ቤተክርስቲያን/Aclesia  

የዘላለም ሕይወት

የዘላለም ሕይወት ምንድነው?

የዘላለም ሕይወት የጊዜ ወሰን በሌለው ሁኔታ ውስጥ ለዘላለም መኖር ብቻ አይደለም፤ ያልዳኑ ሰዎችም ቢሆኑ “በእሳት ባሕር” ውስጥ በሥቃይ የሚኖሩት “ለዘላለም” መሆኑ ተነግሯል፤ “ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ” ይባላሉ (ማቴ.25፡41)። “በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ” (2ተሰ.1፡10፤ ማቴ.25፡46)፣ እንዲሁም “ለዘላለምም እስከ ዘላለም ቀንና ሌሊት ይሣቀያሉ” (ራእ.20፡10) ተብሎ ተጽፏል፡፡ “የዘላለም ሕይወት” ሲባል ግን በዘመን ሳይገደቡ ለዘላለም መኖር ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርን በማወቅ ከእርሱ ጋር ለዘላለም በኅብረት መኖር ነው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጨረሻው ጸሎቱ ውስጥ የዘላለም ሕይወትን ሲገልጸው “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” ብሏል (ዮሐ.17፡2-3)። እግዚአብሔርን ስናውቅ በእርሱ ዘንድ ያለውን ባሕርይ፣ ፈቃድ እና መሻት በአእምሮአችን ብቻ ሳይሆን በመንፈሳችንም ማለት በውስጣዊ ማንነታችን እናውቀዋለን፤ በተግባርም ይዋሐደናል፡፡ ይህ በመለኮት ዘንድ ያለው የዘላለም ሕይወት በክርስቶስ መምጣት የተገለጠ፣ በሐዋርያትም የተሰበከ ነው፤ ሐዋርያት “ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል፣ እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን” በማለት ነግረውናል (1ዮሐ.1:2)፡፡ የዚህም ውጤቱ “ከአባት ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ኅብረት ማድረግ” ነው (1ዮሐ.1፡3)፡፡

ይህም የዘላለም ሕይchወት የሚገኘው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን መሆኑ በተደጋጋሚ ተነግሯል። “በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት *አለው* ” ተብሎ ተጽፏል (ዮሐ.3፡36)። ራሱም ሲናገር “እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት *አለው* ” ብሏል (ዮሐ.6:47)። “አለው” የሚለው ቃል በክርስቶስ ያመነ ሰው የዘላለም ሕይወት ባለቤት የሚሆነው ባመነ ጊዜ እንደሆነ ያሳያል። ይህም የዘላለም ሕይወት ክርስቶስን አምነን ከተቀበልንው በኋላ ለዘላለም የማይወሰድና በውስጣችን የሚኖር መሆኑን ያረጋግጣል። “የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ለምታምኑ ይህን ጽፌላችኋለሁ” የሚለው ቃል ይህን ይበልጥ አስረግጦ የሚናገር ነው (1ኛ ዮሐ. 5፥13)። ጥያቄው ግን ክርስቶስን አምነናል ላሉ ሁሉ የዘላለም ሕይወት ይሰጣልን? ለመሆኑ ክርስቶስን ማመን ምንድን ነው? የዘላለም ሕይወት የሚሰጠው ለምን ዓይነት አማኝ ነው?

ቀጣይ ንባብ


Amharic Bible-|- The Holy Bible [King James Version]