2. ሰማያዊውን ስጦታ የቀመሱ
የዕብራውያን አማኞች ከማመናቸው በፊት የሚያውቁት የምድር የሆነ ስጦታን ነው፡፡ ምድራዊ ተስፋ፣ ምድራዊ በረከትና ምድራዊ ርስት የተሰጣቸው ነበሩ፤ በክርስትና ግን ከሰማያዊ ጥሪ ተካፋዮች ተደርገዋል (ዕብ.3፡1)፡፡ እናም ከሰማይ የወረደ የሕይወት እንጀራ (ክርስቶስ)፣ ከሰማይ የፈሰሰ የሕይወት ውኃ (መንፈስ ቅዱስ) እና አብሮ የመጣ መንፈሳዊ በረከት ተሰጥቷቸዋል። ታዲያ በመካከላቸው የተደባለቁ እነዚያ የአፍ አማኞች ለእውነተኞቹ የተሰጠውን ሰማያዊ ስጦታ ቀምሰው ነበር፤ መቅመስም ለማረጋገጥ ያህል መፈተን ነው እንጂ ወዶና ተቀብሎ መብላትና የራስ ማድረግ አይደለም፡፡ ቀመሱት ማለት ስጦታው ለእነርሱ መጥቷል፣ እነርሱም ተቀበሉት ማለት አይደለም፡፡ ከእስራኤል ጋር የነበሩ ድብልቅ ሕዝብ በምድረ በዳ ለእስራኤል የተሰጠውን በረከት (ከሰማይ የወረደውን መና እና ከዓለት የፈለቀውን ውኃ) አብረው ተካፈሉ ማለት (ዘጸ.12፡38፤ ዘኁል.11፡3-8)፣ እነርሱም የእግዚአብሔር ሕዝብ ነበሩ ማለት እንዳልሆነ ሁሉ እነዚህም ከመጀመሪያው የጌታ አልነበሩም፡፡
ከመንፈስቅዱስ ተካፋዮች የነበሩ ማለት “መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ” ወይም “በመንፈስ ቅዱስ የታተሙ” ማለት አይደለም፡፡ ቃሉ "መንፈስ ቅዱስን ተካፋዮች ሆነው የነበሩ" ሳይሆን "ከመንፈስ ቅዱስ ተካፋዮች የነበሩ" እንደሚል ማስተዋል ይገባል። ይህም ከመንፈስ ቅዱስ የሆነ ሥራን ከእውነተኞቹ ጋር ተደባልቀው ያዩ፣ የሰሙ፣ አፍኣዊ በሆነ መልኩ በጊዜያዊነት አብረው የተደሰቱ፣ ያመሰገኑ፣ አሜን ያሉ፣ የዘመሩ … ማለት ነው፡፡ ሌሎች አማኞች ባያውቋቸውም ጌታ ያውቃቸዋል፤ በጉባኤው ዘንድ ካለው ከመንፈስ ቅዱስ መገኘትና ሥራዎች ቢካፈሉም እነርሱ ግን በግላቸው “መንፈስ የሌላቸው” ሰዎች ናቸው (ይሁ.1፡19)፡፡ የሰማርያው ጠንቋይ ሲሞን ያመነ መስሎ ተጠምቆ ከአማኞች ጋር ተደባልቆ በሐዋርያት እጅ መጫን መንፈስ ቅዱስ ስንዲሰጥ አይቶ ነበር፤ ሆኖም እርሱም እንደነጴጥሮስ ይህን የእግዚአብሔርን ስጦታ በገንዘብ ለማግኘት በሞከረ ጊዜ ማንነቱ ተገለጠ፤ ልቡ በእግዚአብሔር ፊት የቀና አልነበረም፤ ገና በመራራ መርዝና በዓመፅ እስራት ውስጥ ነበር፤ ስለሆነም “ከዚህ ነገር ዕድል ወይም ፈንታ የለህም” ተባለ (የሐ.ሥ.9-24)። በመሆኑም ይህ የአፍ አማኞች እንደ ሲሞን ከእውነተኛ አማኞች ጋር ተደባልቀው በቅዱሳን መካከል የሚደረግ የመንፈስ ቅዱስ መግቦትን ቢካፈሉም የዘላለም ሕይወት ያገኙ አማኞች ናቸው ማለት አይደለም። አንድ ቀንም ነበርንበት፣ አይተንዋል፣ ተካፍልነዋል ሲሉት የነበሩትን ነገር ይክዱታል፡፡
እነዚህ ሰዎች ከስንዴ ጋር ተመሳስሎና ተደባልቆ እንደሚኖር እንክርዳድ ከእውነተኛ አማኞች ጋር ተደባልቀው አብረው የሚኖሩ ስለሆኑ (ማቴ.13፡24-43)፣ መልካሙ የእግዚአብሔር ቃል ሲነበብና ሲሰበክ እነርሱም ይሰማሉ፤ ይሁን እንጂ በጭንጫ ላይ እንደተዘራው ዘር ቃሉ ለጊዜው የበቀለ ቢመስልም ፀሐይ በወጣ ጊዜ (መከራ በመጣ ጊዜ) ይጠወልጋል (ማቴ.13፡5-6)፤ የሰሙት ቃል ጋር ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስለማይዋሐዳቸው አይጠቅማቸውም (ዕብ.4፡2)፤ ከመነሻውም ዳግም ያልተወለዱ ናቸው፡፡ ይህን እያስመሰሉ ሲሰሙትና ሲያደንቁት የነበረውን ቃል አንድ ቀን በይፋ ይክዱታል፡፡
