trinity  


3. ወንጌል ሰባኪዎች

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ ለአሥራ አንዱ ሐዋርያት ተገልጦ «ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ» (ማር.16፡15) ብሎ የሰጣቸውን መመሪያ ስንመለከት በዓለም ላለው ፍጥረት ሁሉ የሚያስፈልገውን የወንጌል ሥራ ሰፊነት እንገነዘባለን፡፡ ጌታም በዚህ ሰፊ ሥራ ላይ የሚተጉ ሠራተኞችን ለቤተክርስቲያን ይሰጣል፤ እነዚህም «ወንጌል ሰባኪዎች» ተብለው ተጠርተዋል፡፡ እነዚህ ስጦታዎች ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በተመለከተ የእርሱን አዳኝነት እና በጠቅላላ ማንነቱን ለሰዎች የሚሰብኩ ናቸው፡፡

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ የመጀመሪያው የወንጌል ሰባኪ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በኢሳ.61፡1 ላይ «የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድሆች የምሥራችን እሰብክ ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና፤ ልባቸው የተሰበረውን እጠግን ዘንድ ለተማረኩት ነጻነትን ለታሰሩትም መፈታትን እናገር ዘንድ ልኮኛል» የሚል ቃል እናነባለን፡፡ በሉቃ. 4፡17 ላይ እንደምንመለከተው ጌታችን ኢየሱስ ይህ ቃል እርሱን የሚመለከት መሆኑን ራሱ አስረግጦ የተናገረ ሲሆን ይህ ቃል ሲጠቀስም «የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛል ...» ተብሏል፡፡ ስለሆነም ጌታችን በምድር ላይ በሕዝብ መካከል የመመላለሱ ዋና ዓላማ ወንጌልን ለመስበክ ነበር፡፡ በዚሁ የወንጌል ስብከት ሥራው ጊዜ የእርሱን ማንነት ሊጠይቁ ከመጥምቁ ዮሐንስ ዘንድ ተልከው ለመጡት ደቀመዛሙርት ጌታ የሰጣቸው መልስ «ሄዳችሁ ያያችሁትን፣ የሰማችሁትንም ለዮሐንስ አውሩለት፤ ዕውሮች ያያሉ አንካሶች ይሄዳሉ፤ ለምጻሞች ይነጻሉ፤ ደንቆሮችም ይሰማሉ፤ ሙታንም ይነሣሉ፤ ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል፤ በእኔም የማይሰናከለው ሁሉ ብፁዕ ነው» የሚል ነበር (ማቴ.11፡4-6)፡፡ ስለሆነም የወንጌል ሰባኪነት አገልግሎት ምን እንደሚመስል ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በሰውነቱ በሰጠው አገልግሎት ውስጥ በግልጽ ማየት እንችላለን፡፡ በተለይም ወንጌል በእርግጥም የምሥራች መሆኑን ማስተዋል ይቻላል፤ ከፍ ብለው በተጠቀሱት ክፍሎች ድሆች የተባሉት በኢሳይያስ 61 ላይ ልባቸው የተሰበረ፣ የተማረኩ .... ተብለው የተገለጡት ናቸው፡፡ ለእነዚህ ሰዎች በክርስቶስ የሚገኘውን ሰላምና ዕረፍት እንዲሁም አርነት መስበክ ታላቅ የምሥራች ነው፤ ወንጌል የሚባለው ይኸው ነውና፡፡

ሐዋርያትን «ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ» (ማር.16፡15) ተብሎ በተሰጣቸው መመሪያ መሠረት የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ በዋነኛነት ሠርተዋል፤ ሐዋርያው ጴጥሮስ «ወንድሞች ሆይ አሕዛብ ከአፌ የወንጌልን ቃል ሰምተው ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር በመጀመሪያው ዘመን ከእናንተ እኔን እንደመረጠኝ እናንተ ታውቃላችሁ» ብሎ እንደተናገረ እናነባለን (የሐ.ሥ.15፡7)፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም በኤፌ.3፡7 ላይ «እንደ ኃይሉ ሥራ እንደተሰጠኝም እንደ እግዚአብሔር ጸጋ ስጦታ መጠን የወንጌል አገልጋይ ሆንሁለት» ብሎ ሲጽፍ በ2ጢሞ.1፡11 ደግሞ «እኔ ሰባኪና ሐዋርያ አሕዛብንም አስተማሪ እንድሆን በተሾምሁበት በወንጌል ....» እያለ ሲጽፍ እንመለከታለን፤ እንዲሁም ይኸው ሐዋርያ በሮሜ15፡19 ላይ «ስለዚህ ከኢየሩሳሌም ጀምሬ እስከ እልዋሪቆን ድረስ እየዞርሁ የክርስቶስን ወንጌል ፈጽሜ ሰብኬአለሁ» በማለት ጽፏል፡፡ በመሆኑም የወንጌል ሰባኪነት (የወንጌላዊነት) ሥራ በሐዋርያነት ሥራ ውስጥ የሚገኝ አገልግሎት እንደሆነ በዚህ መረዳት እንችላለን፡፡

