ወደ ክርስቶስ ስም መሰብሰብ
ሕይወት ከክርስቶስ ጋር
v

መግቢያ

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርት በአንድ ወቅት ጌታን «እንኪያስ ማን ሊድን ይችላል?» የሚል ጥያቄ መጠየቃቸው የሚታወስ ነው (ማቴ.19፡25)፤ ጌታም ለዚህ ጥያቄ የሰጣቸው የሚያሳርፍ መልስ «ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉ ይቻላል» የሚል ነው (ማቴ.19፡26፤ ሉቃ.18፡27)፡፡

በዚሁ ክፍል ውስጥ እንደምናነበው ‹‹የዘላለምን ሕይወት እንዳገኝ ምን መልካም ነገር ላድርግ?›› ብሎ የጠየቀው ጎበዝ ምንም እንኳ ከአለቆች አንዱ ቢሆንም፣ ብዙ ሀብት ቢኖረውም፣ እንዲሁም ከህፃንነቱ ጀምሮ ህግን ሁሉ ቢጠብቅም የዘላለም ሕይወትን ማግኘት ወይም መዳን አልቻለም ነበር፤ ያለውን ሸጦ ለድሆች ከሰጠ በኋላ እንዲከተለው ጌታ ያቀረበለትን ጥሪ ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግም አልቻለም፡፡ ሰው በሕግም ሆነ በሀብት ራሱን ማዳን እንደማይችል በዚህ መገንዘብ ይቻላል፤ በዘመናችንም ከልጅነታቸው ጀምሮ ሕግንና ሥርዓትን በመጠበቅ ቢያድጉም አሁንም የዘላለም ሕይወትን ስለማግኘት የሚጠየቁ፣ ይህን ሰው የሚመስሉ ብዙዎች አሉ፤ እንደ ደቀመዛሙርቱም ‹‹እንኪያስ ማን ሊድን ይችላል?›› የሚል ጥያቄ ያላቸው ይኖራሉ፡፡ ጌታ ለዚህ ጥያቄ በሰጠው መልስ መሠረትም መዳን ወይም መጽደቅ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ ሆኖም በራሱ መዳን እንደማይችል የተረዳ ሰው ተስፋ መቁረጥ የለበትም፤ በሰው ዘንድ የማይቻለው መዳን በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላልና፡፡ ይህም ሰዎችን ሁሉ ማዳን የሚችለው የእግዚአብሔር ጸጋ ስለተገለጠ ነው (ቲቶ 2፡11)፡፡ በሕግ ያልተቻለው መዳን በእግዚአብሔር ጸጋ ሊገኝ ይችላል፡፡

ይህ ‹‹ሕይወት ከክርስቶስ ጋር›› የሚለው መጽሐፍ መዳንንም ሆነ ከዚያ በኋላ ያለውን የክርስትና ሕይወት በተመለከተ ዘወትር ጥያቄ ለሚያቀርቡ ሰዎች ምላሽ ይሆናቸው ዘንድ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ የተሰጡ ተከታታይ የመልስ ደብዳቤዎች የተሰባሰቡበት መጽሐፍ ነው፡፡ አንባቢው በጸሎት ሆኖ ከመጽሐፍቅዱስ ጋር በማነጻጸር እንዲያነበው በፍቅር ይጋበዛል፡፡

ምዕራፍ 1 ሰው በሕይወቱ መለወጥ አለበትን?

ውድ ወዳጄ

ያነሳኸው ርእስ በጣም የተገባ ነገር ነው፤ ስለሆነም ደስ እያለኝ ወደዚያው እገባለሁ፡፡ ከሰዎች ጋር በግል ስትነጋገርም ሆነ በስብሰባዎች ስትገኝ መለወጥ እንደሚያስፈልግህ በተደጋጋሚ እንደተነገረህ ነገር ግን አንተ ይህ ምንም አስፈላጊ መስሎ እንዳልተሰማህ ጽፈህልኛል፡፡ በትምህርትህ እና በሥራህ ሙሉ በሙሉ ተወስደሃል፡፡ ጥሩ መኖሪያ ቤትና የተሻሉ ጓደኞችም አሉህ፡፡ በቅርብ ጊዜ ጥሩ ደረጃ ላይ ለመድረስና ዓለምህን ለማየት በተስፋ ላይ ነህ፤ ባለህባቸው ሁኔታዎች በጣም ረክተሃል፤ በእርግጥም «መለወጥ አለብህ» እየተባለ ሁልጊዜ በተደጋጋሚ የምትሰማው ይህ አነጋገርም እጅግ አድካሚ ሆኖብሃል፤ በዚህ ነገር ተሰላችተሃል፡፡

ይህንንም በደንብ መረዳት እችላለሁ፡፡ የሌሎች ሰዎችን ጉዳይ ሳያቋርጡ የሚያስቡና ቀኑን ሙሉ መልካም ምክርን የሚሰጡ ለሌሎች ደግሞ ስህተታቸውን የሚነግሩ ሰዎች አሉ፡፡ ይህንን በተደጋጋሚ መስማት በተለይ ደግሞ እነርሱ ትክክል የሚሆኑበት አጋጣሚ እንዳለ በምታስብ ጊዜ የሚያስቆጣህ ነው፡፡

እርግጠኛ ለመሆንም ሰዎቹ ልክ ናቸው ወይስ አይደሉም? የሚለው ነገር በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ መለወጥህስ አስፈላጊ አይደለምን? ወይስ ይህ ብዙም አስፈላጊ አይደለም? ጉዳዩ ቀላል ጉዳይ ቢሆን ኖሮ በኋላ ላይ መሳሳትህ ቢረጋገጥ እንኳ ምናልባት ልትገባበት ትችላለህ፤ ከዚያም በሚቀጥለው ጊዜ የተሻለ የምታውቀው ጉዳይ ይሆን ነበር፡፡ ነገር ግን መለወጥ ስንል ለዘላለም የምትኖረው የት ነው? የሚለውን ጥያቄ በተመለከተ የሚገልጽ ነው፤ ይህም አንተ ስለዚህ ጉዳይ እርግጠኛ ለመሆን እንድትፈልግ የሚያደርግህ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡

ለመሆኑ ዘላለማዊ ኑሮ ምን እንደሆነ እስከ አሁን ድረስ አስበህ ታውቃለህን? እዚያ እስክንደርስ ድረስ በሙላት መገንዘብ እንደማንችል ይገባኛል፡፡ ነገር ግን ዘላለምን የተመለከተ ትንሽ ግንዛቤ ለማግኘትም እንኳ ቢሆን ስለዚህ ጉዳይ ጥቂት ቆም ብሎ አንድ ጊዜ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡

በአንድ ወቅት ስለ አንድ ብልህ ልጅ የሚናገር ጥንታዊ አፈ ታሪክ አነበብኩ፡፡ የአገሩም ንጉሥ ሊፈትነው ዘላለም ምን ያህል እንደሚረዝም እንዲነግረው ጠየቀው፡፡ ልጁም «ንጉሥ ሆይ በአንድ ሩቅ አገር ከነሐስ የተሠራ እጅግ ትልቅ ተራራ አለ፤ ተራራውም ረጅም ከመሆኑ የተነሳ ጫፉ ከሰማይ ደመናት በላይ ርቆ ያልፋል፡፡ ይህንንም ተራራ በየመቶ ዓመቱ አንድ ትንሽ ወፍ እየመጣ አፉን አብሶበት በርሮ ይሄዳል፡፡ በዚህም ተራራው በተፋቀ ጊዜ ወደታች እያነሰ ሄደ፤ ሙሉ በሙሉም ተራራው ጠፋ፡፡ ከዚያ የዘላለማዊ ኑሮ አንድ ሴኮንድ አለፈ ብሎ መለሰለት፡፡

ይህ መልስ ዘላለማዊ ኑሮ ፍጻሜ የሌለው መሆኑን ይገልጽልሃል፤ ነገር ግን በዘላለም ውስጥ ሴኮንዶች ስለሌሉ ይህም እንኳ ቢሆን ትክክል አይደለም፡፡ በዚያ አንድ ሺህ ዓመት እንደ አንድ ቀን አንድ ቀንም እንደ አንድ ሺህ ዓመት ነው (2ጴጥ.3፡8) ዘላለም መጨረሻና የሚለካበት ንዑስ ክፍፍል የለውም፡፡

ሆኖም ግን ይህ ታሪክ በዚህ ምድር ላይ የምናሳልፈው የጊዜ ርዝመትና በመቀጠል የሚመጣው ዘላለም ያላቸውን ልዩነት እንድናይ ያደርገናል፡፡ ከዘላለም ጋር ሲነጻጸሩ አሥር ዓመታት፣ አምሳ ዓመታት፣ ሰማንያ ዓመታት ወይም መቶ ዓመታትም እንኳ ቢሆኑ ምንድን ናቸው? ታዲያ እንዲህ ከሆነ የዘላለም ኑሮን እንዴትና የት እንደምንኖር ማወቅ ጠቃሚ አይደለምን?

ሌላም የቆየ ታሪክ ትዝ አለኝ፡፡ በመካከለኛው ክፍለ ዘመናት ብዙዎቹ ነገሥታት በቤተመንግሥታቸው ግቢ ውስጥ እያሳቁ የሚያዝናኑአቸውን ሰዎች ያኖሩ ነበር፡፡ እነዚህም ሰዎች ብዙውን ጊዜ ቅርጻቸው የተበላሸ ሰዎች ሲሆኑ የተቀደደ ልብሶችን የሚለብሱ፣ በቀልዶቻቸውና በሞኝነት ምልክቶች ጌቶቻቸውን የሚያስቁ ሰዎች ናቸው፡፡ በዘመናቸው የታወቁ ቀልደኞች ነበሩ፡፡

አንድ ጊዜ አንድ ልዑል የቤተ መንግሥቱን ቀልደኛ ጠርቶ የሞኝነትን ምልክት የሚያሳይ በአንድ በኩል ሾጣጣ የሆነ በትናንሽ ቃጭሎች ያጌጠ ሹል ባርኔጣና የአሽሙር ክብር መለያ የሆነ የተሸላለመ ዘንግ ሰጠው፡፡ ሆኖም ከእርሱ የበለጠ ብዙ ቀልዶችን የሠራ ሰው ካገኘ ባርኔጣውንና ዘንጉን ለዚያ ሰው መስጠት እንዳለበት ልዑሉ አሳሰበው፡፡ ብዙም ሳይቆይ ልዑሉ በጣም ታመመ፡፡ ቀልደኛውም ሄዶ ጎበኘውና ስለጤንነቱ በቅርቡ ይድን እንደሆነ ጠየቀው፡፡ ልዑሉም ምንም መሻሻል እንደሌለና በቅርቡም እንደሚሞት ሐኪሙ እንደነገረው መለሰለት፡፡ ቀልደኛውም አለ፤ «እንግዲያ ለዚህ ታላቅ ጉዞ በጥንቃቄ ተዘጋጅተዋል? እዚያም ሲደርሱ የሚደረግልዎን አቀባበል አውቀዋል?» ይለዋል፡፡ ልዑሉም «አይ! የሚያሳዝን ነው፡፡ በዚያ የሚደረግልኝ አቀባበል እንዴት እንደሆነ አላውቅም» ሲል መለሰለት፡፡ ቀልደኛው ጠያቂም «ይህ ጉዞ አንድ ቀን እንደሚኖር አላወቁ ኖሯልን?» ሲል ጠየቀ፡፡ ልዑሉም «አውቅ ነበር፤ ነገር ግን በዚህ አልተያዝኩም ነበር፤ የሚሠሩ ብዙ ሌሎች ነገሮች ነበሩ» አለው፡፡ «ነገር ግን ልዑል ሆይ» አለ ፌዘኛው፤ «እርስዎ ከዚህ በፊት ጉዞ ሲያደርጉ የሚሆን ምግብ፣ መጠጥና ሌላም አስፈላጊ ነገር መዘጋጀቱን ለማየት መልእክተኛዎ ቀድሞ ይሄዳል፡፡ ለጥቂት ሳምንታት ወይም ወራት ከተጓዙ ሁሉም ነገር የሚታቀደው ቀደም ብሎ ረዘም ያለ ጊዜ በመስጠት ነው፤ እርስዎ እዚያ በሚደርሱ ጊዜ ሁሉም ነገር በሥርዓቱ እንዲሆን የተለያዩ አገልጋዮች ከጊዜው ቀድመው ይሄዱና ያዘጋጃሉ፡፡ ለዘላለም ወደሚኖሩበት ስፍራ ለሚያደርጉት ለዚህ ጉዞ ግን በፍጹም ምንም ዝግጅት አላደረጉም፤ እንግዲህ የሰጡኝን የሞኝ ባርኔጣ እና ዘንግ ይረከቡኝ፡፡ እኔ በፍጹም ያን ሞኝ አልነበርኩምና» አለ፡፡

ቀልደኛው ልክ አልነበረምን? ከአሥር ዓመታት በላይ ወደ ትምህርት ቤት ተመላልሰሃል፡፡ አሁን ደግሞ ቀን ቀን እየሠራህ ማታ ማታ ከፍተኛ ትምህርት ትማራለህ፤ በቅርቡም ጥሩ ደረጃ ለመድረስ ተስፋ እያደረግህ ነው፡፡ በሚቀጥሉት አርባ ዓመታት ጥሩ ገንዘብ ለመያዝ ለሃያ ዓመታት ያህል በውጥረት ተይዘሃል፡፡ ምናልባትም ከጡረታህና ከቁጠባህ ሌሎች ተጨማሪ አስር ዓመታትን በምቾት ለመኖር ተስፋ ታደርጋለህ፤ ከዚያም በጣም በሽምግልና የምትኖር ከሆነ ሌላ ሃያ ዓመት ልትኖር ትችላለህ፡፡ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት በፍጹም ስለማያስገቡ ሰዎች ምን ታስባለህ? «ልጆች ስለወደፊቱ ምንም ሊያስቡ አይገባም፤ አሁን ይጫወቱ፤ አድገው ራሳቸውን ማወቅ ሲችሉ ያስቡበታል» በማለት ሙያ ስለመማራቸው ግድ ስለማይላቸው ወላጆች ምን ታስባለህ?

አንተ ደግሞ ለአርባና ለሃምሳ ዓመታት የተመቻቸ ኑሮ ለመኖር ብለህ ይህን ያህል ከደከምክ እና መሥዋዕትነትን ከከፈልክ ዘላለምን ቸል ማለትና ራስህን «እኔ ዘላለምን የማሳልፈው የት ነው?» በሚለው ጥያቄ አለመያዝ ያልተገባ አይደለምን? ከዚህም በተጨማሪ በኑሮ ጥሩ ደረጃ ላይ ለመድረስህ እርግጠኛ አይደለህም፤ እዚያ ሳትደርስ እንደማትታመምና ምናልባትም እንደማትሞት የሚያውቅ ማን ነው? ነገር ግን ዘላለማዊ ኑሮ እንደሚጠብቅህ በእርግጠኝነት ታውቃለህ፡፡ ለሰዎች «አንድ ጊዜ መሞት» ተመድቦባቸዋል (ዕብ.9፡27) ማንም ሰው ቢሆን፣ እጅግ በጣም ዘባች የሆነ ሰውም እንኳ ወይም በክህደት ልቡን እጅግ ያደነደነ ሰው፣ ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እስካሁን ሊክድና ሊያስተባብል የቻለ የለም፡፡ ይህን ሊክዱ አይችሉም፡፡ ይህንን ቢክዱ ትርፉ በሰው ሁሉ ዘንድ መሳቂያ መሆን ብቻ ነው፤ ምክንያቱም ወደ ሞት የማይመጣ ማን አለ?፡፡

የዚህ ጥቅስ ቀሪ ክፍል የሆነውና «ከእርሱ በኋላም ፍርድ እንደተመደበባቸው» የሚናገረው ቃልም እኩል እውነት ነው፡፡ ፍጹም ግድ የማይለው መሆን፣ ይልቁንም የመጣው ይምጣ ብሎ የሚመጣውን መጠበቅ ተቀባይነት የሌለው ሞኝነት አይደለምን? በእርግጠኝነት የዘላለም ኑሮህን የት እንደምታሳልፈው ከሄድክ በኋላ ያኔ ራስህ ታረጋግጣለህ፡፡ ነገር ግን ያ በቁርጥ ያከተመለት ነገር ሆኖ ታገኘዋለህ፡፡ በመጽሐፈ መክብብ 11፡3 «... ዛፉም ወደ ደቡብ ወይም ወደ ሰሜን ቢወድቅ ዛፉ በወደቀበት ስፍራ በዚያ ይኖራል» ይላል፡፡ ምናልባት አሁን «እሺ ታዲያ ለምን ጥድፍያ አስፈለገ? አሁን በሥራ ተይዣለሁ፤ ይህችን ያለችኝን ትንሽ ጊዜ ስለእነዚህ አስፈሪ ነገሮች ማለት ስለ ሞትና ስለ መሞት በማሰብ ላሳልፋትን? ትንሽ እያረጀሁ ስመጣ ያንን ማድረግ እችላለሁ፤ እስከዚያው «ሕይወትን» ማየትና ማጣጣም አለብኝ፤ ከዚያ ስለመሞት ለማሰብ ሰፊ ጊዜ ይኖረኛል» በማለት ታስብ ይሆናል፡፡

ነገር ግን የሚቀጥሉትን ሌሎች ሃምሳ ወይም ሠላሳ፣ ወይም አሥር ዓመታት፣ ወይም አስራሁለት ወራት ወይም አስራ ሁለት ሰዓታት በሕይወት እንደምትኖርህ እርግጠኛ ነህን? አንድ ቀን በአንድ ከተማ ውስጥ በሚሠራበት ሱቅ ውስጥ ሆኖ በጊዜ በመንገድ ላይ ሲሰበክ የነበረውን ወንጌል ይሰማ የነበረውን አንድ ሰው አስታውሳለሁ፡፡ መልእክቱ ካበቃ በኋላ ወደቤቱ ሄዶ በወንበር ላይ እንደተቀመጠ ወዲያው እንደሞተ ትዝ ይለኛል!

ገና ረዘም ያለ ዕድሜ መኖር ካለብህ እንኳ የጤንነትና የጉብዝና ጊዜህን ለራስህ ተጠቅመህ የተረፈውን ጊዜህን ለእግዚአብሔር ለመስጠት ነው የምትፈልገው? ይህን ማድረግ ከፈለግክ (እርሱም ረጅም ዕድሜ ካገኘህ ነው) እግዚአብሔር የሚቀበልህ ይመስልሃልን?

ይጠራል (2ቆሮ.5፡20) ከጌታ ጋር አብረው ከተሰቀሉት ክፉ አድራጊዎች አንደኛውንና ሌሎችንም በሞት አፋፍ ላይ ሳሉ ወደእርሱ የተመለሱትን በሺህ የሚቆጠሩትን ተቀብሎአቸዋል፡፡ እኔ ራሴ በ85 ዓመታቸው የተለወጡ አሮጊት አውቃለሁ፡፡ ሆኖም ግን ነገ የሚሆነውን አናውቅምና ይህ የምናሳድረውና ቀጠሮ የምንሰጠው ጉዳይ አይደለም፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ሰዎች ወደ እውነት በመድረስ እንዲድኑ እግዚአብሔር በተለያየ መንገድ እንደሚናገራቸው ከመጽሐፈ ኢዮብ ምዕራፍ.33፡14 እናስተውላለን፡፡ ይህንንም በመደጋገም ሁለት ጊዜ እና ሦስት ጊዜ እንደሚያደርገው ይናገራል፡፡ ከዚያ ወዲያ እየወተወተው ይኖራል የሚል ግን አናገኝም፡፡ ፈርዖን ደግሞ የአለመታዘዝን ፍላጎት አጽንቶ ሲያሳይ እግዚአብሔር ደግሞ በመጸጸት እንዳይመለስ ልቡን አደነደነው፡፡ የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ከተነጠቀች በኋላ ወንጌልን ሰምተው መቀበልን ላልፈለጉ «ፍርድን እንዲቀበሉ ሐሰትን ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር የስሕተትን አሠራር ይልክባቸዋል፡፡» (2ተሰ.2፡11፣12) ደጋግሞ ሲጠራህ አልመለስም ብለህ እምቢ ካልክ ባንተ ላይም ተመሳሳይ ነገርን ሊልክብህ ይችላል፡፡ «እንግዲህ እግዚአብሔር ያለማወቅን ወራት አሳልፎ አሁን በየቦታቸው ንስሐ ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ ያዛል፡፡ ቀን ቀጥሮአልና በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው፤ ስለዚህም እርሱን ከሙታን በማስነሣቱ ሁሉን አረጋግጦአል» (የሐ.ሥ.17፡30፣31) አሁን በዚህ ነገር ግልፅ በመሆን ኃጢአትህን ለእግዚአብሔር በመናዘዝ እንዲቀበልህ ልትጠይቀው አይገባህምን? «እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን፡፡ እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው» (2ቆሮ.5፡20-21)፡፡ «ዛሬ ድምፁን ብትሰሙት ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ» (ዕብ.4፡7)፡፡

ከሰላምታ ጋር

ያንተው ወንድም

ምዕራፍ 2 ሰው የሕይወት ለውጥ ማድረግ ያለበት ለምንድን ነው?

ውድ ወዳጆቼ

መለወጥ ለምን አስፈለገ? የመለወጥስ ትክክለኛ ትርጉሙ ምንድ ነው? ብላችሁ ጠይቃችሁኛል፡፡
የመጀመሪያውን ጥያቄ ለመመለስ መለወጥ ያስፈለገበት ምክንያት እግዚአብሔር መለወጥ ያስፈልጋል ስላለ ነው፡፡ እግዚአብሔር አንድን ነገር ከተናገረ ያ ነገር ለምን የሚል ጥያቄ ሊከተልበት የማይችልና ያለቀለት ነገር ነው፡፡ እኛ የእርሱ ፍጡሮች ማድረግ ያለብን ራሳችንን ዝቅ በማድረግ መታዘዝ ብቻ ነው፡፡ በሮሜ 9፡20 እንዲህ ሲል ይናገራል፤ «ነገር ግን አንተ ሰው ሆይ ለእግዚአብሔር የምትመልስ ማን ነህ? ሥራ ሠሪውን ስለምን እንዲህ አድርገህ ሠራኸኝ ይለዋልን? ...» ይላል፡፡ በሐዋ.ሥ.17፡30 ደግሞ «እንግዲህ እግዚአብሔር ያለማወቅን ወራት አሳልፎ አሁን በየቦታቸው ንስሐ ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ ያዛል ቀን ቀጥሮአልና» ይላል፡፡ ከዚህ ጋር የሚመሳሰሉ የመለወጥን አስፈላጊነት የሚገልጹ በብሉይ ኪዳን ሰማንያ ያህልና በአዲስ ኪዳን ደግሞ ሰባ ያህል ምንባቦች ይገኛሉ፡፡

ሰው ለምን መለወጥ እንዳለበት እግዚአብሔር በቃሉ በግልፅ ተናግሮአል፡፡ ስለዚህም ነገር ጴጥሮስ በሁለተኛ መልእክቱ ምዕራፍ 3 ቊጥር 9 «ለአንዳንዶቹ የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፤ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል» ይላል፡፡ ይህም እንድንለወጥ የሚያዘው ትዕዛዙ ለምን እንዳስፈለገ በሐዋ.ሥራ ምዕራፍ 17 ሲገልጥ በምድር በሚኖሩት ላይ በጽድቅ የሚፈርድበትን ቀን እንደቀጠረ ያስረዳል፡፡

እያንዳንዱ ሰው በምድር ላይ ሕይወቱን እንዴት እንዳሳለፈው ለፈጣሪው የሚያስረዳበት ቀን ትመጣለች፡፡ በሮሜ.3፡23 «ሁሉ ኃጢአት ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል» ተብሎ እንደተጻፈው የሰውን ሕይወት ከነተግባሩ የሚያውቀው እግዚአብሔር ለሰው የሚሰጠው ፍርድ ግልፅ ነው፡፡ ነገር ግን በ1ጢሞ.2፡3-4 እንደተጻፈው «ሰዎች ሁሉ ሊድኑ እና እውነትን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ» ይወዳል፡፡

እግዚአብሔር ለምን ሰው መለወጥ አለበት ብሎ አዘዘ? ምክንያቱም ሰው ፈጣሪውን በማገልገል ፈንታ በኃጢአት የሚመላለስ በመሆኑ ካልተለወጠ በቀር የእግዚአብሔር የጽድቅ ፍርድ ይተላለፍበታልና ተለውጦ ከፍርድ ያመልጥ ዘንድ ነው፡፡

ሰው ኃጢአተኛ ነው

ይህ አስደንጋጭ የሆነ እውነት ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ልብ ብለው የማያስተውሉት ነገር ነው፤ አንዳንዶች ደግሞ ፈፅመው ይክዱታል፡፡ ነገር ግን እነዚህ «ሰው ኃጢአተኛ አይደለም» ብለው የሚክዱ ሰዎች ሐሳባቸው እውነት እንደሆነ ማረጋገጥ ይችሉ ይሆንን? የማይዋሽ ቅን ሰውስ አዘውትሮ የተሳሳቱ ነገሮችን እንደሚያደርግ መካድ ይችላልን?

አንድ በቅንነት እመላለሳለሁ፤ ከሌሎች ጋርም በሚታየኝ መልኩ በመልካም ግንኙነት እኖራለሁ እያለ የሚናገር ሰው ከአንድ ጊዜ በላይ ደጋግሜ የጠየቅኩት ጥያቄ ነበር፡፡ ከሰው ጋር ባለው ዝምድና በሐሳብ፣ በንግግርም ሆነ በተግባር ባደረገው ነገር ኅሊናው ወቅሶት የማያውቅ እንደሆነ እጠይቀው ነበር፡፡ ነገር ግን ኅሊናዬ ወቅሶኝ አያውቅም ብሎ ለመናገር በድፍረት የቆመበት ጊዜ የለም፡፡

ኃጢአተኛ ማለት ኃጢአት ሠርቶ የሚያውቅ ማለት ነው፡፡ ሰው ኃጢአተኛ የሚሆነው ብዙ ስሕተቶችን ደጋግሞ ከሠራ በኋላ አይደለም፡፡ አንድ ጊዜ ብቻ እንኳ የተሠራ ኃጢአት ሰውን ኃጢአተኛ ያደርገዋል፡፡ ይህም በዕለታዊ ኑሮአችን ሁልጊዜ የምናየው ነገር ነው፡፡ እከሌ ሰው የገደለው አንድ ወይም ግፋ ቢል ሁለት ጊዜ ብቻ ነው፤ ስለዚህ ነፍሰ ገዳይ ሊባል አይገባውም የሚል ሰው የለም፡፡ ነገር ግን ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ግንኙነት በተመለከተ ሲናገር ሌላ መስፈርትና መለኪያ ለራሱ ማቆም ይፈልጋል፡፡ ይህን ካላደረገ ደግሞ ራሱን በራሱ ያወግዛል፤ ይኮንናል ማለት ነው፡፡

ኅሊና

እግዚአብሔር ለሁሉም ሰው ስለ ስህተት የሚወቅሰውን ኅሊና በውስጡ እንዳስቀመጠለት በሮሜ 2፡15 ተጽፎአል፡፡ ነገር ግን ኅሊና ስህተት የሆነውን ሁሉ አይጠቁምም፤ ምክንያቱም የኅሊና ሚዛን ያ ሰው በሚኖርበት አካባቢና ሁኔታ ተፅዕኖ ሊወሰን ይችላል፡፡ በሚኖርበት ወይም ባደገበት አካባቢ ስህተት ወይም ጥፋት ተብሎ ሊቆጠር በሚችል ነገር ላይ ብቻ የመሳሳቱን ማስጠንቀቂያ ስሜት ይሰጠዋል፡፡ ስለዚህ ሰዎች ስለ እግዚአብሔር ወይም ስለ ቃሉ የሰሙት ነገር ባይኖርም ስሕተት የሆነውን ነገር ስህተት መሆኑን እያወቁ መሥራት ክፋትና በደለኝነት መሆኑን እንዲረዱ እግዚአብሔር አድርጎአል፡፡ ሕይወትህን ዘወር ብለህ እስኪ ተመልከት፤ እያወቅህ ምን ያህል ኃጢአቶችን ሠርተሃል? ለምሳሌ እንበል አሁን 18 ዓመት ሞልቶሃል፡፡ በመጀመሪያዎቹ የሕይወትህ ስምንት ዓመታትም እያወቅህ ምንም ክፋት እንዳልሠራህ እንቁጠረው፡፡ ከዚያን ወዲህ በቀን አንድ ጊዜም ቢሆን ኅሊናህ ይወቅስሃል፤ ነገር ግን ለጊዜው ምንም እንደማታውቅ አድርገን እናስበው፡፡ ከዚያን ወዲህ በቀን አንድ ጊዜ ኃጢአት ብትሠራ እንኳን በዓመት 365 ጊዜ በአለፉት 10 ዓመታት ደግሞ 3,650 ጊዜ መሆኑ ነው፡፡ 28 ዓመት ለሞላው ሰው ደግሞ 7,300 ጊዜ ሲሆን ለ68 ዓመት ሽማግሌ ደግሞ 21,900 ጊዜ ኃጢአት እንደሠራ ይቆጠራል፡፡ ስለዚህ ኃጢአት መሆኑን እየተሰማህ ላለፉት አሥር ዓመታት እስከ አሁን 3,650 ጊዜ ኃጢአትን ሠርተሃል፡፡ ሆኖም በትክክል ቢቆጠር ከዚህ በጣም የበዛ መሆኑን ታውቃለህ፡፡ ይህን ያህል ኃጢአት የሠራ ሰው ኃጢአተኛ ተብዬ መጠራት የለብኝም ሊል ይችል ይሆንን? ጻድቅ የሆነው እግዚአብሔርስ ነፃ ይለቀዋልን? ይህስ ምሳሌ ሁሉም ሰው በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአተኛ መሆኑን እና ፍርድ የተገባው ሆኖ የዘላለም ቅጣት መቀበል እንዳለበት አያሳይምን?

ባለማወቅ የተሠሩ ኃጢአቶች

ሌላ ጥያቄ ደግሞ አለ፡፡ ሰው ኃጢአተኛ የሚባለው እያወቀ ኃጢአት ሲሠራ ብቻ ነውን? የሚሠራውን ሥራ ስህተት መሆኑን ሳያውቅ ቢሠራው በደል አይደለምን? ሰው ሕግ መኖሩን አላውቅም ቢልም ሕግ የታወጀ እስከሆነ ድረስ ላጠፋው ጥፋት ከበደለኝነት ክስ እንደማያመልጥ የታወቀ ነገር ነው፡፡ ያለማወቅ ከሕግ ለማምለጥ አያስችልም፤ ምናልባት ዳኛው የጥፋተኛውን አለማወቅ በማመዛዘን በፍርድ አሰጣጥ ከግምት ውስጥ ሊያስገባው ይችል ይሆናል፡፡ ያልተማረ ወጣትና አንድ የሕግ ምሁር አንድ ዓይነት ሕግ ቢጥሱ የተማረው ሰው ቅጣት የከፋ ሊሆን ይችላል፡፡ በዳኝነት ውሳኔ አሰጣጥ ግን ሁለቱም ጥፋተኛ ይባላሉ፡፡

ይህንንም የሚመስል መመሪያ በእግዚአብሔር ቃል በዘሌዋ.5፡17 ላይ ይገኛል፡፡ «ማናቸውም ሰው ኃጢአት ቢሠራ እግዚአብሔርም አትሥሩ ካላቸው ትእዛዛት አንዲቱን ቢተላለፍ ባያውቅም ያ ሰው በደለኛ ነው፡፡ ኃጢአቱንም ይሸከማል» ይላል፤ ይህ ግልፅ የሆነ ነገር ነው፡፡ በፈጣሪው ሲጠየቅ መልስ የመስጠት ግዴታ ያለበት ፍጡር የሆነው ሰው ስለ ራሱ በደለኝነት ወይንም ንጽሕና ውሳኔ ማስተላለፍ ይችላልን? ይህ ሊሆን የማይችል ነገር ነው፤ ኃላፊነቱን ተወጥቶአል አልተወጣም ብሎ መወሰን የሚችለው ፍጡርን ፈጥሮ የሚጠየቅበትንም ኃላፊነት ያሸከመው ፈጣሪ ብቻ ነው፡፡ ኃጢአትም ምን ማለት እንደሆነ መግለፅ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ኃጢአት ምን መሆኑን ለማወቅም የእርሱን የእግዚአብሔርን ሐሳብ ማወቅ ይኖርብናል፡፡

ይህንንም ጉዳይ በተመለከተ ያለው የእግዚአብሔር ሐሳብ በቃሉ በግልጽ ሰፍሮአል፡፡ በዘፍ.1፡28 እና 2፡15-17 እግዚአብሔር ለሰው የሰጠውን ግዴታና ኃላፊነት እናያለን፡፡ አዳም በእግዚአብሔር ላይ በመደገፍና ለእርሱም በመታዘዝ የኤድንን ገነት እንዲንከባከባትና እንዲጠብቃትም ተደረገ፡፡ መልካሙንና ክፉውን ከምታስታውቅ ዛፍ አለመብላቱ የመታዘዝ ምልክት ሆነለት፡፡ ሰውስ በአፀፋው ምን አደረገ? በመጀመሪያ ባገኘው አጋጣሚ ሆን ብሎ እያወቀ እግዚአብሔር የሰጠውን ኃላፊነትና ግዴታ ለመተላለፍ ወሰነ፡፡ ይህም የመጀመሪያው ጥፋት ነው፡፡ ይህ ከተከሰተ ከሦስት ሺህ ዓመታት በኋላ እግዚአብሔር በቃሉ እንደዚህ ሲናገር ይሰማል፤ «የሚያስተውል እግዚአብሔርንም የሚፈልግ እንዳለ ያይ ዘንድ እግዚአብሔር ከሰማይ የሰው ልጆችን ተመለከተ፡፡ ሁሉ አመፁ በአንድነትም ረከሱ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም፤ አንድ ስንኳ የለም፡፡» (መዝ.14፡2-3) እንደገናም ከሌላ ሺህ ዓመት በኋላ ቃሉ እንዲህ ይላል፤ «ጻድቅ የለም አንድ እንኳ፤ አስተዋይ የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል፡፡ ቸርነት የሚያደርግ የለም (ሮሜ3፡11-12) ታዲያ በሮሜ.3፡23 «ሁሉ ኃጢአት ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል» የሚለው የእግዚአብሔር ውሳኔ በፍጹም ግልጽና ትክክለኛ አይደለምን?

ኃጢአት ምንድን ነው?

እንዲህ ብለህ ትናገር ይሆናል፤ ‹‹አልፎ አልፎ እንደምንሳሳት ማመን አለብን፡፡ ነገር ግን ሁሉም መልካም አይሠሩም ብሎ መናገር ይከብዳል፡፡ መልካም ተግባር የሚሠሩ ብዙ ሰዎች አሉ፤ ለሌሎች በርካታ መልካም ነገሮችን የሚያደርጉ አሉ፤ ለሰው ልጅ ባበረከቱት መልካም ተግባር የሚታወቁ ብዙ ሰዎችን ልጠራልህ እችላለሁ፡፡›› እዚህ ላይ ኃጢአት ምንድነው? የሚለውን ዋና ጥያቄ እንዳስሳለን፡፡ ሰው በእግዚአብሔር ተፈጠረ፤ እንዲያገለግለውም ታዘዘ፡፡ ስለዚህም ሰው ለፍጡር ከተሰጠው ስፍራ በመልቀቅ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚቃወም ሥራ ቢሠራና እግዚአብሔርን ሳያገለግል ቢቀር በኃጢአት ላይ መሆኑን እናውቃለን፡፡ ይህንንም መመሪያ በ1ዮሐ.3፡4 እናገኛለን፡፡ ‹‹ኃጢአትን የሚያደርግ ሁሉ ዓመፅን ደግሞ ያደርጋል ኃጢአትም ዓመፅ ነው፡፡›› እግዚአብሔር በፍጥረቱ ላይ ያለውን ጌትነትና ሥልጣን ቸል የሚል አድራጎት ሁሉ ኃጢአት ነው፡፡ ለምሳሌ ከእግዚአብሔር ፍቃድ ውጭ የሆነ አመጋገብ ኃጢአት ሊሆን ይችላል፡፡ የእግዚአብሔርም ቃል ግን «በእምነት ያልሆነ ሁሉ ኃጢአት ነው ይለናል፡፡» (ሮሜ14፡23)፡፡

ሁሉንም አካሄዳችንን ከእግዚአብሔር ፈቃድ አንፃር ብናየው የምንመለከተው ምንድር ነው? ከሠራነው ሥራ ወይም በአእምሮአችን ካለፈው ሐሳብ እግዚአብሔርን በመታዘዝ ያደረግነው የትኛውን ነው? «ጌታ ሆይ ምን አደርግ ዘንድ ትወዳለህ?» ብለን በልባችን እግዚአብሔርን የጠየቅነውስ ስለ የትኛው ነው?

መልሱ በማያሻማ ሁኔታ «ስለ ምንም» የሚል ይሆናል፡፡ ስለዚህ የሠራነው ነገር በሙሉ ኃጢአት ነው ማለት ነው፡፡ በሮሜ 3፡12 የእግዚአብሔር ቃል እንደዚህ ይለናል፤ «በአንድነት የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ ቸርነት የሚያደርግ የለም፡፡» በዘፍ.6፡5 ደግሞ «እግዚአብሔር የሰው የልቡ አሳብ ምኞትም ሁል ጊዜ ፈፅሞ ክፉ እንደሆነ አየ» ይላል፡፡ ጻድቅ አምላክ የሰውን ልጅ የኮነነበት ምክንያትም ይኸው ነው፡፡ ከሚመጣው አስፈሪ ቁጣ ያመልጡ ዘንድ መሐሪው አምላክ ሰዎችን ሁሉ እንዲለወጡ የሚጠራውም ለዚሁ ነው፡፡

መለወጥ ምንድን ነው?

አሁን መለወጥ ምንድነው? ብላችሁ ወዳቀረባችሁት ሁለተኛ ጥያቄ እመጣለሁ፡፡ ይህ «መለወጥ» የሚለው ቃል በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም፡፡ አንዳንድ ጊዜ «መለወጥ» የሚለው «ንስሐ መግባት» ተብሎ ሊተካ ይችላል፡፡ ነገር ግን ሜታኖያ የሚለው በጥንታዊ ግሪክ በተጻፉት ቅዱሳት መጻሕፍት የተጠቀሰውን ቃል አይወክልም፡፡

ከ1ተሰ.1፡9 እንደምንረዳው ይህ ሐሳብ «ዘወር ማለት» በሚለው ሐረግ ላይ እንደተጠቃለለ መረዳት እንችላለን፡፡ የተሰሎንቄ ነዋሪዎች አምልኮተ ጣኦት በሰፈነበት ሕይወት ሲመላለሱ ከቆዩ በኋላ አሁን ግን ወንጌልን አምነው ወደ እግዚአብሔር በመመለስ ጀርባቸውን ለጣኦታቱ እንደሰጡ ያሳየናል፡፡ ነገር ግን የሐዋ.ሥራ 2፡37-38፣ 17፡30-31፣ ራእ.9፡20-21 እና ሌሎችንም ብናይ የራስን ስህተት አምኖ ወደ እግዚአብሔር ዘወር ከማለት ጋር የተያያዘ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ስለዚህ መለወጥ ማለት የራስን ስህተት በማመን በእግዚአብሔር ፊት እየተናዘዙ እስከ አሁን ድረስ የነበረውን አለመታዘዝ በፀፀት መግለፅ ማለት ነው፡፡ ከዚህ የተነሳም ስለተሠራ ክፋት ማዘንን ያጠቃልላል፡፡ ምንም እንኳ መለወጥ ለሚለው ቃል ትክክለኛ ሥነ ልቡናዊ ትርጉም ባይሰጠውም ወደ እግዚአብሔር ብርሃን ቀርቦ ማንነቱን በግልፅ ያወቀና የሚገባውንም ፍርድ የተረዳ ሰው የቃሉን ምንነት አይስተውም፡፡ እግዚአብሔር ልብንና ኅሊናን እንጂ የእውቀትን ስፋት አይመለከትም፡፡ ቀራጩን በሉቃ.18፡13 እንደምናየው «አምላክ ሆይ እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ» እያለ ጸሎቱን በቀላሉ ሲያቀርብ «የልቡን ስሜትና ሐሳብ የሚመረምር» አምላክ (ዕብ.4፡12) በእነዚህ ጥቂት ቃላት ውስጥ ሁሉም ነገር እንደተካተተ ያውቃል፡፡ መለወጣችን የሚታወቀው በምንናገረው ቃላት ሳይሆን በእግዚአብሔር ፊት ስንቀርብ ባለው የልባችን ሁኔታ ነው፡፡ አሁን አንድ ነገር ልጠይቃችሁ እወዳለሁ፡፡ ተለውጣችኋልን? መጥፋታችሁን አምናችሁ ኃጢአታችሁን እየተናዘዛችሁ ወደ እግዚአብሔር ቀርባችኋል ወይ? የዘገያችሁበት ያለፉት ዘመናት ይበቃሉና እባካችሁ አሁን አድርጉት፤ ነገን በሕይወት ላትኖሩ ትችላላችሁና፡፡

ከሰላምታ ጋር

በክርስቶስ ወንድማችሁ

ምዕራፍ 3 ከእግዚአብሔር ጋር እንዴት መታረቅ እችላለሁ?

ውድ ወዳጄ

ባለህበት ሁኔታ አሁን በእግዚአብሔር ፊት ብትቀርብ ለዘላለም የጠፋህ ኃጢአተኛ እንደሆንክ መረዳትህን ሰምቼ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ኃጢአትህንም በእግዚአብሔር ፊት ተናዝዘሃል፡፡ ነገር ግን ይቅር መባልህን አላወቅክም፡፡ ስለኃጢአትህ በጥልቀት ንስሐ ስለመግባትህና ስለመለወጥህ ሁኔታ አልፎ አልፎ ጥያቄ እንደሚመላለስብህ ተረድቻለሁ፡፡

እኔ ራሴ ያለፍኩበት ነገር ስለሆነ ያለህበት ሁኔታ በደንብ ይገባኛል፡፡ በወጣትነቴ ዘመን ለብዙ ዓመታት የጠፋሁ ሰው እንደሆንኩ እረዳ ነበር፡፡ ቀን ሲሆን ያን ያህል ትዝ አይለኝም፤ ሌሊት በአልጋዬ ጋደም ስል ግን ሐሳቡ እየተመላለሰብኝ እጨነቅ ነበር፡፡ አሁን ብሞት እኮ ወደ ዘላለማዊ ጥፋት መሄዴ ነው እያልኩ አስባለሁ፤ ግን ወዲያውኑ ኃጢአቴን በመናዘዝ ከእግዚአብሔር ይቅርታን እጠይቃለሁ፡፡ ነገር ግን ይቅር የተባለልኝ አይመስለኝም ነበር፡፡ ስለዚህ ሁሌ ቅር ቅር እያለኝ እኖር ነበር፡፡ አንድ ቀን ታላቅ እህቴ ምንም ጥርጥር በሌለበት ሁኔታ ሰላምን እንዳገኘች ገለፀችልኝ፡፡ እርሷ የተከተለችውን መንገድ ሞክሬ ሊሳካልኝ አልቻለም፡፡

አሥራ ሰባት ዓመት ሲሞላኝ አንድ ምሽት አልጋዬ ላይ ቁጭ ብዬ ነበር፡፡ በተስፋ መቁረጥ በአእምሮዬ «ያ ሁሉ ጸሎቴ ከንቱ ሆነ፤ ለብዙ ዓመታት ሳላቋርጥ ማታ ማታ አድነኝ እያልኩ ስጸልይ ይኸው እስከ አሁን ቆየሁ፤ ምንም ለውጥ ግን አላየሁም» እያልኩ ሳስብ በዚያች ሰዓት አንድ የእግዚአብሔር ቃል ብልጭ አለብኝ፡፡ ይህም ሌላ ሳይሆን በ1ዮሐ.1፡9 «በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነፃን የታመነና ጻድቅ ነው፤» የሚል የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ እኔም ይህ እውነት ነው፤ እግዚአብሔር አይዋሽምና ብዬ አሰብኩ፡፡ በዚያች ሰዓትም እግዚአብሔር ሁሉን ነገር ግልፅ አደረገልኝ፤ ይህም ማለት ኃጢአቴን በመጀመሪያ የተናዘዝኩ ዕለት ይቅር እንደተባለልኝ ገባኝ፡፡ ወዲያውኑም የሚከሰኝ ነገር ተወግዶ ልቤና ኅሊናዬ በሰላም ተሞላ፡፡ ከዚያች ምሽት ጀምሮ ኃጢአቴ የተደመሰሰ መሆኑን አወቅኩ፡፡ ተጠራጥሬ አላውቅም፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ብሎአልና፡፡

ምን ያህል መፀፀት አለብኝ?

ልቤ ሳያርፍ ሰላም ሳላገኝ እንዴት ይህን ያህል ዓመታት ልቆይ ቻልኩ? የበደለኝነት ስሜቴና መፀፀቴ የጠለቀ አለመሆኑ አንድ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ሰው በኃይል ካልተፀፀተና የኃጢአትኝነት ስሜቱም በጣም ካልጠለቀ ይቅር አልልም ብሎ እግዚአብሔር መስፈርት ያወጣበት ጊዜ የለም፡፡ በሚለወጥበት ጊዜ የሚያስፈልገውን ያህል በጥልቀት የተፀፀተና የሚገባውን ያህል ኅሊናው ኃጢአተኝነቱን የተገነዘበለት ሰው ኖሮ አያውቅም፡፡ ምን ያህል በደለኞች እንደሆንን በደንብ የሚገባን ከተለወጥን በኋላ ነው፡፡

ሆኖም ግን እግዚአብሔር የመጥፋታችንን ሁኔታ በተመለከተ በተወሰነ ደረጃ ስሜት እንዲያድርብን ይፈልጋል፡፡ ይህ ስሜት ከፍ ባለ ቊጥር የመለወጣችንም ፍላጎትም እንዲሁ ከፍ እያለ ይሄዳል፡፡ የሚደርስብንን ፍርድ በተረዳነው ደረጃ ደግሞ በዚያው መጠን የበደለኝነት ኑዛዜአችን ከፍ ይላል፡፡ በዚያውም ልክ ሰላማችንና ዕረፍታችንም ይበዛል፡፡ መንፈስ ቅዱስም በኃጢአተኛው ልብ እየሠራ ኅሊናው በእግዚአብሔር ብርሃን እንዲታይ ያደርገዋል፡፡ የኃጢአተኝነቱን ጥልቀትና ብዛትም በመረዳት ቅዱስና ጻድቅ ከሆነው ከእግዚአብሔር ሊመጣ የሚችለውን ፍርድ መገመት አያስቸግረውም፡፡

ለማለት የፈለግሁት ዋናው ነገር እግዚአብሔርን በማየት ፈንታ ራሴን እመለከት ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ቃል በሚለኝም አልረካም ነበር፡፡ በኃጢአቴ ምን ያህል መበላሸቴን ከተገነዘብኩ በኋላ የራሴን ድምፅ ከመስማት ይልቅ የእግዚአብሔር ቃል የሚለኝን መቀበል ነበረብኝ፡፡ የእግዚአብሔር ቃል «በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነፃን የታመነና ጻድቅ ነው» እያለኝ ይቅር መባሌን የሚያረጋግጥልኝ በልቤ ወይም በሕይወቴ ልዩ ምልክትን እፈልግ ነበር፡፡ ኃጢአቱን የተናዘዘ ሁሉ ይቅር ይባላል የሚለኝን የእግዚአብሔርን ቃል በማረጋገጫነት መቀበል ነበረብኝ፡፡

የእግዚአብሔር ጽድቅ

እግዚአብሔር እንደ አንድ ሩህሩህ ምድራዊ ፈራጅ ወይም ዳኛ አይደለም፡፡ በምድራዊ አሠራር ልቡ ጠጣር ከሆነው ይልቅ ለስለስ ያለውን ዳኛ አግባብቶ ቀለል ያለ ፍርድ ተቀብሎ ማምለጥ ይቻል ይሆናል፡፡

የእግዚአብሔር ጸጋ እና ፍቅር ግን ጻድቅነቱን በሚፃረር መንገድ መሥራት አይችሉም፡፡ ይህም አስገራሚ ከሆነው የወንጌል ክፍል አንዱ ነው፡፡ አንድ ቀን በኃጢአተኛው ላይ በጽድቅ የሚፈርደው እግዚአብሔር ጌታችን ኢየሱስን አምኖ ወደ እርሱ የሚመጣውን ኃጢአተኛ ደግሞ አሁን ኃጢአቱን ይቅር በማለትና በደሉን በመደምሰስ ጻድቅነቱን ያሳያል፡፡

በሮሜ.1፡17 «የእግዚአብሔር ጽድቅ ከእምነት ወደ እምነት በእርሱ ይገለጣል» ሲል በሮሜ.3፡26 ደግሞ «ራሱ ጻድቅ እንዲሆን በኢየሱስም የሚያምነውን እንዲያጸድቅ አሁን በዚህ ዘመን ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው» እያለ ቃሉ በእምነት ስላለው ጽድቅ ያስረግጥልናል፡፡

መጽደቅ

እግዚአብሔር ጻድቅ እንደመሆኑ መጠን ፍርዱም ሁል ጊዜ ቅን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በአሳዛኝ ሁኔታ ለዘላለም ሊጠፋ ለነበረው የሰው ልጅ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ መስቀል ላይ ቤዛ ሆኖ በፈፀመው ሥራ የመዳንን መንገድ ከፍቶለታል፡፡ የእግዚአብሔር ፍቅር ኃጢአተኛውን ከዘላለማዊ ጥፋት ሊያድን ተገለጠ፡፡ ግን ነገሩ በዚህ ብቻ አያበቃም፤ በጻድቅነቱ ኃጢአተኛውን መቅጣት አለበት፡፡ የእግዚአብሔር ፍቅር ደግሞ ጻድቅነቱን እየተፃረረ መሥራት አይችልም፡፡

እግዚአብሔር «ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደማወቅ እንዲደርሱ» በወደደ መጠን (1ጢሞ.2፡4) በዕብራውያን 10 እንደምናነብበው አስገራሚው የክርስቶስ የሊቀካህናትነት አገልግሎት ተከናወነ፡፡ እርሱም ጌታ ኢየሱስ «አምላኬ ሆይ ፈቃድህን ለማድረግ ወደድሁ» (ዕብ.10፤ መዝ.40) ባለው መሠረት የሰውን ዘር የኃጢአት ዕዳ በተመለከተ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሔ ይሰጥ ዘንድ በመስቀል ላይ ተቸነከረ፡፡ እርሱ ኃጢአት የሌለው ሲሆን ስለእኛ ኃጢአት ሆኖ ተሰቀለ፡፡ እግዚአብሔርም በኃጢአት ላይ ያለውን የቁጣ ፍርድ በእርሱ ላይ አወረደ፤ በዚህም ፍርድ የእግዚአብሔር ጻድቅነት ምላሽ አገኘ፡፡

ጌታችን ግን ይህንን ፍርድ ለራሱ ሲል አልተቀበለውም፡፡ እርሱ ሁሌም «ቅዱስ፣ ንጹሕና ኃጢአት ያላወቀ» ተብሎ የሚጠራ ነው፤ መድኃኒት አዳኝ ነው ብለው በእምነት ለሚቀበሉትም ሁሉ ምትክ ሆኖ ያንን ኃጢአታቸውን ተሸከመላቸው፡፡

እያንዳንዱ ኃጢአተኛም ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ያስፈልገዋል፤ እግዚአብሔርም በመልእክተኞቹ በኩል ሰዎች ከእርሱ ጋር እንዲታረቁ ይፈልጋል (2ቆሮ.5፡20) በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እምነት በኩል የሚመጣ ሰውም ይቅርታን እንደሚያገኝ የእግዚአብሔር ፍቅርና ጻድቅነቱ ያረጋግጥልናል፡፡

የጌታ ትንሣኤ የእግዚአብሔር ጽድቅ ማረጋገጫ ነው

ይህንን ርእስ ጠለቅ ባለ መልኩ ማየት እፈልጋለሁ፡፡ ጌታ ኢየሱስ ለተቀበሉት ሁሉ ኃጢአታቸውን እንዲሸከምላቸው በመስቀል ላይ ተቸነከረ (1ጴጥ.2፡24)፤ ኃጢአትም በመሆን ተኮነነ (2ቆሮ.5፡21፤ ሮሜ8፡3) ይህንን ፍርድ የተቀበለበት ምክንያትም የኃጢአት ደሞዝ ሞት (ሮሜ6፡23) እና ከእግዚአብሔር መለየት በመሆኑ ነው (ራእ.20፡14-15) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ሁሉ ቅጣት በመስቀል ላይ ተሸከመ፤ በእነዚያ የሥቃይ ሰዓታትም በእግዚአብሔር ተተወ፤ «ተፈፀመ» ብሎም ሞተ፡፡

የቤዛ መሥዋዕትን ከፈፀመ በኋላ ጌታችን መቃብር ውስጥ መቅረት ነበረበትን? በመጀመሪያ በእርሱ ላይ ፍርድ ያስከተለው የእግዚአብሔር ጽድቅ አሁን እርሱ ሞቶ እንዲቀር የሚጠይቅ አይደለም፤ ምክንያቱም ሥራው ተፈጽሞአልና፡፡ የእግዚአብሔር ጽድቅ የጠየቀው ክፍያም ተከፍሎአል፡፡ በመሆኑም እግዚአብሔርም ከሞት አስነሣው (ኤፌ.1፡21)፤ ስለዚህ ለእኛም ሆነ ለዓለም ጌታችን ስለእኛ ሲል በመስቀል ላይ የሠራውን የቤዛነቱን ሥራ እግዚአብሔር እንደተቀበለውና በዚያም እንደረካ ትንሣኤው ማረጋገጫ ነው(ዮሐ.16፡8-10)፤ ባይነሣ ኖሮ ግን ሥራው እንዳልተፈፀመ የሚያሳይ ምልክት ይሆን ነበር፤ በዚህም ምክንያት የሚዋጀንን አናገኝም ነበር (1ቆሮ.15፡17፣18) ከዚህም በመነሣት ትንሣኤ የወንጌል ዋናው አስፈላጊ ነጥብ መሆኑን ማመዛዘን እንችላለን፡፡ ትንሣኤን በተመለከተ የሚኖር ተቃውሞ ካለ የወንጌልን መልእክት ፈጽሞ ያበላሸዋል ማለት ነው፡፡

ለዚህም ነው ቃሉ ስለበደላችን አልፎ የተሰጠው እርሱ እኛን ስለማፅደቅም እንደተነሣ የሚናገረው (ሮሜ 4፡25) አሁን በምንኖርበት የጸጋ ዘመን እግዚአብሔር ለሁሉም ሰው «ሁሉ ኃጢአት ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል» ይልና «ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ፡፡ እርሱንም እግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ በደሙም የሆነ ማስተስረያ አድርጎ አቆመው (ሮሜ3፡23-25) በማለት መድኃኒት ወደ ሆነው እንድናይ ይጋብዘናል፡፡

ይህ መልእክት ለሁሉም ሰው ቢሆንም እንኳን የሚቀበሉት የሚያምኑቱ ብቻ ናቸው (ሮሜ3፡22) ይህም ማለት የእግዚአብሔርን መልእክት ሰምተውና መጥፋታቸውን አምነው ጌታችን ኢየሱስን በእምነት የተቀበሉት የዚህ ጸጋ ተቀባዮች ይሆናሉ ማለት ነው፡፡

አሁን አንተ መንፈስ ቅዱስ በልብህ ከሠራው ሥራ የተነሣ ኃጢአተኝነትህን አውቀሃል፡፡ የጠፋ ሰው መሆንህንም ተረድተሃል፡፡ ስለ ምንነትህም ለእግዚአብሔር ተናዝዘሃል፡፡ ያደረግከውን ሁሉ ተናግረሃል፡፡ እግዚአብሔርም ወደ ጌታ ኢየሱስ በማመላከት እንዲህ አለህ፤ እርሱ ስለ ኃጢአተኞች ሞቶአልና እርሱን ብትቀበለው ግን እኔ አንተ ልትፈፅመው ያልቻልከውንና እርሱ የሠራውን አንተ እንደፈፀምከው እቆጥረዋለሁ፡፡ አንተም ኢየሱስ ክርስቶስን ተቀብለሃል፡፡ አሁን ደግሞ ኃጢአትህ ይቅር መባሉን እግዚአብሔር ነግሮሃልና እውነት መሆኑን ማመን አለብህ፡፡ እግዚአብሔር የተናገረው እውነት ነውና አሁን ኃጢአትህ ይቅር እንደተባለልህ ማመን አለብህ፡፡ ለዚህም ስሜትህ የሚነግርህ ነገር አዎንታዊም ይሁን አሉታዊ ጠቃሚ አይደለም፡፡ ይቅርታ ማግኘታችንን በእግዚአብሔር ቃል እንጂ በስሜት አናረጋግጥም፡፡ ያኔ በፋሲካው ሌሊት ቀሣፊው መልአክ ወደ ግብፅ ምድር በተላከበት ጊዜ ደም የተቀባውን በር ሁሉ እየተሻገረ አለፈ (ዘጸ.12) እንዳይቀሠፍ የተፈራው በኩር ወይም እቤት ውስጥ ያሉት ሌሎች መልአኩን ቢያዩም ባያዩም የሚያመጣው ልዩነት አልነበረም፡፡ እግዚአብሔር አድርጉ ያላቸውን እስካደረጉ ድረስ ነገር ሁሉ በጎ ነው ማለት ነው፡፡ ልባቸው ሰላም እንዲሞላ ደግሞ መቅሠፍቱ ከቤታቸው ያልገባበቱ ምክንያት እግዚአብሔር በተናገረው መሠረት እንደሆነ ማመን ነበረባቸው፡፡

ከሁሉም በላይ የሚያስገርመው ደግሞ እግዚአብሔር ኃጢአተኛን ሲቀበል በሁሉም ነገር ይከብራል፡፡ መሐሪነቱ ጸጋውና ፍቅሩ ይታያል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን ኃጢአተኛ ወደ እግዚአብሔር ሲመጣ ክርስቶስ የፈፀመው ሥራ ኃጢአተኛው እንደሠራው ይቆጠርለታል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢአትን ቅጣት በሙሉ ስለተሸከመ እግዚአብሔር ደግሞ አማኙን አንዳች ቅንጣት ኃጢአት ሠርቶ እንደማያውቅ ይቆጥረዋል፡፡ ስለዚህ ከሚመጣው ፍርድ ያመልጥ ዘንድ አማኙን በማጽደቁ የእግዚአብሔር ጻድቅነት ይገለጣል፡፡ ጻድቅነቱና እውነተኝነቱም ይረጋገጣል፡፡ ይህም ደግሞ «ኃጢአታችንን ብንናዘዝ» እርሱ ይቅር ይለን ዘንድ «የታመነና ጻድቅ» መሆኑ(1ዮሐ.1፡9) በቃሉ በመገለጡ ተረጋግጧል፡፡

እግዚአብሔር ማንነታችንን ያውቃል

እንደዚህ በማለት ትናገር ይሆናል፤ «ከድሮው ምንም ልዩነት አይሰማኝም፡፡ እንዲያውም ከድሮ የባሰ ኃጢአት እየሠራሁ ነኝ፡፡»

ድሮ ካየኸው አሁን በጣም ብዙ ኃጢአቶች በሕይወትህ መኖራቸውን ታውቅ ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ የሚጠበቅና መሆን ያለበትም ነው፡፡ ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ ዓይኖችህን ከፍቶልሃል፡፡ እግዚአብሔር ገና ወደ እርሱ ስትመጣ በሚገባ ያውቅህ ነበር፡፡ ልብህን፣ ሕይወትህንና የሠራሃቸውን ኃጢአቶች፣ ወደፊት የምትሠራቸውን ኃጢአቶችንም ያውቃል፡፡ በዚህ ምድር እስካለህ ድረስ የማታውቀውን ብዙ ነገር ያውቅ ነበር፡፡ «እኛ ደግሞ አስቀድመን የማናስተውል ነበርንና የማንታዘዝ፣ የምንስት፣ ለምኞትና ለልዩ ልዩ ተድላም እንደ ባሪያዎች የምንገዛ፣ በክፋትና በምቀኝነት የምንኖር፣ የምንጣላ፣ እርስ በእርሳችን የምንጠላላ ነበርን፡፡ ነገር ግን የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደዱ በተገለጠ ጊዜ እንደምሕረቱ መጠን አዳነን»(ቲቶ3፡3-4) «ገና ደካሞች ሳለን ክርስቶስ ዘመኑ ሲደርስ ስለ ኃጢአተኞች ሞቶአልና፡፡ ስለ ጻድቅ የሚሞት በጭንቅ ይገኛልና ስለቸር ሰው ግን ሊሞት እንኳ የሚደፍር ምናልባት ይገኝ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን»(ሮሜ5፡6-10)፡፡ እንዲሁም 2ቆሮ.5፡20)፡፡

ከእግዚአብሔር ጋር ታርቀናል

ማንነትህን በደንብ በማወቅ በእርሱ አምነህ የዘላለምን ሕይወት እንድታገኝ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስን ሰጠህ፡፡ ቃሉም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ደም በማመን ወደ እግዚአብሔር ብትቀርብ በነጻ እንዲሁ ትጸድቃለህ በማለት ይናገራል(ሮሜ3፡23-25) በእምነት ብቻ ወደ እርሱ በመቅረብህም ከበደለኝነትህ ነፃ ትወጣለህ፡፡ በዚህም የእግዚአብሔር ጻድቅነት ይገለጣል፡፡ በደልህን እየተናዘዝክ ወደ እርሱ እስከ መጣህ ድረስ እግዚአብሔር በአንተ ላይ አንዳች ክስ አይኖረውም፡፡ በእርሱ አመለካከት ሁሉም የተስተካከለ ሆኖአል ማለት ነው፡፡

አንተም እግዚአብሔርን የምትቃወምበት ወይም በእግዚአብሔር ላይ የምታነሳው ክስ አንዳች እንደሌለህ የታወቀ ነው፡፡ ከመጀመሪያም በደለኛው አንተ ነህ፡፡ ይቅርታ መጠየቅ ያስፈለገህም አንተው ነህ፡፡ ታዲያ ለምን ሰላም አጣህ? ከእግዚአብሔር ጋር በሰላም መሆን ማለትም በአንተና በእርሱ መካከል መፍትሔ ያላገኘ ጉዳይ የለም ማለት ነው፡፡

ይህም ሁሉም ነገር መስተካከሉን ያሳያል፡፡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመንህ ዘላለማዊ ቤዛነትን አግኝተሃልና እግዚአብሔርም እንዲያው በእርሱ ስላጸደቀህ በአንተ ላይ አንዳች ተቃውሞ አይኖረውም (ሮሜ5፡1፤ ዕብ.9፡12) አንተም ከእግዚአብሔር ጋር ስለታረቅህ እርሱን የምትቃወምበት አንዳች የለህም(2ቆሮ.5፡20) ከእርሱ ጋር ሰላም ፈጥረሃል፡፡ በእምነት ጸድቀህ «በእግዚአብሔር ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ» ሰላም መያዝህንም ቃሉ ያሳያል (ሮሜ 5፡1)፡፡

