ቤተክርስቲያን/Aclesia  

በክርስቶስ ደም መንጻት

ወንጌል ተሰብኮልን ወደ ክርስቶስ ከመምጣታችን በፊት የነበረን ማንነት በኃጢአት የረከሰ ነበር። እግዚአብሔር ደግሞ ቅዱስ ስለሆነ እኛ በፊቱ መቅረብ እንችል ዘንድ መንጻት ይገባን ነበር። ከዚህ ኃጢአታችን ሊያጥበንና ሊያነጻን የሚችለው ደግሞ ስለ ኃጢአታችን የፈሰሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ነው። ሰው ከኃጢአቱ በክርስቶስ ደም መንጻት ያስፈለገው የኃጢአት ደመወዝ ሞት በመሆኑ ነው። የደም መፍሰስ ሞትን ያሳያልና። ክርስቶስ በኃጢአተኛ ሥጋ ምሳሌ ሆኖ (ሮሜ 8፡3-4)፥ በመስቀል ላይ ደሙን አፍስሶ የሞተው በእኛ ምትክ በመሆኑ በኃጢአታችን የተነሣ የሚገባን የሞት ፍርድ ተፈጽሟል። ስለሆነም እርሱን ባመንን ጊዜ በውስጣችን ካለው ኃጢአትም ሆነ ከሠራነው ኃጢአት ንጹሐን ተደርገን እንቆጠራለን።

በሕጉ ዘመን ሁሉም ነገር የሚነጻው መሥዋዕት ሆነው በሚቀርቡ የእንስሳት ደም ነበር። "እንደ ሕጉም ከጥቂቶች በቀር ነገር ሁሉ በደም ይነጻል፥ ደምም ሳይፈስ ስርየት የለም" ይላል (ዕብ.9፡22)። በዚህ በጸጋው ዘመን ደግሞ በክርስቶስ የሚያምኑ ኃጢአተኞች አንድ ጊዜ በፈሰሰው በክርስቶስ ደም ታጥበው ይነጻሉ። "ለወደደን ከኃጢአታችንም በደሙ ላጠበን ... ለእርሱ ከዘላለም እስከዘላለም ድረስ ክብርና ኃይል ይሁን" ይላል (ራእ.1፡5-6)። ወደፊት በሚመጣው በመከራው ዘመንም ከታላቁ መከራ የሚድኑት ሰዎች ልብሳቸውን በበጉ ደም አጥበው ያነጹ ናቸው (ራእ.7፡14)።

ነገር ግን በክርስቶስ ደም ነጽተን ወደ ቅዱሱ እግዚአብሔር መቅረብ ከቻልን በኋላ በምድር ላይ በቀረው ዘመናችን ከሥጋ የተነሣ በምንሠራው ኃጢአት ልናድፍ እንችላለን። ይሁን እንጂ በሕጉ ዘመን የነበረው አማኝ ኃጢአት በሠራ ቁጥር የኃጢአት መሥዋዕት ማቅረብ እንደሚያስፈልገው ለእኛ ኃጢአት ክርስቶስ በተደጋጋሚ መሞት አላስፈለገውም። አንድ ጊዜ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ የፈሰሰው ንጹሕ ደሙ ሁል ጊዜም የማንጻት ኃይል አለው። በንስሐ ወደ እርሱ በተመለስን ጊዜ ያው አንድ ጊዜ የፈሰሰው የክርስቶስ ደም ንስሐ ለገባንበት ኃጢአትም ይቆጠራል። ያው የክርስቶስ ሞት ያ ኃጢአታችን ለሚገባው የሞት ፍርድ የሚቆጠር ይሆናል። “የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል። ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም። በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው።” ተብሎ ተጽፏል (1ኛ ዮሐንስ 1፥7)።

በክርስቶስ አምኖ የዘላለም ሕይወት ያገኘ ሰው እግዚአብሔርን ለማምለክ ንጹሕ ኅሊና ሊኖረው ይገባል። ይህንንም ንጹሕ ኅሊና የሚያገኘው ኃጢአቱን በተናዘዘ ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት የቀረበው ያው የክርስቶስ ደም ስለእርሱ እንደሚቆጠር ያመነ በመሆኑ ነው። “ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ ሕያውን እግዚአብሔርን ልታመልኩ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን?” ይላል (ዕብራውያን 9፥14)። ስለዚህ በዚህ ደም ሁል ጊዜም ልባችንን በእምነት ተረጭተን እየነጻን ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ድፍረት ሊኖረን ይገባል (ዕብ.10፥19-22)።

