አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስን በክርስቶስ ማወቅ
ክፍል 1 - የኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት
1) ኢየሱስ በሥጋ ከመገለጡ በፊት
ኢየሱስ የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ ከሴት ከመወለዱ/ገላ4፡4) በፊትም እንደነበረ የሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በግልጽ ይናገራሉ፡፡ዮሐ.1፡15፣27 “ዮሐንስ ስለእርሱ መሰከረ፤ እንዲህም ብሎ ጮኸ፤ ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ከእኔ በፊት ነበረና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኗል ስለእርሱ ያልሁት ይህ ነበረ፡፡”ዮሐ.8፡58 “ኢየሱስም እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ አላቸው”
ኢየሱስ ከመጥምቁ ዮሐንስም ሆነ ከአብርሃም በፊት እንደነበረ ብዙም ጥያቄ ላይነሳ ይችላል፤ ኢየሱስ ከመጥምቁ ዮሐንስና ከአብርሃም በፊት ብቻ ሳይሆን ዓለም ከመፈጠሩ በፊትም ነበረ፤ ነገር ግን ያኔ ዓለም ሳይፈጠር ኢየሱስ ራሱ አብ ነበረ? ወይስ ከአብ የተለየ የነበረ? የሚለው ጥያቄ ቃሉ የሚነግረንን እውነት እንመልከት፡፡
1) ዮሐ.17፡5 “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት፤ እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ በምድር ፈጽሜ አከበርሁህ፤ አሁንም አባት ሆይ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አንተ በራስህ ዘንድ አክብረኝ” በማለት ጌታ የጸለየው ጸሎት እርሱ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት በአብ ዘንድ “ክብር” የነበረውና በኋለኛው ዘመንም አብ ወደ ምድር የላከው ከአብ የተለየ አካል እንደሆነ በግልጽ ያሳያል፡፡ በዚሁ በዮሐ.17 በቊ.24 ላይም “አባት ሆይ ዓለም ሳይፈጠር ስለወደድኸኝ የሰጠኸኝን ክብሬን እንዲያዩ እኔ ባለሁበት የሰጠኸኝ እነርሱ ደግሞ ከእኔ ጋር ይሆኑ ዘንድ እወዳለሁ” ብሎ ጸልዮአል፡፡ በዚህ ጸሎት ውስጥም ዓለም ሳይፈጠር “የወደደው” እና “የተወደደው” ተለይተው ተነግረውናል፤ አባቱ ወደደው እርሱ ኢየሱስ/ወልድ) ተወደደ፡፡ በዮሐ.5፡20 ላይም “አብ ወልድን ይወዳልና የሚያደርገውን ሁሉ ያሳየዋል” ተብሎ የተነገረው ቃልም ይህንኑ ያጠናክራል፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ (ወልድ) ዓለም ከመፈጠሩ በፊት የአብ የፍቅሩ ማረፊያ ማለትም በአብ የሚወደድ ሌላ ማንነት እንጂ ራሱ አብ አልነበረም፡፡
2) ዮሐ.1፡1-2፣ 14 “በመጀመሪያው ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ፡፡ ይህም በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፡፡ ሁሉ በእርሱ ሆነ …. ቃልም ሥጋ ሆነ …”
የእግዚአብሔርን ቃል በመንፈስ ሆነው በጥንቃቄና በማስተዋል የሚያነቡ ሁሉ እውነትን አይስቷትም፤ እስኪ በዚህ ንባብ ውስጥ ያሉትን ቃላት በማስተዋል እንያቸው፤ “በመጀመሪያው ቃል ነበረ” - እዚህ ላይ “በመጀመሪያው” ተብሎ የተገለጸው “መጀመሪያ” በዘፍ.1፡1 ላይ “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” በሚለው ቃል ውስጥ ከተጠቀሰው መጀመሪያ ይቀድማል፤ ስለሆነም “በመጀመሪያው ቃል ነበረ” ሲል ሰማይና ምድር ከመፈጠራቸው በፊት ቃል ነበረ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም በቊ.2 ላይ “ሁሉ በእርሱ ሆነ” ስለሚል እርሱ (ቃል) ሁሉን ከመፍጠሩ በፊት ስለነበረ ነው፡፡ ታዲያ ጥያቄው “ቃል” ያኔ ማን ነበረ? የሚለው ነው፡፡ መልሱንም ቀጥሎ በተነገሩት ቃላት እናገኛለን፡፡ “ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ” - ይህ አገላለጽ “ቃል” በእግዚአብሔር ዘንድ የነበረ ሌላ ማንነት እንደነበረ በግልጽ ያሳያል፤ ሆኖም ይህ በእግዚአብሔር ዘንድ የነበረው ቃል ማን ነበረ? ለሚለው ጥያቄ ቀጥሎ ያለው ቃል መልስ ይሰጣል፡፡ “ቃልም እግዚአብሔር ነበረ” - ይህም በእግዚአብሔር ዘንድ የነበረው ቃል እርሱም እግዚአብሔር እንደነበረ የሚያሳይ ነው፡፡ ስለዚህ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ ሲል ኢየሱስ ዓለም ሳይፈጠር መልአክ ወይም ሰው ወይም ሌላ ነገር ሳይሆን እንደ አባቱ እርሱም እግዚአብሔር እንደነበረ የሚያስረዳ ነው፡፡ በቊጥር 2 ላይ “ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ” ይላል፡፡ – “ቃልም እግዚአብሔር ነበረ” ሲል ቃል አብ ነበረ ማለት እንዳልሆነ የሚያሳየው ከዚያው በመቀጠል ላይ በድጋሚ “ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ” ተብሎ የተነገረው ይህ ቃል ነው፤ ልብ በል፤ ይህ ቃል የተነገረው “ቃልም እግዚአብሔር ነበረ” ከተባለ በኋላ ነው፡፡ “ቃልም እግዚአብሔር ነበረ” ከተባለ በኋላ እንደገና “በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ” መባሉ የቃል እግዚአብሔር መሆን ከአብ የተለየውን የራሱን ማንነት እንደማያጠፋው በግልጽ ያሳያል፡፡
