trinity  


2. ነቢያት

በኤፌ.2፡20 «በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል» ተብሎ ስለተጻፈ እንደ ሐዋርያት ሁሉ ነቢያትም ከአምስቱ ስጦታዎች መካከል የመሠረት ስጦታዎች መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ ነቢያት ሲባልም ትንቢት የሚናገሩ የእግዚአብሔር መልእክተኞች ናቸው፤ ስለሆነም እዚህ ላይ ስጦታዎቹ ራሳቸው ነቢያቱ እንደሆኑ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ለጽሑፋችን መነሻ ባደረግነው በኤፌ.4፡11 ላይም «እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት ሌሎቹም ነቢያት ... እንዲሆኑ ሰጠ» ተብሎ ሲነገር ሰዎቹ ራሳቸው ስጦታ ሆነው እንደተሰጡ የሚያሳይ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ በሮሜ12፡6 ላይ «እንደተሰጠንም ጸጋ ልዩ ልዩ ስጦታ አለን፤ ትንቢት ቢሆን እንደ እምነታችን መጠን ትንቢት እንናገር ...» የሚለውና በ1ቆሮ12፡10 ላይ «ለአንዱም ትንቢትን መናገር ... ይሰጠዋል» የሚለው ነቢያቱ ለቤተክርስቲያን መሰጠታቸውን ሳይሆን ትንቢት የመናገር ስጦታ ከአማኞች መካከል ለአንዳንዶቹ መሰጠቱን ያመለክታል፡፡

በብሉይ ኪዳን ዘመን እግዚአብሔር ማናቸውንም አሳቡን ለሰው ይገልጥ የነበረው በነቢያት በኩል ነበር፡፡ ጌታ ኢየሱስ በሕጻንነቱ ወደ ቤተመቅደስ በተወሰደ ጊዜ የኢየሩሳሌምን ቤዛ ለሚጠባበቁ ስለእርሱ ትናገር የነበረችው ነቢይት ሐና እና «ከነቢይ የሚበልጠው» ተብሎ የተነገረለት (ማቴ.11፡9) መጥምቁ ዮሐንስ ጌታ ከተወለደ በኋላ የነበሩ ነቢያት ቢሆኑም የብሉይ ኪዳን ነቢያት ናቸው፤ ምክንያቱም «ነቢያት ሁሉና ሕጉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናገሩ፤» የቀደሙት የብሉይ ኪዳን ነቢያት ዘመን እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ድረስ መሆኑ በግልጽ ተነግሮናልና ነው (ማቴ.11፡13)፡፡ ሆኖም የእግዚአብሔር ልጅ በሥጋ በተገለጠባቸው ወራትና ዓመታት በምድር ሲመላለስ ሳለ የአባቱን ፈቃድና የልብ ምክር ገልጧል፡፡ እርሱ በዘዳግ.18፡18 ላይ «ከወንድሞቻቸው መካከል እንደ አንተ ያለ ነቢይ አስነሣላቸዋለሁ፤ ቃሌንም በአፉ አደርጋለሁ፤ ያዘዝሁትንም ቃል ሁሉ ይነግራቸዋል፤ በስሜም የሚናገረውን ቃሌን የማይሰማውን ሰው እኔ እበቀልለታለሁ» ተብሎ የተነገረለት ነቢይ ነው (የሐዋ.ሥ.3፡22)፡፡ በመሆኑም በያዘው የነቢይነት ስፍራ ምክንያት «እኔ ከራሴ አልተናገርሁምና ነገር ግን የላከኝ አብ እርሱ የምለውን የምናገረውንም ትእዛዝ ሰጠኝ፡፡ ትእዛዙም የዘላለም ሕይወት እንደሆነች አውቃለሁ፤ ስለዚህ እኔ የምናገረውን አብ እንደነገረኝ እንዲሁ እናገራለሁ» ለማለት ተችሎታል (ዮሐ.12፡49-50)፡፡ ኢየሱስ ነቢይነቱ በሰውነቱ የተገለጠ አገልግሎቱ ቢሆንም እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ ስለሆነ በእርሱ ነቢይነት የተገለጠው ቃል የቀደሙት ነቢያት ከተናገሩት ሁሉ የበለጠና ሁሉን ወደ ፍጻሜ ያመጣ ቃል ነበር፤ መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ሲያስረዳ «ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጐዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን» ይላል (ዕብ.1፡1-2)፡፡

