«ትያጥሮን» በታናሽ እስያ ውስጥ ልድያ በተባለችው ክፍለ ሀገር የምትገኝ ከተማ ነበረች፤ በፊልጵስዩስ ወንጌልን ያመነችው ቀይ ሐር ሻጭ የነበረችው ልድያ የተባለችው ሴት ከትያጥሮን የመጣች እንደነበረች ተገልጿል (የሐ.ሥ.16፡14)፡፡ ትያጥሮን በአሁኑ ጊዜ “አክሂሳር” ተብላ ትጠራለች፡፡ በዚህች ከተማ ውስጥ የነበረችው ቤተክርስቲያን እንደ ሌሎቹ የእስያ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ በወቅቱ ያለችበት ሁኔታንም ሆነ ወደፊት ሊመጣ የነበረውን አጠቃላይ የቤተክርስቲያን ገጽታ የሚመለከት መልእክት ከጌታ የተላከላት ቤተክርስቲያን ነበረች፡፡ ቀደም ሲል በኤፌሶን፣ በሰምርኔስና በጴርጋሞን ለነበሩት የእስያ አብያተ ክርስቲያናት የተላኩትን መልእክታት የተመለከትን ሲሆን በትያጥሮን ለነበረችው ቤተክርስቲያን የተላከውን ደግሞ ቀጥሎ እናቀርባለን፡፡
ቁ.18 - «በትያጥሮን ወዳለው ወደ ቤተክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ እንደ እሳት ነበልባል የሆኑ ዓይኖች ያሉት በእቶንም የነጠረ የጋለ ናስ የሚመስል እግሮች ያሉት የእግዚአብሔር ልጅ እንዲህ ይላል፡፡»ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለትያጥሮን ቤተክርስቲያን ራሱን ያቀረበው በእግዚአብሔር ልጅነቱ ነው፡፡ እርሱ የዘመኑ ፍጻሜ ሲደርስ ከሴት (ከማርያም) በመወለዱ የሰው ልጅ ቢሆንም ከዓለም መፈጠር አስቀድሞ ከእግዚአብሔር የተወለደ የእግዚአብሔር ልጅ ነው፡፡ ይህም ማንነቱ አምላክነቱን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ «የሰው ልጅ» የተባለው ያው ኢየሱስ “የእግዚአብሔር ልጅ” ተብሏል፡፡ በሉቃ.1፡35 ላይ «ካንቺ የሚወለደው ቅዱሱ፣ “የእግዚአብሔር ልጅ” ይባላል» የሚል እናነባለን፡፡ መጥመቁ ዮሐንስ «እኔም አይቼአለሁ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነም መስክሬአለሁ» ብሏል (ዮሐ.1፡34)፤ ጴጥሮስ «አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ» ብሏል (ማቴ.16፡16፤ ዮሐ.6፡69)፡፡ ጳውሎስ እንዳመነ ወዲያውኑ በደማስቆ ምኩራቦች ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ መስክሯል (የሐ.ሥ.9፡20)፡፡ የቤተክርስቲያን ራስ የሆነውና ቤተክርስቲያኑን የሚገዛው ኢየሱስ ሰው ብቻ ሳይሆን አምላክም መሆኑን በትያጥሮን የነበሩ ክርስቲያኖች እንዲያስተውሉ ስለፈለገ ራሱን በእግዚአብሔር ልጅነቱ አቅርቦላቸውዋል፡፡ እርሱ በዚያች ቤተክርስቲያን እየተሠራ የነበረውን አስከፊ ነገር የሚያውቅና ሊፈርድበት የሚቻለው አምላክ መሆኑን ሁሉም እንዲያውቅ ፈልጓል፡፡ ፈራጅነቱንም ለማመልከት «እንደ እሳት ነበልባል የሆኑ ዐይኖች ያሉት» በማለት ራሱን ይገልጻል፡፡ «አምላካችን በእውነት የሚያጠፋ እሳት ነውና» ተብሎ እንደተጻፈ (ዕብ.12፡29)፣ እሳት ለአምላክ መገለጫ ሆኖ ሲቀርብ ፍርድን እንደሚያመለክት ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔር ልጅ ዓይኖች እንደ እሳት ነበልባል ሆነው መገለጣቸው በትያጥሮን ቤተክርስቲያን ውስጥ ከነበረው ክፋት የተነሣ በዚያ የነበሩትን በቁጣና በፍርድ ዓይኖቹ እየተመለከታቸው መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ በተጨማሪም «በእቶን የነጠረ የጋለ ናስ የሚመስሉ እግሮች ያሉት» በማለት ራሱን አስተዋውቋል፡፡ ይህም ማለት የተመለከተውን የትያጥሮንን ክፋት በቁጣ ዓይኖች በመመልከት ብቻ ሳያበቃ በተግባርም እውነተኛውን የጽድቅ ፍርድ የሚፈርድበት መሆኑን፣ በነደደ ቁጣ ይፈርድባቸው ዘንድ ክፋትን ሁሉ በእግሮቹ ለመርገጥ በመካከላቸው ሊመላለስ እንደተዘጋጀ የሚያሳይ አገላለጽ ነው፡፡ ይህንን ማንነቱን ማወቅ ጸጋውንና ምሕረቱን፣ ፍቅሩንና ትዕግሥቱን ሰበብ አድርገው በዓመፃቸው ለቀጠሉ ሁሉ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ይሆንላቸዋል፡፡ ኢየሱስ ሰዎችን በጸጋና በኀዘን በፍቅርም የሚያየውን ያህል በደነደነና በደነዘዘ ልብ በቤቱ ውስጥ ሆነው ክፋትን በዓመፃ የሚደርጉትን የማይጸጸት ኅሊና ያላቸውን ሁሉ በአንድ ወቅት ፈሪሳውያንን እንዳያቸው እንደ እሳት በሚንበለበሉት ዓይኖቹ በቁጣ ያያቸዋል (ማር.3፡5)፡፡ በዚህም ሳይወሰን ለእርሱ ሊሰጠው በሚገባ ስፍራ ላይ እንዲሆን ክፋትንና ርኩሰትን ባስገቡና ሁሉ ላይ ተግባራዊ እርምጃን በመውሰድ ጻድቅ ፈራጅነቱን በተግባር ያረጋግጣል፡፡ ፍቅሩ ወደ እርሱ የተመለሱትን ይቀበል ዘንድ ግድ የሚለውን ያህል ጽድቁ ደግሞ በዓመፃ በሚቀጥሉት ላይ በቁጣ ይፈርድ ዘንድ ግድ የሚለው መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡
ቁ.19 «ሥራህንና ፍቅርህን፣ እምነትህንም፣ አገልግሎትህንም፣ ትዕግሥትህንም፣ ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው እንዲበዛ አውቃለሁ»በቀጣዮቹ ቁጥሮች ላይ በትያጥሮን ቤተክርስተያን ስለነበረው ከፍ ያለ ርኩሰትና ክፋት ስናነብ በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ መልካም ነገር ይገኛል ብሎ ማሰብ ሊከብደን ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ጌታ ኢየሱስ በዚህች በእጅጉ አስከፊ በሆነ የእምነት መበከልና የሞራል (የምግባር) ውድቀት በምትገኘው ቤተክርስቲያን ውስጥ ድል የነሱ ቅሬታዎችን ይመለከታል፤ በመሠረቱ መልእክቱም እየተነገረ ያለው ጥቅጥቅ ባለው የትያጥሮን ጨለማ መካከል ለሚገኙት ለእነዚህ ጥቂት የብርሃን ልጆች ነበረ፡፡ እነርሱ በዚያች ቤተክርስቲያን የነበረችውን ኤልዛቤልን ቸል በማለታቸው ቢነቀፉም በተገኘባቸው መልካም ነገር ተመስግነዋል፡፡ ጌታ ኢየሱስ በአቀራረቡ የጀመረው የማያስደስተው ቸልተኛነታቸውን ከመንቀፍ ሳይሆን ለእርሱ አስደሳች የነበረውን መልካም ነገራቸውን ከማመስገን ነበር፡፡ ይህም እኛ በድካም ውስጥ የሚገኙ አማኞችን ስህተታቸውን ለመንገር ልንከተለው የሚገባንን የቅደም ተከተል መርህ ይሰጠናል፤ በቅድሚያ ላላቸው መልካም ነገር ዋጋ በመስጠት በማመስገን ብንጀምር የምንነቅፈውን ድካማቸውን ለማረም ታዛዦች ስለሚሆኑ የማቅናት አገልግሎቱ ሊሳካ ይችላል፡፡ ብዙ ክፋት ባለበት ከፊተኛው ይልቅ የበዛ መልካም ነገር ማየት አስገራሚ ነው፡፡ በትያጥሮን የነበሩ ቅሬታዎች ሥራቸው ፍቅራቸው፣ እምነታቸው፣ አገልግሎታቸው፣ ትዕግሥታቸው ከፊተኛ ይልቅ የበዛ ነበር፡፡ በዙሪያችን የኤልዛቤል ግልሙትና በነገሠበት በእኛም ዘመን ይህ በእኛም ሊገኝብን ይገባል፡፡ ጌታን የሚያስከፋ ነገር በበዛ ቁጥር በእኛ ያለው መልካም ነገር ከፊት ይልቅ ሊበዛ ይገባዋል፡፡ ይህም በውስጣችን ከሚፈጠረውና ለጌታ ከሚኖረን ብርቱ ቅንዓት የሚነሣ ነው፡፡ ጌታ በታላቅ ኀዘን ሆኖ እንደ እሳት ነበልባል በሆኑ ዓይኖቹ በሚመለከተው የክርስትና ዓለም መካከል እንደ እነዚህ ቅሬታዎች ሆኖ መገኘት በእጅጉ አስደሳች ነው፡፡ በትያጥሮን ለጌታ የቀሩ ጥቂት አማኞች የተገኙባቸውን እነዚህን አምስት መልካም ነገሮች እውነተኛ አማኞች ሁሉ በውድቀት ዘመን ከፊት ይልቅ አብዝተው ሊይዟቸው ይገባል፡፡ መልካም ሐሳብ ማቅረብና መልካም ነገር መናገር ብቻ ሳይሆን ያንኑ በተግባር በመተርጐም መልካም ሥራን መሥራት ይገባል፡፡ ይህም ለታይታ ወይም ለዝና ሳይሆን ለጌታም ሆነ ለሰዎች ከሚኖረን ፍቅር የሚነሣ መሆን አለበት፡፡ ጌታ ሥራችንን ብቻ ሳይሆን ፍቅራችንንም ማየት ይፈልጋል፡፡ እንደዚሁም የምንሠራውን ሥራ ሁሉ በእምነት ልንሠራው ይገባል፤ ይህም እምነት እያደገ እና እየበዛ የሚሄድ እምነት ሊሆን ይገባል፡፡ የሚያድግ እምነት የሚኖረን ከሆነ በትጋት የምናከናውነው አገልግሎትም ይኖረናል፡፡ በተሰጠን ጸጋ በታማኝነት እያገለገልን ጌታን ማክበር ይገባል፤ በፍቅርና በእምነት ሆነን መልካም ሥራን ስንሠራና አገልግሎታችንን ስንፈጽም ደግሞ በትያጥሮን ቤተክርስቲያን የነበረው የኤልዛቤል አሠራር ይጠላናል፣ ያሳድደናልም፤ የተለያዩ ፈተናዎች ይበዛሉ፡፡ ይህን ለመሻገር ደግሞ የበዛ ትዕግሥት ያስፈልገናል፡፡ እነዚህን ሁሉ ከፊት ይልቅ አብዘተን ይዘን ብንገኝ በውድቀት ዘመን ድል ነሺዎች እንሆናለን፤ ጌታም ይደሰታል፡፡
ቁ.20 «ዳሩ ግን ነቢይ ነኝ፣ የምትለው ባሪያዎቼንም እንዲሴስኑና ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉ የምታስተምረውንና የምታስተውን፣ ያችን ሴት፣ ኤልዛቤልን፣ ስለምትተዋት የምነቅፍብህ ነገር አለኝ»ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በትያጥሮን ቤተክርስቲያን የተመለከተውን የአሕዛብ ርኩሰት ያስገባውንና የሚመራውን የክፋት ኃይል በእስራኤል ውስጥ የሲዶናውያንን የጣዖት አምልኮ ባስገባችው በኤልዛቤል ምሳሌነት ሲገልጸው እንመለከታለን፡፡ ኤልዛቤል ሲዶናዊት ስትሆን የሲዶናውያን ንጉሥ የኢትበአል ልጅ ነበረች፤ እስራኤል በሮብዓም ጊዜ ለሁለት ከተከፈለች በኋላ በ10ሩ ነገድ ላይ በሰማርያ ከነገሡት ነገሥታት መካከል ሰባተኛ የነበረው አክዓብ የተባለው ክፉ ንጉሥ ኤልዛቤልን አግብቶ በእስራኤል ላይ ንግሥት ሆና እንድትሰለጥን አድርጓት ነበረ፡፡ እርሱም «በኣል» የተባለውን የሲዶናውያን አምላክ አመለከ፤ በሰማርያም ቤት ሠርቶለት መሠዊያ አቆመለት፡፡ አክዓብ ይህን ያደረገው፡፡ ከእርሱ በፊት የነበሩት ሁሉ የሄዱበት የናባጥ ልጅ የኢዮርብዓም ኃጢአት ታናሽ ነገር መስሎ ስለታየው እንደ ነበር ተጽፏል (1ነገሥ.16፡31-33 ተመልከት)፡፡ አክዓብ እግዚአብሔርን የሚያስቆጣ ነገር ያበዛ ነበር፤ ይህም ብቻ ሳይሆን እስራኤልንም አስቶ ነበረ (1ነገሥ.16፡33፤ 20፡22)፤ ይህንንም ያደርግ የነበረው ሚስቱ ኤልዛቤል እየነዳችው እንደነበረ ተጽፏል፡፡ በ1ነገሥ.20፡24 ላይ «በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ለመሥራት ራሱን እንደሸጠ ሚስቱም ኤልዛቤል እንደነዳችው እንደ አክዓብ ያለ ሰው አልነበረም» የሚል ቃል እናነባለን፡፡ ኤልዛቤል በአክዓብ ቤተመንግሥት ከገባችበት ጊዜ ጀምሮ እስራኤል ሁሉ የበኣል አምልኮን እንዲከተል የማሳት ሥራን ሠርታለች፡፡ ይህንንም ያደረገችው የእግዚአብሔርን ነቢያት በማጥፋት በምትኩ ደግሞ በገበታዋ የሚበሉ የበኣልን ነቢያት በማሰማራት ነበር፡፡ በ1ነገሥ.18፡19፣22 እንደተገለጸው በኤልዛቤል ማዕድ የሚበሉ 450 የበኣል ነቢያት ነበሩ፡፡ በወቅቱ የነበረውን የእስራኤልን ሕዝብ ሁኔታም ስንመለከት ከበኣል እና ከእግዚአብሔር እውነተኛ አምላክ ማን እንደሆነ መለየት እስኪሳነው ድረስ በሁለት አሳብ የሚያነክስ ሕዝብ እስኪሆን ድረስ ስቶ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ውድቀት የመጣው ኤልዛቤል በእስራኤል ላይ እንድትሰለጥን በመደረጉ ነበር፡፡
ኤልዛቤል ንግሥት ከመሆኗ አንጻር ፖለቲካዊ ኃይል ብትሆንም የእግዚአብሔር ሕዝብ በነበረው በእስራኤል ላይ ስትሰለጥንና ዋነኛ አመራሩን በመያዝ አክዓብን እየነዳች የወደደችውን ማድረግ በቻለች ጊዜ ግን ያደረገችው እግዚአብሔርን የሚያስቆጣና አምልኮተ እግዚአብሔርን የሚቃወም ሥራ ነበር፡፡ ይህንንም ዓላማዋን ያስፈጸመችው የሐሰት ነቢያትን በመጠቀም ነበር፡፡ በትያጥሮን ቤተክርስተያን የነበረውን ክፉ ሥርዓት በትክክል መግለጥ የተቻለውም በኤልዛቤል ምሳሌነት ነው፡፡ «ነቢይ ነኝ የምትለውን» ተብላ ተገልጻለች፤ የእግዚአብሔርን ሕዝብ የማሳት ሥራ ለመሥራት «ንግሥት ነኝ» ከማለት ይልቅ «ነቢይ ነኝ» ማለትን መርጣለች፡፡ ጠላት የጌታ የሆኑትን ለማሳት መንፈሳዊ መስሎ መቅረብ የተለመደ አሠራሩ ነው፡፡ «ሰይጣን የብርሃን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና እንግዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስል ራሳቸውን ቢለውጡ ታላቅ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜያቸው እንደ ሥራቸው ይሆናል» ተብሎ ተጽፏል (2ቆሮ.11፡14-15)፡፡ በመሆኑም ውሸተኞች ሐዋርያት ተንኰለኞች ሠራተኞች (2ቆሮ.11፡13)፣ ሐሰተኞች ነቢያት (1ዮሐ.4፡1) በቤተክርስቲያን ውስጥ ገብተው አመራሩን ሲይዙት ብዙ ሕዝብን ማሳት ይችላሉ፤ የማሳት ሥራውንም የሚሠሩት የሐሰት ትምህርታቸውን በማስተማር ነው፤ «ነቢይ ነኝ» የምትለው ኤልዛቤልም የምታስተምርና የምታስት መሆኗ ተገልጧል፡፡ በቤተክርስቲያን ውስጥ የኤልዛቤል አሠራር ሲሰለጥን የሚያደርገው የመጀመሪያ ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ትምህርት በማበላሸት ክፉ ትምህርቶችን ማስተማር ነው፤ ተቀባይነት ለማግኘት ሲባል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን እያጣመሙ በመጥቀስ የማስተማር ስልት ቢከተሉም የሐሰተኞች ነቢያት ትምህርት የአጋንንት ትምህርት መሆኑ ግልጽ ነው (1ጢሞ.4፡2)
የኤልዛቤል ትምህርት ምን እንደሆነ ተገልጧል፡፡ የጌታ ባሪያዎች «እንዲሴስኑና ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉ» የማድረግ አላማ የነበረው ትምህርት ነው፡፡ የኤልዛቤል ሥርዓት ይህንን ሲያደርግ በዝምታ ወይም በቸልታ የሚመለከቱ የጌታ ልጆች በራሱ በጌታ ተነቅፈዋል፤ ስለሆነም አማኞችን የሚያስቱ ክፉ ትምህርቶችን በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ልንጋፈጣቸውና ልናፈርሳቸው ይገባል እንጂ ቸልተኞች መሆን የለብንም፤ በኤልዛቤል ዘመን እንደነበረው እንደ እግዚአብሔር ሰው እንደ ኤልያስ ለእግዚአብሔር በመቅናት እውነትን የምንመሰክር ልንሆን ይገባናል እንጂ ፈርተን ዝም የምንል መሆን የለብንም፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ «ባሪያዎቼ» የሚላቸው ሰዎች በዚህች ቤተክርስቲያን ውስጥ እንደነበሩ መስማት አስደሳች የመሆኑን ያህል እነዚህ የጌታ ባሪያዎች ኤልዛቤል ክፉ ትምህርቷን እያስተማረች የምታስታቸው መሆናቸውን መስማት ግን ልብን በኀዘን የሚሰብር ነው፡፡ እነዚህ የጌታ ባሪያዎች ለኤልዛቤል ትምህርትና ለሐሰት