በዕብ. 6፡6 ላይ “በኋላ የካዱት” የተባሉት ሰዎች “ከእኛ ዘንድ ወጡ፥ ዳሩ ግን ከእኛ ወገን አልነበሩም፤ ከእኛ ወገንስ ቢሆኑ ከእኛ ጋር ጸንተው በኖሩ ነበር፤ ነገር ግን ሁሉ ከእኛ ወገን እንዳልሆኑ ይገለጡ ዘንድ ወጡ” (1ዮሐ.2:19) የተባሉት ዓይነት ሰዎች ናቸው። ይህም ቃል በኋላ ላይ ከእኛ ዘንድ የወጡት ሰዎች በፊት ከእኛ ጋር ሆነው አምነናል ያሉ ወይም አማኞች የመሰሉ፣ እንደነበሩ ያሳያል። በኋላ ላይ ከእኛ ዘንድ በሚወጡ ወይም በሚክዱ ጊዜ፥ በፊትም ቢሆን ከእኛ ወገን እንዳልነበሩ ይታወቃል። ሰዎቹ የአፍ አማኞች ናቸው እንጂ የልብ አማኞች አይደሉም። የካዱትም በሰው ፊት በማስመሰል አምነናል ያሉትን ነው እንጂ በእግዚአብሔር ፊት የሚታይ የልብ እምነትን አይደለም፡፡
በሰው ዘንድ አማኝ እንዲመስሉ ያደረጓቸው ነገሮችም በዕብ 6 ከቁ.4-5 በዝርዝር የተነገሩ ሲሆን እነርሱንም ቀጥሎ እንመለከታለን፡፡
የዕብራውያን አማኞች ከማመናቸው በፊት የሚያውቁት የምድር የሆነ ስጦታን ነው፡፡ ምድራዊ ተስፋ፣ ምድራዊ በረከትና ምድራዊ ርስት የተሰጣቸው ነበሩ፤ በክርስትና ግን ከሰማያዊ ጥሪ ተካፋዮች ተደርገዋል (ዕብ.3፡1)፡፡ እናም ከሰማይ የወረደ የሕይወት እንጀራ (ክርስቶስ)፣ ከሰማይ የፈሰሰ የሕይወት ውኃ (መንፈስ ቅዱስ) እና አብሮ የመጣ መንፈሳዊ በረከት ተሰጥቷቸዋል። ታዲያ በመካከላቸው የተደባለቁ እነዚያ የአፍ አማኞች ለእውነተኞቹ የተሰጠውን ሰማያዊ ስጦታ ቀምሰው ነበር፤ መቅመስም ለማረጋገጥ ያህል መፈተን ነው እንጂ ወዶና ተቀብሎ መብላትና የራስ ማድረግ አይደለም፡፡ ቀመሱት ማለት ስጦታው ለእነርሱ መጥቷል፣ እነርሱም ተቀበሉት ማለት አይደለም፡፡ ከእስራኤል ጋር የነበሩ ድብልቅ ሕዝብ በምድረ በዳ ለእስራኤል የተሰጠውን በረከት (ከሰማይ የወረደውን መና እና ከዓለት የፈለቀውን ውኃ) አብረው ተካፈሉ ማለት (ዘጸ.12፡38፤ ዘኁል.11፡3-8)፣ እነርሱም የእግዚአብሔር ሕዝብ ነበሩ ማለት እንዳልሆነ ሁሉ እነዚህም ከመጀመሪያው የጌታ አልነበሩም፡፡
ከመንፈስቅዱስ ተካፋዮች የነበሩ ማለት “መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ” ወይም “በመንፈስ ቅዱስ የታተሙ” ማለት አይደለም፡፡ ቃሉ "መንፈስ ቅዱስን ተካፋዮች ሆነው የነበሩ" ሳይሆን "ከመንፈስ ቅዱስ ተካፋዮች የነበሩ" እንደሚል ማስተዋል ይገባል። ይህም ከመንፈስ ቅዱስ የሆነ ሥራን ከእውነተኞቹ ጋር ተደባልቀው ያዩ፣ የሰሙ፣ አፍኣዊ በሆነ መልኩ በጊዜያዊነት አብረው የተደሰቱ፣ ያመሰገኑ፣ አሜን ያሉ፣ የዘመሩ … ማለት ነው፡፡ ሌሎች አማኞች ባያውቋቸውም ጌታ ያውቃቸዋል፤ በጉባኤው ዘንድ ካለው ከመንፈስ ቅዱስ መገኘትና ሥራዎች ቢካፈሉም እነርሱ ግን