መግቢያ
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ «የአዲስ ኪዳን መካከለኛ» የሚለውን ቃል ስናገኝ ብዙውን ጊዜ ኅሊናችን የቃሉን ትክክለኛ ትርጉም ለማወቅ ይፈልጋል፡፡ በዚህ ርእስ ሥር ያለውን እውነተኛ አስተምህሮ ለመረዳት የብዙዎች ጥማት ነው፡፡ የዚህም መሠረታዊ ምክንያቱ ብዙዎች በየአካባቢያቸው በዚህ ርእስ ሥር የሚያጋጥማቸው ክርክርና በየመድረኩ የሚያደምጡት የተለያየ አመለካከት ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ያውቃሉ ተብሎ እምነት የሚጣልባቸው ሰዎች ሲጠየቁ የሚሰጡት መልስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ሲተያይ ተቃራኒ በሚሆን ጊዜ በጥያቄ የተሞላ ኅሊና ዕረፍት ሳያገኝ ይቀራል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ጥያቄውና ክርክሩ ምናልባት ሊፈጥር የሚችለው መለያየት በጣም ያሳሰባቸው ሰዎች ይህ ርእስ ጨርሶ ሳይነሳ እንዲታለፍና ሁልጊዜ በሌሎች ርእሶች ላይ ብቻ ተወስነው ስለክርስቲያናዊ ሕይወት በመነጋገር መቀጠል ይፈልጋሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡ ሰዎች ግን ጥያቄ ያነሣሉ፤ ለሚነሡ ጥያቄዎችም መልስ ማቅረቡ ግዴታ ስለሚሆን ርእሱን መሸሽና በዘዴ ማለፍ የሚቻል አልሆነም፡፡ በመሆኑም ለዚህ ችግር ዋነኛ መፍትሔው «የአዲስ ኪዳን መካከለኛ» ማለት ምን ማለት እንደሆነ፣ «የአዲስ ኪዳን መካከለኛ» ማን እንደሆነ፣ የመካከለኛነት ሥራውንስ እንዴት እንደሚሠራ፣ እንዲሁም የመካከለኛነት አገልግሎቱ ለእኛ ያለው አስፈላጊነት ምን ያህል እንደሆነ በማያወላዱና ግልጽ በሆኑ ማስረጃዎች አስረግጦ ማስረዳት ብቻ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
እንደዚሁም ስለ «አዲስ ኪዳን መካከለኛ» መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ግልጽ እውነት በተሳሳተ መንገድ የሚረዱና የተሳሳተ ትምህርት የሚሰጡ ወገኖች ቃሉን በመቃወም ላይ መሆናቸውን አልተገነዘቡም፡፡ ከዚህም የተነሣ በተሳሳተ ቅንዓት ተነሣስተው በስህተት ይከራከራሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ስለ «አዲስ ኪዳን መካከለኛ» የሚነሣው ጥያቄ ዕረፍት የነሳቸውና መጽሐፍ ቅዱስን ደግመው ደጋግመው እንዲመረምሩ የተገደዱ አንዳንድ ሰዎች የራሳቸውን አመለካከት የሚደግፍ መረጃ ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስን ሲያነቡ መጽሐፍ ቅዱሱ ደግሞ ለእነርሱ መልስ ስለሚሰጣቸው እውነቱን በውስጣቸው ማወቃቸው አልቀረም፤ የእነዚህ ሰዎች ችግር ደግሞ ቀደም ሲል መሳሳታቸውን ተቀብለው ቃሉ ለሚናገረው እውነት መሸነፍ አለመቻላቸው ነው፡፡ ነገር ግን አንድ ቀን የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል በልባቸው ውስጥ ሲበራ /2ቆሮ.4፡4-5/ ሁሉም ነገር ግልጽ ይሆንላቸውና የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ማን እንደሆነና መካከለኛነቱስ እንዴት እንደሆነ ተረድተው ለማስረዳት ቀዳሚዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እዚህ ደረጃ ሊደርሱ የሚችሉት ግን በግልጽ በሚረዱትና በሚገባቸው መንገድ በማያሻሙ የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎች የተረጋገጠ ትምህርት ሲያገኙ ነው፡፡ ይህ ትምህርታዊ ጽሑፍ የተዘጋጀበት መሠረታዊ ምክንያትም ይኸው ነው፡፡
ከዚህ እትም አስቀድሞ በታተሙት የዚህ ጽሑፍ እትሞች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ «አዲስ ኪዳን መካከለኛ» ከሚያስተምረው እውነት በተጨማሪ ከአንዳንድ የአገራችን ትውፊታውያን መጻሕፍት ውስጥ ከእውነቱ ጋር የሚስማሙ አንዳንድ ጥቅሶች ተመርጠው ለማብራሪያነት ተጠቅሰው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይህም አቀራረብ ስለ «አዲስ ኪዳን መካከለኛ» ጥያቄ ላለባቸው የትውፊታውያን መጻሕፍቱ ተጠቃሚዎች በመጽሐፍ ቅዱስ የተነገረውን እውነታ ለማስረዳት በር የከፈተ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ሆኖም ስለኢየሱስ ክርስቶስ መካከለኛነት መጽሐፍ ቅዱስ አስረግጦ የሚያስተምረን እውነት በቂ መሆኑ ስለታመነበት በዚህ እትም ውስጥ እንዳይካተቱ ተደርገዋል፤ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ከማይስማሙ ነገሮች ጋር በማቀላቀል አንዳንድ እውነትን የያዙትን የትውፊት መጻሕፍት የመመርመሩን ጉዳይ መጻሕፍቱን ለሚጠቀሙባቸው ሰዎች በመተው በዚህ እትም መጽሐፍ ቅዱስ ስለአዲስ ኪዳን መካከለኛ የሚያስተምረውን እውነት ብቻ እናቀርባለን፡፡
እንደዚሁም በዚህ እትም በቀደሙት እትሞች ውስጥ በቀረቡት ማብራሪያዎችና ትንታኔዎች ላይ አንዳንድ እርማቶችና ተጨማሪ ገለጻዎች ተሰጥተዋል፤ ከአቀራረብም አንጻር አንዳንድ ማሻሻያዎች ተደርገዋል፡፡ ይህም መጽሐፉን ለሚያነቡት ሁሉ ጠቃሚ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ሆኖም በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የቀረበውን እውነት በትክክል ለመረዳት በጸሎት ሆኖ በጽሑፉ የተጠቀሱትን የእግዚአብሔር ቃል ክፍሎች ከመጽሐፍ ቅዱስ እያወጡ በማየት ሊነበብ ይገባል፡፡
የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ማን ነው?
«መካከለኛ» ማለት በደረጃው ከከፍተኛ ነገር ዝቅ ያለ፣ ከዝቅተኛው ነገር ደግሞ ከፍ ያለ በመካከል የሚገኝ ማለት ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ክፍል ግን «መካከለኛ» ስንል ይህን ትርጉም የያዘ አይደለም፤ እዚህ ላይ «መካከለኛ» ማለት ሁለት ወገኖችን ለማገናኘት በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚቆም ማለት ነው፡፡ በዚህ ትርጉም መሠረት መጽሐፍ ቅዱስ «የአዲስ ኪዳን መካከለኛ» የሚለው በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለውን መካከለኛ ነው፡፡
«የአዲስ ኪዳን መካከለኛ» የሚለው ይህ ቃል የሚገኘው ወደ ዕብራውያን በተጻፈው መልእክት ውስጥ ሲሆን በሁለት ስፍራዎች ላይ እናገኘዋለን፡፡ በዕብ.9፡15 ላይ «ስለዚህም የፊተኛው ኪዳን ሲጸና ሕግን የተላለፉትን የሚቤዥ ሞት ስለሆነ የተጠሩት የዘላለምን ርስት የተስፋ ቃል እንዲቀበሉ እርሱ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው» የሚል ሲሆን፣ በዕብ.12፡24 ላይ «... የአዲስም ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ ... ደርሳችኋል» ይላል፡፡ በፊተኛው ኪዳን ጊዜ ሕጉ የተሰጠው በእግዚአብሔርና በእስራኤል ሕዝብ መካከል በነበረው መካከለኛ አማካኝነት ነበር፡፡ ይህም በገላትያ መልእክት ውስጥ የተነገረ ሲሆን በዚያም «እንግዲህ ሕግ ምንድር ነው? ተስፋው የተሰጠው ዘር እስኪመጣ ድረስ በመካከለኛ እጅ በመላእክት በኩል ስለሕግ መተላለፍ ተጨመረ፤ መካከለኛውም ለአንድ ብቻ አይደለም፤ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው» ተብሎ ተገልጿል /ገላ.3፡19-20/፤ ቀደም ሲል ለአብርሃም የተሰጠው የተስፋ ቃል ሳይሻር እንዳለ ሆኖ በኋላ ላይ «ስለ ሕግ መተላለፍ» ሕግ በተጨመረ ጊዜ በእግዚአብሔርና በእስራኤል መካከል የሚያገለግል ሰው ነበር፤ ይህም ሰው ሙሴ ነበር፤ ይህንንም ራሱ ሙሴ ለእስራኤል ሁሉ ሲናገር «እኔ የእግዚአብሔርን ቃል እነግራችሁ ዘንድ በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔርና በእናንተ መካከል ቆሜ ነበር» ብሏል/ዘዳግ.5፡5/፤ ሆኖም ሙሴ ብሉይ ኪዳን በተሰጠ ጊዜ በእግዚአብሔርና በእስራኤል ሕዝብ ብቻ መካከል ያገለገለ መካከለኛ ነበር፡፡ የእስራኤል ሕዝብ በኪዳኑ ባለመጽናታቸው የተነሳ እግዚአብሔር በኋላ ላይ በነቢዩ በኤርምያስ በኩል «እነሆ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል» በማለት በተናገረው መሠረት ወደፊት እስራኤልን ወደራሱ በሚመልስበት ጊዜ ከእነርሱ ጋር አዲስ ኪዳንን ይገባል፡፡ እኛም በዚህ በጸጋው ዘመን ያለን አማኞች ከወዲሁ ወደዚያ አዲስ ኪዳን እንድንገባ ተደርገናል፤ ይህም «በመንፈስ እንጂ በፊደል ለማይሆን ለአዲስ ኪዳን አገልጋዮች እንድንሆን አበቃን» ተብሎ ተነግሯል /2ቆሮ.3፡6/፤ ለዚህ አዲስ ኪዳንም መካከለኛ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ እርሱ እንደሙሴ ከሰው መካከል የተጠራ ሳይሆን ከዘላለም በእግዚአብሔር ዘንድ የነበረ እርሱ ራሱ እግዚአብሔር የሆነ በኋላም ሥጋ የሆነ ቃል ነው/ዮሐ.1፡1-14/፤ እርሱ እንደሙሴ ሕግን ከእግዚአብሔር ተቀብሎ ለእስራኤል የሰጠ ሳይሆን ጸጋና እውነትን ለሰው ሁሉ ያመጣ ነው/ዮሐ.1፡17/፡፡ እርሱ እንደሙሴ በቤቱ ላይ እንደሎሌ የታመነ ሳይሆን እንደ ልጅ የታመነ ነው/ዕብ.3፡2-6/፡፡ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ በነገር ሁሉ ከሙሴ የሚበልጠው ይህ ኢየሱስ ነው፡፡
«ያ ይሻር የነበረው»/2ቆሮ.3፡11/ ፊተኛው ኪዳን በሚሰጥበት ጊዜ ሙሴ ለሚቃጠል መሥዋዕትና ለደኅንነት መሥዋዕት የቀረቡ የጥጆችና የፍየሎች ደም ይዞ «እግዚአብሔር ያዘዘላችሁ የኪዳን ደም ይህ ነው» እያለ በደም ሲመርቀው እንመለከታለን/ዘጸ.24፡6-8፤ ዕብ.9፡18-24/፤ «ጸንቶ የሚኖረው» አዲስ ኪዳን ሲመሠረት ግን የአዲስ ኪዳን መካከለኛ የሆነው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ በመስቀል ላይ ያፈሰሰውን ደሙን በወይን ምሳሌነት አሳይቶ «ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው» በማለት መርቆታል/ማቴ26፡28/፡፡ ወደፊት ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር ለሚገባው አዲስ ቃል ኪዳን መሠረቱ ይኸው የክርስቶስ ደም ነው እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ ሆኖም ይህ በክርስቶስ ደም የተመሠረተው አዲስ ኪዳን በጸጋው ዘመን ለምንኖር ለእኛም ቀደም ብሎ በመግባቱ እርሱ በሰማይ በሚገኝበት በአሁኑ ዘመን የመካከለኛነት ሥራውን ይሠራል፤ ስለዚህ አሁንም ሆነ ወደፊት በመላው የአዲስ ኪዳን ዘመን በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለው መካከለኛ ኢየሱስ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን በሙሴ ጊዜም ሆነ ከሙሴ በኋላ በእግዚአብሔርና በእስራኤል መካከል የመገናኛ መስመር ሆነው የሚያገለግሉ ብዙ ነቢያትና ካህናት ነበሩ፡፡ ነገር ግን ብሉይ ኪዳን ለአዲስ ኪዳን ምሳሌና ጥላ እንደሆነ ሁሉ፣ እነዚህም ለአዲስ ኪዳን መካከለኛ ምሳሌና ጥላ ነበሩ እንጂ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ለዘላለም መካከለኞች ሆነው እንዲቀጥሉ የተሾሙ አልነበሩም፡፡ በአዲስ ኪዳን ዘመን ግን በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለው መካከለኛ አንድ ነው፤ እርሱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ሲያስረዳ «አንድ እግዚአብሔር አለና በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፤ እርሱም ሰው የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው» ይላል/1ጢሞ.2፡5/፡፡ በዚህ ቃል ውስጥ መካከለኛው አንድ መሆኑ የተነገረው አንድ እግዚአብሔር እንዳለ የተነገረውን ተከትሎ መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል፤ በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን አንድ እግዚአብሔር የመኖሩ እውነታ በአጽንኦት የተነገረ ሲሆን በዚህ ክፍል ደግሞ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለው መካከለኛ አንድ መሆኑ የዚያኑ ያህል ተነግሯል፡፡ መካከለኛው አንድ የሆነው እግዚአብሔር አንድ የመሆኑን ያህል ሆኖ ቀርቧል፤ ስለዚህ ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር አምላክ እንደሌለ ሁሉ ከአንዱ ከክርስቶስ በቀርም መካከለኛ የለም፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መካከለኛ የሆነው እንደቀድሞዎቹ እንደነሙሴ በእግዚአብሔርና በእስራኤል መካከል ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔርና በሰው መካከል መሆኑ ተገልጿል፡፡ ይህም «ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደማወቅ ሊደርሱ የሚወድ» እግዚአብሔር/1ጢሞ.2፡3/ ከሰው ሁሉ ጋር ግንኙነት የሚያደርግበት አዲስ መንገድ ነው፤ ጌታ ኢየሱስ ይህን የመካከለኝነት ስፍራውን የያዘው ሰው በመሆኑ ነው፤ አንድ መካከለኛ እንዳለ ከተነገረ በኋላ «እርሱም ሰው የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው» ተብሏልና፡፡ እርሱ ቀደም ሲል እንደ አባቱ አምላክ/መለኮት/ ብቻ ነበር፤ በኋላ በሥጋ ሲገለጥ ደግሞ ከኃጢአት በቀር እንደ እኛ ሰው ሆነ፡፡ ሆኖም ሰው በመሆኑ አምላክነቱ አልቀረም፣ ወይም አልተለወጠም፤ ስለዚህ በሥጋ የተገለጠው ክርስቶስ አምላክም ሰውም ነው፡፡ ይህም ማንነቱ ብቸኛ መካከለኛ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ቅዱሳን መላእክት እንደ እርሱ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል መካከለኞች ለመሆን የሚያስችል ባሕርይ የላቸውም፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔርም የሰውም ባሕርይ የላቸውም፡፡ ቅዱሳን ሰዎችም ቢሆኑ ያላቸው የሰው ባሕርይ ብቻ ነው፡፡ አምላክም ሰውም የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የእግዚአብሔርን መለኮታዊ ጽድቅ በአምላክነቱ፣ ለሰው የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ደግሞ በሰውነቱ የሚያውቅ ባሕርይ አለው፤ እርሱ በአምላክነቱ እግዚአብሔርን/አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስን/ በሰው ፊት፣ በሰውነቱ ደግሞ ሰዎችን ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት መወከል የሚችልበት ማንነት አለው፡፡ ስለሆነም የእግዚአብሔር የሆነውን ነገር ወደእኛ የሚገልጥ የእኛ የሆነውን ጉዳይ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርብ ብቸኛ መካከለኛ እርሱ ነው፡፡ በሰውነቱም «ቅዱስና ያለተንኰል ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞች የተለየ በሰማያትም ከፍ ያለ» ነው /ዕብ.7፡26/፤ ቅዱሳን ሰዎች ግን «ጻድቅ የለም አንድስ እንኳ» ተብሎ እንደተጻፈ /ሮሜ3፡11/ ከኃጢአት መዳን ያስፈለጋቸው ናቸው እንጂ እንደዚህ አይደሉም፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔርን የጽድቅ ፍርድ አስጠብቆ ለሰው የሚያስፈልገው ሁሉ ይደረግ ዘንድ እግዚአብሔርንና ሰውን በፍጹምነት ማገናኘት የሚችል መካከለኛ እርሱ ብቻ ነው፡፡