አሠራሯ በሚያጋልጣቸው ስፍራ በመሆናቸው በተጽዕኖዋ ሥር ሊወድቁ ችለዋል፡፡ የኤልዛቤል ትምህርት በጴርጋሞን ቤተክርስቲያን ውስጥ ከገባው የበለዓም ትምህርት ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ በሁለቱም ስፍራዎች የተሰጠው ትምህርት የጌታ የሆኑት እንዲሴስኑና ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉ የሚያደርግ ነው፡፡ ሆኖም በለዓም ከውጭ ሆኖ እስራኤልን በተንኮል ለማጥመድ (ለማሳት) የማያምነውን ባላቅን ያስተማረ ሲሆን ኤልዛቤል ግን ወደ ውስጥ ገብታ በጌታ ሕዝብ ላይ ሰልጥና የጌታን ባሪያዎች ለማሳት ክፉ ትምህርቷን ያስተማረች ናት፡፡ ኤልዛቤል በዚህ ጠባይዋ በማቴ.13፡33 ላይ ከተገለጠችውና ሁሉ እስኪቦካ ድረስ እርሾዋን በሦስት መስፈሪያ ዱቄት ከሸሸገችው ሴት ጋር አንድ ሆና ትታያለች፡፡ እርሾ የክፉ ትምህርትና የክፉ ምግባር ምሳሌ ሆኖ በቅዱሳት መጻሕፍት ተገልጿል፡፡ (ማቴ.16፡12፤ ሉቃ.12፡1፤ 1ቆሮ.5-8፤ ገላ.5፡7) ሲዶናዊቷ የበአል አምልኮ ተከታይ ኤልዛቤልም የጌታ የሆኑትን ያሳተችው እንደ በለዓም እዚያው ባለችበት በውጭ ሆና ሳይሆን ወደ ውስጥ ገብታ እንደዚህች ሴት እርሾዋን (ክፉ ትምህርቷን) በጌታ ባሪያዎች ውስጥ በማሰራጨት ነው፡፡ በትያጥሮን ቤተክርስቲያንም ሆነ እርስዋን በሚመስሉ በየዘመናቱ በነበሩና ባሉ አብያተክርስቲያናት ሁሉ የኤልዛቤል ሥርዓት ከመጀመሪያ እስከመጨረሻ ሥራውን የሚሠራው የጌታ ባሪያዎች እንዲሴስኑና ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉ የሚያደርግ ክፉ ትምህርትን መድረኩን ይዞ በማስተማር ነው፡፡ በእርግጥም ሴሰኝነትና ጣዖት አምልኮ በክርስትናው ዓለም ውስጥ ሥር ሰዶ የሚመለከቱ አማኞች ሁሉ ይህ ውድቀት የኤልዛቤል ክፉ ትምህርት ያመጣው መሆኑን ለመረዳት አይቸገሩም፡፡
የኤልዛቤል ሥርዓት ይህንን ሲያደርግ በዝምታ ወይም በቸልታ የሚመለከቱ የጌታ ልጆች በራሱ በጌታ ተነቅፈዋል፤ ስለሆነም አማኞችን የሚያስቱ ክፉ ትምህርቶችን በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ልንጋፈጣቸውና መልስ ልንሰጥባቸው ይገባል እንጂ ቸልተኞች መሆን የለብንም፤ በኤልዛቤል ዘመን እንደነበረው እንደ እግዚአብሔር ሰው እንደ ኤልያስ እውነትን የምንመሰክር ልንሆን ይገባል እንጂ ፈርተን ዝም የምንል መሆን የለብንም፡፡ ጌታ ስለ ሥራቸው፣ ስለ ፍቅራቸው፣ ስለእምነታቸውና ስለአገልግሎታቸው የመሰከረላቸውን እና በትያጥሮን ቤተክርስቲያን ለእርሱ የቀሩትን አማኞች፣ የነቀፈበት ነገር ቢኖር በክፉ ትምህርቷ የጌታን ባሪያዎች ያሳተች ያቺን ሴት ኤልዛቤልን ቸል ማለታቸውን ነበር፡፡ እነዚህ ቅሬታዎች በክፉ ትምህርቷ ያልተወሰዱና ከእርስዋ ጋር ያልተባበሩ ቢሆኑም፣ እንዲሁም ጌታን የሚያስደስቱና ከፊት ይልቅ ብዙ የሆኑ መልካም ነገሮች የተገኙባቸው አማኞች ቢሆኑም፣ ያቺን ሴት ቸል በማለታቸው በጌታ ከመነቀፍ አልዳኑም፤ ስለዚህ ጌታ የሚፈልገው ራሳችንን ከክፉ እንድንጠብቅ ብቻ ሳይሆን፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ ሆኖ የጌታን ባሪያዎች እያሳተ ያለውን የኤልዛቤል ሥርዓት በእግዚአብሔር ቃል በመቃወም የክፉ ትምህርቷ ሰለባ እየሆኑ ያሉትን እንድናነቃ ነው፡፡
ቁ.21 «ንስሐ እንድትገባ ጊዜ ሰጠኋት፤ ከዝሙትዋም ንስሐ እንድትገባ አልወደደችም፡፡»የክፉ ሰዎች የክፋታቸው ብዛት የእግዚአብሔርን የጸጋ መጠን ሊቀንሰው አይችልም፤ የኤልዛቤል ሥርዓት የክፋት መጠን እጅግ ቢበዛም እግዚአብሔር ለእርስዋም እንኳ የንስሐ ጊዜ የሚሰጥበት ጸጋ ነበረው፡፡ እግዚአብሔር የጽድቅ ፍርዱን ከመጀመሩ በፊት ሁልጊዜም የሚያደርገው እንደዚህ ነው፡፡ በትያጥሮን ቤተክርስቲያን ውስጥ መሪነቱን የያዘውን በኤልዛቤል የተመሰለውን ክፉ ሥርዓት የሚያራምዱ ሰዎች ንስሐ እንዲገቡ ጊዜ ተሰጥቶአቸው ነበር፡፡ ይሁንና ከፍ ባለ ድፍረት እግዚአብሔርን የሚያስቆጣ ሥራ እያበዙ የነበሩት እነዚህ ሰዎች ንስሐ ለመግባት ፈቃደኛ እንዳልነበሩ «ከዝሙትዋም ንስሐ እንድትገባ አልወደደችም» በሚለው ቃል ተገልጾልናል፡፡ ንስሐ በሚገቡ ሁሉ በጌታ ዘንድ ታላቅ ደስታ የሚሆነውን ያህል የንስሐ ዕድልን በገፉት ላይ ደግሞ ከፍ ያለ ቁጣ ሊነድድ እንደሚችል መገንዘብ አያዳግትም፡፡ በኤልዛቤል መንገድ የሚሄዱት እነዚህ ሰዎች በቤተክርስቲያን መድረክ ላይ ሆነው ክርስቲያን ነን እያሉ የጌታ ባሪያዎች እንዲሴስኑና ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉ ማስተማራቸው እነርሱ የነበሩበትን ሁኔታ በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡ ሴሰኝነት የእግዚአብሔርን አምልኮና የተቀደሰ ሥርዓት ከአጋንንት አምልኮና ከዚህ ዓለም ሥርዓት ጋር ማቀላቀልን የሚያሳይ ሲሆን ለጣዖት የታረደውን መብላት ደግሞ ከአጋንንት ጋር ማኅበረተኛ መሆንን ከጣዖት አምላኪዎች ጋር ቋሚ ኅብረት ማድረግን የሚያሳይ ነው፡፡ «ዝሙትዋ» ተብሎ የተገለጠው የኤልዛቤል ኃጢአትም ይኸው ነው፡፡ «ቤተክርስቲያን» ተብሎ በሚጠራ ማዕከል ውስጥ አምልኮ ለእግዚአብሔር ብቻ ሊቀርብ የሚገባውን አምልኮ ለማይገባቸው መስጠት አመንዝራነት ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን በዙሪያችን ባለው ክፉ ዓለም ከሚከናወነው የአጋንንት ሥራ ጋር ግልጽ የሆነ ልዩነት እንዳይኖር እንዲያውም «ክርስቲያን ነኝ» እያሉ ከጣዖት አምላኪው ማኅበረሰብ ጋር ማኅበረተኞች የሚያደርግ ተግባርን መፈጸም የኤልዛቤል ዝሙት ሌላው መገለጫ ነው፡፡ የዚህ ርኩሰት ዋነኛ ተዋናይ የሆኑትም እንኳ ቢሆኑ ንስሐ ይገቡ ዘንድ ዛሬም ቢሆን ጌታ ጊዜን ሰጥቷል፡፡ ሆኖም እየተፈጸመ ያለውን ርኩሰት ከመሪዎች እስከተራው ሕዝብ ድረስ የሚያውቁት ቢሆንም ንስሐ ለመግባት የመፈለግ ዝንባሌ ግን አይታይም፤ ስለሆነም አስፈሪው የእግዚአብሔር ፍርድ በኤልዛቤል ሥርዓት ላይ መምጣቱ የማይቀር ነው፡፡
ቁ.22-23 «እነሆ በአልጋ ላይ እጥላታለሁ ከእርስዋ ጋር የሚያመነዝሩትን ከሥራዋ ንስሐ ባይገቡ በታላቅ መከራ እጥላቸዋለሁ፤ ልጆችዋንም በሞት እገድላቸዋለሁ፤ አብያተክርስቲያናትም ሁሉ ኩላሊትንና ልብን የምመረምር እኔ እንደሆንሁ ያውቃሉ፡፡ ለእያንዳንዳችሁም እንደ ሥራችሁ እሰጣችኋለሁ፡፡»ለንስሐ የሚሆን በቂ ጊዜ የተሰጣት በኤልዛቤል ማንነት የተገለጸችው በክርስትናው ዓለም ውስጥ የምትገኘው የክፋት ኃይል ከዝሙትዋ ንስሐ ለመግባት ባለመውደድዋ የተነሣ የሚጠብቃትን ፍርድ በዚህ ክፍል እናነባለን፡፡ ጌታ ኢየሱስ «እነሆ በአልጋ ላይ እጥላታለሁ» ሲል አልጋው በሚፈርድባት በእርሱ ስትጣል የምትወድቅበት የመከራ አልጋ እንጂ ለማረፍ የምትተኛበት የምቾት አልጋ አለመሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ዕለተ ሞቱን በመጠበቅ በታላቅ ሥቃይ እየማቀቀ በአልጋ ላይ እንደሚገኝ በሽተኛ እንድትሆን ጌታ በታላቅ መከራ የሚመታት መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ በዚህች