በጌታ በኢየሱስ በእውነት ከማመኑ የተነሣ ከማይጠፋው ዘር ዳግመኛ ተወልዶ የዘላለም ሕይወት ያገኘ እውነተኛ አማኝ ኃጢአት ሊሠራ ይችላል? እውነተኛ (የልብ) አማኝ ኃጢአት የማይገዛው ቢሆንም (ሮሜ 6፡14)፣ አንዳንድ ጊዜ በሥጋ ሲሸነፍ ኃጢአት ሊሠራ የሚችልበት አጋጣሚ ይኖራል። ይህንንም ሐዋርያው ዮሐንስ “ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም” በማለት በግልጽ ተናግሮታል (1ዮሐ.1፡8)። እውነተኛ አማኝ ምንም እንኳ ከእግዚአብሔር የተወለደው አዲሱ ሰው በውስጡ ቢኖርም ከሥጋ የተወለደው አሮጌው ሰውም ያ አማኝ በዚህ ምድር እስካለ ድረስ አብሮት ይኖራል። ስለሆነም ከሥጋ ድካም የተነሣ ኃጢአትን የሚሠራበት ጊዜ ይኖራል። ይህ ማለት ግን ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጭ በሥጋችን ደካማነት ምክንያት እግዚአብሔርን የሚያሳዝንና የሚያስቆጣ ኃጢአት ልንሠራ እንችላለን ማለት ነው እንጂ ኃጢአት መሥራት ይፈቀድልናል ማለት አይደለም።
ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢአትን እንደማያደርግ ተገልጿል (በ1ዮሐ. 3፡9፤ 1ዮሐ. 5፥18)። እዚህ ላይ "ኃጢአትን አያደርግም" ማለት፥ ኃጢአትን ማድረግ የሚችል ባሕርይ የለውም ማለት ሳይሆን ኃጢአትን ማድረግ የእርሱ መገለጫ አይደለም፣ ከእርሱ አይጠበቅም፣ ማድረግ የለበትም ማለት ነው። ሆኖም አማኝ ኃጢአት ማድረግ ባይኖርበትም ሊያደርግ እንደሚችል ታሳቢ ተደርጓል። በ1ዮሐ. 2፥1 ላይ “ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ" ካለ በኋላ "ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ...” ማለቱ ይህን ያስረዳል። ታዲያ አማኝ ኃጢአት ማድረግ የሌለበት ሆኖ ሳለ ሊያደርግ የሚችለው እንዴት ነው? እውነተኛ አማኝ ኃጢአትን ሊያደርግ የሚችለው ወዶ፣ ወይም ደስ እያለው ሳይሆን እየጠላው ነው። ይህም ሊሆን የሚችለው በሥጋው ውስጥ ባለ ምኞትና መሻት ተስቦና ተታልሎ በመሸነፍ ነው (ሮሜ.7፡7-8፤ ያዕ.1፡14-15)። "በእኔ ማለት በሥጋዬ በጎ ነገር እንዳይኖር አውቃለሁና፤ ፈቃድ አለኝና፥ መልካሙን ግን ማድረግ የለኝም። የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን በጎውን ነገር አላደርገውም። የማልወደውን የማደርግ ከሆንሁ ግን ያን የማደርገው አሁን እኔ አይደለሁም፥ በእኔ የሚኖር ኃጢአት ነው እንጂ" ይላል (ሮሜ 7፡15-20)።
እውነተኛ አማኝ በሥጋው ኃጢአትን ቢያደርግም እንደ ጴጥሮስ ንስሐ መግባት የሚችል ሰብእና ያለው ነው (ሉቃ.22፡54-62)። የሚጠላውን ነገር በማድረጉ ወዲያው ልቡ በጸጸት ይመታል። ኃጢአቱንም ይናዘዛል። እግዚአብሔርም ኃጢአቱን ይቅር ሊለው ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻው የታመነና ጻድቅ ነው (1ዮሐ.1፡9)።
