trinity  


4. ከጠማማ ትውልድ መዳን

“በብዙ ሌላ ቃልም መሰከረና። ከዚህ ጠማማ ትውልድ ዳኑ ብሎ መከራቸው። ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ፥ በዚያም ቀን ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስ ተጨመሩ” (የሐ.ሥ.2፡38-40)

የመዳን ወንጌል ተሰብኮለት ኢየሱስን በማመን ወደ መዳን የመጣ ማንኛውም ሰው በክፉ ሰዎች ከተገፋውና በኋላም ከተሰቀለው ከእርሱ ጋር ይተባበራል ወይም አንድ ይሆናል፡፡ ከእርሱ ጋር አንድ በሆነ ቁጥር ደግሞ እርሱን ከጠላችው ዓለም መለየቱ የማይቀር ነው፡፡ ይህም መለየትም ከጠማማው ትውልድ መዳን ተብሎ ተገልጿል፤ ከዚህ በመነሳትም ቃሉ የሚያስተምረንን የመለየት ትምህርት ቀጥሎ እንመለከታለን፡፡

ሐዋርያው ጴጥሮስ ልባቸው ለተነካው ሰዎች ማድረግ ያለባቸውን ነገር በተከታታይ ከነገራቸው በኋላ “በብዙ ሌላ ቃል” እንደመሰከረላቸው በመነሻችን ላይ የጠቀስነው ቃል ያስረዳል፡፡ ሆኖም ያ “ብዙ ሌላ ቃል” የተባለው ምስክርነት በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ አልተጻፈልንም፡፡ ነገር ግን ጴጥሮስ በቃል ከመሰከረው ምስክር በኋላ “ከዚህ ጠማማ ትውልድ ዳኑ” ብሎ የተናገረው ቃል ሳይጻፍ መቅረት ስላልነበረበት መንፈስ ቅዱስ በሉቃስ ብዕር ይህን ወሳኝ ቃል አስቀርቶልናል፡፡ ይህም የሚመለከተው በክርስቶስ ላመኑ ሁሉ ከጠማማው ትውልድ መዳን ማለትም መለየት ምን ያህል አስፈላጊ ነገር እንደሆነ ነው፡፡ በዚህ ስፍራ ላይ ከክፉ ሰዎች “መለየት” የተገለጸው “መዳን” እንደሆነ ተደርጎ ነው፤ ከዚህ “ጠማማ ትውልድ ዳኑ” ማለት፣ የሕይወት ራስ የሆነውን ኢየሱስን በዓመፀኞች እጅ አሳልፎ ከሰጠው እንዲሁም ለንስሐ የሚሆን ፍሬ ከሌለው ትውልድ ተለዩ ማለት ነው፤ ሐዋርያው ጴጥሮስ “ጠማማ ትውልድ” ብሎ የጠራቸው በልብ መነካት ቃሉን እየሰሙ ባሉት ሰዎች ዘሪያ የነበሩት የዚያን ዘመን አይሁድ እንደሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ምክንያቱም ጴጥሮስ ቃሉን እየሰበከ ያለው ለበዓለ ሃምሳ ለተሰበሰቡት አይሁድ መሆኑ ተገልጿልና፡፡ እነዚህም ሰዎች ከሃምሳ ቀን በፊት “ስቀለው ስቀለው” በማለት ክርስቶስን ሰቅለው የገደሉ እና ከዚያ ዓመፅ ጋር የተስማሙ ትውልድ ናቸው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህን ሰዎች “ክፉና አመንዝራ ትውልድ” በማለት ጠርቷቸዋል (ማቴ.12፣39)፤ “ክፉና አመንዝራ” መባላቸውም የጠማማነታቸው አንዱ መገለጫ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ክፉና አመንዝራ ትውልድ ለመባል ያበቃቸው፣ ያድናቸውና ይቤዣቸው ዗ዘንድ የመጣውን መሢሕ እንዲቀበሉት የተሰጣቸውን ሰፊ ዕድል ባለመጠቀም ስለገፉትና ስላልተቀበሉት መሆኑን በተለይ ከማቴዎስ ወንጌል እንገነዘባለን፡፡