በግላቸው “መንፈስ የሌላቸው” ሰዎች ናቸው (ይሁ.1፡19)፡፡ የሰማርያው ጠንቋይ ሲሞን ያመነ መስሎ ተጠምቆ ከአማኞች ጋር ተደባልቆ በሐዋርያት እጅ መጫን መንፈስ ቅዱስ ስንዲሰጥ አይቶ ነበር፤ ሆኖም እርሱም እንደነጴጥሮስ ይህን የእግዚአብሔርን ስጦታ በገንዘብ ለማግኘት በሞከረ ጊዜ ማንነቱ ተገለጠ፤ ልቡ በእግዚአብሔር ፊት የቀና አልነበረም፤ ገና በመራራ መርዝና በዓመፅ እስራት ውስጥ ነበር፤ ስለሆነም “ከዚህ ነገር ዕድል ወይም ፈንታ የለህም” ተባለ (የሐ.ሥ.9-24)። በመሆኑም ይህ የአፍ አማኞች እንደ ሲሞን ከእውነተኛ አማኞች ጋር ተደባልቀው በቅዱሳን መካከል የሚደረግ የመንፈስ ቅዱስ መግቦትን ቢካፈሉም የዘላለም ሕይወት ያገኙ አማኞች ናቸው ማለት አይደለም። አንድ ቀንም ነበርንበት፣ አይተንዋል፣ ተካፍልነዋል ሲሉት የነበሩትን ነገር ይክዱታል፡፡
እነዚህ ሰዎች ከስንዴ ጋር ተመሳስሎና ተደባልቆ እንደሚኖር እንክርዳድ ከእውነተኛ አማኞች ጋር ተደባልቀው አብረው የሚኖሩ ስለሆኑ (ማቴ.13፡24-43)፣ መልካሙ የእግዚአብሔር ቃል ሲነበብና ሲሰበክ እነርሱም ይሰማሉ፤ ይሁን እንጂ በጭንጫ ላይ እንደተዘራው ዘር ቃሉ ለጊዜው የበቀለ ቢመስልም ፀሐይ በወጣ ጊዜ (መከራ በመጣ ጊዜ) ይጠወልጋል (ማቴ.13፡5-6)፤ የሰሙት ቃል ጋር ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስለማይዋሐዳቸው አይጠቅማቸውም (ዕብ.4፡2)፤ ከመነሻውም ዳግም ያልተወለዱ ናቸው፡፡ ይህን እያስመሰሉ ሲሰሙትና ሲያደንቁት የነበረውን ቃል አንድ ቀን በይፋ ይክዱታል፡፡
“ሊመጣ ያለው የዓለም ኃይል” የተባለው ጌታ በሚመጣው ዓለም የሚገልጠው ልዩ ልዩ ተአምራዊ ኃይል ነው፡፡ ጌታ ሐዋርያትን ሁለት ሁለት እያደረገ በላከ ጊዜ አጋንንትን የሚያወጣ፣ ለምጻምን የሚያነጻ፣ ሙታንን የሚያነሣ ኃይል ተገልጦባቸው ነበር (ማቴ.10፡8)፤ ከእነርሱም መካከል አንዱ ይሁዳ እንደነበር ማስታወስ ያስፈልጋል፤ ይህን ተልእኮ ጌታ ሲሰጣቸው “እውነት እላችኋለሁና፥ የሰው ልጅ እስኪመጣ ድረስ የእስራኤልን ከተማዎች አትዘልቁም” ብሏቸዋል (ማቴ.10፡23)። ታዲያ በጌታ ዘመንም ሆነ እርሱ ካረገ በኋላ የተገለጠው ኃይል ወደፊት ሊመጣ ባለው ዓለም የሚገለጥም ኃይል እንደሆነ ከዚህ እንረዳለን፡፡ ነገር ግን በእውነተኛ አማኞች መካከል እንደ ይሁዳ ተደባልቀው እንዲህ ያለውን ኃይል ሊቀምሱ የሚችሉ የአፍ አማኞች ይኖራሉ፤ ማለትም ሲደረግ ያያሉ፣ ሌሎች ሲያደንቁ ያደንቃሉ፣ ሲደሰቱ ይደሰታሉ፣ ሲያመሰግኑ ያመሰግናሉ፤ ሁሉም ግን አፍኣዊ ነው፡፡ እነርሱም “ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፥ በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን?“ የሚሉ እና ጌታ ግን “ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ” ብሎ የሚመሰክርባቸው ሰዎች ናቸው (ማቴ.7:23)። ስለዚህ እነዚህ በኋላ የሚክዱ ሰዎች አምነናል ብለው ከአማኞች ጋር በመቀላቀል እዚህ ምድር ላይ በእነዚህ ነገሮች ቢሳተፉም ጌታ ግን ልባቸውን ስለሚያውቅ የማይተማመንባቸው ሰዎች ናቸው፤ በዚሁ በዕብ.6፡7- 8 ላይ በምሳሌ እንደተገለጸው “የሚጠቅሙ አትክልቶች" እንዲበቅሉ የወረደውን ዝናብ ተጠቅመው "እሾክና ኩርንችት" በዚያ መሬት ላይ ቢበቅሉ እሾኩና ኩርንችትሱ የሚጠቅሙ አትክልት ነበሩ ማለት እንዳልሆነ ሁሉ፥ ከልብ አማኞች ጋር የተደባለቁ የአፍ አማኞች መንፈሳዊ ነገሮችን መካፈል ስለቻሉ ብቻ ዳኑና የዘላለም ሕይወት ያገኙ እውነተኛ አማኞች ነበሩ ማለት አይደለም፤ ከመጀመሪያውም እሾክና ኩርንችት ናቸው፤ “መጨረሻቸውም መረገም እና መቃጠል ነው” ተብሎ ተነግሮናል (ዕብ.6፥8)።
የአፍ አማኞች በኋላ ላይ የካዱ ሲባሉ በፊት ከልብ ያመኑት ነገር የነበራቸው ሆነው አይደለም። ነገር ግን የሚክዱት እውነተኞቹ ከልብ የሚያምኑትን፣ እነርሱ ግን በአፋቸው አምነናል የሚሉትን አፍኣዊ እምነት ነው፡፡ ይሁዳ ከጌታ ሐዋርያት ጋር አብሮ በነበረ ጊዜ ያመነ ወይም ደቀመዝሙር የሆነ ቢመስልም እንኳ ጌታ ግን ከማያምኑት አንዱ እንደነበር ተናግሯል (ዮሐ.6፡64)፤ እንዲያውም "ከእናንተ አንዱ ዲያብሎስ ነው" ብሎ የገለጸው ሰው ነበር (ዮሐ.6፡70-71)፤ ይሁንና ይህ ሰው በእነርሱ መካከል የነበረውን መንፈስ፣ የሚነገረውን መልካሙን የእግዚአብሔር ቃል፣ ሲደረጉ የነበሩ የኃይል ሥራዎች አብሮ ሲካፈልና ሲሳተፍ ነበር፤ ይህ ማለት ግን እውነተኛ አማኝ ነበረ ማለት አልነበረም፡፡ እነዚህ የአፍ አማኞች በኋላ ላይ የሚክዱት እንደ ጴጥሮስ በሰው ፊት (ማቴ.26፡70) ሳይሆን፣ እንደ ይሁዳ በእግዚአብሔርም በሰውም ፊት ነው፡፡ ጴጥሮስ መከራውን መጋፈጥ ስላቃተው በሎሌዎቹ ፊት ቢክድም ለንስሐ ስፍራ አግኝቷል፡፡ ይሁዳ ግን የብስጭት ጸጸት ተጸጸተ እንጂ ንስሐ መግባት ስላልቻለ ታንቆ ሞተ (ማቴ.27፡3-5)፤ በኋላ የካዱትን እንደገና ለንስሐ ማደስ አይቻልም ማለትም እንደዚህ ነው፡፡
በጌታ በኢየሱስ በእውነት ከማመኑ የተነሣ ከማይጠፋው ዘር ዳግመኛ ተወልዶ የዘላለም ሕይወት ያገኘ እውነተኛ አማኝ ኃጢአት ሊሠራ ይችላል? እውነተኛ (የልብ) አማኝ ኃጢአት የማይገዛው ቢሆንም (ሮሜ 6፡14)፣ አንዳንድ ጊዜ በሥጋ ሲሸነፍ ኃጢአት ሊሠራ የሚችልበት አጋጣሚ ይኖራል። ይህንንም ሐዋርያው ዮሐንስ “ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም” በማለት በግልጽ ተናግሮታል (1ዮሐ.1፡8)።
