ስብከት  

/ማቴ.12፡41/

ጊዜና ዘላለም በክርስቲያን ሕይወት ውስጥ

በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 12 ውስጥ የተቀመጡት የእውነት መርሆዎች እጅግ የከበሩና ሕይወትን የሚመረምር ጠባይ ያላቸው ናቸው፡፡ ለእነዚህ መርሆዎች ተግባራዊ ምላሽን መስጠት በአሁኑ ጊዜ እጅግ የበዛ ጥቅም አለው፡፡ በዚህ በተገለጸው እውነተኛ በሆነው ብርሃን ውስጥ ዓለማዊ ፍትወትና ሥጋዊነት ሊኖሩ አይችሉም፤ ከሥራቸውም ይደርቃሉ፡፡ አንድ ሰው ለዚህ እጅግ ውድ ለሆነው የመነ.. ሃሳብ ክፍል አጠር፣ ጠቅለል ያለና ግልጽ ርዕስ እንዲሰጥ ቢጠየቅ ..ጊዜ ከዘለዓለማዊነት አንጻር.. ብሎ ሊጠራው ወይም ርዕስ ሊሰጠው ይችል ይሆናል፡፡ ነገሮች ሁሉ በዚህ ዓለም ከሚገኙበትና ከሚታዩበት በፍጹም ተቃራኒ በሚሆኑበት በዚያኛው ዓለም ብርሃን ውስጥ ደቀመዛሙርቱን ሊያኖር ጌታ በግልጽ ሲያቅድና በማይታዩት ነገሮች ቅዱስ ተጽእኖ ሥር ልባቸው እንዲሆን ሕይወታቸው በሰማያዊ መርሆዎች ኃይልና ሥልጣን ይያዝ ዘንድ ነው፡፡


ምን እንድትመልሱ አትጨነቁ /ቊ.11/

እንደዚህ ዓይነቱ የታመነ መለኮታዊ መምህር ሐሳብ እጅግ ከፍ ላለው ትምህርቱ ..አስቀድማችሁ ከፈሪሳውያን እርሾ ተጠበቁ፣ እርሱም ግብዝነት ነው.. በማለት እጅግ ተፈላጊነት ባላቸው ቃላት ጠንካራ መሠረትን አስቀምጧል፡፡ በነፋስ ውስጥ ማዕበል ወይንም የሚያናጋ ነገር መኖር የለበትም፤ ጥልቅ የሆኑት የሰው ልጅ የሐሳብ ምንጮች ሁሉ ወደ መገለጥ መምጣት ይኖርባቸዋል፡፡ ንጹሕ የሆነውን ሰማያዊ ብርሃን ወደ ሥነምግባራችን ጥልቀት ውስጥ ዘልቆ ይገባ ዘንድ ልንፈቅድለት ይገባናል፡፡ ስውር በሆነው የነፍስ ፍርድና በቋንቋ አመራረጣችንና አጠቃቀማችን መካከል ማለትም ከመንገዱ በተዛባው ሕይወታችንና በከንፈራችን ምስክርነት መካከል ልዩነት እንዲኖር አይጠበቅም፡፡ በአጭሩና ጠቅለል ባለ አገላለጥ በተለይም ከዚህ ተግባራዊ እውነትነት ካለው ትምህርት ተጠቃሚና ትርፋማ እንሆን ዘንድ ከታማኙና መልካሙ ልብ የመነጨው ጸጋ ያስፈልገናል፡፡

ይህን እውነት በቀዘቀዘ ስሜት ወይንም በቸልታ እንድንሰማ የተገባ አይደለም፡፡ ልንወደው አንችል ይሆናል፡፡ ቀለል ያለ የቅዱሳን መጻሕፍትን ሐሳቦች፣ ትምህርቶችንና ትንቢቶችን የመምረጥ ዝንባሌ በብዙዎች ዘንድ ይስተዋላል፡፡ ምክንያቱም እነዚህን ከተለያዩ የዚህ ዓለም ሐሳቦች ከምኞት ልምምዶች /ከመጐምዠት ልምምዶች/ እና የራስን ጥቅም ከመፈለግ ጋር በቀጥታ በማያያዝ ስለሚጠቅሙ ሊሆን ይችላል፡፡ እውነት በእውነትነቱ በቀላሉ መቀበል ሊያዳግት ቢችልም፣ ይህ የእውነት መርህ ግን በማንኛውም ሐሳብ ላይ በፍጥነት የመገለጥና ሥጋዊ ነገሮችን የመቁረጥ ኃይልና ሥልጣን ያለው በጸጋው ራሳቸውን ከፈሪሳውያን እርሾና ግብዝነት ሊያነጹ የሚፈልጉትን ሁሉ የሚደግፍና የሚያድን ነው፡፡ ይህ እርሾ እጅጉን የማስመሰል ጿባይ ያለውና በተለያየ ቅርጽ ወይንም ዓይነት ስለሚገለጥ በጣም አደገኛ ነው፡፡ በእርግጥ በሚገኝበት ስፍራ በነፍስ ተሞክሯዊ እውቀትና ልምምዳዊ ቅድስና እድገት ፊት ሊወጡት የማይቻል መሰናክል ይኖራል፡፡ ሙሉ በሙሉ ማንነታችንን ለመለኮታዊ እውነት ሥራ አሳልፈን ካልሰጠን ከዚህ ከመለኮታዊ ብርሃን እራሳችንን ወደ ሌላኛው ጥግ ወይንም ወደራሳችን ጉድጓድ በመግባት የምንሸሽ ከሆነ የተደበቁና እግዚአ ብሔር የማይከብርባቸውን የራሳችንን፣ ነገሮች ብቻ የምንከባከብ ከሆነ ተአማኒነት በጐደለው ሁኔታ እውነትን ለራሳችን የግል ልምምዶች ማጠናከሪያ ለማዋል የምንፈልግ ከሆነ፣ ሐሳባችንን የእርሱ ባል..ት እንዳያርፍበትና እንዳያስተካክለው የምንሸሽና የምንከላከል ከሆነ በእርግጥም በግብዝነት እርሾ እንደተነካካንና እንደተበከልን ብሎም በመንፈሳዊ እድገታችን በፍጹም ክርስቶስን መምሰል እንደማንችል ያሳያል፡፡ ስለዚህም የክርስቶስ ደቀመዝሙር ለሆነ ሁሉ ከዚህ ክፉ እርሾ አንዳችም ነገር ወደ ልቡ የምስጢር ክፍሎች ይገባ ዘንድ እንዳይፈቅድ ይጠበቅበታል፡፡ እርሾው ከእኛ ይርቅ ዘንድ እኛም በሁሉም ሁኔታ ..ጌታ ሆይ፣ ባሪያህ ይሰማልና ተናገር.. ማለት እንችል ዘንድ የጌታ ጸጋ ይርዳን፡፡

ግብዝነት መንፈሳዊ ሕይወትን ማበላሸት ብቻ ሳይሆን የመንፈሳዊ ህይወትን ዓላማ የሚያስጥልም ነው፡፡ ..የማይገለጥ የተከደነ፣ የማይታወቅ የተሰወረ ምንም የለምና.. እንደተባለው የእያንዳንዱ ሰው ሃሳብ ወደዚህ ብርሃን ይመጣል፣ እያንዳንዱንም ሰው ይህ በተገለጠው እውነተኛ ብርሃን ስፍራውን እንዲያውቅ ያስችለዋል፡፡ ይህም አሁን እውነት የሚያደርገው ነገር ሲሆን በክርስቶስ ፍርድ ወንበር ግን በመጨረ.. ላይ በሚገባ ይገለጣል.. ግብዝነትም ሆነ ማንኛውም ውጤት ከክርስቶስ የፍርድ ወንበር በሚወጣ ብርሃን ይገለጣል፡፡

አንዳችም ነገር ከዚህ ብርሃን እንዲያመልጥ አይፈቀድለትም፡፡ ምንም እንኳን አሁን ያለውና እየሆነ ያለው ከዚህ በተለየ በተቀራኒው ቢሆንም በኋላ ግን እውነትነቱ የተረጋገጠ ይሆናል፡፡ በተጨማሪም እያንዳንዱ ነገር የራሱ በሆነ ስም ባይገለጥም የራሱ ያልሆነውንና ያልተገባውን ስፍራ ቢይዝም በዚያን ጊዜ ግን ሁሉም በትክክል የራሱንና ሊይዝ የተገባውን ስምና ስፍራ ይይዛል፡፡ በዚህ ዓለም ሐሳብ መያዝ ጠንቃቃነት ሁሉንም የመያዝና የምኞት መንፈስ መያዝ የአርቆ አስተዋይነት ችሎታ የሚፈልጉትን በማድረግና ራስን ማርካት እንዲሁም ያለአግባባ በሆነ ራስን ማበልጸግ እንደፍትሐዊ አስተዳደርና በሥራ ውስጥ የሚታይ የተመሰገነ ትጋት ተደርጐ የሚቆጠርበትን ሁኔታ እናያለን፡፡ እነዚህ ነገሮችም ይህንን የተሳሳተ ሥፍራቸውንና ስማቸውን እንደያዙ የሚቀጥሉት ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነው፤ ነገር ግን ወደፊት ሁሉም ከዚህ ፍጹም ተቃራኒ በሆነ በትክክለኛ ማንነትና ምንነታቸው ይገለጣሉ፡፡ በክርስቶስ ወንበር ፊት ሁሉም ነገሮች በትክክለኛው ቀለማቸውና መልካቸው ሲታዩ በተገቢው ስማቸውም ይጠራል፡፡ ስለዚህም የልብ ሁሉ ምስጢር በሚገለጥበት በዚያን ጊዜው ብርሃን አንጻር ነገሮችን ሁሉ ማየት፣ እንደሚገባ መመላለስና የሚገባውን ሁሉ መፈጸም የማንኛውም እውነተኛ ደቀመዝሙር ጥበብ ሊሆን ይገባዋል፡፡

