ትምህርት  

3. እንጀራውን በመቊረስ መትጋት

መላዋን ቤተክርስቲያን በምትገልጠው በአንዲት የአካባቢ (አጥቢያ) ቤተክርስቲያን ውስጥ እንዲፈጸሙ ጌታ የሰጠን የሚታዩና ቁሳዊ የሆኑ ሁለት ሥርዓቶች የውሓጥምቀት እና እንጀራ መቁረስ ሲሆኑ በዚህ ክፍል ስለ እንጀራ መቁረስ እንመለከታለን፡፡ እንጀራ መቁረስ አማኞች በውኃ እየተጠመቁ፣ ከእነርሱ ቀደመው ባመኑ አማኞች ላይ፣ ለጌታ ተጨምረው፣ ወደ አንዲት ጉባኤ ሲገቡ በኅብረት የሚካፈሉት የመታሰቢያ እራት ነው፤ የዚህን እንጀራውን የመቁረስ አመሠራረት እና ዓላማዎችን ቀጥሎ በዝርዝር እንመለከታለን፡፡

ስያሜው

የቀደሙት አማኞች ከሚተጉባቸው አራት ነገሮች አንዱ የሆነው ይህ ሥርዓት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “እንጀራ መቁረስ” ተብሎ ተጠርቷል፤ በሐ.ሥ.2፡42 ውስጥ “እንጀራውንም በመቁረስ … ይተጉ ነበር” ሲል፣ በሐ.ሥ. 20፡7 “… እንጀራ ለመቁረስ ተሰብስበን ሳለን…” ይላል፡፡ ይህም አገላለጽ እንጀራው (ዳቦው) በቁስ አካልነቱ በቁርስ፣ በምሳና በእራት ጊዜ ከሚበላው ከመደበኛው እንጀራ (ዳቦ) ጋር ያው አንድ ቢሆንም፣ በዚህ ስፍራ የሚሰጠው ትርጉም ግን የተለየ መሆኑን የሚያሳይ ቃል ነው፡፡ ስለመደበኛ የእንጀራ መብል ሲገለጽ፣ “ይተጉ ነበር” ሊባል አይችልምና፤ እንዲሁም መደበኛው የእንጀራ መብል ከሳምንቱ ፊተኛውን ቀን ጠብቀው ሰዎች የሚሰበሰቡለት መደበኛ ሥርዓት አይደለምና፡፡ በመሆኑም በእነዚህ ክፍሎች የተጠቀሰው “እንጀራ መቁረስ” በአማኞች ጉባኤ ማለት በአጥቢያ ቤተክርስቲያን በትጋት የሚፈጸም ከጌታ የተሰጠ ሥርዓት ነው፡፡ እንጀራ መቁረስ የሚለው ይህ አጠራርም እንጀራው (ዳቦው) አንድ ወንድም አመስግኖ ቆርሶ የሚሰጠውና በጉባኤ በተሰበሰቡ በሁሉም አማኞች እየተቆረሰ በአንድነት የሚበላ በመሆኑ ከአፈጻጸሙ የተነሳ የተሰጠው ስያሜ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ይኸው ሥርዓት በ1ቆሮ.11፡20 ላይ “የጌታ እራት” ተብሎ ተጠርቷል፤ ይህም አገላለጽ እራቱ የጌታ መሆኑን በአጽንዖት የሚናገር ነው፡፡ ተሰብሳቢዎቹ አማኞች ለዚህ የከበረ እራት የተጠሩ እድምተኞች ናቸው፤ እነርሱ ምንም እንኳ ቦታውን በማስተካከል ገበታውን በመዘርጋት፣ ዳቦውንና ወይኑን በማዘጋጀት ቢያገለግሉም የእራቱ ባለቤት እነርሱ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ በመሆኑም የጌታ እራት የሚለው ስያሜ የእራቱ ባለቤት ጌታ ኢየሱስ ብቻ መሆኑንና እራቱን ይካፈሉ ዘንድ የተጠሩትና የተሰበሰቡት አማኞች ሁሉ በሕይወታቸው ለኢየሱስ የጌትነት ሥልጣን የሚገዙና እንደ ፈቃዱ የሚመላለሱ ሊሆኑ እንደሚገባቸው የሚያመለክት ነው፡፡

አመሠራረቱ

እንጀራውን የመቁረስ ወይም የጌታ እራት ሥርዓትን የመሠረተው የእራቱ ባለቤት የሆነው ራሱ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ይህንንም ያደረገው አልፎ በተሰጠበት ምሽት ከደቀመዛሙርቱ ጋር የፋሲካን እራት ሊበላ በተቀመጠበት ጊዜ ነበር፡፡ ይህ ጉዳይ በሦስቱ ወንጌላት የተለያዩ ክፍሎች ማለትም በማቴ.26፡26-30፣ በማር.14፡22-26 እና በሉቃ.22፡14-20 የተመዘገበ ሲሆን በሉቃስ ወንጌል የተመዘገበውን መሠረት አድርገን ቀጥሎ እንመለከተዋለን፡፡

“ሰዓቱም በደረሰ ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ጋር በማዕድ ተቀመጠ። እርሱም፦ ከመከራዬ በፊት ከእናንተ ጋር ይህን ፋሲካ ልበላ እጅግ እመኝ ነበር፤ እላችኋለሁና፥ በእግዚአብሔር መንግሥት እስኪፈጸም ድረስ፥ ወደፊት ከዚህ አልበላም አላቸው። ጽዋንም ተቀበለ አመስግኖም፦ ይህን እንካችሁ በመካከላችሁም ተካፈሉት፤ እላችኋለሁና፥ የእግዚአብሔር መንግሥት እስክትመጣ ድረስ ከአሁን ጀምሮ ከወይኑ ፍሬ አልጠጣም አለ። እንጀራንም አንሥቶ አመሰገነ ቆርሶም ሰጣቸውና፦ ስለ እናንተ የሚሰጠው ሥጋዬ ይህ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ። እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ እንዲህ አለ፦ ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው።”

ጌታ ኢየሱስ የእርሱ የሆነውን እራት ለመመሥረት የመረጠው ወሳኝ ሰአት ለመጨረሻ ጊዜ በፋሲካ ማዕድ ከደቀመዛሙርቱ ጋር የተቀመጠበትን ጊዜ ነው፡፡ ይህንንም ፋሲካ ሊበላ እጅግ ይመኝ እንደነበር ገልጿል፡፡ የዚህም ምክንያቱ እርሱ በመሢሕነቱ በምድር ላይ ሳለ የእርሱ ከነበሩት እስራኤላውያን ደቀመዛሙርቱ ጋር ለመጨረሻ ጊዜ አብሮ የሚበላው በመሆኑና እንደገና መንግሥቱን ሊመሠርት ወደ ምድር እስኪመጣ ድረስ እርሱ በምድር ላይ በማይኖርበት በቀጣዩ ዘመን የእርሱ የሆኑት በምድር ላይ ሊበሉት የሚገባውን የራሱን እራት የሚመሠርትበት ጊዜ ስለነበር ነው፡፡

ፋሲካ እስራኤል ከግብፅ ባርነት ነጻ በወጡበት ምሽት እግዚአብሔር ያደረገላቸውን ሁሉ የሚያስታውስ በዓል ነው፤ ፋሲካ ማለት ማለፍ ማለት ሲሆን በዕለቱ ለየቤቱ የሚያቀርቡትን ነውር የሌለበትን የአንድ ዓመት ጠቦት ደም የቤታቸውን መቃንና ጉበን እንዲቀቡ ታዘው ነበር፤ እግዚአብሔርም “ደሙን ባየሁ ጊዜ ከእናንተ አልፋለሁ” አለ (ዘጸ.12፡13፣ 23)፤ መሥዋዕቱም “የማለፉ መሥዋዕት” ተብሎ ይጠራ ነበር (ዘጸ.12፡27)፡፡ ያም ቀንም የእግዚአብሔር በዓል አድርገው ለመታሰቢያ እንዲያከብሩት ታዘዙ (ዘጸ.12፡14)፡፡ በዚህ መሠረትም እስራኤል በምድረ በዳም ሆነ በተስፋይቱ ምድር ውስጥ የፋሲካውን ማዕድ እየበሉና ጽዋውንም እየጠጡ እግዚአብሔር እነርሱን ከቁጣው ፍርድ እና ከግብፃውያን ያዳነበትን ይህን የመታሰቢያ በዓል ያደርጉ ነበር፡፡ ይሁንና መሢሐቸው ወደ እነርሱ መጥቶ በመካከላቸው በነበረ ጊዜ አልተቀበሉትም፤ የመጨረሻውን የፋሲካ ማዕድ በበላበት በዚያ ምሽት ሊይዙት፣ ከዚያ ሊገድሉት እየተዘጋጁ ነበር፡፡ እርሱም ከእነርሱ ጋር የነበረውን በቀደመው በብሉይ ኪዳን የፋሲካ ማዕድ የሚገለጠውን ኅብረት ለጊዜው ወደ ጎን እንደተወው ለማሳየት “በእግዚአብሔር መንግሥት እስኪፈጸም ድረስ፥ ወደፊት ከዚህ አልበላም (ቁ.16) አላቸው፤ እንዲሁም “የእግዚአብሔር መንግሥት እስክትመጣ ድረስ ከአሁን ጀምሮ ከወይኑ ፍሬ አልጠጣም” (ቁ.18) በማለት ተናገረ፡፡ ይሁን እንጂ በምትኩ ራሱ ፋሲካ ሆኖ የሚታይበትን ሌላ አዲስ ኪዳን በደሙ ሊመሠርት ነበረው፡፡ ስለሆነም ይህንኑ አዲስ ኪዳን የሚያሳይ አዲስ እራትን መሠረተ፡፡ ይህም እራት “ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዷልና” ተብሎ እንደተጻፈ (1ቆሮ.5፡7) ራሱን ለፋሲካው እንደሚታረደው በግ አድርጎ ማቅረቡን የሚያሳይ ነው፡፡

