5. አስተማሪዎች
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አካሉ ለሆነች ቤተክርስቲያን ከሚሰጣቸው ስጦታዎች መካከል «አስተማሪዎች» አንደኛዎቹ ናቸው፡፡ አስተማሪዎች በኤፌ.4፡11 ላይ ከተዘረዘሩት ስጦታዎች አምስተኛ ሆነው የተጠቀሱ ቢሆንም «ከእረኞች» ጋር ተያይዘው ተገልጠዋል፤ በዚህ ክፍል «እረኞችና አስተማሪዎች» የሚለው አገላለጽ ይህንኑ የሚያስረዳ ነው፡፡ በወንጌል ሰባኪዎች አገልገሎት ወደ ጌታ የመጡት ነፍሳት በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እያደጉ እንዲሄዱ፣ እንዲታነጹ፣ እንዲጸኑ፣ የእረኞችና የአስተማሪዎች አገልግሎት በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ ሁለቱ ስጦታዎች ምንም እንኳ የተለያዩ ቢሆኑም ሁልጊዜም ባይሆን በአብዛኛው በአንድ ሰው ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ነፍሳትን በእረኝነት አገልግሎት ለመጠበቅ የአስተማሪነት ስጦታ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡ ይሁንና እረኞች ነፍሳትን በመጠበቅና በመመገብ ላይ የሚያተኩሩ ሲሆኑ አስተማሪዎች የእግዚአብሔርን እውነት በመግለጥና በማስረዳት ላይ የሚያተኩሩ ስለሆኑ ስጦታዎቹ ሁለት የተለያዩ ስጦታዎች ናቸው፡፡ ስለሆነም ሁለቱንም በተመለከተ የእግዚአብሔር ቃል የሚያስተምረንን እውነት ለይተን ማጥናት ይገባናል፡፡በ1ቆሮ.12፡28 ላይ «እግዚአብሔርም በቤተክርስቲያን አንዳንዶቹን አስቀድሞ ሐዋርያትን፣ ሁለተኛም ነቢያትን፣ ሦስተኛም አስተማሪዎችን... አደረገ፡፡» የሚል ቃል እናነባለን፤ ከዚህም ቃል አስተማሪዎች እንደ ሌሎቹ ስጦታዎች ሁሉ እግዚአብሔር በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገልጣቸው ወይም የሚያስነሣቸው መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ የእግዚአብሔርን እውነት ማስተማር በብዙዎች ሊታሰብ እንደሚችለው ከአእምሮ ብስለት፤ ከእውቀት ብዛት ወይም የተለያዩ ሥልጠናዎችንና ሴሚናሮችን ከመውሰድ ሊገኝ የሚችል አይደለም፡፡ በዘመናችን በቴዎሎጂ ት/ቤት ስለተማሩ ብቻ በአስተማሪነት ሥራ ተቀጥረው የተለያዩ ሥልጠናዎችን እንዲሰጡ የተመደቡ ሰዎችን በየስፍራው እናያለን፡፡ ከእነዚህ መካከል እግዚአብሔር ከመጀመሪያው ጸጋውን ስለሰጣቸው የሚያገለግሉ አንዳንዶች እንዳሉ የማይካድ ቢሆንም ይህ አሠራር ግን አስተማሪዎችን ለቤተክርስቲያን የሚሰጠውና በመካከላችንም የሚገልጣቸው እግዚአብሔር እንደ ሆነ ከሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር ተቃራኒ ነው፡፡ በእውነት የሚኖሩ ክርስቲያኖች ግን እግዚአብሔር በመካከላቸው አስተማሪዎችን እንደሚያስነሣና እንደሚሰጣቸው ይተማመኑበታል፡፡
አስተማሪዎች ሆነው ለቤተክርስቲያን የተሰጡ ወንድሞች የአገልግሎታቸውን ባሕርይ በአዲስ ኪዳን ዘመን የመጀመሪያው መምህር (አስተማሪ) ከሆነው ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ሊማሩ ይችላሉ፡፡ እርሱ «የእስራኤል መምህር» በነበረው በኒቆዲሞስ «መምህር ሆይ፡- እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን» ተብሎ የተመሰከረለት መምህር ነው (ዮሐ.3፡2)፡፡ ኢየሱስ በምድር ላይ ያስተምር በነበረ ጊዜ በደቀመዛሙርቱም ሆነ በሌሎች ሰዎች «መምህር ሆይ» እየተባለ ይጠራ ነበር፡፡ እርሱ በእርግጥም ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጣ መምህር ሰለሆነ መምህር ተብሎ መጠራቱ አግባብነት ነበረው፡፡ ይህንንም ራሱ ለደቀመዛሙርቱ አረጋግጦ ሲናገር «... እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ፤ እንዲሁ ነኝና መልካም ትላላችሁ» ብሏል (ዮሐ.13፡13)፤ በመልካም አስተማሪነቱም የእግዚአብሔርን እውነት በቤተመቅደስ (ዮሐ.7፡14፤ ማቴ.26፡55)፣ በምኲራብ (ማር.1፡21፤ 6፡2)፣ በተራራ ላይ (ማቴ.5፡1-2)፣ በባሕር ዳር (ማር.4፡1) ለሕዝቡና ለደቀመዛሙርቱ ያስተምር ነበር፤ በትምህርቱም የሚሰሙት ሁሉ ይገረሙ ነበር (ማቴ.7፡28፤ 22፡33)፤ ሲገረሙም «እነዚህን ነገሮች ይህ ከወዴት አገኛቸው፣ ለዚህ ሰው የተሰጠችው ጥበብ ምንድር ናት?.....» ይሉ ነበረ (ማር.6፡2)፡፡ በሚከተሉት ደቀመዛሙርቱም ሆነ በማያምኑት አይሁድ ሁሉ ዘንድ ይህን ያህል የተደነቀው እውነተኛው መምህር ጌታ ኢየሱስ በቤተክርስቲያን እግዚአብሔር ለሚያስነሳቸው አስተማሪያዎች ድንቅ አብነት (ምሳሌ) ነው፡፡
ቤተክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ መውረድ ከተመሠረተች በኋላ ሐዋርያት የመስበክ ብቻ ሳይሆን የማስተማር አገልግሎትንም ይሰጡ ነበር፤ በሐ.ሥ.5፡42 ላይ «ዕለት ዕለትም በመቅደስና በቤታቸው ስለ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ማስተማርንና መስበክን አይተውም ነበር» ተብሎ የተጻፈው ቃል ይህንን ይገልጻል፤ ስለሆነም በሐዋርያት አገልገሎት ውስጥ የወንጌል ሰባኪነትን ጸጋ እንደምናገኝ ሁሉ የአስተማሪነትን ጸጋም እናገኛለን፡፡ ይሁንና እግዚአብሔር አስተማሪዎችን በየአብያተክርስያናቱ በማስነሣት እነርሱ ራሳቸውን የቻሉ የተለዩ ስጦታዎች እንደሆነ አረጋግጧል፤ በአንጾኪያ ቤተክርስቲያን መምህራን መኖራቸው ይህን እንድናስተውል ያደርገናል፤ ይህን በተመለከተ የተጻፈው ቃልም «በአንጾኪያ ባለችው ቤተክርስቲያን ውስጥ ነቢያትና መምህራን ነበሩ፤ እነርሱም በርናባስ፣ ኔጌር የተባለው ስምዖን፣ የቀሬናው ሉክዮስም፣ የአራተኛው ገዥ የሄሮድስ ባለሟል ምናሔ፣ ሳውልም ነበሩ» የሚል ነው (የሐ.ሥ.13፡1)፤ በዚህ ቃል ውስጥም የትኞቹ ነቢያት የትኞቹ መምህራን እንደሆኑ ተለይተው ባይነገሩንም በርናባስና ሳውል የአስተማሪነት ስጦታ እንዳላቸው በሌሎች ንባቦች እንረዳለን፡፡ ለምሳሌ በሐ.ሥ.11፡26 ላይ «በቤተክርስቲያንም አንድ ዓመት ሙሉ ተሰበሰቡ፤ ብዙ ሕዝብንም አስተማሩ» ተብሎ ስለ በርናባስና ሳውል የተጻፈው ቃል በይበልጥ ላመኑ ሰዎች ለመታነጽና ለመጽናት ለማደግም የሚሆን የእግዚአብሔር ቃል ሲያስተምሩ እንደ ነበር የሚያሳይ ነው፡፡ እንደዚሁም በሐ.ሥ.15፡35 ላይ «ጳውሎስና በርናባስም ከሌሎች ከብዙ ሰዎች ጋር ደግሞ የጌታን ቃል እያስተማሩና ወንጌልን እየሰበኩ በአንጾኪያ ይቀመጡ ነበር» ሲል እነዚህ ሁለቱ አገልጋዮች በአንጾኪያ አብረው በነበሩ ጊዜ የነበራቸው አገልግሎት ወንጌልን ለማያምኑት መስበክ ብቻ ሳይሆን ላመኑትም የጌታን ቃል ማስተማር እንደነበር ያስገነዝባል፡፡ በተለይም ጳውሎስ ሐዋርያም ስለሆነ ወንጌል ወዳልደረሰበት ቦታ ሄዶ በሚሰብከው ወንጌል የሚያምኑትን ሰዎች የጌታ ደቀመዛሙርት ሆነው እንዲለዩ በማድረግ የተወሰነ ጊዜ እዚያው አብሮአቸው በመኖር የእግዚአብሔርን ቃል ያስተምራቸው ነበር፤ ለምሳሌ በቆሮንቶስ «በመካከላቸው የእግዚአብሔርን ቃል እያስተማረ ዓመት ከስድስት ወር የተቀመጠ ሲሆን በኤፌሶን ደግሞ ደቀመዛሙርትን ለይቶ ጢራኖስ በሚሉት ት/ቤት ዕለት ዕለት እየተነጋገረ ሁለት ዓመት ያህል ተቀምጧል (የሐ.ሥ.18፡11፤ 19፡9)፡፡ ለማያምኑ ሰዎችም ቢሆን በተለይም ለአይሁድ በማስረዳትና መጻሕፍትን በመተርጐም ይመሰክርላቸው ነበር (የሐ.ሥ.17፡2፤ 18፡4፤ 19፡8፤ 28፡23-31)፡፡ ይህም የአስተማሪነት ሥራ ባሕርይ ነው፡፡ ከዚህም የምንረዳው አስተማሪዎች በውስጥ ያሉትን አማኞች ለማጠንከርና ለማጽናት የሚያስችል አገልግሎት እየሰጡ ከዚህ ጐን ለጐን ደግሞ በውጭ ያሉ በጥያቄ የተሞሉ ኢአማንያንን ለማስረዳትና ለማሳመን የሚያስችል አገልግሎትን የሚሰጡ መሆናቸውን ነው፡፡