ስለዚህም ከፍ ባለ መሠረት ላይ የቆመው ሐዋርያው ..መልካምም ቢሆን ወይንም ክፉ እንዳደረገ እያንዳንዱ በሥጋው የተሠራውን በብድራት ይቀበል ዘንድ ሁላችን በክርስቶስ ፍርድ ወንበር ፊት ልንገለጥ ይገባናል፡፡.. አለ /2ቆሮ.5፡10/፡፡ ይህ አገላለጥ የደቀመዝሙርን አእምሮ ይረብሽ ይሆን? ልቡን ከግብዝነት እርሾ ሁ ሉ በተግባር ላይ የማናውለው ከሆነ በሸራ ድንኳን ላይ ሙቀት ሊሰጥ የማይችል የጿሐይ ጮራን/ጨረርን/ ስዕል ስሎ እጅግ በረሃብና በቅዝቃዜ ተቆራምዶ በውስጡ የተቀመጠ ሰውን እንመስላለን፡፡

ምን እንድትመልሱ አትጨነቁ /ቊ.11/

አሁን በዚህ በፊታችን ባቀረብነው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ ከሰው ሐሳብ በላይ የሆነውን የተቀደሰውን ክብር ግልጽና በማንኛውም ሁኔታ ለድርድር ሊቀርብ በማይችል መልኩ ከክርስቶስ ምስክርነት ጋር ተያይዞ ቀርቦልናል፡፡ እንደዚሁም በሕይወታችን ተዘልለን ........ እንድንኖር የሚያስችለንን የአባታችንን ደግነትና ጥበቃ እናነባለን፡፡ ልባችንን ከዚህች ዓለም ከሆነው ፍርሃትና ከሰው ሃሳብ ተጽእኖ በላይ ካደረግንና የራሳችንን ጠጉር እንኳን ሳይቀር ግድ በሚለውና የእኛን ኃላፊነት በወሰደው በእግዚአብሔር ላይ በመደገፍ ተረጋግተን የምንኖር ከሆነ በሰዎች ፊት ክርስቶስን ለመግለጥና ስለእርሱ ለመመስከር እንችላለን/ቁ.8-10/፡፡ ስለሚኖረንም ምስክርነት እርሱ እራሱ ልናደርግና ልንናገር የሚገባን ነገር ሁሉ ይሰጠናል፡፡ የም..ክርነት ሥፍራችን የተጠበቀ እንዲሆን ይረዳናል፡፡ ..ወደ ምኩራባቸው ያመጧችኋል.. ወደገዥዎችም ወደ ነገ..ታትም ትወሰዳላች..፣ አሳልፈውም ሲሰጧችሁ የምትናገሩት በዚያ ሰዓት ይሰጣችኋልና እንዴት ወይስ ምን እንደምትናገሩ አትጨነቁ፤ በእናንተ የሚናገር የአባታችሁ መንፈስ ነው እንጂ የምትናገሩት እናንተ አይደላችሁም.. ተብሏል፡፡ ብቸኛውና ትክክለኛ ለሆነው ለክርስቶስ የሚኖረን ምስክርነት መሠረቱ ከሰዎች ተጽእኖ ሥር ሙሉ በሙሉ መላቀቅና ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር ላይ መታመን ነው፡፡ በሰው ሐሳብ ተጽእኖ ሥር ይበልጥ እየሆንን በመጣን መጠን ለክርስቶስ አገልጋይነት የሚኖረን ብቃት እየወረደ ይመጣል፤ ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ከዚህ ተጽእኖ ሥር ማምለጥና ነጻ መሆን የምንችለው በእግዚአብሔር በሚኖረን ከፍ ያለ እምነት ነው፡፡ ልባችን በእግዚአብሔር ነገር ሲያዝና ሲሞላ ለፍጥረታዊው የዚች ዓለም ሐሳብ ሥፍራ ሊኖረው አይችልም፡፡ ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር የሚያስጨንቁንን ነገሮች ከእኛ ሊያስወግድ የቻለ ወይንም የሚችል ማንም እንደሌለ በፍጹም እርግጠኞች መሆን ይጠበቅብናል፡፡ እግዚአብሔር ብቻውን ይህን ማድረግ ስለቻለና ደግሞም ወደፊት ስለሚችል ከማንም በላይ በእርሱ እንታመናለን፡፡ ለማንኛውም አፋጣኝ ጉዳይ ትንሽም ይሁን ትልቅ እግዚአብሔር ብቻውን በቂ ነው፡፡ እኛም እርሱ እግዚአብሔር መሆኑን በማወቅ ብቻ በእርሱ እንደገፍ፡፡

እግዚአብሔር ሰውን እንደ መገልገያ መጠቀሙ እርግጥ ነው፤ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ይልቅ በሰዎች ላይ፣ መሳሪያውን ከሚጠቀሙበት እጆች ይልቅ በመሳሪያው ላይ የምንደገፍ ከሆነ በራሳችን ላይ መርገምን እናመጣለን፡፡ ..በሰው የሚታመን ሥጋ ለባሹንም ክንዱ የሚያደርግ ልብንም ከእግዚአብሔር የሚመልስ ሰው ርጉም ነው../ኤር.17፡5/ ተብሎም ተጽፏልና፡፡

ጌታ እግዚአብሔር ኤልያስን ይመግቡት ዘንድ ቁራዎችን ተጠቅሟል፤ ነገር ግን ኤልያስ በቁራዎቹ ላይ የመደገፍ ሐሳብም ሆነ ዝንባሌ አልታየበትም፡፡ ይህ ነው በእኛ ህይወትም ለዘለዓለም ሊሆን የሚገባው፡፡ እምነት በእግዚአብሔር ላይ መደገፍ ከእርሱ ብቻ መጠበቅ ወደ እርሱ መጠጋትና እርሱን መከተል በእርሱም ላይ እምነትን መጣል እርሱ እግዚአብሔር ብቻ እንደወደደ ይሠራ ዘንድ ሥፍራን መስጠት ማንኛውንም ፍጥረታዊ ድጋፍ በመፈለግ የጌታ የነጠረ መንገድ እንዳይነቀፍ ማድረግ ሙሉ በሙሉ የእርሱ የጌታ የከበረ እውነት በማንነቱ ይገለጥ ዘንድ መፍቀድና ሁሉንም ነገር ለእርሱ መተው አለበት፡፡ እግዚአብሔር እጅግ የተወደደና በዚች ዓለም የእርሱንና የሰውን በአገባቡ እንድንለይ የሚያስችለንና ተገቢውንም ስፍራችንን የሚሰጥ ነው፡፡



ከዮናስ የሚበልጥ



መጽሐፍ ቅዱስ በብሉይ ኪዳን ክፍሉ በምሳሌና በጥላ ስለክርስቶስ የሚናገር እንደሆነ ግልጥ ነው፤ በማደሪያው ድንኳን ውስጥ የሚገኙት ንዋያተ ቅድሳትና በውስጧም የሚፈፀሙት የመሥዋዕት ዓይነቶች እንዲሁም ሌሎች ሥርዓታት በጥላነት ስለክርስቶስ ይናገሩ ነበር፤ በተጨማሪም በህልምና በራእይ የተገለጡ እንዲሁም ታሪክና ድርጊት የሆኑ በምሳሌነት ስለ ክርስቶስ የሚናገሩ ብዙ የብሉይ ኪዳን ክፍሎች አሉ፤ ከዚህም አንፃር ዮናስ በእርሱ በኩል በተገለጠው ሁኔታ በምሳሌነት ስለ ክርስቶስ የሚናገር የብሉይ ኪዳን ነቢይ ነው፡፡

አንዳንዶቹ ምሳሌያት ከአማናዊው ነገር ጋር በቀጥተኛ መንገድ የሚነጻጻሩ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ የማወዳደር /ማበላለጥ/ መንገድን ተከትለው የሚነጻጸሩ ናቸው፡፡ ዮናስ ከክርስቶስ ጋር ሊነጻጸር የቻለበትን መንገድ ስንመለከት ክርስቶስ ከዮናስ ይልቅ የሚበልጥ መሆኑን በመግለጥ በሁለተኛው መንገድ የተነጻጸረ እንደሆነ እንረዳለን፡፡