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ በእርሱ የተገለጠውን ቃል ወደ ዓለም ሁሉ የላከው በሐዋርያት በኩል ነበር፡፡ እርሱ «የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፤ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም፡፡ ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል» ብሎ በተናገረው መሠረት ኢየሱስ በምድር ከእነርሱ ጋር ሳለ ያልነገራቸውን መንፈስ ቅዱስ በወረደ (በመጣ) ጊዜ ሁሉን እንደነገራቸው እንገነዘባለን (ዮሐ.16፡12-13)፡፡ ሐዋርያትም ከጌታ ኢየሱስ በቀጥታ የተማሩትንና እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ የገለጠላቸውን የእግዚአብሔር ቃል በአይሁድም በአሕዛብም መካከል ያስተምሩ ነበር፤ ይሁንና ከሐዋርያት ጋር ጐን ለጐን የእግዚአብሔርን አሳብ ይገልጹ ዘንድ ከጌታ የተሰጡ ነቢያትም ነበሩ፤ እነዚህም የአዲስ ኪዳን ነቢያት ናቸው፤ ብዙ ጊዜ ከሐዋርያት ጋር አብረው የሚጠሩት ነቢያት የአዲስ ኪዳን ነቢያት ናቸው እንጂ የብሉይ ኪዳን ነቢያት አይደሉም፡፡ በሐዋርያት ዘመን የአዲስ ኪዳን መገለጥ ገና ባለመጠናቀቁና የአዲስ ኪዳን መጻሕፍትም ገና እየተጻፉ ስለነበር እግዚአብሔር ለሰው ያለውን ፈቃድና አሳብ በእነዚህ ነቢያት በኩል ይናገር ነበር፡፡

በትንቢተ ኢዩኤል ምዕ.2 ቊ.28-29 «ከዚህም በኋላ እንዲህ ይሆናል፤ መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈስሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልምን ያልማሉ፤ ጐበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፤ ደግሞም በዚያ ወራት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎች ላይ መንፈሴን አፈስሳለሁ፡፡» የሚል ትንቢትን እናነባለን፡፡ ይህንንም ጴጥሮስ በበዓለ ሃምሳ ስለ ክርስቶስ በሰበከ ዕለት መንፈስ ቅዱስ መውረዱን በተመለከተ ለማስረዳት ጠቅሶታል (የሐ.ሥ.2፡16-21)፡፡ ይህ ትንቢት እስራኤልን በተመለከተ በቀጥታ የሚፈጸምበት ጊዜ ወደፊት ሲሆን ሐሳቡ ግን በቤተክርስቲያን ጅማሬ ላይ የነበረውን የነቢያት አገልግሎት ጠባይም ለመረዳት ያስችለናል፡፡ በእርግጥም መንፈስ ቅዱስ በበዓለ ሃምሳ ከወረደ በኋላ ወንዶችና ሴቶች የሆኑ የጌታ ባሪያዎች በየስፍራው ትንቢት በመናገር ያገለግሉ ነበር፡፡ ለምሳሌ በኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያን ነቢያት እንደነበሩ «በዚያም ወራት ነቢያት ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ ወረዱ» ከሚለው ቃል እንረዳለን (የሐ.ሥ.11፡27)፤ ከእነርሱም አንዱ አጋቦስ የተባለው ነቢይ ነበር (ቊ.28)፡፡ እነዚህ ነቢያት በርናባስና ጳውሎስ ለአንድ ዓመት ያህል ወዳስተማሩባት ወደ አንጾኪያ መውረዳቸውም በዚያ ያለውን አገልግሎት በተሰጣቸው ጸጋ ለማገዝ እንደሆነ መገንዘብ እንችላለን፡፡ እንደዚሁም በዚያው በአንጾኪያም ነቢያት እንደነበሩ መጽሐፍ ቅዱስ ሲያስረዳ «በአንጾኪያ ባለችው ቤተክርስቲያን ነቢያትና መምህራን ነበሩ» በማለት ይናገራል (የሐ.ሥ.13፡1)፡፡ በቂሣርያም የወንጌላዊው የፊልጶስ ልጆች የሆኑና ትንቢትን የሚናገሩ አራት ደናግል ሴቶች ልጆች ነበሩ (የሐ.ሥ.21፡8-9)፤ በቆሮንቶስም እንዲሁ «ነቢያት» ተብለው የተጠሩ ሰዎች እንደነበሩ ግልጽ ነው (1ቆሮ.14፡29)፡፡