የአስተማሪነትን ጸጋ በአጵሎስ ውስጥም እናገኛለን፡፡ እርሱ ገና ሙሉውን የክርስትና እውነት ሳይረዳ በመጥምቁ ዮሐንስ ትምህርት ብቻ ይህ ጸጋው መታየት ጀምሮ ነበር፤ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እርሱ «በመጻሕፍት እውቀት የበረታ ነበረ፤ እርሱ የጌታን መንገድ የተማረ ነበረ፤ የዮሐንስንም ጥምቀት ብቻ አውቆ በመንፈስ ሲቃጠል ስለ ኢየሱስ ይናገርና በትክክል ያስተምር ነበር» (የሐ.ሥ.18፡25)፤ ይህንን ጸጋውን የተመለከቱት አቂላና ጵርስቅላም ወስደው የእግዚአብሔርን መንገድ ከፊት ይልቅ ገለጡለት(የሐ.ሥ.18፡26)፡፡ አስተማሪዎች ሙሉውን የቅዱሳት መጻሕፍት እውቀት ሊይዙ ቢገባቸውም ጸጋው የሚሰጣቸው ግን ከዚያ በፊት እንደሆነ በዚህ መረዳት ይቻላል፤ የተሰጣቸውን ጸጋ በብቃት እንዲያገለግሉበትም ከእነርሱ አስቀድመው የእግዚአብሔርን እውነት ከሚያውቁ አማኞች ዝቅ ብለው መማር እንዳለባቸውም ከአጵሎስ ሕይወት እንማራለን፡፡ አጵሎስ ወደ ቆሮንቶስ ሄዶ በአስተማሪነት ጸጋው ያመኑትንም ሆነ ያላመኑትን አይሁድን ያገለግል ነበር፡፡ «በደረሰም ጊዜ አምነው የነበሩትን በጸጋ ይጠቅማቸው ነበር፡፡ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ ከመጻሕፍት እየገለጠ ለአይሁድ በሁሉ ፊት በጽኑ ያስረዳቸው ነበርና» ተብሎ ስለ እርሱ የተጻፈው ቃል አጵሎስ በቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን የነበረውን የአስተማሪነት አገልግሎት ያመለክታል (የሐ.ሥ.18፡27-28)፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም «እኔ ተከልኩ፤ አጵሎስ አጠጣ» ብሎ በጻፈው ቃል የአጵሎስ አገልግሎት በይበልጥ አስቀድሞ በጳውሎስ ስብከት ያመኑትን አማኞች እንዲጸኑና እንዲጠነክሩ የሚረዳ መሆኑን አመልክቷል፤ የማስተማር አገልግሎት ተተክሎ የበቀለውንና የጸደቀውን ተክል እንደማጠጣት ነውና፡፡ ስለሆነም በጌታ አምነው የጸደቁ አማኞች የአስተማሪዎች አገልግሎት ያስፈልጋቸዋል፡፡
እንደዚሁም ጢሞቴዎስ የወንጌል ሰባኪነት ጸጋ ያለውን ያህል (2ጢሞ.4፡5) የአስተማሪነት ጸጋም እንደነበረው ለእርሱ ከተጻፉለት ሁለት መልእክታት መረዳት እንችላለን፡፡ እርሱ ከሕጻንነቱ ጀምሮ ቅዱሳት መጻሕፍትን ያውቅ ነበር (2ጢሞ.3፡15) ከጳውሎስም ጋር አብሮ ያገለገለ በመሆኑ የጳውሎስን ትምህርት የተከተለ ሰው ነው (2ጢሞ.3፡10)፤ ስለሆነም ጳውሎስን «ስለዚህ ወንድሞችን ብታሳስብ በተከተልከው በመልካም ትምህርት የምትመገብ መልካም አገልጋይ ትሆናለህ» በማለት ይጽፍለታል (1ጢሞ.4፡6)፤ እንዲሁም «ይህን እዘዝና አስተምር፤... እስክመጣ ድረስ ለማንበብና ለመምከር ለማስተማርም ተጠንቀቅ ... ለራስህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ» (1ጢሞ.4፡11-16)፤ «እነዚህን አስተምርና ምከር» (1ጢሞ.6፡3)፣ “… ፈጽመህ እየታገስህና እያስተማርህ ዝለፍ ገሥጽ ምከርም” (2ጢሞ.4፡2) ብሎ ጽፎለታል፡፡ እነዚህ ሁሉ ንባቦች ጢሞቴዎስ ከሌሎች የጸጋ ስጦታዎች ጋር የአስተማሪነት ጸጋ የተሰጠውና እርሱም ራሱ ለቤተክርስቲያን አስተማሪ ሆኖ የተሰጠ መሆኑን እንገነዘባለን፤ በተመሳሳይ መንገድ በቀርጤስ ሲያገለግል የነበረው ቲቶም የአስተማሪነትን ሥራ ይሠራ እንደነበር ከተጻፈለት መልእክት እንረዳለን፤ በቲቶ.2፡1 ላይ «አንተ ግን ሕይወት ለሚገኝበት ትምህርት የሚገባውን ተናገር» ተብሎ የተጻፈለት ቃል እና በቁ.8 ላይ «በትምህርትህም