በክርስትና የተነገረውን የእውነት እውቀት ከተቀበለ በኋላ ወዶ፣ ፈቅዶ፣ ዐቅዶ ኃጢአትን የሚሠራ ሰውን በተመለከተ እንዲህ ተብሏል፡- “የእውነትን እውቀት ከተቀበልን በኋላ ወደን ኃጢአት ብናደርግ ከእንግዲህ ወዲህ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት አይቀርልንምና፥ የሚያስፈራ ግን የፍርድ መጠበቅ ተቃዋሚዎችንም ሊበላ ያለው የእሳት ብርታት አለ” (ዕብ.10፡26-27)። አንድ ሰው የእውነትን እውቀት የተቀበለው ከልቡ አምኖ ከሆነ ኃጢአትን ሊያደርግ የሚችለው በሮሜ 7 ውስጥ እንደተገለጸው "ወዶ" ሳይሆን "ሳይወድ" ነው፤ “የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁና” (ሮሜ7፡19) እንዳለው ነው፡፡ ነገር ግን “የእውነትን እውቀት” ከተቀበልን በኋላ “ *ወደን* ኃጢአት ብናደርግ” ይህን ኃጢአት ለማስተስረይ የቀረ ሌላ መሥዋዕት አይኖረንም፡፡ ወደን ኃጢአት የምናደርግ ከሆነ “የእውነትን እውቀት” የተቀበልነው እንዲሁ "በአእምሮ እውቀት" ደረጃ ነው እንጂ ከልብ በሆነ እምነት አልነበረም ማለት ነው።
እንዲህ ያለ ሰው ኃጢአቱ እንዲሰረይለት እጁን በኃጢአት መሥዋዕቱ ላይ ከመጫን ይልቅ ማለትም የኃጢአት መሥዋዕት የሆነውን ክርስቶስን አምኖ ራሱን ከእርሱ ጋር ከመቁጠር ይልቅ እያወቀ፣ ወዶ፣ ኃጢአትን በማድረግ የቀጠለ ሰው ነው፤ እያወቁ፣ ወዶ፣ ኃጢአትን ማድረግ ደግሞ ያን የኃጢአት መሥዋዕት አለመቀበል ብቻ ሳይሆን፣ መሥዋዕቱን መናቅና ማቃለልም ነው፤ ታዲያ እንዲህ ላለ ሰው ለዚህ ኃጢአቱ ማስተስረያ የኃጢአት መሥዋዕት ከሆነው ከክርስቶስ ሌላ ምን መሥዋዕት ሊቀርለት (ሊመጣለት) ይችላል?፡፡ ይህ ሰው ስፍራው አሁንም ገና ከተቃዋሚዎች ጋር ሲሆን የቀረለት ነገር ቢኖር የሚያስፈራው ፍርድ፣ ተቃዋሚዎችን ሊበላ ያለው የእሳት ብርታት ነው፡፡ ስለሆነም ይህ ሰው የእውነት እውቀት ቢኖረውም ቀድሞውንም የኃጢአት ስርየት ያላገኘ፤ በድፍረት ኃጢአት የቀጠለ፣ ዳግም ያልተወለደ እና የዘላለም ሕይወት ያላገኘ ሰው ነው፡፡ በአካል ከአማኞች ጋር የተቀላቀለ ቢሆንም በልቡ እና በተግባሩ ግን ገና ከተቃዋሚዎች ወገን ነውና፡፡ ይህ ሰው ከልብ በሆነ እምነት ባይሆንም የእውነትን እውቀት ተቀብሎ ከአማኞች ጋር ተቀላቅሎ ከቆየ በኋላ በይፋ በሚወስዳቸው የክህደት እርምጃዎች የአፍ አማኝ እንደነበረ ያረጋግጣል፤ የእግዚአብሔር ቃል ይህን ሰው ሲገልጠው “የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ፣ ያንንም የተቀደሰበትን የኪዳኑን ደም እንደ ርኵስ ነገር የቆጠረ፣ የጸጋውንም መንፈስ ያክፋፋ” ይለዋል (ዕብ.10:31)። ከልቡ አምኖ የነበረ እውነተኛ አማኝ እነዚህን ነገሮች ሊያደርግ አይችልም፡፡ በመሆኑም እነዚህ መገለጫዎች ይህ ሰው የአፍ አማኝ የነበረ መሆኑ የሚያሳዩ ናቸው፤ እስኪ አንድ በአንድ ቀጥሎ እንመለከታቸው፡-
