ቤተክርስቲያን/Aclesia  
የልብ አማኞች እና የአፍ አማኞች

ሰው መዳንንም ሆነ የዘላለም ሕይወትን የሚያገኘው ክርስቶስን በማመን መሆኑ በወንጌል የተመሰከረ እውነት ነው። "ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ። ያመነ የተጠመቀም ይድናል፥ ያላመነ ግን ይፈረድበታል" ይላል (ማር.16፡15-16)። ሆኖም ወንጌል ተሰብኮላቸው ክርስቶስን አምነናል ካሉ ሰዎች መካከል ከልብ በእውነት ክርስቶስን ያመኑ የልብ አማኞች ያሉትን ያህል፣ በአፍ ብቻ በግብዝነት አምናለሁ የሚሉ የአፍ አማኞችም አሉ።

ሰው የዘላለም መዳንንም ሆነ የዘላለም ሕይወትን የሚያገኘው ከልብ በሆነ እውነትኛ እምነት እንጂ የአፍ ብቻ በሆነ እምነት አይደለም። "ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና” ይላል (ሮሜ 10፡9-10)። ይህ የልብ እምነት "ግብዝነት የሌለበት እምነት" ተብሏል (1ጢሞ.1፥5)። እንዲህ ያለው ግብዝነት የሌለበት እምነት በጢሞቴዎስ፣ በእናቱና በአያቱ እንደነበረ ተገልጿል (2ጢሞ.1፥5)። በእውነተኛ አማኞች ዘንድ ሁሉ ያለው እምነት ይህ እምነት ነው። ለመዳንም ሆነ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የሚያስችለውም እምነት፣ ምንም ዓይነት ማስመሰል ወይም ግብዝነት የሌለበት ይህ እውነተኛ እምነት ነው።

በእውነት ከልባቸው ክርስቶስን ያመኑ ሰዎች የእምነታችው እውነተኝነት በሰው ፊት ተገልጦ የሚታይባቸው ወይም የሚረጋገጥባቸው መንገዶች አሉ። ክርስቶስን አምኖ በውኃ መጠመቅ እና ያመኑትን በአፍ መመስከር የልብ እምነት መገለጫዎች መሆናቸው ከላይ በጠቀስናቸው ንባቦች ውስጥ ተመላክቷል። እንዲሁም "መልካም ሥራ" የእውነተኛ እምነት ማሳያ መሆኑ በያዕቆብ መልእክት በስፋት ተነግሯል (ያዕ.2፡18)። ያዕቆብ የአብርሃም እምነት በሥራ የተረጋገጠ እውነተኛ እምነት መሆኑን በገለጸ ጊዜ "እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ያደርግ እንደ ነበረ፥ በሥራም እምነት እንደ ተፈጸመ ትመለከታለህን?" ብሏል (ያዕ.2፡22-23)። ስለዚህ ያለን እምነት እውነተኛነት ከመልካም ሥራ ጋር የሚታይና መልካም ሥራ የማይለየው በመሆኑ ይታወቃል። እንዲህ ያለ እውነተኛ እምነት ያላቸው ለዘላለም የዳኑና የዘላለም ሕይወት ያላቸው ናቸው።

በሌላ በኩል የአፍ አማኞችን በተመለከተ ክርስቶስ ሲናገር “ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፥ ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው” ብሏል (ማቴ.15፥8)። እንዲሁም “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ “ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም” በማለት አስተምሯል (ማቴ. 7፥21)። እንዲሁም እነዚህ "ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ" እያሉ በከንፈር ብቻ የሚያከብሩ የአፍ አማኞች ከእውነተኛ አማኞች ጋር ሊቀላቀሉ እንደሚችሉ ጌታ ሲያስተምር "በስንዴ መካከል በበቀለ እንክርዳድ" (ማቴ.13፡24-30፣36-43)፣ "ከመልካም ዓሣዎች ጋር በተጠመዱ ክፉ ዓሣዎች" (ማቴ.13፡47-50)፣ "ከልባም ቆነጃጅት ጋር አብረው በነበሩ በመብራታቸው ውስጥ ግን ዘይት ባልያዙ ቆነጃጅት" (ማቴ.25፡1-12) ምሳሌነት ገልጿቸዋል። እነዚህን የአፍ አማኞች "አላወቅኋችሁም" እንደሚላቸው በመግለጽ ቀድሞውኑ ያልዳኑ መሆናቸውን፣ መጨረሻቸውም ፍርድ እንደሆነ ተናግሯል (ማቴ.13፡30፤ 40-42)። ስለዚህ የአፍ አማኞች የሚፈረድባቸው መጀመሪያም ስላልዳኑና የዘላለም ሕይወትን ስላላገኙ ነው እንጂ ከዳኑ በኋላ መዳናቸውና ያገኙት ሕይወት ስለሚወሰድ አይደለም።

