መግቢያ
በርካታ ክርስቲያኖች የምእመናን ጥሪ በምድር ላይ ምን እንደሆነ ማስተዋል ይጎድላቸዋል፡፡ የወንጌል አገልጋዮችም ቢሆኑ ኃጢአተኛ በደሉን በመናዘዝ ወደ እግዚአብሔር ከቀረበና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሠራው የማዳን ሥራ አማካይነት ኃጢአቱ እንደተሰረየለት ካወቀ ሁሉም ነገር በአግባቡ ያለቀ የተጠናቀቀ ይመስላቸዋል፡፡ ሰው የሚለወጥበትን የምሥራቹን ወንጌል በተመለከተ ለቃሉ የበለጠውን ስፍራ ይሰጣሉ፤ ነገር ግን ከመለወጥ በኋላ ስላለው ሕይወትም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ ዋንኛ መመሪያ እንደሆነ ቸል በማለት ይህን ለሚያስረዳው ክፍል የሚሰጡት ትኲረት አነስተኛ ነው፡፡ በ1ኛ ተሰ1፡9 ላይ «ለሕያውና ለእውነተኛ አምላክም ታገለግሉ ዘንድ .... ከጣዖቶች ወደ እግዚአብሔር እንዴት ዘወር እንዳላችሁ.......» ተብሎ ተጽፏል፡፡ ሥጋዊ ሰው እግዚአብሔርን ማገልገል ስለማይችል/ሮሜ3፡10-12/ አስቀድሞ የሕይወት ለውጥ ከተደረገ በኋላ ቀጥሎ እግዚአብሔርን ማገልገል ይከተላል፡፡ እግዚአብሔር ለሰው ያለው የመጨረሻውና ዋንኛው አላማ በሕይወት ለውጥ ብቻ የሚያበቃ አይደለም፡፡ የሕይወት ለውጡ ግን እግዚአብሔር ለሰው ያለውን ያን ዓላማ ማለትም ለሕያውና ለእውነተኛ አምላክ ማገልገልን እንድንደርስበት የሚያስችል ብቸኛና አማራጭ የሌለው መንገድ ነው፡፡
ይህ ሐሳብ ለሮሜ ሰዎች በተጻፈው መልእክት ውስጥም ተጠቅሷል፡፡ በመጀመሪያዎቹ 11 የሮሜ መልእክት ምዕራፎች ውስጥ ኃጢአተኛ እንዴት ወደ እግዚአብሔር ሊቀርብ እንደሚችል ተሟልቶ ከተገለጠ በኋላ በምዕራፍ 12 ቊ. 1 ላይ ለአእምሮ የሚመች አገልግሎታችን/Reasonable or intelligent service ማለት ምክንያታዊ ወይም አግባብነት ያለው አገልግሎት/ ሰውነታችንን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብ እንደሆነ እናነባለን፡፡ በቊጥር 2 ላይ ደግሞ በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደሆነ ፈትነን እንድናውቅ ያበረታታናል፡፡ በእርግጥም የእግዚአብሔር ፈቃድ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ብቻ መገኘቱ የማይካድ እውነት ነው፡፡ ስለዚህም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሕያውና እውነተኛውን አምላክ እንዴት ማገልገል እንደሚገባን ለማወቅ ከፈለግን የእግዚአብሔርን ቃል መመርመር ይገባናል፡፡ መዝሙረኛው ዳዊት «ምስክርህ ትዝታዬ ነውና ካስተማሩኝ ሁሉ ይልቅ አስተዋልሁ» ሲል ተናግሯል/መዝ119፡99/፤ እንዲሁም «ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴም ብርሃን ነው»/መዝ119፡105/ ብሏል፡፡
ስለ እግዚአብሔር አገልግሎት ስናስብ ደግሞ ከሁሉ አስቀድሞ ልናስበው የሚገባን ምእመናን ስለሚሰበሰቡበት ስፍራ ነው፡፡ ምክንያቱም ላደረገላቸው ነገር ምስጋና በሚያቀርቡበት በአምልኮ አገልግሎት ቢሆን ወይም የልባቸውን መሻት በሚጠይቁበት በጸሎት ስብሰባ ቢሆን አለበለዚያም ከእግዚአብሔር በሚማሩበት በቃል አገልግሎት ምእመናን በቀጥታ በጋራ ሆነው ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙት በሚሰበሰቡበት ስፍራ ስለሆነ ነው፡፡ እርሱ በእነዚህ ሁሉ ማለት በአምልኮ፣ በጸሎትና በቃል አገልግሎት ስብሰባዎች በመካከላቸው ሊገኝ ይፈልጋል/1ቆሮ14፡25፣ ማቴ18፡20/፡፡
ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ የምእመናንን የመሰብሰቢያ ቦታ በተመለከተ የተሰጡት መመሪያዎች በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን ጠቃሚ ስፍራ አላቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል በኦሪት ዘጸአትና በኦሪት ዘሌዋውያን ብቻ ስለ መገናኛው ድንኳንና በዚያ ስላለው አገልግሎት ምን ያህል ጊዜ ተደጋግሞ እንደተነገረ ማየቱ በቂ ምስክር ነው፡፡ በአዲስ ኪዳንም እንዲሁ ትምህርተ ደኅንነትን ከሚያስጨብጠው ከሮሜ መልእክት ቀጥሎ ባለው በቆሮንቶስ መልእክት ውስጥ ስለምእመናን መሰብሰብ የሚናገረውን መለኮታዊ መመሪያ ማስተዋሉ ተገቢ ነው፡፡
እግዚአብሔር በመካከሏ የሚገኝባት ስብሰባ የሚካሄድባት ቦታ የትኛዋ እንደሆነች ማወቅ የሁሉም ሰው መሻት ነው፡፡ እግዚአብሔር ስለመረጠውና ሰው ሊሰበሰብበት ስለሚገባው ስፍራ ምንነት የተለያየ ግንዛቤ ከመኖሩም በላይ ከዚህ ጉዳይ ይበልጥ ትኲረት ተሰጥቶት የተለያዩ በርካታ ሐሳቦች የሚሰነዘሩበት ሌላ ጉዳይ አለመኖሩ የሚያስደንቅ ነው፡፡ ከሐሳቦቹም አንዱ ሰው እውነትን በተመለከተ በከፊል ወይም በአመዛኙ ልክ እንደ እርሱ ከሚያስቡት ጋር እግዚአብሔርን ለማምለክ መሰብሰብ ይኖርበታል የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሰው ወደ አገር አቀፍ ወይም ወደ ብሔራዊት ቤተክርስቲያን ሄዶ በዚያ መሰብሰብ እንደሚገባው ያስባል፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ባወቀበት በዚያ መቆየት እንዳለበት ያምናል፡፡ አራተኛው ወገንም በበኩሉ በራሱ ግምት ብዙ በረከት አገኛለሁ እባረክበታለሁ ወደሚልበት ስፍራ መሄድ እንዳለበት ያስባል፡፡ የእግዚአብሔር ቃልስ በዚህ ጉዳይ ላይ በግልጥ የሚናገረው የለምን? ወይስ የታወቀ ትእዛዝ የለምን? በአእምሮአችን፣ መታዘዝ ከመሥዋዕት እንደሚበልጥ እያሰብን/1ኛ ሳሙ15፡22/ ይህንን ጠቃሚ ነገር ለመረዳት መጽሐፍ ቅዱስን ከቀደምት የእስራኤላውያን ታሪክ በመነሣት እንመርምር፡፡
እስራኤላውያን በምድረ በዳ
ከሁሉ በፊት ብሉይ ኪዳን ለኛ ስለሚሰጠው ጠቀሜታ እንመልከት፡፡ በ2ኛ ጢሞ3፡16 ላይ «የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል» ይላል፡፡ በ1ኛ ቆሮ10፡11 ላይ ደግሞ እስራኤላውያንን በምድረበዳ ያጋጠማቸው ሁሉ ለኛ ምሳሌ እንደሆነና ለተግሣጻችን እንደተጻፈ እናነባለን፡፡ በመጨረሻም በዕብ9፡23 ላይ የሚታዩት የብሉይ ኪዳን ነገሮች በአዲስ ኪዳን ለተገለጡት ሰማያዊና መንፈሳዊ ነገሮች ምሳሌ እንደሆኑ ተገልጧል፡፡ ስለሆነም የእግዚአብሔር ሰማያዊ ነገሮች ሐሳብ በብሉይ ኪዳን በሚታዩ ሥዕሎች እንደተገለጠ እንረዳለን፡፡ የብሉይ ኪዳን መሥዋዕቶች የጌታ ኢየሱስ የሰብእናውና የሥራው ምሳሌ ናቸው፤ የመገናኛው ድንኳንም ሆነ ቤተ መቅደሱ ማለትም በምድር ላይ የነበረው የእግዚአብሔር ቤት በአዲስ ኪዳን የተገለጠውን መንፈሳዊውን የእግዚአብሔርን ቤት የሚወክል ለሥጋ ዓይን የቀረበ ቤት ነበር/1ኛ ጴጥ2፡5፣ ኤፌ2፡20-22፣ 1ኛ ቆሮ3፡6/፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም በ1ኛ ቆሮ9፡9-10 ላይ ቀላል የሆኑና ለዚህ ዓለም የተነገሩ ትእዛዛት መንፈሳዊ ትርጉም እንዳላቸው ጽፎልናል፡፡ ከዚህም በመነሣት ስለ መሰብሰቢያ ስፍራ ቀደም ሲል የነበረውን የእግዚአብሔርን ሐሳብ ለመረዳት የእስራኤልን ታሪክ በተለያዩ ዘመናት በመክፈል ብሉይ ኪዳንን እናጥና፡፡
በኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ የምእመናን መሰባሰብ አልተገለጠም፡፡ በምትኩም በማያምኑ ሰዎች መካከል እግዚአብሔርን የሚያገለግሉ ግለሰቦችን ብቻ እናያለን፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ህዝብን ለራሱ መለየት እንደጀመረ እርሱም በሕዝቡ መካከል ሊኖር እንደወደደና ሕዝቡም ወደ እርሱ ሊቀርቡ እንደሚገባቸው የሚጠቁሙ ፍንጮችን እንደሰጠ መመልከት ጠቃሚ ነው፡፡ አብራም ከነዓን እንደደረሰ በቤቴል/ትርጓሜው-የእግዚአብሔር ቤት/ የእግዚአብሔርን የያህዌን ስም ጠራ/ዘፍ12፡7-8/፡፡ የቦታው ትክክለኛ ስያሜ በዚያን ጊዜ «ሉዝ» ወይም «ሎዛ» ቢሆንም የእግዚአብሔር ቃል እዚህ ላይ ለቦታው «ቤቴል» የሚለውን ስያሜ ይጠቀማል፡፡ ይኸው ስፍራ ከ162 ዓመታት በኋላ በያዕቆብ ቤቴል ተብሎ ተጠርቷል፡፡ ከቤቴል ርቆ መሄድ ረሃብንና ችግርን ያስከትላል፡፡ ያም አብራም ከቤቴልና በቤቴል ከሠራው መሠዊያ ፊቱን በመለሰ ጊዜ ሆኖ እናገኛለን፡፡
በዘፍጥረት ምዕራፍ 28 ላይ በዚያው ስፍራ በቤቴል እግዚአብሔር ለያዕቆብ በኋላ ልጆቹ በሚወለዱባትና የሕዝበ እስራኤል ልደት ወደሚጀምርባት ወደ ካራን ሲሄድ ሳለ ተገልጦለት ታላቅ ሕዝብ እንደሚሆን ተስፋ ሰጥቶት ነበር፡፡ በዘፍጥረት ምዕራፍ 35 ላይ ደግሞ እግዚአብሔር ያዕቆብን ወደዚያው ስፍራ ሲመልሰውና በዚያው ስፍራ ላይ ራሱን ሲገልጥለት እንመለከታለን፡፡ እነዚህ ሁሉ ወደፊት ለሚገለጠው ነገር ጠቋሚዎች ናቸው፡፡ ትክክለኛው ነገር የተገለጠው ግን ከዘጸአት 19 በኋላ ባለው ክፍል ነው፡፡
ሕዝበ እስራኤል በግብፅ ምድር በባርነት ቀንበር ተይዘው ሳሉ ከራሱ ርኅራኄ በመነሣት የአባቶቻቸው አምላክ እግዚአብሔር በግብፅ ለፈርዖን ከሚገዙበት በነፃነት እርሱን ወደሚያገለግሉበት ወደ ምድረ ከነዓን እንዲገቡ ያለውን ፈቃዱንና ዕቅዱን በባሪያው በሙሴ አማካይነት ወደ ሕዝቡና ወደ ፈርዖን ላከ፡፡ ሙሴም በእርግጥ ሕዝቡ በጋራ እግዚአብሔርን ማገልገል እንደሚኖርባቸውና ለዚህም ሲባል መንገድ መሄድ እንዳለባቸው በፈርዖን ፊት በተደጋጋሚ ተናገረ፡፡ ሆኖም ይህ አገልግሎት በግብፅ ውስጥ እንደማይከናወን በግልጽ ተነግሯል፡፡ አስቀድሞ የፋሲካው በግ ሊታረድ/ዘጸ.12/፣ ሕዝቡም ሊዋጅና ከግብፃውያን ጋር የነበረው ኅብረት ሁሉ ሊቋረጥ ይገባዋል/ምዕ.14/፡፡ ይህ ሁሉ ከተከናወነ በኋላ ነበር እግዚአብሔር እስራኤልን «ሕዝቤ» በማለት የጠራውና በሕዝቡ መካከል ከሕዝቡ ጋር የሚገናኝበት ስፍራ ሊኖረው እንደሚፈልግ ያስታወቀው፡፡ «በመካከላቸውም አድር ዘንድ መቅደስ ይሥሩልኝ»/ዘጸ25፡8/፡፡
በተጨማሪም በኦሪት ዘጸአት ከምዕራፍ 25-40 ድረስ ባሉት ምዕራፎች ሁሉ ስለመገናኛው ድንኳን አሠራርና በውስጡም ስለሚካሄደው አገልግሎት የተሰጡ መመሪያዎችና ትእዛዛት ተለይተው ተጠቅሰው እናገኛለን፡፡ ያም ድንኳን
- ማደሪያ/ዘጸ25፡9/
- የመገናኛ ድንኳን/ዘጸ29፡42/
- የምስክር ድንኳን/ዘኁል 17፡7/
እነዚህ ስሞች ሁሉ በግልጥ የድንኳኑን ትርጉም ያሳያሉ፡፡ ከመጀመሪያው ስም ስፍራው/1/ የእግዚአብሔር ቤት/ማደሪያው ዘጸ25፡8/፣ እግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል የሚያድርበት ወይም የሚኖርበት እንደሆነ እንረዳለን፡፡ በዚህ ማደሪያም ሕዝቡ/2/ ከእግዚአብሔር ጋር ይገናኛል፡፡ ከዚያም በላይ ስፍራው በምድር ላይ የእግዚአብሔር ምስክር ነበር/3/፤ በዚያም እግዚአብሔር በቅድስናው እንዲሁም በፍቅሩና በጸጋው ተገልጧል፡፡
ወደዚህ ስፍራ ሰዎች ሁሉ በዓመት ሦስት ጊዜ ይመጡ ነበር፤ ወደዚህም ቦታ የእህል በኲራት ተወሰዷል/ዘጸ34፡23-26/፡፡ ወደዚህም ስፍራ ለእግዚአብሔር መባ ይመጣ ነበር/ሌዋ1፡7/፤ በዚያም ካህናት ተክነዋል/ሌዋ8 እና 9/፤ አዎ ለመብል የሚታረዱ እንስሳት እንኳን ሳይቀሩ መጀመሪያ ወደዚህ ስፍራ መወሰድ ነበረባቸው/ሌዋ17፡4/፡፡ ስለሆነም የመሰብሰቢያውን ስፍራ በተመለከተ የእግዚአብሔርን ቃል ለሚያውቅ ለአንድ እስራኤላዊ በአእምሮው ውስጥ አንዳች ጥርጥር ሊኖር ይችላልን?