«እነሆ ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ» የሚለውን ማራኪ ቃል የተናገረው ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ይህንንም ቃል የተናገረው «መምህር ሆይ ከአንተ ምልክትን ልናይ እንወዳለን» ላሉት አይሁድ ነው፡፡ እነዚህም አይሁድ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን መካከል አንዳንዶቹ ናቸው፤ ጻፎች የሚባሉት የኦሪት መጻሕፍትን የሚገለብጡ /የሚያባዙ/ ሲሆኑ ፈሪሳውያን ደግሞ ሕግ አጥባቂዎችና ሕግ አዋቂዎች ናቸው፡፡ ከዚህም የተነሣ ጻፎችና ፈሪሳውያን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የሚተርኩትን ነገር ያውቃሉ ብሎ ማሰብ ይቻላል፡፡ በመሆኑም በትንቢተ ዮናስ የተመዘገበውን የዮናስን ታሪክ በሚገባ ሊያውቁ እንደሚችሉ እሙን ነው፤ ይልቁንም በዮናስ ታሪክ ውስጥ የታየውን አስደናቂ ምልክት ማለትም በዓሣ አንባሪ ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት አድሮ መውጣቱንና ለነነዌ ሰዎች መስበኩን በሚገባ የሚያውቁ ሰዎች ናቸው፤ አይሁድ ደግሞ ምልክትን ይሻሉና /1ቆሮ.1፡22/ እንዲህ ያለውን ምልክት በጣም እንደሚያጠኑት ደጋግመውም እንደሚመሰክሩለት መገመት ይቻላል፡፡ እነዚህ ሰዎች ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በማስተማር ዘመኑ በተደጋጋሚ ያደረጋቸውን ምልክቶች አይተዋል /ማቴ.8፡1-34፣ 9፡1-8፣ 18-34፤ 12፡9-22/፡፡ ሆኖም ሕዝቡ «እንዲህ ያለ በእስራኤል ዘንድ ከቶ አልታየም እንጃ ይህ የዳዊት ልጅ ይሆን?» እያሉ ሲደነቁ ፈሪሳውያን ግን «በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል» ወይም «ይህ በብኤል ዜቡል በአጋንንት አለቃ ካልሆነ በቀር አጋንንትን አያወጣም» ይሉ ነበር /ማቴ.9፡34፤12፡24/፡፡ በዓይን የሚታየውንና በግልጥ ምልክት የተረጋገጠውን እውነት ከሕዝብ ሁሉ ተለይቶ መቃወም የጻፎችና የፈሪሳውያን ልማድ ነበር፤ ቅን ልብ ቢኖራቸው ኖሮ ያዩአቸው ምልክቶች ሁሉ የኢየሱስን መሢሕነትና የእግዚአብሔር ልጅነት ለማመን የሚያስችሏቸው ነበሩ፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ አጋንንትን በሥልጣን ማዘዙና ካደሩባቸው ሰዎች ማስወጣቱ ሊክዱት የማይችሉት ተአምር ቢሆንም ስለሚጠሉት ብቻ በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል ለማለት ደፈሩ፤ ከእነርሱ መካከል እውነተኛ ሰው የነበረው ፈሪሳዊው ኒቆዲሞስ እንደመሰከረው ኢየሱስ ያደርጋቸው የነበሩትን ምልክቶች ማድረግ የሚችል አልነበረም /ዮሐ.3፡2/፡፡ ነገር ግን 5 እንጀራ እና 2 ዓሣን ያበረከተበትን ምልክት በፊታቸው ባደረገ ጊዜ «እንኪያ አይተን እንድናምንህ ምን ምልክት ታደርጋለህ? ምንስ ትሠራለህ? ይበሉ ዘንድ ከሰማይ እንጀራ ሰጣቸው ተብሎ እንደተጻፈ አባቶቻችን በምድረ በዳ መና በሉ» በማለት ያዩትን አስደናቂ ምልክት ሊያቃልሉ ሞከሩ /ዮሐ.6፡30-31/፡፡ ጌታ ኢየሱስ «ክፉ ትውልድ» ብሎ እንደጠራቸው ሁሉ የሰውን ልጅ የመጨረሻ የክፋት ባሕርይ ተላብሰው ስለነበር እርሱ ሲያደርጋቸው የነበሩትን ታላላቅ ምልክቶች እያዩ ለማመን ተሣናቸው፤ እነዚህ ሰዎች ክፉ ብቻ ሳይሆኑ አመንዝራ ትውልድም ነበሩና በየጊዜው የተለያየ ምልክትን ማየት ይፈልጋሉ እንጂ በታየው ምልክት አምነው የኢየሱስን የእውነት ቃል ተቀብለው ንስሐ ሊገቡ አልቻሉም፡፡ እንደሚታወቀው «አመንዝራ» የሚለው ቃል በሚያደርገውና በሚያየው ነገር የማይረካ፣ እዚህም እዚያም የሚል፣ ያልተገደበ ፍላጐት ያለው፣ በፊት ያየውንና የያዘውን እየናቀ ሌላ አዲስ ነገርን የሚፈልግ በብዙ ነገሮችና ሁኔታዎች የተጠመደ ሰውን ያመለክታል፡፡ እንዲህ ዓይነት ትውልድ በጌታ በኢየሱስ ሲደረግ በሚያየውና፣ ሲነገር በሚሰማው በአንድ ነገር አይረካም፤ አይረታምም፤ እንዲያውም በምትኩ ለበፊቶቹ ምልክቶችና ስብከቶች የነበረውን አድናቆት እየተወ ሌላ አዲስ ምልክትና አዲስ ትምህርት ፍለጋ አንዴ እዚህ አንዴ እዚያ ሲቅበዘበዝ ይኖራል፡፡ ታዲያ ለእንዲህ ዓይነት ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምን ምልክት ይሰጠዋል?


ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ሌላ ምልክት አይሰጠውም

ጌታ ኢየሱስ ራሱ ከአንዴም ሁለት ጊዜ በግልጥ እንደተናገረው ለእንደዚህ ዓይነት ክፉና አመንዝራ ትውልድ «ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ሌላ ምልክት አይሰጠውም» /ማቴ.12፡39፣ ማቴ.16፡4/ ተመልከት/፡፡ ጌታችን ኢየሱስ የጠቀሰው በነቢዩ በዮናስ የታየው ምልክት ዮናስ በዓሣ አንባሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ማደሩ ነው፡፡ በትንቢተ ዮናስ ላይ እንደተገለጠው ዮናስ ወደ ታላቂቱ ወደ ነነዌ ከተማ ሄዶ እንዲሰብክ ከእግዚአብሔር የተላከ ነቢይ ነበር፡፡ ለእግዚአብሔር ባለመታዝዘ ወደ ነነዌ ከመሄድ ይልቅ ወደ ተርሴስ በመርከብ ቢኰበልልም እግዚአብሔር በባሕሩ ላይ ማዕበል አስነሥቶ የዮናስን አለመታዘዝ በተሳፋሪዎቹ መካከል ከገለጠ በኋላ ወደ ባሕር እንዲጣል አደረገው፤ በባሕሩ ውስጥ እርሱን የሚውጥ ዓሣ አንባሪም እንዲዘጋጅ አደረገ፤ ከሦስት ቀንም በኋላ እግዚአብሔር ዓሣውን አዘዘው፤ ዓሣውም ዮናስን በየብስ ላይ ተፋው /ዮና.1፡1፣2፡11/፡፡ በዮናስ ላይ የታየው ምልክትም ይህ በዓሣ ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት መኖሩ ነው /ዮና.2፡1/፡፡

ኢየሱስን «ከአንተ ምልክት እንድናይ እንወዳለን» ብለው የጠየቁት ጻፎችና ፈሪሳውያን ይህን በዮናስ ላይ የታየውን ምልክት በእርግጥ በዓይናቸው አላዩም፤ ነገር ግን ከነቢያት መጻሕፍት ማለትም ከትንቢተ ዮናስ ውስጥ አንብበው የሚያውቁ ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ ኢየሱስ ‹ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ሌላ ምልክት› አይሰጠውም አላቸው፡፡ ኢየሱስ ራሱ ብዙ ምልክቶችን እያደረገ በነበረበት በዚያ ዘመን የዮናስን ምልክት ለዚያ ትውልድ በቂ እንደሆነ መናገሩ እግዚአብሔር በኋላ ዘመን ለሚነሣ ትውልድ ቀድሞ የተደረገውን ምልክት በበቂ ማስረጃነት እንደሚጠቀምበትና የዚያንም ትውልድ ምልክት የማየት ፍላጐት ለማሟላት ብሎ ሌላ ምልክት እንደማያደርግ ያስረዳል፤ እንዲሁም የኋላ ዘመን ትውልድ ምንም እንኳ በዓይኑ ባያያቸውም በቅዱሳት መጻሕፍት ተመዝግቦ የሚያነባቸውንና ሁልጊዜም በየስብከቱ የሚሰማቸውን ታላላቅ ምልክቶችን ቃሉን የሚያጸኑ ማስረጃዎች መሆናቸውን አውቆ በመቀበል ሊያምን እንደሚገባ ያስገነዝባል፡፡

አንድ ክርስቲያን የሚያምነውን የወንጌል ቃል የሚያጸኑለት የተትረፈረፉ ምልክቶች በቅዱሳት መጻሕፍት ተመዝግበውለታል፤ ኢየሱስ ያደረጋቸውን ምልክቶች በተመለከተ ከተጻፉትም ውጪ ብዙ ምልክቶች ተደርገው እንደነበረ ተገልጧል /ዮሐ.20፡30/፡፡ በሐዋርያትም እጅ ብዙ ድንቅና ምልክት በሕዝብ መካከል ይደረግ ነበር /የሐ.ሥ.2፡43፣5፡12/፡፡ እነዚህም በሐዋርያት እጅ ይደረጉ የነበሩት ምልክቶች የሐዋርያነታቸው ምልክት በመሆን ያገለግሉ ነበር /2ቆሮ.12፡12/፡፡ የምልክቶቹ ዋና ዓላማ ግን ሐዋርያት ከጌታ የሰሙትን የእውነት ቃል ለሌሎች ሲያስተላልፉ ቃሉ ከእግዚአብሔር መሆኑን ማጽናት /ማረጋገጥ/ ነበር /ማር.16፡20፣ ዕብ.2፡4/፡፡ እነዚህ ሁሉ ምልክቶች የኋለኛው ዘመን ትውልድ ሳያያቸው ሊያምንባቸው የሚገቡና የእግዚአብሔርን ቃል ሊያረጋግጡለት የሚችሉ ምልክቶች ናቸው፤ በእነዚህ ሁሉ ምልክቶች ሳይረካ ቀርቶ እንደገና ሌላ ምልክት ሊያይ የሚወድ ቢኖር እርሱ ክፉና አመንዝራ ትውልድ ነው፡፡ ለዚህ ትውልድ ደግሞ ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ሌላ ምልክት አይሰጠውም፤ ነገር ግን ለእኛ እንደዮናስ የሚሆንልን ማን ነው? በእርሱስ ላይ የታየው ዋነኛ ምልክት ምንድር ነው?