ሰላምን የምስራች ብሎ ሰበከ

“መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን፥ ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን *የምስራች* ብሎ ሰበከ” (ኤፌ.2:17)፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የእግዚአብሔርን የጽድቅ ፍርድ ስለእኛ ተቀብሎ ከሞተ በኋላ ከእግዚአብሔር ጋር ስለታረቀን ከትንሣኤው በኋላ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” በማለት ሰላምን “የምስራች” ብሎ ተናግሯል (ዮሐ.20፡19)፡፡ ዛሬም እንዲሁ ጌታ በሞት ፍርሃት ውስጥ ላሉ ሰዎች ጌታ የሚናገረው የሰላም የምስራች አለው፡፡ ይህም የሰላም ወንጌል ይባላል (ኤፌ.6፡14)፤ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ለሚፈሩ እና በጭንቀት ውስጥ ለሚኖሩ ሁሉ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” የሚለው ቃል የምስራች ይሆንላቸዋልና፡፡ ከሕግ በታች በመሆን፣ ወይም የሕግን ሥራ ለመሥራት በመጣር፣ መቼም ቢሆን ከፍርሃት ወጥተን ሰላም ሊሰማን፣ ወደ እግዚአብሔርም ልንቀርብ አንችልም፤ ሰላማችን በመስቀል ላይ ስለኃጢአታችን ሞቶ ከእግዚአብሔር ጋር ያስታረቀን ክርስቶስ ብቻ ነው (ኤፌ2፡15፤ ቆላስ.1፡19-22)፤ እርሱ ርቀው ለነበሩት አሕዛብ ብቻ ሳይሆን ቀርበው ለነበሩት ለእስራኤልም እንኳ ሰላምን “ምስራች” ብሎ ሰብኳል፡፡ ይህን ሰምቶ ከማረፍ ይልቅ ከሕግ በታች ሆኖ ወደ ራስ ብቻ በመመልከት ኃጢአትን እያሰቡ መኖር ሁል ጊዜ ከመቆዘምና ከመፍራት አያወጣም፡፡

ብዙ ሰዎች በቅድሚያ ኃጢአተኝነታቸውን ካወቁ በኋላ ባሳለፉት ዘመን ከፍ ያለ ጸጸት ተሰምቷቸው ንስሐ ሲገቡ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ “እፈራለሁ” ይላሉ፤ ይህም ልክ ሙሴ እግዚአብሔርን በቅዱስ ማንነቱ ባስፈሪ ገጽታው ባየው ጊዜ “እፈራለሁ እንቀጠቀጥማለሁ” እንዳለው ነው (ዕብ.12፡21)፤ አሁን ግን ዘመኑ የእግዚአብሔር የፍቅር እጆች ወደ ሰው ልጆች ተዘርግተው ወደ እኛ የቀረበበት የጸጋ ዘመን ነው፤ በጌታ በኢየሱስ ከልብ ያመኑ እውነተኛ አማኞች ዕዳቸው በመስቀል ላይ ስለተከፈለ፣ እግዚአብሔር “ኃጢአታቸውን ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ” ከእነርሱ አርቆታል (መዝ.103፡12)፤ “ኃጢአታቸውንና ዓመፃቸውን ደግሜ አላስብም” ብሏል (ዕብ.10፡17)፤ ስለሆነም አማኞች በኃጢአታቸው የሚገባቸው የሞት ፍርድ በክርስቶስ ላይ ስለተፈጸመና እግዚአብሔርም ስለረካ ወደ እርሱ ለመቅረብ የሚያስፈራቸው ነገር ተወግዶልናል፤ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” የሚለው አዋጅም ታውጆላቸዋል፡፡

