ታውቃለህን?
መልስህ «አዎ» ሊሆን ይችላል፡፡ከአንዳንድ ጥቂት ሁኔታዎች አንጻር በሐሳቡ ትክክል ነህ፡፡ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እንደዚህ ዘመን ያለ የመረጃ /Information/ ክምችት ታይቶ አይታወቅም፡፡ ታዋቂ የሆነ አንድ የጊዜያችን መጽሐፍም «መረጃ ያለው ኅብረተሰብ» በሚል ርእስ የቀረበውም ያለ በቂ ምክንያት አልነበረም፡፡
ራዲዮና ጋዜጦች የተለያዩ የመረጃ ዘገባዎችን ሳያቋርጡ ማቅረባቸውን ቀጥለዋል፡፡ በሳይንስና ቴክኖሎጂ በኩል እየተመዘገበ ባለው አመርቂ ውጤትም ኮምፒዩተሮቻችን መረጃዎችን ዘወትር ያቀብሉናል፡፡ ዛሬ ዛሬ ለስሌት አስቸጋሪና ከባድ የሆኑ የዘመናት ቀመሮችንና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እውነታዎችንም አንዲትን ቊልፍ ብቻ በመጫን ማግኘት ተችሏል፡፡
በአጠቃላይ ዛሬ ብዙ ነገር ተሰጥቶሃል፤ ብዙም ነገር ተገልጦልሃል፤ ስለ ብዙ ነገሮች በቂ መረጃ አለህ፡፡ ስለ መኪኖች፣ ስለ ስፖርቶች፣ ስለሌሎችም በርካታ ነገሮች በቂ እውቀቶች አሉህ፤ ስለነጭና ጥቁር ወይም ስለከለር ቴሌቪዥን ብዙ ታውቃለህ፤ ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ደስተኛ አድርገውሃልን? ፈጽሞ አላደረጉህም፡፡ በአንጻሩ ዛሬ «ተዝናኑ» የሚለው ተግባራዊ አመለካከት በስፋት ይለፈፋል፤ በተቃራኒው ግን የዚህ ተገላቢጦሽ የሆኑት ብቸኝነት፣ ፍርሃት፣ ጭንቀትና ተስፋ መቁረጥ እንደአሁኑ ጊዜ በሰፊው ተንሰራፍተው አያውቁም፡፡ ይህ ደግሞ አንተ ያለህ መረጃ እውነተኛ ላለመሆኑ ሁነኛ ማስረጃ ነው፡፡ ምን እንደሳትክና እንደዘነጋህ ታውቃለህን? እውነቱን በግልፅ የሚያሳይህና ወደ ተፈላጊው ነጥብ የሚያደርስህን ትክክለኛ መረጃ ነው፡፡
መረጃ ቊጥር 1
የሕይወትህ ጎዳና ወዴት እያመራህ ነው?
ይህን ጥያቄ ጠይቆህ የሚያውቅ ሰው አለን? ጥያቄው በግልጽና በቀላሉ ይህ ነው፤ «የሕይወትህ ጎዳና ወዴት እያመራህ ነው?» መልሱ «ያለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ጥፋት እያመራህ ነው» የሚል ነው፡፡ ይህ በእርግጥም በጣም አስፈላጊ የሆነ መረጃ ነው፣ መረጃ ቊጥር አንድ፡፡ ብዙዎች ስለዚህ አንዳችም የሰሙት ነገር የለም፡፡ ቢሆንም ይህ ሊሻር የማይችል ሐቅ ነው፡፡ ለምን? ብንል ይህ መረጃ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ያለ እውነት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ለመረዳት አስቸጋሪ ባልሆኑ ቃላት ሰው በራሱ ተፈጥሮ በእግዚአብሔር ፊት የመቆም ብቃት እንደሌለው ይናገራል፡፡ እግዚአብሔር ለሰዎች ደኅንነትን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ሰጥቷል፡፡ ይህንንም እስካሁን በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ምናልባት ይህ ስጦታ ነገም መሰጠt ግን አጠያያቂ ነው፡፡ ነገር ግን «ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን» በተመለከተ በጽኑ ቃል እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፤ «በዘላለምም ጥፋት ይቀጣሉ» /2ተስ.1፡8-10/፡፡
«የዘላለም ጥፋት ማለት ምን ማለት ነው? ይህ ዘላለማዊነትን የሚገልጽ ነው፤ እኔ ግን በዚህ አላምንም፤ የሁሉም ነገር ማክተሚያ ሞት ብቻ እንደሆነ አስባለሁ» ብለህ የምታስብ ትሆናለህ፡፡ እግዚአብሔር በቃሉ ሙታን ሁሉ እንደሚነሡ አስረግጦ ስለሚናገር ይህ ሐሳብህ አደገኛ የሆነና የተሳሳተ አመለካከት ነው፡፡ ምናልባትም «ከሞትኩ በኋላ መነሣት አልፈልግም፤ መሻቶቼን በተጣራ መንገድም ይሁን አይሁን ለማርካት የሞከርኩት እዚህ ምድር ላይ ሳለሁና አሁን ባለኝ ዘመን ነው፤ በእርግጥ ለመናገር ውጤት እንዳላገኘሁበት አምናለሁ፤ ዕረፍት ማጣቴም ጨምሯል፤ እኔ በብዙም ይሁን ባነሰ ደረጃ በደለኛ መሆኔን እቀበላለሁ፤ እንዲህ ከሆነ ደግሞ ከሙታን መነሣት አልፈልግም» የምትል ትሆናለህ፡፡
ለምን አትፈልግም- ይህ ከሙታን ለመነሣት ያለመፈለግህ እንቅፋቶችን ሁሉ ለማስወገድ ጠንካራ ኃይል ቢኖርህም ስለ ዘላለማዊነትና ስለ ፍርድ አንዳች ሐቅና ስሜት በውስጥህ በጥልቀት መሥረፁን ያሳያል፤ አንድ ነገር በጣም እርግጥ ነው፤ ፈለግህም አልፈለግህም ጥያቄና ምርጫ ሳይቀርብልህ ከሞትክ በኋላ ትነሣለህ፡፡ ቅዱስ የሆነው እግዚአብሔር በቅዱስ ቃሉ በኩል ይገናኝሃል፡፡ «ለሰዎችም አንድ ጊዜ መሞት ከእርሱ በኋላም ፍርድ እንደተመደበባቸው እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸከም አንድ ጊዜ ከተሠዋ በኋላ ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጠአት ይታይላቸዋል» /ዕብ.9፡27-28/፡፡
ምናልባት የተለያዩ መሰናዶዎችን ለሞት ሥርዓትህ ታዘጋጅ ይሆናል፡፡ ምናልባትም ከሞትክ በኋላ ሬሳህ እንዲቃጠል ትናዘዝም ይሆናል፡፡ ከዚህ ሌላ ምንም ምርጫ የለህም፤ ስለዚህም ከእግዚአብሔርና ከፍርዱ ፈጽሞ ልታመልጥ አትችልም፡፡ እግዚአብሔር ይህንን የመፍረድ ሥልጣን ሰዎች በመስቀል ላይ ለሰቀሉት ለልጁ ሰጥቶታል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር «የሰው ልጅም ስለሆነ ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን ሰጠው.... በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል.... በዚህ አታድንቁ ይላል /ዮሐ.5፡27-29/፡፡ አንተንም ጨምሮ ሰዎች ሁሉ በፊቱ ይቀርባሉ፡፡ የተቀበሩ፣ የተቃጠሉ በባህር የሰጠሙ ሁሉ በፊቱ ይቆማሉ፡፡
በዮሐንስ ራእይ ምዕራፍ 20 ከቊጥር 11-15 ድረስ ያሉትን አስፈላጊ ቃሎች አንብብ፤ እነዚህ የማይሻሩና የማይጣሉ የእውነት ቃሎች ናቸው፡፡ አንተን የበለጠ ለማስገንዘብና ለመርዳት እንዲህም ተብሎ ተጽፏል፤ «ለሕዝብም እንድንሰብክና በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ በእግዚአብሔር የተወሰነ እርሱ እንደ ሆነ እንመሰክር ዘንድ አዘዘን፡፡ በእርሱ የሚያምን ሁሉ በስሙ የኃጢአቱን ሥርየት እንዲቀበል ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል» /የሐዋ. ሥራ. 10፡42-43/፡፡
«አልተረዳሁትም»
በጥያቄዎች፣ በተቃረኑ ሐሳቦች፣ «እንዲህ ቢሆንስ» በሚሉ ሐሳቦች «ነገር ግን» በሚሉ ዓረፍተ ነገሮች የተሞላህ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ «በእግዚአብሔር ቃል፣ በኢየሱስ ፍርድ፣ በትንሣኤ፣ በዚህ ሁሉ አላምንም፣ አይገባኝምም፡፡ሁሉም ነገር የተጋነነና ያለ አግባብ የተገለጠ ነው፤ ከዚህ የተነሣ ከእውነታው የራቀ ነውና» ትላለህ፡፡
ለአንድ አፍታ ላቋርጥህ፡፡ እንደዚህ እያልክ ሐቁን መቃወምህ ተፈጥሮአዊ ያልሆነ ተደርጐ ሊወሰድ አይገባም፡፡ ይልቁኑ በጣም ተፈጥሯዊ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን እንዲህ በማለት ያጸናዋል፡፡ «ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፡፡ በመንፈስም የሚመረመር ስለሆነ ሊያውቀው አይችልም» /1ቆሮ.2፡14/፡፡ በሌላ ስፍራ ደግሞ «የመሰቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና» በማለት ይናገ ራል /1ቆሮ.1፡18/፡፡
ለዐይነ ስውር በዓይኖቹ ማየት አለመቻሉ የዐይነ ስውርነቱ ማስረጃ እንደሆነው ሁሉ አንተም መረዳት አለመቻልህና ለመረዳት አለመፈለግህ እንደዚሁ ለመጥፋትህ በጣም ግልጽ የሆነ ማስረጃ ነው፡፡ ይህ ጽኑ እውነት ነው፤ እግዚአብሔር እኛን አይሸነግለንም፡፡ ቅዱስ ቃሉ በግልጽና በጉልህ ይናገራል፡፡
መልካም ምግባር ያላቸውና ብልሹ ምግባር ያላቸው