እኔ ግን ሰላም አይሰማኝም

ይሁን እንጂ አሁን ምንም ሰላም አይሰማኝም እያልክ ነው፡፡ በእርግጥም ላይሰማህ ይችላል፡፡ ነገር ግን ስላልተቀበልከው ነው እንጂ ሰላም ከአንተ ጋር ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም አድርጎልሃል፤ እርሱም ሰላማችን ነው፡፡ ሰላሙንም ያውጅልናል(ኤፌ.2፡16-17) ይህም ሰላም የተገኘው በመስቀል ከፈሰሰው ደም የተነሣ ነው (ቆላ.1፡20) ስለዚህ ክርስቶስን ስትቀበል ይህን ሰላም ከእርሱ ጋር ተቀብለኸዋል፡፡ ነገር ግን ሰላም እንዲሰማህ ከፈለግህ ሰላምን መቀበልህን ማመን አለብህ፡፡ በመስቀል የፈሰሰው የክርስቶስ ደም ሰላም ማስገኘቱን እግዚአብሔር ከተናገረ ማመኑ ደግሞ ያንተ ፈንታ ነው፡፡

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፓስፊክ ውቅያኖስ በነበረች በአንዲት ደሴት እንደ ነበሩ የጃፓን ወታደሮች አትሁን፡፡ እነዚያም ወታደሮች ጦርነቱ አልቆ አምስት ዓመት ካለፈ በኋላም የሰላሙን ዜና ስላላመኑ በጦርነቱ ወቅት እንደነበረው በጦርነት ዝግጅትና በተጠንቀቅ ይኖሩ ነበር፡፡

እውነትን ለመናገር ከሆነ እስከ አሁን ሰላም ያላገኘህበት ምክንያት የእግዚአብሔርን ቃል በሙሉ ልብህ ስላላመንክ ነው፡፡ ይህም ለአንተ ትልቅ ኪሳራ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ቃሉን አለማመንህ ደግሞ እግዚአብሔርን አለማክበርህን ያሳያል፡፡ «ሐሰትን ይናገር ዘንድ እግዚአብሔር ሰው አይደለም» (ዘኁል.23፡19)፡፡

ቃሉን በሙሉ ልብህ ተቀብለህ ካመንክ ላደረገልህ ሁሉ እግዚአብሔርን ሳታመሰግነው አታልፍም፡፡ ምን ያህል የበዛ ጸጋ እንደሰጠህም ታስተውላለህ፡፡ ልብህም በሰላሙ ይሞላል፡፡ ቃሉን ሳታምን ግን ሰላሙ አይመጣም፡፡ ሰው መጀመሪያ ላይ «እይ ከዚያም እመን» ሲል እግዚአብሔር ግን መጀመሪያ «እመን ከዚያም እይ» ይላል፡፡

ከሰላምታ ጋር
ወንድምህ

ምዕራፍ 4 ከኃጢአት ኃይል ነፃ መውጣት

ውድ ወዳጄ

እንግዲህ አሁን ክርስቶስ በፈፀመልህ ሥራ ኅሊናህ አርፎአል፡፡ ኃጢአትህን በእግዚአብሔር ፊት ተናዝዘህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያደረገልህን አምነህ ተቀብለሃል፡፡ ወደ ፍርድ ቀርቤ ይፈረድብኛል የሚል ፍርሃትም የለብህም፡፡ ኃጢአትህ በሞላ ታላቅና ታናሽ ሳይባል መደምሰሱን እያሰብክ መዘመርም ትችላለህ፡፡

ይህ ሁሉ ሲሆንልህ ግን ከአባባልህ እንደምረዳው እውነተኛ ደስታ ያለህ አትመስልም፡፡ በአንድ ወቅት ደስ ደስ የሚልህ ጊዜ ኖሮ ይሆናል፡፡ አሁን ግን ደስታ የሚባል ነገር አይሰማህም፡፡ ለምንድነው? ብዬ መጠየቅም አያስፈልገኝም፡፡ እኔ ራሴ ያለፍኩበት ነገር ነውና፡፡ የእግዚአብሔር ቃልም ደግሞ የሚመሰክረው ይህንኑ ነው፡፡

ከራስህ ፍሬ ስላጣህ በጣም ተስፋ ቆርጠሃል፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ታርቀህ ስለዳንክ ሕይወትህ ወዲያው ተቀይሮ ለውጥ የምታሳይ መስሎህ ነበር፡፡ ግምትህ የተሳሳተ መሆኑንም ማስተዋል ጀምረሃል፡፡ ድሮ የምታስበው ኃጢአት አሁንም በአእምሮህ ያልፋል፡፡ ከማመንህ በፊት የነበሩ መጥፎ አመሎች አሁንም አልለቀቁህም፡፡ እንደ ድሮው አሁንም ትናደዳለህ፤ ሰውን ለማክበር አልተቻለህም፡፡ እንደዚህ መሆን የለብኝም ብለህ ታስባለህ፤ ልክም ነህ፤ እግዚአብሔርም አይደግፈውም፡፡ ይህንን ነገር ላለማድረግ ብትሞክርም አልሆነልህም፤ እንዲያውም እየባሰብህ ተቸግረሃል፡፡ አሁንስ አሻሽያለሁ ብለህ መፅናናት ስትጀምር እያገረሸብህና ከድሮው እየከፋብህ ግራ ተጋብተሃል፤ ስለሆነም እግዚአብሔር በኃጢአትህ ድል እንዲሰጥህ ብዙ ጸልየሃል፡፡ ግን ምንም ውጤት አላየህም፡፡ «ጧት ጧት በጸለይኩ ቊጥር ነገሩ እየባሰ ይሄዳል» ብላ እንደ ነገረችኝ አንዲት ክርስቲያን እህት የሆንክ ይመስለኛል፡፡

ይህ ሁሉ በሕይወቴ ያየሁት ነገር ነው፡፡ ከዳንኩ ለሁለት ዓመት ያህል አንተ በተቸገርክበት በመቸገሬ ድኛለሁ ብዬ ለሰው ሳልነግር ቆየሁ፡፡ በማሳየው ባሕርይ ከማፈሬ የተነሣ ጌታን መቀበሌን ለእናቴም ሳይቀር አልተናገርኩም፡፡ እርሷም ባለማወቅዋ መለወጥ ያስፈልግሃል እያለች ደጋግማ ትነግረኝ ነበር፡፡ እኔ ግን መለወጤን ወይም ጌታን መቀበሌን አልነግራትም ነበር፡፡ ከማሳየው ባሕርይ የተነሣ ታምነኛለች ብዬ አልገምትም ነበርና፡፡

ይህ ግን ለምን ሆነ? ባሕርይ ሳይለወጥ እየቀረ ክርስቶስን አምኖ ነገር ግን ሳይፈልጉ የሚጠሉትን ኃጢአት በተደጋጋሚ እያደረጉ እጅግ እየተረበሹ መኖር የእግዚአብሔርን ልጅነት ላገኙ ሰዎች የተገባ ሁኔታ አይደለም፡፡

ለዚህም ሁለት ምክንያቶች አሉ፤

  1. የእግዚአብሔር ቃል እንደሚነግረን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የፈፀመልንን በትክክል አላወቅንም ወይም አልተረዳንም፡፡
  2. እውቀቱ ቢኖረንም በሕይወታችን ላይ በተግባር አናውለውም ይሆናል፤ ይህም ቃሉን አለማመናችንን ያሳያል፡፡ የሰው ሁኔታ

ባለፈው ደብዳቤዬ ከሮሜ መልእክት በመነሣት ሁሉም ሰው ኃጢአተኛና በእግዚአብሔር ፊትም በደለኛ እንደሆነ ገልጬልህ ነበር፡፡ በአንፃሩም ደግሞ ጌታችንን ኢየሱስን የተቀበለ ሁሉ የኃጢአትን ይቅርታ ይቀበላል፡፡ ይህም ማለት እግዚአብሔርም ያንን ሰው ያጸድቀዋል ማለት ነው፡፡ በመሆኑም የተለወጠው ኃጢአተኛ «እንግዲህ በእምነት ከጸደቅን በእግዚአብሔር ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እንያዝ» (ሮሜ5፡1) ብሎ መናገር የሚችልበት ደረጃ ደርሶአል ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም በደለኞች ይድኑ ዘንድ እግዚአብሔር አስፈላጊ የሆነውን ነገር ሁሉ አዘጋጅቶአልና፡፡

ከሮሜ5፡12 ጀምሮ ያለውን ብንመለከት ስለ ኃጢአቶች ወይም ስለ ኃጢአት ድርጊቶች አያወራም፡፡ ግን ስለ ጠቅላላ የሰው ሁኔታ ይናገራል፡፡ ሰው ለምንድን ነው ኃጢአትን ያለመቸገር በቀላሉ የሚሠራው? ምክንያቱም ልቡ ከተፈጥሮው ክፉ ስለሆነ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃልም «የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኮለኛ እጅግም ክፉ ነው ማንስ ያውቀዋል?» (ኤር.17፡9) ይለናል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንደዚህ ይላል፤ «ከውስጥ ከሰው ልብ የሚወጣ ክፉ አሳብ ዝሙት፣ መስረቅ፣ መግደል፣ ምንዝርነት፣ መጎምጀት፣ ክፋት፣ ተንኮል፣ መዳራት፣ ምቀኝነት፣ ስድብ፣ ትዕቢት፣ ስንፍና ናቸው (ማር.7፡21-22) በሌላ ቦታ ደግሞ ሐዋርያው ጳውሎስ ምን እንደምንመስል ሲገልፅ «እኛ ደግሞ አስቀድመን የማናስተውል ነበርንና፤ የማንታዘዝ፣ የምንስት በምኞትና በልዩ ልዩ ተድላ እንደ ባሪያዎች የምንገዛ በክፋትና በምቀኝነት የምንኖር የምንጣላ፣ የምንጠላላ ነበርን» ይላል (ቲቶ3፡3) በዚህ ቃል እንደምናየው ተፈጥሮአችን፣ ሁኔታችንና ዝንባሌአችን ተዘርዝሮአል እንጂ አንድም የኃጢአት ድርጊት አልተጠቀሰም፡፡

ሰው በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ

በሮሜ.5፡12-21 እንደምናነበው የኃጢአትኝነትን ባሕርይ የምናሳይበት ምክንያት ሁላችንም የአዳም ልጆች በመሆናችን እንደሆነ ተጠቅሶአል፡፡

አዳም በእግዚአብሔር አምሳል እንደተፈጠረ ቃሉ ይነግረናል (ዘፍ.1፡26) ይህም በእግዚአብሔር አምሳል መፈጠሩ በሥነ ፍጥረት የተሰጠውን ደረጃ ያሳየናል፡፡ አዳም እግዚአብሔርን በመወከል በምድር ላይ በአሳዳሪነት መጋቢ ሆኖ ለምድራውያን ፍጥረታት ራስ ነበር፡፡ ከዚያ ቀጥሎ በተከሰተው ውድቀትና መበላሸት ብዙ ለውጥ ተከትሎ ይምጣ እንጂ አሁንም ቢሆን አዳምም ሆነ የእርሱ ተተኪ የሆነው ሰው በእግዚአብሔር ሥነ ፍጥረት መካከል «የእግዚአብሔር ምሳሌና ክብር» እንደሆነ ቃሉ ይነግረናል (1ቆሮ.11፡7)

«በእግዚአብሔር ምሳሌ» ... (ተፈጠረ)፡፡½ የሚለው ሐረግ የአዳምን ንጽሕናና ኃጢአት አልባነት ያሳየናል፡፡ ብዙ አልቆየም እንጂ ፍጡር በንጽሕናው ከፈጣሪው ጋር ይጣጣም ነበር፡፡ አዳም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመተላለፉ ንጽሕናውን አጠፋ፡፡ በበደል የተሞላ ኃጢአተኛ ሆነ፡፡ ከውድቀቱ በኋላ ለአዳምም ሆነ ለልጆቹ የእግዚአብሔር ምሳሌ ናቸው ተብሎ አልተነገረም፡፡ ይህ ሐረግ ሁል ጊዜ ለሥነ ፍጥረት የተወሰነ ነበር፡፡

ሰው በአዳም መልክና ምሳሌ

ዘፍጥረት 5 ቊጥር 1 ሰው በእግዚአብሔር ምሳሌ እንደተፈጠረ ሲያሳየን፣ ቊጥር 3 ደግሞ አዳም ልጅ እንደወለደና የወለደውም «በምሳሌውና በመልኩ» እንደነበር ይነግረናል፡፡ ስለዚህ ከኃጢአተኛው አዳም የተወለደው የአዳም ልጅ በኃጢአተኛ መልክና አምሳል እንደተወለደ እንረዳለን፡፡ ስለዚህም ከዚያን ጊዜ ወዲህ የተወለደ ሰው ሁሉ ኃጢአተኛ ሆኖ ይወለዳል፡፡

ኢዮብ «ከርኩስ ነገር ንጹሕ ሊያወጣ ማን ይችላል? አንድ እንኳ የሚችል የለም»፣ ሲል ዳዊት ደግሞ «እነሆ በዓመፃ ተፀነስሁ እናቴም በኃጢአት ወለደችኝ» በማለት ይናገራል (ኢዮ.14፡4፤ መዝ.51፡5) ይህንንም በሮሜ መልእክት በምዕ.5 ከቁ.12-21 ካለው መረዳት እንችላለን፡፡ በአንዱ አዳም በደል ብዙዎች ሞተዋል፤ ምክንያቱም በአንዱ አዳም በደል ሞት ነግሦአልና (ቀ.15 እና17) በአንዱ አዳም በደል ምክንያትም ፍርድ ለኩነኔ ወደ ሰው ሁሉ መጣ (ቁ.18) በአንዱ አዳም አለመታዘዝም ዘሮቹ በሙሉ ኃጢአተኞች ሆኑ (ቁ.19)፡፡ ስለዚህ በሌላ አባባል ሰው ገና ሲወለድ ልክ አዳም በበደል ሲወድቅ የነበረበትን ሁኔታ ይወርሳል፤ ከኤደን ገነትና ከእግዚአብሔር ፊት የተባረረና ሞት የሚጠብቀው ኃጢአተኛም ይሆናል፡፡

ይህ ምንባብ ሰው የሠራውን ኃጢአት አያሳይም፡፡ ግን የሰውን ሁኔታ ወይም ባሕርይ ያሳያል፡፡ ሰው አንዲት ቅንጣት ኃጢአት ከመፈፀሙ በፊት ሞት የተገባው የተኮነነ ኃጢአተኛ ነው፡፡ ይህ ተፈጥሮአዊ የሰው ሁኔታ ሲሆን በመወለዱ ግን በደለኛ አይደለም፡፡ በኃጢአተኛው አዳም መልክ በመወለዱ ግን የሕፃንነቱ ወራት እንዳበቁ ለበደል የተሰጠ ይሆናል፡፡ ስለሆነም በደለኛ የሚሆነው በተግባሩ ነው፡፡ በሚሠራቸው ኃጢአቶች በደለኛ ይሆናል፡፡ በእግዚአብሔር ቃል እንደምናየውም ሙታን የሚፈረድባቸው በተፈጥሮአዊ ሁኔታቸው ወይም በጥንተ አብሶ ሳይሆን በሥራቸው እንደሆነ ያስረዳል (ራእ.20፡12) ቢሆንም ግን የሰው ተፈጥሮአዊ ሁኔታ ለመንግሥተ ሰማያት ብቁ እንዳይሆን ያደርገዋል፡፡ እግዚአብሔር በተፈጥሮው የኃጢአተኛነት ባሕርይ ያለውን አንድ ሰው እንኳ በፊቱ ይቆም ዘንድ አይታገሥም፡፡ እግዚአብሔር ቅዱስ ስለሆነ እንደዚህ ዓይነቱን ሰው ለዘላለም ከፊቱ ያባርረዋል፡፡ «እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱም ዘንድ ከቶ የለም›› (1ዮሐ.1፡5)፤ ስለዚህ ጨለማ ከሆኑት ጋር (ኤፌ.5፡8) ተቻችሎ መኖር አይችልም፡፡ «ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወደ አለበት በውጭ ወዳለው ጨለማም» የሚወረውራቸው ለዚሁ ነው (ማቴ.8፡12፤ 22፡13) ስለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ቤዛ ባይሆንልን ኖሮ ወደ ሰማይ የሚገባ ማንም ባልተገኘ ነበር፡፡ ቅንጣት ኃጢአት ሳይሠሩ እንደተወለዱ ወዲያው የሚሞቱ ህፃናትም ቢሆኑ መጽደቅ አይችሉም ነበር፡፡

የኃጢአት ይቅርታ በቂ አይደለም

ለዚህም ነው የኃጢአት ይቅርታን ማግኘት ብቻውን በቂ አይደለም የምንለው፡፡ ጌታ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሠራናቸውን ኃጢአቶቻችንን ተሸክሞ ከዚያ በተጨማሪ ሌላ ምንም ነገር ባያደርግልን ኖሮ በሠራናቸው ኃጢአቶች ምክንያት ባይፈረድብንም ለዘላለም መጥፋታችን ግን የማይቀር ነገር ይሆን ነበር፡፡ እግዚአብሔር በሰው የሚሠሩ ኃጢአቶችን ይቅር ሊል ይችላል፤ ነገር ግን ክፉ ሁኔታን፣ ወይም ክፉ የኃጢአተኝነት ባሕርይን ይቅር ማለት አይችልም፡፡ እግዚአብሔር መሆን በሚችለው በማናቸውም መንገድ ሰው በውስጡ በጎ የሆነ ነገር ካለ ያንን ያሳይ ዘንድ ዕድልን ሰጥቶታል፡፡ ገና አንዲት ትእዛዝ ወይም ሕግ ባልሰጠበት ከጥፋት ውሃ በፊት በነበረው ጊዜ እና ከጥፋት ውሃ በኋላ ደግሞ ክፋትን ለመግታት የመንግሥት ሥርዓትን በሰጠበት ወቅት (ዘፍ.9፡5-6) የተሰጠ ዕድል ነበር፡፡ ከዚያም እስራኤልን ሕዝቡ እንዲሆኑ ለየ፤ ሕግጋትንና ሥርዓታትንም ሰጣቸው፤ ከቸርነቱ የተነሣም በመካከላቸው ሊኖር መጣ (ዘዳግ.4፡6-8) ቀጥሎም መሳፍንትን፣ ነቢያትንና ነገሥታትን ሰጣቸው፡፡ እንዳስፈላጊነቱም ተግሣጹን ያሳያቸው ነበር፡፡ በመጨረሻም እርሱ ራሱ ከጸጋው የተነሣ ወደ ምድር መጥቶ በሥጋ ተገለጠ፡፡ በደላቸውን ሳይቆጥርባቸው «እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበር» (2ቆሮ.5፡19) ነገር ግን የሆነው ነገር ምን ነበር? «የእርሱ ወደሆነው መጣ፤ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም፡፡»፣ ሰዎች ደግሞ «ከብርሃን ይልቅ ጨለማን» ወደዱ (ዮሐ.1፡11፤ 3፡19) ሰው ሙሉ በሙሉ ክፉ ከመሆኑ የተነሣም ራሱን በጸጋ የገለጠውን አምላክ እስካለመቀበል ደረሰ፤ ብሎም «በሥጋ የተገለጠውን አምላክ» (1ጢሞ.3፡16) መስቀል ላይ ወስዶ ቸነከረ፡፡ ሰው ምን ያህል ክፉና የተበላሸ መሆኑም እዚያው መስቀል ላይ ተረጋገጠ፡፡

ጌታችን ኢየሱስ በዮሐ.3 ላይ «ሰው ኃጢአቱ ይቅር ካልተባለለት በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም» ብሎ ያልተናገረው ለዚህም ነው፡፡ ነገር ግን «ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም» ብሎ ተናገረ፡፡

የእግዚአብሔር መልስ

በሮሜ.5፡12-21 ካለው ምንባብ ለዚህ ችግር መልስ ማግኘት እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው ሰው ማለትም ፊተኛው አዳም በኃጢአት ከወደቀ በኋላ የያዘውን ስፍራ እርሱን ተከትለው ለተወለዱት የሰው ዘር በሙሉ አስተላለፈ (1ቆሮ.15፡45-47) እግዚአብሔርም ሁለተኛውን ሰው ማለትም ኋለኛውን አዳም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ላከ፡፡ ክርስቶስም ከእርሱ ጋር አንድ ለሆኑት ሁሉ ሕይወትን እና በመስቀል ላይ የሠራውን ሥራ ከፈጸመ በኋላ የያዘውን ስፍራ ይሰጣቸው ዘንድ መጣ፡፡ ይህ ስፍራ ምንድን ነው? ብለን እንጠይቅ ይሆናል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኃጢአታችንን በመስቀል ተሸክሞ ፍርድን ተቀበለልን (1ጴጥ.2፡24) ይህም ብቻውን አልበቃም፡፡ እግዚአብሔር ልጁን «በኃጢአተኛ ሥጋ ምሳሌ አድርጎ በኃጢአት ምክንያት» በመላክ «ኃጢአትን በሥጋ ኮነነ» (ሮሜ8፡3) ሲል ቃሉ ይነግረናል፡፡ በሌላ ስፍራ ደግሞ «እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው» ይላል (2ቆሮ.5፡21)

እነዚህ ሁለት ምንባቦች በየዕለቱ ስለምንሠራቸው ኃጢአቶች አይናገሩም፡፡ ነገር ግን ስለ ኃጢአተኝነት ወይም በሰው ውስጥ ስላለው የኃጢአተኝነት ባሕርይና በአዳም ውድቀት ምክንያት የወረስነውንና ኃጢአትን የሚያሠራውን ጠባይ በተመለከተ ይናገራሉ፡፡ በሮሜ.8፡3 ላይ «ኃጢአተኛ ሥጋ» የሚለው አጠራር በሮሜ መልእክት ከምዕራፍ አምስት እስከ ስምንት ድረስ የኃጢአተኝነት ባህርያችንን በመግለፅ በተደጋጋሚ ተጽፎ ይገኛል፡፡

እነዚህ ንባቦች እንደሚገልጹት እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በነበረ ጊዜ ኃጢአት እንዲሆን አደረገው፡፡ ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ በዚያ በመስቀል ላይ የዋለው እኛ የሠራናቸውን ኃጢአቶች ለመሸከም ብቻ ሳይሆን የእኛን «የኃጢአተኝነት ባሕርይ ስፍራ» ለመያዝም ነው፡፡ በዚያም ኃጢአት የማያውቀው እርሱ ኃጢአተኛ ባሕርይ እንዳለው እንደ ኃጢአተኛ ሰው ሆኖ በመስቀል ላይ ተፈረደበት፡፡ በሰው የኃጢአተኝነት ባሕርይ እና በዕለታዊ የኃጢአት ሥራዎቹ በሁለቱም ላይ የነበረው የእግዚአብሔር ፍርድ በጌታ በኢየሱስ ላይ ፈሰሰ፡፡ ስለሆነም ጌታ ሞተ ተቀበረም፡፡

ኋለኛው አዳም

የእግዚአብሔር ኃይል ደግሞ ኢየሱስን ከሙታን ተለይቶ እንዲነሣ አደረገው (ኤፌ.1፡20) ይህም በሠራናቸው ኃጢአቶች እና በኃጢአተኝነት ባሕርያችን ላይ የእግዚአብሔር ጽድቅ የሚፈልገው ፍርድ መፈፀሙን ያሳያል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ከሙታን ተነሥቷል፤ ፍርድም ተፈጽሞ አልፎአል፡፡ እርሱም በኃጢአቶችና በኃጢአተኝነት ላይ የተላለፈውን ፍርድ ተቀብሎ በእግዚአብሔር ኃይል ከሙታን በመነሣት የተለየ አዲስ ስፍራን ይዞአል፤ አሁን እርሱ የትንሣኤ ሕይወትን ይኖራል፤ ይህም ፍርዱ ሙሉ በሙሉ ለመጠናቀቁ ማረጋገጫ ነው፡፡ ለአዲስ ቤተሰብ ወይም ለእግዚአብሔር ቤተሰብ ራስ በመሆን የኋለኛው ሰው ማለትም የኋለኛው አዳም የያዘው ስፍራ ይህ ነው፡፡

በሮሜ.5፡12-21 እንደምንረዳው ደግሞ ከእርሱ ጋር አንድ የሆነ ሁሉ ይህንን ስፍራ ይይዛል፡፡ ከእግዚአብሔር ጸጋ የተነሣ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኘው ነፃ ስጦታ ተትረፈረፈ (ቁ.15) «ስጦታው በብዙ በደል ያሉትን ለማጽደቅ መጣ» (ቁ.16) «የጸጋውን ብዛትና የጽድቅን ነፃ ስጦታ የሚቀበሉ በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሕይወት ይነግሣሉ» (ቀ.17) የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ሕይወትን ለጽድቅ ያበቃታል፡፡ በእርሱ መታዘዝም «ብዙዎች ይጸድቃሉ» (ቁ.18 እና 19) ጸጋ ደግሞ በጽድቅ ለዘላለም ሕይወት ትነግሣለች (ቁ.21) ቃሉ «ሞቱን በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን ይላል (ሮሜ6፡5) በኤፌ.2፡5-6 ደግሞ ከዚህ በበለጠ ሲናገር «ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጠን፤ ... ከእርሱ ጋር አስነሣን፤ በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራም ከእርሱ ጋር አስቀመጠን፡፡» ይላል፡፡

ስለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢአታችንን ይቅርታ ብቻ ሳይሆን ከዚያም በላይ እንዳደረገልን ከዚህ ሁሉ እንረዳለን፡፡ ኃጢአተኛ በኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ ኃጢአቱን በመናዘዝ ወደ እግዚአብሔር ሲቀርብ እግዚአብሔር ደግሞ እርሱን የክርስቶስ ወገንና የእግዚአብሔር ቤተሰብ ያደርገዋል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የፈፀመው ሁሉ እርሱ ራሱ እንደሠራው ይቆጠርለታል፡፡ ይህም ማለት የኃጢአት መቀጫ መስቀል ላይ ተፈጽሞ ስርየት ሲያገኝ የኃጢአተኝነት ባሕርይ ደግሞ በክርስቶስ መስቀል በኩል የፍርድ ውሳኔ ተላልፎበት ቅጣት ተፈጽሞበታል፡፡ አሁን ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤው ሕይወት ተካፋይ ይሆናል፡፡ ኋለኛው አዳም «ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ እንደመሆኑ» (1ቆሮ.15፡45)፡፡ በአማኙ ላይ የራሱን የትንሣኤውን ሕይወት እፍ ብሎበታል (ዮሐ.20፡22)፤ ኢየሱስ ክርስቶስም ራሱ በአማኙ ውስጥ ስለሚያድር አማኙ የዘላለም ሕይወት አለው ማለት ነው (ዮሐ.3፡15-16፤ 1ዮሐ.1፡1-2፤ 5፡11-13፣20)፡፡

ከክርስቶስ ጋር መሞት

ይህን ከተረዳን በኋላ ራሳችንን ለማሻሻል ሙከራ አናደርግም፡፡ እግዚአብሔር ተስፋ የለውም ብሎ የተወውን ነገር ለማሻሻል እንደማንችል ተገንዝበናል፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሲሞት እኛም ከእርሱ ጋር እንደሞትን ተቆጥረናል፡፡ ከእርሱ ጋር መሞታችንንና መቀበራችንን ደግሞ በመጠመቅ መስክረናል (ሮሜ6፡3-4) (ሥርዓተ ጥምቀት በማጥለቅ ካልሆነ በመርጨት ሲፈፀም ይህ እውነት ይጋረዳል) ከዚህ ወዲያ እግዚአብሔር ኃጢአት የሌለውና ኃጢአትን መሥራት የማይችል አዲስ ሕይወት ያለው ፍጥረት አድርጎ ይቆጥረናል፡፡ ራሳችንንም ለኃጢአት ሞተን በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ሕያዋን እንደሆንን እንቆጥራለን (ሮሜ6፡11)፡፡

በእኛ ውስጥ ያለውን ኃጢአት ለማሸነፍ መፍጨርጨር የለብንም፡፡ ክርስቲያን እንደዚህ ማድረግ አለበት ተብሎ የተጻፈም አናገኝም፡፡ በተቃራኒው ግን ለኃጢአት እንደሞትን ራሳችንን መቁጠር አለብን (ዕብ.12፡4 ከኃጢአት ጋር ስለመጋደል ይናገራል፤ ሆኖም በዓለም ስላለው ኃጢአት ተናገረ እንጂ በእኛ ውስጥ ስላለው አይናገርም፡፡) በእርግጥ በእኛ ውስጥ ያለው ኃጢአት ተደብቆ ፀጥ አይልም፤ ራሱን መግለጥ ይፈልጋል፤ እኛ ግን ልንፈቅድለት አይገባም፡፡ የኃጢአት ስሜት ከውስጥ ሲጀምር ሐሳባችንን ወደ ክርስቶስ በማዞር ልንከለክለው እንችላለን፡፡ «እኛም ሁላችን በመጋረጃ በማይከደን ፊት የጌታን ክብር እንደመስተዋት እያብለጨለጭን መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ ያን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን» (2ቆሮ.3፡18)፡፡

ይህን ብናደርግ በእኛ የሚኖረው መንፈስ ቅዱስም በኃጢአተኝነታችን ወይም በሥጋችን ላይ ራሱ ይዋጋል (ገላ.5፡17) እንጂ በሥጋ ላይ መዋጋት የእኛ ድርሻ አይደለም፡፡ ነገር ግን ለኃጢአት ሞተን በክርስቶስ ኢየሱስ በመሆን ለእግዚአብሔር ሕያዋን እንደሆንን እንቁጠር (ሮሜ.6፡11)፡፡

ልምምድ

ታዲያ በደብዳቤዬ መጀመሪያ እንደገለጽኩት ብዙ አማኞች ለምን በኃጢአት ሸክም ይቃትታሉ? ‹‹አማኝ በውስጡ ካለው ኃጢአት ጋር ሲጋደል ዕድሜ ልኩን ይወስድበታል›› የሚለው አባባልም ስህተት ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኃጢአትና በሰይጣን ላይ ድል ተቀዳጅቷል፡፡ ስለዚህ ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ያለው በአርነት በመቆም (ገላ.5፡1፣13፣16) የድል ሕይወትን መኖር ይችላል (ሮሜ8፡34)፤ በሮሜ.8፡1-11 ባለው ክርስቲያናዊ ስፍራ ላይ በመቆም ተግባራዊነቱን በሕይወቱ ያሳየ ማንም ሰው ከሰይጣን፣ ከሞትና ከኃጢአት ኃይል ነፃ ይወጣል፡፡ የመንፈስ ፍሬም በሕይወቱ ይታያል(ገላ5፡22-23)፤ ሕግ ከእርሱ የሚጠብቃቸው ነገሮችም በውስጡ ተፈፅመው ይታያሉ (ሮሜ.8፡4)

ሁላችን ደግሞ ይህንን ተጋድሎ በትክክል እናውቀዋለን፤ ምክንያቱም አርነት የሚታወቀው በውስጡ በማለፍ ወይም በልምምድ ነውና፡፡

ሰው ሲለወጥ (አማኝ ሲሆን) ኃጢአቶቹን እያሰበ ይጨነቃል፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ፍርድ ስለሚታየው ነው፡፡ አዲስ ሕይወት በመቀበሉም እግዚአብሔርን ለማገልገል በጣም ይናፍቃል፡፡ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ምን እንደሆነ ከተረዳ በኋላ እንደ ሕግ ሊፈፅመው ይፈልጋል፡፡ ኃጢአተኝነቱን ይበልጥ እየተረዳ ሊሄድ የሚችለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ሮሜ.7ም ይህንን ልምምድ ያሳየናል፡፡

የሮሜ 7 የመጀመሪያዎቹ አራት ቊጥሮች ከክርስቶስ ጋር ለሕግ በመሞት ከሕግ ነፃ ወጥተን ከሙታን ከተነሣው ክርስቶስ ጋር አንድ መሆናችንን ያሳያሉ፡፡ ቊ.5 እና 6 ደግሞ ከዶክትሪን (ትምህርት) ወደ ተግባራዊ ልምምድ ያሻግሩናል፡፡

የመጀመሪያው ልምምድ ሕግ ምንም ኃይል እንደ ሌለው ነው፡፡ ሕጉ «ቅዱስ ነው፤ ጻድቅና በጎ ነው፤» የተሰጠውም ሕይወት ሊሰጥ ነበር፤ «የሚሠራቸው ሰው በእነርሱ በሕይወት ይኖራል» ተብሎ ተጽፎአልና (ዘሌዋ.18፡5) በተግባራዊ ልምምዴ እንደማየው ደግሞ ሕጉ ሞትን የሚያስከትሉ ነገሮችን ያመጣብኛል፡፡ ምክንያቱም ሕግ የሚከለክላቸው የምኞት ኃጢአቶች በትዕዛዛቱ ምክንያት በሕይወቴ መኖራቸውን ተረድቻለሁና፡፡ ይህም የድሮውን አሮጌውን ፍጥረቴን ማንነት በሚገባ እንድረዳ ያስችለኛል፡፡ «በእኔ ማለት በሥጋዬ በጎ ነገር እንዳኖር አውቃለሁ» (ቁ.18) ሆኖም ግን በጎ ነገርን መሥራት እየወደድኩ የምጠላውን መጥፎ ነገር ስሠራ የእግዚአብሔርን ሕግ በመከተል መልካም ነገርን መሥራት በሚወደው በውስጠኛው ሰውና (ቁ.22) መጥፎ ነገርን እንድሠራ በሚገፋፋኝ በእኔ ባለው የኃጢአት ኃይል (ቁ.20) መካከል ያለውን ልዩነት እንዳውቅ ይረዳኛል፡፡ አብሮኝ ለሚኖረው የኃጢአተኝነት ባሕርይ የተማረኩኝ መሆኔንም እረዳለሁ፡፡ ይህን ኃጢአት እንድሠራ የሚያደርገኝ ነገር በእኔ ውስጥ ያለው የኃጢአት ሕግ ስለሆነ በእርሱ ቁጥጥር ሥር በመሆኔ ላስወግደው አልቻልኩም፡፡

መንፈስ ቅዱስም ምን ያህል የተበላሸሁ መሆኔን እንድረዳ ያደርገኛል፤ «እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል?» (ቁ.24) እያልኩ እጮሃለሁ፤ ከዚያ በኋላ በቁ.25 ላይ ከእግዚአብሔር ቃል መልስ አገኛለሁ፡፡ «በኢየሱስ ክርስቶስ በጌታችን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን» የሚል፡፡

አርነት

እኔ ከዚህ ለሞት ከተሰጠ ሥጋ ነፃ ወጥቻለሁ፤ ሥጋም ከክርስቶስ ጋር በመስቀል ላይ ተፈርዶበታል፡፡ አሁን እኔ ሳልሆን ክርስቶስ በእኔ ውስጥ ይኖራል (ገላ.2፡5) እኔም በክርስቶስ እኖራለሁ፡፡ ስለዚህ ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ በተቀመጠበት ስፍራ እኔም ተቀምጫለሁ፡፡ ከእርሱ ጋርም ስለሆንኩ አሁን ኩነኔ የለብኝም (ሮሜ8፡1) መንፈስ ቅዱስም በእኔ ውስጥ አዲስ ሕይወትን ሠርቶአል፡፡ ኃጢአት የሌለውንና ኃጢአት መሥራት የማይችለውን ሕይወት ሰጥቶኛል፡፡ ‹‹ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነው›› እንደተባለ (ዮሐ.3፡5-6)፡፡¿ ከሰጪው ጋር የተስማማ መንፈስ አለኝ፡፡ እንደዚሁም መንፈስ ቅዱስ በሕያው አካሉ ሆኖ በውስጤ ስለሚኖር እንደ ፈቃዱ ይሠራ ዘንድ ለተሰጠኝ አዲስ ሕይወት ኃይል ይሆነዋል (1ቆሮ.6፡14፤ 4፡14)፤ ከሥጋ ጋር ያለውን ጦርነት ደግሞ ራሱ መንፈስ ቅዱስ ያካሂደዋል (ገላ.5፡17)፡፡ ይህም «በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ ነፃ አውጥቶኛል» ማለት ነው (ሮሜ8፡2) ስለዚህም አሁን በሥጋ ነኝ ወይም በአሮጌው ፍጥረት ነኝ ማለት አልችልም፡፡ ነገር ግን በመንፈስ ነኝ እላለሁ፡፡ አሁን ያለሁበት ስፍራ ዳግም በመወለዴ መንፈስ ቅዱስ በሰጠኝ ሕይወት (ዮሐ.3) እና በእኔ ውስጥ በሚኖረው በራሱ በመንፈስ ቅዱስ የተገለጠ ነው (ሮሜ8፡9) ይህም የሚያሳየው እኔ የክርስቶስ ነኝ ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ክርስቲያን እባላለሁ፡፡ ይህ እንግዲህ እውነተኛ አማኝ መሆን ያለበት ትክክለኛ ሁኔታ ነው፡፡ ከሰይጣን፣ ከኃጢአት እና ከሞት ነፃ ወጥቶ እግዚአብሔርን እያገለገሉ ከእግዚአብሔር ጋር የማያቋርጥ ኅብረት እያደረጉ በደስታ መመላለስ ማለት ነው (1ዮሐ.1፡3-4) በዚህ ትክክለኛ ሁኔታ እንድንገኝና እንድንኖር ሁላችንንም እግዚአብሔር ይርዳን፡፡

በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ
ያንተው ወንድም

ምዕራፍ 5 ሰዎች እንዲጠፉ እግዚአብሔር አስቀድሞ ወስኖአልን?

ውድ ወገኖች

መመረጣችሁንና አለመመረጣችሁን ስለማታውቁ በምድር እስካላችሁ ድረስ መዳናችሁንና አለመዳናችሁን ማወቅ አትችሉም ብለው በሚናገሩ ሰዎች ምክንያት ትንሽ ግራ ተጋብታችኋል፡፡

‹‹በእርሱ ያመነ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ...›› (ዮሐ3፡16) በማለት የሚናገረውን የእግዚአብሔርን ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ ጠቅሳችሁ መልስ መስጠት ትችሉ ነበር፡፡ እግዚአብሔር የሚናገረው ነገር ሁሉ እውነት ነውና በዚህ ነገር ግራ ሳትጋቡ ማወቅ ትችላላችሁ፡፡ በእርግጥም ማንም የእርሱን ቃል ማስተባበል አይችልም፡፡

አንድ ጊዜ በዚህ ጥርጥር የተሞላ አንድ ሰው አግኝቼ ነበር፡፡ እኔም ሐዋርያው ጳውሎስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሄዶ የሰማይ መዝገብ አገላብጦ አንብቦ ይሆን እንደሆነ ጠየቅኩት፡፡ ሰውየውም ‹‹አይመስለኝም›› ሲል መለሰልኝ፡፡ ታዲያ ‹‹ወንድሞች ሆይ እንደተመረጣችሁ አውቀናል›› (1ተሰ.1፡4) ብሎ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች እንዴት ሊጽፍ ቻለ? ብዬ ጠየቅኩት፡፡ በመልእክታቱም ይጽፍላቸው ለነበሩ ሰዎች እንዴት ቅዱሳን እያለ ሊጠራቸውስ ቻለ? አልኩት፡፡ መልስ ሊሰጠኝ አልቻለም ነበር፡፡ ነገር ግን በነጋታው መጣና ‹‹እኔም መዳኔን አሁን ተረድቻለሁ›› ሲል ነገረኝ፡፡

በእርግጥ የእግዚአብሔር ቃል መመረጥን በተመለከተ በግልፅ ይናገራል፡፡ ኤፌ.1፡4-5፣ ሮሜ8፡29-30፣ 1ጴጥ.1፡2 ወ.ዘ.ተ አንብቦ ስለ ጸጋው ብዛት እግዚአብሔርን እያመለከ የማያመሰግን ክርስቲያን ማነው?

የሚጠፉትንና የሚድኑትን አስቀድሞ መወሰን

ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ካነበቡ በኋላ ቃሉ በሚለው ሐሳብ በመጽናት ፋንታ በራሳቸው ሐሳብ በመሄድ ከተጻፈው አልፈው መሆን አለበት ብለው የሚያስቡትን የራሳቸውን መደምደሚያ ሲሰጡ ይታያሉ፡፡ የዚህም ውጤት እግዚአብሔርን የማያስከብር ከመሆኑም ባሻገር ቃሉን የሚጻረሩ ሰው ሰራሽ አባባሎችና ሐረጎች ተፈጥረው ሰው እንዲጠቀምባቸው አድርገው እናያለን፡፡ ስለመመረጥ የሚናገረውን የእግዚአብሔርን ቃል በስንጥቅ መስተዋት እንደሚታይ ምስል የሚያጣምም የሁሉም ሰው ዕጣ ፈንታ አስቀድሞ የተቆረጠ ነገር ነው የሚል ዶክትሪን ወጥቶአል፡፡

ይህ ሁሉ አስቀድሞ ተወስኖአል የሚለው ትምህርት ‹‹እግዚአብሔር አንዳንዶችን ለዘላለም ሕይወት መርጦአል›› ይልና ሮሜ.9፡8-23ን በመጠቀም ሌሎች እንዲጠፉ መወሰኑን ያስተምራል፡፡ ይህንን ምንባብ ደግመን ማየት ይኖርብናል፡፡

ጸጋ - ለአይሁድ ብቻ አይደለም

ወደ ሮሜ በተጻፉት በመጀመሪያዎቹ ስምንት ምዕራፎች ሰው ያለበት ሁኔታና እግዚአብሔር ስለሰው ያለው አመለካከት ተገልጦልናል፡፡ ሰው የጠፋ ፍጡር ነው፡፡ ‹‹ልዩነት የለምና፣ ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋል የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፣ በኢየሱስ ክርሰቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ፡፡››(ሮሜ3፡22-24) ስለዚህ ሁሉም በጸጋ ብቻ የሚድኑ ከሆነ ጸጋ ለአይሁድ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ይህም ማለት ጸጋ አይሁድ ላልሆኑት አሕዛብም ጭምር የታደለ ነው ማለት ነው፡፡

አይሁድ ግን ይህንን መቀበል ይቸግራቸዋል፤ ለራሳቸው ብቻ የተከለለ መብት ስለነበራቸው ይህንን ከማንም ጋር ሊጋሩት አይፈልጉም፡፡ የዚህን ወንጌል ለአሕዛብ መስበክ በከባድ ጥላቻ ይቃወሙ እንደነበርም በርካታ ምሳሌዎችን ማየት ይቻላል (ሐዋ.13፡45-50፣ 15፡1፣ 17፡5 እና 28፡25-29 ተመልከት፡፡)፡፡

ወንጌልን በተመለከተ አይሁዳዊም ሆነ የአሕዛብ ወገን በአንድ ዓይነት ሚዛናዊ ዓይን የሚታዩና አንድ ዓይነት ስፍራ ያላቸው ናቸው፡፡ አይሁድ በእግዚአብሔር ዘንድ የተለየ ስፍራ ስለነበራቸው አሕዛብ ደግሞ ከእግዚአብሔር የራቁ ስለነበሩ እነዚህን ሁለት ወገኖች እንዴት ማስታረቅና ማቀራረብ ይቻላል? ለሚለው ጥያቄ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ. መልእክት ከ9-11 ባሉት ምዕራፎች መልስ ሰጥቶበታል፡፡

የአብርሃም ዘር

አይሁድ ያኩራራቸው የነበረው የመጀመሪያው ነጥብ የአብርሃም ዘር መሆናቸው ነው፡፡ መልካም ነው አለ ሐዋርያው፤ ነገር ግን እስማኤልም የአብርሃም ልጅ መሆኑን ማወቅ አለባችሁ ሲል አሳሰባቸው፡፡ ምናልባት እስማኤል ከባሪያ የተወለደ ነበር ተብሎ መከራከሪያ ቢነሳም ከርብቃ የተወለደን የያዕቆብን ወንድም ነገር ግን የአረቦች አባት የሆነውን ኤሳውን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከአንድ አባት ከአንድ እናት የተወለዱ መንትዮች ሲሆኑ ኤሳው መጀመሪያ በመወለዱ በኩር ቢሆንም የሕዝቡ አባት አልሆነም፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝብ አባት የሆነው ያዕቆብ ነው፡፡ ሆኖም ያዕቆብ ከኤሳው ስለተሻለ አልነበረም፤ ሳይወለድ ታላቁ ለታናሹ እንዲገዛ እግዚአብሔር ወስኖ ነበርና፡፡

በዚህም አይሁድ ይህ ልዩ ስፍራ የተሰጣቸው ለእነርሱ ብቻ የተወሰነ መብት በመሆኑ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ወሳኝነት የተነሳ ነው እንላለን፡፡ ለእኛ ብቻ የተገባ ነው የሚሉበትን ምክንያት ካነሱ ምክንያታቸው የግድ ለዐረቦችም የተገባ ምክንያት ነው፡፡ ስለዚህም አይሁድ ዐረቦችንም እንደ እግዚአብሔር ሕዝብ ሊያውቋቸው ይገባል፤ ይህንንም ደግሞ ይጠሉታል፡፡ ከእግዚአብሔር ወሳኝነት በሆነ ምክንያት ነው ይህንን መብት ያገኘነው ብለው ካመኑ ደግሞ ታዲያ እግዚአብሔር በጌትነቱ ለእነርሱ የፈቀደውን መብት ለሌላው ሊፈቅድ አይችልም ወይ ተብለው ሊጠየቁ ይችላሉ፡፡ እንግዲህ ይህ ምን ያሳየናል? ይህ ለዘላለማዊ ደኅንነት ወይም መጠራት ስለሚወሰንበት ዕድል የሚያሳይ ሳይሆን እዚህ ምድር ላይ የተሻለ መብት ስለሚሰጥበት ጉዳይ ነው፡፡

ያዕቆብን ወደድኩ ኤሳውን ግን ጠላሁ፡፡

ይህን በሮሜ መልዕክት ዘጠነኛው ምዕራፍ በ13ኛ ቊጥር የምናገኘውን ጥቅስ የሚጠፉት እንዲጠፉ የተወሰነላቸው ዕጣ ፈንታቸው ስለሆነ ነው ለሚለው ትምህርት ድጋፍ ሰጪ ነጥብ አድርገው ሰዎች ሲጠቀሙበት እናያለን፡፡ ይህን የሚሉትም በቁ.12 ላይ ‹‹ታላቁ ለታናሹ ይገዛል ተባለ›› የሚለውን በቁ.13 ‹‹ያዕቆብን ወደድሁ ዔሳውን ግን ጠላሁ›› ተብሎ እንደተጻፈ ነው ከሚለው ጋር የሚያደባልቁ ሰዎች ናቸው፡፡ በእርግጥ ልክ ነው በቁ.12 ላይ የምናነበውን ልጆቹ ገና ሳይወለዱ እግዚአብሔር ተናግሯል፡፡ ነገር ግን በኤፌ.1፡4 ስለራሳችን ስለክርስቲያኖች እንደምናነበው ዓለም ሳይፈጠር ይህን ወደድሁ ያንን ጠላሁ የሚል አልተነገረም፡፡ ነገር ግን ልጆቹ ገና ሳይወለዱ በእግዚአብሔር ቃል የተነገረው የምርጫ ሐሳብ የሚያመለክተን ልጆቹ ከተወለዱ በኋላ በምድር ላይ ስለሚኖራቸው የኑሮ ደረጃ ነው፡፡ ቁ.13 ደግሞ ከሚልክያስ ምዕ. ቊ. 2 የተወሰደ ነው፡፡

ስለዚህ ‹‹ታላቁ ለታናሹ ይገዛል›› የተባለው ሳይወለድ ሲሆን ያዕቆብን ወደድሁ ኤሳውን ጠላሁ የተባለው ግን ከተወለዱ ከ1400 ዓመታት በኋላ ነው፡፡ የያዕቆብና የኤሳው ዘሮች ምን ዓይነት ኑሮ እንደ ኖሩ ለእግዚአብሔርም ለሰውም ግልፅ ነበር፡፡ የኤሳው ጠባይ ለእግዚአብሔር የማይመች ከመሆኑም ባሻገር እንዲያውም ከሴሰኞች ጋር የተቆጠረበት ጽሑፍም እናገኛለን፡፡ በረከቱን ለማስመለስ የንስሐ እድል እንዳጣም ተገልጾአል (ዕብ.12፡16-17) እንደዚህ ዓይነቱን ሰው እግዚአብሔር እጠላዋለሁ ቢል ምን የሚያስደንቅ ነገር አለው? መዝሙረኛውም ክፉ አድራጊዎችን ሁሉ ጠላህ በማለት ይናገራል (መዝ.5፡5)

በሮሜ መልእክት ምዕራፍ 9 ቊጥር 15 ያለውን እንመልከት፤ ‹‹የምምረውን ሁሉ እምረዋለሁ እምራራለትም ሁሉ እራራለታለሁ›› ይላል፡፡ የእስራኤል ሕዝብ ያህዌህን ትተው የወርቅ ጥጃ ባቆሙ ጊዜ የእግዚአብሔር ቁጣ በላያቸው ነበር፡፡ ሙሴ ግን ስለ እነርሱ ማለደ፡፡ እግዚአብሔርም ጸጋውን አሳየና ሕዝቡን ማረ፡፡ ስለዚህ ይህን በሮሜ መልዕክት የምናገኘውን ጥቅስ በዘጸ.33፡19 እግዚአብሔር ተናገረው፡፡ ይህም ፍርድ ለተገባው ሕዝብ ምሕረት ማድረጉ የእግዚአብሔር ብቸኛ መብት መሆኑን ያሳየናል፡፡ ስለዚህ እስራኤላውያን የእግዚአብሔር ሕዝብ ሆነው የቆዩት በጸጋው መሆኑንም እንረዳለን፡፡ ታዲያ በሮሜ9፡15 ያለው ሐሳብ ይህ ሆኖ ሳለ ‹‹ለዘላለማዊ ቅጣት የተመደቡ አሉ›› የሚለውን ትምህርት ወይም ዶክትሪን እንዴት ከዚህ ንባብ ማውጣት እንችላለን?

ይህ ንባብ ይልቁንስ ስለ እግዚአብሔር ጸጋ ይጠቁምልናል፡፡ ሰዎች ሁሉ ከፍርድ በታች ነበሩ፤ ስለሆነም ነፃ ሊያወጣቸው የሚችለው የእግዚአብሔር ምሕረት ብቻ ነበር፡፡ ከዛሬ ጀምሮ ኃጢአት አላደርግም ብሎ ሰው ቢወስን እንኳን እስከ አሁን ስለሠራው ኃጢአት ፍርድን ይቀበል ዘንድ የግድ ነው፡፡ እግዚአብሔር የአንዳንዶችን ልብ ያደነድናል

የሮሜ ምዕራፍ 9፡17ኛው ቊጥር ከዘጸ.9፡16 የተወሰደ ነው፡፡ አስቀድሞ እግዚአብሔር ለፈርዖን ‹‹ኃይሌን እገልጥብህ ዘንድ ስሜም በምድር ሁሉ ላይ ይነገር ዘንድ ስለዚህ አስነስቼሃለሁ›› በማለት ተናግሮት ነበር፡፡ ነገር ግን ከዚህ ንባብ ቀድሞ የሚገኘውን ሐሳብ ማንበብ ይኖርብናል፡፡ እግዚአብሔር የፈርዖንን ልብ በሚገባ ያውቅ ነበር (ዘጸ.3፡19) ስለሆነም ፈርዖን ሕዝቡን አልለቅም ብሎ ቢገኝ እግዚአብሔር የሚያደርግበትን ነገር አስቀድሞ ተናግሯል፡፡ ይኸውም ‹‹ወደ ግብፅ ስትመለስ በእጅህ ያደረግሁትን ተአምራት ሁሉ በፈርዖን ፊት ታደርገው ዘንድ ተመልከት እኔ ግን ልቡን አጸናዋለሁ ሕዝቡንም አይለቅም››(ዘጸ.4፡21) በማለት ለሙሴ አስገንዝቦት ነበር፡፡ እንደተባለውም ፈርዖን አለመታዘዙን ሲገልጥ በዘጸ.5፡2 ‹‹ቃሉን እሰማ ዘንድ እስራኤልንስ እለቅቅ ዘንድ እግዚአብሔር ማንው? እግዚአብሔርን አላውቅም እስራኤልንም ደግሞ አልለቅቅም›› በማለት እንደተናገረ እናገኛለን፡፡ በመናገር ብቻም ሳያበቃ እስራኤላውያንንም ከድሮው በከፋ የሥራ ብዛት አስጨነቃቸው (ዘጸ.5፡7) ወደ እርሱ የሚላኩትን ቁጣዎችንና ምልክቶችንም ችላ በማለት ያህዌን ባለመታዘዝ ጸና፡፡ በገዛ ኃጢአቱም የገዛ ልቡን ራሱ አደነደነ፡፡ ይኸውም እግዚአብሔር ልቡን እንዳጸናው ከተነገረበት ከዘጸ.9፡12 በፊት ብቻ ፈርዖን ራሱ የራሱን ልብ እንዳደነደነ አምስት ጊዜ ተጽፎ እናገኛለን (ዘጸ.7፡13፣22፤ 8፡15፣32፤ 9፡7) እግዚአብሔርም ፈርዖን ሕዝቡን እንዲለቅ ተደጋጋሚ ምልክቶችን መላኩን ቀጠለ፡፡

ይሁን እንጂ ፈርዖን በእምቢታው በመጽናቱ እግዚአብሔር አደርግበታለሁ ብሎ አስቀድሞ የተናገረውን ማለትም ልቡን ማጽናቱን ተግባራዊ አደረገበት፡፡ በመሆኑም እግዚአብሔር የፈርዖንን ልቡን ያደነደነው ፈርዖንን በተደጋጋሚ ከተናገረው በኋላ፣ ወደ እርሱም ታላላቅ መቅሠፍቶችንና ምልክቶችን ከላከና ፈርዖንም ብዙ ጊዜ ሕዝቡን እለቃለሁ እያለ ነገር ግን ሐሳቡን በመለወጥ እምቢተኛነቱን ካሳየ በኋላ ነው፡፡ ይህንንም የምናገኘው በዘጸ.9፡12 ሲሆን ከዚያ አስቀድሞ አናገኝም፡፡ ታዲያ እንዲመለስ ብዙ ጥረት ከተደረገ በኋላ ራሱ በእምቢተኝነቱ ያደነደነውን ልቡን እግዚአብሔር ከፊት ይልቅ የደነደነ እንዲሆን በማድረግ ቁጣውን ቢገልጥበት ምን እንግዳ ነገር ነው? ‹‹በክፉ ሥራ ላይ ፈጥኖ ፍርድ አይፈርድምና ስለዚህ በሰው ልጆች ውስጥ ልባቸው ክፉን ለመሥራት ጠነከረ›› (መክ.8፡11) ተብሎ እንደተነገረ የሚገርመው ደግሞ እግዚአብሔር ይህን ካደረገበት በኋላም እንኳን ፈርዖን የራሱን ልብ ራሱ እልከኛ እንዳደረገ እናነባለን (ዘጸ.9፡12) ፈርዖን አስቀድሞ ልቡን ዘጋ፤ ይመለስ ዘንድ ወደ እርሱ የተላኩትን ምልክቶችንም ችላ በማለት ልቡን አጠነከረ፡፡ እግዚአብሔርም ስለ ክፋቱ ፍርድን ይቀበል ዘንድ በዚያው እንዲጸና አደረገው፡፡ ይሁን እንጂ ቢመለስ ኖሮ ነገሮች ሌላ መልክ መያዝ በቻሉ ነበር፡፡ እግዚአብሔር የአንዳንዶችን ልብ የሚያጸናው ደጋግሞ እንዲመለሱ ከነገረ በኋላ ነው፡፡ ይህንንም የሚያደርገው ሊመለሱ የሚችሉበትንና ልባቸው ለንስሐ የሚለሰልስበትን ጸጋውን በመንጠቅ ነው፡፡ ይህም ማለት ክፉውን ሰው በክፋቱ ውስጥ ይተወዋል ወይም ለከንቱ ሐሳቡ አሳልፎ ይሰጠዋል ማለት ነው (ሮሜ.1፡24-26-28)፡፡፤ ያም ሰው መድረሻ በፍርድ እስኪወገድ ድረስ ከፊተኛው ይልቅ በክፋቱ ይጠነክራል፡፡ እግዚአብሔርም በፍርድ እስኪያስወግደው ለእርሱ ያለውን በጎነት ከእርሱ በመውሰድ ለበረታበት ክፉው ምኞቱና ለሰይጣን አሳልፎ ይሰጠዋል፡፡ ያስተውልበት ዘንድ የተሰጠውን ማስተዋል ይነጥቀዋል፤ ሰምቶና አይቶ የሚገነዘብበትን ጸጋውን ከላዩ በመግፈፍ ለክፉ ኅሊናው ይተወዋል (ኢሳ.6፡10፣ ሮሜ11፡8-10)

በዚህ ዓይነት እግዚአብሔር አንዳንድ ጊዜ የሰዎችን ልብ እንደሚያፀና እንመለከታለን፡፡ ይህንንም በፈርዖን ላይ አድርጓል፡፡ ዛሬም በእምቢተኝነት በጸኑት ላይ ያደርገዋል፡፡ ቤተክርስቲያን ክርስቶስን ለመቀበል ከምድር ስትነሳም (ስትነጠቅ) ወንጌልን ሰምተው ግን ያልተቀበሉ ‹‹ስለዚህም ምክንያት በእውነት ያላመኑ ነገር ግን በዓመፅ ደስ ይላቸው የነበሩ ሁሉ ፍርድን እንዲቀበሉ ሐሰትን ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር የስሕተትን አሠራር ይልክባቸዋል፡፡›› (2ተሰ2፡11) ነገር ግን እግዚአብሔር ሰዎች የሚለወጡበትን እድልና አጋጣሚ ሳይሰጥ አስቀድሞ ይህንን አድርጎ አያውቅም (ኢዮ.33፡14-30)፤ ስለዚህ ይህ ‹‹ሰዎች አስቀድመው ለጥፋት ተመድበዋል›› በማለት የሚናገረው ዶክትሪን ወይም ትምህርት ከሚያስተምረው አስተምህሮ በብዙ የራቀ ነው፡፡

እግዚአብሔር በሥራው ሁሉ ወሳኝ ባለሥልጣን ነው

በሮሜ.9፡19-21 ያለውን ስንመለከት ዋናው ሐሳብ በፈጠረው ፍጡር ላይ እግዚአብሔር የፈለገውን ሥራ የመሥራት መብት እንዳለው የሚያሳይ ነው፡፡ አንዱን የክብር ሌላውን የውርደት ዕቃ አድርጎ የማዘጋጀት መብት የለውምን? ፍጡር ፈጣሪውን ለምን እንደዚህ ሠራህ ሊለው ይገባልን? እግዚአብሔር ፈጣሪ እንደ መሆኑ በፈጠረው ነገር ሁሉ የፈለገውን ለመሥራት ባለሙሉ መብት ነው፡፡ አንዱን ይቅር ለማለት ሌላውን ለዘላለማዊ ጥፋት መመደብ መብቱ ነው፡፡ ነገር ግን እስከ አሁን እግዚአብሔር ሰውን ለዘላለም ለማጥፋት ያለውን ይህንን መብቱን አልተጠቀመም፡፡ እግዚአብሔር ብርሃን ነው፤ ፍቅርም ነው፡፡ ባህርዩን መቃወም አይቻለውም፡፡

ይህንንም ሐሳብ በቁ.21 ላይ እናገኛለን፡፡ ይኸውም በኤር.18 ላይ ከምናገኘው ሐሳብ ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ የፈለገውን ማድረግ እንደሚችል ስላለው መብቱ በዚሁ ምዕራፍ ተጠቅሶአል፡፡ ሸክላ ሠሪው የሸክላ ዕቃ እየሠራ ሲበላሽበት ሌላ አድርጎ እንደገና እንደሠራው እናያለን፡፡ ‹‹የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፡፡ የእስራኤል ቤት ሆይ ይህ ሸክላ ሠሪ እንደሚሠራ በውኑ እኔ በእናንተ ዘንድ መሥራት አይቻለኝምን? እነሆ ጭቃው በሸክላ ሠሪ እጅ እንዳለ እንዲሁ እናንተ በእኔ እጅ አላችሁ (ኤር18፡5-6)፡፡

ታዲያ እግዚአብሔር ይህንን መብቱን ተግባር ላይ የሚያውለው እንዴት ነው? ‹‹ስለ ሕዝብ፣ ስለ መንግሥትም እነቅል አፈርስም አጠፋም ዘንድ በተናገርሁ ጊዜ ይህ ስለ እርሱ የተናገረሁበት ሕዝብ ከክፋቱ ቢመለስ እኔ አደርግበት ዘንድ ካሰብሁት ክፉ ነገር እጸጸታለሁ፡፡ ስለ ሕዝቡም ስለ መንግሥትም እሠራውና እተክለው ዘንድ በተናገርሁ ጊዜ በፊቴ ክፉን ነገር ቢያደርግ ቃሌንም ባይሰማ እኔ አድርግለት ዘንድ ስለ ተናገርሁት መልካም ነገር እጸጸታለሁ፡፡›› (ኤር18፡7-10) ይህም ሰው ከክፋቱ ቢመለስና ቢለወጥ እግዚአብሔር ሊያመጣበት ካሰበው ፍርድ ተጸጽቶ በምሕረቱ ጸጋውን እንደሚገልጥለት ያሳያል፡፡ እግዚአብሔርም ባለ ሙሉ ሥልጣን እንደ መሆኑ መጠን ይህን መብቱን ለዚህ ዓላማ ይጠቀምበታል፡፡

ለጥፋት የተዘጋጁ የቁጣ ዕቃዎች

ምንም እንኳን ብዙውን ጊዜ ‹‹ለጥፋት እግዚአብሔር የመደባቸው አሉ›› ለሚለው ትምህርት እንደ ማስረጃ የሚጠቀስ ቢሆንም በትክክል ከተገነዘብነው ግን ይህ ጥቅስ ለጥፋት በእግዚአብሔር አስቀድሞ የተመደቡ አሉ የሚለውን ትምህርት አበክሮ የሚቃወም ማስረጃ ነው፡፡ የሮሜ መልእክት ምዕ.9 ቁ.22 እና 23 ሐሳብም ከላይ የደረስንበትን ሁኔታ የሚያረጋግጥ ነው፡፡

ቁ. 22 ለቁጣ ስለተዘጋጁ ዕቃዎች ይናገራል፡፡ ነገር ግን እነዚህን ዕቃዎች ለጥፋት ያዘጋጃቸው ማን ነው? እዚህ ላይ የተገለፀልን ሐሳብ የለም፡፡ ከይዘቱ እንደሚታየው እግዚአብሔር እንዳላዘጋጃቸው መረዳት እንችላለን፡፡ እርሱ ለጥፋት አዘጋጃቸው ካልን ደግሞ በቁ.23 መሠረት እግዚአብሔር ለረጅም ጊዜ በታላቅ ትዕግሥት ጠብቆአቸዋል ለማለት እንዴት ይቻለናል? የምሕረት ዕቃ የተባሉትን ግን እርሱ ራሱ አስቀድሞ እንዳዘጋጃቸው የሚናገረው ቁ.23ን ከቁ.22 ጋር ስናነፃፅረው ያለውን ልዩነት ልብ ልንለው ይገባል፡፡ በመሆኑም ለጥፋት የተዘጋጁት ዕቃዎች ለጥፋት የተዘጋጁት በራሳቸው እንደሆነ ግልጥ ነው፡፡ ይህ ማለት ራሳቸውን ለቁጣ ያመቻቹ ናቸው ማለት ነው፡፡ ‹‹ነገር ግን እንደ ጥንካሬህ እና ንስሐ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቁጣ ቀን ቁጣን በራስህ ላይ ታከማቻለህ›› (ሮሜ2፡5) እንደተባለው ሰው ራሱን ለዘላለማዊ ጥፋት በመዳረግ ድርሻ እንዳለው እንረዳለን፡፡

አስቀድሞ ለጥፋት ስለመመደብ የሚናገር የእግዚአብሔር ቃል አናገኝም

የተወሰኑ ሰዎች ለዘላለም እንዲጠፉ እግዚአብሔር አስቀድሞ እድል ፋንታቸውን ለዘላለም ጥፋት መመደቡን የሚገልፅ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አንዳች አናገኝም፡፡ በአንጻሩ ይህ አባባል እግዚአብሔር በቃሉ ስለራሱ ከሚገልፅልን ሐሳብ ጋር የሚቃረን ነው፡፡

ሰዎች ሁሉ እንዲድኑ የወደደ መድኃኒታችን እግዚአብሔር ራሱን ለሁሉ ቤዛ የሰጠውን(1ጢሞ2፡6) ኢየሱስ ክርስቶስን ሰጠን፡፡ ባዘጋጀልን የመዳን መንገድ ተጠቃሚዎች እንድንሆን ይህንን አደረገ፡፡ ለሁሉ ቤዛ የሚሆነውን ከሰጠ በኋላ ታዲያ የዚህ በረከት ተካፋይ ሳይሆኑ በመከልከል ለዘላለም የሚጠፉትን ወስኖአቸዋል ማለት እንዴት ይቻላል? እስቲ ሌሎች ምንባቦች እንደ ዮሐ.3፡16፤ ሮሜ.3፡22፤ 1ዮሐ.2፡2 ወዘተ የመሳሰሉትን አንብብና አገናዝብ፡፡

እግዚአብሔር ይመስገን! ንስሐ ቢገቡ ምስኪን ኃጢአተኞችን ሁሉ ወደ ዘላለማዊ ክብር እንዲገቡ የሚያደርግ የተወሰነ ምርጫ ግን አለ፡፡ ነገር ግን በቅዱሳት መጻሕፍት በየትኛውም ቦታ ‹‹ለኩነኔ የተመረጡ አሉ›› የሚል አናገኝም፡፡ በአንፃሩ ግን ‹‹ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ የሚወድ›› (1ጢሞ2፡3-4) መድኃኒታችን እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‹‹የተጠማም ይምጣ የወደደም የሕይወትን ውሃ ይውሰድ፡፡›› (ራእ.22፡17) እነዚህን ሁለት ሐሳቦች ማለት አንዳንዶቹን ለዘላለም ሕይወት መምረጥ እና ለሁሉም ጥሪ ማድረግ ማስማማት ካልቻልን ኢሳ.55፡9 ላይ ‹‹ሐሳቤ ከሐሳባችሁ ከፍ ይላል›› የሚለው መልስ ይሆነናል፡፡ የእግዚአብሔርን መንገድና ማስተዋል ተረድቶ መገምገም የሚችል ሰው ይኖር ይሆንን? የእምነት ሰው ግን እግዚአብሔር በግፍ እንደማይፈርድ በማመን ከአብርሃም ጋር ‹‹የምድር ሁሉ ፈራጅ በቅን ፍርድ አይፈርድምን?›› (ዘፍ.18፡25) ይላል፡፡

ከሰላምታ ጋር
በክርስቶስ የናንተው ወንድም

ምዕራፍ 6 ምርጫ

(ካለፈው ደብዳቤ የቀጠለ)፡፡

ውድ ወገኖቼ

መመረጤን በምን አውቃለሁ የሚል ጥያቄ ልታነሱ ትችላላችሁ፡፡ በመጀመሪያ የእግዚአብሔር ቃል የማያምኑ ሰዎችን በተመለከተ ስለ መመረጥ የሚናገርላቸው ነገር እንደሌለ በጥንቃቄ መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት ያልተለወጡና ያላመኑ ሰዎችን የሚያቀርቧቸው የጠፉ እንደሆኑና የእግዚአብሔር ፍርድም በላያቸው እንደሆነ በመግለጥ እንደዚሁም ይለወጡ ዘንድ በእግዚአብሔር የተጠሩ መሆናቸውን በማሳሰብ ነው፡፡ አምነው ከጥፋት እንዲያመልጡም የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝነት ይገልጡላቸዋል፡፡

በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው ሲለወጡም ምርጦች ተብለው ይጠራሉ፡፡ ይህን አሁን እንዴት ሊያውቁት ይችላሉ? መልሱን ሐዋርያው ከጻፈው መልስ እናገኛለን፡፡ ‹‹እንደ ተመረጣችሁ አውቀናል›› ይልና እንዴት እንዳወቀም ምክንያቱን ይገልጻል፡፡ ‹‹ወንጌላችን በኃይልና በመንፈስ ቅዱስ በብዙ መረዳትም እንጂ በቃል ብቻ ወደ እናንተ አልመጣምና በእናንተ ዘንድ ስለ እናንተ እንዴት እንደ ነበርን ታውቃላችሁ፡፡ ደግሞ እናንተ ቃሉን በብዙ መከራ ከመንፈስ ቅዱስ ደስታ ጋር ተቀበላችሁ፤ እኛንና ጌታን የምትመስሉ ሆናችሁ›› (1ተሰ.1፡4-6) በማለት ይናገራል፡፡

ስለዚህ ከዚህ የምንረዳው ቃሉን መቀበላቸው የመመረጣቸው ማስረጃ ሆነ፡፡ ሰው ተመረጠ የምንለው ወንጌል አምኖ ከእግዚአብሔር ጋር በመታረቁ በሚታየው ማስረጃ ነው፡፡

ቅዱሳት መጻሕፍት ስለ መመረጥ ምን ይላሉ?

