የመጽሐፍ ቅዱስ መግቢያ
መጽሐፍ ቅዱስ ምንድነው?
መጽሐፍ ቅዱስ የብዙ ቅዱሳት መጻሕፍት ስብስብ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት መጻሕፍት በሮሜ1፡1 እና በ2ጢሞ.3፡15 ላይ «ቅዱሳን መጻሕፍት» ተብለው ተጠርተዋል፤ እንዲሁም በብዙ ስፍራ «መጻሕፍት» (ማቴ.22፡29፤ ሉቃ.24፣27ና45፤ ዮሐ.5፡39ና 47፤7፡15፤ የሐ.ሥ.17፡2ና11፤18፡28፤ ሮሜ.5፡4) ተብለው መጠራታቸውን እናስተውላለን፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ሁለት ዐበይት ክፍሎች ያሉት ሲሆን እነርሱም ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን ናቸው፤ «ኪዳን» የሚለው ቃል በሁለት ወገኖች መካከል የሚደረግ ውልን ወይም ስምምነትን የሚያመለክት ሲሆን ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን ሲባል ደግሞ እግዚአብሔር ለሰው የሰጠውን ቃል ኪዳን የሚያመለክት ነው፡፡ በእነዚህ በሁለቱ ኪዳናት እግዚአብሔር ኪዳንን ሰጪ ሰው ደግሞ ተቀባይ መሆኑን ማስተዋል ይገባል፡፡ «ብሉይ ኪዳን» እግዚአብሔር በሲና ተራራ በሙሴ አማካኝነት ለእስራኤል የሰጠው ኪዳን ነው (ዘጸ.19፡5-6፤ 24፡1-8)፡፡ «አዲስ ኪዳን» ደግሞ እግዚአብሔር ወደፊት ከሚመልሳቸው የእስራኤል ቤትና የይሁዳ ቤት ጋር የሚገባውን አዲስ ቃል ኪዳን የሚያሳይ ሲሆን (ኤር.31፡31፤ ዕብ.8፡8-13) በክርስቶስ ደም የተመሠረተውንና ክርስቶስ መካከለኛ የሆነለትን፣ እግዚአብሔር በክርስቶስ ለሚያምኑ ሁሉ የሰጠውን የአሁኑን ዘመን ኪዳንም ያመለክታል (ማቴ.26፡28፤ ማር.14፡24፤ ሉቃ.24፡20፤ 1ቆሮ.11፡25፤ 2ቆሮ.3፡6)፤ ዕብ.9፡15፤12፡24) ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን እነዚህን ሁለቱን ኪዳናት ብቻ ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን መጻሕፍት ያመለክታል፡፡ ብሉይ ኪዳን ከክርስቶስ በፊት የተጻፉትን ሲያመለክት አዲስ ኪዳን ደግሞ ከክርስቶስ በኋላ የተጻፉትን ያመለክታል (2ቆሮ.3፡14 ተመልከት)፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር መንፈስ መጻፉ
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉት ቅዱሳት መጻሕፍት በተለያዩ ዘመናት እና በተለያዩ ቦታዎች በኖሩ ቅዱሳን ሰዎች የተጻፉ ናቸው፡፡ በአብዛኛው ሲታይ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በነቢያት የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ደግሞ በሐዋርያት ተጽፈዋል (ዮሐ.1፡46፤ 5፡47፤ 21፡24፤ 2ጴጥ.3፡16፤ ራእ.1፡9-11)፡፡ ይሁን እንጂ መጻሕፍቱን የጻፉት ቃሉን ከእግዚአብሔር ተቀብለውና በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው በመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ቃል የያዘ መጽሐፍ ነው፡፡ ነቢያት የእግዚአብሔር ቃል እንደመጣላቸው በዘሌ.27፡3፤ በዘኁል.36፡13፤ በኢያሱ1፡1፤ በ1ሳሙ.3፡1፣ 21፤ በኤር.1፡2፤ በሕዝ.1፡2-3፤ .... ወዘተ ተገልጿል፣ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጐዳና ለቀደሙት አባቶች የተናገረው በነቢያት በኩል ነበር (ዕብ.1፡1)፡፡ በዘካ.7፡12 እግዚአብሔር ሕጉንና ቃሉን በቀደሙት ነቢያት እጅ በመንፈሱ እንደላከ ተጽፏል፡፡ ነቢያቱም ከእግዚአብሔር የተቀበሉትን የትንቢት ቃል ሲናገሩም ሆነ ሲጽፉ በመንፈስ ቅዱስ ተነድተዋል፤ ሐዋርያው ጴጥሮስም