Aclesia  


2. የውኃ ጥምቀት

በዚህ ጽሑፍ የክርስቶስ ወንጌል ተመስክሮላቸው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑ ሰዎች የውኃ ጥምቀት ምን እንደሆነ እንዲያውቁና በውኃ መጠመቅ የሚያስፈልጋቸውም ለምን እንደሆነ ትክክለኛ ዓላማውን እንዲረዱ የሚያስችላቸውን እውነት ከቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ እናቀርባለን፤ አንዳንድ ጊዜ የውኃ ጥምቀት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተሰጠው ስፍራ ያለፈና የተጋነነ ስፍራ ሲሰጠው የሚታይ ሲሆን ሌላ ጊዜ ደግሞ ቃሉ የሚናገርለትን አስፈላጊነት ወደጐን በመተው ጥምቀትን ቸል ማለት ይታያል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ስለ ጥምቀት የሚናገሩ አንዳንድ የቅዱሳት መጻሕፍት ንባቦች ግልጽ ሳይሆንላቸው በቀሩ ሰዎች ዘንድ የተወሰነ መደነጋገር እንዳለም የታወቀ ነው፤ በመሆኑም የውኃ ጥምቀት ምንድነው? ዓላማውና አስፈላጊነቱስ ለምንድነው? ይህን በተመለከተ ያለው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትእዛዝና የሐዋርያት ትምህርት ምን ይመስላል? የሚሉትን ነጥቦች ቀጥሎ እንመለከታለን፡፡


2.1. የውኃ ጥምቀት ምንድነው? ያመነ የተጠመቀም ይድናል፤
ያላመነ ግን ይፈረድበታል»
/ማር.16፡16/፡፡

የውኃ ጥምቀት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት ከሌሎች የጥምቀት ዓይነቶች ማለትም ከመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት /ማቴ.3፡11፤ሉቃ.3፡16፤ የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፡፡ ሐ.ሥ.1፡5፤ 11፡16፤ 1ቆሮ.12፡13/፤ ከእሳት ጥምቀት /ማቴ.3፡11፤ሉቃ.3፡16፤ራእ.21፡8/ እንዲሁም ከመከራ ጥምቀት /ማቴ.20፡22/ ለይቶ ለማሳየት «የውኃ ጥምቀት» እየተባለ ይጠራል፡፡ ይህም ጥምቀቱ በውኃ የሚከናወን መሆኑን ያሳያል፡፡ የውኃ ጥምቀት ሙሉ ሰውነትን ወደ ውኃ ውስጥ ማስገባትን ወይም ወደ ውኃ ውስጥ መጥለቅን የሚያመለክት ነው፤ ስለሆነም የውኃ ጥምቀት ተጠማቂው ወደ ውኃ ውስጥ መግባቱን እንጂ ውኃው በተጠማቂው ላይ መፍሰሱን ወይም መረጨቱን የሚያሳይ አይደለም፡፡

ከክርስትና ጥምቀት በፊት የመጥምቁ ዮሐንስ ጥምቀት እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፤ መጥምቁ ዮሐንስ ሰዎችን ያጠምቅ የነበረው በዮርዳኖስ ወንዝ /ማቴ.3፡6/ እንዲሁም በሄኖን በነበረው ብዙ ውኃ /ዮሐ.3፡23/ ስለነበር ጥምቀቱ ይከናወን የነበረው ወደ ውኃ ውስጥ በመግባት እንደነበር እንገነዘባለን፤ ምክንያቱም ተጠማቂዎቹ ውኃው ወዳለበት ይመጡ ነበር እንጂ ውኃው ተቀድቶ ወደ እነርሱ አይወሰድም ነበርና፤ ጌታ ኢየሱስም ጽድቅን ለመፈጸም በዮርዳኖስ ወንዝ መጠመቁ ይህንኑ የሚያጸና ነው /ማቴ.3፡13/፤ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባም በፊልጶስ ስለመጠመቁ የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ «... ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃ ወረዱ አጠመቀውም፡፡ ከውኃውም ከወጡ በኋላ የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ነጠቀው ...» የሚል ነው /ሐ.ሥ.8፡38-39/ በዚህም ንባብ የክርስትና ጥምቀትን የምናይ ሲሆን በተለይ «ከውኃ ከወጡ በኋላ» የሚለው አገላለጽ ጥምቀቱ የተከናወነው ወደ ውኃው ውስጥ በመጥለቅ መኾኑን የሚያስረዳ ነው፡፡ የውኃ ጥምቀት የተሰበከው የእግዚአብሔር ቃል በተጠማቂዎቹ ዘንድ ተቀባይነት የማግኘቱ ምልክት ነው፡፡


2.2. የውኃ ጥምቀት የሚያስፈልገው ለመዳን አይደለም፣

«መዳን» የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደየዓረፍተ ነገሩ የሚተረጐም ቢሆንም በዚህ ክፍል ግን ከእግዚአብሔር ፍርድና ቊጣ ወይም ከዘላለም ሞት መዳንን በተመለከተ ያለውን ሐሳብ ይዘን ማንበብ እንዳለብን አስቀድሞ ማስታወስ እንወዳለን፤ የውኃ ጥምቀት ተጠማቂዎችን ከእግዚአብሔር ፍርድ ወይም ከሲኦል የማዳን ዓላማ የለውም፤ መዳን በጌታ በኢየሱስ ብቻ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል፣ /ሐ.ሥ.4፡12/ አዳኙ ኢየሱስ ሲሆን ሰዎች የሚድኑትም በዚህ አዳኝ በማመናቸው ነው እንጂ በውኃ በመጠመቃቸው አይደለም፡፡ መዳን የሚገኘው በእምነት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስረዳል፤ «በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና፤ በእርሱ በሚያምን አይፈርድበትም በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጁ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል /ዮሐ.3፡16-18/፤ «በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን አንተና ቤተሰዎችህም ትድናላችሁ» /ሐ.ሥ.16፡31/፤ «... ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነው» /ሮሜ.1፡16/፤ «... ነገር ግን ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንዲጸድቅ እንጂ በሕግ ሥራ እንዳይሆን አውቀን ...» /ገላ.2፡16/ «ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና» /ኤፌ.2፡8/ የሚሉትና የመሳሰሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንደሚድን የሚናገሩ ናቸው፡፡ ይህን መሠረታዊ እውነት አስረግጦ የያዘ ሰው ከማመን በኋላ የሚፈጸሙ ማናቸውም ሥርዓቶች ያድናሉ ሊል አይችልም፤ ይሁንና መዳን በእምነት ነው ለሚለው እውነት ቸልተኛ ከመሆን አንጻር በአንዳንዶች ዘንድ ጥምቀትም የሚያድን እንደሆነ ተደርጎ ትምህርት የሚሰጥበት ሁኔታ እንዳለ የታወቀ ነው፤ በዚህ የስህተት ትምህርት የተያዙና የሚደነጋገሩ ሰዎችን ወደ እውነት ይመጡ ዘንድ ለመርዳት በስህተት ትምህርቱ ውስጥ በተጣመመ መንገድ የሚጠቀሱ የቅዱሳት መጻሕፍት ንባቦችን እዚህ ላይ እንመለከታቸዋለን፡፡