2) ኢየሱስ በሥጋ መገለጡ
በቊጥር 14 ላይ “ቃልም ሥጋ ሆነ” ይለናል፡፡ ይህም ሥጋ የሆነው ቃል ያ “በእግዚአብሔር ዘንድ” የነበረውና “እግዚአብሔር ነበረ” የተባለው እርሱ ነው እንጂ እግዚአብሔር አብ አይደለም፡፡ ይህንንም ቀጥሎ የተነገረው ቃል ግልጽ ያደርገዋል፤ “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ” ካለ በኋላ “አንድ ልጅ ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነውን ክብሩን አየን” ይለናል፡፡ ስለሆነም ኢየሱስ ከአባቱ ዘንድ የሆነ ክብር አለው፤ ይህም ቀደም ሲል እንዳየነው አባቱ ዓለም ሳይፈጠር በእርሱ ላይ ያኖረው ክብሩ ነው፤ ስለዚህ ክብሩ የተገኘበት “አባቱ” እና ክብሩ የታየበት “ኢየሱስ” ሁለት የተለያዩ ማንነቶች እንደሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በቊጥር 18 ላይ “በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው” ሲል አብ እና ወልድ አባትና ልጅ የሆኑ ሁለት ማንነቶች መሆናቸው በግልጽ ቋንቋ ተመልክቷል፡፡ ስለዚህ ሥጋ ከሆነም በኋላ በአብና በወልድ መካከል ግልጽ የእኔነት ልዩነት መኖሩ ስለተገለጸ ሥጋ የሆነው ቃል ወልድ ነው እንጂ አብ አይደለም፡፡ ቃል ሥጋ ሲሆን ሥጋውን ያመጣው ከየት ነው? ቀጣዩ ጥያቄ ይህ ሊሆን ይችላል፤ ለዚህ ጥያቄም የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ መልሶች በማስተዋል መመልከት ተገቢ ነው፡፡ ዘፍ.3፡15 - “በአንተና በሴቲቱ በዘርህና በዘርዋ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ” የእባቡን ራስ የሚቀጠቅጠው እርሱ የሴቲቱ ዘር መሆኑ በግልጽ ተነግሯል፡፡ ኢሳ.7፡14 - “እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች፡፡” የዚህን ትንቢት ፍጻሜ ማቴ.1፡22-23 ተመልከት፡፡ ማቴ.1፡1 - “የዳዊት ልጅ፣ የአብርሃም ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ትውልድ መጽሐፍ” ሉቃ.1፡35 - “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል፤ ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል” ገላ.3፡16 - “ለአብርሃምና ለዘሩም የተስፋው ቃል ተነገረ፡፡ ስለብዙዎች እንደሚነገር ለዘሮቹም አይልም፤ ስለአንድ እንደሚነገር ለዘርህም ይላል፤ እርሱም ክርስቶስ፡፡” ገላ.4፡4 - “ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ” 2ጢሞ.2:8 – “በወንጌል እንደምሰብከው፥ ከሙታን የተነሣውን፥ ከዳዊት ዘርም የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስብ” ዕብ.2፡14-18 - “እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፣ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፣ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፣ በሕይወታቸው ሁሉ ስለሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ነጻ እንዲያወጣ፣ በሥጋና በደም ተካፈለ፡፡ የአብርሃምን ዘር ይዟል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም፡፡” ዕብ.7፡14 - “ጌታችን ከይሁዳ ነገድ እንደወጣ የተገለጠ ነውና” ራእ.22፡16 - ራሱ ኢየሱስ ሲናገር “እኔ የዳዊት ሥርና ዘር ነኝ” አለ፤ ከሮሜ1፡4 ጋር አነጻጽር፡፡
እነዚህ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የሚገኙት ንባቦች ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሴት ማለትም ከድንግል ሴት እንደተወለደ፣ በተቈጠረለት ትውልድ መሠረት ከአዳም፣ ከአብርሃም ዘር፣ ከይሁዳ ነገድ፣ ከዳዊት ዘር፣ ከአንዲት ድንግል እንደተወለደ በማያሻማ ግልጽነት ይናገራሉ፤ በቅን ልብ ቃሉን ለማመን የፈለገ ማንም ሰው ይህንን እውነት በቀላሉ ይገነዘበዋል፡፡ ይሁንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሴት በመወለድ ሥጋ ሲሆን “ከኃጢአት በቀር” እንደ እኛ ሰው መሆኑን ሁልጊዜም በአጽንኦት ልታስታውስ ይገባል፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቃል ይህንን ሲናገር፡- “ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደእኛ የተፈተነ ነው እንጂ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀካህናት የለንም” ይላልና፡፡ (ዕብ.4፡15)
የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የሆነበት ምክንያት ስለሁላችን በመሞት መሥዋዕት ሆኖ ለመቅረብ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን የእንስሳት መሥዋዕት ይቀርቡ እንደነበር ይታወቃል፤ ሆኖም እግዚአብሔር ኃጢአትን ሊያስወግዱ ከቶ ባልቻሉት በእነዚያ መሥዋዕቶች ደስ ስላልተሰኘ ለመሢሑ ማለትም ለልጁ ሥጋን አዘጋጀለት፡፡ መሥዋዕት መሆን የሚችለው ሥጋ ሲሆን ነውና፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ይህንን ሲናገር እንዲህ ይላል፡- “መሥዋዕትንና ቊርባንን አልወደድህም፤ ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ፤ የሚቃጠለውንና ስለ ኃጢአት የሚቀርበውን መሥዋዕት አልሻህም፡፡ በዚያን ጊዜ አልሁ፤ እነሆ መጣሁ፤ ስለእኔ በመጽሐፍ ራስ ተጽፏል፤ አምላኬ ሆይ ፈቃድህን ላደርግ ወደድሁ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው፡፡” (መዝ.38(39)፡6-8 እና ዕብ.10፡5-11 ተመልከት)
ይህም ሥጋ የተዘጋጀለት ከሴት ማኅፀን ውጪ በሌላ ስፍራ ሳይሆን ከሴት ስለመወለዱ በተመለከትናቸው ንባቦች መሠረት በሴቲቱ ማኅፀን ውስጥ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ሴቲቱ የፀነሰችው በወንድ ዘር ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ አሠራር ነው (ማቴ.1፡18፤ ሉቃ.1፡35 ተመልከት) የሴቲቱ ዘር ብቻውን ወንድ ልጅ ሊሆን የሚችልበት የተፈጥሮ ሕግ ደግሞ የለም፡፡ ስለዚህ ይህን የሴቲቱን ዘር ኃጢአት ያልነካው ወንድ ልጅ እንዲሆን በማኅፀንዋ ውስጥ የማዘጋጀቱን ሥራ እግዚአብሔር ሠርቷል፡፡ መዳናችን ኃጢአትን ባላወቀው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ይፈጸም ዘንድ፣ ስለእኛም መልካም መዓዛ ያለው መሥዋዕት ሆኖ ይቀርብልን ዘንድ ለኢየሱስ ይህን ንጹሕና ቅዱስ ሥጋ በሴቲቱ ማኅፀን ውስጥ ያዘጋጀ እግዚአብሔር ስሙ ይባረክ፡፡
የተወደድህ አንባቢ ሆይ፡- ተነግሮ የማያልቀውን የክርስቶስን ማንነት መናገርም ሆነ መጻፍ እጅግ ደስ ይላል፤ ለመንፈስም እጅግ ይጣፍጣል፡፡ እስኪ በመሐል በቃሉ የተነገረውን አንድ ምክር ስማ፡፡ 1ዮሐ.4፡1-3 - “ወዳጆች ሆይ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፤ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደሆነ መርምሩ፤ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና፡፡ የእግዚአብሔርን መንፈስ በዚህ ታውቃላችሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደመጣ የሚታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደመጣ የማይታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፤ ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚው መንፈስ ነው፤ ይህም እንዲመጣ ሰምታችኋል፤ አሁንም እንኳ በዓለም አለ”፡፡ 2ዮሐ.ቊ.9 “ለሚወጣ ሁሉ በክርስቶስም ትምህርት ለማይኖር ሰው አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት ለሚኖር አብና ወልድ አሉት (በብዙ ቊጥር መነገሩን አስተውል)፤ ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ ይህንንም ትምህርት ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት፡፡”
ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደመጣ የማይታመን መንፈስ ያላቸውንና አብና ወልድ አባትና ልጅ መሆናቸውን ለይቶ ክርስቶስ ራሱ ያስተማረውን እውነት የማያመጡትን ሁሉ የእግዚአብሔር ቃል “አትቀበሉ” ይላል፡፡ እንዲህ ካሉት ጋር ባልንጀራ አትሁን፤ የእግዚአብሔር ቃል “አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል” ይላልና (1ቆሮ.15፡33)
