በክርስቶስ ኢየሱስ ያመኑ ሁሉ በዳግመኛ ልደት ከእግዚአብሔር የተወለዱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆናሉ (ዮሐ.1፡12-13፤ 3፡3፣5)። ዳግመኛ የሚወለዱትም "ከማይጠፋ ዘር" መሆኑ በግልጽ ተነግሮናል (1ጴጥ.1፡23)። ስለሆነም በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው ዳግምኛ የተወለዱ ሁሉ ለዘላለም አይጠፉም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለዘላለም ሕይወት ባስተማረ ጊዜ ሁሉ ስለ አለመጥፋትም አስተምሯል። እስኪ ሁለቱን እንመልከት።
1) "ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል። በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና" (ዮሐንስ 3፡14-16)። ከዚህም ቃል ጌታ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሞተው በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኝ ብቻ ሳይሆን እንዳይጠፋም መሆኑን እንማራለን።
2) በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል፤ እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፥ ለዘላለምም አይጠፉም፥ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም። የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፥ ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም። እኔና አብ አንድ ነን (ዮሐንስ 10፡27-30)። በዚህም ትምህርቱ ጌታችን "በጎቼ" ላላቸው አማኞች "የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ" ካለ በኋላ "ለዘላለምም አይጠፉም" በማለት አስረግጦ ተናግሯል። በዚህ ቃል ውስጥ እጅጉን ደስ የሚለው እኛ የተያዝነው በወልድና በአብ እጅ ሲሆን ከዚያ እጅ ማንም ሊነጥቀን የማይችል መሆኑ ነው። ከዚህም በላይ "እኔና አብ አንድ ነን" የተባለው ወልድና አብ እኛን በአንዲት መለኮታዊ እጅ በመያዛቸው መሆኑ ደስታችንን ወደ አምልኮ ይመራዋል። ታዲያ በወልድና በአብ እጅ ተይዞ እንዴት መጥፋት ይኖራል? ይልቁን "ለዘላለም አይጠፉም" የሚለው ቃል የማይናውጥ ዋስትናችን ሆኖ ይኖራል።
ስለዘላለም ሕይወትና ስለ አለመጥፋት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተማርነው ይህ ትምህርት የወንጌል ዋነኛው ይዘት ነው። "ወንጌል" ማለት "የምሥራች" ማለት እንደመሆኑ መጠን በክርስቶስ ለሚያምኑ ሁሉ የዘላለምን ሕይወትን፣ "የምሥራች" ብሎ ይናገራል። ሆኖም ለዚህ የዘላለም ሕይወት የምሥራች ዋስትና ለመስጠት የአለመጥፋት የምሥራችንም አብሮ ይናገራል። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ሲናገር “እርሱ ሞትን ሽሮአልና እኔ ሰባኪና ሐዋርያ አሕዛብንም አስተማሪ እንድሆን በተሾምሁበት በወንጌል ሕይወትንና አለመጥፋትን ወደ ብርሃን አውጥቶአል” ብሏል (2ኛ ጢሞ. 1፥10-11)። ስለዚህ በወንጌል ሊሰበክ የሚገባው ስለ ሕይወት ብቻ ሳይሆን ስለ አለመጥፋትም ሊሆን ይገባል።