ትእዛዛቱን ሰምቶ በመታዘዝ ፈቃደኛ በሆነ መንፈስ ወደ እርሱ በሚመጣ ሕዝብ የእግዚአብሔር ልብ ምንኛ ይደሰታል /ዘጸ35/! እግዚአብሔር አንዳች እንዲያመጡለት ማንንም አያስገድድም፤ ነገር ግን በልብ ፈቃደኝነትና በደስታ የሚቀርብ መሥዋዕትን ከሰው ይጠብቃል፡፡ ሕዝበ እስራኤልም በዚህ ረገድ የከበረ ምላሽን ላዳናቸው አምላክ ሰጥተዋል፤ ሳይሰጥ የቀረ ማንም ሰው በመካከላቸው ሳይኖር ነገር ግን በፈቃደኛ ልብ ሁሉም ካላቸው መልካሙንና የተመረጠውን ለእግዚአብሔር ሰጡ፡፡ ሴቶች ጌጦቻቸውንና መስተዋቶቻቸውን አቀረቡ/ዘጸ38፡8/፤ ወንዶች ደግሞ ውድ ዕቃዎቻቸውን ብርና ወርቅ ሰጡ፡፡ ምንም ስስት አልነበረም፤ ፍርሃትም አልነበረም፡፡ ለአንድ አፍታ እንኳን የግል ጥቅምን መሻት እንደ እግዚአብሔር ሐሳብ ከማድረግ ወደኋላ አልገታቸውም፡፡ ይሁን እንጂ ሁሉም አንድ ዓይነት መባ ሊሰጡ አልቻሉም፤ አንዳንድ ብልህ ልብ ያላቸው ሴቶች ግን ከሌሎች ይበልጥ ለማድረግ ችለዋል፡፡ ሆኖም ሁሉም ከልብ በሆነ ፈቃደኝነት ያላቸውን ለእግዚአብሔር ሰጥተዋል፡፡ ይህም በመጀመሪያው የነበረችውንና በሐዋ.ሥራ2፡42-47 የተጠቀሰችውን የክርስቲያኖችን ኅብረት እንድናስብ አያደርገንምን?
እግዚአብሔርስ በበጎነቱ ለዚህ የሰጠው ምላሽ ምንድን ነው? እንደ ሐሳቡ መቅደሱ ከተተከለ በኋላ እግዚአብሔር ለሁሉም ለዐይን በሚታይ መልኩ በመካከላቸው ሊያድር መጣ/ዘጸ.40/፤ ከማደሪያውም ሆኖ አነጋገራቸው፣ ድንቅ የሆኑ ሐሳቦቹንም ገለጠላቸው፡፡ ከዚያው ከአንዱ መሥዋዕት እየበሉ እንዴት ወደ እርሱ እንደሚቀርቡና ከእርሱ ጋር ኅብረት እንደሚያደርጉ አስተማራቸው/ሌዋ3፡11፣7፡19/፡፡ የአሮን ልጆች በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ እንዴት እንደሚጠበቁና/ሌዋ8፡35/ የማስተስረያውን አገልግሎት እንዴት እንደሚራዱ/ሌዋ9፡9/ አስተምሯቸዋል፡፡ እያንዳንዱ ሰው ንጽሕናውን እንዴት እንደሚጠብቅና/ሌዋ. ምዕ.11/ ያደፈውም እንዴት ዳግመኛ እንደሚነጻ/ሌዋ.ምዕ.12-15/ ገልጾላቸዋል፡፡ ቀጥሎም የሚያከብሯቸውን በዐላት ካስተማራቸው በኋላ/ሌዋ. ምዕ. 23/ ሰው ርስቱን እንዳያጣ የሚያደርግ ሥርዓት ደንግጎላቸዋ,ል/ሌዋ. ምዕ. 25/፡፡ በሕዝቡ መካከል ለእያንዳንዱ ስፍራና አገልግሎትን በመስጠት ሁሉም አንድ አካል ሆነው በመገጣጠም በሥርዓት እንዲያገለግሉት አድርጓል/ዘኁ. ምዕ.1-4/፡፡ በሰባት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከዘጸ40፡1 እስከ ዘኁ10፡11 ምንኛ ድንቅ ነገሮችን ገልጾላቸዋል፡፡
ይሁን እንጂ በአሳዛኝ ሁኔታ ሕዝቡ በዚህ ከእግዚአብሔር ጋር በነበረው ሁኔታ በበጎነት አልቀጠለም፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር ሕዝቡ በምድረ በዳ መሥዋዕትን እንዳላቀረቡለትና በምትኩም የሞሎክን/የጣዖትን/ ድንኳን እንዳቆሙ ያለውን ቅሬታ በአሞጽ5፡25 እና 26 ገልጿል፡፡ ብቸኛውን የመሰብሰቢያ ቦታ ረስተው እግዚአብሔር ወደሌለበት ወደሌላ ቦታ ሄዱ፡፡
እስራኤላውያን በምድረ ከነዓን
በኦሪት ዘዳግም አዲስ ትምህርትን እናገኛለን፤ ከ40 ዓመት የምድረበዳ ጉዞ በኋላ ወደ ተስፋይቱ ምድር ይገቡ ዘንድ ከዮርዳኖስ ወንዝ ሲደርሱ በተስፋይቱ ምድር እንዴት ሊኖሩ እንደሚገባቸው እግዚአብሔር አዲስ ትምህርትን አስተማራቸው፡፡
የዚህም መጽሐፍ ክፍል በግልጽ ሰው ሊረዳው የሚችለው ነው፡፡ የመጀመሪያቹ 11 ምዕራፎች የሕዝቡን ታሪክና ከእነርሱ ጋር የነበረውን የእግዚአብሔርን ጸጋ የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ ምዕራፍ 12 ሕዝቡ ሊጠብቋቸው በሚገባቸው ሕግጋትና ትእዛዛት የሚጀምር ሲሆን ከምዕራፍ 30-34 ድረስ ባለው ክፍል ደግሞ በሕዝቡ አለመታዘዝ ሊመጣ ያለው ስደት በትንቢት መልክ ተገልጿል፡፡
ከላይ እንደተጠቀሰው 11ዱ ምዕራፎች ሕዝቡ በምድረበዳ ያሳለፈውን ጉዞ የሚዘክሩ ናቸው፡፡ ሆኖም በዘጸአትና በዘኁልቊ የምናገኛቸው ታሪኮች በድጋሚ የተነገሩበት ብቻ አይደለም፤ ይልቁኑ ሕዝቡን የጠበቀው የእግዚአብሔር ፍቅርና ጸጋ የተንፀባረቀበት፤ በታላቁና በአስቸጋሪው ምድረበዳ የተደረገው የ39 ዓመታት ጉዞና የነበረው ችግር ሁሉ ካለመታዘዛቸው የተነሣ የደረሰባቸው መሆኑ የተመሰከረበት ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ጠብቀው ቢሆን ኖሮ ከ11 ቀናት ጉዞ በኋላ ወደ ከነዓን ምድር ይቃረቡ ነበር/ዘዳ1፡2/፤ ይህም ክፍል እግዚአብሔር ሊያወርሳቸው የወደደውን ይወርሱ ዘንድ የሚችሉት ሙሉ በሙሉ በእርሱ ቃል ላይ ሲደገፉና ለቃሉም ሲታዘዙ እንደሆነ በድጋሚ በምዕራፍ 11 ላይ የበለጠውን ትኲረት ሰጥቶ በማሳሰብ ያበቃል፡፡
ልባቸው ቃሉን ለመስማት ፈቃደኛ ከሆነ በኋላ ከምዕራፍ 12-29 ባለው ክፍል እግዚአብሔር ሕግጋቱንና ትእዛዛቱን ይሰጣቸዋል፡፡ እንደማንኛውም ጊዜ ሁሉ እዚህም ተቀዳሚው ነጥብ እግዚአብሔርን ለማገልገል ሕዝቡ የሚያደርገው መሰባሰብ ነው፤ ህዝቡም ሊገባ ያለው አምልኮተ ጣኦት ያውም የአጋንንት አምልኮ /1ቆሮ10፡20/ ወደሞላበት ምድር ነበር፡፡ የሰው ልብ ሁልጊዜ በዙሪያው ያሉትን ነገሮች ወደመለማመድ ያዘነበለ ነው፡፡ በቀጥታ ከክርስትና ታሪክ እንደምንማረው ሁሉ፣ በሚያሳዝን መልኩ ከዚህ በኋላ ባለው በእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ይህንን እናያለን፡፡ የአምላክ አምልኮና የአጋንንት አምልኮ በዓላማ፣ በይዘትና በአፈጻጸም ሁኔታ ዝምድና የሌላቸው እንደሆኑ እግዚአብሔር ያሳወቃቸውም ለዚሁ ነበር፡፡ አጋንንት ብዙ ከመሆናቸው የተነሣ እውነተኛውን አምላክ የማያውቁ ብዙ አረማውያን ሰዎች በተለያዩ ቦታዎች ለብዙ አማልክት ይሰግዳሉ፡፡ በታላላቅ ተራሮች ላይ፣ በኮረብቶችና በእያንዳንዱ ዛፍ ሥር ያመልኳቸዋል፡፡ በተቃራኒው የብሉይ ኪዳን መሠረተ ሐሳብ እንደዚህ ይነበባል፤ «አምላካችን እግዚአብሔር /ያህዌህ/ አንድ እግዚአብሔር/ያህዌህ/ ነው»/ዘዳ6፡4/፡፡ ሕዝበ እስራኤል የሁሉ ፈጣሪ የሆነ ልዑል አምላክ እግዚአብሔር እንደሆነ ያውቁታል፡፡ አንድ የአምልኮ ስፍራና አንድ ዓይነት የአምልኮ ሥርዓት አፈጻጸም መኖሩም ከዚህ የተነሣ ነው፡፡ ይህም ከአምልኮተ ጣዖት ጋር ምንም መስማማት የለውም፡፡ በዘዳ12፡2-7 ለዚህ ጉዳይ ከፍተኛ ትኲረት ተሰጥቶታል፤ እንዲሁም በዚህ መጽሐፍ በምዕራፍ 12 በሙሉና በሌሎችም በርካታ ስፍራዎችና በተከታታይ ምዕራፎችም ጭምር ይኸው ተጠቅሶ እናገኛለን፡፡
ንዱ የሰማይና የምድር ፈጣሪ፤ ልዑልና የእስራኤል የቃል ኪዳን አምላክ ያህዌህ በምድሩ የሚኖሩ ሕዝቦቹ የት እና በምን ዓይነት መንገድ ወደ እርሱ ሊቀርቡ እንደሚገባቸው ሊወስን መብት አለው፡፡ በመሆኑም በዚህ ምዕራፍ ብቻ ስድስት ጊዜ ተደጋግሞ «አምላካችን ስሙ ይጠራበት ዘንድ ወደ መረጠው ስፍራ» በማለት ስለቦታው የተነገረውም ከዚህ የተነሣ ነው፡፡ ይህ ቃል በተቀሩትም ከ14-17 ባሉት ምዕራፎችና በሌሎችም ምዕራፎች በ18ኛ በ26 እና በ31 ላይ በሁሉም በአጠቃላይ 21 ጊዜ ተጠቅሷል፡፡ ይህም እግዚአብሔር ሕዝቡ ለሚሰበሰብበት ቦታ የሰጠው ትኲረትና ቀዳሚነት ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ እንድናስተውል ግድ አይለንምን?
