trinity  


4. እረኞች

ወንጌል ሰባኪዎች በማያምኑት መካከል በሚያቀርቡት የወንጌል ቃል ልባቸው ተነክቶ ወደ ክርስቶስ የመጡት ነፍሳት የሚያስፈልጋቸው ቀጣይ አገልግሎት ደግሞ የእረኝነት አገልግሎት ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ የእርሱ የሆኑት ሁሉ በእረኝነት አገልግሎት እንዲጠበቁ፣ እንዲመገቡና እንዲሰማሩ ይፈልጋል፡፡ ስለሆነም ይህን የሚያገለግሉ እረኞችን ለቤተክርስቲያን በየጊዜው ይሰጣል፤ ከዚህ ቀጥሎ እነዚህን ጌታ ኢየሱስ የሚሰጠንን እረኞች በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረንን እውነት እንመለከታለን፡፡

የእረኝነትን አገልግሎት ምንነት ለመረዳት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መልካም እረኝነት የተጻፈልንን መረዳቱ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ በዮሐ.10፡1-16 ራሱ ኢየሱስ ስለ መልካም እረኝነቱ ያስተማረው ቃል በስፋት ተጽፎልናል፡፡ «እውነት እውነት እላችኋለሁ ወደ በጎች በረት በበሩ የማይገባ በሌላ መንገድ ግን የሚወጣ እርሱ ሌባ ወንበዴም ነው፤ በበሩ የሚገባ ግን የበጎች እረኛ ነው» (ቊ.1)፤ በዚህ ምሳሌ የእውነተኛ እረኛ ባሕርይ ከሌባው እና ከወንበዴው ባሕርይ ተለይቶ በበሩ የሚገባ ሆኖ ቀርቦልናል፡፡ እረኛው በበረቱ ላሉት ለእነዚያ በጎች በእርግጥ እረኛቸው እርሱ እስከሆነ ድረስ ወደ በረቱ ተሰውሮ በድብቅ ለመግባት የሚፈልግበት ምንም ዓይነት ሁኔታ የለም፤ ማንም ሰው እያየው በግልጽ በታወቀው በር ይገባል፡፡ ስለሆነም በበር መግባት ፍጹም ግልጽነትንና እውነተኝነትን ያሳያል፡፡ ጌታ ኢየሱስም «እኔ በግልጥ ለዓለም ተናገርሁ፤ አይሁድ ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኩራብና በመቅደስ እኔ ሁልጊዜ አስተማርሁ፤ በስውር ምንም አልተናገርሁም» ለማለት የተቻለው እውነተኛ እረኛ ነው (ዮሐ.18፡2)፡፡ ይህም የሚያሳየው አገልግሎቱ ሁሉ ማንም የሚያየውና የሚሰማው ለሁሉ የተገለጠ እንደነበረ ነው፡፡ በበሩ የሚገባ የእውነተኛ እረኛ ጠባይ እንዲህ ነው፡፡ በቤተክርስቲያንም ጌታ የሚያስነሣቸው እረኞች አገልግሎታቸው በብርሃን የሆነና ለማንም የተገለጠ አገልግሎት ሊሆን ይገባል፡፡ አንዳንድ ጊዜ የልብ አሳብንና የወደፊት ዓላማን በመሰወር በሕዝብ መካከል በመግባት ነፍሳትን መማረክ እንደሚቻል የሚያስቡ ቢኖሩ ይህ የሌቦቹና የወንበዴዎቹ ባሕርይ እንጂ የእውነተኛው እረኛ ባሕርይ አለመሆኑን ከዚህ ሊማሩ ይገባል፡፡ ጌታ ኢየሱስ በድብቅ ወይም «አዩኝ አላዩኝ» በሚል መሹለክለክ የሚፈጸም የእረኝነት አገልግሎትን ይጸየፋል፤ ምክንያቱም ይህ በበሩ መግባት መውጣት ሳይሆን በሌላ በርና በሌላ መንገድ መግባት መውጣት በመሆኑ ነው፤ ይህም የሌባውና የወንበዴው አገልግሎት ነው፡፡ ወንጌል ለተመሰከረላቸውና ልባቸው ለተነካ ነፍሳት የሚሰጥ የእረኝነት አገልግሎት በብርሃን ወይም በግልጽ ሊሆን ይገባል፤ የሚነገራቸው እውነትም ተድበስብሶ ወይም ተሸቃቅጦ ሊነገራቸው አይገባም፤ በፍጹም ግልጥነት የእግዚአብሔርን እውነት ማወቅ ይኖርባቸዋል፤ በዚህ ዓይነት ነፍሳትን በየግላቸው የሚያገለግሉ እረኞች በበሩ የሚገቡና የሚወጡ እረኞች ናቸው፡፡

«ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል፤ በጎቹ ድምፁን ይሰሙታል፤ የራሱንም በጎች በየስማቸው ጠርቶ ይወስዳቸዋል» (ቊ.3)፡፡ በዚህ ክፍል እረኛው ከበጎቹ ጋር ባለው የቅርብ ግንኙነት የተነሣ በጎቹን በየስማቸው እንደሚያውቃቸው እንረዳለን፡፡ ጌታ ኢየሱስም «የእርሱ የሆኑትን ያውቃል» (2ጢሞ.2፡14)፤ በዚሁ በዮሐ.10፡15 ላይ እንደምናነበው እርሱ ራሱ «መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ አብም እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው የራሴን በጎች አውቃለሁ፤ የራሴም በጎች ያውቁኛል» ብሎ ተናግሯል፡፡ ስለሆነም በእረኝነት አገልግሎት ውስጥ እረኞች የሚያገለግሏቸውን አማኞች በሚገባ ሊያውቋቸው ይገባል፡፡ ከስማቸው ጀምሮ አጠቃላይ ያሉበትን ሁኔታ በቅርበት አውቀው አስፈላጊውን መንፈሳዊ አገልግሎት ሊሰጧቸው ይገባል፡፡