ሐዋርያት የወንጌላዊነት ሥራን የሠሩ ቢሆንም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አካሉን ለማነጽ ከሰጣቸው ስጦታዎች መካከል የወንጌል ሰባኪዎች (ወንጌላውያን) ራሳቸውን የቻሉ ስጦታዎች አድርጎ መስጠቱን ማስተዋል ይገባል፡፡ በመሆኑም የወንጌል ሰባኪዎች ከአምስቱ ስጦታዎች አንዱ ሆነው ተገልጠዋል፡፡ በዚህ ዓይነት ሐዋርያት ሳይሆኑ የወንጌላዊነትን ሥራ ብቻ የሠሩ አገልጋዮችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኛለን፡፡ በተለይም በሰማርያ ወንጌልን የሰበከው ፊልጶስ ወንጌላዊ እንደነበር በግልጽ ተጽፎልናል፡፡ በሐ.ሥ.21፡8 ላይ «በነጋውም ወጥተን ወደ ቂሣርያ መጣን ከሰባቱም አንድ በሚሆን በወንጌላዊው ፊልጶስ ቤት ገብተን በእርሱ ዘንድ ተቀመጥን» ይላል፡፡ ይህ ፊልጶስ በሐ.ሥ.6፡5 ከተዘረዘሩት ሰባት የማዕድ አገልጋዮች አንዱ እንደሆነ «ከሰባቱ አንዱ በሚሆን» በሚለው አገላለጽ እንረዳለን፤ ሆኖም «ወንጌላዊው» ተብሎ በመጠራቱ የወንጌላዊነትን ሥራ እንዲሠራ የወንጌል ሰባኪ ሆኖ ለቤተክርስቲያን የተሰጠ እንደነበር ግልጽ ነው፡፡ ይህም የወንጌል ሰባኪነት ሥራው በሰማርያ ከተማ ተገልጧል፡፡ ወደዚያም ወርዶ ክርስቶስን ሰበከላቸው (የሐ.ሥ.8፡5)፡፡ ወንጌል ደግሞ ስለ ክርስቶስ የሚናገር መልካም የምሥራች በመሆኑ «ክርስቶስን ሰበከላቸው» ሲል ወንጌላዊነቱን ያጎላዋል፡፡ እንደዚሁም የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብ ላገኘው ኢትዮጵያዊ ጃንደረባም የሰበከውን ቃል በተመለከተ «ፊልጶስም አፉን ከፈተ፤ ከዚህም መጽሐፍ ጀምሮ ስለ ኢየሱስ ወንጌልን ሰበከለት» ተብሎ ተጽፏል (የሐ.ሥ.8፡35)፡፡ ስለሆነም የፊልጶስ የወንጌል ሰባኪነት አገልግሎት በየዘመናቱ የወንጌል ሰባኪ ሆነው ለሚሰጡ ወንድሞች አብነትና ምሳሌ የሚሆን ነው፡፡ እንዲሁም ከጳውሎስ ጋር አብረው ከሠሩ ወንድሞች መካከል ብዙዎቹ የወንጌል ሰባኪዎች ነበሩ፤ ለምሳሌ ጢሞቴዎስን በተመለከተ ሐዋርያው ጳውሎስ ሲመሰክር «ስለእምነታችሁ እንዲያጸናችሁና እንዲመክራችሁ ወንድማችንን የእግዚአብሔርንም አገልጋይ ከእኛ ጋርም አብሮ በክርስቶስ ወንጌል የሚሠራውን ጢሞቴዎስን ላክነው» በማለት ጽፎ እናገኛለን (1ተሰ.3፡2-3)፡፡ ስለሆነም ሐዋርያት ሳይሆኑ «ወንጌል ሰባኪዎች» ብቻ ሆነው የተሰጡ እንዲህ ያሉ አገልጋዮች በመጀመሪያይቱ ቤተክርስቲያን ውስጥ ነበሩ፡፡

ወንጌል ሰባኪዎች መልካሙን የምሥራች ለማያምኑ ሰዎች የሚሰብኩ ማለትም የክርስቶስን አዳኝነት ላልዳኑ ሰዎች የሚናገሩ አገልጋዮች እንደመሆናቸው መጠን በየዘመናቱ የሚያስፈልጉ ስጦታዎች ናቸው፡፡ ስለሆነም በዘመናችንም ቢሆን ጌታ የሚሰጠን የወንጌል ሰባኪዎች (ወንጌላውያን) አሉ፤ እነርሱም ላመኑ ሰዎች ስለጌታ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስበክ ሊያገለግሉ ቢችሉም ዋነኛው የአገልግሎታቸው ስፍራ ግን በዓለም ላሉ ለማያምኑ ሰዎች መልካሙን የምሥራች መናገር ነው (ሮሜ.10፡14-16)፡፡ ሆኖም በወንጌል ሰባኪነት ለማገልገል አስቀድሞ የተሰበሰበ ሕዝብ ለማግኘት መፈለግ በዘመናችን ባለው የወንጌል አገልግሎት ላይ የሚታይ ዓይነተኛ ችግር ነው፡፡ ይህም ምንም ሳይደክሙና ዋጋ ሳይከፍሉ አስቀድሞ በተዘጋጀ መድረክ ላይ ብቻ ለመስበክ ከሚኖር ተገቢ ያልሆነ ጥማት የሚመጣ ችግር ነው፡፡ በዚህ ዓይነት የወንጌል ሰባኪ ነኝ ማለት ራስን ማሰማራት እንጂ የአገልግሎቱን ጸጋ ከጌታ ተቀብሎ በራሱ በጌታ መሰማራት አይደለም፤ ጌታ በእርግጥ ያሰማራው የወንጌል ሰባኪ የተሰባሰበ ሕዝብ እና የተዘጋጀ መድረክ ሲያገኝ ብቻ ሳይሆን ምንም አማኝ በሌለበት አካባቢም ክርስቶስን ለመስበክ የታመነ ነው፡፡ እንዲያውም በዋናነት የተጠራው ለዚህ እንደሆነ የሚረዳ አገልጋይ ነው፡፡