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ 15 ውስጥ ከደቀመዛሙርቱ ጋር ያለውን ግንኙነት በወይን ግንድና በቅርንጫፎቹ ምሳሌነት አስተምሯል፡፡ በብሉይ ኪዳን ወይን የእስራኤል ምሳሌ እንደነበር ይታወቃል (መዝ.80፡8፤ ኢሳ.5፡1-8፤ ኤር.2፡21፤ ሆሴ.10፡1)፤ ሆኖም እስራኤል ፍሬ ያልተገኘባት ወይን ብቻ ሳይሆን ሆምጣጤ ያፈራች በመሆንዋ ወደጎን ተትታለች፡፡ በምትኩም እግዚአብሔር ክርስቶስን እውነተኛ የወይን ግንድ ደቀመዛሙርቱንም ቅርንጫፎች አደረገ፡፡ ጌታ ይህን ሲገልጽ “እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ ገበሬውም አባቴ ነው … እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ።” በማለት ገልጿል (ቁ.1ና5)።
በዮሐ.15 ውስጥ በክርስቶስ የወይን ግንድነት ላይ ያሉ ሁለት ዓይነት ቅርንጫፎች እንዳሉ ተነግሮናል፤ 1ኛው በቁ.2 ላይ “በእኔ ያለው” የተባለው ቅርንጫፍ ሲሆን፤ 2ኛው ደግሞ በቁ.6 ላይ “በእኔ የማይኖር” የተባለው ቅርንጫፍ ነው፤ በእነዚህ ሁለት ዓይነት ቅርንጫፎች ላይ የሚፈጸሙትን ሁለት ዓይነት ፍርዶች፣ በዮሐ.10፡28-29 ላይ ጌታ ኢየሱስ በጎቼ ያላቸውን በተመለከተ “ለዘላለም አይጠፉም” ብሎ የሰጠውን ግልጽ ዋስትና ሳንዘነጋ መመልከት ይኖርብናል፡፡ እስኪ ሁለቱንም እንመልከታቸው፡፡
1) የመጀመሪያዎቹ ቅርንጫፍ ዓይነቶች ጌታ ኢየሱስ “በእኔ ያለው” ብሎ የገለጻቸው ቅርንጫፎች ሲሆኑ እነሱም ራሱ ሁለት ዓይነት ናቸው፤ እነርሱም “ፍሬ የማያፈራ” እና “አብዝቶ ያላፈራ” ናቸው፤ ፍሬ የማያፈራውን በተመለከተ ጌታ ሲናገር “ፍሬ የማያፈራውን በእኔ ያለውን ቅርንጫፍ ሁሉ ያስወግደዋል” ብሏል፡፡ “ያስወግደዋል” አለ እንጂ እንደ ቁ.6ቱ “ወደ ውጭ ይጣላል፣ ይደርቅማል፤ … ወደ እሳት ይጥሉአቸዋል፥ ያቃጥሉአቸውማል” አላለም። በመሆኑም በዚህ ስፍራ ላይ “ያስወግደዋል” ማለት በወይን ግንዱ ላይ ካሉ(ከሚኖሩ) ቅርንጫፎች መካከል ይለየዋል ማለት ነው፤ ይህም የወይኑ ገበሬ እግዚአብሔር አባት፣ በክርስቶስ ያለ ሆኖ ሳለ መልካም ፍሬ ያላፈራውን አማኝ፣ በአስተዳደራዊ ቅጣቱ ከሌሎቹ ፍሬ ከሚያፈሩት አማኞች መካከል ይለየዋል ማለት ነው። በሐናንያና በሰጲራ እንዲሁም በአያሌ የቆሮንቶስ አማኞች ላይ እንዳደረገው (የሐ.ሥ.5፡1-11፤ 1ቆሮ.11፡30) እስከ ሥጋዊ ሞት በሚደርስ የቅጣት እርምጃ ይለየዋል ማለት ነው። ምክንያቱም ይህ ቅርንጫፍ “በእኔ ያለው” ስለተባለ በቅጣት ፍርድ ይወገዳል እንጂ ለዘላለም አይጠፋምና፤ መሆኑም “በእሳት የመቃጠል” ፍርድ (የገሃነም እሳት ፍርድ) አይመለከተውም፡፡
“በእኔ ያለው” ከተባሉት ሁለተኛው ዓይነት ቅርንጫፍ ደግሞ ፍሬ ቢያፈራም “አብዝቶ ያላፈራ” ወይም “ብዙ ፍሬ የሌለው” ነው፡፡ ስለዚህኛው ቅርንጫፍ ጌታ ሲናገር “ፍሬ የሚያፈራውንም ሁሉ አብዝቶ እንዲያፈራ ያጠራዋል” ብሏል። “ያጠራዋል” ሲል በአማኙ ሕይወት ውስጥ ያሉ ፍሬውን የቀነሱ አንዳንድ ነገሮችን እግዚአብሔር በራሱ አሠራር በማጽዳት ለበለጠ መንፈሳዊ ፍሬ ያበቃዋል ማለት ነው፡፡ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ትምህርቱን