• «ያመነ የተጠመቀም ይድናል፤ ያላመነ ግን ይፈረድበታል» /ማር.16፡16/

ከዚህ ንባብ ውስጥ «ለመዳን በመጀመሪያ ማመን ቀጥሎ መጠመቅ ያስፈልጋል፤ ጥምቀት ከሌለ ለመዳን ከሚያስፈልጉን ነገሮች አንዱ ስለጐደለ መዳን አይገኝም» የሚል አሳብን ማውጣት አይቻልም፡፡ «ያመነ የተጠመቀ ይድናል» ሲል አማኙ ያመነ ብቻ ሳይሆን ያን እምነቱን በጥምቀት የገለጠ ሰው መሆኑን ለማመልከት ነው፤ መጠመቅ በክርስቶስ የማመን ውጫዊ ምልክት ነው፤ አንድ ሰው በውኃ ሲጠመቅ በክርስቶስ ማመኑን ያረጋግጣል ይመሰክራል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የተሰበከለት የወንጌል እውነት አሳምኖት እያለ ተጠምቆ የክርስቶስ ተከታይ ለመሆን ያልታዘዘ ሰው አመነ ማለት አይቻልም፤ ማመን የወንጌል እውነት ትክክል እና አሳማኝ ስለሆነ ብቻ በመረታት ከልብ ሳይሆኑ መቀበል ሳይሆን በልብ ፈቃደኝነት ተስማምቶ በመቀበል ራስን በዚያ እምነት ለመግለጥና ለመቊጠር መታዘዝ ነው፡፡ በኢየሱስ ያመነ ሰው የሚጠመቀው ላመነው ወንጌል ራሱን መስጠቱን ለመግለጥ ነው፤ ስለዚህ ጥምቀት በልብ ውስጥ ላለው እምነት ውጫዊ መገለጫ ነው፤ ስለዚህ «ያመነ የተጠመቀም» ሲባል የዚህ ሰው እምነት በጥምቀት የተገለጠና የተረጋገጠ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ሰው «ይድናል»፤ ሆኖም ለመዳን ያበቃው በክርስቶስ ማመኑ ነው እንጂ መጠመቁ አይደለም፡፡ «ያመነ የተጠመቀም» ተብሎ መጠመቁ ከማመኑ ጋር አብሮ የተነገረበት ምክንያት ያ አማኝ በውኃ ጥምቀት የተገለጠና የተረጋገጠ እምነት ያለው እንደሆነ ለማስረዳት ነው እንጂ መጠመቁን ለመዳን የግድ የሚያስፈልግ ሥርዓት አድርጐ ለማሳየት አለመሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ የውኃ ጥምቀት ከፍርድ ለመዳን የግድ የሚያስፈልግ ሥርዓት መሆኑን ለመግለጽ ቢሆን ኖሮ ጌታ ኢየሱስ በመቀጠል ሲናገር «ያላመነ ግን ይፈረድበታል» ሳይሆን «ያላመነ ያልተጠመቀ ግን ይፈረድበታል» ሊል በተገባው ነበር፡፡ ነገር ግን ከፍርድ መዳንን በተመለከተ ዋናው ነገር ማመን እንጂ መጠመቅ ባለመሆኑ «ያላመነ ግን ይፈረድበታል» አለ፡፡ የውኃ ጥምቀት እውነተኛ እምነትን ተከትሎና ከእምነት ጋር ተያይዞ የሚመጣ ሥርዓት እንጂ ከፍርድ ለመዳን የሚያበቃ ዋነኛው ነገር አይደለም፡፡

• «ጴጥሮስም ንስሐ ግቡ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ...» /ሐ.ሥ.2፡38/

በዚህ ንባብ ውስጥ «የኃጢአት ሥርየት» የተያያዘው ከኢየሱስ ክርስቶስ ስም ጋር እንጂ ከውኃ ጥምቀት ጋር አይደለም፡፡ ይህን ባለመገንዘብ ጥምቀት ኃጢአትን ያስተሰርያል የሚል ሐሳብ ብዙዎችን ሲገዛ ማየት በእጅጉ አሳዛኝ ነው፡፡ ይሁንና ከንባቡ ውስጥ ይህ አሳብ አይገኝም፤ ጴጥሮስ የኃጢአት ሥርየትን ያያያዘው ከኢየሱስ ክርስቶስ ስም ጋር እንጂ ከጥምቀት ጋር አይደለም፡፡ «ኃጢአታችሁ ይሰረይ ዘንድ ተጠመቁ» አላለም፤ እንዲህ ቢሆን ኖሮ ጥምቀት ለኃጢአት ሥርየት እንደሚያበቃ የሚታሰብ ይሆን ነበር፤ ነገር ግን እንዲህ አላለም፤ «ኃጢአታችሁ ይሰረይ ዘንድ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ» በማለቱ ግን የኃጢአት ስርየቱ የሚገኘው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንጂ በጥምቀቱ እንዳልሆነ ያስረዳል፡፡ በሉቃ.24፡47 «በስሙም ንስሐና የኃጢአት ሥርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ ይሰበካል ተብሎ እንዲህ ተጽፎአል» የሚል ቃል ስናነብ በ1ዮሐ.2፡12 ላይ ደግሞ «ልጆች ሆይ ኃጢአታችሁ ስለ ስሙ ተሰርዮላችኋልና እጽፍላችኋለሁ» የሚል እናነባለን፤ ስለዚህ የኃጢአት ሥርየት የሚገኘው በክርስቶስ ኢየሱስ ስም ነው፡፡

የውኃ ጥምቀት በኢየሱስ ክርስቶስ ያመነ ሰው የሚፈጽመው ውጫዊ ሥርዓት ነው፡፡ እንዲህ ያለው አማኝ በውኃ ጥምቀት የሚገልጸው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ማመኑን ነው፡፡ ስለዚህ ዋናው ነገር ውጫዊ መግለጫ የሆነው ጥምቀት ሳይሆን በውስጡ ያለው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ማመኑ ነው፤ የኃጢአትን ሥርየት የሚሰጠው ይህ ያመነው የኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው፡፡ ስለዚህ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መጠመቅ ማለት በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምኖ መጠመቅ ማለት ነው፡፡ የመጥምቁ ዮሐንስ ጥምቀት የንስሐ ጥምቀት ነበር እንጂ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የሚከናወን ጥምቀት አልነበረም፡፡ ስለሆነም በሐ.ሥ.19፡3-5 በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መጠመቅ በዮሐንስ ጥምቀት ከመጠመቅ የተለየ ሆኖ ቀርቦልናል፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መጠመቅ ማለት ሌላ ምንም ማለት ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ የኢየሱስ ተከታይ ለመሆን መጠመቅ ማለት ነው፤ ይህ መጠመቅም ተጠማቂው ያመነውን እምነት የሚገልጥ ነው፡፡ የኃጢአት ስርየቱ የሚገኘው ግን በጥምቀቱ በተገለጠውና በተመሰከረው በኢየሱስ ስም ባለ እምነት እንጂ በውኃ ጥምቀቱ አይደለም፡፡

• «አሁንስ ለምን ትዘገያለህ? ተነሣና ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ፤ ከኃጢአትህም ታጠብ» /የሐዋ.ሥ.22፡16/