ታዲያ ይህ ባለበት ሁኔታ አሁንም ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ወደ ውስጥ ለመግባት “እፈራለሁ” ማለት አይኖርብንም፤ በክርስቶስ ሥራ የተነሣ ወደ አብ ለመግባት ያለንን ድፍረት ማወቅ ይገባናል፡፡ ቃሉ “በእርሱ ሥራ ወደ አብ መግባት አለን” ይላል (ኤፌ.2፡18)። እንዲሁም “በእርሱም ዘንድ ባለ እምነታችን በኩል በመታመን ድፍረትና መግባት በእርሱ አለን” ይላል (ኤፌ3:12)። በተጨማሪም “ወደ ቅድስት በኢየሱስ ደም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል እንድንገባ ድፍረት ስላለን… በእምነት እንቅረብ” እያለ ወደ ውስጥ እንድንገባ ያደፋፍረናል (ዕብ.10፡19-20)፡፡ ስለሆነም ክርስቶስን ከልብ በሆነ እውነተኛ እምነት ያመንን ሰዎች የማይጠፋ ዘላለማዊ ሕይወት ያለን በመሆኑ ፍጻሜ የሌለው ዘላለማዊ ሰላምም በእርሱ አለን (ኢሳ.9፡7፤ ኤፌ.2፡14)፡፡

የዘላለም ሕይወት የጊዜ ወሰን በሌለው ሁኔታ ውስጥ ለዘላለም መኖር ብቻ አይደለም፤ ያልዳኑ ሰዎችም ቢሆኑ “በእሳት ባሕር” ውስጥ በሥቃይ የሚኖሩት “ለዘላለም” መሆኑ ተነግሯል፤ “ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ” ይባላሉ (ማቴ.25፡41)። “በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ” (2ተሰ.1፡10፤ ማቴ.25፡46)፣ እንዲሁም “ለዘላለምም እስከ ዘላለም ቀንና ሌሊት ይሣቀያሉ” (ራእ.20፡10) ተብሎ ተጽፏል፡፡ “የዘላለም ሕይወት” ሲባል ግን በዘመን ሳይገደቡ ለዘላለም መኖር ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርን በማወቅ ከእርሱ ጋር ለዘላለም በኅብረት መኖር ነው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጨረሻው ጸሎቱ ውስጥ የዘላለም ሕይወትን ሲገልጸው “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” ብሏል (ዮሐ.17፡2-3)። እግዚአብሔርን ስናውቅ በእርሱ ዘንድ ያለውን ባሕርይ፣ ፈቃድ እና መሻት በአእምሮአችን ብቻ ሳይሆን በመንፈሳችንም ማለት በውስጣዊ ማንነታችን እናውቀዋለን፤ በተግባርም ይዋሐደናል፡፡ ይህ በመለኮት ዘንድ ያለው የዘላለም ሕይወት በክርስቶስ መምጣት የተገለጠ፣ በሐዋርያትም የተሰበከ ነው፤ ሐዋርያት “ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል፣ እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን” በማለት ነግረውናል (1ዮሐ.1:2)፡፡ የዚህም ውጤቱ “ከአባት ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ኅብረት ማድረግ” ነው (1ዮሐ.1፡3)፡፡ ይህም የዘላለም ሕይወት የሚገኘው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን መሆኑ በተደጋጋሚ ተነግሯል። “በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት *አለው* ” ተብሎ ተጽፏል (ዮሐ.3፡36)። ራሱም ሲናገር “እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት *አለው* ” ብሏል (ዮሐ.6:47)። “አለው” የሚለው ቃል በክርስቶስ ያመነ ሰው የዘላለም ሕይወት ባለቤት የሚሆነው ባመነ ጊዜ እንደሆነ ያሳያል። ይህም የዘላለም ሕይወት ክርስቶስን አምነን ከተቀበልንው በኋላ ለዘላለም የማይወሰድና በውስጣችን የሚኖር መሆኑን ያረጋግጣል። “የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ለምታምኑ ይህን ጽፌላችኋለሁ” የሚለው ቃል ይህን ይበልጥ አስረግጦ የሚናገር ነው (1ኛ ዮሐ. 5፥13)። ጥያቄው ግን ክርስቶስን አምነናል ላሉ ሁሉ የዘላለም ሕይወት ይሰጣልን? ለመሆኑ ክርስቶስን ማመን ምንድን ነው? የዘላለም ሕይወት የሚሰጠው ለምን ዓይነት አማኝ ነው?