«የራሱንም ሁሉ ካወጣቸው በኋላ በፊታቸው ይሄዳል፡፡ በጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል፤ ከሌላው ግን ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉትም፤ የሌሎችን ድምፅ አያውቁምና» (ዮሐ.4-5)፤ በዚህ ንባብ እረኛው የበጎቹ ባለቤት ሆኖ ይታያል፤ ስለሆነም በጌታ በኢየሱስ ላመኑ ሁሉ ባለቤት የሆነው «ትልቁ የበጎች እረኛ» ራሱ ኢየሱስ ነው (ዕብ.13፡20)፤ እርሱ ለቤተክርስቲያን የሰጣቸው እረኞች ግን የሚጠብቁት የእርሱን በጎች በመሆኑ የበጎቹ ባለቤት አለመሆናቸው ሊታወቅ ይገባል፡፡ ይሁን እንጂ ከእርሱ በአደራ የተሰጧቸውን በጎች ለማገልገል የእርሱን ምሳሌነት ሊከተሉ ይገባል፡፡ ስለሆነም እረኛው በጎቹን ለመምራት በፊታቸው እንደሚሄድ ሁሉ የክርስቶስን በጎች የሚያገለግሉ እረኞችም ቀጣዩን የክርስትና ሕይወት ጉዞ ለማሳየት ሁልጊዜም በፊታቸው ሊሄዱ ይገባል፡፡ ይህም ማለት ነፍሳት በክርስቶስ አምነው ከዳኑ በኋላ እንዴት እንደሚጸልዩ፣ እንዴት እንደሚያመልኩ፣ ክፉውን እንዴት እንደሚያሸንፉ፣ በፈተና እንዴት እንደሚጸኑ በእግዚአብሔር ቃል ከማስረዳት በተጨማሪ በተግባርም በሕይወት እየኖሩ በመልካም ምሳሌነት ጭምር በፊታቸው ሊወጡና ሊገቡ ይገባል ማለት ነው፡፡ እንደዚሁም እረኛው ለበጎቹ የሚሆን ምግብ ወደሚገኝበት የማሰማሪያ ቦታና ወደ ዕረፍት ውኃ እንደሚመራቸው ሁሉ እነዚህም አገልጋዮች ነፍሳትን የእግዚአብሔርን ቃል ተመግበው የነፍስ ዕረፍት ወደሚያገኙበት መንፈሳዊ መሰማሪያ ሁልጊዜም ሊመሯቸው ይገባል፡፡ ይህም ከሆነ የክርስቶስ በጎች ያንኑ የተቀደሰ ፈለግ ተከትለው ይጓዛሉ ማለት ነው፡፡

እረኞች በዮሐንስ 10 ከተነገረው የኢየሱስ መልካም እረኝነት ሊማሩ የሚገባቸው ሌላው ነገር ደግሞ ስለሚጠብቋቸው የክርስቶስ በጎች ራስን እስከመስጠት የሚደርስ ታማኝነትን ነው፤ ክርስቶስ ኢየሱስ ነፍሱን ስለ በጎቹ የሚያኖር መልካም እረኛ መሆኑን ሲገልጥ፡- «መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል፡፡ እረኛ ያልሆነው በጎቹም የእርሱ ያልሆኑ ሞያተኛ ግን ተኩላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኩላም ይነጥቃቸዋል፤ በጎቹንም ይበትናቸዋል፡፡ ሞያተኛ ስለሆነ ለበጎቹም ስለማይገደው ሞያተኛው ይሸሻል፡፡ መልካም እረኛ እኔ ነኝ አብም እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው የራሴን በጎች አውቃለሁ፤ የራሴም በጎች ያውቁኛል፤ ነፍሴንም ስለ በጎች አኖራለሁ» (ቊ.11-15) ብሏል፡፡ በዚህ ክፍል ጌታ ኢየሱስ መልካሙን እረኛ ከሞያተኛው እረኛ በተቃራኒ መልኩ በማነጻጸር የመልካሙን እረኛ ታማኝነትና እውነተኛነት ገልጧል፡፡ ሞያተኛው እረኛ ተኩላ በሚመጣ ጊዜ በጎቹን ትቶ የሚሸሽ ሲሆን መልካሙ እረኛ ግን ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል፤ ሞያተኛው እረኛ በጎቹን ትቶ የሚሸሸው ለበጎቹ ስለማይገደው እንደሆነ ሁሉ መልካሙ እረኛ ደግሞ ነፍሱን ስለበጎቹ የሚያኖረው ለበጎቹ ግድ ስለሚለው ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ነፍሱን ስለ እነርሱ እስከማኖር ድረስ የእርሱ የሆኑትን ሁሉ የወደደ መልካም እረኛ ነው፡፡ እርሱ ለቤተክርስቲያን የሰጣቸው እረኞችም ይህን ባሕርይ ሊይዙ ይገባቸዋል፡፡ ለሚያገለግሏቸው የክርስቶስ በጎች ግድ የሚላቸው፣ ፍቅር ያላቸውና በቅርበት ሆነው በየግላቸው ያሉበትን መንፈሳዊ ሁኔታ የሚከታተሉ፣ ክፉው ሰይጣንና የእርሱ መልእክተኞች እነዚያን ነፍሳት ለመንጠቅ በሚተጉበት ወቅት ስለ እነርሱ ራሳቸውን አሳልፈው በመስጠት የሚጋፈጡ½ የሚደርስባቸውን ፈተናም ሆነ የተለያየ ችግር አብረው የሚካፈሉ መሆን እንዳለባቸው ከመልካሙ እረኛ ከኢየሱስ ሊማሩ ይገባል፡፡