“ሊመጣ ያለው የዓለም ኃይል” የተባለው ጌታ በሚመጣው ዓለም የሚገልጠው ልዩ ልዩ ተአምራዊ ኃይል ነው፡፡ ጌታ ሐዋርያትን ሁለት ሁለት እያደረገ በላከ ጊዜ አጋንንትን የሚያወጣ፣ ለምጻምን የሚያነጻ፣ ሙታንን የሚያነሣ ኃይል ተገልጦባቸው ነበር (ማቴ.10፡8)፤ ከእነርሱም መካከል አንዱ ይሁዳ እንደነበር ማስታወስ ያስፈልጋል፤ ይህን ተልእኮ ጌታ ሲሰጣቸው “እውነት እላችኋለሁና፥ የሰው ልጅ እስኪመጣ ድረስ የእስራኤልን ከተማዎች አትዘልቁም” ብሏቸዋል (ማቴ.10፡23)። ታዲያ በጌታ ዘመንም ሆነ እርሱ ካረገ በኋላ የተገለጠው ኃይል ወደፊት ሊመጣ ባለው ዓለም የሚገለጥም ኃይል እንደሆነ ከዚህ እንረዳለን፡፡ ነገር ግን በእውነተኛ አማኞች መካከል እንደ ይሁዳ ተደባልቀው እንዲህ ያለውን ኃይል ሊቀምሱ የሚችሉ የአፍ አማኞች ይኖራሉ፤ ማለትም ሲደረግ ያያሉ፣ ሌሎች ሲያደንቁ ያደንቃሉ፣ ሲደሰቱ ይደሰታሉ፣ ሲያመሰግኑ ያመሰግናሉ፤ ሁሉም ግን አፍኣዊ ነው፡፡ እነርሱም “ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፥ በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን?“ የሚሉ እና ጌታ ግን “ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ” ብሎ የሚመሰክርባቸው ሰዎች ናቸው (ማቴ.7:23)። ስለዚህ እነዚህ በኋላ የሚክዱ ሰዎች አምነናል ብለው ከአማኞች ጋር በመቀላቀል እዚህ ምድር ላይ በእነዚህ ነገሮች ቢሳተፉም ጌታ ግን ልባቸውን ስለሚያውቅ የማይተማመንባቸው ሰዎች ናቸው፤ በዚሁ በዕብ.6፡7- 8 ላይ በምሳሌ እንደተገለጸው “የሚጠቅሙ አትክልቶች" እንዲበቅሉ የወረደውን ዝናብ ተጠቅመው "እሾክና ኩርንችት" በዚያ መሬት ላይ ቢበቅሉ እሾኩና ኩርንችትሱ የሚጠቅሙ አትክልት ነበሩ ማለት እንዳልሆነ ሁሉ፥ ከልብ አማኞች ጋር የተደባለቁ የአፍ አማኞች መንፈሳዊ ነገሮችን መካፈል ስለቻሉ ብቻ ዳኑና የዘላለም ሕይወት ያገኙ እውነተኛ አማኞች ነበሩ ማለት አይደለም፤ ከመጀመሪያውም እሾክና ኩርንችት ናቸው፤ “መጨረሻቸውም መረገም እና መቃጠል ነው” ተብሎ ተነግሮናል (ዕብ.6፥8)።
የአፍ አማኞች በኋላ ላይ የካዱ ሲባሉ በፊት ከልብ ያመኑት ነገር የነበራቸው ሆነው አይደለም። ነገር ግን የሚክዱት እውነተኞቹ ከልብ የሚያምኑትን፣ እነርሱ ግን በአፋቸው አምነናል የሚሉትን አፍኣዊ እምነት ነው፡፡ ይሁዳ ከጌታ ሐዋርያት ጋር አብሮ በነበረ ጊዜ ያመነ ወይም ደቀመዝሙር የሆነ ቢመስልም እንኳ ጌታ ግን ከማያምኑት አንዱ እንደነበር ተናግሯል (ዮሐ.6፡64)፤ እንዲያውም "ከእናንተ አንዱ ዲያብሎስ ነው" ብሎ የገለጸው ሰው ነበር (ዮሐ.6፡70-71)፤ ይሁንና ይህ ሰው በእነርሱ መካከል የነበረውን መንፈስ፣ የሚነገረውን መልካሙን የእግዚአብሔር ቃል፣ ሲደረጉ የነበሩ የኃይል ሥራዎች አብሮ ሲካፈልና ሲሳተፍ ነበር፤ ይህ ማለት ግን እውነተኛ አማኝ ነበረ ማለት አልነበረም፡፡
እነዚህ የአፍ አማኞች በኋላ ላይ የሚክዱት እንደ ጴጥሮስ በሰው ፊት (ማቴ.26፡70) ሳይሆን፣ እንደ ይሁዳ በእግዚአብሔርም በሰውም ፊት ነው፡፡ ጴጥሮስ መከራውን መጋፈጥ ስላቃተው በሎሌዎቹ ፊት ቢክድም ለንስሐ ስፍራ አግኝቷል፡፡ ይሁዳ ግን የብስጭት ጸጸት ተጸጸተ እንጂ ንስሐ መግባት ስላልቻለ ታንቆ ሞተ (ማቴ.27፡3-5)፤ በኋላ የካዱትን እንደገና ለንስሐ ማደስ አይቻልም ማለትም እንደዚህ ነው፡፡