የልብ አማኞች እና የአፍ አማኞች
ሰው መዳንንም ሆነ የዘላለም ሕይወትን የሚያገኘው ክርስቶስን በማመን መሆኑ በወንጌል የተመሰከረ እውነት ነው። "ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ። ያመነ የተጠመቀም ይድናል፥ ያላመነ ግን ይፈረድበታል" ይላል (ማር.16፡15-16)። ሆኖም ወንጌል ተሰብኮላቸው ክርስቶስን አምነናል ካሉ ሰዎች መካከል ከልብ በእውነት ክርስቶስን ያመኑ የልብ አማኞች ያሉትን ያህል፣ በአፍ ብቻ በግብዝነት አምናለሁ የሚሉ የአፍ አማኞችም አሉ። ሰው የዘላለም መዳንንም ሆነ የዘላለም ሕይወትን የሚያገኘው ከልብ በሆነ እውነትኛ እምነት እንጂ የአፍ ብቻ በሆነ እምነት አይደለም። "ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና” ይላል (ሮሜ 10፡9-10)። ይህ የልብ እምነት "ግብዝነት የሌለበት እምነት" ተብሏል (1ጢሞ.1፥5)። እንዲህ ያለው ግብዝነት የሌለበት እምነት በጢሞቴዎስ፣ በእናቱና በአያቱ እንደነበረ ተገልጿል (2ጢሞ.1፥5)። በእውነተኛ አማኞች ዘንድ ሁሉ ያለው እምነት ይህ እምነት ነው። ለመዳንም ሆነ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የሚያስችለውም እምነት፣ ምንም ዓይነት ማስመሰል ወይም ግብዝነት የሌለበት ይህ እውነተኛ እምነት ነው።

በእውነት ከልባቸው ክርስቶስን ያመኑ ሰዎች የእምነታችው እውነተኝነት በሰው ፊት ተገልጦ የሚታይባቸው ወይም የሚረጋገጥባቸው መንገዶች አሉ። ክርስቶስን አምኖ በውኃ መጠመቅ እና ያመኑትን በአፍ መመስከር የልብ እምነት መገለጫዎች መሆናቸው ከላይ በጠቀስናቸው ንባቦች ውስጥ ተመላክቷል። እንዲሁም "መልካም ሥራ" የእውነተኛ እምነት ማሳያ መሆኑ በያዕቆብ መልእክት በስፋት ተነግሯል (ያዕ.2፡18)። ያዕቆብ የአብርሃም እምነት በሥራ የተረጋገጠ እውነተኛ እምነት መሆኑን በገለጸ ጊዜ "እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ያደርግ እንደ ነበረ፥ በሥራም እምነት እንደ ተፈጸመ ትመለከታለህን?" ብሏል (ያዕ.2፡22-23)። ስለዚህ ያለን እምነት እውነተኛነት ከመልካም ሥራ ጋር የሚታይና መልካም ሥራ የማይለየው በመሆኑ ይታወቃል። እንዲህ ያለ እውነተኛ እምነት ያላቸው ለዘላለም የዳኑና የዘላለም ሕይወት ያላቸው ናቸው።

በሌላ በኩል የአፍ አማኞችን በተመለከተ ክርስቶስ ሲናገር “ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፥ ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው” ብሏል (ማቴ.15፥8)። እንዲሁም “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ “ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም” በማለት አስተምሯል (ማቴ. 7፥21)። እንዲሁም እነዚህ "ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ" እያሉ በከንፈር ብቻ የሚያከብሩ የአፍ አማኞች ከእውነተኛ አማኞች ጋር ሊቀላቀሉ እንደሚችሉ ጌታ ሲያስተምር "በስንዴ መካከል በበቀለ እንክርዳድ" (ማቴ.13፡24-30፣36-43)፣ "ከመልካም ዓሣዎች ጋር በተጠመዱ ክፉ ዓሣዎች" (ማቴ.13፡47-50)፣ "ከልባም ቆነጃጅት ጋር አብረው በነበሩ በመብራታቸው ውስጥ ግን ዘይት ባልያዙ ቆነጃጅት" (ማቴ.25፡1-12) ምሳሌነት ገልጿቸዋል። እነዚህን የአፍ አማኞች "አላወቅኋችሁም" እንደሚላቸው በመግለጽ ቀድሞውኑ ያልዳኑ መሆናቸውን፣ መጨረሻቸውም ፍርድ እንደሆነ ተናግሯል (ማቴ.13፡30፤ 40-42)። ስለዚህ የአፍ አማኞች የሚፈረድባቸው መጀመሪያም ስላልዳኑና የዘላለም ሕይወትን ስላላገኙ ነው እንጂ ከዳኑ በኋላ መዳናቸውና ያገኙት ሕይወት ስለሚወሰድ አይደለም።