ሁሉም ማለት ነው፤ ምግባረ ብልሹዎች ብቻ ሳይሆኑ መልካም ምግባር ያላቸው ዜጎችም ናቸው፤ በወጣትነት አፍላ እድሜ ላይ የሆኑ ሴቶችና ወንዶች ልጆችም ብቻ አይደሉም፡፡ ፈጽሞ እንዲህ አይደለም፤ «ሁል ጊዜ መልካሙን አድርግ እናም ማንንም አትፍራ» የሚል መመሪያ ያላቸውም በሙሉ የጠፉ ናቸው፡፡ ልዩነት የለም ሁሉም ጠፍተዋል፡፡ የጠፋህ መሆንህን ለመግለጽ ባንክ መዝረፍ አልያም የትዳር ጓደኛህን ማታለል አያስፈልግህም፤ አሁን እንዳለህ ሆነህ አንተ የጠፋህ ነህ፡፡ «እንደዚህ ያለውን ነገር ሊናገር ማን ይችላል? በጥቅሉ ሰዎች ሁሉ የተለያዩ ናቸው፡፡ መልካም ሰዎችና መጥፎ ሰዎች አሉ፤ በጣም መጥፎ ሰዎችና በጥቂቱ መጥፎ ሰዎች፣ በጣም መልካም ሰዎችና በጥቂቱ መልካም ሰዎች አሉ» ብለህ ታስብ ይሆናል፤ ከራሳችን አመለካከት ስንነሳ ይህ በራሱ ስህተት አይደለም፤ ይህ ሁሌም በሕይወት ልምዳችን የሚያገኘን ገጠመኝ ነው፡፡ በዕለት ተዕለት ሕይወቱ ውስጥ ይህን መሰል ልዩነቶችን ማስተዋል የማይችል ሰው ለእውነታው ባይተዋር ወይም እንግዳ የሆነ ሰው ብቻ ነው፡፡ ስለ ራሳቸው በጣም የሚያስቡ ራስ ወዳድ ሰዎች አሉ፡፡ ዘወትር የሚሹት የራሳቸውን ጥቅም ብቻ ነው፡፡ እንደዚሁም ደግሞ ራሳቸውን ለሌሎች አሳልፈው የሚሰጡ፣ ሌሎችን ለመርዳት ዝግጁ የሆኑ፣ ስለ ሌሎች አብዝተው የሚጨነቁ፣ ለሌሎች መልካምን ነገር የሚያደርጉ ሰዎች አሉ፡፡
ይህ ከእኛ አኳያ ያለ አመለካከት ነው፤ ይህም አመለካከት ሙሉ ለሙሉ በተበላሸችው ዓለም ጭጋግ የተበከለ ነው፤ ይህም ጭጋግ እንደመርዛማ እንፋሎቶች በተፈጥሮ መንፈሳዊ አድማሳችን ዝቅተኛ ስፍራ ላይ የተንጣለለ ነው፡፡ ይሁንና ነገሮች ከላይ ከሰማይ ሲስተዋሉ ያላቸው ገጽታ ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው፤ በእጅጉ የተለየ፡፡ ይህ ሰማያዊ የሆነ የእግዚአብሔር ምልከታ ደግሞ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ «የሚያስተውል እግዚአብሔርን የሚፈልግ እንዳለ ያይ ዘንድ እግዚአብሔር ከሰማይ የሰው ልጆችን ተመለከተ፤ ሁሉ በደሉ አብረውም ረከሱ፤ አንድ ስንኳ በጎን ነገር የሚያደርጋት የለም»/መዝ.52-53-፡3/፤ ሰማያዊው የእግዚአብሔር እይታ እንደዚህ ያለ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም «ልዩነት የለምና ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና፡፡ ...» /ሮሜ.3፡22-23/ ተብሎ ተጽፏል፡፡
ይህ «ሁሉም ኃጢአትን ሠርተዋል» ሲል በመልካም ሥራቸው የሚታወቁት ሁሉ ያለስህተት አይደሉም ለማለት አይደለም፤ በደለኞች ናቸው ማለት እንጂ፡፡ በአንድ በኩል መልካምና ጨዋ ሰዎች ተብለው በሚፈረጁትና በሌላው ወገን መጥፎ ወይም እኩይ ተብለው በሚመደቡት መካከል ያለው ልዩነት ወደ ጥያቄ ሳይገባ ሁሉም በደለኞች ናቸው ማለት ነው፤ «ልዩነት የለምና» እንደተባለ፡፡
የእኛ አመለካከት የሰው የሆነና ፍጥረታዊ አመለካከት ነው፡፡ ነገር ግን የሚቆጠረው ወይም ሥራ ላይ የሚውለው የእግዚአብሔር መስፈርት ነው፡፡ እንዲህ ስንል ግን እኛ በጉልህ የምናየውን፣ በመልካም ሰዎችና በእኩይ ሰዎች መካከል ያለውን ቀጭን መስመር እግዚአብሔር አይመለከተውም ማለት አይደለም፡፡ ይህ ሁሉን ማየት ከሚችለው ከእርሱ እንዴት ሊሰወር ይችላል- ነገር ግን ይህ በመለኮታዊ ብያኔ ውስጥ ምንም ስፍራ የለውም ማለታችን ነው፤ ሁሉም ኃጢአተኞች ናቸውና፡፡
ሰማርያ በሚገኘው የያዕቆብ ጉድጓድ ለጌታ ኢየሱስ የብቸኝነት ጊዜ ነበር፤ ብርቱ የቀትር ሐሩርም ነበር፤ ጌታ ኢየሱስ ሰው ዝር በማይልበት በዚህ አስቸጋሪ ሰዓት አንዲት ሴት ውኃ ልትቀዳ ስትመጣ ተመለከተ፡፡ ሴቲቱ ይህን ሰዓት የመረጠችበት የራሷ የሆነ ምክንያት አላት፤ ሥነ ምግባራê ባህርይዋ የተበላሸ ስለሆነ ብዙዎች የሚያንጓጥጧት በጣታቸውም የሚጠቋቆሙባት ሴት ናት፡፡ «የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን የመጣው» /ሉቃ.19፡10/ ጌታ ኢየሱስ ግን ይቺን ሴት ከሳሾችዋ እንደሚመለከቷት አልተመለከታትም፤ እንደ እነርሱም አላዋረዳትም፤ አልዘለፋትም፤ ይልቁንም አብዝቶ ተጠነቀቀላት፡፡ አዎ በእርግጥ የእሷ ነገር ግድ ብሎት አስቸጋሪ ጉዞ በማድረግ ወደ እዚህ ስፍራ መጥቷል፡፡ አሁን ለእርሷ ምን ይላት ይሆን- «የእግዚአብሔርን ስጦታና ውኃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑንስ ብታውቂ አንቺ ትለምኚው ነበርሽ፤ የሕይወትም ውኃ ይሰጥሽ ነበር» /ዮሐ.4፡10/ በማለት በዚህ ንግግሩ ትኲረቷን እርሷ በጣም ወደምትሻው ነጥብ በመሳብ እጅግ አስፈላጊ የሆነ ውይይት ከእርሷ ጋር አደረገ፡፡ በእርግጥም የእግዚአብሔር ስጦታ፣ እርሱም ጌታ ኢየሱስ ራሱ፣ እንዲሁም ሕይወት የሚያስፈልጋት ነበረች፡፡ በዚህም ጌታ የተገፉና ከኅብረተሰቡ የተገለሉትን ምን ያህል እንደሚወዳቸው እንመለከታለን፡፡ እርሱ እንደነዚህ ያሉትን ቸል አይላቸውም፡፡
በአንድ ሌሊት የሆነን ሌላ ታሪክ እንመልከት፡- ከፈሪሳውያን ወገን የሆነ የሥነ መለኮት መምህር እና የአይሁድ አለቃ የሆነ ሰው ወደ ኢየሱስ መጣ፡፡ ይህ ሰው በብዙዎች ዘንድ ከፍተኛ ክብር ያለው ሰው ነው፡፡ በሕዝቡም ዘንድ መምህር እና ዳኛ ተደርጐ ይቈጠራል፡፡ በባህርይው የተቸገረን ለመርዳት የተዘጋጀና ትሑት የሆነ መልካም ሰው ነው፡፡ ይህ ሰው አንዳች መልእክትን ለማግኘት በሚችልበት ጠቃሚ የጉዞ መስመር ላይ ወደ ኢየሱስ ሄደ፤ እናም ጌታ ኢየሱስ «ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም» አለው/ዮሐ.3፡3/፡፡ ሁሉም መልካም ምግባራትና ሁሉም የትምህርት ደረጃዎች የሚረዱት ነገር የለም፡፡ የሰዎች ኃይልም ቢሆን፣ በትምህርት የሚገኝ ድግሪና፣ የሰዎች እውቀት ሁሉ አይጠቅሙም፡፡ ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ አትኲሮቱን አስፈላጊና ወሳኝ ወደ ሆነው ነጥብ በማምጣት ስለ ዳግም መወለድ፣ ፍጹም ስለሆነው ለውጥ፣ ሙሉ ለሙሉ አዲስ ስለሆነው ፍጥረት፣ ስለ እውነተኛው ሕይወት እና ስለ ራሱ ጭምር ለዚህ በጣም ለተከበረው ሰው ነገረው፡፡
በጎ ምግባር ያለውም ሆነ የሌለው ወይም ጥሩ የሚባለውም ሆነ መጥፎ የሚባለው፣ ሁሉም ጌታ ኢየሱስ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ያለ እርሱ ሁሉም የጠፉ ናቸው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ደግሞ ስለዚህ የሚናገረው በግልጽ ነው፡፡
ሁለት ሰዎች በባቡር ተሳፍረው ሲጓዙ አንደኛው በባቡሩ ውስጥ እንዳለ መልካም የሆነ ነገር እየሠራ ሲጓዝ ባንጻሩ ሌላኛው ደግሞ አንዳች የሚያፀይፍ ነገር እየሠራ ይጓዛል ብለን እናስብ፤ በእንዲሀ ዓይነት ሁኔታ መንገዳቸውን እየተጓዙ ሳለ የባቡሩ ተቆጣጣሪ እነሱ ወደነበሩበት ፉርጐ ወይም ክፍል በመግባት ትኬታቸውን ጠይቆ ይመለከታል፤ ከትኬታቸውም ሁለቱ ሰዎች ወደሚፈልጉት ስፍራ ሊያደርሳቸው በሚችለው ትክክለኛ ባቡር እንዳልተሳፈሩ ይገነዘባል፡፡ እናም ለሁለቱም ይህንኑ ያሳውቃቸዋል፤ ሁለቱም በተሳሳተ አቅጣጫ እየተጓዙ እንደሆነም ያስረዳቸዋል፡፡ መልካም ነገር ይሠራ የነበረውም ሆነ አፀያፊ ምግባር ይፈጽም የነበረው ሁለቱም መስመራቸውን ስተዋል፤ አዎ ጥሩውም ሰው ሆነ መጥፎው ሰው እየተጓዙ ያሉት በተቃራኒው አቅጣጫ ነበር፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ «ኃጢአት» በሚለው ቃል የሚነግረን እንደዚህ ያለውን መንገድ ነው፡፡ ይህም ለሕይወታችን የማይበጅ ሙሉ በሙሉ ስህተት የሆነና ከእግዚአብሔርም የራቀ ጐዳና ነው፡፡ ሁሉም ሰዎች የተሳፈሩት ይህንኑ ትክክለኛ ያልሆነ ባቡር ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃልም «ሁሉ» የሚለው ይህንኑ ነው፡፡
ኃጢአት ባዕድ ቃል ነውን?