ክፉ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ውስጥ የሚገኙትና የቁጣውን ፍርድ ያስተላለፈባቸው ሰዎች ለሁለት ተከፍለዋል፡፡ የመጀመሪያዎቹ «ከእርስዋ ጋር የሚያመነዝሩት» የተባሉት ሲሆኑ እነዚህ ሰዎች በክፉ ትምህርቷ የሳቱና በፈቃዳቸው ራሳቸውን በአሠራሯና በተጽዕኖዋ ሥር ያደረጉ የጌታ ባሪያዎች እንደሆኑ መገንዘብ ይቻላል፡፡ እነርሱም በኤልዛቤል ሥርዓት በሚመራ የክርስትና ዓለም ውስጥ ሆነው ራሳቸውን ባሳመኑበት የተለያየ ምክንያት ተጠላልፈው ጌታን እያወቁ ለጌታ መለየት የተሳናቸውና ባሉበት ስፍራ ካለው ዓመፅና ክፋት ጋር ተስማምተው የሚኖሩ አማኞች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ እነርሱም ቢሆኑ ራሳቸውን በኤልዛቤል ግልሙትና ስላረከሱ «ከሥራዋ ንስሐ ባይገቡ» ብርቱ ከሆነው የጌታ ፍርድ ሊያመልጡ አይችሉም፡፡ እነዚህ አማኞች በኤልዛቤል ማንነት የተገለጠው ሥርዓት አካል አይደለንም ቢሉም አብረው እስካሉ ድረስ የሥራዋ ተባባሪ ወይም ከተጽዕኖዋ የተነሣ ሥራዋን የሚሠሩ ስለሚሆኑ ከሥራዋ ንስሐ ካልገቡ ፍርዱ አይቀርላቸውም፡፡ ስለዚህ እንደ እነዚህ ላሉት የጸጋው በር ከመዘጋቱና የንስሐው ጊዜ ከማለቁ በፊት አሁኑኑ “ንስሐ ግቡ” የሚለውን የጌታን ጥሪ በፍቅር እናቀርብላቸዋለን፡፡ ሁለተኛዎቹ ደግሞ «ልጆችዋ» ተብለው የተገለጡት ናቸው፡፡ እነዚህ ሙሉ በሙሉ የጌታ ሳይሆኑ የኤልዛቤል ናቸው፡፡ ከእርስዋ ጋር እንዳመነዘሩት ሰዎች የሚታዩ ሳይሆኑ እንደ እርስዋ የሚታዩ ናቸው፤ ማለትም በኤልዛቤል ማንነት የተገለጠው በትያጥሮን ውስጥ የነበረው ክፉ ሥርዓት አካል ናቸው፡፡ ልጆችዋ መባላቸው በሐሰተኛ ትንቢቶቿና በክፉ ትምህርቶቿ የተወለዱና በሂደት ያፈራቻቸው ሰዎች መሆናቸውን የሚያመለክት ነው፡፡ ምን ጊዜም የኤልዛቤል ትምህርትና የኤልዛቤል ሥራ ቸል እስከተባለ ድረስ ብዙ ልጆችን ማፍራቱ አይቀርም፣ ኤልዛቤል በዚህ አገላለጽ በአምሳሏና በጠባይዋ የተወለዱት የክፉ ልጆችዋ እናት ሆና ትታያለች፤ እነዚህም ልጆቿ በየዘመኑ ያሉ የእርስዋ የማንነቷ መገለጫዎች እንጂ ሌላ አይደሉም፡፡ ስለሆነም በአልጋ ላይ የተጣለችው ኤልዛቤል በመጨረሻ በልጆችዋ ላይ የተነገረው የሞት ፍርድ ይደርስባታል ለማለት ይቻላል፤ ይህም በልጆቿ ላይ ተፈጻሚነት ይኖረዋል፡፡ እንደ እሳት ነበልባል የሆኑ ዓይኖች እና በእቶን የነጠረ የጋለ ናስ የሚመስሉ እግሮች ያሉት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ በሰው ልጅ አስመሳይነትና ሃይማኖተኝነት ተሸፍኖ ያለውን በትያጥሮን ቤተክርስቲያንም ሆነ እርስዋን በሚመስሉ አብያተክርስቲያናት የሚገኘውን ክፋት መርምሮ ያውቃል፡፡ በይፋ የሚፈጸሙትን፣ በአፍ የሚነገሩትን ክፋቶች ብቻ ሳይሆን በውስጥ ታምቀው የሚገኙትን ክፋቶች ሁሉ መርምሮ ያውቃል፡፡ በኤልዛቤል ምሳሌነት የሚገለጸው ሥርዓት ሰዎችን ማታለል ይችል ይሆናል፤ በአንድ ወቅት የአክዓብ ሚስት ኤልዛቤል ናቡቴን ለማስገደል «እግዚአብሔርንና ንጉሡን ሰድቦአል» የሚል የሐሰት ክስ ፈጥራ ለክፋትዋ በሰው ፊት ሽፋን ለመስጠት ብትሞክርም በእግዚአብሔር ፊት ግን ልትሸፍነው አልቻለችም፤ ስለሆነም ፍርድዋ አልዘገየም (1ነገሥ. 20፡1-24)፡፡ ዛሬም ጌታ በክርስትናው ዓለም ሌላ ውጫዊ ሽፋን እየተሰጣቸው በመፈጸም ላይ የሚገኙትን ርኩሰቶች በነበልባላዊ ዓይኖቹ እየተመለከተ ነው፤ የክፉዎችን የውስጥ ሐሳብ እያየ ነው፡፡ አንድ ቀንም እንዲህ የሚያስቡትንና የሚያደርጉትን በእቶን የነጠረ የጋለ ናስ በሚመስሉት እግሮቹ ይረግጣቸዋል፤ በተጨማሪም ይህን አስፈሪ ፍርድ የሚፈጽመው እርሱ ልብንና ኩላሊትን የሚመረምር መሆኑ በአብያተ ክርስትያናት ሁሉ እንዲታወቅ ይፈልጋል፡፡ ይህንን ማወቅ በኤልዛቤል ክፉ ትምህርትና ክፉ ሥራ ላልተበከሉ አብያተ ክርስቲያናት የሚያስተላልፈው መልእክት ጠቃሚ ነው፡፡ እርሱ ውስጥን ጭምር የሚያይ መሆኑን ማወቅ በውስጥም በውጭም ለጌታ ታማኝ መሆንን በእጅጉ የሚያሳስብ ነውና፡፡ «እናንተ ግብዞች» የተባሉት ጻፎችና ፈሪሳውያን በውስጡ ቅሚያና ስስት ሞልቶበት ሳለ የወጭቱን ውጭ ያጠራ እንደነበረው ዓይነት፣ በውጭ ለሰው ዓይን የሚያምርና የሚማርክ ነገር እያሳዩ በውስጥ ግን ዓመፅና ክፋትን መሞላት በኤልዛቤል መንገድ የሚሄደው የክርስትና ሥርዓት ጠባይ እንጂ የክርስቶስ አብያተ ክርስቲያናት መለያ አይደለም፤ ጌታ ኢየሱስ ከውጭ አልፎ ወደ ውስጥ የሚያይ ስለሆነ የእርሱ የሆኑት ሁሉ ውጫዊ ነገራቸውን ብቻ ሳይሆን የውስጥ ማንነታቸውን ለእርሱ የሰጡ ናቸው፡፡ ከእርሱ የሚሰውሩት እንደሌለ ያውቃሉና፡፡ በግብዝነት ወይም በአስመሳይነት ለሰው እንዲታዩ መንፈሳዊ ነገሮችን በመፈጸም በውስጥ ግን ሴሰኝነትን፣ ነውረኛ ረብን፣ ዘረኝነትን፣ ምዋርተኝነትን የተሞሉትን በኤልዛበል መንገድ የሚሄዱትን ሁሉ ጌታ ኢየሱስ «ለእያንዳንዳችሁ እንደ ሥራችሁ እሰጣችኋለሁ» ይላቸዋል፡፡ «ለእያንዳንዳችሁ» የሚለው ይህ ቃል ፍርድን የሚቀበሉት እያንዳንዳቸው በየግል በሠሩት የክፉ ሥራቸው መጠን መሆኑን ያመለክታል፡፡ ይህም የጌታን እውነተኝነትና ጻድቅ ፈራጅነት ያረጋግጣል፤ አገላለጹም እያንዳንዳቸው እንደሠሩት የክፋት ሥራቸው መጠን የሚገባቸውን ፍርድ የሚፈርድባቸው መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡
«ዳሩ ግን ይህን ትምህርት ለማትይዙ ሁሉ የሰይጣንንም ጥልቅ ነገር እነርሱ እንደሚሉት ለማታውቁ ለእናንተ በትያትሮን ለቀራችሁት እላለሁ፤ ሌላ ሸክም አልጭንባችሁም፤ ነገር ግን እስክመጣ ድረስ ያላችሁን ጠብቁ፡፡» (ቁ.24-25)በትያጥሮን ከተማ የነበረችውን ቤተክርስቲያን በዋናነት ከሚገልጣት ከአስፈሪው የኤልዛቤል እና የልጆችዋ ገጽታ ዓይናችንን አንስተን በውስጥዋ ወደሚገኙት ቅሬታዎች መመልከት ለልብ መጽናናት የሚሰጥ ነው፡፡ እነዚህ ለጌታ የቀሩለት አማኞች በትያጥሮን ቤተክርስቲያን ውስጥ ካሉት ከኤልዛቤል ጋር ካመነዘሩት ሰዎች ጋርና ከራስዋ ከኤልዛቤል ልጆች ተለይተው ተገልጸውልናል፡፡ ጌታ ኢየሱስ እነርሱን ለይቶ ሲገልጻቸው በቅድሚያ «ይህን ትምህርት ለማትይዙ ሁሉ» ይላቸዋል፡፡ ጌታ «ይህን ትምህርት» ብሎ የገለጠው የኤልዛቤልን ትምህርት ነው፡፡ እጅግ ክፉ በሆነችው በሲዶናዊቷ በኤልዛቤል በተመሰለው ሥርዓት አስተማሪነት ይሰጥ የነበረው ክፉ ትምህርት ብዙ የጌታ ባሪያዎችን ማሳት እንደቻለ ተመልክተናል፤ እነዚህ በትያጥሮነ ለጌታ የቀሩ አማኞች ግን የዚህ ክፉ ትምህርት ሰለባ አልሆኑም፤ ኤልዛቤልና ልጆቿ ብዙ ጥረት ቢያደርጉም እነዚህን ቅሬታዎች ግን ማሳት አልቻሉም፡፡ እነዚህም አማኞች የኤልዛቤልን ትምህርት የእኔ ብለው ያልያዙ ናቸው፡፡ ኤልያስ ሲዶናዊቷ ኤልዛቤል በእስራኤል ላይ ንግሥት በነበረችበት በዚያ የጨለማ ዘመን “እኔ ብቻ ቀርቻለሁ” እስኪል ድረስ ለጌታ የቀሩትን ማየት ባይችልም እንኳ አምላካዊ መልስ ግን «ለበአል ያልሰገዱት ሰባት ሺህ ሰዎች ለእኔ አስቀርቻለሁ» ብሎት ነበር (ሮሜ11፡4)፡፡ ዛሬም ቢሆን የኤልዛቤል አሠራር በሰለጠነበት የክርስትና ዓለም ውስጥ ጌታ ለራሱ ያስቀራቸው የኤልዛቤልን ትምህርት ያልያዙ አማኞች ይኖራሉ፤ እኛ ለይተን ባናውቃቸውም ጌታ ለእርሱ የሆኑትን ያውቃቸዋል (2ጢሞ.2፡19)፡፡