እውነተኛ አማኝ ምንም እንኳ ከእግዚአብሔር የተወለደው አዲሱ ሰው በውስጡ ቢኖርም ከሥጋ የተወለደው አሮጌው ሰውም ያ አማኝ በዚህ ምድር እስካለ ድረስ አብሮት ይኖራል። ስለሆነም ከሥጋ ድካም የተነሣ ኃጢአትን የሚሠራበት ጊዜ ይኖራል። ይህ ማለት ግን ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጭ በሥጋችን ደካማነት ምክንያት እግዚአብሔርን የሚያሳዝንና የሚያስቆጣ ኃጢአት ልንሠራ እንችላለን ማለት ነው እንጂ ኃጢአት መሥራት ይፈቀድልናል ማለት አይደለም።
ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢአትን እንደማያደርግ ተገልጿል (በ1ዮሐ. 3፡9፤ 1ዮሐ. 5፥18)። እዚህ ላይ "ኃጢአትን አያደርግም" ማለት፥ ኃጢአትን ማድረግ የሚችል ባሕርይ የለውም ማለት ሳይሆን ኃጢአትን ማድረግ የእርሱ መገለጫ አይደለም፣ ከእርሱ አይጠበቅም፣ ማድረግ የለበትም ማለት ነው። ሆኖም አማኝ ኃጢአት ማድረግ ባይኖርበትም ሊያደርግ እንደሚችል ታሳቢ ተደርጓል። በ1ዮሐ. 2፥1 ላይ “ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ" ካለ በኋላ "ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ...” ማለቱ ይህን ያስረዳል። ታዲያ አማኝ ኃጢአት ማድረግ የሌለበት ሆኖ ሳለ ሊያደርግ የሚችለው እንዴት ነው?
እውነተኛ አማኝ ኃጢአትን ሊያደርግ የሚችለው ወዶ፣ ወይም ደስ እያለው ሳይሆን እየጠላው ነው። ይህም ሊሆን የሚችለው በሥጋው ውስጥ ባለ ምኞትና መሻት ተስቦና ተታልሎ በመሸነፍ ነው (ሮሜ.7፡7-8፤ ያዕ.1፡14-15)። "በእኔ ማለት በሥጋዬ በጎ ነገር እንዳይኖር አውቃለሁና፤ ፈቃድ አለኝና፥ መልካሙን ግን ማድረግ የለኝም። የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን በጎውን ነገር አላደርገውም። የማልወደውን የማደርግ ከሆንሁ ግን ያን የማደርገው አሁን እኔ አይደለሁም፥ በእኔ የሚኖር ኃጢአት ነው እንጂ" ይላል (ሮሜ 7፡15-20)።
እውነተኛ አማኝ በሥጋው ኃጢአትን ቢያደርግም እንደ ጴጥሮስ ንስሐ መግባት የሚችል ሰብእና ያለው ነው (ሉቃ.22፡54-62)። የሚጠላውን ነገር በማድረጉ ወዲያው ልቡ በጸጸት ይመታል። ኃጢአቱንም ይናዘዛል። እግዚአብሔርም ኃጢአቱን ይቅር ሊለው ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻው የታመነና ጻድቅ ነው (1ዮሐ.1፡9)።
በክርስትና የተነገረውን የእውነት እውቀት ከተቀበለ በኋላ ወዶ፣ ፈቅዶ፣ ዐቅዶ ኃጢአትን የሚሠራ ሰውን በተመለከተ እንዲህ ተብሏል፡- “የእውነትን እውቀት ከተቀበልን በኋላ ወደን ኃጢአት ብናደርግ ከእንግዲህ ወዲህ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት አይቀርልንምና፥ የሚያስፈራ ግን የፍርድ መጠበቅ ተቃዋሚዎችንም ሊበላ ያለው የእሳት ብርታት አለ” (ዕብ.10፡26-27)። አንድ ሰው የእውነትን እውቀት የተቀበለው ከልቡ አምኖ ከሆነ ኃጢአትን ሊያደርግ የሚችለው በሮሜ 7 ውስጥ እንደተገለጸው "ወዶ" ሳይሆን "ሳይወድ" ነው፤ “የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁና” (ሮሜ7፡19) እንዳለው ነው፡፡ ነገር ግን “የእውነትን እውቀት” ከተቀበልን በኋላ “ *ወደን* ኃጢአት ብናደርግ” ይህን ኃጢአት ለማስተስረይ የቀረ ሌላ መሥዋዕት አይኖረንም፡፡ ወደን ኃጢአት የምናደርግ ከሆነ “የእውነትን እውቀት” የተቀበልነው እንዲሁ "በአእምሮ እውቀት" ደረጃ ነው እንጂ ከልብ በሆነ እምነት አልነበረም ማለት ነው።
እንዲህ ያለ ሰው ኃጢአቱ እንዲሰረይለት እጁን በኃጢአት መሥዋዕቱ ላይ ከመጫን ይልቅ ማለትም የኃጢአት መሥዋዕት የሆነውን ክርስቶስን አምኖ ራሱን ከእርሱ ጋር ከመቁጠር ይልቅ እያወቀ፣ ወዶ፣ ኃጢአትን በማድረግ የቀጠለ ሰው ነው፤ እያወቁ፣ ወዶ፣ ኃጢአትን ማድረግ ደግሞ ያን የኃጢአት መሥዋዕት አለመቀበል ብቻ ሳይሆን፣ መሥዋዕቱን መናቅና ማቃለልም ነው፤ ታዲያ እንዲህ ላለ ሰው ለዚህ ኃጢአቱ ማስተስረያ የኃጢአት መሥዋዕት ከሆነው ከክርስቶስ ሌላ ምን መሥዋዕት ሊቀርለት (ሊመጣለት) ይችላል?፡፡ ይህ ሰው ስፍራው አሁንም ገና ከተቃዋሚዎች ጋር ሲሆን የቀረለት ነገር ቢኖር የሚያስፈራው ፍርድ፣ ተቃዋሚዎችን ሊበላ ያለው የእሳት ብርታት ነው፡፡ ስለሆነም ይህ ሰው የእውነት እውቀት ቢኖረውም ቀድሞውንም የኃጢአት ስርየት ያላገኘ፤ በድፍረት ኃጢአት የቀጠለ፣ ዳግም ያልተወለደ እና የዘላለም ሕይወት ያላገኘ ሰው ነው፡፡ በአካል ከአማኞች ጋር የተቀላቀለ ቢሆንም በልቡ እና በተግባሩ ግን ገና ከተቃዋሚዎች ወገን ነውና፡፡ ይህ ሰው ከልብ በሆነ እምነት ባይሆንም የእውነትን እውቀት ተቀብሎ ከአማኞች ጋር ተቀላቅሎ ከቆየ በኋላ በይፋ በሚወስዳቸው የክህደት እርምጃዎች የአፍ አማኝ እንደነበረ ያረጋግጣል፤ የእግዚአብሔር ቃል ይህን ሰው ሲገልጠው “የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ፣ ያንንም የተቀደሰበትን የኪዳኑን ደም እንደ ርኵስ ነገር የቆጠረ፣ የጸጋውንም መንፈስ ያክፋፋ” ይለዋል (ዕብ.10:31)። ከልቡ አምኖ የነበረ እውነተኛ አማኝ እነዚህን ነገሮች ሊያደርግ አይችልም፡፡ በመሆኑም እነዚህ መገለጫዎች ይህ ሰው የአፍ አማኝ የነበረ መሆኑ የሚያሳዩ ናቸው፤ እስኪ አንድ በአንድ ቀጥሎ እንመለከታቸው፡- 1) *የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ* - የእግዚአብሔርን ልጅ መርገጥ ሲባል፣ “ተቀብያለሁ” ያሉትን ነገር ከመካድም የከፋ ነው፤ ይህ ሰው ስለ እግዚአብሔር ልጅ የሚያውቅና የሚናገር ቢሆንም ይህ ከልብ ማመኑን አያመለክትም፤ ርኩሳን መናፍስትም ኢየሱስን “የእግዚአብሔር ልጅ” ብለውታል (ማቴ.8፡29፤ ማር.3:1)፤ በመሆኑም ይህ ሰው ስለ እግዚአብሔር ልጅ ያለው የእውነት እውቀት ከርኩሳን መናፍስቱ አይለይም፤ አውቀዋለሁ ያለውን የእግዚአብሔርን ልጅ ከልቡ አምኖ ከመከተል ይልቅ በጭካኔ የረገጠ ሰው ነው፤ በዕብ.6፡6 “ለራሳቸው የእግዚአብሔርን ልጅ ይሰቅሉታልና ያዋርዱትማልና” ከተባሉትም የባሰ ነው፡፡ ስለሆነም የአፍ አማኝ እንጂ የልብ አማኝ አይደለም፡፡
2) *የተቀደሰበትን የኪዳኑን ደም እንደ ርኩስ ነገር የቆጠረ* - እዚህ ላይ የተቀደሰበትን ሲል እርሱ በግሉ የተቀደሰ ነበር ማለት አይደለም፤ በተቀደሱት መካከል ተቀላቅሎ አብሮ መቆየቱን የሚያሳይ ነው፤ ለምሳሌ በ1ቆሮ.7:14 “ያላመነ ባል በሚስቱ ተቀድሶአልና፥ ያላመነችም ሚስት በባልዋ ተቀድሳለች” የተባለው ከተቀደሰ ወይም ከተቀደሰች አማኝ ጋር በጋብቻ ካላቸው ጥምረት የተነሳ በተቀደሰ ክልል ውስጥ ስላሉ እንጂ ራሳቸው በግላቸው ተቀድሰዋል ማለት አይደለም፤ ይህም በዚህ መልክ የሚታይ ነው፡፡ እውነተኛ አማኞች የተቀደሱት አዲስ ኪዳን በተመረቀበት የክርስቶስ ደም ነው፤ ታዲያ ይህ የአፍ አማኝ የእውነትን እውቀት ተቀብያለሁ በማለቱ እዚህ ምድር ላይ ከቅዱሳን ጋር በውጫዊ መንገድ የተቀደሰውን ስፍራ ይዟል፡፡ በግሉ ግን የተቀደሰ አለመሆኑን ልብ ማለት ይገባል፤ ለዚያም ነው የኪዳኑን ደም እንደ ርኩስ ነገር ለመቁጠር የደፈረው፤ በዚያ ደም በእውነት ተቀድሶ ቢሆን ኖሮ እርሱን የቀደሰውን ደም እንደ ርኩስ ነገር እንዴት ሊቆጥር ይችላል? በዚሁ በዕብ.10፡14 ውስጥ ከፍ ብለን ስናነብ “አንድ ጊዜ በማቅረብ የሚቀደሱትን የዘላለም ፍጹማን አድርጎአቸዋልና” ይላል፡፡ ስለሆነም በእውነት ተቀድሶ ቢሆን ኖሮ "የዘላለም ፍጹማን" ከተደረጉት ወገን ስለሚሆን ያን የቀደሰውን የኪዳኑን ደም እንደ ርኩስ ነገር አይቆጥርም ነበር፤ ሆኖም በዚህ ደረጃ መዳፈሩ እርሱ በፊትም ቢሆን በግል የተቀደሰ እንዳልነበር የሚያሳይ ነው፡፡
3) *የጸጋውን መንፈስ ያክፋፋ* - መንፈስ ቅዱስ በቃሉ በኩል ሰው በሕግ ሥራ ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ቤዛነት በኩል እንደሚጸድቅ (ሮሜ.3፡24)፣ በጸጋ እንደሚድን (ኤፌ.2፡8) የሚናገር መንፈስ ስለሆነ “የጸጋ መንፈስ” ይባላል፤ ሆኖም የእውነትን እውቀት የተቀበለው የአፍ አማኝ ይህን የጸጋውን መንፈስ ያልተቀበለ ብቻ ሳይሆን “ያክፋፋም” ሰው ነው፤ እርሱም በክርስትና መካከል የተደባለቁና “የሚለያዩ፣ ሥጋውያንም የሆኑ፣ መንፈስ የሌላቸው ሰዎች” (ይሁ.19) እንደተባሉት ያለ ነው። ወደ ክርስትና የገቡ ቢመስልም በሥጋ በሆነ አቅም ሕግን መፈጸም እንችላለን ከሚለው ዕብራዊነታቸው (ይሁዲነታቸው) ያልወጡ ነበሩ፤ በኋላም ከተደባለቁበት ክርስትና በይፋ ወጥተው ትክክለኛ ማንነታቸው ባለበት ይሁዲነት ስለሚቀጥሉ በአዲስ ኪዳን የተገለጠውን የጸጋውን መንፈስ ያክፋፋሉ፡፡ ይህም መንፈስ ቅዱስን መስደብ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ሰው ወደ ንስሐ መጥቶ ኃጢአቱን ተናዝዞ በክርስቶስ ደም ስርየት ማግኘት እንዴት ይችላል? ወደዚህ ንስሐ ሊያደርሰው የሚችለውን የጸጋ መንፈስ አክፋፍቷልና፡፡ መንፈስ ቅዱስን የሰደበ ሰው ኃጢአቱ የማይሰረይለትም በዚህ ምክንያት ነው (ማቴ.12፡32)፤ ይህ ሰው ወዶ ባደረገው ኃጢአት ቢጸጸት እንኳ የሚጸጸተው እንደ ይሁዳ ሲሆን ጸጸቱ ወደ ጥፋት የሚወስድ ብስጭት እንጂ ወደ ንስሐ የሚመራው አይደለም (ማቴ.27፡3-5)። እንደ ዔሳው ለንስሐ ስፍራ አያገኝም (ዕብ.12፡17)። ስለዚህ እንዲህ ያለ ሰው ንስሐ መግባት የሚችል ማንነት የለውም።
በአጠቃላይ የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ፣ የተቀደሰበትን የኪዳኑን ደም እንደ ርኩስ ነገር የቆጠረ እና የጸጋውን መንፈስ ያክፋፋ ይህ ሰው፣ የአፍ አማኝ ነው እንጂ እውነተኛ የልብ አማኝ አይደለም፡፡ ስለሆነም ቀድሞውንም ቢሆን ምድቡ የእሳት ባሕር ፍርድ ከሚጠብቃቸው ከተቃዋሚዎች ጋር ነው እንጂ ከእግዚአብሔር ልጆች ጋር አይደለም፡፡
አስተውል፡- በመሆኑም እውነተኛ አማኝ እና የአፍ አማኝ የሚለዩበት ዋነኛ ምልክት ይህ ነው። የአፍ አማኝ ኃጢአት የሚያደርገው ወዶ፣ ፈቅዶ፣ ዐቅዶ እና ደስ እያለው ሲሆን፣ ኃጢአትን ካደረገ በኋላም ምንም እንዳላደረገ ያህል ምንም አይሰማውም። ደጋግሞ በመሥራትም ኃጢአትን ኑሮው ያደርገዋል፤ ኃጢአት ይገዛዋል፤ በሥጋውም ላይ ይነግሥበታል። ስለዚህ ኃጢአትን በኃጢአት ላይ ይጨምራል እንጂ፥ ለይስሙላ ካልሆነ በቀር እውነተኛ ንስሐ መግባትም አይችልም። እውነተኛው አማኝ ግን ምናልባት ኃጢአትን የሚያደርግ ከሆነ፥ የሚያደርገው፥ የሚጠላውን ነገር ሲሆን ካደረገ በኋላም ራሱን ይጸየፋል፣ ሰላሙ ይታወካል፣ ባደረገው ነገር ይጸጸታል፣ እውነተኛ ንስሐም ይገባል። ኃጢአትን ሊያደርግ የሚችለውም በውስጡ ያሉት ሥጋና መንፈስ እርስ በእርሳቸው ፈቃዳቸውን ለማድረግ ሲቀዋወሙ የሥጋ ፈቃድ በሚበረታ ጊዜ ነው (ገላትያ 5፥17)።