በአመዛኙ ይመስላል፤ በዘመናዊው ሰው አስተሳሰብ «ኃጢአት» እና «ኃጢአተኝነት» ትርጉሙ በእጅጉ ተለውጧል፡፡ እነዚህ ቃላት ዛሬ ዛሬ ለብዙዎች ከእግዚአብሔር ጋር ካላቸው ግንኙነት አንጻር ያላቸው ትርጉም ጥቂት ወይም ምንም ነገር ነው፤ በአንፃሩ ከሆዳቸው ከልባቸው፣ ከሰውነት አቋማቸው ጋር ያያይዙታል፤ እንዲህ ያሉ ሰዎች የሚረዱት «ኃጢአተኝነት» በተወሰነ ሁኔታ አንድ ሰው ከመልካም ሥራ የተለየ ሥራ የሚያደርግበት መንገድ እንደሆነ አድርገው ነው፡፡
ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ኃጢአትን በዚህ መልኩ አይገልጸውም፡፡ ኃጢአት ቀላል ግምት የሚሰጠው ነገር አይደለም፡፡ ኃጢአት ማለት ከእግዚአብሔር የመለየትና በውጤቱም ዘላለማዊ ወደ ሆነ ጥፋት መጓዝ ማለት ነው፡፡ ኃጢአት መድረሱ ሳይታወቅ በድንገት እንደሚያጠፋ ጎርፍ ታላቅ ጥፋት የሚያደርስ ኃይል ነው፡፡
ኃጢአት በሁሉ ስፍራ ይገኛል፡፡ ኃጢአት ያለማቋረጥ እንደሚፈነዳ እሳተ ገሞራ ነው፡፡ በቀላሉ በመናገር ማስወገድ አይቻልም፤ እያንዳንዱ የፈንጂ ጥቃት፣ እያንዳንዱ የጦር መሣርያ፣ እያንዳንዱ ግድያና ወንጀል ኃጢአት ነው፡፡ እንደዚሁም እያንዳንዱ ውሸት፣ አስመሳይነት፣ እያንዳንዱ መጥፎ ምኞትና እያንዳንዱ ግብዝነት የሚንፀባረቅበት ምግባር ሁሉ ኃጢአት ነው፡፡ ወንድሙን በቅናት ተነሳስቶ በገደለው ቃየል ዘንድ የነበረው ኃጢአት ዛሬም በእያንዳንዱ ጦርነት ውስጥ አለ፡፡ ዛሬም በሁሉም የሥራ መስኮች፣ በቤት ውስጥ ተገድቦ ከመኖር ነጻ በወጡበት ስፍራ፣ በእያንዳንዱ ውሸት፣ በእያንዳንዱ ስርቆት፣ በሁሉም ምንዝርና እና ግልሙትና ውስጥ በሐሳብም ይሁን በተግባር ይህ ኃጢአት አለ፤ አንተም በግልህ በሚገባ ተለማምደኸዋል፡፡
ስለዚህ ኃጢአት ለአንተም ባዕድ ቃል አይደለም፤ ነገር ግን የሚያስፈራህ እውነታ ነው፡፡ የምታነባቸው ጋዜጦችም በየዕለቱ ስለ እርሱ ይዘግባሉ፡፡ ስለ አደገኛ ዕፆች ሱሰኝነት፣ ስለ አሰቃቂ ወንጀሎች፣ ስለ ረሀብ፣ ስለ ሞት፣ ስለ አስገድዶ መድፈር ዘወትር ያስነብባሉ፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ኃጢአት ያለው በጋዜጣ ገጾች ላይ ብቻ ነው ማለት አይደለም፤ ነገር ግን ሁሉም ሰው ይህንን አስከፊና መራራ ነገር በየዕለቱ በግል ሕይወቹ ውስጥ የሚያስተናግደው ነው፡፡
በአንድ ወቅት ከነበሩበት ማኅበረሰብ መካከል የሚሻል ሌላ አዲስ ማኅበረሰብ እንፈጥራለን ብለው የተወሰኑ ወጣቶች ከኅብረተሰቡ ተገልለው መኖር ጀመሩ፡፡ ይሁንና ከጥቂት ጊዜ በኋላ ተበታተኑ፤ ለምን ብንል በመካከላቸው ሌብነት የቀድሞ መልኩን ቀይሮ ተከሠተ፤ ጠብና ቁጣም ነገሠ፡፡ አንዱ ሌላውን ለራሱ ጥቅም ሲል ማታለል ጀመረ፡፡ በቀደመው ማኅበረሰብ የነበሩት ኃጢአቶች በሙሉ እዚህም ድንገት ማቆጥቆጥ ጀመሩ፡፡ ከወጣቶቹ መሐል አንዱ ይህንን ተመልክቶ «የአሮጌው ሥርዓተ ማኅበር ነቀርሳማ ዕጢ እዚህ እኛ ጋርም ፈነዳ» አለ፡፡
ቅዱሱ እግዚአብሔር አንድ ጊዜ ለሰው ልጅ ፍጹምና ቅዱስ የሆኑ የሥነ ምግባር ትእዛዛትንና ሕግጋትን ሰጥቷል፡፡ ምናልባት አንተም ልታውቃቸው ትችላለህ፤ ምናልባትም «በፍጹም ሰርቄ አላውቅም፤ በሌላ ሰው ላይም ክፉ ለመሥራት አስቤ አላውቅም» ትል ይሆናል፡፡ ይህ መልካም ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን በከፊል ውሸት የሆነና ሙሉ በሙሉ ውሸት የሆነ ነገርን /ሁለቱም እኩል መጥፎ የሆኑትን/ ተናግረህ አታውቅምን? ወይም «ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህም፣ በፍጹም አሳብህም፣ ውደድ፤ ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህቺ ናት፡፡ ሁለተኛይቱም ይህንን ትመስላለች እርስዋም፡- ባልንጀራህን እንደ ነፍሰህ ውደድ የምትለው ናት» /ማቴ.22፡37-39/ የሚለው ይህ የእግዚአብሔር ቃልስ ከሕይወትህ ጋር እንዴት እየሄደ ነው?
ሰው ሁሉ በመለኮታዊው የእግዚአብሔር ቃል ብርሃን እያንዳንዱን ነገርና የሕይወት ምልልሱን ሊመረምር ይገባል፡፡ አዎ የእግዚአብሔር ቃል ጥልቅ ወደሆኑት ነገሮች እንኳ ዘልቆ ይገባል፤ በያዕቆብ መልእክት ምዕራፍ 2፡10 ላይ እንዲህ የሚል ቃል እናነባለን፡- «ሕግን ሁሉ የሚጠብቅ ነገር ግን በአንድ የሚሰናከል ማንም ቢኖር በሁሉ በደለኛ ይሆናል» ይላል፡፡ ይህ ከባድ ቃል ነው፤ ይህም አሥር አያያዦች እንዳሉት ሰንሰለት ነው፤ ይህ ሰንሰለት ለየብቻው የሚለያየውና ወደታች የሚወድቀው መቼ ነው- ዘለበቶቹ እንዲለያዩስ ሁሉም መላቀቅ አለባቸውን- አይደለም አንዱን ብቻ ማላቀቅ በቂ ነው፡፡
ልብ አድርግ፤ እግዚአብሔር አይዋሸንም፤ አንዳች ለማድረግም እርሱ ምክንያት አያቀርብም፤ ነገር ግን ፍቅሩ ስለ ራሳችንም ሆነ ስለ እርሱ ማወቅ ያለብንን በግልፅ ያስተምረናል፡፡ እርሱ ከሰዎች የሚሻውን ነገር በአንድ መንገድ ብቻ ግልጽ የሚሆንና መረዳት የሚቻል ነው፤ ይህንንም በዚያው በአንዱ መንገድ እንድንረዳው ይፈልጋል፡፡ በመቶ ሜትር የሩጫ ውድድር የሚወዳደር ሯጭ ሊሮጥ የሚገባው ዘጠና ዘጠኙን ብቻ ሳይሆን መቶውንም ሜትሮች ነው፡፡ ይህንን ደንብ ተከትሎ የማይሮጥ ከሆነ ከውድደሩ ውጭ ይደረጋል፡፡ ኃጢአተኛም አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ካላደረገ ይጠፋል፡፡ «ከጌታ ፊት ከኃይሉም ክብር ርቀው በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ» /2ተሰ.1፡10/፤ ይህ የማይሻር እውነት ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን አሁንም እጁን ይዘረጋል፡፡ ለኃጥአንም ይቅርታ ሊያደርግላቸው ይሻል፡፡
መረጃ ቊጥር 2
ወደ ልብህ ተመለስ
በዘመናችን በእርግጥ አደገኛ የሆነ ነገር አለ፤ እርሱም ትልቁ የእግዚአብሔር ተቃዋሚ የሆነው ሰይጣን ሰዎች በልባቸው እንዳያስተውሉና ወደ ትክክለኛው ነጥብ እንዳይደርሱ በተለያዩ አቅጣጫዎች መሰናክሎችን ማኖሩ ነው፡፡ ይህንንም አንተ በሚገባ ታውቃለህ፤ በመሥሪያ ቤትህ፣ በቤተሰብህ፣ በዕረፍት ጊዜህ በሁሉም መስክ ጥድፊያ ወይም ያለመረጋጋት አለ፤ አንተም ይህንን ትመለከታለህ፤ ከዚህ በመነሣት ለራስህ እንኳ ጊዜ አላጣህምን- ሁሌም በጥድፊያ ወይም ያለ ዕረፍት በመዋከብ ላይ ነህ፤ ነጻ ጊዜ የሚባል ነገር በቤትህም ሆነ በሌላ ስፍራ ፈጽሞ የለህም፤ ነገር ግን ምንም ጊዜ ስለሌለህ ነገሮች ያለማቋረጥ ይዞራሉ፤ ይህን በቀላሉ ስለምትረዳው ለአንተ ለመግለጽ ቃላት ማባከን አያስፈልግም፡፡
አንተው ራስህ የሚበጅህን መልካም ነገር አድርግና ይህን ዙርያ ጥምጥም ጉዞህን አቁም፤ ከዚያም ማንም ሊረብሽህ እንዳይችል ለጥቂት ጊዜ ተሰብስበህ ተቀመጥ፤ ከዚያም ያለፈውንና አሁን ያለህበትን የወደፊቱንም ተመልከት፡፡ መንገድህ ወዴት እያቀና ነው? ይህ ጎዳና ወደታች የሚጥል አደገኛ ጎዳና ነው፡፡ መልካም ሰዎችንም የሚማርክ አመቺ የአካሄድ ገጽታ አለው፤ ሆኖም ውጤቱ አስፈሪ ግብ በሆነው የዘላለም ጥፋት ይጠናቀቃል፡፡ አንተም ከምታስበው በላይ ወደዚህ ጥፋት በፍጥነት እየተንደረደርክ ነው፡፡
እባክሀ ይህንን ሁሉ በሚገባ አስብ፤ ራስህን እንጂ እግዚአብሔርን አትውቀስ፤ ለማንኛውም ነገር ሁኔታዎች ወይም ክስተቶች ምክንያት ናቸው አትበል፤ ነገር ግን ምክንያቱ አንተው ራስህ እንደሆንክ እመን፡፡ በራስህ ውስጥ ያለውን እንጂ በሌሎች ያለውን ስህተትም ፈላጊ አትሁን፡፡ ነገር ግን መልካም ከሆነው ቤቱ በገዛ እጁ ኮብልሎ ለክፉ መከራ ስለተዳረገው ወጣት ማለትም ስለጠፋው ልጅ ተማር/ሉቃስ.15/፡፡ እርሱ ከአባቱ ቤት ኰበለለ፤ በእሪያዎች መካከል ሆኖ የሚበሉትን ተመኘ፤ በሉቃ.15፡17 ላይ ስለ እርሱ «..... ወደ ልቡም ተመልሶ እንዲህ አለ እንጀራ የሚተርፋቸው የአባቴ ሞያተኞች ስንት ናቸው- እኔ ግን ከዚህ በራብ እጠፋለሁ፡፡ ተነሥቼም ወደ አባቴ እሄዳለሁና፤ አባቴ ሆይ በሰማይና በፊትህ በደልሁ፤ .... እለዋለሁ» ብሎ የተናገረውን እናነበዋለን፡፡
ይህ ወደ ልብ ለመመለስ፣ ያለፈውን ኑሮ ሙሉ ለሙሉ ለማቆምና ራስን ለማወቅ የሚያስችል እንደ እግዚአብሔር ሐሳብ የሆነ የንስሐ የመጀመሪያው ደረጃ ነው፡፡ «.... ንስሐ ግቡ ተመለሱም» ተብሎ እንደተጻፈ/የሐ.ሥ. 3፡19/፡፡ ይህ ላንተ የሆነ መለኮታዊ ትእዛዝ ነው፤ ይህንን በተሳሳተ መንገድ ልትረዳው አይገባም፡፡ ልብ አድርግ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንስሐ በቅጣት የሚከናወን አይደለም፤ የጠፋ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት የሚያገኝበት መንገድም መልካም ሥራ አይደለም፡፡ እውነተኛ ንስሐ ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው፡፡ እውነተኛ ንስሐ ሙሉ በሙሉ ጥፋተኛ መሆናችንን ማመን ነው፡፡ «.... ራስ ሁሉ ለህመም ልብም ሁሉ ለድካም ሆኖአል፡፡ ከእግር ጫማ አንስቶ እስከ ራስ ድረስ ጤና የለውም፡፡ ቁስልና እበጥ የሚመግልም ነው አልፈረጠም፤ አልተጠገነም፤ በዘይትም አልለዘበም» /ኢሳ.1፡5-6/፤ ይህ ቃል ሊጠፋ በማይችል በመጽሐፍ ቅዱስ ብርሃን ውስጥ የሚገኝ የውስጥ ደዌን ገልጦ እንደሚያሳይ መሣሪያ/X-Ray/ ነው፡፡