«እነሆ ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ»

ኢየሱስ ለዚህ ክፉና አመንዝራ ትውልድ እንደ ዮናስ የሚታይ ብቻ ሳይሆን «ከዮናስ የሚበልጥ» መሆኑን ራሱ በማያወላውል ቃል ተናግሯል፤ ጌታ ኢየሱስ ከዮናስ የሚበልጥበትን መጠንም የሰው ልጅ በምንም ዓይነት መስፈሪያ /መለኪያ/ ሊናገረው አይችልም፤ ምክንያቱም በሥጋ ተገልጦ ለምልክት ፈላጊዎች መልስ እየሰጠ ያለው ኢየሱስ የነቢዩ የዮናስ ፈጣሪ ብሎም ዮናስን ወደነነዌ የላከው አምላክ እርሱ ነው፡፡ ፈጣሪ ከፍጡር፣ አምላክ ከነቢይ የሚበልጥበትን መጠን በምን መለካት ይቻላል? ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ ዮናስን ምን ያህል ይበልጠዋል? ተብሎ ቢጠየቅ እንዲያው ዝም ብሎ «ያለ ልክ» ይበልጠዋል ከማለት በቀር ሰው ሊናገረው የሚችለው ልክ የለውም፡፡

ለመሆኑ ከነቢዩ ዮናስ በሚበልጠው በጌታ በኢየሱስ ላይ የታየው ምልክት ምንድር ነው? የሚለው ደግሞ ቀጣዩ ጥያቄ ነው፡፡ በእርግጥ ከላይ እንደተጠቀሰው ጌታ ኢየሱስ እጅግ ብዙ ታላላቅ ምልክቶችን በሕዝብ ሁሉ ፊት አድርጓል፤ የታወሩ ዓይኖችን አብርቷል፤ ለምጻሞችን አንጽቷል፤ ሽባዎችን ተርትሯል፤ ሙታንን አስነሥቷል፤ ኅብስት አበርክቷል፤ በባሕር ላይ ሄዷል፤ ነፋሳትና ማዕበላትን ፀጥ አድርጓል.. .. ወዘተ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህን ሁሉ ምልክቶች ሲያደርግ እያዩና እየሰሙ አልረካ ብለው እንደገና ምልክትን ለማየት ለጠየቁት ሰዎች ኢየሱስ ይሰጣቸው የነበረው መልስ ከእነዚህ ዓይነት ምልክቶች አንዱን በመጥቀስ ሳይሆን ሞቱንና ትንሣኤውን ነበር፡፡ በዚሁ እየተነጋገርንበት ባለንው ንባብ ውስጥም ጌታችን ሲመልስ «ዮናስ በዓሣ አንባሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደነበረ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል» በማለት በግልጽ ተናግሯል /ማቴ12፡40/፡፡ የሰዎችን አለመታዘዝ /ኃጢአት/ ተሸክሞ በመስቀል ላይ ለመሞትና ወደ መቃብርም ገብቶ በምድር ልብ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ለመኖር የተገባው ጌታ ኢየሱስ እንደሞተ አልቀረም፤ ነገር ግን ሞትና መውጊያውን ሰብሮ፣ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን ዲያብሎስን በሞቱ ሽሮ በኃይልና በሥልጣን ሕያው ሆኖ ተነሥቷል፡፡ ስለሆነም ጌታ በዚህ ክፍል «ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ሌላ ምልክት አይሰጠውም» ብሎ ከተናገረ በኋላ በራሱ ላይ የሚሆነውን ይህንን በምድር ልብ ውስጥ ሦስት ቀን ሦስት ሌሊት የመኖሩን ምልክት መናገሩ ለክፉና ለአመንዝራ ትውልድ ከዚህ የጌታ ኢየሱስ የሞቱ እና የትንሣኤው ምልክት በቀር ሌላ ምልክት እንደማይሰጠው ያስረዳል፡፡

ከዚህ ታሪክ ቀደም ብሎ ጌታ ኢየሱስ ገና የምልክቶች መጀመሪያ እያደረገ በነበረ ጊዜ ስለምልክቶች ተጠይቆ የሰጠው መልስም ይህንኑ ዓይነት መልስ ነበር፡፡ ይህም የመጀመሪያውን የቤተመቅደስ የማጽዳት ሥራ በሠራበት ጊዜ ነበር፤ በቤተመቅደስ ውስጥ የነበሩትን በጎችና በሬዎችን በጅራፍ ካስወጣ በኋላ የገንዘብ ለዋጮችን ገንዘብ ሲያፈስ ገበታዎችንም ሲገለብጥ፣ ‹ርግቦቹንም ከዚህ ውሰዱ› ሲልና ‹የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት› ብሎ ሲናገር የሚያደርገውና የሚናገረው ሁሉ በሥልጣን እንደነበረ ያዩት አይሁድ «ይህን ስለምታደርግ ምን ምልክት ታሳየናለህ?» ብለው ጠይቀውት ነበር፡፡ ኢየሱስም የሰጠው መልስ ሲያደርጋቸው ከነበሩት ተአምራት /ምልክቶች/ አንዱን በመጥቀስ አልነበረም፤ ነገር ግን «ይህን ቤተመቅደስ አፍርሱት በሦስተኛውም ቀን አነሣዋለሁ» የሚል አስደናቂ መልስ ሰጣቸው፡፡ አይሁድ በፊደላዊ መንገድ በማሰብ «አፍርሱት» ያላቸው ቤተመቅደስ በጊዜው የነበረው የቤተመቅደስ ሕንፃ መስሏቸው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ጌታ ኢየሱስ ስለ ሰውነቱ «ቤተመቅደስ» ይል ነበር /ዮሐ.2፡21/፡፡ «በሦስት ቀን አነሣዋለሁ» ማለቱም ሞቶ በሦስተኛው ቀን እንደሚነሣ የሚያረጋግጥ ቃል ነበር /ቊ.22/፡፡

ስለዚህ በዘመናት ሁሉ ምልክት ለሚፈልጉ ሰዎች ጌታ ኢየሱስ የሰጠው ምልክት ሞቱና ትንሣኤውን ነው፡፡ በ4ቱ ወንጌላትና በመላው የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ሁሉ በግልጽ የተመዘገበውን የኢየሱስን የሞቱንና የትንሣኤውን ምልክት እያነበቡና ዘወትር ሲነገር እየሰሙ ነገር ግን ለሚያምኑት ነገር ምልክት ፍለጋ በየስፍራው የሚቅበዘበዙ ወገኖች ይህንን እውነት በእርጋታና በማስተዋል ሆነው ሊመለከቱት ይገባል፡፡ ለቶማስ የተነገረው ቃልም እንዲህ ላሉ ሰዎች ተጨማሪ ማስረጃ ሆኖ ሊረዳቸው ይችላል፤ ጌታ ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ለሐዋርያት ራሱን በገለጠበት በመጀመሪያው ቀን ቶማስ በሐዋርያት መካከል አልነበረም፤ ከስምንት ቀን በኋላ ግን ቶማስን ጨምሮ ሁሉም ሐዋርያት በዝግ ቤት ውስጥ ሳሉ ጌታ ኢየሱስ በድጋሚ ተገልጦ ለቶማስ ራሱን አሳየውና «ያመንክ እንጂ ያላመንክ አትሁን» ሲለው ቶማስ «ጌታዬ አምላኬም» ብሎ አመነ፡፡ ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ለሁላችንም የሚሆን ወሳኝና ጠቃሚ ቃል ተናገረው፤ ይህም ቃል «ስለ አየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው» የሚል ቃል ነው /ዮሐ.20፡26-29/፡፡

እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደፈቀደ በምልክትና በድንቅ ነገር በልዩ ልዩ ተአምራትም መንፈስ ቅዱስንም በማደል አብሮ የመሰከረለት /ዕብ.2፡4/ የጸና ቃል በዚህ ዘመን ለምንገኝ ሰዎችም ደርሷል፤ በመሆኑም ካላየሁ አላምንም በሚል የአለማመን ዝንባሌ እየተነሣሣን የእግዚአብሔርን ቃል የሚያጸኑልን ምልክቶች ፍለጋ ልንጠማና ወዲያ ወዲህ ልንል አይገባም፤ በሰው ፍላጎትም ላይ ተመሥርቶ የሚደረግ ምንም የጌታ ምልክት የለም፤ በፊትም ቢሆን ጌታ ምልክትን ያደርግ የነበረው እርሱ ራሱ እንደፈቀደ ነበር እንጂ /ዕብ.2፡4/ ሰዎች ለፈውስና ለሌሎች ምልክቶች ቀን ወስነው ፕሮግራም እያወጡለት አልነበረም፡፡ ስለሆነም እግዚአብሔር በልጁም ሆነ በሐዋርያት እጅ ያደረጋቸው ምልክቶች የጸናውን ቃል ለእኛ ትተውልን አልፈዋልና ምልክቶችን ለማየት ወዲያና ወዲህ ከመንከራተት ይልቅ በጸናው ቃል ላይ ማረፍና መመካት ተገቢ ነው፤ ጴጥሮስ የእርሱን ግርማ አይተው ከሰማይ የመጣውን ድምፅ በቅዱስ ተራራ ሰምተው የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ኃይልና መምጣት እንዳስታወቁ ከገለጠ በኋላ «ከእርሱም ይልቅ እጅግ የጸና የትንቢት ቃል አለን» ይላል /2ጴጥ.1፡19/፡፡ ይህም የጸናው የትንቢት ቃል ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው የተናገሩት ቃል ነው /ቊ.20-21/፡፡ ስለሆነም ምንም እንኳን ያየው የተራራው ምልክት እጅግ የከበረ ቢሆንም ቃሉ ከማናቸውም መንፈሳዊ ምልክት የሚበልጥ በመሆኑ ጴጥሮስ «ከእርሱም ይልቅ እጅግ የጸና የትንቢት ቃል አለን» ማለት ተገብቶታል፡፡ በመሆኑም ከጸናው የእግዚአብሔር ቃል ይልቅ ዛሬ ሰዎች እግዚአብሔር እንዲህ ብሎኛል እንዲያ ተናግሮኛል በሚሉት ከመወሰድ ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡ የጸና የእግዚአብሔር ቃልም በተሟላ ሁኔታ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦልን ስላለ እርሱን የጸናውን የትንቢት ቃል እንደገዛ ፈቃዳችን ሳይሆን እንደመንፈስ ፈቃድ በመካከላችን እየገለጥን ምክሩን ማወቅና ማመን ተገቢ ነው፡፡ በዚህ ፈንታ ግን ተአምራዊ በሆነ መንገድ የሚመጣ አዲስ የትንቢት ቃልና ምልክት ፍለጋ መንከራተት የቀደመውን የጸና ቃል መናቅ ከመሆኑም ባሻገር ካላየሁ በቀር የተጻፈልኝን አላምንም የማለት ያህል ተጠራጣሪነት ነው፡፡ ስለሆነም ምልክት ፍለጋ ወዲያና ወዲህ የሚንከራተቱ ሰዎች በጌታ በኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ላይ በማረፍ ሐዋርያው ጴጥሮስ «እርሱንም ሳታዩት ትወዱታላችሁ፤ አሁንም ምንም ባታዩት በእርሱ አምናችሁ የእምነታችሁን ፍጻሜ እርሱም የነፍሳችሁን መዳን እየተቀበላችሁ በማይነገርና ክብር በሞላበት ሐሤት ደስ ይላችኋል»/1ጴጥ.1፡8-9/ በማለት እንደ ተነናገረው በጸናው የትንቢት ቃል አምነው በእጅጉ ደስ እየተሰኙ እንዲኖሩ ይመከራሉ፡፡



አምላካዊ መልስ

«ለበኣል ያልሰገዱትን ሰባት ሺህ ሰዎች ለእኔ አስቀርቼአለሁ»

እግዚአብሔር ሁሉን የሚያውቅና ሁሉን የሚያይ አምላክ መሆኑ ለዘላለም እውነት ነው፤ የእርሱን እውቀት ማንም ሊደርስበት አይችልም፤ እርሱ ሐሳቡን እንዲገልጡ ሊጠቀምባቸው የመረጣቸው ሰዎች እንኳ እርሱ ካልገለጠላቸው በቀር የልቡን ሐሳብ ሊያውቁ አይችሉም፤ «የእግዚአብሔር ባለጠግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው፤ ፍርዱም እንዴት የማይመረመር ነው፤ በመንገዱም ፍለጋ የለውም፡፡ የጌታን ልብ ያወቀው ማነው? ወይስ ብድራቱን ይመልስ ዘንድ ለእርሱ አስቀድሞ የሰጠው ማነው? ሁሉ ከእርሱና በእርሱ ለእርሱም ነውና፤ ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን፡፡» /ሮሜ11፡33-36/

እግዚአብሔር ብቻ የሚያውቀውን፣ ሰው በራሱ ሊያውቀው የማይችለውን ነገር ያውቅ ዘንድ አምላካዊ መልስ የግድ ያስፈልገዋል፤ እስራኤል በከፍተኛ ውድቀት ውስጥ በነበረችበት በአክዓብ ዘመን ለበኣል አንሰግድም ብለው እግዚአብሔርን በማምለክ ብቻ የጸኑ ሰዎች መኖራቸውን ማወቅ በጊዜው ለነበረው የእግዚአብሔር ነቢይ ለኤልያስ እንኳ አልተቻለውም ነበር፤ ስለዚህ ይህን የሚገልጥ አምላካዊ መልስ አስፈለገው፤ ይህም አምላካዊ መልስ "ለበኣል ያልሰገዱትን ሰባት ሺህ ሰዎች ለእኔ አስቀርቼአለሁ» /ሮሜ.11፡4፤ 1ነገሥ.19፡18/  ነበር፡፡

ኤልያስ በግል ማንነቱ ብዙም ዝናኛ ያልነበረ ሰው ነው፡፡ በሰዎች ዘንድም የተከበረ አልነበረም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ኤልያስ በገለዓድ የነበረችው የቴስቢ ሰው እንደነበረ ይገልጻል /1ነገሥ.17፡1/፤ ቴስብያዊው ኤልያስ በዘመኑ ብዙም ታዋቂነት ባይኖረውም ለአምልኮተ እግዚአብሔር ቀናኢ ነበረ፡፡ ኤልያስ ለነቢይነት አገልግሎት የተጠራበት ዘመን በእስራኤል ምድር አምልኮተ እግዚአብሔር የተናቀበት፣ የእግዚአብሔር ስምና ክብር የተደፈረበት ዘመን ነበር፤ በአምልኮተ እግዚአብሔር ፈንታም አምልኮተ ጣኦት የነገሠበት፣ ልማደ አሕዛብ የተስፋፋበት ሁኔታ በእስራኤል ምድር ላይ ይታይ ነበር፡፡ የ10ሩ ነገድ መንግሥት በሆነው በእስራኤል መንግሥት ውስጥ የነገሡት አብዛኞቹ ነገሥታት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ በማድረግ የሚታወቁ ነበሩ፤ የብዙዎቹም ክፋት በእስራኤል መንግሥት /በ10ሩ ነገድ/ ውስጥ የመጀመሪያው ንጉሥ በነበረው በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓም ኃጢአት መሄዳቸው ነበር፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም 10ሩን ነገድ ከፍሎ በእነርሱ ላይ በነገሠ ጊዜ የግል ሥልጣኑንና ክብሩን ለማስጠበቅ ሲል እንዲሰገድላቸው ሁለት የወርቅ ጥጆችን አቁሞ «እስራኤል ሆይ ወደ ኢየሩሳሌም ትወጡ ዘንድ ይበዛባችኋል፤ ከግብፅ ምድር ያወጡህን አማልክትህን እይ» ብሎ ነበር፡፡ ይህም ሕዝቡ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ለመሠዋት ብሎ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድና ልቡም በይሁዳ መንግሥት እንዳይከፈል ለመከላከል የተጠቀመበት ዘዴ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአት ሆነ /1ነገሥ.12፡25-30/፡፡ ከእርሱ በኋላ የተነሡት ነገሥታትም በእርሱ የኃጢአት መንገድ እየሄዱ የእስራኤልን አምላክ ያስቈጡ ነበር /1ነገሥ.15፡25-26፣34፤ 16፡7፣19፣26/፡፡ ነገር ግን በኤልያስ ዘመን የነበረውና ሰባተኛው የእስራኤል ንጉሥ የሆነው አክዓብ የሠራው ክፋት ከሁሉም የሚበልጥ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ሲገልጥ «የዘንበሪም ልጅ አክዓብ ከእርሱ በፊት ከነበሩት ሁሉ ይልቅ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ፤ በናባጥም ልጅ በኢዮርብዓም ኃጢአት መሄድ ታናሽ ነገር መሰለው፤ የሲዶናውያንንም ንጉሥ የኤትበኣልን ልጅ ኤልዛቤልን አገባ፤ ሄዶም በኣልን አመለከ፤ ሰገደለትም፡፡ በሰማርያም በሠራው በበኣል ቤት ውስጥ ለበኣል መሠዊያ አቆመ፡፡ አክዓብም የማምለኪያ አፀድ ተከለ፤ አክዓብም ከእርሱ በፊት ከነበሩት ሁሉ ይልቅ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን የሚያስቈጣውን ነገር አበዛ» ይላል /1ነገሥ.16፡30-33/፡፡ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ያቆማቸውን ሁለት ጥጆች ማምለክና ማስመለክ ለአክዓብ ታናሽ ነገር ስለመሰለው በሲዶና አገር ይመለክ የነበረውን የበኣልን አምልኮ ወደ እስራኤል ምድር አስገባ፡፡ በዚህም የረከሰ አምልኮ የእስራኤልን ሕዝብ አሳተ /1ነገሥ.16፡18/፡፡ ሚስቱም ኤልዛቤል ይህን ክፉ ድርጊቱን እንዳይቃወሙበት በመፈለግ ስለ እግዚአብሔር ስምና ክብር የሚቈረቈሩ ነቢያተ እግዚአብሔርን ታስገድል ነበር /1ነገሥ.18፡4/፤ ለእርስዋም 450 የበኣል ነቢያትም ነበሯት /1ነገሥ.18፡19/፡፡