ምንም እንኳ የፋሲካው እራት በእስራኤል ዘንድ የሚበላው ከቤተሰብ ጋር ቢሆንም ጌታ ኢየሱስ ግን በደርብ ላይ በተነጠፈው ታላቅ አዳራሽ ውስጥ በማዕድ የተቀመጠው፣ ከአስራ ሁለቱ ደቀመዛሙርቱ ጋር ነበር፡፡ በመሆኑም የእርሱን እራት ያቀረበው በሥጋ በሆነ ቤተሰብ መካከል ሳይሆን በኋላ ላይ ወንድሞቼ ብሎ በሚጠራቸው በእግዚአብሔር ቤተሰብ መካከል ነበር፡፡ አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳ በዚያ ማዕድ አብሮ በመኖሩ ጌታ መንፈሱ የታወከበት ቢሆንም፣ በመጨረሻ ላይ ግን ይሁዳ ቁራሹን ተቀብሎ ከዚያች የደቀመዛሙርቱ ማኅበር እስከ ወዲያኛው ሲለይ እናየዋለን፤ በመሆኑም የጌታ እራት በዋናነት የተሰጠው በየስፍራው ያሉ እውነተኛ አማኞች በስሙ ለሚሰበሰቡበት ማኅበር ቢሆንም እንደ ይሁዳ በመካከላቸው ሳይታወቁ ተመሳስለው የሚገኙ የአፍ አማኞች ካሉ ግን በጊዜው ጌታ እንደሚገልጣቸውና እስከመጨረሻው እንደማይዘልቁ ከዚህ እንማራለን፡፡ ነገር ግን እርሱ ወደፊት መንግሥቱን ለመመሥረት እስኪመጣና በፋሲካው ማዕድና ወይን ምሳሌነት የሚገለጠውን የወደፊት ደስ የሚያሰኝ ኅብረት ከምድራዊው ሕዝቡ ጋር እስከሚያደርግ ድረስ በዚህ ዘመን የእርሱ የሆኑት እውነተኛ አማኞች በእርሱ ዙሪያ ተሰብስበው ይካፈሉት ዘንድ የራሱን እራት መሥርቷል፡፡

ጌታ እራቱን የመሠረተበት መንገድ በቅድሚያ አፈጻጸሙን በማሳየት ነበር፤ ከፋሲካው እራት በመቀጠል የጌታ እራት የሆነው እንጀራ (ዳቦ) እና ወይን የነበረበት ጽዋ በገበታው ላይ ተደረገ፡፡ ከዚያም ፍጹም አዲስ እራት መሆኑን በሚገልጽ መልኩ ጌታ እንጀራውን አንስቶ አመሰገነ፣ ቆርሶም “እንካችሁ ብሉ” ብሎ ለደቀመዛሙርቱ ሰጣቸው፡፡ በተመሳሳይ መልኩም ጽዋውን አንሥቶ አመስገነ፤ “ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ” ብሎ ሰጣቸው (ማቴ.26፡26፣27)፡፡ ዛሬም የጌታን እራት ወይም እንጀራውን ለመቁረስ በክርስቶስ ስም የሚሰበሰቡ አማኞች እርሱ ቃል በገባው መሠረት በመካከላቸው የሚገኝ በመሆኑ እርሱ እንዳሳያቸው አመስግነው እና ቆርሰው ሲካፈሉ ከእርሱ እጅ እንደተቀበሉ በማመን ሊሆን ይገባል፡፡

በመቀጠልም ጌታ እራቱን የመሠረተበት መንገድ “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” ብሎ በማዘዝ ነው (ሉቃ.22፡19፤ 1ቆሮ.11፡24፤25ን ተመልከት)፤ ይህም የእርሱ የሆኑት ሁሉ የጌታን እራት በቀጣይነት እንዲፈጽሙት ለማድረግ የተሰጠ ትእዛዝ ነው፡፡ “አደርጉት” የሚለው ይህ ቃል ትእዛዝን ያመለክታልና፤ የሚያደርጉትም ለሌላ ለምንም ነገር ሳይሆን ለእርሱ ለራሱ መታሰቢያ እንዲሆን መሆኑንም አዟል፡፡ መታሰቢያነቱም ይበልጡን ሞቱን የሚመለከት መሆኑን ከምሳሌነቱ እንገነዘባለን፡፡ ጌታ ኢየሱስ እንጀራውንና ጽዋውን በገበታው ላይ ያቀረባቸው የሥጋውና የደሙ ምሳሌ አድርጎ ነበር፤ ሥጋውና ደሙ ተለያይተው ለየብቻቸው በዳቦውና በወይኑ ምሳሌነት እንዲቀርቡ መደረጋቸው ጌታ በሚቀጥለው ቀን እንደ ታረደ በግ ሆኖ ስለኃጢአተኞች የሚሞተው ማንነቱ መገለጫ እንዲሆን ነበር፡፡ ጌታ የሰጣቸው ይህ ዳቦና ወይን ቀደም ሲል በፋሲካው ከተበላውና ከተጠጣው ዳቦና ወይን የሚለየውም በዚህ ምሳሌነት ከክርስቶስ ሥጋና ደም ጋር የተገናኘ በመሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም የዚህ እራት ዋነኛ ጠባይ የሥጋ ምግብ መሆኑ ሳይሆን በመስቀል ላይ የሞተውን ክርስቶስን በልብ ላይ ማሰብ ወይም ማሰላሰል ነው፡፡

ተግባራዊነቱ

በመቀጠል የምናነሳው እንጀራውን መቁረስ (የጌታ እራት)፣ ጌታ ባሳየውና በደነገገው መሠረት እርሱ ካረገና መንፈስ ቅዱስ ከወረደ በኋላ በየስፍራው ባሉ ጉባኤዎች እንዴት ተግባራዊ ተደርጎ እንደነበር ነው፡፡ በዚህም መሠረት በአይሁድም በአሕዛብም መካከል በተሰበሰቡ ጉባኤዎች ዘንድ የጌታ እራት ይደረግ እንደነበር የሚገልጹ ሦስት ማሳያዎችን ከእግዚአብሔር ቃል እንመለከታለን፡፡

1. በኢየሩሳሌም ባለች ቤተክርስቲያን

የበዓለ ሃምሳ ዕለት መንፈስ ቅዱስ ከወረደ በኋላ በኢየሩሳሌም የተሰበሰበችው የመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን እንጀራውን በመቁረስ የምትተጋ ነበረች፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ሲገልጽ “ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ፥ በዚያም ቀን ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስ ተጨመሩ፤ በሐዋርያትም ትምህርትና በኅብረት እንጀራውንም በመቍረስ በየጸሎቱም ይተጉ ነበር” ይላል(የሐ.ሥ.2፡41-42)፡፡ ይህ ቃል የተመሰከረላቸው የበዓለ ሃምሳው የወንጌል ስብከት በተሰበከበት በዚያው በኢየሩሳሌም ያሉ አማኞች ነበሩ፡፡ እንጀራውን መቁረስ በዚህ ስፍራ ላይ የተወሰደው እንደ “ሐዋርያት ትምህርት”፣ እንደ “ኅብረት”፣ እንደ “ጸሎት” በማኅበር የሚተጋበት ነገር ተደርጎ ነው፡፡ ስለሆነም እንጀራውን መቁረስ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ከምትሰበሰብባቸው ጉዳዮች አንዱ ሆኖ በመቅረቡ መደበኛ መብል እንዳልሆነ እንገነዘባለን፡፡ ይልቁን ጌታ ያሳየውና በቀጣይነት እንዲደረግ ያዘዘው የእርሱ እራት መሆኑን እንረዳለን፡፡ አጠራሩም “እንጀራ መቁረስ” ሳይሆን “እንጀራውን መቁረስ” የሚል መሆኑ አንድ ተለይቶ የታወቀ ሥርዓት መሆኑን ያሳያል፡፡ እነዚህ ቅዱሳን ይተጉ የነበረው በዚህ የጌታን ሥጋና ደም በምሳሌነት በሚያሳየውና ጌታ በመሠረተው የእንጀራ መቁረስ (የጌታ እራት) ጉባኤ ነበር፤ ከዚህ አኳያም በዚህ ዘመን የሌሎቹን የቤተክርስቲያን ጉባኤዎች ያህል እንኳ ለጌታ እራት ጉባኤ ተገቢውን ትኩረት ባለመስጠት የሚታየውን አለመትጋት አማኞች ሊነቁበትና ሊፈርዱበት ይገባል፤ በዚያ ፈንታም የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች እንጀራውን በመቁረስ ይተጉ እንደነበረው እንደዚያው በትኩስ ፍቅር ሆነው እንጀራውን በኅብረት በመቁረስ ሊተጉ ይገባል፡፡

2. በቆሮንቶስ ባለች ቤተክርስቲያን

ይህች የቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን በአብዛኛው ከአሕዛብ የተጠሩ አማኞች የሚገኙባት ማኅበር እንደሆነች ይታወቃል፤ በቀደመው ማንነታቸው ሲገልጹ “አሕዛብ ሳላችሁ …” ተብለዋልና (1ቆሮ.12፡2)፡፡ ቆሮንቶስ በግሪክ አገር የምትገኘው የአካይያ ግዛት ዋና ከተማ የነበረች ስትሆን በዚያ የነበረችው ቤተክርስቲያንም ሐዋርያው ጳውሎስ በሁለተኛው የወንጌል ጉዞው ለ1 ዓመት ከ6 ወር ጊዜ ያህል ቆይቶ በሠራው የወንጌል ሥራ የተመሠረተች ነበረች (የሐ.ሥ.18፡1-11)፡፡ እነዚህም አማኞች ጳውሎስ ባስተማራቸው መሠረት በማኅበር እንጀራውን ይቆርሱ ወይም የጌታን እራት ይካፈሉ ነበር፡፡ ይህም የጌታ እራት በኢየሩሳሌምና ከአይሁድ ባመኑት ዘንድ ብቻ ሳይሆን ከአሕዛብ ባመኑት ዘንድም ተግባራዊ ተደርጎ እንደነበር ተጨባጭ ማሳያ ነው፡፡

ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ ባለች ቤተክርስቲያን ቅዱሳን በማኅበር እየተሰበሰቡ የጌታን እራት እንዲካፈሉ ይህን ሥርዓት ለእነርሱ አሳልፎ የሰጣቸው በቀጥታ ከጌታ ተቀብሎ ነበር፡፡ ይህንንም ራሱ ሲናገር “ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠሁትን እኔ ከጌታ ተቀብያለሁና” በማለት ገልጾታል (1ቆሮ.11፡23)፡፡ ጳውሎስ ጌታ አልፎ በተሰጠባት ምሽት እራቱን ለደቀመዛሙርቱ በሰጠበት ዕለት ያልነበረ ብቻ ሳይሆን በጌታ ያመነውም ጌታ ካረገ በኋላ ቆየት ብሎ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ታዲያ ጌታ በደማስቆ በታየው ጊዜ ገና ከጅምሩ “እኔን ባየህበት ነገር ለአንተም በምታይበት ነገር አገልጋይና ምስክር ትሆንልኝ ዘንድ ታይቼልሃለሁ” በማለት በተናገረው መሠረት (የሐ.ሥ.26፡16) የመታሰቢያውን እራት ሥርዓት በእርሱ አገልግሎት ወደ ጌታ ለሚመጡት ሁሉ አሳልፎ እንዲሰጥ ሊነግረው በአንድ ወቅት እንደተገለጠለት ከዚህ እንገነዘባለን፡፡ ምክንያቱም ጳውሎስ ምንም እንኳ በኋላ የተጠራ ቢሆንም ሐዋርያ በመሆኑ የጌታን እራት ሥርዓት በየጉባኤው አሳልፎ ለመስጠት እንደሌሎቹ ሁሉ የጌታን የራሱን እውቅናን በቀጥታ ማግኘት ስለነበረበት ነው፡፡ በዚህም ሐዋርያነቱን እና የሚሰብከውን ወንጌል እንዲሁም የሚገልጠውን ምስጢር የተቀበለው ከሰው ሳይሆን ከጌታ እንደሆነ ሁሉ የጌታ እራት ድንጋጌንም በቀጥታ ከጌታ መቀበሉን እንረዳለን፤ ምክንያቱም እርሱ ስለጉዳዩ ሲናገር በግልጽ ቃል “እኔ ከጌታ ተቀብያለሁና” በማለት አስረግጦ ተናግሯልና ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ካረገ በኋላ እንኳ ይህን የመታሰቢያ እራት ለሌሎች አሳልፎ ይሰጥ ዘንድ ለጳውሎስ በድጋሚ ማሳሰቡ ለነገሩ የሰጠውን ትኩረትና እርሱ በዚያ እራት አማካኝነት የእርሱ በሆኑት ዘንድ ሲታሰብ ምን ያህል ደስ እንደሚሰኝ የሚያሳይ ነው፡፡ ሆኖም ይህ እራት በምድር ላይ ሳለ የመሠረተው ያው እራት እንጂ የተለየ እንዳልሆነ ለማረጋገጥ ጌታ ኢየሱስ አልፎ በተሰጠባት ሌሊት እንዴት አድርጎ እንደደነገገው በመዘርዘር ቀጥሎ ይጽፋል (1ቆሮ.11፡23-26 ተመልከት)፡፡ በመሆኑም በየትኛውም ስፍራ የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ሆነው የተሰበሰቡ አማኞች የሚካፈሉት እራት ያው አንዱ የጌታ እራት ነው፡፡

3. በጢሮአዳ ባለች ቤተክርስቲያን

ጢሮአዳ በታናሽ እስያ በስተሰሜን ምዕራብ የምትገኝ ከተማ ስትሆን ሐዋርያው ጳውሎስ በሁለተኛው የወንጌል ጉዞ ወቅት ወደ ፊልጵስዩስ ለመሻገር ያስቻለውን ራእይ ያየባት ቦታ ናት (የሐ.ሥ.16፡9)፡፡ በዚያች ከተማ የነበረች ቤተክርስቲያን እንዴት እንደተጀመረች በዝርዝር የተጻፈ ነገር ባይኖረንም ይበልጡን ሐዋርያው ጳውሎስ በአካባቢው በሠራው የወንጌል ሥራ እና በዚያም ሲያልፍ በሚኖረው ቆይታ እንደሚሆን እናስባለን፡፡ ታዲያ ሐዋርያው ጳውሎስ በሦስተኛው የወንጌል ጉዞ ወቅት ከኤፌሶን በስደት ከወጣ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም በጉዞ ላይ ሳለ እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት ወንድሞች በጢሮአዳ ከነበሩ አማኞች ጋር እንጀራውን ለመቁረስ ተሰብስበው እንደነበር የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ይነግረናል፤ “እኛ ግን ከቂጣ በዓል ቀን በኋላ ከፊልጵስዩስ በመርከብ ተነሥተን በአምስት ቀን ወደ ጢሮአዳ ወደ እነርሱ ደረስንና በዚያ ሰባት ቀን ተቀመጥን። ከሳምንቱም በመጀመሪያ ቀን እንጀራ ለመቁረስ ተሰብስበን ሳለን፥ ጳውሎስ በነገው ሊሄድ ስላሰበ ከእነርሱ ጋር ይነጋገር ነበር፥ እስከ መንፈቀ ሌሊትም ነገሩን አስረዘመ” ይላል (የሐ.ሥ.20፡7)፡፡ ስለሆነም በአሕዛብ አገር ባለች በዚች የጢሮአዳ ቤተክርስቲያንም ያው አንዱ የጌታ እራት ተግባራዊ ተደርጎ ነበር፡፡ እንዲያውም እንጀራውን ለመቁረስ ተብሎ መሰብሰብ እንደነበረ የምንማረውም በዚያ ከነበሩ አማኞች ነው፤ ጸሐፊው ይህን ሲናገር “እንጀራውን ለመቁረስ ተሰብስበን ሳለን” በማለት ይገልጻል፡፡ እንጀራውን የመቁረስ ጉባኤ ለዚያ ብለው አማኞች የሚሰበሰቡበት ራሱን የቻለ ጉባኤ እንጂ ከሌሎች ስብሰባዎች ጋር ተጣምሮ እግረ መንገድ የሚደረግ አለመሆኑን ከዚህ እንረዳለን፡፡

በተጨማሪም በጢሮአዳ የነበሩ አማኞች እንጀራውን መቁረስ (የጌታን እራት) ተግባራዊ ያደርጉ የነበረው ከሳምንቱ በፊተኛው ቀን እንደነበረ ተነግሮናል፡፡ ይህም ከሳምንቱ ፊተኛው ቀን ጌታ ከሙታን የተነሣበት (ዮሐ.20፡1)፣ መንፈስ ቅዱስ የወረደበት (የሐ.ሥ.2፡1፤ ዘሌዋ.23፡16)፣ “የጌታ ቀን” ነበር (ራእ.1፡10)፡፡ በመሆኑም እንጀራ መቁረስ በዚህ ቀን ይሁን ተብሎ እንደ ሕግ የተሰጠን ቀን ባይኖርም እኛም የመጀመሪያዎቹን አማኞች በመከተል ከሳምንቱ በፊተኛው ቀን እናደርጋለን፡፡ በዚህችም ቀን በመንፈስ ሆነን በኢየሱስ ስም ተሰብስበን እንጀራውን እየቆረስን ጌታን እናስበዋለን፡፡

ዓላማዎቹ

ከመጀመሪያው አንስቶ እንጀራውን በመቁረስ የጌታን የመታሰቢያ እራት ማድረግ ከአይሁድም ሆነ ከአሕዛብ በተጠሩ ክርስቲያኖች ዘንድ በትጋት ሲፈጸም የኖረ ሥርዓት ቢሆንም ከጊዜ በኋላ ግን ዓላማውን እየሳተ እንደሄደ ከቤተክርስቲያን ታሪክም ሆነ አሁን በዙሪያችን ካለው አፈጻጸም የምንገነዘበው ነገር ነው፡፡ በክርስቶስ የተሰጡትን ትምህርቶቸችና ሥርዓቶች ከዓላማቸው ውጪ በመረዳትና በመተግበር እግዚአብሔርን ማክበርና ሰውን መጥቀም አይቻልም፡፡ ከዚህ አኳያ እንጀራውን የመቁረስ ትክክለኛ ዓላማዎችን ከማቅረባችን በፊት በሰው ዘንድ የሚታሰቡ ነገር ግን ዓላማዎቹ ያልሆኑትን ነገሮች በቅድሚያ እናሳያለን፡፡

1. እንጀራውን የምንቆርሰው የዘላለም ሕይወት ለማግኘት አይደለም

ጌታ ኢየሱስ አልፎ በተሰጠባት በዚያች ሌሊት እንጀራውን አንስቶ፣ ባርኮና ቆርሶ ለደቀመዛሙርቱ በሰጣቸው ጊዜ፣ “ስለ እናንተ የሚሰጠው ሥጋዬ ይህ ነው” (ሉቃ.22፡19) ማለቱ፣ እንዲሁም ጽዋውን አንስቶ አመስግኖ በሰጣቸው ጊዜ፣ “ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው” (ማቴ.26፡27) ማለቱ ይታወቃል፡፡ ይህንንም ፊደል በፊደል በመረዳት ጌታ ኢየሱስ በዮሐ.6፡53 ላይ “እውነት እውነት እላችኋለሁ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም፤ ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው” ብሎ ካስተማረው ጋር በማገናኘት፣ እንጀራውን መቁረስ ጽዋውን መጠጣት የሚያስፈልገው “የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ነው” ወደሚል መረዳት መድረስ ትክክል አይደለም፡፡ “የዘላለም ሕይወት ያላገኘ ሰው እንጀራውን መቁረስ (የጌታን እራት መካፈል) ይችላልን? እንዲሁም እንደየሥርዓቱ ወይም እንደየልምዱ፣ በየዓመቱ ወይም በየወሩ ወይም በየሳምንቱ እንጀራውን የሚቆርስ ሰው፣ የዘላለም ሕይወት የሚያገኘው በተደጋጋሚ ነውን? የዘላለም ሕይወት፣ ቃሉ እንደሚያሳየው “የዘላለም” አይደለምን?” የሚሉ ጥያቄዎችን እያነሱ እውነቱን ለማወቅ ነገሩን በአግባቡ መመርመር ተገቢ ነው፡፡ የጌታን እራት መካፈል ያለብን የዘላለም ሕይወት አግኝተን እንጂ ገና ለማግኘት አይደለም፤ ያም ሕይወት የዘላለም ሕይወት ነውና አንድ ጊዜ ለዘላለም የምናገኘው የማይጠፋ ሕይወት ነው (ዮሐ.3፡16፤ 10፡28 ተመልከት)፡፡ ይህን የዘላለም ሕይወት የምናገኘው ደግሞ የክርስቶስን ሥጋውንና ደሙን በመብላትና በመጠጣት ነው እንጂ ለጌታ እራት የሚቀርበውን እንጀራ (ዳቦ) እና ወይን በመብላትና በመጠጣት አይደለም፡፡

ጌታ ኢየሱስ አልፎ በተሰጠባት ሌሊት እንጀራውን “ሥጋዬ”፣ ወይኑንም “ደሜ” ብሎ የተናገረው ቃል፣ ፊደል በፊደል የሰውነቱ ሥጋና ደም መሆኑን የሚያመለክት አይደለም፤ ወይም ደግሞ እንጀራው ተለውጦ ሥጋውን፣ ወይኑም ተለውጦ ደሙን ስለሆነ፣ አሊያም ከእንጀራው ጋር ሥጋው፣ ከወይኑ ጋር ደሙ አብሮ ስለተሰጠም አይደለም፡፡ ነገር ግን በእጁ ያነሳው እንጀራ (ዳቦ) ሆኖ ሳለ ሥጋዬ ነው ሲል፣ ደግሞም በእጁ ያነሳው ወይን ሆኖ ሳለ ደሜ ነው ሲል ሥጋዬን እና ደሜን የሚወክል ምሳሌ ነው ማለቱ ነው እንጂ በቀጥታ ሥጋዬና ደሜ ሆኗል ለማለት አይደለም፡፡ “ነው” በሚለው ቃል መነገሩም ቢሆን የነገሩ ምሳሌነት በሚሰሙት ደቀመዛሙርት ዘንድ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ስላልነበረ ነው፤ በምሳሌነቱ መግባባት ያለ በመሆኑ በቀጥታ “ሥጋዬ ነው፣ ደሜ ነው” ማለቱ ለደቀመዛሙርቱ ተለውጦ ሥጋውና ደሙ ይሆናል የሚል ትርጉም እንደማይሰጣቸው ስለሚያውቅ ነው፡፡ ስለሆነም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንጀራውንና ወይኑን “እንደ ሥጋዬ፣ እንደ ደሜ ነው”፣ ወይም “ሥጋዬን የሚመስል ወይም ደሜን የሚመስል ነው” ማለት ሳያስፈልገው እንዲሁ በቁሙ “ሥጋዬ ነው፣ ደሜ ነው” በማለት ተናግሯል፡፡ አንድ ምሳሌያዊ አገላለጽ በሁሉ ዘንድ ግልጽ መረዳትን ማግኘቱ የታወቀ ሲሆን (understood ሲሆን)፣ ምሳሌውን በቁሙ “ነው”፣ “ነኝ” እያሉ መናገር በየትኛውም ቋንቋ አገላለጽ ውስጥ የሚታወቅ ነገር መሆኑን፣ በቅንነት የሚያስቡ ሁሉ ይረዱታል፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ ኢየሱስን በተመለከተ “ሙሽራይቱ ያለችው እርሱ ሙሽራ ነው” ብሎታል (ዮሐ.3፡29)፤ ጌታ ኢየሱስ “ሙሽራ ነው” ሲባል “ነው” በመባሉ የተነሳ ምሳሌ መሆኑን የማይረዳ ማን አለ? ሙሽሪት ከተባለች ቤተክርስቲያን ጋር ያለውን የተወደደ ግንኙነት ለማሳየት የተጠራበት ምሳሌ እንጂ በቁሙ ፊደል ለፊደል ወስዶ በአንድ በሆነ ሠርግ ላይ ያለ ሙሽራ ነው የሚል ሰው የለም፤ እንዲሁም ጌታ ስለመጥምቁ ዮሐንስ በምሳሌ ሲናገር እርሱ “የሚነድና የሚያበራ መብራት ነበረ” ብሏል (ዮሐ.5፡35)፡፡ በዚህ አገላለጽ ዮሐንስ “መብራት” ስለተባለ ፊደል ለፊደል ወስዶ የጧፍ፣ ወይም የሻማ ወይም የኩራዝ መብራት ነበረ የሚል የለም፤ ምሳሌነቱ ግልጽ (understood) ነው፡፡ እንዲሁም ጌታ ኢየሱስ ስለራሱ ሲናገር እኔ የሕይወት እንጀራ ነኝ (ዮሐ.6፡35፣41)፣ የዓለም ብርሃን ነኝ (ዮሐ.8፡12፤ 9፡5)፣ የበጎች በር ነኝ (ዮሐ.10፡7)፣ መልካም እረኛ ነኝ (ዮሐ.10፡11)፣ የወይን ግንድ ነኝ (ዮሐ.15፡1)፣ የሚያበራ የንጋት ኮከብ ነኝ (ራእ.22፡16) በማለት ምሳሌውን እየተናገረ፣ “ነኝ” ስላለ ነገሩን ፊደል በፊደል የሚወስድ ማን አለ? “እንደ”፣ “የሚመስል” የሚሉት የማነጻጸሪያ ቃላት ባለመኖራቸው ምሳሌ መሆኑ የሚጠፋው አንባቢ የለም፡፡ እንዲሁም እንጀራውን አንስቶ “ሥጋዬ ነው” ሲል እንጀራው (ዳቦው) የሥጋው ምሳሌ እንጂ፣ በቀጥታ ፊደል በፊደል የሰውነት ሥጋው ነው ማለት እንዳልሆነ፣ የጽዋውን ወይንም አንስቶ “ደሜ ነው” ሲል ወይኑ የደሙ ምሳሌ እንጂ፣ በቀጥታ ፊደል በፊደል የሰውነት ደሙ ነው ማለት እንዳልሆነ አጥብቆ መረዳት ይገባል፡፡ በመሆኑም ለጌታ እራት የሚቀርበውን እንጀራ እና ወይን መብላትና መጠጣት በዮሐንስ ወንጌል ምዕ.6፡53 የተጠቀሰውን የክርስቶስን ሥጋና ደም ከመብላትና መጠጣት ጋር አንድ አይደለም፤ ምክንያቱም ለጌታ እራት የሚቀርበው እንጀራውና ወይኑ የጌታ ሥጋና ደም ምሳሌ ሲሆን፣ በዮሐንስ 6 ውስጥ የተጠቀሰው ግን የራሱን የክርስቶስን ሥጋና ደም የሚያመለክት ነውና፡፡

ጌታ “ሥጋዬን የሚበላ፣ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው” ብሎ በተናገረው የተወደደ ትምህርቱ መሠረት (ዮሐ.6፡53)፣ የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት ሥጋውንና ደሙን መብላት የሚገባቸው እነማን ናቸው? ለዚህ ጥያቄ ምላሽ እንዲሆን ጌታ ኢየሱስ ይህንን ትምህርት ያስተማረው ላላመኑት እንደነበር ማስተዋሉ ጠቃሚ ነው፤ ይህ ትምህርት የተሰጣቸው ሰዎች ጌታን ያላመኑ አይሁድ እንደነበሩ በዚያው በዮሐ.6 ውስጥ በግልጽ ተነግሯል (ዮሐ.6፡29፣41ና 52 ተመልከት)፡፡ እነዚህ ሰዎች የዘላለም ሕይወት ያላገኙ ነበሩ፤ ስለሆነም ሥጋውን ካልበሉ ደሙንም ካልጠጡ በራሳቸው የዘላለም ሕይወት እንደሌላቸው እና ሥጋውን የሚበላ እና ደሙን የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት እንደሚያገኝ ተነገራቸው (ቁ.53)፡፡ በመሆኑም የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ሥጋውን መብላት ደሙን መጠጠት የሚገባቸው ጌታን ያላመኑ የነበሩና በሚሰሙት የወንጌል ቃል ልባቸው ተነክቶ ክርስቶስን የሚያምኑ ሰዎች መሆናቸውን በዚህ እንረዳለን፡፡

ክርስቶስን ሳያምኑ የኖሩ ሰዎች በሚያምኑ ጊዜ ሥጋውን የሚበሉትና ደሙን የሚጠጡት እንዴት ነው? ይህ ጥያቄ አይሁድ ራሳቸውም ያነሱት ጥያቄ ነበር፤ “እንግዲህ አይሁድ። ይህ ሰው ሥጋውን ልንበላ ይሰጠን ዘንድ እንዴት ይችላል? ብለው እርስ በርሳቸው ተከራከሩ” የሚል ቃል ስለ እነርሱ እናባለን (ዮሐ.6:52)፡፡ ይህንንም ጥያቄ ሊያነሱ የቻሉት ሥጋውና ደሙ ፊደል በፊደል በጥርስ የሚበላና በአፍ የሚጠጣ አድርገው ስለወሰዱት ነው፤ አይሁድ ነገሮችን የሚረዱት ፊደል በፊደል ነውና፤ የእስራኤል መምህር የሆነው ኒቆዲሞስም ጌታ ስለዳግመኛ መወለድ ባስተማረው ጊዜ “ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን?” የሚል ጥያቄ ማንሳቱ አይሁድ ነገሮችን ፊደል በፊደል የመውሰድ ጠባያቸውን የሚያሳይ ነው (ዮሐ.3፡4 ተመልከት)፤ ጌታ ያስተማረው ግን ከሰው (ከእናት) ማኅፀን ስለመወለድ ሳይሆን መንፈስ ከሆነው ከእግዚአብሔር ስለመወለድ ነበረ፤ ስለሥጋዊ ልደት ሳይሆን ስለመንፈሳዊ ልደት ነበረ፡፡ እንዲሁም በዮሐ.6 ውስጥ ሥጋውን ስለመብላት ደሙን ስለመጣጣት ያስተማረው ቃል ፊደል በፊደል በቁሳዊ መልክ ስለመብላትና ስለመጠጣት አይደለም፡፡ “ሥጋዬን የሚበላ ደሜን የሚጠጣ” የሚለውን አገላለጽ በቁ.57 ላይ “የሚበላኝ” ብሎታል፤ ይህም የክርስቶስን ሥጋና ደም መብላትና መጠጣት፣ ክርስቶስን መብላት መሆኑን የሚያሳይ ነው፤ ነገር ግን ይህ የክርስቶስን ሥጋና ደም መብላትና መጠጣት ወይም ክርስቶስን መብላት ምን ማለት ነው?

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ 6 በተመዘገበው በዚህ ትምህርቱ ውስጥ ራሱን ያቀረበው ከሰማይ የወረደ የሕይወት እንጀራ አድርጎ ነው፤ ይህንንም ሲያስተምር በምድረ በዳ ሲጓዙ ለነበሩት እስራኤላውን ከሰማይ ከወረደላቸው መና ጋር በማነጻጸር ነው (ቁ.31-33ን፤ ቁ.49-50ን እና ቁ.58ን ተመልከት)፡፡ በቁ.35 እና በቁ 48 ላይ “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ” ያለውን ስናነብ፣ በቁ.51 ላይ ደግሞ “ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ” ብሎ የተናገረውን እናነባለን፡፡ ይህም እንጀራ ሥጋው መሆኑን ሲናገር “እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው” ብሏል (ቁ.51)፡፡ ስለሆነም አንድ የማያምን ነበረ ሰው ኢየሱስን ሲያምን እርሱን የሚበላው፣ ወይም ሥጋውንና ደሙን የሚበላውና የሚጠጣው እንደ ሕይወት እንጀራነቱ ነው፡፡ ይህ የሕይወት እንጀራ ደግሞ በመንፈስ እንጂ ቀጥታ በሥጋ የሚበላ አይደለም፡፡ ኢየሱስ ወደ እያንዳንዱ ሰው እንደ ሕይወት እንጀራ የሚቀርበለት ለእርሱ በሚሰበክለት ወንጌል ወይም በእግዚአብሔር ቃል አማካኝነት ነው፡፡ በዚያ ቃል የተሰበከለትን ኢየሱስን አምኖ ወደልቡ በሚያስገባው ጊዜ ያ ሰው ክርስቶስን በሕይወት እንጀራነቱ ይበላዋል፡፡ ይህ ትምህርቱ የሚያስጨንቅ ንግግር ለሆነባቸው ለእነዚያ ሰዎች ራሱ ኢየሱስ ሐሳቡን ሲያስረዳቸው “ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው፤ ሥጋ ምንም አይጠቅምም፤ እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው” ብሏቸዋል (ዮሐ.6:63)፤ ይህም “ከሰማይ የወረደ የሕይወት እንጀራ፣ እንዲሁም ሥጋዬ፣ ደሜ” በማለት የነገራቸው ቃል በቀጥታ ሥጋ፣ ደም ሳይሆን መንፈስ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፤ በእግዚአብሔር ቃል የሚሰበከው ክርስቶስ እንዲሁም ሥጋውና ደሙ በእርግጥም በሥጋ ሊበላ የሚችል ቁሳዊ መብል አይደለም፤ በመሆኑም በቃሉ የሚሰበከው መንፈስ የሆነው የክርስቶስ ማንነት ሊበላ የሚችለው በመንፈስ ብቻ ነው፤ ያም ኢየሱስን በእምነት በመቀበል የሚፈጸም ነው፤ በተለይ የኢየሱስን ሥጋውን መብላትና ደሙን መጠጣት እርሱ ስለኃጢአታችን እንደታረደ በግ ሆኖ መሞቱን በተመለከተ የተሰበከው ስብከት ልብን በሚነካና በዚህ ማንነቱ ወደ ኃጢአተኛው ልብ ውስጥ በሚገባ ጊዜ የሚከናወን ነው፡፡

በአጠቃላይ የክርስቶስን ሥጋውን መብላትና ደሙን መጠጣት ማለት እርሱን ማመን ወይም በእምነት ተቀብሎ ወደ ልብ ማስገባት ማለት ነው፡፡ ይህም ሲሆን የዘላለም ሕይወት ይገኛል፡፡ ጌታ ኢየሱስ በዚሁ በዮሐ.6 ትምህርቱ ውስጥ “ሥጋዬን የሚበላ ደሜን የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው” ያለውን ያህል “እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው” ብሏል (ዮሐ.6:47)፤ በሌላም ስፍራ “በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው” ብሏል (ዮሐ.3፡36)፤ ስለሆነም የዘላለም ሕይወት የሚገኘው እርሱን በማመን ከሆነ፣ እንዲሁም ሥጋውን በመብላት ደሙን በመጠጣትም ከሆነ፣ ሥጋውን መብላት ደሙን መጠጣት ማለት ስለኃጢአታችን ሥጋውን ለሞት አሳልፎ የሰጠውንና ደሙን ያፈሰሰውን ክርስቶስን ማመን መሆኑ፣ ወይም በእምነት መቀበል መሆኑ በዚህ ግልጽ ይሆናል፡፡ የጌታን እራት የሚካፈል ሰው ግን በእምነት የክርስቶስን ሥጋውን በልቶ ደሙን ጠጥቶ የዘላለም ሕይወት ያገኘ ሰው በመሆኑ ገና የዘላለም ሕይወትን ለማግኘት የሚካፈል አለመሆኑን በዚህ ማረጋጥ ይቻላል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥተ ሰማያት ምን እንደምትመስልና የዚያች መንግሥት መርሆዎች ምን እንደሆነ በቅድሚያ ነገራቸው፤ ይህም ከማቴ.5-7 በሚገኘው በተራራው ስብከቱ ውስጥ የገለጠው ነው፡፡ አገልግሎቱና ትምህርቱ ሁሉ ከእግዚአብሔር እንደሆኑ የሚያረጋግጡ ታምራትና ምልክቶችንም በፊታቸው በተከታታይ እንዳደረገ ከማቴ.8-9 እናነባለን፤ “እነርሱ ግን በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል” አሉ እንጂ አላመኑም ነበር፡፡ “አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ” በተባለው መሠረትም (1ቆሮ.1፡22) ብዙ ጊዜ በተደጋጋሚ ምልክትን እንዲያሳያቸው ይጠይቁት ነበር እንጂ ካዩት ምልክት የተነሣ በእርሱ አያምኑም ነበር፡፡ ዮሐንስ በወንጌሉ ይህን ሲገልጥ “ነገር ግን ይህን ያህል ምልክት በፊታቸው ምንም ቢያደርግ ነቢዩ ኢሳይያስ፡- ጌታ ሆይ ማን ምስክርነታችንን አመነ? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገለጠ? ብሎ የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ በእርሱ አላመኑም” ብሏል (ዮሐ.12፡37-38)፤ ማርቆስም በወንጌሉ ላይ ጌታ ስለአለማመናቸው እንደተደነቀ ጽፏል (ማር.6፡6)፤ አንዳንዶች ደግሞ ያመኑ ቢመስሉም ጌታ ግን በልባቸው ያለውን ያውቅ ነበርና አይተማመናቸውም ነበር፡፡ በእርግጥም ያ ትውልድ ጠማማ ትውልድ ነበር፡፡ ጌታ ኢየሱስ ራሱ የዚያን ትውልድ ጠማማነት ሲገልጽ “ነገር ግን ይህን ትውልድ በምን እመስለዋለሁ? ... ዮሐንስ ሳይበላና ሳይጠጣ መጣ፥ እነርሱም፡- ጋኔን አለበት አለበት። የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፥ እነርሱም፡- እነሆ፥ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ፥ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ ይለታል” (ማቴ.11፡16-19) በማለት ተናግሯል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ በቀጥታ በሚያስተምረው ነገር ያን ትውልድ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በንስሐ ከመጥራቱም ሌላ ደቀመዛሙርቱን ልኮላቸው ነበር፡፡ በቅድሚያ 12ቱን በሌላ ጊዜም 70ዎቹን ሁለት ሁለት እያደረገ “መንግሥተ ሰማያት (የእግዚአብሔር መንግሥት) ቀርባለች” ብለው እንዲሰብኩ ልኮአቸው ነበር (ማቴ.10፡7፣ ለቃ.10፡9)፡፡ ሲልካቸውም በደዌ እና በአጋንንት ላይ ሥልጣን ሰጥቶ ስለነበር መልእክታቸውን ላለመቀበል ለምልክት ፈላጊዎቹ አይሁድ ምክንያት አልነበራቸውም፡፡ እንዲህም ሆኖ በእርሱ በመሢሑ አላመኑም፡፡ ከዚያም በየመንደሮቻቸውና በየምኩራባቸው ድውያንን እየፈወሰ አጋንንትን እያወጣ ተጨማሪ ምልክቶችን በማድረግ ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእነርሱ የተገለጠ ሰው መሆኑን ቢያሳያቸውም እነርሱ ግን እንዴት እንደሚያጠፉት ይማከሩ ነበር (ማቴ.12፡14)፡፡ ቀደም ሲል እንዳሉትም ይህ በብዔል ዜቡል በአጋንንት አለቃ ካልሆነ በቀር አጋንንትን አያወጣም” ይሉ ነበር (ማቴ.12፡24)፡፡ ይህም የእግዚአብሔርን መንፈስ መሳደብ በመሆኑ የመጨረሻው የክፋት ደረጃ ላይ አደረሳቸው፤ ሊመለሱ ወደማይችሉበት ክፋት ውስጥ አስገባቸው፡፡ ታዲያ እነዚህ ክፉ ሰዎች ከዚህ ሁሉ በኋላ ወደ ጌታ መጡና “መምህር ሆይ ከአንተ ምልክትን እንድናይ እንወዳለን” አሉት፤ እርሱ ግን መልሶ “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል፤ ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም” አላቸው (ማቴ.12፡38-39)፡፡ እንዲሁም ከእርሱ የከፉ ሰባት አጋንንትን ይዞ ሰይጣን ተመልሶ እንደገባበት ሰው አድርጎ ያን ክፉ ትውልድ ገልጾታል፤ በመሆኑም በዚህ ደረጃ የአጋንንት ማደሪያ የሰይጣን ቤት የሆነ ትውልድ ክፉ ወይም ጠማማ ትውልድ ሊባል ይችላል ማለት ነው፡፡ ከዚህ ክፉ ትውልድም መዳን (መለየት) በእጅጉ ተገቢ ነው፡፡ በመሆኑም ጌታ ኢየሱስ ራሱ በድጋሚ ከሰማይ ምልክትን እንዲያሳያቸው በጠየቁት ጊዜ በፊት እንዳደረገው “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ምልከት አይሰጠውም” የሚል መልስ ከሰጣቸው በኋላ፣ ትቶአቸው እንደሄደ እናነባለን (ማቴ.16፡4)፡፡ ይህም ጌታ ኢየሱስ ከዚያ ትውልድ ራሱን እንደለየ የሚያሳይ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ደቀመዛሙርቱንም ከዚያ ክፉ ትውልድ በይፋ መለየት ሲጀምር እንመለከታለን፤ በመጀመሪያ “ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁና ተጠበቁ” (ማቴ.16፡6) በማለት ከክፉ ትምህርታቸው እንዲለዩ ከነገራቸው በኋላ ቤተክርስቲያንን በዓለት ላይ እንደሚሠራ ይነግራቸዋል፡፡ ያም ማለት የእርሱ የሆኑት ደቀመዛሙርት ከአይሁድ ተለይተው እርሱ በሚሠራት ቤተክርስቲያን ውስጥ ስፍራቸውን እንዲይዙ የሚገልጽ ነው፡፡

ያ ክፉና አመንዝራ ትውልድ የጌታን ትምህርትና አገልግሎት ያልተቀበለ ብቻ ሳይሆን ተቃውሞውን እስከ መጨረሻው ድረስ አጠናክሮ እርሱን በመስቀል ሞት ገድሎ እግዚአብሔር የሰጣቸውን መሢሕ አለመቀበሉን በተግባር ያረጋገጠ ትውልድ ነው፡፡ ዮሐንስ ጠቅለል ባለ መልኩ እስራኤል መሢሓቸውን አለመቀበላቸውን ሲገልጽ “የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፤ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም” በማለት ገልጾታል (ዮሐ.1፡11)፡፡ ይህም እግዚአብሔር የሚያድናቸውን መሢሕ የሰጣቸው በቅድሚያ እንደ ሕዝብ እንዲቀበሉት እንደነበር ያመለክታል፡፡ ነገር ግን ሕዝቡ በሃይማኖትና በሲቪል መሪዎቻቸው በኩል እርሱን እንዳልተቀበሉት በይፋ አሳዩ፤ ይህንንም “ይህ በላያችን ሊነግሥ አንወድም” (ለቃ.19፡14)፣ ስቀለው ስቀለው አስወግደው ከቄሣር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም” (ዮሐ.19፡6፣15)፣ “ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን” (ማቴ.27፡25) በማለት ገለጹ፡፡ በዚህም ጠማማ ትውልድነታቸውን በተግባራዊ መንገድ አረጋገጡ፡፡ ይሁንና ከዚህ ትውልድ መካከል በየግላቸው መሢሕን የተቀበሉ ጥቂት ቅሬታዎች ነበሩ፡፡ እነዚህ ሰዎች ከአፍኣዊ ተከታዮችም ተለይተው ከተጣሩ በኋላ ቁጥራቸው 120 ብቻ ነበር፡፡ እነርሱም ከዚያ ክርስቶስን ካልተቀበለው ሕዝብ ርቀው በመቅደስ ሳይሆን በሰገነቱ (በደርቡ) ቤት ተሰብስበው ሳለ የበዓለ ሃምሳ ዕለት መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፡፡ በዚህም እግዚአብሔር ከዚያ ጠማማ ትውልድ ተለይተው ከክርስቶስ ጋር ለሆኑት መለኮታዊ እውቅናን ሰጠ፡፡ ቤተክርስቲያንም የዚያን ዕለት ተጀመረች፡፡

“ቤተክርስቲያን” የሚለው ቃል በግሪኩ “ኤክሌሲያ” የሚለው ቃል ሲሆን ኤክሌስያ ማለትም ተጠርቶ የወጣ ጉባኤ ማለት ነው፡፡ ይህም በወንጌል የተጠሩ ሰዎች ከነበሩበት ከማያምነው ዓለም መውጣታቸውን ወይም መለየታቸውን የሚያመለክት ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ከአይሁድና ከአሕዛብ (ከግሪክ ሰዎች) በጸጋው ወንጌል የተጠሩት የተለዩ ወገኖች (አማኞች) የተሰባሰቡባት ማኅበር ናት፡፡ ስለሆነም በወንጌል ስብከት ልባቸው ተነክቶ በክርስቶስ የሚያምኑ አማኞች “ከጠማማው ትውልድ ዳኑ” የሚለው ያው የቀደመው ምክር ዛሬም ይቀርብላቸዋል፡፡ በተለይም አይሁዳዊ ጠባይ ባለው የዚህ ዓለም ሃይማኖታዊ አኗኗር ውስጥ የነበሩ ሰዎች ይህን ምክር ልብ ብለው ሊሰሙት ይገባል፡፡ ምንም እንኳ የዚህ ዘመን ትውልድ በሥጋ አይሁድ ባይሆንም ወደ አይሁዳዊነት ካፈገፈገ “ለራሳቸው የእግዚአብሔርን ልጅ ይሰቅሉታልና ያዋርዱትማልና” እንደተባሉት ሰዎች ይሆናል (ዕብ.6፡6)፡፡ እነዚህም መጀመሪያ ከበራላቸውና መንፈሳዊ ነገሮችን ከቀመሱ በኋላ የካዱ በመሆናቸው እነርሱን ለንስሐ ማደስ የማይቻል መሆኑ ተገልጿል፡፡ ያም ማለት “ጠማማ” ወይም “ክፉ” ትውልድ ወደ መሆን ደረጃ ደርሰዋል ማለት ነው፡፡ ከእንደ እነዚህ ዓይነት ትውልድ መካከል የነበረና በጸጋ ወንጌል ተጠርቶ በክርስቶስ ያመነ ማንኛውም የዳነ ሰው ከዚህ ትውልድ መለየት ይገባዋል፡፡ ከዚያም በክርስቶስ ዓለትነት ላይ በተመሠረተች ቤተክርስቲያን ውስጥ የእርሱ ከሆኑት ጋር ኅብረት ሊያደርግ ይገባዋል፡፡ በዚህም ከዚያ ክፉ ትውልድ ላይ ከሚመጣ ቁጣ የዳነ ይሆናል፡፡

2. ከሥጋ ሕመም ለመፈወስ አይደለም

አማኞች እንጀራውን የሚቆርሱት ወይም የጌታን እራት የሚካፈሉት በአንዳንዶች እንደሚታሰበው ከሥጋ ሕመም ፈውስን ለማግኘት አይደለም፡፡ የጌታ እራት ከጌታ የተሰጠን እጅግ የከበረ ሥርዓት ቢሆንም ጌታ የመሠረተልን ግን ለዚህ ዓላማ አይደለም፡፡ ምናልባት በ1ቆሮ.11፡29-31 በተጻፈው መሠረት ከቆሮንቶስ አማኞች መካከል ራሳቸውን ሳይፈትኑና ሳይመረምሩ፣ ማለትም ሳይገባቸው (ያልተገባቸው ሆነው ሳሉ) እንጀራውን በመብላታቸው እና ከጽዋውም በመጠጣታቸው የተነሣ የታመሙ የደከሙ እና ያንቀላፉ መኖራቸው፣ በተቃራኒው አማኞች ራሳቸውን በመመርመር ንስሐ ገብተው ቢካፈሉት ከሥጋ ሕመም ሊፈወሱ የሚችሉ መሆናቸውን እንደሚያመለክት ተደርጎ መወሰድ የለበትም፡፡ ይህ መደምደሚያ በራስ የተሳሳተ አረዳድ የሚደረስበት ቃሉ የማይናገረው ሐሳብ ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ የሥጋ መውጊያ በነበረበት ጊዜ ከእርሱ እንዲለይ ጌታን ለመነ እንጂ የጌታን እራት አልተካፈለም (2ቆሮ.12፡7-8)፤ ከእርሱ ጋር አብረው ይሠሩ የነበሩት አፍሮዲጡ፣ ጢሞቴዎስ እና ጥሮፊሞስ በታመሙ ጊዜ ከሕመማቸው ይፈወሱ ዘንድ የጌታን እራት እንዲካፈሉ አላደረገም (ፊልጵ.2፡26-27 1ጢሞ.5፡23፤ 2ጢሞ.4፡20 ተመልከት)፡፡ አማኞች በሚታመሙ ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለባቸው በሌላ ስፍራ ተነግሮናል፤ የቤተክርስቲያን ሽማግሌዎችን በመጥራት እንዲሁም እርስ በእርሳቸውም ቢሆን አንዱ ስሌላው የእምነት ጸሎት እንዲያደርጉ እንጂ የጌታን እራት እንዲካፈሉ አልተነገረም (ያዕ.5፡14-16 ተመልከት)፤ የጌታ እራት ራሱ ክርስቶስን እንጂ እኛን ለሚመለከት ዓላማ የተሰጠ አይደለም፡፡

ታዲያ እንጀራውን የመቁረስ (የጌታ እራት) ዓላማዎች ምንድናቸው?

1. ለጌታ መታሰቢያ እንዲሆን

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን አምነው የዘላለም ሕይወት ካገኙ በኋላ በስሙ የሚሰበሰቡ አማኞች ሰው የሆነውንና ኃጢአታቸውን በእንጨት መስቀል ላይ ተሸክሞ፣ ስለእነርሱ የኃጢአት መሥዋዕት ሆኖ የሞተላቸውን የእግዚአብሔርን በግ ዳግም ተመልሶ እስኪመጣ ድረስ ሁል ጊዜም ያስቡት ዘንድ የጌታ እራት ለመታሰቢያነት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ለአንድ ማንነት መታሰቢያ የሚደረገው ያ ማንነት በአካል አብሮ በማይኖር ጊዜ ነው፤ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም ወደ አብ የሚሄድበት ጊዜ ሲደርስ የወደዳቸውን እስከመጨረሻው ወደዳቸውና (ዮሐ.13፡1) የመታሰቢያውን እራት ሰጣቸው፤ ይህም እርሱ ተመልሶ በአካል እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ በዚህ በጸጋው ዘመን የእርሱ በሆኑት ሁሉ ሲታሰብ እንዲኖር የተሰጠ እራት ነው፤ ብዙውን ጊዜ የምድር ታላላቆች የልደት ቀናቸው ወይም የሞቱበት ቀን ወይም አንዳንድ ታላቅ ሥራዎችን የሠሩባቸው ቀናት ለመታሰቢያነት ይከበሩላቸዋል፤ ለእነርሱ መታሰቢያ የሚሆን ሐውልት ይቆምላቸዋል፣ ወይም አንዳንድ ታላላቅ ማዕከላት፣ መንገዶችና አደባባዮች በስማቸው ይሰየምላቸዋል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ግን በተለይ ታላቅ ፍቅሩ የተገለጠበትን የመስቀል ላይ ሞቱን በየትኛውም ደረጃ እና በየትኛውም ስፍራ የሚገኙ አማኞች ተሰብስበው ሊያደርጉት በሚችሉት የመታሰቢያ እራት እንዲያስቡት አድርጓል፡፡

መታሰቢያውን የሚያደርጉት ሰዎች በፍቅሩ የተሸነፉ እና በፍቅሩ የሚኖሩ ናቸው፡፡ መታሰቢያውን ለማድረግ የሚያነሳሳንም ይኸው ለእኛ ያለው ታላቅ ፍቅር ነው፡፡ እንጀራውን ቆርሰን በምንካፈል ጊዜ “ጌታ ስለእናንተ የሚሰጠው ሥጋዬ ይህ ነው” ብሎ በሰጠን መሠረት ስለእኛ የተሰጠው ሥጋውን በእንጀራው ምሳሌነት እናስባለን (ሉቃ.22፡19)፤ በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ ከተያዘ በኋላ ወደ ሊቀካህናቱ ወደ ሐና፣ ከሐና ወደ ቀያፋ፣ ከቀያፋ ወደ ጲላጦስ፣ ከጲላጦስ ወደ ሄሮድስ፣ ከሄሮድስ እንደገና ተመልሶ ወደ ጲላጦስ ተወስዶ የተንገላታውን፣ በአይሁድ ሎሌዎች የተተፋበትንና በጥፊ የተመታውን፣ በጲላጦስ ጭፍሮች የተገረፈውን፣ የተዘበተበትንና የሾክ አክሊል የደፋውን፣ ከዚያም መስቀል ተሸክሞ ወደ ቀራንዮ የተወሰደውንና በዚያ በመስቀል ተቸንክሮ የተሰቀለውን፣ ስለ እኛም ለመስቀል ሞት የተሰጠውን ሥጋውን እናስባለን፤ እንዲሁም ከጽዋው ስንጠጣ በተገረፈ ጊዜ፣ በተቸነከረ ጊዜ እና ተሰቅሎ ሳለ ጎኑን በጦር በተወጋ ጊዜ ስለኃጢአታችን ስርየት የፈሰሰውን ደሙን እናስባለን፡፡ ከዚህም ባሻገር እንጀራውን መቁረሳችንን (የጌታን እራት መካፈላችንን) ለሚመለከቱ ሁሉ እንጀራውን በመብላታችን ጽዋውንም በመጠጣታችን ስለ ክርስቶስን ሞት እንመሰክራለን፤ “ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁ” ተብለናልና (1ቆሮ.11፡26)፡፡

ስለጽድቅ ከሰው መከራ የተቀበለውና ስለኃጢአታችን ከእግዚአብሔር ፍርድን የተቀበለው ሁልጊዜም ሲታሰብ መኖር አለበት፡፡ እርሱ ስለ እኛ እስከመሞት ባደረሰው በዚህ ፍቅር ተነሳስተን፣ ስለእኛ “ኃጢአት ሆኖ” የሞተውን (2ቆሮ.5፡21) እርሱን በዚህ ሁኔታ እናስበዋለን፤ እንዲሁም “ኃጢአት የማያውቀውን” እርሱን “ለእግዚአብሔርም የመዓዛ ሽታ” ይሆን ዘንድ (ኤፌ.5፡2)፣ እንደሚቃጠል መሥዋዕት በአምልኮ እናቀርበዋለን፤ እኛ ቅዱሳን ካህናት እንደመሆናችን፣ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኘውን መንፈሳዊ መሥዋዕት በዚህ መልክ እናቀርባለን (1ጴጥ.2፡5)፡፡ ይህን ሁሉ ወደ ቀራንዮ መስቀል በመንፈስ ተወስደን፣ በምስጋናዎቻችንና በዝማሬዎቻችን አማካኝነት ለእግዚአብሔር የምናቀርበው አምልኮአችን ይሆናል፡፡

2. ኅብረትን ለመግለጥ

እንጀራውን የመቁረስ ሁለተኛው ዓላማ በአንድ የክርስቶስ አካል ውስጥ ያሉ እውነተኛ አማኞች ያላቸውን ኅብረት መግለጥ ነው፡፡ በክርስቶስ አምነው ከዚህ ክፉ ዓለም ተለይተው የወጡ አማኞች በተቀበሉት የእግዚአብሔር ቃል እውነት እና በልባቸው በገባው በእግዚአብሔር መንፈስ አማካኝነት እርስ በእርሳቸው አንድ ሆነዋል፡፡ እያንዳንዳቸውም ክርስቶስ ራስ በሆነላት አንድ አካል ውስጥ በመንፈስ ቅዱስ የተገጠሙ የአካል ብልት ሆነዋል፡፡ እግዚአብሔር የሚያውቃት የክርስቶስ አካል የሆነች ቤተክርስቲያንም አንድ ናት፡፡ በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ ተብሎ ተጽፏል (ኤፌ.4፡4)፡፡ በመሆኑም በዓለም ከሚገኝ ክፉ ማኅበር ተለይተው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የሚሰበሰቡ በመካከላቸው የጌታ ገበታ ተዘርግቶ በዚያ እንጀራውን ሲቆርሱ የክርስቶስን መታሰቢያ ከማድረግ በተጨማሪ በአንድ የክርስቶስ አካል ውስጥ ያላቸውን ኅብረት ይገልጣሉ፡፡ ይህም ዓላማ በስፋት የተነገረው በ1ቆሮ.10፡14-22 ውስጥ ሲሆን ቀጥሎ በዝርዝር እንመለከተዋለን፡፡

የቆሮንቶስ ሰዎች አሕዛብ ሳሉ ድምፅ ወደሌላቸው ጣዖታት ተወስደው ስለነበረ በጌታ ካመኑ እና እንጀራውን በመቁረስ ኅብረት ማድረግ ከጀመሩ በኋላ እንኳ ከእነርሱ አንዳንዶቹ በጣዖት ቤት ውስጥ በማዕድ የመቀመጥ አደጋ ነበረባቸው (1ቆሮ.8፡10)፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ይህ አደጋ እንደነበረባቸው ስለተመለከተ፣ በቅድሚያ “ጣዖትን ከማምለክ ሽሹ” ይላቸዋል (1ቆሮ.10፡14)፡፡ ይህም ማሳሰቢያ በጣዖት ማዕድ ዙሪያ ካለው ኅብረት ሙሉ በሙሉ እንዲለዩ የሚያደርጋቸው ነው፡፡ ምክንያቱም እነርሱ የሚካፈሉት የጌታ እራት እና በጣዖት ቤት ውስጥ ያለው ማዕድ የሚገልጡት ፍጹም ተቃራኒ የሆኑ የተለያዩ ኅብረቶችን ነው፡፡ በጌታ ገበታ ላይ ለጌታ እራት የሚቀርበው ወይን እና እና እንጀራ (ዳቦ) በቁስነታቸው ከየትኛውም ወይንና ዳቦ የማይለዩ ቢሆንም በሚወክሉት ነገር ወይም በምሳሌነታቸው ግን ፈጽሞ ይለያሉ፤ በመሆኑም በቅድሚያ ጽዋውና እንጀራው ከምን ጋር ኅብረት እንዳላቸው ይናገራል፡፡ “ልባሞች እንደ መሆናችሁ እላለሁ፤ በምለው ነገር እናንተ ፍረዱ። የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቆርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን?” ይላል (1ቆሮ.10፡15-16)፡፡ እውነትም ልባም የሆነ ማንም ሰው ሊፈርድ ይችላል፤ በጌታ እራት ጊዜ ጽዋው በገበታው ላይ የተቀመጠው የክርስቶስን ደም በመወከል፣ እንጀራውም የተቀመጠው ሥጋውን በመወከል እንጂ እንዲሁ ለመብልነት እንዳልሆነ እያንዳንዱ ልባም ክርስቲያን ሊፈርድ ይችላል፡፡ በመሆኑም የምንባርከው ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት አለው፤ ምሳሌ ሆኖ የሚገልጠው ሌላ ምንም ነገር ሳይሆን የክርስቶስን ደም ነውና፤ የምንቆርሰውም እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት አለው፤ ምሳሌ ሆኖ የሚገልጠው ሌላ ምንም ነገር ሳይሆን የክርስቶስን ሥጋ ነውና፡፡ ጽዋውን ከክርስቶስ ደም ጋር፣ ደሙንም ከክርስቶስ ሥጋ ጋር የሚያገናቸው ይህ ምሳሌነታቸው ስለሆነ ኅብረት የሚያደርጉትም በዚህ የተባረከ ምሳሌነት ነው፡፡ “የምንባርከው”፣ “የምንቆርሰው” የሚሉት በብዙ ቁጥር የተነገሩ ቃላት የጌታ እራት በየግል ሳይሆን በኅብረት የምንካፈለው ማዕድ መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ታዲያ በዚህ መልክ የክርስቶስን ሥጋና ደም በምሳሌነት የሚወክሉትን ጽዋውንና እንጀራውን በኅብረት የሚካፈሉ አማኞች ከኅብረቱ ተለይተው በጣዖት ቤት ውስጥ ያለውን ማዕድ እንዴት ሊካፈሉ ይችላሉ? ልባሞች ይህንን በትክክል ሊፈርዱ ይችላሉ፡፡

