ትምህርት  


1. የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ መቀበል (ሐ.ሥ.2፡38)

የተሰበከለትን ወንጌል ተቀብሎ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ከልቡ ያመነ ማንኛውም ሰው ይህን እውነተኛ እምነቱን ተከትሎ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታን ይቀበላል፡፡ ‹‹የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ›› የሚለው ይህ ቃል ከዚህ ከሐ.ሥ.2፡38 ሌላ በሐ.ሥ.10፡45 ላይ የሚገኝ ሲሆን ቃሉ የሚያመለክተው የጸጋ ስጦታዎችን ሳይሆን መንፈስ ቅዱስ ራሱ ለአማኙ የተሰጠ ስጦታ መሆኑን ነው፡፡ ምክንያቱም ቃሉ ‹‹የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ›› ይላል እንጂ ‹‹የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች›› አይልም፡፡ በ1ቆሮ.12፡4 ‹‹የጸጋም ስጦታ ልዩ ላይ ነው፤ መንፈስ ግን አንድ ነው›› ይላል፡፡ በመሆኑም የጸጋ ስጦታ ልዩ ልዩ ስለሆኑ በብዙ ቁጥር ‹‹ስጦታዎች›› ሊባሉ እንደሚችሉ ያሳያል፡፡ ስጦታዎቹን የሚሰጠው መንፈስ ቅዱስ ግን አንድ ስለሆነ እርሱ በስጦታነቱ ሲገለጽ በነጠላ ቁጥር ‹‹የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ›› ተብሏል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ማን ነው? አማኞችስ መቼና እንዴት ይቀበሉታል? የሚሉትን ደግሞ ቀጥሎ እንመለከታለን፡፡

መንፈስ ቅዱስ ማነው?

መንፈስ ቅዱስ አንድ መለኮት ከሆኑት ከሦስቱ አካላት አንዱ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፤ ያዘዝኋችሁን ሁሉ እንዳጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀመዛሙርት አድርጓቸው›› ብሎ በተናገረው ቃል ውስጥ (ማቴ.28፡19)፣ መንፈስ ቅዱስ በአብና በወልድ ደረጃ ያለ፣ ነገር ግን እንደ አብና እንደ ወልድ በራሱ አካል የሚኖር እንዲሁም ከአብና ከወልድ ጋር መለኮታዊ የባሕርይ አንድነት ያለው ሆኖ ይታያል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ጌታ ኢየሱስ ስለመንፈስ ቅዱስ ባስተማረው ትምህርት ውስጥ መንፈስ ቅዱስ እንደ አብና እንደ ወልድ ሁሉ የራሱ የተለየ አካል ያለው መለኮታዊ ማንነት መሆኑን እንረዳለን፡፡

ይህንን እውነታ አጉልተው ከሚያሳዩን ንባቦች መካከል ‹‹ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ እኔም አብን እለምናለሁ፤ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል›› የሚለው ቃል አንዱ ነው፡፡ (ዮሐ.14፡15) በዚህ ስፍራ ላይ መንፈስ ቅዱስ ‹‹ሌላ አጽናኝ›› መባሉ እርሱ በአንድ መለኮት ውስጥ ሆኖ ሳለ ከአብና ከወልድ ሌላ የሆነ ማንነት መሆኑን በግልጽ ያሳያል፡፡ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ ‹‹እርሱ›› ተብሎ መጠራቱ የራሱ እርሱነት ያለው ሕያው ማንነት መሆኑን ያረጋግጣል፤ በተጨማሪም መንፈስ ቅዱስ አንድ ሕያው አካል (ማንነት) የሚሠራቸውን ሥራዎች እንደሚሠራ ተገልጿል፡፡ ጌታ ስለ መንፈስ ቅዱስ ሲናገር ‹‹እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል››፣ ‹‹እኔም የነገርኋችሁን ያሳስባችኋል››፣ ‹‹ስለ እኔ ይመሰክራል››፣ ‹‹ዓለምን ይወቅሳል››፣ ‹‹ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል›› ብሏል፡፡ (ዮሐ.14፡25-26፤ 16፡8፣13)

የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ መቀበል ማለት ከአብና ከወልድ ጋር አንድ መለኮት የሆነና እንደ አብና እንደ ወልድ በራሱ አካል (ማንነት) ከዘላለም የነበረ ያለና የሚኖረውን እርሱን መቀበል ማለት ነው፤ ታዲያ ይህ መለኮት የሆነ ማንነት እኛን መኖሪያው ሊያደርገን በእኛ ውስጥ ሊገባ ሲመጣ እንደምን ባለ አክብሮትና ትህትና ልንሆን ይገባናል!

የተስፋው ቃል

ንስሐ የገቡትና የተጠመቁት ማለትም በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑት ሰዎች ‹‹የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ትቀበላላችሁ›› የተባሉት በተስፋው ቃል መሠረት መሆኑ ተገልጿል፡፡ ሐዋርያው ጴጥሮስ ይህን ሲገልጽ ‹‹የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ ጌታ አምላካችንም ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉት ሁሉ ነውና›› ብሏል፡፡ (የሐ.ሥ.2፡39)፡፡