ገና ከጅምሩ መጥምቁ ዮሐንስ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” (ማቴ.3፡1) በማለት እየሰበከ ሲመጣ ስለጌታ ስለኢየሱስ ክርስቶስ መስክሮ ነበር (ዮሐ.1፡29፣34)፡፡ ራሱ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የመስበክ እና የማስተማር አገልግሎቱን የጀመረው “መንግሥተ-ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” በማለት ነበር፡፡ የሰማይ አምላክ በመካከላቸው ስለሚገልጣትና በምድር ላይ ስለሚመሠርታት ስለዚህች መንግሥት የሰማው ያ ትውልድ ወደዚህች መንግሥት ለመግባት የቀረበለት ጥሪ “ንስሐ ግቡ” የሚል ነበር፡፡ ሆኖም ያ ትውልድ ለዚህ የንስሐ ጥሪ አዎንታዊ ምላሸ ከመስጠት ይልቅ በተቃራኒ መንገድ ሲሄድ እንመለከታለን፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥተ ሰማያት ምን እንደምትመስልና የዚያች መንግሥት መርሆዎች ምን እንደሆነ በቅድሚያ ነገራቸው፤ ይህም ከማቴ.5-7 በሚገኘው በተራራው ስብከቱ ውስጥ የገለጠው ነው፡፡ አገልግሎቱና ትምህርቱ ሁሉ ከእግዚአብሔር እንደሆኑ የሚያረጋግጡ ታምራትና ምልክቶችንም በፊታቸው በተከታታይ እንዳደረገ ከማቴ.8-9 እናነባለን፤ “እነርሱ ግን በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል” አሉ እንጂ አላመኑም ነበር፡፡ “አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ” በተባለው መሠረትም (1ቆሮ.1፡22) ብዙ ጊዜ በተደጋጋሚ ምልክትን እንዲያሳያቸው ይጠይቁት ነበር እንጂ ካዩት ምልክት የተነሣ በእርሱ አያምኑም ነበር፡፡ ዮሐንስ በወንጌሉ ይህን ሲገልጥ “ነገር ግን ይህን ያህል ምልክት በፊታቸው ምንም ቢያደርግ ነቢዩ ኢሳይያስ፡- ጌታ ሆይ ማን ምስክርነታችንን አመነ? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገለጠ? ብሎ የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ በእርሱ አላመኑም” ብሏል (ዮሐ.12፡37-38)፤ ማርቆስም በወንጌሉ ላይ ጌታ ስለአለማመናቸው እንደተደነቀ ጽፏል (ማር.6፡6)፤ አንዳንዶች ደግሞ ያመኑ ቢመስሉም ጌታ ግን በልባቸው ያለውን ያውቅ ነበርና አይተማመናቸውም ነበር፡፡ በእርግጥም ያ ትውልድ ጠማማ ትውልድ ነበር፡፡ ጌታ ኢየሱስ ራሱ የዚያን ትውልድ ጠማማነት ሲገልጽ “ነገር ግን ይህን ትውልድ በምን እመስለዋለሁ? ... ዮሐንስ ሳይበላና ሳይጠጣ መጣ፥ እነርሱም፡- ጋኔን አለበት አለበት። የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፥ እነርሱም፡- እነሆ፥ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ፥ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ ይለታል” (ማቴ.11፡16-19) በማለት ተናግሯል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ በቀጥታ በሚያስተምረው ነገር ያን ትውልድ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በንስሐ ከመጥራቱም ሌላ ደቀመዛሙርቱን ልኮላቸው ነበር፡፡ በቅድሚያ 12ቱን በሌላ ጊዜም 70ዎቹን ሁለት ሁለት እያደረገ “መንግሥተ ሰማያት (የእግዚአብሔር መንግሥት) ቀርባለች” ብለው እንዲሰብኩ ልኮአቸው ነበር (ማቴ.10፡7፣ ለቃ.10፡9)፡፡ ሲልካቸውም በደዌ እና በአጋንንት ላይ ሥልጣን ሰጥቶ ስለነበር መልእክታቸውን ላለመቀበል ለምልክት ፈላጊዎቹ አይሁድ ምክንያት አልነበራቸውም፡፡ እንዲህም ሆኖ በእርሱ በመሢሑ አላመኑም፡፡ ከዚያም በየመንደሮቻቸውና በየምኩራባቸው ድውያንን እየፈወሰ አጋንንትን እያወጣ ተጨማሪ ምልክቶችን በማድረግ ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእነርሱ የተገለጠ ሰው መሆኑን ቢያሳያቸውም እነርሱ ግን እንዴት እንደሚያጠፉት ይማከሩ ነበር (ማቴ.12፡14)፡፡ ቀደም ሲል እንዳሉትም ይህ በብዔል ዜቡል በአጋንንት አለቃ ካልሆነ በቀር አጋንንትን አያወጣም” ይሉ ነበር (ማቴ.12፡24)፡፡ ይህም የእግዚአብሔርን መንፈስ መሳደብ በመሆኑ የመጨረሻው የክፋት ደረጃ ላይ አደረሳቸው፤ ሊመለሱ ወደማይችሉበት ክፋት ውስጥ አስገባቸው፡፡ ታዲያ እነዚህ ክፉ ሰዎች ከዚህ ሁሉ በኋላ ወደ ጌታ መጡና “መምህር ሆይ ከአንተ ምልክትን እንድናይ እንወዳለን” አሉት፤ እርሱ ግን መልሶ “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል፤ ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም” አላቸው (ማቴ.12፡38-39)፡፡ እንዲሁም ከእርሱ የከፉ ሰባት አጋንንትን ይዞ ሰይጣን ተመልሶ እንደገባበት ሰው አድርጎ ያን ክፉ ትውልድ ገልጾታል፤ በመሆኑም በዚህ ደረጃ የአጋንንት ማደሪያ የሰይጣን ቤት የሆነ ትውልድ ክፉ ወይም ጠማማ ትውልድ ሊባል ይችላል ማለት ነው፡፡ ከዚህ ክፉ ትውልድም መዳን (መለየት) በእጅጉ ተገቢ ነው፡፡ በመሆኑም ጌታ ኢየሱስ ራሱ በድጋሚ ከሰማይ ምልክትን እንዲያሳያቸው በጠየቁት ጊዜ በፊት እንዳደረገው “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ምልከት አይሰጠውም” የሚል መልስ ከሰጣቸው በኋላ፣ ትቶአቸው እንደሄደ እናነባለን (ማቴ.16፡4)፡፡ ይህም ጌታ ኢየሱስ ከዚያ ትውልድ ራሱን እንደለየ የሚያሳይ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ደቀመዛሙርቱንም ከዚያ ክፉ ትውልድ በይፋ መለየት ሲጀምር እንመለከታለን፤ በመጀመሪያ “ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁና ተጠበቁ” (ማቴ.16፡6) በማለት ከክፉ ትምህርታቸው እንዲለዩ ከነገራቸው በኋላ ቤተክርስቲያንን በዓለት ላይ እንደሚሠራ ይነግራቸዋል፡፡ ያም ማለት የእርሱ የሆኑት ደቀመዛሙርት ከአይሁድ ተለይተው እርሱ በሚሠራት ቤተክርስቲያን ውስጥ ስፍራቸውን እንዲይዙ የሚገልጽ ነው፡፡

ያ ክፉና አመንዝራ ትውልድ የጌታን ትምህርትና አገልግሎት ያልተቀበለ ብቻ ሳይሆን ተቃውሞውን እስከ መጨረሻው ድረስ አጠናክሮ እርሱን በመስቀል ሞት ገድሎ እግዚአብሔር የሰጣቸውን መሢሕ አለመቀበሉን በተግባር ያረጋገጠ ትውልድ ነው፡፡ ዮሐንስ ጠቅለል ባለ መልኩ እስራኤል መሢሓቸውን አለመቀበላቸውን ሲገልጽ “የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፤ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም” በማለት ገልጾታል (ዮሐ.1፡11)፡፡ ይህም እግዚአብሔር የሚያድናቸውን መሢሕ የሰጣቸው በቅድሚያ እንደ ሕዝብ እንዲቀበሉት እንደነበር ያመለክታል፡፡ ነገር ግን ሕዝቡ በሃይማኖትና በሲቪል መሪዎቻቸው በኩል እርሱን እንዳልተቀበሉት በይፋ አሳዩ፤ ይህንንም “ይህ በላያችን ሊነግሥ አንወድም” (ለቃ.19፡14)፣ ስቀለው ስቀለው አስወግደው ከቄሣር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም” (ዮሐ.19፡6፣15)፣ “ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን” (ማቴ.27፡25) በማለት ገለጹ፡፡ በዚህም ጠማማ ትውልድነታቸውን በተግባራዊ መንገድ አረጋገጡ፡፡ ይሁንና ከዚህ ትውልድ መካከል በየግላቸው መሢሕን የተቀበሉ ጥቂት ቅሬታዎች ነበሩ፡፡ እነዚህ ሰዎች ከአፍኣዊ ተከታዮችም ተለይተው ከተጣሩ በኋላ ቁጥራቸው 120 ብቻ ነበር፡፡ እነርሱም ከዚያ ክርስቶስን ካልተቀበለው ሕዝብ ርቀው በመቅደስ ሳይሆን በሰገነቱ (በደርቡ) ቤት ተሰብስበው ሳለ የበዓለ ሃምሳ ዕለት መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፡፡ በዚህም እግዚአብሔር ከዚያ ጠማማ ትውልድ ተለይተው ከክርስቶስ ጋር ለሆኑት መለኮታዊ እውቅናን ሰጠ፡፡ ቤተክርስቲያንም የዚያን ዕለት ተጀመረች፡፡