በዕብ.12፡22-24 ላይ ያለው ቃል አማኞች የደረሱበትን ስፍራ ሲናገር «ነገር ግን ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ ደርሳችኋል፤ ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም በደስታ ወደተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት በሰማያትም ወደተጻፉ ወደ በኲራት ማኅበር የሁሉም ዳኛ ወደሚሆን ወደ እግዚአብሔር ፍጹማንም ወደሆኑት ወደ ጻድቃን መንፈሶች የአዲስም ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል» ይላል፡፡ በዚህ ክፍል ጠቅላላው የእግዚአብሔር ማኅበር ተገልጿል፤ እግዚአብሔር የሁሉ ዳኛ መሆኑ ሲነገር ከእርሱም ጋር አእላፋት መላእክት፣ የበኲራት ማኅበር፣ የጻድቃን መንፈሶች እና ኢየሱስ ተጠቅሰዋል፡፡ ስለሆነም እኛ አማኞች ወደ እግዚአብሔርና ወደ ኢየሱስ ብቻ ሳይሆን በሰማያት ወዳሉ ቅዱሳን መላእክትና ቅዱሳን ሰዎች ደርሰናል፤ ሆኖም ከእነዚህ ቅዱሳን መላእክትና ቅዱሳን ሰዎች መካከል አንዳቸውም የአዲስ ኪዳን መካከለኛ አልተባሉም፡፡ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ኢየሱስ ብቻ ነው፡፡
የመካከለኛው ሊቀ ካህናትነት
በብሉይ ኪዳን ዘመን በእግዚአብሔርና በእስራኤላውያን መካከል በመቆም በተለይ ሕዝቡ ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ግንኙነት በተመለከተ ያገለግል የነበረው ከሰው መካከል የተመረጠ ሊቀ ካህናት ነበር፡፡ ይህም በዕብ.5፡1 ላይ «ሊቀ ካህናት ሁሉ ስለ ኃጢአት መባንና መሥዋዕትን ሊያቀርብ ከሰው ተመርጦ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ስለሰው ይሾማልና» ተብሎ ተነግሯል፤ በዚያን ጊዜ ከቤተ አሮን ከሆኑት እስራኤላውያን ወንዶቹ ሁሉ በቤተመቅደስ ውስጥ ካህናት በመሆን ያገለግሉ ነበር /ዘሌ1፡5፤ 7፡35/፡፡ ካህናቱም ያገለግሉ የነበረው በተራ ነበር /ሉቃ1፡8-9/፤ ሊቀ ካህናት የሚባለው የእነርሱ አለቃ ነው፡፡ ከሰባቱ የእግዚአብሔር በዓላት መካከል «የማስተስረያ ቀን» በሚባለው በዓል ላይ በየዓመቱ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ገብቶ ስለ ሕዝቡና ስለራሱ መሥዋዕት የሚያቀርበው ይህ ሊቀ ካህናቱ ነው እንጂ ሌሎቹ ካህናት አልነበሩም፡፡ ሌሎቹ ካህናት የሚያገለግሉት የዘወትሩን አገልግሎት ሲሆን የሚያገለግሉትም በቤተመቅደሱ በፊተኛው ክፍል /በቅድስት/ ነበር፤ በሁለተኛው /በቅድስተ ቅዱሳን/ ውስጥ መግባት አይፈቀድላቸውም ነበር /ዕብ.9፡6-10/፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን ኃጢአትን የሠራ እስራኤላዊ ለኃጢአት መሥዋዕት የሚሆን ነውር የሌለበት በግ ይዞ ወደ ካህኑ ይሄድና እጁን በበጉ ላይ ጭኖ ኃጢአቱን ከተናዘዘ በኋላ ካህኑ ስለኃጢአቱ ያስተሰርይለት ነበር /ዘሌ.4፡29፤ 5፡6/፡፡ እንደዚሁም በዓመት አንድ ቀን ማለት በማስተስረያ በዓል ቀን ሊቀካህናቱ ስለራሱና ስለሕዝቡ መሥዋዕትን በማቅረብ የራሱንና የሕዝቡን ኃጢአት ያስተሠርይ ነበር /ዘሌ.16፡1-34፤ ዕብ.9፡6-10/፡፡
የአዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት ግን አስቀድሞ ሰው ያልነበረውና በኋለኛው ዘመን ከኃጢአት በቀር እንደ እኛ ሰው የሆነው ራሱን ስለሰዎች መሥዋዕት በማድረግ ወደ ሰማይ የገባና በዚያው መሥዋዕት በሰማያዊት መቅደስ የሚያገለግል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ የእርሱን ሊቀካህናትነት በተመለከተም ወደ ዕብራውያን በተጻፈው መልእክት ውስጥ በዝርዝር ተጽፎልናል፤ ዋና ዋናዎቹ ንባቦች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡
- «ስለዚህ የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀካህናት እንዲሆን በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው» /ዕብ.2፡17-18/
- «የሃይማኖታችንን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልከቱ» /ዕብ.3፡1/፡፡
- «እንግዲህ በሰማያት ያለፈ ትልቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ስላለን ጸንተን ሃይማኖታችንን እንጠብቅ ይላል /ዕብ4፡14/፡፡
- «ከተናገርነው ዋና ነገሩ ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀካህናት አለን» /ዕብ.8፡1-/
ጌታ ኢየሱስ የሊቀ ካህናትነቱን ስፍራ እንዴት እንደያዘ መጽሐፍ ቅዱስ ሲገልጽ «እንዲሁ ክርስቶስ ሊቀ ካህናት ሊሆን ራሱን አላከበረም፤ ነገር ግን 'አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ' ያለው እርሱ ነው፤ እንደዚህም በሌላ ስፍራ ደግሞ 'አንተ እንደመልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ' ይላል» በማለት ይናገራል/ዕብ5፡5-6/፡፡ በዚህ ክፍል የኢየሱስን ሊቀ ካህንነት ለማሳየት ከመዝ.2፡7 ላይ «አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ» የሚለው ቃል እና ከመዝ.109/110/፡4 ላይ ደግሞ «አንተ እንደመልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ» የሚለው ቃል በአንድ ላይ ተጠቅሰዋል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ሰው የሆነውን ክርስቶስን «አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ» ባለው ጊዜ «እንደ መልከጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን» አድርጎታል ማለት ነው፡፡ እዚህ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ «አንተ ልጄ ነህ» ሲባል በመለኮቱ ከዘላለም የነበረውን የእግዚአብሔር ልጅነት የሚያሳይ አይደለም፤ ምክንያቱም ቀጥሎ «እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ» ሲል ከዘላለም ሳይሆን በኋለኛው ዘመን በጊዜ ውስጥ ያለውን ልጅነቱን ስለሚያመለክት ነው፤ ይህም በቀጥታ የሚያመለከተው እርሱ በሰውነቱም ቢሆን የሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔርም ልጅ መሆኑን ነው፡፡ እርሱ ሰው ሲሆን በሥጋው ምድራዊ አባት የሌለው ሲሆን ከሴት የተወለደው በእግዚአብሔር ተአምራዊ ሥራ መሆኑ ይታወቃል፤ ገብርኤል ለማርያም ሲያበስራት «ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል?» ባለችው ጊዜ «መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል፤ ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል» ብሏታል /ሉቃ.1፡34-35/፤ ስለዚህ «እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ» የሚለው በተአምራዊ አሠራር ያለምድራዊ አባት ሰው ሆኖ የተለወደውን ኢየሱስን ነው፡፡ በዚህም የተነሣ ከዘላለም ከአብ የተወለደው ብቻ ሳይሆን የዘመኑ ፍጻሜ ሲደርስ ከሴት የተወለደው እርሱ /ገላ.4፡4/ ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ነው፤ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል ተብሏልና፡፡
እርሱ በምድር ሳለ በሰው ልጅነቱ የተመላለሰ ቢሆንም በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀ ጊዜና በቅዱሱ ተራራ በተገለጠ ጊዜ እግዚአብሔር «በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው» በማለት መሰከረለት/ማቴ3፡17፤ 17፡5/፡፡ በመጨረሻም የቤዛነት ሥራውን ለመፈጸም በሰውነቱ ሞተ፤ ነገር ግን በሥጋ የሞተው እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ይረጋገጥ ዘንድ እግዚአብሔር ከሙታን አስነሳው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በሮሜ1፡4 ላይ ስለወንጌል ምንነት በተናገረበት ክፍል ኢየሱስ «ከሙታን መነሣት የተነሣ በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ» እንደተገለጠ ይናገራል፤ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ደግሞ «... እግዚአብሔር ግን ከሙታን አስነሳው፤ ... ይህን ተስፋ እግዚአብሔር በሁለተኛው መዝሙር ደግሞ 'አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወለድሁህ' ተብሎ እንደተጻፈ ኢየሱስን አስነሥቶ ለእኛ ለልጆቻው ፈጽሟልና» ይላል/የሐ.ሥ.13፡30-33/፡፡ ስለዚህ በዚህ ክፍል «አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወለድሁህ» የሚለው ቃል ኢየሱስ ከሙታን ከመነሣቱ ጋር ተያይዞ መነገሩ ሰው የሆነው እርሱ ምንም እንኳ ሰው በሆነበት ዘመን ሁሉ የእግዚአብሔር ልጅ ቢሆንም ይህ ልጅነቱ ይበልጥ የተረጋገጠውና የተገለጠው ደግሞ በትንሣኤው መሆኑን ያስረዳል፡፡ ከዚያም «አንተ ልጄ ነህ» የተባለው ይኸው ሰው «እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን» ተብሎ በመጠራት ወደ ሰማይ ገብቷል/ዕብ.5፡10፤ 6፡20/፡፡ በዚህም ዘላለማዊ የሊቀካህናትነት ስፍራውንና ክብሩን ይዟል፡፡
የኢየሱስ ክርስቶስ የሊቀካህናትነት አገልግሎቱ «ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ» እንደሆነ ተነግሮናል፡፡ ይህም ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር በሚያደርጉት በማናቸውም ግንኙነት ወይም በፊቱ በሚቀርቡበት በማናቸውም ጉዳይ በመካከለኝነት የሚያገለግል መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ የሊቀካህናት አገልግሎት የሚከናወነው በመቅደስ ውስጥ በተለይም በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ሲሆን አገልግሎቱም ሕዝቡ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት እንዲኖራቸው ስለሕዝቡ መሥዋዕት ማቅረብ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንጻር ሲታይ ኢየሱስ የሚያገለግለው በሰማይ ባለች እውነተኛይቱ ድንኳን መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር «እርሱም የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው እርስዋም በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ናት» ይላል/ዕብ.8፡2/፡፡ እንዲሁም ኃጢአተኞችን ከእግዚአብሔር ጋር ለማገናኘትና በእርሱ ፊት ተቀባይነት እንዲኖራቸው ለማድረግ በሊቀካህናትነቱ ያቀረበው መሥዋዕትም ሌላ ምንም ሳይሆን በቀራንዮ መስቀል ላይ መሥዋዕት ሆኖ የቀረበውን ራሱን ነው፡፡ በሰማይ ወዳለችው መቅደስ የገባውም እንደ ብሉይ ኪዳኑ ሊቀካህናት የእንስሶችን ደም ይዞ ሳይሆን በገዛ ደሙ እንደሆነ «ነገር ግን ክርስቶስ ይመጣ ዘንድ ላለው መልካም ነገር ሊቀካህናት ሆኖ በምትበልጠውና በምትሻለው በእጆችም ባልተሠራች ድንኳን የዘላለምን ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም» ተብሎ ተገልጿል /ዕብ.9፡11-12/፡፡ እንዲሁም አንድ ጊዜ ባቀረበው በዚያው መሥዋዕት ስለእኛ ሊታይ ወዚያች ሰማያዊት መቅደስ እንደገባ ሲናገር «ክርስቶስ በእጅ ወደተሠራች የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደምትሆን ቅድስት አልገባምና፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለእኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ፡፡ ሊቀካህናት በየዓመቱ የሌላውን ደም ይዞ ወደ ቅድስት እንደሚገባ ራሱን ብዙ ጊዜ ሊያቀርብ አልገባም፤ እንዲህ ቢሆንስ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ ሊቀበል ባስፈለገው ነበር፤ አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጧል» ይላል/ዕብ.9፡24-26/፡፡
በአዲስ ኪዳን ያለው የእግዚአብሔር ቤት በሕያዋን ድንጋዮች የተሠራ መንፈሳዊ ቤት መሆኑ የተነገረ ሲሆን በዚያ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን የሚያቀርቡትም ቅዱሳን ካህናት ተብለው ተጠርተዋል /1ጴጥ.2፡5/፤ በዚህ ቤት ላይ የተሾመው ታላቅ ካህን ደግሞ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ የዚህ መንፈሳዊ ቤት ቅድስተ ቅዱሳን ያለው በሰማይ ሲሆን በዚያም ይህ ታላቅ ካህን ስለእኛ ቀዳሚ ሆኖ ገብቷል/ዕብ.6፡20/፤ የእርሱ በዚያ መኖርም እኛን ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ የሚያስችለን ሆኗል፤ ይህን በተመለከተም የተጻፈው ቃል «እንግዲህ ወንድሞች ሆይ በመረቀልን በአዲስና በሕያው መንገድ ወደ ቅድስት በኢየሱስ ደም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል እንድንገባ ድፍረት ስላለን በእግዚአብሔርም ቤት ላይ የሆነ ታላቅ ካህን ስላለን ከክፉ ኅሊና ለመንጻት ልባችንን ተረጭተን ሰውነታችንንም በጥሩ ውኃ ታጥበን በተረዳንበት እምነት በቅን ልብ እንቅረብ» ይላል /ዕብ.10፡19-22/፡፡
ይህ የአዲስ ኪዳን ሊቀካህናት በብሉይ ኪዳን እንደ እግዚአብሔር ሥርዓት ከሰዎች ተመርጠው ከሚሾሙትና በዚህ ዘመን ደግሞ እንደ ሰው ሥርዓት በሰዎች ተመርጠው ከሚሾሙት ሊቃነ ካህናት በብዙ ነገር የተለየ ነው፡፡ በመሆኑም እርሱ ከእነርሱ የሚለይበትንና የሚልቅበትን ባሕርያት ቀጥለን እንመለከታለን፡፡
የሚምር ነው
የእግዚአብሔር ልጅ ልክ እንደ እኛ ሰው ሆኖ ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደእኛ የተፈተነበት ምክንያት የእኛን ኃጢአት ለማስተስረይ የሚችል የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን ነው፡፡ ይህን ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው «ስለዚህ የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው» ተብሎ ተነግሯል/ዕብ.2፡17/፡፡ እርሱ የሚምር ሊቀካህናት መሆኑም በምድር ላይ ሳለ ኃጢአተኞችን በምሕረት በመቀበሉ ሊታወቅ ይችላል፡፡ ሰዎች ቢፈርዱባቸውና ቢጸየፏቸውም ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ኃጢአተኞችን ይቀበል ነበር/ሉቃ.15፡1-2/፡፡ ለምሳሌ በቀራጩ በማቴዎስ ቤት በማዕድ ተቀምጦ በነበረ ጊዜ ከእርሱ ጋር ከተቀመጡት መካከል ብዙ ቀራጮችና ኃጢአተኞች ነበሩ፤ ይህን ሁኔታ ፈሪሳውያን ቢቃወሙም «ምሕረትን እወዳለሁ መሥዋዕትን አይደለም» የሚለውን ቃል ጠቅሶ ተገቢ መልስን በመስጠት እርሱ የሚምር መሆኑን አሳይቷል/ማቴ.9፡10-13/፡፡ ጌታችን በማስተማር ዘመኑ በፈሪሳዊው በስምዖን ቤት በማዕድ ሳለ በእግሩ ሥር ተደፍታ ታነባ በነበረችው ኃጢአተኛ ላይ ፈሪሳዊው ሲፈርድባት፣ ክርስቶስ ግን በ500 ዲናር የተመሰለውን እጅግ የበዛ የኃጢአት ዕዳዋን «ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል» በሚል ቃል እንደማራት ተጽፏል /ሉቃ.7፡36-50/፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ ጌታችን በመቅደስ እያስተማረ ሳለ ጻፎችና ፈሪሳውያን ሊከሱአትና እርሱንም ሊፈትኑት ያመጧትን በምንዝር የተያዘች ሴት «...እኔም አልፈርድብሽም» በሚል የምሕረት ቃል እንደተቀበላት ተጽፎልናል /ዮሐ.8፡1-11/፡፡ የፈሪሳውያን ዋና መለያቸው የራሳቸውን ኃጢአት ሳይመለከቱ በሌላው ኃጢአት ላይ መፍረዳቸው ነው፡፡ ይሁን እንጂ ፈሪሳውያን የፈረዱበትን ሁሉ ጌታ ይምረው ነበር፡፡ ዛሬም እጅጉን ግብዝነት የሞላበትን የሃይማኖተኝነት ወግ የተላበሰው ፈሪሳዊው ዓለም ኃጢአተኛውን ተጸይፎ በእግዚአብሔር ፊት ቢከሰውና ቢፈርድበት የሃይማኖታችን ሊቀካህናት ኢየሱስ ግን ኃጢአተኛው ወደ እርሱ ሲመጣ በምሕረት ይቀበለዋል፡፡ ምድራውያን ካህናት ተጸይፈው ገለል ብለው ቢያልፉትም የሚምረው ሊቀካህናችን ኢየሱስ ግን ከወደቀበት ያነሣዋል /ሉቃ.10፡30-37/፡፡ እርሱ በምድራውያን ሰዎች ስሜትና ምክር ተገፋፍቶ ሊፈርድብን አይነሣም፤ እንዲያውም ኃጢአተኛን የሚከስስ በፊቱ ከተግሣጽ በቀር ተቀባይነትን አያገኝም፡፡ ወደ ኢየሩሳሌም ለመጨረሻ ጊዜ ሲወጣ በመንገድ ላይ ሳምራውያን ባልተቀበሉት ጊዜ ዮሐንስና ያዕቆብ «ጌታ ሆይ ኤልያስ ደግሞ እንዳደረገ እሳት ከሰማይ ወርዶ ያጥፋቸው እንል ዘንድ ትወዳለህን?» ሲሉት በግሣጼ «ምን ዓይነት መንፈስ እንደሆነላችሁ አታውቁም፤ የሰው ልጅ የሰውን ነፍስ ሊያድን እንጂ ሊያጠፋ አልመጣም» ብሎ በመለሰው መልስ አስደናቂ ምሕረቱን ገልጧል /ሉቃ.9፡51-56/፡፡ በሰቀሉትም ጊዜ «አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው» ብሎ መጸለዩን ስንመለከት ጌታ ጠላቶቹን እንኳን የሚምር ልብ እንዳለው እንረዳለን /ሉቃ.23፡14/፡፡ አሁንም በሰማይ ስለእኛ እየታየ ባለበት ዘመን በምድር ያለነውን ኃጢአተኞችና በደለኞች በምሕረት የሚቀበል ሊቀካህናት እርሱ ብቻ ነው፤ ኃጢአታችንንም ያስተሰርይልናል፡፡ በምድር በነበረ ጊዜ የምሕረት ዝናውን የሰሙት ኃጢአተኞች ሁሉ በዘመናቸው የነበሩትን ካህናትና የካህናት አለቆች እንዲሁም ጻፎችና ፈሪሳውያንን አልፈው በመምጣት በኢየሱስ እግር ሥር ወድቀው ያነቡ እንደነበረ ሁሉ ዛሬም ሁሉን አልፈን በመምጣት እግዚአብሔር በሾመው ሰማያዊ ሊቀ ካህናት እግር ሥር ልንወድቅ ያስፈልጋል፤ ምሕረትንም እናገኛለን፡፡