ወንጌል ሰባኪዎች ወደዚህ አገልግሎት የሚመጡት እንዴት እንደሆነ ስናስብ እነርሱን የሚሰጠውና የሚያሰማራው የቤተክርስቲያን ራስ የሆነው ክርስቶስ መሆኑን ምን ጊዜም መዘንጋት አይገባም፡፡ ወንጌላውያን በአንድ በታወቀም ሆነ ባልታወቀ የቲዎሎጂ ት/ቤት በወንጌላዊነት ሠልጥነው የተመረቁ ሊሆኑ እንደሚገባቸው ፈጽሞ መታሰብ የለበትም፡፡ ወንጌላዊነትን እንደ አንድ የሥራ መደብ ከተለያዩ የቲዎሎጂ ት/ቤቶች መመረቂያ ያደረገው አሠራር ከዘመናዊነት ጋር ብቅ ያለው የሰው ሥርዓት እንጂ ከጌታም ሆነ ከሐዋርያት ያገኘነው ልማድ እንዳልሆነ የታወቀ ነው፤ ሆኖም ከጌታ ዘንድ የወንጌል ሰባኪ እንዲሆኑ ጥሪ ይኑራቸው አይኑራቸው ሳይረጋገጥ አንዳንዶች ከቲዎሎጂ ትምህርት ቤት በወንጌላዊነት ስለተመረቁ ብቻ በዚሁ ሙያ ከተመረቁ ሌሎች ሰዎች ጋር ተወዳድረው የወንጌላዊነት ሥራ የሚቀጠሩበት አሠራር በሃይማኖተኛው የክርስትና ዓለም በስፋት ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ በዚህም አሠራር ሥራ አጥ የሆኑ ሰዎች እንደ አንድ የሥራ መስክ ዕድሉን እየተጠቀሙበት ከመሆኑም ሌላ በየትኛውም ዓለማዊ አሠራር እንደተለመደው ሁሉ አንዳንድ ጊዜ በድምፅ ብልጫ፣ በትውውቅና በዝምድናም የወንጌል ሰባኪዎች እየተባሉ በተወሰነ ደመወዝ የሚቀጠሩበት ሁኔታም ይታያል፡፡ ይህም በዚህች ዓለም ላይ የምሥራቹን ቃል የሚናገሩ የወንጌል ሰባኪዎችን ራሱ ማስነሣትና ማሰማራት ለሚፈልገው በሰማይ በአባቱ ቀኝ ላለው ለጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ ልብ እጅግ አሳዛኝ አሠራር ከመሆኑም በላይ ክርስቶስ በቤተክርስቲያን ላይ ያለውን ሥልጣን መጋፋትም ጭምር ነው፡፡ ስለሆነም አንድ ሰው ጌታ ሳይጠራውና ሳያሰማራው፣ የሚሠራው ሌላ ሥራ ስለሌለው ብቻ፣ የወንጌል ሰባኪ ልሁን ብሎ ሊነሣ አይገባም፡፡ ሌሎች አማኞችም በጸጋው ተገልጦ ሲያገለግል ሳያዩና የጌታ ጥሪ እንዳለው የመንፈስ ቅዱስን ምስክርነት ሳያገኙ «የወንጌላዊነት ሥልጠና ወስዷል» በሚል ብቻ «ይህ ሰው ወንጌላዊ ነው» ሊሉ አይገባም፡፡