የነቢያት አገልግሎት

የአዲስ ኪዳን ነቢያት የነበራቸው የትንቢት አገልግሎት ሁለት ዓይነት ነበር፡፡ ይኸውም፡-

  1. 1. የወደፊት ነገሮችን መናገር

እግዚአብሔር ወሳኝ በሆኑ ታላላቅ ጉዳዮች ላይ ወደፊት ምን እንደሚሆን ለነቢያት ሲገልጥላቸው ክስተቱን፣ ቦታውንና፣ ትንቢቱ የሚፈጸምባቸውን ሰዎች በመጥቀስ ትንቢትን ይናገሩ ነበር፤ የዚህ ዓይነቱን ትንቢት በመናገር የታወቀው የአዲስ ኪዳን ነቢይ አጋቦስ ነበር፡፡ በሐ.ሥ.11፡27-28 ላይ «በዚያም ወራት ነቢያት ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ ወረዱ፤ ከእነርሱም አጋቦስ የሚሉት አንድ ሰው ተነሥቶ በዓለም ሁሉ ታላቅ ራብ ሊሆን እንዳለው በመንፈስ አመለከተ፤ ይህም በቀላውዴዎስ ቄሣር ዘመን ሆነ» የሚል ቃልን እናነባለን፡፡ እዚህ ላይ አጋቦስ በመንፈስ ሲያመለክት የምናየው ትንቢት ዓለም አቀፍ ረሃብን የሚመለከት ነበር፤ ይህ በመንፈስ የተገለጠውና ከመሆኑ አስቀድሞ የተነገረው ትንቢት የክርስትናን እውነተኝነት በመላው ዓለም ፊት የሚያረጋግጥ ነበር፤ እግዚአብሔርም እንዲህ ያለውን አለም አቀፍ ጉዳይ ከክርስቲያኖች መካከል ለሆኑት ነቢያቱ መግለጡ እርሱ እውቅና የሚሰጠው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ የተሰበከውንና በሐዋርያትም አማካኝነት በየስፍራው እየተሰበከ የነበረውን የአዲስ ኪዳን እምነት ማለትም ክርስትናን እንደሆነ በዚህች ዓለም ፊት አረጋግጧል፤ ያ በትንቢት የተነገረውም ዓለም አቀፍ ረሃብ ቀላውዴዎስ ቄሣር በተባለው የሮማ ገዢ (ንጉሥ) ዘመን መፈጸሙ የትንቢቱንም ሆነ የተናጋሪውን እውነተኝነት አረጋግጧል፡፡

እንደዚሁም አጋቦስ ያረገው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ልዩ ሐዋርያ አድርጎ ያስነሣውን ሐዋርያው ጳውሎስን የሚመለከት ትንቢትም ተናግሯል፤ ይህን በተመለከተ የተጻፈው ቃልም «... አያሌ ቀንም ተቀምጠን ሳለን ነቢይ የነበረ አጋቦስ የሚሉት አንድ ሰው ከይሁዳ ወረደ፡፡ ወደ እኛም መጣና የጳውሎስን መታጠቂያ ወስዶ የገዛ እጁንና እግሩን አስሮ «እንዲሁ መንፈስ ቅዱስ ይህ መታጠቂያ ያለውን ሰው አይሁድ በኢየሩሳሌም እንደዚህ ያስሩታል በአሕዛብም እጅ አሳልፈው ይሰጡታል ይላል አለ» በማለት ይናገራል (የሐ.ሥ.21፡10-11)፡፡ ጌታ ኢየሱስ ጳውሎስን «ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነው» ብሎ ከመጥራቱም በላይ «ስለ ስሜ ስንት መከራ ሊቀበል እንዲያስፈልገው እኔ አመለክተዋለሁና» በማለት ስለእርሱ ተናግሮአል (የሐዋ.ሥራ9፡15-16)፡፡ ስለሆነም ለጌታ ልዩ የተመረጠ መሣሪያ (ዕቃ) ስለነበረው ስለዚህ ሐዋርያ መታሰር መንፈስ ቅዱስ በነቢዩ በአጋቦስ የተናገረውን ትንቢት ሊገልጥ ቻለ፡፡ እንዲህ ካሉ ዐበይት ጉዳዮች ውጭ የእያንዳንዱን ክርስቲያን የሥራ፣ የትዳር ጉዳይ፣ ወይም የወደፊት ዕድልን የሚመለከት ትንቢት በእግዚአብሔር ስም ተነግሮ አያውቅም፤ በአጠቃላይ ታሪክና ዘመን ስፍራም የማይገድበውን ሥራ ሊሠሩ ጌታ በዓለም ላለች ቤተክርስቲያን የሚያስነሣቸውን የተመረጡ ሰዎችንና ባጠቃላይ ዓለምን ወይም ሕዝቡን የሚመለከት ጉዳይ ካልሆነ በቀር የእያንዳንዱን ግለሰብ የወደፊት ታሪክ ለመናገር እግዚአብሔር ነቢያትን አስነሥቶ አያውቅም፡፡ ስለሆነም ይህንን የሚያደርጉ ሰዎችም ቢሆኑ ራሳቸውን እየመረመሩ ንስሐ በመግባት እግዚአብሔር በቃሉ ወዳስቀመጠው እውነት ሊመለሱ ይገባቸዋል፡፡