በተስፋው ቃል መሠረት መንፈስ ቅዱስ የበዓለ ሃምሳ ዕለት ሲወርድ የተከናወነው ዋነኛ ነገር ‹‹የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት›› እንደነበር እንረዳለን፡፡ ምክንያቱም ጌታ ኢየሱስ ሊያርግ ሲል ለደቀመዛሙርቱ ‹‹ከእኔ የሰማችሁትን አብ የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቁ፤ ዮሐንስ በውኃ አጥምቆ ነበርና እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ›› በማለት ተናግሮ ነበር (የሐ.ሥ.1፡5)፤ ከጥቂት ቀን በኋላ የተባለውም መንፈስ ቅዱስ የወረደበት በዓለ ሃምሳ ነበረ፡፡ ስለሆነም የዚያን ዕለት እነዚያ 120 አማኞች በመንፈስ ቅዱስ ተጠምቀዋል፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ ስለ ጌታ ኢየሱስ ሲመሰክር ‹‹እኔስ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን የጫማውን ጠፍር መፍታት ከማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ ይመጣል፡፡ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል›› ብሎ ነበር (ሉቃ.3፡16) በዚህ አገላለጽ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀትና የእሳት ጥምቀት ‹ና› በሚለው መስተጻምር ተለያየተው መነገራቸውን ማስተዋል ይገባል፡፡ በበዓለ ሃምሳ ዕለት የተከናወነው ጥምቀት ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት መሆኑ በግልጽ ተነግሯል (የሐ.ሥ.1፡5)፡፡ የተስፋው ቃል ሆኖ የተነገረውም የእሳት ጥምቀት ሳይሆን የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ነው፡፡ በበዓለ ሃምሳ ዕለት በተስፋው ቃል መሠረት በመንፈስ ቅዱስ የተጠመቁት ከአይሁድ የተጠሩት ሲሆኑ ተስፋው በሩቅ ላሉትም የተሰጠ በመሆኑ በኋላ ላይ ከአሕዛብ የተጠሩትም በዚያው በአንዱ መንፈስ ተጠምቀዋል፡፡ ይህም የተከናወነው በቆርኔሌዎስ ቤተሰዎች ላይ እንደነበር ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ እናነባለን (የሐ.ሥ.10፡44-45፤11፡15-16)፡፡ በዚህም አንዲቷ ቤተክርስቲያን ማለትም ከአይሁድ የተጠሩትና ከግሪክ ሰዎች (ከአሕዛብ) የተጠሩት አንድ አዲስ ሰው የሆኑባት (ኤፌ.2፡14)፣ በክርስቶስ ራስነት የምትመራዋ አንድ አካል ተፈጥራለች፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ዓላማው ይህችን አንድ አካል ማስገኘት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ሲገለጽ ‹‹አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና፡፡ ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል›› ይላል (1ቆሮ.12፡13)፡፡

መንፈስ ቅዱስ የበዓለ ሃምሳ ዕለት ወደዚህ ዓለም ከመጣ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ከአማኞች ወይም ከቤተክርስቲያን ጋር አለ፡፡ ምክንያቱም ጌታ በሰጠው የተስፋ ቃል ውስጥ ‹‹ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል›› ብሎ ለዘላለም አብሮን እንደሚኖር ተናግሯልና ነው፡፡

በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅ

በተስፋው ቃል መሠረት መንፈስ ቅዱስ የበዓለ ሃምሳ ዕለት ሲወርድ የተከናወነው ዋነኛ ነገር ‹‹የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት›› እንደነበር እንረዳለን፡፡ ምክንያቱም ጌታ ኢየሱስ ሊያርግ ሲል ለደቀመዛሙርቱ ‹‹ከእኔ የሰማችሁትን አብ የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቁ፤ ዮሐንስ በውኃ አጥምቆ ነበርና እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ›› በማለት ተናግሮ ነበር (የሐ.ሥ.1፡5)፤ ከጥቂት ቀን በኋላ የተባለውም መንፈስ ቅዱስ የወረደበት በዓለ ሃምሳ ነበረ፡፡ ስለሆነም የዚያን ዕለት እነዚያ 120 አማኞች በመንፈስ ቅዱስ ተጠምቀዋል፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ ስለ ጌታ ኢየሱስ ሲመሰክር ‹‹እኔስ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን የጫማውን ጠፍር መፍታት ከማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ ይመጣል፡፡ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል›› ብሎ ነበር (ሉቃ.3፡16) በዚህ አገላለጽ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀትና የእሳት ጥምቀት ‹ና› በሚለው መስተጻምር ተለያየተው መነገራቸውን ማስተዋል ይገባል፡፡ በበዓለ ሃምሳ ዕለት የተከናወነው ጥምቀት ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት መሆኑ በግልጽ ተነግሯል (የሐ.ሥ.1፡5)፡፡ የተስፋው ቃል ሆኖ የተነገረውም የእሳት ጥምቀት ሳይሆን የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ነው፡፡ በበዓለ ሃምሳ ዕለት በተስፋው ቃል መሠረት በመንፈስ ቅዱስ የተጠመቁት ከአይሁድ የተጠሩት ሲሆኑ ተስፋው በሩቅ ላሉትም የተሰጠ በመሆኑ በኋላ ላይ ከአሕዛብ የተጠሩትም በዚያው በአንዱ መንፈስ ተጠምቀዋል፡፡ ይህም የተከናወነው በቆርኔሌዎስ ቤተሰዎች ላይ እንደነበር ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ እናነባለን (የሐ.ሥ.10፡44-45፤11፡15-16)፡፡ በዚህም አንዲቷ ቤተክርስቲያን ማለትም ከአይሁድ የተጠሩትና ከግሪክ ሰዎች (ከአሕዛብ) የተጠሩት አንድ አዲስ ሰው የሆኑባት (ኤፌ.2፡14)፣ በክርስቶስ ራስነት የምትመራዋ አንድ አካል ተፈጥራለች፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ዓላማው ይህችን አንድ አካል ማስገኘት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ሲገለጽ ‹‹አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና፡፡ ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል›› ይላል (1ቆሮ.12፡13)፡፡

መንፈስ ቅዱስን የምንቀበለው ምን ጊዜ ነው?