ቤተክርስቲያኑን ከላይ ሆኖ የሚያስተዳድረው ትልቁ የበጎች እረኛ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የአካሉን ሙላት ወደ ፍጻሜ ለማምጣት በውጭ ወዳለው ዓለም እየላከ ከማያምኑት መካከል የእርሱ ብልቶች እንዲሆኑ ይጠራባቸው ዘንድ የወንጌል ሰባኪዎችን ያስነሣል፤ ያሰማራልም፡፡ በዚህ መልኩ በእርግጥ ጌታ የሚሰጠን የወንጌል ሰባኪዎች በዚህ ዓለም ሳሉ የሚያስፈልጋቸውን ቀለብ እንዴት ያገኛሉ? የሚል ጥያቄ ምናልባት ሊነሣ ይችላል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ከጻፈው ቃል ለዚህ ጥያቄ የምናገኘው መልስ «... ወንጌልን የሚሰብኩ ከወንጌል ቀለብ እንዲቀበሉ ጌታ ደንግጎአል» የሚል ነው (1ቆሮ.9፡14)፡፡ ጌታችን ይህን አስመልክቶ ሲናገር «... ለሠራተኛ ምግቡ ይገባዋልና» ብሏል (ማቴ.10፡10)፤ እንዲሁም «ወደምትገቡበት ቤት ሁሉ አስቀድማችሁ ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን በሉ፡፡ በዚያም የሰላም ልጅ ቢኖር ሰላማችሁ ያድርበታል፤ አለዚያም ይመለስላችኋል፡፡ በዚያም ቤት ከእነርሱ ጋር ካለው እየበላችሁና እየጠጣችሁ ተቀመጡ ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋልና ከቤት ወደቤት አትተላለፉ፡፡ ወደምትገቡባትም ከተማ ሁሉ ቢቀበሏችሁ ያቀረቡላችሁን ብሉ...» ብሏል (ሉቃ.10፡5-8)፡፡ ከዚህም እንደምንረዳው ጊዜያቸውን በሙሉ ለጌታ ሥራ በመስጠት ወንጌልን ለሚሰብኩ ወንጌላውያን በቤታቸው የተቀበሏቸው ሰዎች ቀለባቸውን እንዲሰጧቸው መደንገጉን ነው፡፡ ይህ አሠራር እኛ ባለንበት በጸጋው ዘመንም ሆነ ወደፊት የመንግሥት ወንጌል በሚሰበክበት ወቅትም ሥራ ላይ የሚውል ነው፡፡ የወንጌል ሰባኪዎችን በቤታቸው የሚቀበሏቸው ሰዎች ከቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ጀምሮ የሚያስፈልጋቸውን ሊሰጡአቸው ይገባል፡፡ ይህንንም ቢያደርጉ ወደ ቤታቸው ከገባው እና በጌታ ስም ከተቀበሉት የወንጌል አገልጋይ ጋር ዋጋቸው አንድ እንደሆነ ጌታ ተናግሯል (ማቴ.10፡40-42፤ ማር.9፡41)፡፡ ሆኖም የወንጌል ሰባኪው «ያቀረቡለትን ለመብላት» ማለትም በእነርሱ አቅም ለመስተናገድ የተዘጋጀ ሊሆን ይገባል፡፡ ይህም ዘመናችን በስፋት ከሚሠራበት የወር ደመወዝን በፔሮል እየፈረሙ በመቀበል በወንጌላዊነት ከማገልገል በእጅጉ ይለያል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን በዘመናችን «እቤቴ ድረስ መጥታችሁ በመኪና ካልወሰዳችሁኝ» ከሚለው ጥያቄ ጀምሮ «ለሥጋ የተመቻቸ ማረፊያና የላመ የጣመ (ውድ) ምግብ ካላቀረባችሁልኝ» እስከሚለው ጥያቄ ድረስ ራሳቸውን ለወንጌል ሥራ ካሰማሩ ሰዎች ብዙ ጊዜ የሚሰማ ሆኗል፡፡ ሆኖም ይህ ጌታ ካስነሣቸውና ካሰማራቸው የወንጌል ሰባኪዎች የሚጠበቅ አይደለም፡፡