ደኅንነት ጭምትነትን ጤናማና የማይነቀፍ ንግግርን ግለጥ» የሚለው ቃል ቲቶ እንደ ጢሞቴዎስ ሁሉ ከሌሎች ጸጋዎች ጋር አስተማሪነት በዋናነት እንደተሰጠው የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡ በጢሞቴዎስና በቲቶ አገልግሎት ውስጥ የምናየው ይህ የአስተማሪነት ጸጋ በተለይ የአገልግሎቱን ተግባራዊ ገጽታ ለአስተማሪዎች ሁሉ የሚያሳይ ነው፡፡ በየአጥቢያ ቤተክርስቲያኑም በሐዋርያት ወይም እነርሱ ባዘዟቸው ሰዎች ይሾሙ የነበሩት ሽማግሌዎች ወይም በጌታ የሚገዙ ወንድሞች ለማስተማር የሚበቁ መሆን እንዳለባቸው ተነግሯል (1ጢሞ.3፡2፤ ቲቶ.1፡9)፡፡ «መልካም የሚያስተዳድሩ ሽማግሌዎች ይልቁንም በመስበክና በማስተማር የሚደክሙት እጥፍ ክብር ይገባቸዋል» የሚለው ቃል ሽማግሌዎች ከአስተዳደር አገልግሎታቸው ጋር የመስበክና የማስተማር ሥራ ሊሠሩ እንደሚችሉ የሚያመለክት ነው (1ጢሞ.5፡17)፡፡ ይሁንና ሽማግሌዎች ያልሆኑ አስተማሪዎችን እግዚአብሔር በየአጥቢያ ቤተክርስቲያኑ በዘመናት ሁሉ ያስነሣል፤ እነርሱንም አስተማሪዎች አድርጎ የሚሰጠው ለመላይቱ ቤተክርስቲያን በመሆኑ አገልግሎታቸው በአንዲት አጥቢያ ቤተክርስቲያን ብቻ የሚገደብ አይደለም፤ እግዚአብሔር በመንፈሱ እንደመራቸው በየስፍራው እየተዘዋወሩ በቅዱሳት መጻሕፍት የተገለጠውን መለኮታዊ ትምህርት በማስተማር ያገለግላሉ፡፡
አስተማሪዎች የሚያስተምሩት ትምህርት በክርስቶስና በሐዋርያቱ የተገለጠውን የእግዚአብሔርን እውነት ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመጣበትን ዓላማ ሲገልጥ «እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ፤ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ» ብሏል (ዮሐ.18፡37)፤ የሚናገረውንም እውነት «ከእግዚአብሔር የሰማሁት እውነት» በማለት ገልጦታል (ዮሐ.8፡40)፡፡ እርሱ በምድር ላይ እያስተማረ ሳለ አይሁድ ያልተቀበሉት፣ ነገር ግን ከእግዚአብሔር የሆነ ትምህርት ነበረው፡፡ ይህን ትምህርቱን በተመለከተ ሲናገርም «ትምህርቴስ ከላከኝ ነው እንጂ ከእኔ አይደለም፤ ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድ ቢኖር እርሱ ይህ ትምህርት ከእግዚአብሔር ቢሆን ወይም እኔ ከራሴ የምናገር ብሆን ያውቃል» ብሏል (ዮሐ.7፡16-17)፡፡ ይህም ቃል ጌታችን «ትምህርቴ» «ይህ ትምህርት» ብሎ የጠራው፣ ከሌሎች ትምህርቶች የተለየ ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጣና አንድ እውነተኛ ትምህርት እንዳለ ያስገነዝባል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ያስተማራቸው ዋና ዋና ትምህርቶችም ስለአባቱና ስለራሱ፣ ስለመንፈስ ቅዱስም ማንነት ያስተማረው ትምህርት፣ በተራራ ያስተማረው የእርሱ ደቀመዛሙርት የሚለዩበት የሥነምግባር ትምህርት (ማቴ.5-7)፣ በባሕር ዳር ስለመንግሥተ ሰማያት ምስጢር በምሳሌ ያስተማረው ትምህርት (ማቴ.13)፣ ስለዳግም ምጽአት ለደቀመዛሙርቱ ያስተማረው ትምህርት (ማቴ.24-25)፣ እንዲሁም የዘላለም ሕይወትን፣ ዳግም ልደትን፣ አምልኮን፣ ጸሎትን አገልግሎትን ... ወዘተ የሚመለከቱ የተለያዩ ትምህርቶችን አስተምሯል፡፡ ለቤተክርስቲያን የተሰጡ አስተማሪዎች ይህን የክርስቶስን ትምህርት ሊያስተምሩ ይገባቸዋል፡፡ በ2ዮሐ.9 ላይ «ለሚወጣ ሁሉ በክርስቶስም ትምህርት ለማይኖር ሰው አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት ለሚኖር አብና ወልድ አሉት፡፡» የሚል ቃል እናነባለን፡፡ በዚህ ክፍል የቤተክርስቲያን አስተምህሮ «የክርስቶስ ትምህርት» ተብሎ የተጠራ ሲሆን