በበዓለ ሃምሳ ዕለት ሐዋርያው ጴጥሮስ በሰበከው ቃል ልባቸው የተነካ ሰዎች፣ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ እንደሚቀበሉ የተነገራቸው፣ ‹‹ንስሐ ግቡ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ›› ከተባሉ በኋላ ነው (የሐ.ሥ.2፡38)፡፡ ንስሐ መግባታቸውና በውኃ መጠመቃቸው በኢየሱስ ክርስቶስ ማመናቸውን የሚያሳይ ሲሆን ሰው መንፈስ ቅዱስን ሊቀበል የሚችለው በኢየሱስ ክርስቶስ ሲያምን ብቻ እንደሆነ ያስገነዝባል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በሐ.ሥ.8፡15-17 እ ንዲሁም በሐ.ሥ.19፡6 ላይ አማኞች መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉት ከውኃ ጥምቀት በኋላ መሆኑን እናያለን፤ ሆኖም የውኃ ጥምቀት፣ የሐዋርያት ጸሎትም ሆነ የሐዋርያት እጅ መጫን ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ሁል ጊዜም የግድ መደረግ የነበረባቸው ቅድመ ሁኔታዎች እንዳልነበሩ እናስተውላለን፤ ይህንንም በግልጽ የምንረዳው በሐ.ሥ.10፡44-48 በምናነበው ቃል ነው፡፡ ይህም ቃል እንዲህ ይላል፡- ‹‹ጴጥሮስ ይህን ገና ሲናገር ቃሉን በሰሙት ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ ከጴጥሮስም ጋር ከመጡት ሁሉ ከተገረዙት ወገን የሆኑ ምዕመናን በአሕዛብ ላይ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ስለፈሰሰ ተገረሙ በልሳኖች ሲናገሩ እግዚአብሔርንም ሲያከብሩ ሰምተዋቸዋልና፡፡ በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መልሶ እነዚህ እንደ እኛ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ እንዳይጠመቁ ውኃን ይከለክላቸው ዘንድ የሚችል ማን ነው? በኢየሱስ ክርስቶስ ስምም ይጠመቁ ዘንድ አዘዛቸው››

በዚህ ቃል ውስጥ እንደምናየው እነዚህ ከአሕዛብ ወገን የሆኑ የቆርኔሌዎስ ቤተሰዎች መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉት በውኃ ከመጠመቃቸው በፊት ነበር፡፡ እንዲሁም ቃሉን ሲሰብክላቸው የነበረው የሐዋርያው የጴጥሮስ ጸሎትም ሆነ እጅ መጫን ሳይደረግላቸው ቃሉን በሰሙት ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ፡፡ የበዓለ ሃምሳ ዕለትም ቢሆን መንፈስ ቅዱስ የወረደላቸውና የተቀበሉት ሰዎች በውኃ አልተጠመቁም ነበር፤ እነርሱ ራሳቸው በጸሎት ላይ ነበሩ እንጂ መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ የጸለየላቸው ሰው አልነበረም፡፡ እንዲሁም ራሳቸው ሐዋርያትም መንፈስ ቅዱስን ከሚቀበሉት መካከል ስለነበሩ የሐዋርያት እጅ መጫን አልተደረገም፡፡ በመሆኑም በሐዋርያት ዘመን ሁሉም ዓይነት ሰዎች መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል እነዚህን ነገሮች የግድ መፈጸም ያስፈልጋቸው እንዳልነበረ እናያለን፡፡

መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል ለሁሉም ሰው የግድ አስፈላጊ የሆነው ነገር በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ቅዱስን የሚቀበሉት በእርሱ የሚያምኑት እንደሆኑ ሲያስተምር ‹‹ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ፡፡ በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆድ ይፈልቃል›› ብሏል፡፡ ወንጌላዊው ዮሐንስ ጌታ ይህን ቃል የተናገረበትን ምክንያት ሲገልጽ ‹‹ይህን ግን በእርሱ የሚያምኑት ላቀበሉት ስሌላቸው ስለመንፈስ ተናገረ፤ ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ ገና አልወረደም ነበርና›› ብሏል (ዮሐ.7፡37-39)፡፡ ስለዚህ ሰው መንፈስ ቅዱስን የሚቀበለው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ባመነ ጊዜ ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም ወደ ኤፌሶን ለመጀመሪያ ጊዜ እንደገባ ያገኛቸውን 12ቱ የመጥምቁ ዮሐንስም ደቀመዛሙርት የጠየቃቸው ጥያቄ ‹‹ባመናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀበላችሁን?›› የሚል ነበር (የሐ.ሥ.19፡2)፡፡ ምንም እንኳ ከእነዚህ ደቀመዛሙርት ነባራዊ ሁኔታ አንጻር እነርሱ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉት በኢየሱስ ስም ከተጠመቁ በኋላና ጳውሎስ እጁን በጫነባቸው ጊዜ ቢሆንም ጳውሎስ የሚያውቀውና የሚያምነው አጠቃላይ የሆነ መደበኛው እውነታ ግን ሰው መንፈስ ቅዱስን የሚቀበለው ባመነ ጊዜ እንደሆነ መጀመሪያ ላይ ያቀረበላቸው ጥያቄ በግልጽ ያሳያል፡፡ እንዲሁም ለእነዚሁ ለኤፌሶን ሰዎች በጻፈው መልእክት ውስጥ ‹‹እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል ይኸውም የመዳናችሁን ወንጌል ሰምታችሁ፣ ደግሞም በክርስቶስ አምናችሁ በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ›› ብሏል (ኤፌ.1፡13)፡፡ በዚህ ቃል ውስጥ ለማንኛውም ሰው የሚሆን አጠቃላይ መርህ ቀርቧል፡፡ በዚህም መሠረት በቅድሚያ የመዳን ወንጌልን መስማት፣ በመቀጠል ደግሞ በክርስቶስ ማመን፣ በመንፈስ ቅዱስ ለመታተም ያበቃል፡፡ ስለሆነም ከልብ በሆነ እውነተኛ እምነት በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑ ሁሉ መንፈስ ቅዱስን ይቀበላሉ፡፡

