ወንድሞች ሆይ ምን እናድርግ?
/የሐ.ሥ.2፡37-42/
መግቢያ
«ወንድሞች ሆይ ምን እናድርግ?» የሚለውን ይህን ጥያቄ ለጴጥሮስና ለሌሎች ሐዋርያት ያቀረቡት መንፈስ ቅዱስ በወረደበትና ቤተክርስቲያን በተመሠረተችበት በበዓለ ሃምሳ ዕለት ጴጥሮስ ስለ ኢየሱስ ጌትነትና ክርስቶስነት በሰበከው ቃል ልባቸው የተነካ የእስራኤል ሰዎች ናቸው፡፡ ይህ በዓለ ሃምሳ የተባለው ቀን እግዚአብሔር ለእስራኤል ከሰጣቸው ሰባት በዓላት መካከል አራተኛው በዓል እንደሆነ ይታወቃል /ዘሌ.23፡15/፤ ይህም በዓል እስራኤል ሁሉ ከያሉበት ስፍራ እግዚአብሔር ስሙ ይጠራበት ዘንድ ወደ መረጠው ስፍራ ተሰብስበው በአንድነት ከሚያከብሯቸው ሦስት በዓላት አንዱ በዓል ነው /ዘዳ.16፡16/፤ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞተ ከተነሣና ካረገ በኋላ በተከበረው በዚህ በዓለ ሃምሳ ላይ ከሰማይ በታች ካሉ ሕዝብ በጸሎት የተጉ አይሁድ እግዚአብሔር ስሙ ይጠራባት ዘንድ ወደ መረጣት ወደ ኢየሩሳሌም /2ዜና.6፡6/ መጥተው ነበር፤ ቢያንስ በዚያን ጊዜ ከታወቀው ዓለም ማለትም በእስያ፣ በአፍሪካና በአውሮፓ አህጉራት ከሚገኙ 15 አገሮች የመጡ አይሁድ እንደነበሩ ልንገነዘብ እንችላለን /የሐ.ሥ.2፡9‐11/፡፡ ኢየሩሳሌም ከወትሮው ይልቅ በብዙ ሺህ ሕዝብ የምትጨናነቅበትና በተለይም በዓሉ የሚከበርበት ቤተመቅደስ በብዙ ያሸበረቀ ሥርዓት የሚደምቅበት ጊዜ እንደሚሆን ማሰብ ይቻላል፤ ይሁንና እግዚአብሔርን በብዙ ለማክበር የተሰበሰበው የእስራኤል ሕዝብ በሥጋ የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ልጅ ያልተቀበለና ከሃምሳ ቀን በፊት ከሰፈሩ ውጭ አውጥቶ የሰቀለ ሕዝብ ነበር፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከሞተው፣ ከሙታን ከተነሣውና በእግዚአብሔር ቀኝ ካለው ጋር የተባበሩት 120 ደቀመዛሙርት በሚኖሩበት ሰገነት ውስጥ በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር፤ ታዲያ በዕለቱ መንፈስ ቅዱስ የወረደውም ለእነርሱ ነበር እንጂ በቤተመቅደስ በዓሉን ለሚያከብሩት አልነበረም፤ በዚህም እግዚአብሔር እስራኤልን ትቶ የኢየሱስ ክርስቶስ ለሆኑት የሰጠውን እውቅና አሳይቷል፡፡
መንፈስ ቅዱስ በሰገነቱ ውስጥ በነበሩት ላይ በወረደ ጊዜ ሕዝቡን ወደዚያ ስፍራ የሰበሰበው ከሰማይ የመጣው ድምፅ ነበር፤ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ሲገልጥ «ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ ድንገት እንደሚነጥቅ አውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምፅ መጣ፤ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሞላው» /የሐ.