ባለንበት ዘመን ያለው  በስመ ክርስትና የሚጠራው ዓለም የሚገኝበት መንፈሳዊ ውድቀት ኤልያስ በነበረበት ዘመን ካለው የእስራኤል ሕዝብ መንፈሳዊ ውድቀት ጋር በእጅጉ ተመሣሣይነት አለው፡፡ እስራኤል እግዚአብሔርን በማምለክ ሲገባቸው የወርቅ ጥጆችን በማምለክ በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓም ኃጢአት እንደሳቱ ሁሉ ዛሬም በክርስትናው ዓለም በዚሁ መልክ አምልኮተ ጣኦት በተለያየ መንገድ የነገሠበት ዘመን ላይ እንገኛለን፡፡

ዓለማዊ ጠባይን በተላበሰው የክርስትና ዓለም የእግዚአብሔርን ሥራና ክብር የወሰዱ ወይም የሚጋሩ የተለያዩ የሐሳብ ጥጆች መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ የአክዓብ መንፈስ ደግሞ ይህም ታናሽ በደል ሆኖበት የኤልዛቤልን መንፈስ ማለትም አምልኮተ አሕዛብን ወደ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በማስገባት አሁንም በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ የቀደመው የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ይዘት ወደ ጐን ተትቶ በክርስትና ስም የሚጠራው ማኅበረሰብ በልማደ አሕዛብ ተጽዕኖ ሥር ወድቆ ስንመለከት ከልብ ልናዝን ይገባል፡፡ እንደ ኤልያስም በታላቅ መንፈሳዊ ቅንዓት ተነሣስተን ለእግዚአብሔር እውነት እና ለእግዚአብሔር አምልኮ ልንቆም ያስፈልጋል፡፡

«በኣል» የተባለው ጣኦት በሲዶናም ሆነ በአካባቢው ይመለክ የነበረ ጣዖት ነበር፡፡ እስራኤልም በየስፍራው ብዙ የበኣል ጣዖታትን /በኣሊምን/ በማቆም እግዚአብሔርን ቢያስቀኑትም በነቢዩ በኤልያስ በኩል በተነገረው የትንቢት ቃል መሠረት በኣል እግዚአብሔር የዘጋውን ሰማይ ሊከፍት የማይችል እንደሆነ ታወቀ፤ የእግዚአብሔር ነቢይ ኤልያስ ለእግዚአብሔር እጅግ በመቅናት «በፊቱ የቆምኩት የእስራኤል አምላክ ሕያው እግዚአብሔርን ከአፌ ቃል በቀር በእነዚህ ዓመታት ጠልና ዝናብ አይሆንም» ብሎ ለአክዓብ ተናገረው /1ነገሥ.17፡1/፡፡ ለ3 ዓመት ከ6 ወር ያህል ዝናብ ሳይዘንብ በመቅረቱ በእስራኤል ብቻ ሳይሆን ራሱ በኣል በኖረበት አገር በሲዶናም ጭምር ረሀብ ሆነ /ያዕ.5፡17፤ 1ነገሥ.17፡7-12/፤ ይህም ክስተት በተከተሉት ሁሉ ዘንድ በኣልን ከታላቅ ውርደት ላይ የጣለው የእግዚአብሔር ክንድ ነበር፡፡ ዛሬም በተለያዩ ምድራዊ ምክንያቶች እያታለለ የሕዝቡን ልብ የያዘው ክፉ መንፈስ የእግዚአብሔር ክንድ ሲገለጥበት በታላቅ ዕፍረትና መዋረድ እንደሚወገድ እርግጥ ነው፡፡

ኤልያስ የአክዓብንና የኤልዛቤልን ክፋት ፊት ለፊት መቃወሙ በዚህ ዘመን ላሉት የእግዚአብሔር ልጆች ታላቅ መልእክትን ይሰጣል፡፡ ኤልያስ በረሀቡ ዘመን ማብቂያ ላይ ለአክዓብ ተገለጠ፤ ከዚያም በኣልን ከሚያገለግሉት ነቢያትና ካህናት ጋር ፊት ለፊት ገጥሞ በእግዚአብሔር ጉልበት በመታመን ከተቃወማቸው በኋላ አሳፋሪ ሽንፈታቸው በሕዝብ ፊት እንዲገለጥ በማድረግ ኤልዛቤል ከባዕድ ምድር ያመጣችው አምልኮ በእስራኤል ፊት የተናቀ እንዲሆን አድርጓል /1ነገሥ.18፡16-40/፡፡ ይህ ኤልዛቤልን እጅግ ሊያስቆጣትና እርምጃም ለመውሰድ ሊያነሣሣት የሚችል ጉዳይ እንደሆነ ቢታወቅም ከእርሷ የንግሥትነት ሥልጣን ይልቅ በሁሉ ላይ በቅን የሚፈርደው የነገሥታት ንጉሥ እግዚአብሔር እርሱ ታላቅ አምላክ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

በዘመናችን በስመ ክርስትና በሚጠራው ዓለም ውስጥ የሰለጠነውን የኤልዛቤልን መንፈስ በእግዚአብሔር ጉልበት ፊት ለፊት እንቃወመው ዘንድ በኤልያስ ልብ ልንነሣሣ ይገባናል፤ የዘመናችን ዓለማዊት ቤተክርስቲያን በመካከሏ ካለው የኤልዛቤል መንፈስ ጋር ተስማምታ መኖርን ብትመርጥም እግዚአብሔር ግን ጉዳዩን በቸልታ የሚመለከተው አይደለም፡፡ የከበረው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለትያጥሮን ቤተክርስቲያን በተናገረው መልእክት ውስጥ «ሥራህንና ፍቅርህን እምነትህንም አገልግሎትህንም ትዕግሥትህንም ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው እንዲበዛ አውቃለሁ፡፡ ዳሩ ግን ነቢይ ነኝ የምትለውን ባሪያዎቼንም እንዲሴስኑና ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉ የምታስተምረውንና የምታስተውን ያቺን ሴት ኤልዛቤልን ስለምትተዋት የምነቅፍብህ ነገር አለኝ» ብሎ ሲናገር እንሰማዋለን /ራእ.2፡19-20/፡፡ በእርግጥ የዘመናችን ኤልዛቤል ሴሰኝነትንና አምልኮተ ጣዖትን በግልጥ ላትሰብክ ትችላለች፤ አማኞች ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያውቁበትና ወንጌልን የሚሰሙበት ብዙ ዕድል ስላለ በቀላሉ ሊስቱላት እንደማይችሉ ስለምታውቅ ልዩ የማታለል ባሕርይ መላበስን መርጣለች፡፡ አንዳንድ የክርስትና አመለካከቶችን የተላበሱ ሥርዓታትን ፈጥራ በክርስቶስ ፈንታ ታቆማለች፤ የጌታንም ስም ብትጠራ በጌታ ፈንታ የተካቻቸውን ሥርዓቶች የተቀደሱ ለማስመሰል እንጂ ጌታን ለማክበር አይደለም፡፡ ይህ የኤልዛቤል አገልግሎት ሕዝቡን በቀጥተኛ መንገድ ባይሆንም በተዘዋዋሪ መንገድ ወደሚፈጸም ባዕድ አምልኮ የሚመራ የክፋት አሠራር ነው፡፡ ስለዚህም እንደ ኤልያስ በቀናዒነት የሚያገለግሉ የወንጌል መልእክተኞች ኤልዛቤልን ቸል ሊሏት አይገባም፡፡ በቸልታ የሚያዩአት ከሆነ ግን የእግዚአብሔር ልጅ ጌታ ኢየሱስ እያንዳንዳቸውን «ኤልዛቤልን ስለምትተዋት የምነቅፍብህ ነገር አለኝ» ይላቸዋል፡፡

ኤልያስ ለሠራዊት አምላክ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቶ በእግዚአብሔር ጉልበት ባደረገው ተጋድሎ በበኣልና በነቢያቱ ላይ የተቀዳጀው ድል ኤልዛቤልን በእጅጉ አበሳጫት፣ ልትገድለውም በአማልክቷ ስም እየማለች ዛተችበት /ነገሥ.19፡2/፡፡ኤልያስ ለግድያ እንደሚፈለግ ባወቀ ጊዜ ፈርቶ ተሰደደ፡፡ በይሁዳ ከሚገኘው ከቤርሳቤህ በኋላ የአንድ ቀን መንገድ ሄዶ ከክትክታ ዛፍ በታች ተቀመጠና በእግዚአብሔር ፊት ተማረረ፤ በዚያም «ይበቃኛል፤ አሁንም አቤቱ እኔ ከአባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰድ ብሎ እንዲሞት ለመነ» /1ነገሥ.19፡4/፡፡