ክፍል 2 - የኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የእርሱ ወደሆነው ዓለም ቢመጣም የገዛ ወገኖቹ አልተቀበሉትም ነበር (ዮሐ.1፡11) የእርሱን ማንነት በግልጽ የሚያሳዩ ሥራዎችን በመካከላቸው እየሠራ በግልጽ ሲያስተምር ቢሰሙም አላመኑትም ነበር፤ በአንድ ወቅት አይሁድ እርሱን ከበውት “እስከ መቼ በጥርጣሬ ታቆየናለህ? አንተ ክርስቶስ እንደሆንህ ገልጠህ ንገረን” ባሉት ጊዜ የመለሰላቸው መልስ “ነገርኋችሁ አታምኑምም እኔ በአባቴ ስም የማደርገው ሥራ ይህ ስለ እኔ ይመሰክራል እናንተ ግን እንደነገርኋችሁ ከበጎቼ ስላልሆናችሁ አታምኑም” የሚል ነበር (ዮሐ.10፡24-26) በጎቹን በተመለከተ ግን “በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል፤ እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፤ ለዘላለምም አይጠፉም ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም፡፡ የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፤ ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም፤ እኔና አብ አንድ ነን፡፡” ብሏል (ከቊ.27-30) እኛ በኢየሱስ ክርስቶስ ያመንንና እርሱን የተቀበልን ሁላችን የእርሱን ድምፅ የምንሰማና የምንከተለው በጎቹ ነን፡፡ ስለዚህ ክርስቶስ በጎቹ ካልሆኑት ከአይሁድ ተለይቶ በሥራውና በቃሉ ስለራሱና ስለአባቱ ማንነት ያስተማረውን ሁሉ መቀበላችን የዘላለም ሕይወት ያስገኘልንና በአብና በወልድ እጅ እንድንያዝ ያደረገ ነው፡፡
ኢየሱስ ማን ነው? በዚሁ ክፍል ውስጥ ራሱ እንደተናገረው እርሱና አብ አንድ ናቸው እንጂ እርሱ ራሱ አብ አይደለም፡፡ “እኔና አብ አንድ ነን” አለ፤ እስኪ በእርጋታና በትኩረት ይነበብ፤ “እኔ” ያለው የራሱን ማንነት ነው፤ “ና” የምትለው ፊደል ደግሞ ሁለቱን ቃላት ያያያዘች አያያዥ ፊደል ናት፤ “አብ” ደግሞ የአባቱ ማንነት ነው፡፡ “ነን” የሚለው ቃል ደግሞ ነጠላ ሳይሆን ብዙ ቊጥር ነው፡፡ ታዲያ ይህ ቃል ኢየሱስና አብ አንድ የሆኑት የየራሳቸውን ማንነት ሳይተዉ መሆኑን በግልጽ አያሳይምን?፡፡ አንድ መሆናቸው የአብን “አብ”ነት እና የወልድን “ወልድ”ነት የሚያጠፋ አይደለም፤ አብ ያው አብ ሆኖ እያለ፣ ወልድም ያው ወልድ ሆኖ እያለ ሁለቱ አንድ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው፡፡
እንዲሁም ጌታ ኢየሱስ በዮሐ.14 ውስጥ ስለራሱ፣ ስለአብና ስለመንፈስቅዱስ የተናገረውን ከራሱ አንደበት እስኪ እንስማ፡፡ በቅድሚያ በሁለቱ ደቀመዛሙርት በቶማስና በፊልጶስ ለቀረቡለት ጥያቄዎች የሰጣቸውን መልሶች እንመልከት፡፡ በቊጥር 5 ላይ ቶማስ “ጌታ ሆይ ወደምትሄድበት አናውቅም፤ እንዴትስ መንገዱን እናውቃለን?” ብሎ ጠየቀ፤ በዚህ ጥያቄ ውስጥ ቶማስ ያላወቃቸው ነገሮች ኢየሱስ የሚሄደው ወዴት እንደሆነና መንገዱንስ እንዴት ማወቅ እንደሚቻል ነው፡፡ ለሁለቱም ጥያቄዎቹ ጌታ የሰጠው መልስ በቊጥር 6 ላይ ይገኛል፤ “መንገዱን እንዴት እናውቃለን” ለሚለው የቶማስ ጥያቄ “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ” የሚል መልስ ሲሰጥ “ወደምትሄድበት አናውቅም” ላለው ደግሞ “በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” በማለት መልስ ሰጥቷል፤ በቊ.13ም ላይ “እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና” ስላለ የሚሄደው ወደ አብ ነው፤ ሰዎች ወደ አብ የሚመጡት በእርሱ በኩል ወይም በእርሱ መንገድነት ብቻ እንደሆነ ተናገረ፡፡ እዚህ ላይ “በእኔ በቀር” በማለት ራሱን “እኔ” ብሎ፣ “ወደ አብ” በማለት ደግሞ አባቱን “አብ” ብሎ ለይቶ መናገሩን ልብ ማለት ያስፈልጋል፤ እዚህ ላይ እጅግ ደስ የሚለው በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም ሲል እርሱ ሰዎችን የሚጠራው አብ ባለበት በዚያ ሆኖ እንደሆነ ማስተዋል ነው፡፡ በእርሱ መንገድነት ተጉዘን ወደ አብ ስንመጣ ኢየሱስን አብ ሆኖ ሳይሆን በራሱ አካል በዚያ በአብ ዘንድ እናገኘዋለን፡፡ በቊጥር. 7 ላይ ደግሞ “እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁት ነበር፡፡ ከአሁንም ጀምራችሁ ታውቁታላችሁ አይታችሁትማል” በማለት ይናገራል፡፡ በዚህ ቃልም “እኔንስ ብታውቁኝ” ብሎ የራሱን ማንነት፣ “አባቴን ደግሞ” ብሎ የአባቱን ማንነት ለይቶ ገልጿል፡፡ እዚህ ላይ “አባቴን ደግሞ” ያለውን ልብ ማለት ይገባል፤ “ደግሞ” ሲል የአባቱ ማንነት ሌላ መሆኑን ያሳያል፤ ኢየሱስን ያወቀ አባቱንም ደግሞ እንደሚያውቅ የተሰጠ ማረጋገጫ ነው እንጂ ራሱ ኢየሱስ አብ ነው ማለት አይደለም፤ ከአሁን ጀምራችሁ ታውቁታላችሁ አይታችሁትማል ብሎ ስለአብ ሲናገርም አብን ሌላ አድርጎ መሆኑን እናስተውል፤ ምክንያቱም “ታውቁኛላችሁ” ሳይሆን “ታውቁታላችሁ”፣ “አይታችሁኛል” ሳይሆን “አይታችሁታል” ብሏልና፡፡