መመረጥን በተመለከተ በብዙ ቦታዎች ተጠቅሶ እናገኛለን፡፡ ለምሳሌ በ1ጴጥ.1፡2፤ 2ጢሞ.1፡9፤ ቲቶ.1፡2 መመልከት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ይህ ሐሳብ በዋነኝነት ተጽፎ የሚገኘው በሮሜ.8፡28-30 እና ኤፌ.1፡3-14 ነው፡፡

በሮሜ.8፡29-30 ‹‹ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኩር ይሆን ዘንድ አስቀድሞ ያወቃቸውን የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤ አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚያን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው ይላል፡፡

ከሁሉም በፊት እግዚአብሔር አስቀድሞ ያወቃቸው ሰዎች መኖራቸውን ልብ እንበል፡፡ ስለ ሁኔታቸው፣ እንዴት እንደሚኖሩና፣ ያምኑ ወይም አያምኑ እንደሆን በተመለከተ ያውቃቸው ነበረ አይልም፡፡ ሰዎቹን እንዳወቃቸው ግን ይናገራል፡፡ በኤፌ.1፡14 እንዲሁ አስቀድሞ ያወቃቸውን ዓለም ሳይፈጠር ከዘላለም እንዳወቃቸው ይገልጻል፡፡ Slz!H እነዚያን ያወቃቸውን ሰዎች አንድ እንኳን ሳይጎድል የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ የወሰነው ጉዳይ ነው፡፡

መመረጥ ይሏችኋል እንደዚህ ነው ሳንወለድ አዳም ሳይፈጠር ሰማይና ምድርም ሳይፈጠሩ ማለትም ዘፍ.1፡1 የሚናገርለት ሳይከናወን እግዚአብሔር በዘላለም ምክሩ አስቦ የልጁን መልክ እንድንመስል ወሰነልን፡፡ የእግዚአብሔር ቃል በሌላ ቦታ ላይ ስለልጁ ‹‹እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው›› (ቆላ1፡15) ይለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የእርሱን መልክ እንድንመስል መወሰኑን ይነግረናል፡፡ በወንድሞች መካከልም በኩር ሊሆን ተገብቶታል፡፡ እርሱም ቀዳሚውን ስፍራ ይዞ እኛም እርሱን እንድንመስል ሆኖልናል፡፡

በወንድሞች መካከል በኩር የሆነውን መልክ እንድንመስል ተወሰነ ማለት ግን ይህ የምንመስለው የነበረ ያለና የሚኖር ሆኖ በሰማያት የነበረውን እግዚአብሔር ወልድን አይደለም፡፡ እርሱ ዘላለማዊ አምላክ ነው፡፡ ይህም ባሕርይ ደግሞ የእርሱ ብቻ ነው፡፡ አምላክነቱን አንመስለውም፡፡ የምናጠናው ምንባብ የሚናገረው ግን ይህ የዘላለም አምላክ ወደ ምድር መጥቶ ሥጋን በመልበስ ታዛዥና ትሑት ሆኖ በመስቀል ላይ የማዳን ሥራ በመሥራት መላው የእግዚአብሔር ምክር የተፈፀመበትን ማንነቱን ስለመምሰል ነው፡፡ ቆላ.1፡19-21፤ ኤፌ.1፡10፤ 20-23 አገናዝብ፡፡

የበረከታችን መሠረትም ከእርሱ ዘላለማዊነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በረከታችን ሰማይና ምድር ሳይፈጠሩ ከነበረው ዘላለማዊነቱና ሰማይና ምድር ካለፉ በኋላም ካለው ዘላለማዊነቱ ጋር ተያይዞ ይገኛል፡፡ በቃሉ እንደቀረበልንም ከእግዚአብሔር የተወሰነችልን ምክር ተፈፃሚነት እስከምታገኝ ድረስ አትቋረጥም፡፡ ‹‹ቢገለጥ እርሱ እንዳለ እናየዋለንና እርሱን እንድንመስል እናውቃለን፡፡›› (1ዮሐ.3፡2) ‹‹የትንሳኤ ልጆች›› (ሉቃ.20፡36) እንደመሆናችን ‹‹ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል፡፡››(ፊልጵ.3፡21) በዚያን ጊዜም የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን እንገለጣለን፡፡

የተጠሩ፣ የጸደቁና የከበሩ

በሮሜ 8 ቁ.30 ላይ እንደምናነበው በእግዚአብሔር ምክርና በመዋዕለ ዘመን መካከል ግንኙነት እንዳለ እናያለን፡፡ ከልጅነታችን ጀምሮ ጀርባችንን ለእግዚአብሔር የሰጠን ኃጢአተኞች ነበርን፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ጠራን፡፡ በዚህ ቊጥር ላይ የምናየው ሰው ሁሉ ይለወጥ ወይንም ንስሐ ይገባ ዘንድ ለሰዎች ሁሉ ስለቀረበ አጠቃላይ የእግዚአብሔር ጥሪ አይደለም፡፡ ነገር ግን ‹‹የሌለውን እንዳለ አድርጎ ስለሚጠራው›› (ሮሜ.4፡17) የእግዚአብሔር የመፍጠር ተግባር ነው፡፡ ሰው ሳይፈጠር የሌለውን እንዳለ ሊጠራ ለእግዚአብሔር ይቻለዋል፡፡ ስለሆነም የጠራቸውን እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፡፡

እዚህ ላይ ሁሉም ነገር የሚታየው ከእግዚአብሔር እይታና ከእግዚአብሔር ሐሳብ አንፃር ነው፡፡ መልእክቱ ወደ ሮሜ ሰዎች ሲጻፍ የተመረጡት ሁሉም አልተጠሩም ነበር፡፡ የተመረጡት ዓለም ሳይፈጠር እንደመሆኑ በዚህ ወቅት የተጠሩት በጣም ጥቂቶች ነበሩ፡፡ ይህም ደግሞ ማኅበረ ምዕመናኑን ብቻ ነበር፡፡ ቤተክርስቲያን ከምድር ከተነሳች (ከተነጠቀች) በኋላ የሚቀሩት አማኞችና እስራኤልም የተመረጡት ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ እንደሆነ ይታወቃል (ራእ.13፡8)

አሁንም ቢሆን ሁሉም አልተጠሩም፡፡ ይህ የሚሆነው ቤተክርስቲያን ከምድር ከተነጠቀች በኋላ ነው፡፡ ቁጥሩም ያኔ ይሞላል፡፡ ይህ ደግሞ የእግዚአብሔር ሐሳብ ነውና በእርግጥም ይፈፀማል፡፡ ከእግዚአብሔር ጸጋ የተነሳ ወደተጠራንበት ስፍራ በእርግጥ እንደርሳለን፡፡ ከጥረታችን ሳይሆን ሁሉም ነገር በእግዚአብሔር እጅ ይከናወናል፡፡ በዚህም እርግጠኞች ነን፡፡

አምላካችንና አባታችን

በኤፌ.1፡4-5 እግዚአብሔር የክርስቶስ ኢየሱስ አባት እና አምላክ ተብሎ ሲጠራ እናያለን፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሰው እንደመሆኑ አምላኬ ሲለው ተሰምቷል (ማቴ.27፡46) እንደዚሁም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ መሆኑ ጌታችን እግዚአብሔርን አባቴ ብሎ ጠርቶታል (ዮሐ.17፡1) ከትንሣኤው በኋላ ደግሞ የራሱ የሆኑትን ከእግዚአብሔር ጋር እርሱ እራሱ ወዳለው ዝምድና አደረሳቸው፡፡ ስለሆነም ‹‹ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዐርጋለሁ›› ሲል በዮሐ.20፡17 ተሰምቷል፡፡ ልዩነት መኖሩን ግን ልብ እንበል፡፡ ወደ አባታችንና ወደ አምላካችን አላለም፡፡ ዋናው ነገር በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እግዚአብሔር አባታችን መሆኑ ነው፡፡

በኤፌ.1፡4-5 በመመረጥ የተቀበልነውን ስፍራ እንመልከት፡፡ በቁ.4 እግዚአብሔርን አምላካችን ብለን ልንጠራው ከምንችልበት ሁኔታ ስንገኝ በቁ.5 ደግሞ እግዚአብሔርን አባታችን በምንልበት ሁኔታ እንደምንገኝ እናያለን፡፡ ለዚህ አጠራር የበቃን እንሆን ዘንድ ደግሞ በክርስቶስ ተመረጥን፡፡ ለዚህ እንድንመረጥ የሆነውም ከታላቅ ክብሩና በወልድነቱ ካለው ሥልጣን መለኮት የተነሳ ነው፡፡ እግዚአብሔርን አምላካችንና አባታችን ብለን ለመጥራት የምንችለውም በራሱ በክርስቶስ ነው፡፡

በፊቱ ቅዱሳን፣ ያለ ነውርና በፍቅር መሆን

ኤፌ.1፡4 ያለውን መልሰን እንመልከተው፤ ‹‹ዓለም ሳይፈጠር በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን›› ይላል፡፡

የእግዚአብሔርን መለኮታዊ ባሕርይ ስናይ እርሱ ቅዱስ በሥራው ነቀፋ የሌለው በባህርዩም ፍቅር መሆኑን እናስተውላለን፡፡ እርሱ እንደሚፈልገው ወደ እርሱ ለመቅረብም ለባሕርዩ በሚመች ባሕርይ ይዘን መገኘት አለብን፡፡ በኃጢአት የተበላሹ ሰዎች ቅዱስ ወደሆነው እግዚአብሔር እንዴት መጠጋት ይችላሉ? እርሱ ኃጢአትን አይቶ ማለፍ የማይችል እንደመሆኑ ከኃጢአት ጋር የተያያዘውን ነገር ሁሉ ወደ እሳት ባሕር ሊጥለው ቀን ቆርጦለታል፡፡ እኛን ግን ለባሕርዩ እንድንመች መርጦናል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፤ ፍቅር ወደሆነው ወደ እግዚአብሔር ሐሳብ መግባት ይኖርብናል፡፡ በመሆኑም ቁ.4 በፊቱ በፍቅር እንሁን ይለናል፡፡

በመጨረሻም ከእርሱ ጋር ስንሆን በፊቱ ቅዱሳንና ያለነውር ሆነን በፍቅር እንቆማለን፡፡ ከኃጢአት የተራረፈው ድክመታችንና እንከናችን ከእኛ ለዘላለም ይወገዳል፡፡ ያን ጊዜም ይህ ሥጋችንም ይለወጣል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር አሁንም ቢሆን ያለ ነቀፋና ያለ ነውር እንደሆንን አድርጎ ይመለከተናል፡፡ እኛ ፍጥረቱ ነንና እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን(ኤፌ.2፡10) እንደተባለው በክርስቶስ ባገኘነው አዲስ ሕይወት ያየናል፡፡ በሌላ ስፍራ እንደምናየው ደግሞ አንድ ጊዜ በማቅረብ የሚቀደሱትን የዘላለም ፍጹማን አድርጎአቸዋልና (ዕብ.10፡14) የሚል ሲሆን በተጨማሪም እርሱ እንዳለ እኛ ደግሞ እንዲሁ በዚህ ዓለም ነንና (1ዮሐ.4፡17) በማለት ይናገራል፡፡ ከክርስቶስ ውጭ ራሳችንን ስንመለከት ምን ያህል ኃጢአተኞች እንደሆን እናውቃለን፡፡

የልጅነት መብት

‹‹በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን፡፡›› (ኤፌ.1፡3) ልጅ ለመባል ቀርቶ አገልጋይ ለመሆን እንኳ ሁሉም የሚሆነው በክርስቶስ ከሚገኘው ጸጋ ብቻ ነው፡፡ ማንም መልካም ቢሆን ለእግዚአብሔር ክብርና ቅድስና ተመችቶ መቆም ይኖርብታል፡፡ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ተወሰነልን ሲባል እንግዲህ ግልፅ የሆነ ግንኙነት በእኛና በእግዚአብሔር መካከል እንዳለ እንረዳለን፡፡ አባት ወደ ልጆቹ፣ ልጆች ወደ አባታቸው ያላቸውን ግንኙነት መገመት ይቻላል፡፡ እግዚአብሔር ወልድ በመስቀል ላይ በፈፀመው ሥራ ምክንያት ከሞት ከተነሳ በኋላ ከራሱ ጋር አስቀምጦናል፡፡ ይህም ያገኘነው ስፍራ የልጅነት መብት ነው፡፡ በኤፌሶን መልእክት እንደምናነበው ደግሞ እግዚአብሔር ዓለም ሳይፈጠር ለዚህ ስፍራ እንደመረጠን እንረዳለን፡፡

ይህም ማለት ይህንን የልጅነት ስፍራ እንድንይዝ እግዚአብሔር አስቀድሞ ወሰነ ማለት ነው፡፡ ለዚህ ውሳኔ የተሰጠው ምክንያትም በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ ተብሎ መነገሩ የዚህ በረከት ምንጭ ፍቅሩ ብቻ መሆኑን ያሳየናል፡፡
ክርስትና
ከቅድመ-ዓለም እስከ ዘለዓለም

ዓለም ሳይፈጠር በክርስቶስ እንደመረጠን ከቃሉ ተረድተናል፡፡ ይህም ምርጫ ወቅቶችና ጊዜያት ከመፈጠራቸውና ከመደንገጋቸው በፊት ጀምሮ የነበረና እስከ ዘለዓለምም የሚቀጥል መሆኑን ያሳያል፡፡ ‹‹በክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን...›› (ኤፌ1፡3) ሲል መመረጡ ለምድር የተወሰነ እንዳልሆነ ያሳያል፡፡ ለዚህ ምድር የተመረጡት ሕዝቦች ግን እሥራኤል መሆናቸውን ቃሉ ይነግረናል (ዘጸ19፡5፣ ዘሌ25፡2-3፣ ዘዳ7፡6)፡፡ ‹‹የአባቴ ቡሩካን ኑ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ›› (ማቴ.25፡34) የሚለውን ስናይ ‹‹ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ›› የሚለው አባባል በረከቱ በጊዜ የተወሰነ በረከት መሆኑን ያሳያል፡፡

ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ግን የአንድ የተወሰነ ሥርዓት (የክርስትና) እና የአንድ የተወሰነ አካል (የቤተክርስቲያን) አባል ነው፡፡ ይህ ሥርዓትና አካል ደግሞ ከዘመን አቆጣጠር ውጭ ያለና ዓለም ሳይፈጠር እግዚአብሔር በክርስቶስ የወሰነው ነገር ነው፡፡ ከዚህ ዓለምም አይደለም (ዮሐ17፡14) ይህ ዓለም ካለፈ በኋላም መኖሩን ይቀጥላል፡፡ ይህ ሥርዓትና አካል መንፈሳዊነትና ዘላለማዊነትን ይዟል፡፡ ይህም ጥልቅ የሆነውን የክርስትናን ጠባይ እንድንረዳ ያስችለናል፡፡

በኤፌሶን መልእክት ምዕራፍ 1 ከቁ.3-5 የተጻፈውን ስንመለከት ክርስቲያን ስላለበት ኃላፊነት አይናገርም፡፡ የሰው ኃላፊነትና ከእርሱ ጋር የተያያዘው ነገር ሁሉ አዳም ከተፈጠረ በኋላ በኤድን ገነት የተጀመረ ሲሆን ከነጩ ዙፋን ፍርድ (ራእ.20) በኋላም ያቆማል፡፡ በገነት ኤድን ውስጥ ሁለት ዛፎች ነበሩ፡፡ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ የተባለለት መልካምና ክፉ የሚያሳውቅ ለሰው ያለበትን ኃላፊነት የሚያሳስብ ዛፍ እና ለዘለዓለም በሕይወት መኖርን የሚያስችል የሕይወት ዛፍ ነበር፡፡ አዳም የተከለከለውን ዛፍ ፍሬ በመብላቱ የሞት ፍርድ ስለተቀበለ ሕይወት ወደምትሰጠው ዛፍ ሳይደርስ ቀረ፡፡ መስቀል ላይ ሁለቱም የተለያዩ ዛፎች አንድ ላይ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ሰው ኃላፊነቱን በመሳቱ የመጣበትን መዘዝ በተመለከተ ለሚያምኑበት ሰዎች ሁሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኃጢአታቸውን በመስቀል ተሸክሞላቸዋል፡፡ በትንሳኤው ደግሞ በሞት ፈንታ ሕይወት ሰጥቶአቸዋል፡፡ እርሱ ራሱም የሕይወት ዛፍ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ግን ከዓለም መፈጠር በኋላ ቀናትና ወቅቶችን መቁጠር ከተጀመረ በኋላ የሆነ ነገር ስለሆነ በዘላለማዊው እቅድ ውስጥ የተካተተ አይደለም፡፡ ነገር ግን አስፈላጊ እንደመሆኑ ምርጫው በክርስቶስ ውስጥ ሆኖ የእግዚአብሔር እቅድና ምክርም ካለቀለት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ኋለኛው አዳም የአዲስ ፍጥረት (የእግዚአብሔር ቤተሰብ) ራስ ሊሆን ተገለጠ፡፡ ጥልቅ የሆነውን የእግዚአብሔርን ምክርና ድንቅ ጥበቡን ስናይና እኛም የዚህ የጥልቅ ሃሳቡ ማዕከል መሆናችን ስናስብ ምንኛ እንገረማለን!

ከሰላምታ ጋር
በእግዚአብሔር ፍቅር ወንድማችሁ

ምዕራፍ 7 ክርስቶስ ለእኛ ታላቅ ሊቀ ካህናት ነው

ውድ ወገኔ

በአማኝ ያለውን ባለጠግነት የተረዳ ሰው ‹‹ይህን ካገኘሁ ከአሁን ወዲያ ምን ያስፈልገኛል?›› ብሎ ሊያስብ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ኃጢአቱ ይቅር ተብሎለት ከእግዚአብሔር ጋር ታርቋል፤ በአዲስ ልደት አዲስ ሕይወትን፣ አዲስ ተፈጥሮንና ኃጢአት ሊሠራ የማይችል ሰማያዊ ሕይወትን ተቀብሎአል፡፡

እግዚአብሔርም አሮጌውን ፍጥረቱን በመስቀል ላይ ፈርዶበት አስወግዶለታል፡፡ አሁን ደግሞ እግዚአብሔር አማኙን በአዲስ ሕይወት ብቻ ይመለከተዋል፡፡ በክርስቶስ ለሆኑትም ኩነኔ የለባቸውም፡፡ በዚህም ምክንያት መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ውስጥ ይኖራል፤ ከሰይጣን ኃይል፣ ከዓለምና ከኃጢአት ኃይል ነፃ ወጥቶአል፤ ነፃ መውጣቱም እግዚአብሔርን ለማገልገል ነው፡፡

በወልድ በፍቅር ምክንያትም በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት አለው፤ በእግዚአብሔርም የክብር ተስፋ ተካፋይ እንደሚሆን በመተማመን በልበ ሙሉነት ይናገራል፡፡ ይህ ክብር እንደተዘጋጀለትም ያውቃል፡፡

የክርስቲያን ተጋድሎ

ለክርስቲያን የወዲያኛውን ዘላለማዊ ኑሮና መንግሥተ ሰማያትን በተመለከተ በተስፋ ከተቀበለው ወዲያ ሌላ ምንም የሚጠብቀው ነገር የለም፡፡ ነገር ግን እዚህ ምድር ላይም የሚያስፈልገው ነገር አለ፡፡ ሰማያዊ ዜግነት ያለው ስለሆነም(ፊልጵ.3፡20) በዚህ ምድር ላይ ኃላፊ መንገደኛ ነው፡፡ ከሰይጣን ኃይል ነፃ ስለወጣም እግዚአብሔርን ማገልገል ይፈልጋል፤ የልቡ መሻትም ይህ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ከሰይጣንና ካልተለወጡ (ካላመኑ) ሰዎች ጋር ይጋጫል፡፡ የሰይጣን ሥራ ሰዎች እግዚአብሔርን እንዳይታዘዙ ማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ ሙሉ ኃይሉን ተጠቅሞ አማኙን በተንኮሉ እያባበለ በእግዚአብሔር ላይ እንዲያምፅና ኃጢአት እንዲሠራ ያደርገዋል፡፡ የማያምኑትን ኃጢአት ለማሠራት ሰይጣን ብዙም አይቸገርም፤ በተፈጥሮ እግዚአብሔርን መታዘዝ አይፈልጉምና፡፡ ልባቸው ኃጢአት መሥራት ይፈልጋል፤ ኃጢአት ሲሠሩ ደግሞ ልባቸው ደስ ይለዋል (ዘፍ.6፡5፣ ማር.7፡20-23፣ ሮሜ.3፡10-20) ይህ ደግሞ ዓለምና የተሸከመችው ማኅበረሰብ የታነፀበት መሠረት ነው፡፡ ሰዎች በእግዚአብሔር ላይ ላለመደገፍ እና በገዛ ሐሳባቸው ለመመራት እንዲችሉ አንድ ላይ ኅብረት አድርገው የሚኖሩበትን ሁኔታ ለራሳቸው አመቻችተዋል (ዘፍ.9፡1፣ 11፡4-9) ነገር ግን ሰው ብቻውን ነፃ ሆኖ መኖር ስለማይችል በሕይወቱ ሰይጣንን አነገሠ፡፡ የእግዚአብሔርን ልጅ ላለመቀበል ከወሰነ በኋላም በሕይወቱ ሰይጣንን አምላኩ አደረገ (ዮሐ.12፡31፣ 2ቆሮ.4፡4)፡፡

የክርስቲያን ድርጊቶች ዓለም ከምታሳያቸው ድርጊቶች በጣም የተለዩና ተቃራኒ ናቸው፡፡ ዓለማዊም ክርስቲያኑን ከልቡ ይጠላዋል፡፡ እንደ አስቸጋሪ እና የሚያናድድ አድርጎ ይቆጥረዋል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ስለማያምኑት ሲናገር ‹‹ዓለም እናንተን ሊጠላ አይቻለውም፤ እኔ ግን ሥራው ክፉ መሆኑን እመሰክርበታለሁና እኔን ይጠላኛል››(ዮሐ.7፡7) ሲል ስለሚያምኑት ደግሞ ‹‹እኔም ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉምና ዓለም ጠላቸው››(ዮሐ.17፡14) ብሎ ተናግሮአል፡፡ ደቀመዛሙርቱንም ‹‹በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ››(ዮሐ.16፡33) ብሎአቸዋል፡፡

ክርስቲያን በዓለማውያን ተቀባይነት የሚያገኘው ክርስቲያናዊ ባሕርይ ሳያሳይ ሲቀርና የማያምኑ ሰዎች የሚያሳዩትን ፀባይ በማሳየት የሰይጣን ተገዥ ሲሆን ነው፡፡ ይህን የሚያደርግ ክርስቲያን ለእግዚአብሔር ያልታመነና የሰይጣንም ተባባሪ የሆነ ነው፡፡ የክርስቲያን ተጋድሎ እዚህ ላይ ነው፡፡ ሰይጣን መጥቶ ኃጢአት ሊያሠራው ይሞክራል፡፡ ንጹሕ ያልሆኑ ርኩስ ሐሳቦችን ያንሾካሹክበታል፡፡ ኃጢአትን በሚያሳስቡ ነገሮች ላይ እንዲመለከት ያደርገዋል፡፡ ከእግዚአብሔር ቃል ውጭ የሆኑ ንግግሮች እንዲያደምጥና ንጹሕ ወዳልሆኑ ቦታዎች እንዲሄድ ያነሳሳዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ዓለም እንድትጠላው ያነሳሳበታል፡፡ ይህ ሁሉ አዲስን ሰው ያስቸግረዋል፡፡ ምንም እንኳ ክርስቲያን ቢሆንም አሮጌው ሰው ከእርሱ ጋር አለና፡፡ አሮጌው ፍጥረት ደግሞ እግዚአብሔርን ከማስደሰት ይልቅ ኃጢአትን ቢሠራ ይመርጣል፡፡ ሰይጣን አማኙን የሚገናኝበት ቦታ ደግሞ አሮጌው ፍጥረት ላይ ነው፡፡ አሮጌውን ተፈጥሮ በመጠቀምም ሰይጣን ሰውየውን አሳስቶ ኃጢአት በማሠራት ድል የማድረግ አጋጣሚ ሊያገኝ ይችላል፡፡ የእግዚአብሔር ፍቅር ግን ለዚህም መልስ አዘጋጅቶአል፡፡ የእኛ ሊቀ ካህናት ክርስቶስ

በዕብራውያን መልእክት ላይ ክርስቲያን እንደ እንግዳና መጻተኛ ተገልጧል፡፡ ጥሪው ሰማያዊ ነውና (ዕብ.3፡1) የሚጓዘው ወደ ተዘጋጀለት ክብር ነው (ዕብ.11፡40) ይሁን እንጂ ለጊዜው በምድር ላይ ብዙ መከራዎችና ፈተናዎች ያጋጥሙታል፡፡ ለዚህም ካህን አለለት፡፡ በሰማይ ያለው ሊቀ ካህናችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓይኖቹን በከበበን አደጋና ፈተና ላይ በማድረግ ስለ እኛ በእግዚአብሔር ፊት ይማልድልናል፡፡

ብዙውን ጊዜ የጌታችን ኢየሱስን ክህነት ከኃጢአታችን ጋር በተያያዘ መልክ ብቻ ሊያዩት የሚሞክሩ አሉ፡፡ ይህ ግን ሙሉ በሙሉ ትክክል አይደለም፡፡ በእርግጥ በዕብራውያን 2፡17 ‹‹የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀካህናት እንዲሆን...›› ተብሎ እንደተጻፈው መጀመሪያ የተገለጠው ከኃጢአታችን ጋር በተያያዘ መልኩ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በዕብራውያን 10፡12 ደግሞ ‹‹እርሱ ግን ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ›› ይለዋል፡፡ በዚሁ ምዕራፍ በቁ.14 ላይ ደግሞ በመቀጠል ‹‹አንድ ጊዜ በማቅረብ የሚቀደሱትን የዘላለም ፍፁማን አድርጎአቸዋልና›› ይላል፡፡

የዕብራውያን መልእክት በአማኙና በእግዚአብሔር መካከል ያለውን ግንኙነት በፍጡርና በፈጣሪ መካከል ያለ ግንኙነት አድርጎ ይወስደዋል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ እግዚአብሔር የረካበትን ሥራ በመስቀል ላይ ስለፈፀመ ኃጢአትን በተመለከተ የሚነሳ ጥያቄ አይኖርም፡፡ ‹‹ክርስቶስ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር በመገለጡ›› (ዕብ.9፡26) ‹‹ዘላለማዊ ቤዛነትን አግኝቶ››(ዕብ.9፡12) አማኙ ለዘላለም ፍጹምነትን አግኝቷል፡፡ በእግዚአብሔርና በአማኙ መካከልም ኃጢአትን በተመለከተ ምንም ዓይነት ጥያቄ ሊነሳ አይችልም፡፡ በመሆኑም ስለዚህ ነገር በዕብራውያን መልእክት አንዳች አልተባለም፡፡ ሰው ካመነ በኋላ የሚሠራው ኃጢአት በእግዚአብሔር እና በፍጡር መካከል የሚነሳው ጥያቄ ሳይሆን በአባትና በልጅ መካከል የሚነሳ ጉዳይ ነው፡፡ ይህንንም የምናገኘው በመጀመሪያይቱ የዮሐንስ መልእክት ነው፡፡

በሰማይ ያለ ካህን

ምንም እንኳ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያው የክህነት አገልግሎቱ ምድር ላይ ቢፈፀምም በአሁኑ ጊዜ ግን ክህነቱ በምድር እንደተፈፀመው ዓይነት ያለ ባሕርይ የለውም፡፡ ሥራውን አንድ ጊዜ ከፈፀመ በኋላ በአብ ቀኝ ለዘላለም በሰማይ ተቀምጦአል፡፡ ኃጢአት ለሚያስነሳው ማንኛውም ጥያቄ መልስ ያስገኘ፣ ለዘላለም የሚኖር፣ የማይለወጥ ክህነት ያለው፣ ዘወትር ሊያማልድ በሕይወት የሚኖር ሊቀካህናት አለልን(ዕብ.7፡24-27)፡፡

የዚህን ሊቀ ካህናት ማንነት ዕብራውያን ምዕራፍ 1 ይነግረናል፡፡ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ ነው፡፡ ሁል ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ስለእኛ ሊማልድልን መቻሉም ከዚሁ የተነሳ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለአምላክ ካልሆነ በቀር ለማን ይቻላል? ይሁን እንጂ ስለ ሰዎች እንዲያማልድ ደግሞ ሰው መሆን አስፈለገው፡፡ ዕብራውያን ምዕራፍ 2ም ፍጹም ሰው መሆኑን ያሳየናል፡፡ ‹‹እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፡፡ እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ›› (ገላ.4፡4) ሲል ሊቀካህናታችን ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መሆኑን ቃሉ ይነግረናል፡፡ ምንኛ ድንቅ ነው! እግዚአብሔር በሥጋ ተገለጠ፤ ቃል ሥጋ ሆነ፡፡ እርሱ ሰማይንና ምድርን የፈጠረ ሰውንም የፈጠረ ሆኖ ሳለ ራሱ ሰው ሆነ፡፡

የዕብራውያን መልእክት ምዕራፍ 2፡14-17 የእግዚአብሔር ልጅ ለምን ሰው መሆን እንዳስፈለገው ሲገልፅልን ኃጢአታችንን ለማስተስረይ የሚችል የቤዛነትን ሥራ ሊፈጽም፣ ከሞትና ከዲያብሎስ ኃይል ነፃ ሊያወጣን ነው ይለዋል፡፡ ይህን ብቻ ሳይሆን የጥቅሱ ቀሪ ክፍል ደግሞ ሰው የመሆኑን ሌላ ምክንያት የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት ይሆንልን ዘንድ ነው፤ በማለት ያስቀምጠዋል፡፡ ይህ ደግሞ ለልባችን ምንኛ ድንቅ ሐሳብ ነው!

ጌታችን ኢየሱስ የእኛን ፍጥረታችንን ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ በጉዞአችን ላይ አደጋና ችግሮችም እንዳሉ ያውቃል፡፡ ስለዚህም ጌታችን ኢየሱስ ከራሱ ልምምድ በመነሳት እያንዳንዱን የእኛን ችግርና ኀዘን እንደዚሁም እያንዳንዱን ፈተናችንን አውቆ በእነዚህ ሁሉ አሸናፊዎች እንድንሆን በሙሉ መረዳት ከጎናችን መቆም ይችል ዘንድ እንደእኛው ሰው ሆኖ ከኃጢአት በቀር የእኛ በሆነው ሁሉ ሊካፈል ወደ ኑሮአችን ገባ፡፡
መታዘዝን ተማረ

አስቸጋሪና ለእግዚአብሔር ጠላቱ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ለእግዚአብሔር መታዘዝ ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍለን ጌታችን ያውቃል፡፡ ለራሱስ መታዘዝን አልተማረምን? በቃሉ ላይ ‹‹ምንም ልጅ ቢሆን ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ››(ዕብ.5፡8) ይለናል፡፡ ልዑልና ከፍ ያለ ጌታ እንደመሆኑ መጠን ማንንም ታዝዞ አያውቅም፤ ነገር ግን በምድር ላይ ፍጹም ሰው በሆነ ጊዜ መታዘዝን ተማረ፡፡ ስለእርሱም እንደዚህ ተጻፈ፣ ‹‹የደከመውን በቃል እንዴት እንደምደግፍ አውቅ ዘንድ ጌታ እግዚአብሔር የተማሩትን ምላስ ሰጥቶኛል፡፡ ማለዳ ማለዳ ያነቃኛል እንደ ተማሪዎችም ትሰማ ዘንድ ጆሮዬን ያነቃቃል፡፡ ጌታ እግዚአብሔር ጆሮዬን ከፍቶአል፤ እኔም ዓመፀኛ አልነበርሁም ወደ ኋላዬም አልተመለስሁም›› (ኢሳ.50፡4-5) ይልና ይህ ዓለም ከእግዚአብሔር ጋር ካለው ጥላቻ የተነሳና የእርሱ እንዲህ መሆን ያስከተለበትን መዘዝ ሲገልፅ ‹‹ጀርባዬን ለገራፊዎች ጉንጬንም ለጠጉር ነጪዎች ሰጠሁ፡፡ ፊቴንም ከውርደትና ከትፋት አልመለስሁም›› (ኢሳ.50፡6) ይላል፡፡ በዚህ ትንቢት እንደተነገረውም በመናገሩ ‹‹ከሎሌዎቹ አንዱ ... በጥፊ መታው›› (ዮሐ.18፡23) ይህም የሆነው እውነትን ስለተናገረ ብቻ ነበር፡፡ ቅዱሱን የእግዚአብሔርን ልጅ ‹‹ሳምራዊ እንደሆንህ ጋኔንም እንዳለብህ በማለታችን እኛ መልካም እንል የለምን?›› (ዮሐ.8፡48) ሲሉት ምን ተሰምቶት ይሆን? በአንጻሩ ደግሞ የእግዚአብሔር ኃይልና ማጽናናት ግን ከእርሱ አልተለየውም፡፡

በትንቢተ ኢሳይያስ 50፡7-8 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ጌታ እግዚአብሔር ይረዳኛልና ስለዚህም አልታወክሁም፤ ስለዚህም ፊቴን እንደ ባልጩት ድንጋይ አድርጌዋለሁ፤ እንዳላፍርም አውቃለሁ የሚያፀድቀኝ ቅርብ ነው፡፡››

እኛ ግን ኃጢአተኞችና የማንታዘዝ በመሆናችን መታዘዝን መማር አስፈልጎናል፡፡ መታዘዝን ስንማር በሚያጋጥመን ሁሉ ይረዳልናል፡፡ በመታዘዛችንም ምክንያት ሰዎች ቢያፌዙብን፣ ቢስቁብን፣ የገቢ ምንጫችን ቢቋረጥ ወይም በዚህ ዓለም ከሚገኝ እድገት የሚገታን ሌላ እንቅፋት ቢያጋጥመን ጌታ በርኅራኄው ከእኛ አይለይም፡፡ ‹‹እርሱ ራሱ ተፈትኖ መከራን ስለተቀበለ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላል›› (ዕብ.2፡18) እንደተባለ በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት ብንቀርብ (ዕብ.4፡16) ፍጹም በሆነው ርኅራኄው ያግዘናል፡፡

እግዚአብሔርን መታዘዝ ስንጀምር ልባችን ከሚመኛቸው ነገሮች ወይም ሰዎች እንድንለይ ያስፈልገናል፡፡ ምናልባትም እግዚአብሔር ከሰጠን መልካም ከሆኑ ነገሮች እንኳ መለየት ቢያስፈልግ ልንለይ እንችላለን፡፡ እንደዚሁም እግዚአብሔር ፈቃዱ ከሆነ በጣም የምንወዳቸውን ሰዎች ይወስድብናል ወይም እርሱን ለመታዘዝ ከመፈለጋችን የተነሳ እኛ ራሳችን ከምንወዳቸው ሰዎች በፈቃዳችን እንርቃለን፡፡ ተግባራችንን ከምናከናውንበት አካባቢም ሆነ እንድንፈጽመው እግዚአብሔር የሰጠንና ለእርሱ ልንሠራለት የምንወደው መንፈሳዊ አገልግሎት ቢሆን አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ስለፈቃዱ ብለን እንተዋለን፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ባዶ አድርጎ እስከ ሞት ድረስ ታዘዘ (ፊል.2፡5-8)፤ በጌቴሴማኒም ‹‹አባት ሆይ ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ›› (ሉቃ.22፡42) እያለ ለአባቱ በመታዘዝ ቅዱስ የሆነውና ኃጢአት ያላወቀው እርሱ ኃጢአታችንን በመስቀል ላይ በሥጋው ተሸክሞ ስለ እኛ ኃጢአት የሆነበትን የመታዘዝ መንገድ ተጓዘ (1ጴጥ2፡24፣ 2ቆሮ5፡21)፤ በመስቀል ላይም ስለእኛ ኃጢአት በመሆኑ በአባቱ የተተወበትንና የእግዚአብሔር ፍርድ በላዩ የወደቀበትን መንገድ በመታዘዝ ሄደ (ማቴ.27፡46፣ ዘካ13፡7፤ ሮሜ.8¬፡3) የእግዚአብሔር ሰዎች ሁሉ እስከ ዛሬ ከተጓዙት የመታዘዝ መንገድ ሁሉ በላቀ ሁኔታ ለአባቱ ታዘዘ፡፡ ይህን ያህል ሊታዘዝ የሚችል ወይም የቻለ ሰው አልነበረም፡፡ በዚህም ምክንያት የልባችንን ስሜትና ችግሮቻችንን ሳይረዳ የመታዘዝ መሥዋዕት ሊኖር ባልቻለ ነበር፡፡ ነገር ግን ‹‹የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ›› እያለ የመታዘዝን ጎዳና እስከመጨረሻው በመጓዙ በእንደዚህ ዓይነቱ ሁኔታ ውስጥ እግዚአብሔር ለልባችን የሚኖረውን ትርጉምና ለችግራችን የሚሰጠውን እርዳታ ከራሱ ልምምድ በመነሳት የሚያውቀው በመሆኑ ሊረዳልን ይችላል፡፡ ሊሰቀል በተያዘበት ማለዳ አጽንቶ ሲጸልይ ከሰማይ መጥቶ የሚያበረታው መልአክ የታየው ስለሆነ (ሉቃ.22፡43) አሁንም በብቸኝነታችን ሰዓት ሊያበረታን፣ በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ ሊሰጥን ከጎናችን ይቆማል፡፡

የሰይጣን ፈተናዎች

ሰይጣን ፈተና ይዞ ሲቀርበን ልባችን በጣም ያዝናል፡፡ የተቀበልነውን አዲስን ሕይወት የሚያስቸግሩ ርኩስ ሐሳቦችን እየለቀቀብን ልባችን እንዲያምፅ ይፈታተናል፡፡ ያለ ዕረፍት እየደጋገመ ልባችንን ለአለመታዘዝ ለማነሳሳት ጥቃቱን ይሰነዝራል፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል በምናነብበት ጊዜ፣ ለጸሎትና ለአምልኮ በምንሰበሰብበት ጊዜ አእምሮአችንን የሚሰርቅ ሐሳብ በመልቀቅ ያውከናል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከማንም በላይ በሰይጣን ተፈትኖአል፡፡ ለአርባ ቀናት በተከታታይ ከሰይጣን ተፈተነ (ሉቃ.4፡2) ሰይጣን ያለ የሌለ ኃይሉንና ተንኮሉን እየተጠቀመ ንጹሕና ቅዱስ የሆነውን ክርስቶስን ተፈታተነ፡፡

አዳም ከወደቀ በኋላ የአዳም ዘር ሁሉ ለሰይጣን ፈተና በቀላሉ የሚጋለጥ ሆነ፡፡ ሰይጣን በወደቀው የሰው ዘር ተባባሪ የሚሆነውን ማረፊያ ልብ አገኘ፡፡ ይህም ተባባሪ ልብ በኃጢአት ደስ ይለዋል፡፡ የሰው የልቡ አሳብና ምኞት ሁልጊዜ ርኩስ ነው (ዘፍ.6፡5)፡፡

አዳም ከመውደቁ በፊት ግን እንዲህ አልነበረም፤ አዳም በእግዚአብሔር ንጹሕ ፍጥረት ሆኖ ነበር የተፈጠረው፡፡ ሰይጣን ወደ አዳም ልብ ምንም መግቢያ ባይኖረውም ዓላማውን ለማሳካት አንዴ የከፈተው ጥቃት በቂ ሆኖ አገኘው፤ አዳምም ሳተ፡፡ በዚህ ራሱን ለሰይጣን አስገዝቶ ባሪያ ሆነ፡፡

ከዘመናት በኋላ ግን በልቡ ምንም ኃጢአት የሌለበት አምላክ ሥጋን ለብሶ ሰው ሆኖ ተገለጠ፡፡ ይህም ሰው ኃጢአት ሠርቶ አያውቅም፡፡ ሆኖም ሰይጣን በዚህም ሰው ላይ ጥቃቱን አነጣጠረ፡፡ ጦርነቱ ግን የተለየ ሆኖ ተገኘ፡፡

አዳም ላይ ጥቃቱ የተከፈተው የእግዚአብሔር ደግነትና በጎነት በሚታይበት በኤድን ገነት ውስጥ ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ግን የተፈተነው ምንም በሌለበትና የእርግማን ምልክት በሆነው በምድረበዳ ነበር፡፡ ሰይጣን መላ ኃይሉንና ተንኮሉን ተጠቅሞ ቅዱሱን ኃጢአት ለማሠራት የሞከረውም በዚሁ በረሃ ውስጥ ነበር፡፡ ሰይጣን ያለ አቅሙን ሁሉ ተጠቅሞ እስኪሸነፍ ድረስ ጥቃቱ ለአርባ ቀናት ቆየ፡፡ ከጦርነቱም የሸሸው የተሸነፈው ሰይጣን ነበር፡፡ ክርስቶስ ግን ስፍራውን አልለቀቀም፡፡ ጌታችን ያሳለፈውን ፈተና ሁሉ ያውቅ ዘንድ በዚያ ማን ነበር? የሰይጣንን የተንኮል ወጥመዶችንና የጭለማው ገዢ ሙሉ የውጊያ ትጥቆችንስ ማን አውቋል? እዚህ ላይ የተገለፁልን የመጨረሻዎቹ ሦስቱ ብቻ ናቸው፡፡ ኃጢአት ለማያውቀውና ንጹህ የሆነው ክርስቶስ እነዚያ የሰይጣን የፈተና ፍላፃዎች ሲወረወሩበት ምን ተሰምቶት ይሆን? ቅድስት ነፍሱ ምንኛ ትጨነቅ ይሆን? በዚህ ሁሉ የተፈተነው እርሱ ሰይጣን የተንኮል ወጥመዱን በእኛ ላይ በዘረጋብን ጊዜ በድካማችን ይረዳልና፤ አብልጦም ይራራልናል፡፡

ጌታችንን ያልፈተነበትና እኛን ሊፈትንበት ያለው ፈተና ለሰይጣን ቀርቶለታልን? ጌታ ሊረዳንም የተቻለው ከዚሁ የተነሳ ነው፡፡ ‹‹እርሱ ራሱ ተፈትኖ መከራን ስለተቀበለ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላል›› (ዕብ.2፡18) እንደተባለው እምነቱ እንዳይጠፋ ለጴጥሮስ ጸለየለት፡፡ ‹‹ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም›› (ዕብ.4፡15)፡፡

በመከራችንና በኀዘናችን የእርሱ ርኅራኄ

የምንወዳቸው ሰዎች በሞት ሲለዩን በሚሰማን የልብ ኀዘን በወዳጁ በአልዓዛር መቃብር አጠገብ እንዳነባው እንደ ኢየሱስ ስሜታችንን የሚረዳልን ማን ይኖራል? ማንም የለም፡፡ ብቸኝነት ቢሰማን ‹‹እንደ ምድረበዳ እርኩም መሰልሁ፤ በፈረሰ ቤት እንዳለ እንደ ጉጉት ሆንሁ››(መዝ.102፡7) ተብሎ በትንቢት ከተነገረለት ይበልጥ በብቸኝነት የተሰቃየና በብቸኝነታችን የሚራራልን ሌላ ማን አለ? በወዳጆቻችን ብንጣል ‹‹ሁሉም ትተውት ሸሹ›› (ማር.14፡50) ከተባለለት ይበልጥ ሥቃያችንን የሚረዳልን ማነው? እርሱ ብቸኝነትንና በሌላ መተውን ከማንም ይበልጥ ያውቃልና፡፡ ለሰዎች ችግራችንን ስንነግራቸው ችግራችን ላይገባቸው ቢችል ወይም እኛን ለመርዳት ፈቃደኞች ሆነው ባይገኙ ‹‹አስተዛዛኝም ተመኘሁ አላገኘሁም የሚያጽናናኝም አጣሁ›› (መዝ.69፡20) ካለው ይበልጥ ሐሳባችን ፈጥኖ የሚገባውና እኛን ለመርዳት ፈቃደኛ የሚሆን ማነው? እርሱ ለደቀመዛሙርቱ ከእነርሱ አንዱ አሳልፎ እንደሚሰጠውና ስለእነርሱም እንደሚሞት ሲነግራቸው ልብ ብለው በማስተዋል ፈንታ ከእነርሱ መካከል ማን ታላቅ እንደሆነ በተነሣው ጥያቄ ክርክርና ኩርፊያ ውስጥ በመግባታቸው አጽናኝ አጥቶ በብቸኝነት የተቸገረ ቅዱስ ጌታ ነው (ሉቃ.22፡19¬-24) ልቦናችን ሲጨልምና የሚረዳንን ስንሻ በሉቃስ ወንጌል ላይ ሊጸልይ እንደሄደ ሰባት ጊዜ ያህል ከተነገረለትና ሌሊቱን ሙሉ ሲጸልይ ያድር ከነበረው ክርስቶስ ይበልጥ ሊረዳን የሚችል ማነው?

ይህም ጌታ በሰማያት ያለውና የሚያማልድልን ሕያው ሊቀ ካህናታችን ነው (ዕብ.7፡25) ሰልፉ አልቋልና አሁን እርሱን የሚያገኘው ፈተና የለም፡፡ ስለሆነም አሁን በእኛ ችግርና መከራ በመግባት ባገኘው የግሉ ልምምድ እውቀት በመጠቀም ሙሉ በሙሉ እኛን ለመርዳት የተሰጠ ሊሆን ተችሎታል፡፡

በምድራዊ ጉዞአችን ጥቃትና ችግሮች የሚበዙብን ከሆንን በክርስቶስ አማላጅነት ረድኤት ልናገኝ እንችላለን፡፡ በምድር ላይ በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ በነበረበት ከእግዚአብሔር ይላክለት በነበረው መፅናናት የእግዚአብሔር ጸጋ ምን ያህል እንደሚያጽናና ስለሚያውቅ እኛንም እንዲሁ በመከራችን ሁሉ ሊረዳን ስለእኛ በእግዚአብሔር ፊት ይታይልናል፡፡ እርሱ የተቸገረችን ነፍስ እንዴት እንደሚያጽናና ያውቅበታል፡፡ ስለችግራችን በሚያውቅልን መጠን በሚያስፈልገን ሁሉ ይረዳናል፡፡ ማስተዋል ቢያስፈልገን ማስተዋል ይሰጣል፡፡ ምሪት ብንፈልግ ምሪት ይሰጣል፡፡ በፈለግነው ነገር ሁሉ የእግዚአብሔር እርዳታ የሚደርስልን በእግዚአብሔር ፊት ክርስቶስ ከሆነልን የተነሳ ነው፡፡

ይህ ሁሉ የሚሆንልን ግን ስለጸለይን ይመስላችኋልን? ስለ ጴጥሮስ የጸለየው ጴጥሮስ ከፊቱ ስለሚመጣው ነገር አንዳች ሳያውቅ ነው፡፡ አማልደን ብለን ወደ ክርስቶስ አንጸልይም፤ ከልቡ በሚመነጭልን ጸጋ የሚያስፈልገንን ያሟላልናል፡፡ ስለዚህም በሚያስፈልገን ሁሉ ረድኤትንና ምሕረትን እንድንቀበል ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት ደፍረን እንቅረብ፡፡

ከሰላምታ ጋር
የእናንተው ወንድም

ምዕራፍ 8 አዲስ ልደት

ውድ ወገኖቼ

ባለፈው ደብዳቤ ክርስቲያን ማለት ከክርስቶስ ጋር የሞተ ማለት እንደሆነ ተነጋግረናል፡፡ የአሮጌው ፍጥረት ባሕርይም በጣም የተበላሸ ወይም ርኩስ ከመሆኑ የተነሳ ከእግዚአብሔር ፍርድ ውጭ ምንም የሚጠብቀው እንደሌለ አይተናል፡፡ በዮሐ 3 ላይ ጌታችን ኢየሱስ ይህንን ችግር ከነመፍትሔው ለኒቆዲሞስ አውስቶታል፡፡

ምንባቡ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 2፡23 ጌታችን በኢየሩሳሌም ሳለ ይጀምራል፡፡ ጊዜው የፋሲካ ሰሞን ሆኖ ብዙ ድንቅ ምልክቶችን ይሠራ ነበርና ከሚሠራቸው ሥራዎች የተነሳ ብዙዎች በስሙ እንዳመኑ ቃሉ ይነግረናል፡፡ ‹‹ነገር ግን ኢየሱስ ሰዎችን ሁሉ ያውቅ ነበር፤ ስለሰውም ማንም ሊመሰክር አያስፈልገውም ነበርና አይተማመናቸውም ነበር፤ ራሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና›› (ዮሐ.2፡25)፡፡ ከእነዚህ ጌታ ከሚያውቃቸው ሰዎች መካከልም አንዱ መጣና አነጋገረው፤ ጌታም ‹‹ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም›› (ዮሐ.3፡3) ሲል አስረዳው፡፡

በሰማይ የሚኖር የሰው ልጅ

በማያያዝም ጌታ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 3 ቁጥር 11 እና 13 ስለ ራሱ ነገረው፤ ማንነቱንም ገለፀለት፡፡ ‹‹ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው››(ዮሐ.3፡13) ሲል አስረዳው፡፡ ዮሐ.1፡1 ደግሞ እርሱ ዘላለማዊ የሆነው እግዚአብሔር አምላክ እንደሆነ ይነግረናል፡፡ በዚሁ ምዕራፍ በቊጥር 14 ‹‹ቃልም ሥጋ ሆነ ጸጋንና እውነትን ተሞልቶ በእኛ አደረ›› ሲል በሌላ ቦታ ደግሞ ‹‹በሥጋ የተገለጠ አምላክ››(1ጢሞ3፡16) ይለዋል፡፡ ይህ ሁሉ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው በአንድ አካል እንደተገለጠ ያሳያል፡፡ ታላቅ ምስጢር ነው!

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ዘላለማዊው አምላክ ነው፡፡ ራሱን ዝቅ አድርጎ ሰው ሆነ፡፡ ሰው ቢሆንም አምላክነቱን አላጣም፡፡ በአንድ ስፍራ ‹‹በሥጋና በደም ተካፈለ››(ዕብ.2፡15) ሲለው በሌላ ስፍራ ደግሞ ‹‹ሰው የሆነው›› (1ጢሞ2፡5) ብሎ ይጠራዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ሰው ሆነ እየተባለ የተመሰከረለት ኢየሱስ ሰው ሆኖም እንኳ ‹‹የዘላለም አምላክ›› ነው (ኢሳ.9፡6)፡፡

ሕፃን ሆኖ ተወልዶ በግርግም ተኝቶ ሳለም በዚያው ሰዓት ፍጥረትን ሁሉ በሥልጣኑ ደግፎና አጽንቶ የሚያኖር ሁሉን የያዘ፣ ሁሉን የሚመግብ ነበር፡፡ በመንገድ በረሃብና በውሃ ጥም ደክሞ የሰማርያዋን ሴት ውሃ እንድታጠጣው ሲጠይቃት ወዲያውኑ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን ሊሰጣት የሚችል ሁሉን ቻይ አምላክነቱን ገልጾላታል፤ የሕይወት ታሪኳን በመንገርም ሁሉን አዋቂ የሆነ አምላክነቱን አሳይቷታል (ዮሐ.4) ፍጹም ሰው እንደመሆኑ በታንኳ ውስጥ ተኛ፡፡ ነቅቶም ነፋሱንና ማዕበሉን ገሠፀ፡፡ ኢየሱስ ‹‹እኔ ነኝ›› ብሎ ስሙን ሲጠራላቸው ሊይዙት የመጡት ወታደሮች ወደ ኋላ አፈግፍገው በመሬት ላይ እየወደቁ ተዘረሩ (ዮሐ.18፡6) ወዲያውኑ ደግሞ አስረው ሲዘብቱበት ይታያል፡፡

በምድር ከኒቆዲሞስ ጋር እያወራ ከሰማይም አልተለየም፡፡ ስለሚያውቀው ነገርም ነገረው፡፡ ‹‹ማወቅ›› የሚለውን ቃል ማወቁ ከባድ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር በስተቀርም ትክክለኛውን ትርጉሙን የሚያውቀው የለም፡፡ ወደ ሰማይ የወጣ ሰው ስለሌለ ስለሰማያውያን ነገሮች ሊናገር የሚችል ማንም የለም፡፡ ነገር ግን እርሱ የሰው ልጅ የሆነ ጌታ በሰማያት ነበረ፤ ከሰማያትም መጥቷል፤ አሁንም በሰማያት አለ፡፡ ስለ ሰማይ ሲናገር ስላየው እና ሊያየው ስላለ ነገር ይናገራል፡፡ የሰማይን ነገር የሚናገረው ሰማያዊ ስለሆነ ነው፡፡ መለኮትና ሰው በአንድ አካል በእርሱ ታዩ፡፡ ሲወለድም መላእክት ‹‹ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ›› (ሉቃ.2፡14) እያሉ የዘመሩት ለዚሁ ነው፡፡ እርሱ እግዚአብሔርንና ክብሩን ያውቃል፤ ሰውንም ያውቃል፡፡

የሰው ባሕርይ

በዮሐ.2፡23-25 ጌታ ስለ ሰው ያለውን አመለካከት እናያለን፡፡ በቦታው የምናያቸው ሰዎች የእግዚአብሔር አምልኮ የሌላቸውና በግልጥ ጠላትነት የተነሱበት አይደሉም፡፡ የሚሠራቸውን ምልክቶች አይተው መሲሕ መሆኑን አምነዋል፡፡ ይህንን ንባብ በጥልቀት ካላየነው እነዚህ ሰዎች በምዕራፍ 1 ቁ.12 ላይ ‹‹የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው›› የተባለላቸው ናቸው ብለን እንገምት ይሆናል፡፡ ነገር ግን በዚህ በተጠቀሰው ምዕራፍ ስናይ ስለ እነዚህ ሰዎች እንዲህ የሚል እናገኛለን፤ ‹‹ነገር ግን ኢየሱስ ሰዎችን ሁሉ ያውቅ ነበር ስለ ሰውም ማንም ሊመሰክር አያስፈልገውም ነበር አይተማመናቸውም ነበር ራሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና፡፡›› (ዮሐ.2፡23-25)፡፡

እነዚህ ሰዎች መሢሕ መሆኑን እንዲያምኑ ሆነው ነበር፤ ይመኑት እንጂ ግን አልተለወጡም ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ የመሆን ሥልጣን የሚሰጣቸው ማን መሆኑን ሲቀበሉት ብቻ ነው (ዮሐ.1፡12) ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች ተአምራቱንና ምልክቶቹን በማየታቸው ስሜታቸውና አእምሮአቸው መሢሕ መሆኑን ለማመን በቃ እንጂ አልተቀበሉትም፡፡

በዚያን ጊዜ እንደነበሩት ዓይነት ሰዎች ያሉ ብዙ ሚሊዮን ሰዎች ከዚያን በኋላም ሆነ ዛሬ አሉ፡፡ እነዚያ ሰዎች ምልክቶቹን አዩ፤ ኢየሱስ መሢሕ መሆኑንም አመኑ፡፡ ዛሬም ብዙ ሰዎች የክርስትናን እውነቶች አይጠራጠሩም፡፡ በማመዛዘንም ይህ ነገር ትክክል ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ክርስትናን በዚህ መንገድ ይቀበሉታል፡፡ ይህ ደግሞ ለፍጥረታዊው ሰው የሚስማማ መንገድ ነው፡፡ ራሱን ከእውነት በላይ በማስቀመጥ በራሱ ፍርድ መዝኖ ትክክል መስሎ የታየውን ይቀበላል፡፡ ይህን በማድረጉም ራሱን ከእግዚአብሔርና ከእውነት በላይ ለማድረግ ይጠቀምበታል፡፡

ኅሊና በእግዚአብሔር ብርሃን ሲጎበኝ የጠፋና ኃጢአተኛ መሆኑን ራሱ ያውቃል፡፡ በእግዚአብሔርና እግዚአብሔር በገለጠው ላይ ከመፍረድም ይቆጠባል፡፡ በራሱ ላይ ፈርዶ ኃጢአተኛ ነኝ ብሎ እየታመነ እንዲቀበለው ወደ እግዚአብሔር ይጮሃል፡፡

ፍጥረታዊው ሰው ዳግመኛ መወለድ የሚያስፈልገው ጣኦትን ለሚያመልኩ ወይም በከባድ ኃጢአት ለሚመላለሱ ሰዎች ብቻ አድርጎ ይቆጥረዋል፡፡ እያንዳንዱ ሰው ዳግመኛ መወለድ አለበት የሚለውን ሐሳብ ሊረዳ አይችልም፡፡ የኢየሱስን ምልክቶች አይተው የተገረሙና ያመኑትን ፈሪሳውያንም ሳይቀር አይተናል፡፡ ኒቆዲሞስንም እንመልከት፡፡ እርሱ ፈሪሳዊ፣ በእስራኤልም ዘንድ አስተማሪና የአይሁድ አለቃም ነው፡፡ ወደ ጌታም መጥቶ ‹‹መምህር ሆይ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን›› (ዮሐ.3፡2) በማለት ለጌታ ክብርን ሲሰጥ ይታያል፡፡ ኢየሱስም የዳግመኛ መወለድ አስፈላጊነትን ቢገልጽለትም የአይሁድ መምህሩ ግን ቶሎ ሊገባው አልቻለም፡፡ ጌታም ‹‹የእስራኤል መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን?›› በማለት ዘላለማዊ አምላክነቱን በሚያሳይ መልኩ ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም እንደሌና እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ መሆኑን በመጠቆም ኒቆዲሞስን ስላስገረመው ነገር አስረዳው፡፡ ዳግመኛ መወለድ ለማይታዘዙት ብቻ ሳይሆን መሢሕነቱን ላወቁለትም ሁሉ ጭምር እንደሚያስፈልግ አስረዳው፡፡ ጌታ ይህን የተናገረው ለጠላቶቹ ብቻ ሳይሆን ማንነቱን ላወቁትም ጭምር ነው፡፡ ይህም የሰው ልጅ ምን ያህል የጠፋና ከእግዚአብሔር የራቀ እንደሆነ ያሳየናል፡፡ ድርጅታዊ ሃይማኖተኝነት ወይም እውቀት ሊያድነው እንደማይችል ኒቆዲሞስም ሳይገነዘብ አይቀርም፡፡

ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም

ከኒቆዲሞስ ጋር በሚነጋገርበት ጊዜ ክርስቶስ የሚናገረው በዚያን ሰዓት ስለተገለጠችው የእግዚአብሔር መንግሥት ነበር፤ አይተው ያወቁትና ወልድነቱን ያመኑት በእርሱ የነበረችውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ማየት ይችላሉ፡፡ እነዚህ ዳግመኛ የተወለዱ ተብለው ይጠራሉ፡፡

ዘመዶቹ እንኳን የእርሱን ማንነት አይተው ባለማወቃቸው እንገረም ይሆናል፡፡ አበደ ብለው ሊይዙት እንደመጡም እናነባለን (ማር.3፡21)፡፡ እንዴት እንዳላወቁትም ይገርማል፡፡ ፍጹምና ቅዱስ የሆነው ሕይወቱን በናዝሬት በነበረበት ጊዜ አይተዋል፡፡ በየሰዓቱና በየቀኑ አብረውት ሳሉ ማስተዋል ይችሉ ነበር፡፡ ማርያምና ዮሴፍ ከፅንሰቱ ጀምሮ እስከ ልደቱ እና እስከ ዕድገቱ ድረስ እግዚአብሔር መልአኩን እየላከ ስላደረገው ነገር አልነገርዋቸውም ይሆንን? የቅርብ ዘመዳቸው መጥምቁ ዮሐንስ ስለ እርሱ መመስከሩን እንዴት አላወቁም? ሰማያት ከላይ እየተከፈቱ ‹‹የምወድህ ልጄ አንተነህ በአንተ ደስ ይለኛል››(ማር.1፡11) እንደተባለ አልሰሙም ይሆን? ‹‹አንድ ልጅም በአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነውን ክብሩን አየን›› (ዮሐ.1፡14) ተብሎ የተመሰከረለትን እርሱን ዘመዶቹ አብዷል ብለው ሊያስሩት መጡ፡፡ ይህ ጌታ “እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” ብሎ ለተናገረው ቃል ታላቅ ማስረጃ ነው!

