1.በትምህርት መትጋት
በክብር ያለውን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የልባቸው ማረፊያ አደርገው በእርሱ ማዕከልነት ዘወትር መሰብሰብ የጀመሩት እነዚያ የመጀመሪያዎቹ አማኞች በጊዜው በአካል የነበሩት ሐዋርያት በሚያስተምሩት ትምህርት ይተጉ ነበር፤ ይህም ማለት በወቅቱ በአንድ ላይ በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋርያት ከእግዚአብሔር የተቀበሉትን እውነት በሚያስተምሩባቸው ክፍለ ጊዜያት በጌታ ያመኑት ወገኖች ሁልጊዜም በአካል በመገኘት እየተማሩ ሥርና መሠረት ይዞ ለማደግና ለመታነጽ ይተጉ ነበር ማለት ነው፡፡ በዚህ ዘመን ያለን አማኞችም በጌታ በኢየሱስ ስም እየተሰባሰብን ማድረግ ያለብን የመጀመሪያው ነገር በሐዋርያት ትምህርት መትጋት ነው፡፡ ለመሆኑ እነዚህ ሐዋርያት እነማን ናቸው? ትምህርታቸውንስ ያገኙት ከማን ነው? በክርስቶስ ማዕከልነት የሚሰበሰቡ ሁሉ በሐዋርያት ትምህርት ሊተጉ የሚገባው በምን ምክንያት ነው?
ሐዋርያት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌልን እንዲሰብኩና ተሰውሮ የኖረውን የእግዚአብሔርን ምስጢር እንዲገልጡ ወደ ዓለም ሁሉ የላካቸው የእርሱ መልእክተኞች ናቸው፤ ለዚሁ ጉዳይ የመረጣቸውና የሾማቸውም ራሱ ክርሰቶስ ነው፡፡ ማርቆስ በወንጌሉ ይህን ሲገልጥ “ወደ ተራራም ወጣ፥ ራሱም የወደዳቸውን ወደ እርሱ ጠራ፥ ወደ እርሱም ሄዱ። ከእርሱም ጋር እንዲኖሩና ለመስበክ እንዲልካቸው፥ ድውዮችንም ሊፈውሱ አጋንንትንም ሊያወጡ ሥልጣን ይሆንላቸው ዘንድ አሥራ ሁለት አደረገ” ብሏል (ማር.3፡13-15)፤ ሉቃስም በበኩሉ “በነጋም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ጠራ፥ ከእነርሱም አሥራ ሁለት መረጠ ደግሞም ሐዋርያት ብሎ ሰየማቸው” በማለት ይገልጸዋል (ለቃ.6:13)፡፡ እነዚህንም ሐዋርያቱን “አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ” በማለት ወደ ዓለም ሁሉ ልኳቸዋል (ዮሐ.20፡21)፡፡ እነዚህም ሐዋርያት ከኢየሱስ ጋር አብረው በመኖር ያደረገውንና ያስተማረውን ያዩና የሰሙ ከመሆናቸውም በላይ ከሙታን ከተነሣ በኋላ በዓይናቸው ስላዩ በዚህች ዓለም ፊት የእርሱና የትንሣኤው ምስክር እንዲሆኑ ያደረጋቸው ናቸው፡፡ በተለይም አስራ ሁለቱን ሐዋርያት ከመጀመሪያ ጀምሮ ከእርሱ ጋር እንዲኖሩ የጠራቸው ጌታ ወደ ሰማይ ዐርጎ በእግዚአብሔር ቀኝ ከተቀመጠና መንፈስ ቅዱስን ከላከ በኋላ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ስለእርሱ እንዲመሰክሩ ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ ራሱ ጌታ ሲናገር “ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፤ እናንተም ደግሞ ከመጀመሪያ ከእኔ ጋር ኖራችኋልና ትመሰክራላችሁ” (ዮሐ.15:26-27)፡፡ በዚህም ቃል እንደምንረዳው መንፈስ ቅዱስ ከሰማይ የመጣ የክርስቶስ መለኮታዊ ምስክር ሲሆን ሐዋርያት ደግሞ ከምድር የተጠሩ ምስክሮች ናቸው ማለት ነው፡፡ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ሁለተኛ ምስክር ሆነው የተቆጠሩ መሆናቸውን ሐዋርያው ጴጥሮስም በኋላ ላይ ሲናገር “… እኛም ለዚህ ነገር ምስክሮች ነን፥ ደግሞም እግዚአብሔር ለሚታዘዙት የሰጠው መንፈስ ቅዱስ ምስክር ነው።” ብሏል (የሐ.ሥ.5:32)፡፡ ስለዚህ ሐዋርያት እግዚአብሔር በዚህች ምድር ላይ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ለልጁ ምስክር አድርጎ ያቆማቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ይህም ታላቅ ስፍራ ነው፡፡