በመቀጠልም ጌታ «የሰይጣንንም ጥልቅ ነገር እነርሱ እንደሚሉት ለማታውቁ» ይላቸዋል፡፡ ኤልዛቤል እና ተከታዮቿ የሚከተሉት ክፉ ትምህርት ሴሰኝነት እና ለጣዖት የታረደውን መብላት ግቡ ያደረገ በመሆኑ ዋነኛው የትምህርቱ ባለቤት ራሱ ሰይጣን መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ትምህርት በ1ጢሞ.4፡2 እንደተጠቀሰው «የአጋንንት ትምህርት» ቢባል ተገቢ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሰይጣን የትምህርቱን ተከታዮች ከዚህም አልፎ ወደ ራሱ ጥልቅ ነገሮች እንዲገቡ ያደርጋቸዋል፡፡ ኤልዛቤል ዛሬም “ነቢይ ነኝ” እያለች በምታስተምረው በክፉ ትምህርቷ ሰውን ማድረስ ወደምትፈልግበት ወደ ሰይጣን ጥልቅ ነገር የተወሰዱ ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡ ምናልባት «ሰይጣንን ማሸነፍ የምንችለው ወደ አሠራሩ ውስጥ ራስን በማስገባት እርሱ በምስጢር የሚሠራባቸውን ጥልቅ ነገሮች ስናውቅ ነው» በሚል እምነት ብዙዎች ተታለው ይሆናል፡፡ ይህ ግን የእርሱን ሥራ የምናፈርስባቸውን የእግዚአብሔርን የጦር ዕቃዎች በተለይም ቃሉን ለማስጣል ሰይጣን ራሱ የሚያሠርፀው አመለካከት መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ይሁንና እነርሱ እንደሚሉት ይህን ሰይጣን በማስመሰል ብዙዎችን ያታለለበትን ጥልቅ ነገር የማያውቁ ቅሬታዎች መኖራቸው አሁንም ልብን የሚያጽናና እና በተስፋ የሚሞላ ነው፡፡ እንደዚህ ያሉት ቅሬታዎች ለጌታ ተጠብቀው ሊቆዩ የቻሉት በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፈውን የእውነት ቃል በጥልቀት ስለተማሩና ከሌሎች አማኞች የበለጠ ብዙ እውቀት ስላላቸው አይደለም፡፡ በቀላሉ ከጌታ ጋር ያጣበቃቸው እና ለእርሱ ታማኝ እንዲሆኑ ያደረጋቸው ያላቸው ያው ትንሹ ነገር ነበር፡፡ በማቴ.25፡24 ላይ በተጠቀሰው በመክሊት ምሳሌ ላይ እንደምንመለከትው አንድ መክሊት ተቀብሎ እንደነበረውና ሌላ ከማትረፍ ይልቅ መሬት ቆፍሮ እንደቀበረው ሰው ያላቸውን ነገር ያልተጠቀሙበት ሰዎች አይደሉም፡፡ አንዳንዶች ለመዳከማቸውና በኤልዛቤል አሠራር ውስጥ ለመውደቃቸው «የሚያስተምረን፣ የሚያገለግለን አጣን፣ ለአገልግሎት የሚሆኑ ማቴሪያሎች አልተሟላልንም፣ … ወዘተ» የሚሉ ምክንያቶች እያቀረቡ የሚከራከሩ ሁሉ በትያጥሮን ከነበሩት ከእነዚህ ቅሬታዎች መማር ይገባቸዋል፡፡ እነዚህ ቅሬታዎች ምንም የተሟላ ነገር ባልነበረበት ሁኔታ፣ በዙሪያቸውም ያለው ሁሉ የኤልዛቤል ግልሙትና ሆኖ ሳለ፣ ባላቸው ጥቂት ነገር ለጌታ ታማኝ ሆነው ተገኝተዋል፤ ስለሆነም ጌታ «ሌላ ሸክም አልጭንባችሁም፤ ነገር ግን እስክመጣ ድረስ ያላችሁን ጠብቁ» ይላቸዋል፡፡ ሁሉም ነገር ልቡን የሚያስከፋ ብሎም እርሱን የሚያስቆጣው በሆነበት ስፍራ ለእርሱ የሚሆን ጥቂት ነገር ይዘው በመገኘታቸው ልቡ ተደስቶ፣ “የመምጣቱን ተስፋ” እየነገራቸው ያላቸውን ነገር ጠብቀው እንዲቆዩ ያበረታታቸዋል፡፡
በእስያ ለነበሩት ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ከተጻፉት መልእክታት ውስጥ የጌታ መምጣት ለመጀመሪያ ጊዜ የተነገረው፣ ለትያጥሮን በተላከው መልእክት ውስጥ ሲሆን፣ ይኸውም በዚህ ስፍራ ላይ ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ «እስክመጣ ድረስ ያላችሁን ጠብቁ» ሲል በልቡ ያስባቸው የነበሩት ቅሬታዎች፣ በዚያን ጊዜ በትያጥሮን በነበረች ቤተክርስቲያን ውስጥ የነበሩትን ቅሬታዎች ብቻ እንዳልሆነ መገንዘብ ይቻላል፤ ምክንያቱም እነርሱ ያን የመምጣቱን ተስፋ የሚቀበሉት በትንሣኤ እንጂ በሕይወት ሳሉ እንዳልሆነ ግልጽ ነውና፡፡ ይልቁኑ እርሱ ለቅዱሳኑ ከሰማይ ሲመጣ የትያጥሮን ቤተክርስቲያንን ገጽታ ከያዘው የክርስትና ዓለም ውስጥ ጌታ ለእርሱ የሆኑትን ቅሬታዎች እንደሚያገኝ የሚያሳይ ትንቢታዊ ቃል ነው፡፡ ይህም የትያጥሮን ቤተክርስቲያን ገጽታ በትንቢትነቱ ሲታይ በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ መፈጸም ከሚጀምርበት ጊዜ አንስቶ ጌታ እስኪመጣ ድረስ የሚቆይ መሆኑን ያመለክታል፡፡
በምዕራቡም ይሁን በምሥራቁ ዓለም ከ6ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እስከ 16ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የነበረው የጨለማው ዘመን የቤተክርስቲያን ታሪክ በትያጥሮን ቤተክርስቲያን ገጽታ ሊታይ የሚችል ነው፤ ሆኖም ይህ ገጽታ እስከ ቤተክርስቲያን ማብቂያ ድረስ በቀጣዮቹ 3 መልእክታት በሰርዴስ፣ በፊልድልፊያና በሎዶቅያ ለነበሩ አብያተክርስቲያናት በተጻፉ መልእክታት ውስጥ ከተገለጡ ገጽታዎች ጋር አብሮ የሚቀጥል ነው፡፡ በዚህ የቤተክርስቲያን ገጽታ ወስጥ የኤልዛቤል ጠባይ ጎልቶ የሚታይ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃና በየአገሩ ባሉ አብያተክርስቲያናት የሚንፀባረቅ ነው፤ ከዚህ ከመካከለኛው የቤተክርስቲያን ታሪክ ክፍለ ዘመን ቀደም ብሎ በተለይም በ440 ወደ መንበር ከመጣው “ልዮን” ከተባለው የሮም ፓፓ ጀምሮ የሮም ቤተክርስቲያን በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ላይ የበላይ ሆና የምትሰለጥንበትን መሠረት ለመጣል ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡ መልካም ሥራ ይሠሩ እንደነበረ የሚነገርላቸውን አንዳንድ ፓፓዎችን ጨምሮ እጅግ ክፉ የሆኑት ፓፓዎች ሁሉ የሮም ቤተክርስቲያንን የበላይነት ለማረጋገጥ የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል፤ ለዚህም ዓላማቸው መሳካት የምድር ነገሥታትን ተጠቅመዋል፡፡ ሮም የሐዋርያው የጴጥሮስ መንበር ናት ብለው ያምኑ የነበሩት እነዚህ የሮም ቤተክርስቲያን መሪዎች ይህንኑ አሳባቸውን በመጠቀም በዓለም ቤተክርስቲያን የበላይነትን ለመቀዳጀት ብዙ ሠርተዋል፡፡
የቤተክርስቲያን ታሪክ የመካከለኛው ዘመን መነሻ ከሆነው ከ590 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ሥልጣን የመጣው ታላቁ ግሪጎሪ ተብሎ የሚታወቀው ፓፓ ብዙ መልካም ነገር እንደነበረው ቢነገርለትም ለሮም ቤተክርስቲያን የበላይነት ከተጉት መሪዎች ቀዳሚው ነበር፤ በወቅቱ የሮም ግዛት ዋና ከተማ በነበረችው በቁስጥንጥንያ ከተማ የነበረው ዮሐንስ የተባለው ጳጳስ በበኩሉ የቁስጥንጥንያ ቤተክርስቲያንን የበላይነት ለማስፈን በሞከረ ጊዜ ግሪጎሪ ይህን አምርሮ በመቃወም ለሮም ቤተክርስቲያን የበላይነት ይምዋገት ነበር፡፡ እንዲያውም ለሮም ቤተክርስቲያን የበላይነት ተቀናቃኝ አድርጎ የሚያየውን ይህን የቁንጥስጥንያውን ጳጳስ ዮሐንስን የደገፈው ሞራይስ (Maurice) የተባለው የወቅቱ ንጉሥ ጨካኝና ተንኮለኛ በነበረው “ፎካስ” በተባለው ሰው አማካኝነት መናፍቅ ተብሎ ከነቤተሰቡ በመገደሉ ግሪጎሪ በጣም ተደስቶ ነበር፡፡ እንዲሁም በዚያ ወቅት የሮም ቤተክርስቲያንን የበላይነት ያልተቀበሉትን የማስገድል ሥራም በየስፍራው ጀምሮ ነበር፡፡