1) *የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ* - የእግዚአብሔርን ልጅ መርገጥ ሲባል፣ “ተቀብያለሁ” ያሉትን ነገር ከመካድም የከፋ ነው፤ ይህ ሰው ስለ እግዚአብሔር ልጅ የሚያውቅና የሚናገር ቢሆንም ይህ ከልብ ማመኑን አያመለክትም፤ ርኩሳን መናፍስትም ኢየሱስን “የእግዚአብሔር ልጅ” ብለውታል (ማቴ.8፡29፤ ማር.3:1)፤ በመሆኑም ይህ ሰው ስለ እግዚአብሔር ልጅ ያለው የእውነት እውቀት ከርኩሳን መናፍስቱ አይለይም፤ አውቀዋለሁ ያለውን የእግዚአብሔርን ልጅ ከልቡ አምኖ ከመከተል ይልቅ በጭካኔ የረገጠ ሰው ነው፤ በዕብ.6፡6 “ለራሳቸው የእግዚአብሔርን ልጅ ይሰቅሉታልና ያዋርዱትማልና” ከተባሉትም የባሰ ነው፡፡ ስለሆነም የአፍ አማኝ እንጂ የልብ አማኝ አይደለም፡፡
2) *የተቀደሰበትን የኪዳኑን ደም እንደ ርኩስ ነገር የቆጠረ* - እዚህ ላይ የተቀደሰበትን ሲል እርሱ በግሉ የተቀደሰ ነበር ማለት አይደለም፤ በተቀደሱት መካከል ተቀላቅሎ አብሮ መቆየቱን የሚያሳይ ነው፤ ለምሳሌ በ1ቆሮ.7:14 “ያላመነ ባል በሚስቱ ተቀድሶአልና፥ ያላመነችም ሚስት በባልዋ ተቀድሳለች” የተባለው ከተቀደሰ ወይም ከተቀደሰች አማኝ ጋር በጋብቻ ካላቸው ጥምረት የተነሳ በተቀደሰ ክልል ውስጥ ስላሉ እንጂ ራሳቸው በግላቸው ተቀድሰዋል ማለት አይደለም፤ ይህም በዚህ መልክ የሚታይ ነው፡፡ እውነተኛ አማኞች የተቀደሱት አዲስ ኪዳን በተመረቀበት የክርስቶስ ደም ነው፤ ታዲያ ይህ የአፍ አማኝ የእውነትን እውቀት ተቀብያለሁ በማለቱ እዚህ ምድር ላይ ከቅዱሳን ጋር በውጫዊ መንገድ የተቀደሰውን ስፍራ ይዟል፡፡ በግሉ ግን የተቀደሰ አለመሆኑን ልብ ማለት ይገባል፤ ለዚያም ነው የኪዳኑን ደም እንደ ርኩስ ነገር ለመቁጠር የደፈረው፤ በዚያ ደም በእውነት ተቀድሶ ቢሆን ኖሮ እርሱን የቀደሰውን ደም እንደ ርኩስ ነገር እንዴት ሊቆጥር ይችላል? በዚሁ በዕብ.10፡14 ውስጥ ከፍ ብለን ስናነብ “አንድ ጊዜ በማቅረብ የሚቀደሱትን የዘላለም ፍጹማን አድርጎአቸዋልና” ይላል፡፡ ስለሆነም በእውነት ተቀድሶ ቢሆን ኖሮ "የዘላለም ፍጹማን" ከተደረጉት ወገን ስለሚሆን ያን የቀደሰውን የኪዳኑን ደም እንደ ርኩስ ነገር አይቆጥርም ነበር፤ ሆኖም በዚህ ደረጃ መዳፈሩ እርሱ በፊትም ቢሆን በግል የተቀደሰ እንዳልነበር የሚያሳይ ነው፡፡