ይህ ቃል ሐናንያ የተባለው በጸሎት የተጋ ደቀመዝሙር ለጳውሎስ የተናገረው ቃል ነው፡፡ «ተነሣና ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ» ካለው በኋላ «ከኃጢአትህም ታጠብ» ሲለው ጳውሎስ በሚጠመቅ ጊዜ በሰዎች ዘንድ ከተቈጠረውና ከሚታወቀው ኃጢአቱ መታጠቡን የሚያመለክት ነው፡፡ ጳውሎስ ሳውል እየተባለ ይጠራ በነበረ ጊዜ ቤተክርስቲያንን ያፈርስና ያለ ልክ ያሳድድ ነበር፡፡/ሐ.ሥ. 8፡3፤ ገላ.1፡13/፤ ክርስቲያኖችን እያሰረ ወደ ወኅኒ ያስገባቸው ነበር፤ ይህንንም እስከ ውጭ አገር ከተማዎች ድረስ እየሄደ ያደርግ ነበር፤ በምኵራብም ክርስቲያኖችን እየቀጣ ጌታ ኢየሱስን ይሰድቡት ዘንድ ግድ ይላቸው ነበር፡፡ ወደ ደማስቆ ለዚሁ ጉዳይ በመሄድ ላይ ሳለ ጌታ ኢየሱስ ራሱ ተገልጦ ካናገረው በኋላ ግን ያሳድድ የነበረውን እምነት ተቀበለ፤ ይሁን እንጂ ሐናንያም ሆኑ ሌሎች ክርስቲያኖች የሚያውቁት በዚያው በቀደመ የኃጢአት ሥራው ነበር፤ ጌታ ሐናንያን በራእይ ስለ ሳውል ባናገረው ጊዜ «ጌታ ሆይ በኢየሩሳሌም በቅዱሳንህ ላይ ስንት ክፉ እንዳደረገ ስለዚህ ሰው ከብዙዎች ሰምቼአለሁ፤ በዚህም ስምህን የሚጠሩትን ሁሉ ለማሰር ከካህናት አለቆች ሥልጣን አለው፡፡» ብሎ የመለሰው ቃል ይህንኑ ያረጋግጣል /ሐ.ሥ.9፡13-14/፡፡ በተለይም «ከብዙዎች ሰምቼአለሁ» ሲል በብዙዎች ዘንድ ሳውል የሚታወቀው በክፉ ሥራው እንደነበረ ያሳያል፡፡ ይህን የቀደመ ሕይወቱን ራሱ ጳውሎስ ሲናገር «ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ» ብሏል /1ጢሞ.3፡15/፡፡ ታዲያ ምንም እንኳ ክርስቶስን ሲያምን በእግዚአብሔር ፊት ከዚህ ኃጢአቱ የታጠበ ቢሆንም በሰው ፊት ማለትም በብዙዎች አማኞች ፊት ገና አልታጠበም ነበር፡፡ ይሁንና ያሳድደው የነበረውን እምነት መቀበሉን በውኃ ጥምቀት ሲገልጥ መለወጡን ባላወቁና ባላመኑ ክርስቲያኖች ዘንድ ከኃጢአቱ ይታጠብ ስለ ነበር «ተነሣና ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ ከኃጢአትህም ታጠብ» ሊባል ቻለ፡፡ ስለዚህ ሰው በመጠመቅ ከኃጢአቱ የሚታጠበው በሰው ፊት እንጂ በእግዚአብሔር ፊት አይደለም፤ ሰው በእግዚአብሔር ዘንድ ከኃጢአቱ ታጥቦ የሚነጻው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ነው፡፡ በ1ዮሐ.17 ላይ «የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻል» ተብሎ የተጻፈው ቃል ይህን ያረጋግጣል፡፡ እግዚአብሔር አማኙን ከኃጢአቱ የታጠበ ሆኖ የሚያየው በውኃ ከተጠመቀ በኋላ አይደለም፤ ጥምቀት በሰው ዓይን የሚታይ ውጫዊ ሥርዓት ነው፤ እግዚአብሔር ግን ሊጠመቅ በተዘጋጀው በዚያ ሰው ውስጥ ያለውን ነገር ሁሉ ያያል፡፡ ስለዚህ ያ ሰው በእውነት ካመነ በእግዚአብሔር ዘንድ ከኃጢአቱ የሚታጠበው በዚያን ጊዜ ነው፡፡

•«ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፡፡» /1ጴጥ.3፡21/

ሐዋርያው ጴጥሮስ በዚህ ክፍል «ይህም ውኃ» ያለው በኖኅ ዘመን ኖኅና ቤተሰቡ ማለትም ስምንቱ ነፍሳት የዳኑበትን መርከብ ያንሳፈፈው ውኃ ነው፡፡ ከፍ ብሎ በቊ.20 ላይ እንደምናነበው ስምንቱ ነፍስ የዳኑበት መርከብ እነርሱን ያዳነው «በውኃ» ነው፡፡ «በውኃ የዳኑበት መርከብ» የሚለው ቃል የሚያሳየው ይህንን ነው፡፡ ውኃው በጊዜው በነበረው ያልታዘዘ ዓለም ላይ የወረደ የእግዚአሔር ፍርድ ነበር፡፡ ይህ ውኃ ያልታዘዘውንና ከመርከቡ ውጪ የሆነውን ዓለም ወደታች ሲያሰጥም የእግዚአብሔር የሆኑትን 8 ነፍሳት ግን ወደ ላይ በማንሳፈፍ ለመዳናቸው ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህ በምሳሌነት የሚያሳየንን እውነታ ስንመለከት የጥፋት ውኃው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በነበረ ጊዜ በእርሱ ላይ የወረደውን የእግዚአብሔርን ፍርድ ወይም ቊጣ ያሳያል፡፡ ይህም ፍርድ በኃጢአተኛው ዓለም ላይ የነበረው የእግዚአብሔር ፍርድ ነው፤ ጌታ ኢየሱስ በዚህ ስፍራ ሆኖ እስከምድር ታችኛ ክፍል /ኤፌ.4፡9/ ከወረደ በኋላ ከሙታን ተነሥቶ አሁን በእግዚአብሔር ቀኝ አለ፡፡ ውኃው መርከቡን ወደ ላይ በማንሳፈፉ እነዚያ ነፍሳት እንደዳኑ እኛም በዓለም ላይ ካለው የእግዚአብሔር ቊጣ የዳንነው ክርስቶስ ከሞት ተነሥቶ ወደላይ በመውጣቱ ነው፡፡ ክርስቶስ ስለበደላችን አልፎ ከተሰጠ በኋላ ከሙታን የተነሣው እኛን ስለማጽደቅ መኾኑ ተነግሮናል፤ /ሮሜ.4፡1/ ይህም ሁኔታ በምሳሌነት የሚገለጠው በውኃ ጥምቀት ነው፤ በክርስቶስ ያመነ ሰው በሚጠመቅ ጊዜ ወደ ውኃ ውስጥ ሲገባ ከክርስቶስ ሞት ጋር መተባበሩን ይገልጣል፤ ማለትም ተጠማቂው በኃጢአተኛው ዓለም ላይ ያለው ፍርድ በክርስቶስ ላይ በወረደ ጊዜ በእኔ ላይ የነበረው ፍርድ በእርሱ ላይ ተፈጽሟል በማለት ይመሰክራል «ከክርስቶስ ጋር ተሰቅያለሁ» የሚለው ቃል ትርጉሙም ይህ ነው፤ ከውኃው በሚወጣ ጊዜ ደግሞ ከክርስቶስ ጋር በትንሣኤው አንድ መሆኑን ይገልጣል፤ ይህም ደግሞ ከፍርድ የዳነና በአዲስ ሕይወት የሚመላለስ አዲስ ሰው መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ ሰው ወደዚህ ወዳዳነበት ስፍራ ያመጣው ግን የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነው እንጂ ጥምቀቱ አይደለም፡፡ «ይህም ውኃ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል» የሚለውን ይህን ክፍል የሚያነቡ ሁሉ ሊያስተውሉት የሚገባው ነገር ያድነናል የተባለው «ይህም ውኃ» የተባለው ነው እንጂ ጥምቀት አለመሆኑን ነው፤ ጥምቀት እዚህ ላይ «ምሳሌው ሆኖ» ተብሎ የተገለጠው ነው፤ ምሳሌነቱም ለውኃው ነው፤ ይህ ውኃ ደግሞ የኖኅ መርከብ 8ቱን ነፍሳት ያዳነበት ውኃ ነው፡፡ ታዲያ «ይህ ውኃ ያድነናል» ሲባል በጥምቀት በሚገልጸው መንፈሳዊ አሳብ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ቀጥሎ ያለውን ንባብ ስንመለከት «የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም፤ ለእግዚአብሔር የበጎ ኅሊና ልመና ነው እንጂ» የሚል እናነባለን፤ በውኃ «የሰውነትን እድፍ ማስወገድ» ውጫዊ የሆነ የሚታይ ፍጥረታዊ ክንውን ነው፤ «ለእግዚአብሔር የበጎ ኅሊና ልመና» ግን መንፈሳዊ ነገር ነው፤ በኖኅ ዘመን የነበረው መርከቡን ያንሳፈፈው ውኃ የሚያመለክተው ይህን ለእግዚአብሔር የሆነ የበጎ ኅሊና ነው፡፡ «በጎ ኅሊና» ማለት በጎ ነገር የተሞላ ኅሊና ማለት ነው፤ እዚህ ላይ የበጎ ኅሊና ልመና ሲል በውስጥ ካለው በበጎ ነገር ከተሞላው ኅሊና ወጥቶ የቀረበ ልመና ወይም ጥያቄ ማለት ነው፤ ይህም ለእግዚአብሔር የሚሆን ነው፤ ማለትም የሰሙትን የእግዚአብሔር ቃልና እውነት ከመቀበል የተነሣ ከበጎ ኅሊና ወጥቶ የቀረበ ጥያቄ ነው፤ ከቃሉና ከአሳቡ ጋር ተስማምቶ ለመኖር የቀረበ የበጎ ኅሊና ልመና ነው፡፡ በመቀጠልም ይህም «በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ነው» የሚል ቃል እናነባለን፡፡ ስለሆነም የበጎ ኅሊና ልመናው በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ የተረጋገጠ አዲስ ሕይወት ለማግኘት የቀረበ ጥያቄ መሆኑን ያሳያል፡፡ ከዚያም ቀጥሎ «እርሱም መላእክትና ሥልጣናት ኃይላትም ከተገዙለት በኋላ ወደ ሰማይ ሄዶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ» ስለሚል ጌታ ኢየሱስ ከትንሣኤው በኋላ ወደ ሰማይ ሄዶ በእግዚአብሔር ቀኝ መኖሩ እኛንም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር ያስቀመጠን መኾኑን ያሳያል /ኤፌ.2፡7/፤ የበጎ ኅሊና ልመናው ክርስቶስ ከእርሱ ጋር እንዲያስነሣን እና በሰማያዊ ስፍራ እንዲያስቀምጠን በፈቃደኝነት የቀረበ ጥያቄ ነው፡፡ የውኃ ጥምቀት ምሳሌ የሚሆንለት እውነታ ይህ የበጎ ኅሊና ልመና ነው፤ ይህም የበጎ ኅሊና ልመና በሌላ አገላለጽ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ነው፡፡ ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ የሚያድነን ውኃ የሚያመለክተው ይህን እምነት ነው፡፡ በአጭር ቃል በዚህ ንባብ ውስጥ ጥምቀት ለሚያድነው ነገር ምሳሌ ሆኖ ቀርቧል እንጂ የሚያድን ሆኖ አለመቅረቡን ምን ጊዜም ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡


2.3. የውኃ ጥምቀት የሚያስፈልገው ለዳግመኛ ልደት አይደለም

ዳግመኛ ልደት ማለት ሰዎች በኢየሱስ ክርስቶስ ሲያምኑ የእግዚአብሔር ልጅ ለመሆን ከእግዚአብሔር የሚወለዱበት መንፈሳዊ ልደት ነው፡፡ በዮሐ.1፡12 «ለተቀበለት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም» ይላል፡፡ ስለዚህ ዳግመኛ የሚወለዱት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የተቀበለት ማለትም በስሙ ያመኑት መሆናቸውን ከዚህ እንረዳለን፡፡ ይሁንና ቃሉ የሚናገረውን እውነት በጥንቃቄና በአግባቡ ካለመለየት የተነሣ የውኃ ጥምቀት ለዳግመኛ ልደት እንደሚያበቃ ተደርጎ የሚሰጥ የስህተት ትምህርት መኖሩ አልቀረም፡፡ ይህ ትምህርት በዮሐ.3፡5 ላይ «ኢየሱስም መለሰ እንዲህ ሲል፡ እውነት እልሃለሁ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም» የሚለውን ቃል ከአሳቡ ውጪ በመጥቀስ ማስረጃ አድርጎ ስለሚጠቀምበት እዚህ ላይ ትክክለኛ አሳቡ ምን እንደሆነ መመልከቱ ተገቢ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከፈሪሳውያን ወገን የአይሁድ አለቃ ለሆነው ለኒቆዲሞስ ያስተማረው ትምህርት ዳግመኛ ስለመወለድ እንጂ ስለ ውኃ ጥምቀት አለመሆኑን ከሁሉ አስቀድሞ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ «ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር» ይላል እንጂ «በውኃና በመንፈስ ካልተጠመቀ በቀር» አይልም፡፡ በንባቡ ውስጥ «ውኃ» የሚል ቃል ስላለ ብቻ ጥምቀትን ሊያመለክት ይችላል ብሎ ማሰብ ግምት እንጂ እውነት ሊሆን አይችልም፡፡ ንባቡ የሚናገረው ከውኃና ከመንፈስ ስለመወለድ ነው፡፡ ይህም ልደት መንፈሳዊ መሆኑ ቀጥሎ ያለው ንባብ ሲያስረዳ «ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነው፡፡ ዳግመኛ ለትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አታድንቅ፤ ነፋስ ወደሚወለደው ይነፍሳል፣ ድምፁንም ትሰማለህ ነገር ግን ከወዴት እንደመጣ ወዴትም እንደሚሄድ አታውቅም ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው፡፡» ይላል /ዮሐ.3፡6-8/፤ ውኃ ደግሞ ፍጥረታዊ ነገር እንጂ መንፈሳዊ ነገር አይደለም፤ ስለዚህ ከፍጥረታዊ ነገር መንፈሳዊ ልደት ሊጠበቅ አይችልም፤ ታዲያ «ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር» በሚለው ሐረግ ውስጥ «ውኃ» የሚለው ምን ሊያመለክት ነው? ብሎ መጠየቅ አግባብነት አለው፤ በቲቶ.3፡5 ላይ ለአዲስ ልደት ስለሚሆን መታጠብ እናነባለን፡፡ በሕዝ.36፡25 ላይ «ጥሩ ውኃ እረጨባችኋለሁ፤ እናንተም ትጠራላችሁ ከርኵሰታችሁም ሁሉ ከጣዖቶቻችሁም ሁሉ አጠራችኋለሁ» ይላል፡፡ በዚህ ክፍል የተጠቀሰው «ጥሩ ውኃ» ፍጥረታዊው ውኃ እንዳልሆነ ከንባቡ ይዘት ግልጥ ነው፤ ምክንያቱም ፍጥረታዊ ውኃ ከርኩሰትና ከጣዖቶች የሚያጠራ አይደለምና፡፡» በኤፌ.5፡26 ላይ ደግሞ «በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለ እርሱ ራሱን አሳልፎ ሰጠ» ይላል፤ በዮሐ.15፡3 ላይም «እናንተ ስለነገርኳችሁ ቃል አሁን ንጹሐን ናችሁ» ይላል፡፡ በመሆኑም የእግዚአብሔር ቃል የሚያጥብና የሚያነጻ መሆኑን እነዚህ ጥቅሶች ያስገነዝቡናል፡፡ ለአዲስ ልደት የሚሆነው መታጠብም የሚከናወነው በእግዚአብሔር ቃል መሆኑን በዚህ መረዳት ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ «ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፣ በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ፡፡» በማለት ይናገራል፡፡ /1ጴጥ.1፡23/፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔር ቃል ዳግመኛ ልደትን እንደሚያስገኝ ይህ ንባብ ያረጋግጣል፡፡ ከእነዚህ ሁሉ የቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃዎች አኳያ «ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለዳችሁ በቀር» በሚለው ንባብ ውስጥ የተጠቀሰው «ውኃ» የእግዚአብሔር ቃል እንጂ ለጥምቀት የሚውለው የወንዝ ወይም የኩሬ ውኃ አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡

እስከ አሁን ድረስ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የውኃ ጥምቀት ዓላማ እንደሆኑ በአንዳንድ የስህተት ትምህርቶች የሚነገሩትን ነገር ግን በእግዚአብሔር ቃል እንደተጻፈው እንደዚያው በማስተዋልና በአግባቡ ስናጠናቸው የጥምቀት ዓላማ ያልሆኑትን ነጥቦች ተመልክተናል፡፡ ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን ትክክለኛው የውኃ ጥምቀት ዓላማ ምንድነው? ወይም በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን መዳንም ሆነ ዳግመኛ ልደት የሚገኝ ከሆነ በውኃ መጠመቅ የሚያስፈልገው ለምንድነው? ይህንንና ከዚህ ጋር የተያያዙ ሌሎች ነጥቦችን ቀጥሎ እንመለከታለን፡፡