ይህንኑ እውነታ ሲገልጽ «ይህን በመጀመሪያ እወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጐም አልተፈቀደም፤ ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ» ብሏል (ጴጥ.1፡20-21)፡፡ የዘመኑ ፍጻሜ (መጨረሻ) ሲደርስ ደግሞ እግዚአብሔር ሰው በሆነው፡- በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ተናገረ (ዕብ.1፡2፤ ዮሐ.1፡18)፡፡ ኢየሱስ ደግሞ የተናገረውንና ያስተማረውን ቃል በተመለከተ ሲናገር «እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው» ብሏል (ዮሐ.6፡63)፤ ጴጥሮስ እንደመሰከረውም እርሱ «የዘላለም ሕይወት ቃል» አለው (ዮሐ.6፡68)፡፡ ሐዋርያትም ይህን የሕይወት ቃል በቀጥታ ከእርሱ ተቀብለዋል (1ዮሐ.1፡1)፡፡ ይሁንና ጌታ ኢየሱስ የሚነግራቸው ብዙ ነገር ቢኖረውም በዚያን ጊዜ ሊሸከሙት የማይችሉት ስለነበር ያልነገራቸው ነገር ነበር፤ «… የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል» ብሏቸው ነበር (ዮሐ.16.12-13)፡፡ በዚህም መሠረት ሐዋርያት የእግዚአብሔርን ቃል በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ተናግረዋል፣ ጽፈዋል፡፡ እነርሱ የሚያስተምሩት ቃልም «የእግዚአብሔር ቃል» ተብሏል (የሐ.ሥ.4፡31፤ 6፡7፤ 8፡14፤ 11፡2፤ 12፡24)
ስለሆነም የብሉይ ኪዳንም ሆነ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት የተጻፉት በቅዱሳን ሰዎች ቢሆንም ጸሐፊዎቹ የእግዚአብሔርን ቃል ተቀብለው እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ ተመርተውና ተነድተው የጻፉአቸው በመሆኑ መጻሕፍቱ ራሳቸው የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው መጻሕፍት ናቸው፤ ይህን በተመለከተ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ሲጽፍ «የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል» ብሏል (2ጢሞ.3፡16)፡፡ በዚህ ቃል ውስጥ «የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ» የሚለው በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች «ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው መጻሕፍት ናቸው» ተብሎ ተገልጿል (አ.መ.ት፣ KJV፣ JND ተመልከት)፡፡ ይህ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ መሆኑን የሚነግረን የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ የተዘጋጀ እንዲሆን ለማድረግ ካለው ብቃት አንጻር ነው፡፡ የእግዚአብሔር መንፈስ የሌለበት መጽሐፍ ይህን ማድረግ አይችልምና፤ መጽሐፍ ቅዱስን በመጠቀም ግን የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ ትምህርት መስጠት፣ ተግሣጽ ማድረግ፣ ልብን ማቅናት እና በጽድቅ ያለውን ምክር መስጠት ይቻላል፡፡ ይህም የአማኞች የሕይወት መመሪያ መጽሐፍ ቅዱስ መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስ ቀኖና