እግዚአብሔር ሕዝቡ አንድ እንዲሆንለት ይፈልጋል፡፡ በዘመናት ሁሉ በቅድስት ውስጥ በሚቀመጠው በ12ቱ የገጽ ኅብስት/ሌዋ 24፡5/ በሊቀካህኑ ትከሻ ላይ በሚቀመጡ ሁለት የመረግድ ድንጋዮች፤ በደረት ኪስ ላይ በሚቀመጡ 12 ዕንቊዎች /ዘጸ28፡9-11/ አማካይነት ሕዝቡን እንደ አንድ አድርጎ ይመለከት ነበር፡፡ ዮርዳኖስን ከተሻገሩ በኋላም ይኸው አንድነት በ12 ድንጋዮች ምሳሌነት ተገልጿል/ኢያ4፡1-10/፡፡ በዕዝራ ዘመንም አንድነቱ ለመላው እስራኤል የኃጢአት ማስተስረያ ሆነው በታረዱት በ12 አውራ ፍየሎች ታይቷል/ዕዝ6፡17/፡፡
ይህም ኅብረት የተመሠረተው በጋራ ዓላማ፤ በጋራ በሚመለክ አንድ አምላክ እና በሐሳብ አንድነት ላይ ነበር/1ቆሮ1፡10/፡፡ የአምላካችን የእግዚአብሔር ስም በድንቅ ሁኔታ አንድ አድርጎ የሚያዋህድ ኃይል አለው፡፡ ሰይጣንም ይህን ስለሚያውቅ እንደዚህ የሚያስፈራው ሌላ ኃይል የለም፡፡ ያለመታከትም አንድነትን ለማጥፋት የሚታገለውም ለዚሁ ነው፡፡ ሆኖም በርካታ ምእመናን ይህን አይረዱም፡፡ ከእግዚአብሔር የራቀው ኢዮርብዓም ግን ይህን በሚገባ ያውቅ ነበር፡፡ «በጌታ ስም» የሚከናወን የጋራ አምልኮ መከፋፈልን እንደሚያስወግድ በመረዳቱ ሕዝቡ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድ ሌላ የአምልኮ ስፍራን አዘጋጀ፡፡ በዚህ ክፋቱም አምልኮን ጌታ እግዚአብሔር ከመረጠውና ስሙን ካኖረበት ቦታ ወደ ሌላ ቦታ አዛወረ /1ኛ ነገሥ12፡25-33/፡፡
በዘዳግም 12 ላይ የሕዝቡን ኅብረትና አንድነት ለማጠንከር ብዙ ነገሮች እንደተመቻቹ እናያለን፡፡ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ሊያወርስ ያለውን የባለጠግነቱን ታላቅነት ያውቃል፡፡ ሕዝቡም ካገኙት በረከት ለሰጣቸው ጥቂቱን መልሰው እንዲሰጡ እግዚአብሔር ይጠብቃል፤ ይፈልጋልም፡፡ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ በርካታ የፈቃድ መባ የተዘረዘረውም ለዚሁ ሲባል ነው፡፡ አሥራትና በኲራት ብቻ የግዴታ ስጦታዎች ነበሩ፡፡ እግዚአብሔር ከቀደሰው ነገር ሁሉ ሰዎች በፈቃደኝነት፣ በምስጋናና በመታዘዝ እርሱ ወዳለበት ስፍራ እንዲያመጡ ይሻል፡፡ በግል ከእያንዳንዳቸው እጅ ተቀብሎ በጋራ ከእነርሱ ጋር ሊደሰት ይፈልጋል፡፡ ከዚህ መሥዋዕት ከፊሉ ለእግዚአብሔር የሚደረግ የቊርባን መብል ነው /ሌዋ.3፡11 እና 16/፡፡ የተረፈው ደግሞ ለሕዝቡ፤ ለሴቶችና ለወንዶች ልጆቻቸው፣ ለወንድ አገልጋዮቻቸውና ለሴት አገልጋዮቻቸው ሲሆን እንዲሁም ሌዋውያን በልተው በፊቱ ደስ ይሰኙበታል /ዘዳ12፡7፣ 12፣18/፡፡ ለምድራውያን ሰዎች ከዚህ ከላይ ከቀረበው ዓይነት አገልግሎት የላቀ ድንቅ አገልግሎት ሊታሰብ ይችላልን? ነገር ግን ይህ ሁሉ ታላቅ በረከት ሆኖ የሚታየው የእግዚአብሔር ፍቅር በልባቸው ባደረባቸውና ከእርሱም ጋር ላለውም ኅብረት ዋጋ ለሚሰጡት ሰዎች ብቻ ነው፡፡
በሉቃስ 15 ላይ የተጠቀሰው ታላቁ ልጅ ከአባቱ ጋር ካለው አንድነት ለሚገኘው ደስታ ብዙም ዋጋ አልሰጠም፡፡ ነገር ግን አባቱ በሌለበት ከጓደኞቹ ጋር ለመደሰት ፈለገ፤ አድራጎቱም በግልጽ ዝሙት ነው፡፡ ይህም በኢሳ26፡8 ላይ «ስምህም መታሰቢያህም የነፍሳችን ምኞት ነው» ተብሎ ከተነገረውና በዘዳግም 18፡6 ላይ ሌዋዊው «በፍጹም ፈቃድም እግዚአብሔር ወደመረጠው ስፍራ ቢመጣ» ተብሎ ከተጻፈው ጋር ሲነጻጸር ያለው ልዩነት ምንኛ ጉልህ ነው፡፡
ኦሪት ዘዳግም ከምዕራፍ 12 ቀጥሎ ባሉት ምዕራፎች ሁሉ በእግዚአብሔር የተመረጠው ስፍራ ጠቀሜታ በሕዝቡ ሕይወት ውስጥ ምን ያህል እንደሆነ እንመለከታለን፡፡ ይህም በሌላ ምክንያት ሳይሆን የእግዚአብሔር ሕዝብ ሕይወት በመካከላቸው በሚኖረው እግዚአብሔር መሞላት ስላለበት ነው፡፡ በዘዳግም 14 እና 15 ላይ ስለ አሥራትና ስለበኲራት መብልነት የተገለጠውን እናነባለን፡፡ ምዕራፍ 16 ደግሞ ስለ ፋሲካ፣ ስለሰባቱ ሱባዔ በዓልና ስለዳስ በዓል ይናገራል፡፡ በምዕራፍ 17 ላይ ክፋት ከመካከላቸው ስለሚወገድበት ሁኔታ የተነገረ ሲሆን በምዕራፍ 18 ላይ ደግሞ ስለሌዋውያን አገልግሎት እናገኛለን፡፡ በምዕራፍ 26 ላይ በዕንቅብ ሙሉ በእግዚአብሔር ፊት ስለቀረበው የምድር ፍሬ እናነባለን፡፡ በምዕራፍ 31፡11 ላይ ደግሞ በዕዳ ምሕረት ዘመን በሰባተኛው ዓመት መጨረሻ ሕጉ በእስራኤል ሁሉ ፊት እንዲነበብ የተሰጠ መመሪያ ይገኛል፡፡
በ1ኛ ነገሥ11፡36 ላይ እንደምናነበው በዘዳግም የተጠቀሰውና ለአምልኮ የተመረጠው ስፍራ ኢየሩሳሌም መሆኗን እንገነዘባለን፡፡ እግዚአብሔር የጽዮንን ተራራ እንደወደደ መቅደሱንም በዚያ ለማኖር እንደፈቀደ ከመዝ78፡68 ላይ እናነባለን፡፡ ቀጥሎም በዚሁ መዝሙር በቊጥር 70 ላይ ይህ ስፍራ እግዚአብሔር ከመረጠው ከባሪያው ከዳዊት ጋር የተያያዘ መሆኑን እናገኛለን፡፡ በአንጻሩም እርሱም ዳዊት ምሳሌው የሚሆንለት የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ከስሙ ጋር በተያያዘው ቦታ ሁሉ በሚሰበሰቡበትና የእርሱ በሆኑት መካከል እንደሚገኝ የሰጠውን ተስፋ በማቴ18፡20 ላይ እናነባለን፡፡
ዳዊት ከወጣትነቱ ዘመን ጀምሮ ለእግዚአብሔር ማደሪያ ስፍራ ይፈልግ እንደነበር ይታወቃል/መዝ132፡5/፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ስፍራው ለካሌብ ከተሰጠው ርስት ላይ በኬብሮን እንደሆነ /ኢያ14፡13/ የቆሬ ልጆች በምድረ በዳ ሆነው መንገዱ መልካም እንደሆነ የዘመሩለት/መዝ 84/ ቦታ ላይ ይሆናል በማለት በልቡ አሰበ፡፡ ስለዚህ ቦታ የሚናገረውን የእግዚአብሔርን ቃል በሙሉ ልብ በእምነት ካልተቀበልነውና በልባችን ካላወቅነው እግዚአብሔር የመረጠውን ስፍራ የት እንደሆነ ማግኘት አይቻለንም፡፡ ዳዊትም ቢሆን የዚህን ስፍራ ትክክለኛ ቦታ የጽዮን ተራራ እንደሆነ ያወቀው በእግዚአብሔር ቊጣ ከተጸጸተ በኋላ ነበር፡፡ በ1ኛዜና መዋዕል 21 እና 22 እንደምናነበው ዳዊት በመታበዩ የእግዚአብሔር ፍርድ በላዩ ላይ ሊመጣበት እንዳስፈለገ እናያለን፡፡ ለዚህም ዳዊት ለበደሉ ሙሉ ዋጋ ከከፈለ በኋላ ነበር እግዚአብሔር ቤቱ የሚሠራበትን ትክክለኛ ስፍራ የገለጠለት፡፡ በማናቸውም ጊዜ ቢሆን ዐይንን ከሥጋዊ ነገሮች ላይ አንሥቶ እንደ እግዚአብሔር ሐሳብ ብቻ ለመሄድ ዋጋና መሥዋዕት ያስከፍላል፡፡
በሚያሳዝን ሁኔታ እስራኤል የእግዚአብሔርን ትእዛዝ አልጠበቀም፤ የእግዚአብሔር የታላላቅ ሥራዎቹ ምስክሮች ሲሞቱ ሕዝቡ በፍጥነት ወደ አምልኮተ ጣዖት ተመልሰዋል /መሳ2፡7-13/፡፡ በሆሴዕ 4፡13 ላይ ሕዝቡ «በተራሮች ራስ ላይ፣ ከኮምበልና ከልብን ከአሆማም ዛፍ በታች በኮረብቶች ላይም» በማጠናቸው እግዚአብሔር ቅሬታውን እንደገለጠ እናነባለን፡፡ ይህም በቀጥታ እግዚአብሔር በዘዳግም 12 በፍጹም እንዳያደርጉ የከለከለውን ማድረግ ነው፡፡ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰሎሞን እንኳን ሳይቀር እግዚአብሔር አስተዋይና ጠቢብ ልብ እስከሰጠው ጊዜ ድረስ በኮረብታ መስገጃ ይሠዋና ያጥን ነበር/1ኛነገሥ3/፡፡ ምንም እንኳን በሌላ መልኩ ፈሪሃ እግዚአብሔር ቢኖራቸውም ከሞላ ጎደል ሁሉም ነገሥታት በዚህ አድራጎታቸው እግዚአብሔርን አሳዝነዋል፡፡ በዘመናት እንደነበረ ሁሉ ሰው በዚህ ነገርም እግዚአብሔር የሰጠውን አበላሽቷል፡፡
እስራኤላውያን ከባቢሎን ምርኮ በኋላ
በዕዝራና በነህምያ ጊዜ የእስራኤልን ታሪክ በአዲስ መልኩ እናገኛለን፡፡ ከሕዝቡ እምነት ማጣትና አለመታዘዝ የተነሣ በሕዝቅኤል 8 እንደተገለጠው የእስራኤል አምላክ ክብር ኢየሩሳሌምን ለቆ ሄዷል፡፡ ኢየሩሳሌምን እግዚአብሔር የስሙ ማደሪያ አድርጎ የመረጣት ናት¬፤ በውስጧም የእግዚአብሔር ዙፋን ነበር/1ኛዜና29፡23/፡፡ ነገር ግን በኋላ በእግዚአብሔር አመንዝራ ሚስት እና ጋለሞታ ተብላ ተጠርታለች/ሕዝ16፡32 እና35/፡፡ አሥሩም ነገድ በስልምናሶር ወደ አሦር በምርኮ ከተወሰዱ ከ134 ዓመታት በኋላም ይሁዳ በናቡከደነጾር እጅ ወድቃ ነዋሪዎቿም በአብዛኛው ወደ ባቢሎን ተወስደዋል፡፡
እግዚአብሔር በጸጋው የሕዝቡን ቅሬታዎች በማሰብና የፋርስን ንጉሥ ቂሮስን ልብ በማነሳሳት ኢሳይያስ ከ150-200 ዓመት በፊት እንደተነበየው ከ70 ዓመት ምርኮ በኋላ አይሁድን ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመለሱ አደረገ/ኢሳ.45/፡፡ በዚህም ዕድል የተጠቀሙት ጥቂት የይሁዳና የብንያም ነገዶች ናቸው፡፡ በዕዝ2፡64 መሠረት ከዘሩባቤል ጋር የተመለሱት 42,000 ያህል ሲሆኑ ይሁዳና እስራኤል በጋራ 1,200,000 ጦረኞች እንደነበሯቸው/2ዜና13፡3/ ስናስብ ከምርኮ የተመለሱት ቅሬታዎች በቊጥር ምን ያህል አነስተኛ እንደነበሩ መገመት እንችላለን፡፡ ከሕዝቡ አብዛኛው ከእግዚአብሔር ለተሰጠችው ምድር ወይንም መቅደሱ ለነበረባት ለኢየሩሳሌም ናፍቆት አልነበራቸውም፡፡ ሌሎች እንደዳንኤል ያሉ በነበራቸው ሥልጣን ወይም በዕድሜ ምክንያት ከመመለስ ተከልክለው ነበር፡፡
ነገር ግን እግዚአብሔር ከነዚያ ከጥቂት ቅሬታዎች ጋር በመሆን ያበረታታቸውና ያደፋፍራቸው ነበር፡፡ ከጠላቶቻቸው ጠብቋቸዋል፤ ምሕረቱንና ረድኤቱንም በላያቸው አኑሯል፡፡ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ቀደም ሲል እስራኤል ወደነበረችበት ተመሳሳይ ደረጃ እንድትመለስ አላደረጋትም፡፡ ሰው በኃጢአቱና ባለመታመኑ ምክንያት ባጣው ስፍራ ተመልሶ እንዲቀመጥ ያደርግ ዘንድ እግዚአብሔር አለመታዘዝን ችላ የሚል አምላክ አይደለም፡፡ እነዚህ ከምርኮ የተመለሱ ቅሬታዎች አሁን ቀደም ሲል የነበረውና በዐይን ይታይ የነበረው የእግዚአብሔር ክብር በሌለበት ሁኔታ መኖር ነበረባቸው፤ የእግዚአብሔር ዙፋንም በኢየሩሳሌም እንደቀድሞው የለም፡፡ ከንጉሥ ዳዊት ወገን የሆነ ዘሩባቤል ወደ ዙፋኑ ቢገባም እንደ አንድ ተራ የፋርስ ነገሥታት ገዥ በመሆን ነው፡፡ የእግዚአብሔር ክብር ከኢየሩሳሌም ለቆ ወጥቷል፤ መንግሥቱንም እግዚአብሔር ለአህዛብ ነገሥታት ሰጥቷል/1ኛ ዜና.29፡23፣ ዳን2፡38፣ ኢሳ45፡1/ እግዚአብሔር የአረማውያንንም መንግሥታት ሙሉ መብት ይጠብቃል፡፡ የሐጌና የዘካርያስ ትንቢት የቀን አቆጣጠር የአረማውያንን ዘመነ መንግሥት የተከተለ ነው፡፡ እግዚአብሔር መልካም ሥራውን ለሕዝቡ ይሠራ የነበረው የሚገዙአቸውን በማጥፋት ሳይሆን በእነዚህ አረማውያን ነገሥታት ልብ ውስጥ ለአይሁድ መልካም የሆነውን በማስቀመጥ ነበር፡፡
እነዚያም ቅሬታዎች ዛሬ ብዙዎች እንደሚናገሩት ተናግረው ቢሆኑ ኖሮ ወደ ይሁዳ ባልተመለሱም ነበር፡፡ ሙሴ ለአሥራ ሁለቱ ነገድ ስለሚሆን ስለብቸኛው የአምልኮ ስፍራና ስለካህናት አገልግሎት በግልጥ የሚወስነውን የእግዚአብሔርን ትእዛዛትና ሕግጋትን ካሳወቃቸው 1,000 ዓመታት አልፈዋል፡፡ ሰሎሞን ውብ የሆነውን ቤተመቅደስ ሠርቶ ለዳዊት እግዚአብሔር እንደገለጠው አድርጎ ሁሉንም ካከናወነ 5 ምዕተ ዓመታት ተቆጥረዋል፤ ሆኖም አለማመን ለእግዚአብሔር ቃል ላለመታዘዝ በቂ ምክንያት ሆኖ የተገኘበት ጊዜ የለም፡፡ አሁን አዲስና ልዩ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ከ1,000 ዓመታት በፊት ቀደም ሲል እግዚአብሔር በሙሴ መጻሕፍት እንዳስቀመጠው ትእዛዝ መፈጸም አስፈላጊ ነውን? እግዚአብሔር ከኢየሩሳሌም ለቆ ከተማዋንና ቤተመቅደሱን እንዲቃጠሉ አልፈቀደምን? በባቢሎንና በሌሎች ከተሞች የሚኖሩትን አይሁድን እግዚአብሔር አልባረከምን? ለዚህም ዳንኤልና ጓደኞቹን፣ አስቴርንና መርዶክዮስን ማሰብ ይበቃል፡፡ በባቢሎን የሚኖሩት በትክክለኛው መንገድ ለመሆናቸው ይህ ማስረጃ አይሆንምን? የጠላት መኖሪያ ወደ ሆነችና ወደ ወደመችው ፍልስጥኤም ምድር፣ ለመኖሪያ የሚሆን ቤትና የቆመ መሠዊያ ወደማይታይባት፣ የማምለኪያው ቤተመቅደስ፣ ከጠላት የሚከላከሉባትና ከክፉ ራሳቸውን የሚለዩባት ቅጥሯ ወደ ፈረሰባት ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ መመለስ ይገባቸዋልን? ከዚህም በላይ የቀደመውን መልሶ ለማምጣት ፈጽሞ የማይቻል ነው፡፡
ታሪክ የሚያስተምረውን ትምህርት ከግምት ማስገባት አስፈላጊ አይደለምን? በእርግጥም ለምእተ ዓመታት ሁሉ ሁለት ነገድ ብቻ በኢየሩሳሌም እግዚአብሔርን ያገለግል እንደነበር ይታወቃል፡፡ ባለፉት 70 ዓመታት ሁሉም ነገር ተቀይሯል፤ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ፍጹም እንግዳና ልዩ የሆነ ነገር ተከስቷል፡፡ አሁን ደግሞ ከይሁዳና ከብንያም ነገድ ጥቂቶች ከአነስተኛ ካህናትና ሌዋውያን ጋር ከምርኮ ተመልሰዋል፡፡ ይህንንም ለመወሰን የሚመለከታቸው እነዚህ ብቻ ናቸውን? ከመቶ 90 የሚሆኑትና ያልተመለሱት እነዳንኤልንም ጨምሮ ሁሉም ተሳስተዋልን?
ያለአንዳች ጥርጥር ብዙዎች እንደዚያ ሊገምቱ ይችላሉ፡፡ አለበለዚያ ከአጠቃላይ ሕዝቡ 5 በመቶ የሚሆኑ 42,000 ሰዎች ብቻ ወደ ኢየሩሳሌም እንደተመለሱ ስለሚናገረው የእግዚአብሔር ቃል ማብራሪያ ለመስጠት የሚያስችል ሌላ መንገድ የለም፡፡
ነገር ግን ተገቢና ትክክል መስለው ቢታዩም እምነት በበጎ ሐሳቦች የሚመራ አይደለም፤ ራሱንም ለሁኔታዎች አይተውም፡፡ የተጀመሩ ክንውኖችም ትክክለኛነት ከወዲሁ ሊኖራቸው በሚችለው ውጤት አይለካም፡፡ ለሥራው ምክንያት በሚሆኑ ሰዎች ቊጥርም አይወሰንም፡፡ እምነት አምላካዊ መርሆችን በታሪክ አይዳኝም፤ ነገር ግን ለእግዚአብሔር ሕግጋት ከመገዛት አኳያ ታሪክን ይዳኛል፡፡ እምነት በሌሎች ነገሮች ላይ ሳያመካኝ በእግዚአብሔር ቃል ላይ ብቻ ይገደዋል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል እንደሚለው ፍልስጥኤም የተስፋይቱ ምድር ናት፤ ኢየሩሳሌምም እግዚአብሔር ስሙን በዚያ ያኖርባት ዘንድ የተመረጠችና ሕዝቡም ወደ እርሱ የሚቀርቡበት የእግዚአብሔር ቤት የተሠራባት ከተማ ናት፡፡ ስለዚህም የእግዚአብሔርን መልእክት በሰሙ ጊዜ ያምኑ የነበሩ አይሁድ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፡፡ በእርግጥ በመንገዳቸው ላይ ብዙ አስጊ ነገር ነበር፤ በኢየሩሳሌም ዙሪያ የሚኖሩ ሰዎች ጠላትነት ታላቅ ሆኖ ሳለ ነገር ግን ከቁም ነገር አልቆጠሯቸውም፤ እንዲያውም አልተጠቀሱም፡፡ ኢየሩሳሌምም በደረሱ ጊዜ የሚኖራቸው የጋለ ፍላጎት ምንኛ ታላቅ እንደነበር መገመት ይቻላል፡፡
ኢየሩሳሌም እንደደረሱም የተመለሱት ሁሉ በትክክል የእስራኤል ተወላጅ ስለመሆናቸውና ካህናትም በትክክል የካህናት ወገን ስለመሆናቸው የማጣራት ተግባር ተካሂዷል፡፡ በሌላው ጊዜ ማን እስራኤላዊ፣ ካህንና መጻተኛ እንደሆነ የሚታወቅ ስለሆነ ማንነትን ለማረጋገጥ የሚደረግ ሙከራ አስፈላጊ አልነበረም፡፡ ነገር ግን ችግር ባለበትና ጥፋት በሆነበት ሰዓት እንደዚህ ዓይነቱ ማጣራት አግባብነት ያለው ነው፡፡ ከባቢሎን እንግዳ የሆነ ሰው በቀላሉ አብሮአቸው ሊመጣ ይችላል፤ በምድር በመበተናቸው እነርሱም ከሌሎች በመቀላቀላቸውና እንዲሁም እንግዶች በምድራቸው ይኖሩ ስለነበሩ እንግዳ የሆነው ሰው እስራኤላዊ ነኝ ለማለት የሚችልበት ወይም ካህኑ ንጹሕ የካህናት ተወላጅ የማይሆንበት አጋጣሚ ሰፊ ነው፡፡ ስለዚህ የሰውየው እስራኤላዊ ነኝ ማለት ብቻውን በቂ አልነበረም፡፡ በእንደዚህ ዓይነቱ የጥፋት ጊዜ ማዕርግ ወይም የአገልግሎት ድርሻ አለኝ የሚል ሰው ለመብቱ ማረጋገጫ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ ሆኖም ዘሩባቤል ለእግዚአብሔር ተወ እንጂ የመብትና የማንነታቸውን ጥያቄ አልጠየቀም፡፡ ጌታ ለእርሱ የሆኑትን ያውቃልና/2ጢሞ2፡19/፡፡ ነገር ግን ማንነታቸውን በትክክለኛ ማስረጃ ይወስን ነበር፡፡ በኋላ በኡሪምና በቱሚም /ብርሃንና ፍጹምነት/ በመካከላቸው የሚፈርድ ካህን ሲነሣ ግን የመጨረሻው የማንነታቸውና የመብታቸው ውሳኔ ሁሉን አዋቂ በሆነው እግዚአብሔር ይወሰናል/ዕዝ2፡63/፡፡
እያንዳንዱ የእግዚአብሔር ሕዝብ ወገን መሆኑና በክህነት ማን እንደሚያገለግል ከተረጋገጠ ቀጥሎ የሚከናወነው የመጀመሪያው ነገር ለአምልኮ መሰባሰብ ነው፡፡ የት እንደሚሰበሰቡ አጠራጣሪ አይደለም፤ «ሁሉም እንደ አንድ ሰው ሆነው ወደ ኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ»/ዕዝ3፡1/፡፡ ምን እናድርግ በሚለውም አንዳችም የሐሳብ ልዩነት አልነበረም፤ በእርግጥም ለእግዚአብሔር ቃል ትልቅ ቦታ ሰጥተውታል፡፡ በነህምያ 8፡2-13 የእግዚአብሔር ቃል ምን ያህል ታላቅ ዋጋ እንደተሰጠው እንመለከታለን፡፡ በእግዚአብሔር መሪነት ወደ ምድራቸው የተመለሱ እነዚህ ሰዎች መጀመሪያ ያደረጉት ነገር ቢኖር ለእግዚአብሔር መሥዋዕት መሠዋት፣ ምስጋናንና አምልኮን ለረዳቸው አምላክ ማቅረብ ነው፡፡
አምልኮው በሚካሄድበት ቦታ ላይ በሕዝቡ ውስጥ ቅንጣት ያህል እንኳን ጥርጥር የለም፡፡ ያለው አንድ ቦታ ብቻ ነው፤ ያውም «ስሙን ያኖርባት ዘንድ እግዚአብሔር የመረጣት» ኢየሩሳሌም ናት፡፡ በዚያም ለእግዚአብሔር እንደ ሐሳቡ መሥዋዕት ለመሠዋት የሚያስችላቸው አንድ ብቻ የሆነ መሠዊያ ቆሟል፤ መሠዊያውም የቆመው ቀደም ሲል በነበረበት በኦርና አውድማ ላይ ከእግዚአብሔር ቤት በቤተመቅደሱ አደባባይ ነው፡፡
በእርግጥ የቆመ መቅደስ የለም፤ ነገር ግን ፍርስራሽ ነበር፡፡ መሠዊያውም አልነበረም፤ ሆኖም ቆሞበት የነበረበት ስፍራ ይታወቃል፡፡ በዚያም ላይ አዲሱን መሠዊያ መልሰው አቆሙ፡፡ ይህም መሠዊያ በሚልክያስ «የእግዚአብሔር ገበታ»/ሚል1፡7/ ተብሎ ተጠርቷል፡፡ በዚህም መሠዊያ ላይ ከምርኮ የተመለሱ እነዚህ ሰዎች በቤተመቅደሱ ፍርስራሽ ውጭ በአደባባዩ ውስጥ «በእግዚአብሔር ሰው በሙሴ መጻሕፍት ሕግ እንደተጻፈ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ሠዉ፤ በዚያውም እንደተጻፈው የቤተመቅደሱን በኣል አደረጉ፤ በታዘዘው መሠረትም ለበዐሉ የሚሆን መባንና ስጦታን ይዘው መጡ፡፡ የእግዚአብሔር ስሙ ባለበት ቦታ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ከአምልኮም በላይ እንደ እግዚአብሔር ቃል ከማድረግ ይበልጥ የተወደደ ልብንም የሚያረካ ሌላ ምን ሊኖር ይችላል?
በነገር ሁሉ ታዛዥ ከሆኑ በኋላም እግዚአብሔር የበለጠውን ብርሃንና ታዛዥነትን ሰጣቸው፡፡ የቤተመቅደሱንም ፍርስራሽ ተመልክተው ዝም አላሉም፤ በምትኩም መልሰው ለመሥራት ተጣደፉ እንጂ፤ ቤተመቅደሱ ሙሉ በሙሉ ወድሞ ስለነበር በቀደመ ክብሩ መልሶ መሥራት አስቸጋሪ ነበር፡፡ የመጀመሪያውን ቤተመቅደስ አይተው የነበሩት የሁለተኛው መሠረት ሲጣል አለቀሱ፡፡ በውስጧ ጽላተ ሕጉንና ኅብስተ መናን ያያዘች መሶበ ወርቅ የነበሩባት ታቦተ ጽዮን የለችም፡፡ በታቦተ ሕጉ ላይ የነበረውና በየዓመቱ አንድ ጊዜ ሊቀ ካህኑ በታላቁ የስርየት ቀን ደም የሚረጭበት የስርየት መክደኛ/ሌዋ16/ እንዲሁም የእግዚአብሔር ክብር በመካከላቸው ይኖርባቸው የነበሩ ኪሩቤል በዚያ የሉም፤ ኡሪምና ቱሚምም የሉም፡፡ በቊጥር ጥቂት ሰዎች ከመሆናቸውም ሌላ በነበረባቸው ድህነት ሳቢያ ሰሎሞን እንደሠራው ቤተመቅደስ ውብ አድርገው መሥራት የሚችሉ አልነበሩም፡፡
ጥረታቸው ደካማ ቢመስልም፣ ሕንጻውም ከፊተኛው ጋር ሲነጻጸር በሰው ዓይን ጎስቋላ ሆኖ ቢታይም በእግዚአብሔር ዐይን ፊት ሕንጻውም ሆነ ጥረታቸው ድንቅ ነበር፡፡ እግዚአብሔር የልባቸውን መሻት አይቷል፤ ለቃሉ ያላቸውን መታዘዝ በማየቱ ሥራቸው በዐይኑ ፊት ደስ የሚያሰኝ ነበር፡፡ ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር የሠሩት መቅደስ በዐይኑ ፊት ሰሎሞን እንደሠራው መቅደስ እንደሆነና የኋላ ክብሩ ከፊተኛው እንደሚበልጥ እየነገራቸው ያበረታታቸው ነበር፡፡ የሰሎሞን፣ የዘሩባቤል፣ የሄሮድስና የሺህው ዓመት ቤተመቅደስ/ሕዝ40-43/ ሁሉም በእግዚአብሔር ዐይን ፊት እኩል ናቸው፡፡ የእግዚአብሔር ቤት አንድ ብቻ ነው፡፡ ሆኖም ሊመጣ ካለው መሲሕ የተነሣ «ከፊተኛው ይልቅ የዚህ የሁለተኛው ቤት ክብር ይበልጣል ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር»/ሐጌ2፡9/፡፡
ከምርኮ የተመለሱት እስራኤላውያን በባቢሎን ከቀሩት ወንድሞቻቸው በራሳቸው የተሻሉ አይደሉም፡፡ እነርሱም ቢሆኑ በእግዚአብሔር ቊጣ ሥር ካሉት ጋር የሚመደቡ ናቸው፡፡ በመጽሐፈ ነህምያና በመጽሐፈ ዕዝራ እንደምናነበው እነዚህም እንደሌሎች ሁሉ ብዙ ድካምና ኃጢአት የሚገዛቸው ናቸው፡፡ ከዚህም የተነሣ ያላጠፋቸውን የእግዚአብሔርን ፍቅር እንድናደንቅ እንገድዳለን፤ በነቢዩ ሐጌ አማካይነት ሕዝቡ የእግዚአብሔርን ቤት ቸል በማለት ባማሩ ቤቶቻቸው ውስጥ በመኖራቸው እግዚአብሔር ያለውን ቅሬታ ገልጧል፡፡ ከአራት ባላነሱ ምዕራፎች ሕዝቡ በፍጹም እንቢተኝነት የእግዚአብሔርን ቃል ወደ ጎን በመተው ዝርያቸውን በጋብቻ ከእንግዶች ጋር እንደደባለቁ እናገኛለን/ዕዝ9፣10፤ ነህ.9 እና 13፡3፣23/፡፡ ሊቀካህኑ ኤልያሴብ እንኳን ሳይቀር በዚህ በደል ግንባር ቀደም ነበር፡፡ ነገሥታቶቻቸው ድሆችን አሠቃይተዋል፤ ለባርነትም ሸጠዋቸዋል፡፡ በአንዳንድ ሁኔታዎች በባቢሎን ወይም በፋርስ የቀሩት ከተመለሱት የሚሻሉ ናቸው፤ ለዚህም መርዶክዮስ ምስክር ነው፡፡ ሆኖም እግዚአብሔር የሕዝቡ ተወካዮች አድርጎ ስለሚያያቸው በአንድ በኩል ታሪካቸው እንዲወድቅ ቢፈቅድም በሌላ በኩል የሚረዷቸውን ነገሥታት እያስነሳላቸው ነቢያቱን በመላክ ተስፋውን ይሰጣቸው ነበር፡፡ ከምርኮ ከተመለሱት ጋር በተያያዘ መልኩ የተነገረላቸው ሌሎች ቢኖሩም ለምሳሌ በመጽሐፈ አስቴር እንደምናገኘው አጠቃላይ ሕዝቡንና ቅሬታዎችን ከጥፋት በማዳን ረገድ የተጠቀሱት ናቸው፡፡ ምንም እንኳን ድካምና ነቀፋ ቢኖራቸውም መታዘዛቸውን እግዚአብሔር ተቀብሎታል፡፡ አንዳንድ ከሚዘነጉት በቀር በምን ዓይነት ሁኔታ እግዚአብሔርን እንደፈቃዱ ሊያገለግሉ እንደሚገባቸውና እንዴት ማከናወን እንዳለባቸው እግዚአብሔርን ይጠይቁ ነበር፡፡ እንደ ሐሳቡ የተዘጋጀውን ብቸኛ የመሰብሰቢያ ስፍራ ማለትም «ስሙን በዚያ ያኖር ዘንድ ጌታ እግዚአብሔር ወደ መረጠው ስፍራ» ለመድረስ የቻሉበት መርሆም ይኸው ነው፤ «መታዘዝ ከመሥዋዕት ማዳመጥም የአውራ በግ ስብ ከማቅረብ ይበልጣል»/1ኛሳሙ15፡22/ የሚለው እውነት ለዘላለም የጸና ነውና፡፡
በአዲስ ኪዳን ያለው የመሰብሰቢያ ማዕከል
>በጥሞና የሚያነብ ሁሉ እንደሚያረጋግጠው በማቴዎስ ወንጌል ውስጥ ጌታ ኢየሱስ መንግሥቱን ሊመሠርት ወደ ሕዝቡ ወደ እስራኤል የመጣ ንጉሥ እንደሆነ ተገልጧል፡፡ በሐረገ ትውልዱም ልደቱ ከንጉሥ ዳዊት እንደሆነ ጎልቶ የተነገረ ሲሆን በምዕራፍ ሁለት ደግሞ የምሥራቅ ነገሥታት ለንጉሥነቱ ስጦታ ይዘው እንደመጡ እናነባለን፡፡
መንግሥቱም ምንም እንኳን በምድር ላይ ብትሆንም የምትመራው በሰማያዊ መርሆዎች በመሆኑ «መንግሥተ ሰማያት» ተብላ ተጠርታለች፡፡ በማቴ4፡17-25 ጌታ ኢየሱስ «መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ» በማለት የተናገረውን ኃይል የተሞላ ታላቅ መልእክት እናነባለን፡፡ ተአምራቱን በማየት ብዙ ሕዝብ በተከተሉት ጊዜ በተራራው ስብከት/ምዕራፍ5፣ 6 ና 7/ ጌታችን የመንግሥቱን መሠረታዊ ሕግጋት፣ የመንግሥቱን መርሆዎች ወይንም በትክክል ለማስቀመጥ የመንግሥቱ ተካፋዮች ሊኖራቸው ስለሚገቧቸው ባሕርያት አስተምሯል፡፡ ሆኖም እነዚህ መርሆዎች የአይሁድን የትዕቢት ሐሳቦች የሚቃወሙ በመሆናቸው ከምዕራፍ 8 እስከ 12 ባለው ክፍል ውስጥ ጌታችን በሕዝቡ እንደተነቀፈ እንመለከታለን፡፡ በምዕራፍ 13 ላይ ደግሞ የመንግሥቱ ሌላ ገጽታ ተገልጧል፤ ንጉሥዋ ለጊዜው የሌለባትን፣ እንክርዳዱ በስንዴ መካከል የተዘራባትን፣ ሁሉ እስኪቦካ ድረስ በሊጡ ውስጥ የተሸሸገ እርሾ ያለባትን መንግሥት እናያለን/1ቆሮ5፡6-8 ያነጻጽሩ/፡፡ ይህም ለአይሁድ ብቻ የተነገረ አይደለም፤ ምክንያቱም የእርሻው ቦታ ዓለም በሙሉ ነውና፡፡ በምዕራፍ 16 ላይ ደግሞ ሙሉ በሙሉ የተለየና አዲስ ስለሚመጣ ጉዳይ ተጽፎ እናገኛለን፤ ያውም በክርስቶስ የምትታነጸው ቤተክርስቲያን ወይም ጉባኤ ናት፡፡