ለእግዚአብሔር አምልኮ በመቅናት በኤልያስ ስሜት ተነሣስተው የወንጌልን እውነት የሚገልጡ አገልጋዮች የኤልዛቤል መንፈስ ለሚያሰማቸው ዛቻ ጆሮ በሚሰጡ ጊዜ እንዲህ ያለ የስንፍና ቃልን ይናገራሉ፡፡ «ብዙ አገለገልኩ፣ ብዙ ተጋደልኩ ከእኔ የሚጠበቀውን አድርጌአለሁ፣ ግን መከራው ከአቅሜ በላይ ሆነ፤ አሁንስ በቃኝ ጌታ ሆይ ውሰደኝ» የሚሉ ቃላት ፊሪና ድንጉጥ ከሆነው ልባችን የሚወጡ የስንፍና ቃላት ናቸው፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት የሚኖር ቀናኢ አገልጋይ ግን «በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ ነገር ግን አይዟችሁ እኔ ዓለምን አሸነፌዋለሁ» የሚለውን የኢየሱስን ቃል ሁል ጊዜም ያስባል /ዮሐ.16፡33/፤ እግዚአብሔርም አገልጋዩ ሥጋ ለባሽ እንደሆነ ያወቃልና በመከራ የተሰቀቀችውን የባሪያውን ነፍስ ለማረጋጋት በጸጋ አሠራሩ አይለየውም፤ ስለሆነም እግዚአብሔር ኤልያስን በመልአኩ በኩል ጎብኝቶት ነበር፤ እጅግ ደክሞት ከተኛበት ስፍራ በመልአክ ተቀስቅሶ ምግብ እንዲበላ ተደረገ፤ በዚያም ምግብ እስከ እግዚአብሔር ተራራ ድረስ 40 ቀንና 40 ሌሊት ሄደ /1ነገሥ.19፡7-8/፤ በክርስትና ሕይወታችን በደከምንበት እና በጠወለግንበት ጊዜ ልዩ የሆነ የእግዚአብሔር መግቦት ያስፈልገናል፡፡ በእርግጥም እግዚአብሔር በፊቱ ለምንናገረው የስንፍና ንግግራችን አሳልፎ አይሰጠንም፡፡ ኤልያስ እንዲሞት ቢለምንም እግዚአብሔር ግን እንዲኖር መገበው፤ በተበሳጨን ቊጥር የምንጸልየውን ክፉ ጸሎት ሰምቶ አዎንታዊ መልስ የማይሰጥበት እግዚአብሔር ስሙ ቡሩክ ይሁን፡፡

ኤልያስ በእግዚአብሔር መግቦት ከበረታ በኋላ በእግዚአብሔር ተራራ /ደብረ ሲና/ ሥር ባለ ዋሻ ውስጥ እናገኘዋለን፡፡ በዚያም ሳለ «ኤልያስ ሆይ በዚህ ምን ታደርጋለህ?» የሚል የእግዚአብሔር ቃል መጣለት /ቊ.9/፤ በዚህ ጊዜ ነበር ኤልያስ እስራኤልን የሚከስ ቃል በእግዚአብሔር ፊት የተናገረው፤ እንዲህ በማለት፡ «ለሠራዊት አምላክ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቻለሁ፤ የእስራኤል ልጆች ቃል ኪዳንህን ትተዋልና፤ መሠዊያዎችህንም አፍርሰዋልና፤ ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋልና፤ እኔም ብቻዬን ቀርቻለሁ፤ ነፍሴንም ሊወስዱአት ይሻሉ»/ነገሥ.19፡10/፡፡ በሮሜ.11፡2 ላይ ይህ የኤልያስ ንግግር ክስ መሆኑ ተገልጧል፤ ምክንያቱም ይህ አባባሉ ከራሱ ይልቅ የሕዝቡን በደል የሚናገር በመሆኑ ነው፡፡

ሁልጊዜም ተስፋ በቈረጠና በሚነጫነጭ ስሜት ውስጥ ያለ ክርስቲያን ከራሱ ይልቅ የሌሎች በደል ይታየዋል፤ በእርግጥ በሰው ሚዛን ሲመዘን ወይም በሰው ዓይን ሲታይ ከእኛ በቀር ለእግዚአብሔር የሚገዛ ልብ ያለው በምድር ላይ ፈጽሞ የሌለ ሊመስለን ይችላል፡፡ ነገር ግን በስም ብቻ «ክርስቲያን» የሚባለውን ጨምሮ በምድር ላይ ያለው ሕዝብ በጥቅሉ የእግዚአብሔርን እውነትና የእግዚአብሔርን አምልኮ የሚጋፋ ነገር ሲያደርግ ብንመለከትም በእግዚአብሔር ዓይኖች ብቻ የሚታዩ ለስሙ የሚሆኑ ወገኖችም ሊኖሩ እንደሚችሉ ማሰብ ይገባናል፡፡ ኤልያስ ይህንን ይማር ዘንድ አምላካዊ መልስ መጣለት፡፡ ይህም አምላካዊ መልስ «... እኔም ከእስራኤል ጉልበታቸውን ለበኣል ያላንበረከኩትን ሁሉ፣ በአፋቸውም ያልሳሙትን ሁሉ፣ ሰባት ሺህ ሰዎች ለእኔ አስቀራለሁ» የሚል ነው /1ነገሥ.19፡18/፡፡ «እኔ ብቻ ቀርቻለሁ» በማለት ሲናገር ለነበረው ኤልያስ ይህ አምላካዊ መልስ በተናገረው ነገር የሚያጸጽት ብርቱ ቃል ሆኖለታል፡፡ «እኔ ብቻ» በማለት እኔነትን ለሚሰብኩና ለሚያወሩ ይህ አምላካዊ መልስ እንዴት ያለ ትምህርትን ይሰጣቸዋል!

በስመ ክርስትና የሚጠራው ዓለም በጥቅሉ በታላቅ መንፈሳዊ ውድቀት ውስጥ ቢገኝም እግዚአብሔር ግን ከዚህ መሐል ለስሙ የሚሆን ወገንን ለራሱ ያስቀራል፡፡ በጢሞቴዎስ መልእክት እንደተጻፈው «ጌታ ለእርሱ የሆኑትን ያውቃል» /2ጢሞ.2፡19/፤ ወንጌል ለአይሁድም ለአሕዛብም እየተሰበከ በነበረበት በዘመነ ሐዋርያት የእግዚአብሔር ሕዝብ ተብሎ የሚታወቀው ከአይሁድም ከአሕዛብም በኢየሱስ ያመነ ሕዝብ ነበር፡፡ ይሁንና ከአይሁድ ካመኑት መካከል ብዙዎቹ «የእግዚአብሔር ሕዝብ እኛ ብቻ ነን» ብለው ለወንጌል እውነት አልሸነፍ አሉ፤ ወደ ወንጌልም ከመጡ በኋላ ወደ ኋላ ያፈገፈጉ ነበሩ፡፡ ከዚህ በኋላ ሐዋርያት ወደ አሕዛብ ዘወር ብለው ወንጌልን ስለሰበኩ ቤተክርስቲያን በአሕዛብ መካከል መስፋፋት ቀጠለች፣ ይህ ሲባል ግን እግዚአብሔር እስራኤልን ሙሉ በሙሉ ትቷቸዋል ማለት አልነበረም፡፡ ይህንን ይረዱ ዘንድ በሮሜ ለሚገኙት ክርስቲያኖች ጳውሎስ መልእክትን ሲጽፍላቸው ለኤልያስ የተነገረውንና እግዚአብሔር ለራሱ የሚሆኑ ወገኖችን እንደሚያስቀር የሚናገረውን አምላካዊ መልስ በማስረጃነት በመጥቀስ እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደማይጥል ካስረዳቸው በኋላ «እንደዚህም በአሁን ዘመን በጸጋ የተመረጡ ቅሬታዎች አሉ» ይላቸዋል /ሮሜ11፡5/፡፡ ዛሬ በዙሪያችን ያለው በስመ ክርስትና የሚጠራውን ዓለም ጨምሮ ዓለሙ ሁሉ በክፋት አሠራር ተይዞ ስንመለከት ታዲያ ከእኔ በቀር እግዚአብሔር ሌላ ምን ሰው አለው? ብለን በከንቱ እንዳንመጻደቅ ይህ ቃል በብርቱ ያሳስበናል፡፡

ጌታ ኢየሱስ ልብንና ኲላሊትን የሚመረምር ስለሆነ የእርሱ የሆኑትን ለይቶ ያውቃል /2ጢሞ.2፡19/፤ በትያጥሮን ቤተክርስቲያን ውስጥ በኤልዛቤል አምልኮ ያልሳቱ ቅሬታዎች እንደነበሩባት ያውቅ ነበር /ራእ.2፡23/፡፡ እንደዚሁም በዘመናችን በታላቅ መንፈሳዊ ውድቀት ውስጥ በሚገኙ አብያተክርስቲያናት ውስጥ ሕዝብን በምታስተው በኤልዛቤል አሠራር ያልተያዙ የዋሃን አማኞችን ጌታ ለራሱ እንደሚያስቀር ልንረዳ ይገባናል፡፡ እነዚህንም ከሚገኙበትና ባለማወቅ ከሚኖሩበት የማይታዘዝ ማኅበር ጌታ በጸጋው ለይቶ ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አንድ ቀን ያፈልሳቸዋል /ቈላ.1፡13፤ ዕብ.13፡13/፡፡