እንደገና መወለድ

ይህ ዳግመኛ መወለድ ኒቆዲሞስ ይሆናል ብሎ እንዳሰበው አልነበረም፡፡ ወይንም የሩቅ ምሥራቅ የአረማውያን ፍልስፍናና ሃይማኖት ሰው ከሞተ በኋላ ተመልሶ እንደገና ሕፃን ሆኖ ይወለዳል ወይም ታድሶ ወጣት ይሆናል ብሎ እንደሚያስተምረው አይደለም፡፡ አዲስ የተወለደ ህፃን እንደ ወላጆቹ ያለ ተፈጥሮና ባሕርይ ይዞ ይወለዳል እንጂ ጥቂት እንኳ የተሻለ አይሆንም፡፡ ሰው ከእናቱ ዳግመኛ መወለድ ቢችል እንኳን ይህ መወለዱ ሰውን በምንም ሊያሻሽለው አይችልም፡፡ ከኃጢአተኛው አዳም የተወለደው የአዳም ልጅ ሴት የአባቱን ምሳሌና መልክ ይዞ እንደተወለደ ሁሉ (ዘፍ.5፡3) ሕፃን ልጅ የሚወለደው የወላጆቹን ተፈጥሮ ይዞ ነው፡፡ ነገሩ በመጽሐፈ ኢዮብ እንደምናነበው ነው፤ ‹‹ከርኩስ ነገር ማን ንፁሕ ሊያወጣ ይችላል?›› (ኢዮ.14፡4)፡፡ ከሮሜ.5፡19 ደግሞ ‹‹በአዳም አለመታዘዝ ምክንያት ብዙዎች ኃጢአተኞች ሆኑ›› ሲል የእርሱ ዘር የሆነ ሁሉ ያለጽድቅ የተወለደና ለመጽደቅም ክርስቶስ አስፈላጊው እንደሆነ እንረዳለን፡፡ በሌላ ስፍራም የእግዚአብሔር ቃል ‹‹ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው›› ሲል ያስረዳል (ዮሐ.3፡6) ኒቆዲሞስ አሥር ጊዜ ያህል የተመላለሰ ሕፃን እየሆነ መጀመሪያ እንደተወለደው ከኃጢአተኛ ወላጅ መወለድ ቢችል እንኳን ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ዝምድና በተመለከተ አንዳች ለውጥ ሊያሳይ አይችልም፡፡

የሰው ዳግመኛ መወለድ ሙሉ በሙሉ አዲስ በሆነ ሁኔታ ከላይ በሆነው በአዲስ የሕይወት ምንጭ መሆን አለበት፡፡ ይህ የሕይወት ምንጭም ኢየሱስ እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም (ዮሐ.3፡5) ያለው ምን መሆኑን መረዳት እንችላለን፡፡ ከኤፌ.5፡26 እንደምንረዳውና እንዲሁም ደግሞ ከዮሐ.13፡10 እና ዮሐ.15፡3 እንደምናየው ውኃ ከማንፃት ጋር የተያያዘ እንደመሆኑ መጠን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሰው ሕይወት ላይ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ለሚሠራው የእግዚአብሔር ቃል ዓይነተኛ ምሳሌ ነው፡፡

ውኃ የሚታጠብበትን ያነጻል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የሆነ የእግዚአብሔር ቃልም ሰውን ከስህተት ሐሳብ፣ ዝንባሌና ድርጊት ያነጻዋል፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ቃሉን ተጠቅሞ አዲስ ሕይወትን በሰው ውስጥ ይሠራል፡፡ ይህም ሕይወት አዲስ ከመሆኑ የተነሳ ሰው ከሥጋ ወላጆቹ ከሚወርሰው ባሕርይ የተለየ በአንጻሩ ግን ይህንን ሕይወት በውስጡ የሰጠውን የእርሱን ባሕርይ የሚመስል ነው፡፡ ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነውና (ዮሐ.3፡16)

አዲስ ልደት ከእግዚአብሔር ቃል እንደሚገኝ በመጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቦታ በተደጋጋሚ ተጠቅሷል፡፡ ጳውሎስ የቆሮንቶስን ሰዎች በወንጌል መልካም ዜና እንደወለዳቸው(1ቆሮ.4፡15) ሲናገር ያዕቆብ ደግሞ በመልእክቱ ‹‹ለፍጥረቱ የበኩራት ዓይነት እንድንሆን በእውነት ቃል አስቦ ወለደን››(ያዕ.1፡18) ይላል፡፡ ጴጥሮስም በመልእክቱ እንዲሁ ዳግመኛ መወለድ የሚከናወነው በቃሉ መሆኑን ሲያስረዳ እንዲህ ይላል፤ ‹‹ለእውነት እየታዘዛችሁ ግብዝነት ለሌለበት ለወንድማማች መዋደድ ነፍሳችሁን አንጽታችሁ እርስ በርሳችሁ ከልባችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ፡፡ ደግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፡፡ በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ፡፡››(1ጴጥ1፡22-25) ወደ ተሰሎንቄ ሰዎችም በተጻፈው መልእክትም የእግዚአብሔር ቃልና መንፈስ ቅዱስ በአንድነት ተጠቅሰዋል (1ተሰ1፡5)፡፡

ጌታ ለኒቆዲሞስ እንደተናገረው የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማየትም ሆነ ወደ እርሷ ለመግባት እንደገና መወለድ ያስፈልጋል፡፡ ለኒቆዲሞስ ብቻ ሳይሆን ይህ ጥሪ ለሁሉም ሰው የተሰጠ ጥሪ ነው፡፡ አዳም ከወደቀበት ጀምሮ እስከ ዓለም ፍፃሜ ድረስ ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ለማድረግ ዳግመኛ መወለድ አስፈላጊ ነው፡፡

የሰው ልጅ ሊሰቀል ይገባዋል

ስለሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ? (ዮሐ.3፡12) ብሎ ኒቆዲሞስን ከጠየቀው በኋላ ጌታ ሌላ ጠቃሚ ነገርን ተናግሯል፡፡ ይኸውም ብርሃን ስለሆነውና በእርሱም ውስጥ ምንም ጨለማ ስለሌለው የእግዚአብሔር ማደሪያ ስፍራ፣ ስለመንግሥተ ሰማያት ክብርና በዚያም ስለሚገኘው ክብር የሚያውቀው እርሱ ከሰማይ የወረደና በሰማያት የሚኖር የእግዚአብሔር ልጅ ብቻ መሆኑን ነው፡፡ ወደዚህ ወልድ ብቻ ወደሚያውቀው ክብር ለመግባት ደግሞ በመጀመሪያ የኃጢአት ጥያቄ መፍትሔ ሊያገኝ ይገባዋል፡፡ በሰው ኃጢአት የተበደለው እግዚአብሔር ሊረካበት የሚችልበት አንዳች ነገር መከናወን አለበት፡፡ ሰውም ወደ እግዚአብሔር ክብር እንዳይገባ ከሚከለክለው ነገር መንፃት አለበት፡፡ በኃጢአት ምክንያት ከምድራዊ ገነት የተባረረው ሰው ሺህ እጥፍ የከፋ ኃጢአት ሲሠራ ቆይቶ እንዴት ወደ እግዚአብሔር ማደሪያ ወደ ሰማያዊት ገነት ሊገባ ይችላል?

በአንድ አካል ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው የሆነው የሚያስፈልገውን ሁሉ ፈጽሞ ካልሠራ በስተቀር እግዚአብሔር የሚፈልገውን መስፈርት ማን ሊፈጽም ይችላል? ስለሆነም ‹‹በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ሊሰቀል ይገባዋል፡፡›› (ዮሐ.3፡14)

እግዚአብሔር ከዚህ በላይ ምን ሊሰጠን ይችላል? ከዚህ ስጦታ ጋር የተያያዙ ብዙ ነገሮችም አሉ፡፡ አባ አባት ብለን ወደ እርሱ መጮህ እንችላለን፡፡ ምክንያቱም ‹‹የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን መንፈስ ቅዱስ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክርልናል፡፡›› (ሮሜ.8፡15-16) ከክርስቶስ ጋር ወራሾች ሆነናል፤ በሚመጣው ዘመንም ከእርሱ ጋር ሆነን እንገዛለን (ሮሜ8፡17፣ኤፌ1፡10፣ 1ቆሮ.6፡23) ክርስቶስ ሲገለጥም ‹‹እርሱ እንዳለ እናየዋለንና እርሱን እንድንመስል እናውቃለን፡፡››(1ዮሐ3፡2) ሌሎችን የምናፈቅረውም ከእግዚአብሔር በመወለዳችን መሆኑን ቃሉ ያሳየናል (1ዮሐ4፡7)፤ ዓለምን ልናሸንፍ የቻልነውም እንዲሁ ከእግዚአብሔር በመወለዳችን ነው (1ዮሐ5፡4)፡፡

ከሰላምታ ጋር
የእናንተው ወንድም፡፡

ምዕራፍ 9 ከአብና ከወልድ ጋር ኅብረት

ውድ ወገኖቼ

በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምን ሁሉ የኃጢአትን ይቅርታ ብቻ ሳይሆን በአዲስ ልደት አዲስ ሕይወት እንደሚያገኝ ተረድተናል፡፡ ከእግዚአብሔር ይወለዳል (ዮሐ.1፡13) ከዚህም የተነሳ የመለኮታዊ ሕይወትና የመለኮታዊ ባሕርይ ባለቤት ይሆናል (2ጴጥ.1፡4)፡፡ ይህ ሕይወት ግልጽ በሆነ አገላለፁ ዘላለማዊ ሕይወት ተብሎ ይጠራል፡፡ በ1ዮሐ.5፡20 ስለ ጌታችን ኢየሱስ እንደዚህ ይላል እርሱ እውነትኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው፡፡ ስለዚህ ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ሕይወታችን ነው፡፡

ይህ እውነታ ማለቂያ የሌለው በረከትን አስገኝቶልናል፤ በአባቱ ዘንድ የተወደደ እንደመሆኑ እኛም ተወደናል (ኤፌ1፡6) ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥትም አፍልሶናል (ቆላ.1፡13) በእግዚአብሔር ፊትም ከእርሱነቱ የተነሳ ተቀባይነት አግኝተን መቆም ችለናል፡፡ እግዚአብሔር ፍጥረታትን ሲፈጥር በሰውና በእንስሳ መካከል ልዩነትን የሚያደርግ መረዳትን ለአዳም ሰጠው፡፡ የሰው መረዳት ግን ምድራዊ ብቻ ስለነበር ሰው ሊረዳ የቻለው ምድራዊ የሆነን ነገር ብቻ ነበር፡፡ መላእክትም ቢሆኑ እንኳን ከሰው ይልቅ ከፍ ያለ የፍጥረት ደረጃ ቢኖራቸውም እግዚአብሔርን ማወቅ ግን አይችሉም፡፡ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈፀም ዘወትር የተዘጋጁ ብርቱ አገልጋዮች ቢሆኑም ለእኛ የተሰጠው ተስፋ የሚፈፀምበትንም ቀን ለማየት በናፍቆት የሚጠባበቁ ናቸው (1ጴጥ.1፡12)፡፡

አሁን ደግሞ በኃጢአት ምክንያት ጠፍተው ለነበሩና ጠላቶቹ ሆነው ለቆዩት ኃጢአተኞች እግዚአብሔር ልጁን በመቀበላቸው ራሱን ልጁን አዲስ ሕይወት አድርጎ ሰጣቸው፡፡ ከዚህም ጋር በእርሱ በልጁ በኩል እግዚአብሔርን የማወቅ መረዳትን ሰጣቸው፡፡ የክብሩን ታላቅነት አሁን ራሱን ለእኛ በሚገልጥልን መጠን ብቻ ሳይሆን ጌታችን በደመና ሆኖ ዳግመኛ በዚህች ምድር ላይ ከሰማይ ሲገለጥ የሰው ሁሉ ዓይን እንደሚያየው እርሱነቱን እንዳለ ሆኖ የምናይበት ቀን ይመጣል፡፡ ሐሳቡንም አሁን ልንረዳው እንችላለን፡፡ ልባችንም በክብሩ ይሞላል፡፡ ከእግዚአብሔር ስሜትና ሐሳብ የሚስማማ አእምሮ አለን፡፡ የልቡንም ሐሳብ ያካፍለናል፡፡ የሚነግረንም ሁሉ ይገባናል፡፡

ከእግዚአብሔር አብና ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለው ኅብረት

በአብ ልብ የሚመላለሰው ሐሳብ ምን ይሆን? ሐሳቡ በወልድና በሥራው ክብር ዙሪያ አይደለምን? ወልድ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት ‹‹እግዚአብሔር ሙላቱ ሁሉ በእርሱ እንዲኖር .. .. .. ፈቅዶአል፡፡››(ቆላ1፡19) ጌታ ምድራዊ አገልግሎቱን ሊጀምር ሲልና(ሉቃ3፡22) በአገልግሎቱ መጨረሻ አካባቢም(ማቴ.17፡5) ‹‹በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ›› በማለት አብ ከሰማይ በልጁ ስላለው ደስታ ተናግሮ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ነበር የጎልጎታው ሥራ የተከናወነው፡፡

እርሱ ራሱም ‹‹ነፍሴን ደግሞ አነሳት ዘንድ አኖራለሁና ስለዚህ አብ ይወደኛል››(ዮሐ.10፡17) በማለት ተናግሯል፡፡ በእርግጥም አብ ይወደዋል፡፡ እርሱ በፈቃደኝነቱ ወደ መስቀል በመሄድ የእግዚአብሔርን ስም ለማክበርና ፈቃዱን ለመፈፀም እስከ ሞት ድረስ የታዘዘ ሆኖ ተገኝቷልና፡፡ ለዚህም ሲል በሥጋው ኃጢአታችንን በመሸከም(1ጴጥ.2፡24) ስለእኛ ኃጢአት ሆነ (2ቆሮ.5፡21)፤ ስለ እኛ ሆነ ብሎ የእግዚአብሔርን ፍርድ ተሸክሞልን በእግዚአብሔርም የተተወ ለመሆን በቃ፤ እስከመጨረሻውም ፍጹምነቱን ሳይለቅ ‹‹ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር አቀረበ፡፡››(ዕብ.9፡14)

ስለዚህም አብ ‹‹ይህ የምወደው ልጄ ነው›› ብሎታል፤ እኛ ደግሞ ‹‹ይህ የምንወደው አዳኛችን ነው›› እንለዋለን፡፡ አብ ‹‹ለእኔ ካለው ፍቅር የተነሳ ልጄ በጎልጎታ መከራን ተቀብሎ ሥራውን ፈጸመ›› ሲል እኛ ደግሞ ‹‹እኛን ስለ ወደደን ራሱን አሳልፎ ሰጠ››(ኤፌ.5፡2) እንላለን፡፡ ወይንም እኔም በግሌ እናንተም በየግላችሁ አሁን የምኖረው ኑሮ ‹‹በወደደኝና ስለእኔ ራሱን በሰጠ በእግዚአብሔር ልጅ ነው›› ልንል እንችላለን (ገላ2፡20)

ይኸው አንዱ የአብን ልብ ደስ ያሰኘውና ልቡን ያሳረፈው የከበረው ወልድ የኛንም ልብ ሞልቶ ያሳርፋል፡፡ አብ የወልድን ክብር ያሳየናል፡፡ በወልድ ስላገኘነውም ክብር ሁሉ ለአብ እንነግረዋለን፡፡ ኅብረት ማለትም ይህ ነው፡፡ ይህም የጋራ ስሜትና የጋራ ፍላጎት ከአብና ከወልድ ጋር ያለን ኅብረት ነው፡፡ ልባችንን በደስታና በፍስሐ የሚሞላንም እርሱ ራሱ ወልድ ነው፡፡

በወልድ በኩልም እንዲሁ አይደለምን? እርሱ አብን ለእኛ ገልጾልናል፡፡ እርሱ አብን ‹‹አባት››(ማር.14፡36) ብሎ እንደጠራ እኛም ‹‹አባ አባት›› ብለን እንጠራዋለን (ሮሜ.8፡15)፡፡ በረከቱን በመቀበል ብቻ ሳይሆን ራሱ እግዚአብሔርን በመቀበል ያለው ደስታ ትልቅ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር አብና ከእግዚአብሔር ወልድ ጋር በኅብረት ከመሆን የበለጠ ምን አለ? ይህን በሕይወታችን ብንለማመደው ልባችን በፍጹም ደስታ ተሞልቶ በዚህ ምድር መመላለስ እንችላለን፡፡ ሐዋርያው ‹‹ኅብረታችንም ከአባት ጋር ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው፤ ደስታችሁም ፍጹም እንዲሆን ይህን እንጽፍላችኋለን›› ያለውም ለዚሁ ነው (1ዮሐ1፡4)

እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም

ይህ ከአብና ከልጁ ጋር ያለው ኅብረታችን ከእግዚአብሔር ባሕርይ ጋር የተስማማ መሆን አለበት፡፡ እግዚአብሔር ብርሃን ነው፡፡ ከእርሱ ጋርም ኅብረት እንዲኖረን በብርሃን መመላለስ ይኖርብናል፡፡ ቀድሞ ጨለማ የነበርን አሁን ግን በጌታ ብርሃን ነን (ኤፌ.5፡8) እርስ በእርሳችን ኅብረት እያደረግን በብርሃን እንጓዛለን፡፡ አሁን ለያዝነውም ስፍራ መሠረትና ሕጋዊ ማረጋገጫ የሆነልን ቢኖር የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ነው፡፡

በ1ዮሐ.1፡7 እንደምናስተውለው ዋናው ነገር እንዴት እንደምንመላለስ ሳይሆን የት እንደምንመላለስ ነው፡፡ ከብርሃን ጋር የተስማማ ጉዞ ስንል ዕለታዊ ኑሮአችንን በተመለከተ እየተነጋገርን ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ላይ ዋናው ሐሳብ የምንመላለስበት ቦታ ምንነት ነው፡፡ ዳግመኛ የተወለደ፣ ከጨለማ ሥልጣን ነፃ የወጣና በብርሃን ላሉት ቅዱሳን ከተሰጠ ርስት ተካፋይ ይሆን ዘንድ ብቃት ያገኘ ሁሉ በብርሃን ይመላለሳል (ቆላ.1፡12-13) ደሙ ዕለት ዕለትና በሁሉም ወቅት ስለሚያነጻኝ በብርሃን እንደምመላለስ አረጋግጣለሁ፡፡ ለዚህም የሚከተለውን አጭር ማብራሪያ እንመልከት፡፡ እጄን የሳሙና ውኃ ባለበት ባልዲ ነክሬ ስሠራ እጄ መቆሸሽ አይችልም፡፡ እጄን እስከነከርኩ ድረስ መጀመሪያ እጄን ያነጻልኝ በሳሙናው ውኃ ላይ ያለው ቆሻሻን የማንፃት ኃይል እጄን ከመቆሸሽ ይጠብቀዋል፡፡ እጆቼ ቆሻሻ የሆነውን ሁሉ የማንጻት ባሕርይ ባለው ፈሳሽ ውስጥ እስከቆዩ ድረስ እንዴት ሊቆሽሹ ይችላሉ? በብርሃን ውስጥ የሚሠራው የደሙ ኃይልም እንዲሁ በብርሃን የሚመላለሱትን በንፅህና ይጠብቃቸዋል፡፡ በደሙ እስከተጠበቅኩ ድረስም ከብርሃኑ ጋር በተስማማ ሕይወት መመላለሴን እረዳለሁ፡፡

ይህ ግን የእኔን አሮጌውን ፍጥረት ይሽራል ማለት አይደለም፡፡ ይህን በመካድ ኃጢአት የለብኝም ብል ራሴን አታልላለሁ፡፡ እውነትም በእኔ ዘንድ የለችም፤ ኃጢአት ሠርቼ አላውቅም ብዬ ብናገርም ‹‹ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋል›› ተብሎ የተነገረውን ቃል ውሸት አደረግኩት ማለት ነው፡፡

1ዮሐ.1፡10ን ስናይ ‹‹ኃጢአት አላደረግንም ብንል›› የሚል እናገኛለን እንጂ ኃጢአት አናደርግም ብንል አይልም፡፡ ይህም ያለፈን ሁኔታ እንጂ የወደፊቱን የሚያሳይ አይደለም፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትም ለአማኝ ኃጢአት መሥራት አስፈላጊ እንደሆነ ፈፅሞ አያሳዩም፡፡ ኃጢአት ሊሠራ የማይችል አዲስ ፍጥረት አለን፡፡ ለአዲስ ሕይወት በሚመች አካሄድ እንድንመላለስም በእኛ ውስጥ ያለው የመለኮት ኃይል እርሱም መንፈስ ቅዱስ ያስችለናል፡፡ መመላለሳችን በብርሃን ውስጥ ስለሆነ ከብርሃን ጋር የማይስማማውን በራሱ በብርሃኑ በግልጥ ማየት እንችላለን፡፡

በሚያሳዝን ሁኔታ በያዕ.3፡2 ላይ ‹‹ሁላችን በብዙ ነገር እንሰናከላለንና›› የሚል ቢገኝም ይህ ደግሞ ብንሰነካከልም ምንም ችግር የለውም ለማለት የተነገረ አይደለም፡፡ ይህን ነገር በሚቀጥለው መልእክት እንነጋገርበታለን፡፡

ከሰላምታ ጋር
በክርስቶስ የናንተው ወንድም

ምዕራፍ 10 ጠበቃችን ክርስቶስ

ውድ ወዳጆቼ

> ያለፈውን ደበዳቤ ካቋረጥኩበት ልቀጠል፤ የመነጋገሪያ ነጥቦቻችንንም እስኪ አብረን እንያቸው፡፡

አማኝ ኃጢአት ቢሠራ

> አማኞች ሆነን ኃጢአት ብንሠራ የእግዚአብሔር ልጆች እንድንሆን የተሰጠንን መብት ይቀይረዋል ወይ? ኃጢአት ስለሠራንም ከእግዚአብሔር ራሳችንን ማግለል ይገባናል ወይ? መልሱንም በዕብራውያን 9 እና 10 እናገኘዋለን፡፡ ክርስቶስ ዘላለማዊ ቤዛነትን አስገኝቶልናል፤ ምክንያቱም ‹‹አንድ ጊዜ በማቅረብ የሚቀደሱትን የዘላለም ፍፁማን አድርጎአቸዋልና›› (ዕብ.10፡14)፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነትና ያገኘነውን ቤዛነት በተመለከተ እስከ ዘለዓለም በዚህ ማረጋጋጫ የታተመ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች ሆነናል፡፡ ይህም ዝምድና አይሻርም፡፡

> አባታችን እግዚአብሔርስ የልጆቹን ኃጢአት በቸልታ ይመለከታል ወይ? አባታችን እግዚአብሔር ብርሃን ነው፤ በእርሱ ዘንድ ከቶ ጨለማ የለም፡፡ ፍጹም ቅዱስ ከመሆኑ የተነሳ ኃጢአትን አይቶ ቸል ማለት አይችልም፡፡ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡትም በቅድስና መቅረብ ይገባቸዋል፡፡ እግዚአብሔር እርሱን የሚጠሉት ዓለማውያን የሚሠሩትን ኃጢአት ቸል ሊለው ይችላል፡፡ ማንኛውንም በልጆቹ ያለን ኃጢአት ግን ቸል ሊል አይችልም፡፡ እርሱ ቅዱስ ስለሆነ ከኃጢአት ጋር ወይም በኃጢአት ከተበከለ ሰው ጋር ኅብረት ማድረግ አይችልም፡፡ አእምሮአችን በኃጢአት ሐሳብ ሲረክስ ወይም ኃጢአትን ያዘለ የስንፍና ቃል ስንናገር ወይም ኃጢአት ስንሠራ ከአብና ከወልድ ጋር ያለን ኅብረት በቅፅበት ይቋረጣል፡፡ ይህም ኅብረት ሊቃና የሚችለው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ኃጢአታችንን ስናስወግድ ነው፡፡ ‹‹በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነፃን የታመነና ጻድቅ ነው፡፡››(1ዮሐ.1፡9) በመሆኑም የምንነጻው በመናዘዝና በራሳችን ላይ በመፍረድ ነው፡፡ ጥፋተኛነትን ማመን ኅብረታችን የሚቃናበት ብቸኛ መንገድ ነው

> ይህ በቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የምናገኘው መመሪያ ነው፡፡ በብሉይና በአዲስ ኪዳናት ተደጋግሞ የተጻፈ ነገር ነው፡፡ ከብሉይ ኪዳን ዓይነተኛ ምሳሌዎች እስቲ እንመልከት፡፡

> በዘሌዋውያን 4 እና 5 በከፊልም ደግሞ በምዕራፍ 6 እና 7 ኃጢአት ስለሠራ እስራኤላዊ የተሰጠ መመሪያ እናነባለን፡፡ እነዚህን ምንባባት ምንም እንኳን የወንጌል አስተማሪ ለወንጌል ትምህርት መንደርደሪያ ሊያደርገው እና ሊጠቀምበት ቢችልም የምንባባቱ ፍሬ ሐሳብ ስለ ኃጢአተኛ መለወጥና አለመለወጥ አይደለም፡፡ አሁን የጠቀስናቸው ምዕራፎች እስራኤል በታላቁ የስርየት ቀን በሚቀርብለት የቤዛ መሥዋዕት ላይ ተመሥርቶ ወደ እግዚአብሔር የመጣ ሕዝብ እንደሆነና ዕለት ዕለት በሚቃጠለው መሥዋዕት ምክንያትነት ደግሞ እግዚአብሔር ማደሪያውን በመካከላቸው ያደረገላቸው ሰዎች እንደሆኑ የሚያሳዩ ናቸው (ዘጸ.29፡38-46) ከዚህም የተነሳ በኦሪት ዘሌዋውያን በተደነገጉት የመሥዋዕት ሥርዓታት እንደምናየው እግዚአብሔር በመካከላቸው እንደነበረ ብቻ ሳይሆን እነርሱም ወደ እግዚአብሔር መቅረብ የሚችሉበት ሁኔታና ኅብረት እንደነበረ እናስተውላለን፡፡ በተጨማሪም ዕለት ዕለት ስለሚደረጉ ኃጢአቶች ምን መደረግ አለበት? የሚል ጥያቄ አስፈላጊ ይሆናል፡፡

> ዘሌዋውያን 5፡1-4 በየዕለቱ ሕይወታችን የሚከሠቱ ሦስት ዋና ዋና የርኩሰት ዓይነቶችን ይዘረዝርልናል፡፡ ቁ.1ን ስንመለከት ኃጢአት እየተሠራ አይተን እንዳላየን መሆን ወይም መልካም ለሆነው ነገር መልካምነቱን ባንመሰክር ኃጢአት እንደሚሆንብን ይናገራል፡፡ መደረግ ያለበትን አለማድረግም ኃጢአት ነው፡፡ ቁ.2ን ስንመለከት ደግሞ ሰው ከራሱ ውጭ ከሆኑ ነገሮች ጋር ሲነካካ ርኩሰትን እንደሚያስከትልበት ያሳያል፡፡ ይህም ከዓለማዊ ነገሮች አለመለየት በተግባር የሚያስከትልብንን ችግር ያሳየናል፡፡ ቁ.4 ደግሞ ራስን ካለመግዛትና ከግዴለሽነት ከራሳችን ውስጥ ስለሚወጣ ርኩሰት ይናገራል፡፡ ይህም አንደበትን አለመቆጣጠር ወይም ከልብ የሚወጣ ርኩሰት ነው፡፡ ቁ.15 እና ከዚያ ቀጥሎ ያለው ደግሞ እግዚአብሔር ለራሱ የወሰነውንና የለየውን ነገር ለራስ ማድረግ የሚያስከትለውን ኃጢአት ይጠቅሳል፡፡ በምዕራፍ 6 ከቁ.1-7 ያለው ደግሞ የሌላ ሰው የሆነውን ነገር በመውሰድ ስለሚመጣ ኃጢአት ይናገራል፡፡

> አንድ እስራኤላዊ በበደል ቢረክስ እንዴት መንጻት ይችላል? አንድ መንገድ ብቻ አለ፡፡ ከእነዚህ ነገሮች በአንዲቱ በደለኛ ሲሆን የሠራውን ኃጢአት ይናዘዛል፤ ስለሠራው ኃጢአት ለእግዚአብሐር የበደል መሥዋዕት ያመጣል (ዘሌ.5፡5-6)፡፡ በተጨማሪም በተቀደሰ ነገር ላይ ስለተሠራው ኃጢአትም ሆነ ከወንድሙ አንዳች በመውሰድ የበደለ ሰው ዕዳ መክፈል እንዳለበት(ዘሌ.5፡16፣ 6፡5) ሕጉ ይናገራል፡፡ ነገር ግን ዋንኛውና መሠረታዊው ነገር ኃጢአትን መናዘዝና የበደልን መሥዋዕት ማቅረብ ነው፡፡

> ራስን መርምሮና በኃጢአተኝነትና በውድቀት ላይ መሆንን አምኖ መቅረብ ለማናቸውም ይቅርታ ማግኘትና መንፈሳዊ ሕይወት መቃናት በቅድመ ሁኔታነት የሚያስፈልግ ነገር ነው፡፡ ለዚህም ለምሳሌ ያህል 1ቆሮ.11፡31 እና 1ዮሐ.1፡9ን ማየቱ በቂ ነው፡፡ የሠራነውን ኃጢአት መናዘዝ ብቻ ሳይሆን ዳዊት በመዝ.51፡1-7 እንዳደረገው ስለሁኔታችንና ስለማንነታችንም ራሳችንን መርምረን ትክክለኛ ማንነታችንን በእግዚአብሔር ፊት ማስቀመጥ አለብን፡፡ እግዚአብሔርም መስቀሉን አይተን ኃጢአት ማለት ምን ማለት እንደሆነ እንድንረዳ ዓይኖቻችን ወደ ልጁ መስቀል ያነሳቸዋል፡፡ ይህም ዳግመኛ እንደ አዲስ አማኝ የክርስቶስ ደም አስፈልጎን አይደለም፡፡ ምክንያቱም ይህ አንድ ጊዜ ተከናውኖአልና፡፡ ሆኖም ኃጢአት አንዲትም እንኳን ብትሆን ምን ያህል አስከፊ እንደሆነችና ከዕዳዋም ነፃ ለመውጣት የተከፈለውን ዋጋ እናስተውል ዘንድ ጌታ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ስለ ኃጢአታችን የተቀበለውን መከራ ማለትም ስለከፈለው የበደል መሥዋዕት መገንዘብ ይኖርብናል፡፡

> ስለ ኃጢአታችን ጎልጎታ ላይ ምን ያህል እንደተሰቃየ በማስተዋል ብቻ የኃጢአትን አስከፊነት መረዳት እንችላለን፡፡ እግዚአብሔር እስኪተወው ድረስ ብቻውን ተሰቃየ፤ ኃጢአታችንንም በሥጋው ተሸክሞ በእንጨት ተቸንክሮ ዋለ፡፡ እያንዳንዱ ኃጢአት በቸልታ ሊታለፍ አይገባምና የተበላሸ ኅብረት ካለን ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት እንዲስተካከል ኃጢአታችንን እንናዘዝ፡፡ ባደረግነው በደል ሰዎችም የሚነኩ ከሆነ ለእነርሱም እንናዘዝ፡፡ የማይታወቁ ኃጢአቶች

> አሁን ቀላል ወዳልሆነ ርእስ ገብተናል፡፡ ብዙ ጊዜ ሳይታወቀን ኃጢአት እንሠራለን፡፡ አንዳንድ ጊዜም በጎ የሠራን እየመሰለን እናጠፋለን፡፡ ያለማወቃችን ግን ንፁሐን አያደርገንም፡፡ ‹‹ማናቸውም ሰው ኃጢአት ቢሠራ እግዚአብሔርም አትሥሩ ካላቸው ትዕዛዛት አንዲቱን ቢተላለፍ ባያውቅም ያ ሰው በደለኛ ነው፡፡ ኃጢአቱንም ይሸከማል›› (ዘሌ5፡17)፤ ዳዊትም ‹‹ከተሰወረ ኃጢአት አንፃኝ›› (መዝ.19፡12) እያለ የጸለየው ለዚሁ ነበር፡፡

> እነዚህን ኃጢአቶች ተናዝዘን ከአባታችን ጋር የነበረንን ኅብረት ማስተካከል ከፈለግን በመጀመሪያ እነዚህን ኃጢአቶች ለይተን ልናውቃቸው ይገባል፡፡ ስለሆነም በዘሌዋውያን መጻሕፍት በተደጋጋሚ ‹‹ሰው ኃጢአት ቢሠራ ለእርሱም የሠራው ኃጢአትም ቢታወቀው›› የሚል ተጽፎ እናገኛለን፡፡ ታዲያ እንዴት አድርገን ነው ትክክል ነን እያልን ሳለን ሌላ ሰው የማያውቀውን ሐሳብ፣ ድርጊትና ንግግር ኃጢአት መሆኑን አውቀን የምንናዘዘው? እንዳልተሳሳትን እያሰብን ሳለን ስለተሰወረው ኃጢአታችን ማን ይወቅሰናል? የእግዚአብሔር ፍቅር ለዚህ ችግርም መውጫውን ሳይሰጠን አልተወንም፡፡ ቃሉ ‹‹ልጆች ሆይ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ፡፡ ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፤ እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው›› (1ዮሐ.2፡1) ይለናል፡፡ ይህንን ጥቅስ አንብበን የሚለንን ለመረዳት በጥሞና እንየው፡፡

ክርስቶስ ጠበቃችን

> የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት መጀመሪያ የተጻፉበትን የግሪክ ቋንቋ ስንመለከት በዚህ ጥቅስ ላይ በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ‹‹ጠበቃ›› ተብሎ የተተረጎመው በግሪኩ ‹‹ጰራቅሊጦስ›› ከሚለው ቃል መሆኑን እንረዳለን፡፡ ቃሉ የሚገኘውም በአዲስ ኪዳን በሦስት ስፍራ ብቻ ሲሆን ይኸውም በዚህ ጥቅስና በዮሐንስ ወንጌል በምዕራፍ 14 እና በ16 ላይ ነው፡፡ በዮሐንስ 14 እና 16 ላይ ስለመንፈስ ቅዱስ የሚናገር በመሆኑ በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ አጽናኝ ተብሎ ተተርጉሟል፡፡ ሰፋ ባለ መልኩ ግን የቃሉን ትርጉም ስናጠና የሌላውን ሰው ጉዳይ የራሱ አድርጎ ከዚያ ሰው ጎን በመቆም የሚረዳ፣ የሚያግዝ ማለት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በመሆኑም ጌታ ኢየሱስ አሁን በሰማይ ይህን ያደርግልናል፡፡ ይኸውም አገልግሎት የሚከናወነው ልጅነትን ባላገኙ ሰዎችና በእግዚአብሔር መካከል ላለ ጉዳይ ሳይሆን በአባታችንንና በእኛ በልጆቹ መካከል ላለ ጉዳይ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ልጅነት ያላገኙ ሰዎች ከዚህ አገልግሎቱ ተሳታፊነት የላቸውም፡፡ ከዚህ ደብዳቤ ቀደም ብሎ በሚገኘው ደብዳቤ ላይ ጌታችን በዚህ ምድር ላይ ሳለን ስላለብን ድካም ጸጋ ይበዛልንና እንበረታ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት አማላጃችን መሆኑን ተመልክተናል፤ እዚህ ላይ ደግሞ የተመለከትነው ጌታ ዕለት ዕለት የምንፈፅመውን ኃጢአታችንን በተመለከተ የሚያገለግለንን አገልግሎት ነው፡፡ እዚህ ላይ ‹‹ኃጢአት ብንሠራ ጌታ ኢየሱስ በአብ ዘንድ ጠበቃችን ነው›› ይላል፡፡ ጠበቃችን የሚሆንልን በድለን ኃጢአታችንን በተናዘዝን ጊዜ ብቻ አይደለም፤ ኃጢአት በሠራንባት ቅጽበት እርሱ እኛንና ጉዳያችንን ይዞ በአባታችን ዘንድ ሥራውን ይሠራል፡፡ ይህም ጠበቃ ጻድቅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱ ከአብ ጋር በጽድቅ በኩል ነው፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ ለእኛም ጽድቃችን ነው (1ቆሮ.1፡30) እርሱ ለእኛ ይህን ያህል ብቻ አይደለም፡፡ ቤዛነቱ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለዓለሙ ሁሉ ጭምር እንዲሆን ሊያደርገው የሚያሻውን ሥራ በመስቀል ላይ ፈፅሟል፡፡ ስለሆነም በአብ ፊት በሥራውም ሆነ በራሱ ማንነት ፍጹም ተቀባይነት አለው፡፡ ኃጢአት በሠራን ጊዜም በጠበቃነቱ እንዲሁ ፍጹም ተቀባይነት አለው፡፡

> ባለፈው ይቅርታ የሚገኘው ከንስሐ በኋላ ብቻ መሆኑን ተነጋግረናል፡፡ ስለዚህ ሌላው የጌታችን ኢየሱስ አገልግሎት ጠበቃችን በመሆን በማናውቃቸው ኃጢአቶቻችን በደላችንን አውቀን ወደ ንስሐ እንድንመጣ በእኛ ላይ መትጋቱ ነው፡፡

እግር ማጠብ

> ታስሮ በተወሰደባት ሌሊት ጌታ ይህንን የእግር እጥበትን አገልግሎት በምሳሌ አድርጎ አሳይቶአል፡፡ ይህን ያደረገው ሊያድናቸው የሞተላቸው አዳኙ ክርስቶስና የክርስቶስ አካል አባላት የሆኑት በሙሉ ከእርሱ ከክርስቶስ ጋር ስላላቸው ኅብረት ምልክት እንዲሆን (1ቆሮ10፡16-17) የቁርባን ሥርዓትን በመሠረተበት ወቅት ነበር፡፡ ኃጢአትን ለመደምሰስ በሚሞተው ጌታና በኃጢአት ባደፉ ደቀመዛሙርት መካከል ግን ይህ ኅብረት እንዴት ሊመሠርት ይችላል? በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉ ይህን ኅብረት ለመመሥረት ቢሞክሩ ደግሞ ውጤቱ ንጹሓን ባልሆኑት ላይ ፍርድን ማስከተል ነው (1ቆሮ.11፡26-30)፡፡

> ስለሆነም ጌታ ማንነቱን እያወቀ ነገር ግን ከፍቅሩ ፅናትና ታላቅነት የተነሳ የአገልጋይን ስፍራ ወስዶ የደቀመዛሙርቱን እግሮቻቸውን አጠበ፡፡ ጌታ የሚሠራው ሁሉ ትክክል እንደ ሆነ ጴጥሮስ ሳይገባው ሲቀር ‹‹አንተ አታጥበኝም›› በማለት ሲከራከር ይታያል፡፡ ጌታ የሚያደርገው ሁሉ ሁልጊዜ መልካም መሆኑን አውቀን እኛም እርሱ የሚለንን ሁሉ አሜን ብለን ልንቀበል ይገባናል፡፡ ይሁን እንጂ ጌታ የጴጥሮስን ግራ መጋባት በመጠቀም የእግር ማጠብን ትርጉም ሁሉም እንዲረዱት አደረገ፡፡ ደቀዛሙርቱ በዳግም ልደት ምክንያት ንፁሐን ነበሩ፡፡ ሆኖም ከእርሱ ጋር በኅብረት እንዲቀመጡ ከዕለታዊ የኃጢአት ቆሻሻ ንጹሓን መሆን አስፈልጓቸዋል (ዮሐ.13፡8-11)፡፡

የጴጥሮስ ክሕደት

> ጴጥሮስ በአንድ ወቅት ከጌታ ጋር ያለውን ኅብረት ያቋረጠበት ሰዓት ነበር፡፡ የሠራው ትልቅ ኃጢአት አልነበረም፡፡ ራሱም አላወቀውም፤ የነገረውም አልነበረም፡፡ ሁሉም እንደሚክዱት ጌታችን ሲናገር ጴጥሮስ ግን እንደሌሎቹ እንዳልሆነና ታማኝነቱና ፍቅሩ ከሌሎቹ እንደሚበልጥ በመገመት ‹‹ሁሉም በአንተ ቢሰናከሉ እኔ ከቶ አልሰናከልም›› አለው (ማቴ.26፡33) ከክርስቶስ ጋር እውነተኛ ኅብረት ኖሮት ቢሆን ጴጥሮስ ይህንን ባላለም ነበር፤ ምክንያቱም በትክክለኛ ኅብረት ውስጥ ካለ ሥጋና ትዕቢት ስፍራ አይኖራቸውም ነበርና ነው፡፡

> ኢየሱስ ሁሉም እንደሚሰነካከሉ የተናገረውም ጴጥሮስን ማስጠንቀቅና ሁሉንም ነገር እንደሚያውቅ ለማስረዳት ነበር፡፡ ከካደው በኋላ ጴጥሮስ ይህንን ማስተዋል አለበት፡፡ ኢየሱስ አስቀድሞ ይህንን እያወቀ በደቀመዛሙርቱ ላይ ምንም ቅሬታ እንዳላደረበት አስታውሶ ሊጽናና ይገባል፡፡

> እንዴት ያለ ጸጋ እንዴት ያለ ፍቅር ነው፡፡ ጴጥሮስ ኃጢአት ውስጥ ሳይገባ ክርስቶስ ይጸልይለት ነበር፡፡ ሰይጣን እንዳይፈትነው ግን አልነበረም፡፡ ጴጥሮስ ማንነቱን እንዲያውቅ በዚህ ሁኔታ እንዲያልፍና የራሱን ማንነት እንዲያውቅ መደረጉ አስፈላጊ ነበርና፡፡ ኢየሱስ በፍቅር የተናገረው ግቡን አልመታም፡፡ ሁሉም እንደሚሰነካከሉ በግልፅ ሲነገረው ጴጥሮስ ራሱን በወቅቱ መመርመር ይችል ነበር፡፡ ግን ወደ ሌላ ሐሳብ ተሻግሮ እኔ እንደዚህ ነኝ ይል ጀመር፡፡ ስለዚህ ጌታ የጸለየው ጴጥሮስ እንዳይፈተን ሳየሆን ‹‹እምነቱ እንዳይጠፋ›› ነበር፡፡

> ጴጥሮስ ልብ ብሎ ያስተዋለው ነገር አልነበረም፡፡ ጌቴሰማኒ ሄደው ሲጸልዩም ጴጥሮስን አንዲት ሰዓት ስንኳ ልትተጉ አልቻላችሁም (ማቴ.26፡40) ብሎ ቢናገረውም ጸሎት የሚያስፈልግበት ሰዓት ነው ብሎ ከመጠንቀቅ ይልቅ እንደገና ተኛ፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላም እንደሌሎቹ ጌታን ጥሎ ሸሸ (ማቴ.26፡56) ‹‹አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ›› ብሎ የመሰከረለት ጴጥሮስ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ አላውቀውም እያለ ሦስት ጊዜ ሲክድ ተሰምቶአል፡፡ ከዚያን በኋላ እንኳን ጌታ እስኪያየው ድረስ ጴጥሮስ ባደረገው ነገር አልተፀፀተም፡፡ አቤት የሰው ልጅ ልብ ምንኛ አስቸጋሪ ነው! አገልጋዮቹ በጥፊ ሲመቱት ሲተፉበት እና ሲያፌዙበት ጌታ ዘወር ብሎ ጴጥሮስን አየው፡፡ የተናገረውንም ነገር በዶሮው ጩኸት አስታወሰው፡፡ ጌታ ጴጥሮስን ዘወር ብሎ ያየበት የፍቅር እይታና የዶሮው ጩኸት የጴጥሮስ ዓይኖች እንዲከፈቱ አደረጉ፡፡ ወደ ውጭም ወጥቶ መራራ ልቅሶ አለቀሰ፡፡

መስተካከል (መቃናት)

> ጌታ ለጴጥሮስ ያለውን አገልግሎት በዚህ አላበቃም፤ ከትንሣኤው በኋላ መጀመሪያ ያደረገው ነገር ቢኖር በተለይ የጴጥሮስን ስም በመጥቀስ የትንሣኤውን ዜና መልእክት ወደ ጴጥሮስ መላክ ነበር፤(ማር.16፡7) ከዚህ መልዕክት በኋላም ለእርሱ ለብቻው እንደታየው ተገልጧል (ሉቃ.24፡34) ምን እንደተነጋገሩ ግን አልተገለፀልንም፡፡ ጌታ የእርሱ ለሆኑት ለእያንዳንዳቸው የሚሆን ልዩ ቃል አለው፡፡ ነገር ግን ሁሉም በተሰበሰቡበት አንድ ቀን ከጴጥሮስ ጋር እንደተነጋገሩ የጴጥሮስም ልብ እንደተነካ የሚገልፅ በዮሐንስ 21 እናገኛለን፡፡

> ጴጥሮስ እስኪያዝን ድረስ ጌታ ደጋግሞ ‹‹ትወደኛለህን?›› እያለ ለምን መጠየቅ አስፈለገው? ጴጥሮስ ተፀፅቶ አልቅሶ የለም ወይ? እንል ይሆናል፡፡

> ክርስቶስ የሰውን ልብ በፍጹም እውቀት ያውቀዋል፡፡ የራሱ የሆኑትንም በፍጹም ፍቅር ይወዳቸዋል፡፡ ፍጹም በሆነችው ጥበቡም ለጴጥሮስ የሚሻለውን ያውቃል፡፡ ጴጥሮስ ሥራውንና ድክመቱን በደንብ በመገንዘብ በእርሱ ውስጥ የጌታ ፍቅር እንዳለች ለማወቅ ሁሉን አዋቂ በሆነው በእግዚአብሔር መመርመር እንዳስፈለገው በማስተዋል የራሱን ምንነት ካወቀ በኋላ እግዚአብሔርም ሕይወቱን ሙሉ በሙሉ አስተካክሎለታል፤ በጎቹን እንዲጠብቅ ጠቦቶቹንም እንዲመግብ አደራ ሰጥቶታል፡፡

> ይህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአብ ዘንድ ለእኛ በጠበቃነት የሚያገለግለው አገልግሎት ነው፡፡ እርሱ ጠበቃችን ባይሆንልን ኖሮ የት ነበርን? እያንዳንዱ በሐሳብ የምንሠራው ኃጢአት የምንናገረው የስንፍና ቃልና በራሳችን ተመክተን የምንሠራው ሥራ ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረንን ኅብረት ያበላሽብናል፡፡ ይህም ኅብረት የሚቃናው በራሳችን ላይ በመፍረድና በመናዘዝ ብቻ ነው፡፡

> ጠበቃዬም ኃጢአት ከመሥራቴ አስቀድሞ እምነቴ እንዳይጠፋ ይጸልይልኛል፡፡ ቅንጣት ኃጢአት ከመሥራቴ በፊት በቃሉ ይነግረኛል፤ ራሴን እንድመረምርም ያደርገኛል፡፡ በተገቢው ሰዓት ወደ እኔ ያያል፤ የሚናገሩኝ ወንድሞች፣ መጻሕፍትና ሁኔታዎች ካስፈለገም አውራ ዶሮ ተጠቅሞ ቃሉን ያስታውሰኛል፡፡ በዚህም ከአብና ከወልድ ጋር ያለኝ ኅብረት ይቃና ዘንድ እኔው በራሴ ላይ በመፍረድ እንድናዘዝ ያደርገኛል፡፡ እርሱ በአብ ዘንድ ደጋፊዬ እና ጠበቃዬ ነው፡፡ ተስተካክዬ እስክቆም፣ ሙሉ በሙሉ ወደነበረኝ ኅብረት እስክመለስ ድረስ አያርፍም፡፡ አሁንም እንኳ በላይ በክብር ባለበት ጊዜ ከእርሱ ዘንድ ድርሻ እንዲኖረኝና ደስታዬም በዚህ ምድር ላይ ፍጹም እንዲሆን እግሬን ያጥባል፤ ያገለግለኛልም፡፡

> ከሰላምታ ጋር
የእናንተው ወንድም

ምዕራፍ 11 መቀደስ

ውድ ወገኖቼ

ደስ እያለኝ ስለ መቀደስ ልጽፍላችሁ እወዳለሁ፡፡ ወደ ሃሳቡ ከመግባታችን በፊት ይህ አባባል በእግዚአብሔር ቃል አገላለፅ ምን ትርጉም እንደሚሰጥ እንመልከት፡፡ በተራ ቋንቋ ጻድቅ ሰው ማለት ኃጢአት ወይም እንከን የሌለው ሰው ወይም ቢያንስ ቢያንስ የታወቀ ኃጢአት የሌለው ሰው ማለት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በቅድስና ትምህርት የተሳሳቱ አማኞች አንዳንድ ጊዜ ቅድስናዬን እያሻሻልኩ ነው፤ የማውቀውን ኃጢአት መሥራትን አቁሜአለሁ ሲሉ ይሰማል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ መልኩ ጳውሎስ ‹‹በራሴ እንኳ አልፈርድም በራሴ ላይ ምንም አላውቅም ነገር ግን በዚህ አልጸድቅም›› (1ቆሮ.4፡4) ይላል፡፡ ዳዊት ደግሞ በበኩሉ ‹‹ከተሰወረ ኃጢአት አንጻኝ›› (መዝ.19፡12) እያለ ሲጸልይ ይታያል፡፡ እንደዚሁም 1ዮሐ.3፡20 እና ኦሪት ዘሌዋውያን ምዕራፍ 5ን ተመልከት፡፡ ጌታችን ሲመለስ ደግሞ በጨለማ የተሰወረውን ወደ ብርሃን ያወጣል፤ የልብን ምክር ይገልጣል፤ ለእያንዳንዱ ምስጋናው ከእግዚአብሔር ዘንድ ይሆናል (1ቆሮ4፡5) ስለዚህ በውስጣችን የምናውቀው ስህተት የለም ማለት በእርግጥ አንዳች ጉድለት እንደሌለብን ማረጋገጫ አይሆንም፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ብርሃን ውስጥ ራሱን በእግዚአብሔር ቃል መርምሮ በውስጡ ብዙ ስህተቶችን የማያይ ማን ነው?፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ንፅሕናና ቅድስና የተለያዩ መሆናቸውን ቅዱሳት መጻሕፍት ያሳዩናል፡፡ ዘጸ.28፡38ን ስንመለከት የእስራኤል ልጆች በሚያቀርቡትና በሚቀድሱት ቅዱስ ስጦታቸው ሁሉ ላይ ያለውን ኃጢአት አሮን ይሸከም በማለቱ በተቀደሰው ቅዱስ ነገር ላይ ኃጢአት ሊኖር እንደሚችል እንመለከታለን፡፡ በሌላ ቦታ ደግሞ ቅዱሱን ዕቃ ማንፃት እንዳስፈለገ ይታያል፡፡ 1ዜና.23፡28፣ ኤፌ1፡4 እና ቆላ.1፡22 ስንመለከት ደግሞ ቅዱሳንና ነውር የሌለን መሆን እንዳለብን ያሳያል፡፡ በዚህ ሁሉ ቅድስናና ንጽሕና የተለያዩ ሁለት ነገሮች መሆናቸውን እንረዳለን፡፡

ቅድስና ምንድን ነው?