በዚህ የመካከለኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ፣ በእናቱ በማርያም፣ በቅዱሳንና በመስቀል ስም የተሠሩ ሥዕሎችና ቅረጻ ቅርጾች ከበፊቱ ይልቅ በእጅጉ እንዲስፋፉና እንዲሰገድላቸው ተደርጎ ነበር፡፡ ታላቁ ግሪጎሪ «ቅዱሳን ሰዎች ሲሞቱ በሚተዋቸው በልብሳቸውና የእነርሱ በሆነ አንዳች ነገር ወይም በዐፅማቸው ታምራት ሊደረግ ይችላል፤ በችግር ጊዜም በእነዚህ ቅርሶቻቸው ተማጽኖ ቢደረግ እርዳታና መፍትሔ ይገኛል» ብሎ ያምን ነበር፤ ከዚህም በላይ ደግሞ ሰዎች ከሞቱ በኋላ ነፍሳቸው ለሰማይ ብቁ ትሆን ዘንድ በምትነጻበት ስፍራ (መካነ ንስሐ) ለጊዜው ትቀመጣለች የሚለው ትምህርት (the Doctrine purgatory)፣ ለቅዱሳን የሚቀርብ ስግደት፣ ቅዱሳን ወደሚባሉ ቦታዎች መስገድ (መሳለም)፣ ታላቁ ግሪጎሪ በሚመራው የሮም ቤተክርስቲያን ውስጥ ከበፊት ይልቅ የተስፋፋበት ጊዜ ነበር፡፡ ሆኖም በ717 ወደ ሥልጣን የመጣው ሊዮ 3ኛ የተባለው የቢዛንታይን ንጉሥ እግዚአብሔርን ከመፍራት አንጻር ሳይሆን የራሱ በሆነ ምክንያት በአዋጅ ለሥዕል መስገድን የከለከለ ሲሆን ሥዕሎቹ ሊታበሱም ሆነ ሊሳሙ በማይችሉበት ከፍ ባለ ስፍራ እንዲሰቀሉ ደንግጎ ነበር፡፡ ነገር ግን በምሥራቁም በምዕራቡም የነበሩ ጳጳሳት፣ መነኮሳትና ሕዝቡም ይህን ድርጊት ክፉኛ ተቃወሙ፡፡ በወቅቱ የነበረው ግሪጎር 2ኛ የተባለው የሮም ጳጳስ ለንጉሥ ደብዳቤ በመጻፍ ከድርጊቱ እንዲቆጠብ አስጠነቀቀ፤ ግሪጎሪ 3ኛ ደግሞ በጉዳዩ ላይ 93 ጳጳሳት የተገኙበትን ስብሰባ አድርጎ ለሥዕል ያልሰገደ ከቤተክርስቲያን ተወግዞ እንዲለይ የሚያደርግ ውሳኔ አስወሰነ፡፡ ንጉሡ ከሞተ በኋላም የተተካው ኮንስታንታይን የተባለው ልጁ ለሥዕል የሚሰግዱትን በመቃወምና በመጥላት የሚታወቅ ነበር፤ የኮንስታንታይን ልጅም በዚያው የቀጠለ ቢሆንም እርሱ ከሞተ በኋላ “አይሬኔ” የተባለችው ሚስቱ የተዳከመው ለሥዕል መስገድ ተመልሶ እንዲያንሠራራና ሕጋዊ እውቅና እንዲያገኝ የምትፈልግ ነበረች፡፡ 10 ዓመቱ የነበረው ልጇ መንግሥትን ለመያዝ እስኪደርስ ያለውን ጊዜ በመጠቀም የሥዕልን ጉዳይ በተመለከተ በ787 በኒቂያ አለም አቀፍ ጉባኤ እንዲጠራ አደረገች፡፡ ይህም ጉባኤ 350 ሰዎች የተሳተፉበት ሲሆን ለሥዕል ስግደት ይገባል በሚሉ ሰዎች የተመራ የንግሥቲቱን ፈቃድ የሚያስፈጽም ነበር፡፡ ስለሆነም ለሥዕል ስግደት እንደሚገባ በይፋ ከተወሰነ በኋላ ይህን የሚቃወምም ደግሞ ከቤተክርስቲያን እንደሚለይ አብሮ ተወሰነ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሐዋርያትና በመጀመሪዎቹ ክርስቲያኖች መንገድ ለመሄድ የሚፈልጉና መጽሐፍ ቅዱስን በተለይም አዲስ ኪዳንን በማጥናት ጌታን ይከተሉ የነበሩና ለጌታ የቀሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች በተለይም በምሥራቁ የሮም ግዛት ይታዩ ነበር፤ እነርሱም ምንም እንኳን ሙሉ በሙሉ እውነትን ተረድተዋል ባይባልም ከመንግሥት ሃይማኖት የተለዩና በጊዜው በክርስትና ውስጥ ገብቶ የነበረውን አጠቃላይ ከቃሉ ውጪ የሆነ አሠራር የሚቃወሙ፣ የየጥንቱ ክርስትናም ተመልሶ እንዲመጣ የሚፈልጉ፣ ባላቸው ጥቂት ነገር ለጌታ የሚኖሩ ቅሬታዎች ነበሩ፤ ይሁንና በጊዜው የነበሩት የቤተክርስቲያን መሪዎች ነገሥታቱን እና አገረ ገዢዎችን በመጠቀም እነዚህን ሰዎች ያስገድሏቸው ነበር፡፡ ለምሳሌ በአርሜንያ ሲሰብክ የነበረ ቆስጠንጢኖስ የሚባለውን አንዱን አገልጋያቸውን በድንጋይ ተወግሮ እንዲገደል ካደረጉ በኋላ የገደለውን ወጣት ልጅ ጎልያድን እንደገደለው እንደ ዳዊት ቆጥረውት እንደነበር ተመዝግቧል፡፡ ከሁሉም እጅግ የከፋ ግድያ የተፈጸመባቸው ደግሞ በ842 ሥልጣን ላይ በወጣችው ቴዎዶራ በተባለች ንግሥት አማካኝነት የተፈጸመባቸው ነበር፤ ይህች ቴዎዶራ በተለይ በምሥራቅ አብያተክርስቲያናት የሥዕል የሚደረግ ስግደት እንዲስፋፋ ያደረገች ናት፡፡ ራሷ የሰባሰበቻቸው ብዙ ሰዎች በቁስጥንጥንያ ባለች “ቅድስት ሶፍያ” በምትባል የቤተክርስቲያን ሕንጻ ግቢ ውስጥ ሥዕሎችን ይዘው ችቦዎችን እያበሩ ለሥዕል በመስገድ ለሥዕል የሚቀርበውን ስግደት ይፋ ማድረጋቸው ተጽፏል፡፡ ይሁን እንጂ ለጌታ የቀሩት ክርስቲያኖች ለሥዕልና ለቅርጻ ቅርጾች፣ ለቅዱሳን ቅርሶች እንዲሁም ለዕፀ መስቀል ስግደት እንደማይገባ በማስተማራቸው ይህን ትተው ወደ ግሪክ ቤተክርስቲያን አቋም ካልተመለሱ በቀር በእሳት እንዲቃጠሉ ወይም በሰይፍ እንዲገደሉ ታወጀባቸው፤ እነርሱም በምስክርነታቸው በመጽናታቸው የተነሣ በአጭር ጊዜ ውስጥ እስከ መቶ ሺህ የሚደርሱ አማኞች በሰይፍ እንዲገደሉ እና በእሳት እንዲቃጠሉ ተደርገዋል፡፡
ከዚሁ ከመካከለኛው የቤተክርስቲያን ክፍለ ዘመን ሳንወጣ ከ1198-1216 በነበረው ኢኖሰንት 3ኛ (Innocent III) በተባለው ፓፓ ዘመንና የሮም ቤተክርስቲያን መንበረ ጵጵስና ክብር (Pontificial Glory) ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት ጊዜ ነበር፡፡ ኢኖሰንት ራሱ “መንበረ ጴጥሮስ” ብሎ ስለሚጠራት ስለ ሮም ቤተክርስቲያን መንበረ ጵጵስና የበላይነት ሲናገር “ከፍጥረት መካከል በቀን እንዲሰለጥን በተደረገው በትልቁ ብርሃን በፀሐይ መስሎታል፤ የቤተ መንግሥት ሥልጣንን ደግሞ በትንሹ ብርሃን በጨረቃ ከመሰለ በኋላ ጨረቃ ብርሃኗን ከፀሐይ እንደምትቀበል ቤተመንግሥትም ሁሉንም ክብሩንና ውበቱን የሚያገኘው ከቤተክህነት ነው” በማለት ገለጿል፡፡ ይህም የጊዜው ቤተክርስቲያን በምድር ነገሥታት ላይ እንደሠለጠነች በግልጽ የሚያሳይ ነው (ራእ.17፡3) ፡፡ በተግባርም ሲታይ የሮም ቤተክርስቲያን የፈረንሳይ የጀርመንና የእንግሊዝን እንዲሁም የስፔንና የሌሎች አገሮችን ነገሥታት ማዘዝና በእነርሱ በኩል ዓላማዋን ማስፈጸም ችላ ነበር፡፡ በተለይም እርስዋ “መናፍቃን” ብላ የምትጠራቸውን ነገር ግን የቅዱሳት መጻሕፍትን እውነት እንደተጻፈው የሚያምኑትን ክርስቲያኖች ለማስጨፍጨፍ ያላትን ኃይል ሁሉ ተጠቅማለች፡፡ የእውነተኞቹን አማኞች ጨዋነትና ለክርስቶስ ስም መከራ ለመቀበል የነበራውን ዝግጁነት በመጠቀም የሚችሉትን ያህል አሳድደዋቸዋል፡፡ በኢኖሰንት 3ኛ ዘመን በተለይ በአፕል ተራሮች ግራና ቀኝ ባሉ ሸለቆዎች ውስጥ ይኖሩ የነበሩና የሸለቆ ሰዎች በመባል ይታወቁ የነበሩት ሰዎች ክርስቲያኖች የነበሩ ሲሆን የሮም ቤተክርስቲያንን የበላይነት ካመቀበላቸውም ሌላ ትምህርታቸውና እምነታቸውም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነበር፡፡ ለዚህም የረዳቸው ወንጌላትንና ሌሎች የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎችን ከላቲን ቋንቋ ወደ ራሳቸው ቋንቋ ወደ ቩልጋር እንዲተረጎም ማድረጋቸው ነበር፡፡ +ከዚህም የተነሣ እውነትን በመረዳታቸው በመላው የሮም ግዛት በገነነችዋ ቤተክርስቲያን ውስጥ ተቀባይነት የነበራቸውን ለሥዕልና ለቅርጻ ቅርጽ መስገድ፣ የሕጻናት ጥምቀት፣ እንዲሁም “በቁርባን” ጊዜ ኅብስቱና ወይኑ ወደ ክርስቶስ ሥጋና ደምነት ይለወጣል … የሚሉ ትምህርቶችን ካለመቀበላቸውም በላይ ተቃውመዋል፡፡ በመሆኑም በፓፓው አስተዳደር ውስጥ የሚገኙ እነዚህ አማኞች “መናፍቃን ናቸው” ተብለው ዘግናኝ እልቂት ተፈጽሞባቸዋል፡፡ በተለይም በ1209 ዓ.