3) *የጸጋውን መንፈስ ያክፋፋ* - መንፈስ ቅዱስ በቃሉ በኩል ሰው በሕግ ሥራ ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ቤዛነት በኩል እንደሚጸድቅ (ሮሜ.3፡24)፣ በጸጋ እንደሚድን (ኤፌ.2፡8) የሚናገር መንፈስ ስለሆነ “የጸጋ መንፈስ” ይባላል፤ ሆኖም የእውነትን እውቀት የተቀበለው የአፍ አማኝ ይህን የጸጋውን መንፈስ ያልተቀበለ ብቻ ሳይሆን “ያክፋፋም” ሰው ነው፤ እርሱም በክርስትና መካከል የተደባለቁና “የሚለያዩ፣ ሥጋውያንም የሆኑ፣ መንፈስ የሌላቸው ሰዎች” (ይሁ.19) እንደተባሉት ያለ ነው። ወደ ክርስትና የገቡ ቢመስልም በሥጋ በሆነ አቅም ሕግን መፈጸም እንችላለን ከሚለው ዕብራዊነታቸው (ይሁዲነታቸው) ያልወጡ ነበሩ፤ በኋላም ከተደባለቁበት ክርስትና በይፋ ወጥተው ትክክለኛ ማንነታቸው ባለበት ይሁዲነት ስለሚቀጥሉ በአዲስ ኪዳን የተገለጠውን የጸጋውን መንፈስ ያክፋፋሉ፡፡ ይህም መንፈስ ቅዱስን መስደብ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ሰው ወደ ንስሐ መጥቶ ኃጢአቱን ተናዝዞ በክርስቶስ ደም ስርየት ማግኘት እንዴት ይችላል? ወደዚህ ንስሐ ሊያደርሰው የሚችለውን የጸጋ መንፈስ አክፋፍቷልና፡፡ መንፈስ ቅዱስን የሰደበ ሰው ኃጢአቱ የማይሰረይለትም በዚህ ምክንያት ነው (ማቴ.12፡32)፤ ይህ ሰው ወዶ ባደረገው ኃጢአት ቢጸጸት እንኳ የሚጸጸተው እንደ ይሁዳ ሲሆን ጸጸቱ ወደ ጥፋት የሚወስድ ብስጭት እንጂ ወደ ንስሐ የሚመራው አይደለም (ማቴ.27፡3-5)። እንደ ዔሳው ለንስሐ ስፍራ አያገኝም (ዕብ.12፡17)። ስለዚህ እንዲህ ያለ ሰው ንስሐ መግባት የሚችል ማንነት የለውም።
በአጠቃላይ የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ፣ የተቀደሰበትን የኪዳኑን ደም እንደ ርኩስ ነገር የቆጠረ እና የጸጋውን መንፈስ ያክፋፋ ይህ ሰው፣ የአፍ አማኝ ነው እንጂ እውነተኛ የልብ አማኝ አይደለም፡፡ ስለሆነም ቀድሞውንም ቢሆን ምድቡ የእሳት ባሕር ፍርድ ከሚጠብቃቸው ከተቃዋሚዎች ጋር ነው እንጂ ከእግዚአብሔር ልጆች ጋር አይደለም፡፡
አስተውል፡- በመሆኑም እውነተኛ አማኝ እና የአፍ አማኝ የሚለዩበት ዋነኛ ምልክት ይህ ነው። የአፍ አማኝ ኃጢአት የሚያደርገው ወዶ፣ ፈቅዶ፣ ዐቅዶ እና ደስ እያለው ሲሆን፣ ኃጢአትን ካደረገ በኋላም ምንም እንዳላደረገ ያህል ምንም አይሰማውም። ደጋግሞ በመሥራትም ኃጢአትን ኑሮው ያደርገዋል፤ ኃጢአት ይገዛዋል፤ በሥጋውም ላይ ይነግሥበታል። ስለዚህ ኃጢአትን በኃጢአት ላይ ይጨምራል እንጂ፥ ለይስሙላ ካልሆነ በቀር እውነተኛ ንስሐ መግባትም አይችልም። እውነተኛው አማኝ ግን ምናልባት ኃጢአትን የሚያደርግ ከሆነ፥ የሚያደርገው፥ የሚጠላውን ነገር ሲሆን ካደረገ በኋላም ራሱን ይጸየፋል፣ ሰላሙ ይታወካል፣ ባደረገው ነገር ይጸጸታል፣ እውነተኛ ንስሐም ይገባል። ኃጢአትን ሊያደርግ የሚችለውም በውስጡ ያሉት ሥጋና መንፈስ እርስ በእርሳቸው ፈቃዳቸውን ለማድረግ ሲቀዋወሙ የሥጋ ፈቃድ በሚበረታ ጊዜ ነው (ገላትያ 5፥17)።