ስለ ቅድስናና ስለ መቀደስ በእግዚአብሔር ቃል የምናገኘውን ሐሳብ ብንወስድ መቀደስ ማለት መለየት ማለት እንደሆነ እንረዳለን፡፡

ለእግዚአብሔር በመሰጠት ቀደም ሲል ከነበርንበት ክፉ ዓለም መለየት እኛን የሚመለከት ሐሳብ ነው፡፡ እንደዚሁም ደግሞ ከመለየት ጋር በተስማማ ባሕርይ እየተመላለስን ለእግዚአብሔር መሰጠታችንን የሚያሳይ አካሄድ ማንፀባረቅ ይጠበቅብናል፡፡ ስለናዝራዊነት የተፃፈውን በዘኁል.6፡1-11 ተመልከት፡፡

የቅድስና መለኪያው በእኛ ዘንድ አይደለም፤ ስለ እግዚአብሔር ግን መጻሕፍት ‹‹እንደ እግዚአብሔር ቅዱስ የለምና ... ከአንተ በቀር ቅዱስ የለም››(1ሳሙ.2፡2) ይላሉ፡፡ እንደዚሁም ‹‹አንተ ብቻ ቅዱስ ነህና›› ተብሎለታል (ራእ.15፡4) እኛን በተመለከተ ደግሞ እግዚአብሔር ‹‹እኔ ቅዱስ እንደሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ››(1ጴጥ.1፡16) ይለናል፡፡ የቅድስና መለኪያ እርሱ እግዚአብሔር ለራሱ እንጂ ሰው ሊሆን እንደማይችል በዚህ እንረዳለን፡፡ መጽሐፍ ራሳቸውን ከሚያመሰግኑ ከአንዳንዶቹ ጋር ራሳችንን ልንቆጥር ወይም ራሳችንን ልናስተያይ አንደፍርም፤ ነገር ግን እነርሱ ራሳቸውን ከራሳቸው ጋር ሲያመዛዝኑ ራሳቸውን ከራሳቸው ጋር ሲያስተያዩ አያስተውሉም(2ቆሮ10፡12) እንደሚል ራሱን ከራሱ ጋር በማነፃፀር ራሱን የሚፈትን ሰው ግን ሞኝ ነው፡፡ በመሆኑም ምንም ያህል እንኳን ቅድስናችን ከፍ ቢልም የቅድስናችንን ደረጃ ሊመዝንና ሊለካ የተገባው እግዚአብሔር ብቻ መሆኑ ግልጥ ነው፡፡

ጌታችን ‹‹በእውነትህ ቀድሳቸው ቃልህ እውነት ነው›› (ዮሐ.17፡17) ብሎ እንደጸለየ በወንጌል እናነባለን፡፡ እውነት እግዚአብሔር ራሱን የገለጠበትና እኛም ከእርሱ ጋር ያለንንና ሊኖረን የሚገባን ዝምድና ነው፡፡ ለዚህም ነው ኢየሱስ እርሱ እውነት እንደሆነ የገለፀው (ዮሐ.14፡6) እግዚአብሔርን ያየ የለም እርሱ ኢየሱስ ግን ተረከው (ዮሐ.1፡18) እግዚአብሔርም ራሱን የገለጠበት ቃሉ እውነት ነው፡፡

እግዚአብሔር ስለራሱ ራሱን በገለፀበትና ከሰው የሚጠብቀውን ነገር በተናገረበት እውነት በመጠቀም ሰው አስቀድሞ ከነበረበት ነገር ተላቅቆ ለእግዚአብሔር ይለያል፡፡

በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር በሙላት ማን እንደሆነ ተገልጦ አይታይም፡፡ ነገር ግን ራሱ በመረጣቸው ሕዝቦቹ መካከል ማደሪያ መቅደሱን በማድረግ በመካከላቸው የተገለጠ ያህዌህ እንደሆነ ይታወቅ ነበር፡፡ በብሉይ ኪዳን ውስጥም የነበረው ቅድስናም ከዚሁ መገለጥ ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ ተራራው፣ ከተማው፣ ድንኳኑ፣ ቤተመቅደሱ፣ ካህናቱ፣ ሌዋውያኑ፣ መላው ሕዝቡ፣ የአገልግሎት ንዋያተ ቅድሳቱና መሥዋዕቶቹ ወዘተ ሁሉም የተቀደሱ ነበሩ፡፡ ማናቸውም ነገሮች ሁሉ በሕዝቡ መካከል ካደረው ከያህዌ ጋር የተያያዙ ነበሩ፡፡ እግዚአብሔርም ወደ እርሱ በሚቀርቡ ነገሮች ይቀደስ ነበር፤(ዮሐ.1፡18) ስለሆነም መዝሙረኛው ‹‹እስከ ረጅም ዘመን ድረስ ለቤትህ ቅድስና›› ይገባል በማለት ተናገረ (መዝ.92(93)፡5)፡፡

አሁን ግን እግዚአብሔር በሥጋ በተገለጠ አምላክ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጧል፡፡ ኢየሱስ ፍጹም ሰው ሆኖ በምድር ላይ ሲያገለግል ቢታይም የአገልግሎቱ ጠባይ እግዚአብሔርን መግለጥ ነበር፡፡ በመስቀል ላይ አምላክነትን ከገለጠና ዘላለማዊ ቤዛነትንም ካስገኘ በኋላ ከሙታን መካከል ተለይቶ በመነሳት በእግዚአብሔር አብ ቀኝ ተቀመጠ፡ ፡

በዮሐ.17፡4-5 እንደምናነበውም ጌታ ዓለም ሳይፈጠር በዘላለማዊ ክብር ከአብ ጋር እንደነበረና በኋላም ደግሞ በጎልጎታ የማዳን ሥራውን አከናውኖ አብን በፍጹም በማክበሩ አብ እርሱን አሁን ሥጋ በመልበስ በተገለጠበት ሰውነቱ በቀደመ ክብሩ እንዲያከብረው ሲጠይቅ ይታያል፡፡ አሁንም በአብ ቀኝ የተቀመጠው በወልድነቱ ሥጋውን እንደለበሰ በሰማይ የሚኖር ሰው ሆኖ ነው፡፡

እርሱ በብዙ ወንድሞች መካከል በኩር ይሆን ዘንድ እኛ የልጁን መልክ እንድንመስል የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ዕቅዱ ነበር (ሮሜ.8፡29) እዚህ በዮሐ.17፡17-19 ደግሞ የእርሱ የራሱ የሆኑትን ሰዎች ራሱ ጌታ እንደሚቀድሳቸው ይናገራል፡፡ እርሱ በራሱ ራሱን ለእግዚአብሔር በሰማይ በመለየት የእርሱ የሆኑትን በእውነት እንዲቀደሱ አድርጓል፡፡ እዚህ ላይ እውነተኛውን የቅድስናችንን መስፈርትና መቀደስ የምንችልበትንም መንገድ ከዚህ መረዳት እንችላለን፡፡ ይኸውም የከበረው ክርስቶስ ነው፡፡

በመንፈስ መቀደስ

በአዲስ ኪዳን እንደምናነበው መቀደሳችን በሁለት መንገድ ነው፡፡ መጻሕፍት መቀደሳችንን በግልጥ ይነግሩናል (1ቆሮ.6፡11፣2ተሰ.2፡13፣ 1ጴጥ.1፡2) ስለዚህም በተለያየ ቦታ ቅዱሳን ተብለን ስንጠራ ይነበባል፡፡ ለምሳሌ ያህል በመልዕክታት መክፈቻ ላይ ቅዱሳን የሚል ቃል ተደጋግሞ ተጽፎ ይገኛል፡፡ ይህም መቀደስ በአዲስ ልደት የተገኘ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስም እኛን ከነበርንበት ዓለም በመለየት ለአዲስ ልደት የተስማማ የቅድስና ባሕርይ ሰጠን (ዮሐ.3፡3-8፣ 2ጴጥ.1፡4፣ ኤፌ.4፡24)፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በመንፈስ መቀደስ እንዳለብን ሁሉ በተግባር መቀደስ እንዳለብን ተነግሯል (ዕብ.12፡14፣ ኤፌ.5፡25-27) ሁለቱ ነጥቦች ደግሞ በራእ.22፡11 ‹‹ቅዱሱም ወደፊት ይቀደስ›› በሚል ሐሳብ መዋሐዳቸውን እንረዳለን፡፡ ይህን መመሪያ በብዙ የእግዚአብሔር ቃል ምንባቦች ላይ እናገኛለን፡፡ በሮሜ.8፡29 እንዳየነው የልጁን መልክ እንድንመስል እግዚአብሔር አስቀድሞ ወስኗል፡፡

1ቆሮ.15፡49 ‹‹የዚያንም የመሬታዊውን(የአዳምን) መልክ እንደለበስን የሰማያዊውን(የጌታ ኢየሱስን) መልክ ደግሞ እንለብሳለን›› ሲል 1ዮሐ.3፡2 ደግሞ ይህ ነገር ሲፈፀም የሚሆነውን ሲናገር ‹‹ቢገለጥ እርሱን እንዳለ እናየዋለንና እርሱን እንድንመስል እናውቃለን›› ይላል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በሌሎች የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍሎች እንደምናየው ከጌታ ኢየሱስ ጋር ተገልጠናል፡፡ በ1ዮሐ3፡1 ‹‹ዓለም እርሱን ስለማያውቀው እኛንም አያውቀንም›› ተብሎ እናገኛለን፡፡ በ1ዮሐ4፡17 ደግሞ ‹‹እርሱ አሁን በክብር እንዳለ እኛ ደግሞ አሁን በዚህ ዓለም ነን›› የሚል እናነባለን፡፡

ለዚህም ምክንያት ሊሆን የሚችለው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ነው፡፡ የተሰጠንን ስፍራ በተመለከተ ሁሉም ነገር አሁን በክርስቶስ እንደተደረገልን እናስተውላለን (1ቆሮ.1፡30) በዳግም ልደት ከዓለም ተለይተን ዘላለማዊ ሕይወት አለን፡፡ በአንድ መሥዋዕትም ፍጹማን ሆነን በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ሆነን ቆመናል፡፡ የእግዚአብሔር ልጆችና የመንግሥቱ ወራሾች በመሆናችን በሰማያዊው ስፍራ ከክርስቶስ ጋር ነን (ኤፌ.2፡6) ነፍሳችን የምትፈልገው ነገር ሁሉ አለን፡፡ ሥጋችን ግን ሁሉንም ነገር አላገኘም፤ አሮጌው ሰውም ገና አሁንም አለ፡፡ ስለሆነም በዕለታዊ ተግባራችን በጌታችን ኢየሱስ ሥራ እንደደረስንበት ሁኔታ መሆን አልቻልንም፡፡

በተግባር መቀደስ

ተግሣጽና ምክር ሁሉ በዚህ ተግባራዊ ቅድስና አስፈላጊነት የተሞሉ ናቸው፡፡ የአገልግሎቶችም ሁሉ ዋና ዓላማ ደግሞ ይህ ነው፡፡ በተለይም አሁን ወደፊት አንድ ቀን የምንሆነውን መገንዘብ ይኖርብናል (ኤፌ.4፡11-16፣ ቆላ.1፡28) ወደፊት ማንን እንመስላለን? በሰማያት ከብሮ የተቀመጠውን ወልድን እንመስላለን፡፡ እርሱም ደግሞ ለዕለታዊ አካሄዳችን ትክክለኛነት ዋንኛ የመመዘኛ ቱምቢ ነው፡፡ ‹‹በእርሱም ይህን ተስፋ የሚያደርግ ሁሉ እርሱ ንጹሕ እንደ ሆነ ራሱን ያነፃል›› (1ዮሐ.3፡3)

በተግባር እርሱን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው? የተለወጠና የተቀደሰ ሕይወት እንዲኖረን መጣርና መልፋት ይኖርብን ይሆንን? ይህ የሚቻል ቢሆን ‹‹እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ? ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል? (ሮሜ.7፡24) ተብሎም ባልተጻፈ ነበር፡፡ በጥረታችን ሳይሆን የተሻለ መንገድ እንዳለ የእግዚአብሔር ቃል ይነግረናል፡፡ ‹‹እኛም ሁላችን በመጋረጃ በማይከደን ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያብለጨለጭን መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ ያን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን፡፡››(2ቆሮ.3፡18) ጌታችንን አሁን በክብር ባለበት በማየት፣ ስለ እርሱ የተጻፈውን ቃሉን በሙሉ በማንበብና በማሰላሰል ሕይወታችን ይለወጣል፡፡ ከዚያም በሥነ ምግባራችን የእርሱን መልክ እየወሰድን እንሄዳለን፡፡ ልባችን የናፈቀው ነገር ሁሉ ከቶውን በሕይወታችን ሳይቀረፅ አያልፍም፡፡

መቀደስም እንደዚሁ ነው፡፡ የመቀደሳችንም መስፈርት ጣሪያው አንድ ቀን ወደ እርሱ ወደ ከበረው ጌታ ኢየሱስ መልክ መለወጥ ነው፡፡ እርሱን መመልከትም ይህንን ቅድስና ያስገኝልናል፡፡ ቅድስናም ከነሙሉ ጠባዩና ከነባሕርይው ክርስቶስ በእኛ ውስጥ ሲገለጥ በሕይወታችን ይገለጣል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ‹‹እነርሱም ደግሞ በእውነት የተቀደሱ እንዲሆኑ እኔ ራሴን ስለ እነርሱ እቀድሳለሁ (ዮሐ.17፡17-19) ያለውም ስለዚሁ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ ‹‹ቅዱስና ያለ ተንኮል፣ ነውርም የሌለበት፣ ከኃጢአተኞችም የተለየ፣ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ›› (ዕብ.7፡26) ሆኖ በለበሰው ሥጋ ማለትም በሰውነቱ በክብር በግርማ በእግዚአብሔር ዙፋን ተቀምጧል፡፡ ይህንንም እውነት የእግዚአብሔር ቃል ይገልጽልናል፡፡ ቃሉም የጌትነቱን ታላቅነት ያሳየናል፡፡ ስለእርሱ የሚናገረውን የእግዚአብሔር ቃል ስናውቅም የክርስቶስ ፍጹምነትና ከእርሱ ጋር የተያያዘው በሙሉ ልባችንን ይሞላል፡፡ ያን ጊዜም ልባችን ለዓለምና ለዓለም ነገሮች ስፍራ አይኖረውም፡፡ የዓለምን ነገር እየተውንም በሥነ ምግባር እርሱን እየመሰልን ከምድራዊ ነገሮች ርቀን ለእግዚአብሔር ብቻ እንሰጣለን ወይንም እንለያለን፡፡ ይህም መቀደስ ማለት ነው፡፡

ይህም እንዲሆንልን በእግዚአብሔር ታማኝነት ላይ እንታመናለን፡፡ ‹‹ሳትሰናከሉም እንዲጠብቃችሁ ከክብሩም ፊት በደስታ ነውር የሌላችሁ አድርጎ እንዲያቆማችሁ ለሚችለው ብቻውን ለሆነ አምላክና መድኃኒታችን ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘላለም ድረስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ግርማ ኃይልም ሥልጣንም ይሁን አሜን›› (ይሁ.24-25)፡፡

ከሰላምታ ጋር
የናንተው ወንድም

ምዕራፍ 12 የእግዚአብሔርን ቃል የማንበብ ጥቅም

ውድ ወገኖቼ

መጽሐፍ ቅዱሳችሁን በማዘውተር ታነቡ እንደሆነ ልጠይቃችሁ እወዳለሁ፡፡ ቤተሰብ በገበታ ሲሰበሰብ ወይም በተለምዶ እንደሚደረግ ማለቴ ሳይሆን ለራሳችሁ ብላችሁ ብቻችሁን ስትሆኑ ታነቡ እንደሆነ ልጠይቅ ፈልጌ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ማዘውተሩ ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡ አማኝ የእግዚአብሔርን ቃል የማያነብ ከሆነ ከእግዚአብሔር ጋር የቅርብ ኅብረት አይኖረውም፤ ደስታውም የተሟላ አይሆንም፡፡

እንደዚህ ማለታችንም የመጽሐፍ ቅዱስን ጥቅም ማጋነን አይሆንም፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቃል ስለሆነና እግዚአብሔርንና ሐሳቡንም ማወቅ የምንችለው ደግሞ በቃሉ ብቻ ስለሆነ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን እግዚአብሔር በቃሉ ራሱን ገለጠ፤ ቃሉንም እንዲጻፍ አደረገው፡፡ በዚህ ቃሉም ማንነቱን ገለጠ፡፡ ያደረገውን፣ ሊያደርገው ያለውንና ሰው እንዴት ሊያገለግለው እንደሚገባም በቃሉ ተናገረ፡፡ ከዚያም ወልድ ወደ ምድር መጣና እግዚአብሔርን ተረከው (ዮሐ.1፡18) እንደዚሁም ስለወልድ ሕይወት ማለትም ስለ ልደቱ፣ ኑሮውና ሞቱ ስለ ተናገረውና ስለ ሥራውም ማወቅ የምንችለው በቃሉ ብቻ ነው፡፡ አሁን በምድር ላይ በአማንያን የሚያድር እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም በቃሉ በኩል ሁሉን ነገር ይገልጽልናል፡፡

ስለሆነም መጽሐፍ ቅዱስን የማይወድ አማኝ ካለ አሳዛኝ ነው፡፡ በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና እውቀት ማደግም ለቃሉ ካለን ፍቅርና ከቃሉ አጠቃቀም ጋር የተያያዘ ነው፡፡

አዲሱ ልደት- በእግዚአብሔር ቃል

ለምሳሌ መዝ.119ን ስንመለከት የዘማሪው እያንዳንዱ መንፈሳዊ ደረጃ ከቃሉ ጋር የተያያዘ ሆኖ እናገኛለን፡፡ በዚሁ መዝሙር ቁ.93ን ስናይ ‹‹በእርሱ ሕያው አድርገኸኛልና ፍርድህን ለዘላለም አልረሳም›› በማለት አዲሱ ሕይወት ከቃሉ እንደሚገኝ ይናገራል፡፡ እንደዚሁም በሌሎች ቁጥሮች ማለትም ቁጥር 25፣ 37፣ 41፣ 50፣ 88፣ 107፣ 116፣ 144፣ 149፣ 154፣ 156፣ 159 እና 175ን መመልከት ይቻላል፡፡ ይህ ሐሳብ በሌሎች በርካታ ምንባቦችም በግልጥ ይገኛል፡፡ ስለሆነም ‹‹ለፍጥረቱ የበኩራት ዓይነት እንሆን ዘንድ በእውነት ቃል አስቦ ወለደን›› (ያዕ.1፡18) የሚል እናያለን፡፡ በሌላ ስፍራም ‹‹ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፤ በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ›› (1ጴጥ.1፡23) ይላል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ‹‹ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም››(ዮሐ.3፡5) በማለት ተናግሯል፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደምናየው ውኃ በመንፈስ ቅዱስ በሰው ውስጥ ለሚሠራ የእግዚአብሔር ቃል ምሳሌ ነው (ኤፌ.5፡26)፡፡

የእግዚአብሔር ቃል የኃጢአተኛን ሰው ኅሊና ወደ እግዚአብሔር ብርሃን እንዲመጣ ያደርገዋል፡፡ በዚህም ሰው ማን መሆኑን አይቶ ራሱን ያወግዛል፤ ወደ እግዚአብሔርም ይናዘዛል፤ ይህም መለወጥ ማለት ነው፡፡ ራስን መመርመርና በራስ መፍረድም የሰውን ልብ ያነፃል፤ መንፈስ ቅዱስም በቃሉ በኩል አዲስ ሕይወትን በሰውዬው ውስጥ ይሠራል፡፡

ስለዚህ ለማያምኑት ሰዎች ወንጌልን ስንነግር የእግዚአብሔርን ቃል ማወቅ አለብን፡፡ የራሳችን ቃል ሰውን ወደ እምነት ሊያመጣ አይችልም፡፡ ሰውን መለወጥ የሚችለው የእግዚአብሔር ቃል ብቻ ነው፡፡ ‹‹እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡›› (ሮሜ.10፡17)፡፡

የአዲሱ ሕይወት ምግብ

በተጨማሪም መዝሙረኛው ስለ እግዚአብሔር ቃል ሲናገር ‹‹ቃልህ ለጉሮሮዬ ጣፋጭ ነው ከማርና ከወለላ ይልቅ ለአፌ ጣፈጠኝ፤››(መዝ.119፡103) ‹‹ከማርና ከማር ወለላም ይጣፍጣል››(መዝ.19፡10) በማለት የቃሉን ጣፋጭነትና ምግብነት በማድነቅ ተናግሯል፡፡ ይህም ጣፋጭ ምግብ ደግሞ ለአዲስ ሕይወት ምግብ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስም ሰው ‹‹ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም›› በማለት ቃሉ በሕይወት የምንኖርበት ምግብ እንደሆነ ተናግሯል (ማቴ.4፡4፣ ዕብ.5፡12-14፣ 1ጴጥ1፡25-2፡2)፡፡

በቃሉ የተገኘው አዲሱ ሕይወታችን የሚስማማውን ምግብ ማግኘት አለበት፡፡ ይህም ምግብ አዳኛችንና የሞተልን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤(ዮሐ.6፡56) እርሱ በምድር ቅዱስ ሰው ሆኖ የተመላለሰና በሰማይ ደግሞ የከበረ ጌታ ሆኖ የተቀመጠ የአማኞች ምግብ ነው፡፡ እርሱ የምድረ በዳውን መና የተካ፣ የከነዓን የምድር ፍሬ፣ እንደዚሁም ለአማኞች የዘወትር መብል የሆነ ከሰማይ የወረደ አማናዊ መና ነው (ኢያ.5፡11-13) ይህንንም ምግብ የምናገኘው በቃሉ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ጌታ በብሉይ ኪዳን በጥላዎችና በምሳሌዎች እየሆነ በትንቢቶች እና በነቢያት ይታያል፡፡ በአዲስ ኪዳን ደግሞ በሕይወቱ በሞቱና በክብሩ ከወንጌላት እስከ ራእይ በተጻፈው ይታያል፡፡

ታዲያ ብዙዎች መንፈሳዊ ሕይወታቸው ደክሞ አቅመቢስ ሆነው ጠንካራ ምግብ መውሰድ ተስኖአቸው ወተት ብቻ የሚያስፈልጋቸው (ዕብ.5፡12-14) ወደ ጉባኤ ስለማይመጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስለማይከታተሉ ራሳቸውም ቃሉን ስለማያነቡ አይደለምን?

ልናድግና ጤናማ የሆነ መንፈሳዊ ሕይወት ሊኖረን የሚችለው ዕለት ዕለት ያለማቋረጥ ቃሉን ስንመገብ ብቻ ነው፡፡

የእግዚአብሔር ቃል መሪያችን ነው

መዝሙረኛው በመዝ.119፡9 ‹‹ጎልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል? ቃልህን በመጠበቅ ነው›› ይላል፡፡ ወረድ ብሎም በቊጥር 11 ላይ ‹‹አንተን እንዳልበድል ቃልህን በልቤ ሰወርሁ›› ሲል በቁ.105 ላይ ደግሞ ‹‹ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴ ብርሃን ነው›› ይላል፡፡

እግዚአብሔር ለኢያሱ እንደዚህ አለው ‹‹ነገር ግን ጽና እጅግ በርታ ባሪያዬ ሙሴ ያዘዘህን ሕግ ሁሉ ጠብቅ አድርገውም፤ በምትሄድበትም ሁሉ እንዲከናወንልህ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል፡፡ የዚህ ሕግ መጸሐፍ ከአፍህ አይለይ፡፡ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው፡፡ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም›› (ኢያ.1፡7-8)፡፡

አስቸጋሪ ሁኔታ በነበረበት ጊዜ ጳውሎስ ለኤፌሶን ሽማግሌዎች ‹‹ለጸጋው ቃል አደራ ሰጥቻችኋለሁ›› (ሐዋ.20፡32) ሲል ለጢሞቴዎስ ደግሞ ‹‹መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳት መጻሕፍትን አውቀሃል›› (2ጢሞ.3፡15) ይለዋል፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል የማናውቅ ከሆነ ኃጢአት ምን መሆኑን እንዴት እናውቃለን? ነገር ግን አለማወቃችን ነፃ ሊያወጣን አይችልም (ዘሌ.5፡17) እግዚአብሔር ስለሁሉም ነገር የተናገረበትን ቃሉን ካላጠናን ማድረግ የሚገባንንና እንደ እግዚአብሔር ሐሳብ የሆነውንስ እንዴት ልናውቅ እንችላለን? ቃሉን የማናውቅ ከሆንን አንዳንድ አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች እንዴት ልንወሰንና የምንሄድበትንም መንገድ እንዴት ልንመርጥ እንችላለን?

‹‹ትእዛዝህ ከጠላቶቼ ይልቅ አስተዋይ አደረገኝ፡፡ ምስክርህ ትዝታዬ ነውና ካስተማሩኝ ሁሉ ይልቅ አስተዋልሁ፡፡ ትእዛዝህን ፈልጌአለሁና ከሽማግሌዎች ይልቅ አስተዋልሁ፡፡ ... የቃልህ ፍቺ ያበራል ሕፃናትንም አስተዋዮች ያደርጋል፡፡›› (መዝ.119፡98-100፣130)

ቃሉ የጦር ዕቃችን ነው

‹‹የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ፤ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡›› (ኤፌ.6፡17) ‹‹በቃልህ ታምኛለሁና ለሚሰድቡኝ በነገር እመልስላቸዋለሁ፡፡››(መዝ.119፡42)

ይህን ሰይፍ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዴት እንደተጠቀመበት እንመልከት፡፡ ከሰይጣን የሚመጣበትን ጥያቄ ሁሉ ተጽፎአል እያለ ይመክት ነበር (ማቴ.4፡4፣7፣10) ውጤቱም ሰይጣንን እንዲሸሽ አስገድዶታል፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔርን ቃል መቋቋም የሚችል ኃይል አልነበረውምና ነው፡፡

ጌታችን ቃሉን በቀጥታ ሰይጣንን ለማሸነፍ ብቻ ሳይሆን የሰዎችንም ሐሳብ ለማክሸፍ ተጠቅሞበታል፤ በሉቃስ 20፡17 ለሚያስተምራቸው ሕዝብ ‹‹... ተብሎ የተጻፈው ይህ ምንድር ነው?›› ብሎ ሲያሳስብ ይታያል፡፡ በዮሐ.10፡34 ደግሞ ‹‹... ተብሎ በሕጋችሁ የተጻፈ አይደለምን?›› ሲል ይጠይቃል፡፡

‹‹የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና የሚሠራም ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፡፡ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፡፡ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል እኛን በሚቆጣጠር በእርሱ ዓይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቆተና የተገለጠ ነው እንጂ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም፡፡›› (ዕብ.4፡12-13) ሰይጣንና ዓለምን ለመከላከልና ለማጥቃትም ልንጠቀምበት የምንችለው ብቸኛ መሣሪያ የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ የሕያው እግዚአብሔር ቃል በመሆኑ በውስጡ ኃይል እንዳለው ልንረሳ አይገባንም፡፡ ስንጠቀምበት ቃሉን የምንሰነዝርበት ሰው ሁሉ የቃሉን ኃይል ያውቃል፡፡ በቃሉ የምናነጋግረው ግለሰብ ቢቀበለውም ባይቀበለውም ወይም ያልተሰማው በመምሰል የተረጋጋ ለመምሰል ቢሞክር ወይም ተቃውሞው ቢቀጥልም እንኳን ሕሊናውን ግን ይወቅሰዋል፡፡ የተባለው ነገር እውነት እንደሆነም ያውቃል፡፡

ወጣት በነበርኩበት ጊዜ ከዕለታት በአንዱ ቀን ይህን ነገር በተግባር አይቼዋለሁ፡፡ በነበርኩበት መኪና ውስጥ ለሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል እነግር ነበር፡፡ አንድ ከበርቴ መሳይ ሰውም ክርስትናን እያጥላላ ተቃወመኝ፡፡ መጽሐፍ ቅዱሴን አወጣሁና ሰውዬው የሚለውን ነገር በቃሉ መቃወም ጀመርኩ፡፡ ሁለት ሦስት ጊዜም ጠቀስኩለት፡፡ ሰውዬውም አቋረጠኝና ‹‹ስማ ጌታዬ እኔኮ አንተን እንጂ መጽሐፍ ቅዱሱን አልተቃወምኩም›› ብሎ ጮኸ፡፡ እኔም የአገልግሎቴ መሠረት መጽሐፍ ቅዱስ መሆኑን ገለፅኩለት፡፡ ጥቂት ጊዜ ለመከራከር ሞከረና አቋርጦ ፊቱን አዙሮ ማንበቡን ቀጠለ፡፡

በዚያን ሰሞን ተመሳሳይ ነገር አጋጠመኝ፡፡ በዚህ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱሴን ሳላወጣ ሰውየውን ተከራከርኩት፡፡ መሸነፌን ለመረዳት ግን ረጅም ጊዜ አልወሰደብኝም፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት በሰው በተጨናነቀ አውቶቡስ ላይ ተሳፍሬ እጓዝ ነበር፡፡ ከተሳፋሪዎቹ አንዱ ስለ ጊዜው አስከፊነትና በመሻሻል ፋንታ እየተባባሰ መሄድ ያማርር ነበር፡፡ እኔም ወደ ውይይቱ ጣልቃ በመግባት መልካም ዘመን መምጣቱ እንደማይቀርና እኔም ተካፋይ እንደምሆን ገለፅኩለት፡፡ በማያያዝም ጥቂት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አነበብኩለት፡፡ እየሳቀም አፌዘብኝ፤ እኔም በመቀጠል በዓለም ስላለው የሰው ሁኔታና በክርስቶስ ኢየሱስ ስላለው መዳን አነበብኩለት፡፡ ፊቱን አዞረና ከሌላ ሰው ጋር ማውራት ጀመረ፡፡ ነገር ግን 15 ደቂቃ ያህል ቆይቶ ከእርሱ ጋር እንድሄድ ጠየቀኝ፡፡ ዓይኖቹ በእንባ ተሞልተው መጽሐፍ ቅዱስ ካለኝ እንድሰጠው ለመነኝ፡፡ ምክንያቱም ቃሉን ለማወቅ በጣም ጓጉቶ ነበርና፡፡

የእግዚአብሔር ቃል ያነጻል

የእግዚአብሔር ቃል የምንፀዳበትና የምንቀደስበት ብቸኛ የእግዚአብሔር መንገድ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቶስ ለቤተክርስቲያን ያደረገላትን ሲገልጥ ‹‹በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለ እርስዋ ራሱን አሳልፎ ሰጠ›› (ኤፌ.5፡25) ይላል፡፡ በዮሐ.17፡17ም እንዲሁ ‹‹በእውነትህ ቀድሳቸው ቃልህ እውነት ነው›› የሚል እናገኛለን፡፡

አዘውትረን የእግዚአብሔርን ቃል ለአካሄዳችንና ለመንገዳችን የምንጠቀም ከሆንን ሕይወታችን ነጽቶ ከክፉ ተለይተን መኖር እንችላለን፡፡ በአብ ዘንድ ያለው ጠበቃችን እግሮቻችንን በቃሉ ያጥባቸዋል (1ዮሐ.2፡2)፤ ነገር ግን እግሮቻችን እንዲታጠቡ መፍቀድ የእኛ ኃላፊነት ነው፡፡

መዝሙረኛውም አንተን እንዳልበድል ቃልህን በልቤ ሰወርሁ (መዝ.119፡11) ይላል፡፡ በሌላ ስፍራም ባሪያህ ደግሞ ይጠብቀዋል በመጠበቁም እጅግ ይጠቀማል ይላል(መዝ.19፡11)፡፡

ልምምድ እና ትምህርት ሁሉ በቃሉ ይመዘናል

አሁንም በመዝ.119፡168 ‹‹መንገዶቼ ሁሉ በፊትህ ናቸውና ትእዛዝህንና ምስክርህን ጠበቅሁ›› ሲል ‹‹መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ›› እያለ ደግሞ በራእይ 2 እና 3 የሚያሳስብ ቃል ተጽፎ እናገኛለን፡፡ በአብያተ ክርስቲያናት (በአማኞች ማኅበር) ውስጥ የሚደረጉ ነገሮችን ሁሉ መፈተን አለብን፡፡ የሚሰጠው ትምህርትና የሚደረገው ተግባር ሁሉ መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት ከሚለው አንፃር ታይቶ በቃሉ መፈተን አለበት፡፡ በሌላ ስፍራም እንዲህ ይላል ‹‹ነቢያትም ሁለት ወይም ሦስት ሆነው ይናገሩ ሌሎችም ይለዩአቸው›› (1ቆሮ.14፡29) አካሄዳችንንና ሐሳባችንንም በቃሉ መፈተን አለብን፡፡ ሐሳቦቻችን ምንም ጥቅም የላቸውም፡፡ ወሳኙ የእግዚአብሔር ቃል የሚለው ነገር ብቻ ነው፡፡

በሐዋ.17፡11 ስናይ በቤሪያ የነበሩት አይሁዳውያን በተሰሎንቄ ከነበሩት የሚሻሉበት ነበረ፡፡ ምክንያቱም የጳውሎስን ትምህርት ከቃሉ አንፃር እያስተያዩ ይመረምሩት ነበርና፡፡ ጳውሎስም የትምህርቱ መነሻ ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሆኑ በግልጥ ያሳየበት ተጽፎ ይገኛል (1ቆሮ.15፡3-4)፡፡

‹‹የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል፡፡››(2ጢሞ.3፡16-17)፡፡

መታዘዝና ለፈቃዱ መገዛት

‹‹ትእዛዛትህን እጅግ እንጠብቅ ዘንድ አንተ አዘዝህ›› (መዝ.119፡4) ‹‹ባሪያህ ደግሞ ይጠብቀዋል በመጠበቁም እጅግ ይጠቀማል›› (መዝ.19፡11) ‹‹እኔ የአባቴን ትእዛዝ እንደ ጠበቅሁ በፍቅሩም እንደምኖር ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ›› (ዮሐ.15፡10)፡፡ ‹‹የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን›› (ዮሐ.14፡23)፡፡ ‹‹ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም›› (1ዮሐ.5፡3)፡፡

ከእነዚህም ንባቦች ሰው ቃሉን አውቆ መታዘዝ እንዳለበት እግዚአብሔር ለመታዘዝ ምን ያህል ዋጋ እንደሰጠ መገመት ይቻላል፡፡ ምን አድርግ ዘንድ ትወዳለህ? ለሚለው ጥያቄ የሚሰጠን መልስ ትእዛዜን ጠብቅ የሚል ይሆናል፡፡

በመጀመሪያ የተከሰተው ኃጢአት የእግዚአብሔርን ቃል አለመታዘዝ ነበር፡፡ እግዚአብሔር በእኛ ላይ ያለውን ሥልጣን ግምት ውስጥ ሳናስገባ አንዳች ማድረግ ወይም እናደርገው ሲገባን ሳናደርገው ብንቀር ኃጢአት ይሆናል፡፡ ኃጢአት በ1ዮሐ.3፡4 ዓመፅ ተብሎ ተገልጾአል፡፡ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ሳንጠይቅ እንደፈቃዱ ሳይሆን በገዛ ፈቃዳችን የምንሠራው ሁሉ ኃጢአት ነው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ መታዘዝን እንዴት እንዳሳየ እስኪ እንመልከት፡፡ በዕብራውያን 10፡7 ላይ ‹‹ፈቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ›› ይላል፡፡ ፈቃድን ለማድረግ ደግሞ መታዘዝን መማር ነበረበት (ዕብ.5፡6) እርሱ ዘላለማዊው አምላክ እንደመሆኑ መጠን መታዘዝ ለእርሱ እንግዳ ነበርና፡፡ በወልድነቱም በምድር በነበረበት ጊዜ ሁልጊዜ አብን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ይሠራ ነበር፡፡ እንዲህም አለ፤ ‹‹የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አድርግ ዘንድ ሥራውንም እፈፅም ዘንድ ነው፡፡›› (ዮሐ.4፡35)

ሰው ሁሉ በየመንገዱ በሚሄድበትና ሁሉም የራሱን ፈቃድ በሚሠራበት በዚህች ምድር ይህ ሰው (ወልድ) ግን ፍጹም ቅዱስ ሆኖ ሳለ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ብቻ ሲፈፅም መታየቱ ለእግዚአብሔር ምንኛ ደስ ያሰኘዋል!

በአሁኑ ጊዜም እግዚአብሔርንና ፈቃዱን አውቀው ለማገልገል ደስተኞች የሆኑና ይህንንም ለመረዳት ቃሉን በትጋት የሚመረምሩ ሰዎች ሲገኙ እግዚአብሔር ምን ያህል ደስ ይሰኝ!

ቃሉን ለማወቅ በመፈለግ ስናጠና የሚሰጠንን ጥቅም ታላቅነት መገመት ይቻላል፡፡ በቃሉ ውስጥ የጌታን ክብርና ጌታ በፍቅሩ ያዘጋጀልንን በረከት ስናይ ልባችን በደስታ ይሞላል፡፡ ቃሉን በማወቅ የእግዚአብሔርን ሐሳብ በበለጠ መረዳት እንችላለን፡፡ ከሰይጣን ጥቃት የምንከላከልበትንና ራሳችንም መልሰን ለሌላው ሰው የነፍሱን ደኅንነት በመንገር ጠላትን የምናጠቃበት የጦር ዕቃችን ቃሉ ነው፡፡

እባክህ ተወኝ ጭንቅላቴ ወንፊት ነው ምንም መያዝ አይችልምና ማጥናቱ ይከበደኛል የሚል ሰው ሊኖር ይችላል፤ ነገር ግን ወንፊቱም ደጋግሞ ውኃ ሲያልፍበት ማቆር ባይችልም ራሱ ግን ይፀዳል፡፡ ውኃውም የወንፊቱን ቆሻሻነት ያስወግዳል፡፡ የእግዚአብሔር ቃልም ሰውን እንዲሁ ያነፃል፡፡ ማንበብ ብቻ ሳይሆን በቃሉ ላይ ጊዜ ወስዶ ማሰላሰል አስፈላጊ ነው፡፡ ጥሩ የሆኑ ማብራሪያዎችንም መጠቀም መልካም ነው፤ ሆኖም ማብራሪያውን ራሱንም በቃሉ ልንፈትነው የተገባ ነው፡፡ ማብራሪያው ቃሉን እንዲተካ ማድረግ የለብንም፤ ምክንያቱም ቃሉን የሚተካ ሌላ የአማራጭ አስተያየት ሊኖር አይገባምና እንደዚህ ማድረግም በራሱ ስሕተት ነው፡፡ ‹‹ልጄ ሆይ ቃሌን ብትቀበል ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽገህ ብትይዛት ጆሮህ ጥበብን እንዲያደምጥ ታደርጋለህ፤ ልብህንም ወደ ማስተዋል ታዘነብላለህ፤ ረቂቅ እውቀትን ብትጠራት ለማስተዋልም ድምፅህን ብታነሳ እርስዋንም እንደ ብር ብታፈላልጋት እርስዋንም እንደ ተቀበረ ገንዘብ ብትሻት የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት ታውቃለህ፡፡›› (ምሳ.2፡1-5)፡፡

ከሰላምታ ጋር
የእናንተው ወንድም

ምዕራፍ 13 ጸሎት

የተወደድህ ወዳጄ

ባለፈው ደብዳቤ ቃሉን እንደታነብ አሳስቤህ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ የጸሎት ሕይወትህን በተመለከተ መጠየቅ እወዳለሁ፤ ሁሉም የተያያዙ እንደመሆናቸው ጥቅማቸውም ይህ ነው ተብሎ የሚወሰን አይደለም፡፡ ሰው ቃሉን ብቻ እያነበበ ጸሎት ባይጸልይ አውቃለሁ ከሚል የተነሳ ትዕቢት ላይ ሊወድቅ ይችላል፡፡ ሌላው ደግሞ ቃሉን ሳያነብ ጸሎት ብቻ ቢያዘወትር ወደ ጠባብ ሃይማኖተኝነትና ከአክራሪነት ጋር ወደ ተያያዘው ጨለማ ሊወድቅ ይችላል፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔርን ሐሳብ ሊያውቅ ከሚችልበት ከቃሉ ተለይቶአልና፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል ቸል የሚል ሰው የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማወቅ የማይፈልግና በሐሳቡም ደንታ የሌለው ሰው ነው፡፡ የዚህ ዓይነቱ ሰው ጸሎትም እኔ በሚል ትኩረት ዙሪያ የሚሸከረከር ይሆናል፡፡ ለወንጌል አገልግሎት ቀናዒ ይመስላል፤ ነገር ግን ይህ የእኔነት ፍላጎቱ መሸፈኛ ነው፡፡ ለመንፈሳዊ ሕይወት በረከት ሊገኝ የሚችለው ጸሎትና የእግዚአብሔር ቃል ጥናት ጎን ለጎን ሲሄዱ ብቻ ነው፡፡

በቅዱሳት መጻሕፍትም ለጸሎት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎቱን የጀመረው በጸሎት ነበር (ሉቃ.3፡21) የክርስቲያኖች ጉባኤ ተመሥርቶ ሦስት ሺህ ሰዎች ወደ ክርስትና የገቡት የአሥር ቀን ጸሎት ከተደረገ በኋላ ነበር (የሐዋ.ሥ.1፡13-14) በአረማውያን መካከል ታላቅ የወንጌል አልግሎት የተጀመረውም ከጸሎት በኋላ ነበር (የሐዋ.ሥ.13፡2-3) አሥራ ሁለቱ ሐዋርያትም ሌላውን ሥራ ትተው ራሳቸውን ለጸሎትና ለቃሉ አገልግሎት እንደለዩም ተጽፎአል (የሐዋ.ሥ.6፡4) የሐዋርያት ሥራን መጽሐፍ ስናነብ ሳውል ሁል ጊዜ ይሰብክ የነበረ ይመስላል፡፡ መልእክታቱን ስናነብ ደግሞ ጊዜውን ሁሉ በጸሎት ያሳልፍ የነበረ ይመስላል፡፡ ለአብነት ያህል ሮሜ.1፡9-10፤ 1ቆሮ1፡4፣ ኤፌ1፡16፤ 3፡14 ፊልጵ1፡4፤ ቆላ1፡3-9፤ 1ተሰ.1፡2 መመልከት በቂ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃልም ‹‹ሁል ጊዜ ዘወትር››(ኤፌ.6፡8) ‹‹ሳናቋርጥ››(1ተሰ.5፡17) መጸለይ እንዳለብን ይናገራል፡

ጸሎት የዳግም ልደት ምልክት ነው

ጸሎት ከልብ የሚፈልቅ እንጂ የጸሎት መጻሕፍትን ማንበብ ወይም መድገም አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ በምድራችን ላይ በየቀኑ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ የተለያየ ርዝማኔ ያላቸው የተጻፉ ጸሎቶች ይደገማሉ ወይም ይጸለያሉ፡፡ አንዳንዶቹ የመጻሕፍት ጸሎቶች የሚወደዱት በርዝማኔያቸው ሲሆን አንዳንዶቹ የመጻሕፍት ጸሎቶች ደግሞ ጸሎቶቹን ባዘጋጁአቸው ሰዎች የድርሰት ችሎታ ነው፡፡ አንድ ጊዜ በአንድ ከተማ በተደረገ የአምልኮ ፕሮግራም በአንድ ጋዜጣ ላይ ረጅም ጸሎት ስለጸለየ አንድ ሰው በከተማው በተደረጉት ጉባኤያት ሁሉ የእርሱን ዓይነት ደስ የሚል ጸሎት የጸለየ ሰው እስካሁን አልተገኘም የሚል ተጽፎ ነበር፡፡ ሆኖም እነዚህ ጸሎቶች የአእምሮ ሥራዎች እንጂ ከልብ የማይፈልቁ ወይም ሌሎች ሰዎች ከልባቸው ለእግዚአብሔር ያቀረቡአቸው ነገር ግን ለሚደግማቸው ሰው እንግዳና አፍአዊ በመሆናቸው ተቀባይነት የላቸውም፡፡ ጌታችንም ስለፈሪሳውያን ሲናገር ጸሎትን በማስረዘም ያመካኛሉ ብሎአቸዋል (ማር.12፡40)፡፡

በእውነት መጸለይ የሚችሉት እውነትኛ አማኞች ብቻ ናቸው፡፡ ከእግዚአብሔር የተሰጠን አዲስ ሕይወት በእግዚአብሔር ላይ ለመደገፉ ራሱን የሚገልጸው በጸሎት ነው፡፡ እግዚአብሔር የማያምኑ ሰዎችን ጸሎት አይመልስም ማለት አይደለም፡፡ የቁራ ጫጩትን ጩኸት ሰምቶ ምግብን በመስጠት የሚመልስ አምላክ ጸሎታቸው ቅን እስከሆነ ድረስ አንዳንድ ጊዜ ለጸሎታቸው መልስ ይሰጣል፡፡ ለዚህም ዘፍጥረት 21፡17 እና ዮናስ 1፡14 ላይ ያለውን ማየቱ በቂ ምስክር ነው፡፡

ጳውሎስም ፈሪሳዊ ሳለ ብዙ ጸሎት አቅርቦ ይሆናል፡፡ ጌታ በደማስቆ መንገድ ከተገናኘው በኋላ ግን ሐናንያን ወደ እርሱ እንዲሄድ ባዘዘው ጊዜ ስለ ሳውል እየጸለየ ነው ብሎ ተናግሮለታል፡፡ ይህም ሳውል ለመለወጡና በእግዚአብሔር ላይ የሚደገፍን አዲስ ሕይወት መቀበሉን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ነበር፡፡

ይህም አዲስ ሕይወት በእግዚአብሔር ላይ መደገፉን የሚያሳይበት ጸሎት አዲስ የተወለደ ሕፃን እንደሚያሰማው ጩኸት ይመስላል፡፡ ብዙም ግልፅ ያልሆኑ ነገሮች ይናገራል፡፡ እግዚአብሔር ግን የተዘበራረቀውንና ጥበብ የጎደለውን ጸሎቱን ይረዳለታል፡፡ መጸለያችን በእግዚአብሔር በአባታችን ላይ ለመደገፋችን ምልክት ነው፤ እንደ ባለጠግነቱም መጠን መልካምን መልስ ይሰጣል፡፡

ጸሎት ለጠነከሩ አማኞች ብቻ የተወሰነ አይደለም

አዲስ የተለወጡ አማኞች እንዴት መጸለይ እንደሚገባቸው ካላወቁ ወይም የሚጸልዩበት ነገር መልካም ይሁን መጥፎ ግልፅ ካልሆነላቸው ሳይጸልዩ ቢቆዩ የሚሻል ይመስልሃልን? ጳውሎስ የመጀመሪያውን መልእክቱን ሲጽፍላቸው የተሰሎንቄ ሰዎች ወንጌልን አምነው ከዳኑ ጥቂት ወራት ብቻ አሳልፈው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ጳውሎስ ሲጽፍላቸው ‹‹ሳታቋርጡ ጸልዩ››(1ተሰ.5፡17) ብሎአቸው ነበር፡፡ ታላቁ ሐዋርያ በዚህ አላበቃም፡፡ በእርሱ ስብከት የተለወጡ እንደመሆናቸው በደብዳቤው ከሚጽፍላቸው ትምህርት ባሻገር ‹‹ወንድሞች ሆይ ለእኛም ጸልዩልን›› በማለት የእነርሱን ምልጃ ሲጠይቅ ይታያል (1ተሰ.5፡25)፡፡

ከዚህ በመነሳትም እግዚአብሔር ለጸሎት ትልቅ ዋጋ እንደሚሰጥና ጸሎትን እንደሚወድ መረዳት እንችላለን፡፡ አንደበታቸው በትክክል ባይፈታም እንዲያናግሯቸው ወይም ልጆቻቸው ስለሚፈልጉት ነገር እንዲጠይቁ ወይም እንዲናገሩ የማይፈልጉ ወላጆች አሉ? የጠየቋቸውን ነገር ሊሰጧቸው ስለማይችሉ ወይም የጠየቁት ነገር ጎጂ በመሆኑ እንዲለምኗቸው የማይፈልጉ ወላጆችስ አሉ? አዲስ የተወለደው አማኝ በሚያስፈልገው ነገር እየጠየቀ በእርሱ ያለውን መደገፍ ሲያሳይ እግዚአብሔር ደስ ይለዋል፡፡ የአማኙን ጸሎት ለመመለስም ደስተኛ ነው፡፡ ነገር ግን የሚጸልየው ሰው የሚጠቅመውንና የማይጠቅመውን ለይቶ ስለማያውቅ እግዚአብሔር ከፍቅሩ የተነሳ ሁልጊዜ የጠየቀውን ሁሉ አይሰጠውም፡፡ ይሁን እንጂ ለጥያቄው መልስ ባይሰጠውም ልቡን በሰላም ይሞላዋል፡፡ ‹‹በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ፡፡ አእምሮን ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቀዋል››(ፊልጵ4፡6-7)፡፡

የጸሎት መልስ እርግጠኝነት

ጳውሎስ በመልእክቱ ‹‹ለገዛ ልጁ ያልራራለት ነገር ግን ስለ ሁላችን አሳልፎ የሰጠው ያው ከእርሱ ጋር ደግሞ ሁሉን ነገር እንዲያው እንዴት አይሰጠንም›› ይላል (ሮሜ.8፡31-32) ኢየሱስም ‹‹አብ እርሱ ራሱ ይወዳችኋል››(ዮሐ.16፡27) ብሎ ነግሮናል፡፡ ልዑል እግዚአብሔር ካፈቀረንና ሁሉን ነገር ሊሰጠን ከወደደ ጸሎት ምን ያህል ኃይል እንዳለው መገመት ይቻላል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በስሙ ብንጸልይ እንደምናገኝ ቃል ገብቶልናል፤(ዮሐ.14፡13-14) እንደዚሁም በተጨማሪ ‹‹አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል›› ብሎናል (ዮሐ.16፡23) ይህም ያለ አንዳች ጥርጥር አንድም ሳይቀር ሁሉንም እንደሚሰጠን ያሳየናል፡፡

የጌታችንን ሕይወት በመጻሕፍት ወስጥ ብንመለከት ይህ ግልጥ ይሆንልናል፡፡ ስለ ጌታም በመዝ.109፡4 ‹‹እኔ እጸልያለሁ›› ተብሎ ተጽፎለታል፡፡ የእርሱም ሕይወት በዚህ ተገልጧል፡፡ እርሱም በአንድ በኩል ምንም እንኳን ፍጹም አምላክ ቢሆንም ሥጋን በመልበሱ ፍጹም ሰው ነውና በሰውነቱ በጸሎት አማካይነት በእግዚአብሔር ላይ መደገፍ ተገብቶታል፡፡ ፈጣሪ አምላክ ሰውን በራሱ የሚደገፍ ፍጡር አድርጎ አልፈጠረውምና ሰው ደግሞ በእግዚአብሔር ላይ ካልተደገፈ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በዲያብሎስና የእርሱ በሆኑት ላይ የሚደገፍ ይሆናል፡፡

በጌታ ኢየሱስ ሕይወት ውስጥ ፍጹም ሰውነትን እንመለከታለን፡፡ በኢሳ.50፡4 እርሱ ስለ እግዚአብሔር ሲናገር ‹‹ማለዳ ማለዳ ያነቃኛል፤ እንደ ተማሪዎችም ትሰማ ዘንድ ጆሮዬን ያነቃቃል›› ብሏል፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ይህን ያህል በእግዚአብሔር ላይ መደገፍ ካስፈለገው ፍጡር የሆነው ሰውስ ምንኛ ተግቶ መጸለይ ያስፈልገዋል፡፡

በሉቃስ ወንጌል ጌታችን እንደ ፍጹም ሰው ወይም የሰው ልጅ ሆኖ ሲታይ በጸሎት ምን ያህል ይተጋ እንደነበረ መመልከት ይቻላል፡፡ በዚህ ወንጌል ብቻ ስምንት ጊዜ ያህል እንደጸለየ ተጠቅሷል፡፡ አንዳንድ ጊዜም ሌሊቱን ሙሉ ሲጸልይ እንዳደረ ተጠቅሷል (ምዕ.3፡21፣ 5፡16፣ 6፡12፣ 9፡18፣ 29፣ 11፡1፣ 22፡41 እና 23፡34 ተመልከት) ከመሰቀሉ በፊት በአገልግሎት ወቅት ሰባት ጊዜ ያህል ጸለየ፡፡ ስምንተኛው ደግሞ መስቀል ላይ ተቸንክሮ ባለበት ወቅት ነበር፡፡ ጌታ ጸሎት የጸለየባቸውን ሁኔታዎች ብንመለከት አስደናቂ ትምህርቶችን እናገኝባቸዋለን፡፡ እያንዳንዱ ጌታ የጸለየበት ሁኔታ ለእኛ ታላቅ ትምህርት ሰጪና ልባችንንም ለአምልኮ የሚያበረታታ ነው፡፡ አሁን እንድናይ የፈለግሁት ግን ስለእነዚህ ሁኔታዎች ሳይሆን ይህን ያህል የጸለየው ጌታ ኢየሱስ ‹‹ሁል ጊዜ እንድትሰማኝ አወቅሁ›› (ዮሐ.11፡42) ያለበትን ሐሳብ ነው፡፡ ይህ ማለት ለሚጸልየው ሁሉ መልስ ያገኝ ነበር ማለት ነው፡፡ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 11 ቁ.41 እንደምናነበው ከሞተ አራት ቀን ያስቆጠረውንም አልአዛርን ለማስነሳት በጸለየ ጊዜ ጸሎቱ እንደተሰማለት አስቀድሞ ያውቅ ነበር፡፡

‹‹የምወድህ ልጄ አንተ ነህ ባንተ ደስ ይለኛል›› (ሉቃ.3፡21-22፤ 9፡35፤ ማቴ.17፡5) ብሎ እግዚአብሔር ሁለት ጊዜ ሲመሰክርለት፣ በሁለቱም ጊዜያት ጌታ እየጸለየ ባለበት ሁኔታ እንደነበረ መገንዘብ እንችላለን፡፡ እርሱም ጌታ ‹‹የእኔ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው››(ዮሐ.4፡34) ብሏል፡፡ እንደዚሁም ‹‹እኔ ደስ የሚያሰኘውን ዘወትር አድርጋለሁ›› (ዮሐ.8፡29) ሲል እንሰማዋለን፡፡ እግዚአብሔር ሁሉንም የኢየሱስን ጸሎቶች የመለሰበት ምክንያት ሁሉም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የተጠየቁና ለእግዚአብሔር ክብር የሚያስገኙ በመሆናቸው ነው፡፡

ስለዚህ በጌታችን ኢየሱስ ስም ስንጸልይ ጸሎታችን መልስ እንደሚያገኝ የተረጋገጠ ነው፡፡ ምክንያቱም በስሙ በመጸለይ ጸሎታችን ወደ እግዚአብሔር የሚቀርበው ልክ ኢየሱስ እንደጸለየው ተቆጥሮ ነው፡፡

በጌታችን በኢየሱስ ስም መጸለይ
ምን ማለት ነው?

በኢየሱስ ስም የሚደረግ ጸሎት ውጤት እንደሚያመጣ አይተናል፡፡ ይህም ለፈለግነው ነገር ሁሉ ጸልየን በመጨረሻው በኢየሱስ ስም ብሎ መቋጨት የሚመስላቸው ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ብዙውን ጊዜ ሰዎች የሚያደርጉትና የሚያስቡት እንደዚህ ሲሆን በትክክል ግን ይህ ብቻውን ጸሎቱን በኢየሱስ ስም የተጸለየ ጸሎት አያደርገውም፡፡ በኢየሱስ ስም መጸለይ ማለት ግን ኢየሱስ በዚህ ምድር በነበረው ቦታ ሆኖ እርሱ ያሰጠንን የልጅነት ሥልጣንና የእርሱን መብት ተጠቅሞ መጸለይ ማለት ነው፡፡ ይህን ስናደርግ ደግሞ ጸሎታችን የእርሱን ጸሎት ጠባይ ይዞ መገኘት ይኖርበታል፡፡

አንድ ሰው ወደ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መሸጫ ሄዶ በሌላ እውነተኛ ክርስቲያን ስም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሰጠው ቢጠይቅ የሱቁ ባለቤትም እውነተኛውን አማኝ ስለሚያውቀው ወዲያውኑ ሰውዬውን ሊያምነው ይችላል፡፡ ነገር ግን የቁማር መጫወቻ ካርታ ወይም ልበወለድ ወይም ሌላ በክርስቲያኖች የተናቀ ጽሑፍ ስጠኝ ቢለው ባለሱቅ ክርስቲያኑን ስለሚያውቀው የሰውዬውን ጥያቄ አይቀበልም፤ ምክንያቱም አማኝ እንደዚህ ዓይነት ነገሮችን ለሰውዬው እንደማያዝ ያውቃል፡፡ ጠያቂውም በአፉ በክርስቲያኑ ስም ቢመጣም በተግባር ግን በአማኙ ስም አልመጣምና ጥያቄው አይመለስለትም፡፡

የእኛ ጸሎትም የጌታችን የኢየሱስን ጸሎት ጠባይ መያዝ ይኖርበታል፡፡ ይኸውም ፍጹም በእግዚአብሔር ላይ የመደገፍ ጸሎት ማለትም እግዚአብሔር የሚከብርበትና እንደ ፈቃዱ የሆነ ጸሎት ሊሆን ይገባል ማለት ነው፡፡

መልስ የሚያስገኝ ጸሎት

በዮሐ.15፡7 ‹‹በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል›› ይላል፡፡ እዚህ ላይ ለምንጸልየው ጸሎት ሁሉ ከዚህ በቀር የሚል ገደብ ሳይኖር እግዚአብሔር መልስ እንደሚሰጥ ትልቅ ማረጋገጫ ቀርቦልናል፡፡ ‹‹የምትወዱትን›› ከሚለውና ‹‹ይሰጣችኋል›› ከሚለው ቃል በላይ ሌላ ምን አለ? ነገር ግን ‹‹የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል›› ከሚለው የተስፋ ቃል የሚቀድም ሌላ ሁኔታ አለ፡፡ እርሱም ‹‹በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ›› የሚለው ነው፡፡ ይህም ጸሎታችን እንደሚመለስ እርግጠኛ ለመሆን ከፈለግን መሟላት ያለበት ቅድመ ሁኔታ ይህ መሆኑን ያስገነዝበናል፡፡ ስለዚህ የጸሎት መልስ እንድናገኝ ከተፈለገ በክርስቶስ መሆን ያስፈልጋል፡፡ በእርሱ ከሆንን የእርሱን መልክ እየመሰልን እንመጣለን፡፡ ቃሉም በእኛ ውስጥ ቢኖር ፍላጎቶቻችንና ስሜቶቻችን፣ ደስ የተሰኘንባቸው ነገሮቻችንና ልንሆን የወደድነው ከእርሱ ፍላጎት፣ ስሜትና መሻት ጋር ይስማማል፤ እናም ይህ ከጌታ ሐሳብ ጋር የተስማማው ሁሉ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር በፍጹም የተስማማ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ በሌላ ስፍራም በስሙ የምንለምነው ሁሉ መልስ እንደሚያገኝ ሲገልጥ ‹‹እናንተ ስለወደዳችሁኝ ከእግዚአብሔርም ዘንድ እንዳወጣሁ ስላመናችሁ አብ እርሱ ራሱ ይወዳችኋል›› (ዮሐ.16፡23-27) ይላል፡፡

ዕብራውያን 11፡6 ደግሞ ሌላ ቅድመ ሁኔታ ያስቀምጥልናል፤ ‹‹ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋል›› በማለት የሚጸልይ በእምነት ሊጸልይ እንደሚገባው ያሳያል፡፡ እንደዚሁም ያዕ.1፡6-7 ደግሞ ‹‹ነገር ግን በምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባሕርን ማዕበል ይመስላልና›› በማለት የሚጠራጠር ሰው አንዳች ማግኘት እንደማይችል ይነግረናል፡፡

በእምነት ለሚጠይቅ እግዚአብሔር መልስ ይሰጣል፡፡ የሚጸልየው ሰው በጸሎት የሚጠይቀውን ነገር እግዚአብሔር እንደሚሰጠው ያምን ዘንድ የሚያስችለው መተማመን በውስጡ ሳይኖር እግዚአብሔር እንዴት ጸሎቱን ሊመልስለት ይችላል?

በማቴ.21፡21-22 ጌታችን ይህንን ዓይነት ነገር ተናግሯል፡፡ የእምነት መኖር ማረጋገጫም ሊኖር እንደሚገባም አስረድቷል፡፡ በአንድ ወቅት አንድ የአክሮባት ስፖርተኛ የኒያጋራን ፏፏቴ ከዳር እስከዳር በተዘረጋ ገመድ ላይ እየተረማመደ ተሻገረው፡፡ እንደገናም ባለ አንድ እግር ጋሪ ወይም ኩርኩር እየገፋ ተሻገረ፡፡ ከዚያም ሙሉ ሰው የሚያክል አሻንጉሊት ተሸክሞ ተሻገረ፡፡ በመቀጠልም ይመለከቱት ለነበሩ ሰዎች ሰውን ተሸክሜ መሻገር እንደምችል ታምናላችሁን ብሎ ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም አዎን ሰውን ተሸክመህ መሻገር እንደምትችል እናምናለን ብለው በአንድነት ጮኹ፡፡ ነገር ግን ተሸክሞት እንዲያሻግረው ፈቃደኛ ሰው ካለ ቢጠይቅ አንድም ለዚያ የሚበቃ ድፍረት ያለው ፈቃደኛ ሰው አልተገኘም፡፡

ጌታ ኢየሱስም ስለ እምነት ብቻ ሳይሆን እምነት እንዳለንም ስለሚገልጥ ማስረጃ ያስተማረውም ለዚህ ነው፡፡ ይህም ማስረጃ የሚገለጠው ተራራውን ‹‹ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር›› ብሎ በመናገር ነው፡፡

የጸሎት መልስ እንቅፋቶች

ብዙ ቢጸለይም መልስ የማይመጣው ለምንድን ነው? ቅዱሳት መጻሕፍት ለዚህ ብዙ ምክንያት ይሰጣሉ፡፡ ዳን.10 ላይ እንደምናየው አንዳንድ ጸሎቶች ጥሩ ቢሆኑም አልፎ አልፎ መልስ የማያገኙበት ጊዜ እንዳለ ያሳየናል፡፡ ሰይጣን ባለ በሌለ ኃይል ለጸሎታችን መልስ እንዳይመጣ ይጥራል፡፡ ፈፅሞ መከልከል ግን አይችልም፡፡ እግዚአብሔር እስከፈቀደለት ድረስ ግን የጸሎታችንን ቀጥተኛ መልስ ሊያዘገይ ይችላል፡፡ የትዕግሥታችንንና የእምነታችንን ጽናት ለመፈተን እግዚአብሔር አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ዓይነቱን ሁኔታ ይፈቅዳል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ መልስ ፈፅሞ የማይመጣበት ሁኔታ ከእኛ ዘንድ በሆነ አንዳች ምክንያትም ሊሆን ይችላል፡፡ እግዚአብሔር ለምን ለጸሎት ዝም እንደሚል በኢሳ.59፡2 ላይ ለእስራኤል የተናገረውን ስናይ ‹‹በደላችሁ በእናንተና በአምላካችሁ መካከል ለይታለች፤ እንዳይሰማም ኃጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሰውሮታል›› ይላል፡፡ መዝሙረኛውም ‹‹በልቤስ በደልን አይቼ ብሆን ጌታ አይሰማኝም ነበር›› (መዝ.66፡18) ብሏል፡፡ በሌላ ስፍራም ‹‹እንዲሁ ወዳጆች ሆይ ልባችንስ ባይፈርድብን በእግዚአብሔር ዘንድ ድፍረት አለን ትዕዛዙንም የምንጠብቅና በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን የምናደርግ ስለሆንን የምንለምነውን ሁሉ ከእርሱ እናገኛለን››(1ዮሐ.3፡21-22) ይላል፡፡

ቅዱሳት መጻሕፍት ልባችን እንዲፈርድብንና ጸሎቶቻችን መልስ እንዳያገኙ የሚያደርጉ ብዙ ነገሮችን እየጠቀሱ ያቀርባሉ፡፡ በማር.11፡22-26 ይቅር አለማለት ለችግሩ መንስኤ ሆኖ ተጠቅሶአል፤ ኤፌ.4፡32ንም ተመልከት፡፡ ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት ዋናው መሠረቱ ኃጢአታችን በክርስቶስ ይቅር ስለተባለልን ነው፡፡ ሌላውን ይቅር አንልም እያልን ታዲያ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ እንዴት ድፍረት ሊኖረን ይችላል?

በያዕ.4፡3 ላይ ‹‹ትለምናላችሁ በምቾቶቻችሁም ትከፍሉ ዘንድ በክፉ ትለምናላችሁና አትቀበሉም›› ይላል፡፡ የአሮጌውን ሰው ምኞት ለማርካት በሥጋ ፍላጎት ተነሳስተን ብንጸልይ እግዚአብሔር እንዴት ሊሰጠን ይችላል? እግዚአብሔር አሮጌውን ፍጥረት ይጠላል፤ በመስቀል ላይም ቸንክሮ ገድሎታል (ሮሜ.8፡3) ራሳችንን እንደ ሞተ ሰው መቁጠር እንዳለብንም ተነግሮናል (ሮሜ.6፡11) በምድር ያሉትን ብልቶቻችንንም እንድንገድል(ቆላ.3 ፡5-17) ቃሉ ያሳስባል፡፡ በተጨማሪም እንዲህ ይላል፤ ‹‹የክርስቶስ ኢየሱስም የሆኑት ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ፡፡››(ገላ.5፡24) ከመንገድ ወጥተን የሥጋን አምሮት ብንለምን ይህ ሁሉ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስንና የእግዚአብሔርን ሐሳብ በፍጹም የሚፃረር ዝንባሌ በውስጣችን እንዳለ አያመለክትምን?፡፡

1ጴጥ.3፡1-7ን ስናይ ደግሞ በቤተሰብ መካከል ያለው ኅብረት ጤናማ አለመሆን ለጸሎት መልስ ማጣት በምክንያትነት ቀርቧል፡፡ በባልና ሚስት፣ በወላጆችና በልጆች፣ በልጆችና በልጆች መካከል አንድነትና ፍቅር ከሌለ የጸሎት መልስ ሊከለከል ይችላል፡፡ ቤተሰባችን ውስጥ ሥርዓት ከሌለና ያልተመለሱ ጥያቄዎች ካሉ እንዴት ደፍረን ወደ እግዚአብሔር እንቀርባለን?

እንደ ፈቃዱ መጸለይ

ራሳችንን እግዚአብሔር እንደሚመለከተን እያየን ኃጢአቶቻችንን በሙሉ ወደ እግዚአብሔርና እንደ አስፈላጊነቱም ወደ ሰው እየተናዘዝን ራሳችንን እየመረመርን ራሳችንን ካፀዳን በእግዚአብሔር ፊትም አንዳች ለመጠየቅ ድፍረት እናገኛለን፡፡ የጠየቅነውንም እንደምናገኝ እርግጠኞች ለመሆንም እንደ ፈቃዱ መጸለይ አለብን፡፡ የአባታችን ፈቃድስ ምን እንደሆነ በምን እናውቃለን? ሐሳቡን በቃሉ አካፍሎናል፡፡ እናም ዕለት ዕለት በመንፈስ ቅዱስ ኅብረት ከእርሱ ጋር ስንጓዝ ቃሉን እያነበብን ፈቃዱን እናውቃለን፡፡ ቃሉን በየቀኑ ማንበብ ጠቃሚነቱ ታላቅ የሆነውም ለዚሁ ነው፡፡ እግዚአብሔር አስቀድሞ የሰጠንን ነገር አምጣ እያልን ብንጸልይ እግዚአብሔር ለዚህ እንዴት መልስ ይሰጣል፡፡ ለምሳሌ መንፈስ ቅዱስ ወርዶ በቤተክርስቲያን እንዳደረና አሁን በእያንዳንዱም አማኝ ውስጥ እንደሚኖር በግልፅ ተፅፎአል፡፡ ወይም ደግሞ በመስቀል ላይ ከክርስቶስ ጋር ስለተቸነከረው ኃጢአተኛ ሥጋችን አዘውትረን ብናለቅስ ምን ፋይዳ አለው? ተከናውኖ የለምን?(ሮሜ.8፡2-3¬፣2ቆሮ 5፡21)

ስለዚህ ቃሉን እያነበብን ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት በማድረግ ፈቃዱን ስናውቅ እንደ ፈቃዱ መጸለይ እንችላለን፡፡ በዚህም የጸሎት መልስ እንደምናገኝ እርግጠኞች እንሆናለን፡፡ ‹‹በእርሱ ዘንድ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ እንደፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል ተብሎ እንደተጻፈ›› (1ዮሐ5፡14)፡፡

ሳታቋርጡ ጸልዩ

መጸለይ የሚችሉት ያደጉና ቃሉን በደንብ ያጠኑ አማኞች ብቻ ናቸውን? አይደለም፡፡ ልጃቸውን እስክታድግ ድረስ አንዳች ነገር እንዳትጠይቀን የሚሉ ወላጆች አሉን? ሕፃኑ አስተካክሎ በቅንብር መናገር ስለማይችል ወይም የጅል ጥያቄ ስለሚጠይቅ ወላጅ ልጁን እስኪያድግ ድረስ ያንተን ነገር አልሰማም ብሎ አይዘጋም፡፡ ነገር ግን ልጁ ጥያቄውን ይዞ በቀረበ ሰዓት በደስታ ያደምጠዋል እንጂ ይህን በፍጹም አያደርግም፡፡ ልጁም ብዙ ባይገባውም በዚህ ደስታቸው እነርሱ ወላጆቹ እንደሆኑ፣ ያለ እነርሱም አንዳች ማድረግ እንደማይችል እንደሚወዱትና እንደሚያስቡለት ያውቃል፤ በእነርሱም ይተማመናል፡፡

ወደ እርሱ ስንቀርብ እግዚአብሔር አባታችንም በጠለቀ ደስታ ያደምጠናል፡፡ ጳውሎስ ገና ወደ ክርስቲያኖች ሳይቀላቀል እየጸለየ ነው ብሎ እግዚአብሔር ተናገረለት፡፡ እርሱም አገልግሎት ከጀመረ በኋላ ለተሰሎንቄ ሰዎች ሳታቋርጡ ጸልዩ ብሎ አሳስቧል፤ እንዲሁም ይህንን መልእክት በጻፈ ጊዜ በእርሱ ብዙ ሚሊዮን ሕዝብ የተገለገለ፣ በልዩ መገለጥ ሙሉው የእግዚአብሔር ምክር የተሰጠው፣ ወደ ሦስተኛው ሰማይም የተነጠቀና በገነትም የማይነገረውን ቃል የሰማ ይህ ሐዋርያ አዲስ አማኞች ለነበሩት ለተሰሎንቄ ሰዎች ‹‹ወንድሞች ሆይ ለእኛም ጸልዩልን›› ሲላቸው እናያለን (2ቆሮ.12፡2-4፣ 1ተሰ.5፡25)፡፡

አማኝ እያደገ ለመሄዱ የሚያረጋግጥልን የማያጠራጥረው ማስረጃ የጸሎትን ጥቅም እያወቀ መሄዱ ነው፡፡ ያለ ጸሎት ሁሉም ነገር ከንቱ ነው፡፡ እግዚአብሔር አባታችን እንዲህ ይለናል፡፡ በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ አእምሮን ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል (ፊልጵ.4፡6-7) የጸሎትን ጥቅም በበለጠ እንድናውቅና ይህን ወሰን የሌለውን መብት በአግባቡ እንድንጠቀምበት እግዚአብሔር ይርዳን፡፡ በሕይወታችን ደስተኞች እንሆናለን፤ ምስክርነታችንም የሰፋ ይሆናል፡፡

ከሰላምታ ጋር
በጌታ ወንደምህ

ምዕራፍ 14 ጥምቀት

ውድ ወገኖቼ

አሁን ስለጌታ እራት ልጽፍላችሁ እወድ ነበር፡፡ ነገር ግን ከእርሱ በፊት መምጣት ስላለበት ነገር እስኪ ልጠይቃችሁ፡፡ ተጠምቃችኋል ወይ?