በቊጥር 8 ላይ ደግሞ ፊልጶስ “ጌታ ሆይ አብን አሳየንና ይበቃናል” ብሎ ለኢየሱስ የተናገረውን ቃል እናያለን፡፡ ኢየሱስ ለዚህ ጥያቄ የሰጠው መልስ “አንተ ፊልጶስ ይህን ያህል ዘመን ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቷል፤ እንዴትስ አንተ አብን አሳየን ትላለህ? እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? እኔ የምናገረውን ቃል ከራሴ አልናገረውም ነገር ግን በእኔ የሚኖረው አብ እርሱ ሥራውን ይሠራል፡፡ እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ፤ ባይሆንስ ስለራሱ ስለሥራው እመኑኝ፡፡” የሚል ነበር (ቊ.9-10)፡፡ በዚህም ቃል ውስጥ ኢየሱስ እርሱንና አባቱን ለይቶ ሲያስቀምጥ ራሱን “እኔ”፣ አባቱን “አብ” ብሎ እየጠራ ተናግሯል፡፡ ሆኖም እርሱና አብ አንድ በመሆናቸው ምክንያት እርሱን ማወቅ አብን ማወቅ ነው፤ እርሱን ማየትም አብን ማየት ነው፡፡ አብን ለብቻው ማወቅና ማየት ሳያስፈልግ ኢየሱስን በማወቅና በማየት ብቻ አብን ማወቅም ማየትም ይቻላል፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ፊልጶስ ስለአብ ጠይቆት እያለ እርሱ ሲመልስለት “ይህን ያህል ዘመን ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን?” አለው፡፡ ለዚህም ከሰጣቸው ምክንያቶች አንዱ “እኔን ያየ አብን አይቷል” የሚል ነው፤ ይህም አብና ኢየሱስ አንድ ስለሆኑ በሥጋ የታየውን ኢየሱስን ማየት በሥጋ ያልታየውን ሌላውን ማለትም አብን ማየት ማለት ስለሆነ ነው እንጂ ራሱ ኢየሱስ አብ ስለሆነ አይደለም፡፡ ሌላው ምክንያት ደግሞ ኢየሱስ በአብ፣ አብም በኢየሱስ የመኖራቸው እውነታ ነው፡፡ ይህም ኢየሱስ በሚናገረው ቃል እና በሚሠራው ሥራ ይገለጣል፤ ጌታ ይህን ሲገልጥ “እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን?” ካለ በኋላ “እኔ የምነግራችሁን ቃል ከራሴ አልናገርም፤ ነገር ግን በእኔ የሚኖረው አብ እርሱ ሥራውን ይሠራል” ሲል እንሰማዋለን፡፡ ስለዚህ አብ “በኢየሱስ” ሆኖ መናገሩና መሥራቱ ሁለቱም አንዳቸው በአንዳቸው ዘንድ መኖራቸውን ያሳያል፤ ሆኖም ይህ ሲሆን ሁለቱም በየራሳቸው እኔነት ያሉ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ነው፤ በዚህ ክፍል ጌታ ኢየሱስ አብን “እርሱ” ብሎ እንደጠራው ልብ ማለት ይገባል፤ ራሱ ኢየሱስ አብ ቢሆን ኖሮ አየሱስ ስለአብ ሲናገርን “እርሱ ሥራውን ይሠራል” እንዴት ሊል ይችላል? ነገር ግን የየራሳቸው እነኔነት ያላቸው አብና ወልድ አንዱ በሌላው ዘንድ የሚኖሩ በመሆናቸው ኢየሱስን ማየት ማለት ያልታየውን አብን ማየት ነው፡፡ ፊልጶስ የማይታየውን አብን በሚታይና በሚዳሰስ መልኩ ለማየት ፈልጎ ነበር፤ ኢየሱስ ደግሞ በሚታይ ሥጋ ቢገለጥም ያልታየው የአብ መለኮታዊ ባሕርይ እርሱም አለው፤ በቈላስ.2፡9 ላይ “በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና” ተብሎ የተነገረው ቃል ይህን ያረጋግጣል፡፡ ጌታ “እኔን ያየ” ሲልም ከሰውነቱ አልፎ መለኮታዊ ማንነቱን በእምነት ዓይኖች ያየ ማለት ነው፤ በሥጋውማ ፊልጶስም ሆነ ሌሎቹ ደቀመዛሙርት እንዲሁም ማንኛውም ሰው እያየው ነበር፤ ያላዩት ነገር በእርሱ ያለውን የመለኮት ሙላት ነበር፤ ይህን በእምነት የሚያይ አብንም ያያል፤ ስለሆነም ከሚታየው የኢየሱስ ሥጋ ባሻገር የኢየሱስን መለኮታዊ ማንነት ማየት የማይታየውን አብን ማየት ነው፡፡
በመቀጠል ደግሞ በዚሁ በዮሐ.14 ውስጥ ከቊ15-17 ያለውን ጌታ የተናገረውን ቃል እንመልከት፤ እንዲህ ይላል፤ “ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ፡፡ እኔም አብን እለምናለሁ፤ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል”፡፡ በዚህ ቃል ውስጥ ኢየሱስ “እኔ”፣ “አብ” እና “ሌላ አጽናኝ” በማለት የተናገራቸውን ሦስት ቃላት ልብ ማለት ይገባል፤ እነዚህም ቃላት የሚያመለክቱት አንድ መለኮት የሆኑትን ሦስት አካላትን እንጂ ከሰው ወይም ከመላእክት ወገን የሆኑ አካላትን አይደለም፡፡ ጌታ ኢየሱስ እኔ አብን “እለምናለሁ” ሲል ልመናውን የሚለምነው ከዚያ ጊዜ ወደፊት ሆኖ መንፈስ ቅዱስን ከመላኩ በፊት እንደነበረ እንረዳለን፤ በቊጥር 13 ላይ “ወደ አብ እሄዳለሁና” ብሎ መናገሩን አንርሳ፤ ወደ አብ ከሄደ በኋላ አብን ይለምናል፤ አብ ደግሞ ሌላ አጽናኝ ምድር ላይ ላሉት የጌታ ደቀመዛሙርት ይሰጣቸዋል፡፡ ይህ ሌላ አጽናኝ ማን እንደሆነ ሲነግረን በቊጥር 17 ላይ “እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውስጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ” በማለት ይገልጻል፡፡ ስለሆነም ያ ሌላ አጽናኝ የእውነት መንፈስ የተባለው መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ይህ የእውነት መንፈስ/መንፈስ ቅዱስ) “ሌላ” መባሉን እናስተውል፤ ከአብም ከወልድም ሌላ የሆነ አጽናኝ ነው፤ ጌታ ኢየሱስ ወደ አብ እሄዳለሁ ባላቸው ጊዜ የታወከውን ልባቸውን የሚያጽናና በእርግጥም እርሱ ነበረ፡፡ ይህም የእውነት መንፈስ አንድ ነገር ወይም እምቅ ኃይል ሳይሆን “ሌላ አጽናኝ” የተባለ ማንነት ነው፤ “እርሱ” ተብሎም የተጠራ የራሱ እኔነት ያለው አጽናኝ ነው፡፡ በቊጥር 23 ላይ ደግሞ ኢየሱስ እርሱን ለሚወዱና ቃሉን ለሚጠብቁ በተናገረው የተስፋ ቃል ውስጥ አብና ወልድ በየራሳቸው እኔነት እንዴት እንደተገለጡ እንመልከት፤ ኢየሱስ እንዲህ አለ “የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል፤ ወደ እርሱም እንመጣለን፤ በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን” (ዮሐ.14፡23) የተወደድክ አንባቢ ሆይ፡- ጌታን ትወደዋለህን? ቃሉንስ ትጠብቃለህን? መልስህ “አዎን” እንደሚሆን ይታሰባል፤ እንደዚያ ከሆነ ደግሞ ወደ አንተ ለመኖር የሚመጡት አብና ወልድ ናቸው፤ “ወደ እርሱ እንመጣለን፤ በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን” ብሎ በብዙ ቁጥር ጌታ መናገሩን አትርሳ፤ አለመርሳትም ብቻ ሳይሆን ከልብህ እመነው፡፡ ያን ጊዜ የኢየሱስ ብቻ ወይም የአብ ብቻ ሳይሆን የኢየሱስም የአብም መኖሪያ ትሆናለህ፤ ደስ አይልም? ክብርና ምስጋና፣ ውዳሴና አምልኮ ለአብ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ ይሁን አሜን፡፡
ክፍል 3 - አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ
ባለፉት ሁለት ተከታታይ ክፍሎች በእግዚአብሔር ቃል የተገለጠውን የክርስቶስን ማንነት፣ በተለይም ከአባቱ ጋር ያለውን የአካል ልዩነትና የመለኮት አንድነት ትኲረት በመስጠት ተገልጾ ነበር፤ እንደዚሁም ከዓለም መፈጠር በፊት ከአብ በተለየ አካል ከአብ ጋር ለዘላለም የነበረው ቃል፣ የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ ሥጋ የሆነው እንዴት እንደሆነ የሚያሳዩትን የከበሩ እውነቶች ከቃሉ መዝገብ ውስጥ እያወጣን ተመልክተናል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር በየዘመናቱ ራሱን ለሰው እንዴት እንደገለጠ ሲናገር “ከጥንት ጀምሮ በብዙ ዓይነትና በብዙ ጐዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፣ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን” ይላል (ዕብ.1፡1)፤ ስለሆነም በዚህ በሦስተኛው ክፍል የሁሉ ፈጣሪ የሆነው አንዱ አምላክ ከመጀመሪያው ጀምሮ በተለያዩ መንገዶች የራሱን ማንነት እንዴት እንደገለጠና በኋላም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ በመጣ ጊዜ ይበልጡን እንዴት እንደገለጠው የሚያሳዩ እውነቶች ይቀርባሉ፡፡
በዘዳግ.6፡4-5 ላይ እግዚአብሔር “አንድ አምላክ” ስለመሆኑ ሲናገር “እስራኤል ሆይ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው፤ አንተም አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹምም ኃይልህ ውደድ” ይላል፡፡ እዚህ ላይ እግዚአብሔር አንድ እንደሆነ መነገሩ አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ሦስት መሆናቸውን እንዳንቀበል የሚያደርግ ነውን? በፍጹም አይደለም፤ በዚህ የእግዚአብሔር ቃል ክፍል የእግዚአብሔር ማንነት የተነጻጸረው አሕዛብ ከሚያመልኳቸው ብዙ አማልክት ጋር እንጂ ከራሱ ማንነት ማለትም ከአብ ከወልድና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አይደለም፡፡ በዚሁ ምዕራፍ ውስጥ ንባቡን ተከትለን ወረድ ብለህ ስናነብ ከቊጥር 12 ጀምሮ “… በዚያን ጊዜ፣ ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳ ተጠንቀቅ፡፡ አምላክህን እግዚአብሔርን ፍራ፤ እርሱንም አምልክ፤ በስሙም ማል፡፡ በመካከልህ ያለው አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነውና፤ የአምላክህ የእግዚአብሔር ቊጣ እንዳይነድድብህ ከምድርም ፊት እንዳያጠፋህ፣ በዙሪያችሁ ያሉት አሕዛብ የሚያመልኳቸውን ሌሎች አማልክትን አትከተሉ” ይላል፡፡ ስለሆነም በዚህ ውስጥ ያለው ዋና ሐሳብ አሕዛብ ከሚያመልኳቸው “ብዙ” አማልክት በተቃራኒ የእስራኤል አምላክ “አንድ” መሆኑን የሚያሳይ እንጂ የአብ የወልድና የመንፈስ ቅዱስን “ሦስትነት” የሚያጠፋ አይደለም፡፡
በዘፍ.3፡22 ላይ “እግዚአብሔር አምላክም አለ፣ እነሆ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ” ይላል፡፡ እስኪ በመንፈስ ሆነን አናስተውል፤ “እነሆ አዳም መልካሙንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ” የሚለውን ይህን ቃል የተናገረው ያው አንዱ እግዚአብሔር ነው፡፡ እዚህ ላይ እግዚአብሔር ራሱን “እኛ” ብሎ ይጠራል፡፡ “እኛ” የሚለው ከማን ጋር ሆኖ ነው? ከመላእክት ጋር ሊሆን አይችልም፤ እርሱ ከፍጡራን ጋር አይማከርምና፤ አዳምም ከመላእክት እንደ አንዱ አልሆነምና፡፡ ወይስ እኛ የሚለው እንደ ቀደሙት ነገሥታት ራሱን በክብር ለመጥራት ይሆን? እንዲህም ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ ይላልና፡፡ “እንደ አንዱ ሆነ” ካለ እኛ የሚሉት አካላት ከአንድ በላይ እንደሆኑ ያሳያልና፤ አንዱ የተባለው በሌሎች መካከል ያለ አንድ ማንነት (አካል) ነውና፡፡ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእነርሱ እንደ አንዱ መሆኑን ያመለክታል፡፡