ሥ.2፡1/ በማለት በዕለቱ የነበረውን ክስተት ከነገረን በኋላ «ይህ ድምፅ በሆነ ጊዜ ሕዝብ ሁሉ ተሰበሰቡ» ይለናል /ቊ.6/፤ በመሆኑም የካህናት አለቆችም ሆኑ የሕዝብ ሽማግሌዎች ሊከላከሉት በማይችሉት መልኩ ለበዓሉ የመጣው ሕዝብ ድምፁ ወደተሰማበት በሰገነቱ ቤት ወደሚኖሩት የክርስቶስ ደቀመዛሙርት መጣ፤ «እያንዳንዱም በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ ይሰማ ስለነበር የሚሉትን አጡ» /ቊ.6/፡፡ አንዳንዶች አመነቱ ሌሎች ደግሞ አፌዙ /ቊ.12‐13/፡፡ ከዚያ በኋላ ጴጥሮስ ከአስራ አንዱ ጋር ቆሞ በቅድሚያ ከትንቢተ ኢዩኤል ቃሉን በመጥቀስ ያዩት ነገር የመንፈስ ቅዱስ ሥራ መሆኑን ካሳያቸው በኋላ «የእስራኤል ሰዎች ሆይ ስሙ» /ቊ.22/ በማለት ስለ ክርስቶስ በሰፊው ሰበከላቸው፤ ጌታ አልፎ በተሰጠባት ምሽት በገረዶችና በሎሌዎች ፊት «አላውቀውም» ብሎ የነበረው ጴጥሮስ /ሉቃ.22፡54(61/ የበዓለ ሃምሳ ዕለት በመንፈስ ቅዱስ በተሞላ ጊዜ በሙሉ ድፍረትና ሥልጣን ስለኢየሱስ መሰከረ፤ ከጌታ የተሰጡትን የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻዎች ተጠቅሞ ለብዙዎች በሩን መክፈት ጀመረ፤ በተለይ በዕለቱ በሰበከው ቃል ውስጥ ትኲረት የሰጠው ጉዳይ ስለ ክርስቶስ ሞት እና ትንሣኤ፣ እንዲሁም ኢየሱስ በእግዚአብሔር ቀኝ ስለመቀመጡ ሲሆን ከመዝሙራት መጽሐፍ እየጠቀሰ ልብን በሚነካ መልኩ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ሰብኮ ነበር፡፡ በስብከቱ ማጠቃለያ ላይም «እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ» አላቸው /ቊ.36/፡፡ ቀደም ሲል በክርስቶስ መገደል የተስማሙት እነዚህ የእስራኤል ሰዎች «እርሱ ሊገደል የቻለው ሰንበትን ስለሻረ፣ ቤተመቅደስን አፈርሳለሁ ስላለ፣ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላለ በመሆኑ፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ይተባበራል» ብለው ያስቡ እንደነበር መገንዘብ ይቻላል፤ ነገር ግን አሁን ያዩትና የሰሙት ነገር እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ሳይሆን ከተሰቀለው ጋር መሆኑን የሚያሳይ ነበር፤ እነርሱ የሰቀሉትን ከሙታን አስነሥቶ በቀኙ በማስቀመጥ ጌታም ክርስቶስም አድርጎታልና፤ ስለሆነም በጴጥሮስ የተሰበከውን ይህን ቃል በሰሙ ጊዜም ልባቸው ተነካ፤ የሰሙት ቃል እነርሱ እንደተሳሳቱና ጥፋተኞች እንደሆኑ ለልባቸው ስላሳያቸው ልባቸው ሊነካ ቻለ፤ ከዚህ በኋላ ከእግዚአብሔር ጋር ለመስማማትና ከፍርድ ለመዳን ምን ማድረግ እንዳለባቸው ስለማያውቁ ጴጥሮስንና ሌሎችን ሐዋርያት «ወንድሞች ሆይ ምን እናድርግ?» ብለው ለመጠየቅ ቻሉ፡፡ ጌታ ይህን ጥያቄ የሚያነሱ ሰዎችን ዛሬም ይፈልጋል፡፡ ሐዋርያት የሰበኩት ክርስቶስ ዛሬም በተለያየ መንገድ እርሱን ለማይከተሉት ሁሉ እየተሰበከ ነው፡፡ እርሱ ስለኃጢአታችን መሞቱ ስለ ጽድቃችን መነሣቱ፣ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ የአካሉ ራስ፣ የእግዚአብሔር ቤት ሊቀካህናት ሆኖ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት እየሠራ እንዳለ ዘወትር እየተነገረ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ስለክርስቶስ ማንነት በሚሰበከው በዚህ የወንጌል ቃል ልባቸውን የነካቸው ሰዎች አንድ ቀን የወንጌልን እውነት የመሰከሩላቸውን ሰዎች ወንድሞች ሆይ ምን እናድርግ? ብለው መጠየቃቸው አይቀርም፤ እነዚያ የእስራኤል ሰዎች እነ ጴጥሮስን ጥቂት ቀደም ብሎ «እነዚህ የሚናገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን? እኛም እያንዳንዳችን የተወለድንበት የገዛ ቋንቋችንን እንዴት እንሰማለን?» ብለዋቸው ነበር፤ ይህም አነጋገር የንቀትና የማቃለል ነበር፤ ምክንያቱም ገሊላ በእነርሱ ዘንድ መልካም የሆነ ነገር ወይም ነቢይ ይገኝባታል ተብላ የማትታሰብ ቦታ እንደሆነች ከሌሎች ንባቦች እንረዳለን /ዮሐ.1፡47፤ 7፡52/፡፡ አሁን ግን በሰሙት ቃል ልባቸው ሲነካ ጴጥሮስንና ሌሎችን ሐዋርያት «ወንድሞች ሆይ» ብለው በመጥራት ምን ማድረግ እንዳለባቸው ለመጠየቅ ቻሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ቀደም ሲል የሚመኩበት የኦሪት ሥርዓት የነበራቸውና ከእነርሱ ውጭ እግዚአብሔር ለራሱ ሕዝብ ሊወስድ እንደሚችል የማያውቁና የማያስቡ ነበሩ፤ ልባቸው ሲነካ ግን ለወንጌል እውነት ተሸነፉ፡፡ በኋላ ላይ በሐዋርያው በጳውሎስ ሕይወት የሆነው ለውጥም እንዲሁ ነበር፤ እርሱ አስቀድሞ ስለ ሕጉ በመቅናት «ቤተክርስቲያንን ያፈርስ ነበር፤ ወደ ሁሉም ቤት በመግባት ወንዶችንም ሴቶችንም እየጎተተ ወደ ወኅኒ አሳልፎ ይሰጥ ነበር» /የሐ.ሥ.8፡1/፤ ይሁን እንጂ በደማስቆ መንገድ ላይ ጌታ ባገኘው ጊዜ እየተንቀጠቀጠና እየተደነቀ «ጌታ ሆይ ምን አደርግ ዘንድ ትወዳለህ?» ነበር ያለው፤ ዛሬም አፍኣዊ በሆነ ሥርዓት እግዚአብሔርን ያገለገሉ የሚመስላቸው ሰዎች በክርስቶስ ፍቅርና በወንጌል እውነት ሲሸነፉ «ምን እናድርግ?» የሚለውን ይህን ጥያቄ ሊጠይቁ ይገባል፤ ስለኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ በወንጌል የሚሰሙ ሁሉ ይህን ጥያቄ ቢጠይቁ ነፍሳቸውን የሚያሳርፍ ምላሽ ያገኛሉ፡፡
ጌታ ይህን ጥያቄ የሚያነሡ ሰዎችን ዛሬም ይፈልጋል፡፡ ሐዋርያት የሰበኩት ክርስቶስ ዛሬም በተለያየ መንገድ እርሱን ለማይከተሉት ሁሉ እየተሰበከ ነው፡፡ እርሱ ስለኃጢአታችን መሞቱ ስለ ጽድቃችን መነሣቱ፣ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ የአካሉ ራስ፣ የእግዚአብሔር ቤት ሊቀካህናት ሆኖ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት እየሠራ እንዳለ ዘወትር እየተነገረ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ስለክርስቶስ ማንነት በሚሰበከው በዚህ የወንጌል ቃል ልባቸውን የነካቸው ሰዎች አንድ ቀን የወንጌልን እውነት የመሰከሩላቸውን ሰዎች ወንድሞች ሆይ ምን እናድርግ? ብለው መጠየቃቸው አይቀርም፤ እነዚያ የእስራኤል ሰዎች እነ ጴጥሮስን ጥቂት ቀደም ብሎ «እነዚህ የሚናገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን እኛም እያንዳንዳችን የተወለድንበት የገዛ ቋንቋችንን እንዴት እንሰማለን?» ብለዋቸው ነበር፤ ይህም አነጋገር የንቀትና የማቃለል ነበር፤ ምክንያቱም ገሊላ በእነርሱ ዘንድ መልካም የሆነ ነገር ወይም ነቢይ ይገኝባታል ተብላ የማትታሰብ ቦታ እንደሆነች ከሌሎች ንባቦች እንረዳለን/ዮሐ.1፡47፤ 7፡52/፡፡ አሁን ግን በሰሙት ቃል ልባቸው ሲነካ ጴጥሮስንና ሌሎችን ሐዋርያት «ወንድሞች ሆይ» ብለው በመጥራት ምን ማድረግ እንዳለባቸው ለመጠየቅ ቻሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ቀደም ሲል የሚመኩበት የኦሪት ሥርዓት የነበራቸውና ከእነርሱ ውጭ እግዚአብሔር ለራሱ ሕዝብ ሊወስድ እንደሚችል የማያውቁና የማያስቡ ነበሩ፤ ልባቸው ሲነካ ግን ለወንጌል እውነት ተሸነፉ፤ በሐዋርያው በጳውሎስ ሕይወት የሆነው ለውጥም እንዲሁ ነበር፤ እርሱ አስቀድሞ ስለ ሕጉ በመቅናት «ቤተክርስቲያንን ያፈርስ ነበር ወደ ሁሉም ቤት በመግባት ወንዶችንም ሴቶችንም እየጎተተ ወደ ወኅኒ አሳልፎ ይሰጥ ነበር» /የሐ.ሥ.8፡1/፤ ይሁን እንጂ በደማስቆ መንገድ ላይ ጌታ ባገኘው ጊዜ እየተንቀጠቀጠና እየተደነቀ «ጌታ ሆይ ምን አደርግ ዘንድ ትወዳለህ?» ነበር ያለው፤ ዛሬም አፍኣዊ በሆነ ሥርዓት እገዚአብሔርን ያገለገሉ የሚመስላቸው ሰዎች በክርስቶስ ፍቅርና በወንጌል እውነት ሲሸነፉ «ምን እናድርግ?» የሚለውን ይህን ጥያቄ ሊያነሱ ይገባል፤ ስለኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ በወንጌል የሚሰሙ ሁሉ ይህን ጥያቄ ቢያነሡ ለነፍሳቸው ጥያቄ የሚያሳርፍ ምላሽ ያገኛሉ፡፡ የበዓለ ሃምሳ ዕለት «ወንድሞች ሆይ ምን እናድርግ?» የሚለውን ጥያቄ ላቀረቡት ሰዎች ምን ምን ማድረግ እንዳለባቸው በጴጥሮስ በተሰጠው መልስ የተገለጸ ሲሆን ከዚያም እነርሱ በምን በምን ይተጉ እንደነበር ተነግሯል፤ ይኸውም «ጴጥሮስም ንስሐ ግቡ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ፤ የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ ጌታ አምላካችንም ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ሁሉ ነውና አላቸው፤ በብዙ ሌላ ቃልም መሰከረና ከዚህ ጠማማ ትውልድ ዳኑ ብሎ መከራቸው፡፡ ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ በዚያም ቀን ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስ ተጨመሩ፤ በሐዋርያትም ትምህርትና በኅብረት እንጀራውንም በመቊረስ በየጸሎቱም ይተጉ ነበር» ይላል /የሐ.ሥ.2፡38‐42/፡፡ ቤተክርስቲያን በተመሠረተችበት በዚያ የመጀመሪያ ቀን የተሰጡት እነዚህ መልሶችና በመጀመሪያቱ ቤተክርስቲያን ሲደረጉ የነበሩ ነገሮች ዛሬም ቢሆን በወንጌል ቃል ልባቸው የተነካ ሰዎች በመቀጠል ምን ማድረግ እንዳለባቸው ትምህርትን የሚሰጡ በመሆናቸው እያንዳንዳቸውን ቀጥሎ እንመለከታቸዋለን፡፡