እውነተኛ ንስሐ መላ ሕይወቴ ውሸት እንደነበረና፣ እኔም ራሴ ውሸተኛ እንደነበርኩ ማወቅ ነው፡፡ ይህ የሕይወት በጣም ታላቅ ርእሰ ጉዳይ ነው፤ በእውነተኛ ንስሐ ውስጥ ቸልተኝነትና ዋዘኝነት ፈጽሞ ሊኖር አይችልም፡፡ ማንኛውም ሰው ሕይወቱን በእግዚአብሔር ብርሃን ባየ ጊዜ በውስጡ ቅዱስ የጥሪ ደወል ይሰማዋል፡፡ አንድ ሰው ይህን ሲሰማ በጥልቅ ኀዘን ያልፋል፤ ኀዘኑ ከልብ ከሆነ ግን የእግዚአብሔርም ቃል ኪዳን አለው፤ ይህም «እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን ጸጸት የሌለበትን ወደ መዳንም የሚያደርሰውን ንስሐ ያደርጋልና» ተብሎ የተጻፈው ነው/2ቆሮ.7፡10/፡፡
በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 15 ከቊጥር 11 ጀምሮ በተመዘገበው የጠፋው ልጅ ታሪክ የምናየውም ይህንኑ ነው፤ እርሱ ወደ ወደልቡ ሲመለስ ትልቁን ስህተቱን ተገነዘበ፡፡ ቀጥሎም «አባቴ ሆይ በሰማይና በፊትህ በደልሁ .... በማለት በደሉን ሲናዘዝ ከቃሉ እንሰማለን፡፡ በመጀመሪያ ወደልቡ ተመለሰ፤ ከዚያም ኃጢአቱን ተናዘዘ፤ ሁለቱም ቀላል ጉዳዮች አልነበሩም፤ በኋላ በተግባር እንዲፈጸሙ የተጠበቁና በቀላሉ ዕቅድ ሆነው የቀሩ አልነበሩም፤ «... ተነሥቼ ወደ አባቴ እሄዳለሁ ...» አለ፤ ከዚህም ንግግር በኋላ ወዲያው ተግባር ይከተላል፡፡ ተነሥቶም ወደ አባቱ መጣ፡፡
ለጉዞ ተነሥተው የነበሩ ብዙ ሰዎች በጅማሬያቸው ላይ ሲቆዩ ይታያል፡፡ በእርግጥ ተነሣሥተው ነበር፤ የእግዚአብሔር ቃል በእነርሱ ላይ ተጽዕኖ አድርጓል፤ ስለጠፉበት ሁኔታም በተወሰነ ደረጃ እውቅና መስጠት ነበረ፤ ይሁንና ነገሮች ወደፊት አልተጓዙም፡፡ ውጫዊ ሥራ ብቻ ነበር፤ የዚህ ዓለም ክፉ ሐሳቦች በሰፊው የጥፋት ጐዳና ላይ ጥለዋቸዋል፡፡
ምናልባት አንተም «ንስሐ ገብቼ ከኃጢአቴ መንጻት እፈልጋለሁ፡፡ ነገር ግን ሌሎች ሰዎች ስለዚህ ምን ይላሉ? ምናልባትስ ወደፊት እነርሱ የሚያደርጉትን አብሬ ባላደርግ ይስቁብኝ /ያፌዙብኝ/ ይሆን-» ብለህ ታስብ ይሆናል፡፡ አንድ ነገር ታውቃለህ- ጲላጦስ እንኳ ኢየሱስ ኃጢአት የሌለበት ንጹህ ሰው እንደነበረ ያውቅ ነበር፡፡ ሚስቱ «.....በዚያ ጻድቅ ሰው ምንም አታድርግ» የሚል ቃል ልካበት ነበር/ማቴ.27፡19/፤ እርሱም ኢየሱስን ነጻ መልቀቅ ፈልጎ ነበር፤ ይሁን እንጂ ከፍላጎት አልፎ ሊሄድ አልቻለም፡፡ ምክንያቱም ሕዝቡ «ይህንስ ብትፈታው የቄሣር ወዳጅ አይደለህም፤ ...» እያሉ ይጮኹ ነበር፤/ዮሐ.19፡12/ እናም ጲላጦስ በርባን የተሰኘውን አደገኛ ወንጀለኛና ወንበዴ ፈትቶ ኢየሱስን ግን እንዲሰቅሉት አሳልፎ ሰጣቸው፡፡
ተመልከት፤ ይህ እስከ ዛሬ ድረስ አልተለወጠም፤ «ምን ይሉናል» እያሉ ስለሌሎች ሰዎች፣ ስለ ጓደኞቻቸው፣ ስለ ወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ በመጠየቅ ለእውነት የማይታዘዙት ለዘላለም ይጠፋሉ፡፡ በዮሐንስ ራእይ ምዕራፍ 21 ቊጥር 8 ዕድላቸው የዘላለም ፍርድ የሆኑት ተገልጠዋል፤ ይህን ክፍል በሚገባ አስተውል፤ በዚህ ክፍል በመጀመሪያ የተገለጹት «የሚፈሩ» ናቸው፤ ስለዚህ ፈሪ አትሁን፡፡ በቅዱስ እግዚአብሔር ፊት ለፍርድ በምትቀርብ ጊዜ ጓደኞችህ፣ የምታውቃቸው ሰዎች እና ዘመዶችህ ሁሉ ከቶ ሊረዱህ አይችሉም፡፡ እነሱም ንስሐ ካልገቡና ካልተለወጡ ያንኑ ፍርድ የሚቀበሉ ናቸው፡፡
ከእነዚህ ሁሉ ትምህርት ውሰድና መለኮታዊውን ትእዛዝ ተቀብለህ አሁን ከልብህ በእውነት ንስሐ ግባ፡፡ የጠፋው ልጅ በራሱ መንገድ ተጓዘ፤ ሆኖም «ምናልባት ከሆነ» ወይም «ነገር ግን» ሳይል በአንድ ጊዜ ወሰነ፡፡ ምን ያህል ሰዎች- በራሳቸው ሲጠፉና በድንገትም ወደ ኋላ ሲቀሩና ሲዘገዩ እያስተዋልን ነው- የእግዚአብሔር ቃል ግን «ዛሬ ድምፁን ብትሰሙ ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ»/ዕብ.4፡7/ ይላል፤ ዛሬ- ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥሪ ነው፡፡ በራስህ መንገድ እንድትሄድበት የተተወ የነገ ጊዜ የለም፤ ሕይወታችን በእኛ በራሳችን እጅ ያለ አይደለም፡፡ በየዕለቱ በጎዳናዎቻችን ላይ ብቻ ገና ከፊታቸው በርካታ ዓመታት ያሉ የሚመስላቸው ብዙዎች በድንገት ሲቀጩ ይታያል፤ ስለዚህ አንተ ውሳኔህን ለሌላ ጊዜ ልታስተላልፈው አይገባም፤ ውሳኔን ማዘግየት ወይም ለሌላ ጊዜ ማስተላለፍ የሰይጣን ሁነኛ ማጥመጃ ነውና፡፡
አሁን እግዚአብሔር ሊገናኝህ ወደ አንተ ይመጣል
የልብህን ምሥጢራዊ ሐሳቦች የሚታዩት ልዑል እግዚአብሔር በታመነ ሁኔታ ውስጥ እንዳለህ ባየ ጊዜ ልክ እንደጠፋው ልጅ አባት ሊገናኝህ ወደ አንተ ይመጣል፡፡ እርሱ ላንተ መልካም ነው «እኔ ሕያው ነኝና ኃጢአተኛው ከመንገድ ተመልሶ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንጂ ኃጢአተኛው ይሞት ዘንድ አልፈቅድም ይላል ጌታ እግዚአብሔር፡፡ የእስራኤል ቤት ሆይ ተመለሱ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ ስለ ምንስ ትሞታላችሁ- ......»/ሕዝ.33፡11/፡፡
እግዚአብሔር ሊገናኝህ ወደ አንተ የሚመጣው እንዴት ነው? እርሱ ወደ አንተ የሚመጣው በታላቅ ፍቅርና መልካምነት ነው፤ ላንተ ያዘጋጀውን ምትክ ማለትም ለአንተም ኃጢአት በቀራንዮ መስቀል ላይ የሞተው ውድ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን በማሳየት ወደ አንተ ይመጣል፡፡ እዚያ መስቀል ላይ የእርሱ ውድ ደም ስለ አንተ ፈስሷል፡፡ እግዚአብሔር ቅዱስ ስለሆነ ኃጢአትን ሳይቀጣ አያልፍም፡፡ ስለዚህም መፍትሔ አገኘ፤ ይህ ጥልቅ የሆነ ፍቅርና የእግዚአብሔር ጸጋ ነው፡፡ «በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና፡፡» /ዮሐ. 3፡16/
እርሱ ለእኔና ለአንተ ኃጢአት የገዛ ልጁን አሳልፎ ሰጠ፤ የታመነ አዳኝ የሆነው እርሱ ቅዱስና ታዛዥ የሆነ እውነተኛ የእግዚአብሔር በግ ሆነ፡፡ እርሱ ከፍርድና ከሞት ወደኋላ አላፈገፈገም፡፡ «በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፡፡ ህመማችንንም ተሸክሟል፤ እኛ ግን እንደተመታ በእግዚአብሔርም እንደተቀሠፈ እንደተቸገረም ቈጠርነው፤ እርሱ ግን ሰለመተላለፋችን ቆሰለ፤ ስለበደላችንም ደቀቀ፡፡ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፡፡ በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን፡፡ እኛ ሁላችን እንደበጐች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ፤ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ»/ኢሳ.53፡4-6/፡፡
ነገር ሁሉ ለእርሱና በእርሱ የሆነው ጌታ ኢየሱስ የሾህ አክሊልን በራሱ ላይ እንዲደፉና በእጆቹና በእግሮቹ ላይ ችንካርን እንዲያደርጉ ኃጢአተኛ ለሆኑ ሰዎች ፈቀደላቸው፤ የሰዎች ንዴት፣ ዘግናኝ የሆነው ዘበታቸውና ፌዛቸው በላዩ ላይ ወደቀበት፤ ከዚያም ቅዱሱ እግዚአብሔር በእነዚያ ሶስት የጨለማ ሰዓታትም ከእርሱ ፊቱን ማዞር ነበረት፤ አዎ እርሱን መተው ነበረበት፤ ለምን- ምክንያቱም እኔና አንተ ልንቀበለው የሚገባንን ቅጣት እርሱ እየተቀበለ ነበርና፡፡ በመደነቅም እንደሚንበለበል ነበልባል ባለ ሥዕል በነፍስህ ፊት የሚታይህ በዚያ በቀራንዮ መስቀል ላይ የተከናወነው ሥራ ምንድነው- ትል ይሆናል፤ የማቴዎስ ወንጌል ሃያ ሰባተኛ ምዕራፍንና የመዝሙረ ዳዊትን ሃያ ሁለተኛ መዝሙር በታላቅ አክብሮት አንብብ፡፡ ኦ- በዚያ በቀራንዮ መስቀል ላይ የፈጸመው ወደ አንተ ያለው የእግዚአብሔር የማዳን ሐሳብ እንደምን ያለ ነው- «እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልእክተኞች ነን፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን፡፡ እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው» /2ቆሮ.5፡20-21/፡፡
በከፍተኛው ፍርድ ቤት በነጻ መለቀቅ
መዳን የሚቻል ነውን? አዎ- - ከፍርድ ነጻ መሆን? አዎ- እግዚአብሔር በታላቅ ቅዱስነቱና እውነቱ ኃጢአተኝነትህንና በዚህም ኃጢአተኝነትህ መጥፋት የሚገባህ ለምን እንደሆነ ያሳይሃል፤ ነገር ግን እርሱ የፍቅር አምላክም ስለሆነ አዳኙን ያሳይሃል፤ ኢየሱስን፡፡ ከዚህ ውጭ ደኅንነት ሊገኝ ፈጽሞ አይችልም፡፡
«መዳንም በሌላ በማንም የለም፡፡ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለስዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና»/ሐዋ.4፡12/፤ ጌታ ኢየሱስም ራሱ ስለራሱ ሲናገር «እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ማንም ወደ አብ ሊመጣ አይችልም» /ዮሐ.14፡6/ በማለት ተናግሯል፡፡ ሰላም፣ ደስታ፣ እና እርካታ ለጊዜውም ሆነ ለዘላለሙ በእርሱ ብቻ ይገኛሉ፤ የዘላለም ሕይወት፣ የሚገኘው በእርሱ ብቻ ነው፤ የበዛ ሕይወት በእርሱ ይገኛል፤ «እኔ ግን ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ» እንዳለ /ዮሐ.10፡10/፡፡
በኃጢአትህ እውነተኛ ንስሐ በመግባት በእርሱ የማስታረቅ ሥራ እንደ ሕፃን ልጅ እምነት ባለ እምነት አምነህ ወደ ጌታ ኢየሱስ ትመጣለህን- ከዚያስ ምን ይሆናል- እርሱ አንተን ይቀበልሃል- አዎን ይቀበልሃል፡፡ «አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፡፡ ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም» እንዳለ /ዮሐ.6፡37/፡፡ በዚህ እምነት ትጸድቃለህ፤ የእግዚአብሔር ልጅም ትሆናለህ፡፡