ክርስቲያኖች የሚያምኑትና አስተማሪዎችም የሚያስተምሩት ትምህርት ክርስቶስ ያስተማረው ትምህርት ሊሆን እንደሚገባ ያሳያል፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣበትን ዓላማ ፈጽሞ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት የገለጠው እውነት ነበረ፡፡ ኢየሱስ ይህን አስመልክቶ ሲናገር «ከእናንተ ጋር ስኖር ይህን ነግሬአችኋለሁ፤ አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱሰ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል፤ እኔም የነገርኳችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል» ብሏል (ዮሐ.14፡25-26)፤ እንዲሁም «የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፤ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም፡፡ ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፡፡» በማለት አስቀድሞ ተናግሯል (ዮሐ.16፡12)፡፡ ስለዚህ ሐዋርያት ክርስቶስ ያስተማራቸው ትምህርት እንዳለ ሆኖ እርሱ ያልነገራቸውን ቀሪ እውነት ወይም ትምህርት ደግሞ መንፈስ ቅዱስ እንዳስተማራቸው በእነዚህ ጥቅሶች እንረዳለን፤ እነርሱም ከጌታ ኢየሱስና ከመንፈስ ቅዱስ ያገኙትን (የተቀበሉትን) ሙሉውን የእግዚአብሔር እውነት አስተምረዋል፤ ትምህርታቸውም «የሐዋርያት ትምህርት» ተብሎ የተጠራ ሲሆን በሐዋርያት ሥራና በመልእክታት ውስጥ በስፋት የተገለጠ ትምህርት ነው፡፡ የመጀመሪያዎቹ አማኞች ከሚተጉባቸው ነገሮች አንዱና የመጀመሪያው የሐዋርያት ትምህርት እንደ ነበር በሐ.ሥ.2፡42 ላይ እናነባለን፡፡ ከሐዋርያት ትምህርት ቀጥሎ እነዚህ አማኞች ይተጉ እንደነበር የተገለጠው በኅብረት ነው፡፡ ሁሉም አማኞች በሐዋርያት ትምህርት ያምኑ ስለነበር ኅብረት ሊኖራቸው ችሏል፡፡ እውነተኛ ኅብረት ወይም የመንፈስ አንድነት ሊኖር የሚችለው አማኞች ሁሉ የሚያምኑት ትምህርት የክርስቶስና የሐዋርያት ትምህርት ብቻ ሲሆን ነው፡፡ በተለያየ ዘመን በቤተክርስቲያን ጌታ የሚያስነሣቸው አስተማሪዎችም ሊያስተምሩት የሚገባው ትምህርት ክርስቶስና ሐዋርያት ያስተማሩትን ትምህርት ብቻ ሊሆን ይገባል፡፡ ሐዋርያት ጌታንም እነርሱንም ባልተቀበሉት አይሁድ ዘንድ የሚታወቅ በጊዜው ከነበረው የፈሪሳውያንና የሰዱቃውያን ሃይማኖታዊ ትምህርት የተለየ ትምህርት ነበራቸው፤ ይህም ትምህርት በጌታ በኢየሱስ ስም የሚያስተምሩት ሲሆን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ፣ ስለ በደላችን እንደ ሞተ እኛን ስለማጽደቅም ከሙታን እንደተነሣ በእግዚአብሔር ቀኝ እንደተቀመጠ፣ ወደፊትም በሕያዋንና በሙታን ላይ የሚፈርደው እርሱ እንደሆነ እንዲሁም ሌሎችን እውነቶች ያካተተ ትምህርት ነው፡፡ ይህን ትምህርት ሲያስተምሩ «በዚህ ስም እንዳታስተምሩ አጥብቀን አላዘዝናችሁምን? ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞልታችኋል» በማለት የአይሁድ ሸንጎ ይቃወማቸው ነበር (የሐ.ሥ. 5፡27)፡፡ ስለሆነም «በትምህርታችሁ» ተብሎ ሊገለጽ የቻለ በጊዜው ሐዋርያት ብቻ የሚያስተምሩት ትምህርት እንደነበር ከዚህ እንረዳለን፡፡ አስተማሪዎች በየስፍራው ሊያስተምሩት የሚገባው ትምህርትም ያንኑ የሐዋርያትን ትምህርት ሊሆን ይገባል፡፡
የክርስትናው ዓለም በተለያየ ትምህርት ተከፋፍሎ በሚታይበት ዘመን ሁሉ እውነተኛ አስተማሪዎች የክርስቶስንና የሐዋርያትን ትምህርት በማስተማር ያገለግላሉ፡፡ በክርስትናው ዓለም መከፋፈል የመጣውም የሐዋርያትን ትምህርት ከመከተል ይልቅ የተለያዩ የሐሰት አስተማሪዎች በሚፈጥሩት የሐሰት ትምህርት በመወሰድ ነው፡፡ እውነተኛ ትምህርት የመኖሩን ያህል ከሰይጣን የሆኑ የሐሰት ትምህርቶች መኖራቸውን ልንዘነጋ አይገባም፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እነዚህ የሐሰት ትምህርቶች «ልዩ ወንጌል» (ገላ.1፡6)፣ «ልዩ ትምህርት (1ጢሞ.1፡3፤ 6፡3)፣ እንግዳ ትምህርት» (ዕብ.13፡9)፣ «የአጋንንት ትምህርት» (1ጢሞ.4፡2) .... ተብለው ተገልጸዋል፡፡ በሐዋርያት ዘመን «የበለዓም ትምህርት» (ራእ.2፡14)፣ «የኒቆላውያን ትምህርት» (ራእ.2፡15) ተብለው የተገለጡ ክፉ ትምህርቶች ነበሩ፡፡ እነዚህን ትምህርቶች የሚያስተምሩትም «ሐሰተኞች አስተማሪዎች» የተባሉ ሲሆን ክፉ ሥራቸውን በተመለከተ «እነርሱም የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ክደው የሚፈጥንን ጥፋት በራሳቸው ላይ እያሰቡ የሚያጠፋ ኑፋቄን አሾልከው ያገባሉ፤» ተብሎ ተጽፏል (2ጴጥ.2፡1)፡፡ ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ እስከ ዘመናችን ድረስ እነዚህ የሐሰት አስተማሪዎችና ክፉ ትምህርታቸው በዙሪያችን አሉ፡፡ በተለይም በእኛ ዘመን ብዙዎች ለሥልጣንና ለገንዘብ ጥቅም ሲሉ የፈጠሯቸው ብዙ ክፉ ትምህርቶች የሚያጠፉ ኑፋቄዎች ሆነው ብዙዎችን ሲያጠፉ ይታያል፡፡ በመሆኑም እውነተኛ አስተማሪዎች ከምን ጊዜውም ይልቅ ያስፈልጉናል፡፡ የሐሰተኛ ትምህርት ባሕርይው ከእውነተኛው ትምህርት ጋር ተደባልቆና ተመሳስሎ መቅረብ በመሆኑ ብዙ አማኞች የእውነትንና የሐሰትን ትምህርቶች ለይተው ለማወቅ ይቸገራሉ፡፡ ስለሆነም የእውነት ትምህርትን ከሐሰት ለይተው በአግባቡ የሚያስተምሩ ከጌታ የተሰጡ አስተማሪዎች ያስፈልጋሉ፡፡
የክርስቶስንና የሐዋርያትን ትምህርት የምናገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙት ቅዱሳት መጻሕፍት ነው፡፡ ስለሆነም አስተማሪዎች በተሰጣቸው ጸጋ ሲያገለግሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተገኘ ትምህርትን ብቻ ሊያቀርቡ ይገባል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበት አንዱ ዓላማም ለትምህርት መሆኑን ከራሱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንረዳለን፡፡ በሮሜ.15፡4 «በመጽናትና መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ ይሆንልን ዘንድ አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፏልና» የሚል ቃል እናነባለን፡፡ በ2ጢሞ.3፡16 ላይ ደግሞ «የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል» ተብሎ ተጽፏል፡፡ ስለዚህ አስተማሪዎች ለትምህርታቸው የሚጠቅሱት ማስረጃና ማስተማሪያ “መጽሐፍ ቅዱስ” ሊሆን ይገባል፡፡ በተከፋፈለው የክርስትና ዓለም አንዱ ከሌላው የሚለይበትን እምነት የሚገልጹ ትምህርቶችን የያዙ የእምነት መግለጫዎች በበዙበት በዚህ ዘመን ከእግዚአብሔር የተሰጠንን ቅዱሱን መጽሐፍ የእምነት ትምህርታችን ብቸኛ ማስረጃ አድርጎ መጠቀም እጅግ የተባረከ መንገድ ነው፡፡ ከቅዱሳት መጻሕፍት አንዳንድ ክፍሎችን በመውሰድ በትክክል የሚናገሩትን እውነት ሳይሆን አጣምሞ በመተርጐም የተዘጋጁ የእምነት መግለጫዎች የእምነት መመሪያ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ከጌታ ዘንድ የተሰጠ እውነተኛ አስተማሪ መጽሐፍ ቅዱስን እንጂ እነዚህን የእምነት መግለጫዎችንም ሆነ ሌሎች ድርሰቶችን በማስረጃነት አይጠቀምም፤ እንዲያውም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚቃረኑ መጻሕፍት የያዙትን በእግዚአብሔር እውቀት ላይ የሚነሣ የሰው ሐሳብ በተረዳው የእውነት ቃል እያፈረሰ ያገለግላል (2ቆሮ.10፡5)፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የክርስቶስንና የሐዋርያትን ትምህርት የያዘ መጽሐፍ በመሆኑ ከዚህ መጽሐፍ ብቻ የተገኙ ትምህርቶችን የሚያስተምር አስተማሪ ለተጠሙት ሁሉ ውኃውን ከምንጩ እየቀዳ የሚያጠጣ ሰውን ይመስላል፡፡ በተለያዩ የሰው አሳቦች አመለካከቶች ያልተበከሉ ትምህርቶችን ማስተላለፍ የሚቻለው መጽሐፍ ቅዱስን ብቸኛ መመሪያ በማድረግ ነው፡፡ አስተማሪዎች መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ቃል የያዘ መጽሐፍ መሆኑን አምነው የሚናገረውን ቃል በትክክል ከተረዱትና በሚገባ ካወቁት በኋላ ሊያስተላልፉ ይገባቸዋል፤ ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ሲጽፍለት «የእውነትን ቃል በቅንነት (በትክክል) የሚናገር የማያሳፍርም ሠራተኛ ሆነህ የተፈተነውን ራስህን ለእግዚአብሔር ልታቀርብ ትጋ፡፡» ብሎአል (2ጢሞ.2፡15)፡፡ ስለሆነም አስተማሪ የእውነትን ቃል በቅንነት ማለትም በትክክል ወይም በአግባቡ ለይቶ ለመናገር ይችል ዘንድ በግሉ ከጸሎት ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በማስተዋል ሊያጠና ይገባዋል፡፡ በዙሪያችን ብዙ ክፉና ሐሰተኛ የሆኑ ትምህርቶች በበዙበት በዚህ ዘመን ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቦች በማይናገሩት ሐሳብ ላይ እየተጠቀሱ ስለሆነና ብዙ አማኞችም ትክክለኛውን እውነት ለይቶ የሚነግራቸው እውነተኛ አስተማሪ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ አስተማሪዎች የእውነትን ቃል ለይተው በመረዳት ለይተው መናገር ይገባቸዋል፡፡ በዚህም የሚተጉ ከሆነ የማያሳፍር ሠራተኛ ሆነው ጌታን ማገልገል ይችላሉ፡፡
አስተማሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ለማስተማር ሰው እንዲያሰማራቸው ወይም እንዲመድባቸው የሚያስተምሩትን የትምህርት ርእስም በፕሮግራም አውጪዎች እንዲወሰንላቸው መጠበቅ የለባቸውም፡፡ በተሰጣቸው ጸጋ መሠረት ለሚያገለግሏቸው ሰዎች በጊዜው አስፈላጊ የሆነውን ትምህርት የእግዚአብሔር መንፈስ እንደመራቸው መርጠው ከተገልጋዮቹ ጋር በተስማሙበት ጊዜና ቦታ ተገኝተው የማስተማር አገልግሎታቸውን ሊሰጡ ይገባቸዋል፡፡ የሚያስተምሯቸው አማኞች የጌታ ደቀመዛሙርት እንደሆኑ እንጂ የእነርሱ ደቀመዛሙርት አለመሆናቸውንም ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ ስለሆነም አስተማሪዎች በሰርተፊኬት ወይም በዲፕሎማ ለማስመረቅ ብለው የሚያስተምሩ መሆን የለባቸውም፡፡ የማስተማር አገልግሎት ዋነኛ ግቡ የሚማሩት (የሚገለገሉት) ሰዎች የእግዚአብሔርን እውነት በይበልጥ ያውቁና ይረዱ ዘንድ በልባቸውም የነበሩ ጥያቄዎች ተመልሰውላቸው በጌታ ያርፉ ዘንድ ከስህተትና ከሐሰት እንዲሁም ከክፉ ትምህርቶችም ይጠበቁ ዘንድ ማስቻል ነው፡፡ ይህን ውጤት ማስገኘት የሚችል የማስተማር አገልግሎት ለዚህ ዘመን አማኞች በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡ እንደ አንድ የሙያ ትምህርት በኮርስ መልክ ተምሮ የወረቀት ማስረጃዎችን መቀበል በሕይወት ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም፤ እንደዚህ ዓይነት የማስተማር አገልግሎት የተኰረጀው ከዓለማዊ አሠራር ነው እንጂ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰደ አይደለም፡፡