የታመነ ነው
ኢየሱስ ክርስቶስ በንስሐ ወደ እርሱ የሚመጡትን ኃጢአተኞች የሚምር ካህን ብቻ ሳይሆን ለሾመው የታመነ ካህንም ነው፡፡ እርሱ በዕብ.2፡17 ላይ «የሚምርና የታመነ ሊቀካህናት» ተብሎ ተጠርቷል፤ የታመነ መሆኑን በተመለከተ በዕብ. 3 ላይ እርሱን ከሙሴ ጋር በማነጻጸር የቀረበ ተጨማሪ ገለጻ እናገኛለን፡፡ ይኸውም «ስለዚህ ከሰማያዊ ጥሪ ተካፋዮች የሆናችሁ ቅዱሳን ወንድሞች ሆይ የሃይማኖታችንን ሐዋርያና ሊቀካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልከቱ፤ ሙሴ በቤቱ ሁሉ የታመነ እንደሆነ እርሱ ለሾመው የታመነ ነበረ፡፡ ... ሙሴስ በኋላ ስለሚነገረው ነገር ምስክር ሊሆን በቤቱ እንደሎሌ የታመነ ነበረ፤ ክርስቶስ ግን እንደ ልጅ በቤቱ ላይ የታመነ ነው» የሚል ነው/ዕብ3፡1-6/፡፡ መታመን አንድን ሥራ ወይም አደራ ለሰጠ ለሌላ ማንነት ሁልጊዜም እውነተኛ ሆኖ መገኘትን የሚያመለክት ነው፡፡ ሙሴ በቀደመው ኪዳን በነበረው የእግዚአብሔር ቤት ማለትም በማደሪያው ድንኳን ውስጥ እንደሎሌ የታመነ ነበረ/ዘኁል.12፡7/፤ ሆኖም ሙሴ ሎሌ ነውና ታማኝነቱ የልጅን ያህል ሊሆን አይችልም፡፡ «አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ» የተባለው ኢየሱስ ግን ልጅ ነውና እርሱ በተሾመበት የእግዚአብሔር ቤት ላይ ታማኝነቱ ፍጹም ነው፡፡ እርሱ በባሕርዩ ከአባቱ ጋር አንድ ነው/ዮሐ.10፡30/፤ ስለዚህ ታማኝነቱ የእግዚአብሔርን ታማኝነት ያህል ፍጹም ነው፤ ስለእርሱ «ባናምነው እርሱ የታመነ ሆኖ ይኖራል፤ ራሱን ሊክድ አይችልምና» ተብሎ ተጽፏል/2ጢሞ.2፡13/፡፡
ሕጉ ይሾማቸው የነበሩት ከቤተ አሮን የሆኑት ካህናት ይጐድላቸው ከነበረው ነገር አንዱ ታማኝነት ነበር፡፡ አሮንን ብንመለከት የእስራኤል ሕዝብ በሲና ተራራ ሰፍሮ ሳለ ሙሴ ወደ ተራራው ላይ በወጣ ጊዜ የሕዝቡን የዓመፅ ጥያቄ በመቀበል ያመልኩት ዘንድ ጥጃን በመሥራቱ ምን ያህል ታማኝነቱን እንዳጐደለ እናያለን /ዘጸ.32፡1-6/፤ ምንም እንኳን በልቡ የሠራው ሥራ ስህተት እንደሆነ ቢያውቅም ለእግዚአብሔር ከመታመን ይልቅ ለሕዝቡ ድምፅ ታዝዞ ይህን አደረገ /ዘጸ.32፡21-24/፡፡ እንደዚሁም በዘመነ መሳፍንት ማብቂያ አካባቢ የነበረው ኤሊ የተባለውን ካህን ስንመለከት ልጆቹ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ እጅግ አስጸያፊ የሆነ ኃጢአት ሲፈጽሙ እየተመለከተ ባለመከልከሉ ታማኝነት እንዳልነበረው እናያለን /1ሳሙ.2፡29፤ 3፡13/፡፡ ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር ወደፊት የታመነ ካህን እንደሚያስነሳ ተናገረ /1ሳሙ.2፡35/፡፡ ክፉ በሆነው በንጉሡ በአካዝ ዘመን የነበረው ኦርያ የተባለው ካህንም ንጉሡ በደማስቆ ያየውን መሠዊያ አስመስሎ እንዲሠራ ባዘዘው ጊዜ በትእዛዙ መሠረት ሌላ መሠዊያን ሠራ፤ ከዚያም በእግዚአብሔር ፊት የነበረውን የናሱን መሠዊያ ከእግዚአብሔር ቤት መካከል ፈቀቅ አድርጎ ራሱ የሠራውን መሠዊያ ሲያቆም እናያለን፤ ይህንንም ያደረገው ለእግዚአብሔር ከመታመን ይልቅ ለንጉሡ ሊታመን ስለፈለገ ይህን እንዳደረገ እንገነዘባለን /2ነገሥ.16፡10-16/፡፡ እነዚህ ሁሉ በኦሪቱ ዘመን በተለያየ ጊዜ የነበሩ ሊቃነ ካህናት በቤተመቅደስ ውስጥ ሲሾሙ ተጠሪነታቸው ለእግዚአብሔር በመሆኑ ለእርሱ የታመኑ ሊሆኑ ይገባ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ሲጎድላቸው እንመለከታለን፤ አንዳንዶቹ ታማኝነትን ለማሳየት የጣሩ እንኳ ቢኖሩ ታማኝነታቸው ፍጹም አልነበረም፡፡
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በምድር ላይ በተመላለሰበት በማናቸውም ጊዜ በእግዚአብሔርም ሆነ በሰው ፊት የታመነ ሰው ሆኖ አለፈ፤ ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ሲገልጥ «ሁሉን በሕይወት በሚጠብቅ በእግዚአብሔር ፊት በጴንጤናዊውም በጲላጦስ ዘንድ መልካሙን መታመን በመሰከረ በክርስቶስ ኢየሱስ ፊት አዝሃለሁ» ብሎ ለጢሞቴዎስ በጻፈው ቃል ውስጥ ተናግሯል/1ጢሞ.6፡13/፡፡ በዮሐንስ ራእይ መጽሐፍም እርሱ የታመነና እውነተኛ መሆኑ በተደጋጋሚ ተነግሯል/ራእ.1፡5፤ 3፡14፤ 19፡11/፡፡ እርሱ በታማኝነቱ ለእግዚአብሔር ጽድቅ ይቆማል፤ ኃጢአተኞችን በምሕረት የሚያይና የሚቀበል መሆኑ ለእግዚአብሔር ጽድቅ ያለውን ታማኝነቱን አያጠፋበትም፤ ስለዚህ እኛ ምሕረትን እንድናገኝ የሚያደርገው በኃጢአት ላይ ፈርደን በእውነተኛ ንስሐ ስንመለስ ብቻ ነው፤ ምክንያቱም እርሱ የሚምር ብቻ ሳይሆን ለሾመው የታመነም ነውና፡፡ እንዲህ ያለውን ፍጹም ታማኝ ካህን እግዚአብሔር ሰጥቶናል፡፡ በመሆኑም እንደ አሮንና እንደ ኤሊ ለእግዚአብሔር ታማኝ ሊሆኑ ባልቻሉት ሰዎች መገልገልን ትተን እግዚአብሔር በሰማያዊት መቅደስ ወዳስቀመጠልን ወደታመነው ሊቀካህናት ወደ ኢየሱስ ዘንድ ዘወር ልንል ያስፈልጋል፡፡
የሚራራ ነው
በዚህ የአዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት ውስጥ የምናየው ገና ብዙ ውበት አለ፡፡ ብዙ የሚቀሰም ጣፋጭ እንደያዘና ንቦችን ሁሉ ወደ እርሱ እንደሚስብ ደማቅ አበባ ሊቀካህናችን ኢየሱስም ኃጢአተኞች የሆኑ ነፍሳትን ወደ እርሱ የሚስብ አስደናቂ ውበት አለው፡፡ እስከ አሁን የተመለከትነው ኢየሱስ የሚምር እና የታመነ ሊቀካህናት እንደሆነ ነው፡፡ አሁን ደግሞ የሚራራ ሊቀካህናት እንደሆነ እንመለከታለን፡፡ በዕብራውያን መልእክት ውስጥ ይህንን የሚገልጸው ቃል «እንግዲህ በሰማያት ያለፈ ትልቅ ሊቀካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ስላለን ጸንተን ሃይማኖታችንን እንጠብቅ፡፡ ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀካህናት የለንም»ይላል /ዕብ.4፡14-15/፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ሰው የሆነው በችግሮቻችን፣ በፈተናዎቻችንና በመከራዎቻችን ሊሳተፍ ነው፡፡ በእርግጥም «ከኃጢአት በቀር፣ በነገር ሁሉ» እንደ እኛው ተፈትኗል፡፡ በመሆኑም በመስማትና በማየት ብቻ ሳይሆን ደርሶበትም ስለሚያውቀው ችግራችን፣ ፈተናችን፣ መከራችንና ድካማችንም ሁሉ በግልጽ ይገባዋል፡፡ ስለዚህ ሊራራልን ይችላል፡፡ የተቸገሩና በፈተና ውስጥ ያሉ ደካሞችን እንደ ኢየሱስ ሊገነዘባቸው የሚችል የለም፤ ከመላእክትም ሆነ ወይም ከሌሎች ፍጥረታት ወገን ማንም የለም፡፡ ለምሳሌ ሐና ልጅ ስላልነበራት በልቧ እጅግ አዝና በእግዚአብሔር ፊት እያለቀሰች ስትጸልይ ድምፇን ሳታሰማ ከንፈሯን ግን ስታንቀሳቅስ ያያት የወቅቱ ካህን ኤሊ እንኳን ሊራራላትና ሊገነዘባት አልቻለም ነበር፡፡ እንዲያውም እንደሰከረች ቈጥሯት ነበር /1ሳሙ.1፡9-14/፡፡ በምድር ላይ ያሉ መንፈሳዊ መሪዎች ሁሉ ምንም እንኳ መንፈሳዊ ቢሆኑ የምስኪኑን የልብ ችግር ሊያውቁና ሊገነዘቡ አይችሉም፡፡ ዝቅ ብለው የአማኞች የችግራቸውና የፈተናቸው ተካፋይ ስለማይሆኑ ሊገባቸው አይችልም፡፡ እንዲያውም በችግር ላይ ችግርን ለመጨመር ከአማኞች የሚፈልጉትን ሁሉ እየሰበሰቡና በጸሎት ርዝመት በማመካኘት የመበለቶችን ቤት እየበሉ /ማቴ.23፡14/ በሥጋ ተጠቃሚዎች ሲሆኑ ይታያሉ፡፡ እግዚአብሔር እንዲህ ያደርጉ በነበሩት የእስራኤል እረኞች አዝኖ ሲናገር «ራሳቸውን ለሚያሰማሩ ለእስራኤል እረኞች ወዮላቸው! ... በኃይልና በጭቆና ገዛችኋቸው...» /ሕዝ.34፡1-4/ ይላል፡፡ ይህም ቃል የእስራኤል እረኞች ምን ያህል ለበጎቹ የማይራሩ ጨካኞች እንደነበሩ ያስረዳል፡፡ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ወደፊት ራሱ በሚያስነሣው እረኛ እንደሚታደጋቸው ተስፋ ይሰጣቸዋል /ቊ.23-24/፡፡ ሊቀካህናት የሆነው ኢየሱስ በሌላ ስፍራ መልካም እረኛ እንደሆነ ተነግሮናል /ዮሐ.10፡11/፡፡ እርሱም ለበጎቹ ለአማኞች እጅግ የሚራራ እረኛ ነው፡፡ ስለዚህ በጨካኝነት ያለ ርኅራኄ አማኞችን በየምክንያቱ እየበዘበዙ እንመራቸዋለን ከሚሉ እረኞች ተለይተን ለበጎቹ ወደሚያዝነው እረኛ /ማቴ.9፡35/ ማለትም ወደሚራራው ሊቀካህናት ወደ ኢየሱስ ልንፈልስ ያስፈልጋል፡፡ ምናልባት ከእነዚህ ምድራውያን ካህናት አንዳንዶቹ እነርሱም ሰው ስለሆኑ አንዳንድ ጊዜ በችግራችንና በፈተናችን ሊያዝኑና ሊራሩ የሚችሉበት ጥቂት አጋጣሚዎች ሊኖሩ ቢችሉም ከዚህ አልፈው ግን ምንም ሊረዱን አይፈልጉም፣ ቢሞክሩም አይችሉም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን «እርሱ ራሱ ተፈትኖ መከራን ስለተቀበለ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላልና» ተብሎ እንደተጻፈው በችግራችንና በመከራችን የሚራራልን ብቻ ሳይሆን ሊረዳን የሚቻለው ካህን ነው/ዕብ.2፡18/፡፡ ስለዚህም በኑሮአቸው ውስጥ ብዙ የተመሰቃቀለ ነገር ያለባቸውና በብዙ ነገር የሚጨነቁ ችግራቸውንም ለማን እንደሚያማክሩት ግራ የተጋቡ ብዙ ፈተናና መከራ ያለባቸው ሁሉ «የሚረዳ ጸጋን» ለማግኘት ወደ ኢየሱስ ይምጡ፡፡ ቃሉም «እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ» እያለ ሁሉንም ይጠራል /ዕብ.4፡16/፡፡
ድካም የሌለበት ፍጹም ነው
እስከ አሁን ከተመለከትነው ይልቅ ከአሮንና ከአሮናውያን በእጅጉ የሚለይበትን የሊቀ ካህናችንን ማንነት ደግሞ ቀጥሎ እንመለከታለን፡፡ እርሱም የአዲስ ኪዳን ሊቀካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ድካምን የማይለብስ መሆኑ ነው፡፡ ይህም ማለት በቅድስናውና በንጽሕናው ፍጹም የሆነ ምንም ኃጢአት የሌለበት ካህን መሆኑን ያመለክታል፤ በዕብራውያን መልእክት ውስጥ ስለዚህ እውነት የተጻፈው ቃል «ቅዱስና፣ ያለተንኰል፣ ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ያለ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባናል» /ዕብ.7፡26/ ይላል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የሆነው «ከኃጢአት በቀር» መሆኑን ቀደም ሲል ተመልክተናል፤ በመሆኑም ምንም እንኳ በሥጋና በደም ተካፍሎ እንደ እኛ በምድር ላይ ቢመላለስም ምንም ኃጢአት የለበትም፡፡ እርሱ «ቅዱስ» ሆኖ የተወለደ ነው/ሉቃ.1፡35/፤ ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ እርሱ ኃጢአት እንደሌለበት ሲመሰክሩ «ኃጢአት ያላወቀው»/2ቆሮ.5፡21/፣ «እርሱ ኃጢአትን አላደረገም...»/1ጴጥ.2፡22/፣ «በእርሱ ኃጢአት የለም»/1ዮሐ.3፡5/ ይላሉ፡፡ ራሱም ሲናገር «ከእናንተ ስለ ኃጢአት የሚከሰኝ ማነው?» ለማለት ተችሎታል/ዮሐ.8፡46/፡፡ ለሞት አሳልፈው የሰጡት ተቃዋሚዎቹ እንኳ ሳይቀር ምንም ኃጢአት እንደሌለበት መስክረዋል፤ ይሁዳ «ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ» /ማቴ.27፡4/ ሲል ጲላጦስ ደግሞ ለሦስት ጊዜ ያህል «በዚህ ሰው አንድ በደል ስንኳ አላገኘሁበትም» /ሉቃ.23፡4፤ ቊ.14ና22/ ብሏል፡፡ የገሊላው ሄሮድስም ቢሆን «ምንም አላገኘበትም» /ሉቃ.23፡15/፡፡ አብረውት ከተሰቀሉት ክፉ አድራጊዎችም አንደኛው «ይህ ግን ምንም ክፋት አላደረገም» ብሏል/ሉቃ.23፡41/፡፡ ከዚህ ሁሉ እንደምንረዳው ሊቀ ካህናችን ኢየሱስ በእግዚአብሔርም ሆነ በሰው ፊት፣ የእርሱ በሆኑት በደቀመዛሙርቱም ሆነ በተቃዋሚዎቹ ፊት ያለ ነውር የሆነ፣ ቅዱስና ተንኰል የሌለበት፣ ከኃጢአተኞችም የተለየ መሆኑን ነው፡፡ በሕግ የሚሾሙትን የብሉይ ኪዳን ካህናት ስንመለከት ግን ድካምን የሚለብሱ/ዕብ.5፡2፤ 7፡28/ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ በጣም የተገለጠ ኃጢአት የታየባቸው ስንመለከት የኤሊ ልጆችን እናገኛለን፤ እነርሱ በእግዚአብሔር ላይ የድፍረት ኃጢአት የፈፀሙ ናቸው፡፡ አፍኒንና ፊንሐስ የተባሉት እነዚህ የኤሊ ልጆች ምናምንቴዎች ነበሩ፤ እግዚአብሔርንም አያውቁም ነበር፤ የእግዚአብሔርንም ቊርባን ይንቁ ነበር፡፡ ከዚህም በላይ ደግሞ በመገናኛው ድንኳን ከሚያገለግሉ ሴቶች ጋር ያመነዝሩ እንደነበር ተጽፏል /1ሳሙ.2፡12-22/፡፡ ታዲያ በእነዚህ ሰዎች ፊት ኃጢአትን መናዘዝና በእነዚህ ሰዎች መገልገል እንዴት ይቻላል? እነዚህ ሕዝቡን በጸሎትና በአምልኮ እንዴት ሊመሩ ይችላሉ? እንደዚሁም ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ዘመን የነበሩትን የካህናት አለቆች ብንመለከት ነፍስ በመግደልና በማስገደል የታወቁ ነበሩ፡፡ ይህንንም «ዕለት ዕለት በመቅደስ ያስተምር ነበር፤ ነገር ግን የካህናት አለቆችና ጻፎች የሕዝቡ ታላላቆችም ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር» ተብሎ ከተጻፈው መረዳት ይቻላል /ሉቃ.19፡47/፡፡ ኢየሱስን ብቻ ሳይሆን አልዓዛርንም ሊገድሉ እንደተማከሩ ዮሐንስ ሲገልጥ «የካህናት አለቆችም አልዓዛርን ደግሞ ሊገድሉት ተማከሩ» ብሏል /ዮሐ.12፡10/፡፡ እንዲሁም ሳውል ክርስቲያኖችን እንዲገድላቸው እየዛተ አስሮ ለማምጣት የሚችልበትን ደብዳቤ ያጻፈው በጊዜው ከነበረው የአይሁድ ሊቀካህናት ነበር /የሐ.ሥ.9፡1-2/፡፡ ስለሆነም በእንደዚህ ዓይነት የከፋ በደል ውስጥ ሆነው የእግዚአብሔርን ሕዝብ ኃጢአት እናስተሰርያለን ከሚሉት አሮናውያን ባፋጣኝ ተለይቶ ስለ ኃጢአት ማንም ሊከሰው ባልቻለውና ተቃዋሚዎቹ እንኳ ስለ ንጽሕናው በመሰከሩለት ሊቀካህናት ፊት ኃጢአትን መናዘዝ አስፈላጊ ነው፡፡
አንዳንድ አሮናውያን ካህናት ሕገ እግዚአብሔርን በመጠበቅ የተመሰከረላቸው ቢሆኑም እንኳ ፍጹምነት ስለሌላቸው በሰውነታቸው ውስጥ ባለው ኃጢአት መድከማቸው የማይቀር ነው፡፡ ስለዚህ ማንኛውም የብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናት መሥዋዕት የሚያቀርበው ስለ ሕዝቡ ስህተት ብቻ ሳይሆን ስለ ራሱም ኃጢአት ነበር/ዕብ.7፡27፤ 8፡3/፡፡ ኢየሱስ ግን እንደ እነዚያ ሊቃነ ካህናት ድካምን የሚለብስ ባለመሆኑ ስለራሱ መሥዋዕት ማቅረብ አላስፈለገውም፡፡ ስለ ኃጢአተኞች ግን ራሱን አንድ ጊዜ መሥዋዕት አድርጎ አቅርቧል፡፡ በዚህም መሥዋዕት በሰማያዊት መቅደስ በሊቀካህናትነቱ ያገለግላል፡፡ እርሱ ከእነዚያ ሊቃነ ካህናት ምን ያህል በእጅጉ የበለጠ እንደሆነ አንባቢው ያስተውል፡፡ ወደዚህም ቅዱስና ነውር ወደሌለበት ሊቀካህናት በነፍሱ ለመገሥገስ ሊወስን ይገባዋል፡፡ የእኛ ሊቀካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ በሁለንተናው ፍጹም ሲሆን በሕጉና በሰው ሥርዓት የሚሾሙት ግን ምንም ያህል መልካም ሰዎች ቢሆኑ እንኳ ፍጹምነት የላቸውም፤ «ሕጉ ድካም ያላቸውን ሰዎች ሊቀ ካህናት አድርጎ ይሾማል ከሕግ በኋላ የመጣ የመሓላው ቃል ግን ለዘላለም ፍጹም የሆነ ልጅን ይሾማል» ተብሏል/ዕብ.7፡28/፡፡ ኢየሱስ በሊቀ ካህናትነት የተሾመው «አንተ እንደ መልከ ጹዴቅ ሥርዓት ለዘላለም ካህን ነህ» በሚለው የመሓላ ቃል ነው እንጂ በሕግ አይደለም /መዝ.109/110/፡4/፡፡ እርሱም «ፍጹም የሆነ ልጅ» ተብሎ ተጠርቷል፡፡ የተወደድክ አንባቢ ሆይ ይህ በሁለንተናው ፍጹም የሆነውና እንደ አሮን ሳይሆን እንደ መልከ ጹዴቅ ለዘላለም ሊቀካህናት የሆነው ይህ ኢየሱስ አይሻልህምን?