3. የውኃ ጥምቀት ዓላማዎች


1. በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ለመመስከር

ከእግዚአብሔር ፍርድ መዳን የሚቻለው ሆነ በዳግመኛ ልደት የእግዚአብሔር ልጅ መሆን የሚቻለው በጌታ በኢየሱስ በማመን መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ሲናገሩ «ጸጋው በእምነት አድኖአችኋል»/ኤፌ.2፡8/፣ እንዲሁም «ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙም ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው»/ዮሐ.1፡12/ በማለት ይገልጻሉ፡፡ ይህ እምነት የሚገለጥበት ውጫዊ ሥርዓት ደግሞ የውኃ ጥምቀት ነው፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ ስንመለከት አስቀድሞ ፊልጶስ ስለኢየሱስ ወንጌልን ሰብኮለት ነበር፤ ከዚያም እንዴት እንደተጠመቀ ስለእርሱ የተጻፈውን ስናነብ «በመንገድም ሲሄዱ ወደ ውኃ ደረሱ፤ ጃንደረባውም፡- እነሆ ውኃ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድር ነው? አለው፤ ፊልጶስም በፍጹም ልብህ ብታምን ተፈቅዷል አለው፡፡ መልሶም ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምናለሁ አለ፡፡ ሰረገላውም ይቆም ዘንድ አዘዘ ፊልጶስና ጃንደረባውም ሁለቱም ወደ ውኃ ወረዱ አጠመቀውም፡፡» የሚል እናገኛለን /ሐ.ሥ.8፡36-38/፡፡ ከዚህም የምንረዳው ጃንደረባው የተጠመቀው በኢየሱስ ማመኑን በሚታይ ሥርዓት በሰው ፊት ለማረጋገጥ መሆኑን ነው፡፡ እንዲሁም ሐዋርያው ጳውሎስ የሚናገረውን ታዳምጥ ዘንድ ጌታ ልብዋን የከፈተላት ልድያ ከቤተሰዎቿ ጋር ከተጠመቀች በኋላ «በጌታ የማምን እንድሆን ከፈረዳችሁልኝ ወደ ቤቴ ገብታችሁ ኑሩ» ብላ እርሱንና አብረውት የነበሩትን እንደለመነቻቸው እናነባለን /የሐ.ሥ.16፡15/፤ ይህም አገላለጽዋ እርስዋ የተጠመቀችው በጌታ ማመኗን ለማሳየት እንደነበረ በግልጽ የሚያስረዳ ነው፤ በተጨማሪም እርስዋ በነበረችበት በዚያው በፊልጵስዩስ ከተማ ለነበረው ለወኅኒ ጠባቂው ጳውሎስና ሲላስ «በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን አንተና ቤተሰዎችህም ትድናላችሁ» ካሉት በኋላ ለእርሱና በቤቱ ላሉት ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ነግረዋቸው ያን ጊዜውንም እርሱ ከቤተሰዎቹ ሁሉ ጋር እንደተጠመቀ እናነባለን፡፡ ከዚያም ቀጥሎ «በእግዚአብሔርም ስላመነ ከቤተሰዎቹ ሁሉ ጋር ሐሴት አደረገ» የሚል ቃል ስለእርሱ ተጽፎ እናገኛለን/የሐዋ.ሥ. 16፡33-34/፤ ይህ ሰው ከተጠመቀ በኋላ በእግዚአብሔር ስላመነ ከቤተሰዎቹ ሁሉ ጋር ሀሴት ማድረጉ የተጠመቀው እምነቱን ለመግለጥ እንደነበር በግልጽ የሚያስረዳ ነው፡፡ ስለዚህ ወንጌል የተመሰከረለት ማንኛውም ሰው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ካመነ በኋላ ያን እምነቱን በውኃ ጥምቀት ሊመሰክር ይገባል፡፡ ሰው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በእውነት ያመነ ከሆነ ለመጠመቅ አልፈልግም የሚል መንፈስ ሊኖረው አይችልም፤ ነገር ግን አምኜአለሁ እያለ በውኃ መጠመቅ የማይፈልግ ወይም ጥምቀትን በማቃለል የሚቃወም ከሆነ እምነቱ እውነተኛ እምነት አለመሆኑን ማወቅ ይቻላል፡፡


2. ደቀመዝሙር መሆንን ለማሳየት፣

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ 11ዱን ሐዋርያት ወደ አሕዛብ በላካቸው ጊዜ «እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀመዛሙርት አድርጓቸው፡፡» ብሎ እንዳዘዛቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ እናነባለን /ማቴ.28፡19/፤ ደቀመዝሙር ማለት የአንድ መምህር ቋሚ ተማሪ እና የትምህርቱም ተከታይ ማለት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የእርሱ ለሆኑት ሁሉ መምህር እንደሆነ እርሱ የተናገራቸውን ዓረፍተ ነገሮች እናነባለን /ማቴ.23፡8-10፤ ዮሐ.13፡13/ ስለዚህ ክርስቲያኖች ማለትም በክርስቶስ ያመኑት ሁሉ የእርሱ ደቀመዛሙርት ናቸው፡፡ የውኃ ጥምቀት በሚወስዱበት ጊዜ የሚገልጡትም የክርስቶስ ቋሚ ደቀመዛሙርት ሆነው ለመቀጠል የወሰኑ ሰዎች መሆናቸውን ነው፤ የመጀመሪያዎቹ አማኞች «ደቀመዛሙርት» እየተባሉ ይጠሩ እንደነበር ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ እናነባለን /6፡7/፤ ለምሳሌ ጳውሎስን ብንመለከት በጌታ አምኖ ከተጠመቀ በኋላ ደቀመዝሙር እንደሆነ እንገነዘባለን/የሐ.ሥ.9፡18 እና 26/፡፡ በክርስቶስ ያመኑ ሰዎች በውኃ ከተጠመቁ በኋላ እርሱ ያዘዘውን እንዲጠብቁ የሚማሩ ደቀመዛሙርት ናቸው፤ ይህም ደቀመዝሙርነት የክርስቶስን ትእዛዛትና ትምህርቶች በቃል ደረጃ መማር ብቻ ሳይሆን መኖርን ወይም መታዘዝን ጭምር የሚያካትት መሆኑን ያስረዳል፤ ጌታ ኢየሱስ «እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀመዛሙርቴ ናችሁ፤» በማለት ተናግሯል /ዮሐ.8፡31/፡፡ ስለዚህ በክርስቶስ ያመኑ ሰዎች በውኃ ሲጠመቁ እየመሰከሩ ያሉት ከዚህ በኋላ ክርስቶስን በቋሚነት የምከተል የእርሱን እውነቶች ሁልጊዜም ከቃሉ የምማር በተግባርም የምጠብቅ ደቀመዝሙር ሆኛለሁ የሚል ምስክርነት ነው፡፡