የጌታ ደቀመዛሙርት ለሆኑም ሆነ ላልሆኑ ሰዎች የሚቀርቡ ትምህርቶች የሚገለገሉት ሰዎች በወቅቱ የሚያስፈልጋቸውን ርእስ ወይም ያልተረዱትን እውነት የሚገልጽ ቢሆን መልካም ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን በተለያዩ አርእስት እየከፋፈሉ በሚገለገሉ ሰዎች የመቀበል አቅም መሠረት ለመረዳት በሚያስችልና በቀላሉ በሚገባ መልክ ማስተማር አስተማሪዎች ሊያገለግሉ የሚችሉበት አንዱ መንገድ ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን የነበረውን የማስተማር አገልግሎት ሲገልጽ «ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ንስሐንና በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ለአይሁድና ለግሪክ ሰዎች እየመሰከርኩ በጉባኤም በየቤታችሁም አወራሁላችሁና አስተማርኋችሁ እንጂ ከሚጠቅማችሁ ነገር አንዳች ስንኳ አላስቀረሁባችሁም» ብሏል (የሐ.ሥ.20፡20)፡፡ ለአይሁድና ለግሪክ ሰዎች፣ ማለትም ለማያምኑ ሰዎች የሚያስፈልጉትን ሁለት ትምህርቶች፣ ንስሐንና በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ያስተምር እንደነበር ከንባቡ እንረዳለን፡፡ እንዲሁም በዕብ.5፡11-14 ላይ የእግዚአብሔርን እውነት የሚናገሩ ትምህርቶች «ወተት» እና «ጠንካራ» ምግብ ተብለው በደረጃ ለሁለት ተከፍለዋል፡፡ በዚህ ክፍል ወተት የተባለው «አንድ ሰው ስለ እግዚአብሔር ቃላት መጀመሪያ ያለው የሕጻንነት ትምህርት» ሲሆን (ቁ12)፣ «ጠንካራ ምግብ» የተባለው ደግሞ «መልካሙንና ክፉውን ለመለየት በሥራቸው የለመደ ልቡና ላላቸው ለፍጹማን ሰዎች» የሚሰጥ ትምህርት ነው (ቁ.14)፡፡ ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን በተለያዩ ርእሶች እየመደቡ በየደረጃው ማስተማር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ልምድ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ይህ ግን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን በተለይ በአንድ የትምህርት ዓይነት ባለሙያ ለማድረግ ከማሠልጠን በእጅጉ የተለየ ነው፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ለአማኞች ሁሉ የሚያስፈልግ የሕይወት ትምህርት ነው እንጂ ለሚያገለግሉ ብቻ ወይም ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ የሚሰጥ የሙያ ትምህርት አይደለምና፡፡
አስተማሪዎች ምንም እንኳ የጠለቀው የእግዚአብሔር ቃል እውቀት ቢኖራቸውም በዚህ እውቀታቸው መመካትና መታበይ የለባቸውም፡፡ የሚታበዩ ከሆነ ግን እንደ ማንኛውም የዓለም እውቀት ስለ እግዚአብሔር ያውቃሉ እንጂ እግዚአብሔርን ያውቃሉ ማለት አይቻልም፤ ሰው እግዚአብሔርን እያወቀ በሄደ ቁጥር የራሱን ታናሽነት እያየ ስለሚሄድ የበለጠ ትሑት እየሆነ ይሄዳል እንጂ አይታበይም፡፡ አስተማሪዎች ከጌታ ከኢየሱስ ፍጹም ትህትናን ይማራሉ (ማቴ.11፡28)፡፡ ይህም ትህትና ከጌታ የተሰጡ የእውነተኛ አስተማሪዎች ምልክት ነው፡፡ እነዚህ እውነተኛ አስተማሪዎች «መምህር» ወይም «ሊቃውንት» ተብለው መጠራትን የሚጸየፉ ናቸው፤ ምክንያቱም ጌታ ኢየሱስ ሲያስተምር «.. .. እናንተ ግን መምህር ተብላችሁ አትጠሩ መምህራችሁ አንድ ስለሆነ እናንተም ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ.. .. .. ሊቃችሁ አንድ እርሱም ክርስቶስ ነውና ሊቃውንት ተብላችሁ አትጠሩ» ብሎ ለተናገረው ቃል ይታዘዛሉና (ማቴ.23፡8-10)፡፡