አስተውል፡- "ከእርሱም የሰማናት ለእናንተም የምናወራላችሁ መልእክት፦ እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም የምትል ይህች ናት። ከእርሱ ጋር ኅብረት አለን ብንል በጨለማም ብንመላለስ እንዋሻለን እውነትንም አናደርግም" ይላል (1ኛ ዮሐ. 1፡5-6)። ስለሆነም አማኝ በኃጢአት ሆኖ ወደ እግዚአብሔር የሚያደርገው ጸሎትና አምልኮ የተከለከለ ይሆናል እንጂ ተሰሚነት አይኖረውም (መዝ.66፡18፤ ኤር.14፡11-12፤ ማቴ. 5፡23-24፤ 1ጴጥ.3፡7፤ ያዕ.4፡3)፡፡
እግዚአብሔር በእውነት ቃል አስቦ የወለዳቸው ልጆቹ ኃጢአትን ሲያደርጉ በመንፈሱና በቃሉ በሚወቅሳቸው ጊዜ ካልተመለሱ በአባትነት ይቀጣቸዋል፡፡ ይህም ለልጆቹ ካለው ፍቅር የተነሣ የሚያደርገው ነው፡፡ “… ለመቀጣት ታገሡ፤ እግዚአብሔር እንደ ልጆች ያደርግላችኋልና፤ አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው? … ይላል (ዕብ.12:6-11፤ ምሳሌ 3፡12)፡፡ ቅጣቱም በሥጋ እንደሆነ በግልጽ ተነግሯል፤ ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን ኃጢአት ስለሠራውና ከመካከላቸው መወገድ ስላለበት ሰው ሲናገር “መንፈሱ በጌታ በኢየሱስ ቀን ትድን ዘንድ እንደዚህ ያለው ለሥጋው ጥፋት ለሰይጣን እንዲሰጥ ፍርዴ ነው” ብሏል (1ቆሮ.5:5)፡፡ ይህም ዓይነት የቅጣት ፍርድ ጌታ በጽድቅ አሠራሩ በሚወስነው መሠረት በየደረጃው የሚፈጸም ነው፡፡ የጌታን እራት በማይገባ ሁኔታ ይካፈሉ ከነበሩት የቆሮንቶስ አማኞች መካከል የተፈረደባቸውን በተመለከተ የተጻፈው ቃል “ሳይገባው የሚበላና የሚጠጣ የጌታን ሥጋ ስለማይለይ ለራሱ ፍርድ ይበላልና፥ ይጠጣልምና። ስለዚህ በእናንተ ዘንድ የደከሙና የታመሙ ብዙዎች አሉ፤ አያሌዎችም አንቀላፍተዋል።” ይላል (1ቆሮ.11:29-30)
በ2ቆሮ.5:10 “መልካም ቢሆን ወይም ክፉ እንዳደረገ፥ እያንዳንዱ በሥጋው የተሠራውን በብድራት ይቀበል ዘንድ ሁላችን በክርስቶስ በፍርድ ወንበር ፊት ልንገለጥ ይገባናልና” ይላል። በዚህ ቃል ውስጥ እያንዳንዱ አማኝ በሥጋው መልካም ወይም ክፉ ሊያደርግ እንደሚችል የተነገረ ሲሆን፣ በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት፣ ለመልካሙም ሆነ ለክፉ ሥራው የሚገባውን ብድራት (ዋጋ) ይቀበላል፡፡ ለመልካም ሥራው የሚከፈለው ብድራት “መዳን” እንዳልሆነ ግልጽ ነው፤ መዳን በሥራ አይደለምና (ኤፌ.2፡8-9)፤ እንዲሁም ሐዋርያው ጳውሎስ “ሁላችን” በማለት ራሱን ጨምሮ በመናገሩ በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት የሚገለጡት የዳኑ እውነተኛ አማኞች ብቻ መሆናቸውን እናውቃለን፡፡ ያልዳኑትና ወደ እሳት ባሕር የሚጣሉት ለፍርድ የሚቀርቡት በነጩ ዙፋን ፊት እንደሆነ በራእ.20፡11 ላይ ተገልጿል፡፡ ስለዚህ በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት ቀርበው ለክፉ ሥራቸው የሚገባውን ብድራት የሚቀበሉት የዳኑ አማኞች መሆናቸውን ማስተዋል ይገባል፡፡ በክፉው ፈንታ መልካም ሠርተው ቢሆን ኖሮ ለመልካም ሥራቸው የሚገባ ብድራት ይከፈላቸው ነበር፤ ሆኖም ያንን ዋጋ (ሽልማት) ያጣሉ፡፡ የሲኦል ፍርድ ግን አይመከለታቸውም፤ ከዚያ የዳኑ ናቸውና፡፡