ዘላለማዊ ነው
ከአሮን ቤት የሆኑት የብሉይ ኪዳን ሊቃነ ካህናት የሚጎድላቸውን ነገር ስንመለከት እነርሱም ድካምን የሚለብሱ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን በጊዜና በሞት የተገደቡ መሆናቸውም ነው፡፡ የአዲስ ኪዳን ሊቀካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ግን «ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው»/ዕብ.7፡23-24/፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ በሊቀካህናትነቱ ዘላለማዊ መሆኑን ለመግለጽ የእርሱ ካህንነት እንደ መልከ ጼዴቅ መሆኑ ተነግሯል፡፡ ይህን በተመለከተ በመዝሙረ ዳዊት የተነገረው ቃል «አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ» የሚል ነው /መዝ109/110/፡4/፡፡ ይህም ቃል በዕብራውያን መልእክት ውስጥ የኢየሱስ ክርስቶስን ዘላለማዊ ክህነት ለማስረዳት ሦስት ጊዜ ያህል ተጠቅሷል /ዕብ.5፡6፤ 7፡17፤ 7፡21/፡፡
መልከ ጼዴቅ በአብርሃም ዘመን የነበረ የሳሌም ንጉሥ ነበር፤ ሆኖም ይህ ንጉሥ የልዑል እግዚአብሔር ካህንም ነበር /ዘፍ.14፡18/፡፡ የመልከ ጼዴቅ የስሙ ትርጓሜ «በመጀመሪያ የጽድቅ ንጉሥ ነው፤ በኋላም ደግሞ የሳሌም ንጉሥ ማለት የሰላም ንጉሥ ነው» ተብሎ ተነግሮናል /ዕብ.7፡2/፡፡ ስለዚህ ይህ ሰው ንጉሥ የሆነ ካህን መሆኑን እንረዳለን፡፡ በዚህ ማንነቱም ንጉሥ የሆነ ካህን ለሆነው ለኢየሱስ ፍጹም ምሳሌ ነበር፡፡ ጌታ ኢየሱስ ጽድቅንና ሰላምን የሚያመጣ ንጉሥ መሆኑ በትንቢት ተነግሯል፤ ኢሳይያስ ስለ እርሱ «ከዛሬ ጀምሮ እስከዘላለም ድረስ በፍርድና በጽድቅ ያጸናውና ይደግፈው ዘንድ በዳዊት ዙፋንና በመንግሥቱ ላይ አለቅነቱ ይበዛል፤ ለሰላሙም ፍጻሜ የለውም» ብሏል /ኢሳ.9፡7/፡፡ ይህም የሚሆነው ወደፊት ኢየሱስ የዳዊትን ዙፋን ሲወርስ ነው፡፡ ገብርኤል ለማርያም እርሱን እንደምትወልድ በነገራት ጊዜ «እርሱ ታላቅ ይሆናል፤ የልዑል ልጅም ይባላል፤ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘላለም ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም» ብሏል /ሉቃ.1፡32-33/፡፡ ይህም ጊዜ እርሱ ወደፊት ዳግመኛ ሲመጣ በሕያዋን ላይ በጽድቅ ከፈረደ በኋላ ለሺህ ዓመት በሚነግሥ ጊዜ የሚፈጸም ነው/ራእ.19 እና 20/፡፡ በዚያን ጊዜ እርሱ የጽድቅና የሰላም ንጉሥ ብቻ ሳይሆን የልዑል እግዚአብሔር ካህንም ይሆናል፡፡ ንጉሥነቱን ከክህነቱ ጋር ባንድ ላይ ይይዛል፡፡ ይህን በተመለከተ የተነገረው ትንቢትም «እነሆ ስሙ ቊጥቋጥ የሚባል ሰው በስፍራው ይበቅላል፤ የእግዚአብሔርንም መቅደስ ይሠራል፤ ክብርንም ይሸከማል፤ በዙፋኑም ላይ ካህን ይሆናል ...» ይላል /ዘካ.6፡12-13/፡፡ ስለዚህ እንደ መልከ ጼዴቅ የሆነው ክህነቱ በሙላት የሚገለጠው በሺው ዓመት መንግሥቱ ጊዜ ነው፡፡ ሆኖም በመዝ.109/110/፡4 ላይ «አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዓት ለዘላለም ካህን ነህ» ከመባሉ በፊት በቊ.1 ላይ «እግዚአብሔር ጌታዬን ጠላቶችህን የእግርህ መቀመጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው» የሚል ቃል እናነባለን፡፡ ስለሆነም ጌታ ኢየሱስ ዐርጎ ወደ ሰማይ ከገባና በእግዚአብሔር ቀኝ ከተቀመጠ ጊዜ ጀምሮ እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዓት ለዘላለም ካህን መሆኑን እንረዳለን፤ ምክንያቱም በዕብ.5፡10 ላይ «ከተፈጸመም በኋላ/በመከራ ፍጹም ከተደረገ በኋላ-ዕብ.2፡10-/»፣ በእግዚአብሔር እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ሊቀ ካህናት ተብሎ ስለተጠራ ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላላም መዳን ምክንያት ሆነላቸው» ይላል፡፡ እንዲሁም በዕብ.6፡20 ላይ እርሱም እርግጥና ጽኑ ወደ መጋረጃው ውስጥ የገባ ነው፤ በዚያም ኢየሱስ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ሊቀ ካህናት የሆነው ስለ እኛ ቀዳሚ ሆኖ ገባ» ይለናል፡፡ በእነዚህ ንባቦች መሠረትም ኢየሱስ እንደ መልከ ጼዴቅ የሆነው ክህነቱ ወደፊት በሺው ዓመት ጊዜ በሙላት የሚታይ ቢሆንም እርሱ ወደ ሰማይ ገብቶ በእግዚአብሔር ቀኝ ከተቀመጠ ጀምሮ በዚሁ ክህነት አማኞችን እያገለገለበት ያለ መሆኑን እናስተውላለን፡፡
ጌታ ኢየሱስ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን መባሉ እርሱ እንደ አሮናውያን ካህናት በሞት ያልተከለከለ ዘላለማዊ ክህነት ያለው መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ መልከጼዴቅ በነበረበት በዚያ ዘመን በሙሴ በኩል በኋላ የተሰጠው የክህነት ሕግ ባለመኖሩ ከዚህ ሰው በቀር ካህን ተብሎ የተጠራ አልነበረም፤ የዕብራውያን ጸሐፊም ስለዚህ ሰው ማንነት ሲናገር «አባትና እናት የትውልድም ቊጥር የሉትም፤ ለዘመኑም ጥንት ለሕይወቱም ፍጻሜ የለውም፤ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ልጅ ተመስሎ ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል» ብሏል /ዕብ.7፡3/፡፡ በእርግጥ ይህ መልከ ጼዴቅ የተባለው የልዑል እግዚአብሔር ካህን በባሕርዩ ሰው መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ በአብርሃም ዘመን የነበረ የሳሌም ንጉሥም እርሱ ነበር፤ በዘመኑም ይህ ሰው አብርሃም ነገሥታትን ድል ነስቶ ከተመለሰ በኋላ ከእርሱ ጋር ተገናኝቶ አብርሃምን ባርኮታል፤ አብርሃምም አሥራትን ሰጥቶት ነበር /ዘፍ.14፡18-20፤ ዕብ.7፡1-3/፡፡ ስለዚህ መልከ ጼዴቅ ከመላእክት ወገን የሆነ ወይም ልዩ ፍጡር ሳይሆን በእርግጥ ሰው መሆኑን ከእነዚህ እውነታዎች የምንረዳ ስለሆነ «አባትና እናት አልነበሩትም፤ ለዘመኑ ጥንት ለሕይወቱም ፍጻሜ የለውም» ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት ከፍተኛ ፍላጎት ያድርብናል፡፡
«የትውልድም ቊጥር የሉትም» ከሚለው አነጋገር በመጀመር ሐሳቡን ስንመረምረው ይህ ማለት በብሉይ ኪዳን ሐረገ ትውልድ ውስጥ ቊጥር የለውም ወይም አልተመዘገበለትም ማለት እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ እንዲሁም «አባትና እናት የሉትም» ማለት በብሉይ ኪዳን ውስጥ ስላልተገለጡ አልታወቁም ወይም በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት አልተመዘገቡለትም ማለት ነው፤ «ለዘመኑ ጥንት ለሕይወቱም ፍጻሜ የለውም» ማለትም ምን ጊዜ እንደተወለደና ምን ጊዜ እንደሞተ የተመዘገበ ነገር በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ የለም ማለት ነው፡፡ ባጠቃላይ ስለመልከ ጼዴቅ አባትና እናት፣ ስለትውልዱ ቊጥር፣ ስለ ዘመኑ ጥንትና ፍጻሜ የሚታወቅ ነገር የለም ማለት ነው፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ይህ ሁሉ ለምን እንዳይታወቅ አደረገ? ብሎ መጠየቁ አግባብነት አለው፡፡ በዕብ.7፡3 ላይ የተነገሩትን ቃላት በጥንቃቄ ስናጠና የልዑል እግዚአብሔር ካህን መልከ ጼዴቅ ለዘላለማዊው ካህን ለልጁ ለኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ እንዲሆን እግዚአብሔር ይህን ሆን ብሎ እንዳይታወቅ እንዳደረገው እንረዳለን፡፡ ስለዚህም መልከጼዴቅ በአብርሃም ዘመን ታይቶ ከጠፋ ከብዙ ዘመን በኋላ በዳዊት ዘመን «አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ» ተብሎ መነገሩ መልከ ጼዴቅ በክህነቱ ለአዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት ለኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ተደርጎ በእግዚአብሔር የተዘጋጀ ሰው እንደነበር ያስረዳል፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ስለእኛ ቢሞትም ሞት እርሱን ይዞ ያስቀረው ዘንድ አልቻለም /የሐ.ሥ.2፡24/፤ «ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቶ ወደፊት እንዳይሞት ሞትም እንዳይገዛው እናውቃለንና» ተብሎ ተጽፏል/ሮሜ6፡9/7፡፡ ስለዚህ የኢየሱስ የክህነት አገልግሎት በሞት የተከለከለ አይደለም፤ ከሙታን ከተነሣ በኋላ በክብር ዐርጎ በሰው እጅ ባልተሠራችው በእውነተኛይቱ ድንኳን /መቅደስ/ ውስጥ በማይለወጠው ክህነቱ የሚያገለግል ዘላለማዊ ካህን ሆኗል፡፡ ከዚያ በኋላም እርሱ ለምን ጊዜም የማይሞት በመሆኑ ሌላ ሊቀካህናት አላስፈለገንም፤ እርሱ ካረገ በኋላ ወደ ዓለም ሁሉ የላካቸው 12ቱ ደቀመዛሙርትም ሐዋርያት ናቸው እንጂ ሊቃነ ካህናት አልነበሩም፡፡ በእርግጥ እንደማንኛውም አማኝ እነርሱም በክርስቶስ ደም የተዋጁ ከመሆናቸው የተነሣ የአዲስ ኪዳን ካህናት ናቸው /ራእ.5፡9-10/፤ ነገር ግን በክርስቶስ ምትክ የተሾሙ ሊቃነ ካህናት አልነበሩም፤ አይደሉም፡፡ ዛሬም ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያምን ሰው ሁሉ ክርስቶስ ስለ እርሱ ያቀረበለትን መሥዋዕት ይዞ በእግዚአብሔር ፊት በመቅረብ ካህን ለመሆን ከመቻሉ በቀር ከክርስቶስ ወደ ሐዋርያት፣ ከሐዋርያት ወደ ተከታዮቻቸው እየተባለ ሲወርድ ሲዋረድ እስከ ዘመናችን የደረሰ የተለየ የክህነት መስመር የለም፡፡ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ በሥርዓተ ሢመት፣ በቅብዓ ክህነት የሚገኝ ክህነት ያለው በብሉይ ኪዳን በነበረው አሮናዊው ሥርዓተ ክህነት ውስጥ ነበር እንጂ በአዲስ ኪዳን አይደለም፡፡ በአዲስ ኪዳን ግን እንደዚህ ዓይነቱን ክህነት በተመለከተ «ሕጉ ምንም ፍጹም አላደረገምና ስለዚህም የምትደክም የማትጠቅምም ስለሆነች የቀደመች ትእዛዝ ተሽራለች» ተብሎ ተጽፏል /ዕብ.7፡18/፤ ስለዚህ በተሻረው በቀደመው ሥርዓተ ክህነት የሚሾሙ ካህናት በቤተክርስቲያን ውስጥ የሉም፡፡
በሐዋርያት ሥራ 20፡28 ላይ «ጳጳሳት» የተባሉት፣ በፊልጵ.1፡1 ላይ «ኤጲስ ቆጶሳትና ዲያቆናት» ተብለው የተጠሩትና እንዲሁም በሐዋርያት ሥራ 14፡23 እና በሌሎችም ክፍሎች «የቤተክርስቲያን ሽማግሌዎች» እየተባሉ የተጠሩትም ቢሆኑ በቤተክርስቲያን ውስጥ በእረኝነት ወንጌልን በማስተማርና በሌሎችም በልዩ ልዩ ተልእኮዎች የሚያገለግሉ ናቸው እንጂ መሥዋዕትን በማቅረብ ስለሰዎች በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙ ሊቃነ ካህናት አይደሉም፤ ስለሆነም በተሰጣቸው ስም «ጳጳሳት፣ ኤጲስ ቆጶሳት፣ የቤተክርስቲያን ሽማግሌዎች፣ ዲያቆናት» ተብለው ተጠርተዋል እንጂ ከሌሎች አማኞች በተለየ መልኩ «ካህናት» ወይም «ሊቃነ ካህናት» ተብለው አልተጠሩም፡፡ ነገር ግን በዚህ ባለንበት ዘመን ከዚህ እውነት ጋር በሚጋጭ መልኩ ከአማኞች ተለይተው የተወሰኑ ሰዎች ብቻ ካህናት የሚባሉበት ሥርዓት መኖሩ ከአዲስ ኪዳን እውነት ጋር የሚቃረን ነው፡፡ ምክንያቱም በአዲስ ኪዳን ዘመን ሊቀካህናት የሆነው ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን /ዕብ.2፡17፤ 9፡6-11/ ካህናት የሆኑት ደግሞ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑና ከነገድ ከቋንቋ በክርስቶስ ደም የተዋጁ አማኞች ሁሉ ናቸውና /1ጴጥ.2፡5-9፤ ራእ.1፡6፤ ራእ.5፡9-10/፡፡
አንዳንድ ጊዜ «የብሉይ ኪዳን ክህነት ከአሮን ዘር ለሆኑት ብቻ የሚሰጥ ሲሆን የአዲስ ኪዳን ክህነት ግን ዘር ሳይወሰን ከማንኛውም ዘር መካከል ለክህነት ለበቁት ሁሉ የሚሰጥ ነው» የሚል ማሻሻያ የተደረገበት ሐሳብ በክርክር መልክ ይቀርባል፡፡ ሆኖም እነዚህ ለክህነት በቅተዋል የሚባሉ ሰዎች በዚህ በአዲስ ኪዳን ዘመን በብሉይ ኪዳን የክህነት ሕግ መሠረት ቅብዓ ክህነት እየተቀቡ በተለየ ሥርዓት እንዲሾሙ መጽሐፍ ቅዱስ አያስተምረንም፡፡ ስለሆነም በአዲስ ኪዳን ከሌሎች አማኞች የተለዩ ካህናት ወይም ሊቃነ ካህናት እንዲኖሩ ማድረግ በክርስቶስ የተሻረውን ሥርዓት መልሶ መመሥረት ስለሆነ ይህ በአዲስ ኪዳን የእግዚአብሔር ቤት ለሆነችው ቤተክርስቲያን ተገቢዋ አይደለም!