ታዲያ በክርስቶስ አምነናል የሚሉ ሰዎች እምነታቸው "የልብ" መሆንኑን፥ ወይም "የአፍ ብቻ" መሆኑን፥ በትክክል የሚያውቀው ልብን የሚያውቅ ጌታ ብቻ ነው። ምልክት አይተው "አመኑ" የተባሉ ሰዎችን በተመለከተ የተጻፈው ቃል “ነገር ግን ኢየሱስ ሰዎችን ሁሉ ያውቅ ነበር፤ ስለ ሰውም ማንም ሊመሰክር አያስፈልገውም ነበርና አይተማመናቸውም ነበር ፤ ራሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና” ይላል (ዮሐ. 2፥24-25)። በዮሐ.8 ውስጥ "ያመኑት አይሁድ" ተብለው የተጠሩትን (ቁ.31)፣ ነገር ግን በቃሉ የማይኖሩትን አይሁድ ጌታ "የኃጢአት ባሪያዎች" (ቁ.34)፣ "የዲያብሎስ ልጆች" (ቁ.44) ብሎ ገልጿቸዋል። እነዚህ ሰዎች "አመኑ" የተባለው ጌታ በሚያደርገውና በሚናገረው ነገር አሳማኝነት ምክንያት ምርጫ ስለሌላቸው የግድ ሆኖባቸው በማመናቸው ነው እንጂ ከልብ ተቀብለው ስላመኑ አልነበረም። ከልብ አለማመናቸውንም "የሁሉን ልብ የሚያውቅ ጌታ" (የሐ.ሥ.1፡24፤ ዮሐ.21፡17) ያውቀዋል። እንዲህ ያሉ የአፍ አማኞች በሰዎች ዘንድ የሚታወቁት ከፍሬያቸው መሆኑ ተገልጿል (ማቴ.7፡16)። አማኞች ነን ብለው ፍሬያቸው ክፉ ከሆነ እምነታቸው አፍኣዊ ነው። ይህም “ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው” (ያዕ.2፥26) ተብሎ የተገለጸው የሞተ እምነት ነው። እነዚህ የአፍ አማኞች "በጭንጫ ላይ የተዘራው ዘር" ፀሐይ በወጣ ጊዜ እንደሚጠወልግ በቃሉ ምክንያት መከራና ስደት በሚመጣ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላሉ (ማቴ.13፡20-21)። ከእኛ ጋር ተደባልቀው ቢቆዩም “ከእኛ ወገን እንዳልነበሩ ይገለጥ ዘንድ” ከእኛ ተለይተው ይወጣሉ (1ዮሐ.2፡19)። ስለዚህ ሰዎች በውጫዊ መልኩ በአፍ ብቻ አማኝ መስለው እየታዩ በተግባር ግን የማያምኑ ሰዎችን ኑሮ የሚኖሩ ከሆነ ጌታን አምነዋል ማለት አይቻልም።

የአፍ አማኞች "የእውቀትና የእውነት መልክ" ያላቸው፣ ነገር ግን በተግባር "በሥራቸው የካዱ" ናቸው (ሮሜ.2፡19-24፤ ቲቶ 1፡16)። "የአምልኮት መልክ ያላቸው ኃይሉን ግን የካዱ" ናቸው (2ጢሞ.3፡5)። ስለሆነም "መልክ" እንጂ "እውነተኝነት" የሌላቸው መሆኑ በጌታ ስለሚታወቅ ቀድሞውኑ ያልዳኑና ሕይወትን ያላገኙ ናቸው እንጂ በኋላ መዳናቸው ወይም ሕይወታቸው የተወሰደባቸው አይደሉም። በእውነት ከልብ ጌታን አምነው የዳኑና የዘላለም ሕይወት ያገኙ ግን ለዘላለም የዳኑና ለዘላለም የማይጠፉ ናቸው። ይህም በክርስቶስ ያገኘነው የዘላለም መዳንና የዘላለም ሕይት ዋስትና ነው።