የዳነውና የዘላለም ሕይወት ያገኘው አማኝ በእግዚአብሔር መንፈስ እና በእግዚአብሔር ቃል አማካኝነት ተወቅሶ ከኃጢአቱ ንስሐ በሚገባ ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው ኅብረት ይታደሳል። ሆኖም ኅብረቱ ቢታደስም በዳዊት ሕይወት እንደምናውቀው እንደ እግዚአብሔር የጽድቅ ውሳኔ ቅጣቱ ላይቀር ይችላል (2ሳሙ.12፡11-15)። በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት ሲቀርብ የሚያገኘው ብድራትም በእግዚአብሔር ፍጹም ጽድቅ የሚወሰን ይሆናል። በተረፈ የዳነ አማኝ ምናልባት ኃጢአት ከሠራ፣ ንስሐ የሚገባው ልክ ገና እንዳላመንና እንዳልዳነ ሰው ከሲኦልና ከዘላለም ፍርድ ለመዳን ሳይሆን ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን ኅብረት ለማደስና ለማስቀጠል መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።
እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን ወደ ራሱ ለመመለስና ከእርሱ ጋር ኅብረት እንዲያደርጉ ለማድረግ በጸጋው የሰጠው ዕድል ንስሐ ነው፡፡ ንስሐ በሠሩት ኃጢአት መጸጸት፣ ኃጢአትን መናዘዝ እና መተው፣ እንዲሁም ከልብ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነው፡፡ ንስሐ በጌታ በኢየሱስ ለማያምኑም ሆነ ለአማኞች የተሰጠ ወደ እግዚአብሔር የመመለሻ መንገድ ሲሆን ለሁለቱም ዓይነት ሰዎች የተሰጠውን ንስሐ ቀጥሎ እንመለከታለን፡፡
በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ያላመኑ በውጭ ያሉ ሰዎች ከኃጢአት በታች ያሉ መሆናቸው የሚታወቅና በእግዚአብሔር ቃልም የተገለጸ ነው፡፡ “… አይሁድም የግሪክ ሰዎችም ሁሉ ከኃጢአት በታች እንደ ሆኑ አስቀድመን ከሰናቸዋልና፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፦ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል፥በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ ቸርነት የሚያደርግ የለም፥ አንድ ስንኳ የለም” (ሮሜ 3፡9-12)። እንዲሁም “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል” ይላል (ሮሜ.3:23) ። ስለሆነም የማያምኑ ሰዎች በውስጣቸው ኃጢአት አለ፣ እንዲሁም ከዚያ የተነሣ የኃጢአት ሥራዎችን ይፈጽማሉ፤ ከዚህም የሚከፋው ደግሞ ከኃጢአት የሚያድነውን ኢየሱስን አለማመናቸው ከኃጢአት በታች ሆነው እንዲኖሩና በኃጢአታቸው እንዲሞቱ ያደርጋቸዋል (ዮሐ.8፡24፤16፡8-10)። ለማያምኑ ሰዎች “ንስሐ” እና “በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን” ሊነጣጠሉ የማይችሉ ተያያዥ ነገሮች ናቸው (ማር.1፡15፤ የሐ.