  1. 2. የሚያንጽ ቃልን መናገር

የአዲስ ኪዳን ነቢያት አስፈላጊ በሚሆን ጊዜ አንድ የተለየ ጉዳይን በተመለከተ እግዚአብሔር የሚገልጥላቸውን የወደፊት ነገር የሚናገሩ ከመሆናቸውም ሌላ የሚያንጽ ቃልን በመናገር ያገለግሉ ነበር፡፡ እንዲያውም የነቢያት መደበኛ አገልግሎታቸው ለማነጽ የሚሆን ቃልን ለሰዎች መናገር ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ነቢያት በማኅበር የነበራቸው አገልግሎት የዚህ ዓይነቱ ትንቢት ነበር፡፡ የቆሮንቶስ አማኞች «ፍቅርን ተከታተሉ መንፈሳዊ ስጦታንም ይልቁንም ትንቢት መናገርን በብርቱ ፈልጉ» የተባሉት የሚያንጽና የሚመክር የሚያጽናናም ቃል ማግኘት እንዲችሉ ነው (1ቆሮ.14፡1)፡፡ በልሳን ከመናገር ይልቅ ትንቢት መናገር የበለጠበት ምክንያትም ይኸው ነው፤ «በልሳን የሚናገርስ ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰው አይናገርም፤ የሚያስተውለው የለምና፤ በመንፈስ ግን ምስጢርን ይናገራል፡፡ ትንቢትን የሚናገር ግን ለማነጽና ለመምከር ለማጽናናትም ለሰው ይናገራል፡፡ በልሳን የሚናገር ራሱን ያንጻል፤ ትንቢትን የሚናገር ግን ማኅበሩን ያንጻል፤ ሁላችሁ በልሳኖች ልትናገሩ እወድ ነበር፤ ትንቢትን ልትናገሩ ግን ከዚህ ይልቅ እወዳለሁ፤ ማኅበሩ ይታነጽ ዘንድ ንግግሩን ባይተረጉም በልሳኖች ከሚናገር ይልቅ ትንቢት የሚናገር ይበልጣል፡፡» ተብሎ በተጻፈው መሠረት ነቢያት ማኅበርን የሚያንጽ ቃል የሚናገሩበት አገልግሎት ነበራቸው (1ቆሮ.14፡2-5)፤ በዚህ ዓይነት ወደ ማኅበር የሚመጣው ቃል ከማነጽ ጋር የመምከርና የማጽናናትም ሥራ ይሠራል፡፡

የዚህ ዓይነቱ ትንቢት በመደበኛ ሁኔታ የሚመጣው ለአማኞች ቢሆንም በዚያ ስፍራ ግን ድንገት የማያምን ሰው ቢገኝ እርሱንም የሚጠቅም ሆኖ ይሠራል፡፡ ይህን በተመለከተም «እንግዲህ ማኅበር ሁሉ አብረው ቢሰበሰቡ ሁሉም በልሳኖች ቢናገሩና ያልተማሩ ወይም የማያምኑ ሰዎች ቢገቡ አብደዋል አይሉምን? ሁሉ ትንቢት ቢናገሩ ግን የማያምን ወይም ያልተማረ ሰው ቢገባ በሁሉ ይወቀሳል በሁሉም ይመረመራል በልቡም የተሰወረ ይገለጣል፤ እንዲሁም እግዚአብሔር በእውነት በመካከላቸው ነው ብሎ እየተናገረ በፊቱ ወድቆ ይሰግዳል» ተብሎ የተጻፈው ቃል ያስረዳል (1ቆሮ.14፡23-25)፤ ይህ በማኅበር ከተሰበሰቡ ሰዎች መካከል አንድን የሚያምን ሰው ለይቶ በመጠቆም «እንዲህ ያለ የተሰወረ ነገር በልብህ ውስጥ አለ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር» በማለት የሚነገር ትንቢት አይደለም፤ ነገር ግን ያ ሰው ለጉባኤ ሁሉ የቀረበውን የሚያንጽ ቃል በሚሰማ ጊዜ ግን መንፈስ ቅዱስ በዚያ ቃል የእርሱን ማንነት ገልጦ ለራሱ ያሳየዋል፡፡ ትንቢታዊ ቃሉን የተናገረው ወንድም የተናገረው ቃል በማን ልብ ውስጥ ምን የተሰወረ ነገር እንደተገለጠ ላያውቅ ይችላል፤ ሆኖም በዕብ.4፡12 ላይ «የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፤ የሚሠራም ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፤ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፤ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል» ተብሎ እንደተጻፈ በመንፈስ ቅዱስ ቊጥጥር ሥር ሆኖ የሚነገር የእግዚአብሔር ቃል የተሰወረ ማንነትን ይመረምራል (ዕብ4፡12)፤ ወደ ንስሐም ይመራል፡፡

በሐዋርያት ዘመን በአማኞች መካካል አንዳንድ የስህተት ትምህርትና የምግባር ችግሮች በሚከሰቱበት ወቅት ነቢያት በምክር ቃል አማኞችን ያበረታቱ ነበር፤ የይሁዳና የሲላስ የነቢይነት አገልግሎት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጠው በዚህ ዓይነት ነው፤ በሐ.ሥ.15፡32 ላይ «ይሁዳና ሲላስም ደግሞ ነቢያት ነበሩና ወንድሞችን በብዙ ቃል መክረው አጸኑአቸው» ተብሎ ስለእነርሱ የተጻፈው ቃል እንደሚያስረዳው የይሁዳና የሲላስ የነቢያትነታቸው አገልግሎት ወንድሞችን በብዙ ቃል መክሮ ማጽናት ነበር፡፡ ይህንንም ያደረጉት ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ መጥተው ነው፤ ቀደም ሲል «ካልተገረዛችሁ ትድኑ ዘንድ አትችሉም» በሚለው የሐሰት ትምህርት ምክንያት በአንጾኪያ ቤተክርስቲያን ባሉ አማኞች ዘንድ ተፈጥሮ የነበረው ክርክርና ጥል በኢየሩሳሌም በተደረገው ጉባዔ መፍትሔ ቢያገኝም በነገሩ መንፈሳዊ ሁኔታቸው የተናጋባቸውን አማኞች ለማበረታታትና ለማጽናት የቃል አገልግሎት ያስፈልግ ነበር፤ ስለሆነም በብዙ ቃል መክረው አጸኗቸው፡፡