3. ከክርስቶስ ሞት ጋር አንድ ለመሆን

በሮሜ.6፡3 ላይ «ወይስ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደተጠመቅን አታውቁምን?» የሚል ቃል ተጽፎልናል፡፡ ይህም የጥምቀትን ዋነኛ ዓላማ የሚገልጽ ነው፡፡ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የሞተው በሁላችን ፈንታ መሆኑ ይታወቃል፤ ስለዚህ የእርሱ ሞት በእርሱ ያመንን የሁላችንም ሞት ነው «አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ፤ እንግዲያስ ሁሉ ሞቱ» የሚለው ቃል ይህን እውነታ በግልጽ ያስረዳል /2ቆሮ.5፡14/፡፡ ይህም ማለት ከስፍራ አንጻር ሊታይ የሚገባው ሲሆን በዓለም ከነበርንበት ስፍራ ወጥተን ክርስቶስ በምድር ሳለ ይዞት ወደነበረው ስፍራ መምጣታችንን ወይም ከእርሱ ጋር መቈጠራችንን የሚገልጽ ነው፤ ከክርስቶስ ጋር አንድ መሆን ማለትም ይኸው ነው፡፡ በዚህ ስፍራ ላይ የሚገኝ መሆኑን ለማሳየት የተጠመቀ አማኝ የክርስቶስን ህይወትና ማንነት የተላበሰ ሰው ነው፤ «ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁላችሁ ክርስቶስን ለብሳችኋልና» ተብሎ ተጽፏል /ገላ.3፡27/፡፡ ይህም ከክርስቶስ ጋር አንድ መሆን እኛ ክርስቶስ በተመላለሰበት መንገድ ወደምንመላለስበት ስፍራ መምጣታችንን የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ ከክርስቶስ ጋር አንድ መሆን በውጫዊ ሥርዓት የሚገለጠው ደግሞ በውኃ ጥምቀት ነው፤ እናም በውኃ መጠመቅ ከክርስቶስ ጋር አንድ መሆናችንን የሚያሳይ በመሆኑ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሞቷልና ከዚህ ሞቱ ጋር አንድ መሆናችንንም ይገልጣል ማለት ነው፡፡ ይኸው ሐሳብ በሰፊው በተተነተነበት በሮሜ ምዕ.6 ላይ «ከእንግዲያስ ወዲያ ለኃጢአት እንዳንገዛ የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደተሰቀለ እናውቃለን፤ የሞተስ ከኃጢአቱ ጸድቋልና» የሚል ቃል ስለምናነብ/ቊ.6/ ከክርስቶስ ጋር መሞት ከአሮጌው ማንነታችንና ከኃጢአተኛው ሕይወታችን ሙሉ ለሙሉ መለየትን የሚናገር ነው፤ ምክንያቱም ክርስቶስ በመስቀል ላይ የሞተው የእኛን ኃጢአት ተሸክሞ ወይም የእኛን የኃጢአተኞቹን ስፍራ ይዞ ነውና፤ እኛም ከእርሱ ጋር አንድ ስንሆን ከሞቱ ጋር አንድ ስለምንሆን ኃጢአተኛው ሰዋችን /ማንነታችን/ ተፈርዶበት ከእርሱ ጋር እንደተሰቀለ ወደ ማወቅ እንመጣለን፤ በተግባርም ከአሮጌው ሰው ፈቃድ እንለያለን፤ ይህንንም ከክርስቶስ ጋር የመሞታችንን ድንቅ ምስጢር በውኃ ጥምቀት እንመሰክራለን፡፡ ይሁን እንጂ እዚህ ላይ ሊስተዋል የሚገባው ክርስቶስ ሞቶና ተቀብሮ አልቀረም፤ ከሙታን መካከል በክብር ተነሥቷል፤ ወደፊትም ሞት እንዳይገዛው እናውቃለን/ሮሜ6፡9/፡፡ እንዲሁም ከሞቱ ጋር አንድ የሆኑ አማኞች ከትንሣኤውም ጋር ይተባበራሉ፤ ይህም አማኞች ከአሮጌው ሰውነት የሚለዩ ብቻ ሳይሆኑ በምትኩ በአዲስ ሕይወት የሚመላለሱ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ «እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፣ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን፤ ሞቱን በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን» ተብሎ የተጻፈው ቃል የሚያስረዳውም ይህንኑ ነው /ሮሜ.6፡4-5/፡፡ ይህም ከእርሱ ጋር የመሞታችን ዋነኛ ግብ ከእርሱ ጋር ለመነሣት መሆኑን የሚያሳይ ነው፤ ስለዚህ ጥምቀት በዋነኛነት ከእርሱ ጋራ መሞትን የሚያሳይ ሲሆን ይህ በራሱ ግን ከእርሱ ጋር መነሣትን አስከትሎ የሚያመጣ በመሆኑ መነሣቱንም ጨምሮ ሊያመለክተን ይችላል፡፡ «በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ» የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ይህን ያረጋግጥልናል /ቈላ.2፡12/፡፡ ስለዚህ በውኃ ጥምቀት ይህን የሚመሰክሩና የመሰከሩ ሰዎች በተግባርም ከአሮጌው ሰው ተለይተው ክርስቶስ በተመላለሰበት ሕይወት ማለትም በአዲስ ሕይወት እየተመላለሱ የተጠመቁበትን ዓላማ ሊፈጽሙትና ሊያረጋግጡት ይገባቸዋል፡፡


4. ቀደም ሲል በነበሩ አማኞች ላይ መጨመርን ለማሳየት

በሐ.ሥ.2፡41 ላይ «ቃሉን የተቀበሉ ተጠመቁ በዚያም ቀን ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስ ተጨመሩ» ይላል፡፡ ይህም ወንጌል ተሰብኮላቸው በክርስቶስ ያመኑ ሰዎች በቀደሙት አማኞች ላይ የሚጨመሩበት ሥርዓት ጥምቀት መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ቃሉ የተሰበከላቸው ሰዎች በሰሙት ቃል ልባቸው ተነክቶ ጌታን ለመከተል የእርሱም ደቀመዝሙር ለመሆን ሲወስኑ አስቀድመው ደቀመዛሙርት ከሆኑ ሰዎች ጋር መተባበር ይጀምራሉ፤ ከእነርሱ በፊት የነበሩት አማኞች የእነርሱን ማመን የሚያውቁበት ማስረጃም ጥምቀት ስለሆነ አዲሶቹ አማኞች በውኃ ይጠመቃሉ፤ ከዚያም በኋላ በቀድሞዎቹ አማኞች ላይ ይጨመራሉ፡፡ የሚጨመሩት በቀጣይ መንፈሳዊ ነገሮች ለመትጋት ሲሆን በዚህም የጌታ ደቀመዛሙርት መሆናቸውን ያረጋግጣሉ፤ በእርግጥ ያመኑና የጌታ ለመሆን ልባቸውን የሰጡ ከሆኑ በዙሪያቸው ካለው ዓለም ተለይተው የጌታ ከሆኑት ጋር ለመተባበር ፈጽሞ አያፍሩም አይፈሩምም፡፡


የውኃ ጥምቀት የሚከናወንበት ስም

በተሰበከለት የወንጌል ቃል ልቡ ተነክቶ ንስሐ በመግባት በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ያመነ ሰው ከክርስቶስ ጋር አንድ መኾኑን በውኃ ጥምቀት ይመሰክራል፡፡ ተጠምቆም የክርስቶስ ደቀመዝሙር ይሆናል፡፡ ቀደም ሲል በነበሩ አማኞች ላይም ለጌታ ይጨመራል፡፡ ከዚህ በፊት በታተሙት በእውነት ጋዜጣ እትሞች ላይ እነዚህን የውኃ ጥምቀት ዓላማዎችና ሌሎችንም በመዘርዘር የውኃ ጥምቀት ዓላማዎች ካልሆኑት ነገሮች ለይተን በማሳየት ማስነበባችን የሚታወስ ሲሆን አሁን ደግሞ አማኙ በትክክለኛዎቹ የጥምቀት ዓላማዎች መሠረት ሲጠመቅ በማን ስም እንደሚጠመቅ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረንን እንመለከታለን፡፡

የውኃ ጥምቀት የሚከናወንበትን ስም አስመልክቶ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሳኤው በኋላ ለደቀመዛሙርቱ የተናገረው ቃል «እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀመዛሙርት አድርጓቸው» የሚል ነው /ማቴ.28፡19/፡፡ ከዚህም የምንረዳው ወንጌል ሰባኪዎች የጌታ ደቀመዛሙርት ለመሆን የወሰኑ ሰዎችን በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እንዲያጠምቁ ከጌታ የተሰጠውን መመሪያ ነው፡፡ እዚህ ላይ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ማጥመቅ ምን ማለት ነው? የሚለውን በቅድሚያ መመልከቱ ጠቃሚ ነው፡፡ በአብ በወልድና በመንፈስቅዱስ ስም ማጥመቅ የውኃ ጥምቀት በሚከናወንበት ጊዜ አጥማቂው «በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም» ብሎ እየተናገረ ተጠማቂውን ወደ ውኃው ውስጥ ማጥለቁን ከማመልከት ያለፈና የጠለቀ ትርጉም እንዳለው በብዙዎች ዘንድ አልተስተዋለም፡፡ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ማጥመቅ በወንጌል ያመኑ ሰዎችን ከአይሁድም ሆነ ከአሕዛብ መካከል የሚለዩበትን በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ማመንን የሚያመለክት ነው፡፡ ክርስቶስ በሥጋ ከመገለጡ በፊት እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ራሱን ሲገልጥ የነበረው በአንድ አምላክነቱ ነበር፡፡ በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በአንዳንድ ክፍሎች ውስጥ በመለኮት ዘንድ ከአንድ በላይ አካላት እንዳለ የተጠቆመ ነገር ቢኖርም/ዘፍ1፡26፤ 3፡22/፣ በኋለኛው ዘመን ሰው በሆነው በክርስቶስ ኢየሱስ የተገለጠልንን ያህል በግልጽ የምናነብበት ስፍራ የለም፡፡ ይህ የእግዚአብሔር ማንነት በግልጽ የተነገረው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በብዙ ስፍራዎች ስለአብ ስለወልድና ስለመንፈስ ቅዱስ የተናገረ ቢሆንም ሐዋርያትን በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እንዲያጠምቁ የተናገረበት ክፍል ከሁሉም የጎላ ነው፡፡ አንድ ሰው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ካመነ አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ሶስት አካላት ሆነው ሳለ አንድ አምላክ ወይም አንድ መለኮት መኾናቸውን ያምናል፤ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም በሚጠመቅበት ጊዜም የሚመሰክረው ይህንን እምነቱን ነው፡፡