ትልቁ እረኛ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ገና ወደ በረቱ ያልገቡ ሌሎች በጎችንም በተመለከተ የሚያደርገውን የእረኝነት ሥራ በተመለከተ ሲናገር «ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል፡፡ ድምፄንም ይሰማሉ አንድም መንጋ ይሆናሉ እረኛውም አንድ» ብሏል (ቊ.16)፡፡ በመጀመሪያ ወደ ክርስቶስ የመጡት አማኞች ከአይሁድ ወገን በመሆናቸው በበረቱ ውስጥ አስቀድመው የገቡት በጎች አይሁድ የነበሩ ናቸው፤ ስለሆነም በዚህ ክፍል ሌሎች በጎች ብሎ የጠራቸው ከአሕዛብ በእርሱ የሚያምኑ መሆናቸውን እንረዳለን፡፡ በዚህም አባባሉ በወንጌል ሥራ አማካኝነት የቤተክርስቲያን ዘመን እስኪጠናቀቅ ድረስ ስለሚጨመሩ በጎች (ነፍሳት) ተናግሯል፡፡ ይህም ከአሕዛብ መካከል ያሉትን በጎች ወደ በረቱ ማምጣት በመልካም እረኝነቱ በልቡ ያለው የእርሱ ዕቅድ ነው፡፡ ስለሆነም ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በወንጌል ስብከት ልባቸው ተነክቶ በኢየሱስ የሚያምኑት ሁሉ የእርሱ በጎች እየሆኑ በእርሱ እረኝነት እንዲጠበቁ ወደ በረቱ እየገቡ ይገኛሉ፡፡ ይህም የሚያመለክተን የእረኝነት አገልግሎት በቤተክርስቲያን ዘመን ሁሉ ጌታ ለሚጠራቸው ነፍሳት በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን ነው፡፡ አንዱ እረኛ እርሱ በዘመናት ሁሉ የሚጠራቸውን በጎቹን የሚያስጠብቀው በየጊዜው በጸጋ በሚሰጠን የታመኑ እረኞች ነውና፡፡