የበዓለ ሃምሳ ዕለት «ወንድሞች ሆይ ምን እናድርግ?» የሚለውን ጥያቄ ላቀረቡት ሰዎች ምን፣ ምን ማድረግ እንዳለባቸው በጴጥሮስ በተሰጠው መልስ ውስጥ የተገለጸ ሲሆን ከዚያም እነርሱ በምን፣ በምን ይተጉ እንደነበር ተነግሯል፡፡ ይኸውም «ጴጥሮስም ንስሐ ግቡ፤ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ፤ የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ ጌታ አምላካችንም ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ሁሉ ነውና አላቸው፤ በብዙ ሌላ ቃልም መሰከረና ከዚህ ጠማማ ትውልድ ዳኑ ብሎ መከራቸው፡፡ ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ፤ በዚያም ቀን ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስ ተጨመሩ፤ በሐዋርያትም ትምህርትና በኅብረት እንጀራውንም በመቊረስ በየጸሎቱም ይተጉ ነበር» ይላል /የሐ.ሥ.2፡38‐42/፡፡ ቤተክርስቲያን በተመሠረተችበት በዚያ የመጀመሪያ ቀን የተሰጡት እነዚህ መልሶችና በመጀመሪያይቱ ቤተክርስቲያን ሲደረጉ የነበሩ ነገሮች ዛሬም ቢሆን በወንጌል ቃል ልባቸው የተነካ ሰዎች ቀጥለው ምን ማድረግ እንዳለባቸው ትምህርትን የሚሰጡ በመሆናቸው እያንዳንዳቸውን ቀጥሎ እንመለከታቸዋለን፡፡
1. ንስሐ
ልባቸው በቃሉ ተነክቶ «ወንድሞች ሆይ ምን እናድርግ?» ላሉት ሰዎች በመጀመሪያ የተሰጣቸው ምላሽ «ንስሐ ግቡ» የሚል ነው፡፡ «ንስሐ» የሚለው ቃል አማኞች ከሥጋ ድካም የተነሳ ኃጢአትን በሚሠሩ ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ኅብረት የሚያድሱበትን መንገድ ጭምርም የሚያመለከት ሲሆን በዚህ ስፍራ ላይ ግን ክርስቶስን ላላመኑና ላልተከተሉ ሰዎች የቀረበ ጥሪ ነው፤ ይህም ንስሐ ያላመኑ ሰዎች ያለክርስቶስ በነበሩበት ባለፈው ዘመን ሁሉ ተጸጽተውና በራሳቸው ፈርደው ወደ ጌታ ዘወር እንዲሉ የሚያደርግ ነው፡፡ በሮሜ.3፡11 ላይ «ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ» ሲል በቊ.23 ላይ ደግሞ «ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሏቸዋል» ይላል፡፡ በኤፌ.2፡1 ላይም «በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ» ተብሎ ተጽፏል፡፡ ስለዚህ ማንኛውም ሰው ኢየሱስን ካላመነ ኃጢአተኛ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ አስረግጦ ይናገራል፡፡ ኃጢአት ወደ ዓለም የገባው በአንድ ሰው በአዳም በኩል መሆኑን ሲናገርም «ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ፣ በኃጢአትም ሞት፤ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ፡፡» ይላል /ሮሜ5፡12/፤ ስለዚህ ኃጢአት በሰው ውስጥ ከመወለዱ ጀምሮ አብሮት የሚኖር ለእግዚአብሔር ያለመታዘዝ ጠባይ ነው፤ በዚህ ጠባዩም በሐሳብ፣ በመናገርም ሆነ በተግባር የሚሠራው ኃጢአት አለ፤ ከዚህ ሁሉ የሚበልጠው ኃጢአት ግን ከኃጢአት የሚያድነውን አዳኝ ኢየሱስን አለማመን ነው፤ ጌታ ራሱ በእርሱ አለማመን ኃጢአት መሆኑን ሲናገር «እኔ እንደሆንሁ ባታምኑ በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁ» ብሏል /ዮሐ.8፡24/፤ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ ዓለምን ስለኃጢአት የሚወቅስበትን ምክንያት ኢየሱስ ሲናገር «ስለኃጢአት በእኔ ስለማያምኑ ነው» ብሏል /ዮሐ.16፡10/፡፡
ሰዎች እንደ አሕዛብ ያለ ሕግ ቢኖሩ ወይም እንደ እስራኤል ከሕግ በታች እንኳ ሆነው ቢኖሩ ኢየሱስን ካላመኑ ከኃጢአት በታች መሆናቸው የማይቀር ነው፤ በመሆኑም «ንስሐ ግቡ» የሚለው መልእክት በኢየሱስ ያላመኑትን ሁሉንም ዓይነት ሰዎችን ይመለከታል፡፡ ይህም ንስሐ እነዚህ ሰዎች በኃጢአታቸው መፍረዳቸውን የሚገልጽ ሲሆን ይህም ኢየሱስን ሳያምኑ በኃጢአት በኖሩበት ባለፈው ኑሮአቸው ተጸጽተው ከዚህ በኋላ ግን ኢየሱስን አምነው ለመከተል መወሰናቸውን የሚያመለክት ነው፤ ስለሆነም ንስሐና በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን እርስ በእርሳቸው የተያያዙና የማይነጣጠሉ ናቸው፡፡ ንስሐ ኢየሱስን ወደማመን የሚያደርስ ነውና፡፡ ይህም የሁለቱ ተያያዥነት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በማር.1፡15 ላይ «ዘመኑ ተፈጸመ፤ ንስሐ ግቡ በወንጌልም እመኑ» ብሎ በተናገረው ቃል ውስጥ ይታያል፤ እንደዚሁም ሐዋርያው ጳውሎስ «ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ንስሐንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ለአይሁድና ለግሪክ ሰዎች እየመሰከርሁ በጉባኤም በየቤታችሁም አወራሁላችሁና አስተማርኋችሁ እንጂ ከሚጠቅማችሁ ነገር አንዳች ስንኳ አላስቀረሁባችሁም» ብሎ ለኤፌሶን ቤተክርስቲያን ሽማግሌዎች በተናገረው ቃል ውስጥ ንስሐንና በኢየሱስ ማመንን በአንድ ላይ አያይዞ የተናገረ መሆኑን እናያለን /የሐ.ሥ.20፡21/፡፡ በእርግጥም ኢየሱስን ባለማመን ባሳለፈው ዘመን ከኃጢአት በታች እንደኖረ የተሰማውና በዚህም ተጸጽቶ ንስሐ የሚገባ አንድ ሰው ወዲያውኑ ኢየሱስን ወደማመን ሊመጣ ይገባዋል፤ ኢየሱስ ከኃጢአት የሚያድን ብቸኛ አዳኝ ነውና፡፡ ይህን መልእክት ስታነቡም ክርስቶስን ካለማመናችሁ የተነሣ በኃጢአት እየኖራችሁ እንዳለ የተረዳችሁና በወንጌል ቃል ልባችሁ ተነክቶ ምን እናድርግ የምትሉ ሁሉ በኃጢአታችሁ እንዳትሞቱ አሁኑኑ ንስሐ ግቡ፤ በኢየሱስ እመኑ እንላለን፡፡