አንዱ አምላክ እግዚአብሔር ሶስት አካላት ሆኖ መገለጡን በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በግልጥ እናነባለን፡፡ የክርስቶስን መወለድ አስመልክቶ ለድንግል ማርያም በመልአኩ በገብርኤል ከተነገረው ቃል መካከል «መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑልም ኃይል ይጸልልሳል፤ ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል» የሚል ይገኛል /ሉቃ.1፡35/፡፡ በዚህ ንባብ ውስጥ የተሰመረባቸው ቃላት እንደሚያሳዩን መንፈስ ቅዱስ፣ አብ /ልዑል/ እና ወልድ /የእግዚአብሔር ልጅ/ በሶስትነት ተገልጠዋል፡፡ በዚህ ዓይነት በመጽሐፍ ቅዱስ ባሉ በተለያዩ ዐረፍተ ነገሮች አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስን በአንድ ንባብ ውስጥ በሶስትነት እናገኛለን፡፡ ሶስቱም አካላት በየራሳቸው በይፋ የተገለጡት ደግሞ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ በተጠመቀ ጊዜ ነበር፡፡ ይህንን ከሚያስረዱት የወንጌላት ክፍሎች መካከል በሉቃ.3፡21-22 «ሕዝቡም ሁሉ ከተጠመቁ በኋላ ኢየሱስ ደግሞ ተጠመቀ፡፡ ሲጸልይም ሰማይ ተከፈተ፣ መንፈስ ቅዱስም በአካል መልክ እንደ ርግብ በእርሱ ላይ ወረደ፣ የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፣ በአንተ ደስ ይለኛል፤ የሚል ድምፅም ከሰማይ መጣ፡፡» የሚል እናነባለን፡፡ በዚህ ክፍል «መንፈስ ቅዱስ»፣ «‘የምወድህ ልጄ’ የሚለው አባት» እና «‘ልጄ’ የተባለው ኢየሱስ» በግልጽ ተለይተው ተጠቅሰዋል፡፡ ሶስቱም አንድ የመለኮት ባሕርይ ያላቸው ናቸው፡፡ እንደዚሁም ኢየሱስ ካስተማራቸው ትምህርቶች መካከል «እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል» የሚለው እዚህ ላይ ሊጠቀስ ይገባዋል /ዮሐ.14፡15/፡፡ እኔ ሲል ወልድን ያመለክታል፤ አብን እለምናለሁ ሲል አብና ወልድ የየራሳቸው የተለያየ አካል /ማንነት/ ያላቸው መኾኑን ያሳያል፡፡ «ሌላ አጽናኝ» የሚለው ደግሞ መንፈስ ቅዱስን ሲሆን /ቊ.17/ «ሌላ» በመባሉ ከአብና ከወልድ የተለየ የራሱ አካል/ማንነት/ ያለው መሆኑን ያመለክታል፡፡ ይሁን እንጂ ሶስቱም አንድ አምላክ አንድ መለኮት ናቸው፡፡ በተጨማሪም ጌታ ኢየሱስ «ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል» ብሎ በተናገረው ቃል ውስጥ የአብ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ ሶስትነት በግልጽ ይታያል /ዮሐ.15፡26/፡፡ በዚህ ዓይነት ኢየሱስ የተናገራቸው ብዙ ዓረፍተ ነገሮች አሉ፡፡ አንድነታቸውንም በተመለከተ ኢየሱስ ሲያስተምር «እኔና አብ አንድ ነን» /ዮሐ.10፡30/፣ «እኔን ያየ አብን አይቷል» /ዮሐ.14፡9/፣ «እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ» /ዮሐ.10፡11/፣ «እርሱ /መንፈስ ቅዱስ/ ያከብረኛል ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና፡፡ ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው፤ ስለዚህ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል አልሁ፡፡» /ዮሐ.16፡12-15/ በማለት የተናገራቸው እውነቶች የአብ የወልድና የመንፈስ ቅዱስን አንድ አምላክነት በግልጽ የሚያስረዱ ናቸው፡፡ ሐዋርያትም በትምህርታቸው እግዚአብሔር በሶስትነትና በአንድነት የሚኖር አምላክ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ጎላ ጎላ ያሉትን ብንጠቅስ እንኳ በ2ቆሮ.13፡14 «የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ የእግዚብሔር ፍቅር፣ የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን» የሚል ቃልን እናነባለን፡፡ በዚህ ንባብ ሶስቱም አካላት በአንድ ዐረፍተ ነገር ውስጥ ተጠቅሰዋል፡፡ በ2ተሰ.2፡17 ላይ ደግሞ «ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ የወደደን በጸጋም የዘላለምን መጽናናት በጎንም ተስፋ የሰጠን እግዚአብሔር አባታችን ልባችሁን ያጽናኑት፤ በበጎ ሥራና በቃል ሁሉ ያጽኑአችሁ» ይላል፡፡ በዚህ ክፍል መንፈስ ቅዱስ ባይጠቀስም ኢየሱስ /ወልድ/ እና እግዚአብሔር አባታችን /አብ/ አንድን ሥራ የሚሠሩ ማለትም የአማኞችን ልብ የሚያጽናኑ እንዲሁም በበጎ ሥራና በቃል ሁሉ የሚያጸኑ ሆነው ተገልጠዋል፡፡ ይህም በአካል የተለያዩ ቢሆኑም አንድ መለኮታዊ ሥራን የሚሠሩ መሆናቸውን ያረጋግጣል፡፡ ያጽናኑት፣ ያጽኑአችሁ የሚሉት ቃላትም በብዙ ቊጥር መነገራቸው በአካል የተለያዩ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ በ1ጴጥ.1፡1 ላይ «የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ጴጥሮስ፣ እግዚአብሔር አብ አስቀድሞ እንዳወቃቸው በመንፈስም እንደሚቀደሱ ይታዘዙና በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ይረጨ ዘንድ ለተመረጡት ...» የሚል እናነባለን በዚህም ጴጥሮስ የጻፈላቸው አማኞች በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ሥራ የተመረጡ መሆናቸውን እንረዳለን፡፡ በራእ.1፡5 ላይም «ካለውና ከነበረው ከሚመጣውም፣ በዙፋኑም ፊት ካሉት ከሰባቱ መናፍስት፣ ከታመነውም ምስክር ከሙታንም በኲር የምድርም ነገሥታት ገዢ ከሆነ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን» ይላል፡፡ በዚህም ክፍል «ያለው የነበረው የሚመጣው» የሚለው አብን፣ «በዙፋኑ ፊት ያሉት ሰባቱ መናፍስት» መንፈስ ቅዱስን፣ «የታመነ ምስክር የሙታን በኲር የምድር ነገሥታት ገዢ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ» ወልድን የሚመለከት ነው፤ ጸጋና ሰላም እንዲሆን የተባለው ከሶስቱም በመሆኑ ሶስቱ አካላት ሶስት ቢሆኑም አንድ መለኮታዊ ሥራን በአንድ ባሕርይ እንደሚሠሩ ያሳያል፡፡ እግዚአብሔር በዚህ ማንነቱ ሊታወቅና ሊታመን ይገባዋል፡፡ ክርስትና እግዚአብሔርን በዚህ ማንነቱ ያወቅንበትና ያመንበት እምነት ነው፤ ይህም እምነት ሰዎች ሁሉ በወንጌል ስብከት በኩል ሊቀበሉት የተገባ እምነት ነው፡፡

እንግዲህ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ማጥመቅ ማለት ወንጌል ተሰብኮላቸው በኢየሱስክርሰቶስ ያመኑ ሰዎች እግዚአብሔርን በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስነት የሚያምኑ መኾናቸውን በሚገልጥና በሚመሰክር ጥምቀት ማጥመቅ ማለት ነው፤ ክርስትና እግዚአብሔርን የሚያውቀውም ሆነ የሚያስተዋውቀው በዚህ ማንነቱ ነው፤ ኢየሱስም ሆነ ሐዋርያቱ የእግዚአብሔርን ማንነት በዚህ መልክ በጥልቀት አስተምረውናል፤ ስለዚህ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት ባጠቃላይ የተመሠረተው እርሱ አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ በማመን ነው፤ በአምልኮም ሆነ በጸሎት ወደፊቱ ስንቀርብ እርሱን የምንረዳው በዚህ ማንነቱ ነው፡፡ ከመታወቅና ከመነገር ያለፈውን ይህን ማንነቱን በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ የገለጠ እርሱ ስሙ ይባረክ፤ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ተጠምቀን የክርስቶስ ደቀመዛሙርት ሆነን ይህን ድንቅ ማንነቱን እንድንመሰክር የረዳን እርሱ ስሙ ይባረክ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ እግዚአብሔር እርሱ አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ መሆኑን ማመናችንን በመመስከር ደቀመዛሙርት እንሆን ዘንድ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እንድንጠመቅ በማቴ.28፡19 የተጻፈው የክርስቶስ መመሪያ እንዳለ ሆኖ በሐ.ሥ.2፡38፤ 8፡16፤ 10፡48፤ 19፡5 ላይ ሐዋርያት አማኞችን በኢየሱስ ክርሰቶስ ስም አጥምቀው እንደነበር እናነባለን፤ ታዲያ ይህስ እንዴት ይታያል? የሚል ጥያቄ መነሳቱ የማይቀር ነው፡፡ በቅድሚያ ሐዋርያት በኢየሱስ ክርሰቶስ ስም ማጥመቃቸውን በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ማጥመቅን የሚያስቀር አድርጎ ከሚያስብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ አስተሳሰብ መራቅ ያስፈልጋል፤ ሐዋርያትን ወደ ዓለም የላካቸውና በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እንዲያጠምቁ ያዘዛቸው ራሱ ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር አብሮ ይሠራ እንደነበር በማር.16፡20 ላይ እናነባለን፡፡ በሐዋርያት እየሠራ የነበረውም መንፈስ ቅዱስ የኢየሱስ መንፈስ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፤ በአጠቃላይ ኢየሱስ /ወልድ/ እና መንፈስ ቅዱስ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስን የላከው አብ በሐዋርያት በኩል እየሠሩ የነበረ መኾኑን መረዳት ያስፈልጋል፤ በመሆኑም ሐዋርያት በጊዜው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሲያጠምቁ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ እንደነበረ እንገነዘባለን፡፡ ይህን እያሰብን የሐዋርያት ሥራን አጠቃላይ ትኲረት ስንመለከት ሐዋርያት በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የማጥመቃቸውን ምክንያት ለመረዳት እንችላለን፡፡ በሐ.ሥ. ም.2 ላይ ስንመለከት የጴጥሮስ የስብከቱ ትኲረት ኢየሱስ እርሱ «ጌታ»፣ «ክርስቶስም» እንደሆነ ማስተዋወቅ ነበር/2፡36/፤ ለቆርኔሌዎስ ቤተሰዎችም በሚሰብክበት ጊዜ የክርስቶስን ማንነት ይልቁንም ሞቱንና ትንሳኤውን ነበር የመሰከረው/ሐዋ.ሥ.10፡35-43/፡፡ ከአይሁድ ወንጌልን የተቀበሉት ወገኖቻቸው ሰቅለው በገደሉት እግዚአብሔር ግን ከሙታን ባነሳው በዚያው ጌታ አምነው የእርሱ ደቀመዛሙርት መኾናቸውን ያሳዩ ዘንድ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መጠመቃቸው ይበልጥ አስፈላጊ ሆኖ ነበር፡፡ እንዲሁም የሰማርያ ሰዎችም ሆኑ አሕዛብ ወንጌል ሲሰበክላቸው በመጀመሪያ የሚመሰክርላቸው ስለኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ በተሰበከው ወንጌል ልባቸው ተነክቶ የሚያምኑትም ኢየሱስ ክርስቶስን ነው፤ ስለዚህ በዚህ ሁኔታ ዋነኛ የእምነታቸው ማረፊያ ኢየሱስ ክርሰቶስ ስለሆነ በዚሁ ባመኑበት ስም መጠመቃቸው ተገቢ ሊሆን ችሏል፡፡ ይህ ግን በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ማመንም ሆነ በዚህ ስም መጠመቅን የሚያስቀር ወይም የሚቃረን አይደለም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተከናወነው ጥምቀት የክርስትናን ጥምቀት ከመጥምቁ ዮሐንስ ጥምቀት ለመለየት የተደረገ ጥምቀት ሆኖ እናየዋለን፤ በሐ.ሥ.19፡3 ላይ እንደምናነበው ጳውሎስ በኤፌሶን ያገኛቸው 12 ደቀ መዛሙርት «እንኪያ በምን ተጠመቃችሁ?» ሲላቸው «በዮሐንስ ጥምቀት» ብለውት ነበር፡፡ ጳውሎስም «ዮሐንስስ ከእርሱ በኋላ በሚመጣው በኢየሱስ ክርስቶስ ያምኑ ዘንድ ለሕዝብ እየተናገረ በንስሐ ጥምቀት አጠመቀ» እንዳላቸው ከተመለከትን በኋላ «ይህንንም በሰሙ ጊዜ በጌታ በኢየሱስ ክርሰቶስ ስም ተጠመቁ» የሚል እናነባለን፡፡ በዚህም በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መጠመቅ ከዮሐንስ ጥምቀት ጋር ተነጻጽሮ የቀረበበትን ሁኔታ እንመለከታለን፡፡ ስለሆነም ከዚህ አንጻር የዮሐንስ ጥምቀት እርሱ የሰበከውን ንስሐ ተቀብሎ የእርሱ ደቀመዝሙር መሆንን ለመግለጽ የተከናወነ እንደነበረ ሁሉ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መጠመቅ ደግሞ የአየሱስ ክርስቶስን ትምህርቶች አምኖ የእርሱ ደቀመዝሙር መሆንን ለማሳየት የተደረገ ጥምቀት መሆኑን የሚያመለክት እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ሆኖም ይህም በራሱ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ማጥመቅም ሆነ መጠመቅ ሥራ ላይ መዋሉን የሚያስቀር አይደለም፡፡ በዚህም መሠረት በሐዋርያት አገልገሎት በነበረው ትኲረትና እነሱ የሚያጠምቁትን ጥምቀት ከዮሐንስ ጥምቀት ለመለየት በሚያስችል ምክንያት በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ቢያጠምቁም በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ማጥመቁም አግባብነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ነው፡፡ ስለሆነም ዛሬ ወንጌሉ በየስፍራው ተሰብኮ የኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት በታወቀበትና አብ ወልድና በመንፈስ ቅዱስን ማመን የክርስትና መለያ በሆነበት ሁኔታ የውኃ ጥምቀት በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ መከናወን ይኖርበታል እንላለን፡፡


Amharic Bible-|- The Holy Bible [King James Version]