የመካከለኛው አስታራቂነት
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመካከለኛነቱ ከሚሠራቸው ሥራዎች አንዱ ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር የማስታረቅ ሥራ ነው፡፡ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል የነበረው መልካም ግንኙነት ለመበላሸቱና ጠብ ለመፈጠሩ ምክንያቱ ሰው እንጂ እግዚአብሔር አይደለም፤ በሰው አለመታዘዝ የተፈጸመው ኃጢአት ሰውን ከእግዚአብሔር አጣልቶና ለይቶ በጠላትነት ስፍራ እንዲቀመጥ አድርጎታል፤ «ልዩነት የለምና ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሏቸዋል» ተብሎ እንደተጻፈ /ሮሜ3፡23/ ሰው ሁሉ ኃጢአተኛ ስለሆነ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ የሚያስፈልገው ጠላት ሆኗል፡፡ ስለሆነም መካከለኛው የሚያስታርቀው እግዚአብሔርን ከሰው ጋር ሳይሆን ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር መሆኑን ልብ ልንል ይገባል፡፡ እግዚአብሔርን በተመለከተ ግን «ታዲያ ምንድነው¬? የማያምኑ ቢኖሩ አለማመናቸው የእግዚአብሔርን ታማኝነት ያስቀራልን? እንዲህ አይሁን፤ ... ሰው ሁሉ ውሸተኛ ከሆነ እግዚአብሔር እውነተኛ ይሁን» ተብሎ ተጽፏል፤ እርሱ ከመጀመሪያ ጀምሮ በታማኝነቱና በፍጹምነቱ አለ፡፡ ሰው ግን እርሱን ስለበደለ መታረቅ የሚያስፈልገው ሆነ፡፡
የአዲስ ኪዳን መካከለኛ የሆነው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስታርቀው በሞቱ በኩል ነው፡፡ የማስታረቅ ሥራው በዋናነት የሚመለከተውም በእርሱ ያመኑትን ሳይሆን በእርሱ ያላመኑትን ማለትም ገና በጠላትነት ስፍራ ያሉትን ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ለቈላስይስ አማኞች ይህንን ሲጽፍ «እግዚአብሔር ሙላቱ ሁሉ በእርሱ እንዲኖር በእርሱም በኩል በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማይ ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዷልና፡፡ እናንተም ነውርና ነቀፋ የሌላችሁና ቅዱሳን አድርጎ በእርሱ ፊት ያቀርባችሁ ዘንድ በፊት የተለያችሁትን ክፉ ሥራችሁንም በማድረግ በአሳባችሁ ጠላቶች የነበራችሁትን አሁን በሥጋው ሰውነት በሞቱ በኩል አስታረቃችሁ» ይላል /ቈላ.1፡18-22/፡፡ ስለዚህ በሰው ሁሉ ላይ የተፈረደውን ሞት ራሱ በመሞት የማስታረቅ ሥራን ሠርቷል፡፡
ከተስፋው ቃል ርቀው የነበሩት አሕዛብም ብቻ ሳይሆኑ የተስፋ ቃል የነበራቸው እስራኤልም ኃጢአተኞች በመሆናቸው ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ አስፈልጓቸዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ይህንንም ሲገልጥ «እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥልን ግድግዳ በሥጋው ያፈረሰ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው፤ መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን ቀርበው ለነበሩት ሰላምን የምሥራች ብሎ ሰበከ» ይላል /ኤፌ.2፡13-17/፡፡ ስለዚህ ወንጌል ለእስራኤልም ይሁን ለአሕዛብ ሲሰበክ ከእነርሱ መካከል በክርስቶስ የሚያምኑ ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር ይታረቃሉ፡፡ መታረቁ የሚያስገኘውን ሰላም በመያዝም /ሮሜ5፡1/ በደስታ ይኖራሉ፡፡
እንደዚሁም «ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቷልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል፤ ይልቁንስ እንግዲህ አሁን በደሙ ከጸደቅን በእርሱ ከቊጣው እንድናለን፡፡ ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን አሁን መታረቁን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ደግሞ እንመካለን» ይላል /ሮሜ5፡8-11/፡፡ በዚህ ቃል ውስጥም ገና ኃጢአተኞች ሳለን ወይም ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት እንደታረቅን ተገልጿል፡፡ ይህም ኢየሱስን በማመን በሞቱ በኩል መታረቃችንን የሚያሳይ ነው፡፡ በሕይወቱ ማለትም ከትንሣኤ በኋላ ባለው ሕይወቱ ደግሞ ወደፊት ከሚመጣው ቊጣ/1ተሰ.1፡10/ እንድናለን፡፡ አሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ሞት ከእግዚአብሔር ጋር የታረቀ ሰው ከሚመጣው ቊጣ ስለሚድን በኢየሱስ በኩል በእግዚአብሔር ሊመካ ይችላል፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በመሞቱ በዓለም ውስጥ ያሉ ያላመኑ ሰዎችን ከእግዚአብሔር ጋር ለማስታረቅ የሚያስችለውን መሠረት ጥሏል፡፡ ይህን የማስታረቅ ሥራ ለመሥራትም የእርሱ ለሆኑት መልእክተኞቹ የማስታረቅ አገልግሎት ሰጥቷል፡፡ ይህን በተመለከተ የተጻፈው ቃል እንዲህ ይላል፤ «ነገር ግን የሆነው ሁሉ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን ከእግዚአብሔር ነው፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና በደላቸውን አይቈጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልእክተኞች ነን፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን» ይላል /2ቆሮ.5፡18-21/፡፡ ከዚህ ቃል እንደምንረዳውም የማስታረቁ አገልግሎት የሚከናወነው እግዚአብሔር በክርስቶስ መልእክተኞች ውስጥ ባኖረው የማስታረቅ ቃል በኩል ነው እንጂ እነርሱ በሚያቀርቡት ምልጃ በኩል አይደለም፡፡ በዚህ የማስታረቅ አገልግሎት እግዚአብሔር በእነርሱ ሰዎችን ይማልዳል እንጂ እነርሱ እግዚአብሔርን ስለሰዎች አይማልዱትም፤ እነርሱ በምድር ላይ ያሉ ስለክርስቶስ የሆኑ መልእክተኞች/አምባሳደሮች/ ናቸው፡፡ የተሰቀለውን ክርስቶስን እየሰበኩ/1ቆሮ.1፡23/ «ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ» ብለው ሰዎችን ይለምናሉ፡፡ ስለዚህ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ጋር ያልታረቁ ሰዎችን የሚያስታርቀው በሰማይ ስለእነርሱ እግዚአብሔርን በመለመን ሳይሆን በመልእክተኞቹ በኩል እነርሱን ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብሎ በመለመን ነው፡፡ እግዚአብሔርማ «በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበር» ተብሏል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ በመሆኑና በእርሱ የመለኮት ሙላት በመኖሩ እርሱ ስለኃጢአተኞች ሲሞት እግዚአብሔር ሰውን ከራሱ ጋር ለማስታረቅ ያለው ያለው መሻት ተረገግጧል፡፡ እርሱ ለሞት አሳልፎ የሰጠው ልጁን ነውና፡፡ ከዚህም አልፎ ደግሞ በክርስቶስ መልእክተኞች በኩል ሰዎችን ከራሱ ጋር ለማስታረቅ እነርሱን መማለዱ ወይም መለመኑ እንዴት ያለ ታላቅ ፍቅር ነው? እንደምን ያለ የጸጋ ባለጠግነት ነው? የተወደድህ አንባቢ ሆይ ምናልባት አንተ ከእግዚአብሔር ጋር ያልታረህ ከሆንክ ሁሉን የፈጠረውና ሁሉን የሚያሳልፈው ልዑል እግዚአብሔር በማስታረቅ ቃል በኩል እንዲህ ሲለምህ ይህ ልብህን አይነካውምን? እጁን ዘርግቶ በታላቅ ፍቅርና በብዙ ጸጋ እየለመነህ ባለበት በዚህ ወቅት ከእርሱ ጋር ለመታረቅ አሁኑኑ አትወስንምን?
የመካከለኛው አማላጅነት
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የመካከለኛነቱ ሌላው አገልግሎቱ ደግሞ አማላጅነቱ ነው፡፡ እርሱ ይህን የሚሠራው በእግዚአብሔር ፊት ስለሰዎች ምልጃን በማቅረብ ነው፤ እርሱ በአምላክነቱ የሚማለድ፣ ጸሎትንና ምልጃን የሚቀበል የመሆኑን ያህል በሰውነቱ ደግሞ ስለእኛ ይማልዳል፤ ሆኖም እርሱ ካረገ በኋላ አምላክ ብቻ ሳይሆን ሰውም እንደሆነ ባለማስተዋል ኢየሱስ ያማለደው በምድር ሳለ በሥጋው ወራት ብቻ ነው ወደሚል ድምዳሜ የደረሱ ብዙዎች ናቸው፤ ካረገ በኋላ ይማልዳል ማለት አምላክነቱንና ፈራጅነቱን ዝቅ የሚያደርግ እየመሰላቸው ለነፍስ እጅግ ጣፋጭ የሆነውን የእርሱን የአማላጅነት እውነታ ከማመን ጐድለዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ኢየሱስ በሥጋው ወራትም ሆነ ከዕርገቱ በኋላ እንደሚማልድ በግልጽ ይናገራል፡፡ ይህንንም ቀጥሎ በዝርዝር እንመለከታለን፡፡
በሥጋው ወራት
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በኖረበት በሥጋው ወራት ምልጃን አቅርቧል፤ ለምሳሌ ጴጥሮስን እምነቱ እንዳይጠፋ ሲያማልደው እንመለከታለን፤ ይህንንም ራሱ ኢየሱስ ሲናገር «ስምዖን ስምዖን ሆይ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ፤ እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ አማለድሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና» ብሎ በግልጥ ተናግሯል /ሉቃ.22፡31-32/፡፡ ኢየሱስ «አማለድሁ» ብሎ ከተናገረ እኛም ይህንኑ ቃል በመጠቀም አማልዷል ብለን ለመናገር እንችላለን፡፡ በዚህ ክፍል ላይ እንደተጠቀሰው ሰይጣን ያቀረበው ጸሎት ወይም ልመና ጴጥሮስንም ሆነ ሌሎቹን የጌታ ደቀመዛሙርት እንደ ስንዴ ለማበጠር እንዲፈቀድለት ነው፤ ልክ በእግዚአብሔር ፊት ቀርቦ ኢዮብ እግዚአብሔርን እንዲሰድብ ለማድረግ በሥጋው ላይ ክፉ እንዲደርስበት እንደለመነው ማለት ነው/ኢዮ.1፡9-11፤ 2፡4-6/፡፡ ጌታ «አማለድሁ» ያለው ግን ሰይጣን እንደ ስንዴ እንዳያበጥራቸው ሳይሆን የጴጥሮስ እምነት እንዳይጠፋ ነበር፤ እውነትም ጌታችን በተያዘባት ምሽት ደቀመዛሙርቱ ሁሉ ትተውት ሸሽተው ነበር/ማቴ.26፡56/፤ ጴጥሮስም ቢሆን ዶሮ ሳይጮህ ሦስት ጊዜ ክዶት ነበር/ሉቃ.22፡34ና54-60/፡፡ ስለዚህ ሰይጣን ባበጠራቸው ጊዜ ሁሉም ወድቀዋል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን የጴጥሮስ እምነት ጠፍቶ እንዳይቀር ኢየሱስ ስለእርሱ ይማልድ ነበር፤ ይህ ኢየሱስ ስለ ጴጥሮስ ወደ እግዚአብሔር ያቀረበው ምልጃ ነበር፤ ሆኖም እርሱ መካከለኛ ነውና ጴጥሮስ ለሦስተኛ ጊዜ ሲክድ እርሱን ዘወር ብሎ እንደተመለከተው እናነባለን፡፡ በዚህም ጴጥሮስ የጌታ ቃል ትዝ አለውና ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ በማልቀስ ሲመለስ እናያለን/ሉቃ22፡61-62/፡፡
ስለዚህ የኢየሱስ አማላጅነት ዋነኛ ዓላማ የእርሱ የሆኑት ማለትም አማኞች ፈተናዎችን ማለፍ አቅቷቸው በእምነት ነገር በሚወድቁ ጊዜ እምነታቸው እንዳይጠፋ ማድረግና እነርሱን ወደ ስፍራቸው መመለስ ነው፡፡ ጴጥሮስ ከዚያ በኋላ በጎቼን ጠብቅ የሚል አደራን ሲቀበል እናያለን፤ በበዓለ ሃምሳ ዕለትም ከአስራ አንዱ ጋር ቆሞ በፊት ክዶት ስለነበረውና አይሁድ ስለሰቀሉት፣ ነገር ግን ከሙታን ስለተነሣውና በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ስላለው ስለኢየሱስ በሙሉ ድፍረት ሲመሰክር እናየዋለን /የሐ.ሥ.2፡14-36/፡፡ ይህ ሁሉ የኢየሱስ የአማላጅነቱ ውጤት ነበር፡፡ ዛሬም ቢሆን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው የእርሱ ደቀመዛሙርት የሆኑ አማኞችን ሰይጣን ሊያበጥራቸው ምን ያህል እንደሚተጋ ይታወቃል፡፡ ሆኖም እኛን ለማበጠር በእኛ ላይ በክፋት የሚጸልይብን/ልመና የሚያቀርብብን/ ጠላት ያለውን ያህል ስለእኛ የሚማልድልን ኢየሱስ አለን፡፡ እንደ ጴጥሮስ በፈተናው ተሰነካክለን ብንወድቅ እንኳ ይህ የኢየሱስ አማላጅነት እኛን ወደራሱ በመመለስ እንደገና በእምነት እንድንጸና ያደርገናል፡፡
እንደዚሁም በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 17 ላይ የተመዘገበውን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በስቅለቱ ዋዜማ ያቀረበውን ጸሎት ስንመለከት የእርሱ ስለሆኑት የጸለየው የምልጃ ጸሎት እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ይህንንም በዚሁ ጸሎቱ ውስጥ ሲገልጥ «እኔ ስለ እነዚህ እለምናለሁ ስለ ዓለም አልለምንም ስለሰጠኸኝ እንጂ፤ የአንተ ናቸውና፤ የእኔም የሆነ የአንተ ነው፤ የአንተውም የእኔ ነው፤ እኔም ስለ እነርሱ ከብሬአለሁ» ብሏል /ዮሐ.17፡9-10/፡፡ እንዲሁም ይህ ምልጃ በዚያ ጊዜ ስለነበሩት ደቀመዛሙርቱ ብቻ ሳይሆን በኢየሱስ ስለሚያምኑት ሁሉ የቀረበ ምልጃ እንደሆነ ሲናገር «ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ ከቃላቸው የተነሣ በእኔ ስለሚያምኑ ደግሞ እንጂ ስለእነዚህ ብቻ አልለምንም» ብሏል/ዮሐ.17፡21/፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ በምድር እያለ ያቀረበው ይህ የምልጃ ጸሎት በእርሱ ለምናምን ሁሉ የቀረበ ነው፡፡
ኢየሱስ በሥጋው ወራት ጸሎትንና ምልጃን ስለማቅረቡ መጽሐፍ ቅዱስ ጠቅለል አድርጎ ሲናገር «እርሱም በሥጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፤ እግዚአብሔርንም ስለመፍራቱ ተሰማለት» ይላል /ዕብ.5፡7/፡፡ ይህ ቃል ጌታ ኢየሱስ በጌቴ ሴማኒ «ወዙ በምድር ላይ እንደሚወርድ እንደ ደም ነጠብጣብ» ሆኖ፣ «በፍርሃት ሲያጣጥር» በነበረ ጊዜ አጽንቶ ይጸልይ የነበረውን ጸሎትና ምልጃ ያመለከታል/ሉቃ.22፡44/፡፡ «ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር» የሚለው ቃል በዚያን ጊዜ እርሱ የነበረበትን ጥልቅ ስሜት የሚያሳይ ነው፤ በእርግጥ ራሱን በተመለከተ የጸለየው ጸሎት የተሰማለት ወይም ለጸሎቱ መልስ የተሰጠለት እርሱን እንዳይሞት በማድረግ ሳይሆን ከሙታን በማስነሣት ነበር፡፡ ይሁንና ምልጃም እንዳቀረበ ስለተነገረን በዚያ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ የእርሱ ስለሆኑቱም ያቀረበው ልመና እንደነበር ለማሰብ እንችላለን፡፡
ጌታ ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በመስቀል ላይ በነበረ ጊዜ ስለሰቀሉት ሰዎች «አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው» በማለት ማልዷል /ሉቃ.23፡34/፤ በእርሱ ስላላመኑትና ከእግዚአብሔር ጋር ስላልታረቁ ሰዎች ምልጃን ያቀረበው በዚህ ስፍራ ብቻ ነው፤ ይህን በተመለከተ ኢሳይያስ ሲናገር «ስለ ዓመፀኞች ማለደ» ብሏልና/ኢሳ.53፡12/፡፡ የዚህ ምልጃ ውጤትም ሰዎቹ ንስሐ ገብተው ከእግዚአብሔር ጋር መታረቃቸው ነው፤ ይህንንም በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የምንመለከት ሲሆን የበዓለ ሃምሳ ዕለት ሦስት ሺህ ያህል ሰዎች ሲያምኑ፣ የአርባ ዓመቱ ሽባ በተፈወሰ ጊዜ ደግሞ አምስት ሺህ ያህል ሰዎች እንዳመኑ እናነባለን /የሐ.ሥ.4፡4/፡፡ ይሁንና ቀደም ሲል በዮሐ.17፡9-10 እንዲሁም በቊ.21 ላይ እንደተመለከትነው ኢየሱስ በመደበኛነት የሚማልደው በእርሱ ለሚያምኑት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
ከዕርገቱ በኋላ
በሥጋው ወራት ያቀረበው ምልጃው ከዚያ በኋላ እስከዚህ ዘመን ድረስ በእርሱ ለሚያምኑት ሁሉ የቀረበ ምልጃ እንደሆነ ይታወቃል/ዮሐ.17፡21/፡፡ በመስቀል መሞቱ ለዚህ ዘመን አማኞችም እንደሆነ ሁሉ በዚያን ወቅት ያደረገው ምልጃውም እንደዚሁ ለዚህ ዘመን አማኞች ይቈጠርላቸዋል፡፡ የኢየሱስ ደም በዕብ.12፡24 ላይ እንደተገለጠው ከአቤል ደም ይልቅ የሚሻለውን የሚናገር የመርጨት ደም ነው፡፡ የአቤል ደም የገደለውን ቃየልን የሚከስ ነገር ሲናገር የኢየሱስ ደም ግን ስለ ሰቀሉት ሰዎች ምልጃን የሚናገር ነውና፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ማለት ኢየሱስ ካረገ በኋላ በምድር ላለ ሕዝቡ በየጊዜው የሚያስፈልገውን ነገር ከመማለድ አቋርጧል ማለት አይደለም፡፡ ካረገ በኋላም ሕዝቡን ለመርዳት ዘወትር እንደሚማልድ ከሚከተሉት የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎች ማረጋገጥ እንችላለን፡፡