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ካረገ በኋላ የሾመው ሐዋርያው ጳውሎስም ቢሆን በኋላ ላይ ራሱ እንደተናገረው ከዋነኞቹ ሐዋርያት በምንም አይጎድልም (2ቆሮ.12፡11)፤ እንዲያውም “ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋው ከንቱ አልነበረም ከሁላቸው ይልቅ ግን ደከምሁ” በማለት ይናገራል (1ቆሮ.15፡10)፡፡ ያረገውን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በተደጋጋሚ በዓይኑ ያየ (1ቆሮ.9፡1) በመሆኑም እንደሌሎቹ ሐዋርያት ሁሉ የእርሱ የክርስቶስ የምድር ላይ ምስክር እንዲሆን የተጠራ ሐዋርያ ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ጳውሎስን በጠራው ጊዜ ይህንን ሲነግረው “ነገር ግን ተነሣና በእግርህ ቁም፤ ስለዚህ እኔን ባየህበት ነገር ለአንተም በምታይበት ነገር አገልጋይና ምስክር ትሆን ዘንድ ልሾምህ ታይቼልሃለሁና” ብሎታል (የሐ.ሥ.26:16)፡፡ ስለዚህ ሐዋርያው ጳውሎስ ለጌታ “የተመረጠ ዕቃ” እንዲሆን በኋላ የተጠራ ልዩ ሐዋርያ ይሁን እንጂ (የሐ.ሥ.9፡15) ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት እኩል የክርስቶስ ምስክር ነው፡፡
ሐዋርያት የክርስቶስ ምስክር ሆነው ወደ ዓለም ሲላኩ የሚያስተምሩትን ትምህርት የተቀበሉትም ከራሱ ከጌታ ነው፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ ይህንን ሲናገር “ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን” ብሏል (1ዮሐ.1:1)፡፡ በዚህ ክፍል የሐዋርያት ትምህርት “የሕይወት ቃል” ተብሎ የተጠራ ሲሆን ይህም “ከመጀመሪያ የነበረ” እንደሆነና በኋላ ደግሞ ሐዋርያት ከክርስቶስ የሰሙትና በእርሱም ያዩት እንደሆነ ተገልጧል፡፡ በመቀጠልም ይህንን ይበልጥ ሲያብራራ “ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን” በማለት ይናገራል (1ዮሐ.1:2)፡፡ በመሆኑም “ከመጀመሪያ የነበረው” ሲል እነርሱ አሁን የሚያወሩት ወይም የሚመሰክሩት ትምህርት ሰው በሆነው በክርስቶስ ለእነርሱ ከመገለጡ በፊት “በአብ ዘንድ የነበረ” እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡
በአብ ዘንድ የነበረውን ይህንን እውነትም ወልድ ሰው ሆኖ በሥጋ በተገለጠ ጊዜ በምድር ላይ ለእነርሱ አስተማራቸው፤ ቃል ሥጋ ሲሆን “ጸጋና እውነትን ተመልቶ” እንደመጣ ተነግሮናል (ዮሐ.1፡14)፡፡ በመቀጠልም “መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው” ተብሎ ተጽፏል (ዮሐ.1፡18)፡፡