አማኞች ለመተናነጽ በሚሰበሰቡ ጊዜ ትንቢትን በብርቱ እንዲፈልጉ በታዘዘበት በ1ቆሮ.14 ውስጥ ነቢያቱ እንዴት መናገር እንዳለባቸው የተደነገገ ሥርዓትም ነበር፡፡ በቊ.29 ላይ «ነቢያትም ሁለት ወይም ሦስት ሆነው ይናገሩ፤ ሌሎችም ይለዩአቸው» ይላል፡፡ በዚህም ትንቢትን መናገር ያላቸው ነቢያት ቊጥራቸው ሁለት ወይም ሦስት ተብሎ ተወስኗል፤ ሌሎች ሊለዩአቸው እንደሚገባም ተነግሯል፤ ይህም ማለት የተናገሩበት መንፈስም ሆነ የተናገሩት ቃል ከእግዚአብሔር ስለመሆኑ በእግዚአብሔር ቃል መፈተሽ አለበት ማለት ነው፤ ምክንያቱም ሐሰተኞች ነቢያትም በሕዝቡ መካከል ገብተው ዕድሉን በመጠቀም ሊናገሩ የሚችሉበት አጋጣሚ ስለሚኖር ሌሎች ይለዩአቸው ተባለ፤ ይህም የእውነትንና የስህተትን መንፈስ ለይቶ በማወቅ ከስህተት መንፈስ ለመጠበቅ ለእውነት መንፈስ ለመታዘዝ ያስችላል (1ዮሐ.4፡1-6)፡፡ እንደዚሁም ትንቢታዊ ቃል በሚነገርበት ጊዜ ተራ በመጠበቅ ሁከት በሌለበት መንገድ ሊሆን እንደሚገባም ተደንግጓል፡፡ ከቊ.30ን «በዚያ ለሚቀመጥ ለሌላ ግን አንድ ነገር ቢገለጥለት ፊተኛው ዝም ይበል፡፡ ሁሉ እንዲማሩ ሁሉም እንዲመከሩ ሁላችሁ በእያንዳንዳችሁ ትንቢት ልትናገሩ ትችላላችሁ፡፡ የነቢያት መናፍስት ለነቢያት ይገዛሉ፡፡ እግዚአብሔርስ የሰላም አምላክ ነው እንጂ የሁከት አምላክ አይደለምና» ይላል፡፡ በዚህ ክፍል እንደተገለጠው የእግዚአብሔር ቃል በጉባዔ መካከል ሲገለጥ በመደማመጥና ተራ በመጠበቅ ሊነገር የሚገባ መሆኑን እንገነዘባለን፤ የሚያንጸው ቃል በሚነገርበት ጊዜ አንዱ ሲናገር ሌላው ዝም እያለ ሊሆን ይገባል፡፡ «ሁላችሁ በእያንዳንዳችሁ ትንቢት ልትናገሩ ትችላላችሁ» ሲልም «አንድ በአንድ ትንቢት ልትናገሩ ትችላላችሁ» ለማለት ነው፡፡ ቃሉ የሚያመለክተው በየተራ መናገርን ነው፤ ይህንንም ለመረዳት ከአማርኛው ሌላ የሌሎች ቋንቋዎች መጽሐፍ ቅዱስን መመልከት ይቻላል፡፡ እግዚአብሔር የሰላም አምላክ እንጂ የሁከት አምላክ አለመሆኑም የሚገለጠው በመደማመጥ ትንቢታዊ ቃልን መከፋፈል ሲቻል ነው፡፡

የእግዚአብሔርን እውነት ለመበረዝም ሆነ ለማጥፋት እንዲሁም የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለማሳት ጠላት ከሚጠቀምባቸው መሣሪያዎች መካከል ሐሰተኞች ነቢያት ዋነኞቹ ናቸው፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን አክዓብ የተባለው የሰማርያ ንጉሥ በሐሰት ትንቢትን የሚናገሩለት 400 ነቢያት ነበሩት፤ ኤልዛቤልን ያገባውንና በኣልና አስታሮትን የተከተለውን ይህን ክፉ ንጉሥ እግዚአብሔር ለሰይጣን አሳልፎ ሰጥቶት እንደነበርና ሰይጣንም በንጉሡ ነቢያት አፍ ሐሰተኛ መንፈስ ሆኖ እንዳሳሳተው እናነባለን (1ነገሥ.22፡5-36)፡፡ እንደዚሁም በነቢዩ ኤርምያስ ዘመንም የሐሰት ነቢያት ነበሩ፤ እነዚህም እግዚአብሔር ሳይልካቸው በእግዚአብሔር ስም ትንቢትን የሚናገሩ ነበሩ (ኤር.28፡15፤ 29፡21-23)፤ ልክ በዚሁ ዓይነት በአዲስ ኪዳንም በዘመነ ሐዋርያት «ሐሰተኞች ነቢያት በሕዝቡ መካከል ነበሩ» (2ጴጥ.2፡1)፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደዚህ ያሉ ሐሰተኞች ሊመጡ እንደሚችሉ ሲናገር «የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውስጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኩላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ» በማለት አስጠንቅቋል (ማቴ.7፡15)፤ በመሆኑም ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም በወጡ ጊዜ ሐዋርያው ዮሐንስ በመልእክቱ ሲጽፍ «ወዳጆች ሆይ፡- መንፈስን ሁሉ አትመኑ፤ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደሆነ መርምሩ፤ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና» በማለት አስገንዝቧል (1ዮሐ.4፡1)፡፡ በዚያን ጊዜ ከእግዚአብሔር የተላኩ እውነተኞች ነቢያት ስለነበሩ ሐሰተኞቹም በእግዚአብሔር ስም ይመጡ ስለነበር መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደሆነ መመርመር በእጅጉ አስፈላጊ ነበር፤ ስለሆነም አስቀድመን እንዳልነው ነቢያት ትንቢት ሲናገሩ ሌሎች እንዲለዩአቸው ሊደነገግ ቻለ፡፡