«ቀኖና» የሚለው ቃል በዕብራይስጥ ካኔህ፣ በግሪከኛ ደግሞ ካኖን ተብሎ የሚታወቀው ቃል ነው፡፡ የቃሉ ፊደላዊ ትርጉም «መለኪያ ዘንግ» ማለት ሲሆን በተግባራዊ ትርጉሙ ደግሞ ቅዱሳት መጻሕፍትን፣ እንዲሁም እምነትንና ሥርዓትን የሚመለከቱ ውሳኔዎችንና ድንጋጌዎችን የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል፤ በአማርኛው ትርጉም ውስጥ በሕዝ.40፡3፤42፡16 እና በራእ.11፡1 ላይ «መለኪያ ዘንግ» ተብሎ የተተረጐመ ሲሆን፣ በ1ቆሮ10፡13-15 ላይ «ልክ»፣ በገላ.6፡16 ላይ ደግሞ «ሥርዓት» ተብሎ ተተርጐሟል፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስ ቀኖና ሲባል በእግዚአብሔር መንፈስ የተጻፉ የቅዱሳት መጻሕፍትን ቁጥርና ዝርዝር ያመለክታል፡፡ የቅዱሳት መጻሕፍትን ቁጥርና ዝርዝር መወሰን ያስፈለገበት ምክንያትም የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸውን መጻሕፍት ከሌሎች መንፈሳዊ መጻሕፍት በተለይም ሐሰተኞች ሰዎች ቅዱሳት መጻሕፍትን አስመስለው ከጻፏቸው የሐሰት መጻሕፍት ለመለየት ነው፡፡ በመቀጠል የብሉይ ኪዳን ቀኖናንና የአዲስ ኪዳን ቀኖናን ለየብቻ እንመለከታለን፡፡
3.1 የብሉይ ኪዳን ቀኖና
የብሉይ ኪዳንን መጻሕፍትን ቀኖናዊነት የሚያሳዩ ማስረጃዎች ከራሱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኛለን፡፡
ሀ. ከብሉይ ኪዳን፡- ዘዳግ.31፡26፤ ኢያሱ.1፡8፤ 2ነገሥ.22፡8-20 ነህ.8፡1-8፤ ኤር.36፡1-32፤ ዳን.9፡2
ለ. ከአዲስ ኪዳን፡- ማቴ.5፡17፤ ሉቃ.16፡29-31፤ ሉቃ.24፡44፤ ዮሐ.1፡46
የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ቁጥርና ዝርዝር በተመለከተ በአይሁድና በክርስቲያኖች ዘንድ የተለያዩ ቀኖናዎች አሉ፡፡ እነርሱንም ቀጥሎ እንመለከታለን፡፡
1) የዕብራይስጥ የብሉይ ኪዳን ቀኖና
የዕብራይስጥ የብሉይ ኪዳን ቀኖና የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በመጀመሪያ የተጻፉት በዕብራያን ቋንቋ ነው፡፡ አይሁድም የሚቀበሉት የዕብራይስጡን የብሉይ ኪዳን ቀኖና ነው፡፡ በዚህ ቀኖና መሠረት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት. 24 ተደርገው ይቈጠራሉ፡፡ የመጻሕፍቱ አከፋፈል ዝርዘራቸውና ቅደም ተከተላቸውም እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
24ቱ የዕብራይስጥ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ዝርዝር
| የመጻሕፍቱ አከፋፈል | የመጻሕፍቱ ዝርዝር | የመጻሕፍቱ ቊጥር |
|---|---|---|
| 1)ሕግ | ዘፍጥረት፣ ዘጸአት፣ ዘሌዋውያን፣ ዘኁልቊ፣ ዘዳግም | 5 |
| 2) ነቢያት |
| 8 |
| (3) ጽሑፋት | ሆሴዕ፣ ኢዩኤል፣ አሞጽ፣ አብድዩ፣ ዮናስ፣ ሚክያስ፣ ናሆም፣ ዕንባቆብ፣ ሶፎንያስ፣ ሐጌ፣ ዘካርያስ፣ ሚልክያስ (12) = (1) 8 መዝሙረ ዳዊት፣ ምሳሌ፣ ኢዮብ፣ መኃልይ፣ ሩት፣ ሰቆቃወ ኤርምያስ፣ መክብብ፣ አስቴር፣ ዳንኤል፣ ዕዝራና ነህምያ፣ 1ኛና 2ኛ ዜናመዋዕል 11 |
11 |
| ጠቅላላ ድምር | 24 | |
በሉቃ.24፡44 ላይ እንደምናነበው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው» ብሎ በተናገረው ቃል ውስጥ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን የሙሴ ሕግ፣ ነቢያትና መዝሙራት ብሎ ለ3ከፍሎ መናገሩ ይህንኑ የዕብራይስጡን ብሉይ ኪዳን አከፋፈልና ቅደም ተከተል የሚያሳይ ነው፡፡ 24 ቅዱሳት መጻሕፍትን የያዘው ይህ የዕብራየስጡ ብሉይ ኪዳን ቀኖና ለመጨረሻ ጊዜ የተወሰነው ጃምኒያ በተባለች ቦታ፣ በ90 ዓ.ም.፣ ዮሐናን ቤን ዘካይ በተባለ የአይሁድ ረቢ (ሊቅ) ሰብሳቢነት በተካሄደ የረበናት ጉባኤ ነው፡፡
የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ለመጀመሪያ ጊዜ የተተረጐሙት ከዕብራይስጥ ወደ ግሪክ ቋንቋ ነው፤ የተተረጐመውም በ280 ከክርስቶስ ልደት በፊት በእስክንድርያ ሲሆን የተረጐሙትም በዚያው በእስክንድርያ ከነበሩት አይሁድ የተሰባሰቡ ሰባ ሊቃውንት ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ብሉይ ኪዳንን ወደ ግሪክ ቋንቋ ሲተረጐሙ በዕብራይስጡ ብሉይ ኪዳን ውስጥ ያልነበሩ በአብዛኛው በግሪክ ቋንቋ የተጻፉ 14 መጻሕፍትን ከመጨመራቸውም ሌላ በዕብራይስጡ ብሉይ ኪዳን ቀኖና ሁለት ሆነው ሳለ እንደ አንድ ተቆጥረው የነበሩትን መጻሕፍት ለየብቻቸው ቆጥረዋቸዋል፤ በመሆኑም በሰባ ሊቃናት የተተረጐመው የግሪኩ ብሉይ ኪዳን ቀኖና 49 መጻሕፍትን ይዟል፤ እነዚህ መጻሕፍትም በ4 የሚከፈሉ ሲሆን ዝርዝርራቸው ቅደም ተከተላቸው እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
49ኙ የግሪክ የብሉይ ኪዳን ቀኖና መጻሕፍት ዝርዝር
| የመጻሕፍቱ አከፋፈል | የመጻሕፍቱ ዝርዝር | የመጻሕፍቱ ቊጥር | |
|---|---|---|---|
| 1) | የሕግ መጻሕፍት ዘፍጥረት፣ ዘጸአት፣ ዘሌዋውያን፣ ዘኁልቁ፣ ዘዳግም | 5 | |
| 2) | ኢያሱ፣ መሳፍንት፣ ሩት፣ 1ኛ ሳሙኤል፣ 2ኛ ሳሙኤል፣ 1ኛ ነገሥት፣ 2ኛ ነገሥት፣ 1ኛ ዜናመዋዕል፣ 2ዜናመዋዕል፣ 1ኛ ዕዝራ፣ ዕዝራና ነህምያ፣ አስቴር፣ ዮዲት፣ ጦቢት፣ 1ኛ መቃብያን፣ 2ኛ መቃብያን፣ 3ኛ መቃብያን | 17 | |
| 3) | መዝሙረ ዳዊት፣ ጸሎተ ምናሴ፣ ኢዮብ፣ ምሳሌ፣ መክብብ፣ መኃልይ፣ ጥበብ፣ ሲራክ | 8 | |
| 4) | ሆሴዕ፣ አሞጽ፣ ሚክያስ፣ ኢዩኤል፣ አብድዩ፣ ዮናስ፣ ናሆም፣ ዕንባቆም፣ ሶፎንያስ፣ ሐጌ፣ ዘካርያስ፣ ሚልክያስ፣ ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ፣ ባሮክ፣ ሰቆቃወ ኤርምያስ፣ መልእክተ ኤርምያስ፣ ሕዝቅኤል፣ ዳንኤል (ከሶስና፣ ጸሎተ ሠለስቱ ደቂቅ፤ ቤልና ደራጐን ጋር) | 19 | |
| ጠቅላላ ድምር | 49 | ||
| ተ.ቁ | የጀሮም (የቩልጌታ) ቀኖና | ተ.ቁ | የአማርኛው ቀኖና |
| 1 | ኦሪት ዘፍጥረት | 1 | ኦሪት ዘፍጥረት |
| 2 | ኦሪት ዘጸአት | 2 | ኦሪት ዘጸአት |
| 3 | ኦሪት ዘሌዋውያን | 3 | ኦሪት ዘሌዋውያን |
| 4 | ኦሪት ዘኁልቁ | 4 | ኦሪት ዘኁልቁ |
| 5 | ኦሪት ዘዳግም | 5 | ኦሪት ዘዳግም |
| 6 | መጽሐፈ ኢያሱ | 6 | መጽሐፈ ኢያሱ |
| 7 | መጽሐፈ መሳፍንት | 7 | መጽሐፈ መሳፍንት |
| 8 | መጽሐፈ ሩት | 8 | መጽሐፈ ሩት |
| 9 | መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ | 9 | መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊና ካልዕ |
| 10 | መጽሐፈ ሳሙኤል ካልዕ | 10 | መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊና ካልዕ |
| 11 | መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ | 11 | መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ |
| 12 | መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ | 12 | መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ |
| 13 | መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ | 13 | መጽሐፈ ኩፋሌ |
| 14 | መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ | 14 | መጽሐፈ ሄኖክ |
| 15 | መጽሐፈ ዕዝራ | 15 | መጽሐፈ ዕዝራ እና ነህምያ |