ታዲያ እግዚአብሔር ራሱን “እኛ” ብሎ ሲጠራ “እኛ” ያለው እነማንን ነው? በብሉይ ኪዳን ውስጥ እንኳ ሳይቀር የዚህን ጥያቄ መልስ እናገኛለን፡፡ ለምሳሌ በመዝሙረ ዳዊት መጽሐፍ ውስጥ አብና ወልድ ሲነጋገሩ እንሰማቸዋለን፤ የሚከተሉት ንባቦች ይህንን ያሳያሉ፡፡ በመዝ.2፡7 - “እግዚአብሔር አለኝ፣ አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወለድሁህ” ይላል፤ ይህ ቃል በዕብ.1፡5 ላይ የኢየሱስን ታላቅነት ለማሳየት ተጠቅሷል፡፡ በመዝ.109(110)፡1-3 - “እግዚአብሔር ጌታዬን ጠላቶችህን ለእግርህ መቀመጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው፡፡ እግዚአብሔር የኃይልን በትር ከጽዮን ይልክልሃል፤ በጠላቶችህም መካከል ግዛ፡፡ ከአንተ ጋር ቀድሞ በኃይልህ ቀን፤ በቅዱሳን ብርሃን፤ ከአጥቢያ ኮከብ አስቀድሞ ከሆድ ወለድሁህ” ይላል፡፡ ይህም ቃል በአዲስ ኪዳን በተደጋጋሚ ተጠቅሷል (ማቴ.22፡43-45፤ የሐ.ሥ.2፡35፤ ዕብ.1፡13 ተመልከት)
እግዚአብሔር ልጁን “አንተ ልጄ ነህ” ሲለው አባትና ልጅ የተለያዩ አካላት መሆናቸውን አያሳይምን? እንዲሁም ዳዊት “እግዚአብሔር ጌታዬ … አለው” ሲል “እግዚአብሔር” እና “ጌታዬ” ብሎ የጠራቸው የተለያዩ አካላትን አይደለምን፡፡ በመዝ.44(45)፡6-7 ደግሞ “አምላክ ሆይ ዙፋንህ ለዘላለም ነው፤ የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ነው፤ ጽድቅን ወደድህ ዓመፅንም ጠላህ፤ ስለዚህ ከባልንጀሮችህ ይልቅ እግዚአብሔር አምላክህ የደስታን ዘይት ቀባህ” ይላል፡፡ ይህም ቃል የተነገረው “ስለ ልጁ” ማለት ስለ ወልድ መሆኑ በዕብ.1፡8-9 ላይ ተጠቅሷል፡፡ ስለዚህ በዚህ ቃል ውስጥ ወልድ “አምላክ ሆይ” ተብሎ መጠራቱን እናያለን፤ ከዚህም ሌላ “…እግዚአብሔር አምላክህ የደስታ ዘይትን ቀባህ” ተብሏል፤ ስለዚህ “አምላክ ሆይ” የተባለው ኢየሱስ (ወልድ) አምላክ ቢሆንም “እግዚአብሔር አምላክህ” ከተባለው ከሌላው አካል የተለየ መሆኑን በግልጽ እናያለን፡፡
ወደ አዲስ ኪዳን ስንመጣ ደግሞ በብዙ ስፍራዎች እግዚአብሔር “አንድ አምላክ” እንደሆነ በግልጽ ተነግሯል፤ የተወሰኑትን እንደሚከተለው እንመለከታለን፡፡
- 1ቆሮ.8፡4 - “እንግዲህ ለጣኦት የተሠዋውን ስለመብላት ጣኦት ሁሉ በዓለም ከንቱ እንደሆነ ከአንዱም በቀር ማንም አምላክ እንደሌለ እናውቃለን”
- ኤፌ.4፡6 - ላይ “ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ”
- 1ጢሞ.2፡5 - “አንድ እግዚአብሔር አለና … “
- ያዕ.2፡19 - “እግዚአብሔር አንድ እንደሆነ አንተ ታምናለህ፤ መልካም ታደርጋለህ …”
ስለሆነም እኛ ክርስቲያኖች የምናመልከው ይህንን አንድ እግዚአብሔር ወይም አንድ አምላክ ነው፤ ይህ አንዱ እግዚአብሔር ራሱ አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ነው ብሎ ማመን ሦስት አማልክትን ማምለክ አይደለም፡፡ አንዱ እግዚአብሔር አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ሆኖ በሦስትነት ያለና የሚኖር መሆኑን የሚክዱ ሰዎች “እኛ ሦስት አማልክትን አናመልክም” በማለት በአማኞች ላይ የሳይኮሎጂ ተጽዕኖ እያሳደሩ ከእውነት የማሳት ዘዴ እንደሚጠቀሙ ይታወቃል፤ ነገር ግን በዚህ የሰው ዘዴ መደናገር አይገባም፡፡ በአባባል ሳይሆን በተጻፈው እውነት ማመንና መጽናት ያስፈልጋል፡፡
የአብ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክነት
የሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ንባች የአብን የወልድንና የመንፈስ ቅዱስን አምላክነት የሚናገሩ ናቸው፡፡
- የአብ አምላክነት - “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” (ዮሐ.17፡3) “… ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን፤ ነገር ሁሉም በእርሱ በኩል የሆነ እኛም በእርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን” (1ቆሮ.8፡6) class="trinity"አምላክነት - “ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ መጣ፤ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው” (ሮሜ 9፡5) “የእግዚአብሔር ልጅ እንደመጣ እውነተኛ የሆነውን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደሰጠን እናውቃለን፤ እውነተኛም በሆነው በእርሱ አለን፤ እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው”፡፡ (1ዮሐ.5፡20/
