ንሰሓ  


1. ንስሐ


ልባቸው በቃሉ ተነክቶ «ወንድሞች ሆይ ምን እናድርግ?» ላሉት ሰዎች በመጀመሪያ የተሰጣቸው ምላሽ «ንስሐ ግቡ» የሚል ነው፡፡ «ንስሐ» የሚለው ቃል አማኞች ከሥጋ ድካም የተነሳ ኃጢአትን በሚሠሩ ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ኅብረት የሚያድሱበትን መንገድ ጭምርም የሚያመለከት ሲሆን በዚህ ስፍራ ላይ ግን ክርስቶስን ላላመኑና ላልተከተሉ ሰዎች የቀረበ ጥሪ ነው፤ ይህም ንስሐ ያላመኑ ሰዎች ያለክርስቶስ በነበሩበት ባለፈው ዘመን ሁሉ ተጸጽተውና በራሳቸው ፈርደው ወደ ጌታ ዘወር እንዲሉ የሚያደርግ ነው፡፡ በሮሜ.3፡11 ላይ «ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ» ሲል በቊ.23 ላይ ደግሞ «ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሏቸዋል» ይላል፡፡ በኤፌ.2፡1 ላይም «በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ» ተብሎ ተጽፏል፡፡ ስለዚህ ማንኛውም ሰው ኢየሱስን ካላመነ ኃጢአተኛ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ አስረግጦ ይናገራል፡፡ ኃጢአት ወደ ዓለም የገባው በአንድ ሰው በአዳም በኩል መሆኑን ሲናገርም «ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ፣ በኃጢአትም ሞት፤ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ፡፡» ይላል /ሮሜ5፡12/፤ ስለዚህ ኃጢአት በሰው ውስጥ ከመወለዱ ጀምሮ አብሮት የሚኖር ለእግዚአብሔር ያለመታዘዝ ጠባይ ነው፤ በዚህ ጠባዩም በሐሳብ፣ በመናገርም ሆነ በተግባር የሚሠራው ኃጢአት አለ፤ ከዚህ ሁሉ የሚበልጠው ኃጢአት ግን ከኃጢአት የሚያድነውን አዳኝ ኢየሱስን አለማመን ነው፤ ጌታ ራሱ በእርሱ አለማመን ኃጢአት መሆኑን ሲናገር «እኔ እንደሆንሁ ባታምኑ በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁ» ብሏል /ዮሐ.8፡24/፤ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ ዓለምን ስለኃጢአት የሚወቅስበትን ምክንያት ኢየሱስ ሲናገር «ስለኃጢአት በእኔ ስለማያምኑ ነው» ብሏል /ዮሐ.16፡10/፡፡

ሰዎች እንደ አሕዛብ ያለ ሕግ ቢኖሩ ወይም እንደ እስራኤል ሰዎች ከሕግ በታች እንኳ ሆነው ቢኖሩ ኢየሱስን ካላመኑ ከኃጢአት በታች መሆናቸው የማይቀር ነው፤ በመሆኑም «ንስሐ ግቡ» የሚለው መልእክት በኢየሱስ ያላመኑትን ሁሉንም ዓይነት ሰዎችን ይመለከታል፡፡ ይህም ንስሐ እነዚህ ሰዎች በኃጢአታቸው መፍረዳቸውን የሚገልጽ ሲሆን ይህም ኢየሱስን ሳያምኑ በኃጢአት በኖሩበት ባለፈው ኑሮአቸው ተጸጽተው ከዚህ በኋላ ግን ኢየሱስን አምነው ለመከተል መወሰናቸውን የሚያመለክት ነው፤ ስለሆነም ንስሐና በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን እርስ በእርሳቸው የተያያዙና የማይነጣጠሉ ናቸው፡፡ ንስሐ ኢየሱስን ወደማመን የሚያደርስ ነውና፤ ይህም የሁለቱ ተያያዥነት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በማር.1፡15 ላይ «ዘመኑ ተፈጸመ፤ ንስሐ ግቡ በወንጌልም እመኑ» ብሎ በተናገረው ቃል ውስጥ ይታያል፤ እንደዚሁም ሐዋርያው ጳውሎስ «ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ንስሐንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ለአይሁድና ለግሪክ ሰዎች እየመሰከርሁ በጉባኤም በየቤታችሁም አወራሁላችሁና አስተማርኋችሁ እንጂ ከሚጠቅማችሁ ነገር አንዳች ስንኳ አላስቀረሁባችሁም» ብሎ ለኤፌሶን ቤተክርስቲያን ሽማግሌዎች በተናገረው ቃል ውስጥ ንስሐንና በኢየሱስ ማመንን በአንድ ላይ አያይዞ የተናገረ መሆኑን እናያለን /የሐ.ሥ.20፡21/፡፡ በእርግጥም ኢየሱስን ባለማመን ባሳለፈው ዘመን ከኃጢአት በታች እንደኖረ የተሰማውና በዚህም ተጸጽቶ ንስሐ የሚገባ አንድ ሰው ወዲያውኑ ኢየሱስን ወደማመን ሊመጣ ይገባዋል፤ ኢየሱስ ከኃጢአት የሚያድን ብቸኛ አዳጅ ነውና፡፡ ይህን መልእክት ስታነቡም ክርስቶስን ካለማመናችሁ የተነሣ በኃጢአት እየኖራችሁ እንዳለ የተረዳችሁና በወንጌል ቃል ልባችሁ ተነክቶ ምን እናድርግ የምትሉ ሁሉ በኃጢአታችሁ እንዳትሞቱ አሁኑኑ ንስሐ ግቡ፤ በኢየሱስ እመኑ እንላለን፡፡


Amharic Bible-|- The Holy Bible [King James Version]