ነቢያት ከሐዋርያት ጋር የነበሩ የመሠረት ስጦታዎች እንደሆኑ በኤፌ.2፡20 ላይ «በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል» የሚለውን በመጥቀስ ማስረዳታችን ይታወሳል፡፡ እውነቱ ይህ ሆኖ እያለ በቤተክርስቲያን ዘመን መጨረሻ ገደማ በምንገኝበት በዚህ ዘመን ነቢያት ነን የሚሉ ብዙ ሰዎች በየስፍራውና በየጊዜው መነሣታቸው አልቀረም፤ ከእግዚአብሔር ቃል የተለየ መገለጥና ራእይ ተቀብያለሁ በማለት በእግዚአብሔር ስም የልባቸውን አሳብ የሚናገሩና ብዙዎችን እያሳቱ የሚገኙ ሐሰተኞች ነቢያት በብዙ ክርስቲያኖች መካከል ይገኛሉ፡፡ በብሉይ ኪዳን የነበሩ የሐሰት ነቢያትን በተመለከተ በኤር.23፡16 ላይ የተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል «የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ትንቢት የሚናገሩላችሁን የነቢያትን ቃል አትስሙ፤ ከንቱነትን ያስተምሯችኋል፤ ከእግዚአብሔር አፍ ሳይሆን ከገዛ ልባቸው የወጣውን ራእይ ይናገራሉ» ይላል (ኤር.23፡16)፡፡ በዙሪያችን ባለው ሃይማኖተኛ ዓለም እንዲህ ያለ አገልግሎት እየታየ በመሆኑ መልእክቱ ለዚህ ዘመን ክርስቲያኖችም በእጅጉ ጠቃሚ ነው፤ በመድረክ ላይ ቆሞ «በዚያ በኩል ያለህ ወይም ያለሽ፣ እንዲህ ያለ ልብስ የለበስክ ወይም የለበስሽ፤ በእንዲህ ያለ አሳብ ውስጥ የምትገኝ ወይም የምትገኚ ... እንዲህ ይልሃል ወይም ይልሻል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር» በማለት የግለሰቦችን ኑሮ የሚመለከቱ መልእክቶችን ማስተላለፍ ከእግዚአብሔር ቃልና ከእግዚአብሔር መንፈስ ያልተገኘ እና ሰው ነቢይ ለመባል ሲፈልግ ከምስኪን ልቡ የሚያወጣውና በድፍረት የሚናገረው መላምት እንደሆነ መገንዘብ ያሻል፡፡ መነሻቸው የሰው ልብ ወይም ወቅታዊ ሁኔታ የሆነላቸውን እነዚህን አሳሳች መልእክቶች እንደ ትንቢት በመቁጠር ከመነዳት መቆጠብ ትልቅ አስተዋይነት ነው፡፡ ዓይን በተጨፈነ ቊጥር በአእምሮ ውስጥ የሚያልፍ ብዙ የተዘበራረቀ አሳብና ትርዒት ሊኖር ይችላል፤ ከዚያ መሐል አንዱን በመገለጥ ያገኘሁት ትንቢት ነው ብሎ በእግዚአብሔር ስም ለመናገር መዳፈር የእግዚአብሔር ነቢይ አያደርግም፤ ሆኖም በዚህ ዓይነት ነቢያት ነን በሚሉ ሰዎች ከሚመሩት የዋሃን መካከል «እግዚአብሔር ይህን ትዳር ቆርጬዋለሁ ብሏል» ተብለው ትዳራቸውን ያፈረሱ፣ «እኔ ለራሴ ስለምፈልግህ ሥራህን እንድትተው፣ ወይም ገዳም እንድትገባ ይልሃል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር» ተብለው ከጥሩ ሥራቸው ወይም ትምህርታቸው እንዲፈናቀሉና ወደማኅበራዊ ቀውስ ውስጥ እንዲገቡ የተደረጉ፣ እንዲሁም «እኔ የምፈውስህ በእጅህ የያዝከውን መድኃኒት ስትጥል ነው ብሎሃል እግዚአብሔር» እየተባሉም በየጠበል ቤቱና በየጸሎት ቤቱ ተንከራተው በመጨረሻም ለኅልፈት የሚዳረጉ ብዙዎች መሆናቸው በእጅጉ የሚያሳዝን ነው፡፡ ሐዋርያው ጴጥሮስ የሐሰተኞች ነቢያትን እና የሐሰተኞች አስተማሪዎችን ጠባዮች በተናገረበት ክፍል «ነገር ግን ሐሰተኞች ነቢያት ደግሞ በሕዝቡ መካከል ነበሩ፤ እንዲሁም በመካከላችሁ ደግሞ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ይሆናሉ፤ እነርሱም የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ክደው የሚፈጥንን ኑፋቄን አሾልከው ያገባሉ፤ ብዙዎችም በመዳራታቸው ይከተሏቸዋል፤ በእነርሱም ጠንቅ የእውነት መንገድ ይሰደባል፤ ገንዘብንም በመመኘት በተፈጠረ ነገር ይረቡባችኋል፤ ፍርዳቸውም ከጥንት ጀምሮ አይዘገይም፤ ጥፋታቸውም አያንቀላፉም» ብሏል (2ጴጥ.2፡1-3)፡፡ ስለሆነም እነዚህ ሰዎች ኑፋቄን አሾልከው በማስገባት፣ በመዳራት፣ ገንዘብን በመመኘት የሚታወቁ ናቸው፤ ስለ እኔ የወደፊት ዕድል ያውቁልኝ ይሆናል ብለው ባለማዋቅ ተጠግተዋቸው የተበዘበዙና የተነወሩ ሰዎች ይህን ሊናገሩ ይችላሉ፤ ስለሆነም ጌታ «ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ» እንዳለው በዘመናችንም ነቢያት ነን የሚሉት ሁሉ እነዚህን መራራ ፍሬዎች የያዙ ስለሆኑ ሐሰተኝነታቸውን አውቀን ልንርቃቸው ይገባል፡፡