በእረኝነት አገልግሎት ውስጥ ራሱን ለክርስቶስ በጎች አሳልፎ እስከ መስጠት የሚደርስ ፍቅር ሊኖረን እንደሚገባ ተመልክተናል፤ ይህም የእውነተኞች እረኞች ዓይነተኛ ምልክት ነው፡፡ እረኞች ሆነው ለቤተክርስቲያን የተሰጡ ወንድሞችን ወደዚህ እውነተኛ አገልግሎት ሊያደርሳቸው የሚችለውና የእረኝነት አገልግሎታቸው ዋነኛ መንስኤ ሊሆን የሚችለው የእረኞች አለቃ የሆነውን ክርስቶስን መውደድ ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በጎቹን በአደራ ከሚሰጣቸው እረኞች የሚፈልገው የመጀመሪያ ነገር ቢኖር እረኞቹ ለእርሱ ያላቸው ፍቅር ነው፡፡ ይህም ለጴጥሮስ የእረኝነት አገልግሎትን በአደራ በሰጠበት ወቅት ተገልጧል፡፡ በዮሐ.21፡15-17 ያለውን ክፍል በምናነብ ጊዜ ጌታ ለ3 ጊዜያት ያህል «የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ ትወደኛለህን?» እያለ ጴጥሮስን የጠየቀውን ጥያቄ ስንመለከት ይህን በሚገባ እንረዳለን፤ ጴጥሮስ ቀደም ሲል «ሁሉ ቢሰናከሉ እኔ ከቶ አልሰናከልም፤... ከአንተ ጋር የምሞት እንኳ ቢሆን ከቶ አልክድህም» በማለት በራሱ ቢተማመንም (ማር14፡2931) ይህን ቃሉን ባለመጠበቅ ውድቀትን አሳይቶ ስለነበር «ትወደኛለህን?» ለሚለው የጌታ ጥያቄ የሰጠው መልስ «ጌታ ሆይ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ» የሚል ነበር፡፡ በዚህን ጊዜ ጴጥሮስ በጌታ የሚታመንና የሚደገፍ ሆኖ ስለነበር በጎቹን ከጌታ በአደራ ለመቀበል ቻለ፡፡ ጌታም አደራውን ሲሰጠው «ግልገሎቼን አሰማራ፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ፣ በጎቼን አሰማራ» ሲለው እናያለን፡፡ በዚህም መልካሙ እረኛ ኢየሱስ የእረኝነት አገልግሎትን እርሱን ለሚወዱ እና በእርሱ ለሚደገፉ ራሱ ለሚያስነሣቸው እረኞች አሳልፎ እንደሰጠ ለመረዳት እንችላለን፡፡ ስለሆነም እረኞች የሚያገለግሏቸው በጎች ከትልቁ እረኛ ከኢየሱስ በአደራ የተረከቧቸው እንደሆኑ ምንጊዜም መዘንጋት የለባቸውም፤ እነርሱም በመንፈሳዊ ዕድገታቸው የተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሊሆኑ እንደሚችሉ «ግልገሎቼ»፣ «ጠቦቶቼ» እና «በጎቼ» ከሚሉት አገላለጾች እንረዳለን፤ ጌታችን በዚህ መልክ የበጎቹን የዕድገት ደረጃ በ3 ከፍሎ ማስቀመጡም የእረኝነት አገልግሎት፣ የሚገለገሉት ነፍሳት ያሉበትን መንፈሳዊ ዕድገት ማገናዘብ የሚገባው መሆኑን ያስተምረናል፡፡ ይህም የሚያመለክተው በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ገና ግልገል ለሆኑትና የስሜታዊነቱን ወራት ማለትም ጠቦትነቱን አልፈው በመንፈሳዊ ነገር ለጎለመሱት በጎች የሚያስፈልገው አገልግሎት «ማሰማራት» መሆኑን ነው፡፡ አዲስ አማኞች እስኪጠነክሩ ድረስ እንደ አቅማቸው አንድ ሰው ስለ እግዚአብሔር ቃላት መጀመሪያ ያለውን የሕፃንነት ትምህርት በሚማርበት መስክ ላይ ሊሰማሩ ይገባቸዋል፡፡ ከዚያ በኋላ የማሰማራቱ አገልግሎት የሚቀጥል ቢሆንም በእግዚአብሔር ቃል እያደጉ ሄደው በራሳቸው አንዳንድ እውነቶችን መመርመር በሚጀምሩ ጊዜ ከመለኮታዊው እውነት እንዳይስቱና በክፉ ትምህርቶች እንዳይደናገሩ በይበልጥ «የመጠበቅ አገልግሎት» ሊደረግላቸው ይገባል፤ ይህ የጠቦትነት ጊዜ ስለሆነ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ የሚገባበት ወቅት ነው፡፡ ከዚያም ሁሉን ለይተው በእግዚአብሔር እውነቶች ሁሉ ካረፉ በኋላም ቢሆን የእረኝነት አገልግሎት ያስፈልጋቸዋል፤ ያም የማሰማራቱ አገልግሎት ነው፤ በመንፈሳዊ ነገር የጎለመሱት እነዚህ አማኞች በለመለመው መስክ የማይሰማሩ ከሆነ የሥጋ ፈቃድና ዓለማዊነት ሊበረቱባቸው ይችላሉ፡፡ ስለሆነም ከእነዚህ አደጋዎች እንዲጠበቁ የእግዚአብሔርን ቃል በሚመገቡበት መንፈሳዊ መስክ ላይ ሁልጊዜም ሊሰማሩ ይገባል፤ ይህም እረኞች እነዚህ «በቃ አድገዋል ምንም አያስፈልጋቸውም» ብለው አንዳንድ በጎችን መተው እንደሌለባቸው ሁልጊዜም ሊያሰማሯቸው እንደሚገባ ያሳያል፡፡ ይሁን እንጂ በሁሉም የዕድገት ደረጃ ላይ የሚገኙት በጎች የክርስቶስ እንጂ የእረኞቹ አይደሉም፡፡ በመሆኑም ለበጎቹ የሚሆን ተገቢ አገልግሎት ለመስጠት እረኞች ለበጎቹ ባለቤት ለክርስቶስ ያላቸው ፍቅር እጅግ ወሳኝ ነው፤ እንዲያውም ለበጎቹ ከሚኖራቸው ፍቅር አስቀድሞ ለእርሱ ለበጎቹ ባለቤት የሚኖራቸው ፍቅር የአገልግሎታቸው መነሻ ሊሆን ይገባል፡፡