- የመንፈስ ቅዱስ አምላክነት - “ጴጥሮስም ሐናንያ ሆይ መንፈስ ቅዱስን ታታልልና ከመሬቱ ሽያጭ ታስቀር ዘንድ ሰይጣን በልብህ ስለምን ሞላ … እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አልዋሸህም አለው” (የሐ.ሥ.5፡3-4/
እግዚአብሔር አንድ አምላክ መሆኑ እርሱ ራሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም አብ ወልድና መንፈስቅዱስ ሆኖ በሦስትነት ያለና የሚኖር መሆኑን የሚያጠፋ አይደለም፡፡ አብ፣ ወልድ እና መንፈስቅዱስ ሲቈጠሩ ሦስት መሆናቸውን ቊጥር መቊጠር የሚችል ማንም ቀና ሰው በቀላሉ ሊያውቀው የሚችል ነው፡፡ ይህ የሦስትነት እውነት በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ በግልጽ የሚታይ ነውና፡፡ እስኪ ጥቂት ክፍሎችን እንመልከት፡፡
- ማቴ.28፡19 - “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀመዛሙርት አድርጓቸው”
- ሉቃ.1፡35 - “መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት፤ መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፣ የልዑል ኃይል ይጸልልሻል፤ ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል”
- ሉቃ.3፡21-22 - “ሕዝቡም ከተጠመቁ በኋላ ኢየሱስ ደግሞ ተጠመቀ፡፡ ሲጸልይም ሰማይ ተከፈተ፤ መንፈስ ቅዱስም በአካል መልክ እንደ ርግብ በእርሱ ላይ ወረደ፤ የምወድህ ልጄ አንተ ነህ በአንተ ደስ ይለኛል የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ”
- ዮሐ.14፡15 - “እኔም አብን እለምናለሁ፤ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው”
- ዮሐ.14፡23-26 - “ኢየሱስም መለሰ እንዲህም አለው፤ የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል አባቴም ይወደዋል ወደእርሱም እንመጣለን፤ በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን፡፡ … ከእናንተ ዘንድ ስኖር ይህን ነግሬአችኋለሁ አብ በስሜ የሚልከው መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል፤ እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል”
- ዮሐ.15፡26 - “ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ እርሱ ስለእኔ ይመሰክራል”
- የሐ.ሥ.1፡4-5 - ኢየሱስ ሲናገር “ከእኔ የሰማችሁትን አብ የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቁ፤ ዮሐንስ በውኃ አጥምቆ ነበርና እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ”
- የሐ.ሥ.2፡32-33 - “ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሳው፤ ለዚህም ነገር እኛ ሁላችን ምስክሮች ነን፤ ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ብሎና የመንፈስቅዱስን የተስፋ ቃል ከአብ ተቀብሎ ይህን እናንተ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው”
- ኤፌ.1፡3-14 - ባለው ክፍል ቊ.3 ላይ “…የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ” ብሎ አብን፣ በቊ.6ና 7 ላይ “በውድ ልጁም …” ብሎ ወልድን፣ በቊ.13 ላይ ደግሞ “… በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ” ብሎ መንፈስ ቅዱስን በመጥቀስ ሦስቱንም ለይቶ ይገልጻል፡፡
- 1ጴጥ.1፡1 - “የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ጴጥሮስ እግዚአብሔር አብ አስቀድሞ እንዳወቃቸው፣ በመንፈስም እንደሚቀደሱ፣ ይታዘዙና በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ይረጩ ዘንድ ለተመረጡት …”
ውድ አንባቢ ሆይ እነዚህን ከላይ የተጠቀሱትን የአብ የወልድንና የመንፈስ ቅዱስን ሦስትነት የሚያሳዩ ንባቦችን በማስተዋል ደጋግመህ አንብብና ለኅሊናህ የቀረበውን እውነት ተቀበለው፤ ወደ ውስጥህ ከገቡ ሌሎች ሐሳቦች ጋር አታጠላልፈው፤ ቃሉ የሚነግርህን እንዳለ በእምነት ተቀበለው፤ ይህን ብታደርግ ልብህ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ሦስትነት ላይ ያርፋል፤ ለእነርሱ መኖሪያ ለመሆንም ራሱን ያዘጋጃል፤ ከዚያም በአንዱ አምላክ ዘንድ ያለውን ይህን ሦስትነት በማድነቅ፣ በአምልኮ መንፈስ ሆነህ በፊቱ ትደፋለህ፡፡ ጌታ ኢየሱስ ከመንፈስህ ጋር ይሁን፡፡