የዘላለም ሕይወትና ለዘላለም አለመጥፋት
በክርስቶስ ኢየሱስ ያመኑ ሁሉ በዳግመኛ ልደት ከእግዚአብሔር የተወለዱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆናሉ (ዮሐ.1፡12-13፤ 3፡3፣5)። ዳግመኛ የሚወለዱትም "ከማይጠፋ ዘር" መሆኑ በግልጽ ተነግሮናል (1ጴጥ.1፡23)። ስለሆነም በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው ዳግምኛ የተወለዱ ሁሉ ለዘላለም አይጠፉም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለዘላለም ሕይወት ባስተማረ ጊዜ ሁሉ ስለ አለመጥፋትም አስተምሯል። እስኪ ሁለቱን እንመልከት። 1) "ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል። በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና" (ዮሐንስ 3፡14-16)። ከዚህም ቃል ጌታ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሞተው በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኝ ብቻ ሳይሆን እንዳይጠፋም መሆኑን እንማራለን።

2) በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል፤ እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፥ ለዘላለምም አይጠፉም፥ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም። የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፥ ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም። እኔና አብ አንድ ነን (ዮሐንስ 10፡27-30)። በዚህም ትምህርቱ ጌታችን "በጎቼ" ላላቸው አማኞች "የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ" ካለ በኋላ "ለዘላለምም አይጠፉም" በማለት አስረግጦ ተናግሯል። በዚህ ቃል ውስጥ እጅጉን ደስ የሚለው እኛ የተያዝነው በወልድና በአብ እጅ ሲሆን ከዚያ እጅ ማንም ሊነጥቀን የማይችል መሆኑ ነው። ከዚህም በላይ "እኔና አብ አንድ ነን" የተባለው ወልድና አብ እኛን በአንዲት መለኮታዊ እጅ በመያዛቸው መሆኑ ደስታችንን ወደ አምልኮ ይመራዋል። ታዲያ በወልድና በአብ እጅ ተይዞ እንዴት መጥፋት ይኖራል? ይልቁን "ለዘላለም አይጠፉም" የሚለው ቃል የማይናውጥ ዋስትናችን ሆኖ ይኖራል። ስለዘላለም ሕይወትና ስለ አለመጥፋት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተማርነው ይህ ትምህርት የወንጌል ዋነኛው ይዘት ነው። "ወንጌል" ማለት "የምሥራች" ማለት እንደመሆኑ መጠን በክርስቶስ ለሚያምኑ ሁሉ የዘላለምን ሕይወትን፣ "የምሥራች" ብሎ ይናገራል። ሆኖም ለዚህ የዘላለም ሕይወት የምሥራች ዋስትና ለመስጠት የአለመጥፋት የምሥራችንም አብሮ ይናገራል። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ሲናገር “እርሱ ሞትን ሽሮአልና እኔ ሰባኪና ሐዋርያ አሕዛብንም አስተማሪ እንድሆን በተሾምሁበት በወንጌል ሕይወትንና አለመጥፋትን ወደ ብርሃን አውጥቶአል” ብሏል (2ኛ ጢሞ. 1፥10-11)። ስለዚህ በወንጌል ሊሰበክ የሚገባው ስለ ሕይወት ብቻ ሳይሆን ስለ አለመጥፋትም ሊሆን ይገባል።

በክርስቶስ የሚኖሩና የማይኖሩ ቅርንጫፎች (ዮሐ.15፡1-6)

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ 15 ውስጥ ከደቀመዛሙርቱ ጋር ያለውን ግንኙነት በወይን ግንድና በቅርንጫፎቹ ምሳሌነት አስተምሯል፡፡ በብሉይ ኪዳን ወይን የእስራኤል ምሳሌ እንደነበር ይታወቃል (መዝ.80፡8፤ ኢሳ.5፡1-8፤ ኤር.2፡21፤ ሆሴ.10፡1)፤ ሆኖም እስራኤል ፍሬ ያልተገኘባት ወይን ብቻ ሳይሆን ሆምጣጤ ያፈራች በመሆንዋ ወደጎን ተትታለች፡፡ በምትኩም እግዚአብሔር ክርስቶስን እውነተኛ የወይን ግንድ ደቀመዛሙርቱንም ቅርንጫፎች አደረገ፡፡ ጌታ ይህን ሲገልጽ “እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ ገበሬውም አባቴ ነው … እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ።” በማለት ገልጿል (ቁ.1ና5)።