| 16 | መጽሐፈ ነህምያ | 16 | መጽሐፈ ዕዝራ ካልእና ዕዝራ ሱቱኤል |
| 17 | መጽሐፈ ጦቢት | 17 | መጽሐፈ ጦቢት |
| 18 | መጽሐፈ ዮዲት | 18 | መጽሐፈ ዮዲት |
| 19 | መጽሐፈ አስቴር | 19 | መጽሐፈ አስቴር |
| 20 | መጽሐፈ ኢዮብ | 20 | መጽሐፈ መቃብያን ቀዳማዊ |
| 21 | መዝሙረ ዳዊት | 21 | መጽሐፈ መቃብያን ካልዕና ሣልስ |
| 22 | መጽሐፈ ምሳሌ | 22 | መጽሐፈ ኢዮብ |
| 23 | መጽሐፈ መክብብ | 23 | መዝሙረ ዳዊት |
| 24 | መኃልየ መኃልይ | 24 | መጽሐፈ ምሳሌ |
| 25 | መጽሐፈ ጥበብ | 25 | መጽሐፈ ተግሣጽ |
| 26 | መጽሐፈ ሲራክ | 26 | መጽሐፈ ጥበብ |
| 27 | ትንቢተ ኢሳይያስ | 27 | መጽሐፈ መክብብ |
| 28 | ትንቢተ ኤርምያስ | 28 | መጽሐፈ መኃልየ መኃልይ |
| 29 | ሰቆቃወ ኤርምያስ | 29 | መጽሐፈ ሲራክ |
| 30 | መጽሐፈ ባሮክ | 30 | ትንቢተ ኢሳይያስ |
| 31 | ትንቢተ ሕዝቅኤል | 31 | ትንቢተ ኤርምያስ |
| 32 | ትንቢተ ዳንኤል (መጽሐፈ ሶስና፣ መዝሙረ ሠለስቱ ደቂቅ፣ ቤልና ደራጎን) | 32 | ትንቢተ ሕዝቅኤል |
| 33 | ትንቢተ ሆሴዕ | ትንቢተ ዳንኤል | |
| 34 | ትንቢተ አሞጽ | 34 | ትንቢተ ሆሴዕ |
| 35 | ትንቢተ ሚክያስ | 35 | ትንቢተ አሞጽ |
| 36 | ትንቢተ ኢዩኤል | 36 | ትንቢተ ሚክያስ |
| 37 | ትንቢተ አብድዩ | 37 | ትንቢተ ኢዩኤል |
| 38 | ትንቢተ ዮናስ | 38 | ትንቢተ አብድዩ |
| 39 | ትንቢተ ናሆም | 39 | ትንቢተ ዮናስ |
| 40 | ትንቢተ ዕንባቆም | 40 | ትንቢተ ናሆም |
| 41 | ትንቢተ ሶፎንያ | 41 | ትንቢተ ዕንባቆም |
| 42 | ትንቢተ ሐጌ | 42 | ትንቢተ ሶፎንያ |
| 43 | ትንቢተ ዘካርያስ | 43 | ትንቢተ ሐጌ |
| 44 | ትንቢተ ሚልክያስ | 44 | ትንቢተ ዘካርያስ |
| 45 | መጽሐፈ መቃብያን ቀዳማዊ | 45 | ትንቢተ ሚልክያስ |
| 46 | መጽሐፈ መቃብያን ካልዕ | 46 | መጽሐፈ ዮሴፍ ወልደ ኮርዮን |
የብሉይ ኪዳን የአፖክሪፋ መጻሕፍት
«አፖክሪፋ» የሚለው ቃል የላቲን ቃል ሲሆን ትርጉሙ ኅቡዕ ማለት ነው፤ የአፖክሪፋ መጻሕፍት ሲባል ለሕዝብ ይፋ የማይሆኑ ኅቡዓን መጻሕፍት ለማለት ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ይህን ስያሜ የሰጠው በ4ኛው ምዕተ ዓመት የነበረውና ቅዱሳት መጻሕፍትን ወደ ላቲን ቋንቋ የተረጐመው ጀሮም ነው፡፡ እነዚህ የብሉይ ኪዳን የአፖክሪፋ መጻሕፍት በአንዳንዶች ዘንድ “2ኛ ቀኖናውያን መጻሕፍት” ተብለው የሚጠሩ ሲሆኑ ብዙውን ጊዜ በዕብራይስጡ 24 ተደርገው ከሚቆጠሩት ከ39ኙ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በመቀጠል ከአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በፊት ሲቀመጡ ይታያል፡፡ በአማርኛው ትርጉም ውስጥ «የብሉይ ኪዳን 2ኛ ቀኖናውያን መጻሕፍት» ተብለው የተዘረዘሩት 18 መጻሕፍት ሲሆኑ እነርሱም የሚከተሉት ናቸው፡፡
| ተ.ቁ | የአማርኛው የብ.ኪ. አፖክሪፋ ዝርዝር | ማስታወሻ |
|---|---|---|
| 1 | መጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤል | በሰባ ሊቃናት የለም፣ በላቲን ዕዝራ ካልዕ ከምዕ.3 ጀምሮ ያለው ነው |
| 2 | መጽሐፈ ዕዝራ ካልዕ | በሰባ ሊቃናት “ዕዝራ ቀዳማዊ” የተባለው ነው |
| 3 | መጽሐፈ ጦቢት | ከሌሎች ትርጉሞች ጋር አንድ ነው |
| 4 | መጽሐፈ ዮዲት | ከሌሎች ትርጉሞች ጋር አንድ ነው |
| 5 | መጽሐፈ አስቴር | በዋናው መጽሐፈ አስቴር ላይ ተጨማሪ ቃል የያዘ |
| 6 | መጽሐፈ መቃብያን ቀዳማዊ | ከሌሎች ትርጉሞች የተለዩ ናቸው |
| 7 | መጽሐፈ መቃብያን ካልዕ | |
| 8 | መጽሐፈ መቃብያን ሣልስ | |
| 9 | መጽሐፈ ሲራክ | ከሌሎች ትርጉሞች ጋር አንድ ነው |
| 10 | ጸሎተ ምናሴ | ከ2ዜና33፡12፣18 ጋር አንጻጽር |
| 11 | ተረፈ ኤርምያስ | ከሰቆቃወ ኤርምያስ የሚቀጥል ተደርጓል፤ ከምዕ.6 በቀር “ከመልእክተ ኤርምያስ” ጋር አይመሳሰልም፡፡ |
| 12 | ሶስና | በሰባ ሊቃናት ከትንቢተ ዳንኤል ጋር የተቈጠረ |
| 13 | መጽሐፈ ባሮክ | ከሌሎች ትርጕሞች ጋር አንድ ነው |
| 14 | መጽሐፈ ጥበብ | ከሌሎች ትርጕሞች ጋር አንድ ነው |
| 15 | መዝሙረ ሠለስቱ ደቂቅ | በሰባ ሊቃናት ከትንቢተ ዳንኤል ጋር የተቈጠረ |
| 16 | ተረፈ ዳንኤል | በሌሎች ትርጉሞች “ቤልና ደራጐን” የተባለው ነው |
| 17 | መጽሐፈ ኩፋሌ | በሰባ ሊቃናትም ሆነ በሌሎች ትርጕሞች የለም፡፡ |
| 18 | መጽሐፈ ሄኖክ | በሰባ ሊቃናትም ሆነ በሌሎች ትርጕሞች የለም፡፡ |
እነዚህ መጻሕፍት ከዕዝራ ስቱኤል፣ ከመጽሐፈ ኩፋሌና ከመጽሐፈ ሄኖክ በቀር ሰባ ሊቃናት የጨመሯቸው ናቸው፡፡ 3ቱ የአማርኛ መጻሕፍተ መቃብያን በሰባ ሊቃናት የግሪክኛ ትርጉም ውስጥ ከሚገኙት ይለያሉ፡፡
የብሉይ ኪዳን የአፖክሪፋ መጻሕፍት ከሚልክያስ በኋላ ባለው ዘመን የተወሰነ ታሪካዊ መረጃን ከመስጠታቸው ባሻገር በመጽሐፍ ቅዱስ ገብተው ሊቆጠሩ የሚችሉ መጻሕፍት አይደሉም፡፡
3. 39 መጸሕፍት፡- ከጥንት ጀምሮ በሁሉም ክርስቲያኖች ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ትንቢተ ሚልክያስ ያሉት 39ኙ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ናቸው፡፡ ቀደም ሲል እንደገለጽነው እነዚህ መጻሕፍት በዕብራይስጡ የብሉይ ኪዳን ቀኖና ዝርዝር ውስጥ የሚገኙት 24ቱ መጻሕፍት ናቸው፡፡ እነርሱም እኛ በምንጠቀምበት የአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ሲሆኑ ቀጥሎ የተዘረዘሩት ናቸው፡፡
| የመጻሕፍቱ አከፋፈል | የመጻሕፍቱ ዝርዝር | የመጻሕፍቱ ቊጥር |
|---|---|---|
| 1) የሕግ መጻሕፍት | ዘፍጥረት፣ ዘጸአት፣ ዘሌዋውያን፣ ዘኁልቁ፣ ዘዳግም | 5 |
| 2) የታሪክ መጻሕፍት | ኢያሱ፣ መሳፍንት፣ ሩት፣ 1ኛ ሳሙኤል፣ 2ኛ ሳሙኤል፣ 1ኛ ነገሥት፣ 2ኛ ነገሥት፣ 1ኛ ዜናመዋዕል፣ 2ዜናመዋዕል፣ ዕዝራ፣ ነህምያ፣ አስቴር | 12 |
| 3) የቅኔ መጻሕፍት | ኢዮብ፣ መዝሙረ ዳዊት፣ ምሳሌ፣ መክብብ፣ መኃልይ | 5 |
| 4) የትንቢት መጻሕፍት | ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ፣ ሰቆቃወ ኤርምያስ፣ ሕዝቅኤል፣ ዳንኤል ሆሴዕ፣ አሞጽ፣ ሚክያስ፣ ኢዩኤል፣ አብድዩ፣ ዮናስ፣ ናሆም፣ ዕንባቆም፣ ሶፎንያስ፣ ሐጌ፣ ዘካርያስ፣ ሚልክያስ | 17 |
| ጠቅላላ ድምር | 39 | |
እነዚህ መጻሕፍት ለአራት መከፈላቸውና በዕብራይስጡ ተደርበው የተቈጠሩት መጻሕፍት በነጠላ ተዘርዝረው መቈጠራቸው የሰባ ሊቃናትን አከፋፈልና አቆጣጠር የተከተለ ቢሆንም መጻሕፍቱ ግን በዕብራይስጡ የብሉይ ኪዳን ቀኖና ውስጥ የሚገኙት 24ቱ መጻሕፍት ብቻ ናቸው፡፡ ክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱስነት ሊቀበሏቸው የሚገባቸው የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትም እነዚህ ብቻ ናቸው፤ ምክንያቱም፡-
በሮሜ3፡1-2 «እንግዲህ የአይሁዳዊ ብልጫው ምንድር ነው? ወይስ የመገረዝ ጥቅሙ ምንድር ነው? በሁሉ ነገር ብዙ ነው፡፡ አስቀድሞ የእግዚአብሔር ቃላት አደራ ተሰጡአቸው፡፡» ተብሎ እንደተጻፈው አይሁድ እንደ እግዚአብሔር ቃል የተቀበሏቸው መጻሕፍት እነዚህ ብቻ በመሆናቸው፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዕውቅና የሰጣቸው የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የሙሴ ሕግ፣ ነቢያትና መዝሙራት ተብለው ለ3 የተከፈሉት መጻሕፍት እነዚህ በመሆናቸው (ሉቃ.24፡44)
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሆነ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ሲጠቅሱ የተጠቀሙት የሰባ ሊቃናትን የግሪክኛ ትርጉም እንደነበረ ቢታወቅም ከእነዚህ መጻሕፍት ውጪ ከብሉይ ኪዳን የአፖክሪፋ መጻሕፍት ያልጠቀሱ በመሆናቸው ነው፡፡
የአዲስ ኪዳን ቀኖና
በአዲስ ኪዳን የተፈጸመውን የክርስቶስንና የሐዋርያትን ትምህርትና ሥራ የተመለከቱ ብዙ መጻሕፍት ተጽፈው ነበር፤ በሉቃ.1፡1-4 ላይ እንደምናነበው ሉቃስ ሲጽፍ «.... በኛ ዘንድ ስለተፈጸመው ነገር ብዙዎች ታሪክን በየተራው ለማዘጋጀት ስለሞከሩ እኔ ደግሞ ስለተማርኸው ቃል እርግጡን እንድታውቅ በጥንቃቄ ሁሉን ከመጀመሪያው ተከትዬ በየተራው ልጽፍልህ መልካም ሆኖ ታየኝ፡፡» ብሏል፡፡ ይሁንና ስለተፈጸመው ነገር ብዙዎች ቢጽፉም የተጻፉት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው እውነተኞች መጻሕፍት ነበሩ ማለት አይቻልም፤ ከእውነተኞቹ መጻሕፍት ጋር የተደባለቁ የሐሰት መጻሕፍትም ነበሩ፤ ለምሳሌ ሐሰተኞች ከነጳውሎስ እንደሚመጣ አስመስለው በመልእክት የሚያስቱበት ሁኔታ እንደ ነበረ ተጠቅሷል (2ተሰ.2፡2)፡፡ በመሆኑም ጳውሎስ በመልእክቶቹ መጨረሻ የመልእክቱን ማስረጃ ማስቀመጥ አስፈልጎት ነበር (2ተሰ.3፡17-18፤ ቈላ.4፡18)፡፡
ከሐዋርያት ዘመን በኋላ ከአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ጋር እየተቀላቀሉ ብዙዎችን ግራ ሲያጋቡ የነበሩት እነዚህ መጻሕፍት “የአዲስ ኪዳን የአፖክሪፋ መጻሕፍት” ተብለው የሚጠሩ ሲሆኑ ከጥንት ጀምሮ ከአዲስ ኪዳን ቀኖና ዝርዝር ወጪ እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡ እውነተኞቹ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በቁጥር 27 ሲሆኑ የእነዚህን መጻሕፍት ቁጥርና ዝርዝር ያስታወቁ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች እና በቀኖና የተወሰኑ የቤተክርስቲያን ጉባኤዎች ነበሩ፤ ከእነዚህም ዋና ዋና የሆኑትን ሁለቱን ብቻ እንመለከታለን፡፡
1. የእስክንድርያው አትናቴዎስ
አትናቴዎስ በቤተክርስቲያን ታሪክ በ325 ዓ.ም. በኒቅያ የተደረገውን ዓለም አቀፍ የቤተክርስቲያን ጉባኤ እንደመራ የሚታወቅ ሲሆን በዓለም ላሉ አብያተክርስቲያናት በሚያስተላልፈው ዓመታዊ መልእክቱ ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ይጽፍ ነበር፡፡ በ367 ዓ.ም. ባስተላለፈው በ39ኛው መልእክቱ ያነሣው ወቅታዊ ጉዳይ የቅዱሳት መጻሕፍትን ቀኖና ጉዳይ ነበር፤ በዚህ መልእክቱም የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት 27 መሆናቸውን ያስታወቀ ሲሆን ዝርዝራቸውንም ተናግሯል፡፡ ይህም አትናቴዎስ ያስታወቀው የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ቁጥርና ዝርዝር እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
| የመጻሕፍቱ አከፋፈል | የመጻሕፍቱ ዝርዝር | የመጻሕፍቱ ቊጥር |
|---|---|---|
| አራቱ ወንጌላ | ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስ፣ ዮሐንስ | 4 |