ኤልዛቤል ሲዶናዊት እንጂ እስራኤላዊት አልነበረችም፤ እስራኤላዊት አለመሆኗ ብቻ ሳይሆን የእስራኤልን አምላክ ሕያው እግዚአብሔርን የምታምንና የምታመልክ አልነበረችም፡፡ በተቃራኒው ግን የዚህን ሕያው አምላክ ክብሩንና አምልኮውን የሚዳፈር የረከሰ አምልኮ በእስራኤል ምድር ውስጥ እንዲሰለጥን ያደረገች ሴት ናት፡፡ ከንጉሡ ከአክዓብ ጀምሮ እስራኤልን ሁሉ አሳተች፤ የእግዚአብሔርን ነቢያት ሁሉ በሰይፍ አስገደለች፣ በመጨረሻም ለእግዚአብሔር አምልኮ እጅግ ቀንቶ የነበረውን ነቢዩ ኤልያስን ልታስገድል አሳደደችው፤ እግዚአብሔር ይህ ሁሉ ሲሆን እያንደንዱን የኤልዛቤልን የክፋት እርምጃ በትዕግሥት ይመለከት ነበር፡፡ ይሁንና ጊዜያቸውን ይጠብቃሉ እንጂ በእግዚአብሔር አምልኮ ላይ የተነሣሱ የክፋት አገልጋዮች እንዲህ በሥርዓተ አልበኝነትና በአረመኔያዊ ሥራቸው እንደሠለጠኑ አይቀጥሉም፤ ስለሆነም «በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ» ያለው ጌታ ኤልዛቤልን በፍርድ ሲበቀላት እንመለከታለን፡፡ ኤልዛቤል ክፋቷ እያደገ መጥቶ ጾም በማሳወጅ ኢይዝራኤላዊውን ናቡቴን አስገድላ ርስቱን አክዓብ እንዲወርስ ባደረገች ጊዜ /1ነገሥ.20፡1‐16/፣ እግዚአብሔር በባሪያው በኤልያስ በኩል «በኢይዝራኤል ቅጥር አጠገብ ኤልዛቤልን ውሾች ይበሉአታል» ብሎ ተናግሮ ነበር /1ነገሥ.20፡23/፡፡ ይህም የእግዚአብሔር ፍርድ «ኢዩ» በአክዓብ ፈንታ በእስራኤል ንጉሥ በሆነ ጊዜ ተፈጽሟል፤ ኢዩ ኤልዛቤልን የገዛ ጃንደረቦቿ በመስኮት እንዲወረውሯት ካደረገ በኋላ ውሾች በሏት፤ ሊቀብሯትም በሄዱ ጊዜ ከአናትዋና ከእግርዋ ከመዳፍዋም በቀር ምንም አላገኙም /2ነገሥ.9፡30-36/፤ እግዚአብሔር በኤልያስ የተናገረው የፍርድ ቃልም በተግባር ተፈጸመ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ቀጥተኛ የወንጌል እውነት እንዳያምኑና እንዳይኖሩበት አቅጣጫ በማሳት የክርስቲያን ካባ ለብሶ ክፋትን የሚያገለግለውን የኤልዛቤልን መንፈስ እግዚአብሔር በፍርድ የሚበቀልበት ጊዜ ይመጣል፤ እግዚአብሔር በኤልዛቤል ብቻ ላይ ሳይሆን ከእርስዋ ጋር አብረው በእግዚአብሔር ላይ ባመፁት ሁሉ ላይ ይፈርዳል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ለትያጥሮን ቤተክርስቲያን ይህንን የፍርድ ቃል ሲናገር «...ንስሐ እንድትገባ ጊዜ ሰጠኋት፤ ከዝሙትዋ ንስሐ እንድትገባ አልወደደችም፡፡ እነሆ በአልጋ ላይ እጥላታለሁ፤ ከእርስዋ ጋር የሚያመነዝሩትንም ከሥራዋ ንስሐ ባይገቡ በታላቅ መከራ እጥላቸዋለሁ ልጆችዋንም በሞት እገድላቸዋለሁ» ብሏል /ራእ.2፡21-23/፡፡

ኤልዛቤል ሲዶናዊት እንጂ እስራኤላዊት አልነበረችም፤ እስራኤላዊት አለመሆኗ ብቻ ሳይሆን የእስራኤልን አምላክ ሕያው እግዚአብሔርን የምታምንና የምታመልክ አልነበረችም፡፡ በተቃራኒው ግን የዚህን ሕያው አምላክ ክብሩንና አምልኮውን የሚዳፈር የረከሰ አምልኮ በእስራኤል ምድር ውስጥ እንዲሰለጥን ያደረገች ሴት ናት፡፡ ከንጉሡ ከአክዓብ ጀምሮ እስራኤልን ሁሉ አሳተች፤ የእግዚአብሔርን ነቢያት ሁሉ በሰይፍ አስገደለች፣ በመጨረሻም ለእግዚአብሔር አምልኮ እጅግ ቀንቶ የነበረውን ነቢዩ ኤልያስን ልታስገድል አሳደደችው፤ እግዚአብሔር ይህ ሁሉ ሲሆን እያንደንዱን የኤልዛቤልን የክፋት እርምጃ በትዕግሥት ይመለከት ነበር፡፡ ይሁንና ጊዜያቸውን ይጠብቃሉ እንጂ በእግዚአብሔር አምልኮ ላይ የተነሣሱ የክፋት አገልጋዮች እንዲህ በሥርዓተ አልበኝነትና በአረመኔያዊ ሥራቸው እንደሠለጠኑ አይቀጥሉም፤ ስለሆነም «በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ» ያለው ጌታ ኤልዛቤልን በፍርድ ሲበቀላት እንመለከታለን፡፡ ኤልዛቤል ክፋቷ እያደገ መጥቶ ጾም በማሳወጅ ኢይዝራኤላዊውን ናቡቴን አስገድላ ርስቱን አክዓብ እንዲወርስ ባደረገች ጊዜ /1ነገሥ.20፡1‐16/፣ እግዚአብሔር በባሪያው በኤልያስ በኩል «በኢይዝራኤል ቅጥር አጠገብ ኤልዛቤልን ውሾች ይበሉአታል» ብሎ ተናግሮ ነበር /1ነገሥ.20፡23/፡፡ ይህም የእግዚአብሔር ፍርድ «ኢዩ» በአክዓብ ፈንታ በእስራኤል ንጉሥ በሆነ ጊዜ ተፈጽሟል፤ ኢዩ ኤልዛቤልን የገዛ ጃንደረቦቿ በመስኮት እንዲወረውሯት ካደረገ በኋላ ውሾች በሏት፤ ሊቀብሯትም በሄዱ ጊዜ ከአናትዋና ከእግርዋ ከመዳፍዋም በቀር ምንም አላገኙም /2ነገሥ.9፡30-36/፤ እግዚአብሔር በኤልያስ የተናገረው የፍርድ ቃልም በተግባር ተፈጸመ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ቀጥተኛ የወንጌል እውነት እንዳያምኑና እንዳይኖሩበት አቅጣጫ በማሳት የክርስቲያን ካባ ለብሶ ክፋትን የሚያገለግለውን የኤልዛቤልን መንፈስ እግዚአብሔር በፍርድ የሚበቀልበት ጊዜ ይመጣል፤ እግዚአብሔር በኤልዛቤል ብቻ ላይ ሳይሆን ከእርስዋ ጋር አብረው በእግዚአብሔር ላይ ባመፁት ሁሉ ላይ ይፈርዳል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ለትያጥሮን ቤተክርስቲያን ይህንን የፍርድ ቃል ሲናገር «...ንስሐ እንድትገባ ጊዜ ሰጠኋት፤ ከዝሙትዋ ንስሐ እንድትገባ አልወደደችም፡፡ እነሆ በአልጋ ላይ እጥላታለሁ፤ ከእርስዋ ጋር የሚያመነዝሩትንም ከሥራዋ ንስሐ ባይገቡ በታላቅ መከራ እጥላቸዋለሁ ልጆችዋንም በሞት እገድላቸዋለሁ» ብሏል /ራእ.2፡21-23/፡፡

በኤልዛቤል አሠራር ዙሪያ ያላችሁ ወገኖች ሆይ ይህን የከበረውን የእግዚአብሔርን ልጅ ቃል ስሙ፡፡ ከሚመጣውም አስፈሪ የእግዚአብሔር ፍርድ ትድኑ ዘንድ ዛሬ ነገ ሳትሉ አሁኑኑ ንስሐ ግቡ፡፡ ጌታ ኢየሱስንም እመኑትና ተከተሉት፤ እርግጥ ኤልዛቤል በብዙ ብልሃት እናንተን ለማታለል ትሞክራለች፤ ነገር ግን ንቁባትና ከእርስዋ ተለይታችሁ ከልብ ታምኑበት ዘንድ በንስሐ ወደ ኢየሱስ ኑ፡፡ «ከእርስዋ ጋር የሚያመነዝሩትን ከሥራዋ ንስሐ ባይገቡ በታላቅ መከራ እጥላቸዋለሁ ልጆችዋንም በሞት እገድላቸዋለሁ» ብሎ ጌታችን የተናገረው ሁሉ ሳይደርስባችሁ ለንስሐ ፍጠኑ/ራእ2፡22-23/፤ ያለማወቃችሁም ወራት አሁኑኑ ያብቃ፡፡ በነፍሳችሁም ትድናላችሁ፡፡

«እንግዲህ እግዚአብሔር ያለማወቅን ወራት አሳልፎ አሁን በየቦታቸው ንስሐ ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ ያዛል፤ ቀን ቀጥሮአልና፤ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው» /የሐ.ሥ.17፡30‐31/

 


Amharic Bible-|- The Holy Bible [King James Version]