ከ5ቱ ስጦታዎች መካከል አንዱ የሆነው የእረኞች ስጦታ እንደሌሎች አራቱ ስጦታዎች ሁሉ ለመላይቱ ቤተክርስቲያን የሚሰጥ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ስጦታው የሚገለጠውና ሥራ ላይ የሚውለው በየአጥቢያ ቤተክርስቲያናቱ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በተለያዩ ከተሞችና መንደሮች በሚኖሩ አብያተ ክርስቲያናት ብዙ እረኞች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ሆኖም እያንዳንዷን ቤተክርስቲያን በመልካም ያስተዳድሩ ዘንድ ጌታ በየአጥቢያው የሚያስነሣቸው ወንድሞችም የእረኝነት ሥራን ይሠራሉ፡፡ እነዚህም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ «ሽማግሌዎች» ወይም «በጌታ የሚገዙ» ተብለው የተገለጡት ናቸው፡፡ የእነርሱ የእረኝነት ሥራ ባሉበት አጥቢያ ቤተክርስቲያን ያሉትን ሁሉንም የእግዚአብሔርን መንጋ (አማኞች) በመልካም ማስተዳደር ነው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ደግሞ እንደ መንጋው ብዛት ጌታ በአንድ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ውስጥ በተጨማሪ የሚያስነሣቸው እረኞች ይኖራሉ፤ እነዚህ እረኞች ጉባኤውን የሚያስተዳድሩ ላይሆኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን በተሰጣቸው የእረኝነት ጸጋ የተወሰኑ አማኞችን በግል የመከታተልና የመጠበቅ እንደዚሁም የመመገብ አገልግሎት ይኖራቸዋል፡፡ ሌሎች አማኞች ጸጋቸውን አይተው እንዲያገለግሉ ሊያበረታቷቸው ከሚችሉ በቀር እረኞች ሆነው እንዲያገለግሉ የሚመድባቸውም ሆነ የሚያሰማራቸው ለሥራቸውም ፕሮግራም የሚያወጣላቸው ማንም ሰው ሊኖር አይገባም፡፡ ጠቅለል ባለ አነጋገር ሽማግሌዎች ሁሉ እረኞች ሲሆኑ እረኞች ሁሉ ግን ሽማግሌዎች አለመሆናቸው ሊታወቅ ይገባል፡፡ ይሁን እንጂ በየአጥቢያ ቤተክርስቲያናቱ በመልካም በሚያስተዳድሩ ማለትም የሽማግሌነትን ሥራ በሚሠሩ ወንድሞች አገልግሎት ውስጥ የእረኝነት አገልግሎትን ስለምናገኘው የእረኝነት አገልግሎት ምን ምን እንደሆነ ስለ ሽማግሌዎች አገልግሎት ከተነገሩ ክፍሎች እናጠናለን፡፡

  1. 1ኛ. መንጋውን መጠበቅ

በሐዋ.ሥ.20፡28-30 ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ቤተክርስቲያን ሽማግሌዎች የተናገረውን የእረኝነት ሥራ እናነባለን፡፡ «በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፡፡ ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፣ ደቀመዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ» ብሏቸዋል፡፡ በዚህ ክፍል «ጳጳሳት» የተባሉት ሰዎች ከፍ ብሎ በቊ.17 ላይ ደግሞ «ሽማግሌዎች» ተብለው ተጠርተዋል፤ እነርሱም በእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ያለውን መንጋ እንዲጠብቁ መንፈስ ቅዱስ የሚሾማቸው ናቸው፡፡ መንጋውን የሚጠብቁትም ከውጪ ወደ ውስጥ ከሚገቡ ጨካኞች ተኩላዎች እና በውስጥ ደግሞ ከአማኞች መካከል ተነሥተው ደቀመዛሙርትን ወደ ኋላ ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን ከሚናገሩ ሰዎች ነው፡፡ ሁለቱም ዓይነት ሰዎች ለክርስቶስ መንጋ ጠንቅ ናቸው፡፡ ሥራቸውን የሚሠሩት ደግሞ በተኩላው ባሕርይ ተመሳስሎ በመቅረብ የሐሰትና የክህደት ትምህርትን በመዝራት ወይም የእግዚአብሔርን ቃል በማጣመም ነው (2ጴጥ.3፡16)፡፡ በ2ቆሮ.11፡13-15 ላይ ተንኰለኞች ሠራተኞች የተባሉትም በዚህ የተነሣ ነው፡፡ ሽማግሌዎች ይህንን ተንኰላቸውን አውቀው ከውጪ ሾልከው ከገቡትም ሆነ በውስጥ ተመሳስለው ከተቀመጡት ተንኰለኞች ሠራተኞች እና ከሚያሰራጩት ክፉና ሐሰተኛ ትምህርት መንጋውን ሊጠብቁ ይገባል፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት የክርስቶስንና የሐዋርያትን ትምህርት በማስተማር ነው፡፡ ሽማግሌዎች ይህን አገልግሎት በአጥቢያ ቤተክርስቲያን ደረጃ የሚያከናውኑ ሲሆኑ አጥቢያ ቤተክርስቲያኑን የማስተዳደር ኃላፊነት የሌላቸው ነገር ግን የእረኝነት ጸጋ የተሰጣቸው ሌሎች ወንድሞችም በተሰጣቸው ጸጋ ይህንኑ ሥራ ይሠራሉ፡፡ ስለዚህ አንዱ የእረኞች አገልግሎት በቅርበት የሚያገለግሏቸውን ነፍሳት ከውጭ ከሚገቡ ጨካኞች ተኩላዎችና በውስጥ ሊነሱ ከሚችሉ ጠማማ ነገርን ከሚናገሩ ሰዎች መጠበቅ ነው፤ በ1ጴጥ.5፡2 ላይም «በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ» ተብሎ ለሽማግሌዎች የተመከረው ቃልም ይህንኑ የሚገልጽ ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስም «ጠቦቶቼን ጠብቅ» ብሎ ለጴጥሮስ የነገረውን ስናስብ ገና ብዙ ነገሮችን ማስተዋል የሚጠበቅባቸውና በመንፈሳዊ ነገር ያልጎለመሱ፣ በጠቦትነት ደረጃ ያሉና በስሜታዊነትም ለሚመላለሱ አማኞች «የመጠበቅ አገልግሎት» በይበልጥ አስፈላጊ መሆኑን እንረዳለን፡፡