ነገር ግን በሐዋርያት ዘመን የነበሩት ነቢያት የሚያገለግሉት የሚያንጽ፣ የሚመክር፣ የሚያጽናና የሚወቅስ ወይም የሚመረምር ቃልን የማምጣት አገልግሎት በዘመናት ሁሉ አስፈላጊ ነው፤ ስለሆነም ይህን አገልግሎት የሚሰጡ ወንድሞች በየአጥቢያ ጉባኤው ይኖራሉ፡፡ «ነቢያት» ሆነው ለቤተክርስቲያን የተሰጡ ስጦታዎች ግን በዚያው በሐዋርያት ዘመን የነበሩት ብቻ እንደሆኑ የመሠረት ስጦታ ከመሆናቸው አንጻር እንረዳለን፤ ስለዚህ በዘመናችን የሚያንጽ ቃልን በጊዜው የሚያመጡ ወንድሞች ነቢያት ተብለው ሊጠሩ አይችሉም፤ በወንጌል ሰባኪነት ወይም በእረኝነትና በአስተማሪነት ከተሰጡን ወይም በሌላ ጸጋ ከሚያገለግሉ ወንድሞች መካከል ትንቢታዊ የሆነ የጊዜው ቃልን የሚያመጡ ወንድሞች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ይህ ግን እነርሱን ነቢያት አያደርጋቸውም፤ ምክንያቱም ነቢያት ለመባል የሚያንጽ ቃልን የሚያመጡ ብቻ ሳይሆኑ ተአምራዊ በሆነ መገለጥ እግዚአብሔር ለሕዝብ ወይም ለዓለም የሚሆን የወደፊት ነገርን የሚመለከት ትንቢት ወይም አዲስ መገለጥን የሚናገሩ መሆን አለባቸው፤ ሆኖም የወደፊት ነገሮችን በተመለከተ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ የተነገሩ ትንቢቶች የተመዘገቡ በመሆናቸው፣ በሐዋርያው ጳውሎስም በኩል የመጨረሻውን ዘመን አስመልክቶ ብዙ ነገር ስለተጻፈ በተለይ ደግሞ በዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ በቤተክርስቲያን ዘመንም ሆነ ከዚያ በኋላ የሚሆነው እስከ ዓለም ፍጻሜ ያለው ነገር በትንቢት የተነገረ በመሆኑ እግዚአብሔር ለሰው የሚገልጠው ነገር ተገልጦ ተጠናቅቋል፡፡ የክርስትናም እውነትነት እነአጋቦስን የመሳሰሉ ነቢያት የተናገሩአቸው ታላላቅ ትንቢቶች በመፈማቸውና ሌሎችም ተአምራትና ድንቆችም በመደረጋቸው ተረጋግጧል፡፡ በእነዚህ ተአምራዊ ትንቢቶችና በሎሎችም ድንቅ ምልክቶች የጸናው ቃልም በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎልናል፤ ስለዚህ ሁሉንም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምናገኘው በመሆኑ፣ በዚያም ያልተገለጠ የቀረ መገለጥ ስለሌለ፣ እግዚአብሔር ከሐዋርያት ዘመን በኋላ ነቢያትን አስነሥቶ አያውቅም፡፡ አሁንም ሆነ ወደፊት እግዚአብሔር ነቢያት አድርጎ የሚያስነሳቸው ሰዎች የሉም፡፡