ይህም እጅግ ጠቃሚው ነጥብ ነው፡፡ ጴጥሮስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ከመመስከሩም ሌላ እርሱ ክርስቶስ ሕይወት የሚሰጥ ኃይል ያለውና ራሱም ሕይወት ሰጪ ኃይል እንደሆነ መስክሯል፡፡ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ በመሆኑና በትንሣኤው የሲኦልን ደጆች በመሰባበር በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ በመገለጡ/ሮሜ1፡4/ የሕያው እግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን/1ኛጢሞ3፡15/ በራሱ መሠረትነት ላይ ያንጻል፡፡ እዚህ ላይ አዲስ መሠረት ተጥሏል፤ ሆኖም እስራኤል ጨርሶ አልተተወም፡፡ በተቀሩት የወንጌል ክፍሎችም «የሰው ልጅ» አንድ ቀን በክብር መንግሥቱን እንደሚመሠርት እናነባለን፡፡ ነገር ግን ለጊዜው የምእመናን ጉባኤ እስራኤልን በመተካት በምድር ላይ የእግዚአብሔር ምስክር ሆናለች/ማቴ21/፡፡
በማቴዎስ 18 ላይ ይህ ሐሳብ በሰፊው ተብራርቶ እናገኛለን፤ የሥነ ሥርዓት ውሳኔዎችም እንደ ቀድሞው ከምኲራብ ጋር የተያያዙ ሳይሆኑ ከምእመናን ጉባኤ ጋር የተያያዙ ናቸው /¬ማቴ18፡15-20፤ ዮሐ9፡22፣34/፡፡ የምእመናን ጉባኤ ወይንም የቤተክርስቲያን ሥልጣንም የተመሠረተበት እውነታ ወደ ኢየሱስ ስም መሰብሰቧና እርሱ በመካከሏ መገኘቱ ነው፡፡
እዚህ ላይ ጌታ ይህን የተናገረው ከዕርገቱ በኋላ ላለው ጊዜ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ለጥያቄዎች ሁሉ ራሱ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ በምዕራፍ 16 ላይ ደግሞ እንደተመለከትነው የእግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ ያልነበረችና ገና እንደምትታነጽ ሆኖ እናነባለን፤ 1ኛቆሮ12፡13 እና ሌሎችም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጌታ የምእመናንን ጉባኤ የመሠረተው በበዐለ ሃምሳ ዕለት/ሐ.ሥ.2/ እንደሆነ ያስተምሩናል፡፡
ማቴ18፡20 በአዲስ ኪዳን ጌታ የራሱ በሆኑት መካከል ሊገኝ ቃል የገባበት ብቸኛ ጥቅስ ነው፡፡ በእርግጥ ከጥንት ጀምሮ ከእያንዳንዱ ምእመን ጋር ለመሆን ቃል የገባ ቢሆንም ይህ ደግሞ ሙሉ በሙሉ የተለየ ነው፡፡ እዚህ ላይ ቃል የገባው ቀደም ሲል በትንቢት «በጉባኤ መካከል አመሰግንሃለሁ» ተብሎ በተነገረው መሠረት /መዝ22፡23/ ከሚሰበሰቡት መካከል እንደ አንዱ ሆኖ በመካከላቸው ሊገኝ ነው፡፡ ወደ ስሙ መሰብሰብም ለእርሱ መገኘት እንደ ቅድመ ሁኔታ የቀረበውም ለዚሁ ነው፡፡ ጉባኤ ሠርተው ለሚሰባሰቡት ደቀመዛሙርቱ ወደ ስሙ ከተሰበሰቡ በመካከላቸው ሊገኝ ቃል ገብቶላቸዋል፡፡
፡
ይህ ክፍል ብዙ ጊዜ የተሳሳተ ትርጉም የሚሰጠው ስለሆነ ትክክለኛውን ሐሳብ ለማግኘት ትኲረት ሰጥቶ ማብራራት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህም ጋር የጥቅሱን ትክክለኛ ትርጉም ለመረዳት የምንችለው ከጥቅሱ ጋር የተያያዘውን ሙሉውን ንባብ ስናነብ ብቻ መሆኑንም መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ ጥቅሱ የያዘው ቃል ከተነገረበት ቀዳሚና ተከታይ ሐሳብ ተገንጥሎ የሚተረጎም ትርጉም በቂ ያልሆነና የተሳሳተ ነው፡፡ ይህም ብዙ ጊዜ እንደሚደረገው ገንጥለን በመተርጎም የምንመኘውን ሁሉ ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ጥቅስ መጥቀስ ወደመቻል ይወስደናል፤ ይህም ወዮታ ውስጥ ይከተናል፡፡
በማቴ. 18 በሙሉ በትህትናና በጸጋ መንፈስ እንድንመላለስ ጌታ ያስተምረናል፡፡ ይህንንም ትምህርቱን ከቊጥር 15 ጀምሮ ወንድማችን ቢበድለን ምን ማድረግ እንዳለብንና እንዴት ተግባራዊ እንደምናደርገው ይገልጣል፡፡ በትህትና መንፈስ ከበደለን ወንድማችን ጋር ለመታረቅ የምናደርገው ጥረት ከንቱ ቢሆን ምን እናደርጋለን? ቀጥለን ወደ ማንስ እንሄዳለን? ለዚህም ጌታ መልስ ሰጥቷል፡፡ ለራሱና በራሱ ላይ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የመሠረታት ጉባኤው በወንድሞች መካከል የሚነሡ ጥያቄዎችን ሁሉ ልትዳኝ እንድትችል ሥልጣን ተሰጥቷታል፡፡ በምድር ላይ የምትሰጠው ውሳኔ፣ ማሰርና መፍታቷ በሰማይ ተቀባይነት ያለው፣ ሰማያዊ ድጋፍ የተሰጠውና በሰማይ የታወቀ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን በምድር ላይ በጸጋውና በእግዚአብሔር ላይ በመደገፍ ብትኖር በሰማይ ከሚኖር ከአብ ዘንድ የምትለምነው ሁሉ ይደረግላታል፡፡ ይህም ቃል ኪዳን የተሰጠበት ቅድመ ሁኔታ ለደቀመዛሙርቱ ግልጽ ይሆን ዘንድ ጌታ «ሁለት ወይም ሦስት በ[ወደ]S»* በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁ» በማለት ተናገረ፡፡ ቤተክርስቲያን በጌታ ኢየሱስ ስም ከተሰበሰበች እርሱ በመካከሏ ስለሚገኝ ውሳኔዎቿ በእርሱ ሥልጣን የተረጋገጡ ናቸው /1ኛቆሮ5፡4፣5 ይመልከቱ/፡፡
ሁለት ወይም ከዚያን በላይ የሆኑና በተለያዩ ቦታዎች የሚኖሩ ምእመናን በአንድ በተወሰነ ሰዓት በተወሰነ ጉዳይ ላይ ቢጸልዩ በማቴ18፡19 የተገለጠው ሐሳብ አይደግፋቸውም፡፡ በእርግጥ የእያንዳንዱን ክርስቲያን ጸሎት የሚቀበል እግዚአብሔር ጸሎታቸውን ይሰማል፤ ሆኖም ይህ ከቊጥር 19 ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፡፡ እንዲሁም ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ምእመናን በማናቸውም መልኩ ለመንፈሳዊ ነገር ወይም ለአምልኮ፣ ወይም ለስብከት ይሁን ለጸሎት ወይም በሌላ ጉዳይ ምክንያትነት ቢሰበሰቡ ወደ ጌታ ኢየሱስ ስም እስካልተሰበሰቡ ድረስ ስብሰባቸው ጌታ በመካከላቸው ከማይገኝባቸው ስብሰባዎች በማናቸውም ዓይነት መንገድ የተለየ አይደለም፡፡ የእግዚአብሔር ጉባኤ መሰብሰብ ያለባት የግድ በጌታ በኢየሱስ ስም ብቻ ነው፡፡ ጌታም የሰጠውን ተስፋ የሚፈጽመው ይህ ሲሟላ ነው፡፡
ጌታ በጉባኤ መካከል እንዲገኝ ሁለት ቅድመ ሁኔታዎች አሉ፡-
1ኛ. በማቴ 18 በቊጥር 17 ላይ የተጠቀሰችው የታወቀችው አንዲት ቤተክርስቲያን ናት እንጂ አንድነት የሌላቸው በርካታ አብያተክርስቲያናት አይደሉም፡፡ በምዕራፍ 16 ላይም የተጠቀሰችው ያችው አንዲት ቤተክርስቲያን ናት፡፡ የሕያው የእግዚአብሔር ጉባኤ አንዲት ናት/1ኛጢሞ3፡15/፡፡ ሁሉም በአንድ በተወሰነ ቦታ የሚኖሩ እውነተኛ ምእመናን በዚያ ስፍራ የአንዷ ጉባኤ፣ የአንዲቷ ቤተክርስቲያን አንድነት መግለጫ ናቸው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም «ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች ቤተክርስቲያን»፣ «በቆሮንቶስ ላለችው ለእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን»....ወዘተ እያለ ሲጽፍ የነበረው ከዚህ በመነሣት ነበር፡፡ ከቦታ ርቀት ወይም ከስፍራ ጥበት የተነሣ የአንዷ ቤተክርስቲያን ወይም የአማኞች ጉባኤ አካል የሆኑ ሌሎች ጉባኤዎች በተለያዩ አጥቢያዎች እንደሚገኙ እንጂ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ አብያተ ክርስቲያናት ስለመኖራቸው መጽሐፍ ቅዱስ አይገልጽም፡፡
አንድ ብቻ የሆነ የክርስቶስ አካል አለ፤ ስለሆነም ጌታ ሁለት ወይም ሦስት ሆነው በሚሰበሰቡት መካከል እንዲገኝ በቤተክርስቲያን አንድነት ላይ መሰባሰባቸው እጅግ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ የሆነበት ምክንያቱ ይህ ነው፡፡ በሚሰበሰቡበት ዕለት የጉባኤው አባላት ሁሉም ላይገኙ ይችላሉ፤ አንዳንዶች ሊደክሙ ወይም ሊታመሙ አለበለዚያም በሌላ ምክንያት ሊቀሩ ይችላሉ፡፡ ብዙዎች ሌሎች ደግሞ አንዲት የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ወይም ጉባኤ ከምትሰበሰብበት ምክንያት በተለየ መሠረት ላይ ለመሰብሰብ ሲሉ ራሳቸውን አርቀው ሊቀመጡ ይችላሉ፡፡ ይኸው መሠረት ጠባብ ይሆንባቸውና በአንዲት ቤተክርስቲያን ላይ ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎችን ይጨምራሉ፡፡ ነገር ግን ሁለት ወይም ሦስት በአንድ ስፍራ በጌታ ስም ቢሰባሰቡ የአንዲቷና ሁሉም አማኞች የሚሰባሰቡባት ቤተክርስቲያን አካል በመሆን ይሰባሰባሉ፡፡ ጥቂቶች ከመካከላቸው ቢቀሩ እንኳን በማዘን ፈንታ የእምነት ዐይናቸው ሁሉም በአንድነት የክርስቶስ አካል ብልቶች እንደሆኑ ያያል፤ በአንዲት ቤተክርስቲያን ተሰብስበዋልና፡፡
2ኛ. ሁለተኛው ቅድመ ሁኔታ አማኞች ወደ ጌታ ኢየሱስ ስም መሰብሰባቸው ነው፡፡ ስሙ የአማኞችን ስፍራ መግለጥ ለመሰብሰባቸውም ዋና ነጥብ መሆን ይኖርበታል፡፡ ወደዚህ ስም ከተሰበሰቡ ስሙ ሰብሳቢያቸው ነው፤ ይህ ማለት ሁሉንም ነገር የሚቆጣጠረው የጌታችን የኢየሱስ ስም ነው ማለት ነው፡፡ ስብሰባው ወዴት ማምራት እንዳለበትና የስብሰባው አካሄድም ምን መሆን እንዳለበት፣ የትኛው ስብሰባ መካሄድ እንዳለበት፣ አምልኮው እንዴት እንደሚከናወንና ከስብሰባው ጋር የተያያዙ ነገሮች ሁሉ እንዴት መመራት እንዳለባቸው በተሰብሳቢዎቹ መወሰን የለበትም፡፡ ጌታ ኢየሱስ ሁሉንም ሊቆጣጠር ይገባዋል፤ ወደ ስሙ የተሰበሰቡ ሁለት ወይም ሦስት ግን «ጌታ ሆይ ምን እናደርግልህ ዘንድ ትወዳለህ?» በማለት ከመጠየቅና ከማድረግ በቀር ሌላ ምንም ማድረግ የለባቸውም፡፡ ቃሉን በጥንቃቄ በማንበብ የግል አስተሳሰብን ወደ ጎን በመተውና ከክርክር በመራቅ «ሥርዓቱንና ፍርዱን»/ዘዳ12/ በሥራ ላይ ማዋል ይኖርባቸዋል፤ «ስለዚህ ርኲሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ፡፡ ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ»እንደተባለ/ያዕ1፡21-22/፡፡ ስለሆነም ምእመናን ወደ ስሙ በሚሰበሰቡበት ጊዜ ሁለት ወይም ሦስት ቢሆኑ እንኳን ጌታ በመካከላቸው ይገኛል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ በሚገኝበት ቦታ ታዳሚዎች መሆን ምንኛ ታላቅ ዕድል ነው! ስፍራውስ ምንኛ የተባረከ ነው! በአንጻሩም ጌታ ኢየሱስ ባለበት ስፍራ ተሰብስቦ እንደሆነ ወይም በራሱ ምርጫ ጌታ በመካከሏ በማይገኝባት ጉባኤ ተሰብስቦ ይገኝ እንደሆን ለይቶ ማወቅ በእያንዳንዱ ምእመን ላይ የተጣለ ምንኛ ታላቅ ኃላፊነት ነው!
በማቴ18፡20 ላይ የምናነበው የጌታ ቃል በቀጥታ በዘዳግም 12 የተጻፈውን ቃል ማለትም «አምላክም እግዚአብሔር ስሙን በዚያ ያኖር ዘንድ የመረጠው ስፍራ» የሚለውን ቃል እንድናስብ አያደርገንም? በዚህም በማቴዎስ 18ም ቢሆን «ስሙን» እንደመሰብሰቢያ ስፍራ ሆኖ እናገኛለን፡፡ ሙታን የሆኑ ኃጥኣንን ወደ ሕያዋን ድንጋዮች የሚቀይራቸውና ከእነርሱም ቤተክርስቲያኑን የሚሠራ ጌታችን ኢየሱስ/ማቴ16፡18፣ 1ኛጴጥ2፡4-5/ ጉባኤውን በስሙ ለመሰብሰብ በመካከሏም ሊገኝ ይፈልጋል፡፡ የጌታ ኢየሱስ ለሆኑት ሁሉ የሚሆን ብቸኛ የመሰብሰቢያ ስፍራ በዚህ ይገኛል፡፡ ያም ከስሞች ሁሉ በላይ የሆነ ስሙ ነው፡፡
በመንፈስና በእውነት ማምለክ
ማቴ18፡20ን እና ዘዳግም12ን ስናነፃፅር በሁለቱም ቦታ የተጠቀሱት ስፍራዎች አንድ ስለመሆናቸው ወይም ስላለመሆናቸው ጥያቄ ሊነሣ ይችላል፡፡ በዘዳግም የተጠቀሰው የጆኦግራፊ ስሙ ኢየሩሳሌም ተብሎ የተጠቀሰለትና የታወቀ ስፍራ ነው፡፡ በማቴ18፡20 ላይ የተጠቀሰውስ? መልሱ በዮሐ4፡20-26 ይገኛል፡፡
የሰማርያዋ ሴት ጌታ ኢየሱስ የሥነምግባር ማንነቷን ገልጦ በተናገራት ንግግር አማካይነት ነቢይ እንደሆነ ተናግራ ነበር፡፡ በሰማርያ ሰዎችና በአይሁድ መካከል ስለነበረው ውዝግብ ማለትም ለእግዚአብሔር ሊሰገድለት የሚገባው በኢየሩሳሌም ወይስ በገሪዛን ተራራ ስትል ጠይቃዋለች፡፡ ጌታም አወዛጋቢውን ጥያቄ ከእግዚአብሔር ቃል አኳያ መልሶላታል፡፡ ኢየሩሳሌም «የተመረጠች ስፍራ» ናት፡፡
ጌታ በብሉይ ኪዳን ሥርዓተ አምልኮ በመጀመር በመቀጠልም ከእርሱ ወደ ምድር መምጣት የተነሣ ነገሮች ሙሉ በሙሉ እንደተቀየሩ አሳይቷል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እስራኤል እርሱን ባለመቀበላቸው አሁን ቃል የተገባላቸውን የምድርን በረከቶች ፍጻሜ ያጡ ሲሆን ጌታ ግን ተስፋውንና በረከቱን ለተቀሩት የሰው ልጆች ጭምር ለዓለም ሁሉ በማድረግ/ማቴ13፡38/ ያመኑትን ከዓለም ጠርቶ ጉባዔውን ሰብስቧል/ማቴ16፡18/፡፡ የኋለኛው በረከት ምድራዊ/ሥጋዊ/ ሳይሆን መንፈሳዊ ነው፡፡ እርሱም በምድር ላይ በሞተው፣ ባረገውና በከበረው በጌታ ኢየሱስ ላይ የተመሠረተ በራሱ ሰማያዊና መንፈሳዊ አካል የሆነ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የሚኖርበት በረከት ነው /1ኛቆሮ3፡16/፡፡ የአካሉ ማለት የቤተክርስቲያኑ ብልት የሆኑት እግዚአብሔርን እንደ አምላክነቱ ማወቅ ብቻ ሳይሆን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባትና አምላክ የእነርሱም አባትና አምላክ እንደሆናቸው አውቀው ያመልኩታል¬፤ «አባ አባ» ብለው የሚጮኹበት የልጅነት መንፈስም አላቸው/ኤፌ1፡17፣ 3፡14፣ ዮሐ20፡17፣ ሮሜ8፡15/፡፡ ስለሆነም አምልኮአቸው ሙሉ በሙሉ የተለየ ነው፤ አብን በመንፈስና በእውነት ያመልኩታል፡፡
«በመንፈስ» የሚለው ቃል የተለወጠ የውስጥ ማንነትን ያመለክታል፡፡ በመንፈስ ማምለክ ሰው በምድር ላይ ከተለማመደው ተፈጥሮአዊ አስተሳሰብና ምድራዊ ጠባይ ማለትም ከእግዚአብሔር ለመገናኘት ሲባል ተለይቶ ወደተሰየመ ቦታ ከመሄድ፣ በምድር ላይ ከሚገኝ ውድና ክቡር ነገሮች በተሠራ ቤተመቅደስ ለመገልገል ከመሻት፣ ከምድር ፍሬ ሁሉ በሚቀርብ መሥዋዕት አማካይነት ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ከመሞከር፣ ውድ በሆኑ ጌጠኛ አልባሳትና ድንቅ በሆነ የሙዚቃ ቅንብር በመታገዝ ሰው ሊያቀርበው በሚችለው ምርጥና ከፍተኛ አገልግሎት እግዚአብሔርን ለማምለክ ከመጣርና በአጠቃላይ ምድራዊ ሰው በምድራዊ ነገሮች ምድራዊ ሐሳቦች ወደሌሉት አምላክ ከሚቀርብበት መንገድ መለየትና መራቅ ማለት ነው፡፡
ስለሆነም እውነተኞች ምእመናን የሚያመልኩት በተሟላ እውቀት የእግዚአብሔርን ማንነት ተረድተው ወደ እርሱ በመቅረብ መሆን ይኖርበታል፡፡ «እግዚአብሔር መንፈስ ነውና» እውነተኛ ምእመንም በአዲስና በዳግመኛ ልደት ባገኘው በአዲስ ሕይወት ኃይል ወደ እግዚአብሔር ይቀርባል/ዮሐ3፡5-8/፡፡ ይህም አሁን በሚታይና የሰማያዊ ነገሮች ምሳሌ በሆነ ነገር የሚከናወን ሳይሆን በመንፈስ የሚፈጸም ነው/ዕብ9፡23፣ 24/፡፡
>«በእውነት» ማምለክ ማለትም እግዚአብሔር ራሱን ለኛ ከገለጠበት መንገድ ጋር በመስማማት ማምለክ ማለት ነው፡፡ እስራኤላውያን የቃል ኪዳን አምላክ በሆነ በእግዚአብሔር ፊት በቆሙ ጊዜ እንደሆነው «ሊዳሰስ ወደሚችል ወደሚቃጠልም እሳት ወደ ጭጋግም ወደ ጨለማም ወደ ዐውሎ ነፋስም ወደ መለከት ድምፅም ወደ ቃሎችም ነገር» ሳይደርሱ «የሰሙትም ሌላ ቃል እንዳይጨመርባቸው» እንደለመኑት ሳይሆን በአባቱ ፊት እንደቆመ ልጅ ወደ እግዚአብሔር እንቀርባለን/ዕብ12፡18-21/፡፡ «አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና»/ዮሐ4፡23፣ ሮሜ8፡15፣ 1ኛዮሐ3፡1/፡፡
ይህም ለውጥ በዕብ.13፡10-16 ትኩረት ተሰጥቶበት እናገኛለን፤ የዕብራውያን መልእክት ሙሉ በሙሉ የሚያወሳው በሕጉና ከሕጉ ጋር በተያያዘው አምልኮ መካከል ስላለው ልዩነትና ግንኙነት እንዲሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በክርስቲያን አምልኮ ውስጥ ዋና ማዕከልና ራስ ስለመሆኑ ነው፡፡ እያንዳንዱ ምዕራፍ የሰማያዊው ጌታና የአገልግሎቱ ምድራዊ ምሳሌ የሆነው አሮጌው ኪዳን ወይም ብሉይ ኪዳን እንዳበቃና በምትኩ ጌታ ኢየሱስ ብቻ እንደቀረ ያሳያል፡፡ ስለሆነም የመልእክቱ መዝጊያ ምዕራፍ «ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም ያው ነው»/ዕብ13፡8/ በማለት እርሱ ብቻ ዘላለማዊ እንደሆነና ያሳየናል፡፡
ወደ እግዚአብሔር የሚወስደን መንገድ ባልተገለጠባት /ዕብ9፡8/ የድንኳን አገልግሎት የሚያገለግሉ አገልጋዮች ከክርስቲያን መሠዊያ ሊበሉ አይችሉም የሚለው የዕብ13፡10 ሐሳብም የተወሰደው ከዚህ ነው፡፡ «በኢየሱስ ደም ወደ ቅድስት ለመግባት ድፍረት» ያላቸው ብቻ ከዚህ መሠዊያ ሊበሉ ይችላሉ/ዕብ10፡19/፡፡ መንፈስ ቅዱስ በእያንዳንዱ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ መፈጸሙን እንደሚያረጋግጠው፣ ማንም ከጌታ ኢየሱስ ጋር ሊሆን የወደደ ቢኖር እርሱ ቀድሞውኑ በሰማይ ነው/ዕብ9፡12/፤ ወይም በዚህ ምድር ካለ ወደ እርሱ ወደ ሰፈሩ ውጭ ይወጣል/ዕብ13፡13/፡፡ ይህም ማለት ከምድራዊ የአምልኮ ሥርዓት ውጭ መውጣት ነው፡፡ ከዕብ13፡12 እንደምንመለከተው ያለጥርጥር መልእክቱ ለተጻፈላቸው የአይሁድ ክርስቲያኖች ሰፈር የተባለችው ቀድሞ በነበረው ሥርዓት እግዚአብሔር «ስሜን በዚያ አኖራለሁ» ብሎ ያላት የኢየሩሳሌም ከተማ እንደሆነች ግልጥ ነው፡፡ አሁን ግን ጌታ ኢየሱስ የእርሱ ለሆኑት ሁሉና ከብሉይ ኪዳን የአምልኮ አፈጻጸም ራሳቸውን ለለዩት በዙሪያው የሚሰበሰቡበት ማዕከላቸው ነው፡፡
በዕብ13፡10 ላይ ስለማይበላ መሥዋዕት እናነባለን፡፡ የኃጢአት ወይም የእሳት ቊርባን መሥዋዕት ቢሆን ካህናቱ ወይም ቤተሰቦቻቸው ብቻ ሊበሉት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ንጹሕ ካልሆነ ሰው በቀር ከደኅንነት መሥዋዕት ማንም እስራኤላዊ እንዲበላ ተፈቅዷል/ሌዋ6፡8 እስከ 7፡38/፤ ከደኅንነት መሥዋዕት ከፊሉ «ለእግዚአብሔር የቊርባን መብል ነው»/ሌዋ3፡11/፡፡ ከእርሱም የተረፈው ንጹሕ እስከሆነ ድረስ መሥዋዕቱን ላመጣው እስራኤላዊና ለሚሠዋው ካህን የሚሆን ነው፡፡ መሠዊያውም የእግዚአብሔር ገበታ ተብሏል/ሚል1፡7-14/፡፡ የክርስቲያኖችም መሠዊያም «የጌታ ማዕድ» ተብሏል/1ኛቆሮ10፡21/፤ ይህም በአጋጣሚ አይደለም¬፤ በብሉይ ኪዳን የነበረው የደኅንነት መሥዋዕትና ከእርሱ ጋር የተያያዘው የሚቃጠል መሥዋዕት በ1ኛ ቆሮ10 ለተገለጠው የጌታ እራት ምሳሌ በመሆኑ ነው/ዘጸ29፡19-33፣ ሌዋ8፡31/፡፡
በ1ኛ ቆሮ11 የጌታ እራት የተገለጠው ጌታ ራሱ መጀመሪያ ስለዚሁ በገለጠልን ትርጉም መሠረት ማለትም ለሞተልንና ለአዳነን ጌታ መታሰቢያ የሚደረግ እንደሆነ ነው፤ «ይህንንም ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ» ተብሎ እንደተጻፈ /ሉቃ22፡20/፡፡ ስለሆነም በጌታ እራት ለመሳተፍ ሁሉም ነገር በግል የሆነበት ምክንያትና ለግለሰቡ ሁኔታና ለምእመኑ ኃላፊነት ትኲረት መሰጠቱ ከዚህ የተነሣ ነው፡፡
በ1ኛ ቆሮ10፡16-22 ደግሞ ስለጌታ እራት የተለየ ገጽታ አለ፡፡ እዚህ ላይ የምንመለከተው በአዳኝነቱ በመሠዊያ ላይ የሞተውን ክርስቶስንና እንዲሁም አብረውት ካሉት ምእመናንና ከራሱም ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት እያደረገ ራሱን ከመሥዋዕቱ የሚመግብ መሥዋዕት አቅራቢ ነው፡፡ የተፈጸመው የማዳን ሥራ ለሚኖረው ኅብረት መገኘት ብቸኛ መሠረት በመሆኑ ደሙ በፍጹም ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ስፍራ ብቻ ተጠቅሷል፡፡ ይህም የሚደረገው ውህደት ወይም ኅብረት ቀዳሚ ስፍራ ስለሚይዝ ሌላው የግል የሆነ ሁሉ ጉዳይ ይወገዳል፡ ፡
በቊጥር 16 ላይ ጽዋውን ስንጠጣ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት እንደምናደርግ ተገልጧል፡፡ ይህ ደግሞ ምእመናን ሁሉ በእንጀራ መቊረስም ጭምር ከክርስቶስ ሥጋና ደም ጋር የሚያደርጉት መካፈል ነው፡፡ ያም የምንባርከው ጽዋና የምንቆርሰው እንጀራ ነው፡፡ የጌታን እራት የሚያከብሩ ምእመናን ሁሉ ከጌታ ጋርና እርስበርሳቸው ኅብረት ያደርጋሉ፡፡ ይኸው ሐሳብ በቊጥር 17 ላይ የበለጠ ዋጋ ተሰጥቶት በድጋሚ ተጠቅሷል፤ «አንድ እንጀራ ስለሆነ እኛ ብዙዎች ስንሆን አንድ ሥጋ ነን» ተብሎ ተብራርቷል፡፡ ስለዚህም የጌታን እራት ተሰብስበን በምናከብርበት ጊዜ በግልጥ ከጌታ ደምና ሥጋ ጋር ኅብረት እንደምናደርግ መግለጣችን ሲሆን አንድ እንጀራ የመቊረሳችንን ያህል ከሌሎች አማኞች ጋር ደግሞ አንድ የክርስቶስ አካል እንሆናለን/1ኛቆሮ12፡13/፡፡