ይህም ጥያቄ እጅግ አስፈላጊ ጥያቄ ነው፡፡ ማር.16፡16 «ያመነ የተጠመቀም ይድናል፤ ያላመነ ግን ይፈረድበታል» ይላል፡፡ ያልተጠመቀ አይድንም ማለት ነው! በሌላ ምንባብም ተጠቅሶአል፤ ለምሳሌ በ1ጴጥ.3፡21 «ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል» ይላል፡፡

አስቀድሜ ከጻፍኩላችሁ ደበዳቤ የተለየና የሚጋጭ መስሎ ሊታያችሁ ይችላል፡፡ ይህም ደግሞ መዳን ሲባል ብዙውን ጊዜ ሰዎች ወደ ሰማይ መግባት ወይም ደግሞ ተለውጦ የኃጢአትን ይቅርታ ማግኘት ብቻ አድርገው ስለሚረዱት ነው፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት መዳን ከሌላ ሐሳብም ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይህንንም በሐ.ሥ.2፡40 «ከዚህ ጠማማ ትውልድ ዳኑ» ተብሎ ከተጻፈው መረዳት ይቻላል፡፡ በግልፅ እንደሚታየው በዚህ ጥቅስ ላይ የነፍስን መዳን ወይም ወደ ሰማይ መግባትን የሚያሳይ ነገር የለም፡፡ ሮሜ10፡9-10 ያለውን ተመልከት፡፡

ጥምቀት ወደ ሰማይ ከመግባት ጋር አንዳች ግንኙነት የለውም፡፡ ከእግዚአብሔር ያለን ዘላለማዊ ግንኙነትና ወደ ፊት የምንኖርበት ዘላለማዊ ስፍራችንም የሚወሰነው ኃጢአታችንን በእግዚአብሔር ፊት ተናዝዘን በጌታ ኢየሱስ በማመናችን ወይም ባለማመናችን ነው፡፡ ከኢየሱስ ጋር የተሰቀለው ነፍሰ ገዳይ አልተጠመቀም፤ ነገር ግን ጌታ ‹‹ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ›› ብሎታል (ሉቃ.23፡43) ከዚህም በኋላ በሺህ የሚቆጠሩ ብዙዎች ሌሎች ሊሞቱ ሲቃረቡ ከእግዚአብሔር ጋር እየታረቁ በሞት አልጋቸው እየተለወጡ ሳይጠመቁ ከጌታ ጋር ለመሆን ሄደዋል፡፡ በምድር ላለንበት ሁኔታ ግን ጥምቀት እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡

ጥምቀት ምንን ያመለክታል?

ጥምቀት በአይሁድ ዘንድ በይፋ የተለመደ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ነው፡፡ ከአሕዛብ ወገን የሆነ ሰውም ከወገኖቹ ተለይቶ ከእስራኤላውያን እንደ አንዱ ለመሆን ቢፈልግ ጥምቀትን በመውሰድ ይቀላቀል ነበር፡፡ በመጥምቁ ዮሐንስ ጥምቀትም ይህንኑ ሐሳብ እናገኛለን፡፡ ዮሐንስ በአይሁድ ላይ ሊመጣ ስለተቃረበው ቁጣ ሰበከ (ሉቃ.3፡7-9፣16-21) ያመኑትም አይሁድ በመጠመቅ ራሳቸውን ከማያምኑት ወገን ለዩ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ራሱን ከአማኞች ጋር አንድ ለማድረግ ተጠመቀ፡፡ ወደ በጎች በረት በበሩ ገባ (ዮሐ.10፡1-3) የክርስቲያን ጥምቀትም በግልጥ ይህንኑ ሐሳብ አዝሎ ይገኛል፡፡ በማቴዎስ ወንጌል ላይ ጌታችን እንደ እስራኤል ንጉሥ ሆኖ ተገልጿል፡፡ ደቀመዛሙርቱን እንዲሰብኩ ሲልካቸው «በአሕዛብ መንገድ አትሂዱ ወደ ሳምራውያንም ከተማ አትግቡ፤ ይልቅስ የእስራኤል ቤት ወደሚሆኑ ወደ ጠፉት በጎች ሂዱ እንጂ» አላቸው፡፡

እስራኤል ግን ንጉሥዋን አልተቀበለችም፡፡ በማቴዎስ 13 ላይ ስለ መንግሥተ ሰማያት የተነገረውን ምሳሌ ስናይ ንጉሡ ለጊዜው እንደሚቆይና ጠላት እየተጋ እንደሚሠራ ያሳያል፡፡ በቊጥር 37 እና 38 እንደሚታየውም የእርሻው ቦታ ዓለም ከሆነች የእግዚአብሔር መንግሥት ለእስራኤል ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም እንደሆነ ያሳያል፡፡ ጌታችን በእስራኤል ተቀባይነት አጥቶ ከተሰቀለ በኋላ ደቀመዛሙርትን ከኢየሩሳሌም ራቅ አድርጎ ወደ ገሊላ ወሰዳቸው፤ ወደ ዓለም ሁሉ ሄደው ወንጌልን እንዲሰብኩም ነገራቸው፡፡ ወንጌልን ያመኑ ወደ እስራኤል መቀላቀል አያስፈልጋቸውም፡፡ ነገር ግን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መጠመቅ አለባቸው፡፡ ምክንያቱም አሁን የእግዚአብሔር መንግሥት በንጉሡ ማንነት ተገልጣለችና፡፡ በእርሱም ሦስትነት ያለው አምላክ ተገልጧል፡፡ ወደ እርሱ ለመምጣትም በኢየሱስ እንጂ በሌላ በኩል አይቻልም፡፡ በተጨማሪም እግዚአብሔር በምድር የሚታወቀው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ብቻ ስለሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት የሚያምኑ በስሙ እንደሚጠመቁ ይናገራሉ፡፡

ከተሰቀለው ክርስቶስ ጋር ለመተባበር መጠመቅ

1ቆሮ10፡2 ከአንድ ሰው ጋር ለመተባበር መጠመቅ ምን ማለት እንደሆነ በግልፅ ያሳያል፡፡ ከአንድ ሰው ጋር ለመተባበር መጠመቅ ከዚያ ሰው ጋር ወገን መሆን ወይም እርሱ ወዳለበት ቦታ መምጣት ማለት እንደሆነም ያስረዳል፡፡ እስራኤላውያን ከሙሴ ጋር ይተባበሩ ዘንድ በባሕርና በደመና ተጠመቁ፡፡ እኛም በጌታችን በኢየሱስ ስም እንጠመቃለን (የሐዋ.ሥ.19፡5) ነገር ግን የምንጠመቀው በሰማያት በክብር ወደ ተቀመጠው ኢየሱስ ክርስቶስ አይደለም፡፡ ይህም ማለት የምንጠመቀው ከጌታ ሞት ጋር ኅብረት ለማድረግ እንጂ አሁን እርሱ በሰማያት ካለው ክብሩ ጋር ኅብረት ለማድረግ አይደለም፡፡

ይሁን እንጂ ከክብሩም ጋር ኅብረት አለን፡፡ አሁንም ኅብረት ሊኖረንና እርሱ በመስቀል ላይ ከሠራው ሥራ የተነሳ ካገኘው ክብሩ ሁሉ ለዘለዓለም ተካፋዮች ልንሆን እንችላለን፡፡

ይህ ዓለም ግን እኛ እንደምናውቀው ኢየሱስን የተነሣና የከበረ ጌታ እንደሆነ አያውቀውም፡፡ እኛ የምናውቀውን ትንሣኤውንና አሁን ያለበትን ክብሩን አያውቅም፡፡ ዓለም ክርስቶስን ለመጨረሻ ጊዜ ያየችው በመስቀል ላይ ሲሞትና ሲቀበር ነው፡፡ እርሱ ለዓለም በመስቀል ላይ የውርደትን ሞት የሞተና በዓለም ታርዶ የተቀበረ ችግረኛ ነው፡

እኛ ደግሞ አሁን ይህን የተሰቀለውን ጌታ አምነን ተቀብለነዋል፡፡ መዳን በዚሁ ዓለም ባልተቀበለችውና በሰቀለችው በጌታ በኢየሱስ ስም ብቻ እንደሆነ እግዚአብሔር እንድናውቅ አደረገን (የሐዋ.ሥ.4፡11-12)፡፡ እኛም በስሙ አምነን የኃጢአታችንን ይቅርታና የዘላለምን ሕይወት በእርሱ አገኘን፡፡ በወዲያኛው ዓለምም የክብሩ ተካፋዮች እንሆናለን፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ አሁን እርሱ በምድር የነበረው ስፍራ ተካፋዮች እንሆናለን፤ ይኸውም በዓለም መጠላትን ከእርሱ ጋር እንካፈላለን፡፡ ይህም እግዚአብሔር ለእኛ የነበረው ዕቅዱ ነው፤ «አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን፡፡» (ሮሜ.8፡17)፡፡

ዓለም በሞላው በክፉ እንደተያዘ እናውቃለን (1ዮሐ.5፡19)

እግዚአብሔር አዳምን ንጹህና ኃጢአት አልባ አድርጎ ፈጠረው፡፡ አዳም ለእግዚአብሔር ስላልታዘዘ ግን ኃጢአተኛ ሆነ፤ ዘሮቹም ደግሞ ኅብረት በማድረግ እግዚአብሔርን ለመቃወምና ምድር የተረገመችበትን እርግማን በጥበባቸው ለመቋቋም ኃያላን ሆኑ፡፡ ቃየል በምድር ላይ የመጀመሪያ ከተማ ቆረቆረ፤ የእርሱም ዝርያዎች ለሕይወት ተድላን የሚሰጡ ነገሮችን የሚፈጥሩ የታወቁ ጠቢባን ነበሩ፡፡ በመጨረሻም ሰዎች አንድ ላይ ኅብረት በማድረግ ኃይላቸውን ከፍ ለማድረግ ሞከሩ (ዘፍ.11፡4) በዚህ ዓይነትም ሰው ያዋቀረው ዓለም ማለትም የመጀመሪያው ማህበረሰብ ተፈጠረ፡፡

እግዚአብሔር የሰውን አካሄድ በቸልታ ያየበት ጊዜ የለም፡፡ በኖህ በኩል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡ ከጥፋት ውኃ በኋላም በፀዳችው ምድር ላይ አዲስ አሠራርን ጀመረ፤ ነገር ግን ሰው ዳግመኛ አዲስ ጣኦት አምልኮን ሲጀምር እግዚአብሔር አብራምን ለራሱ ለየ፡፡ ከእርሱም ጋር ተነጋገረ፤ ዘሮቹንም ከሌሎች ሕዝቦች ለይቶ ሕጉንና ሥርዓቱን ሰጣቸው፤ ከእነርሱም ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፤ ወደ ምድሩም ወደ አማኑኤል ምድር አመጣቸው፡፡

የዚህንም ውጤት ምን እንደሆነ እናውቃለን፡፡ የአብርሃም ዘሮችም ከእግዚአብሔር ተመለሱ፡፡ በመሳፍንት፣ በነገሥታትና በነቢያት ቢገሥጻቸውም አልተመለሱም፡፡

ከዚያም እግዚአብሔር ልጁን ላከ፡፡ ኃጢአታቸውን ይቅር ብሎ በኢየሱስ ክርስቶስ ሊታረቃቸው ወደደ፡፡ ‹‹እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፡፡››(2ቆሮ5፡19) ዓለም ግን ለእርቅ የተዘረጋውን የእግዚአብሔርን እጅ በመቀበል ፈንታ ኢየሱስን አልቀበልም አለች፡፡ ሰዎች ጌታ ኢየሱስ እንዲገዛቸው አልፈለጉም፡፡ የተሰቀለበትም ዋናው ምክንያት የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ይላል የሚል ነበር፤ ጉዳዩ ከተጠያቂነታቸው አንጻር ሲታይ እርሱን በጭካኔ ገድለውታል፡፡

የእግዚአብሔርን ልጅ በመስቀል ረገድ ዓለም በሙሉ ተባብሯል፡፡ ሄሮድስና ጲላጦስ ጓደኛሞች ሆነውበታል፡፡ በጊዜው ታላቅ የነበረው ሃይማኖት ባለሥልጣናት የነበሩ ሊቀካህናቱና ጻፎች በጊዜው ታላቅ ከነበረው የሮማ መንግሥት የፖለቲካ አስተዳደር መሪዎች ጋር አብረውበታል፡፡ በሦስት የዘመኑ ትላልቅ ቋንቋዎች የተጻፈ ጽሑፍ ከመስቀሉ በላይ አደረጉ፡፡ ሁሉም የሰይጣንን ምሪት በመቀበል በኅብረት የእግዚአብሔርን ልጅ ለመቃወም ቆሙ፡፡

መስቀሉ ላይ የዓለም ነገር በመላው ገሃድ ወጣ፡፡ ጌታ ሲሰቀል በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ማንነት ብቻ ሳይሆን በሰው የተዋቀረው መላው የሰው ልጅ ማኅበራዊ አስተዳደርም በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ያለው ጥላቻ ይፋ ሆነ፡፡ ኅብረተሰቡ ባለው አቅሙ ሁሉ እግዚአብሔርን ተዋጋ፡፡ በመሆኑም ከዚህ የሚበልጥ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ለዓለም ያስቀረው ሌላ ጸጋ የለም፡፡ ከመስቀል ወዲያ እግዚአብሔር ለሰው ሊሰጥ ያለው ምንም ነገር የለም፡፡ ለእግዚአብሔር የቀረለት የዚህ ዓለም ድርሻ ፍርድ ብቻ ነው፡፡ ያንንም እግዚአብሔር በቀኑ ይፈጽመዋል፡፡ ስለዚህም ሁኔታ በዮሐንስ ራእይ ከ6 እስከ 20 ባሉት ምዕራፎች ተጽፎ ይገኛል፡፡

ፍርዱን እስከ አሁን ድረስ ማዘግየቱም አሁንም የመዳንን ጸጋ ለግለሰቦች ለመስጠት ካለው ትዕግሥቱ የተነሳ ነው፡፡ እነዚህንም ግለሰቦች በንስሐ እንዲለወጡ ያዛል፤ ኑ እንታረቅ ብሎም ይጠራቸዋል (2ጴጥ.3፡8-9)፡፡

የክርስቶስ መስቀል

ልጁ ኃጢአታችንን በመስቀል ላይ በመሸከሙ ጻድቅ እግዚአብሔር ፊቱን ሰውሮበት ወልድ ለምን ተውከኝ ብሎ ቢጮኽም መታዘዝን በመፈጸሙ ዓለም በልጁ ላይ ሲተባበር እግዚአብሔር ግን ያለ ጥርጥር ከእርሱ ጋር በመሆኑ ዓለም በክፋቷ የሰቀለችውን ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሳው ሊባልለት ችሏል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በእነርሱ እጅ አልፎ መሰጠቱ ለሚድኑት ቤዛ ለመሆን ቢሆንም ኃጢአት ባላወቀው ላይ ይህን መሰል ክፋት በማድረጓና በእርሱም ባለማመኗ ምድር በእግዚአብሔር ፍርድ ስር ወድቃለች (ዮሐ.3፡18)፡፡

ከስቅለት ወዲህም ባለው ጊዜ ዓለም እንዲሁ በክፋቷ ናት፡፡ ይሁን እንጂ በመስቀሉ ዙሪያ ሁለት ወገኖችን እናያለን፡፡ እነርሱም በአንድ በኩል ክርስቶስን የገደለች፣ ከመሞቱና ከመቀበሩ ባሻገር ስለ እርሱ ምንም የማታውቅ ዓለም ስትሆን በሌላ በኩል ደግሞ የተሰቀለውና ከእርሱ ጋር የተባበሩት ናቸው፡፡

እግዚአብሔር አሁንም ጸጋውን ለግለሰቦች በስጦታ ያቀርባል፤ ነገር ግን ይህን የሚያደርገው በኢየሱስ በኩል ብቻ ነው፡፡ ለዚህም እግዚአብሔር ኢየሱስን ከሙታን አስነስቶ ‹‹ጌታም ክርስቶስም አደረገው›› (የሐዋ.ሥ.2፡36) ከፍርድ ማምለጥና ደኅንነትን ማግኘት የሚቻለው የተሰቀለውን በማመንና እርሱን በመቀበል ብቻ ነው፡፡ ‹‹እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው፡፡ ለተጠሩት ግን አይሁድ ቢሆኑ የግሪክ ሰዎችም ቢሆኑ የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው ክርስቶስ ነው፡፡›› (1ቆሮ1፡23-24)፡፡

አሁን አንተ ወንድሜ ኃጥእ ሰው ለኃጢአቱ ይቅርታ የሚያገኝበትና ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብበት ብቸኛ መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን አምነህ ተቀብለሃል፡፡ ደግሞም ጌታህ መሆኑን አምነህ ተቀብለኸዋል፡፡ ስለዚህም ከእርሱ ጋር ለዘላለም ተባባሪ ነህ፤ በመስቀል ላይ ከፈፀመው ከዚያ ክቡር ሥራው የተነሳም የሚመጣው ክብር ተካፋይ ነህ፡፡

ይህ ግን በምድራዊ ሕይወትህ የሚሰጥህ ትርጉም ምንድነው? በትክክል ለመናገር ዓለም ክርስቶስን ስትሰቅል እንደተሳሳተች በማመን ዓለም ከቆመችበት ክልል ኢየሱስ ክርስቶስ ወዳለበት ተሻግረህ የእግዚአብሔር ቤተሰብ ሆነሃል ማለት ነው፡፡ ይህን ደግሞ በግልፅ መናገር አለብህ፡፡ ይህን በልብህ ተቀብለህ ዝም ማለት በቂ አይደለም፡፡ ከዓለም መለየትህ በግልፅ መታወቅ አለበት፡፡ እስራኤል የበግ ደም ከተቀባው ቤት ውስጥ ተደብቀው አልቀሩም፤ ግብፅን ጥለው መሸሽ ነበረባቸው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል መቤዠታቸውን ማለትም መዳናቸውን የሚነግረን ባሕረ ኤርትራን ተሻግረው ካመለጡ በኋላ ነው፡፡ በ1ቆሮ.10 ላይ እንዳየነውም ባሕሩን መሻገር የጥምቀት ምሳሌ ተደርጎ ተወስዶአል፡፡

ስለዚህ ተቀባይነት አጥቶ በክፉው ዓለም ከተሰቀለው ከኢየሱስ ጋር ተባባሪ ሆነን ከጎኑ መቆማችንን በአደባባይ በጥምቀት አረጋግጠን ከእርሱ ጋር በዚህ ዓለም የሚገባንን ስፍራ መያዝ ይኖርብናል፡፡ ይህ እያንዳንዱ አማኝ በግል ሊያደርገው የሚገባው የእምነት መገለጫ ነው፡፡ ጥምቀት የተሰቀለው ጌታዬ ነው ብለን ለዓለም የምንነግርብትና ዓለምን የምንቃወምበት ከእርሱም ከጌታ ኢየሱስ ጋር መሆንን መምረጣችንን በግልፅ የምናሳይበት ነው፡፡ ‹‹ከክርስቶስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን?›› (ሮሜ.6፡3)

ስለሆነም በተጠመቅን ጊዜ በእግዚአብሔርና በመንግሥቱ በፍርድ ሥር ከወደቀው ከዚህ ዓለም ወጥተን ፍርዳችንን በትዕግሥት ወደ ተሸከመልንና ወደ ሞተልን አዳኝ ክልል መሻገራችንን እናሳያለን፡፡ ስለዚህም የሚበልጠው ፍርድ ካለበት ስፍራ፣ ከኃጢአት ኃይል፣ ከዓለም፣ ከሰይጣንና ከሕግ ነፃ ወጥተናል ማለት ነው፡፡ ሐናንያም ጳውሎስን ‹‹አሁን ስለምን ትዘገያለህ? ተነሣና ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ ከኃጢአትህም ታጠብ›› (የሐዋ.ሥ.22፡16) ያለው ለዚሁ ነው፡፡

እስከዚያን ጊዜ ድረስ የጳውሎስ ኃጢአቶች አልታጠቡምን? ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ዘላለማዊ ግንኙነት ከመረመርን በእርግጥ ኃጢአቱ ተወግዶለት ነበር፡፡ ከጌታ ከተገናኘ በኋላ በአጋጣሚ ከመጠመቁ በፊት ሞቶ ቢሆን እንኳን ገነት ይገባ ነበር፡፡ ሐናንያም ወንድም ብሎ ጠርቶት የለምን? በምድር ላይ ካለው የእግዚአብሔር መንግሥት አኳያ ስናየው ግን ጳውሎስ ኃጢአቶቹ አልተወገዱለትም፡፡ ምክንያቱም በግልጥ ሰው እያየው እስካልተጠመቀ ድረስ በሰው ዓይን ሲታይ የተፈረደባት ዓለም ወገን ነውና፡፡

በ1ጴጥ. ምዕራፍ 3 በኖህ ዘመን የነበረውን ውኃ በተመለከተ ‹‹ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል››(1ጴጥ.3፡21) ተብሎ የተጻፈውም ለዚሁ ነው፡፡ ኖህ በፍርድ ውኃ በኩል ከተፈረደበት ቦታ እግዚአብሔር ወደ ተደሰተባትና በውኃው ወደ ፀዳችው ምድር እንደተሻገረ(ዘፍ.8፡21) እኛም በመስቀል ላይ ክርስቶስ በተሸከመው ኃጢአታችን ላይ ለወረደው የእግዚአብሔር ቁጣ ምሳሌ በሆነው በውኃ ተጠምቀን ከተፈረደባት ዓለም አልፈን የእግዚአብሔር ዓይን በደስታ ወደ ተመለከተው ማለትም የተሰቀለውና የሞተው ክርስቶስ ወዳለበት ቦታ እንሻገራለን ማለት ነው፡፡ በሐዋ.ሥራ 2፡40 ላይ ጴጥሮስ ከዚህ ጠማማ ትውልድ ዳኑ ብሎ የተናገረውና ሰዎቹም ቃሉን ተቀብለው የተጠመቁት ለዚህ ነው፡፡

አሁንም ዳግመኛ የምጠይቀው ተጠምቀሃል ወይ? ካልተጠመቅህ በምድር እስካለህ ድረስ ክርስቲያን ተብለህ አትቆጠርም፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቃል እንደሚፈልገው በግልፅ መስክረህ ራስህን አልለየህምና ነው፡፡ በጌታ ኢየሱስ ሞት ምክንያት የኃጢአት ይቅርታ አግኝተህ ዘላለማዊ ሕይወት እንደተሰጠህ ካመንክና በዘለዓለምም ክብር ከእርሱ ጋር ኅብረት እንዳደረግህ ካወቅህ በዚህ ምድር እስካለህ ድረስ ታዲያ ለምን ከእርሱ ጋር ኅብረት ማድረግህን በግልፅ በጥምቀት አትመሰክርም? እርምጃው በዓለም ሰዎች የተናቀና የተጠላ ቢሆንም መፈፀም ይገባሃል፡፡

በተናገርኩት ነገር ጥምቀትን በተመለከተ ሁሉንም ነገር አልጻፍኩም፡፡ ትኩረት ያደረግኩት ቀዳሚው ትርጉም ላይ ነው፡፡ ዋናው መታወቅ ያለበትም ደግሞ ይህ ነው፡፡

ከሰላምታ ጋር በጌታ ወንድማችሁ

ምዕራፍ 15 የጌታ እራት

ውድ ወገኖቼ

ባለፈው ጊዜ እንደነገርኳችሁ ስለጌታ እራት ልጽፍላችሁ እወዳለሁ፡፡
ሁለቱ ታላላቅ የክርስትና መንፈሳዊ ሥርዓታት ማለትም ጥምቀትና የጌታ እራት ከሞተልን ከጌታችን ከኢየሱስ ጋር ያለንን ኅብረት ያመለክታሉ፡፡ ባለፈው እንዳየነው ጥምቀት ከዓለም አኳያ ሊኖረን ከሚገባ ውጫዊ ስፍራ ጋር የተያያዘ ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህም ጥምቀት የእያንዳንዱ ሰው ግላዊ ጉዳይ ነው፡፡ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2 ላይ ሦስት ሺህ ያህል ሰዎች ቢጠመቁም ለእያንዳንዱ ተጠማቂ ጥምቀቱ የግል ጉዳይ ነበር፡፡ እርስ በእርሳቸውም ኅብረት አልነበራቸውም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የጌታን እራት ስናይ እንደጥምቀት ሁሉ እርሱም ለዚህ ምድር የተሰጠን ሥርዓት ነው፤ ይሁን እንጂ በእኛ ከዓለም በተለየነው መካከል እንደ ክርስቶስ አካልነታችን ካለን ኅብረት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ስለዚህ ከጌታ እራት አንጻር ሲታይ የእርስ በርስ ኅብረት ዋነኛ ጠባይ ነው፤ ለአንድ ግለሰብ ዳቦና ወይን አዘጋጅቶ ብቻውን የጌታን እራት መውሰድ ፍጹም ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የሚቃረን አሠራር ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከክርስቶስ ጋር ያላትን አንድነትና የማንነቷን እውነት ለመግለጥ ልዩ ተልእኮ የተሰጠው ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ የአማኞች ማኅበር በጻፈው መልእክቱ ምንም እንኳ ራሱ የተጠመቀና አልፎ አልፎ ሌሎችንም ያጠመቀ ቢሆንም ‹‹ለማጥመቅ ክርስቶስ አልላከኝምና›› (1ቆሮ.1፡17) ሲል ይታያል፡፡ ነገር ግን የጌታን እራት በተመለከተ በዚሁ መልእክቱ ‹‹ለእናንተ የሰጠሁትን ከጌታ ደግሞ ተቀብያለሁና›› (1ቆሮ.11፡23) በማለት ስለ ጌታ እራት ልዩ መገለጥን ከጌታ እንደተቀበለ በማስታወቅ ሁለት ምዕራፎችን በዚሁ ጉዳይ ላይ ጽፏል፡ ፡

ሰው በግል ሊያደርገው የሚገባው ነገር በቅዱሳት መጻሕፍት ትልቅ ስፍራ ተሰጥቶታል፡፡ እያንዳንዱ ሰው በግሉ አምኖ መለወጥ አለበት፤ በግሉም ወደ እግዚአብሔር መቅረብ፣ በግሉም በክርስቶስ ኢየሱስና በደሙ ማመን አለበት፡፡ በግሉም ከተሰቀለውና በዓለም ዘንድ ከተጠላው ጋር በጥምቀት የመነቀፍን ስፍራ መያዝ ይኖርበታል፡፡ አንዳንድ በስመ ክርስትና ያሉ ሃይማኖት ድርጅቶች አማኙ በግሉ ሊወስን በሚገባው የክርስትና ጉዳዮች ላይ የቤተክርስቲያን አባል ሆኖ ቤተክርስቲያን በምታደርግለት ሥርዓት በመሳተፍ ካልሆነ በቀር ዘላለማዊ መዳን እንደማይገኝ አድርገው እንዲያስቡ በማድረግ ሰዎችን ያስታሉ፡፡ በአንጻሩ ሌሎች ደግሞ በጋራ በማኅበር ሊያደርጉት የሚገባቸውን ጨርሶ ችላ በማለትና ሁሉንም ነገር በግል የሚከናወን አድርጎ ሁሉም በተናጥል በየሐሳቡ እንደወደደ የሚሻውን ከሚመስለው ጋር እንዲያከናውን መፍቀዳቸው ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ነገር ግን በቅዱሳት መጻሕፍት ኅብረት በማድረግ ታላቅ በረከት እንዳለ ግልጽ ነው፡፡

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን የእራቱን ሥርዓት ሲመሠርት ደቀመዛሙርቱ የተሰባሰቡት በአጋጣሚ አልነበረም፡፡ መሰባሰቡ የግድ አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡ የጌታ እራት በሥርዓት የተደነገገው ለጌታችን ሞት መታሰቢያ እንዲሆን ነው፡፡ ከዚህ ተለይቶ የማይታየው ሌላው እውነታ ደግሞ የጌታ እራት መፈፀም ያለበት የክርስቶስ አካል በሆነ ኅብረት መሆኑ ነው (1ቆሮ.10፡16-17)፤ የጌታን እራት በተናጠል መውሰዱ ትርጉሙን የሳተ እንዲሆን ያደርገዋል ማለት ነው፡፡ በጌታ እራት የሚሳተፍ ግለሰብ መሳተፍ የተገባው ሰው መሆን ይኖርበታል፡፡ ክርስቶስ ይህን ሥርዓት ደንግጎ ለደቀመዛሙርቱ ሲያስተላልፍላቸው ይናገራቸው የነበረው በነጠላ ሳይሆን በብዙ ቊጥር ነበር፡፡ ይህም በኅብረት እንጂ በግል የማይወሰድ መሆኑን ያሳያል፡፡ ከወንጌላት ሌላ ስለዚህ በሚናገሩ ብቸኛ ምንባቦች ማለትም በ1ቆሮ.10 ና 11 ስለአፈፃፀሙ በዝርዝር ተጽፎ እናገኛለን፡፡

የጌታ እራት አመሠራረት

ማቴ.26፣ ማር.14 እና ሉቃ.22 የጌታ እራት የተደነገገበትን ሁኔታ የሚያሳዩን ምዕራፎች ናቸው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ምንባቦች ይህ የተከናወነው ጌታ ይሁዳ እንዴት አሳልፎ እንደሚሰጠው ከተናገረ በኋላ እንደሆነ ያመለክታሉ፤ ከዚያም ይህ ሰው ጥሎ ወጣ፡፡ ይሁን እንጂ ከሉቃስ አጻጻፍ ይሁዳ ጥሎ የወጣው በማዕድ ከተቀመጡ በኋላ እንደሆነ መደምደም ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሉቃስ በወንጌሉ በሙሉ ሲጽፍ የነገሮችን የሥነ ምግባር ታላቅነትን እንጂ የታሪክን ቅደም ተከተል የማይጠብቅ ሆኖ እናገኛለን፡፡

በአጠቃላይ ከእነዚህ ምንባቦች እንደምንረዳውም ይህ የጌታ እራት ሥርዓት በፋሲካ በዓል ጊዜ እንደተከናወነ ማየት ይቻላል፡፡ ይህም በዓል በዘጸአት 12 መሠረት ሕዝበ እስራኤል ከእግዚአብሔር ፍርድ ይድኑ ዘንድ በግብፅ ለታረደው በግ መታሰቢያ ለማድረግ ሲካሄድ የቆየ ሥርዓት ነው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ አሁን እውነተኛው የፋሲካ በዓል በግ የሚሠዋበትና (1ቆሮ.5፡7) ደሙም ስለ ብዙዎች የኃጢአት ይቅርታ የሚፈስበት (ማቴ.26፡28) ጊዜ መድረሱን እናያለን፡፡ በዚህ ምሽት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተይዞ እንደሚሰቀል፣ በሥጋው ኃጢአታችን በእንጨት ላይ እንደሚሸከም (1ጴጥ.2፡24)፣ በእኛም ፈንታ ኃጢአት እንደሚሆንና (2ቆሮ.5፡21) ይህም በእግዚአብሔር መተውን እንደሚያስከትልበት ተረድቶአል፡፡ እኛ ነጻ እንወጣ ዘንድ እርሱ ሊከፍለው የሚገባውን ዋጋ አውቋል፡፡ ከጥቂት ሰዓታት በኋላም በጌቴሴማኒ ሰይጣን በዚያች የመጨረሻ ሰዓት እንኳን እርሱን ከመታዘዝ መንገድ ለማውጣት ይችል እንደሆነ ለመሞከር ለጌታ የሚያስከፍለውን ዋጋ በፊቱ ባስቀመጠ ጊዜ የሚከፍለው ዋጋ ትርጉም ለጌታ ምን እንደነበር መመልከት እንችላለን፡፡

በዚያች ሰዓት ጌታ የደቀመዛሙርቱን ኅብረት ፈልጎ ነበር፡፡ ወዲያውኑም በጌቴሴማኒ ለደቀመዛሙርቱ ‹‹በዚህ ቆዩ ከእኔም ጋር ትጉ›› ሲላቸው እናገኛለን (ማቴ.26፡38) ቀጥሎም ወደ እነርሱ ተመልሶ ተኝተው ባገኛቸው ጊዜ እያዘነ ከእኔ ጋር አንዲት ሰዓት እንኳን ልትተጉ አልቻላችሁምን? እንዳላቸው እናነባለን (ማቴ.26፡38-40)፡፡ ስለዚህም እርሱ ጌታ ኢየሱስ አልፎ በተሰጠባት በዚያች ሌሊት ይህንን ሥርዓት እስኪመጣ ድረስ የሞቱ መታሰቢያ እንዲሆን ደነገገ (1ቆሮ.11፡23)፡፡

ይህ ነገር ለደቀመዛሙርቱ አዲስ ነገር አልነበረም፡፡ በጥምቀት እንዳደረገው ሁሉ የቆየ የፋሲካ በዓል ልማድን በመውሰድ ከራሱና ከሞቱ ጋር በማያያዝ አዲስና ጥልቅ ትርጉም ያለውን ሥርዓት ሰጣቸው፡፡ በኤር.16፡5-7 ከተጻፈው አይሁድ የእዝን እንጀራ ልማድ እንደነበራቸውና በለቅሶ ቤት የተገኘ ሁሉ ለሟች ወዳጃቸው መታሰቢያ ከእዝኑ እንጀራ ይበሉ ይጠጡ እንደነበር መገንዘብ ይቻላል፡፡ እግዚአብሔርም ራሱ በግብፅ ለታረደው በግና በበጉ ደም ከራሱ ከእግዚአብሔር ፍርድ ድነው ከፈርዖን ጽኑ እጅ ነጻ ለወጡበት ድንቅ የአምላካቸው መታደግ መታሰቢያ ይሆናቸው ዘንድ የፋሲካን በዓል ሥርዓት ሠርቶላቸው ነበር፡፡ በዚህ መታሰቢያ በዓል ላይ ጽዋ ስለመኖሩ አናይም፡፡ ነገር ግን ጌታችን ጽዋን አክሎበታል (ሉቃ.22፡17) የዚህን የአዲስን ሥርዓት ምሳሌ የሆነውን ፋሲካን መንደርደሪያ አድርጎ በመጠቀም አዲስን ሥርዓት ለመመሥረት ‹‹እንጀራም አንስቶ አመሰገነ፤ ቆርሶም ሰጣቸውና ስለእናንተ የሚሰጠው ሥጋዬ ይህ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ፡፡ እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንስቶ እንዲህ አለ፤ ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው›› (ሉቃ.22፡19-21)፡፡ አይሁድ ይህን የመታሰቢያ በዓል ሲያከብሩ የሚበሉትን ዳቦ ሲባርኩ ‹‹ይህ አባቶቻችን በግብፅ ምድር የበሉት የመከራ እንጀራ ነው›› እያሉ ይቆርሱ እንደነበር ጌታም በዚያ ምትክ የሚሰጣቸውን ዳቦና ጽዋ ‹‹ይህ ሥጋዬ ነው ይህ ደሜ ነው›› ብሎ እንደሰጣቸው እንመለከታለን፡፡

የጌታ እራት ትርጉም

‹‹ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት›› ብሎ እስከሰጠን ድረስ የጌታችን እራት እርሱን የሚያስታውሰን ነው ማለት ነው፡፡ በሥጋ ሳይገለጥ ከአብ ጋር የነበረውን ክብሩን ወይም በምድር ሳለ ስለሠራው ሥራ የሆነ መታሰቢያ ሳይሆን ‹‹ይህን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁ›› (1ቆሮ11፡26) እንደተባለው ሞቱን የሚያሳስበን ነው፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በመከራ የሚደቀውን ሥጋውን የሚወክለውን ዳቦውን መጀመሪያ ቆርሶ ሰጣቸው፡፡ ከዚያም ወይኑን ከዳቦው ለይቶ ቆይቶ ለሚፈሰው ደሙ መታሰቢያ አድርጎ ሰጣቸው፡፡ ዳቦውንና ወይኑን ለያይቶ እንጂ ቀላቅሎ አልሰጣቸውም፡፡ ይኸውም የሥጋውንና የደሙን መለያየት ያሳያል፤ ይህም ሞቱን ይናገራል፡፡

የጌታ እራት ዋናው ጥቅሙም ይህ ነው፡፡ መድኃኒታችን በአንድ ወቅት ሞቶ እንደነበረ በኅብረት የሚደረግ የእርሱ መታሰቢያ ነው፡፡

ዝግጅቱም በጣም ቀላል ነው፡፡ ዳቦ በማንኛውም አገር በቀላሉ የሚገኝ ምግብ ሲሆን ወይኑም እንዲሁ እዚህ አገር ሻይና ቡና እንደምንጠጣው በዚያ ምድር የሚዘወተር መጠጥ ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህ ማዕድ ጋር ጌታ ያያያዘው ትርጉም ታላቅ ነው፡፡

ምግቡ በሌላ ጊዜ ከምንመገበው ማዕድ የተለየ ነገር የለውም፡፡ በትንሽ ጉርሻና ጥቂት ጠብታም መወሰን የለበትም፡፡ እንደሌላው ዳቦ ይበላል፤ እንደሌላም ወይን ይጠጣል፡፡ ሲዘጋጅም ሆነ ከዝግጅት በኋላ ዳቦው እንደማንኛውም ዳቦ ነው፤ ወይኑም እንደማንኛውም ወይን ነው፡፡ በሚቀርበው ምስጋናም በዳቦውና በወይኑ ላይ የሚመጣ መለወጥ የለም፡፡ ከዚህ ጋር የሚቀርበውን ምስጋና በተመለከተ በ1ቆሮ.11፡24ና በሉቃ22፡19 ላይ ‹‹አመሰገነ›› የሚል እናነባለን፡፡ ያው አንዱ ድርጊት በማቴ.26፡26 እና በማር.14፡22 ላይ ‹‹ባረከ›› ተብሏል፡፡ በሁለቱ መካከል የትርጉም ልዩነት የለም፤ ጳውሎስስ እግዚአብሔርን ባርኮ የለም ወይ? (ኤፌ.1፡3) በማቴ.14፡19 ጌታችን አምስት እንጀራና ሁለት ዓሳ ባርኮአል፤ ነገር ግን ከባረከ በኋላ አምስቱ እንጀራና ሁለቱ ዓሳ ወደሌላ ነገር ተለውጠዋል የሚል ማንም የለም፡፡

‹‹ካህኑ በሚናገረው ምስጢራዊ ቃል ዳቦውና ወይኑ ወደ እውነተኛ የክርስቶስ ሥጋና ደም ይለወጣል›› የሚለው የሮም ካቶሊክ ትምህርትም ሆነ ወይም ‹‹ክርስቶስ ራሱ በአካል ከዳቦው ጋር በዳቦው ውስጥ ይገለጣል›› የሚለው የሉተራን አመለካከት በቅዱሳት መጻሕፍት ምንም ድጋፍ የለውም፡፡ ጌታ ራሱን በተመለከተ ሲናገር በተደጋጋሚ ምሳሌዎችን ተጠቅሟል፡፡ በዮሐ.10 እርሱ ‹‹የበጎች በር›› እና ‹‹መልካም እረኛ›› እንደሆነ ተናግሯል፡፡ በዮሐ.14 ‹‹እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ›› ብሏል፡፡ በመሆኑም ጌታ ምሳሌ እየተጠቀመ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

[ከመታሰቢያነቱ አልፎ ወደ ሥጋው ይለወጣል ወይም ራሱ ክርስቶስ ይገለጥበታል ብሎ ማመን እርሱ አንዴ የፈፀመውን የማዳን ሥራ መካድ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከመለኮት ጋር ተዋህዶ ከድንግል ማሕፀን ከወጣውና በመስቀል ላይ ከተሠዋው ሥጋውና ደሙ ጋር ኅብረት እንዳለው ሐዋርያው በ1ኛ.ቆሮ.10፡16 ላይ በግልጥ አስቀምጦታል፡፡ ይህም ኅብረት እኛ የምንባርከው እንጀራ(ዳቦ) እና ጽዋ አሁን በክብር ላለው ሳይሆን ለታረደው በግ መታሰቢያ መሆኑ ነው፡፡ የምንቆርሰው እንጀራ ለዚያ መከራን ለተቀበለው፣ ለተሰቀለው፣ ለታረደውና ለሞተው በግ ዓይነተኛ መታሰቢያ ነው፡፡ የእርሱ ማለትም የክርስቶስ የሆኑቱ የታረደውን በግ እርሱንም ኢየሱስ ክርስቶስን እንደተሰቀለ ሆኖ በፊታቸው ተስሎ በሚቆርሱት እንጀራና በሚባርኩት ጽዋ ውስጥ በእምነት ያዩታልና፡፡ በመከራና በሞት የደቀቀው ሰውነቱ በሚቆረሰው እንጀራ አማካኝነት ይታሰባል፡፡

ዳቦው ወይም እንጀራው እግዚአብሔር ከሰጠን የመቅመስ፣ የማየትና የማሽተት ስሜቶች ውጭ በሆነ መንገድ ወደ ክርስቶስ አማናዊ ሥጋ ይለወጣል ብሎ ማሰብ ራስን በማታለል እግዚአብሔርን ባልሆነው ነገር ለማክበር መጣር ነው፡፡ ምክንያቱም ዳቦው ከጸሎቱ በፊትና በኋላ ምንም ዓይነት ለውጥ እንደሌለው ለማንም ራሱን ለማይዋሽና ዳቦውን ለሚያይ ሁሉ ግልጥ ነውና ነው፡፡ ቃሉንም በሚገባ ብንመለከተው ከመባረኩ በፊት ‹‹ይህ የምንባርከው እንጀራ›› ተብሎ ሲገለጥ ከጸሎቱም በኋላ እንጀራ (ዳቦ) እንጂ ሌላ አለመሆንኑን ሲያመለክት ‹‹ያን አንዱን እንጀራ እንካፈላለን›› ይላል (1ቆሮ10፡16-17)፤ በ1ቆሮ.11፡26 ‹‹ይህን እንጀራ የበላ፣ ይህን ጽዋ የጠጣ›› ይላል እንጂ ‹‹ሥጋና ደም›› አይልም፡፡ ዳቦው መልኩንና ጣዕሙን አይቀይርም፤ ዳቦ እንደሆነ ይቆያል፡፡ በጽዋውም ውስጥ ያለው በማቴ.26፡29 ‹‹እንካችሁ ጠጡ›› ካላቸው በኋላ የጠጡትን ‹‹የወይን ፍሬ›› ብሎ እንደጠራው የወይን ፍሬ ወይንም ዘቢብ ብለን እንጠራዋለን እንጂ ደም አንለውም፡፡

ይህ ሥጋዬ ነው ማለቱም የሰጣቸው ሥጋውን ሆኖ አይደለም፤ ዳቦው የሥጋው ምሳሌ ሆኖ ነው እንጂ፡፡ ዮሴፍ ቤተሰቦቹ ፊቱን እንደሚያዩና እንደሚሰግዱለት በነዶ፣ በፀሐይና በጨረቃ ምሳሌ እንዳየ(ዘፍ.37፡5-11)፣ እንዲሁም እርሱ ዮሴፍ ለፈርዖን የተረጎመለት የሰባት የጥጋብና የሰባት የረሃብ ዓመታት እውነታ በሰባት ላሞችና እሸቶች ምሳሌ እንደተገለጠ(ዘፍ.41፡26-27)፣ ጌታም በዘሪው ምሳሌ፣ የስንዴውን ዘርና እንክርዳዱን ለዚህ ዓለም ሰዎች መስሎ እንደተናገረ(ማቴ13)፣ ጳውሎስም ሙሴ መትቶት ለእስራኤል ውኃ ያፈለቀውን አለት ‹‹ያም አለት ክርስቶስ ነበረ›› ብሎ እንደተናገረ(1ቆሮ.10፡4) የምንቆርሰው ዳቦም እንዲሁ ለጌታ ሥጋ መታሰቢያው ስለሆነ ጌታ ‹‹ይህ ሥጋዬ ነው›› ብሎአል፡፡ ከላይ እንደተገለጸው በዮሐ.10 ‹‹የበጎች በር ነኝ፤ መልካም እረኛ እኔ ነኝ›› በማለቱና እንደዚሁም በዮሐንስ 14 ስለራሱ ‹‹እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ›› ስላለ ሐረጉን በቁሙና በጥሬው ወስዶ ጌታን ከቁሳቁስ የተሠራ በር ነው፣ አስፋልት መንገድ ነው ወዘተ ብሎ መውሰድ እንደማይቻል የተረጋገጠ ነው፡፡ ምክንያቱም ጌታችን ይህንን የተናገረው ራሱን በምሳሌ ለመግለጥ በመፈለጉና እነዚህ ምሳሌዎችም ማንነቱን የመግለጥ አቅም ስላላቸው ነው፡፡

ይህም ብቻ አይደለም ጌታ ስለራሱ በሌላ ምሳሌም ተናግሯል፤ ራሱንና እንደዚሁም ሞቱና ትንሳኤው የሚያስከትለውን በረከት ወደ ምድር በምትወድቅ በስብሳ ብዙ ፍሬ በምታፈራ የስንዴ ቅንጣት መስሏል (ዮሐ.12፡24)፤ ታዲያ ይህ ማለት ዛሬም ሆነ ትናንት በዚህ ዓለም በየማሳው የሚዘሩና የተዘሩ ስንዴዎች ሁሉ የኢየሱስ ሥጋ ናቸው ማለት ነውን? አይደለም፡፡ ይህ የስንዴው መበስበስና ዳግመኛ ፍሬ ማፍራት ግን ለመከራውና ለሞቱ እንደዚሁም ለሚያምኑበት ሁሉ ይኸው መከራውና ሞቱ ለሚያስገኝላቸው በረከት ምሳሌ ሆኖ ያገለግለናል፡፡ ስንዴ ለሰው ምግብነት ከመቅረቡ በፊት በውድማ ተወቅቶ፣ በመንሽ ወይም በወንፊት ለነፋስ ተሰጥቶ፣ ከዚያም ተፈጭቶና ተቦክቶ በእሳት ላይ በምጣድ ይጋገራል፤ ይህም ስንዴ በብዙ መከራ ለተንገላታው፣ ለቆሰለው፣ ለተወጋውና ተሰቅሎ ሞቶ ለሚያምኑበት የእምነት ምግብ ለሆነው ክርስቶስ ዓይነተኛ መታሰቢያ ነው፡፡ ከስንዴ የሚዘጋጀው የጌታ እራትም እንዲሁ የክርስቶስ ሥጋ መታሰቢያ ነው፡፡

በዚሁ መልክ ወይኑም የክርስቶስ ደም መታሰቢያ ነው፡፡ ራሱም ‹‹እኔ የወይን ግንድ ነኝ›› ብሏል(ዮሐ.15፡1)፤ የወይኑም ጭማቂ ኃጥኣን ከበደል ለሚነጹበት ደሙ ዓይነተኛ መታሰቢያ ነው (ዘፍ.49፡11)፤ ይህም ወይን በጸሎት በክርስቶስ የደም ሥሮች ወስጥ ወደነበረው አማናዊ ደም አይለወጥም፤ ምክንያቱም ጌታም ‹‹እንካችሁ ጠጡ›› ካላቸው በኋላ የወይን ፍሬ ብሎታልና (ማቴ.26፡28-29)፡፡ ነገር ግን እኛ የምንጠጣው የወይን ፍሬ በደም ሥሩ ውስጥ እንዳለው ያለ ሳይሆን ለፈሰሰው ደሙ መታሰቢያ ነውና ጌታም ቀድሞ በስንዴ ምሳሌ ራሱን እንደገለጠ አሁንም የወይኑን ፍሬ በማግስቱ በመስቀል ላይ ለሚፈሰው ደሙ በዋዜማው ምሽት ወይኑን አንስቶ ይህ ደሜ ነው እንካችሁ አለ፡፡ የወይን ጭማቂ አስቀድሞ በመጭመቂያው ውስጥ ተጨምቆ ይገኛልና በጌታ እራት የምንጠጣው ወይን ከበደላችን የተነሳ ክርስቶስ በፍርድ መጭመቂያ ውስጥ በገባ ጊዜ ከእግሮቹ፣ ከእጆቹና በጦር ከተወጋ ጎኑ በመስቀል መከራ ተጨምቆ ከእርሱ ለፈሰሰው ደሙ ምሳሌ ነው፡፡ የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን?(1ቆሮ10፡16) የተባለበት ምክንያቱም ይኸው ነው፡፡ ‹‹ይህንን ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁ›› (1ቆሮ.11፡26) እንደተባለ የሚያምኑት ሁሉ እንደሞተላቸው ለማሰብ ተሰብስበው ጽዋውን ያከብራሉ፡፡

ዮሐንስ ምዕ. 6 ስለ ጌታ እራት ይናገራልን?

ይህ ምዕራፍ ስለ ጌታ እራት የሚናገር አይደለም፡፡ የምዕራፉን አጀማመር ስንመለከት ከመጀመሪያው አንስቶ እስከ ቊጥር 15 ያለው ጌታ አምስት ሺህ ለሚያክሉ ሰዎች አምስት እንጀራና ሁለት ዓሳ አበርክቶ መመገቡንና ከዚህም የተነሳ ሰዎቹ ሊያነግሡት ፈልገው ጌታ ከእነርሱ ፈቀቅ ብሎ እንደሄደ ያሳየናል፡፡ ቀጥሎ ያለውም አይሁድ ጌታን አግኝተውት የተነጋገሩትን ይገልጥልናል፡፡ በዚህም መሠረት ጌታ እነዚህ ሰዎች ለምን እንደፈለጉት አውቆባቸው ‹‹ለሚጠፋ መብል አትሥሩ›› ሲላቸው እናያለን፡፡ እነርሱም መልሰው ‹‹የእግዚአብሔርን ሥራ እንድንሠራ ምን እናድርግ›› ብለው በጠየቁት ጊዜ ‹‹ይህ የእግዚአብሔር ሥራ እርሱ በላከው እንደታምኑ ነው›› ብሎአቸዋል፡፡ ቀጥሎም እንድናምንብህ እንደሙሴ ምልክትን አሳየን ባሉት ጊዜ መናን በምድረ በዳ ከሰማይ ያወረደላቸው እግዚአብሔር እንጂ ሙሴ አለመሆኑን ነግሮአቸው በቊጥር 35 ላይ ‹‹የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም በእኔ የሚያምንም ሁልጊዜ ከቶ አይጠማም›› በማለት ያስተምራቸው ጀመረ፡፡ ቀጥሎም በቊጥር 39 ላይ ‹‹ልጅን አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኝ የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሳዋለሁ›› አላቸው፡፡ ሰዎቹም እንደዚህ ማለቱ በመንፈስ ቅዱስ ከማህፀን የወጣውን ሥጋውን ትበላላችሁ ያላቸው መስሎአቸው ቢያንጎራጉሩ ከቊጥር 47 እስከ 59 ባለው ክፍል ‹‹እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ ሞቱም ሰው ከእርሱ በልቶ እንዳይሞት ከሰማይ አሁን የወረደ እንጀራ ይህ ነው፡፡ ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው፡፡ ... እውነት እውነት እላችኋለሁ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም፤ ሥጋዬን የሚበላ ደሜን የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፡፡ ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና፡፡ ሥጋዬን የሚበላ ደሜን የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ ... የሚበላኝ ደግሞ ከእኔ የተነሣ ሕያው ይሆናል ... ይህን እንጀራ የሚበላ ለዘላለም ይኖራል›› በማለት ለቅፍርናሆም ሰዎች አስተማረ፡፡ ቀጥሎም ይህ ትምህርት ለደቀመዛሙርቱም ግልፅ ሳይሆን በመቅረቱ ጌታ በቊ.63 ላይ ‹‹ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው፤ ሥጋ ምንም አይጠቅምም እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው›› አላቸው፡፡ የዘላለምን ሕይወት ማግኘትን በተመለከተም በእምነት እንደሆነ ጌታ በቊጥር 40፣ 47እና 48 በእርሱ ማመንን ቅድመ ሁኔታ አድርጎ አስቀምጧል፡፡ ሰዎች እንዳይራቡም መፍትሄው ወደእርሱ መምጣት እንደሆነና ላለመጠማትም መፍትሄው በእርሱ ማመን መሆኑን በቊጥር 35 ላይ በግልጥ ተናግሯል፡፡ ጌታ ይህን በማለቱም እርሱ በበደላቸው ሙታን ለሆኑ ኃጥአን እውነተኛ እንጀራቸው መሆኑን ገልጧል፡፡ ‹‹አይራብም፣ አይጠማም›› ማለቱም በሥጋ አይራቡም አይጠሙም ማለት አይደለም፤ ወይም የጌታን እራት የበሉ አይራቡም አይጠሙም ማለትን አያመለክትም፤ ምክንያቱም ከጌታ እራት የተሳተፉ ሐዋርያትም ምግብና መጠጥ አላቆሙምና ነው፡፡ ታዲያ እዚህ ላይ ሥጋዬና ደሜ ያለውስ የጌታን እራት ነውን? በትክክል ለመናገር አይደለም፤ ጌታ በዚህ ምዕራፍ ፈጽሞ ስለዚህ አላነሳም፤ ምክንያቱም ይህ ታሪክ በተነገረበት ጊዜ ገና ሥርዓቱ አልተመሠረተምና፡፡

ይህ ሥጋና ደምም በአፍ ገብቶ በጉሮሮ የሚዋጥ እንዳይደለ ሲያመለክትም ጌታ ራሱ በጥያቄ ውስጥ ለነበሩት ደቀመዛሙርቱ ‹‹ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ›› እንጂ በሆድ የሚገባ ‹‹ሥጋ›› እንዳይደለና ሥጋው በመስቀል ላይ በመሥዋዕትነት በመቅረብ እንጂ ወደ ሆድ እንዲገባ ቢበላ እንኳን የዘላለም ሕይወትን እንደማይሰጥና ምንም እንደማይጠቅም ‹‹ሥጋ ምንም አይጠቅምም›› በማለት ነግሮአቸዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ታዲያ ሥጋዬና ደሜ ያለው ምን ሊሆን ይችላል? ብለን ብንጠይቅ መልሱ ከዚያው ይገኛል፡፡ ይህንኑ ጌታ ሲያስረዳቸው ‹‹እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው›› ብሏቸዋል፡፡ ስለዚህ በመንፈስ ቅዱስ የተነገረ የክርስቶስ ትምህርት ማለትም ቃሉ ለሰው በሕይወት የሚያኖረው እንጀራ ነው፡፡ አስቀድሞ እንደተነገረው ‹‹ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም›› ተብሎ የተነገረለት ከእግዚአብሔር ዘንድ የወጣ የሕይወት ቃል እርሱ ጌታ ኢየሱስ ነው፡፡ በዚሁ ምዕራፍ ውስጥ ብዙዎች ከደቀመዛሙርቱ መካከል በተሰናከሉ ጊዜ ጴጥሮስ ግን ከጌታ የማይለይበትን ምክንያት ሲያቀርብ በቊጥር 68 ላይ እኛስ ከአንተ ወዴት እንሄዳለን ‹‹አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ›› በማለት ተናገረ እንጂ አንተ የሚበላ ሥጋ የሚጠጣ ደም አለህ አላለውም፡፡ ቃል ይበላል ወይ ብንል ሕዝቅኤል ‹‹የሰው ልጅ ሆይ ይህን መጽሐፍ ብላ ሄደህም ለእስራኤል ቤት ተናገር አለኝ፡፡ አፌንም ከፈትሁ መጽሐፉንም አጎረሰኝ፡፡ እርሱም የሰው ልጅ ሆይ አፍህ ይብላ በምሰጥህ በዚህ መጽሐፍ ሆድህን ሙላ አለኝ እኔም በላሁት በአፌም ውስጥ እንደማር ጣፈጠ›› በማለት አልተናገረምን? መብላት መጠጣቱስ እንዴት ይከናወናል ብለን እንጠይቅ ይሆናል፡፡ ጌታን በሙሉ ልብ አምኖ የጌታን ቃል ዘወትር በመንፈስ ቅዱስ በማንበብና በመስማት ማሰላሰልና በእርሱም መኖር፣ ቃሉን መጠበቅና በቃሉ መመራት ማለት ነው፡፡ አበላሉና አጠጣጡም ኢየሱስን ማመንና ወደእርሱ መምጣት ነው፡፡ ይህን ብናደርግ ቃሉ በውስጣችን በክርስቶስ የሚረካ ሕያው የሆነ ሕይወትን ይፈጥራል፡፡ ያን ጊዜ ነፍሳችን ሌላውን አትራብም አትጠማም፡፡ ይህን ቢያደርጉ በበደላቸው ሙታን የሆኑ ሁሉ ሕይወትን ያገኛሉ፡፡

የጌታችን ሞት

የጌታችን ሞት ታላቅ ትርጉምን ያዘለ ነው፡፡ እርሱ ጌታ ሲሆን ሞተ፤ ምንኛ ታላቅ ጸጋ፣ ፍቅርና ምሕረት ነው! ድንቅ የእግዚአብሔር ምክር ነው፡፡ የሕይወት መስፍን የሆነውና የሕይወት ምንጭ የሆነው እርሱ ሞቶ ተቀበረ፡፡ ይህ ሁሉ የእኛን ቦታና ፋንታ ሙሉ በሙሉ ለመውሰዱ ማረጋገጫ ነው፡፡ በሥጋው ኃጢአታችንን መሸከሙ ብቻ ሳይሆን በእኛ ፋንታም ስለእኛ ኃጢአት ሆነ፡፡

ይህን ሁሉ ስናይ ምንኛ ታላቅ የምስጋና፣ የውዳሴና የአምልኮ ስሜት በልባችን ውስጥ ይቀሰቀሳል! ለእኛ ያለው ፍቅሩ እጅግ ታላቅ በመሆኑ እኛ እንድንድን ይህንን ታላቅ ዋጋ ከፈለልን፡፡

‹‹ፍቅር እንደሞት የበረታች ናትና፤ ቅንዓትም እንደ ሲኦል የጨከነች ናትና፤ ፍንጣሪዋም እንደ እሳት ፍንጣሪ እንደ እግዚአብሔር ነበልባል ነው፡፡ ብዙ ውኃ ፍቅርን ያጠፋት ዘንድ አይችልም፤ ፈሳሾችም አያሰጥሙአትም፤ ሰው የቤቱን ሀብት ሁሉ ስለፍቅር ቢሰጥ ፈጽሞ ይንቁታል›› (መኃ.8፡6-7)

ከመሞት በላይስ እንደምን እግዚአብሔርን መታዘዝ ይቻላል? የእግዚአብሔርን ፈቃድ ካለመፈፀም የሚበልጥስ የከፋ ምን ሞት አለ? እስከ ሞት መታዘዝ ያውም የመስቀል ሞትን ለመሞት ፈቃደኛ የሚሆን ምን አእምሮ ነው፡፡

ጌታ ኢየሱስም እንደ ማዕድ አዘጋጅ ሆኖ እርሱን እንድናስታውሰውና ሞቱን እንድንናገር ወደ ገበታው ይጋብዘናል፡፡ ወደዚህ ገበታ አንዳች ለመቀበል አንመጣም፡፡ የጌታ እራት ጸጋን የምንቀበልበት ምስጢር አይደለም፡፡ ይህን የሚያሳይ አንድም ጥቅስ የለም፡፡ ይሁን እንጂ ካለማስተዋል የተነሳ ሰዎች ለዚህ ማስረጃ ይሆናቸው ዘንድ የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 6ን ይጠቅሳሉ፡፡ ጌታ ከ19 ምዕተ ዓመታት በፊት በምድር ተሠቃይቶ መሞቱን እንድናስብ ወደ ማዕዱ ይጠራናል፡፡ ይህ ነገር ድኅረ ዓለምም አይረሳም፡፡ ራእይ 5 ላይ ጌታ ከዚህ በፊት በምድር በአንድ ወቅት እንደነበረው እንደታረደ በግ ቆሞ በሰማያት እንደታየ እናነባለን፡፡ ዮሐንስ ያየው የታረደው በግ እይታ ሰማያትን በምስጋናና በአምልኮ እንደሞላ ሁሉ አሁንም በዚህ ምድር ላይ ሞቱን ስንናገር በመካከላችን እንዲሁ ይሆናል፡፡ ወደ እርሱ መመልከት ልባችንን ይሞላል፡፡ ሞቱን ለማሰብ ስንሰበሰብም በዝማሬያችን፣ በምስጋና ጸሎታችንና በየጣልቃው በሚኖረን ፅሞናና ውዳሴያችን፣ ለእርሱ ያለን አድናቆትና አምልኮ ወደ ላይ ወደእርሱ ያርጋል፡፡

በዚህ ስብሰባ መሳተፍ የሚችሉት ግን ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው፡፡ ኃጢአታቸው ይቅር እንደተባለላቸው የሚያውቁና ከእግዚአብሔር ጋር የታረቁ ብቻ በዚህ ማዕድ መቀመጥ ይችላሉ፡፡ የሚካፈሉትም በዚህ አድራጎታቸው ከጌታ ጋርና ከሥራው ጋር ኅብረት እንዳላቸው ይመሰክራሉ (1ቆሮ.10፡16)፤ እዚህ ላይ በተለይም ኅብረት አለን ካልንና ስለ ኃጢአታችን የምንጨነቅ ከሆንን ጌታ የእርሱ የሆኑትን ለዘላለም ፍጹማን ያደረገበትን ፍጹም ሥራውን መካድ አይሆንብንምን?(ዕብ.10፡14)

በዚህ ስብሰባ ላይ ልዩ ተሰጥኦ ወይም በተለዩ ሰዎች የተያዘ ክህነታዊ ሥልጣን ስፍራ የለውም፡፡ ሁሉም አማኝ እንደ ካህን በመሆን ምስጋናና ውዳሴ ማለትም ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ (ዕብ.13፡15) ይዞ ይቀርባል፡፡ ሐዋርያም ቢቀርብ በዚህ ስብሰባ ላይ የጌታን ሞት ለማሰብ እንደማንኛውም አማኝ ይቀርባል፤ ምንም እንኳን በአማኞች ጉባኤ መካከል ታላቅ ስፍራ የሚሰጠውና ምናልባትም ታላቅ የአገልግሎት ስጦታ ያለው ቢሆን እንኳን ከጉባኤው ጋር አብሮ በመሆን የተደረገለትን እያሰበ አብሮአቸው ያመልካል፡፡ እኛስ ጥሪውን ሰምተን ወደ ገበታው ቀርበናልን? የሰጠነው ምላሽስ አዎንታዊ ነውን?

የጌታ እራት መቼ መደረግ አለበት?

ለዘላለም በጉ ምስጋናና አምልኮ ሲቀበል ይኖራል፡፡ ቤተክርስቲያን በተመሰረተችበት በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ‹‹በየቀኑም በአንድ ልብ ሆነው በመቅደስ እየተጉ በቤታቸውም እንጀራ እየቆረሱ በደስታና በጥሩ ልብ ምግባቸውን ይመገቡ ነበር፡፡›› (የሐዋ.ሥ.2፡46) የኋላ ኋላ ሁኔታዎች እየተቀየሩ ሲሄዱ ግን በአንድ ላይ መሰባሰብ ባልቻሉበት ጊዜ ከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን አንድ ጊዜ እንጀራን ይቆርሱ ጀመር፡፡ ስለእነዚህ ነገሮች ሁሉ እንድናውቅ ፈቃዱ የሆነ ጌታ አውቀን እንጠቀምበት ዘንድ በቅዱሳት መጻሕፍት ተጽፎ እንድናገኘው አደረገልን፡፡ በሐዋ.ሥራ20፡7 እንደምናየው ወንድሞች እንጀራን ለመቁረስ ተሰብስበው እንደነበር እናነባለን፡፡ ምንም እንኳን ሐዋርያ ቢሆንም የተሰበሰቡት ጳውሎስን ለመስማት አልነበረም፡፡ የተሰበሰቡት ከዚህ ለላቀ ጉዳይ ማለትም እንጀራውን ለመቁረስ ነበር፡፡ ሆኖም ጳውሎስ ይናገር ዘንድ አጋጣሚውን ተጠቅሞበታል፡፡ ከላይ ከቀረበልን ከዚህ ማስረጃ አኳያ ለዚህ ዓላማ የመሰብሰብ ልማድ እንደነበራቸው መረዳት እንችላለን፡፡

በዚህ ዓይነቱ ቦታ ለመቀመጥ ፈቃድ አግኝተን ይህን አገልግሎት ማለትም እስኪመጣ ድረስ የጌታን ሞት መናገርን ለመፈፀም ይህ ድንቅ መብት እንደተሰጠን በአግባቡ ከተረዳንና ካወቅን፣ በይበልጥም በወደደንና ራሱንም ለእኛ በሰጠ በእግዚአብሔር ልጅ ‹‹ይህንን ለመታሰቢያዬ አድርጉት›› ተብለን ከተጠየቅንና ከእርሱ ከውድ ጌታ ጥሪ ከተደረገልን በተቻለን መጠን አዘውትረን ለማድረግ ልባችን አይናፍቅምን?

ይህንንም ለማድረግ ‹‹የጌታ ቀን›› ተብሎ ከሚጠራው፣ ጌታ ከሙታን ከተነሣባትና ከትንሣኤው በኋላም አከታትሎ ሁለት ጊዜ በተሰበሰቡ ደቀመዛሙርቱ መካከል ከተገለጠባት ቀን ሌላ ምን ቀን ይስማማናል? (ዮሐ.20)፡፡

ራስን መመርመር

ይህን በተመለከተ ራሳችንን እንድንመረምር ቃሉ ያሳስበናል፡፡ ራሳችንን የምንመረምረው ግን ሁሉም ክርስቲያን በጌታ እራት ሊሳተፍ ብቁ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ ምክንያቱም ይህን መጠራጠር የክርስቶስን ሥራ ብቃት መጠራጠር ነው፡፡ እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ ግን ለመሳተፍ የሚከለክል አንዳች ነገር በሕይወታችን እንዳለና እንደሌለ ማወቅ ነው፡፡

ይኸውም ማለት ለመቅረብ በተገባ ሁኔታ ውስጥ ሆነን መገኘት ማለት ነው፡፡ የጌታን እራት ከሌላው ገበታ የሚለየው አንዳች ነገር የለም፡፡ ዳቦውም ወይኑም ያው እንደሌላው ነው፡፡ ነገር ግን ይህ የክርስቶስ ማዕድ ነው፡፡ የማዕዱ ባለቤትም ጌታ ነው፡፡ ወደዚህ ስፍራ ስንቀርብ ወይኑ ስለእኛ ለፈሰሰው ደሙ ዳቦው ስለእኛ ለተሰጠው ሥጋው መታሰቢያ መሆኑን ተገንዝበን ይህ የምንካፈልበት ኅብረት ቅዱስ እንደመሆኑ መጠን ራሳችንን መመርመር ይጠበቅብናል፡፡ ከስፍራው ጋር የማይሰማማ ማንኛውም ነገር ካለ ከሕይወታችን መወገድ ይኖርበታል፡፡

የቆሮንቶስ ሰዎች ይህንን የዘነጉ ይመስላሉ፡፡ ለክርስቶስ ሥጋ ምሳሌነት የተለየውን እራት ከተራው እራታቸው ለይተው ሊያዩ አልቻሉም፡፡ ስለዚህ ጌታም በቅጣት መጣባቸው፡፡ ‹‹ስለዚህም በእናንተ ዘንድ የደከሙና የታመሙ ብዙዎች አሉ አያሌዎችም አንቀላፍተዋል›› (1ቆሮ.11፡30) እንደተባለው እኛ እርሱን በክብር ካላየነው ጌታ የራሱን ክብር ለመጠበቅ ይገደዳል፡፡ ይህም እንደቀላል የሚታይ ነገር አይደለም፡፡

ከሰላምታ ጋር
በጌታ ወንድማችሁ

ምዕራፍ 16 የጌታ ገበታ

ውድ ወገኖቼ

ባለፈው ደብዳቤዬ የእግዚአብሔር ቃል ስለጌታ እራት በወንጌልና በ1ቆሮ.11 የሚለውን አይተናል፡፡ ስለ ጌታ ኢየሱስ ሞት መታሰቢያ የሚደረግ ማዕድ እንደሆነም ተመልክተናል፡፡ አሁን ደግሞ የጌታ እራትን ሌላ ገጽታ እንመለከታለን፡፡ ይህም በ1ቆሮ10 የተጻፈውን ኅብረት በተመለከተ ይሆናል፡፡

ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ በጻፈው የመጀመሪያው ደብዳቤ ለብዙ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል፡፡ ከቀረቡለት ጥያቄዎች መካከል ለምሳሌ አንዱ ክርስቲያን ለጣኦት የተሠዋውን ሥጋ መብላት ይችል እንደሆነና እንዳልሆነ የሚጠይቅ ነበር፡፡ ሐዋርያው ይህንን ጥያቄ በምዕራፍ 8 እና 10 ላይ መልስ ሰጥቶበታል፡፡

የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ስለጣኦታት የነበራቸው ግምት ጣኦት ሕይወት የሌለው እንጨት ወይም ድንጋይ አይደለምን? ለእንደዚህ ዓይነቱ ነገር የቀረበን ምግብ ብንበላ ምን ጉዳት አለው? ለምን ከዚያው ከቤተ ጣኦት ሄደን አንበላም? ያለው አንድ አምላክ እስከሆነ ድረስ ጣኦታት ተራ ነገሮች ናቸውና የማያምኑትን አረማውያንን ቅር እንዳይላቸው ለምን አንበላም? የሚል ልዩ ልዩ አስተሳሰብ ነበራቸው፡፡

ሐዋርያውም ጣኦት በራሱ ምንም እንዳይደለ ተገንዝቧል፡፡ ነገር ግን በዘዳግም 32፡17 እንደተነገረው ከጣኦታት በስተጀርባ አጋንንት እንዳሉ ተጠቅሷል፡፡ ስለዚህ ለጣኦቱ የሚቀርበው መሥዋዕት ለአጋንንት የሚቀርብ የአጋንንት መሥዋዕት ነው ማለት ነው፡፡ በአረማውያንም ሆነ በአይሁድ ሥርዓት ሰው በመሠዊያ ላይ መሥዋዕትን ቢያቀርብ ወይንም በመሠዊያው ላይ የተሠዋውን ቢበላ ከመሠውያው ጋር ኅብረት እንዳለው ሐዋርያው አስረግጦ ጽፏል፡፡ ይህም አንድ ሰው በራሱ በግሉ የሌላውን ሰው ርኩሰት ባይከተልም ቅሉ በዚህ ዓይነት ተሳትፎ በሌላ ሰው ርኩሰት መሳተፍ እንደሚችል ያሳያል፡፡ ከእንደዚህ ዓይነቱ ነገር መራቅ ትልቅ ጥበብ ነው፡፡ ስህተት በሆኑ ሃይማኖታዊ ክንውኖች መካፈል ወይም በሚከናወኑበት አካባቢ መገኘት በራሱ ራስን ማሳት ነው፡፡ በልብ እስካላመንኩበት ድረስ በውጭ ስለሚደረገው ነገር መከታተል ምን ጉዳት አለው ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡ በእንደዚህ ዓይነት የስህተት ማህበር መካፈል ከሥነ ምግባር ውጭ መሆን ብቻ ሳይሆን ክርስቶስን ማቃለልና የሰይጣንን ኃይል ችላ ማለት ነው፡፡ ክርስቲያን ከሰይጣን ኃይል ነፃ የወጣው ሕያውንና እውነተኛውን እግዚአብሔርን ለማምለክ አይደለምን? እግዚአብሔርን ያከብር ዘንድ በውድ ዋጋ አልተገዛምን? መንፈስ ቅዱስ ይህን ትምህርት ተጠቅሞ ስለ ጌታ እራት ይናገራል፤ በአራቱ ወንጌላትም ያላየነውን ሌላውን ገፅታውን ያሳየናል፡፡ የወንጌላት ታሪክ በተፈጸመበት ጊዜ ገና ቤተክርስቲያን ያልነበረች ሲሆን ቤተክርስቲያንን የተመለከተ ትምህርትም ገና አልተገለጠም ነበር፡፡

እዚህ ላይ የተጠቀሱት ነገሮች ጠቃሚነታቸው በቀዳሚነት በመቅረባቸው የሚታወቅ ሲሆን ስለጌታ እራት አከባበር የሚናገረው ደግሞ በተከታይነት በምዕራፍ 11 ላይ ቀርቧል፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት የተለያዩ ጉዳዮችን የሚያነሱበት ቅደም ተከተል ጠቃሚነት አለው፡፡ በ1ቆሮ.10፡15-22 የተሰጠውን ትምህርት ሳያውቁ የጌታን እራት በትክክለኛው መንገድ መፈጸም አይቻልም፡፡

ከክርስቶስ ደምና ሥጋ ጋር የሚደረግ ኅብረት

‹‹ልባሞች እንደመሆናችሁ እላለሁ፡፡ በምለው ነገር እናንተ ፍረዱ፡፡ የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቆርሰው እንጀራ(ዳቦ) ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን?›› (1ቆሮ.10፡15-16)፡፡

የእግዚአብሔር ቃል በመጀመሪያ መንፈሳዊ እውቀታችንን ይመዝናል፡፡ አዲስ ሕይወትንና እንደዚሁም ቅዱሱን ቅባት (1ዮሐ.2፡20) ወደ እውነት ሁሉ ከሚመራን ከመንፈስ ቅዱስ ተቀብተናል(ዮሐ.16፡13፣ 1ቆሮ2፡9-15) ክርስቲያን የሚያደርገውን ነገር እያወቀ ማድረግ እንዳለበት የእግዚአብሔር ቃል ያሳያል፡፡ ለክርስቲያን ያልተረዳውን ነገር ማድረግ ወይም በስሜት ተገፋፍቶ በቃሉ ሳያመዛዝን የማያውቀውን እርምጃ መውሰድ ከክርስትና መንፈስ ጋር የሚፃረር አካሄድ ነው፡፡

በጌታ እራት የሚካፈል ሁሉ ዳቦውና ወይኑ መታሰቢያው ከሆኑለት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደም በመንፈስ ተካፋይ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ነገር ግን ይህ ብቻ አይደለም፤ ይህን ሥጋና ደም ከሚካፈሉት ጋርም ኅብረት ያደርጋል፡፡ ስለዚህ ኅብረት ሲባል አንድን ነገር በአንድነት መካፈል ስለሆነ ከሚካፈሉት ነገር ጋር ተያይዞ በሚመጣው መብትና ግዴታም ተካፋይ መሆንን ያመለክታል፡፡

ደሙና ሥጋው ተለያይተዋል፤ ይህም የሞተውን አዳኝ የሚያመለክት ነው፡፡ የጌታ እራት ሲታደል ወይኑ የሚሰጠው ከዳቦው በኋላ ቢሆንም እዚህ ላይ ግን ደሙ ከመጀመሪያ ላይ ተጠቅሶ እናገኘዋለን፤ ይህም የሆነው የኢየሱስ ደም የሁሉም ነገር መሠረት ስለሆነ ነው፡፡

ስለዚህ በዚህ ዓይነት ከሞተው አዳኝ ከኢየሱስ ጋር ተካፋይ የሆኑ ሰዎች ኅብረት ተፈጠረ ማለት ነው፡፡ ከወይኑ የሚጠጡ ከደሙ ጋር ኅብረት አላቸው፡፡ ይህም ታላቅ መብት ነው፡፡ በደሙ ታጥበናል (ራዕ.1፡5)፣ ተቤዥተናል (ኤፌ1፡7)፣ ጸድቀናል (ሮሜ.5፡9)፣ ተቀደስናል (ዕብ.13፡12) ለእግዚአብሔር በዋጋ ተገዝተናል (ራእ.5፡9)፣ ወደ እርሱም ቀርበናል (ኤፌ.2፡13) ደሙ ከኃጢአት ሁሉ ያነፃናል (1ዮሐ1፡7) በደሙ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን እንደንገባ ድፍረት አለን (ዕብ.10፡19)፡፡ እግዚአብሔር ቤተክርስቲያንን በክርስቶስ ደም ዋጃት (ሐዋ.20፡28)፡፡

የክርስቶስ አካል ተብሎ በ1ቆሮ.12፡27 እና ኤፌ.4፡12 የተገለፀው ቤተክርስቲያንን ያመለክታል፡፡ ሮሜ.7፡4 እና ዕብ.10፡10 ከክርስቶስ ጋር ስለመሞታችን ይናገራል፡፡ ይህም መስቀሉ ላይ በሥጋ ያለው ሰው እንደሞተ ያሳያል፡፡ ስለዚህ በክርስቶስ ሞት ከተፈጥሮ ይዘነው የመጣነው ነገር ሁሉ አበቃለት፡፡ በቆላ.1፡21-22 ‹‹እናንተንም ነውርና ነቀፋ የሌላችሁ ቅዱሳን አድርጎ በእርሱ ፊት ያቀርባችሁ ዘንድ በፊት የተለያችሁለትን ክፉ ሥራችሁንም በማድረግ በአሳባችሁ ጠላቶች የነበራችሁትን አሁን በሥጋው ሰውነት በሞቱ በኩል አስታረቃችሁ›› ይላል፡፡

በመሆኑም ይህ ኅብረት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ካስገኘው ክቡር ውጤት የተካፈሉ እንደዚሁም ከእርሱ ጋር የሞቱና አሁን እርስ በርሳቸው እንደ አዳዲስ ሰዎች በአንድነት የተጣመሩበት ኅብረት ነው፡፡ ይህ ኅብረት በምድር ላይ የተቋቋመ ቢሆንም አሮጌው ሰው ወይም የተፈጥሮ እኛነታችን እዚህ ላይ ስፍራ የለውም፡፡

የክርስቶስ አካል - ቤተክርስቲያን

በ1ቆሮ.10፡17 ላይ ‹‹አንድ እንጀራ(ዳቦ) ስለሆነ እኛ ብዙዎች ስንሆን አንድ ሥጋ ነን፤ ሁላችን ያን አንዱን እንጀራ(ዳቦ) እንካፈላለንና›› የሚል እናነባለን፡፡ ይህም ማለት እንጀራው(ዳቦው) አንድ ስለሆነ እኛ ብዙዎች ብንሆንም እንኳን አንድ አካል ነን ማለት ነው፤ ምክንያቱም ከአንዱ እንጀራ እንካፈላለንና፡፡ በዚሁ ምዕራፍ ቀደም ብሎ በቊጥር 16 የሚገኘው ሐሳብ በዚህ በቊጥር 17 ላይ ተገልጾአል፡፡ በወይኑና በዳቦው በኩል በጌታችን በኢየሱስ ደምና ሥጋ የሚካፈሉት ሁሉም አንድ ላይ አንድ ኅብረት ያደርጋሉ፤ ያውም አንድ አካል ይፈጥራሉ፡፡ የዚህ ክፍል ዋናው ይዘት ኅብረት እና ኅብረት ሊኖረው ስለሚገባው ጠባይ ሲሆን ስለ አንድ አካል መሆን ደግሞ የዚሁ መልእክት ምዕራፍ 12 እና የኤፌሶን መልእክት በይበልጥ ይናገራሉ፡፡

በ1ቆሮ.12፡13 ይህ ኅብረት እንዴት እንደተፈጠረ ተነግሯል፤ ለዚህም ኅብረት ቀዳሚ መሠረቱ መስቀል ላይ የተጠናቀቀው የክርስቶስ ሥራ ሲሆን የተከናወነው ግን በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ነው፡፡ ይህ መቼ እንደ ተከናወነ ቅዱሳት መጻሕፍት በግልፅ ይነግሩናል፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ እንደሚያጠምቅ ተናገሮ ነበር፡፡ በሐዋ.ሥራ 1፡5 ላይ ጌታችንም ከጥቂት ቀናት በኋላ ይህንን የመንፈስቅዱስን ጥምቀት እንደሚቀበሉ ለሐዋርያት ተናግሮአቸው ነበር፡፡

የእግዚአብሔር ቃል ቤተክርስቲያንን በተመለከተ በክርስቶስ አካልነቷ በሁለት መንገድ ያስቀምጣታል፡፡ በኤፌ.1፡22 እንደምናየው ቤተክርስቲያን በእግዚአብሔር ምክር ጸንታ ለወደፊቱ በሰማያት እንደምትሆን ይናገራል፡፡ ስለዚህም ቤተክርስቲያን በበዓለ ሃምሳ ወደ አካሉ የተጠመቁትን (የሐዋ.ሥ.2)፣ ከዚያ በኋላ የተጨመሩትንና (የሐዋ.ሥ.2፡47) የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን በክብር እስከምትወሰድበት ጊዜ የሚጨመሩትን አማኞችን ያካተተች ኅብረት ናት፡፡ ቤተክርስቲያን አንድ ቀን በአንድ በተወሰነ ጊዜ በምድር ሳለች ምልኣቷ ይፈፀማል፡፡ በክርስቶስ ሆነው የሞቱትም ተነስተው ይለወጣሉ፡፡ ያች ጊዜ አንድ የተወሰነች ጊዜ ናት፡፡ ይህን በተመለከተ 1ተሰ.4፡15-17 እና 1ቆሮ.15፡51-54 ተመልከት፡፡

በአጠቃላይ የእኛን ኃላፊነት ወይም በዚህ ምድር ላይ ሊኖረን የሚገባንን ጠባይ በተመለከተ የእግዚአብሔር ቃል ቤተክርስቲያን በአንድ በተወሰነ ጊዜ በምድር ላይ የሚኖሩ አማኞች ማኅበር አድርጎ ይወስዳታል፡፡ የሞቱት ማለትም በክርስቶስ ሆነው ያንቀላፉት በምድር ላይ የሉምና ምክር ወይም ተግሣጽ አያስፈልጋቸውም፡፡

1ቆሮ.12፡27 የክርስቶስ አካል የሆነች የእግዚአብሔር ጉባኤ ያላትን ባሕርይ በዚህ መልኩ ያስተምረናል፡፡ በዚህ ስፍራ የቆሮንቶስ ሰዎች ‹‹እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ፤ እያንዳንዳችሁም ብልቶች ናችሁ›› ተብሎ ተነግሯቸዋል፡፡ ሆኖም ይህን ቃል በአግብቡ ካልተረዳነው ምናልባት በአንድ በተወሰነ ቦታ የሚኖሩ አማኞች አንድ ላይ የክርስቶስን አካል ይመሠርታሉ ብለን እንደመድም ይሆናል፡፡ ይህም ደግሞ አማኞች እንደሚኖሩበት ቦታ ብዛት እንዲሁ ብዙ የክርስቶስ አካላት አሉ ወደ ማለት ያደርሰናል፡፡ [ነገር ግን የቆሮንቶስ አማኞች ‹‹እናንተ የክርስቶስ አካል ናችሁ›› ሲላቸው የአንዱ ክርስቶስ አካል ክፍል ሆነው በስፍራቸው አንዱን አካል ስለሚወክሉና ስለሚገልጡ ነው እንጂ ለብቻቸው የክርስቶስ አካል ስለሆኑ አይደለም፡፡] በ1ቆሮ.10፡16-17 ከተጻፈው እንደምንረዳውም በየስፍራው ብዙ የክርስቶስ አካላት አሉ ማለት ልክ ሊሆን እንደማይችል ግልጥ ነው፡፡ በዚሁ መልእክት ምዕራፍ 12 ቁ.28 እና ቀጥለው በሚገኙ ቊጥሮች ላይ የምናገኘው ሐሳብ ደግሞ እግዚአብሔር ለጉባኤው የሰጠውን ልዩ ልዩ ስጦታዎች ያሳየናል፡፡ በዚህ ዝርዝርም ሐዋርያት መጀመሪያ ተጠቅሰዋል፤ ሆኖም በቆሮንቶስ ላይ ሐዋርያት እንዳልነበሩ እናውቃለን፡፡ ስለዚህ በቆሮንቶስ የነበረችው የእግዚአብሔር ጉባኤ ወይም ቤተክርስቲያን እንግዲህ በዚያ ስፍራ አንዷን የክርስቶስን አካል የምትገልጥ ማህበር ነበረች ማለት ነው፡፡ ወይም በሌላ አባባል በቆሮንቶስ ትታይ የነበረችው ጉባኤ የክርስቶስ አካል የሆነችው የአንዲቱ ቤተክርስቲያን ክፍል ብቻ የሆነች ጉባኤ ነበረች፡፡ ይህንን ከተረዳን ደግሞ ወደ 1ቆሮ.10፡16 እንመለስ፡፡

የጌታ እራት የክርስቶስ አካል አንድ ብቻ መሆኑን የሚገልጥ ነው

የአካሉ አንድነት በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት እንጂ የጌታን እራት በመካፈል እንዳልተገኘ አይተናል፡፡ የአካል አንድነት የተገኘው በጌታ እራት ቢሆን ኖሮ ቤተክርስቲያን ተብላ የምትጠራው በማዕድ የተካፈሉት ሰዎች ብቻ ኅብረት ትሆን ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ከእግዚአብሔር ቃል ውጭ ነው፡፡

ጌታችን ዳቦውን ቆርሶ ሲሰጥ ‹‹ይህ ሥጋዬ ነው›› በማለት ሥጋውን የሚወክል የሚታይ ምሳሌን እንደሰጠን ሁሉ በተጨማሪም ዳቦውና ወይኑ እንደዚሁም የእግዚአብሔርን ጉባኤ ማለትም የክርስቶስን አካል ለመግለጥ የሚታዩ ምሳሌዎች ሆነው እንደሚያገለግሉ መጻሕፍት ያሳዩናል፡፡ እያንዳንዱ ከወይኑ የሚጠጣና ከዳቦው የሚበላ አማኝ በመስቀል ላይ የፈሰሰው የክርስቶስ ደምና ተላልፎ የተሰጠው የክርስቶስ ሥጋ ከሚያስገኘው ክቡር በረከት ከሚካፈል ኅብረት ማኅበረተኛ እንደሆነ ይገልጣል፡፡ እርሱም የክርስቶስ አካል አንድ ብልት ነው፡፡ ስለዚህ ቃሉ እዚህ ላይ ከጌታ እራት ጋር በተያያዘ መልኩ ማንነታችንን የሚነግረን ሲሆን በምዕራፍ 11 እና በወንጌሎች ግን ምን እንደምናደርግ ያሳየናል፡፡

ስለዚህ የጌታን እራት በግል ሳይሆን የዚያ የአንዱ አካል ብልቶች ሆነን በጋራ እንወስዳለን፡፡ በተጨማሪም ዳቦውን ስንቆርስ የክርስቶስ አካል ብልቶች ከሆኑት ሁሉ ጋር ያለንን አንድነት እናሳያለን፡፡ እንደዚሁም የክርስቶስ አካል ብልቶች የሆኑ ሁሉ የጌታን እራት መውሰድ እንዳለባቸው ግልጥ ነው፡፡ ነገር ግን ይህን ማድረግ የሚችሉት ሁሉም ሰዎች ሳይሆኑ የክርስቶስ አካል ብልቶች የሆኑቱ ብቻ ናቸው፡፡ የማያምኑ ሰዎች እንዲካፈሉ ቢጋበዙ ወይም የማይገባቸውና የክርስቶስ አካል ብልቶች ስለመሆናቸው እርግጠኛ መሆን ባልተቻለበት ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎች በጌታ እራት ከተካፈሉ ያ እነርሱ የተካፈሉበት እራት የጌታ እራት መሆኑ ቀርቶ በዚያ ያሉና እራቱን ያዘጋጁ ሰዎች እራት ብቻ ሆኖ ይቀራል፡፡ እንደዚሁም ከዚህ እንደሚከለክል እግዚአብሔር ካቆመው በቂ ምክንያት ማለትም የቅድስና ጉድለት፣ የተሳሳተ አካሄድ፣ የተሳሳተ ዶክትሪን ወይም ንጹህ ካልሆነው ጋር በሚደረግ ኅብረት ካልሆነ በቀር በእርግጥ የክርስቶስ አካል እንደሆነ የሚታወቀውንም ሰው ከጌታ እራት እንዳይሳተፍ መከልከልም በተመሳሳይ ሁኔታ ያንን እራት የጌታ እራት እንዳይሆን ያደርገዋል፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት የተለዩትን መመዘኛዎችን ስናቆም የጌታ እራት የጌታ መሆኑ ይቀርና የእኛ እራት ይሆናል፡፡ ለምሳሌ መሠረታዊ ባልሆኑ ጥቃቅን እውነቶች ላይ መስማማትን መመዘኛ ስናደርግ የምናዘጋጀው እራት ቅዱሳት መጻሕፍት ለጌታ እራት የሚሰጡትን ጠባይ እንዲያጣ እናደርጋለን፡፡

ይሁን እንጂ ቅዱሳት መጻሕፍት ከላይ እንዳየነው የጌታን እራት ጠባይ በትክክል ያስቀምጡልናል፡፡ እርሱም ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስና የእርሱ ከሆኑቱ ከወገኖቹ ሁሉ ጋር ያለንን ኅብረት የምናሳይበት ማዕድ ነው፡፡ በዚህ እራት የሚሳተፉት ሁሉ ከክርስቶስ ጋር የሞቱ ናቸው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል በዮሐ3፡6 መንፈስ ብሎ የሚጠራውን አዲስን ሕይወት የተቀበሉና መንፈስ ቅዱስ ያደረባቸው ናቸው፡፡ ‹‹ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ ሁሉም አዲስ ሆኖአል (2ቆሮ.5፡17)፡፡

ስለዚህ የጌታ እራት በአሮጌው ፍጥረት ሥርዓት አይካሄድም ማለት ነው፡፡ ይህም እራት ሞቶ የተነሳውና ከዚያም እግዚአብሔር ‹‹ጌታና ክርስቶስ›› ያደረገው (የሐ.ሥ.2፡36)፣ የጌታ የኢየሱስ እራት ነው፡፡ ሞትን ድል ነስቶ የተነሳው ጌታችን የእርሱ የሆኑትን እንግዶቹን ጠርቶ በእራቱ እንዲካፈሉ ይጋብዛል፡፡ የማዕዱ ባለቤትና ጠሪውም እርሱ ነው፡፡ አንዳች ሊናገር የሚገባውም እርሱ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ለእርሱ ይህ ስፍራ ሳይሰጠው ሰዎች ሁሉንም ነገር በራሳቸው ሐሳብ አርቅቀው ያዘጋጁት እራት የጌታ እራት ሊሆን ይችላልን?

በጌታ እራት የሚካፈሉ

በጌታ እራት መካፈል የሚችሉት እውነተኛ አማኞች ብቻ መሆናቸውን አይተናል፡፡ በ1ቆሮቶስ ምዕ.5 እና በ2ኛ ዮሐንስ እንደሚታየው አንዳንድ እውነተኛ አማኞች እንደሆኑ የሚታወቁ አማኞች እንኳ ከማኅበሩ መካከል እንዲወጡ ማድረግ እነደሚገባ ተጽፎአል፡፡

በያዝነው ምዕራፍ ማለትም በ1ቆሮንቶስ ምዕራፍ 10 ከቁ.18-22 ባለው ግን አንድ ሰው በግሉ ርኩሰት ባያደርግም ርኩስ ከሆነው ጋር የሚያደርገው ኅብረት ከጌታ እራት ለመካፈል ፍጹም እንቅፋት እንደሆነ መንፈስ ቅዱስ ትኩረት ሰጥቶበት ያስተምረናል፡፡

በቆሮንቶስ የነበሩ አንዳንድ ወንድሞች ‹‹ጣኦታት የእንጨትና የድንጋይ ቁርጥራጭ ከመሆን በላይ ምንም አይደሉም፤ ምክንያቱም ያለው አንድ አምላክ ብቻ ነውና፤ ስለዚህ እኛ እግዚአብሔርን እያመንን ለጣኦት የታረደውን ብንበላ ወይም በቤተ ጣኦት ውስጥ ብንበላ ያን ያህል ችግር አያመጣም›› ብለው እንደሚያስቡ አስቀድመን ተመልክተናል፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል እንደዚህ ዓይነቱ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ስሕተት መሆኑን አበክሮ ያሳየናል፡፡ አማኞች እነርሱን ከሌላው ሰው በሚለያቸው ከጌታ ደምና ሥጋ ጋር ኅብረት ካለው ማዕድ ይሳተፋሉ፡፡ ከዚህ እየተካፈሉ ግን ይህንን ከሚቃረን ነገር ጋር ኅብረት ማድረግ አይቻልም፡፡ ይህም ማለት ከክርስቶስ ጉባኤ ውጭ ባለው አምልኮ እየተካፈለ ከክርስቶስ ሥጋና ደም ጋር ኅብረት ሊያደርግ ለማንም አይቻለውም፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ይህንኑ ጉዳይ የእስራኤላውያንና የአረማውያንን መሥዋዕት በምሳሌነት በመጠቀም ያብራራልናል፡፡ ማንኛውም እስራኤላዊ ከእርሱ እንዲበላለት የተፈቀደለት መሥዋዕት በዘሌዋውያን ምዕራፍ 3 እና 7 የተጠቀሰው የምስጋና መሥዋዕት ብቻ ነው፡፡ በዚህ በቆሮንቶስ መልዕክት የተነገረለትም መሥዋዕት ይህ ነው፡፡

ይህም መሥዋዕት ለጌታ እራት ዓይነተኛ ምሳሌው ሲሆን ከእርሱ ጋር የተያያዘው አምልኮም በእግዚአብሔር ጉባኤ በክርስቶስ ቤተክርስቲያን ለሚደረገው አምልኮ ዓይነተኛ ምሳሌ ነው፡፡

የምስጋና መሥዋዕት ሰው በፈቃዱ የሚያመጣው መሥዋዕት ነው፡፡ እንዲያመጣ የሚገደድ ማንም አልነበረም፡፡ እስራኤላዊው በልቡ ለእግዚአብሔር ምስጋናና ውዳሴ ካለውና ለእግዚአብሔር መባ ለማቅረብ ከወደደ መባው በእግዚአብሔር ፊት እንዲሠምርለት ምን ማምጣት እንዳለበት የሚያስረዳው አምላካዊ መመሪያ ቀርቦለታል (ዘሌ.7፡12) በተጨማሪም ወዴት ማምጣት እንዳለበትም በአጽንኦት ተገልጦለታል፡፡ የሚያመጣውም እግዚአብሔር በሚኖርበትና ሕዝቡ ከእርሱ ጋር በሚገናኝበት በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ከመሠዊያው ዘንድ ነው፡፡ አገልግሎቱ ከመሠዊያው እንደማይለይ እናያለን፡፡ ደሙም የሚረጨው በመሠዊያው ላይና በዙሪያው ነው (ዘሌ.3፡2)፡፡ አቅራቢው ፍርምባውን በያህዌህ ፊት ለመወዝወዝ ቁርባን ካመጣው በኋላ ስቡንና ኩላሊቶቹን በመሠዊያው ላይ ይሠዋል፤ ይህንንም እግዚአብሔር መብሌ ነው ብሎታል (ዘሌ.7፡29-31፤ 3፡3-5፣11፣16)፡፡ አገልግሎቱን የሚያከናውነው ካህን የመሥዋዕቱን ቀኝ ወርች ይወስዳል፡፡ አሮንና ልጆቹ ፍርምባውን ሲወስዱ መሥዋዕቱን ያመጣው ሰው ደግሞ የቀረውን ሥጋ ከሕዝቡ ንጹህ ከሆኑት ሁሉ ጋር አብሮ ይበላል፡፡

በሌዋ.7፡19-21 ንጹህ ስላልሆኑ ነገሮች የተሰጠ ትእዛዝ እናነባለን፡፡ ርኩስ ነገርን የነካ ሥጋ መቃጠል ይኖርበታል፡፡ መባችንን በምናመጣበት ቦታ ላይ ያመጣነውንና በራሱ ንጹህ የሆነውን መባ እንዳይበላ የሚያደርግ ንፁሕ ያልሆነ ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ እንደዚሁ በግሉ ንጽህና ለሌለው ሰው ከመሥዋዕቱ መብላትን ፈፅሞ የተከለከለ ነው፡፡ ሰው በራሱ በግሉ ንጹህ ቢሆንም አውቆም ሆነ ሳያውቅ የሌላውን ርኩሰት ቢነካ በተመሳሳይ መልኩ ከመሥዋዕቱ እንዲበላ አይፈቀድለትም፡፡ ዘኁልቁ ምዕራፍ 19ን እና ዘሌዋውያን 5ና17ን ይመልከቱ፡፡ በራሱ ለረከሰም ሆነ ከሌላው ርኩሰት ለተባበረ ለሁለቱም ፍርዱ አንድ ነው፤ ‹‹ያች ነፍስ ከሕዝቡ ተለይታ ትጥፋ›› የሚል ነው፡፡ ክፉውን ለራስ እስካላደረጉት ድረስ የስህተት ትምህርት ካላቸው ወይም ርኩሰትን ከሚያደርጉት ጋር መተባበር በራሱ ስህተት አይደለም በሚለው የሰው ሐሳብ ላይ ምንኛ የከፋ የእግዚአብሔር ፍርድ አለ!

ከመሠዊያው ጋር በተያያዘ መልኩ ሌላ ተጨማሪ ነገር በዘሌ.7፡15-18 እናነባለን፡፡ ለእግዚአብሔር በሚቀርበው የምስጋና/የደህንነት መሥዋዕት ሥጋው /መሥዋዕቱ/ በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር በቀረበበት በዚያው ዕለት መበላት አለበት፡፡ ከመሠዊያው ጋር የተያያዘው አገልግሎት ሊካሄድ የሚችለው መባው የመባነት ጠባዩን ሳይቀይር ሲቀር ብቻ ነው፡፡ የፈቃድና የስለት መሥዋዕቶች ግን በነጋታውም ሊበሉ ይችላል፤ ምክንያቱም እዚህ ላይ ከበድ ያለ የልብ መሰጠት ስላለ ከመሠዊያው ጋር የተያያዘው ስሜት ከፊተኛው ይልቅ ስለሚዘገይ ነው፡፡ በዘሌ.7 መሠረት ለምስጋና የሚቀርበውን የደኅንነት መሥዋዕት በመጀመሪያ ወደ መገናኛው ድንኳን ሳያመጡ፣ ደሙና ስቡም በመሠዊያው ላይ ሳይቀርብ በሌላ ስፍራ ሊከናወን አይችልም፡፡ ይህንንም ሥርዓት የጣሰ ከሕዝቡ ይለያል፡፡

ይህንኑ በአዲስ ኪዳን ቀለል ባለ ቋንቋ እናገኘዋለን፡፡ በማቴ.23፡19 ጌታችን መባው በመሠዊያው እንደሚቀደስ አመልክቷል፡፡ ስለዚህ መሠዊያው ከመባው ይበልጣል፡፡ መባውም ከመሠዊያው ጋር በመያያዙ የመሠዊያውን የተቀደሰ ባሕርይ ይይዛል፡፡

የጌታችን ገበታ

የምስጋና መሥዋዕት ይቀርብበት የነበረው መሠዊያ የእግዚአብሔር ገበታ ተብሎ ይጠራ እንደነበር በሚልክያስ 1፡7 እና እንደዚሁም በሕዝ.41፡22 እናነባለን፡፡ ከሁለቱም ጥቅሶች መሠዊያና ገበታ አንድ መሆናቸውን እንረዳለን፡፡ መሠዊያ የሚለው ቃል በላዩ ላይ ከሚቀርበው መሥዋዕት ጋር የተያያዘ ሲሆን ገበታ ደግሞ ከመብሉና ከእርሱም ጋር የተያያዘውን ኅብረት የሚገልጽ ቃል ነው፡፡ የምስጋና መሥዋዕት እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር በማዕድ ኅብረትን የሚያደርግበት መብል ነው፡፡ እግዚአብሔር ድርሻውን ይወስዳል፡፡ ሁል ጊዜ የካህናት ቤተሰብ ምሳሌ የሆኑት አሮንና የአሮን ቤት ድርሻቸውን ይወሰዳሉ፡፡ ከሕዝቡም ንጹህ የሆነው ሁሉ እያንዳንዱ የራሱን ድርሻ ይወስዳል፡፡

በአዲስ ኪዳንም የምናገኘው ይህንኑ ነው፡፡ በዕብ.13፡10 እንደምናነበው ‹‹መሠዊያ አለን ከእርሱም ሊበሉ ድንኳኒቱን የሚያገለግሉ መብት የላቸውም›› የሚል እናገኛለን፡፡ እነዚህም ‹‹መብት የላቸውም›› የተባሉት የአይሁድን ድንኳን የሚያገለግሉ ናቸው፤ ምክንያቱም መሠዊያው የክርስቲያኖች መሠዊያ ነውና፡፡ በ1ቆሮ.10፡18-21 ባለው ንባብም መሠዊያ የሚለው ቃል ማዕድ (ገበታ) ለሚለው ቃል በተለዋጭነት አገልግሏል፡፡

መንፈስ ቅዱስ ራሱ ለብሉይ ኪዳን የምስጋና መሥዋዕት መሠዊያ የሰጠውን ስያሜ ከጌታ እራትና አብሮት ላለው ኅብረት ሲያውለው እናያለን፡፡ የጌታ ገበታ እና የጌታ እራት የሚሉ እነዚህ ገላጭ ሐረጎች የሚያመለክቱን ነገር አለ፡፡ ይኸውም ገበታው፣ እራቱና ተጋባዦቹ የእርሱ መሆናቸውንና ጋባዡም እርሱ ራሱ መሆኑን ያሳየናል፡፡ በእርግጥ እዚህ ላይ የምናነሳው ገበታ ወይኑና ዳቦው የሚቀመጡበት የእንጨት ጠረጴዛ አይደለም፡፡ ነገር ግን ይህ ገበታ የሞተውና ዳግመኛም የተነሳው ጌታ የእርሱ ከሆኑትና ከእርሱ ጋር ከሞቱት ጋር አብሮ በማዕድ የሚቀመጥበት መንፈሳዊ ገበታ ነው፡፡ ይህ መንፈሳዊ ገበታ ጌታ የራሱ የሆኑትን ከእርሱ ጋር እንዲሆኑ የሚጋብዝበት መንፈሳዊ ቤት ማለት ነው፡፡ በዚህ ቦታ የጌታ እራት አለ፡፡

በጌታችን ገበታ(ማዕድ) ሥልጣን ያለው አንድ ብቻ ነው፡፡ በዚህ የሚካፋሉት እነማን ሊሆኑ እንደሚገባቸው የሚወስነውም እርሱ ብቻ ነው፡፡ አገልግሎት እንዴት መካሄድ እንዳለበት ማዘዝ የሚችለውም ባለ ሥልጣን ጌታ ብቻ ነው፡፡ በማን ሊገለገል እንደሚፈልግም የሚወስነው እርሱ ራሱ ነው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ በኩል ሁሉንም የሚካሄደውን ነገር የሚመራ እርሱ ነው፡፡ ጌታ ሊገለገልበት ካልፈለገ በዚያ ማንም አንዳች ሊናገር አይችልም፡፡

የጌታ እራት መለየትን የሚፈልግ መሆኑን መንፈስ ቅዱስ ትኩረት ሰጥቶበት እዚህ ላይ ይናገረናል፡፡ ሰው ከጌታ ማዕድና ከአጋንንት ማዕድ ሊሳተፍ አይችልም፡፡ ፍቅር ቀናተኛ ነው፡፡ ጌታ የራሱ የሆኑትን ከመውደዱ የተነሳ ስለእነርሱ ያውም በመስቀል ላይ የሞትን ፍርድ ተቀበለ፡፡ አሁንም በዚሁ ፍቅር ሊማልድላቸው በሰማይ ዘወትር ሕያው ሆኖ ይኖራል (ዕብ.7፡25) ከፍቅሩ የተነሳም የእርሱን እራት የሚበሉበትንና ከእርሱ ጋር የሚሆኑበትን ገበታ አዘጋጀላቸው፡፡ ስለዚህም ለፍቅሩና ከእርሱ ጋር ላለው ኅብረት ቸልተኛ ከሆነ ሰው ጋር ተቻችሎ መሄድ አይችልም፡፡ የራሱ የሆኑትን ከሰይጣን ኃይል እና ከዓለም አድኖአቸዋል፡፡ በሥጋ የሆነው ሰው ቅዱስና ጻድቅ አምላክ ፍርድ ሥር ውሎ በደሉ ፍጻሜ ያገኝ ዘንድ እርሱ ስለእነርሱ ኃጢአት ሆነ፡፡ ይህን ሁሉ ያደረገላቸው ወገኖቹ ከዓለምና ከሰይጣን ጋር እንደ ፍጥረታዊው ሰው አካሄድ ሲተባበሩ እንዴት ዝም ማለት ይችላል? በተለይም ደግሞ ይህ ሁሉ ድንቅ ፍቅሩ፣ በራሱ መሥዋዕትነት በመስቀል ላይ የዋለው ውለታውና ይህ ሁሉ በወይኑ መቀዳትና ዳቦው መቆረስ ይታሰብ ዘንድ ‹‹ይህ ስለ እናንተ የሚሰጠው ሥጋዬ ነው እንካችሁ ይህ ስለእናንተ የሚፈሰው ደሜ ነው ለመታሰቢያዬ አድርጉት›› በሚለው መመሪያው መሠረት መታሰቢያው በሚካሄድበት በዚህ ስፍራ ላይ ከክፉ ጋር ኅብረት ያለው ሰው እንዴት ሊቀመጥ ይችላል?

በእውነት የሚወዱትም በዚህ ስፍራ ለጌታ ሊሰጠው ለሚገባ ክብር ግዴለሾች ሊሆኑ ይገባልን? በጸሎት ጌታ ሆይ ምን አድርግ ዘንድ ትወዳለህ? ወደ የትኛውስ ቦታ እንደሄድ ትፈልጋለህ? እራትህንስ የምበላበት ገበታህ የት ነው? ብለው ሳይጠይቁ አንዳች ማድረግ አይሆንላቸውም፡፡

ከእኔ ጋር ያልሆነ ይቃወመኛል (ማቴ.12፡30) እንደተባለው አማኝ ነኝ እያለ በገበታው መሆን እንደሚገባው ሆኖ ባይቀርብ ከናቁት ጋር ይቆጠራል፡፡ ‹‹ወይስ ጌታን እናስቀናውን? እኛስ ከእርሱ ይልቅ እንበረታለንን?›› (1ቆሮ.10፡22) ሁላችንም የዚህ ገበታ ተካፋዮች ነን ወይ?

በጌታ ፍቅር
የእናንተው ወንድም

ምዕራፍ 17 አምልኮ

ውድ ወገኖቼ

ባለፉት ደብዳቤዎቼ የጌታን እራት በተመለከተ ተነጋግረናል፤ አሁን ደግሞ ስለ አምልኮ ልጽፍላችሁ እወዳለሁ፡፡ አምልኮ ከጌታ እራት ጋር የተያያዘ ነገር ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደምናየው የጌታ እራት ወደ አምልኮ ይመራል እንጂ በራሱ አምልኮ አይደለም፡፡

አምልኮ ምንድን ነው? እርሱነቱና ለሚያመልኩት እርሱ ያደረገላቸውን መሠረት በማድረግ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ክብር ነው፡፡ በዕብራይስጥ ቋንቋ ብዙውን ጊዜ ለአምልኮ የሚያገለግለው ቃል ‹ስግደት› የሚለው ቃል ነው፤ ለምሳሌ በዘፍ.18፡2 እግዚአብሔር ለአብርሃም ሲገለጥለት አብርሃም እንደሰገደ የተጻፈውም በዚሁ ሐሳብ ነው፡፡ አዲስ ኪዳን መጀመሪያ በተጻፈበት በግሪክ ቋንቋም ብዙ ጊዜ ተደጋግሞ የምናገኘው የግሪክ ቃል ፕሮስኩንዮ (proskuneo) የሚለው ቃል ሲሆን ይኸውም ለእግዚአብሔርም ሆነ ለሰው ክብር ማሳየትን ያመለክታል፡፡

ማስተዋል ለተሰጠው ማንኛውም ፍጡር እግዚአብሔርን ማምለክ እንደሚገባው ግልጥ ነው፡፡ መላእክት ያመልኩታል (ነህ.9፡6)፡፡ ቅዱሳኑም ያመልኩታል፡፡ በዘላለም ወንጌልም ሰዎች እግዚአብሔርን እንዲፈሩና እንዲያከብሩ እንደተጠሩ ተናግሮአል (ራእ.14፡6-7) በመጨረሻም በምድር ያለው ሁሉም ፍጥረት እግዚአብሔርን ያመልካል (ሶፎ.2፡11፣ ዘካ.14፡16፣ መዝ.86፡9)

መላእክት እግዚአብሔርንና ማንነቱን በማወቅ በእውነት ያመልኩታል፤ ዳግመኛ ያልተወለዱ ሰዎችም ወደፊት የቁጣውን ኃይል የሚቀምሱ በመሆናቸው ምክንያት ወይም በሚመጣው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ግዛት ሥር ያለውን ሕይወትን ለመኖር በመፈለጋቸው ምክንያት ያመልኩታል፡፡ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ከዚህ ከፍርሃት ከመነጨ የውጭ አምልኮ የሚበልጥን አምልኮ ከሰው ይጠብቃል፡፡ ይኸውም ሰው ለእግዚአብሔር ካለው የፍቅር ስሜት የመነጨ ክብርን ለእግዚአብሔር ሊሰጥ ይገባል፡፡ በቃሉም አማካይነት ስለዚህ አምልኮ ጠባይና ኃይል እንደዚሁም አምልኮው ስለሚካሄድበት እውነተኛ ስፍራ እግዚአብሔር ነግሮናል፡፡ ለምሳሌ በዮሐ.4 ስናነብ ጌታችን ስለዚህ በግልፅ የተናገረውን እናገኛለን፡፡

እውነተኛው የአምልኮ ስፍራ

ሳምራዊቷ ሴትም ጌታ ሆይ አንተ ነቢይ እንደ ሆንህ አያለሁ፡፡ አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰገዱ እናንተም ሰው ሊሰግድበት የሚገባው ስፍራ በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ አለችው (ዮሐ.4፡19-20) እናንተ ትላላችሁ አለች እንጂ እግዚአብሔር ስለጉዳዩ እንዲህ ይላል የሚል የተናገረችው አንድም ቃል የለም፡፡ በዘመናችን ያሉ ሰዎች እንደሚያደርጉት የሰዎችን ሐሳብ ፈለገች፡፡ የእግዚአብሔርን ሐሳብ ሳይሆን የሰውን አመለካከት ብቻ ጠብቀው የሚመሩ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ምናልባትም አንዱ ስፍራ ከሌላው ይሻላል ብሎ እግዚአብሔር ያሳወቀው ፍቃዱ ይኖር ይሆን ወይ ብላ ለመጠየቅ የሚያስችላት ሐሳብም ሊመጣላት አልቻለም፡፡ ያህዌህ ኢየሩሳሌምን እንደመረጠ በግልጥ አልተናገረምን? ዳዊት በኦርና አውድማ መሥዋዕትን ለእግዚአብሔር አቅርቦ እግዚአብሔር መሥዋዕቱን በተቀበለለት ጊዜ ዳዊት የስፍራውን ትክክለኛነት ተረድቶ ነበር (1ዜና.21፡28) ሰሎሞንም ቤተመቅደሱን ማሠራት ሲጀምር እግዚአብሔር የመረጠው ስፍራ የት እንደሆነ ተረድቶ ነበር (2ዜና3፡1) መቅደሱን ሠርቶ በጨረሰ ጊዜም ትክክል እንደሠራ እግዚአብሔር ሲያረጋግጥለትም ስሙን ለዘላለም በዚያ ያኖር ዘንድ ያን ቤት እንደቀደሰውና እንደመረጠው ነግሮታል (2ዜና.7፡16)፡፡

ይህን የመሰለ ግልፅ ማስረጃ በቅዱሳት መጻሕፍት ተጽፎ ቢገኝም ሴትዮዋ ሰምታው የምታውቅም አትመስልም፡፡ ነገር ግን ስሕተቱ የማነው? ምናልባት የተወለደችበት ሁኔታ ይህንን እንድታውቅ የማያስችል ቤተሰባዊ ተጽዕኖ የነበረበት ስለሆነ ይሆናል፡፡ ይህ ግን በቂ ምክንያት አይደለም፤ ከያዕቆብ አምላክ ጋር ኅብረት አለኝ እስካለች ድረስ እርሱ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን ሐሳብ ማወቅ ወይም መጠየቅ ይገባታል፡፡

አባቶች እንዲህ አሉ እንዲህ አደረጉ የሚለውን እንደ ማስረጃ ለመጥቀስ ችላለች፡፡ ለብዙ ምዕተ ዓመታት ገሪዛን ተራራ ላይ ያለው መቅደስ ለሰማሪያ ሰዎች የአምልኮ ማዕከል ነበር፤ ነገር ግን ይህ ደግሞ ይህ ቤተመቅደስ እውነተኛ የአምልኮ ስፍራ ለመሆኑ በቂ ማስረጃ አይደለም፡፡ አባቶች የምትላቸውን ወገኖቿን ተከትላ በእነርሱ እግር እንደእነርሱ የምታመልክ ልትሆን ትችላለች፡፡ ነገር ግን ሕዝቡ ወደ እርሱ እንዲቀርብና አምልኮን እንዲያመጡለት እግዚአብሔር የመረጠው ስፍራ ይህ ነውን የሚለው ጥያቄ መልስ ይፈልጋል፡፡ በመሆኑም ስለዚህ እግዚአብሔር እንደዚህ ይላል የሚለው አንዱ የእግዚአብሔር ቃል አንድ ጊዜ ሲጠቀስላት ሁሉም ምክንያቶቿ፣ የመከራከሪያ ሃሳቦቿና ስሜቶቿ ሊፈራርሱ በቅተዋል፡፡

ስለ ኢየሩሳሌም በእግዚአብሔር የተነገረውን ሰምታ አታውቅም ይሆናል ብለን ብናስብ እንኳ ባለማወቅዋ ወደ ገሪዛን ተራራ የምታመጣው አምልኮዋ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷልን? የእነርሱ አምልኮ እውነተኛ አምልኮ እንደሆነ በልባቸው በቅንነት አምነው በገሪዛን አምልኮ ይፈጽሙ የነበሩ በርካታ የሰማርያ ሰዎች እንደነበሩ አያጠራጥርም፡፡ ታዲያ እግዚአብሔር አምልኮታቸውን ይቀበለው ነበርን? የሰው ሕሊና በግልጥ ከተቀመጠው ከእግዚአብሔር ቃል በላይ ይሆናል ወይ? በፍጹም ሊሆን አይችልም፡፡

ከዚህም በመነሳት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን›› (ዮሐ.4፡22) በማለት የሰማርያ ሰዎችን ሐሳብ ውድቅ አድርጎታል፡፡
በዚህ ጌታና ሴትዮዋ ባደረጉት ውይይት ውስጥ ሦስት ሊስተዋሉ የሚገባቸው ነገሮች የሚከተሉት ናቸው፤

  1. እግዚአብሔር በቃሉ ግልፅ ያደረገልንን ነገር ሰው በራሱ ሐሳብ ባዘጋጀው ነገር መተካት ወይም ከሰው ሐሳብ ጋር ማደባለቅ በጣም አደገኛና ርኩስ ተግባር መሆኑን፣
  2. አባቶቻችን እንዳደረጉት እያደረግን እግዚአብሔርን ማምለክ በትክክለኛ መንገድ ለማምለካችን ፍጹም ዋስትና አለመሆንኑንና፣
  3. አንድን ነገር በመልካም ሕሊና ብናደርገውም ከቃሉ ውጭ እስከሆንን ድረስ እግዚአብሔር ይቀበለዋል ማለት አለመሆንኑን ነው፡፡

አንዳች ነገርን አስመልክቶ ጥያቄ ቢነሳም የሚፀናው እግዚአብሔር የሰጠው መልስ ብቻ ነው፡፡ ሐሳባቸውን ከእግዚአብሔር ሐሳብ ጋር ማጣጣም የእግዚአብሔር ሰዎች ግዴታቸው ነው፡፡ ‹‹ማናቸውም ሰው ኃጢአት ቢሠራ እግዚአብሔር፡- አትሥሩ ካላቸው ትዕዛዛት አንዲቱን ቢተላለፍ ባያውቅም ያ ሰው በደለኛ ነው ኃጢአትንም ይሸከማል፡፡›› (ዘሌ.5፡17)፡፡

ጌታችን ከላይ ካየነው በተጨማሪ ስለ ኢየሩሳሌም የተናገረው ነገር አልነበረም፡፡ በግልፅ አነጋገር እውነት ምን እንደሆነ ከነገራት በኋላ ሌላ አዲስ የሆነን ነገር ነገራት፡፡

በሕግ ሥር በእግዚአብሔር ውሳኔ መሠረት ኢየሩሳሌም የአምልኮ ስፍራ ናት፡፡ አሁን ግን የእግዚአብሔር ልጅ ማለትም በሥጋ የተገለጠ አምላክ (1ጢሞ.3፡16) ወደ ምድር መጥቷል፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ በሥጋ ተገልጦ አባቱን ተረከው (ዮሐ.1፡18) ‹‹ከወልድም በቀር ወልድም ሊገልጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን የሚያውቅ የለም፡፡›› (ማቴ.11፡27) ታዲያ ይህ ሁሉ በሰው አምልኮት ላይ አንዳች ተፅዕኖ ሊኖረው አይችልምን? አምልኮስ እግዚአብሔርን በማወቅ የሚደረግ አይደለምን?

የክርስትና ፍሬ ሐሳብ

በዮሐ.4፡10 ጌታ የክርስትናን ዘመን የአምልኮ ሁኔታ አስመልክቶ በአጭሩ ገልጾታል፡፡ አሁን ጊዜው የቤተክርስቲያን ዘመን ነው፡፡ ለሴቲቱም ‹‹የእግዚአብሔርን ስጦታና ውሃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑንስ ብታውቂ አንቺ ትለምኝው ነበርሸ የሕይወትም ውሃ ይሰጥሽ ነበር አላት (ዮሐ.4፡10)፡፡

‹‹የእግዚአብሔር ስጦታ›› የሚለው ሐረግ የእግዚአብሔርን ማንነት ገልጦ ያሳየናል፡፡ በሕግ እግዚአብሔር እንደ ሰጪ ሆኖ አልተገለጠም፤ እርሱ የሚጠይቅ ሆኖ ይታይ ነበር፤ ሰዎች እንዲያገለግሉት ጠይቆ ነበር፡፡ በረከቱንም የሚሰጠው ለትዕዛዛቱ በሚኖር መታዘዝ ላይ ብቻ ተመሥሮቶ ነበር፡፡ እርሱም በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ይኖር ነበር (ዘዳ.4፡11፣5፡22-23፣ መዝ.18፡11-12) ይህም ማለት መኖሪያውን ከዚያ አደረገ ማለት ሳይሆን ራሱን አይገልጥም ነበር ማለት ነው፡፡ ሕጉ ምንም ቅንጣት ስሕተት የለውም፤ ቅዱስ፣ ጻድቅ በጎም ነበረ፡፡ ሰው ግን ኃጢአተኛ ነው፡፡ ሕግ እንዲፈጸም ጫና በተደረገ ቊጥር የሰው ኃጢአትም ግልፅ እየሆነ ሄደ፡፡ አንዳንድ ሊቃውንት ነን የሚሉት ሕግ የእግዚአብሔር ነፀብራቅ ነው ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ይህ እውነት ቢሆን የሰው ዘር ጠፍቶ ይቀር ነበር፡፡ አባባላቸው ግን ልክ አይደለም፡፡ ሕግ ከእግዚአብሔር ቢሆንም በራሱ እግዚአብሔር አይደለም፤ ስጦታውም አይደለም፡፡ ሕግ ኃጢአተኛ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ምን መሆን እንዳለበት የሚያሳይ የሥነ ምግባር መስፈርት ብቻ ነው፡፡

እግዚአብሔር ብርሃን ነው፤ እግዚአብሔር ፍቅርም ነው፡፡ ሰው በከባድ ችግር ውስጥ ባለበት ወቅት ነፃና ፍጹም ስጦታን ሰጠ፡፡ እርሱ በሥጋ የተገለጠ አምላክ ‹‹ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው›› (የሐዋ.ሥ.20፡35) ብሎ ተናገረ፡፡ እግዚአብሔር ስጦታን በመስጠቱ የሚሰጥ ብፁዕ ነው ሲል አንዳች የሚጎድለው ኖሮ ነውን?

በሕግ፣ ሰው ሕጉን ባይጥስ ኖሮ እግዚአብሔር ተቀባይ ይሆን ነበር፡፡ በወንጌል ግን እግዚአብሔር ሁልጊዜ ሳያቋርጥ ሰጪ ሆኖ ይታያል፤ የሚያስደንቀው ደግሞ ሊሰጥ ከሚቻለው ከፍተኛውን ስጦታ ዘላለማዊ ጥፋት ለተገባቸው ሰዎች መስጠቱ ነው፡፡

በዕብራውያን መልዕክት ውስጥ በሕግ ሥር የሚኖረው እስራኤላዊ ያለው ስፍራና እና ክርስቲያን ያለው ስፍራ ተነፃፅሯል፡፡ ለእስራኤላዊው ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የሚወስደው መንገድ ገና አልተገለጠም (ዕብ 9፡8) መባና መሥዋዕትን ቢያቀርብም ኃጢአቶቹን ሊያስወግዱለት አይችሉም (ዕብ.9፡9፣ 10፡4፣11) የኦሪት ሊቀ ካህናት ራሱ በድካም የተሞላ ስለ ነበር ስለ ራሱ መሥዋዕት ማቅረብ ግድ ነበረበት (ዕብ.5፡3)

ክርስቲያኑ ግን ለዘላለም ፍጹም ሆኖአል (ዕብ.10፡14) ንጹሕ ኅሊና አለው(ዕብ.9፡14) ስለዚህ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የመግባት ድፍረት አለው፤ ምክንያቱም መጋረጃው ለሁለት ተቀዶለት ወደ እግዚአብሔር የሚያስገባው በር ተከፍቶለታል፡፡ ለዘላለም ፍጹም የሆነ በእግዚአብሔር ቤት ላይ የተሾመ ታላቅ ሊቀካህናት አለውና (ዕብ.10፡19-22¬፣ 7፡28) እዚህ ላይ እግዚአብሔር ምን ያህል ሰጪ እንደሆነ ልብ እንበል፡፡

ይህ ሁሉ የተገኘውም ወደ ዓለም መጥቶ የእግዚአብሔር ጠላቶች ለሆኑ ኃጢአተኞች ሲል ታላቅ ሥቃይን ለመቀበል ራሱን ዝቅ ባደረገልን በእግዚአብሔር ልጅ ነው፡፡ በዮሐንስ ምዕራፍ 4 የተጠቀሰችውና ውሃ ልትቀዳ የመጣችው ሴት እንደ አንድ ደግ አይሁዳዊ አየችው እንጂ ማንነቱን ለይታ አላወቀችውም፡፡ እርሱ ያህዌህ፣ የሰማይና የምድር ጌታ፣ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ መሆኑ በአእምሮዋም አላለፈም፡፡ ከዚህ ጥቂቱን እንኳ አውቃ ቢሆን ኖሮ የሕይወትን ውሃ በጠየቀችውና እርሱም በሰጣት ነበር፡፡ በዮሐ.7፡39 መሠረት የሕይወት ውሃ በአማኝ ውስጥ ለሚኖረው ለመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ነው፡፡

ስለሆነም የእግዚአብሔር ጸጋ የሁሉም በረከት ምንጭ እንደሆነና፣ ከዚያም ለወልድ ያለውን ክብርና እርሱም ራሱን ዝቅ አድርጎ በምድር ላይ በሰዎች መካከል መገኘቱን እናያለን፡፡

በመጨረሻም ከራሱ ባለጠግነት የተነሳ ወልድ ለተጠሙት ነፍሳት የሕይወት ውሃ ማለትም መንፈስ ቅዱስን እንደሚሰጥ እንመለከታለን፡፡ እነዚህ ለክርስቲያን አምልኮ አስፈላጊ የሆኑ መሠረታዊ ነገሮች ናቸው፡፡

አብ የሚያመልኩትን ይፈልጋል

አብን ማምለክ የሚለው አባባል ሴትዮዋን እንደ አዲስ ነገር ሳያስገርማት አይቀርም፡፡ እስራኤል የእግዚአብሔር የበኩር ልጅ ነበር (ዘጸ.4፡22)፡፡ እነርሱም የአምላካቸው የያህዌህ ልጆች ነበሩ (ዘዳ.14፡1)፡፡ ያህዌህ የእስራኤል አባት ሲሆን ኤፍሬምም ደግሞ የበኩር ልጁ ነበር (ኤር.31፡9) ነገር ግን እግዚአብሔርን አባት ብለው ያመለኩበት ጊዜ የለም፤ ምክንያቱም ‹‹ከወልድ በቀር ወልድም ሊገልጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን የሚያውቅ የለምና›› (ሉቃ.10፡22)፡፡ በክርስትና አምልኮ ወሳኝ ነጥብ እግዚአብሔር ከሚያመልከው ሕዝቡ ጋር ባለው ግንኙነት በአባትነቱ መታወቁ ነው፡፡ ይህም መገለጥ ደግሞ በራሱ የግል ጉዳይ ነው፤ ምክንያቱም ‹‹ወልድ ሊገልጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን የሚያውቅ የለምና፡፡››

በመሆኑም ይህ እውቀት ያለው እርሱ ወልድ የገለጠለት ነው ማለት ነው፡፡ በአብ እቅፍ ያለው አንድ ልጁ አባቱን ተረከልን፤ ሥራውን ከፈጸመ በኋላም የራሱ የሆኑትን ከአብ ጋር እርሱ ወዳለው ኅብረት አመጣቸው፡፡ ይህም ማለት አባቱ የእኛም አባት ወደሚሆንበት መብት አደረሰን፡፡ ‹‹ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ዐርጋለሁ›› (ዮሐ.20፡17) በማለትም ተናገረ፡፡ ይህ ደግሞ የአዲስ አማኝ ድርሻ ነው፡፡ ሐዋርያው ገና አዳዲስ ክርስቲያኖች ለነበሩ እንዲህ ብሎ ጽፎላቸዋል፤ ‹‹ልጆች ሆይ አብን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ›› (1ዮሐ.2፡13)፤ ይህን ጌታ በዮሐ.17 ከተናገረው ጋር ልናነጻጽረው ይገባል፤ ‹‹እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት፡፡›› (ዮሐ.17፡2-3)፡፡

አብ የሚያመልኩትን ይሻል፡፡ ይህ ደግሞ ትልቅ ጸጋ ነው፡፡ በእስራኤል እያንዳንዱ ሰው በዓመት ሦስት ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ማምለክ ይጠበቅበታል (ዘዳ.16፡16) በሺህ ዓመት መንግሥትም እግዚአብሔርን ያመልኩት ዘንድ የምድር ቤተሰቦች በየዓመቱ ወደ ኢየሩሳሌም መሄድ አለባቸው፤ ይህን ያልሠሩ ይቀጣሉ (ዘካ.14፡16-19)፤ አብ ግን በእውነት የሚያመልኩትን ይሻል፡፡ በእውነት የሚያመልኩትም አምልኮአቸው ከአፍአዊ አምልኮ የተላቀቀና ከልብ የሆነ ነው፡፡ እግዚአብሔር በእውነት የሚያመልኩትን ይፈልጋል ስንል ምን ማለታችን ነው?

በእውነትና በመንፈስ ማምለክ

‹‹ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል፡፡ አሁንም ሆኖአል አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል፡፡›› (ዮሐ.4፡23-24)፡፡

እዚህ ላይ የክርስቲያንን አምልኮ ዓይነተኛ ጠባይ እናገኛለን፡፡ በሥርዓት እና በወግ የተተበተበ ምድራዊ አምልኮ አይደለም፡፡ የክርስቲያን አምልኮ ከእግዚአብሔር ማንነት ጋር የሚጣጣም ነው፤ እግዚአብሔርም በትክክል እንደተገለጠ ያሳያል፡፡

የማያምን በዚህ መልኩ ማምለክ አይችልም፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቃል መንፈስ ብሎ የሚጠራውን አዲስ ሕይወት በአዲስ ልደት በኩል ብቻ ነውና፡፡ ‹‹ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፡፡ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው፡፡›› (ዮሐ.3፡6፣ ሮሜ.8፡16) ይህም ከእግዚአብሔር ባሕርይ የተስማማ በአዲስ ሰው የሚከናወን መንፈሳዊ አምልኮ ነው፡፡

መንፈሳዊ ያልሆኑ አማኞችም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች ሲጽፍ የሥጋ እንደሆኑ እንጂ መንፈሳውያን አለመሆናቸውን ይገልጻል (1ቆሮ.3፡1)፡፡ እነዚህም ሰዎች አስቀድመው አምነው ሳይለወጡ ቀርተው በሥጋ ናቸው ማለት ሳይሆን ዳግመኛ የተወለዱና መንፈስ የሆነው አዲስ ሕይወት ያላቸው ነገር ግን በሥጋ እንደ ሆነው እንደ ፍጥረታዊ ሰው የሚያስቡና የሚያደርጉ ነበሩ፡፡

የእስራኤላውያን አምልኮ ምድራዊ ነበር፡፡ በአንድ በተወሰነ ቦታ ግሩም በሆነ ቤተ መቅደስ ውስጥ በማይዛነፍ ሥርዓትና ቁጥጥር ሥር ይካሄድ ነበር፡፡ ሰዎች ውድና ያማሩ አልባሳትን ለብሰው በድንቅ ሙዚቃ ታጅበው ምድር ልትሰጠው ከምትችለው ታላቁንና ምርጡን ያቀርቡ ነበር፡፡ ይህም በመንፈስ የሆነ አንዳችም ነገር የለውም፡፡ ካህኑም ሆነ መዝሙረኛው ወይም ለቤተመቅደስ መባ ይዞ የሚመጣው ሰው ዳግመኛ እንዲወለድ አይገደድም፡፡ ይህም ሥርዓት በእግዚአብሔር የተደነገገና ምድራዊ ሰው ራሱን ላልገለጠና በመጋረጃ ውስጥ ለተሰወረ አምላክ አምልኮ የሚያቀርብበት ሥርዓት ነው፡፡

ፍጥረታዊውን ሰው ግን እግዚአብሔር በመስቀል ላይ አስወግዶታል፡፡ እኛ ዳግመኛ የተወለድንና በኢየሱስ ክርስቶስ ያመንን ሁላችን ከክርስቶስ ጋር ሞተናል (ሮሜ.6፡8)፤ መንፈስ ቅዱስ በእኛ ውስጥ በሠራው አዲስ ሕይወት ልንመላለስ ይገባል፡፡ በእኛ የሚኖረው መንፈስ ቅዱስም በዚህ በአዲስ ሕይወት የምንመላለስበትን ኃይል ይሰጠናል፡፡ በመሆኑም አምልኮአችን መንፈሳዊ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ይህ ወሳኝ የሆነ በምንም ምክንያት የማይታለፍና በሁሉም አማኝ ላይ ተፈፃሚ ሊሆን የተገባው የአምልኮ ሥነ ምግባር ነው፡፡ ጌታችን በዮሐ.4፡14 የተናገረው የእውነተኛ ክርስቲያናዊ አምልኮ ኃይል መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ያሳያል፡፡

ከዚህ ሌላ አንዲት ቅንጣት የአምልኮ ሥርዓት አልተሰጠንም፡፡ እስራኤልን ስንመለከት ከጅማሬ እስከ ፍጻሜ ከትልቅ እስከ ጥቃቅኑ ድረስ አምልኮአቸውን በምድር የሚቆጣጠር ሥርዓት ተሰጥቶአቸው ነበር፡፡ ለእኛ ግን እንደዚህ እንደ እስራኤል ሊደነገግልን ቀርቶ ጌታ የመታሰቢያውን እራት ሲመሠርትልን እንኳ ምን ብሎ እንዳመሰገነ የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ከዚያን በኋላም ከሐዋርያት አንዱ እንኳ እንዴት እንጀራውን(ዳቦውን) እንደቆረሰ የምናውቀው ዝርዝር ነገር የለም፡፡ ዳቦውንና ጽዋውን ከመባረክ በቀር ወደ ፊት የሚነሱ አማኞች ሲባርኩ እንዲህ እያሉ ይቁረሱ ተብሎ የተላለፈልንም ነገር የለም፡፡ በሐዋርያት ዘመን ጉባኤም ይዘመሩ ከነበሩት መዝሙሮች የምናውቀው አንድም መዝሙር የለም፡፡ የክርስቲያን መዝሙር ተብሎ የተጻፈ መጽሐፍም አልተላለፈልንም፡፡ ምክንያቱም በእግዚአብሔር መንፈስ ማምለክ ስላለብን ነው (ፊልጵ.3፡3)፡፡ ወደ ጥንቱ የብሉይ ኪዳን አምልኮ ሥርዓት ተመልሰን የክርስትናን አምልኮ ከዚያ ጋር እንዲስማማ በማድረግ የራሳችንን ቀርፀን ለማምለክ ብንጥር ዋናው የክርስቲያን አምልኮ መለያ ባሕርይ የሆነውን እግዚአብሔርን በመንፈስ ማምለክን እናጣለን፡፡

አምልኮ ግን በመንፈስ ብቻ ሳይሆን በእውነትም ጭምር ሊሆን ይገባል፡፡ ‹‹እውነት ምንድን ነው?›› ብሎ ጲላጦስም ጠይቆ ነበር፡፡ የእሾክ አክሊል ደፍቶ በፊቱ የቆመው እውነት መሆኑን አላወቀም ነበር፡፡ እውነት ማለት እግዚአብሔር ስለ ራሱ የገለጠው ነው፣ ያም እግዚአብሔርን የገለጠ ወልድ ነው፡፡

እስራኤልም በተወሰነ መልኩ እግዚአብሔርን በእውነት ያመልክ ነበር፡፡ ምክንያቱም አምልኮአቸው በጊዜው እግዚአብሔር እንደ ያህዌህነቱ ራሱን ከገለጠበት እውቀት ጋር የሚሄድ ስለነበረ ነው፡፡ አሁን ግን እግዚአብሔር በፍጹም ተገልጧል፤ ምክንያቱም በሥጋ የተገለጠ አምላክ በዚህች ምድር ላይ ስለነበር ወሰን በሌለው ጸጋው እናውቀው ዘንድ እንችላለን፡፡ በምድር ታይቶአል፡፡ ወሰን በሌለው ጸጋውም እንድናውቀው አደረገን፡፡ ‹‹የእግዚአብሔር ልጅ እንደመጣ እውነተኛም የሆነውን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደሰጠን እናውቃለን (1ዮሐ.5፡20)

እውነትን በማወቅ እያደግን መሄዳችን እርግጥ ነው፡፡ የእግዚአብሔር መንፈስ እውነት ወደ ሆነው ሁሉ ሊመራን በውስጣችን ይሠራል (ዮሐ.16፡13) በዚህ ረገድ በአማኞች መካከል ያለው ልዩነት በአንድ ዳግመኛ ባልተወለደና በአንድ አዲስ አማኝ መካከል ካለው የእውቀት ልዩነት ጋር ሲነፃፀር በአማኞች መካከል ያለው ልዩነት ከግምት የሚገባ አይደለም፡፡ ዳግመኛ ያልተወለደ ሰው እግዚአብሔርን ሊያውቅ ይችላል ብሎ መገመት በሬ ሳይንስንና ፍልስፍናን መረዳት ይችላል ብሎ ማሰብ ነው፡፡ በአዲስ ልደት መንፈስ የሆነ ሕይወት በመቀበላችን እግዚአብሔርን ማወቅ እንችላለን፡፡ ይህም ሕይወት የመለኮት ባሕርይ አለው (2ጴጥ.1፡4) በአዲስ ሕይወት በእኛ ውስጥ የሚኖረው መንፈስ ቅዱስ ሥራውን ይሠራል፡፡ ይህ መንፈስ ራሱ በውስጣችን ይህንን ሕይወት እንዲኖር ያደርጋል (ዮሐ.4፡14) ሐዋርያው ዮሐንስ ልጆች እያለ ለሚጠራቸው አዳዲስ አማኞች ‹‹እናንተም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋል ሁሉንም ታውቃላችሁ፡፡ እውነትን የምታውቁ ስለ ሆናችሁ ውሸትም ሁሉ ከእውነት እንዳልሆነ ስለምታውቁ እንጂ እውነትን ስለማታውቁ አልጽፍላችሁም በማለት ጽፎላቸዋል›› (1ዮሐ.2፡20-21)፡፡

ስለዚህም ወደ እግዚአብሔር መቅረብ እንችላለን፡፡ አዲስን ሕይወት በሚሰጠንና ይህችንም ሕይወት ከእግዚአብሔር ጋር በሚያገናኛት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እግዚአብሔርን እናየዋለን፤ ደስም እንሰኝበታለን፡፡ እርሱን አይቶ የማያደንቅ ወይንም አምልኮቱንና ደስታውን በፊቱ የማይገልፅ ማን ነው? የልብን ደስታ በፊቱ ከመግለጥ መታቀብ ይቻላልን? በረከትን በተቀበለበት በዚያ ቆሞ የማይቀርና ዓይኖቹን ከበረከቱ ላይ አንስቶ የበረከቱን ሰጪ ራሱን በላይ መመልከት የሚችል የእግዚአብሔር ልጅ ሁሉ ይህ እንደማይቻል ያውቃል፡፡ ማየት ብንችልም የአብና የወልድ ክብር ታላቅ በመሆኑ የልባችን እጅግ ትንሽ መሆን ለእርሱ ያለንን አድናቆት በሙላት እንዳናቀርብ ሊወስነን ይችላል፡፡ ስለዚህም ይህንን ክብሩን በቃላት ለመግለጥ ምን ያህል የሚያስቸግር ነው? ነገር ግን በመንፈስ ብናመልክ የምናመልክባቸው ቃላት የእኛ አምልኮ ሳይሆኑ ከልባችን ወደ ላይ የሚወጡ መንፈሳዊ ስሜቶች ናቸው፡፡ አሁንም ሌላ ያልተነጋገርንበት ጥያቄ አለ፡፡

የት ማምለክ ይኖርብናል?

ሁሉም አማኝ በግሉ ማምለክ እንዳለበት አጠያያቂ አይደለም፡፡ ከአብ ጸጋና ፍቅር የተነሳ ጌታ ለሠራልን ሁሉ ሳናመሰግንና ሳናወድስ እንዴት ማለፍ እንችላለን? ይህ ደግሞ የግላችን ብቻ ሳይሆን ከሌሎችም የእግዚአብሔር ልጆች ጋር የምንጋራው ጉዳይ ነው፡፡ ታዲያ ይህ በራሱ ወደ ኅብረት አምልኮ አይመራንምን? የክርስቶስን ሞት ለመናገርና የተቆረሰውን ኅብስትና የሚቀዳውን ወይን ከእጁ ለመቀበል ከምንሰበሰብበት ቦታ ይበልጥ ወደ አምልኮ የሚመራን ምን አለ? በዚያም እርሱን ፍጹምነት ባለው ፍቅሩና ሥራው እናየዋለን፡፡ የታረደው በግ እይታ በሰማይ ለእርሱ ዝማሬንና አምልኮን እንደቀሰቀሰ (ራእ.5) በምድርም እንዲሁ ይሆናል፡፡ አዎን ሞቱን ለመናገር አንድ ላይ እንሰበሰባለን፡፡ የጌታን እራት ማክበር ብቻውን በራሱ አምልኮ አይደለም፡፡ የጌታን እራት ለማክበር የሚሰበሰቡት መንፈሳውያን ሰዎች ከሆኑ ምስጋናና አምልኮን ለጌታ ይሰጣሉ፡፡ እንዲህ ካልሆነ የጌታን እራት ማክበር የአምልኮ አገልግሎት ሊሆን አይችልም፡፡ አምልኮና ምስጋና ሲኖረው ግን በእርግጥ ነው፡፡

በ1ቆሮ.14 እንደምናየው አምልኮን ከጉባኤ ጋር በተያያዘ መልኩ እናገኘዋለን፡፡ በዚህም ምዕራፍም አምልኮ በምን መንገድና በማን ወደ እግዚአብሔር እንደሚቀርብ እንማራለን፡፡ ይህም ለእኛ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅ ተጨማሪና ጠቃሚ መረጃ ነው፡፡ ዝማሬ፣ ምስጋናና ውዳሴ ከመጀመሪያው የአምልኮ ክፍሎች መሆናቸውን እንረዳለን፡፡ እነዚህም ከግለሰቦች ጋር ያልተያያዙ ነገር ግን በሥርዓት እንደ እግዚአብሔር አሠራር በጉባኤ የሚከናወኑ ነገሮች መሆናቸውንም እንገነዘባለን፡፡ በዚሁ ምዕራፍ ከ12 እስከ 17 ያሉትን ቊጥሮች ብንመለከት ማስተዋል ያለውን አምልኮ እግዚአብሔር ከሕዝቡ እንደሚፈልግ እንረዳለን፡፡

በመካከላቸው ሥልጣን ያለው ጌታ ብቻ መሆኑን በማወቅ በአንድነት ይቀርባሉ፡፡ በማን ሊጠቀም እንደሚፈልግም ወሳኝ እርሱ ራሱ ነው፡፡ ጌታም በጉባኤ መካከል ባለው መንፈስ ቅዱስ አማካይነት ይህንን ሥልጣን ያፀናል፡፡ ዋናው ነገር በአገልግሎቱ የሚሳተፉት ሰዎች ቊጥር አሥር ወይም ሃያ የመሆን ጥያቄ ሳይሆን መንፈስ ቅዱስ የፈለገውን ሰውና የፈለገውን ያህል ብዛት ያለውን ሰው ሳይከለከል መጠቀም መቻሉ ነው፡፡

ይህንን አምልኮ ከልምዳችን እናውቀዋለንን? እስከ አሁን እንዳየነው ጉዳዩ የአእምሮ ጉዳይ አይደለም፡፡ ጉዳዩ አንድ ልጁን በመስቀል ላይ እንዲሞትላቸው በሰጠ በአባታቸው ፍቅርና ስለ እነርሱ ራሱን አሳልፎ ሊሰጥ በወደደ በመድኃኒታችን በእግዚአብሔር ልጅ ፍቅር የተሞሉ ልቦች ምላሽ ነው፡፡

ከሰላምታ ጋር
የእናንተው ወንድም

ምዕራፍ 18 አገልግሎት

ውድ ወዳጆቼ

የክርስቲያን ሕይወት መስጠትና መቀበል እኩል ሚዛናዊ የሚሆኑበት ሕይወት ነው፡፡ በአንድ በኩል እየተቀበለ በሌላ በኩል እንደሚያፈስ ግድብ ወይም የውሃ ማጠራቀሚያ ነው፡፡ ተቀብሎ የማያስተላልፍ ክርስቲያን ሊጨበጥ ወደማይችል የህልም ዓለም እንደገባ አጉል ፈላስፋ ይሆናል፡፡ በመስጠት ብቻ ራሱን የሚያደክም ለመቀበል ግን ጊዜ የሌለው መንፈሳዊ ኪሳራ ላይ ይወድቃል፡፡

ባለፈው ደብዳቤዬ እንደገለጽኩት እያንዳንዱ የአገልግሎት ዓይነት ከጌታችን ኢየሱስ ሥር በመቀመጥና ከእርሱ ጋር ኅብረት በማድረግ ከተገኘ ልምድ የመነጨ መሆን አለበት፡፡ ይህንንም ከማርያም የአምልኮ ሕይወት መማር እንችላለን፤ ትክክለኛውን ወቅት ጠብቃ የክርስቶስን እግር ውድ የሆነ ሽቶ ቀባች (ዮሐ.12፡3) ለምን ብለን ብንጠይቅ ከእግሩ ሥር በአጠገቡ መቀመጥን ታዘወትር ስለነበረ ነው (ሉቃ.10፡39)፤ በዚህም የእርሱንም ማንነት ሆነ ሐሳቡን በደንብ ለመረዳት ችላ ነበር፡፡ ማርታም ደግሞ ሐሳቡን በደንብ ትረዳ ነበር፡፡ ምክንያቱም በኀዘን ከተቀበለችው በኋላ እንዳገለገለችው እንረዳለንና፡፡

በእነዚህ ሁለት አብነቶች ሁለት ገጽታ ያለውን የክርስቲያኖችን አገልግሎት ማየት እንችላለን፡፡ በማርያም በኩል ወደ ጌታና ወደ እግዚአብሔር የሆነውን አገልግሎትና በማርታ በኩል ደግሞ ወደ ሌሎች ሰዎች ያተኮረውን የአገልግሎት ክፍል እናያለን፡፡ በ1ጴጥ.2፡5 ‹‹በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ›› የሚለንን እናነባለን፡፡ ከዚህ በኋላ ደግሞ በቊጥር 9 ላይ ‹‹ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃን የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትነግሩ የተመረጠ ትውልድ የንጉሥ ካህናት›› በማለት የሚኖረንን አገልግሎት ይገልጻል፡፡ የመጀመሪያው የአገልግሎት ገጽታ ስለ ጌታ እራትና ስለ አምልኮ ስንነጋገር ያየነው ሲሆን ሁለተኛውን ገጽታ ደግሞ ከዚህ ከጴጥሮስ መልእክት እንመለከታለን፡፡

በዚህ አገልግሎት በጌታ መላክና ለተቀበልነውም ኃላፊነት ተጠያቂነታችን ለእርሱ መሆኑን አውቀን ማገልገል የቅዱሳት መጻሕፍት መሠረታዊ መርሆ ነው፡፡ ስለአገልግሎት ለሚያስብ ሁሉ ይህ በጣም ግልጥ ነው፡፡ በቃል የሚያገልግል መልእክትን ከእግዚአብሔር ወደ ሰዎች ያስተላልፋል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ እግዚአብሔር እንደዚህ ዓይነት ሰዎችን ካልጠራና የሚያስፈልጋቸውን ስጦታዎች ካልሰጠ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ኤፌ.4፡7-12 እና መዝ.68፡18ን አንድ ላይ አጣምረን ስንመለከት ከሙታን የተነሣው ጌታ እነዚህን ስጦታዎች የተቀበለና የራሱ ለሆኑት የሚያከፋፍል እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ከዚህ ጋር የሚዛመዱ ሌሎች የቅዱሳት መጻሕፍት ምንባቦችም ይህንኑ ያረጋግጣሉ፡፡

የወደዳቸውን ጠራቸው

‹‹ወደ ተራራም ወጣ ራሱም የወደዳቸውን ወደ እርሱ ጠራ፤ ወደ እርሱም ሄዱ፡፡ ከእርሱም ጋር እንዲኖሩና ለመስበክ እንዲልካቸው... ሥልጣን ይሆንላቸው ዘንድ አሥራ ሁለት አደረገ›› (ማር.3፡13-14)፡፡

የዚህ ክፍል አርእስተ ጉዳዩ የ12ቱ ሐዋርያት መጠራት ነው፡፡ የተሰጣቸው ተልእኮ ግን ጌታችን አሁን ለአገልጋዮቹ ከሚሰጣቸው ጋር ሊነጻጸር አይችልም፡፡ በማቴዎስ 10 መሠረት ሐዋርያት መጀመሪያ የተላኩት ወደ ቤተ አይሁድ ብቻ ነበር፡፡ በማር.16፡15 ወደ ዓለም ሁሉ ሄደው እንዲሰብኩ የተላኩት ጌታ በእስራኤል ዘንድ ተቀባይነትን ካጣና የማዳን ሥራውን በመስቀል ላይ ከፈጸመ በኋላ ነበር፡፡ ነገር ግን በሁለቱም አጠራሩ አንድ ነው፡፡

በእነዚህ ጥቅሶች ሦስት ጠቃሚ ነገሮችን እናስተውላለን፡፡ በመጀመሪያ ‹‹ራሱ የወደዳቸውን›› እንደ ጠራቸው እናያለን፡፡ ከዚያም ለምን እንደጠራቸው ሲያሳይ ‹‹ከእርሱ ጋር እንዲኖሩ›› ካለ በኋላ በሦስተኛ ደረጃም ‹‹ለመስበክ እንዲልካቸው›› ይላል፡፡

በመጀመሪያ የተጠቀሰው የአጠራሩ መርሆ ጌታችን አገልጋዮችን የሚጠራው በራሱ ነጻ ፈቃድ መሆኑ ነው፡፡ ለኤርምያስ የተነገረውን ብንመለከት ‹‹በሆድ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ፤ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ፤ ለአሕዛብም ነቢይ አድርጌሃለሁ›› ብሎታል (ኤር.1፡5) መጥምቁ ዮሐንስም እንዲሁ ተመሳሳይ አጠራር ነበረው (ሉቃ.1፡13-17) ጳውሎስም ‹‹ነገር ግን በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ የለየኝ በጸጋውም የጠራኝ እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ልጁን በእኔ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ ... (ገላ.1፡15-16)››፡፡ እያለ ስለራሱ አጠራር ሲናገር እንሰማዋለን፡፡

የእግዚአብሔር አገልጋይም ሆነ ሌላ ማንም ሰው፣ ወይንም ቤተክርስቲያን፣ ማንም ወገን ቢሆን በጌታ አገልጋይ ጥሪ ላይ ድርሻ የለውም፡፡ ጌታ ይህን የወደደውን አገልጋይ ራሱ የመጥራት መብቱን በተለይ ለራሱ ብቻ አስቀርቶታል፡፡ ይህ የእግዚአብሔር መብት ነው፡፡ ለኤርምያስ በተነገረውና ስለዚህ ጉዳይ በገላትያ መልእክት ከተጻፈው እንደምናየው የጥሪው ዝግጅት ከልደት ወይም ከዚያ በፊት ጀምሮ ያን ሰው ጌታ ጠርቶት እስኪለወጥ ድረስ የሚቀጥል እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡

ከእርሱ ጋር መሆን

እግዚአብሔር የሚጠራን ወዴት ነው? የተጠራውስ ሰው ወዲያውኑ እንደተለወጠ ትልቅ ሥራ ይሰጠዋልን? ደቀመዛሙርቱን ከእርሱ ጋር እንዲሆኑ ጠራቸው የሚለውን ስናይ እግዚአብሔርን ለማገልገል አስፈላጊው ቅድመ ሁኔታ ከጌታ ጋር መሆንና ከእግዚአብሔር መማር ነው፡፡ ደቀመዛሙርት በተጠሩበት በማርቆስ 3፡13 እና ደቀመዛሙርት ለአገልግሎት በተላኩበት በማርቆስ 6፡7 መካከል ረጅም ጊዜ ነበር፡፡ ልዩ የሆነውን ተልዕኮአቸውን ፈጽመው ከተመለሱ በኋላም ጌታ ከእርሱ ጋር እንዲሆኑ ለብቻቸው ወሰዳቸው፡፡ አገልግሎቱን ሲጀምር አገልጋዩ ከጌታ ዘንድ ወጥቶ ካልሄደና አገልግሎቱን ሲፈጽምም ተመልሶ ወደጌታ ፊት ካልቀረበ የተባረከ አገልግሎት ይኖራል ተብሎ ሊታሰብ አይገባም፡፡ እኛስ እንደ ሐዋርያቱ እንደዚህ እናደርጋለንን? ‹‹ሐዋርያትም ወደ ኢየሱስ ተሰብስበው ያደረጉትንና ያስተማሩትን ሁሉ ነገሩት›› (ማር.6፡30-33) ያደረጉትንና ያስተማሩትን ሁሉ ሊነግሩት ጌታ ብቻቸውን ለይቶ ሲወስዳቸው እንዴት ያለ የመባረክና የመታነፅ ሰዓት ይሆንላቸው ነበር! እኛም እንደዚሁ አብልጠን ብናደርግ አገልግሎታችን እንዴት አብዝቶ ይባረክ ነበር?

በአንድ ወቅት ደቀመዛሙርቱ በአካል ከጌታችን ጋር እንደነበሩ በአካል ከእርሱ ጋር መሆን አንችልም፤ ነገር ግን በመንፈስ ከእርሱ ጋር መሆን እንችላለን፡፡ በዮሐ.14፡21 ላይ ‹‹ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው፡፡ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል እኔም እወደዋለሁ ራሴንም እገልጥለታለሁ›› ይላል፡፡ ቀጥሎም በቊጥር 23 ላይ እንዲህ የሚል እናገኛለን፤ ‹‹የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል፡፡ ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን፡፡››

ለጌታ ያለን ፍቅር የሚታወቀው ትዕዛዛቱን በመጠበቅ ነው፡፡ 1ዮሐ.5፡3ም ይህንኑ ያሳያል፡፡ ለአንድ ሰው ጌታን እወደዋለሁ እያለ ነገር ግን በዚያ ልክ ከቃሉ ጋር በሚጋጭ አካሄድ መጓዝ ምንኛ የሚቃረን ነገር ነው!

ነገር ግን ከላይ በቁ.23 ያየነው ከዚህም በላይ ያሳስበናል፡፡ አንድ ሰው ጌታችንን በእውነት የሚወደው ከሆነ ጌታ በግልጥ አድርጉ ያለውን ብቻ በማድረግ አይረካም፤ በተጨማሪም ፈቃዱን በመሻት ሁል ጊዜ ጌታውን ለማስደሰት ይናፍቃል፡፡ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ብዙ ትዕዛዛት የሉም፡፡ ነገር ግን ጌታችን የራሱ የሆኑትን እንደቃሉ እንደሚያደርጉ በማሰብ ሐሳቡን በቃሉ ውስጥ አስቀምጦልናል፡፡ በቃሉ መሠረት እንዲሄዱም ይፈልጋል፡፡ ይህ ተፈጽሞ ሲገኝም አብና ወልድ በዚያ ሰው ዘንድ ማደሪያ ለማድረግ ይመጣሉ፡፡ ስለዚህ ዛሬም ቢሆን እኛ በየቀኑ ከእርሱ ጋር መሆን እንችላለን፡፡ ይህ ደግሞ በትክክል እርሱ ለሚፈልገን አገልግሎት በእርሱ ብቁ እንሆን ዘንድ አስፈላጊው ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡

በእርሱ መላክ

በማርቆስ 6፡7 ላይ ጌታ ደቀ መዛሙርቱን ሲልካቸው ይታያል፡፡ ላዘዛቸው አገልግሎት ብቁ እስኪሆኑ ድረስም አስተምሮአቸዋል፡፡ በሰዎች በኩል ሲታዩ ግን ምንም ፊደል ያልቆጠሩና ያልተማሩ ሆነው ተገኝተዋል (የሐ.ሥ.4፡13)፡፡

በሰው መስፈርት ሲታዩ የተሰጣቸው ስፍራ ይህ ነበር፡፡ የዘመኑን የቲኦሎጂ ትምህርት አላጠናቀቁም፡፡ የተለያዩ የአይሁድ ሃይማኖት ምሁራን መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት እንደሚተረጉሙ አያውቁም፡፡ ጌታ የጠራቸው ከዕለታዊ ሥራቸው ላይ ነበር፡፡ ነገር ግን ከእርሱ ጋር ቆይተዋል፡፡ ይህንን ደግሞ ጠላቶቻቸውም አስተውለዋል (ሐ.ሥ.4፡13)፤ ጌታም ለዚያ ትልቅ አገልግሎት ሊጠቀምባቸው የቻለውም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ በጴጥሮስ ስብከት በአንድ ቀን ብቻ ሦስት ሺህ ነፍሳት ተለውጠዋል፡፡ ትምህርታቸውና ኅብረታቸው በዚያች ዕለት እግዚአብሔር ለጀመረው ሥራ ማለትም ለሕያው እግዚአብሔር ቤተክርስቲያን መታነጽ መሠረት ነበር (ሐ.ሥ.2፡42)፡፡

ከዚህ ቀን በፊት ደቀመዛሙርቱ የሠሩት ነገር አልነበረም ማለት አይደለም፡፡ ከእርሱ ጋር መሆን ከጀመሩበት ቀን ጀምሮ ጌታ አንዳንድ የሚሠሩትን ነገር ይሰጣቸው ነበር፡፡ እኛ እንደምናስበው በቀላል ሥራዎች ማገዝ አልነበረም፡፡ ከወንጌል የተነሣ ይመጣ በነበረው ችግርና ጥላቻ ሁሉ አብረውት ተካፍለዋል (ማር.3) ጌታ በባሕር ሲሻገር ይቀዝፉለት ነበር (ሉቃ.4፡35-41)፡፡

ከተለወጥንበት ቀን ከመጀመሪያይቱ ዕለት አንስቶ ከእርሱ ጋር እስከሆንን ድረስ ጌታ ኢየሱስ እንድናገለግለው ይፈልጋል፡፡ ለእርሱ ማገልገል ከፈለግን ሁልጊዜ የምንሠራው ሥራ ይኖረናል፡፡ የወንጌል ጽሑፎችን ማስነበብ እንችላለን፤ ወደ ወንጌል ጉባኤያትና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ዝግጅቶች ሰዎችን መጋበዝ እንደዚሁም የዚህ ዓይነት ዝግጅቶች ሲኖሩ በአቅማችን በመሳተፍ መርዳት እንችላለን፡፡ ልናገለግለው የምንፈልግ ከሆንን ወይም ዝግጁ ሆነን ከተገኘን ጌታ ሁል ጊዜ የምንሠራውን ሥራ ይሰጠናል፡፡ ይህም ማለት እርሱ ወደሚልከን ለመሄድ ወይም እርሱ የሚፈልገውን ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኞች መሆን ይኖርብናል ማለት ነው፡፡ በአንድ ጊዜ ጌታ ትልቅ አገልግሎት ይሰጠናል ብለን መጠበቅ የለብንም፡፡

በማቴ.25፡15 እንደምናየው ጌታ ለባሮቹ ሲሰጣቸው ለእያንዳንዱ እንደአቅሙ የሚሠሩበትን መክሊት እንዳደላቸው እናያለን፡፡ ሰነፍና ክፉ ባሪያ ተብሎ የተጠራው አገልጋይ ባለ አንድ መክሊት ነበር እንጂ አምስት መክሊት የተሰጠው ወይም ሁለት መክሊት የተሰጠው አይደለም፡፡ ያም ባለአንድ መክሊት በአንዲቱ ሊያተርፍባት ባለመቻሉ ያችው የተሰጠችው መክሊት ከእርሱ ተነጥቃ በተሰጠው መክሊት በታማኝነት ጠንክሮ ለሠራው ለሌላው በተጨማሪ ልትሰጥ በቅታለች፡፡ ይህ ደግሞ ከፊት የሚበልጥን አገኘ፡፡ እንድንሠራው በአደራ በእጃችን የሰጠንን ትናንሽ ነገሮችን በታማኝነትና በትጋት ባከናወንን ቊጥር ጌታም ወዲያውኑ ታላላቅ ሥራዎችን እንድንሠራ ይሰጠናል፡፡ ይህም ሊሆን የሚችለው ትናንሹን ሥራ በመታዘዝና በእርሱ ላይ በመደገፍ ከሠራን ነው፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት በአንድ ተራራማ አገር የምትኖርና ከሦስት ወራት በላይ ትምህርት ያልተከታተለች ትንሽ ሠራተኛ ልጅ ነበረች፡፡ በወር ከምታገኘው አራት ብር ደሞዟ አንዱን ለመንፈሳዊ ጉባኤ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ኪራይ አንዱን ለሰባክያን ወንጌልና የተቀረውን ሁለቱን ብር ብዙ ቤተሰብ ለሚያስተዳድረው ድሃ አባቷ ትሰጥ ነበር፡፡ በዚያ መንደር ከሚኖሩት ሁሉ አስበልጣ ትሰጥ ነበር፡፡ ከምሽት እስከ እኩለ ሌሊት ባለው ጊዜ ደግሞ ሌላ ሥራ በመሥራት በምታገኘው ልብሷን ትገዛ ነበር፡፡ አንድ ቀን አንድ የእግዚአብሔር ቅን አገልጋይ ወደዚያ እርሷ ወዳለችበት መንደር መጣ፡፡ እርሷ ባለችበት ቤትም ደረሰ፡፡ የማደሪያው ስፍራ ተጣብቦ ስለነበር የራሷን አነስተኛ መኝታ ክፍል ለቀቀችለት፡፡ መጽሐፍ ቅዱሷን በጠረጴዛ ላይ ትታው ስለነበር ሰውየውም አንስቶ በእያንዳንዱ ገጽ ላይ ያኖረችውን ማስታወሻ ያነብ ነበር፡፡ ከእነዚያም ማስታወሻዎች አንዱ ግን የሰውዬውን ትኩረት ሳበ፡፡ ያም በማርቆስ.16፡15 ‹‹ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ›› ከሚለው ቊጥር አንፃር ያኖረችው ማስታወሻ ነበር፤ እርሱም ‹‹እኔም መሄድ የምችል ሆኜ ብገኝ!›› የሚል ነበር፡፡

በነጋታውም ሰውዬው ይህንን አስመልክቶ አናገራት፤ ሠራተኛዋ ግን መልስ መስጠት ተስኗት በጣም ታነባ ነበር፡፡ ሰውየውም ቆይቶ ታሪኳን ሰማ፡፡ የተለወጠችው የ14 ዓመት ልጅ ሳለች ነበር፡፡ ከዕለታት በአንዱም ቀን ከውጭ ወደ ቤት ስትገባ ‹‹የቻይና የወንጌል ጥሪ›› የሚል አርዕስት የተጻፈበት ወረቀት ወድቆ አገኘች፡፡ ወረቀቱ ግን ከየት እንደመጣ ማንም አላወቀም፡፡ ይሁን እንጂ ከዚያች ቀን ጀምሮ ሐሳብዋ በሞላ ስለ ቻይና ብቻ ሆነ፡፡ ለአሥር ዓመታት በየቀኑ እግዚአብሔር ወደቻይና እንዲልካት ጸለየች፡፡ ከጥቂት ጊዜ በፊት ግን ይህንን ጸሎት አቆመች፡፡ እስከ አሁንም ተሳስቻለሁ ብላ ደመደመች፤ እግዚአብሔር ወደ ቻይና ሄዳ እንድታገለግለው ሳይሆን በማዕድቤት እየሠራች እንድታገለግለው እንደፈለገ በመረዳቷ ጌታ ሆይ በማዕድቤት ውስጥ እየሠራሁ እንዳገለግልህ እርዳኝ እያለች መጸለይ ጀመረች፡፡ ጌታም ጸሎቷን መለሰላት፡፡ ለአሥር ዓመታት ታላላቅ ነገሮችን ስትናፍቅ ነበር፡፡ ይህም ሆኖ ግን የአቅሟን ያህል በትናንሽ ነገሮች ማገልገልንም ቸል አላለችም፡፡ በገንዘቧ የምታደርገው አስተዋፅኦም ይህንኑ ያረጋግጣል፡፡ አሁን ግን ትልቅን ነገር መመኘት በማቆም ማዕድቤት ውስጥ ምስክር ሆና የጌታን ቃል ልታበራ ፈቃደኛ ሆነች፡፡ ታሪኳን ያደመጠው መንገደኛው አገልጋይም ይህችን ልጅ ይረዳ ዘንድ እግዚአብሔር ወደዚህ ገጠር እንደላከው ተረዳ፡፡ እርሷም ወደ ቻይና ሄደች፡፡ ‹‹ከሁሉ በሚያንስ የታመነ በብዙ ደግሞ የታመነ ነው›› (ሉቃ.16፡10)፡፡

በእግዚአብሔር መደገፍ

እግዚአብሔር አገልጋዮቹን ራሱ እንደሚጠራቸው አይተናል፡፡ እንደ ፈቃዱ ይጠራቸዋል፤ በእርሱም ብቻ ይላካሉ፡፡ ይህ ብቻ በቂ አይደለም፤ አገልግሎቱም በእግዚአብሔር ላይ በመደገፍ መከናወን አለበት፡፡ ‹‹አገልግሎትም ልዩ ልዩ ነው፤ ጌታም አንድ ነው›› (1ቆሮ.12፡5) እንደተባለው በማቴዎስ 25 ያየናቸው ባሪያዎች ስላከናወኑት ሥራ በጌታ ፊት ቀርበው በዝርዝር ማስረዳት ነበረባቸው፡፡ በዚሁ መልክ በማርቆስ 6፡30 እንደምንመለከተው ‹‹ሐዋርያትም ወደ ኢየሱስ ተሰብስበው ያደረጉትንና ያስተማሩትን ሁሉ ነገሩት››፡፡

የተረከብነውን ኃላፊነት በብቃት እንድንወጣ መንፈስ ቅዱስን ተቀብለናል፡፡ እርሱም እኛ የራሳችንን ፈቃድ እንዳንሠራ በሁሉም ነገር ሊመራን ይፈልጋል፤ ስናመልክም (በአምልኮ አገልግሎት) በእርሱ ኃይል እናመልካለን (ፊልጵ.3፡3) ስናገለግልም (የወንጌል አገልግሎት) እርሱ በሚሰጠን ስጦታ እናገለግላለን (1ቆሮ12፡11፤ ሐ.ሥ.16፡6-10)፡፡ ስለዚህ በአገልግሎታችን በመንፈስ ቅዱስ እንመራለን፡፡ ይህም ታላቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ትልቅ ነገር ነው፡፡ በመጀመሪያ በድፍረት እንድንጓዝ ያደርገናል፡፡ አማኝ ራሱን የሚመለከት ከሆነ ድፍረት ሊኖረው አይችልም፡፡ በራሱ ላይ ብዙ ድክመቶችንና ጉድለቶችን ስለሚመለከት አንዳች ነገር ለመሥራት ድፍረት አይኖረውም፡፡ ከእግዚአብሔር የተቀበለው ስጦታ መኖሩንና በጌታም መጠራቱን ቢያውቅም እንኳ በራሱ ላይ ስለሚያተኩር በውስጡ እኔ በረከት አላሰጥም ይላል፡፡ ኃጢአተኛ በሰው ቃላት ተለውጦ አያውቅም፤ አማኝም በሰው ቃላት ሊባረክ አይችልም፡፡ ለሚናገራቸው ሰዎች የሚያስፈልገውን በራሱ ማን ሊያውቅ ይችላል? ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ ሲገለገልብን ውጤቱ በረከት ይሆናል፤ መንፈስ ቅዱስ ለሰዎች በወቅቱ የሚያስፈልጋቸውን ያውቃል፡፡ ለአገልጋዮችም መንፈሳዊ ነገሮችን የሚናገሩበትን መንፈሳዊ ቃል ይሰጣቸዋል (1ቆሮ.2፡13)፡፡

ይህም ትልቅ ኃላፊነት ነው፡፡ የፈለገውን እንደ ፈቃዱ ሊጠቀምበት ይችል ዘንድ ለመንፈስ ቅዱስ ምሪት ልቦናችንን ከፍተን በጥንቃቄ ማዳመጥ አለብን፡፡ ምክንያቱም በግል አገልግሎትም ሆነ በጉባኤ እንደወደደ ሊመራ መብት ያለው መንፈስ ቅዱስ ብቻ ነው፡፡ በቤተክርስቲያን ጉባኤዎች ማን ማን ማገልገል (መምራት) እንዳለበት መወሰን እንደምንችል በምናስብ ጊዜ ይህ ከቅዱሳት መጻሕፍት ውጭ ከመሆኑም በላይ የመንፈስቅዱስን መገኘት መናቅ ነው፡፡ እያንዳንዱ የጉባኤው ሰው ለማገልገል መብት አለው ካልን ወይም ደግሞ ይህንን መብት ለአንድ ወይም ለጥቂት ሰዎች ከወሰንነው ይህም ያው ስህተት ነው፡፡ ማንን ለመጠቀም እንደሚፈልግ መወሰን ያለበት መንፈስ ቅዱስ ብቻ ነው፡፡ የእኛ ሥራ እርሱ ሊገለገልብን በፈለገ ጊዜ እኛ ደግሞ መገልገያዎቹ እንሆን ዘንድ ዝግጁዎች ሆነን መገኘት ነው፡፡

አንድ ሰው በብዙዎች ፊት በሚናገርባቸው ስብሰባዎች በሚያገለግልበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ጌታ አስቀድሞውኑ ለዚሁ አገልግሎት የሰጠውን ስጦታዎች ይጠቀማል፡፡ ይሁን እንጂ ትላልቅ ስጦታዎች በስብሰባው መካከል እያሉም እንኳን በትናንሽ ስጦታዎች ሊገለገል ይችላል፡፡ ጸሎትና ምስጋናን ወይም ዝማሬን በተመለከተ እነዚህ ስጦታዎች አይደሉም፡፡ እከሌ የጸሎት ስጦታ አለው ብለው ደጋግመው የሚናገሩ ሰዎች ካሉ ይህ ስህተት ነው፡፡ ለጸሎትና ለምስጋና መንፈስ ቅዱስ ማንንም አማኝ ካለው መንፈሳዊ ሁኔታ በመነሳት ሊጠቀምበት ይችላል፡፡ ለወጣትም ሆነ ለአዛውንት መንፈስ ቅዱስ እንደፈለገው እንዲጠቀምብንና ሊጠቀምብንም ሲፈልግ እንዲጠቀመብን ራሳችንን መስጠት በእያንዳንዳችን ላይ የተጣለ ምን ያህል ኃላፊነት ነው!

ከሰላምታ ጋር
በጌታ አገልገሎት ወንድማችሁ

ምዕራፍ 19 ስፍራችን በምድር ላይ

ውድ ወዳጄ

ባለፈው መልእክቴ እኛ በእግዚአብሔር ፊት ያለንን ስፍራ በተመለከተ ጽፌልህ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በምድር ስላለን ስፍራ ልነግርህ እወዳለሁ፡፡ ይህም ደግሞ እንደሌላው ሁሉ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ፊት መቆም የምንችለው በክርስቶስ እንደሆነ ሁሉ በምድርም እንዲሁ በክርስቶስ ሆነን መገለጥ ይኖርብናል፡፡ ወይም በሌላ አባባል በእርሱ በኩል በእግዚአብሔር ፊት እንደሆንን ሁሉ በዚህ ምድርም የእርሱ ቦታ ተሰጥቶናል፡፡ ይህንንም እውነታ ዘወትር በነፍሶቻችን ፊት ልናቆየው የተገባ ነው፡፡ በምድር ላይ ያለንን ስፍራ በተመለከተ ሁለት ሊታወቁ የሚገባቸው ጠቃሚ ገጽታዎች አሉ፡፡ አንደኛው ከዓለም ጋር በተያያዘ ሲሆን ሁለተኛው ከሰፈር ጋር በተያያዘ ይሆናል፡፡ ሰፈር ስንልም ለእግዚአብሔር የአፍ ምስክር ለመሆን በዚህ ዘመን የአይሁድን ሃይማኖት መተካት የቻለውን የተደራጀ አፍኣዊ ክርስትናን ማለታችን ነው፡፡ (ሮሜ 11ን እና ማቴ 13ን ማንበብ ይጠቅማል)

ስፍራችን ከዓለም አኳያ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአይሁድ ጋር ሲነጋገር ‹‹እናንተ ከታች ናችሁ እኔ ከላይ ነኝ እናንተ ከዚህ ዓለም ናችሁ እኔ ከዚህ ዓለም አይደለሁም›› (ዮሐ.8፡23) ሲል ሌላ ጊዜ ደግሞ የራሱ የሆኑትን ወደ አባቱ ሲያቀርብ ‹‹እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም›› (ዮሐ.17፡16) ብሏል፡፡ በዮሐንስ 17 ከ14 እስከ 19 ያሉትን ቊጥሮች ስንመለከት ደግሞ ደቀ መዛሙርቱን በዓለም እስካሉ ድረስ በራሱ ስፍራ ሲያቆማቸው እናያለን፡፡ ከፍ ብለን ከቊ.6-13 ብናይ በአባቱ ፊት የራሱን ስፍራ ሲያስይዛቸው ይታያል፡፡ በዓለም ላይ የራሱን ስፍራ ማስያዙ ግን እርሱ ከዓለም እንዳልሆነ ሁሉ እነርሱም ከዓለም ስላልሆኑ ነው፡፡ ዳግመኛ በመወለዳቸው ከዚህ ዓለም ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ስለሆነም እርሱደረሰበት ጥላቻ እንደሚደርስባቸው ደጋግሞ ይነግራቸው ነበር፡፡ ለመጥቀስ ያህልም ‹‹ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ እወቁ ከዓለምስ ብትሆኑ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፡፡ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል፡፡ ባሪያ ከጌታው አይበልጥም ብዬ የነገርኋችሁን ቃል አስቡ፡፡ እኔን አሳደውኝ እንደሆኑ እናንተንም ደግሞ ያሳድዱአችኋል፡፡ ቃሌን ጠብቀው እንደ ሆኑ ቃላችሁን ደግሞ ይጠብቃሉ›› (ዮሐ.15፡18-20) ብሏል፡፡ ዮሐንስም በአማኞች እና በዓለም መካከል ያለውን ግልጽ ልዩነት ሲያሳይ ‹‹ከእግዚአብሔር እንደሆንን ዓለምም በሞላው በክፉው እንደተያዘ እናውቃለን›› ሲል ጽፏል (1ዮሐ.5፡19)፡፡

እነዚህም ምንባቦች ከላይ ከሚታየው ባሻገር ብዙ የተሸከሙት ሐሳብ አለ፡፡ እግዚአብሔር እያንዳንዱን አማኝ ከክርስቶስ ጋር ሞቶ እንደተነሳ ይቆጥረዋል (ሮሜ6፡3-5፤ ቆላ.3፡1-3) እስራኤል በኤርትራ ባህር በኩል ከግብፅ እንደወጣ ክርስቲያንም በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ከዚህ ዓለም ተለይቶ ወጥቶአል፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳ ተመልሶ በውስጧ ለክርስቶስ እንዲኖር ወደ ዓለም ቢላክም (ዮሐ.17፡18) ክርስቲያን ከዚህ ዓለም አይደለም፡፡ ጳውሎስም በአገልግሎት እየተጋ ሲደክም በነበረበት በዚህ ዓለም ውስጥ ስላለበት ሁኔታ ሲናገር ‹‹ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ›› (ገላ.6፡14) ሲል ተናግሮአል፡፡ በክርስቶስ መስቀል ዓለም እንደተፈረደበት ተመልክቷል (ዮሐ.12፡31) መስቀሉን ከራሱ አኳያ ሲያየው ደግሞ ራሱ ለዓለም እንደተሰቀለና እንደሞተ ተረዳ፡፡ ሞት የሚለየውን ያህል እርሱና ዓለም ተለያይተዋል፡፡

ይህን ትምህርት ለማጠቃለል ክርስቲያን በምድር ቢሆንም ከዓለም እንዳልሆነ አይተናል፤ ክርስቶስ ከዚህ ዓለም እንዳልሆነ ያህል ክርስቲያንም ከዚህ ዓለም አይደለም፡፡ ምክንያቱም ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነውና፡፡ አስቀድመን እንዳየነው በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ምክንያት ከዓለም ወጥቷል፡፡ ስለዚህ ከዓለም ፍጹም መለየት አለበት፤ ከዓለም ጋርም መስማማት የለበትም (ገላ.1፡3፤ ሮሜ12፡2) ይህም ማለት በመንፈስ፣ በጠባዩ በአመሉና በሁሉም አካሄዱ ከዚህ ዓለም አለመሆንኑን ማሳየት አለበት ማለት ነው፡፡ ይህ የመስቀሉ ሕይወት ተግባራዊ በመሆኑም እርሱ እንደ ተሰቀለበት ሆኖ ከመስቀሉ ጋር ተጣብቆ ይኖራል፡፡ ይህ ከሆነ በተፈረደባቸው ሁለት ነገሮች ማለትም በመስቀል በተሰቀለው ሰውና በመስቀል በተፈረደበት ዓለም መካከል መነፋፈቅም ሆነ መቀላቀል አይኖርም፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ዓለም ውስጥ በክርስቶስ ፈንታ ይኖራል፡፡ ይህም ማለት ለክርስቶስ ሲል ራሱን በክርስቶስ በመግለጥ ይኖራል ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ለክርስቶስ እየመሰከረ ክርስቶስ እንደተመላለሰ በመመላለስ በዓለም ውስጥ ይኖራል (ፊልጵ.2፡15፤ 1ዮሐ.2፡6) ክርስቶስን ያጋጠመው ሁሉ ለእርሱም እንደሚተርፈው አስቀድሞ ሊያውቅ ይገባል፡፡ ክርስቶስ እንደተሰቀለ እንሰቀላለን ማለት አይደለም፤ ነገር ግን ታማኝ አገልጋዮች ከሆንን እርሱን ያጋጠመው የተቃውሞ መንፈስ ያጋጥመናል፡፡ እርሱን እየመሰልን በሄድን ቊጥር ስደታችን ይበዛል፡፡ በአሁን ጊዜ አማኞች ከዓለም የሚደርስባቸው መከራ አነስተኛ ለመሆኑ ዋናው ምክንያት ከዓለም የተለዩት በጥቂቱ በመሆኑ ነው፡፡

ከዚህ ርእስ ወደተያያዘው ሌላ ክፍል ከመሄዴ በፊት ከዓለም ጋር የሚያገናኛችሁን ማንኛውንም የሥነምግባር ቁርኝት ከሕይወታችሁ እንድታስወግዱ አጥብቄ አሳስባችኋለሁ፡፡ የዚህ ዓለም መንፈስ ትንሽ ቀዳዳ በመጠቀም በእግዚአብሔር ጉባኤያት ውስጥ የዓለምን ነገር በማሾለክ በጌታ ማዕድ ዙሪያም እንኳ ሳይቀር ራሱን እስከ ማስቀመጥ ደርሶአል፡፡ ይህም ሞቱን ልንናገርለት ለተሰበሰብንለት ጌታ የሚያሳዝነው ታላቅ ድፍረት ነው፡፡ እኛ ዓለም አልቀበልም ያለችውና የሰቀለችው የክርስቶስ ወገን መሆናችንን ራሷም ታውቅ ዘንድ ሁሉም ቅዱሳን ራሳቸውን በእግዚአብሔር ፊት ዝቅ ብለው የሚያመልኩበት አዲስ ጸጋ እንዲሰጣቸው እንዲፈልጉ የቀረበላቸው ጥሪ እንደምን ያለ ጥሪ ነው! የከበረውን ክርስቶስ የልባችን ሐሳብና የተስፋችን ግብ አድርገን እንደ ጳውሎስ ከመከራው ጋር መካፈልንና በሞቱ እርሱን መምሰልን የምንፈልግ ስንቶቻችን ነን?

ስፍራችን ከሰፈር አኳያ

ወደ ዕብራውያን በተጻፈው መልእክት በ13ኛው ምዕራፍ ከ11 እስከ 13 ባሉት ቊጥሮች ‹‹ሊቀ ካህናት ስለ ኃጢአት ወደ ቅድስት የእንስሶችን ደም ያቀርባልና ሥጋቸው ግን ከሰፈር ውጭ ይቃጠላል፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ደግሞ በገዛ ደሙ ሕዝቡን እንዲቀድስ ከበር ውጭ መከራን ተቀበለ፡፡ እንግዲህ ነቀፌታውን እየተሸከምን ወደ እርሱ ወደ ሰፈሩ ውጭ እንውጣ›› የሚል ቃል ተጽፎ እናገኛለን፡፡ በዚህ ምንባብ ውስጥም ሁለት ግልጽ ሐሳቦች አሉ፡፡ የእንስሶቹ ደም ወደ ቅድስት ሲገባ ሥጋቸው ደግሞ ከሰፈር ውጭ የሚጣል በመሆኑ ለእነዚህ መሥዋዕቶች ምሳሌ የሆነው ክርስቶስ በሞቱ ከሁለቱም ነገሮች ጋር እንደሚዛመድ ሐዋርያው አሳይቶናል፡፡ ስለዚህም አማኝ የደረሰባቸው ሁለት ቦታዎች አሉ ማለት ነው፡፡ እነዚህም ቦታዎች በእግዚአብሔር ፊት ደሙ የገባባት ቅድስትና በምድር ላይ ደግሞ ክርስቶስ መከራ የተቀበለበት ከሰፈር ውጭ ያለው ቦታ ነው፡፡ በክርስቶስ ሆነን ከእርሱ በሆነው መዓዛ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነትን ካገኘን በምድርም እንዲሁ ከእርሱ ጋር በመሆን በእርሱ ቦታ ሆነን ስድብ፣ ጥላቻና መገለልን እንቀበላለን ማለት ነው፡፡ ስለሆነም በምድር ላይ የአማኙ ስፍራ ከሰፈር ውጭ ነው፡፡ ከዚህም በመነሳት የዕብራውያን ጸሐፊ ‹‹ነቀፌታውን እየተሸከምን ወደ እርሱ ወደ ሰፈሩ ውጭ እንውጣ›› ይለናል፡፡

ሰፈር ምንድነው? ብለን እንጠይቅ ይሆናል፡፡ የጠቀስኩትን ምንባብ መሠረት አድርገን ስናየው በማያሻማ ሁኔታ ሰፈር የተባለው የአይሁድ ሃይማኖት እንደሆነ በግልጽ እንረዳለን፡፡ ታዲያ ከአሁኑ ጊዜ ጋር ምን ያገናኘዋል ብለን ብንጠይቅ ደግሞ መልሱ እንዲህ ነው፡፡ የአይሁድ ሃይማኖት ከእግዚአብሔር የተሰጠ ሃይማኖት ነበር፡፡ በምድርም የእግዚአብሔር ምስክር በመሆን አገልግሏል፡፡ ይህም የአይሁድ ሃይማኖት [በሰው አለመታዘዝ ምክንያት] የተሰጠበትን ዓላማ መወጣት ተሳነው፤ በሐዋርያት ስብከት የተሰበከውን ክርስቶስን ለመመጨረሻ ጊዜ ባለመቀበላቸው ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ወደ ጎን ተትቶ በሮሜ.11 በተገለጠው መሠረት ክርስትና በምትኩ ተተካ፡፡ ስለሆነም አሁን ያለው ሰፈር በዚያው በአይሁድ ሰፈር መልክና ሥርዓት የተዋቀረውን ክርስትና ማለት ሁሉንም ቤተ እምነት የምታካትተውን አፍኣዊቷን ቤተክርስቲያን የሚያመለክት ነው፡፡ ሰፈር በስመ ክርስትና የሚጠሩትን ሁሉ ማለትም ከግዙፎቹ የሃይማኖት ድርጅቶች አንስቶ እስከ ትናንሾቹ ድረስ ያሉትን፣ በቡድን ስሜትና በብልሹ ስብከት ላይ በስመ ክርስትና የተዋቀሩ የእምነት ድርጅቶችን ያጠቃልላል፡፡ ከዚህ ከሰፈር እንድንወጣ የምንጠየቀው ለምንድነው? የሚል ጥያቄ ቢነሳም ይህ ሰፈር የእግዚአብሔር ምስክር ለመሆን ብቃት የሌለው ስለሆነ ነው፡፡ መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ(ራዕ.2፡11ወዘተ) የእግዚአብሔር ቃል እግዚአብሔር የሚለውን ለማወቅ ዋስትናችን ነው፡፡ በእግዚአብሔር ቃል ሁሉንም እንድንመዝን ደግሞ ኃላፊነት አለብን፡፡ እነዚህን ዲኖሚኔሽኖች በቃሉ መሠረት ብንመረምራቸው ባለመታዘዝና በውድቀት ውስጥ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ እንደ እግዚአብሔር ሐሳብ ለመመላለስ የሚነሳው አማኝ ከእነዚህ ድርጅቶችና ከተሸከሙት ስህተታቸው ራሱን በማግለል በዚህ አደናጋሪ ክፉ ዘመን ክፋት እንዳይጠለፍም ተጠንቅቆ ለቃሉ በመታዘዝ በክርስቶስ ስም ከሚሰበሰቡት ጋር ከመሰብሰብ በቀር የሚቀርለት ነገር አይኖርም፡፡ በዚህ በኩልም በዘጸአት 33 ያለው ታላቅ ትምህርት መመሪያ ሊሆነን ይችላል፡፡ በዘጸአት 32 እንደምናየው ሙሴ ከተራራው እንደወረደ ሰፈሩ በሙሉ ወደ ጣኦት አምልኮ ገብቶ አገኘ፡፡ ሙሴም ስለ እስራኤል ለመማለድ ተመልሶ ሄደ፡፡ በምዕራፍ 33 ቊጥር 7 ላይ እንደምናነበውም ሙሴም ድንኳኑን እየወሰደ ከሰፈሩ ውጭ ይተክለው ነበር፤ ከሰፈሩም ራቅ ያደርገው ነበር፤ ‹‹የመገናኛውም ድንኳን›› ብሎ ጠራው፡፡ እግዚአብሔርንም የፈለገ ሁሉ ከሰፈር ውጭ ወዳለው ወደ መገናኛው ድንኳን ይወጣ ነበር፡፡ ሙሴ ይህን ያደረገበት ምክንያትም በተበላሸና ባደፈ የአምልኮ ሥርዓት ውስጥ እግዚአብሔር የሚገለጥበትን ድንኳን መትከል እንደማይቻል በመረዳቱ ነበር፡፡ እኛም ለዘመናችን የሚሆነን ነፀብራቅ እናገኝበታለን፡፡ ይህም በጥንቃቄ እናስብበትና በማስተዋል እናጤነው ዘንድ የሚገባን ጉዳይ ነው፡፡

አሁን እንዳየነው እንግዲህ በምድር ላይ የአማኝ ስፍራ የት መሆኑን መረዳት እንድትችል በቂ ነገር ተብሏል፡፡ በአንድ በኩል ከዓለም በመለየት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ከሰፈር ውጭ በመሆን ነው፡፡ በእነዚህ ቦታዎች መሆንም ከዓለም ጥላቻን ከሰፈር ደግሞ ስድብና ነቀፋን ያስከትልብናል፡፡ ይህም ከሆነ ደግሞ ከተባረከው ጌታችን ጋር በሙላት እንቆጠራለን፡፡ ስለዚህ ከዓለም ጥላቻም ሳንሸሽ በሰፈርም ነቀፌታ ሳናፍር በሁለቱም ስፍራዎች ‹‹ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለተቆጠሩ ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ፤ ዕለት ዕለትም በመቅደስና በቤታቸው ስለኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ ማስተማርንና መስበክን አይተዉም ነበር›› (ሐ.ሥ.5፡41-42) ተብሎ ለቀደሙት እንደተነገረ ስለስሙ በሚደርስብን ነገር ሁሉ ደስተኞች እንድንሆን ያብቃን፡፡

በክርስቶስ የምወድህ ወንድምህ፡፡ HLH ‹‹ይህንንም በሰሙ ጊዜ ልባቸው ተነካ፤
ጴጥሮስንና ሌሎቸንም ሐዋርያት
ወንድሞች ሆይ ምን እናድርግ?
አሉአቸው፡፡
ጴጥሮስም፡-

  • ንስሐ ግቡ
  • ኃጢአታችሁም የሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ
  • የመንፈስቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ፤ ተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ ጌታ አምላካችንም ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉት ሁሉ ነውና አላቸው፡፡
  • በብዙ ሌላ ቃልም መሰከረና ‹ከዚህ ጠማማ ትውልድ ዳኑ› ብሎ መከራቸው፡፡

ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ፤ በዚያን ቀን ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስ ተጨመሩ፤

  • በሐዋርያትም ትምህርትና
  • በኅብረት
  • እንጀራውንም በመቁረስ
  • በየጸሎቱም ይተጉ ነበር
  • (የሐ.ሥ.2፡37-42)

    አድራሻ
    የእውነት ቃል አገልግሎት፣ ፖ.ሣ.ቁ. 14787፣ አዲስ አበባ