በመሠረቱ በዚህ ዘመን ያለነው አማኞች በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስ ከወረደ ጊዜ አንሥቶ ባለችው አንዲት ቤተክርስቲያን ውስጥ የምንገኝ በመሆናችን ለእኛም ቢሆን የተሰጡት ነቢያት እነዚያው በሐዋርያት ዘመን የነበሩት ነቢያት ናቸው፤ ሐዋርያው ጳውሎስ «እግዚአብሔር በቤተክርስቲያን አስቀድሞ ሐዋርያትን፣ ሁለተኛም ነቢያትን፣ ሦስተኛም አስተማሪዎችን፣ ቀጥሎም ተአምራት ማድረግን፣ ቀጥሎም የመፈወስ ስጦታ፣ እርዳታንም፣ አገዛዝንም፣ የልዩ ልዩ ዓይነት ልሳኖችንም አድርጓል» በማለት ጽፏል (1ቆሮ.12፡28)፤ በዚህ ንባብ ውስጥ ቤተክርስቲያን የተገለጠችው በዓለም አቀፍና በዘመን አቀፍ ገጽታዋ ወይም በአንድ አካልነቷ መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል፤ እግዚአብሔር በቤተክርስቲያን ካደረጋቸው ከእነዚህ ስጦታዎች መካከል ሐዋርያትና ነቢያት ቤተክርስቲያን በምትመሠረትበት ጊዜ የነበሩ ስጦታዎች መሆናቸውን ደግሞ በኤፌ.2፡20 ላይ «በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል» ከሚለው የእግዚአብሔር ቃል ተምረናል፤ ስለሆነም በ1ጢሞ.3፡15 ላይ «የእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት» የተባለችው ቤተክርስቲያን ተሠርታ በመጠናቀቅ ላይ ባለችበት በዚህ ዘመን በመሠረቱ ላይ እንደነበሩት ሐዋርያትና ነቢያት ሌሎች ሐዋርያትና ነቢያት ይነሣሉ ብሎ መጠበቅ የእግዚአብሔርን አሠራር አለማወቅ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ በሐዋርያትና በነቢያት ይነገር የነበረው ቃል ሁሉ የእግዚአብሔር እስትንፋስ በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኘዋለን፤ ስለዚህ አማኞች ይህንን ተገንዝበው በቀደመውና በመጻሕፍት ላይ በተመዘገበው ትንቢት ብቻ ሊመሩ ይገባቸዋል፤ ጴጥሮስ ይህን በተመለከተ ሲጽፍ «ከእርሱም ይልቅ እጅግ የጸና የትንቢት ቃል አለን፡፡ ምድር እስኪጠባ ድረስ የንጋትም ኮከብ በልባችሁ እስኪወጣ ድረስ ሰው በጨለማ ስፍራ የሚበራን መብራት እንደሚጠነቀቅ ይህን ቃል እየጠነቀቃችሁ መልካም ታደርጋላችሁ፡፡ ይህን በመጀመሪያ እወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም...» ብሏል (2ጴጥ.1፡19-20)፡፡ ስለሆነም የቀደሙት ነቢያት በመጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈው በጸናው የትንቢት ቃል በኩል ዛሬም ስላሉ በዚያው ልንጸና ይገባል እንጂ «የልብን አዋቂ የሆነ መገለጥ ያለው ነቢይ አለ» በተባለ ቊጥር «የወደፊት ዕድሌ ምን እንደሆነ ይነግረኝ ይሆናል» በማለት እንዲሁም «ያለኝ እንዲባረክልኝ ይጸልይልኛል» ብሎ ለየት ያለ ግምት በመስጠት ገንዘብንና ጊዜን ማባከን ተገቢ አይደለም፡፡ በዚህ ዓይነት ባለማወቅና በየዋህነት ሁለንተናዊ ኪሳራ የደረሰባቸውና ነቢይ ነው በተባለው ሁሉ ዘንድ እየተዘዋወሩ በመባከን ዕረፍት ያጡ ብዙ ሰዎች ወደ ጸናው የትንቢት ቃል እንዲመለሱ በጌታ ፍቅር ይመከራሉ፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል በጉባኤ ሆነን ስንሰማም ሆነ በየግላችን መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ ይህንን የጸና የትንቢት ቃል እናገኛለን፡፡ በዚህ ዓይነት እግዚአብሔር በቃሉ በኩል በዚያ ወቅት ያለንበትን ሁኔታ ይናግረናል፡፡ ነቢያቱ ሊነሱ ባይችሉም የቀደሙት ነቢያት የማነጽ የመምከርና የማጽናናት አገልግሎት ግን በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ከወንድሞች በአንዱ በኩል ሊደርሰን እንደሚችል ልናምን ይገባል፡፡


ወንጌልን ስባኪዎች



Amharic Bible-|- The Holy Bible [King James Version]