1ኛ. በሮሜ 8፡34 ላይ «የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው የሚኰንንስ ማን ነው? የሞተው ይልቁንም ከሙታን የተነሣው በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው ደግሞ ስለእኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው» ይላል፡፡ እዚህ ላይ «የሞተው፣ ከሙታን የተነሣው፣ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው» የሚሉትን ቃላት ልብ ልንል ይገባል፤ የሞተውና የተነሣው የሚሉት በኃላፊ አንቀጽ/ግስ/ የተቀመጡ ሲሆን «በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው» የሚለው ግን በአሁን ጊዜ ግስ ተቀምጧል፡፡ ጌታችን በማር.16፡19 መሠረት በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ የተባለው ካረገ በኋላ ነውና፡፡ አሁንም በዚያው አለ፡፡ ይህንንም ጴጥሮስ «እርሱም መላእክትና ሥልጣናት ኃይላትም ከተገዙለት በኋላ ወደ ሰማይ ሄዶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ» በማለት ገልጦታል /1ጴጥ.3፡22/፡፡ ስለዚህ ጳውሎስ «በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው» ካለ በኋላ «ስለእኛ የሚማልደው» ሲል ካረገ በኋላ አሁን በእግዚአብሔር ቀኝ ሳለ የሚማልድ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ኢየሱስ ስለእኛ ምን እንደሚያደርግም ሲገልጥ «ስለእኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው» ብሎ ጸሐፊው በሙሉ መንፈሱና በሙሉ ስሜቱ ይናገራል፤ ሆኖም ይህን እውነት መቀበል ያልፈለጉ ሰዎች ይህንን ንባብ «ስለእኛ ይፈርዳል» ብለው በመተርጐም ቃሉን በድፍረት ለመለወጥ ሞክረዋል፡፡ ነገር ግን የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ሁሉ በመጀመሪያ በተጻፉበትና ለሁሉም ትርጓሜዎች መሠረት በሆነው የግሪክ ቋንቋም ይኸው ይማልዳል የሚለው ቃል εντνγχανει/ኤንትንግሃኒ/ ተብሎ ተቀምጧል፤ ትርጒሙም ስለሌሎች መጸለይ፣ መማለድ ማለት ነው እንጂ መፍረድ ማለት አይደለም፡፡ «ስለእኛ ይፈርዳል» ብለው ቃሉን የለወጡት ሰዎችም ቢሆኑ ይህን እውነት መቀበል ባይፈልጉም መካድ ስላልቻሉ በግርጌ ማስታወሻ ላይ «በግሪኩ ግን ይማልዳል ይላል» ብለው ለመመስከር ተገደዋል፡፡ በዚህም እነርሱ አዲስ ኪዳን መጀመሪያ ከተጻፈበት ከግሪኩ ትርጉም ጋር የሚቃረን ትርጉም ማስቀመጣቸውን አሳይተዋል፡፡
በመሠረቱ ኢየሱስ ክርስቶስ በሕያዋንና በሙታን ላይ የሚፈርድ መሆኑን ማንም ክርስቲያን ሊቀበለው የሚገባ እውነት ነው፤ ነገር ግን ፈራጅነቱን የምናስረዳበት ጥቅስ ሮሜ8፡34 አይደለም፡፡ አስፈላጊ ከሆነ ስለፈራጅነቱ ዮሐ.5፡23-30፤ 2ጢሞ.4፡1 ይመልከቱ፡፡ ስለሆነም በፈሪሃ እግዚአብሔር መኖር የሚፈልግ ክርስቲያን ጥቅሶችን በተነገሩበት ቃልና ሐሳብ መሠረት መተርጐም አለበት እንጂ ይማልዳል የሚለውን ንባብ ይፈርዳል ብሎ በመለወጥ ቃሉን መዳፈር የለበትም፡፡
2ኛ. በዕብ7፡25 ላይ ደግሞ «እነርሱ እንዳይኖሩ ሞት ስለከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው፤ እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ስለእነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራል፤ ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል» ይላል፡፡ በዚህ ቃል ውስጥ «ስለእነርሱ ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራል» ከሚለው ከዚህ ንባብ ውስጥ «ዘወትር» የሚለውን ቃል ስንመለከት የምልጃውን ክፍለ ጊዜ በግልጽ እንረዳለን፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ ክህነት እንደተሻረው እንደ አሮን ክህነት ሳይሆን ለዘመኑ ጥንት ለሕይወቱ ፍጻሜ እንደሌለው እንደ መልከ ጼዴቅ ክህነት መሆኑን ቀደም ሲል ተመልክተናል፤ የብሉይ ኪዳን ካህናት እንዳይኖሩ ሞት ስለሚከለክላቸው በየጊዜው ብዙዎች ካህናት ተሹመዋል፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ለዘላለም የሚኖር ሕያው ካህን ስለሆነ ስለሁላችን ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራል/ዕብ.7፡23-25/፡፡ «ዘወትር በሕይወት ይኖራል» የሚለው ይህ ቃል ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት የነበረውን የምድር ላይ ሕይወቱን ሳይሆን ሞትን ድል አድርጎ ከተነሣ በኋላ ለዘላለም ያለውን ሕያውነቱን የሚያሳይ ነው፡፡ እርሱ ራሱ ስለዚህ ሕያውነቱ ሲናገር «ሞቼም ነበርኩ» ካለ በኋላ «እነሆም ከዘላለም እስከዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ» ብሏል/ራእ.1፡18/፡፡ ስለዚህ ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራል የሚለው ቃል ከሙታን ከተነሣ በኋላና ዐርጎ በእግዚአብሔር ቀኝ ባለበት በአሁኑ ወቅት የሚማልድ መሆኑን የሚገልጽ ነው፡፡
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የሊቀካህናትነቱ አገልግሎት በሰማይ ባለች እውነተኛይቱ ድንኳን መሆኑን ቀደም ሲል አይተናል፡፡ «ከተናገርነውም ዋና ነገሩ ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀካህናት አለን፤ እርሱም የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፤ እርስዋም በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ናት» በማለት እርሱ በእግዚአብሔር ቀኝ ባለበት በዚያ የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ እንደሆነ ይናገራል /ዕብ.8፡1-2/፤ ይህም ሌላ ምንም ሳይሆን ስለእኛ መማለዱ ነው፤ ስለዚህ ኢየሱስ በሊቀ ካህናትነቱ የሚማልደው በግርማው ዙፋን ቀኝ በተቀመጠበት ሰማይ ነው፡፡
3ኛ. በ1ዮሐ.2፡1 «ልጆቼ ሆይ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ፤ ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፤ እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው» ይላል፡፡ እዚህ ላይ ደግሞ «ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን» የሚለውን ስንመለከት ክርስቶስ በሰማይ ስለሁላችን ጠበቃ መሆኑን እንረዳለን፡፡ እርሱ ጠበቃችን እንደሆነ ስለተነገረን እኛ ከሳሽ እንዳለብን ልናውቅ እንችላለን፤ ይህም ከሳሻችን ሰይጣን ነው፤ በትንቢተ ዘካርያስ 3፡1-2 ላይ ታላቁን ካህን ኢያሱን ይከስሰው ዘንድ ሰይጣን በስተቀኙ ቆሞ እነደነበር እናነባለን፤ በራእ.12፡10 ላይም ሰይጣን «ቀንና ሌሊት በአምላካችን ፊት የሚከሳቸው የወንድሞቻችን ከሳሽ» ተብሏል፡፡ ሰይጣን «ዓለምን የሚያስተው» መሆኑ ተነግሯል/ራእ.12፡9/፡፡ ሆኖም እርሱ አሳች ብቻ ሳይሆን ከሳሽም እንደሆነ እንመለከታለን፤ ነገር ግን ሰይጣን ክፉውን ሁሉ በእኛ ላይ በሚለምን ጊዜ ስለእኛ የሚማልድ እንዳለልን ሁሉ፣ በአምላካችን ፊት በሚከሰን ጊዜ ደግሞ የእርሱን ክስ ውድቅ የሚያደርግ ጠበቃ አለን፤ እርሱም ኢየሱስ ነው፡፡
በዚህ ዓለም ሥርዓት ሰዎች ጉዳዮቻቸውን ወደ ፍርድ ቤት ለማቅረብ ጠበቃን የሚያገኙት ገንዘብ ከፍለው ነው፡፡ ይህን ለማድረግ የገንዘብ አቅም ለሌላቸው ሰዎች ደግሞ በሕጉ መሠረት መንግሥት ጠበቃ ያቆምላቸዋል፤ በእግዚአብሔር የፍርድ ዙፋን ፊት ግን ሰዎች አስቀድመው በስዕለት መልክ ቃል በሚገቡት የገንዘብም ሆነ የንብረት ስጦታ ሊያቆሙት የሚችሉት ጠበቃ የለም፡፡ እኛ ምንም ያህል አቅምና መልካም ሥራም ቢኖረን በእግዚአብሔር ፊት ለራሳችን ጠበቃ ማቆም አንችልም፤ ነገር ግን በቃሉ ውስጥ በግልጽ እንደተነገረን «ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፤ እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው»፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ እኛ ያቆምነው ሳይሆን እግዚአብሔር ለእኛ ያቆመልን ጠበቃችን ነው፡፡
የኢየሱስ ክርስቶስ ጠበቃነት በእርሱ ያመኑት ሁሉ ድንገት በሥጋ ምክንያት ኃጢአት ቢሠሩ እንኳ አንድ ጊዜ ያገኙት የዘላለም ሕይወት እንደማይጠፋ የሚያረጋግጥ ዋስትና ነው፤ አማኞች ኃጢአትን እንዲያደርጉ አይፈቀድላቸውም፤ ስለዚህ ቃሉ ገና ሲጀምር «ልጆቼ ሆይ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ» ይላል፤ ሆኖም ጌታን በማመን ከሞት ወደ ሕይወት የተሻገርን ቢሆንም በዚህች ምድር ላይ እስካለን ድረስ ሰይጣን እያሳተን ወይም ሥጋ እያሸነፈን ኃጢአት የምንሠራበት አጋጣሚ ይኖር ይሆናል፤ ያን ጊዜ «በቃ ጠፋን የዘላለም ሞት ይፈረድብናል» እንዳንል «ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን» የሚል የዋስትና ቃል ተነገረን፤ ይህ ማለት ግን ኢየሱስ እኛ ኃጢአት በመሥራታችን ይስማማል ማለት አይደለም፤ ይህ ሊሆን የሚችል ነገር አይደለም፡፡ በምድር ሳለ ፈሪሳውያን ወደእርሱ ያመጧት በምንዝር የተያዘችውን ሴት ባይፈርድባትም ከሳሾቿን ካሳፈረ በኋላ እርስዋን «ከአሁንም ጀምሮ ደግመሽ ኃጢአት አትሥሪ» ብሏት ነበር/ዮሐ.8፡11/፤ ጴጥሮስም መካዱ ጌታን ያሳዘነው በመሆኑ ስለእርሱ ከማለደለት በኋላ ወደ እርሱ «ዘወር ብሎ» ሲመለከተው እናያለን፡፡ ዛሬም የሰይጣንን ክስ ውድቅ ለማድረግ እርሱ በጠበቃነቱ ስለእኛ ከቆመ በኋላ በቃሉና በመንፈሱ ደግሞ እኛን ለመገሠጽ ወደ እኛ ይመለከታል፤ የመካከለኛነቱ ጠባይም ይኸው ነው፡፡ በውጤቱም እኛ ኃጢአታችንን ወደመናዘዝ እንመጣለን፡፡ «በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው» ተብሎ በተጻፈው መሠረት/1ዮሐ.1፡9/ የእርሱ ከመሆናችን የተነሣ ይቅርታን እናገኛለን፤ ከዓመፃም ሁሉ እንነጻለን፡፡ በሠራነው ኃጢአት የተበላሸው ከእግዚአብሔር ጋር የነበረን ኅብረት በሙላት ይመለሳል፡፡
ከላይ በተዘረዘሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎች መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋው ወራት ብቻ ሳይሆን ካረገ በኋላም እንደሚማልድ አይተናል፡፡ ሆኖም ካረገ በኋላ ይማልዳል ማለት በምድር ላይ ሲያደርግ እንደነበረው በእያንዳንዱ ጉዳይ ስለእነርሱ ይጸልያል ማለት አይደለም፤ ይህንን በተመለከተ ሲናገርም «በዚያ ቀን በስሜ ትለምናላችሁ፤ እኔም ስለእናንተ አብን እንድለምን የምላችሁ አይደለሁም» በማለት ተናግሯል/ዮሐ.16፡26/፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ካረገ በኋላ አያማልድም ማለት አይደለም፡፡ አማኞች ልመናቸውን በጸሎት ማቅረብ በሚፈልጉ ጊዜ ራሳቸው በቀጥታ ሊጸልዩ ይችላሉ፤ ነገር ግን ልመናቸው ተቀባይነት እንዲያገኝ በስሙ ሊጸልዩ ያስፈልጋል እንጂ እርሱ ይለምንልኛል በማለት ሳይጸልዩ መቅረት የለባቸውም፤ ጌታ በዚህ ቃል እየነገራቸው ያለው ይህንን ነው እንጂ ካረገ በኋላ እንደማያማልድ አይደለም፤ ካረገ በኋላ እንደሚያማልድማ ቀደም ሲል በስፋት እንዳየነው «በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው ደግሞም ስለእኛ የሚማልደው» /ሮሜ8፡34/፣ እንደዚሁም «ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራል» /ዕብ.7፡25/ ተብሎ ተነግሮናል፡፡ በስሙ መጸለይ ራሱ ጸሎታችን ከእርሱ የተነሣ ወይም ስለእርሱ ተሰሚነት እንዲኖረው መጠየቅ ስለሆነ የእርሱን መካከለኛነት ወይም አማላጅነት የሚያሳይ ነው፤ ምልጃውም እኛ መለመን ያለብንን እርሱ መለመኑን የሚያሳይ ሳይሆን ቀደም ሲል እንደተገለጠው እርሱ ራሱ እምነታችን እንዳይጠፋ፣ በምንወድቅ ጊዜ ከውድቀታችን እንንድንነሣ፣ በምንደክም ጊዜ ከድካማችን እንድንበረታ፣ በሚያስፈልገን ጊዜ ሁሉ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ የሚያደርገው ምልጃ ነው፡፡ ይህን ምልጃውን በሰማይ እንዴት እንደሚያከናውነው ባይገባን እንኳ በግልጽ እንደተጻፈው «ስለእኛ ይማልዳል»፣ «ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራል» ብለን አስረግጠን ልናምንና ልንናገር ይገባል፡፡
የእግዚአብሔር ቀኝ
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካረገ በኋላ በእግዚአብሔር ቀኝ መቀመጡ የሚያሳየው በአምላክነቱ ከአብ ጋር እኩል መሆኑን አይደለምን? እንዲህስ ከሆነ እርሱ በአምላክነቱ እንዴት ያማልዳል? አምላክ ከአምላክ ያማልዳልን? የሚል ጥያቄ ብዙ ጊዜ ሲነሣ ይሰማል፡፡ ይህም ጥያቄ የሚመጣው ክርስቶስ ካረገ በኋላ ስላለበት የእግዚአብሔር ቀኝ ምንነትና እርሱ በዚያ ስላለበት ባሕርዩ ካለመረዳት ነው፡፡ «በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ» የሚለውን ንባብ ከአብ እኩል ሆኖ ተቀመጠ በሚል መልክ ከመረዳት የሚነሣ ጥያቄ ነው፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ቀኝ መቀመጥ ከአብ ጋር እኩል መሆንን የሚያሳይ ከሆነ ከዕርገቱ በፊት ከአብ ጋር እኩል አልነበረም ወደሚል ስህተት የሚወስድ ይሆናል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ክብር ለእርሱ ይሁንና ከማረጉ በፊት በሥጋው ወራት እያለም ከአባቱ ጋር እኩል ነው፡፡ እርሱ በቤተልሔም ግርግም ተኝቶ ሳለ፣ ወደ ግብፅ በተሰደደ ጊዜም፣ እየታዘዘላቸው በናዝሬት በኖረበት ወራት ሁሉ፣ በዮርዳኖስ ወንዝ ቆሞ ሳለ፣ በገሊላ በሰማርያና በይሁዳ ሲመላለስ በነበረ ጊዜ፣ በጌቴሴማኒ በፍርሃት ሲያጣጥር፣ በመስቀል ላይ ተቸንክሮም ሳለ፣ ወደመቃብርም ወርዶ በታችኛይቱ የምድር ክፍል በገባ ጊዜም ከአብ ጋር እኩል ነበር፡፡ ወንጌላዊ ዮሐንስ አይሁድ ለምን ሊገድሉት እንደፈለጉ ሲያስረዳን «ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ...» በማለት ጽፏል /ዮሐ.5፡18/፡፡ እርሱ ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም «እኔና አብ አንድ ነን»/ዮሐ.10፡30/፣ «እኔን ያየ አብን አይቷል»/ዮሐ.14፡9/፣ «ለአብ ያለው ሁሉ የኔ ነው»/ዮሐ.16፡15/ በማለት በምድር ሳለ ከአብ ጋር ያለውን እኩልነት ገልጧል፡፡ እርሱ በእግዚአብሔር ቀኝ በተቀመጠ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሰው ከመሆኑ በፊት፣ በሰውነቱም ወራት፣ አሁንም ምን ጊዜም ከአብ ጋር እኩል ነው፡፡ ስለዚህ ክርስቶስ በምድር ላይ ሳለ ሰው ብቻ ሳይሆን አምላክም ነው፤ የዚያኑ ያህል በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ሳለም አምላክ ብቻ ሳይሆን ሰውም ነው፡፡ ይህን መረዳት ብቸኛው መካከለኛ እርሱ መሆኑን ለመረዳት ያስችላል፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ተነሥቶ ወደ ሰማይ ያረገው በዚያው መለኮት በተዋሐደው ሰውነት መሆኑን በቅድሚያ ማስተዋል ካረገ በኋላ ያለውን የክርስቶስን ማንነት ለመረዳት ወሳኝ ነጥብ ነው፡፡ ከሞት ከተነሣ በኋላ መቃብሩ ባዶ እንደሆነና ሥጋው እንደተነሣ በብዙ ማስረጃዎች ተረጋግጧል፡፡ ሐዋርያት በዝግ ቤት እያሉ በመካከላቸው ሲገለጥ መንፈስን ያዩ በመሰላቸው ጊዜ «በእኔ እንደምታዩት መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውም» ብሎ መናገሩና ይህንንም ለማረጋገጥ በፊታቸው ምግብ መብላቱ አንዱ ማስረጃ ነው/ሉቃ.24፡36-43/፡፡ ሌላው ማስረጃ ደግሞ ክርስቶስ ከሞት መነሣቱን ካላየሁ አላምንም ያለው ቶማስ ከስምንት ቀን በኋላ እጁን በጎኑ አግብቶ ዳስሶ ማመኑን የሚያስረዳው ክፍለ ንባብ ነው /ዮሐ.20፡26-27/፡፡ ከሞት በተነሣው በዚያው ሰውነት አርባ ቀን እየታያቸው በምድር ላይ ከቆየ በኋላ በ40ኛው ቀን ሐዋርያት ሁሉ ደመና ከዓይናቸው ሰውራ እስክትቀበለው ድረስ እያዩት ዐርጓል /የሐዋ.ሥራ1፡9-11/፡፡ ካረገ በኋላም እስጢፋኖስ ባየው ጊዜ «እነሆ ሰማያት ተከፍተው የሰውን ልጅ በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ» ብሏል/የሐ.ሥ.7፡55/፤ ጌታ ራሱ ለሳውል በደማስቆ መንገድ በተገለጠ ጊዜም «አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ እኔ ነኝ» በማለት ስለራሱ ተናግሯል/የሐ.ሥ.22፡8/፤ እንዲሁም ለዮሐንስ በፍጥሞ ደሴት በተገለጠ ጊዜ አምላክም ሰውም መሆኑን በሚያመለክት ቃል «ፊተኛውና መጨረሻው እኔ ነኝ ሞቼም ነበርሁ፤ እነሆም ከዘላለም እስከዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ» ይላል/ራእ.1፡18/፡፡ ስለዚህ በዚያው መለኮት በተዋሐደው ሰውነቱ ከሞት ተነሥቶ ወደ ሰማይ ማረጉና በእግዚአብሔር ቀኝ መቀመጡ እርግጥ ነው /ማር.16፡19/፡፡