የመንፈስ ቅዱስ መኖሪያ

መንፈስ ቅዱስ የበዓለ ሃምሳ ዕለት በይፋ ወደዚህ ዓለም ከመጣ ጊዜ ጀምሮ በዚህ ዓለም ውስጥ የራሱ የሆነ መኖሪያ አለው፡፡ ይኸውም ከዓለም ተለይተው በዚህች ዓለም ውስጥ የሚኖሩ አማኞች ናቸው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ስለመንፈስ ቅዱስ መምጣት በተናገረው ቃል ውስጥ ይህን በተመለከተ ሲናገር ‹‹እኔም አብን እለምናለሁ፤ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፡፡ እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለሆነ ላቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውስጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ›› ብሏል (ዮሐ.14፡15-17) በዚህ ቃል ውስጥ መንፈስ ቅዱስ አንድ ጊዜ ወደ ዓለም ከመጣ በኋላ ቤተክርስቲያን በምድር እስካለች ድረስ ለዘላለም ከእኛ ጋር እንደሚኖር እንረዳለን፡፡ የሚኖረውም በሁለት መንገድ ሲሆን አንደኛው አማኞች በአንድ ላይ በጉባኤ ስንሆን በመካከላችን ይኖራል፡፡ ይህም ‹‹ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር›› በሚለው ቃል ተገልጿል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በእያንዳንዱ አማኝ ውስጥ ገብቶ መኖሩ ሲሆን ይህም ‹‹በውስጣችሁም ስለሚሆን›› በሚለው ቃል ተገልጿል፡፡

በሌላ አገላለጽ መንፈስ ቅዱስ በምድር ላይ በሚኖርበት በዚህ ዘመን አማኞች በጉባኤም ሆነ በግል የመንፈስ ቅዱስ መኖሪያ ቤተመቅደስ ናቸው ማለት ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ የክርስቲያኖች ጉባኤን (ቤተክርስቲያንን) ቤተመቅደስ አድርጎ እንደሚኖር መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር ‹‹የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ እንደሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን? ማንም የእግዚአብሔርን ቤተመቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፡፡ የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ ቅዱስ ነውና ያውም እናንተ ናችሁ›› ይላል (1ቆሮ.3፡16)፡፡ ይህም ጌታ ኢየሱስ ‹‹በእናንተ ዘንድ ስለሚኖር›› ብሎ ከተናገረው ጋር አብሮ የሚሄድ ነው፡፡ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ የእያንዳንዱን አማኝ ሰውነት (ሥጋ) ቤተመቅደስ አድርጎ እንደሚኖርበት ሲገልጽ ‹‹ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖርው የመንፈስ ቅዱስ ቤተመቅደስ እንደሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ›› ይላል፡፡ ‹‹ሥጋችሁ›› በሚል ጊዜ የእያንዳንዱን አማኝ ሰውነት ያመለክታል፡፡ አማኝ በክቡር የክርስቶስ ደም የተገዛ (የተዋጀ) እንደመሆኑ መጠን ማንነቱ (ሁሉንተናው) የእግዚአብሔር ነው፡፡ ሥጋውም ከእግዚአብሔር የተቀበለው የመንፈስ ቅዱስ ቤተመቅደስ ነው፡፡ ስለሆነም ለቅዱሱ ማነነት የተገባ የቅድስና ሕይወት ሊኖረው ይገባል፡፡

ወልድ በሥጋ ተገልጦ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ ስሙ አማኑኤል ተብሎ መጠራቱን እናውቃሉን፡፡ ይህም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው ማለት ነው፡፡ ስለሆነም በወልድ ሰው መሆን እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆኗል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ወደዚህ ዓለም ሲመጣ ግን በእኛ ዘንድና በውስጣችን ኖሯል፡፡ ስለሆነም በመንፈስ ቅዱስ ወደ ምድር መውረድ እግዚአብሔር በእኛ ውስጥ ሆኗል፡፡ ይህ እንዲህ ከሆነ ደግሞ በጉባኤም ሆነ በየግል ሕይወታችን እግዚአብሔርን እያከበርን ልንኖር ይገባል፡፡ ‹‹አቤቱ እስከረጅም ዘመን ድረስ ለቤትህ ቅደስና ይገባል›› ተብሎ ተጽፏልና፡፡ በ2ቆሮ.6፡16 ላይ አማኞች እግዚአብሔር የሚኖርባቸው ቤተመቅደስ እንደሆኑ ሲናገር ‹‹ለእግዚአብሔር ቤተመቅደስ ከጣፆት ጋር ምን መጋጠም አለው? እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤተመቅደስ ነንና፡- እንዲሁም እግዚአብሔር ተናገረ እንዲህ ሲል፡- በእነርሱ እኖራለሁ በመካከላቸውም እመላለሳለሁ አምላካቸውም እሆናለሁ፡፡ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ›› ይላል፡፡ በዓለም ካለው ርኩሰት ተለይተው የእግዚአብሔር የሆኑት እነዚህ አማኞች የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ እንደመሆናቸው በቅድስና ሊኖሩ እንደሚገባ ተጽፏል፤ በቀጣዩ ምዕራፍ ማለት በ1ቆሮ.7፡1 ላይ ‹‹እንግዲህ ወዳጆች ሆይ የዚህ ተስፋ ቃል ካለን በእግዚአብሔር ፍርሃት ቅድስናን ፍጹም እያደረግን ሥጋንና ነፍስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ›› ተብሎ በአጽንፆት ተነግሮናል፡፡ መንፈስ ቅዱስን ተቀብለን የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ የሆንን ሁላችን ይህን ቃል ልብ ልንለው ይገባናል፡፡ ይህ ሰውነታችን መንፈስ ቅዱስ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ የእርሱ እንጂ የእኛ አይደለም፤ ስለዚህ የእርሱን ቤት በከንቱ ንግግር፣ በረከሱ ሐሳቦችና ተግባሮች ልናሳድፈው አይገባም፡፡ ይልቁን በየጊዜው ራሳችንን በእግዚአብሔር ቃል እያነጻን ቅድስናን ፍጹም ልናደርግ ይገባል፡፡

በመንፈስ ቅዱስ መቀባትና መታተም

“በክርስቶስም ከእናንተ ጋር የሚያጸናንና የቀባን እግዚአብሔር ነው፤ ደግሞም ያተመን የመንፈሱንም መያዣ በልባችን የሰጠን እርሱ ነው፡፡” (2ቆሮ.1፡21-22)

በጌታ በኢየሱስ በእውነት (ከልብ) ያመነ ማንኛውም ሰው የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ እንደሚቀበል ከእግዚአብሔር ቃል የተማርነው እውነት ነው፡፡ አማኙ መንፈስ ቅዱስን በሚቀበል ጊዜም በመንፈስ ቅዱስ ይቀባል፣ በመንፈስ ቅዱስ ይታተማል፡፡ እነዚህን በመንፈስ ቅዱስ የሚከናወኑ ሁለት ነገሮችንም ቀጥሎ እንመለከታለን፡፡

2. በመንፈስ ቅዱስ መቀባት

“በመንፈስ ቅዱስ መቀባት” ለእግዚአብሔር የተለየ መሆንን ወይም መቀደስን የሚያመለክት ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን (በሕጉ ዘመን) ስለመቀባት የተሰጠ ሕግን በዘጸ. ምዕ.29 እና ምዕ. 30 እናገኛለን፡፡ በሕጉም መሠረት የመገናኛው ድንኳንና ሁሉም የመቅደስ ዕቃዎች እንዲሁም በክህነት የሚያገለግሉት አሮንና ልጆቹ ለእግዚአብሔር ይቀደሱ ዘንድ መቀባት ነበረባቸው፡፡ የሚቀቡበትም ቅብዓት ‹‹የተቀደሰ የቅብዓት ዘይት›› ተብሎ የሚጠራ ሲሆን አሠራሩን በተመለከተም በዝርዝር ተጽፎ እናነባለን (ዘጸ.30፡22-33)፡፡

የመገናኛው ድንኳን (የምድረ በዳ መቅደስ) የሕያው እግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ምሳሌ መሆንዋ ይታወቃል (1ጢሞ.3፡16፤ 1ቆሮ.3፡17)፣ አሮንና ልጆቹም የአዲስ ኪዳን ሊቀካህናት የሆነው የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስና የአዲስ ኪዳን ቅዱሳን ካህናት የሆኑት የሁሉም እውነተኛ አማኞች ምሳሌ መሆናቸው (ዕብ.3፡1፤ 1ጴጥ.2፡5) የሚታወቅ ነው፡፡ በክርስቶስ ያመኑና ‹‹ቅዱሳን ካህናት›› የሆኑት አማኞች የሚቀቡበት ቅብዓት እንደብሉይ ኪዳን ዘመን ከወይራ ዘይትና በሕጉ ላይ ከተዘረዘሩት ልዩ ልዩ ቅመሞች ተቀምሞ የሚሠራ ቅብዓት ሳይሆን በኢየሱስ ማመናችንን ተከትሎ የተቀበልነው መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹በመንፈስ ቅዱስ በኃይልም›› የተቀባ መሆኑ ስለተነገረ (ሐዋ.ሥ.10፡38) የዚህ የጸጋው ዘመን ቅብዓት መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ አሮንና ልጆቹ በተቀደሰው የቅብዓት ዘይት ተቀብተው ለክህነት ከመቀደሳቸው (ከመለየታቸው) በፊት የኃጢአት መሥዋዕት የሆነ ወይፈን እንደቀረበላቸው ሁሉ በክርስቶስ ላመኑት ሁሉ ክርስቶስ የኃጢአት መሥዋዕታቸው ነው፡፡ እርሱ ራሱን ስለእነርሱ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበ በመሆኑ የኃጢአታቸው ደመወዝ ተከፍሏልና እነርሱ ለዘላለም የዳኑ ናቸው፡፡ በመሆኑም ለእግዚአብሔር የተቀደሱ ይሆኑ ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ ተቀብተዋል፡፡ ከዚህም የተነሣ ቅዱሳን ካህናት እንዲሆኑ የተቀቡት ሁሉም አማኞች ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኘውን መንፈሳዊ መሥዋዕት በማቅረብ የሚያመልኩ ሕዝብ ሊሆኑ ይገባል፡፡ እግዚአብሔር እነርሱን በመንፈስ ቅዱስ የቀባበት ምክንያት ሌላ ምንም ሳይሆን እርሱን ብቻ እንዳያመልኩና እንዳያገለግሉ ነውና፡፡

“በክርስቶስ ከእናንተ ጋር የሚያጸናንና የቀባን እግዚአብሔር ነው” የሚለው ቃል የመቀባቱን ሥራ ራሱ እግዚአብሔር እንደሚያከናውን የሚያሳይ ነው፡፡ እንደብሉይ ኪዳን ዘመን የመቀባት ሥርዓትንና ሥልጣንን በመስጠት የሃይማኖት መሪዎች ሌሎችን በቅብዓት ዘይት እንዲቀቡ አላደረገም፡፡ ቅብዓቱ መንፈስ ቅዱስ እንደመሆኑ መጠን በዚህ መለኮታዊ ቅብዓት መቀባት የሚችለውም ራሱ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡

በመንፈስ ቅዱስ መቀባት ለተወሰኑ አገልጋዮች ብቻ የሚከናወን ሳይሆን ለሁሉም እውነተኛ አማኞች የሚደረግና ሁሉንም አማኞች ለእግዚአብሔር የሚቀድስ ነው፤ አማኞች በመንፈስ ቅዱስ ከመቀባታቸው የተነሣ የሚያገኙት ዋናው ነገርም እውነትን ከውሸት ለይተው የሚያውቁበትን መንፈሳዊ እውቀት ነው፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ ይህን በተመለከተ ሲጽፍ “እናንተም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋል፤ ሁሉንም ታውቃላችሁ፡፡ እውነትን የምታውቁ ስለሆናችሁ ውሸትም ሁሉ ከእውነት እንዳልሆነ ስለምታውቁ እንጂ እውነትን ስለማታውቁ አልጽፍላችሁም” (1ዮሐ.2፡20-21) ብሏል፡፡ በዚህ ቃል ውስጥ “እናንተም ከቅዱሱ ቅብዓት ተቀብላችኋል” ሲል በአማኞች መካከል ልዩነት ሳይደረግ ሁሉም እውነተኛ አማኞች “የተቀቡ” መሆናቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ የዚህ መገለጫውም ሁሉን ማወቃቸው በተለይም እውነትን ከውሸት ለይተው ማወቃቸው ነው፡፡ በዚያ ዘመን ከመካከላቸው እየወጡ የሐሰት ትምህርትን የሚያስተምሩ የክርስቶስ ተቃዋሚዎች የነበሩ ቢሆንም በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡት አማኞች ግን የእነዚህ ተቃዋሚዎች የሐሰት ትምህርት ከእውነት እንዳልሆነ በቀላሉ ይለዩታል፡፡ ሐዋርያው ይህን በተመለከተ ቀጥሎ ሲናገር “ስለሚያስቷችሁ ሰዎች ይህን ጽፌላችኋለሁ እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅብዓት በእናንተ ይኖራል ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፡፡ ነገር ግን የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ እውነተኛም እንደሆነ ውሽትም እንዳልሆነ እናንተንም እንዳስተማራችሁ በእርሱ ኑሩ” ብሏል (1ዮሐ.2፡26-27)፡፡ አማኞች በመንፈስ ቅዱስ ከመቀባታቸው የተነሣ የሚማሩትና የሚያውቁት እውነት በማንበብም ሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች በመማር በአእምሮአቸው ውስጥ የሚያከማቹት ጥልቅ እውቀት ነው ማለት አይደለም፡፡ እያንዳንዱ እውነተኛ የሆነ አዲስ አማኝም ቢሆን በመንፈስ ቅዱስ የተቀባ በመሆኑ ይህ ጥልቅ የሆነ እውቀት ሳይኖረውም እውነትን ከሐሰት ለይቶ ማወቅ ይችላል፡፡ ስለሆነም ይህ ከእኛም ሆነ ከሌሎች ሰዎች በሆነ ጥረት የሚገኝ እውቀት ሳይሆን መንፈስ ቅዱስ በእያንዳንዱ እውነተኛ አማኝ ውስጥ የሚያኖረው ማስተዋል ነው፡፡ ነፍሳትን በእረኝነት ሥራ በመጠበቅና በመንከባከብ ለሚተጉ ወንድሞች ይህ እንዴት ዕረፍትን የሚሰጥ ነው! ብዙ የሐሰት ትምህርት በበዛበት በዚህ ዘመን ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ ቅባት መታመን እንደምን በእጅጉ አስፈላጊ ነው!

በነፍሳት ላይ ለሚዘሩ ኑፋቄዎችና የሐሰት ትምህርቶች ሁሉ መልስ በመስጠት ብቻ በራስ ችሎታና ጥረት ከመታመን ይልቅ ነፍሳትን ለመንፈስ ቅዱስ መተው ለችግሩ ዋናው መፍትሔ ነው፡፡ በእርግጥ በአስተማሪነት የጸጋ ስጦታ የተገለጡ ወንድሞች ለሚያገለግሏቸው ነፍሳት እግዚአብሔር በቃሉ ያስተማራቸውን እውነት በሐሰተኞች ከሚዘሩ ክፉ ትምህርቶች ለይቶ ማሳየት የአገልግሎታቸው ዋነኛ ገጽታ ነው፡፡ ይህን የሚያደርጉ ሁሉ ሊበረታቱ ይገባቸዋል፡፡ ሐዋርያትም ይህን ያደርጉ ነበርና፡፡ ከመልእክታት መካከል አንዳንዶቹ ለሐሰት ትምህርቶች መልስ ሆነው የተጻፉ ነበሩ፡፡ ስለሆነም አማኞች በትምህርት ነፋስ እንዳይፍገመገሙ የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ሊኖርባቸው ይገባል (ቈላ.3፡16)፡፡ ሆኖም ወደዚህ ደረጃ ያልደረሱ የዋሃንና በቅንነት የተሞሉ እውነተኛ አማኞም ቢሆኑ በተሟላ እውቀት ለሐሰት ትምህርቶች መልስ መስጠት ባይችሉም፣ እነርሱ በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡ ናቸውና “የእውነት መንፈስ” እውነትን ከሐሰት ለይተው እንዲያውቁ በማድረግ እንደሚጠብቃቸው እርግጠኛ ዋስትና ተሰጥቷል፡፡ አንዳንዶች ከመንጋው መካከል የሚወሰዱ ቢኖሩ እነርሱ “ከእኛ ዘንድ ወጡ ዳሩ ግን ከእኛ ወገን አልነበሩም ከእኛ ወገንስ ቢሆኑ ከእኛ ጋር ጸንተው በኖሩ ነበር፤ ነገር ግን ከእኛ ወገን እንዳልሆኑ ይገለጡ ዘንድ ወጡ” በሚለው ቃል የተገለጹት ናቸው (1ዮሐ.2፡19)፡፡ እንዲሁም በጌታ ትምህርት ውስጥ “የሰማዩ አባቴ ያልተከለው ተክል ሁሉ ይነቀላል” ተብለው ተገልጸዋል (ማቴ.15፡13)፤ ስለሆነም እንዲህ ያሉቱ ከመጀመሪያውም ቢሆን በመንፈስቅዱስ ተቀብተዋል ማለት የሚችል አይይደለም፡፡ የተቀቡትን በተመለከተ ግን የእርሱ ቅባት በእነርሱ እንደሚኖርና ሁሉን እንደሚያስተምራቸው የተነገረው ቃል ሁል ጊዜም የጸና ሆኖ ይኖራል (1ዮሐ.2፡26-27)፡፡

3. በመንፈስ ቅዱስ መታተም

በመንፈስ ቅዱስ መቀባት ለእግዚአብሔር መለየት (መቀደስ) እንደሆነ ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ መታተም ደግሞ የእግዚአብሔር መሆን ነው፡፡ ይህም ማለት በመንፈስ ቅዱስ ተቀብተው ለእግዚአብሔር የተለዩ ሁሉ ለዘላለም የእርሱ መሆናቸው ይረጋገጥ ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ ይታተማሉ ማለት ነው፡፡ ማኅተም ያረፈበት የማንኛውም ዕቃ ወይም ሰነድ ባለቤቱ ባለማኅተሙ እንደሆነ ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ የታተመ ማንኛውም አማኝ ባለቤቱ እግዚአብሔር ነው፡፡ አማኙን በማኅተም እያተመ የእኔ ነው የሚ ለው ራሱ እግዚአብሔር ነው እንጂ ከወንጌል ሰባኪዎች ወይም ከቤተክርስቲያን መሪዎች አንዱም አይደለም፤ ማኅተሙም መለኮታዊ ማኅተም የሆነው መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡

ከሁሉ አስቀድሞ እኛ የእግዚአብሔር የሆንበት ዋና መሠረቱ ስለእኛ ቤዛ (ዋጋ) ሆኖ የተከፈለው እና የተዋጀንበት የክርስቶስ ደም ነው፡፡ “በዋጋ ተገዝታችኋልና የራሳችሁ አይደላችሁም” ተብሎ እንደተጻፈ (1ቆሮ.6፡20) በመንፈስ ቅዱስ መታተም ደግሞ በዋጋ ተገዝተን የእግዚአብሔር መሆናችንን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ “በክርስቶስ የሚያጸናንና የቀባን” እግዚአብሔር መሆኑን የነገረንን ያህል፣ ደግሞም “ያተመን የመንፈሱንም መያዣ በልባችን የሰጠን እርሱ ነው” በማለት ይናገራል (2ቆሮ.1፡22)፡፡ በዚህ ቃል ውስጥ ያተመን እግዚአብሔር መሆኑን ብቻ ሳይሆን የመንፈሱን መያዣ የሰጠንም እርሱ መሆኑ ተነግሮናል፡፡ “የመንፈሱ መያዣ” ማለት እግዚአብሔር የእርሱ ስለመሆናችን ለእኛ የሰጠን ማስረጃ ማለት ነው፡፡ በዚህ ምድረበዳ በሆነ ዓለም ስንኖር ጠላት እኛን ከእግዚአብሔር ለመነጠል፣ እምነትን ከመሸርሸር ጀምሮ በተግባርም ከራሱ ጋር እስከማሰለፍ ድረስ ሁሉንም ከንቱ ጥረት ቢያደርግ እኛ የእግዚአብሔር የመሆናችን ማስረጃ በልባችን ያለን ሰዎች ሆነን እንጸናለን፡፡

በመንፈስ ቅዱስ መታተማችን እኛ የእግዚአብሔር መሆናችንን የሚያረጋግጥ የመንፈስ መያዣ ብቻ ሳይሆን ለእግዚአብሔር ያለውን ሁሉ የምንወርስ መሆናችንን የሚያረጋግጥልን የርስታችን መያዣም ነው፡፡ ይህም “እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል ይኸውም የመዳናችሁን ወንጌል ሰምታችሁ ደግሞም በክርስቶስ አምናችሁ በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ፡፡ እርሱም የርስታችን መያዣ ነው፤ ለእግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እስኪዋጅ ድረስ፤ ይህም ለክብሩ ምስጋና ይሆናል” ተብሎ ተነግሯል (ኤፌ.1፡13-14)፤ በዚህ ቃል ውስጥ አማኞች በመንፈስ ቅዱስ ከመታተማቸው በፊት የሚያደርጉት ነገር ቢኖር የእውነትን ቃል ሰምቶ በክርስቶስ ማመን መሆኑ ተገልጿል፡፡ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ በመንፈስቅዱስ ለመታተም የሚያስፈልግ የተለየ አገልግሎት ወይም ልዩ ፕሮግራም ወይም ልዩ ሥርዓት እንደሌለ ከዚህ እንገነዘባለን፡፡ ይህም በክርስቶስ አምነው ሳሉ ባለማወቅ መንፈስ ቅዱስን ፍለጋ በየፕሮግራሙ ለሚንከራተቱ ሁሉ ዕረፍትን የሚሰጥ ቃል ነው፡፡ በዚህ ቃል የልባቸው ዓይን ሲከፈት መንፈስ ቅዱስ በውስጣቸው እንዳለና የእግዚአብሔር ወራሾች አድርጎ እንዳተማቸው ያስተውላሉና፡፡

የእውነትን ቃል ሰምተው በክርስቶስ ያመኑ ሁሉ ከእግዚአብሔር ተወልደው የእግዚአብሔር ልጆች እንደሚሆኑ በቃሉ ውስጥ ተነግሮአል፡፡ “ለፍጥረቱ የበኵራት ዓይነት እንድንሆን በእውነት ቃል አስቦ ወለደን” የሚለው ቃል ይህን የሚሳይ ነው (ያዕ.1፡18)፡፡ እግዚአብሔር እኛን የወለደን ደግሞ ርስትን ሊያወርሰን መሆኑም ተጽፏል፤ “ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ እድፈትም ለሌለበት ለማያልፍም ርስት እንደምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ” (1ጴጥ.1፡3-5) የሚለው ቃል ይህን የሚያሳይ ነው፡፡ ስለዚህ አማኞች የሚወርሱት ርስት የተዘጋጀላቸው የእግዚአብሔር ወራሽ ልጆች ናቸው፡፡ ይህም በመንፈስ ቅዱስ በመታተማቸው የተረጋገጠ ነው፡፡