ጌታ ያሰማራቸው የወንጌል ሰባኪዎች ምንም እንኳ ከወንጌል ቀለብ እንዲቀበሉ ጌታ መደንገጉን የሚያውቁ ቢሆንም በሚያገለግሏቸው ሰዎች ላይ ለመክበድ ስለማይፈልጉ ለቀለብ የሚያስፈልጋቸውን ለማግኘት በገዛ እጃቸው በመሥራት ይተዳደራሉ፤ ሐዋርያው ጳውሎስ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ እርሱ ድንኳን በመስፋት እየሠራ ራሱንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ይጠቅም ነበር (የሐ.ሥ.18፡1-3)፤ ይህን በተመለከተ ራሱ ጳውሎስ ሲናገር «ከማንም ብር ወይም ወርቅ ወይም ልብስ አልተመኘሁም፤ እነዚህ እጆቼ በሚያስፈልገኝ ነገር ለእኔና ከእኔ ጋር ላሉት እንዳገለገሉ እናንተ ታውቃላችሁ» ብሏል (የሐ.ሥ.20፡33-34)፡፡ እንዲያውም ስለሚያገለግላቸው ሰዎች ገንዘቡንም ራሱንም እስከመስጠት ዋጋ እንደሚከፍል ይናገራል፤ «ወላጆች ለልጆች እንጂ ልጆች ለወላጆች ገንዘብ ሊያከማቹ አይገባቸውምና፤ እኔ ግን ስለ ነፍሳችሁ በብዙ ደስታ ገንዘቤን እከፍላለሁ፤ ራሴንም እንኳ እከፍላለሁ» ብሏል (2ቆሮ.12፡14-15)፡፡ ከዚህም የምንረዳው የወንጌል ሰባኪዎች ወርቅና ብርን እንዲሁም ልብስን የሚያስፈልጋቸውንም እንኳ ቢሆን ከሚያገለግሏቸው ሰዎች ከመጠበቅ ይልቅ ራሳቸው በገዛ እጃቸው እየሠሩ ከራሳቸው አልፈው ስለሚያገለግሏቸው ሰዎች እንኳ ሳይቀር በብዙ ደስታ ገንዘባቸውን የሚከፍሉ ሊሆኑ እንደሚገባ ነው፡፡ ይሁንና ይህን ለማድረግ ጊዜ የማይበቃቸውና ሙሉ ለሙሉ ጊዜያቸው በወንጌል ስብከት ሥራ የተያዘባቸው፣ ለአገልግሎቱ የተሰጡ አገልጋዮች ከሆኑ ግን ከወንጌል ቀለብ እንዲቀበሉ ጌታ ደንግጎአል፤ ብርና ወርቅ ወይም ሌላ የከበረ ነገር ሳይፈልጉ ለኑሮአቸው አስፈላጊ ከሆኑ ነገሮች መካከል ያገኙትን እየተጠቀሙ ጌታን ከልብ የሚያገለግሉ ሊሆኑ ይገባል፡፡ በእርግጥ ጌታ ያሰማራቸው የወንጌል ሰባኪዎች የሚታወቁበት ምልክትም ይኸው ነው፡፡ ከኑሮ አንጻር ወንጌል ሰባኪዎች ሊከተሏቸው የሚገቡት እነዚህ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ መርሆዎችም ማለትም ከወንጌል ቀለብ በመጠቀም ወይም በገዛ እጃቸው ሠርተው በማግኘት ጌታን ማገልገል ለወንጌል ሰባኪዎች ብቻ ሳይሆን በእረኞችና በአስተማሪዎች አገልግሎት ሥራ ላይ የሚውሉ መርሆዎች መሆናቸውን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡

የወንጌል ሰባኪዎች በመካከላችን በተሰጣቸው ጸጋ ሊገለጡ የሚችሉት እንዴት ነው? የሚለው ጥያቄ የብዙዎች እንደሚሆን አያጠራጥርም፤ ወንጌላውያን በሰዎች ምርጫና ምልመላ ወይም በልዩ የወንጌላዊነት ሥልጠና ሳይሆን ጌታ በራሱ መንገድ በሕይወታቸው የጠራቸውና ያሠለጠናቸው ሆነው በመካከላችን የወንጌላዊነትን ሥራ በመሥራት በሚያሳዩት ትጋት ሊገለጡ ይችላሉ፡፡ በዚህም አገልግሎት እየተጉ ሲታዩ የአብያተ ክርስቲያናትን ምስክርነት እያገኙ ይሄዳሉ፡፡ ወደዚህ ሁኔታ የሚደርሱት በግል ከጌታ ጋር ካላቸው የጠበቀ ኅብረት ተነሥተው ቅዱሳት መጻሕፍትን በጸሎት ሆነው፣ ጊዜ ሰጥተው፣ በማጥናት በእግዚአብሔር ቃል ተሞልተው፣ በነፍሳት ፍቅር ተይዘው፣ ክርስቶስን መስበክ ሲጀምሩና በዚህም አገልግሎት እያደጉና እየተጉ ሲሄዱ ነው፡፡ ይህ ጸጋቸው በየስፍራው ሥራ ላይ ሲውል ያዩ አብያተ ክርስቲያናት የሚሰጡት ምስክርነት ይበልጥ በዚህ ጸጋ የሚያገለግሉትን ይገልጣቸዋል፤ ለምሳሌ የልግስና ስጦታን ለመረከብ ወደ ቆሮንቶስ ከተላኩት ሦስት ወንድሞች አንዱ «ስለወንጌል ስብከት በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የተመሰገነ ወንድም» ተብሏል (2ቆሮ.8፡18)፡፡