እምነት ምንድነው? እምነት ማለት እግዚአብሔርን በቃሉ እንደተገለጠው መቀበል ማለት ነው፤ እንዲሁም እምነት ማለት መታዘዝ ማለት ነው፡፡ ናፖሊዮን ተብሎ ይታወቅ የነበረው የፈረንሳይ ንጉሥ በአንድ ወቅት ፈረሱን ግልቢያ ለመሞከር ይቀመጥበታል፤ ፈረሱም በድንገት ደንብሮ ንጉሡን ይዞ ሽምጥ መጋለብ ይጀምራል፡፡ ይህንም ድርጊት አንድ ተራ ወታደር ይመለከት ኖሮ የንጉሡን ሕይወት ለመታደግ በድፍረትና በቆራጥነት ብርቱ ትግል አድርጐ የፈረሱን ግልቢያ መግታት ቻለ፡፡ በዚህ ጊዜ ናፖሊዮን ይህን ሰው እንደዚያው ተራ ወታደር እያለ «አመሰግናለሁ ሻምበል» ይለዋል፡፡ ያም ወታደር የንጉሡን ቃል እንዳለ ተቀብሎ ሄደ፡፡ ንጉሡን አመነው፤ ታዘዘው፤ እናም ያለምንም መዘግየት የወታደራዊ መኮንኖችን ስም ዝርዝር በያዘው መዝገብ ውስጥ ሰፈረ፤ ይህንን ማንም ሊቃወም አልቻለም፤ ንጉሡ ራሱ ከተራ ወታደርነት ወደ ሻምበልነት አሳድጎታልና፡፡ ተመልከት፤ እምነት ማለት እግዚአብሔርንም በቃሉ መቀበል ማለት ነው፡፡
ገና እጅግ በጣም አስፈላጊው የሆነ ሌላ ነገር አለ፤ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ የሞተ ብቻ አይደለም፡፡ ሞትን ድል አድርጐ እንደገና ተነሥቷል፤ በአካል ተነሥቷል፡፡ በዚህም የኢየሱስ ትንሣኤ ለእርሱ የማስታረቅ ሥራ ማረጋገጫ የሚሆን ጉልህ ማኅተም ነው፡፡ እግዚአብሔር የእርሱን መሥዋዕት ተቀብሏል፤ ሊነገር በማይችል ትህትና ራሱን ዝቅ አድርጐ እስከ መስቀል ሞት ድረስ የተጓዘውን እርሱን አሁን ያለ ልክ አክብሮታል፤ ከስም ሁሉ በላይ የሆነ ስምንም ሰጥቶታል፡፡ በእርሱ የሚያምኑ ሁሉ ሙሉ በሙሉ ጸድቀዋል፡፡ «ስለ በደላችን አልፎ የተሰጠውን እኛን ስለማጽደቅም የተነሣውን ጌታችንን ኢየሱስን ከሙታን ባስነሣው ለምናምን ለእኛ ይቈጠርልን ዘንድ አለው» ተብሎ ተጽፏልና/ሮሜ.4፡25/፡፡ ይህም የምስጋና፣ የአምልኮና የደስታ ምክንያት ነው፡፡ በሰማይም እንኳ ንስሐ ገብቶ ወደ ኢየሱስ በሚመጣው በእያንዳንዱ ሰው ነፍስ ምክንያት ከፍተኛ ደስታ አለ፡፡ በሉቃስ.15፡10 ላይ «እንዲሁ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል» የሚል እናነባለን፡፡
አሁን ባለንበት ዘመን በርካታ ድፍረት የበዛባቸው አደገኛ ክንውኖች፣ ስሜትን የሚወስዱ የበረራ ትዕይንቶችና ታላላቅ የስፖርት ውድድሮች አሉ፡፡ ሚሊዮኖችም በእነዚህ ነገሮች የተተበተቡ ናቸው፤ ውይይቶችም ሁሉ በእነዚህ ዙሪያ ሆነዋል፤ እነዚህ ፕሮግራሞች በሚከፈቱ ጊዜ በግርግርና በሁከት ይታመሱ የነበሩት የከተሞቻችን አውራ ጐዳናዎች ንጹሕ ይሆናሉ፡፡ ነገር ግን ሰማያት በደስታ የሚንቀሳቀሱት መቼ ነው? ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር ቃል ብርሃን ተመርቶ ወደ ልቡ ሲመለስና ወደ ጌታ ሲመጣ ነው፤ ኃጢአተኛ ወደልቡ ሲመለስ የንስሐ እንባ ዘለላዎች በኃጢአተኛው ሰው ፊት ላይ ቁልቁል ይወርዳሉ፡፡ ኃጢአተኛ ከአዳኙ ዘንድ መሸሸጊያ ይሻል፤ ከዚያም በሰማይ ውስጥ ሐሴት ይሞላል፡፡ የጠፋ መሆኑን ካወቀ፣ ይቅርታንና ሰላምን ከሚጠይቅ ልብ እና እነዚህን ሁለቱንም ሊሰጥ ከሚፈልገው ከአዳኙ በተሻለ የሚፈላለግና በተገናኘ ጊዜ ደግሞ በትክክል ሊጋጠም የሚችል ሌላ ምን ነገር አለ?
ስለዚህ ይህንን በጣም ልታስብበት ይገባል፤ ነገ ዛሬ ሳትል አሁኑኑ ወደ ጌታ ና፡፡ «የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ሳታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን?»/ሮሜ.2፡4/
እባክህ ላንተ ያቀረበውን ስጦታውን አታቃልል፤ ወደ ኢየሱስ አሁኑኑ ና- መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡-
«በፊታችሁ ሕይወትንና ሞትን፤ በረከትንና መርገምን እንዳስቀመጥሁ እኔ ዛሬ ሰማይንና ምድርን በአንተ ላይ አስመሰክራለሁ፤ እንግዲህ አንተና ዘርህ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ሕይወትን ምረጥ» /ዘዳ.30፡19/፡፡
«አላውቅም» ማንም አይልም
ፍርድስ ለምን- ብሎ አይልም
ስለዚህ ቶሎ ይወስን
እያንዳንዱ ይምረጥ አንዱን
ኢየሱስን ወይ ዓለምን፡፡
መረጃ ቊጥር 3
ከዚያ ብኋላስ
ከዚህ በኋላ ሙሉ በሙሉ አዲስ የሆነ ክፍል ይጀምራል፤ ልክ ይህ ገጽ አዲስ ሆኖ እንደጀመረ እግዚአብሔርም በአንተ ውስጥ አዲስ ሕይወት መጀመር ይፈልጋል፤ አንተ ለእግዚአብሔር ትእዛዝ ታዛዥ ስትሆን፣ ንስሐ ስትገባና ኃጢአትህን ስትናዘዝ በቀራንዮ መስቀል ላይ ለአንተ የፈጸመውን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥራ አንተ በግልህ በእምነት ትቀበላለህ፡፡ አዎ ይህን አድርግና ሙሉ የሆነ የመዳን እርግጠኝነት ይኑርህ፡፡ ከዚያም «አዳኜ ለእኔ ስለሞተ የዕዳዬ ጽሕፈት እንደተቀደደልኝ ማወቅና እርግጠኛ መሆን እችላለሁ» ብለህ መመስከር ትችላለህ፡፡
አሮጌ ነገሮች¬ በሙሉ አልፈዋል፡፡ ሙሉ ለሙሉ አዲስ የሆነ ነገር ተጀምሯል፤ በጌታ ኢየሱስ በኩል፣ ከጌታ ኢየሱስ ጋር እና ለጌታ ኢየሱስ የሆነ አዲስ ሕይወት ተጀምሯል፡፡ ይህም ሕይወት ጥቂት ወይም ብዙ የሚባል ሕይወት አይደለም፤ ነገር ግን ወሰን የሌለው የብዙ ብዙ ሕይወት- የዘላለም ሕይወት- ነው፤ ስለሆነም ከዚህ በኋላ ያሉ ቀጣይ ገጾች ከጌታህና ከአዳኝህ ከኢየሱስ ኋላ በግልጽ ለመከተል የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን የሚያሳዩ ናቸው፡፡
የየትኛውም ፍጥረታዊ ሕይወት ወይም ህልውና የሚጀምረው ከልደት ነው፡፡ አንተ ተወልደህ ስለነበር አንተና የተወለድክበት ቀን በሚመለከተው የምዝገባ ቢሮ ይመዘገባል፤ በመንፈሳዊ ሕይወት ጅማሬ ላይም ልደት አለ፤ ይኸውም አዲስ ልደት ነው፡፡ የዘላለምን ሕይወት የተቀበለ ማንኛውም ሰው ዳግመኛ ተወልዷል፤ በሕይወት መጽሐፍም ላይ ተመዝግቧል፡፡ ልክ አንድ ሰው በሥጋ የሚወለደው አንዴ ብቻ እንደሆነው ሁሉ አዲስ ልደትም አንድ ብቻ ነው፤ ሌላ ምንም የለም፡፡ ሰው በየዕለቱ ዳግም መወለድ አለበት ማለት ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ነው፡፡ «የዘላለምን ሕይወት የምቀበለው ወደፊት በእግዚአብሔር ፊት ስታይ ብቻ ነው» ብሎ መከራከርም እንደ እግዚአብሔር ቃል አይደለም፡፡ ይህ የከፋ እልከኝነት ነው፡፡ የዘላለምን ሕይወት እዚህ ምድር ላይ ማግኘት ያልቻለ ሰው እዚያ በሰማይም በፍጹም ሊያገኘው አይችልም፡፡ በዚህም ምክንያት የእግዚአብሔር ቃል በኢየሱስ የሚያምን ማንኛውም ሰው አሁን በምድር ላይ እያለ የዘላለምን ሕይወት እንዳገኘ አጉልቶና አስረግጦ ይናገራል/ዮሐ3፡16/፤ የዘላለምን ሕይወት በዕድልና በአጋጣሚ የሚቀበል አይደለም፤ እባክህ ዮሐ3፡16ን በድጋሚ ካነበብህ በኋላ የሚከተሉትን ንባቦች በሚገባ ተመልከት፤ «እውነት እውነት እላችኋለሁ ቃሌንም የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም»/ዮሐ.5፡24/፣ «በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው...»/ዮሐ.3፡36/፤ «የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ሰለምታምኑ ይህን ጽፌላችኋለሁ»/1ዮሐ.5፡13/፤ ስለዚህ በኢየሱስ ያመንን የዘላለም ሕይወት እንዳለን ልናውቅ እንችላለን፤ ይገባናልም፡፡
የሕይወት ምልክቶች
አንድ ህፃን ገና ከእናቱ ማህፀን ሲወጣ ወይም ሲወለድ ምን ያደርጋል? ብለን ብንጠይቅ መልሱ «ያለቅሳል» የሚል ነው፡፡ ለወላጆቹም የአዲሱን ልጃቸውን ልቅሶ የመሰማትን ያህል የሚያስደስታቸው ሌላ ነገር የለም፡፡ በዚህም ሁሉም ሰው ሕፃን መወለዱን ያውቃል፡፡ ልቅሶው አዲስ ሕይወት የመጀመሩ ማስረጃ ነውና፡፡ በተለወጠና ከእግዚአብሔር በተወለደ በማንኛውም ሰው የሚሆነውም እንዲሁ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ «ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና፡፡» ይላል/ሮሜ.10፡10/፡፡ ከእግዚአብሔር የሆነ አዲስ ሕይወት በዚያ መኖሩን በዙሪያህ ያሉ ሁሉ ሊያውቁ ይገባል፡፡ ያለፈው ነገርህ በመለኮታዊ መንገድ የተስተካከለልህ በመሆኑ ኃጢአትህ ተሰርዮልሃል፤ በቀራንዮ መስቀል በተገኘው ድልም ምክንያት የተባረከ ስጦታ ተሰጥቶሃል፤ የከበረ የወደፊትም ጊዜም በፊትህ አለ፡፡ ይህ ለታላቅ ደስታ ምክንያት ነው፡፡ ለወዳጅ ዘመዶችህ ይህን የምስራች አብስር፤ በቅድሚያም ዕዳ ላለብህና ከዚህ በፊት ላምታታሃቸው ሰዎች ተናገር፡፡ በደስታ ለሚመሰክር ሰው ከዓለም ጋር ያለውን የቆየ ግንኙነት ለማቋረጥ በጣም ቀላል ነው፤ ብርሃንንና ጨለማ ምንም ኅብረት የላቸውምና፡፡ «ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፡፡ አሮጌው ነገር አልፎአል፡፡ እነሆ ሁሉም አዲስ ሆኖአል» ተብሎ ተጽፏል/2ቆሮ.5፡17/፡፡ ምናልባት ይህ ሰዎችን ላያስገርማቸው ይችላል፤ ምናልባትም አንዳንዱ ሊያሾፍብህ ወይም ሊቀልድብህ ይችላል፡፡ ቢሆንም «ስለ ክርስቶስ ስም ብትነቀፉ የክብር መንፈስ የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ላይ ያርፋልና ብፁዓን ናችሁ»/1ጴጥ.4፡14/ ተብሎ የተጻፈውን በማስተዋል ልትጽናና ይገባል፡፡