ታዲያ በክርስቶስ አምነናል የሚሉ ሰዎች እምነታቸው "የልብ" መሆንኑን፥ ወይም "የአፍ ብቻ" መሆኑን፥ በትክክል የሚያውቀው ልብን የሚያውቅ ጌታ ብቻ ነው። ምልክት አይተው "አመኑ" የተባሉ ሰዎችን በተመለከተ የተጻፈው ቃል “ነገር ግን ኢየሱስ ሰዎችን ሁሉ ያውቅ ነበር፤ ስለ ሰውም ማንም ሊመሰክር አያስፈልገውም ነበርና አይተማመናቸውም ነበር ፤ ራሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና” ይላል (ዮሐ. 2፥24-25)። በዮሐ.8 ውስጥ "ያመኑት አይሁድ" ተብለው የተጠሩትን (ቁ.31)፣ ነገር ግን በቃሉ የማይኖሩትን አይሁድ ጌታ "የኃጢአት ባሪያዎች" (ቁ.34)፣ "የዲያብሎስ ልጆች" (ቁ.44) ብሎ ገልጿቸዋል። እነዚህ ሰዎች "አመኑ" የተባለው ጌታ በሚያደርገውና በሚናገረው ነገር አሳማኝነት ምክንያት ምርጫ ስለሌላቸው የግድ ሆኖባቸው በማመናቸው ነው እንጂ ከልብ ተቀብለው ስላመኑ አልነበረም። ከልብ አለማመናቸውንም "የሁሉን ልብ የሚያውቅ ጌታ" (የሐ.ሥ.1፡24፤ ዮሐ.21፡17) ያውቀዋል።

እንዲህ ያሉ የአፍ አማኞች በሰዎች ዘንድ የሚታወቁት ከፍሬያቸው መሆኑ ተገልጿል (ማቴ.7፡16)። አማኞች ነን ብለው ፍሬያቸው ክፉ ከሆነ እምነታቸው አፍኣዊ ነው። ይህም “ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው” (ያዕ.2፥26) ተብሎ የተገለጸው የሞተ እምነት ነው።

እነዚህ የአፍ አማኞች "በጭንጫ ላይ የተዘራው ዘር" ፀሐይ በወጣ ጊዜ እንደሚጠወልግ በቃሉ ምክንያት መከራና ስደት በሚመጣ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላሉ (ማቴ.13፡20-21)። ከእኛ ጋር ተደባልቀው ቢቆዩም “ከእኛ ወገን እንዳልነበሩ ይገለጥ ዘንድ” ከእኛ ተለይተው ይወጣሉ (1ዮሐ.2፡19)። ስለዚህ ሰዎች በውጫዊ መልኩ በአፍ ብቻ አማኝ መስለው እየታዩ በተግባር ግን የማያምኑ ሰዎችን ኑሮ የሚኖሩ ከሆነ ጌታን አምነዋል ማለት አይቻልም።

የአፍ አማኞች "የእውቀትና የእውነት መልክ" ያላቸው፣ ነገር ግን በተግባር "በሥራቸው የካዱ" ናቸው (ሮሜ.2፡19-24፤ ቲቶ 1፡16)። "የአምልኮት መልክ ያላቸው ኃይሉን ግን የካዱ" ናቸው (2ጢሞ.3፡5)። ስለሆነም "መልክ" እንጂ "እውነተኝነት" የሌላቸው መሆኑ በጌታ ስለሚታወቅ ቀድሞውኑ ያልዳኑና ሕይወትን ያላገኙ ናቸው እንጂ በኋላ መዳናቸው ወይም ሕይወታቸው የተወሰደባቸው አይደሉም። በእውነት ከልብ ጌታን አምነው የዳኑና የዘላለም ሕይወት ያገኙ ግን ለዘላለም የዳኑና ለዘላለም የማይጠፉ ናቸው። ይህም በክርስቶስ ያገኘነው የዘላለም መዳንና የዘላለም ሕይት ዋስትና ነው።

ቀጣይ ንባብ፨

Amharic Bible-|- The Holy Bible [King James Version]