“ቤተክርስቲያን” የሚለው ቃል በግሪኩ “ኤክሌሲያ” የሚለው ቃል ሲሆን ኤክሌስያ ማለትም ተጠርቶ የወጣ ጉባኤ ማለት ነው፡፡ ይህም በወንጌል የተጠሩ ሰዎች ከነበሩበት ከማያምነው ዓለም መውጣታቸውን ወይም መለየታቸውን የሚያመለክት ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ከአይሁድና ከአሕዛብ (ከግሪክ ሰዎች) በጸጋው ወንጌል የተጠሩት የተለዩ ወገኖች (አማኞች) የተሰባሰቡባት ማኅበር ናት፡፡ ስለሆነም በወንጌል ስብከት ልባቸው ተነክቶ በክርስቶስ የሚያምኑ አማኞች “ከጠማማው ትውልድ ዳኑ” የሚለው ያው የቀደመው ምክር ዛሬም ይቀርብላቸዋል፡፡ በተለይም አይሁዳዊ ጠባይ ባለው የዚህ ዓለም ሃይማኖታዊ አኗኗር ውስጥ የነበሩ ሰዎች ይህን ምክር ልብ ብለው ሊሰሙት ይገባል፡፡ ምንም እንኳ የዚህ ዘመን ትውልድ በሥጋ አይሁድ ባይሆንም ወደ አይሁዳዊነት ካፈገፈገ “ለራሳቸው የእግዚአብሔርን ልጅ ይሰቅሉታልና ያዋርዱትማልና” እንደተባሉት ሰዎች ይሆናል (ዕብ.6፡6)፡፡ እነዚህም መጀመሪያ ከበራላቸውና መንፈሳዊ ነገሮችን ከቀመሱ በኋላ የካዱ በመሆናቸው እነርሱን ለንስሐ ማደስ የማይቻል መሆኑ ተገልጿል፡፡ ያም ማለት “ጠማማ” ወይም “ክፉ” ትውልድ ወደ መሆን ደረጃ ደርሰዋል ማለት ነው፡፡ ከእንደ እነዚህ ዓይነት ትውልድ መካከል የነበረና በጸጋ ወንጌል ተጠርቶ በክርስቶስ ያመነ ማንኛውም የዳነ ሰው ከዚህ ትውልድ መለየት ይገባዋል፡፡ ከዚያም በክርስቶስ ዓለትነት ላይ በተመሠረተች ቤተክርስቲያን ውስጥ የእርሱ ከሆኑት ጋር ኅብረት ሊያደርግ ይገባዋል፡፡ በዚህም ከዚያ ክፉ ትውልድ ላይ ከሚመጣ ቁጣ የዳነ ይሆናል፡፡

መትጋት


Amharic Bible-|- The Holy Bible [King James Version]