በንጹሕ አየር ውስጥ መተንፈስ
ለሰው ልጅ ከሚያስፈልጉት ነገሮች ሁሉ በጣም አስፈላጊው ነገር አየር ነው፡፡ በጣም አጭር ለሆነ ጊዜ አየር ብናጣ እንታፈናለን፡፡ ጸሎት ብዙ ጊዜ ከመተንፈስ ጋር ተነጻጽሯል፤ ይህም ትክክል ነው፡፡ አየር ለሳምባችን የሚያስፈልገንን ያህል ጸሎትም ደግሞ ለነፍሳችን በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ብዙዎች ጸሎት በቃል ተሸምድዶ የሚባል ይመስላቸዋል፤ ነገር ግን ጸሎት ያ አይደለም፡፡ ጸሎት ወደ እግዚአብሔር መናገር ነው፤ ይህንንም በቤትህ ተንበርክከህ አሊያም በሥራ ስፍራህ ቆመህ በማንኛውም ጊዜና በየትኛውም ቦታ ልታደርገው ትችላለህ፡፡ እግዚአብሔር አባትህ እስከ ሆነ ድረስ የሚያውኩህን ነገሮች በሙሉ ለምን ለእርሱ አትነግረውም- ሐሳብህን፣ የሚያስጨንቅህን፣ ላንተ ሊደረግልህ የምትፈልገውን ሁሉ ልትነግረው ትችላለህ፤ በእርግጥም እነዚህን ነገሮች በጸሎት ወደ ጌታ ልታቀርባቸው ይገባል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ «እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት» /1ጴጥ.5፡7/፣ «ሁል ጊዜ ደስ ይበላችሁ ሳታቋርጡ ጸልዩ በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና»/1ተሰ.5፡17/ በማለት ይህን እንድናደርግ ይመክረናል፡፡ ጌታ ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱ ሳይታክቱ ዘወትር ሊጸልዩ እንደሚገባቸው በምሳሌ ነገሯቸዋል/ሉቃስ.18፡1/፡፡ በሌላ አጋጣሚ ደግሞ «ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ፡፡» በማለት አጥብቆ አሳስቧቸዋል /ማቴ.26፡41/፡፡ ይህ ሁሉ መልእክት እንደ ዛሬ ላለው ፈተና ለበዛበት ጊዜ በተለይ አስፈላጊ ነው፡፡ ስለዚህ ልጅ በአባቱ ላይ ባለው መተማመን ዓይነት ተማምነህ ያለማቋረጥ ጸልይ፤ ለጸሎት ጊዜ ስጥ፤ የእግዚአብሔርም ኃይል በሕይወትህ ይሠራል፡፡ ያዕቆብ በመልእክቱ «አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም» ብሎ የተናገረው በእኛ ላይ ሊፈጸም አይገባም/4፡6/፡፡
ምግብ
በየቀኑ የተወሰነ ምግብ ትመገባለህ፤ ሰአቱን ጠብቀህ በሚገባ ካልበላህ ትራባለህ፡፡ አንድ ቀን ቁርስህን ሳትበላ ወደ ሥራ ብትሄድ፣ ምሳህንም ሳትመገብ ብትውል በእራት ሰአት በምን ያህል መጣደፍ እንደምትበላ ማወቅ ይቻላል፡፡ ነገር ግን እራትህንም መብላት ባትችል በጣም በጣም አስፈሪ ነው፡፡ ነገሮች በዚህ ሁኔታ የሚቀጥሉ ቢሆን ረሃብ ይጐዳሃል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ አዲሱ ሰውም መንፈሳዊ ምግብን ካላገኘ መንፈሳዊ ረሃብ ያገኘዋል፤ ዳግም ቢወለዱም እንኳ በብዙ ሰዎች ላይ አዲስ ሕይወትን በጥቂቱም ማየት የማይቻለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡
ለአዲሱ ሰው የሚሆን ምግብ የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ መዝሙሮችና ሙሉውን እውነት የያዘ ሥነ-ጽሑፍ ለእርሱ መልካም ናቸው፡፡ ስለሆነም አንድ ሰው ለራሱ በተከታታይ የእግዚአብሔርን ቃል ማንበብ አስፈላጊው የሆነውም ለዚህ ነው፡፡ ለመሆኑ አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ የሚችለው እንዴት ነው? በቅድሚያ እጆችህን አጥፈህ ቃሉን መረዳት እንዲያስችልህ ጌታን ጠይቅ፤ ከዚያም ይህ ምንባብ ለእኔ ምን መልእክት ያስተላልፋል- በማለት ራስህን እየጠየቅህ አንብብ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ከመጀመሪያው ቊጥር እስከፍጻሜው ቊጥር ድረስ በእግዚአብሔር መንፈስ የተጻፈ የእግዚአብሔር ቃል ስለሆነ ማንም ሰው ራሱን ከመጽሐፍ ቅዱስ በላይ ሊያስቀምጥ አይችልምና፡፡ መለኪያ የሌላቸውና ባለጠግነታቸው የበዛ እውነቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍረው በአንተ ሊነበቡ አንተን በግል ይጠብቁሃል፡፡
ለእግዚአብሔር ልጆች ተብሎ በየዕለቱም ሆነ በተለያየ ጊዜ በተከታታይ የሚታተሙ የተለያዩ መንፈሳዊ ጽሑፎችም ለመንፈሳዊ ዕድገትህ የሚረዱ ናቸው፡፡ እድገትም በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ሕፃናት ልጆች ደስታን ይሰጡናል፤ ሆኖም እድሜያቸው በጨመረ ቊጥር የማያድጉ ከሆነ ምናልባት በእጅጉ ታመው ሊሆን ስለሚችል ያሳስበናል፤ በዚህም ምክንያት ዳግም የተወለደ ሰውም በመንፈሳዊ ሕይወቱ ጠንክሮ ማደግና የእግዚአብሔር ቃልን በማንበብ የበለጠ ደስታ ሊኖረው ይገባል፡፡ እንዲህም ከሆነ ከመዝሙረኛው ጋር «ብዙ ምርኮ እንዳገኘ በቃልህ ደስ አለኝ»/መዝ.118-119-፡162/፣ «ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴም ብርሃን ነው» ማለት ይችላል/መዝ.118-119-፡105/፡፡ ጌታም «.....የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል» ብሎ ተናግሯል /በዮሐ.14፡23/፡፡ ነገር ግን የማናነብ ከሆነ ቃሉን እንዴት ልናውቅ እንችላለን- ስለዚህ የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ፤» ተብለናልና ልናነብ ይገባናል/ቈላ3.16/ ፡፡
በመጨረሻም በአሮጌው ሰው ውስጥ የሞላውን የተበከለ ምግብ ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህም ዓለማዊ መጽሔቶችና ሌሎች ዓለማዊ ሥነጽሑፎች፣ ፊልሞችና ጨዋታዎች ... ናቸው፤ እነዚህ ደግሞ አዲሱን ሰው በጣም የሚጐዱ ሲሆኑ ክርስቶስን በመከተል ውስጥ ምንም ቦታ የላቸውም፡፡ «እኔ እችል ይሆን ወይስ አልችል ይሆን-» የሚል ጥያቄ የሚያስከትሉና በተወሰነ ደረጃ አለማዊነት ያለባቸው ብዙ ነገሮች ለእምነት ሕይወት እንቅፋት ብቻ ናቸው፡፡
የሥራ እንቅስቃሴ (አገልግሎት)
አንድ ልጅ በግሩም ሁኔታ እና ቀስ በቀስ እያለ ጤናማና ጠንካራ ሰው ለመሆን ያድጋል፤ እንዲህ ያለው ሰው ሙሉ ለሙሉ ራሱን ከሥራ ለይቶ በአልጋ ላይ ተኝቶ የሚያሳልፍ ከሆነ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ጡንቻዎቹና የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቹ የማይሠሩ እየሆኑ ይሄዳሉ፡፡ ሁኔታዎቹ በዚሁ ከቀጠሉ አካለ ስንኩል ሊሆንም ይችላል፤ እንቅስቃሴ የሕይወት አንድ ክፍል ነውና፡፡ ውሱን የሆነ እንቅስቃሴ ባለበት በእኛ ዘመን ትኩረታችን ሁሉ ጤናማ ያልሆነው የኑሮ መንገድ በሚመጣው አደጋ ላይ ይሆናል፤ «በስፖርቶች በኩል የስውነትህን ቅርጽ አስተካክል» የሚለው አባባል የዘመኑ የይለፍ ቃል ሆኗል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ ለተፈጥሮአዊ ሰውነት አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉ ከጌታ ጋር ለጀመርነው አዲሱ ሕይወታችንም መንፈሳዊ የሆነ እንቅስቃሴ ማለትም ጌታን ማገልገል በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ እርሱ የሚፈልገው አንተ ለራስህ እንድትኖር ሳይሆን ለእርሱ እንድትኖር ነው፤ ስለሆነም እርሱ ላንተ ሥራዎችን እንዲሰጥህ እና ለእርሱ በሚገባ የምትሠራ መሆን እንድትችል ጸልይ፡፡ የአንተን ጉብኝት የሚጠባበቁ ምን ያህል በሽተኞች በዙሪያህ አሉ? እርዳታንና ርኅራኄን የሚሹ ብቸኞች ምን ያህል ናቸው? በሰፊው ጐዳና ላይ ወዳለ ጥፋት እየተጓዙ ያሉት ስንቶች ናቸው? እነዚህ ሁሉ ያንተን እርዳታና ኢየሱስ አዳኝና ረዳት መሆኑን የሚገልጽ ምስክርነት ይፈልጋሉ፡፡
ሁሉም ሰው የግድ በብዙ ሕዝብ ፊት መልካሙን የምስራች የሚያውጅ ወንጌላዊ መሆን አይችልም፤ ነገር ግን አንተ ወደ አንድ ግለሰብ ሄደህ ልትጸልይለትና ከእርሱ ጋር ስለጌታ ልትነጋገር ትችላለህ፤ በእርግጥም ይህንን ማድረግ አለብህ፡፡ በብዙ አጋጣሚዎች ልታሰራጫቸው የምትችላቸው መልካም የሆኑ የወንጌል ትራክቶችም አሉ፤ የእነዚህ ትራክቶች ወይም በራሪ ጽሑፎች ጥቅምም ከሰዎች ጋር ሁልጊዜ ስለ ጌታ ለመነጋገር የሚያስችል ግንኙነት እንዲኖርህ ማድረግ ነው፡፡ እግዚአብሔርን የሚክደው ፈረንሳዊው ፈላስፋ ቮልቴር እነዚህን በራሪ ወረቀቶች በጣም ይፈራቸው ስለነበር «እነዚህ ትናንሽ በራሪ ወረቀቶች ሊፈሩ ይገባል፤ ሃያ ትላልቅ መጻሕፍት የእነሱን ያህል ለውጥ ማምጣት አይችሉም» በማለት ተናግሯል፡፡ የወንጌል በራሪ ወረቀቶችን ለማሰራጨት ይዘው የሚወጡ ክርስቲያኖች ያልተጠበቀ ታላቅ የወንጌል መልእክተኝነት ኃይል ሊገልጡ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ራስህን በወንጌል፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አስታጥቅ፡፡ በምትንቀሳቀስባቸው ስፍራዎች ሁሉ የምሥራቹን ቃል ምንም ሳያስቀሩ የሚያውጁ ትራክቶች በእጅህ ያዝ፡፡
በእርግጥ አብዛኞቻችን ለራሳችን የወንጌልን ባርኮትንና በሰማያት ያለ ርስትን መቀበል በጣም ያስደስተናል፤ ሆኖም ግን ወንጌል እንዲዳረስ መትጋት አንፈልግም፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ግን ይህን ማድረግ እንዳለብን በማያጠራጥር ሁኔታ ሲገልጽ «በሕይወትም ያሉት/ማለትም በንስሐና በመለወጥ የዘላለም ሕይወትን የተቀበሉ/ ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ» ይላል/2ቆሮ.5፡15/፡፡