ይሁን እንጂ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ ሲባል እግዚአብሔር ቀኝና ግራ አለውን? የሚል ጥያቄም ሊነሣ ይችላል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር «መንፈስ» መሆኑን በግልጽ ስለሚነግረን/ዮሐ.4፡24/ የሚዳሰስ አካል እንዳላቸው ፍጡራን ግራና ቀኝ የሌለው መሆኑ ከማንም ክርስቲያን የተሰወረ አይደለም፡፡ ታዲያ ኢየሱስ የተቀመጠበት የእግዚአብሔር ቀኝ የት ነው? እንደሚታወቀው «ቀኝ» የሚለውን ቃል እኛ ስንጠቀምበት መልካም የሆነ፣ የተመረጠና የከበረ ስፍራን ይገልጣል፡፡ በተለይም የንጉሥ ቀኝ በጣም የከበረ ስፍራ ነው፡፡ ንጉሥ በቀኙ የሚያስቀምጠው የሚያቀርበውን የሚያከብረውን ሰው ነውና፡፡ በተለይም ንግሥቲቱን በቀኙ ያስቀምጣል /መዝ.44(45)፡9/፡፡ ኢየሱስም «በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ» ሲባል ባረገበት ሰውነት ከፍ ባለ የክብር ስፍራ መቀመጡን ያመለክታል፡፡ መዝሙረኛው ዳዊት ስለዚህ ነገር አስቀድሞ አይቶ ሲናገር «እግዚአብሔር ጌታዬን ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው» በማለት ተናግሮ ነበር ፡፡ ይህንንም ቃል በአዲስ ኪዳን በተደጋጋሚ ተጠቅሶ የምናገኘው ሲሆን በተለይም ጴጥሮስ የበዓለ ሃምሳ ዕለት በሰበከው ስብከት ውስጥ ክርስቶስ ሞቶ ከተነሣ በኋላ ወደ ሰማያት ወጥቶ የሚገኝበት ስፍራ የእግዚአብሔር ቀኝ እንደሆነ ለመግለጽ በማስረጃነት ጠቅሶት እናገኛለን/የሐ.ሥ.2፡33-36/፡፡ ይህም የእግዚአብሔር ቀኝ የተባለው የክብር ስፍራ የሚገኘው «በሰማያት» እንደሆነ ተጽፏል፡፡ ይኸውም «ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል» የሚል ነው/ኤፌ.1፡19-21/፡፡ በዚህ ቃል ውስጥ እግዚአብሔር በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ያስቀመጠው ከሙታን ያስነሣውን እንደሆነ መነገሩ ኢየሱስ በእግዚአብሔር ቀኝ የተቀመጠው ከሞት በተነሣበት ሰውነቱ እንደሆነ ያረጋግጣል፡፡ ይህ ሰማያዊ ስፍራ እርሱ ስለእኛ ራሱን እጅግ በማዋረዱ ምክንያት የተሰጠው የክብር ስፍራ ነው፤ ይህን በተመለከተም «እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፤ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፤ በምስሉም እንደሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፤ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ፡፡ በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር ያለልክ ከፍ ከፍ አደረገው፤ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው» ተብሏል/ፊልጵ.2፡6-11/
በመሠረቱ «ተቀመጠ» የተባለው እየታየ ያረገው የክርስቶስ ሰውነት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔር ቀኝ የተባለው ከላይ እንደተመለከትነው ክርስቶስ በሰውነቱ የተቀመጠበት ሰማያዊ የክብር ስፍራ ነው፤ ይህም ስፍራ እርሱ የእርሱ ከሆኑት ጋር በሰማይ አሁን ያለበት ቦታ ነው፤ ይህን ለመረዳትም ቀጥሎ የተገለጡትን የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎችን መመልከቱ ጠቃሚ ነው፡፡
1. ኢየሱስ ያለበት ቦታ «ገነት» መሆኑን ራሱ ከተናገረው ቃል እንገነዘባለን፤ ይህም ከእርሱ ጋር ከተሰቀሉት ክፉ አድራጊዎች መካከል «በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ» ላለው ሰው «ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ» ብሎ በተናገረው ቃል ታውቋል /ሉቃ.23፡43/፡፡ «ገነት» የሚለው ቃል በብሉይ ኪዳን ውስጥ በቅድሚያ ኤድን በተባለች ቦታ እግዚአብሔር የተከላትን፣ ከኤድን የሚወጣ ወንዝ የሚያጠጣትን፣ ደስ የሚያሰኙና ለመብላት መልካም የሆኑ ዛፎች የበቀሉባትን ስፍራ ያመለክታል፡፡ ይህንንም የምንረዳው ዘፍ.2፡8-17 ያለውን ስናነብ ነው፡፡ ይህc ስፍራ የመጀመሪያው ሰው አዳም በኃጢአት ከመውደቁ በፊት በደስታ እንዲኖርባት እግዚአብሔር ያዘጋጀለት በምድር ላይ ያለች ስፍራ ነበረች፡፡ በዘፍ.2፡8 ላይ «እግዚአብሔር አምላክም በምሥራቅ በዔድን ገነትን ተከለ የፈጠረውንም ሰው በዚያ አኖረው» ይላል /ቊ.15ንም ተመልከቱ/፡፡ በአዲስ ኪዳን ግን ሁለተኛው አዳም /ሁለተኛው ሰው/ ኢየሱስ ክርስቶስ /ሮሜ5፡14፤ 1ቆሮ.15፡47/ የእርሱ ከሆኑት ጋር የሚኖርበት ሰማያዊ ስፍራ እንደሆነ «ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ» ባለው ቃል እንረዳለን፡፡ ይህም ከሞት በኋላ ነፍሳት ከክርስቶስ ጋር የሚኖሩበት ስፍራ «ገነት» መሆኑን ያመለክታል፡፡ ጳውሎስም ስለራሱ በ3ኛ መደብ ሲናገር «... እስከ ሦስተኛው ሰማይ ተነጠቀ» ካለ በኋላ «... ወደ ገነት ተነጠቀ ሰውም ሊናገር የማይገባውን የማይነገረውን ቃል ሰማ» ብሎ መናገሩ ገነት በአዲስ ኪዳን በምድር ላይ ያለች ቦታ ሳትሆን በሰማይ ያለች ስፍራ መሆኗን ያስረዳል /2ቆሮ.12፡2-4/፡፡ ስለዚህ ገነት ጌታ እስኪመጣ ድረስ ከዚህች ዓለም የተለዩ አማኞች ከክርስቶስ ጋር የሚኖሩባት ሰማያዊ ስፍራ ናት፡፡
2. ኢየሱስ አገልጋዮቹን እርሱ በሚኖርበት ቦታ እንደሚያኖራቸው ራሱ ተናግሯል፤ ይህንንም «የሚያገለግለኝ ቢኖር አባቴ ያከብረዋል፤ እኔ ባለሁበት አገልጋዬ ደግሞ በዚያ ይሆናል» ብሎ ገልጦታል /ዮሐ.12፡26/፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ አሁን ያለው «ለአገልጋዮቹ በተዘጋጀው ስፍራ» ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ወደፊትም ዳግመኛ ሲመጣ የእርሱ የሆኑትን የሚወስደው እርሱ ወዳለበት መሆኑን ሲናገር «ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፤ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ ትሆኑ ዘንደ ሁለተኛ እመጣለሁ፤ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ» ብሏል/ዮሐ.14፡3/፤ ይህም አማኞች በትንሣኤ አካልም የሚወሰዱት ወደዚያው ስፍራ መሆኑን ያሳያል፡፡ በቈላ.3፡1 ላይም «እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ» ተብሎ የተጻፈልን ቃል ክርስቶስ ተቀምጦ ያለበት የእግዚአብሔር ቀኝ እኛም ከእርሱ ጋር በክብር የምንሆንበት በላይ በሰማይ ያለ ስፍራ መሆኑን ያሳያል፡፡ 3. በዕብ.8፡1-2 ላይ ቀደም ሲል የተመለከትነው ቃልም ኢየሱስ «በሰማያት በግርማው ቀኝ የተቀመጠ ሊቀካህናት» መሆኑን ከተናገረ በኋላ «እርሱም የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፤ እርሷም በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ናት» ይላል፡፡ በዚህ ቃል መሠረትም ኢየሱስ የተቀመጠበት በሰማያት ያለው የግርማው ዙፋን ቀኝ፣ «ሰማያዊቱ» መቅደስ መሆንዋን እንገነዘባለን፡፡
ከላይ በተጠቀሱት ሦስት ማስረጃዎች መሠረት ኢየሱስ ያለበት ቦታ «ገነት» ወይም «አገልጋዮቹን የሚያኖርበት ቦታ» ወይም «ሰማያዊቱ መቅደስ» መሆናቸውን አይተናል፡፡ እነዚህም የተለያዩ ቦታዎች ሳይሆኑ በተለያዩ ቃላት የተጠራ አንድ ቦታ ነው፡፡ ኢየሱስ «በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ» የሚለውን ንባብ ካየን በኋላ ኢየሱስ ያለበትን ሰማያዊ ቦታ ስንመለከት የእግዚአብሔር ቀኝ የተባለው ቦታ ገነት ወይም ሰማያዊ ቤታችን ወይም ሰማያዊ መቅደስ መሆኑን እንረዳለን፤ እርሱ ካረገ በኋላ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ ማለት ከአብ እኩል ሆኖ ተቀመጠ ማለት ከሆነ ግን ይህ በራሱ ክርስቶስ ከጊዜ በኋላ ከአብ ጋር እኩል እንደሆነ አድርጎ የሚገልጽ ስለሆነ ስህተት ነው፡፡ በእግዚአብሔር ቀኝ መቀመጡ በሰማይ በሰውነቱ የሚገኝበትን የክብር ስፍራ የሚያመለክት ነው፤ እንዲሁም በምድር ላይ በሰውነቱ ሲመላለስ መለኮቱ እንዳልተለየው ሁሉ በሰማይም መለኮቱ ከሰውነቱ መዘንጋት የለብንም፡፡ ተዋሕዶው ዘላለማዊ ነው፡፡ «በእርሱ የመለኮት ሙላት በሰውነት ተገልጦ ይኖራል» ተብሎ የተጻፈው ቃል ለዘላለም እውነት ነው /ቈላ.2፡9/፡፡ በመሆኑም ሥጋው ከመለኮት ጋር ባለው ተዋሕዶ በሰማይ በእግዚአብሔር ቀኝ እንደሚገኝ ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ ከሚለው ንባብ ውስጥ «ተቀመጠ» የሚለውን ቃል በመውሰድ ተቀመጠ ሲባል ሥራውን ጨርሶ ያለምንም ሥራ ዐርፎ ቁጭ አለ ማለት ነው የሚል ትርጒም በመስጠት ክርስቶስ በሰማይ ምንም አገልግሎት የሌለው የሚመስላቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን በዕብ.8፡1-2 ላይ «በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ» መሆኑ ከተነገረ በኋላ «የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው» መባሉን ማስተዋል ተገቢ ነው፤ እንዲሁም በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ የተባለውን ያህል በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ መታየቱንም ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ እስጢፋኖስ በተወገረ ጊዜ ወደ ሰማይ ትር ብሎ ተመለከተና «እነሆ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ» ብሎ ተናግሯል /የሐ.ሥ.7፡56/፡፡ በዮሐንስ ራእይ 5፡6 ላይም «በዙፋኑና በአራቱ እንስሶች መካከልም በሽማግሌዎችም መካከል እንደታረደ በግ ቆሞ አየሁ» የሚል ቃል እናነባለን፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ «በእግዚአብሔር ቀኝ» መቀመጡን ብቻ ሳይሆን ቆሞ መታየቱንም መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳል፡፡
ኢየሱስ በእግዚአብሔር ቀኝ «ተቀመጠ» መባሉ ግን መሥዋዕት ከማቅረብ አንጻር መሆኑ ተገልጿል፤ «ሊቀካህናት ሁሉ ዕለት ዕለት እያገለገለ ኃጢአትን ሊያስወግዱ ከቶ የማይችሉትን እነዚያን መሥዋዕቶች ብዙ ጊዜ እያቀረበ ቆሞአል፤ እርሱ ግን ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ» የሚለው ቃል ይህን የሚያስረዳ ነው/ዕብ.10፡11-12/፡፡ ስለሆነም ተቀመጠ ሲል በመስቀል ላይ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ የሠራውን የቤዛነት ሥራው መጠናቀቁን የሚያሳይ ነው እንጂ በሰማይ ምንም ዓይነት አገልግሎት የማይሰጥ መሆኑን የሚያሳይ አይደለም፡፡
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ መስቀል ላይ የማዳን ሥራውን በጨረሰ ጊዜ «ተፈጸመ» ብሎ መናገሩ/ዮሐ19፡30/ እርሱ በሰማይ ምንም ዓይነት የምልጃ አገልግሎት እንደሌለው ለማሳየት የሚጠቀስበት ሁኔታም አለ፤ ነገር ግን ይህም ቢሆን ጌታ ወደዚህ ዓለም የመጣበትን ዓላማ ማለትም በምድር ላይ መሥራት የነበረበት ሥራ መፈጸሙን የሚያመለክት ነው፤ ይህንንም ራሱ ሲናገር «እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ በምድር ፈጽሜ አከበርሁህ» ብሏል /ዮሐ.17፡4/፡፡ በሌላ ስፍራ ደግሞ «...የዘላለምን ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም» ይላል/ዕብ.9፡12/፡፡ ስለዚህ በሰማይ በእግዚአብሔር ቀኝ ሆኖ ስለእኛ ይማልዳል ማለት በመስቀል ላይ የፈጸመውን ሥራ ይደጋግማል ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን እኛ ወደፊት በምንኖርበት በዚያ ስፍራ በትስብእቱ መኖሩ /መገኘቱ/ ስለእኛ ነውና በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር ስንቀርብ እርሱ ስለእኛ ይታያል ማለት ነው፤ እንደዚሁም በዚያች በሰማያዊት መቅደስ ውስጥ ሊቀካህናት እንደመሆኑ መጠን የካህንን የማማለድ ሥራ እየሠራ ያገለግላል ማለት ነው/ዕብ.8፡2/፤ የማማለድን ሥራ የሚሠራው እንዴት እንደሆነ እርሱ ያውቃል፤ እኛም በቃሉ የተነገረንን ያህል ስለእኛ እንደሚማልድ ወይም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት እንደሚኖር እናውቃለን፡፡
እርሱ «ተፈጸመ» ባለው የመስቀል ላይ ሥራው ከኃጢአት ወደ ጽድቅ የሚያሸጋግረን ሲሆን አሁን እያከናወነው ባለው ምልጃው ደግሞ ከደረስንበት ጽድቅ እንዳንወድቅ፣ ወደነበርንበት እንዳንመለስና እርሱን ወደመምሰል ተለውጠን የተዘጋጀልንን ክብር እንድንወርስ ያግዘናል፡፡ አማኝ በነፍሱ ከእግዚአብሔር ጋር ከመታረቁ በተጨማሪ ዕለት ዕለት የሚያስፈልገውን የሚረዳ ጸጋ ለማግኘት ወደዚህ አንድ መካከለኛ ቀርቦ ችግሩን ቢናገር መፍትሔ ለማግኘት ይችላል፡፡ እርሱ የማንም ሰው ነፍስ ወደ ሌላ ፍጡር የምትሄድበት ምንም ምክንያት እንዳይኖራት ተደርጎ ከእግዚአብሔር የተሰጠ አማላጅ ነው፤ እርሱ በማዳን ሥራው ነፍሳችንን ያዳነውን ያህል በአማላጅነቱ ደግሞ በየዕለቱ ስለእኛ ይማልዳል፡፡
በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ወደ እግዚአብሔር መቅረብ
በብሉይ ኪዳን በሕጉ መጽሐፍ ውስጥ «ከዚህም በኋላ ኃጢአትን እንዳይሸከሙ እንዳይሞቱም የእስራኤል ልጆች ወደ መገናኛው ድንኳን አይቅረቡ» የሚል ቃል እናነባለን /ዘኁል.18፡22/፡፡ በአዲስ ኪዳን ግን «ሕጉ ምንም ፍጹም አላደረገምና ስለዚህ የምትደክም የማትጠቅምም ስለሆነች የቀደመች ትእዛዝ ተሽራለች፤ ወደ እግዚአብሔርም የምንቀርብበት የሚሻል ተስፋ ገብቷል» የሚል ቃል እናነባለን/ዕብ.7፡19/፡፡ እንዲሁም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የሞተው እኛን ወደ እግዚአብሔር ለማቅረብ መሆኑን ሲገልጽ «ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቷልና» ይላል/1ጴጥ.3፡18/፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በተሰቀለ ጊዜ «የቤተመቅደሱ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት መቀደዱም» ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ የሚያስችል በር መከፈቱን የሚያሳይ ነው/ማቴ.27፡51/፡፡ በመሆኑም በክርስቶስ የምናምን ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ለምንገናኝበት ለማናቸውም ጉዳይ በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር መቅረብ እንችላለን፡፡
ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ እንድንችል ያደረገንም ምን እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ሲነግረን «እንግዲህ ወንድሞች ሆይ በመረቀልን በአዲስና በሕያው መንገድ ወደ ቅድስት በኢየሱስ ደም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል እንድንገባ ድፍረት ስላለን፣ በእግዚአብሔርም ቤት ላይ የሆነ ታላቅ ካህን ስላለን፣ ከክፉ ኅሊና ለመንጻት ልባችንን ተረጭተን፣ ሰውነታችንንም በጥሩ ውኃ ታጥበን፣ በተረዳንበት እምነት በቅን ልብ እንቅረብ» ይላል /ዕብ.10፡19-22/፡፡ በዚህም መሠረት በኢየሱስ ሞት ማለትም በደሙና በሥጋው በኩል ለመግባት ያገኘነው ድፍረት እና እርሱ ስለእኛ ታላቅ ካህን መሆኑ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ያስችለናል፡፡ ስለሆነም ወደ እግዚአብሔር መቅረብ የሚቻለው በክርስቶስ በኩል ብቻ ነው፤ እርሱም ሲናገር «እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም» ብሏል/ዮሐ.14፡6/፡፡ ይሁንና ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ እየፈለጉ የመቅረቢያ መንገዱን ባለማወቅ ብቻ ሰውና እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በተቀራረበበት በዚህ በአዲስ ኪዳን ዘመን በሩቅ ሆነው የሚታዩ ሰዎች ጥቂቶች አይደሉም፡፡ የዚህም መንስኤው ብዙዎች ኃጢአተኛነታቸውን በማሰብ ራሳቸውን ከእርሱ በጣም ስለሚያርቁ ነው፤ በእርግጥ ይህ ኃጢአተኝነትን ማመን አስፈላጊ ነው፡፡ ነገር ግን ክርስቶስ ስለኃጢአታችን መሞቱን ማመን ከዚያ በላይ አስፈላጊ ነው፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ የምናምን በኃጢአታችን ምክንያት ራሳችንን ከእግዚአብሔር ማራቅ የለብንም፤ ይልቁኑ «ከክፉ ኅሊና ለመንጻት ልባችንን ተረጭተን» ማለትም ውስጣዊ ማንነታችንን በደሙ አንጽተን፣ እንዲሁም «ሰውነታችንን በጥሩ ውኃ ታጥበን» ማለትም ውጫዊ ማንነታችን ወይም አካሄዳችንን በእግዚአብሔር ቃል አንጽተን ወደ እግዚአብሔር ልንቀርብ ያስፈልጋል፡፡
አማኞች በግልም ይሁን በኅብረት ወደ እግዚአብሔር ሲቀርቡ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ሊሆን እንደሚገባ መረዳት ይኖርባቸዋል፤ አማኞች ወደ እግዚአብሔር ከሚቀርቡባቸው መንገዶች መካከል አምልኮ፣ ምስጋና፣ ልመና እና ምልጃ ዋና ዋናዎቹ መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ ሁሉንም ለእግዚአብሔር ስናቀርብ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ሊሆን ይገባል፡፡ ይህም የምናደርገውን ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በማድረግ ይገለጣል፤ ይህንንም እናደርግ ዘንድ መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር «እግዚአብሔር አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ በቃል ቢሆን በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት» ይላል /ቈላ.3፡17/፡፡ ስለሆነም አምልኮን፣ ምስጋናን፣ ልመናንና ማቅረብ ያለብን በኢየሱስ ስም ብቻ ነው፡፡
መካከለኛነቱና አምላክነቱ
ኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊና እውነተኛ አምላክ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጣል፤ ለምሳሌ ዮሐንስ በወንጌሉ ላይ «ቃልም እግዚአብሔር ነበረ» /ዮሐ1፡1/ ሲል ጳውሎስ ደግሞ በሮሜ መልእክት ውስጥ «እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው» በማለት ጽፏል /ሮሜ9፡5/፡፡ ከእነዚህ ማስረጃዎች እንደምንረዳው ኢየሱስ ክርስቶስ ከዘላለም ከአብ ጋር የነበረ ዘላለማዊ አምላክ መሆኑን ነው፡፡ በአምላክነቱ ከአብ አያንስም አንድ ነው እንጂ፤ ይህንንም ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ «እኔና አብ አንድ ነን» ብሎ አረጋግጧል /ዮሐ.10፡30/፡፡ ሰው መሆኑ አምላክነቱን አላስቀረውም፤ ሰው ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ በሥጋው ወራት ሁሉ አምላክም ሰውም ነው እንጂ ሰው ብቻ አይደለም፤ ካረገ በኋላም ቢሆን በትንሣኤ አካል ባለው ማንነቱ ስናየው አምላክ ሰውም ነው እንጂ አምላክ ብቻ አይደለም፡፡
ሆኖም ኢየሱስ ክርስቶስን ካረገ በኋላ በአምላክነቱ ብቻ የሚረዱት ወገኖች «እንደሚማልድ የተነገረለት እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ አይደለም፤ እግዚአብሔር አብና እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም ተነግሮላቸዋል፤ እግዚአብሔር አብ እንደሚማልድ በኤር.7፡25 እና በ2ቆሮ.5፡20 ላይ የተነገረ ሲሆን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እንደሚማልድ ደግሞ በሮሜ.8፡26-27 ላይ ተነግሮአል፡፡ ስለዚህ ሦስቱም የሚማልዱ ከሆነ ማን ከማን ያማልዳል?» የሚል ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡ በዚህ ጥያቄ ውስጥ የተጠቀሱት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ትክክለኛ ሐሳባቸው ምን ማለት እንደሆነ በትዕግሥትና በልበ ሰፊነት መመልከት እውነቱን በትክክል ለመረዳት ያስችላል፤ ስለሆነም በመቀጠል ሁሉንም በየተራ እናያቸዋለን፡፡
በቅድሚያ እስኪ «አብ እና መንፈስ ቅዱስም እንደ ኢየሱስ እንደሚማልዱ ያስረዳሉ» የተባሉትን ጥቅሶች እንመልከታቸው፡፡ 1ኛ. ሀ/ ኤር7፡25 «አባቶቻችሁ ከግብጽ ምድር ከወጡበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፣ በየዕለቱ እየማለድሁ ነቢያትን ልኬባችሁ ነበር፡፡»
ይህ ቃል እግዚአብሔር አብ ከእርሱ ወደሚበልጥ ሌላ አካል የሚማልድ መሆኑን ለማስረዳት የተነገረ አለመሆኑን በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ ቃሉ በግልጽ የሚያስረዳው እውነት ቢኖር እግዚአብሔር እየማለደ ነቢያትን የላከው ወደ ሕዝቡ ወደ እስራኤላውያን መሆኑ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ሕዝቡ ከሕጉ ፈቀቅ ሲሉ ወደ እርሱ እንዲመለሱ ለማድረግ እግዚአብሔር ነቢያትን ይልክባቸው እንደነበር ጥቅሱ ያስረዳል፡፡ ነገር ግን «በየዕለቱ እየማለድሁ» የሚለው ቃል «በየዕለቱ ምልጃ እያቀረብሁ» ማለት ሳይሆን «በየቀኑ በማለዳ /በጠዋት/ እየተነሣሁ» ማለት ነው፤ በእንግሊዘኛ መጽሐፍ ቅዱሶች ውስጥ «... daily rising up early ... ማለትም በየቀኑ በማለዳ እየተነሣሁ» ይላል /JND, KJV ተመልከት/፤ ስለዚህ በዚህ ጥቅስ ውስጥ የተነገረው «እየማለድሁ የሚለው የአማርኛ ቃል አማላጅነትን የሚያመለክት አይደለም፡፡ ጥቅሱ የሚያስረዳው እግዚአብሔር ሕዝቡን ወደራሱ ለመመለስ በየማለዳው ሁልጊዜ ነቢያትን ከመላክ እንዳላቋረጠ ብቻ ነው፡፡
ለ/ 2ቆሮ.5፡20 «እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልእክተኞች ነን፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለክርስቶስ እንለምናለን» በዚህ ቃል ውስጥ «እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ» የሚለው ቃል ቀደም ሲል ስለ መካከለኛው የማስታረቅ ሥራ ሲብራራ እንደተገለጸው እግዚአብሔር ወደ ሕዝቡ በሚልካቸው የወንጌል መልእክተኞች በኩል ሕዝቡን እንደሚማልድ ያመለክታል፡፡ ይህንንም ለመረዳት «በእኛ» የሚለውን ቃል ማስተዋሉ ጠቃሚ ነው፤ እነርሱ ማለትም ስለ ክርስቶስ መልእክተኞች የሆኑት «ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ» እያሉ በተቀበሉት «የማስታረቅ ቃል» ወይም በወንጌል ስብከት ሕዝቡን ይለምናሉ፡፡ ይህም ወደ ሰው የተላከ የእግዚአብሔር ምልጃ /ልመና/ ነው፡፡ ይህን ቃል የሚያነብና ሲነገር የሚሰማ ሰው እግዚአብሔር ለእኛ ለሰው ልጆች ምን ያህል ፍቅር እንዳለውና ይህም ፍቅር እግዚአብሔር እኛ ከእርሱ ጋር እንድንታረቅ በመልእክተኞቹ በኩል በተደጋጋሚ በመማለዱ እንደተገለጠ ሊረዳ ይገባዋል፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቡን በመልእክተኞቹ የሚማልደው በጸሎት ወይም በመሥዋዕት ሳይሆን በማስታረቅ ቃል /በመልእክት/ ነው፡፡ ስለዚህ 2ኛቆሮ.5፡20ን የሚያነብ ሰው እግዚአብሔር በክርስቶስ መልእክተኞች በኩል በሚናገረው ቃል ሰዎችን ሲማልድ ልቡ ተነክቶ ከእግዚአብሔር ጋር ለመታረቅ የሚፈቅድ ሰው እንዲሆን ይማራል፡፡ ይህን ትቶ እግዚአብሔር ወደ ሌላ አካል የሚማልድ መሆኑን ይህ ቃል ያስረዳል ብሎ ማሰብም ሆነ መናገር በእጅጉ የተሳሳተ መረዳት ነው፡፡
2ኛ/ ሮሜ8፡26-27 «እንዲሁ ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፣ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፤ ልብንም የሚመረምረው የእግዚአብሔር አሳብ ምን እንደኾነ ያውቃል፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለቅዱሳን ይማልዳልና» ይላል፡፡
በዚህም ቃል ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ከሰው ተነጥሎ ለብቻው እንደሚማልድ የሚያስረዳ ሐሳብ የለም፡፡ ነገር ግን የዚህ ንባብ ዋነኛ ሐሳብ «ድካማችንን ያግዛል» በሚለው ቃል ይብራራል፡፡ በመሠረቱ በኢየሱስ የሚያምኑ ሁሉ መንፈስ ቅዱስን እንደሚቀበሉ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል /ዮሐ.14፡17፤ 1ቆሮ.3፡16፤ 6፡19/፡፡ መንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ በሚያምኑት ዘንድና በውስጣቸውም የሚኖርበት ምክንያት አማኞችን በድካማቸው ለማገዝ ነው፡፡ የሚያግዝበት መንገድም በንባቡ ውስጥ የተጠቀሰ ሲሆን እንዴት እንደሚጸልዩ ስለማያውቁ እርሱ ራሱ «በማይነገር» /ሰው ሊናገረውና ሊገልጸው በማይችል/ መቃተት በመማለድ ነው፡፡ ምክንያቱም እርሱ አማኙ መማለድ /መጸለይ/ ያቃተውን በልቡ የተሰወረውን አሳብ መርምሮ ስለሚያውቅ ነው፡፡ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ ይህን የሚያደርገው በአማኙ ውስጥ ሆኖ ነው እንጂ ከአማኙ ውጪ ሆኖ አይደለም፡፡
ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በተያያዘ መልኩ «መማለድ» የሚለው ቃል የተነገረበት መንገድ ስለኢየሱስ ክርስቶስ «ይማልዳል» ተብሎ ከተነገረበት መንገድ ጋር በእጅጉ የተለያየ እንደሆነ አይተናል፡፡ ሁልጊዜም ልናስተውለው የሚገባን ኢየሱስ ክርስቶስ ይማልዳል ሲባል ሰው ከመሆኑ አንጻር መሆኑን ነው፡፡ አብና መንፈስ ቅዱስ ሰው ሆነው በሰውነት የሚማልዱ ባለመሆናቸው መማለድን በተመለከተ ስለ እነርሱ የተነገረው ቃል ከኢየሱስ ክርስቶስ ምልጃ ጋር ፈጽሞ ሊነጻጸር አይችልም፡፡
ማጠቃለያ
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ እንደሆነ ሁሉ ፍጹም ሰው ነው፡፡ ከማረጉ በፊትም ካረገ በኋላም ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ነው፡፡ በእኛና በእግዚአብሔር መካከል መካከለኛ ሆኖ የቆመው ደግሞ አምላክ ብቻ በመሆን ሳይሆን አምላክም ሰውም በመሆን ነው፤ በ1ጢሞ.2፡5 ላይ የጠቀስነው ማስረጃ ይህን ግልጽ ያደርጋል፤ ይኸውም «አንድ እግዚአብሔር አለና፤ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ» ይልና «እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው» ይላል፡፡ ስለዚህ በአምላክነቱ ከአብ ጋር ጸሎትን፣ ዝማሬን፣ ስግደትን/አምልኮን/ ይቀበላል፡፡ በዚያው ቅጽበት ደግሞ በሰውነቱ ስለ እኛ ይማልዳል፡፡ በመሆኑም የክርስቶስ መካከለኛነት አምላክነቱን አይቀንስም፤ አያስቀርምም፡፡ መካከለኛ ነው ስንል አምላክነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ነው፡፡ ስለዚህ እኛም በአምልኮ፣ በምስጋና፣ በልመናም ሆነ በምልጃ ወደ እግዚአብሔር በኢየሱስ በኩል ስንቀርብ ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህን ሁሉ በአምላክነቱ ከአባቱ ጋር የሚሰማና የሚቀበል ሲሆን በሰውነt ደግሞ ከእኛ ጋር ሆኖ ተቀባይነት እንዲኖረው የሚያደርግ መካከለኛ እንደሆነ ልናውቅ ይገባል፡፡
«ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነው» የሚለው እውነት ቤተክርስቲያን የተመሠረተችበት ዓለት መሆኑ ይታወቃል/ማቴ.16፡18/፤ ክርስቶስ ማለትም የተቀባ ማለት ሲሆን በሰውነቱ የያዛቸውን የነቢይነት፣ የሊቀካህናትነት እና የንጉሥነት ስፍራዎቹን የሚያመለክት ነው፡፡ እርሱ በምድር ሳለ የእግዚአብሔር የሆነውን ነገር ወደ ሰው የገለጠ ነቢይ ሆኖ አልፏል፤ ወደፊት ደግሞ በሺው ዓመት ዘመን መንግሥትን ለእስራኤል በመለሰ ጊዜ እርሱ ጠላቶቹን ሁሉ የእግሩ መረገጫ እስኪያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋል፤ በአሁኑ ጊዜ በሰማይ ባለች እውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ የሆነ ሊቀካህናት ነው፤ ወደፊት በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥ ጊዜ በዙፋኑ ላይ ካህን ይሆናል፤ ይህም እንደ መልከጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን መሆኑ የሚገለጥበት ሁኔታ ነው፡፡ የእርሱ ክህነት ዘላለማዊ ሊሆን የቻለውም በሞት ሊከለከል ባለመቻሉ ሲሆን ይህም ከሙታን ተነሥቶ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ በሊቀካህናትነቱ የሚያገለግል መሆኑን ያሳያል፡፡
ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ማለትም እኛ ወደ እግዚአብሔር በምንቀርብበት በማናቸውም ጉዳይ በሰማይ ስለእኛ ያለ ሊቀ ካህናት እርሱ ነው፡፡ በሊቀካህናትነቱ ልዩ የሚያደርጉት ጠባዮቹም የሚምርና የታመነ መሆኑ፣ የሚራራ፣ ዘላለማዊና ፍጹም መሆኑ ናቸው፤ በዚህ ማንነቱም ስንደክም ይረዳናል፣ ስንወድቅ ያነሳናል፣ ወደ እግዚአብሔር በምንቀርብበት በማናቸውም ጉዳይ ተቀባይነት እንዲኖረን ያደርጋል፤ እርሱ የእግዚአብሔር የሆነውን ወደ እኛ የሚያቀርብ ብቻ ሳይሆን የእኛ የሆነውን ነገር ለእግዚአብሔር የሚያቀርብ ነው፤ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል የሚሠራው የመካከለኝነት ሥራውም ይኸው ነው፡፡
«እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለከለከላቸው ካህናት የሆኑ ብዙ ናቸው፤ እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ስለእነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና፤ ስለዚህ ደግሞ በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል»