እውነተኛ አማኝ ለዘላለም እንደማይጠፋ በጌታ ትምህርት በግልጽ የተነገረ በመሆኑ የዘላለም ፍርድ አይደርስበትም፤ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም” የሚል ዋስትና ተስጥቶታል (ዮሐንስ 5፥24)። ነገር ግን ሳይወድም ቢሆን በሥጋው ባሕርይ ምክንያት ድንገት ኃጢአትን ቢሠራ የሚከተሉት 3 ዓይነት ፍርዶች ይደርሱበታል።
"ከእርሱም የሰማናት ለእናንተም የምናወራላችሁ መልእክት፦ እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም የምትል ይህች ናት። ከእርሱ ጋር ኅብረት አለን ብንል በጨለማም ብንመላለስ እንዋሻለን እውነትንም አናደርግም" ይላል (1ኛ ዮሐ. 1፡5-6)። ስለሆነም አማኝ በኃጢአት ሆኖ ወደ እግዚአብሔር የሚያደርገው ጸሎትና አምልኮ የተከለከለ ይሆናል እንጂ ተሰሚነት አይኖረውም (መዝ.66፡18፤ ኤር.14፡11-12፤ ማቴ. 5፡23-24፤ 1ጴጥ.3፡7፤ ያዕ.4፡3)፡፡
እግዚአብሔር በእውነት ቃል አስቦ የወለዳቸው ልጆቹ ኃጢአትን ሲያደርጉ በመንፈሱና በቃሉ በሚወቅሳቸው ጊዜ ካልተመለሱ በአባትነት ይቀጣቸዋል፡፡ ይህም ለልጆቹ ካለው ፍቅር የተነሣ የሚያደርገው ነው፡፡ “… ለመቀጣት ታገሡ፤ እግዚአብሔር እንደ ልጆች ያደርግላችኋልና፤ አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው? … ይላል (ዕብ.12:6-11፤ ምሳሌ 3፡12)፡፡ ቅጣቱም በሥጋ እንደሆነ በግልጽ ተነግሯል፤ ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን ኃጢአት ስለሠራውና ከመካከላቸው መወገድ ስላለበት ሰው ሲናገር “መንፈሱ በጌታ በኢየሱስ ቀን ትድን ዘንድ እንደዚህ ያለው ለሥጋው ጥፋት ለሰይጣን እንዲሰጥ ፍርዴ ነው” ብሏል (1ቆሮ.5:5)፡፡ ይህም ዓይነት የቅጣት ፍርድ ጌታ በጽድቅ አሠራሩ በሚወስነው መሠረት በየደረጃው የሚፈጸም ነው፡፡ የጌታን እራት በማይገባ ሁኔታ ይካፈሉ ከነበሩት የቆሮንቶስ አማኞች መካከል የተፈረደባቸውን በተመለከተ የተጻፈው ቃል “ሳይገባው የሚበላና የሚጠጣ የጌታን ሥጋ ስለማይለይ ለራሱ ፍርድ ይበላልና፥ ይጠጣልምና። ስለዚህ በእናንተ ዘንድ የደከሙና የታመሙ ብዙዎች አሉ፤ አያሌዎችም አንቀላፍተዋል።” ይላል (1ቆሮ.11:29-30)
በ2ቆሮ.5:10 “መልካም ቢሆን ወይም ክፉ እንዳደረገ፥ እያንዳንዱ በሥጋው የተሠራውን በብድራት ይቀበል ዘንድ ሁላችን በክርስቶስ በፍርድ ወንበር ፊት ልንገለጥ ይገባናልና” ይላል። በዚህ ቃል ውስጥ እያንዳንዱ አማኝ በሥጋው መልካም ወይም ክፉ ሊያደርግ እንደሚችል የተነገረ ሲሆን፣ በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት፣ ለመልካሙም ሆነ ለክፉ ሥራው የሚገባውን ብድራት (ዋጋ) ይቀበላል፡፡ ለመልካም ሥራው የሚከፈለው ብድራት “መዳን” እንዳልሆነ ግልጽ ነው፤ መዳን በሥራ አይደለምና (ኤፌ.2፡8-9)፤ እንዲሁም ሐዋርያው ጳውሎስ “ሁላችን” በማለት ራሱን ጨምሮ በመናገሩ በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት የሚገለጡት የዳኑ እውነተኛ አማኞች ብቻ መሆናቸውን እናውቃለን፡፡ ያልዳኑትና ወደ እሳት ባሕር የሚጣሉት ለፍርድ የሚቀርቡት በነጩ ዙፋን ፊት እንደሆነ በራእ.20፡11 ላይ ተገልጿል፡፡ ስለዚህ በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት ቀርበው ለክፉ ሥራቸው የሚገባውን ብድራት የሚቀበሉት የዳኑ አማኞች መሆናቸውን ማስተዋል ይገባል፡፡ በክፉው ፈንታ መልካም ሠርተው ቢሆን ኖሮ ለመልካም ሥራቸው የሚገባ ብድራት ይከፈላቸው ነበር፤ ሆኖም ያንን ዋጋ (ሽልማት) ያጣሉ፡፡ የሲኦል ፍርድ ግን አይመከለታቸውም፤ ከዚያ የዳኑ ናቸውና፡፡
የዳነውና የዘላለም ሕይወት ያገኘው አማኝ በእግዚአብሔር መንፈስ እና በእግዚአብሔር ቃል አማካኝነት ተወቅሶ ከኃጢአቱ ንስሐ በሚገባ ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው ኅብረት ይታደሳል። ሆኖም ኅብረቱ ቢታደስም በዳዊት ሕይወት እንደምናውቀው እንደ እግዚአብሔር የጽድቅ ውሳኔ ቅጣቱ ላይቀር ይችላል (2ሳሙ.12፡11-15)። በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት ሲቀርብ የሚያገኘው ብድራትም በእግዚአብሔር ፍጹም ጽድቅ የሚወሰን ይሆናል። በተረፈ የዳነ አማኝ ምናልባት ኃጢአት ከሠራ፣ ንስሐ የሚገባው ልክ ገና እንዳላመንና እንዳልዳነ ሰው ከሲኦልና ከዘላለም ፍርድ ለመዳን ሳይሆን ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን ኅብረት ለማደስና ለማስቀጠል መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።
እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን ወደ ራሱ ለመመለስና ከእርሱ ጋር ኅብረት እንዲያደርጉ ለማድረግ በጸጋው የሰጠው ዕድል ንስሐ ነው፡፡ ንስሐ በሠሩት ኃጢአት መጸጸት፣ ኃጢአትን መናዘዝ እና መተው፣ እንዲሁም ከልብ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነው፡፡ ንስሐ በጌታ በኢየሱስ ለማያምኑም ሆነ ለአማኞች የተሰጠ ወደ እግዚአብሔር የመመለሻ መንገድ ሲሆን ለሁለቱም ዓይነት ሰዎች የተሰጠውን ንስሐ ቀጥሎ እንመለከታለን፡፡
በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ያላመኑ በውጭ ያሉ ሰዎች ከኃጢአት በታች ያሉ መሆናቸው የሚታወቅና በእግዚአብሔር ቃልም የተገለጸ ነው፡፡ “… አይሁድም የግሪክ ሰዎችም ሁሉ ከኃጢአት በታች እንደ ሆኑ አስቀድመን ከሰናቸዋልና፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፦ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል፥በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ ቸርነት የሚያደርግ የለም፥ አንድ ስንኳ የለም” (ሮሜ 3፡9-12)። እንዲሁም “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል” ይላል (ሮሜ.3:23) ። ስለሆነም የማያምኑ ሰዎች በውስጣቸው ኃጢአት አለ፣ እንዲሁም ከዚያ የተነሣ የኃጢአት ሥራዎችን ይፈጽማሉ፤ ከዚህም የሚከፋው ደግሞ ከኃጢአት የሚያድነውን ኢየሱስን አለማመናቸው ከኃጢአት በታች ሆነው እንዲኖሩና በኃጢአታቸው እንዲሞቱ ያደርጋቸዋል (ዮሐ.8፡24፤16፡8-10)።
ለማያምኑ ሰዎች “ንስሐ” እና “በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን” ሊነጣጠሉ የማይችሉ ተያያዥ ነገሮች ናቸው (ማር.1፡15፤ የሐ.ሥ.20፡20)፡፡ ጌታን ያላመኑ ሰዎች ወንጌል በሚሰበክላቸው ጊዜ ልባቸው ሲነካ ባለፈው ዘመናቸው በኖሩት የኃጢአት ኑሮ ተጸጸተው ንስሐ ከገቡ በኋላ በኃጢአት ምክንያት ከተፈረደው ፍርድ ለመዳንና የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የተሰበከላቸውን ክርስቶስን ወዲያውኑ ሊያምኑ ይገባል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ኃጢአተኞችን ሁሉ ወደ ንስሐ ሊጠራ መጣ (ማቴ.9፡13)፤ ጥሪውን ተቀብለው ንስሐ የሚገቡ ሰዎች ደግሞ ለመዳንና የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት ጌታ ኢየሱስን ማመን ይኖርባቸዋል (የሐ.ሥ.16፡31)፡፡ በበዓለ ሃምሳ ያመኑ ከአይሁድ የሆኑ ሰዎች “ምን እናድርግ?” ባሉ ጊዜ “ንስሐ ግቡ” ተብለዋል (የሐ.ሥ.2፡42)፤ ከአሕዛብም የሆኑ ሰዎችም ባመኑ ጊዜ “እንኪያስ እግዚአብሔር ለአሕዛብ ደግሞ ለሕይወት የሚሆን ንስሐን ሰጣቸው” ተባለ (የሐ.ሥ.11፡18)፡፡ ስለሆነም የማምኑ ሰዎች የሚገቡት ንስሐ በጌታ በኢየሱስ ከማመን ጋር የተያያዘ ንስሐ ነው፡፡
ቀደም ሲል በተከታታይ እንደተመለከትነው ለዘላለም የዳኑ አማኞች በዚህ ምድር ላይ በሥጋ እንዲኖሩ በቀረላቸው ዘመን ውስጥ ከሥጋ የተነሣ ተሰናክለው ሳይፈልጉ በኃጢአት ሊወድቁ ይችላሉ (ሮሜ 7፡19-20)፡፡ “ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም” ይላል (1ዮሐ.1፡8)፡፡ እነዚህ አማኞች የዘላለምን ሕይወት ያገኙት በጌታ በኢየሱስ እንጂ በራሳቸው ባለመሆኑ ያገኙትን ሕይወት ባያጡትም፣ በኃጢአታቸው እግዚአብሔርን ያሳዝናሉ (ኤፌ.4፡30)፤ ኃጢአትን እያደረጉ ከእርሱ ጋር ኅብረት ሊኖራቸው አይችልም (1ዮሐ.1፡6)፤ እንደ እርሱ የጽድቅ ውሳኔም በአባት ፍቅር ይቀጣሉ (ዕብ.12፡5-11)፡፡
ታዲያ በኃጢአት ምክንያት እግዚአብሔርን ያሳዘኑ አማኞች ወደ እርሱ ተመልሰው ኅብረታቸውን የሚያድሱበት መንገድ ንስሐ ነው፤ “በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው” ይላል (1ዮሐ.1:9)። ስለሆነም ንስሐ የሚተገበርበት መንገድ ኃጢአትን በመናዘዝ ነው፤ “መናዘዝ” በራስ ላይ እየፈረዱ ኃጢአትን በግልጽ ለእግዚአብሔር በጸሎት መናገር ነው፡፡ “ኃጢአቴን ለአንተ አስታወቅሁ፥ በደሌንም አልሸፈንሁም፤ ለእግዚአብሔር መተላለፌን እነግራለሁ አልሁ፤ አንተም የልቤን ኃጢአት ተውህልኝ” እንዳለ (መዝ.32:5)።
ሕያውና የሚሠራ በሆነው የእግዚአብሔር ቃል ተመርምሮና ተወቅሶ (ዕብ.4፡12)፣ በኃጢአት መውደቁን የተቀበለ አማኝ ከእግዚአብሔር አባቱ ጋር የነበረውን ኅብረት ለማደስ፣ በተሰበረ ልብና በእፍረት ሆኖ ወደ ጌታ በመመለስ ኃጢአቱን እየተናዘዘ ንስሐ መግባት ይኖርበታል፡፡ “እንግዲህ ከወዴት እንደ ወደቅህ አስብ ንስሐም ግባ፤ የቀደመውንም ሥራህን አድርግ፤ አለዚያ እመጣብሃለሁ ንስሐም ባትገባ መቅረዝህን ከስፍራው እወስዳለሁ” የሚለው ጥሪ ዛሬም በኃጢአት ለወደቀው አማኝ የቀረበ የንስሐ ጥሪ ነው! (ራእ.2፡5)። ይህ ምናልባት ተሰናክሎ በኃጢአት የወደቀ እውነተኛ አማኝ የሚገባው ንስሐ ሲሆን የአፍ አማኝን ግን ለንስሐ ማደስ አይቻልም (ዕብ.6፡6)፡፡ እንዲህ ያለው ሰው ንስሐ ሊገባ ስለማይችል “ንስሐ ቢገባስ?” ተብሎ የሚል ጠያቄ ሊነሳለት አይችልም፡፡
“ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” (1ዮሐ.2:1)። ሐዋርያው ዮሐንስ ይህን ቃል የጻፈው “ልጆቼ” ብሎ ለጠራቸው አማኞች ነው፤ በተጨማሪም እነዚህን የመልእክቲቱን ተቀባዮች “ወንድሞች ሆይ” (1ዮሐ.2፡7)፣ “ልጆች ሆይ” (1ዮሐ.2፡12፣18፣28) ብሎ ጠርቷቸዋል፡፡ ስለሆነም እነዚህ አማኞች ዮሐንስ በኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የወለዳቸው ማለትም ወንጌል መስክሮ ለእምነት ያበቃቸው ናቸው (1ቆሮ.3፡15)፡፡ ከዚህ አንጻር ስንመለከት በወንጌል አምነው እንደዳኑና “የእግዚአብሔር ልጆች” እንደሆኑ፣ የዘላለም ሕይወት እንዳገኙም እናስተውላለን፡፡ ይህንንም ሲያረጋግጥ ዮሐንስ “የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደ ሰጠን እዩ፥ እንዲሁም ነን” በማለት ራሱን ጨምሮ ይናገራል (1ዮሐ.3:1)። ስለዚህ የኢየሱስ ጠበቃነት “የእግዚአብሔር ልጆች” ለሆኑ ወይም ከዘላለም ሞት ለዳኑ እና የዘላለም ሕይወት ላገኙ ሰዎች ነው፡፡ ሐዋርያው ከአብ ዘንድ ጠበቃ “አለን” በማለት ራሱን ጨምሮ መናገሩም ይህንኑ የሚያስረግጥ ነው፡፡
“ጠበቃ” የሚለው ቃል በአንዳች ጥፋት ተከሶ ፍርድ ቤት በቀረበ ሰው ጎን በመቆም ክርክር የሚያደርግ ሰው ነው፡፡ ስለሆነም “ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን” የሚለው ቃል በፍርድ ቤታዊ አሠራር ምሳሌነት የቀረበ ትምህርት ሲሆን አማኝ ድንገት ኃጢአትን ቢያደርግ የኢየሱስ ጠበቃነት ዋስትና እንደሚሆነው የተሰጠ ማረጋገጫ ነው፡፡ አማኝ ኃጢአትን ማድረግ የሚችል ማንነት ቢኖረውም ኃጢአትን እንዲያደርግ አልተፈቀደለትም፤ ሆኖም ግን አማኝ ከዚህ መርህ ወድቆ ኃጢአትን ሊያደርግ እንደሚችል ታሳቢ በማድረግ እግዚአብሔር በአባታዊ ፍቅሩ ከእርሱ ዘንድ የሆነ ጠበቃን ሰጥቶታል፡፡ ይህም አማኙ በኃጢአት በሚወድቅ ጊዜ ከሳሽ እንዳለበት የሚያሳይ ነው (ራእ.12፡10)፡፡ ከአብ ዘንድ የሆነው ጠበቃ ግን አማኙ ስለተከሰሰበት ኃጢአት አስቀድሞ ሞቷል፤ በዚህም የከሳሹን ክስ ውድቅ ያደርገዋል፡፡
አማኙ የሠራው ኃጢአት የሞት ፍርድ የሚገባው ቢሆንም ያንን ሞት ጠበቃው ስለሞተለት ቀደም ሲል ባመነ ጊዜ ያገኘው የዘላለም ሕይወት የተጠበቀ ይሆንለታል፡፡ ነገር ግን ከአብ ዘንድ የሆነው ጠበቃ ምንም እንኳን የአማኙን የዘላለም ሕይወት ዋስትና ቢያስጠብቅለትም፣ አማኙ አሁን ለሠራው ኃጢአት የሚገባውን የአባት ቅጣት እንዲቀጣ፣ ከዚያም ንስሐ ገብቶ ኃጢአቱን በመናዘዝ ወደ አባት እንዲመለስ ያደርገዋል፡፡ ይህንንም የሚያደርገው እርሱ “ጠበቃ” ብቻ ሳይሆን “ጻድቅም” ስለሆነ ነው፡፡ “ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን” ብሎ ጠበቃነቱን ከተናገረ በኋላ “እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” ብሎ ጻድቅነቱን የተናገረው ለዚያ ነው (1ዮሐ.2፡1)፡፡ አማኙ ለሠራው ኃጢአት የእርሱ ሞት እንዲቆጠርለት፣ አማኙ በሥጋው እንዲቀጣ፣ እንዲሁም በኃጢአቱ ፈርዶ ንስሐ እንዲገባ የሚያደርገው ጻድቅ ስለሆነ ነውና፡፡
ወንጌል ተሰብኮልን ወደ ክርስቶስ ከመምጣታችን በፊት የነበረን ማንነት በኃጢአት የረከሰ ነበር። እግዚአብሔር ደግሞ ቅዱስ ስለሆነ እኛ በፊቱ መቅረብ እንችል ዘንድ መንጻት ይገባን ነበር። ከዚህ ኃጢአታችን ሊያጥበንና ሊያነጻን የሚችለው ደግሞ ስለ ኃጢአታችን የፈሰሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ነው።
ሰው ከኃጢአቱ በክርስቶስ ደም መንጻት ያስፈለገው የኃጢአት ደመወዝ ሞት በመሆኑ ነው። የደም መፍሰስ ሞትን ያሳያልና። ክርስቶስ በኃጢአተኛ ሥጋ ምሳሌ ሆኖ (ሮሜ 8፡3-4)፥ በመስቀል ላይ ደሙን አፍስሶ የሞተው በእኛ ምትክ በመሆኑ በኃጢአታችን የተነሣ የሚገባን የሞት ፍርድ ተፈጽሟል። ስለሆነም እርሱን ባመንን ጊዜ በውስጣችን ካለው ኃጢአትም ሆነ ከሠራነው ኃጢአት ንጹሐን ተደርገን እንቆጠራለን።
በሕጉ ዘመን ሁሉም ነገር የሚነጻው መሥዋዕት ሆነው በሚቀርቡ የእንስሳት ደም ነበር። "እንደ ሕጉም ከጥቂቶች በቀር ነገር ሁሉ በደም ይነጻል፥ ደምም ሳይፈስ ስርየት የለም" ይላል (ዕብ.9፡22)። በዚህ በጸጋው ዘመን ደግሞ በክርስቶስ የሚያምኑ ኃጢአተኞች አንድ ጊዜ በፈሰሰው በክርስቶስ ደም ታጥበው ይነጻሉ። "ለወደደን ከኃጢአታችንም በደሙ ላጠበን ... ለእርሱ ከዘላለም እስከዘላለም ድረስ ክብርና ኃይል ይሁን" ይላል (ራእ.1፡5-6)። ወደፊት በሚመጣው በመከራው ዘመንም ከታላቁ መከራ የሚድኑት ሰዎች ልብሳቸውን በበጉ ደም አጥበው ያነጹ ናቸው (ራእ.7፡14)። ነገር ግን በክርስቶስ ደም ነጽተን ወደ ቅዱሱ እግዚአብሔር መቅረብ ከቻልን በኋላ በምድር ላይ በቀረው ዘመናችን ከሥጋ የተነሣ በምንሠራው ኃጢአት ልናድፍ እንችላለን። ይሁን እንጂ በሕጉ ዘመን የነበረው አማኝ ኃጢአት በሠራ ቁጥር የኃጢአት መሥዋዕት ማቅረብ እንደሚያስፈልገው ለእኛ ኃጢአት ክርስቶስ በተደጋጋሚ መሞት አላስፈለገውም። አንድ ጊዜ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ የፈሰሰው ንጹሕ ደሙ ሁል ጊዜም የማንጻት ኃይል አለው። በንስሐ ወደ እርሱ በተመለስን ጊዜ ያው አንድ ጊዜ የፈሰሰው የክርስቶስ ደም ንስሐ ለገባንበት ኃጢአትም ይቆጠራል። ያው የክርስቶስ ሞት ያ ኃጢአታችን ለሚገባው የሞት ፍርድ የሚቆጠር ይሆናል። “የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል። ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም። በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው።” ተብሎ ተጽፏል (1ኛ ዮሐንስ 1፥7)።
በክርስቶስ አምኖ የዘላለም ሕይወት ያገኘ ሰው እግዚአብሔርን ለማምለክ ንጹሕ ኅሊና ሊኖረው ይገባል። ይህንንም ንጹሕ ኅሊና የሚያገኘው ኃጢአቱን በተናዘዘ ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት የቀረበው ያው የክርስቶስ ደም ስለእርሱ እንደሚቆጠር ያመነ በመሆኑ ነው። “ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ ሕያውን እግዚአብሔርን ልታመልኩ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን?” ይላል (ዕብራውያን 9፥14)። ስለዚህ በዚህ ደም ሁል ጊዜም ልባችንን በእምነት ተረጭተን እየነጻን ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ድፍረት ሊኖረን ይገባል (ዕብ.10፥19-22)።
ከሕግ በታች በመሆን፣ ወይም የሕግን ሥራ ለመሥራት በመጣር፣ መቼም ቢሆን ከፍርሃት ወጥተን ሰላም ሊሰማን፣ ወደ እግዚአብሔርም ልንቀርብ አንችልም፤ ሰላማችን በመስቀል ላይ ስለኃጢአታችን ሞቶ ከእግዚአብሔር ጋር ያስታረቀን ክርስቶስ ብቻ ነው (ኤፌ2፡15፤ ቆላስ.1፡19-22)፤ እርሱ ርቀው ለነበሩት አሕዛብ ብቻ ሳይሆን ቀርበው ለነበሩት ለእስራኤልም እንኳ ሰላምን “ምስራች” ብሎ ሰብኳል፡፡ ይህን ሰምቶ ከማረፍ ይልቅ ከሕግ በታች ሆኖ ወደ ራስ ብቻ በመመልከት ኃጢአትን እያሰቡ መኖር ሁል ጊዜ ከመቆዘምና ከመፍራት አያወጣም፡፡
ብዙ ሰዎች በቅድሚያ ኃጢአተኝነታቸውን ካወቁ በኋላ ባሳለፉት ዘመን ከፍ ያለ ጸጸት ተሰምቷቸው ንስሐ ሲገቡ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ “እፈራለሁ” ይላሉ፤ ይህም ልክ ሙሴ እግዚአብሔርን በቅዱስ ማንነቱ ባስፈሪ ገጽታው ባየው ጊዜ “እፈራለሁ እንቀጠቀጥማለሁ” እንዳለው ነው (ዕብ.12፡21)፤ አሁን ግን ዘመኑ የእግዚአብሔር የፍቅር እጆች ወደ ሰው ልጆች ተዘርግተው ወደ እኛ የቀረበበት የጸጋ ዘመን ነው፤ በጌታ በኢየሱስ ከልብ ያመኑ እውነተኛ አማኞች ዕዳቸው በመስቀል ላይ ስለተከፈለ፣ እግዚአብሔር “ኃጢአታቸውን ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ” ከእነርሱ አርቆታል (መዝ.103፡12)፤ “ኃጢአታቸውንና ዓመፃቸውን ደግሜ አላስብም” ብሏል (ዕብ.10፡17)፤ ስለሆነም አማኞች በኃጢአታቸው የሚገባቸው የሞት ፍርድ በክርስቶስ ላይ ስለተፈጸመና እግዚአብሔርም ስለረካ ወደ እርሱ ለመቅረብ የሚያስፈራቸው ነገር ተወግዶልናል፤ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” የሚለው አዋጅም ታውጆላቸዋል፡፡
ታዲያ ይህ ባለበት ሁኔታ አሁንም ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ወደ ውስጥ ለመግባት “እፈራለሁ” ማለት አይኖርብንም፤ በክርስቶስ ሥራ የተነሣ ወደ አብ ለመግባት ያለንን ድፍረት ማወቅ ይገባናል፡፡ ቃሉ “በእርሱ ሥራ ወደ አብ መግባት አለን” ይላል (ኤፌ.2፡18)። እንዲሁም “በእርሱም ዘንድ ባለ እምነታችን በኩል በመታመን ድፍረትና መግባት በእርሱ አለን” ይላል (ኤፌ3:12)። በተጨማሪም “ወደ ቅድስት በኢየሱስ ደም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል እንድንገባ ድፍረት ስላለን… በእምነት እንቅረብ” እያለ ወደ ውስጥ እንድንገባ ያደፋፍረናል (ዕብ.10፡19-20)፡፡ ስለሆነም ክርስቶስን ከልብ በሆነ እውነተኛ እምነት ያመንን ሰዎች የማይጠፋ ዘላለማዊ ሕይወት ያለን በመሆኑ ፍጻሜ የሌለው ዘላለማዊ ሰላምም በእርሱ አለን (ኢሳ.9፡7፤ ኤፌ.2፡14)፡፡
--------//------>