ስለዚህ ጌታህንና አዳኝህን በታማኝነት ልታገለግለው እንደሚገባህ በጣም ልናበረታታህ እንወዳለን «... የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለ ፈሰሰ ተስፋ አያሳፍርም» ተብሎ በሮሜ 5፡5 ላይ ተጽፎአል፤ የእግዚአብሔር ፍቅር ፈሰሰ እንጂ ጠብ ጠብ አላለም፡፡ ስለዚህ «በደስታ ለእግዚአብሔር ተገዙ በሐሴትም ወደ ፊቱ ግቡ» የሚለውን ጥሪ በትኲረት እንስማ/መዝ.99-100-፡2/፡፡ እርሱን ለማገልገል የምንቆጥበው አንዳችም ነገር አይኑር፤ «በጥቂቱ የሚዘራ በጥቂቱ ደግሞ ያጭዳል፤ በበረከትም የሚዘራ በበረከት ደግሞ ያጭዳል» ተብሎ ተጽፏልና/2ቆሮ.9፡6/፡፡
ሳትሰናከሉም እንዲጠብቃችሁ፥ በክብሩም ፊት በደስታ ነውር የሌላችሁ አድርጎ እንዲያቆማችሁ ለሚችለው ብቻውን ለሆነ አምላክና መድኃኒታችን ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘላለምም ድረስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ግርማ ኃይልም ሥልጣንም ይሁን፤ አሜን።ኅብረት
በዕለታዊ ኑሮው ራሱን የሚያስጠጋበት መጠለያ ቤት የሌለው ሰው በእውነት የሚሳዝን ነው፤ እንደዚሁም ውጫዊው መጠለያ ቤት በእርግጥ እያለው በውስጡ ግን በዚያ ቤት ውስጥ እንደሆነ የማይሰማው ሰው ደግሞ ይበልጥ ያሳዝናል፡፡ በቤት ውስጥ ከመሆን ጋር የማናያይዘው ምን ነገር ይኖራል- በጋራ የተያዘ ፍቅር፣ መረዳዳት፣ የጋለ ስሜት፣ ጸጥታ እንዲሁም አንዳችን ሥራ ለመሥራት የሚያስችል ኃይል ሁሉ በቤት ውስጥ ይገኛል፡፡ አንተም በዳግም ልደት የእግዚአብሔር ልጅ ሆነሃል፤ በመሆኑም አሁን የኢየሱስ አካል ማለት የቤተክርስቲያን ብልት ሆነሃል፤ አንዳንዶች በተሳሳተ መልኩ እንደሚያስቡት ብዙ ቤተክርስቲያናት የሉም፤ ነገር ግን አንዲት ቤተክርስቲያን ብቻ አለች፤ ዳግም የተወለዱ ሁሉ በዚህች ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ከዚህ ውጭ ያሉት ግን ሁሉም በዚህች ቤተክርስቲያን የሉም፡፡ ዳግም ያልተወለዱት ሰዎች ምናልባት የተለያዩ ሃይማኖታዊ ድርጅቶች /Denominations/ አባል ወይም ከዚያ ውጪ ሊሆኑ ቢችሉም እንኳ የክርስቶስ አካል ብልቶች አይደሉም፤ ያ መሠረታዊ የሆነ ልዩነት ነው፡፡ እግዚአብሔር በያዘው የሕይወት መጽሐፍ ላይ የተመዘገበው ዳግም የተወለደ ብቻ ነው፤ ዳግም ያልተወለደው ግን በሕይወት መጽሐፍ ላይ ያልተመዘገበ ሲሆን እርሱም ወደ እሳት ባሕር የሚጣል ነው፡፡ «በሕይወት መጽሐፍ ላይ ተጽፎ ያልተገኘው ማንኛውም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣለ» ተብሎ እንደተጻፈ ነው/ራእ.20፡15/፡፡
ከዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነታ አኳያ ሁለት ዓይነት ብቻ ሰዎች አሉ፤ እነርሱም ዳግም የተወለዱ እና የጠፉ ናቸው፡፡ እነዚያ ዳግመኛ የተወለዱት ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ጉባኤ አለማቀፋዊ ክበብ አባላት ናቸው፡፡ እነርሱ ተጠርተው የወጡ ማለትም ከዚህ ከአሁኑ ክፉ ዘመን ተጠርተው የወጡ ናቸው፡፡ የእግዚአብሔር ጉባኤ ወይም የቤተክርስቲያን እውነተኛውና የመጀመሪያው ማንነቷም እነዚህ ተጠርተው የወጡ ሰዎች ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ብቻ መሰብሰባቸው እና ከዓለም መለየታቸው ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ከመወለድና በሰማይ ዜግነትን ከማግኘት የበለጠ ክቡር ነገር አለን?
ለመንፈሳዊ ሕይወትህ ዕድገት ዳግም ከተወለዱ ከሌሎች ወገኖች ጋር ኅብረት ማድረግ ያስፈልግሃል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ለብቻ የሚያዝ ክርስትናን ጨርሶ አያውቀውም፤ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች «በሐዋርያት ትምህርትና በኅብረት እንጀራውንም በመቁረስ በየጸሎቱም ይተጉ ነበር»/ሐዋ.2፡42/፡፡ እነዚህ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች በዙሪያቸው ላሉት እንደምን ያለ ምስክርነት ይሰጡ ነበር-
ነገር ግን አሁን እየሆነ ያለው ምንድን ነው- ሁሉንም ሊያሳፍሩ የሚችሉ ምክንያቶች አሉ፤ ግልጽ ለሆነው የእግዚአብሔር ቃል ታዛዥ ባለመሆን በጣም ታላላቅም ሆኑ በጣም ታናናሽ የሆኑ የክርስቲያን የእምነት ድርጅቶች /Denominations¼ ተፈጠረዋል፤ ይህም የቡድናውያን መንፈስ በየትኛም ቦታ ተንሰራፍቶ ይገኛል፡፡ ስለሆነም ዛሬ ከማንኛውም ጊዜ ይበልጥ ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር «ክርስቶስ ተከፍሏልን-» /1ቆሮ.1፡13/ እያልን ጩኸታችንን ልናሰማ ይገባናል፡፡
ጌታ ዛሬም ቢሆን በዚህ ወይም በዚያ ቦታ ለእርሱ ቃል ታዛዥ የሆኑ፣ ወደ ስሙ ብቻ የሚሰበሰቡ፣ እንዲሁም ራሳቸውን ከዓለማዊነት ተግባራት የለዩ የራሱ የሆኑ ሰዎች አሉት፡፡ እነዚህም «ክርስቲያን» ተብለው ከመጠራት ወዲያ ለራሳቸው ሌላ ማናቸውንም ስም ያልሰጡ ናቸው፡፡ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ ስያሜ ሌላ ስም አይጠቅስምና/ሐዋ.ሥራ11፡26 ተመልከት/፡፡ እነዚህም ክርስቲያኖች በሕይወታቸው ሁሉ የእግዚአብሔር ቃል ብቻ መሪያቸው ሲሆን በስብሰባቸውም ጌታ ብቻ ሥልጣን አለው፡፡ የእግዚአብሔርን ልጆች በሙሉ ከልባቸው ማፍቀር ይፈልጋሉ፤ ነገር ግን በአማኞች መካከል ባሉ ዓለማዊ ተግባራት እና የመከፋፈል መንፈስ በጥልቅ ያዝናሉ፤ ይህንንም ይቃወማሉ፡፡
ነገር ግን ይህን በተሳሳተ መንገድ አትረዳው፤ በአማኞች መካከል አንድነትን የሚያመጣው ሰው አይደለም፤ ብዙ ጊዜ ሰብአዊ በሆኑት የሃይማኖት ድርጅቶች ወይም ከማያምኑ ሰዎች አብሮ በመሆን በሚዘጋጅ ጽሑፍ ሥር ሆኖ በእውነት ሰው አንድነትን ሊያመጣ እንዴት ይችላል? እዚህ ላይ የሰው ጥረቶች ሁሉ ቦታ የላቸውም፡፡ እግዚአብሔር ለቃሉ ከመታዘዝ የበለጠ ወይም ያነሰ ነገር አይፈልግም፤ የእርሱ ቃልም የአማኞችን የአካል አንድነት እርሱ እንደመሠረተ ይነግረናል፡፡ ለእኛ ያለው ትእዛዙም በቀላሉ «በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ፡፡ በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ» በማለት በቀላሉ ይዖገራል /ኤፌ.4፡3-4/፡፡ ይህን በተመለከተ በተለይ 1ቆሮ. ምዕ. 12ን አንብብ፡፡
አሁን ልብ በል መሠረታዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱቂ እውነታዎች ሁሉ ግልጽና ቀላል ናቸው፡፡ ይህ ለምን ሆነ? ምክንያቱም ትንሽ የተባለ ልጅ እንኳ እነዚህን እውነቶች ሊረዳችው ስለሚችል ነው፡፡ ንስሐን፣ መለወጥን፣ እና ደኅንነትን የሚመለከት እውነት ግልጽና ለመረዳት ቀላል ነው፡፡ እንደዚሁም አማኞችን ሁሉ አንድነት የሚመለከተው እውነትም እኩል ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን የሰው ልጅ አሮጌው ተፈጥሮ፣ ፊት ለፊት መታየት ወደሚቻልበት ስፍራ በመምጣት ይደሰታል፤ ቀጥታ የክርስቶስ አካል ብልት መሆንን አይወድም፡፡ ነገር ግን ብልት የሆነ አማኝ የአካሉ ራስ ለሆነው ለኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ይገዛል፡፡ በአማኞች መካከል እንኳን ያለ የራስ ፈቃድ ቢኖር ይህ በራሱ አለመታዘዝና ጌታን አለማከበር ነው፤ የመከፋፈል ሁሉ ሥር ተዘርግቶ የሚገኘው በዚህ ውስጥ ነው፡፡
እግዚአብሔር በቅዱስ ቃሉ ባስቀመጣቸው መመሪያዎች መሠረት ከሌሎች አማኞች ጋር ብትሰበሰብ ይህ በራሱ መልካም ይሆናል፡፡ ነገር ግን በዚህ መልኩ ቃሉን በታማኝነት የሚታዘዙ ሰዎችን ፈልገህ ብታጣ ይህን ጉዳይ ትልቅ የጸሎት ርእስህ አድርገህ በጌታ ፊት ልታቀርበው ይገባል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ሲሰበክ ለማዳመጥ በምትሄድባቸው ስፍራዎች ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስ ምንም ሳይቀነስበት/ሳይጎድል/ እንደ እግዚአብሔር ቃል ተቀባይነት ማግኘት አለማግኘቱን በጥንቃቄ መርምር፡፡ በጥርጥር እና በማናቸውም የሐሰት ትምህርቶች ከእውነት ፈቀቅ ከማለት ትጠበቅ ዘንድ ያለማቋረጥ ጸልይ፡፡
ወደ ኋላ አትመልከት
ወደ ኋላ መመልከት ጥሩ አይደለም፤ ስለዚህ ይህን አታድርግ፡፡ በጌታ በኢየሱስ ያለው ሕይወት ብዙና ያማረ ስለሆነ አንድ በእርሱ ያመነ ሰው ወደየትም ስፍራ መመልከት አያስፈልገውም፡፡ ይህን የምታደርግ ከሆነ ከዚያ ወዲያ ምንም ዓይነት መሻሻል ማድረግ አትችልም፡፡ ጌታ ኢየሱስ «ማንም ዕርፍ በእጁ ይዞ ወደ ኋላ የሚመለከት ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም» ብሏል /ሉቃ 9፡62/፡፡
ወደ ኋላ መመልከት ደስተኞች አያደርገንም፤ ከኋላችን ያለው ምን ነበር- አስከፊ የሆነ በኃጢአት የተሞላ ጊዜ ነበር፡፡ መራራ ጣዕማቸውን ለረጅም ጊዜ ትተው የሚልፉ አስመሳይ ደስታዎች የነበሩበት ጊዜ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ለመያዝ ፈልገነው የነበረው ትልቅ ነጻነት ለራስ ማንነት ከመገዛት ውጪ ሌላ ምንም አልነበረም፤ ከዚህም ነገር መለኮታዊው አዳኝ ነጻ አወጣን፡፡