በሰው ሥርዓት ሳይሆን በቀጥታ በራሱ በጌታ በኢየሱስ አሠራር በመካከላችን የሚገለጡት የወንጌል ሰባኪዎች «ወንጌላዊ እከሌ» ተብለው እንዲጠሩ የሚፈልጉ አይደሉም፡፡ ይሁን እንጂ «ወንጌላዊ» የሚለውን ቃል ከግለሰብ የመጠሪያ ስም በፊት በማድረግ እንደ ማዕረግ ስም መጠቀም በብዙዎች ዘንድ የተለመደ ሆኖ ይታያል፡፡ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ «ወንጌላዊ» የሚለውን ቃል ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ስጦታዎች የሚገልጹ ቃላትን በማዕረግ ስምነት መጠቀምን ፈጽሞ አያስተምርም፤ ይህ ሊመጣ የሚችለው ግን ሥጋ በወንጌል አገልግሎት ስም ከብሮ ለመጠራት ሲፈልግ እንደሆነ ማሰብ ይቻላል፤ አንዳንድ ጊዜ ከሰባቱ አንዱ ፊልጶስ «ወንጌላዊው» ተብሎ በሐዋ.ሥ.21፡8 ላይ መጠራቱን በተሳሳተ መንገድ በመጠቀም «ወንጌላዊ እከሌ» ተብሎ መጠራት እንደሚቻል ሲነገር ይሰማል፤ ይሁን እንጂ በዚህ ጥቅስ ላይ ፊልጶስ «ወንጌላዊው» ተብሎ መጠራቱ የሚያገለግልበትን የጸጋ ስጦታ ለመግለጽ ነው እንጂ በማዕርግ ስም ለመጥራት አይደለም፤ እንዲያውም ፊልጶስ በዚህ ክፍል የተጠራው «ወንጌላዊው ፊልጶስ» ተብሎ እንጂ «ወንጌላዊ ፊልጶስ» እንዳልሆነ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ በሌሎች ቋንቋዎች በተጻፈ መጽሐፍ ቅዱስ ስም አቀማመጡ እንዲሁ ነው፤ ለምሳሌ ብዙ ሰዎች ሊያነቡት የሚችሉትን የእንግሊዘኛ መጽሐፍ ቅዱስን ብናነጻጽር እንኳ “Philip the Evangelist” ይላል እንጂ “Evangelist Philip” አይልም፡፡ በሁለቱ አነጋገሮች መካከል ጉልህ ልዩነት አለ፤ «ወንጌላዊው ፊልጶስ» ሲባል ፊልጶስን በሚሠራው የወንጌላዊነት ሥራ ለይቶ ለመጠቆም (ለመግለጽ) መፈለግን ሲያስረዳ «ወንጌላዊ ፊልጶስ» ሲባል ግን «ወንጌላዊ» የሚለውን ቃል በማዕርግ ስምነት መገልገልን ይገልጻል፤ ልብ ብሎ ለሚያስተውል ሁሉ ይህ ግልጽ ይሆንለታል፡፡ ወንጌላዊ የሚለውን ቃል በማዕርግ ስምነት መጠቀም ተገቢ ቢሆን ኖሮ ፊልጶስ በተጠራባቸው ቦታዎች ሁሉ ከስሙ በፊት «ወንጌላዊ» የሚል ቃል ይኖር ነበር፤ ሆኖም በሐዋ.ሥ.8 ውስጥ የፊልጶስ ስም 14 ጊዜ ያህል ሲጠራ አንድም ጊዜ ወንጌላዊ ፊልጶስ አልተባለም (ቊ.5፣ 6፣ 12፣ 13፣ 26፣ 29፣ 30፣ 31፣ 34፣ 35፣ 37፣ 38፣ 39፣ 40)፡፡ ስለሆነም አንድን ሰው በወንጌል ሰባኪነት አገልግሎቱ ለመግለጽ ስንፈልግ «እገሌ የትኛው?» ተብሎ ቢጠየቅ «ወንጌላዊው ነዋ! ወንጌላዊው እከሌ» ብለን ከመናገር በቀር ሁል ጊዜም ስንጠራው ወይም ስናስተዋውቀው ወይም ስሙን ስንጽፍ «ወንጌላዊ እከሌ» ካልን ወይም ያ ወንድም ራሱን ለእኛ ሲያስተዋውቅ «ወንጌላዊ እከሌ» እባላለሁ ካለ ይህ አጠቃቀም ወንጌላዊ የሚለውን ቃል የማዕረግ ስም ማድረግ ነው፡፡ ይህም ዛሬ በዘመናችን በስፋት የሚታይ ሲሆን ማዕረግና ክብር ከሚጠማው የሥጋ ፍላጐት የሚነሳና ከእግዚአብሔር ቃል ውጪ የሆነ ልማድ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያሉትን ጌታ ነጻ አውጥቷቸው ምንም ዓይነት የማዕረግ ስም ሳይፈልጉ ዝቅ ብለው ሲያገለግሉ ማየት የዘወትር ምኞታችን ነው፡፡