  1. 2ኛ. መንጋውን መጐብኘት

በ1ጴጥ.5፡2 ላይ የእግዚአብሔርን መንጋ በእረኝነት ለሚጠብቁ ሽማግሌዎች ከተሰጠው ምክር አንዱ «እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፣ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት» ይላል፡፡ ይህ በጥቅሉ ለሽማግሌዎች በአጥቢያ ቤተክርስቲያን ደረጃ ያላቸውን ኃላፊነት የሚያሳይ ሲሆን መመሪያው ግን የእረኞችን ሁሉ አገልግሎት ያሳያል፡፡ የክርስቶስ መንጋ ከሚያስፈልገው አገልግሎት አንዱ መጐብኘት ነው፡፡ አንድ እረኛ በጎቹን በሚጎበኝበት ጊዜ እነዚያ በጎች ያሉበትን የኑሮ፣ የጤና የአመጋገብና... የሌላም ሁኔታ ያያል፤ በዚያ የጎደላቸው ነገር ካለ የሚሟላበትን መንገድ ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ ጉብኝቱ ለመንጋው ሲባል እንጂ ለእረኛው ሲባል አይደለም፡፡ እረኞች ይህንን ተረድተው የሚያገለግሏቸውን የክርስቶስን መንጎች በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ ያውቁ ዘንድ በየጊዜው ጉብኝት ሊያደርጉላቸው ይገባል፡፡ ይሁን እንጂ ጉብኝቱ የሚከናወነው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ መሆን የለበትም፡፡ እረኞች የጉብኝት ሥራ በሚሠሩበት ጊዜ ወደውና ፈቅደው በደስታ ሊያደርጉት እንደሚገባ እንጂ በኃይል የተጫነባቸው ይመስል በግድ መሆን እንደሌለበት የሚገልጽ ነው፡፡ እንደዚሁም በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት መሆን የለበትም፤ እረኞች ከሚጎበኟቸው አማኞች ሊያገኙት የሚችሉትን ሥጋዊ ጥቅም እያሰቡ ሊጎበኙ የሚዞሩ መሆን እንደሌለባቸው በዚህ ቃል ተመክረዋል፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ ጥቅም «መጥፎ ረብ» ተብሏል፡፡ ስለዚህ እረኞች በሌላ በምንም ዓይነት ጥቅም ተነድተው ሳይሆን በቃሉ እንደተነገረው በበጎ ፈቃድ ላይ ብቻ ተመሥርተው፣ አደራውን የሰጣቸው የክርስቶስ ፍቅር ብቻ ግድ ብሏቸው ለመንጋው የተቀደሰ ጉብኝት ሊያደርጉ ይገባል፡፡

  1. 2ኛ. መንጋውን መጐብኘት

ጌታ ኢየሱስ ስለ እውነተኛ እረኛ በተናገረበት ክፍል «... የራሱንም ሁሉ ካወጣቸው በኋላ በፊታቸው ይሄዳል» የሚለውን ቃል ተመልክተናል፤ እረኞች የክርስቶስን መንጋ በመልካም ምሳሌነት እየመሩ የክርስትና ሕይወትን የጉዞ አቅጣጫ ሊያሳዩ እንደሚገባም አይተናል፡፡ በእርግጥም መልካም ምሳሌነት ሁል ጊዜም ቢሆን በእረኞች ላይ ሊታይ የሚገባው ነገር ነው፤ በ1ጴጥ.5፡3 ላይ ከሌሎቹ ምክሮች ቀጥሎ ለሽማግሌዎች የተሰጠው አንዱ ምክር «ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ» የሚል ነው፡፡ እረኞች የክርስቶስ ለሆኑት አማኞች የሚያስተምሯቸውን ቃል እንዲታዘዙ በኃይለ ቃል ወይም በማስጨነቅ መናገርና በግድ እንዲታዘዙ ማድረግ ተገቢ እንዳልሆነና ውጤትም እንደሌለው ከዚህ ንባብ እንረዳለን፡፡ ተገቢ የሆነውና ውጤት የሚያስገኘው አገልግሎት ግን በተግባር ለመንጋው ምሳሌ ሆኖ መገኘት ነው፡፡ በ1ጢሞ.4፡12 ላይ «... ለሚያምኑት ምሳሌ ሁን እንጂ...» የተባለውም ለዚህ ነው፡፡