ይሁንና ሰይጣን አሁንም ሆነ ሌላ ጊዜ እነዚህን ነገሮች በዐይናችን ፊት እንደገና ለመደቀን አጋጣሚን ሁሉ ይጠቀማል፡፡ እርሱ ወደ ኋላ ለመመለስና ለጌታ አገልግሎት የማንስማማ እንድንሆን ለማድረግ ከፍ ያለ ፍላጎት አለው፡፡ ሰይጣን ከጌታ የተቀበልነውን የዘላለም ደኅንነት ሊነጥቀን እንደማይችል ያውቃል፤ ስለዚህ ቢንስ ቢያንስ ደስተኞች እንዳንሆንና ለምንም ነገር መልካም እንዳንሆን ሊያደርገን ይፈልጋል፡፡ በዚህ መንገድ በሰይጣን ማባበል ወደ ኋላው የሚመለከት ክርስቲያንም ደስታ የሌለው ሰው ነው፡፡
የዚህ ወደ ኋላ መመልከት ዓይነቶቹ ሁለት ናቸው፡-
የመጀመሪያው ዓይነትም ሰይጣን አማኙ ቀደም ሲል በፀፀት የተናዘዛቸውንና በእግዚአብሔርም ይቅር የተባሉትን የቀድሞ ኃጢአቶቹን በነፍሱ ፊት በማምጣትና እነርሱ በእውነት ይቅር መባላቸውን በማጠራጠር ሊያስጨንቀው መሞከሩ ነው፡፡ «የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባህርን ማዕበል ይመስላልና»/ያዕቆብ1፡5/፡፡ ይህ ከሆነ አሮጌው ባሕርይ እንደገና ይቀሰቀስና ከፍ ያለ ስሜታዊነት ልብን ይቆጣጠራል፡፡ ይህም ለሰይጣን በጣም አስፈላጊና ጠቃሚው ነገር ነው፤ እንደዚህ ዓይነት ክርስቲያንን ወደታች ገፍትሮ ይጥለው ዘንድ ይችላልና፡፡
አንድ ሰው ጥርጣሬዎችን በራሱ ሊቋቋም እንዴት ይችላል? የመንፈስ ሰይፍ በሆነው በእግዚአብሔር ቃል እንጂ ማንም በራሱ አስተሳሰቦችና ስሜቶች ጥርጣሬን ሊያስወግድ አይችልም፤ መጽሐፍ ቅዱስ «ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ እንዲሁ ኃጢአታችንን ከእኛ አራቀ» ይላል/መዝ.102-103-፡12/፡፡ ምናልባት የሰሜን ዋልታ ከደቡብ ዋልታ ምን ያህል እንደሚርቅ በትክክል መናገር ይቻል ይሆናል፤ ነገር ግን አንድ ሰው ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ ምድርን በሚዞር ጊዜ ሁልጊዜም ወሰን የሌለው ርቀት ስለሚኖር በምሥራቅና በምዕራብ መካከል ያለውን ርቀት መለካት ፈጽሞ አይቻልም፤ ስለዚህ ኃጢአትህን ይህን ያህል አርቆታል፡፡ በኢሳ.44፡22 ላይ «መተላለፍህን እንደ ደመና፣ ኃጢአትህንም እንደ ጭጋግ ደምስሼአለሁ፡፡ ተቤዥቼሃለሁና ወደ እኔ ተመለስ» ይላል፤ ስለዚህ ያለፈው ነገርህ እንዲህ መሆኑን እመን፡፡
ሁለተኛውና በጣም አደገኛ የሆነው ወደ ኋላ የመመልከት ዓይነት ደግሞ ሰይጣን የዚህ ዓለም ነገሮችን ለእኛ የሚማርኩ ለማደረግ መሞከሩ ነው፡፡ እርሱ በዚህ ውጤት ካገኘ እኛ ደስታ የሌለን እንሆናለን፡፡ ኢየሱስ በማያጠራጥርና ግልጽ በሆነ መንገድ «ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፡፡ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል፤ ሁለተኛውንም ይንቃል፡፡ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም» ብሏል /ማቴ.6፡24/፡፡ እንደዚሁም በሌላ ቦታ የእግዚአብሔር ቃል አሁንም በማያሻማ መልኩ «ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፡ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም፤ ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል» ይላል/1ዮሐ.2፡15-17/፡፡
አንድ ህፃን ልጅ ገና በእግር መራመድ ሲጀምር አንዳንድ ጊዜ ቢወድቅ የሚደንቅ አይደለም፤ እንዲሁ ገና ለጋ የሆነ የእግዚአብሔር ልጅም አልፎ አልፎ በኃጢአት ሊወድቅ ይችላል፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ልጅ መሆን ማለት ኃጢአት አልባ መሆን ማለት አይደለምና፡፡ ይሁንና ጌታ ኢየሱስ ደሙን ያፈሰሰው ላለፉት ኃጢአቶቻችን ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ኃጢአቶቻችን ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ታዲያ እኛ በኃጢአት ብንወድቅ ምን መደረግ አለበት? ኃጢአቶቻችንን መሸሸግና ጉዳት እንደማያደርሱ ማሰብ የለብንም፤ ነገር ግን የግድ ልንናዘዛቸው ይገባል፤ «በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነፃን የታመነና ፃድቅ ነው» ተብሏልና /1ዮሐ.1፡9/፡፡ ይህን ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ከጌታ ጋር ባለህ ኅብረት የምታገኘው ደስታ በኃጢአት ምክንያት ከተቋረጠ ይህን ኃጢአት በእርሱ ፊት ለመናዘዘ አትታክት፡፡ ይህን ካደረግህ ስሜቶችህን አታዳምጥ፤ ይቅርታን ማግኘት የእምነት ጉዳይ እንጂ የስሜቶች ጉዳይ አይደለምና፡፡ በውስጥህ ሊኖሩም ላይኖሩም የሚችሉትን ስሜቶችህን ሳይሆን የእግዚአብሔርን ቃል እመን፡፡ ከዚያም ሰላምና ደስታ እንደገና ወደ ልብህ ተመልሰው ይገባሉ፡፡
ወደ ላይ ተመልከት
ራስህንም ሆነ ሌሎችን አትመልከት፡፡ ከዚያ ይልቅ «የእምነታችንን ራስና ፈጻሚ» ወደ ሆነው ወደ ጌታ ኢየሱስ አብዝተህ ተመልከት/ዕብ.12፡2/፡፡ እርሱን ደግሞ በቃሉ ልትመለከተው ትችላለህ፤ ይህ ደስተኛ ወደሆነ የክርስቲያን ሕይወት የሚወስድ መንገድ ነው፤ ከዚያም ይበልጣል፡፡ ጌታን እየጠበቅህ ወደ ላይ ተመልከት፤ የእርሱ እንደገና ተመልሶ የመምጣቱ ተስፋ በመጽሐፍ ቅዱስ ስፍራ የያዘውን ያህል ማንኛውም ትንቢት ስፍራ አልያዘም፡፡ ሕያዋን የሆኑ ክርስቲያኖች ጌታ ኢየሱስን የሚጠባበቁ ናቸው፡፡
አሁን የምንኖረው ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ሁከትና ግራ መጋባት ባለበት ዘመን ላይ ነው፡፡ በየስፍራው ወደፊት ስለሚመጣው ነገር ያልተገለጠ ፍርሃት አለ፡፡ ለዓለም የደህንነትን ዋስትናና ሰላምን ለማምጣት ይንቀሳቀስ የነበረው ሳይንስ፣ ኃይል የሌለው መሆኑን ብቻ ሳይሆን አደገኛና የሚያጠፋ መሆኑንም ራሱ በራሱ በቀላሉ አረጋግጧል፤ እናም አለማመን፣ ንፉግነትና ጭካኔ ከመቼውም ይልቅ በእጅጉ እየተስፋፉ ነው፡፡
አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስ ለመጨረሻው ዘመን ከሚሰጠው ሥዕል ጋር የእኛ ዘመን እንዴት እንደሚመሳሰል ላለማወቅ በዕውርነት የተጠቃ ሊሆን ይችላል፡፡ ከእነዚህ ከሚያሸብሩ ሁኔታዎች በስተጀርባ ከእስራኤል ጋር የሚያያዙ ክስተቶች እየተፈጸሙ ነው፡፡
ነገር ግን እኛ የምንጠብቀው የዓለምን መጨረሻ ወይም ፍርዶችን አይደለም፤ ይልቅስ እኛ አብዝተን የምንጠባበቀው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ዳግመኛ ተመልሶ መምጣት ነው፡፡ ይህም ግልጽ የሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል ኪዳን ነው እንጂ የማይጨበጥ ሕልም አይደለም፡፡ ኢየሱስ ራሱ ስለዚህ ሲናገር «በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር፤ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፤ ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ፤ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ» ብሏል/ዮሐ.14፡3/፡፡ በተጨማሪም በ1ቆሮ.15፡51-58 እና በ1ተሰ.4፡13-18 ላይ ይህ የጌታ ለአማኞች ተመልሶ መምጣት እንዴት እንደሚፈጸም የተጻፈውን አንብብ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ የዘመናችን ዘባቾችና ፌዘኞች በዚህ ተስፋ ላይ ምን እንደሚሉ አስቀድሞ ተናግሯል፡፡ «በመጨረሻው ዘመን እንደ ራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ ዘባቾች በመዘበት እንዲመጡ ይህን በፊት እወቁ፤ እነርሱም የመምጣቱ የተሰፋ ቃል ወዴት ነው? አባቶች ከሞቱባት ጊዜ ከፍጥረት መጀመሪያ ይዞ ሁሉ እንዳለ ይኖራልና ይላሉ» ይላል /2ጴጥ.3፡3-4/፡፡ በሁሉም ሃይማኖተኛ ዓለም ላይ ተቀምጦ የሚነገረው ይህ የዓለም ዘበት በትክክል የሚገለጠው በስውር ፍርሃት ነው፤ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች በጌታ መመለስ ውስጥ ከአስፈሪዎቹ የመጨረሻ ፍርዶች ጋር የተያያዙ አስፈሪ ክስተቶችን ያያሉና ነው፡፡ እነርሱ ካሉበት ሁኔታ አንጻር ሁሉም በጣም ትክክል ናቸው፤ ሆኖም ዳግመኛ የተወለደ ሰው ግን ደኅንነቱ ሙሉ ለሙሉ የተጠበቀ ነው፤ የትኞቹንም ፍርዶች መፍራት የለበትም፤ ከዚህ የተነሳ ሁሉም አማኞች በሙሉ ወደ ላይ ይመልከቱ፤ ጌታንም ይጠብቁ፡፡ ይህም ሁኔታ ብዙዎች አሁንም ገና መልካሙን የምሥራች ይሰሙ ዘንድ እና መዳንንና አርነትን በእርሱ ለማግኘት ወደ ጌታ ኢየሱስ በፍጥነት ይቀርቡ ዘንድ እንዲችሉ በዚህ ምድር ላይ ያለንን ጊዜ በአግባቡ እንድንጠቀም ይገፋፋናል፡፡
«ሳትሰናከሉም እንዲጠብቃችሁ በክብሩም ፊት በደስታ ነውር የሌላችሁ አድርጎ እንዲ!ያቆማችሁ ለሚችለው ብቻውን ለሆነ አምላክና መድኃኒታችን ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘላለምም ድረስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ግርማ ኃይልም ሥልጣንም ይሁን አሜን» (ይሁዳ 24-25)