ሐዋርያት በክርስቶስ ከተማሩት የቀረውን ትምህርት ደግሞ በኋላ ላይ መንፈስ ቅዱስ አስተምሯቸዋል፤ እንዲሁም ክርስቶስ ያስተማራቸውንም መንፈስ ቅዱስ አስታውሷቸዋል፡፡ ይህንንም ጌታችን ቀደም ብሎ ሲናገር “ከእናንተ ዘንድ ስኖር ይህን ነግሬአችኋለሁ፤ አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል” ብሏል (ዮሐ.14:25-26)፤ በተጨማሪም “የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፥ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም። ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፡፡” (ዮሐ.16:12-13) በማለት በጊዜው ሊሸከሙት የማይችሉት ወደነበረው ቀሪ እውነት ሁሉ መንፈስ ቅዱስ እንደሚመራቸው አስቀድሞ ነግሯቸው ነበር፡፡ ለእነርሱ የሥጋና የደም አስተሳሰብ ብሎም ለማስታወስ ችሎታቸው የተተወ ቃል የለም፡፡ ስለሆነም በተስፋው ቃል መሠረት መንፈስ ቅዱስ ወደ ምድር ከመጣ በኋላ በመንፈስ ቅዱስ እየተሞሉ የእግዚአብሔርን ቃል በግልጥ ይናገሩ ነበር (የሐ.ሥ.4፡8 እና 31)፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም ራሱን ከሁሉም ሐዋርያት ጋር አብሮ በማቅረብ ከዘመናት በፊት ተሰውሮ የነበረው የእግዚአብሔር ጥበብ ለእነርሱ በእግዚአብሔር መንፈስ እንደተገለጠላቸው ሲናገር “መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ስንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራልና ለእኛ እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል ገለጠው” ብሏል (1ቆሮ.2:10)፡፡ እንዲሁም በሌላ ስፍራ ከዘላለም የነበረውን የክርስቶስን ምስጢር በተመለከተ ሲጽፍ “ለቅዱሳን ሐዋርያትና ለነቢያት በመንፈስ አሁን እንደተገለጠ በሌሎቹ ትውልዶች ዘንድ ለሰው ልጆች አልታወቀም” ብሏል (ኤፌ.3፡4-6)፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ራሱ ደግሞ ከዘላለምና ከትውልዶች ተሰውረው ማለትም “ምስጢር” ሆነው የነበሩትን እውነቶች በመግለጥ የእግዚአብሔርን ቃል ፈጽሞ (አጠናቅቆ) እንዲገልጥ ልዩ ጥሪ የነበረው አገልጋይ ነበር፤ ይህንንም ሲናገር “ስለ እናንተ እንደ ተሰጠኝ እንደ እግዚአብሔር መጋቢነት፥ የእግዚአብሔርን ቃል ፈጽሜ እንድሰብክ እኔ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሆንሁ። ይህም ቃል ከዘላለምና ከትውልዶች ጀምሮ ተሰውሮ የነበረ ምሥጢር ነው፥ አሁን ግን ለቅዱሳኑ ተገልጦአል” በማለት ይናገራል (ቆላ.1:25)፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ እግዚአብሔር በሐዋርያት የተነገረውንና የተሰበከው የእግዚአብሔር ቃል በምልክቶችና በተአምራት እየመሰከረ አጽንቶታል፤ ይህን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር “እነርሱም ወጥተው በየስፍራው ሁሉ ሰበኩ፥ ጌታም ከእነርሱ ጋር ይሠራ ነበር፥ በሚከተለትም ምልክቶች ቃሉን ያጸና ነበር” ይላል (ማር.16:20)፡፡ እንዲሁም በሌላ ስፍራ “ይህ በጌታ በመጀመሪያ የተነገረ ነበርና፥ የሰሙትም ለእኛ አጸኑት፥ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ እንደ ፈቀደ በምልክትና በድንቅ ነገር በልዩ ልዩ ተአምራትም፥ መንፈስ ቅዱስንም በማደል አብሮ መሰከረለት” ይላል (ዕብ.2:3-4)፡፡ ይህም ሐዋርያት ሲያስተምሩት የነበረው ትምህርት የእግዚአብሔር ቃል ለመሆኑ መለኮታዊ ምስክርነት የተሰጠበት እንደሆነ ያሳያል፡፡