በዮሐ.15 ውስጥ በክርስቶስ የወይን ግንድነት ላይ ያሉ ሁለት ዓይነት ቅርንጫፎች እንዳሉ ተነግሮናል፤ 1ኛው በቁ.2 ላይ “በእኔ ያለው” የተባለው ቅርንጫፍ ሲሆን፤ 2ኛው ደግሞ በቁ.6 ላይ “በእኔ የማይኖር” የተባለው ቅርንጫፍ ነው፤ በእነዚህ ሁለት ዓይነት ቅርንጫፎች ላይ የሚፈጸሙትን ሁለት ዓይነት ፍርዶች፣ በዮሐ.10፡28-29 ላይ ጌታ ኢየሱስ በጎቼ ያላቸውን በተመለከተ “ለዘላለም አይጠፉም” ብሎ የሰጠውን ግልጽ ዋስትና ሳንዘነጋ መመልከት ይኖርብናል፡፡ እስኪ ሁለቱንም እንመልከታቸው፡፡ 1) የመጀመሪያዎቹ ቅርንጫፍ ዓይነቶች ጌታ ኢየሱስ “በእኔ ያለው” ብሎ የገለጻቸው ቅርንጫፎች ሲሆኑ እነሱም ራሱ ሁለት ዓይነት ናቸው፤ እነርሱም “ፍሬ የማያፈራ” እና “አብዝቶ ያላፈራ” ናቸው፤ ፍሬ የማያፈራውን በተመለከተ ጌታ ሲናገር “ፍሬ የማያፈራውን በእኔ ያለውን ቅርንጫፍ ሁሉ ያስወግደዋል” ብሏል፡፡ “ያስወግደዋል” አለ እንጂ እንደ ቁ.6ቱ “ወደ ውጭ ይጣላል፣ ይደርቅማል፤ … ወደ እሳት ይጥሉአቸዋል፥ ያቃጥሉአቸውማል” አላለም። በመሆኑም በዚህ ስፍራ ላይ “ያስወግደዋል” ማለት በወይን ግንዱ ላይ ካሉ(ከሚኖሩ) ቅርንጫፎች መካከል ይለየዋል ማለት ነው፤ ይህም የወይኑ ገበሬ እግዚአብሔር አባት፣ በክርስቶስ ያለ ሆኖ ሳለ መልካም ፍሬ ያላፈራውን አማኝ፣ በአስተዳደራዊ ቅጣቱ ከሌሎቹ ፍሬ ከሚያፈሩት አማኞች መካከል ይለየዋል ማለት ነው። በሐናንያና በሰጲራ እንዲሁም በአያሌ የቆሮንቶስ አማኞች ላይ እንዳደረገው (የሐ.ሥ.5፡1-11፤ 1ቆሮ.11፡30) እስከ ሥጋዊ ሞት በሚደርስ የቅጣት እርምጃ ይለየዋል ማለት ነው። ምክንያቱም ይህ ቅርንጫፍ “በእኔ ያለው” ስለተባለ በቅጣት ፍርድ ይወገዳል እንጂ ለዘላለም አይጠፋምና፤ መሆኑም “በእሳት የመቃጠል” ፍርድ (የገሃነም እሳት ፍርድ) አይመለከተውም፡፡