በጌታ እራት ጊዜ ጊዜ የምንቆርሰው እንጀራ በቀዳሚውና በዋነኛው ትርጉሙ የክርስቶስን ሥጋ የሚወክል ቢሆንም፣ በመቀጠል ግን ክርስቶስ ራስ የሆነላትን አንድ አካል የሆነች ቤተክርስቲያንን ያመለክታል፡፡ እርስዋም ከበዓለ ሃምሳ እስከ ጌታ መምጣት ባለው ዘመን በመላው ዓለም ያሉ እውነተኛ አማኞችን የያዘች አንዲት ማኅበር ናት፡፡ ሐዋርያው ይህንን ሐሳብ ሲገልጥ “አንድ እንጀራ ስለ ሆነ፥ እኛ ብዙዎች ስንሆን አንድ ሥጋ (አካል) ነን፤ ሁላችን ያን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና” ብሏል (1ቆሮ10፡17)፡፡ የጌታ እራት በሚደረግ ጊዜ በገበታው ላይ የሚኖረው እንጀራ ወይም ዳቦ አንድ መሆን እንዳለበት ከዚህ ቃል እንረዳለን፤ ብዙ ብልቶች የሆንን ሁላችን ከዚህ አንድ እንጀራ ስንካፈል አንድ አካል መሆናችንን እናሳያለን፡፡ በዚህ ንባብ ውስጥ በአማርኛው “አንድ ሥጋ” የሚለው በሌሎች ትርጉሞች “አንድ አካል” ተብሎ ተገልጿል(KJV, JND)፡፡ ይህ ቃል በሮሜ 12፡5 ላይም “ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን” ተብሎ ተነግሯል፡፡ በመሆኑም አንዱን እንጀራ ሁላችንም መካፈላችን በክርስቶስ አካል ውስጥ ካሉ ብዙ ብልቶች ጋር አንድ አካል መሆናችንን የሚያሳይ መገለጫ ነው፡፡

ከመደበኛ መብልነት ውጪ የተለየ ዓላማ ያለውን አንድ ማዕድ አብሮ መብላት፣ አብረው የሚበሉት ሰዎች ማዕዱ በሚገልጠው ዓላማ ላይ ያላቸውን ኅብረት የሚገልጽ ነው፡፡ ሐዋርያው ከዚህ አኳያ ከጌታ ማዕድ ጋር በማነጻጸር በቅድሚያ ያቀረበው በሥጋ የሆኑት እስራኤል ከመሠዊያው የሚበሉትን ማዕድ ነው፤ “በሥጋ የሆነውን እስራኤል ተመልከቱ፤ መሥዋዕቱን የሚበሉ የመሠዊያው ማኅበረተኞች አይደሉምን?” ይላል (1ቆሮ.10:18)፡፡ በሥጋ በሆነው እስራኤል ዘንድ ያለው መሠዊያ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት የሚቀርብበት መሠዊያ ነው፡፡ በዚያ መሠዊያ ላይ ከሚቀርቡት መሥዋዕቶች መካከል አንዳንዶቹን እንዲበሉ ለካህናቱ ተፈቅዷል (ዘሌ.7፡11-34፤ ዘኁል.18፡6-11 ተመልከት)፤ ከእነርሱ ውጪ ግን ለማንም አይፈቀድም፡፡ ስለሆነም እነዚህ የካህናት ቤተሰብ ብቻ የመሠዊያው ማኅበረተኞች ናቸው፡፡ እንዲሁም መሠዊያውም ሆነ መሥዋዕቶቹ ምሳሌ በሆኑለት በክርስቶስ ያመኑና ቅዱሳን ካህናት የሆኑ አማኞች የጌታን እራት ሲካፈሉ የመሠዊያው ማኅበረተኞች ሆነዋል፡፡ የእግዚአብሔር የመሥዋዕት በግ የሆነውን የክርስቶስን ሥጋና ደም የሚወክሉትን እንጀራውንና ወይኑን በመካፈላቸውም ይህን ማኅበረተኝነታቸውን ያሳያሉ፡፡

በተቃራኒው ደግሞ በአሕዛብ ዘንድ ለአጋንንት መሥዋዕት የሚያቀርቡ የአጋንንት ማኅበረተኞች እንዳሉ ጳውሎስ ይገልጻል፡፡ በተለይ የቆሮንቶስ አማኞችን የከበባቸውና የሚፈትናቸው ይህ ማኅበር ነው፡፡ ከእነርሱ አንዳንዶቹ በጣዖት ቤት በማዕድ እስኪቀመጡ ድረስ ያደረሳቸው ነገር ደግሞ ምናልባት “ለጣዖት የተሠዋው ያ መብል ከመብልነት ውጪ ምንም ስላልሆነ ብንበላው በእኛ ላይ ምንም ለውጥ አያመጣም” በሚል ከንቱ ሐሳብ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ያላስተዋሉት ነገር መሥዋዕቱ የሚቀርበው ለአጋንንት በመሆኑ እነርሱ ከጣዖት አምላኪዎቹ ጋር አብረው መብላታቸው ከአጋንንት ጋር ማኅበረተኞች የሚያደርጋቸው መሆኑን ነው፡፡ ሐዋርያው ይህን በጽኑ ሲያስረዳቸው “እንግዲህ ምን እላለሁ? ለጣዖት የተሠዋ ምናምን ነው እላለሁን? ወይስ ጣዖት ምናምን እንዲሆን እላለሁን? አይደለም፤ ነገር ግን አሕዛብ የሚሠዉት ለአጋንንት እንዲሆን እንጂ ለእግዚአብሔር እንዳይሠዉ እላለሁ፤ ከአጋንንትም ጋር ማኅበረተኞች እንድትሆኑ አልወድም።” ብሏቸዋል የጌታን ጽዋና የአጋንንትን ጽዋ ልትጠጡ አትችሉም፤ ከጌታ ማዕድና ከአጋንንት ማዕድ ልትካፈሉ አትችሉም” ብሏቸዋል (1ቆሮ.10:19-22)፡፡

ስለዚህ በዙሪያችን ባለው ዓለም ከሚገኝ ከክርስቶስ ማኅበር ውጪ በሆነ በሌላ ማኅበር ውስጥ ማኅበረተኛ የማድረግ ዓላማ ካለው ከየትኛውም ጽዋና ማዕድ ራሳችንን ልንጠብቅ ይገባል፡፡ ምናልባት በቀጥታ ለጣዖት ከቀረበው የአጋንንት ጽዋና የአጋንንት ማዕድ መራቅ ቀላል ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም በክርስቲያኖች ዘንድም እንኳ ሳይቀር ከጌታ እራት ውጪ ሌሎች ኅብረቶችን በሚገልጡ ማዕዶች መካፈል የዚያ ማኅበር ማኅበረተኛ እንደሚያደርግ ብዙዎች አያስተውሉም፡፡ ስለሆነም ማዕዱ የሚቀርበው እንደ ሰርግ፣ ምርቃት፣ … በመሳሰሉ በአንዳች ማኅበራዊ ምክንያት ሳይሆን ከአምልኮ ጋር በተያያዘ ሃይማኖታዊ ምክንያት ከሆነ ነገሩን በመንፈስ ሆኖ እንደ እግዚአብሔር ቃል በጥንቃቄ በመመርመር ራስን መጠበቅ ተገቢ ነው፡፡ እኛ “ኅብረታችን ከአባት ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው” (1ዮሐ.1፡3)፤ በመሆኑም ከዚህ ኅብረታችን ጋር ከሚቃረንና በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከአጋንንት ጋር ማኅበረተኛ ከሚያደርግ ከየትኛውም ጽዋ እና ማዕድ መካፈል አይገባንም፤ በዚህ የተነሣ ሊመጣ የሚችለውን ፈተና በመፍራት፣ ወይም ከጌታ ይልቅ ወደዚያ ማዕድ የጋበዙንን በማክበርና በማፈር ብንካፈል ግን ጌታን እናስቀናዋለን፡፡ ሐዋርያው እንዲህ ያሉትን አማኞች “ወይስ ጌታን እናስቀናውን? እኛስ ከእርሱ ይልቅ እንበረታለንን?” በማለት ይጠይቃቸዋል (1ቆሮ.10፡22)፤ በመሆኑም ከጌታ ይልቅ የሚበረታ ማንም አማኝ ስለሌለ እርሱን ከሚያስቀና ከየትኛውም ማዕድ ሊርቅ ይገባዋል፡፡


Amharic Bible-|- The Holy Bible [King James Version]