እየሰሙ ያሉትና "እናንተ" እያለ የሚጠራቸው ደቀመዛሙርቱ ይሁዳ የሌለባቸው 11ዱ ደቀመዛሙርት መሆናቸውን እናውቃለን፡፡ እነርሱን በተመለከተ “እናንተ ስለ ነገርኋችሁ ቃል አሁን ንጹሐን ናችሁ” ይላቸዋል (ቁ.3)፡፡ እነርሱና እንደ እነርሱ ያሉ በክርስቶስ ላይ የሚኖሩ ማለትም ከእርሱ ጋር ሕያው ግንኙነት ያላቸው አማኞች ምንም እንኳን ከሰሙት የእግዚአብሔር ቃል የተነሣ ንጹሐን ቢሆኑም አብዝተው እንዲያፈሩ ሊያጠራቸው ተገብቶታል፡፡
2) ሁለተኛዎቹ የቅርንጫፍ ዓይነቶች ጌታ ኢየሱስ “በእኔ የማይኖር” ያለው ዓይነት ናቸው፤ ይህን ቅርንጫፍ በተመለከተ ጌታ ሲናገር “በእኔ የማይኖር ቢሆን እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል ይደርቅማል፤ እነርሱንም ሰብስበው ወደ እሳት ይጥሉአቸዋል፥ ያቃጥሉአቸውማል።” ብሏል (ቁ.6)። ይህ ዓይነቱ ቅርንጫፍ ጨርሶውኑ ከእርሱ ጋር ምንም ዓይነት ሕያው ግንኙነት የሌለው ነው፤ “በእኔ የማይኖር” መባሉ ይህን ያሳያል፤ ከዚህ ዓይነት ቅርንጫፍ ቀድሞውኑ ምንም ፍሬ ስለማይጠበቅ ከዚህ ቅርንጫፍ ጋር ተያይዞ ፍሬ ስለማፍራት አልተነሣም፡፡ ይልቁን በክርስቶስ የማይኖር በመሆኑ እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ እንደሚጣልና በእሳት እንደሚቃጠል ይናገራል፡፡ ይህም የእሳት ባሕር ፍርድ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ሰው በቅርንጫፎች (የክርስቶስ በሆኑ አማኞች) መካከል ያለ ይምሰል እንጂ፣ እርሱም በአፉ “የክርስቶስ ከሆኑት መካከል ነኝ” ይበል እንጂ፣ ከክርስቶስ ጋር ሕያው ግንኙነት ስለሌለው እውነተኛ አማኝ ሳይሆን የአፍ አማኝ ነው፡፡ እንደ ይሁዳ በጌታ ደቀመዛሙርት መካከል የነበረ ቢሆንም ከመነሻው ጀምሮ ከጌታ ጋር ሕያውና እውነተኛ ግንኙነት ያልነበረው ነው።
እንዲህ ያሉ የአፍ አማኞችን በተመለከተ “ከእኛ ዘንድ ወጡ፥ ዳሩ ግን ከእኛ ወገን አልነበሩም፤ ከእኛ ወገንስ ቢሆኑ ከእኛ ጋር ጸንተው በኖሩ ነበር፤ ነገር ግን ሁሉ ከእኛ ወገን እንዳልሆኑ ይገለጡ ዘንድ ወጡ” ተብሎ ተጽፏል። (1ዮሐ.2፥19)። ስለዚህ ከእኛ ዘንድ ቢወጡም ቀድሞውንም ከእኛ ወገን አልነበሩም፤ ማለትም አማኝ መስለው በመካከላችን ቢኖሩም ቀድሞውንም እውነተኛ አማኝ አልነበሩም፥ ቀድሞውንም አልዳኑም ነበር። በክርስቶስ (በግንዱ) የማይኖሩ ቅርንጫፎች ናቸው። ስለሆነም እንዲህ ያለው ሰው ፍሬ ማፍራት አለማፍራቱ ታይቶ ሳይሆን በክርስቶስ የማይኖር ከመሆኑ የተነሣ ወደ እሳት ፍርድ ይጣላል፡፡ በእውነት አምኖ የዳነና በክርስቶስ የሚኖር (በጎቼ ካላቸው መካከል የሆነ) ሰው ግን “ለዘላለም አይጠፋም” (ዮሐ.10፡30)፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን ይህንንና ሌሎቹንም ከዚህ በፊት ያየናቸውን "ስለዘላለም ሕይወት" እና "ለዘላለም ስለአለመጥፋት" የሚናገሩ የራሱ የጌታ ቃላትን ሳንዘነጋ እናንብብ፡፡ ክብር ይግባውና ጌታ ከራሱ ጋር ሊቃረን አይችልም፡፡ ዛሬም ዘወትርም እስከ ዘላለም ክብር ይግባው!!
በሰው ዘንድ አማኝ እንዲመስሉ ያደረጓቸው ነገሮችም በዕብ 6 ከቁ.4-5 በዝርዝር የተነገሩ ሲሆን እነርሱንም ቀጥሎ እንመለከታለን፡፡