በዘመናችን የክርስቶስ መንጋ ከፍ ባለ ግራ መጋባት ወዲያና ወዲህ እየተቅበዘበዘ ሲባዝን ይታያል፡፡ ይህ ደግሞ ለክርስቶስ ልብ በእጅጉ የሚያሳዝን ነው፤ እርሱ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተጥለውና ተጨንቀው ለነበሩ ሕዝቦች እንዳዘነላቸው የተጻፈው ቃል ይህን የእርሱን ስሜት እንድናውቅ ያስችለናል (ማቴ.9፡36)፡፡ ስለሆነም ይህን የሚቅበዘበዝ ሕዝብ የሚጠብቁና የሚያሰማሩ እረኞችን ጌታ በዘመናችንም ቢሆን ይሰጣል፤ እነዚህ በእርግጥ ጌታ የሰጠን እረኞች ለእርሱ ባላቸው ፍቅር ነፍሳትን በታማኝነትና በቅርበት የሚያገለግሉ እረኞች ናቸው፡፡ በአንድ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ብዙ እረኞች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በዚህ ዘመን በዙሪያችን ባለው የክርስትና ዓለም ያለውን አሠራር ስንመለከት ግን ከዚህ በተቃረነ መልኩ በአንድ አጥቢያ «አንድን ሰው ብቻ» ፓ¬ስተር የሚያደርግ ወይም በአንዳንድ ቦታ እንደሚታየው «ረዳት ¬ፓስተሮችን» ጨምሮ የሚሾም የሰው ሥርዓት ይታያል፡፡ ይህም የቤተክርስቲያን ሥልጣን ተደርጎ ሲቆጠርና ከፓ¬ስተሩና ከረዳት ፓ¬ስተሩ ውጪም በዚያው አጥቢያ ሌሎች ¬ፓስተሮች (እረኞች) ሊኖሩና ሊያገለግሉ እንደማይችሉ ተደርጎ ሲወሰድ ይታያል፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ የሰው ሐሳብ ተለይተን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ስንመለስ እረኝነት «ዋና ¬ፓስተርም» ሆነ «ምክትል (ረዳት) ፓስተር» እየተባለ በሰው የሚሰጥ የሥልጣን ሹመት ሳይሆን ከጌታ የምንቀበለው የጸጋ ስጦታ መሆኑን እንረዳለን፤ እንደዚሁም ጌታ በአንዲት አጥቢያ ቤተክርስቲያን ውስጥ እንደሚያስፈልገው መጠን ከአንድ በላይ ፓ¬ስተሮችን (እረኞችን) ሊሰጥ እንደሚችል እንገነዘባለን፡፡ እነዚህ ጌታ የሚሰጠን እረኞችም የሚጠብቋቸውን፣ የሚያሰማሯቸውንና የሚጎበኟቸውን በጎች ራሱ ጌታ ይሰጣቸዋል፤ ይህንንም እርሱ በየጊዜው በተለያየ መንገድ ወደ እነርሱ በማምጣትና በማገናኘት የሚያከናውነው ይሆናል፡፡ በዚህ መልክ ጌታ ወደ እነርሱ ያቀረባቸውን ነፍሳት እረኞች በታማኝነትና በትጋት ሊያገለግሏቸው ይገባል፡፡

ጌታችን ለቤተክርስቲያን የሰጣቸው እረኞች በሰው ሥርዓት መሾምንና «¬ፓስተር» ተብለው መጠራትን የሚፈልጉ አይደሉም፤ በዚህ ባለንበት ዘመን በክርስትናው ዓለም ያለውን የእረኝነት አገልግሎት ስንቃኝ ግን በብዛት የተለመደው አሠራር በአንድ ጉባኤ ላይ አንድን ሰው «¬ፓስተር» ብሎ በመሾም የሚታየው አሠራር ነው፡፡ አንዲትን አጥቢያ ቤተክርስቲያን (ጉባኤ) በመልካም የሚያስተዳድሯት እረኞች መንፈስ ቅዱስ የሚያስነሣቸውና የሽማግሌነትን ሥራ የሚሠሩ ወይም በጌታ የሚገዙ ወንድሞች ናቸው እንጂ አንድ እረኛ (¬ፓስተር) አይደለም፡፡ በዘመናችን በድርጅታውያን አብያተ ክርስቲያናት የሚታየው የአንድ ሰው አስተዳደር ግን የሰው ሥርዓት ነው እንጂ ከእግዚአብሔር ቃል የተገኘ አይደለም፡፡ እንደዚሁም ጌታ ለቤተክርስቲያን የሚሰጣቸው እረኞች ራሱ በጊዜው በእረኝነት አገልግሎት እያተጋ በየአጥቢያ ቤተክርስቲያኑ የሚገልጣቸው እንጂ ከአንድ ሥልጠና ወይም ከአንድ የቲዎሎጂ ት/ቤት የተመረቁ ስለሆኑ ብቻ በሰው የሚሾሙ አይደሉም፡፡ ፓ¬ስተርነት (እረኝነት) ዲግሪ ወይም ዲፕሎማ የሚቀበሉበት አንድ ምድራዊ ሙያ ሳይሆን ጌታ መንጋውን ለማስጠበቅና ለማስመሰግ ለቤተክርስቲያኑ የሚሰጠው ስጦታ ነው፤ ስለሆነም በዚህ ዓለም ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንደተመረቁበት የትምህርት ዓይነት «ዶክተር እከሌ» ወይም «ኢንጂነር እከሌ» .... እየተባሉ በሙያዊ የማዕረግ ስም እንደሚጠሩበት ልማድ «¬ፓስተር እከሌ» ተብሎ የመጥራትም ሆነ የመጠራት ልማድ መኖር የለበትም፡፡ በመሠረቱ «ፓስተር» የሚለው ቃል የላቲን ቃል ሲሆን በእንግሊዘኛና በሌሎች ቋንቋዎች ሁሉ የተለመደ ቃል ሆኗል፤ ትርጉሙ ግን ሌላ ምንም ሳይሆን «እረኛ» ማለት ነው፡፡ ሆኖም በአገራችን በሰው የሚሾሙት ወይም ራሳቸውን የሚሾሙት ግለሰቦች «¬ፓስተር» እንጂ «እረኛ» ተብለው ሲጠሩ አይሰማም፤ የዚህን ምክንያት በጥንቃቄ የመረመረ ሰው «እረኛ» ብሎ በአማርኛ ከመጥራትም ሆነ ከመጠራት ይልቅ «ፓ¬ስተር» ብሎ መጥራትም ሆነ «¬ፓስተር» ተብሎ መጠራት ለሥጋ ይበልጥ ደስ ስለሚያሰኝ መሆኑ ሊሰወረው አይችልም፡፡ ሆኖም በጥቅሉ «¬ፓስተር» የሚለው የላቲን ቃልም ሆነ «እረኛ» የሚለው የአማርኛ ቃል ከመጠሪያ ስም በፊት እየገባ የሚነገር የማዕረግ ስም (ቅጽል) አለመሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ይህ አጠቃቀም በዓለም ካለው የሰው ሥርዓት ወይም «መምህር መምህር» ተብለው መጠራት ከሚወዱት ከፈሪሳውያን ልማድ የተወረሰ ጠባይ እንጂ (ማቴ.23፡7) ከመጽሐፍ ቅዱስ የተገኘ ባለመሆኑ ልንርቀው ይገባል፡፡

እረኞች በአንድ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ሥር በገንዘብ ተቀጥረው የሚያገለግሉም አይደሉም፡፡ እንዲህ ያለው አሠራር በዘመናችን በብዙ ስፍራ የተለመደ ቢሆንም ከመጽሐፍ ቅዱስ የተገኘ ግን አይደለም፡፡ በእርግጥ የእረኝነት አገልግሎቱ የእረኞቹን ሙሉ ጊዜ የሚወስድ ከሆነ እንደማንኛውም የወንጌል አገልጋይ የወንጌል ቀለብን ከሚያገለግሏቸው አማኞች መቀበል በእግዚአብሔር ቃል የሚገኝ አሠራር ነው፡፡ ሆኖም እረኞች በዓለማውያን መሥሪያ ቤቶች እንደሚሠሩ ሠራተኞች በደመወዝ ተቀጥረው የሚያገለግሉ ከሆነ ግን የሞያተኛ እረኞችን ባሕርይ ይይዛሉ፤ ስለሆነም ከዚህ ዓለማዊ አሠራር መለየት ያስፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ቃል ከሚያገለግሏቸው አማኞች የወንጌል ቀለብን እየተቀበሉ ጊዜያቸውን ለእረኝነት አገልግሎት የሰጡ ወንድሞችም ቢሆኑ ስለሚቀበሉት ቀለብ ብለው የክርስቶስን እውነት ለመንጋው ከመግለጥ ወደ ኋላ ማለት የለባቸውም፤ የመንጋውን መንፈሳዊ ዕድገት ሳይሆን ከመንጋው የሚገኘውን ረብ (ጥቅም) አይተው ጌታ ሳያሰማራቸው እረኞች ነን ብለው ለማገልገል የተነሡ ሰዎች ግን ስለሚያገኙት ጥቅም እንጂ ስለ እግዚአብሔር እውነት ግድ የላቸውም፡፡ ስለሆነም ለሰው ደስ የሚያሰኘውን እንጂ ለጌታ ደስ የሚያሰኘውን አያዩም፡፡ በዘመናችን እጅግ ብዙ በጎች እንዲህ ያለውን ነውረኛ ረብ በሚያጋብሱ ሰዎች አላግባብ ሲሸለቱ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ «ስጡ ይሰጣችኋል» የሚለው የተቀደሰ መርህ ተጣምሞ እየተተረጐመላቸው «ለተቀባውና ለባለራእዩ ወይም ለነፍስ አባታችሁ ስትሰጡ እግዚአብሔር ለእናንተ ይሰጣል» የተባሉና በእጅጉ የተበዘበዙ ብዙ የዋሃንን በዙሪያችን ስንመለከት የሞያተኞች እረኞችን የተንኰል አሠራር በእግዚአብሔር ቃል ገልጦ ለማሳየትና ለየዋሃኑ ለማሳወቅ ያለን ፍላጎት እየጨመረ ይሄዳል፡፡ የሚገርመው ደግሞ እጅግ በተገለጠ ማጭበርበር እየተበዘበዙ ያሉት ምስኪኖች እውነቱን ቢረዱም እንኳ ከዚያ የዓመፅ አሠራር ሊለዩ አለመቻላቸው ነው፤ ስለሆነም እግዚአብሔር የእነዚህን የዋሃን ዓይኖች እንዲከፍት በቃልና በጸሎት ልንተጋ ያስፈልጋል፡፡

እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተጥለውና ተጨንቀው ያሉትንና በሞያተኛ እረኞች እየተታለሉ በየስፍራው የሚቅበዘበዙትን የክርስቶስን በጎች በየግል እየቀረቡ የሚያስፈልጋቸውን አገልግሎት የሚሰጡ እረኞች በየዘመናቱ የሚያስፈልጉ በመሆናቸው በዘመናችንም ጌታ ያስነሣቸው እውነተኛ እረኞች በየስፍራው እንዳሉት የታመነ ነው፤ እንዲህ ያሉት እረኞች በዙሪያቸው ባለው የሃይማኖተኛ ዓለም አሠራር ሳይደናገሩ ከክርስቶስ የተቀበሉትን አደራ በትጋት ሊወጡ ይገባል፡፡ በብዙ መደነጋገርና በብዙ ጥያቄ ውስጥ የሚገኙ ብዙ የዋሃን የክርስቶስ በጎች እንዲህ ያለው አገልግሎት በእጅጉ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ጌታ በዚህ አገልግሎት የተገለጡ እውነተኛ እረኞችን አብዝቶ እንዲሰጠንም የዘወትር ጸሎታችን ሊሆን ይገባል፡፡


አስተማሪዎች



Amharic Bible-|- The Holy Bible [King James Version]