በተከታታይ ቊጥሮች ደግሞ እነዚህን የተቀደሱ ነገሮች ካልተቀደሱት ነገሮች ጋር ልናነካካ እንደምንችል ተብራርቶ ተገልጧል፡፡ የአይሁድንና የአረማውያንን መሠዊያዎች እንደምሳሌ በመውሰድ ሐዋርያው መሥዋዕቱን የሚበሉ ከመሠዊያው ጋርና መሥዋዕቱ ከተሠዋለት አምላክ ጋር ኅብረት እንደሚያደርጉ ይገልጣል፡፡ በተጨማሪም ጠንከር ያለ የግሣፄ ቃል ሲጠቀም የጌታን ጽዋና የአጋንንትን ጽዋ ልትጠጡ አትችሉም፤ ከጌታ ማዕድና ከአጋንንት ማዕድ ልትካፈሉ አትችሉም ወይስ ጌታን እናስቀናውን? እኛስ ከእርሱ ይልቅ እንበረታለንን?» በማለት ጽፏል/1ኛቆሮ10፡17-22/፡፡ የጌታ ማዕድ ቅዱስ መሆን ለእግዚአብሔር ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነና ለዚያም የተቀደሰ ከበሬታ ልንሰጠው እንዲገባን ከዚህ ቃል ልንረዳ እንችላለን፡፡
በዚህም ክፍል የጌታን እራት በምናከብርበት ጊዜ ከሁሉም አማኞች ጋር አንድ መሆናችንን በማወቅ ማለትም በጽዋና በእንጀራ በመሳተፋችን አንድ የክርስቶስ አካል መሆናችንን እንገልጣለን፡፡ እንዲሁም የጌታን እራት ማክበር ያለብን በጌታ ገበታ ላይ ከጌታ ሐሳብ ጋር ከሚጋጭ ከማናቸውም ነገር ተለይተን መሆኑን ማረጋገጥ እንዳለብን ተመልክተናል፡፡ ለጌታ ማዕድ የሚሰበሰብ ጉባኤ በማቴ18፡20 እንዳለው አይደለምን? በዚህም ምእመናን የሚሰበሰቡት በፍጹም የቤተክርስቲያን አንድነት፣ ጌታ ራሱ የስብሰባው ሰብሳቢ በሆነበትና በማዕዱ ማን መካፈል እንዳለበት በሚወስንበት፣ ራሱም የጉባኤው ዋና ራስ በሆነበት በጌታ ገበታ ዙሪያ ነው፡፡
በውድቀትና በክህደት ዘመን መሰብሰብ
አሁን ያለንበት ዘመን በእምነት የሳቱ ሰዎች የሞሉበት /2ጢሞ4፡10፣ ዕብ6፡6፣ 1ዮሐ2፡18-19/፣ በእነርሱም አማካይነት ሙሴ ወደ ተራራ በወጣ ጊዜ እስራኤል ከአምልኮተ እግዚአብሔር ወደ አምልኮተ ጣዖት እንደገባ ብዙ ሕዝብ ወደ ስህተት የገባበት /ዘጸ32፡1፣ ዘዳ13፡13፣ መሳ2፡17፣ ነህ9፡26፣ ሐዋ.ሥራ7፡39/ ከሰማይ ከወረደውና ወደ ሰማይ ከወጣው ጌታ ዐይኑን በማንሣት ወደ ክህደት የሄደበት፣ በወንጌል ከተገለጠችው የክርስትና እምነት ወደ አይሁድ መሰል አምልኮ ፈቀቅ ያለበት የክህደት ዘመን ነው፡፡ ይህ ሁሉ እጅግ በበዛበት ሁኔታ ውስጥ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ተሰብስቦ እግዚአብሔርን ማገልገልና ማምለክ የሚቻለውስ እንዴት ነው?
የእግዚአብሔር ቤት የሆነች የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን /ጉባኤ/ በጌታ ኢየሱስ የተመሠረተችው ከሕያዋን ድንጋዮች ነው /ማቴ16፡18፣ 1ጴጥ2፡4-7/ ስለዚህም ያለነውር ናት፡፡ ሰማያዊው አናፂ የተበላሸ ሕንጻ ሊሠራ ይችላልን? ፈጽሞ ሊሆን አይችልም፡፡
በ1ኛ ቆሮ3፡9-17 ውስጥ ስለ እግዚአብሔር ቤት በተነገረበት ስፍራ ግን በጌታ ፈንታ ጳውሎስ ለእግዚአብሔር ቤት እንደ ብልሃተኛ አናፂ ተገልጾ እናገኛለን፡፡ እርሱም መልካም የሆነ መሠረትን መሠረተ፤ ሌሎች እርሱ በመሠረተው መሠረት ላይ እንዴት መገንባት እንዳለባቸው መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል፡፡ በኃላፊነት ለሰው የተተወው የእግዚአብሔር ቤት ስለሆነ እያንዳንዱ ሰው ስለሥራው ይጠየቅበታል፡፡ የእያንዳንዱ ሥራ በአምላክ የመፈተሻ መንገድ በእሳት ይፈተናል፡፡ የሰዎችንም የሥራ ውጤት ዛሬ በክርስትናው አለም እናያለን፡፡ በርካታ ሕንጻዎች ከሕያዋን ድንጋዮች/በመንፈስ ቅዱስ ዳግመኛ ከተወለዱ አማኞች/ ይልቅ በይበልጥ ከሙታን ነገሮች/የስምና የሐሰት ከሆኑ ክርስቲያኖች/ የተሠሩ ናቸው፡፡ አንዳንድ ግንበኞች መሠረቱን በማጥቃት ህንጻውን ለማፍረስ ጥረዋል፡፡ በዚህም ቢሆን በታሪክ እንደነበረው ሁሉ ሰው ከእግዚአብሔር የተሰጠውን የሚያፈርስ ሆኖ እናያለን፡፡
">መንፈስ ቅዱስ ግን በሐዋርያው ጳውሎስ አማካይነት «እያንዳንዱ ግን በእርሱ ላይ እንዴት እንደሚያንጽ ይጠንቀቅ» በማለት ያስጠነቅቃቸዋል፡፡ ጳውሎስ እንደ ብልሃተኛ አናፂ ኢየሱስ ክርስቶስን መሠረት አድርጎ መሥርቷል፤ ሌሎች ደግሞ በዚህ መሠረት ላይ ያንጻሉ፡፡ ይህም በሦስት መንገዶች ሊሠራ ይችላል፡፡
1ኛ. በተመሠረተው መሠረት ላይ የእሳትን ፈተና በሚቋቋሙ «በጥሩ ዕቃዎች በወርቅ በብር ወይም በከበረ ድንጋይ» ማነፅ ሲሆን እንደዚህ የሚያደርጉ ሽልማት ያገኛሉ፡፡
2ኛ. በዚሁ መሠረት ላይ የእሳትን ፈተና በማይቋቋሙት ነገሮች «በእንጨት በሣር ወይም በአገዳ» ማነፅ ሲሆን እነዚህም በፈተና ወቅት በእሳት ስለሚነዱ ሕንጻውም ይወድማል፤ ግንባታው የማይጠቅም ከመሆኑም በላይ ሕንጻው ጤናማ የሆነ ሌላ ሕንጻ እንዳይገነባ ቦታ በመያዝ እንቅፋት ሆኗል፡፡ አናፂው ሽልማት የሚያጣ ሲሆን እርሱ ራሱ ግን ይድናል፤ «ነገር ግን በእሳት እንደሚድን» ይሆናል፤ አገልግሎቱ ዋጋ የሌለው በመሆኑ በእግዚአብሔር ፊት ባዶ እጁን ይቆማል፡፡
ሦስተኛው ዓይነት ሕንጻ ሙሉ በሙሉ በሌላ መሠረት ላይ የሚታነፀው ሲሆን ከኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ መሠረት ጽናት ስለሌለውና እግዚአብሔርም ስለማይቀበለው ሕንጻውና በላዩ የተሠራበት መልካም ሥራ እንኳን ሳይቀር አብሮ ይፈርሳል፡፡ በእንደእነዚህ ዓይነቶቹ አናፂዎች ላይ አስፈሪ የእግዚአብሔር ፍርድ አለ፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቤት የሆነውን ሰው ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጭ በሚፈርስ መሠረት ላይ መሥርተውት እንዲፈርስ አድርገዋልና ነው፡፡ «ማንም የእግዚአብሔርን ቤተመቅደስ ቢያፈርስ እርሱን እግዚአብሔር ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ ቅዱስ ነውና ያውም እናንተ ናችሁ»/1ኛቆሮ3፡17/፡፡
በ1ኛይቱ የጢሞቴዎስ መልእክት ላይ እንደምንመለከተው የእግዚአብሔር ቤት በነጳውሎስ እና ሌሎች ታማኝ ሠራተኞች ቀደም ሲል እንደታነፀው በሙሉ ክብሩ እንደነበር እናነባለን፡፡ ምንም እንኳን የስህተት ትምህርትና ሌሎች አደጋዎች ሊመጡ እንዳሉ በትንቢት ቢነገርም/1ኛጢሞ4፡1/ ቤቱ «የእውነት ዓምድና መሠረት»/1ኛጢሞ3፡15/ ተብሎ ተጠርቷል፡፡ ምእመንም በዚህ ቤት ውስጥ እንዴት መመላለስ እንደሚገባው መመሪያ ተሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል ለመጨረሻ ጊዜ በጳውሎስ በተጻፈው በሁለተኛው የጢሞቴዎስ መልእክት ውስጥ ነገሮች ተለውጠው እናገኛለን፡፡ ይህ መልእክት ሲጻፍ በትንቢት የተነገረለት ክፋት አድጎ በአንጻሩም ምእመን እንዴት ሊቋቋመው እንደሚችል የተሰጠ መመሪያ እናነባለን፡፡ በ1ቆሮ3 ላይ የተገለጡት የስህተት አናፂዎች በዚህ ተከሥተዋል/2ጢሞ4፡6-18/፤ የስም ክርስቲያኖች ታይተዋል/2ጢሞ3፡5/፤ በእስያ ያሉት ሁሉ በጳውሎስ ላይ ፊታቸውን አዙረውበታል/2ጢሞ1፡15/፤ በሙግቱ ወቅትም እስረኛ ሆኖ አንድም እንኳ አልደረሰለትም/2ጢሞ4፡16/፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በሐዋ.ሥራ2፡42-47 አዲስ ስለተወለደችው ቤተክርስቲያን ውብ ሥዕል እናያለን፤ ይኸውም «ያመኑትም ሁሉ አብረው ነበሩ» እንደዚሁም «ከሌሎችም አንድ ስንኳ ሊተባበራቸው የሚደፍር አልነበረም»/ሐዋ.ሥራ 5፡13/፡፡ እያንዳንዱ ሰው አማኝ እንደሆነና እንዳልሆነ ይታወቃል፤ በክርስቶስ ያለውን እምነት የሚመሰክር ሁሉ ክርስቲያን ነበር፤ ሆኖም ጳውሎስ 2ኛውን መልእክቱን ለጢሞቴዎስ ሲጽፍለት ነገሮች በነበሩበት መልካቸው አልቆዩም፡፡ በጥፋት መካከል የሚኖር ምእመን በእርግጥ ማን የጌታ እንደሆነና እንዳልሆነ ሊያስተውል እንዴት ይችላል? የእግዚአብሔር መልስ ይህ ነው፤ «ጌታ ለእርሱ የሆኑትን ያውቃል»/2ጢሞ2፡19-23/፡፡ ሰው ግን ሊያውቃቸው አይችልም፡፡ ብዙዎች ነን በሚሉበት ሁኔታ ማን ዳግመኛ እንደተወለደ ለሰው ማወቅ አይቻለውም፤ አስፈላጊውም አይደለም፡፡ ሰው ያንን ልብንና ላሊትን ለሚመረምር አምላክ መተው ይኖርበታል፡፡ ምንኛ የሚያጽናና እና ዕረፍት የሚሰጥ ሐሳብ ነው! ሰው ክርስቲያን ነን ስለሚሉት ስለሌሎች ሰዎች ትክክለኛ ማንነት አያውቅም፤ በጌታ ፊት ግን ያለጥርጥር ይታወቃሉ፤ እርሱ ማንንም አይዘነጋም፡፡
ይህም ማለት ምንም ነገር እንደሌለ በግዴለሽነት መመላለስ አለብን ማለት አይደለም፡፡ ክህደት አለና በጠባያችን ይህንን ከግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብናል፡፡ ማን የጌታ ወገን እንደሆነ መፍረድን ለእግዚአብሔር ትተን ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ «የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ከዓመፅ ይራቅ»/2ጢሞ2፡19/ በማለት የሚናገረንን ልናደምጥ ይገባናል፡፡
ከ2ጢሞ2፡20 ጀምሮ ባሉት ቊጥሮች በዚህ ምድር ያለው የእግዚአብሔር ቤት በክህደት ጊዜ የወርቅና የብር ብቻ ሳይሆን የእንጨትና የሸክላም ዕቃ ካለው ትልቅ ቤት ጋር ተነጻጽሮ ተገልጧል፡፡ አንዳንድ ዕቃዎች ለክብር ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ ለውርደት ናቸው፡፡ ቤቱን እንዳለ መተው አይቻለንም፤ ይህን ማድረግ ማለት ደግሞ ከክርስትና በመውጣት ወደ አይሁድ ሃይማኖት ወይም ወደ አረማዊነት መግባት ነው፡፡ የከበረ፣ የተቀደሰ፣ ለጌታ የሚጠቅምና ለበጎ ሥራም የተዘጋጀ ዕቃ እንድንሆን በቤቱ ውስጥ ካሉት ከውርደት ዕቃዎች ራሳችንን ማንጻት ያሻናል፡፡ ከሚታይ እድፍ ራሳችንን በማንጻት ጀምረን በመቀጠልም ውስጣችንን ማንጻት አለብን፡፡ «ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት በመሸሽ»፣ «በንጹሕ ልብ የጌታን ስም ከሚጠሩ ጋር» ኅብረት ማድረግ ይኖርብናል፡፡