ቀደም ሲል እንደገለጽነው የወንጌል ሰባኪዎች በዋናነት ለማያምኑ ሰዎች ቀጥሎም ላመኑ ሰዎች ስለክርስቶስ መስበክ የአገልግሎታቸው ዓላማ ነው፡፡ ጊዜያቸውን በሙሉ ለዚሁ አገልግሎት የሰጡም ቢሆኑ የራሳቸውን ሥራ እየሠሩ የሚያገለግሉ ወንጌላውያን ትኲረት ሊሰጡበትና ሊጠነቀቁበት የሚገባው ነገር የአገልግሎታቸውን ዓላማ እንዳይስቱ ነው፤ ሐዋርያው ጳውሎስ «ስለ እርሱም (ስለክርስቶስ) የምንናገረው ብዙ ነገር አለን....» እንዳለው (ዕብ.5፡11) ወንጌላውያን ስለ ጌታ ኢየሱስ የሚናገሩት ብዙ ነገር እያለ ስለራሳቸው ወይም ስለሌሎች ሰዎች የሚናገሩ መሆን የለባቸውም፤ በ2ቆሮ.4፡5 «ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታ እንደሆነ እንጂ ራሳችንን አንሰብክምና ስለ ኢየሱስም ራሳችንን ለእናንተ ባሪያዎች እናደርጋለን» የሚል ቃል እናነባለን፡፡ አንድ እውነተኛ የወንጌል ሰባኪ ሊከተለው የሚገባ መርህ ይህ ነው፡፡ ሆኖም የራስ ነገር ጎልቶ እንዲታይ በሚፈለግበት ጊዜ ለማያምኑ ሰዎች በተዘጋጁ ታላላቅ የወንጌል ስርጭት መድረኮችም ይሁን ለአማኞች ወንጌል በሚሰበኩባቸው ጉባኤያት «በዚህ አገር ይህን ሠርቼ፣ ይህን ሰብኬ፤ በዚህ ቦታ አንድ ወንድም አነጋግሮኝ፣ አንዲት እኅት ጸልይልኝ ብላኝ ... እንዲህ ሆኖ ... እንዲያ ተብሎ....» የሚሉ ገጠመኞችን በመደርደር ስለራስ መተረክ የበዛበት አገልገሎት በስፋት ይታያል፡፡ እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ ጠቃሚ ያልሆኑ አስቂኝ ቀልዶችና ተረቶች ጊዜውን ሲያጣብቡት ማየት የተለመደ ነው፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ወንጌል እሰብካለሁ በማለት በተረከቡት መድረክ «አሁን በመገለጥ የሚታየኝ ነገር አለ» እያሉ ከዚያ አስቀድሞ በነበረው በዚሁ ዓይነት ነገር የተሰላቸውን ሕዝብ እንደገና ወደማሰላቸትና ብሎም ወደማሰናከል የሚወስዱ የሐሰተኛ መገለጥ አገልግሎቶች ሃይማኖተኛውን የክርስትና ዓለም ሞልተውት ይታያሉ፡፡ ተነግሮ የማያልቀው የክርስቶስ ማንነት እያለ ራስን በሕዝብ ፊት ሊያሳውቁና ሊያስከብሩ የሚችሉ እንዲህ ያሉ ነገሮችን በማንሣት ጊዜ መውሰድ ክርስቶስን መስበክ ሳይሆን ራስን መስበክ ነው፡፡ እውነተኛ የወንጌል ሰባኪዎች ከዚህ መራቅ አለባቸው፡፡

የአዲስ ኪዳንም ይሁን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ዋነኛ ትኲረት ክርስቶስ መሆኑ ይታወቃል (ዮሐ.5፡39፣46)፤ ወንጌል መስበክም ማለት ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ማንነት መመስከር ነው (ሮሜ.1፡4)፡፡ ስለሆነም የወንጌል ሰባኪዎች የስብከታቸው ዋና ይዘት ስለ ክርስቶስ ሆኖ፣ ይህም ከብሉይ ኪዳንና ከአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በማስረጃነት በተጠቀሱ የእግዚአብሔር ቃላት የተሞላ ሊሆን ይገባዋል፡፡ የሰሚዎችን ልብ ሊነካ የሚችለውና መንፈስ ቅዱስ የማያምነውን ሊጠራበት የሚችለው ስብከት ይህ ነው፡፡ በሐ.ሥ.2 ውስጥ የምናየውን በበዓለ ሃምሳ ዕለት የተሰበከውን የጴጥሮስን ስብከት ስንመለከት ዋና ርእሰ ጉዳዩ የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ እንዲሁም በአባቱ ቀኝ በክብር መቀመጡ፣ «ጌታ» እና «ክርስቶስ» መደረጉ ሲሆን ለዚሁ ማስረጃ የሚሆኑ ሦስት የተለያዩ ንባቦች ከቅዱሳት መጻሕፍት ተጠቅሰው ነበር፡፡ በውጤቱም የሰሚዎች ልብ ሲነካ እናያለን (ቊ.37)፡፡ እንዲሁም በሐ.ሥ.13፡16-41 የምናነበውን የጳውሎስን ስብከት ስንመለከት ከቅዱሳት መጻሕፍት በተወሰዱ ታሪኮችና ጥቅሶች የተመሠረተና የተሞላ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ስለ ክርስቶስ በመስበክ ጊዜውን ሁሉ መጨረስ ለሚፈልጉ ሁሉ እነዚህ ስብከቶች አብነት ሊሆኗቸው ይችላሉ፡፡ የወንጌል ሰባኪዎች የሐዋርያትን አብነት በመከተል ስለሰው ወይም ስለ ራስ ከመስበክ ተለይተው የእግዚአብሔር ቃል ስለክርስቶስ የሚናገራቸውን ማንነቶቹን በመስበክ ሊጠመዱ ይገባቸዋል፡፡

ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ሲጽፍለት «አንተ ግን ነገርን ሁሉ በልክ አድርግ፤ መከራን ተቀበል፤ የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ አድርግ፤ አገልግሎትህን ፈጽም» ብሎታል (2ጢሞ.4፡5)፡፡ ይህ ቃል የወንጌል ሰባኪነት ጸጋው ኖሯቸው የሰነፉትን ወይም የተዳከሙትን ሰዎች የሚያበረታታና የሚያነቃቃ ቃል ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ወንጌል ሰባኪዎች ብዙ ሥራዎችን በመጀመር ራሳቸውን በአላስፈላጊ ውጥረት ውስጥ ስለሚከቱ ከጌታ የተሰጣቸውን የወንጌል ሰባኪነት አደራ ሳይወጡ ይቀራሉ፡፡ ከተያዙባቸው ሥራዎች መካከል አንዳንዶቹ የቱንም ያህል አስፈላጊ ቢሆኑም ከጌታ ሥራ ይልቅ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚችሉ አይደሉም፤ ስለዚህ ነገርን ሁሉ በልክ እያደረጉ ወንጌልን ለመስበክ ቅድሚያ መስጠት ጥሪው ካላቸው ሁሉ የሚጠበቅ ነው፤ እውነተኛ የወንጌል ሰባኪዎች የጌታ ሥራ እየተበደለ በራሳቸው ነገር እንዲያዙ የሚያደርግ ልብ የላቸውምና፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ወንጌልን ከመስበክ አኳያ ስለ ክርስቶስ በሚደርስ መከራ ምክንያት ተሰላችተው መዳከም በአንዳንድ ወንጌላውያን ዘንድ ይታያል፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ጊዜ መከራው ከአቅም በላይ እስኪሆን ድረስ ያለልክ ሊከብድ ይችላል (2ቆሮ.1፡8)፡፡ ሆኖም ጌታ በመከራ ውስጥ አሳልፎ በእኛ ሊሠራ ያለውን እንደሚሠራ ማመን ያስፈልጋል፤ እርሱ ሳይፈቅድ ሊሆን የሚችል ነገር የለም፤ እርሱ የራሳችንን ጠጉር ቆጥሮአል፤ መልእክተኞቹ ለሆኑት ሁሉ እርሱ ዋጋ ሰጥቷል (ማቴ.10፡28-30) እስከሞት መታመንን የሚጠይቅ ከሆነም ጌታ ለዚሁ የሚሆን ጸጋንና እምነትን ይሰጣል፡፡ ይህንን ተረድቶ በወንጌል ሰባኪነት ሥራ በመበርታትና በመትጋት ፈንታ ወደ ኋላ ማፈግፈግ ወይም ተስፋ ቆርጦ «ሁለተኛ አላገለግልም» ማለት ከጌታ በተቀበሉት መክሊት አለማትረፍ ነው፡፡ የወንጌል ሰባኪ የሆነ ሰው ገና ከጌታ ዘንድ ጥሪ እንዳለው ሲያውቅና ሲያምን ስለስሙ መከራ መቀበል እንዳለ ሊያውቅ ይገባል፡፡ ይህንንም አውቆ መከራ እየተቀበለ የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ እንዲያደርግ አገልግሎቱንም እንዲፈጸም የእግዚአብሔር ቃል ያበረታታዋል!

በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ የምናምን ሁላችን ስለክርስቶስ የመመስከር ኃላፊነት በእርግጥ አለብን፤ ይሁንና በወንጌል ሰባኪነት ለቤተክርስቲያን የተሰጡ ወንድሞች በዚሁ ጸጋ ተገልጠው ቢሠሩ ለክርስቶስ አካል ብልቶች ሆነው የሚገጠሙትን ነፍሳት ወደ ጌታ ለማምጣት ብዙ ሊሠሩ ይችላሉ፡፡ ቃሉም ወደማያምኑት መካከል በፍጥነት እየሮጠ በዓለም በሚጣለው የወንጌል መረብ ብዙ ነፍሳት ሊጠመዱ ይችላሉ፡፡ ይህ ይሆን ዘንድ ጌታ እንዲህ ያሉ የወንጌል ሠራተኞችን እንዲያስነሣ በጸሎት ልንለምነው ይገባል፡፡ እርሱ በምድር ሳለ ብዙ ሕዝብ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ባየ ጊዜ አዘነላቸውና ለደቀመዛሙርቱ «መከሩስ ብዙ ነው ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፡፡ እንግዲህ የመከሩን ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞችን እንዲልክ ለምኑት» ብሎ ነበር (ማቴ.9፡36-38)፡፡ በዘመናችንም በተመሳሳይ ሁኔታ ባለማወቅ የጠፋና በሰው ሥርዓተ ሃይማኖት የተያዘ፣ ተጨንቆና ተጥሎ ያለ፣ የተወደደውንና የከበረውን የክርስቶስን ማንነት መስማት የሚያስፈልገው ብዙ ሕዝብ በዙሪያችን አለ፡፡ ጌታ ኢየሱስ ዛሬም ለዚህ ሕዝብ ያዝናል፡፡ የክርስቶስ ልብ ያለንና ይህ የሚሰማን ሁላችን ጌታ እውነተኛ የመከር ሠራተኞችን እንዲያስነሳ ልንጸልይ ይገባል፡፡

እርኞች



Amharic Bible-|- The Holy Bible [King James Version]