሳልፈው ሰጡህ ምን አድርገሃል?» ብሎ ከተናገረው ቃል እንደምንረዳው «ኢየሱስ የአይሁድ ንጉሥ ነው» የሚለውን ነገር ከራሳቸው ከአይሁድ የሰማው ይመስላል፤ አይሁድ ንጉሣችን ነው ብለው አምነውበት ሳይሆን ከቄሣር ቤተመንግሥት ለማጣላት እንዲያመቻቸው «የአይሁድ ንጉሥ ነኝ» ይላል እያሉ በሐሰት ይከሱት ነበር /ሉቃ.23፡2፣ ዮሐ.19፡21/፡፡ እንደዚሁም ምድራዊ ሐሳብ ያላቸው እንደ አይሁድ ያሉ ዓለማዊ ሃይማኖት ያላቸው ሰዎችና እንደ ጲላጦስ ያሉ ምድራዊ አኗኗርን ብቻ የሚከተሉ ሰዎች በጥላቻ ለአማኞች ሐሰተኛ ማንነትን ሊሰጡ ይችላሉ፤ ለመክሰስና ስማቸውን በክፉ ለማንሣት ወይም እንደራሳቸው ዓይነት ምድራዊ ቅርጽ ለመስጠት የሚገምቱትን ማንነት በአማኞች ላይ የመሰላቸውን ሊያስወሩ ይችላሉ፣ ይሁን እንጂ ጌታ ኢየሱስ ለጲላጦስ የሰጠው ቀጣዩ መልስ በእርሱ በኢየሱስ የምናምንና የእርሱ ደቀመዛሙርት የሆንን ሁላችንም ልንሰጠው የሚገባ መልስ ነው፤ እርሱም እንዲህ አለ፤ «መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴስ ከዚህ ዓለም ብትሆን ወደ አይሁድ እንዳልሰጥ ሎሌዎቼ ይዋጉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም» አለ /ቊ.36/፡፡ ጲላጦስ ይህንን ቢረዳ ኖሮ ምንም ዓይነት ስጋት ባላደረበት ነበር፡፡ ዛሬም ሐሳባቸው ምድራዊ የሆነ ሰዎች በእኛ በአማኞች ማንነት ዙሪያ ብዙ ይጨነቁ ይሆናል፤ የእኛ ማንነት ብዙ ያሳስባቸው ይሆናል፤ እኛ ግን በዚህ ዓለም ምንም የለንም፤ ሀገራችንም በሰማይ ነው /ፊልጵ.3፡20/፤ ምክንያቱም የእምነታችን ራስና ፈጻሚ የሆነው ኢየሱስ መንግሥቱ ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚል «በዚህ የምትኖር ከተማ የለችንም» /ዕብ.13፡14/፡፡ በዚህ ዓለም ለጥቂት ጊዜ ስንኖር እንኳ የሚኖረን ስፍራ ኢየሱስ በዚህ ዓለም ይዞት የነበረው የነቀፋ ስፍራ ነው፤ እርሱን የጠላችው ዓለም ደቀመዛሙርቱንም ትጠላለችና፤ ስለዚህ እርሱ በዚህ ዓለም ይኖር በነበረበት መከራ ልንኖር ከእርሱ ጋር ተጣብቀናል፡፡

 

አማኞች «እናንተ እነማን ናችሁ?» የሚለው ጥያቄ ከዚህ ዓለም ሰዎች በተደጋጋሚ ሲቀርበላቸው የሚመልሱትን የመጨረሻ መልስ ከጌታ ከኢየሱስ ይማራሉ፤ የጲላጦስ የምርምር ጥያቄ ቀጥሎ «እንግዲያ ንጉሥ ነህን?» ባለው ጊዜ ጌታችን የመለሰለት ቃል «እኔ ንጉሥ እንደሆንኩ አንተ ትላለህ፤ እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ፤ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል» የሚል ነው /ቊ.37/፡፡ እንደ አይሁድና እንደ ጲላጦስ ያሉ ሰዎች የሚሉንን ያንኑ አባባል የማንነታችን መግለጫ አናደርገውም፤ ያን ምድራዊ ግምታቸውን «እናንተ ትላላችሁ» ብለን ለእነርሱ ልንተወው ይገባል፤ የእኛ የክርስቲያኖች ማንነት ግን በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ከተገለጠው እውነት ጋር የሚነገር ሊሆን ይገባል፡፡ «እኛ ስለ እውነት ልንመሰክር በምድር ላይ የምንኖር ነን፤ ከእውነት የሆነም ይሰማናል» በማለት ራሳችንን በዚህ ዓይነት ልንገልጥ ይገባል፡፡ ምናልባት የዚህ ዓለም ሰዎች ከአንድ የሃይማኖት ጎራ መድበው እነ እገሌ ናቸው እያሉ የመሰላቸውን ሊያስቡም ሆነ ሊናገሩ ይችሉ ይሆናል፤ ያንን ግን የሚሉት እነርሱ ናቸው፤ የክርስቲያኖች ማንነት ግን የሚገኘው «እውነትን ሊመሰክሩ በዚህ ዓለም የሚኖሩ» በሚለው ቃል ውስጥ ነው፡፡

 

ይ ቀ ጥ ላ ል........


Amharic Bible-|- The Holy Bible [King James Version]