እግዚአብሔር ለልጆቹ ርስትን ሁሉ የሚያወርሰው ወደ ፊት ሲሆን ያ ርስት አሁን ለእነርሱ የተሰጠው በተስፋ ነው፡፡ ይህም ተስፋቸው የሚፈጸመው እግዚአብሔር በዘመን ፍጻሜ በሰማይና በምድር ያሉትን በክርስቶስ በሚጠቀልል ጊዜ ነው (ኤፌ.1፡10)፤ እግዚአብሔር “ክርስቶስን ሁሉን ወራሸ” አድርጎታል (ዕብ.1፡2)፤ ለእርሱ “ሁሉን ከእግሮቹ በታች አስገዝቶለታል” (ኤፌ.1፡22፤ ዕብ.2፡5-8)፡፡ “አሁን ግን ሁሉ እንደተገዛለት ገና አናይም” (ዕብ.2፡9)፤ ጠላቶቹ የእግሩ መረገጫ እስኪደረጉ ድረስ ወደፊት ይጠብቃል (ዕብ.10፡13)፡፡ ያን ጊዜ በሰማይና በምድር ያሉትን በመጠቅለል ሁሉን ይወርሳል፡፡ አማኞችም የእርሱ እንደመሆናቸው መጠን እርሱ የወረሰው ሁሉ የእነርሱ ይሆናል፡፡

ወደፊት ለእኛ የሚያወርሰን ዓለም በዚህ ዘመን በዚህ ዓለም ገዢ ሥር የሚገኘውን ዓለም ነው፤ ይህም የራሱ የእግዚአብሔር ርስት መሆኑ መዘንጋት የለበትም፤ ጌታ ኢየሱስ ወደፊት ጠላቶቹን ሁሉ የእግሩ መረገጫ በሚያደርግ ጊዜ ለእግዚአብሔር ያለውን ሁሉ ይዋጃል፡፡ ዛሬ እኛን የዋጀን በመስቀል ላይ ራሱን ቤዛ አድርጎ በመስጠት ነው፡፡ ያን ጊዜ ግን ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ያለውን ሁሉ የሚዋጀው በኃይል ነው፡፡ ከዚያም በኃይል የሚዋጀውን ይህን ርስት እኛም ከእርሱ ጋር እንወርሳለን፡፡ ታዲያ ወደፊት እንደምንወርሰው ዛሬ በተስፋ የተነገረንን ይህን ርስት ለመውረሳችን ማረጋገጫው በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ መታተማችን ነው፡፡ ይህ መታተማችንም “የርስታችን መያዣ” ተብሎ የተገለጸውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ከአባቱ፣- ቤትን ወይም መሬትን ወይም ሌላ ንብረትን ወደፊት የሚወርስ ልጅ በማኅተም የተረጋገጠ የዚያ ንብረት ሰነድ በእጁ ከገባ ርስቱን አስቀድሞ በሰነዱ እንደሚይዘው ሁሉ እኛም ለእግዚአብሔር ያለውን ርስት ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ማኅተም በተረጋገጠው የርስታችን መያዣ ይዘነዋል፡፡

ጌታ ያን ርስት የሚዋጀው በኃይል መሆኑን ማለትም ጠላቶቹን የእግሩ መረገጫ አድርጎ መሆኑ ተመልክተናል፡፡ “ለምነኝ አሕዛብን ለርስትህ የምድር ዳርቻን ለግዛትህ እሰጥሃለሁ በብረት በትር ትጠብቃቸዋለህ፣ እንደሸክላ ሠሪ ዕቃም ትቀጠቅጣቸዋለህ” የሚለው ቃል ከዚሁ ሐሳብ ጋር የሚስማማ ነው (መዝ.2፡8-9)፤ ታዲያ ያን ጊዜ ለእግዚአብሔር ያለውን ሁሉ ለመዋጀት በዓለም ሁሉ ላይ ፍርድን ከማድረጉ በፊት የሚዋጀውን ርስት የሚያወርሳቸውን ልጆቹን ወደ ክብር ወደ ላይ ይወስዳቸዋል፤ ይህም ለእነርሱ የቤዛ ቀን ይባላል፡፡ እነርሱ በመንፈስ ቅዱስ መታተማቸውም በዚህ የቤዛ ቀን ከሚመጣው ቁጣ ለመዳናቸው ዋስትናን የሚሰጥ ነው፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን ለእነርሱ የተሰጠው ምክር “ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ” የሚል ነው (ኤፌ.4፡30)፡፡ በኤፌ.4 ውስጥ ከዚህ ቃል በፊትና በኋላ የተነገሩትን ቃላት ስንመለከት መንፈስ ቅዱስ የሚያዝነው በምን በምን እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ከቁ.25 ጀምሮ ያለውን ስናነብ ውሽትን መናገር፣ ኃጢአት ያለበትን ቁጣ መቈጣት፣ ስርቆት፣ ከአፍ የሚወጣ ክፉ ቃል በመንፈስ ቅዱስ ለታተመ ሰው የማይገቡ ናቸው፡፡ ከቁ.31 ጀምሮ ደግሞ “መራርነትና ንዴት፣ ቁጣም፣ ጩኸትም፣ መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ ይላል፡፡ እነዚህ ነገሮች ለቤዛ ቀን የታተምንበትን መንፈስ ቅዱስን የሚያሳዝኑ በመሆናቸው ከእኛ በማስወገድ ሁሉን ወራሽ የሆነውን ጌታ በተስፋ ልንጠባበቀው ይገባል፡፡ ይህን ብናደርግ መንፈስ ቅዱስ ከማዘን ይልቅ ደስ ይሰኛል፡፡

ከጠማማ ትውልድ መዳን


Amharic Bible-|- The Holy Bible [King James Version]