ም ገደማ ቤዚርስ (Beziers) በተባለች ከተማ ይኖሩ የነበሩ ከ20 ሺህ በላይ የሚደርሱ ክርስቲያኖች ባሠቃቂ ሁኔታ ተጨፍጭፈዋል፡፡ ፓፓዊው ኃይል ከ300 ሺህ በላይ ሠራዊትን ያዘመተባቸው ሲሆን ሠራዊቱ ለ3 ተከፍሎ በእያንዳንዱ ቡድን ውስጥ ለሠራዊቱ መመሪያ በሚሰጡ ጳጳሳት ተመድበው ከዘመቱ በኋላ ወንድ፣ ሴት፣ ሽማግሌ፣ ሕጻን ሳይለዩ አርኖልድ (Arnold) በተባለ የቤተክርስቲያን መሪ አመራር ሰጪነት እንዲገደሉ አድርገዋል፡፡ ግድያው ተጀምሮ እስኪፈጸም ድረስም የቤተክርስቲያን ደወል ይጮህ የነበረ ሲሆን ፈርተው ወደዚያ ግቢ የሄዱት እንኳ ከመገደል አላመለጡም ነበር፤ ይህም የእነዚህን ቅዱሳን ደም ለማፈሰስ ዋነኛዋ ተዋናይ አፍኣዊቷ ቤተክርስቲያን እንደነበረች በግልጽ ያሳያል፡፡ ይህም በትክክል የኤልዛቤል መንፈስ በቤተክርስቲያን ውስጥ እንዴት ይሠራ እንደነበር ለማሳየት ግልጽ ማስረጃ ነው፡፡ በኢትዮጵያም ቢሆን በዚሁ በመካከለኛው ዘመን በቅዱሳት መጻሕፍት በተጻፈው እውነት ለመኖር በመፈለጋቸው በግፍ የተገደሉ ክርስቲያኖች ነበሩ፤ እነርሱም “ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ እንጂ ለንጉሥ አንሰግድም፣ እንዲሁም ለማርያምና ለመስቀል አንሰግድም ብለዋል፤ ቅዱስ ቁርባንን በታቦት ላይ ሳይሆን በጠረጴዛ ላይ ያደርጋሉ” ተብለው እየተከሰሱ በምስክርነታቸው እንደጸኑ ሲታይ ክፉኛ እየተደበደቡና በተለያየ መንገድ እየተሠቃዩ እንዲገደሉ ተደርገዋል፡፡
እንግዲህ በመካከለኛው የቤተክርስቲያ ክፍለ ዘመን የታየው በጌታ በኢየሱስና በእናቱ እንዲሁም በቅዱሳኑ ስም ለተሠሩ ሥዕሎች መስገድ ለጣዖት መስገድ አይደለም በሚል አመለካከለት ብዙዎችን በማታለል የጣዖት አምልኮ በቤተክርስቲያን ስፍራ እንዲኖረው ማድረግ ብቻ ሳይሆን የተቃወሙትን ሁሉ እንዲገደሉ ማድረግ የኤልዛቤልን ሥራ አጉልቶ የሚያሳይ ሥራ ነው፡፡ ኤልዛቤል አሠራርዋን የተቃወሙትን የእግዚአብሔርን ነቢያት ስትገድል እንደነበር በግልጽ ተጽፏል (1ነገሥ.18፡4፤ 19፡10)፤ በዚህም የቤተክርስቲያን የጨለማው ዘመን የኤልዛቤል የጣኦት አምልኮና የነፍሰ ገዳይነት መንፈስ በቤተክርስቲያን ምን ያህል ሰልጥኖ እንደነበር ማየት ይቻላል፡፡
በትያጥሮን ቤተክርስቲያን ውስጥ የነበረው ይህ የኤልዛቤል ገጽታ በቤተክርስቲያን ውስጥ መታየት ከጀመረ ጊዜ አንስቶ ጌታ እስኪመጣ ድረስ የሚቀጥል ይሆናል፤ ጌታ ኢየሱስ የእርሱ የሆኑትን ወደ ራሱ ከወሰደ በኋላ ጌታ የበቀል ፍርዱን መፈጸም ይጀምራል፤ በምድር ላይ የምትቀረው ሐሰተኛዋና አፍኣዊዋ ቤተክርስቲያን ወደ መከራው ዘመን የምትገባ ሲሆን በመጨረሻም ወዳጆችዋ በነበሩት የምድር ነገሥታት አማካኝነት እንድትደመሰስ በማድረግ ይፈረድባታል፡፡ ይህን ሁኔታም በራእ. 17 እና 18 ላይ በግልጽ የተነገረ ሲሆን “ታላቂቱ ባቢሎን የጋለሞታዎችና የምድር ርኩሰት እናት” የተባለችው ኃይል (17፡5) የነበራትን ክፋትና የሚደርስባትን ፍርድ እናነባለን፤ “የምድር ነገሥታት ከእርሷ ጋር ሴሰኑ”(17፡2) እርሷም በአውሬው ላይ የተቀመጠች ሆና ትያታለች (17፡3)፤ ይህም አፍአዊቷ ቤተክርስቲያን ከምድር መንግሥታት ጋር ያላትን ትስስር የሚያመለክት ነው፤ እንዲሁም “ሴቲቱ በቅዱሳን ደምና በኢየሱስ ምስክሮች ደም ሰክራ” ትታያለች (17፡6) እንዲሁም “በእርሷ ውስጥ የቅዱሳንና የነቢያት ደም ተገኘባት” ተብሎ ተነግሯል (18፡24)፡፡ ይህም በቤተክርስቲን ታሪክ ውስጥ ከቀድሞ ጀምሮ እንዲገደሉ በተደረጉትና ወደፊትም በመከራ ዘመን ጭምር የሚገደሉት የቅዱሳን ደም እጇ እንዳለበት የሚያመለክት አገላለጽ ነው፡፡ በመሆኑም ብርቱ የሆነው የሚፈርድባት እግዚአብሔር ጋለሞታይቱን ቤተክርስቲያን የምድር ነገሥታት እንዲያስወግዷት ያደርጋል፡፡ ይህንን በተመለከተም “ያየሃቸው አሥር ቀንዶችና አውሬው ጋለሞታይቱን ይጣላሉ፤ ባዶዋንና ራቁቷን ያደርጓታል፤ ሥጋዋንም ይበላሉ፤ በእሳትም ያቃጥሏታል እግዚአብሕር አሳቡን እንዲያደርጉ አንድንም አሳብ እንዲያደርጉ የእግዚአብሔርም ቃል እስኪፈጸም ድረስ መንግሥታቸውን ለአውሬው እንዲሰጡ በልባቸው አግብቷልና” ተብሎአል (ራእ.17፡16-17)፤ እንዲሁም “ኃጥአቷ እስከሰማይ ደርሷልና ዐመፃዋን አሰበ፤ እርሷ እንደሰጠች መጠን ብድራት መልሱላት፤ እንደ ሥራዋም ሁለት እጥፍ ደርቡባት፤ በቀላቀለችው ጽዋ ሁለት እጥፍ አድርጋችሁ ቀላቅሉባት፤ ራስዋን እንዳከበረችና እንደተቀማጠለች ልክ ሥቃይና ኀዘን ስጧት”፤ ተብሎ ተነግሯል (18፡6)፡፡ ስለ ኤልዛቤል ውሾች ሥጋዋን እንደሚበሉ የተነገው ትንቢት እንደተፈጸመ ሁሉ (1ነገሥ. 20፡23፤ 2ነገሥ. 9፡30-37) ለእውነቱ የተለዩትን ስለ እውነት የመሰከሩትን ቅዱሳን በገደለችና ባስገደለች ቤተክርስቲያን ላይ የተነገረው ይህ ትንቢትም መፈጸሙ የማይቀር ነው፡፡
“ድል ለነሳውና እስከ መጨረሻም ሥራዬን ለጠበቀው እኔ ደግሞ ከአባቴ እንደተቀበልሁ በአሕዛብ ሁሉ ላይ ሥልጣንን እሰጠዋለው በብረትም በትር ይገዛቸዋል፤ እንደ ሸክላ ዕቃም ይቀጠቀጣሉ፤ የንጋትም ኮኮብ እሰጠዋለው፡፡” (ቁ. 26-28)በትያጥሮን ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገኘው ድል የነሳ አማኝ የኤልዛቤልን የሚያስት ትምህርት ያልተቀበለና ስለ እውነት የመሰከረ፣ ራሱንም ከኤልዛቤል ርኵሰት የለየ፣ አማኝ መሆኑ አያጠራጥርም፤ ይህም በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ራሳቸውን ከገናናው የአፍአዊቷ ቤተክርስቲያን ሥርዓትና ትምህርት ለይተው በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በመኖራቸው መናፍቃን እየተባሉ የተሠውትን ቅዱሳን የሚያመለክት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ እነዚህ ቅዱሳን በዚህ ዓለም ታላላቆች ስለተገደሉ ለሰው ድል የተነሡ ቢመስልም እውነተኛውን እምነት ሊያስጥሏቸው በኃይል ለመጡባቸው አልተሸነፉምና በጌታ ዓይን ሲታዩ ድል የነሡ እነሱ ናቸው፡፡ የትያጥሮን ድል ነሺ “እስከ መጨረሻው ሥራዬን ለጠበቀው” ተብሎም ተገልጿል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የኤልዛቤልን ሥራ በተመለከተ “ሥራዋ” እያለ ተናግሯል፤ “ከእርሷ ጋር የሚያመነዝሩትን ከሥራዋ ንስሐ ባይገቡ በታላቅ መከራ እጥላቸዋለው” ይላል (ራእ.2፡22)፡፡ እነዚህ “ከእርስዋ ጋር የሚያመነዝሩ” የተባሉ አማኞች በኤልዛቤል ተጽዕኖ ሥር የወደቁና የምትሠራውን ሥራ የሚሠሩ ናቸው፡፡ እነዚህም በኤልዛቤል ሥራ ደል የተነሡ ናቸው፡፡ ይህን የክፋት ሥራ ድል የነሡት ግን ከኤልዛቤል ሥራ የተለዩ ብቻ ሳይሆን ጌታ ”ሥራዬ” ብሎ የጠራውን የከበረ ሥራ የሠሩ ናቸው፤ ይህንንም ሥራ ለጊዜው ሳይሆን እስከ መጨረሻ ድረስ በታማኝነት የጠበቁ ናቸው፡፡ በዘመናችንም በቀጠለውና የኤልዛቤል ሥራ በነገሠበት የክርስትና ዓለም የሚገኙ አንዳንድ አማኞች የኤልዛቤልን ሥራ አለመሥራት ብቻ በቂ አድርገው ያስባሉ፤ ይሁንና ጌታ የሚፈልገው ከኤልዛቤል ሥራ እንድንለይ ብቻ ሳይሆን የእርሱን ሥራ እስከ መጨረሻው እንድንጠብቅ(እንድንሠራ) ጭምር ነው፤ ከኤልዛቤል ሥራ ተለይተን የጌታን ሥራ በምንሥራበት ጊዜ የኤልዛቤል አሠራር የሚችለውን ያህል ያሳድደናል፤ በቀደሙት ላይ እንደደረሰው በኤልዛቤል ሥርዓት ሥር ያሉ ሰዎች ከእኛ እንዳይገናኙ ጉርብትና፣ የንግድ ልውውጥ እንዳያደርጉ፣ በማህበራዊ ኑሮ እንዳንሳተፍ፣ መቀበሪያ እንዳናገኝ፣ ሊታወጅብን ይችላል፤ ይህ በዘመናችን በሁሉም ሀገሮች የሚታይ የኤልዛቤል ሥራ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ብዙዎች መንግሥታት የእምነት ነፃነት የሰጡ ቢሆንም ኤልዛቤል ግን ባህርይዋ አልተቀየረችም፤ ስለዚህ ዛሬም ቢሆን ጌታ ከኤልዛቤል ሥራ ተለይተው ስለ ስሙ የሚደርስባቸውን መከራ እየተቀበሉ እስከ መጨረሻ ሥራውን የሚጠብቁ ድል ነሺዎችን ይፈልጋል፡፡ ለእነዚህ ድል ነሺዎች ጌታ ሊመጣ ያለ የከበረ ተስፋን ሰጥቷቸዋል፡፡ በቅድሚያ በሺው ዓመት ጊዜ ከእርሱ ጋር ሲነግሡ በአሕዛብ ላይ ስለሚኖራቸው ሥልጣን ይነግራቸዋል፤ “እኔ ደግሞ ከአባቴ እንደተቀበልኩ በአሕዛብ ሁሉ ላይ ሥልጣንን እሰጠዋለው፤ በብረት በትር ይገዛቸዋል፤ እንደ ሸክላ ዕቃም ይቀጠቀጣሉ” ይላል፡፡ ይህ አገላለጽ በመዝ.2፡8-9 የሚገኝ ሲሆን በቅድሚያ መሢሁ ጌታ ኢየሱስ የሚኖረውን ሥልጣንና ኃይል የሚመለከት መሆኑ በአዲስ ኪዳን ተገልጧል(ራእ.12፡5፤ 19፡15)፡፡ በ1ጢሞ.2፡11-12 ላይ “ቃሉ የታመነ ነው እንዲህ የሚለው፦ ከእርሱ ጋር ከሞትን ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንኖራለን፤ ብንጸና ከእርሱ ጋር ደግሞ እንነግሣለን …” የሚል ቃል እናነባለን፡፡ ስለሆነም በዙሪያችን ያለውን የኤልዛቤልን የክፋት ሥራ ድል ነስተን እስከ መጨረሻው በጌታ ሥራ ብንጸና በሺው ዓመት ጊዜ ከእርሱ ጋር በታላቅ ክብር እንነግሣለን፡፡ ኤልዛቤል ንግሥት በሆነችበት ዘመን ሁሉ የኤልዛቤል ልጆችና ከእርሷ ጋር ያመነዘሩት ሁሉ ከእርሷ ጋር በዚህች ዓለም እንዲከበሩ ሲደረግ የጌታ ልጆች ግን መብታቸው ተረግጦ በታላቅ ሥቃይና መከራ እንዲሁም በስደት እንዲኖሩ ብሎም እንዲታሰሩና እንዲገደሉ በመደረጉ በዚህ ዓለም ምንም ክብር ያልነበራቸው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ጻድቅ ፈራጅ ከሆነው ከእርሱ ከንጉሡ ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በክብር ሲገለጡና እርሱም ጠላቶቹን የእግሩ መረገጫ ሲያደርግ ወይም አሕዛብን እንደ ሸክላ ዕቃ ሲቀጠቅጣቸው የኤልዛቤል አሠራርም ለአንዴና ለዘላለም ይፈረድባታል፤ የጌታ የሆኑትም ከእርሱ ጋር በምድር ላይ ይነግሣሉ (ራእ.5፡10)፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእነዚህ ድል ነሺዎች አሁን የሚያልፉበትን የጨለማ ዘመን እስከወዲያኛው የሚገፍ የተባረከ ተስፋንም ጨምሮ ይሰጣቸዋል፡፡ ይህም “የንጋትን ኮኮብ እሰጠዋለሁ” በሚለው የተስፋ ቃል ውስጥ የተነገረ ነው፡፡ “የንጋት ኮኮብ” የተባለው ራሱ ጌታ ኢየሱስ ነው፤ ይህንንም በተመለከተ ”እኔ የዳዊት ሥርና ዘር ነኝ፤ የሚያበራም የንጋት ኮኮብ ነኝ” በማለት ራሱ ጌታ ተናግሯል (ራእ.22፡16)፤ የሚያበራ የንጋት ኮኮብ ሌሊቱ እያለፈ ንጋትም እየቀረበ መሆኑን የሚያሳይ ነው፤ ስለሆነም በትያጥሮን ቤተክርስቲያን የታየውን የኤልዛቤልን ሥራ ድል የነሱ አማኞች በዙሪያቸው ያለው ድቅድቅ ጨለማ የሚያልፍበትና ለእነርሱ ለዘላለም የሚነጋበት ተስፋ እንደቀረበ የተባረከ ተስፋ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ይህን ሁል ጊዜ በነፍሳችን ብናሰላስለው በታመነው ምስክርነት ይበልጥ እንድንጸና በልባችን ብርቱ ድጋፍ ይሆንልናል፡፡ እየጨመረ በሚሄድ መንፈሳዊ ጽናት እውነትን እንድንይዝና እንድንመሰክር ያደርገናል፡፡ አንዳንዶች እውነትን ከተረዱ በኋላ የኤልዛቤል ሥራ ባለበት ሃይማኖተኛ ዓለም ተጽዕኖ ምክንያት እየፈሩ ወደ ኋላ የሚያፈገፍጉት ወይም ወደፊት ከመሄድ ይልቅ ባሉበት የሚቆሙት ይህ አሁን ያለው የጨለማ ዘመን እንደሚያልፍና የዘላለም ንጋት ወይም የዘላለም ብርሃን እንደሚመጣ ከመዘንጋት ወይም ካለማመን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ጌታ የሰጠው ተስፋ እርግጥና ጽኑ ነው፡፡ ተስፋውን የሰጠው እርሱም የታመነ ነው፤ ስለዚህም በዚህ ተስፋ ልንበረታታና ድል ልንነሳ ይገባናል፡፡
“መንፈስ ለአብያተክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ” ቁ. 29ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቀደም ሲል ለኤፌሶን ቤተክርስቲያን፣ ለሰምርኔስ ቤተክርስቲያንና ለጴርጋሞን ቤተክርስቲያን በላካቸው በሦስቱ መልእክታት ውስጥ “መንፈስ ለአብያተክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ” በማለት ይህን ምክር የሰጠው ድል ለነሱት ብቻ ሳይሆን ለሁሉም አማኞች ነበር፤ ምክንያቱም ቃሉን የተናገረው ለድል ነሺዎች ከሰጠው የተስፋ ቃል በፊት ስለነበር ነው፡፡ ስለሆነም መንፈስ ለአብያተክርስቲናት የሚለውን ሊሰሙ የሚችሉ የውስጥ ጆሮ ያላቸውን አማኞች ከመላው ጉባኤ ውስጥ ይጠብቅ ነበር፡፡ ለትያጥሮን ቤተክርስቲያን እና ቀጥለው ለሚገኙት ሦስት መልእክታት ግን ይህን ምክር ለድል ነሺዎቹ ከሰጠው ተስፋ በኋላ ይናገራል፡፡ ምክንያቱም መንፈስ የሚለውን ለመስማት ጆሮ እንዳላቸው ያየው ድል ነሺዎቹን ብቻ ስለሆነ ነው፡፡ ለአንዷ ለትያጥሮን ቤተክርስቲያን ቅሬታዎች የተላለፈውን መልእክት መንፈስ ቅዱስ የተናገረው አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዲጠቀሙበት መሆኑን የቃሉ አገላለጽ ያመለክታል፡፡ ስለሆነም ”ነብይ ነኝ” የምትለውን ነገር ግን የጌታን ባሪያዎች እንዲሴስኑና ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉ ወይም የጣዖት ማኅበርተኛ እንዲሆኑ የምታደርገውን ያቺን ሴት ኤልዛቤልን ቸል እንዳይል፣ ከእርሷ ጋር ያመነዘሩትም ንስሐ እንዲገቡ፣ የተላለፈውን መልእክት ተቀብለው ሌሎቹም አብያተክርስቲያናት ሊጠቀሙበት ይገባል፣ እንደዚሁም በኤልዛቤልና በልጆች ላይ የተነገረውን ከባድ ፍርድ አውቀው ከወዲሁ ጌታ ላስተላለፈው መልእክት መታዘዝ ይጠበቅበቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለቅሬታዎቹ ወይም ለድል ነሺዎቹ የተሰጠውን የከበረ ተስፋ በመመልከት በዙሪያቸው ያለውን የኤልዛቤልን ሥራ ድል ለመንሳት መበርታት ይገባቸዋል፡፡ መንፈስ ለትያጥሮን ቤተክርስቲያን ድል ነሺዎች የተናገረውን ሁሉ ለእኛም ነው ብለው በልብ ጆሮአቸው መልእክቱን የሰሙ ሁሉ የተሰጠው ለእነርሱ የከበረ ተስፋ ባለቤት ይሆናሉ፡፡
ለታሪካዊ ገለጻው የተጠቀምንበት ዋቢ፡ክፍል አምስት>>>>
Miller’s Church history by, Andrew Miller, pp 291-314, 324-357, 499-503, 533-547, 1999