ሥ.20፡20)፡፡ ጌታን ያላመኑ ሰዎች ወንጌል በሚሰበክላቸው ጊዜ ልባቸው ሲነካ ባለፈው ዘመናቸው በኖሩት የኃጢአት ኑሮ ተጸጸተው ንስሐ ከገቡ በኋላ በኃጢአት ምክንያት ከተፈረደው ፍርድ ለመዳንና የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የተሰበከላቸውን ክርስቶስን ወዲያውኑ ሊያምኑ ይገባል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ኃጢአተኞችን ሁሉ ወደ ንስሐ ሊጠራ መጣ (ማቴ.9፡13)፤ ጥሪውን ተቀብለው ንስሐ የሚገቡ ሰዎች ደግሞ ለመዳንና የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት ጌታ ኢየሱስን ማመን ይኖርባቸዋል (የሐ.ሥ.16፡31)፡፡ በበዓለ ሃምሳ ያመኑ ከአይሁድ የሆኑ ሰዎች “ምን እናድርግ?” ባሉ ጊዜ “ንስሐ ግቡ” ተብለዋል (የሐ.ሥ.2፡42)፤ ከአሕዛብም የሆኑ ሰዎችም ባመኑ ጊዜ “እንኪያስ እግዚአብሔር ለአሕዛብ ደግሞ ለሕይወት የሚሆን ንስሐን ሰጣቸው” ተባለ (የሐ.ሥ.11፡18)፡፡ ስለሆነም የማምኑ ሰዎች የሚገቡት ንስሐ በጌታ በኢየሱስ ከማመን ጋር የተያያዘ ንስሐ ነው፡፡
ቀደም ሲል በተከታታይ እንደተመለከትነው ለዘላለም የዳኑ አማኞች በዚህ ምድር ላይ በሥጋ እንዲኖሩ በቀረላቸው ዘመን ውስጥ ከሥጋ የተነሣ ተሰናክለው ሳይፈልጉ በኃጢአት ሊወድቁ ይችላሉ (ሮሜ 7፡19-20)፡፡ “ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም” ይላል (1ዮሐ.1፡8)፡፡ እነዚህ አማኞች የዘላለምን ሕይወት ያገኙት በጌታ በኢየሱስ እንጂ በራሳቸው ባለመሆኑ ያገኙትን ሕይወት ባያጡትም፣ በኃጢአታቸው እግዚአብሔርን ያሳዝናሉ (ኤፌ.4፡30)፤ ኃጢአትን እያደረጉ ከእርሱ ጋር ኅብረት ሊኖራቸው አይችልም (1ዮሐ.1፡6)፤ እንደ እርሱ የጽድቅ ውሳኔም በአባት ፍቅር ይቀጣሉ (ዕብ.12፡5-11)፡፡
ታዲያ በኃጢአት ምክንያት እግዚአብሔርን ያሳዘኑ አማኞች ወደ እርሱ ተመልሰው ኅብረታቸውን የሚያድሱበት መንገድ ንስሐ ነው፤ “በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው” ይላል (1ዮሐ.1:9)። ስለሆነም ንስሐ የሚተገበርበት መንገድ ኃጢአትን በመናዘዝ ነው፤ “መናዘዝ” በራስ ላይ እየፈረዱ ኃጢአትን በግልጽ ለእግዚአብሔር በጸሎት መናገር ነው፡፡ “ኃጢአቴን ለአንተ አስታወቅሁ፥ በደሌንም አልሸፈንሁም፤ ለእግዚአብሔር መተላለፌን እነግራለሁ አልሁ፤ አንተም የልቤን ኃጢአት ተውህልኝ” እንዳለ (መዝ.32:5)።
ሕያውና የሚሠራ በሆነው የእግዚአብሔር ቃል ተመርምሮና ተወቅሶ (ዕብ.4፡12)፣ በኃጢአት መውደቁን የተቀበለ አማኝ ከእግዚአብሔር አባቱ ጋር የነበረውን ኅብረት ለማደስ፣ በተሰበረ ልብና በእፍረት ሆኖ ወደ ጌታ በመመለስ ኃጢአቱን እየተናዘዘ ንስሐ መግባት ይኖርበታል፡፡ “እንግዲህ ከወዴት እንደ ወደቅህ አስብ ንስሐም ግባ፤ የቀደመውንም ሥራህን አድርግ፤ አለዚያ እመጣብሃለሁ ንስሐም ባትገባ መቅረዝህን ከስፍራው እወስዳለሁ” የሚለው ጥሪ ዛሬም በኃጢአት ለወደቀው አማኝ የቀረበ የንስሐ ጥሪ ነው! (ራእ.2፡5)። ይህ ምናልባት ተሰናክሎ በኃጢአት የወደቀ እውነተኛ አማኝ የሚገባው ንስሐ ሲሆን የአፍ አማኝን ግን ለንስሐ ማደስ አይቻልም (ዕብ.6፡6)፡፡ እንዲህ ያለው ሰው ንስሐ ሊገባ ስለማይችል “ንስሐ ቢገባስ?” ተብሎ የሚል ጠያቄ ሊነሳለት አይችልም፡፡
“ጠበቃ” የሚለው ቃል በአንዳች ጥፋት ተከሶ ፍርድ ቤት በቀረበ ሰው ጎን በመቆም ክርክር የሚያደርግ ሰው ነው፡፡ ስለሆነም “ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን” የሚለው ቃል በፍርድ ቤታዊ አሠራር ምሳሌነት የቀረበ ትምህርት ሲሆን አማኝ ድንገት ኃጢአትን ቢያደርግ የኢየሱስ ጠበቃነት ዋስትና እንደሚሆነው የተሰጠ ማረጋገጫ ነው፡፡ አማኝ ኃጢአትን ማድረግ የሚችል ማንነት ቢኖረውም ኃጢአትን እንዲያደርግ አልተፈቀደለትም፤ ሆኖም ግን አማኝ ከዚህ መርህ ወድቆ ኃጢአትን ሊያደርግ እንደሚችል ታሳቢ በማድረግ እግዚአብሔር በአባታዊ ፍቅሩ ከእርሱ ዘንድ የሆነ ጠበቃን ሰጥቶታል፡፡ ይህም አማኙ በኃጢአት በሚወድቅ ጊዜ ከሳሽ እንዳለበት የሚያሳይ ነው (ራእ.12፡10)፡፡ ከአብ ዘንድ የሆነው ጠበቃ ግን አማኙ ስለተከሰሰበት ኃጢአት አስቀድሞ ሞቷል፤ በዚህም የከሳሹን ክስ ውድቅ ያደርገዋል፡፡
አማኙ የሠራው ኃጢአት የሞት ፍርድ የሚገባው ቢሆንም ያንን ሞት ጠበቃው ስለሞተለት ቀደም ሲል ባመነ ጊዜ ያገኘው የዘላለም ሕይወት የተጠበቀ ይሆንለታል፡፡ ነገር ግን ከአብ ዘንድ የሆነው ጠበቃ ምንም እንኳን የአማኙን የዘላለም ሕይወት ዋስትና ቢያስጠብቅለትም፣ አማኙ አሁን ለሠራው ኃጢአት የሚገባውን የአባት ቅጣት እንዲቀጣ፣ ከዚያም ንስሐ ገብቶ ኃጢአቱን በመናዘዝ ወደ አባት እንዲመለስ ያደርገዋል፡፡ ይህንንም የሚያደርገው እርሱ “ጠበቃ” ብቻ ሳይሆን “ጻድቅም” ስለሆነ ነው፡፡ “ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን” ብሎ ጠበቃነቱን ከተናገረ በኋላ “እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” ብሎ ጻድቅነቱን የተናገረው ለዚያ ነው (1ዮሐ.2፡1)፡፡ አማኙ ለሠራው ኃጢአት የእርሱ ሞት እንዲቆጠርለት፣ አማኙ በሥጋው እንዲቀጣ፣ እንዲሁም በኃጢአቱ ፈርዶ ንስሐ እንዲገባ የሚያደርገው ጻድቅ ስለሆነ ነውና፡፡