“በእኔ ያለው” ከተባሉት ሁለተኛው ዓይነት ቅርንጫፍ ደግሞ ፍሬ ቢያፈራም “አብዝቶ ያላፈራ” ወይም “ብዙ ፍሬ የሌለው” ነው፡፡ ስለዚህኛው ቅርንጫፍ ጌታ ሲናገር “ፍሬ የሚያፈራውንም ሁሉ አብዝቶ እንዲያፈራ ያጠራዋል” ብሏል። “ያጠራዋል” ሲል በአማኙ ሕይወት ውስጥ ያሉ ፍሬውን የቀነሱ አንዳንድ ነገሮችን እግዚአብሔር በራሱ አሠራር በማጽዳት ለበለጠ መንፈሳዊ ፍሬ ያበቃዋል ማለት ነው፡፡ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ትምህርቱን እየሰሙ ያሉትና "እናንተ" እያለ የሚጠራቸው ደቀመዛሙርቱ ይሁዳ የሌለባቸው 11ዱ ደቀመዛሙርት መሆናቸውን እናውቃለን፡፡ እነርሱን በተመለከተ “እናንተ ስለ ነገርኋችሁ ቃል አሁን ንጹሐን ናችሁ” ይላቸዋል (ቁ.3)፡፡ እነርሱና እንደ እነርሱ ያሉ በክርስቶስ ላይ የሚኖሩ ማለትም ከእርሱ ጋር ሕያው ግንኙነት ያላቸው አማኞች ምንም እንኳን ከሰሙት የእግዚአብሔር ቃል የተነሣ ንጹሐን ቢሆኑም አብዝተው እንዲያፈሩ ሊያጠራቸው ተገብቶታል፡፡ 2) ሁለተኛዎቹ የቅርንጫፍ ዓይነቶች ጌታ ኢየሱስ “በእኔ የማይኖር” ያለው ዓይነት ናቸው፤ ይህን ቅርንጫፍ በተመለከተ ጌታ ሲናገር “በእኔ የማይኖር ቢሆን እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል ይደርቅማል፤ እነርሱንም ሰብስበው ወደ እሳት ይጥሉአቸዋል፥ ያቃጥሉአቸውማል።” ብሏል (ቁ.6)። ይህ ዓይነቱ ቅርንጫፍ ጨርሶውኑ ከእርሱ ጋር ምንም ዓይነት ሕያው ግንኙነት የሌለው ነው፤ “በእኔ የማይኖር” መባሉ ይህን ያሳያል፤ ከዚህ ዓይነት ቅርንጫፍ ቀድሞውኑ ምንም ፍሬ ስለማይጠበቅ ከዚህ ቅርንጫፍ ጋር ተያይዞ ፍሬ ስለማፍራት አልተነሣም፡፡ ይልቁን በክርስቶስ የማይኖር በመሆኑ እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ እንደሚጣልና በእሳት እንደሚቃጠል ይናገራል፡፡ ይህም የእሳት ባሕር ፍርድ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ሰው በቅርንጫፎች (የክርስቶስ በሆኑ አማኞች) መካከል ያለ ይምሰል እንጂ፣ እርሱም በአፉ “የክርስቶስ ከሆኑት መካከል ነኝ” ይበል እንጂ፣ ከክርስቶስ ጋር ሕያው ግንኙነት ስለሌለው እውነተኛ አማኝ ሳይሆን የአፍ አማኝ ነው፡፡ እንደ ይሁዳ በጌታ ደቀመዛሙርት መካከል የነበረ ቢሆንም ከመነሻው ጀምሮ ከጌታ ጋር ሕያውና እውነተኛ ግንኙነት ያልነበረው ነው። እንዲህ ያሉ የአፍ አማኞችን በተመለከተ “ከእኛ ዘንድ ወጡ፥ ዳሩ ግን ከእኛ ወገን አልነበሩም፤ ከእኛ ወገንስ ቢሆኑ ከእኛ ጋር ጸንተው በኖሩ ነበር፤ ነገር ግን ሁሉ ከእኛ ወገን እንዳልሆኑ ይገለጡ ዘንድ ወጡ” ተብሎ ተጽፏል። (1ዮሐ.2፥19)። ስለዚህ ከእኛ ዘንድ ቢወጡም ቀድሞውንም ከእኛ ወገን አልነበሩም፤ ማለትም አማኝ መስለው በመካከላችን ቢኖሩም ቀድሞውንም እውነተኛ አማኝ አልነበሩም፥ ቀድሞውንም አልዳኑም ነበር። በክርስቶስ (በግንዱ) የማይኖሩ ቅርንጫፎች ናቸው። ስለሆነም እንዲህ ያለው ሰው ፍሬ ማፍራት አለማፍራቱ ታይቶ ሳይሆን በክርስቶስ የማይኖር ከመሆኑ የተነሣ ወደ እሳት ፍርድ ይጣላል፡፡ በእውነት አምኖ የዳነና በክርስቶስ የሚኖር (በጎቼ ካላቸው መካከል የሆነ) ሰው ግን “ለዘላለም አይጠፋም” (ዮሐ.10፡30)፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን ይህንንና ሌሎቹንም ከዚህ በፊት ያየናቸውን "ስለዘላለም ሕይወት" እና "ለዘላለም ስለአለመጥፋት" የሚናገሩ የራሱ የጌታ ቃላትን ሳንዘነጋ እናንብብ፡፡ ክብር ይግባውና ጌታ ከራሱ ጋር ሊቃረን አይችልም፡፡ ዛሬም ዘወትርም እስከ ዘላለም ክብር ይግባው!!


ቀጣይ ንባብ


Amharic Bible-|- The Holy Bible [King James Version]