ስለዚህ ባጠቃላይ ሐዋርያት ሲያስተምሩት የነበረው ትምህርት ከመጀመሪያው በአብ ዘንድ የነበረ፣ በክርስቶስ (በወልድ) የተነገረ (የተተረከ)፣ በመንፈስ ቅዱስም የተገለጠ እንዲሁም በምልክትና በተአምራት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ትምህርት ነው እንጂ የራሳቸው ትምህርት አይደለም፡፡ እነርሱ ስላስተማሩት “የሐዋርያት ትምህርት” ይባል እንጂ የትምህርቱ መገኛና ባለቤት እነርሱ ሳይሆኑ እግዚአብሔር ራሱ ነው፡፡ ስለዚህም በሐዋርያት ትምህርት መትጋት ማለት በእግዚአብሔር ትምህርት መትጋት ነው፡፡
አስራ ሁለቱ ሐዋርያት በዚያን ጊዜ በኢየሩሳሌም በአንድ ላይ ስለነበሩ በውጪ ብቻ ሳይሆን በውስጥም በቤታቸውም በየዕለቱ ስለኢየሱስ ክርስቶስ በማስተማር ይተጉ ነበር፤ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ሲገልጽ “ዕለት ዕለትም በመቅደስና በቤታቸው ስለ ኢየሱስ፣ እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ ማስተማርንና መስበክን አይተዉም ነበር” (የሐ.ሥ.5:42)፡፡ እንዲያውም በጅማሬው ላይ አብዛኛውን የቤተክርስቲያንን አገልግሎት የሚሰጡት እነርሱው ራሳቸው የነበሩ ቢሆንም በኋላ ላይ “እኛ ግን ለጸሎትና ቃሉን ለማገልገል እንተጋለን።” በማለት ራሳቸውን ለጸሎትና ለቃሉ አገልግሎት እንደለዩም ተነግሮናል (ሐ.ሥ.6:4)፡፡ በዚህ መልክ እነርሱ በየዕለቱ ቃሉን ለማስተማር ሲተጉ ቅዱሳን ሁሉ ደግሞ በሐዋርያት ትምህርት ይተጉ ነበር፡፡
በዚያን ጊዜ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ገና ባለመጻፋቸው ሐዋርያት በሚያስተምሩ ጊዜ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ለአዲስ ኪዳን ዘመን የሚሰጡትን መልእክት በመንፈስ ቅዱስ በመተርጎም ያስተምሩ ነበር (የሐ.ሥ.2፡16-36፤ 17፡2-3)፡፡ ከዚህ በላይ ግን እነርሱ ራሳቸው የሚያስተምሯቸው የአዲስ ኪዳን የእምነትና የሥነምግባር ትምህርቶች እስትንፋሰ እግዚአብሔር ያለባቸው በመሆናቸው መለኮታዊ ሥልጣን ነበራቸው፡፡ ከላይ እንደተመለከትነው ባለፉት ትውልዶች ተሰውሮ የኖረው “የክርስቶስ ምስጢር” በእነርሱ ትምህርት ይገለጥ ነበር፡፡
በዚያን ጊዜ የነበሩ አማኞች ሐዋርያት ሲያስተምሩ ዘወትር በአካል እየተገኙ በመማርና በመታነጽ ይተጉ ነበር፡፡ ሐዋርያት በአካል በማይገኙ ጊዜ ደግሞ የሚጽፏቸውን መጻሕፍት በማንበብና በማጥናት በትምህርታቸው ይተጉ ነበር፡፡ በይሁዳ መልእክት ውስጥ በቁጥር 17 ላይ “እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ቀድሞ የተነገረውን ቃል አስቡ” ተብሎ የተጻፈውን ቃል ስንመለከት የሐዋርያት ትምህርት (ቃል) በየስፍራው በመለኮታዊ ማስረጃነት እየቀረበ እንደነበርና ከስህተት ለመጠበቅም አማኞች የእነርሱን ትምህርት ማሰብ እንዳለባቸው ያስረዳል፡፡ እንዲሁም ሐዋርያው ጴጥሮስ “እንዲህም የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ ደግሞ እንደ ተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ፥ በመልእክቱም ሁሉ ስለዚህ ነገር ተናገረ” በማለት ጳውሎስ ለጻፈው መልእክት እውቅናን ሲሰጥ እናያለን (2ጴጥ.3፡15)፡፡ በቆላስይስ 4፡16 “ይህችም መልእክት በእናንተ ዘንድ ከተነበበች በኋላ፥ በሎዶቅያ ሰዎች ማኅበር ደግሞ እንድትነበብ አድርጉ። ከሎዶቅያም የምትገኘውን መልእክት እናንተ ደግሞ አንብቡ” በማለት ጳውሎስ የጻፈው ቃልም ሆነ ሐዋርያት ሲጽፏቸው የነበሩት መጻሕፍት በየጉባኤው በመዘዋወር ይነበቡ እንደነበር ያስረዳል፡፡ ስለዚህ የቀደሙት አማኞች ሐዋርያት በአካል በማይገኙባቸው ስፍራዎች መጻሕፍቶቻቸውን በማንበብና በማጥናት በሐዋርያት ትምህርት ይተጉ እንደነበር እንገነዘባለን፡፡ ይህም ከዘመነ ሐዋርያት በኋላ ያለ አማኞች ሁሉ በሐዋርያት ትምህርት የሚተጉበት መንገድ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ እኛም ሐዋርያትን በአካል ባናገኛቸውም ትምህርታቸውን በመጻሕፍቶቻቸው በኩል እናገኛለን፤ 27ቱ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በሙሉ የሐዋርያት ትምህርት የሚገኝባቸው መጻሕፍት ናቸው፡፡ እነርሱን ማንበብ፣ መማርና ማጥናት ከዚያም በሚሰጡት ትምህርት፣ ምክርና ተግሣጽ መታነጽ በሐዋርያት ትምህርት መትጋት ነው፡፡ ይህንን በግልም ሆነ በማኅበር ልናደርገው የምንችል ሲሆን በተለይ ደግሞ በጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርትና ጥናት መልክ ይበልጥ ሊተገበር ይገባዋል፡፡ ከዚህ አንጻር የራሳችንን ሕይወት እየመረመርን “በሐዋርያት ትምህርት በተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ምን ያህል እየተጋን ነው?” ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል፡፡ ለብዙ አማኞች ክርስቲያናዊ ሕይወት መዳከም ዋነኛው መንስኤ ቃሉ በሚጠናበትና በሚነገርበት ጉባኤ እየተገኙ ለመማርም ሆነ በየግል ቃሉን ለማንበብና ለማጥናት ያለን ትጋት አነስተኛ መሆን ነው፡፡ ከዚያ ይልቅ በጨዋታ፣ ጠቃሚ ያልሆኑ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመከታተል፣ ለአማኝ ባልተገቡ ስፍራዎች በመገኘት፣ … ወዘተ፣ በከንቱ የምናባክናቸው ጊዜያት መኖራቸው በእጅጉ አሳዛኝ ነው፡፡ ስለሆነም ከእነዚህ ከንቱ ነገሮች ወጥተን ድል ነሺውን ሕይወት መኖር እንድንችል ዛሬ ተብሎ ሲጠራ ነቅተን በሐዋርያት ትምህርት ልንተጋ ይገባናል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በክርስትናው ዓለም ውስጥ ሰዎች የሐዋርያት ትምህርትን ትተው ይልቅ የሐሰተኞች ሐዋርያትና ነቢያትን ቃል ለመስማት እንዲሁም ሐሰተኛ ምልክቶችን ለመከተል ሲተጉ መታየታቸው የዘመናችን አስከፊው ገጽታ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ደግሞ በክርስትናው ዓለም የሚታየው አጠቃላይ ውድቀት ያስደነገጣቸውና ራሳቸውን ከአፍኣዊነት የለዩ ሰዎች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ግራ ሲጋቡ ይታያል፤ እነዚህ ቅሬታዎች ግራ ከመጋባት ይልቅ ማድረግ ያለባቸው ነገር በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ቀድሞ የተነገረውን አውቀውና ተረድተው በእነርሱ ወደ ተገለጠው እውነት መምጣት ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የሚገኘውን የሐዋርያት ትምህርት ለመከተል መትጋት ይገባቸዋል፡፡