| የታሪክ መጽሐፍ | የሐዋርያት ሥራ | 1 |
| ሰባቱ መልእክታት | &ያዕቆብ፣ 1ኛ ጴጥሮስ፣ 2ኛ ጴጥሮስ፣ 1ኛ ዮሐንስ፣ 2ኛ ዮሐንስ፣ 3ኛ ዮሐንስ፣ የይሁዳ መልእክት | 7 |
| የጳውሎስ መልእክታት | ሮሜ፣ 1ኛ ቆሮንቶስ፣ 2ኛ ቆሮንቶስ፣ ገላትያ፣ ኤፌሶን፣ ፊልጵስዩስ፣ ቆላስይስ፣ 1ኛ ተሰሎንቄ፣ 2ኛ ተሰሎንቄ፣ ዕብራውያን፣ 1ኛ ጢሞቴዎስ፣ 2ኛ ጢሞተዎስ፣ ቲቶ፣ ፊልሞና | 14 |
| የትንቢት መጽሐፍ | የዮሐንስ ራእይ | 1 |
| ጠቅላላ ድምር | 27 | |
አትናቴዎስ እነዚህን መጻሕፍት በተመለከተ ሲናገር «እነዚህ የተጠማ በውስጣቸው በሚገኙ ቃላት ይረካ ዘንድ የእውነተኛ ደኅንነት ምንጮች ናቸው፤ በእነዚህ ብቻ የቅድስና ትምህርት ይሰበካል፤ ከእነዚህ ማንም ምንም መጨመር ወይም መቀነስ አይችልም» ብሏል፡፡
2. የካርቴጅ ጉባኤ
ካርቴጅ በሰሜን አፍሪካ በዛሬዋ ቱኒስያ ውስጥ የነበረች ከተማ ስትሆን ብዙ ዓለም አቀፍ የቤተክርስቲያን ጉባኤዎች ተካሂደውባታል፡፡ ከእነዚህም መካከል የቅዱሳት መጻሕፍትን ቀኖና በተመለከተ የተካሄዱ ሁለት ጉባኤዎች እንዳሉ ይታወቃል፤ እነርሱም የሚከተሉት ናቸው፡፡
ሀ) በ397 ዓ.ም. የተካሄደው ጉባኤ ሲሆን በ47ኛው ቀኖና ላይ የቅዱሳት መጻሕፍትን ቁጥርና ዝርዝር ወስኗል፡፡ ይህም ጉባኤ ቀደም ሲል በ393 ዓ.ም. ኤጴን (ሂፖ) በተባለች የአልጄሪያ ከተማ በተካሄደው የቤተክርስቲያን ጉባኤ በ6ኛው ቀኖና የተወሰነውን የቅዱሳት ቁጥርና ዝርዝር ያጸደቀ ጉባኤ ነው፡፡
ለ) በ419 ዓ.ም. የተካሄደው ጉባኤ ሲሆን በጊዜው ከተወሰኑት ከ32ቱ ቀኖናት መካከል 29ኛው ቀኖና ከዚያ በፊት በኤጰንና በዚያው በካርቴጅ የተወሰኑት ሁለት የቅዱሳት መጻሕፍት ቀኖናዎች የጸደቁበት ጉባኤ ነው፡፡
በእነዚህ የካርቴጅ ጉባኤዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ቀኖና መሠረት የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ቁጥር 27 ሲሆን ዝርዝራቸውም የሚከተለው ነው፡፡
| የመጻሕፍቱ አከፋፈል | የመጻሕፍቱ ዝርዝር | የመጻሕፍቱ ቊጥር |
|---|---|---|
| አራቱ ወንጌላ | ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስ፣ ዮሐንስ | 4 |
| የታሪክ መጽሐፍ | የሐዋርያት ሥራ | 1 |
| ሰባቱ መልእክታት | &ያዕቆብ፣ 1ኛ ጴጥሮስ፣ 2ኛ ጴጥሮስ፣ 1ኛ ዮሐንስ፣ 2ኛ ዮሐንስ፣ 3ኛ ዮሐንስ፣ የይሁዳ መልእክት | 7 |
| የጳውሎስ መልእክታት | ሮሜ፣ 1ኛ ቆሮንቶስ፣ 2ኛ ቆሮንቶስ፣ ገላትያ፣ ኤፌሶን፣ ፊልጵስዩስ፣ ቆላስይስ፣ 1ኛ ተሰሎንቄ፣ 2ኛ ተሰሎንቄ፣ ዕብራውያን፣ 1ኛ ጢሞቴዎስ፣ 2ኛ ጢሞተዎስ፣ ቲቶ፣ ፊልሞና | 13 |
| የዕብራውያን መልእክት | 1 | |
| የትንቢት መጽሐፍ | የዮሐንስ ራእይ | 1 |
| ጠቅላላ ድምር | 27 | |
በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተጻፉትና በመመሪያነት የምንቀበላቸው የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት እነዚህ 27ቱ መጻሕፍት ብቻ ናቸው፡፡ ይሁንና ባገራችን በእነዚህ በ27ቱ መጻሕፍት ላይ ሌሎች 8 የሥርዓት መጻሕፍትን በመጨመር የአዲስ ኪዳን መጻሕፍትን 35 አድርገው የሚቆጥሩ አሉ፤ ይህ ቀኖና ግን በየትኛውም የክርስትና ዓለም ተቀባይነት የሌለው ቀኖና ነው፡፡
ባጠቃላይ ተቀባይነት ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቀኖና ስንመለከት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት 39 ሲሆኑ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ደግሞ 27 ናቸው፤ በድምሩ መጽሐፍ ቅዱስ 66 መጻሕፍትን ይዟል፡፡