ሆኖም እዚህ ላይ የስም ክርስቲያኖች የውርደት ዕቃ ሌሎች አማኞች የክብር ዕቃ ናቸው ተብሎ እንዳልተጠቀሰ ልብ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ በእርግጥ የወርቅ ዕቃዎችና የሸክላ ዕቃዎች አሉ፤ የክብር ዕቃ ለመሆናችን ግን መለኪያው «ማንም ራሱን ከእነዚህ ቢያነጻ የክብር ዕቃ ይሆናል» የሚለውን የእግዚአብሔር ቃል በመከተል ከውርደት ዕቃዎች ራሳችንን መለየታችን ነው፡፡
በ2ኛጢሞ2 ውስጥ ቅራኔው በሚያምኑና በማያምኑት መካከል ሳይሆን በታማኝ አገልጋዮችና ታማኝ ባልሆኑ አገልጋዮች መካከል ነበር፡፡ በቊጥር 2 ላይ የታመኑ ሰዎች፣ በቊጥር 3 ላይ በጎ ወታደር ወዘተ....ተብሎ ሲጠቀስ/4-6፣ 11-13፣ 15-18/ በምዕራፉ ውስጥ በሙሉ ስለአማኞች የተጠቀሰው ሁለት ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ይህም እነዚህ ሰዎች ቢያንስ ቢያንስ አማኞች መሆናቸው ግልጥ እንዲሆን ነው፡፡
ከቊጥር 16 እስከ 18 ባለው ክፍል ውስጥ የተጠቀሱት ሄሜኔዎስና ፊሊጦስም ሆኑ ሌሎች በእነርሱ ትምህርት የተበከሉ ሰዎች ኢአማንያን አይደሉም፤ ይልቁንም ሥራቸው አደገኛ ስለሆነ «መርከብ አለመሪ እንደሚጠፋ በእምነት ነገር የጠፉ» ታማኝ ያልሆኑ አገልጋዮች ማለትም ከትክክለኛው የክርስቲያን እውነት ፈቀቅ ያሉ ናቸው፡፡ ከቊጥር 20 እስከ 26 ባለው ክፍል የተነገረውም ቢሆን ስለሚያምኑ ወይንም ስለማያምኑ ሰዎች ሳይሆን ስለታማኝ አገልጋዮችና ታማኝ ስላልሆኑ አገልጋዮች፣ ስለክብር ዕቃና ስለውርደት ዕቃ ነው፡፡
ዕቃው የተሠራበት ነገር ሳይሆን ዋናው ቁምነገር ዕቃው ለክብር መዋል አለመዋሉ ነው፡፡ ያልነጻ ዕቃ ለክብር አይሆንም፡፡ የወርቅ ይሁን የብር ዕቃ ቆሻሻ ከሆነ ወይም በፋንድያ ላይ ከተጣለ ሳይጸዳ በቤታችን ውስጥ በሚታይ ቦታ ብንገልጠው ለክብራችን አይሆንም፡፡ ሳይታጠብም በቤታችን ውስጥ በሳሎን ብናስቀምጠው ለቤቱ ውርደት ነው፡፡ የክብር ዕቃ ማለት የነጻ ዕቃ ማለት ነው፡፡ ዋናው ቁምነገር ባልዳነ ኃጢአተኛ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ የሚሠራው ሥራ ሳይሆን እያንዳንዱ ሰው ራሱን ክርስቲያን ነኝ ብሎ ሲጠራ ሊሰማው የሚገባው ኃላፊነት ነው፡፡ «ማንም ራሱን ከእነዚህ ቢያነጻ» የጌታው ስም የሚከብርበት የክብር ዕቃ ታማኝም አገልጋይ ነው፡፡
በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ራሳቸውን በማያነጹ ዕቃዎች መካከል አማኞች ይኑሩ አይኑሩ የኛ ኃላፊነት አይደለም፡፡ ያንን ጌታ ይፈርዳል፤ ምክንያቱም «ጌታ ለእርሱ የሆኑትን ያውቃል» በመካከላቸውም ብዙ አማኞች ስላሉ ስለእምነታቸው ጌታን እያመሰገኑ በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ አማኞች ለውርደት ከሆኑት ዕቃዎች ጋር ባላቸው ግንኙነት ራሳቸው ጌታን የሚያዋርዱ መሆናቸውን በማሰብ ልናለቅስላቸው ይገባል፡፡ ይህም ያስፈለገበት ምክንያት ጌታ ለብዙ በጎ ሥራዎች ሊጠቀምባቸው የሚችለው በቊጥር 21 መሠረት ራሳቸውን ለውርደት ከሆኑት ዕቃዎች ያነጹትን ብቻ ነው፡፡ እነርሱም ራሳቸውን «ለበጎ ሥራ ሁሉ» ያዘጋጁ ናቸው፡፡
በዚህ ክፍል ውስጥ የተጠቀሰው ራስን ማንጻት ራስን ከተጠቀሱት የውርደት ዕቃዎች መለየት ማለት ነው፡፡ ይህም ራስን የመለየት ሂደት መጀመሪያ ከውጭ ቀጥሎ ከውስጥ መሆን እንዳለበት መገንዘብ ይቻላል፡፡ ሆኖም ውስጣችንን ካጸዳን ከክፉም ከራቅን ውጫዊው ብዙም አስፈላጊ አይመስለንም፡፡ እግዚአብሔር ግን ቅድሚያ የሚሰጠው ለውጫዊው መንጻት ነው፡፡ ይህም ማለት ሰው አስቀድሞ ከእነዚህ የውርደት ዕቃ ከተባሉ ሰዎች ራሱን ማራቅ አለበት፤ ቀጥሎም የግሉን ሕይወት በእግዚአብሔር ቃል አማካይነት ያነጻል፡፡ ከበደል ጋር ከተያያዘ ባልጀርነታቸው ራሳችንን ማራቅ፣ ከእነርሱ ጋር ያለንን በጎ ያልሆነውን ግንኙነት ማቋረጥ፣ ከስህተት ትምህርታቸውና በኃጢአታቸው ከምንጠመድበት አካባቢና ኅብረት ራስን ማግለል ቀዳሚና የመጀመሪያው ራስን ከውርደት ዕቃዎች የማንጻት ሂደት ሲሆን ይህም ውጫዊው ወይም አፍአዊ ራስን የማንጻት ተግባር ነው፡፡ ይህም ሲባል ለእግዚአብሔር ምስክር ከምንሆንበት ከዚህ ዓለም ርቀንና በተወሰኑ ስፍራዎች የራሳችንን ደሴቶች ፈጥረን ተለይተን መኖር ማለት አይደለም፡፡ በኃጢአት የወደቀ ሰው ምንም እንኳን ኃጢአቱን ለመተው ቢወስንም ኃጢአት መሥራትን ለማቋረጥ የግድ ከሚፈተንባቸው ነገሮች ራሱን መለየት ይኖርበታል፡፡ ስለዚህም ስናስብ ትክክለኛነቱን ግልጽ ሆኖ እናገኛለን፡፡ ውጫችንን ለማንጻት ፈቃደኞች ካልሆንን ውስጣችንን ለማንጻት እንዴት ይቻለናል? ራሳችንን ከውስጥ ማንጻት ቀርቶ ንጹሕ ባልሆነ አካባቢ ንጹሕ ሆኖ መቆየት በራሱ ምን ያህል የሚያስቸግር ነው!
በሌላ በኩል ደግሞ «ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ሽሽ» እንደተባለ ውጫችንን አንጽተን ውስጣችንን ማሳዳፍም በራሱ እጅግ የከፋ ነው¬፤ ይህም ማስመሰል ነው፡፡ ራሳችን ከውጭም ከውስጥም ካጠራን በኋላ በንጹሕ ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር ጽድቅን፣ እምነትን፣ ፍቅርን፣ ሰላምን አጥብቀን መከተል እንችላለን/ቊ.22/፡፡ እነዚህም እንድንከተላቸው የተበረታታንባቸው ድንቅ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች ናቸው፡፡
ለጌታ በመታዘዝ ከነውረኞች ራሳችንን ከለየን በኋላ በዚህ በተለየንበት ጠባብ መንገድ የምንሄደው ብቻችንን ሳይሆን «በንጹሕ ልብ ጌታን ከሚጠሩት ጋር» ነው፡፡ የእነዚህም ማንነት ቀደም ብሎ ባለው ቊጥር በግልጥ ተቀምጧል፤ እነርሱም ለውርደት ከሆኑት ዕቃዎች ራሳቸውን የለዩና ውስጣቸውን ያጠሩ የክብር ዕቃዎች ናቸው፡፡
ለጌታ በመታዘዝ ከነውረኞች ራሳችንን ከለየን በኋላ በዚህ በተለየንበት ጠባብ መንገድ የምንሄደው ብቻችንን ሳይሆን «በንጹሕ ልብ ጌታን ከሚጠሩት ጋር» ነው፡፡ የእነዚህም ማንነት ቀደም ብሎ ባለው ቊጥር በግልጥ ተቀምጧል፤ እነርሱም ለውርደት ከሆኑት ዕቃዎች ራሳቸውን የለዩና ውስጣቸውን ያጠሩ የክብር ዕቃዎች ናቸው፡፡
እዚህ ላይ ፍርድን ልንመሠርት ኃላፊነት አለብን፤ ከእግዚአብሔር ሕይወት ያላገኘ ሰው «ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ» ሊሆን ይችላልን? ከዚህም በላይ ለማያምን ሰው ውስጡንና ውጭውን ለማጥራት አዳጋች ይሆንበታል፡፡ በዚህ መልኩ አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ሕይወት እንዳለውና እንደሌለው ለመፍረድ ኃላፊነት አለብን፤ ይህንን ለማድረግ ኃላፊነት እንዳለን የሚክዱ አሉ፡፡ ሊያደርጉት የማይችሉትን እግዚአብሔር ለልጆቹ አዟልን? ይህንን ለማለትስ እንደፍራለንን? በእርግጥ አንችልም፡፡ በጌታ በሆኑ፣ የክርስትና ሕይወት ልምምድ ባላቸው ክርስቲያኖችና በመንፈስ ቅዱስ በተቃኘ መረዳት አማካይነት አዲስ የእምነት ሕይወት በውስጣችን እንዳለን ተለይቶ ከታወቀ በግልጥ ሕይወት ያለበትንና ሞት ያለበትን ለይተን ማወቅ እንችላለን፡፡
መንፈሳዊ ውድቀት ባለበት ዘመን አማኝ ነኝ ማለት ብቻውን ማንነትን የሚገልጥ አይደለም፤ ነኝ የሚል ማንም ቢኖር በእንደዚህ ዓይነቱ ጊዜ ራሱን ማረጋገጥ አለበት፡፡ ስለዚህም በዕዝራ ዘመን በትውልድ መጽሐፍ ስማቸው ተጽፎ ያልተገኘላቸው ካህናት «ከክህነት ተከለከሉ»/ዕዝ2፡62/ «አንተ እምነት አለህ እኔም ሥራ አለኝ እምነትህን ከሥራም ለይተህ አሳየኝ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ»/ያዕ2፡18/ በሚለው መሠረት ከጌታ ጋር በኖሩ ክርስቲያኖች የሚታወቅ ከሕይወት ጋር የተዋሃደ እምነት ካለን በኛ የመለኮት ሕይወት እንዳለ የተረጋገጠ ነው፡፡ ሆኖም ከድክመት የተነሣ የሰው ትክክለኛ ማንነት ሊታወቅ ባይችልም እንኳን «ጌታ ለእርሱ የሆኑትን ያውቃል»፡፡ እኛም በሰውየው ትክክለኛ ማንነት መፍረድ አንችልም፤ ነገር ግን እንደ ክብር ዕቃ ልንቀበለው አይገባም/ዕዝ2፡59-63/፡፡
ስለዚህም ራሳችንን ንጹሕ ካልሆኑት ሁሉ ለይተን በንጹሕ ልብ ጌታን ከሚጠሩት ጋር በመቀላቀል የጌታን ትእዛዛት መከተል እንችላለን፡፡ ከሰፈር ውጭ ወደ እርሱ ወጥተናል/ዕብ13፡13/ «ከመጀመሪያው ወደነበረው» መመለስ እንችላለን/1ዮሐ1፡1፣ 2፡7፣ 2፡24፣ 2ኛዮሐ5፣6/፤ ሁለት ወይም ሦስት እንኳን ብንሆን በመንፈስ ቅዱስ በጌታ በኢየሱስ ስም ተሰብስበን በእርሱ በመካከላችን መገኘት እየተደሰትን መሰባሰብ እንችላለን/ማቴ18፡20/፤ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን እንናገራለን/1ኛቆሮ11፡26/ ቃሉን ጠብቀን ስሙን ሳንክድ በትዕግሥት እንኖራለን/ራእ3፡8-11/፡፡ ድንቅ የሆነውም ተስፋው «እነሆ ቶሎ ብዬ እመጣለሁ ማንም አክሊልህን እንዳይወስድብህ ያለህን አጽንተህ ያዝ»ይላል/ራእ3፡11/፡፡
በመንፈሳዊ ውድቀት ጊዜም ለእግዚአብሔር ልጆች የመሰብሰቢያ ስፍራ መኖሩ እውነት ነው፤ ያም «በንጹሕም ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር» በቤተክርስቲያን አንድነት፣ ከሰፈር ውጭ፣ በጌታ ማዕድ ዙሪያና ጌታ ኢየሱስ የራሱ በሆኑት መካከል የሚገኝበት ስፍራ ነው፡፡