ቤተክርስቲያን/Aclesia  

ክፍል 5

በሰርዴስ ላለች ቤተክርስቲያን የተላከች መልእክት


> ሰርዴስ በእስያ ከነበሩ አገሮች አንዷ የነበረችው የልድያ ዋና ከተማ ነበረች በአሁኑ ጊዜ በእስያ ውስጥ ባለው የቱርክ ግዛት በምዕራባዊ ዳርቻ የምትገኘው ሳርት (Sart) የተባለች አነስተኛ መንደር ሰርዴስ በነበረችበት ስፍራ ትገኛለች፡፡ በሰርዴስ ወንጌል እንዴት እንደደረሰ የተመዘገበ ነገር ባይኖርም በጳውሎስም ሆነ በለሌሎች የወንጌል አገልጋዮች በእስያ ወንጌል በተሰበከ ጊዜ እንደሆነ መረዳት ይቻላል (የሐ.ሥ.19፡10)፡፡ በሰርዴስ የነበረችው ቤተክርስቲያን በእስያ ከነበሩት ሰባት አብያተክርስቲያናት (1ቆሮ.16፡19፤ ራእ.1፡11) አንድዋ የነበረች ስትሆን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በባሪያው በዮሐንስ በኩል ለሌሎቹ አብያተክርስቲያናት መልእክታትን እንደላከ ሁሉ ለእርስዋም ልኮላታል፡፡ በራእይ ምዕ.3 ከቁ1-6 ድረስ የሚገኘውን ይህን መልእክትም ቀጥሎ እናጠናለን፡፡

“በሰርዴስም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስትና ሰባቱ ከዋክብት ያሉት እንዲህ ይላል፦” (ራእ.3:1)፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰርዴስ ላሉ አማኞች ራሱን ያቀረበላቸውን “ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስ እና ሰባቱ ከዋክብት ያሉት” ሆኖ ነው፡፡ “ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስት” የሚለው አገላለጽ በዮሐንስ ራእይ ውስጥ በሌሎች ክፍሎች ውስጥም ይገኛል (1፡5፤ 4፡5፤ 5፡6)፡፡ በተለይ በራእይ 1፡5 ላይ ዮሐንስ ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ያቀረበውን ሰላምታ ስንመለከት “ካለውና ከነበረው ከሚመጣውም፥ በዙፋኑም ፊት ካሉት ከሰባቱ መናፍስት፥ ከታመነውም ምስክር ከሙታንም በኵር የምድርም ነገሥታት ገዥ ከሆነ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።” ብሏል፡፡ በዚህ ቃል ውስጥ “ሰባቱ መናፍስት” የተባለው አንድ መለኮት ከሆኑት ከሦስቱ አካላት አንደኛው አካል ሆኖ ቀርቧል፡፡ ስለሆነም “ሰባቱ የእግዚአብሑር መናፍስት” ከሥላሴ አንዱ የሆነው መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ በእርግጥ በኤፌ.4፡4 ላይ “አንድ አካል አካልና አንድ መንፈስ አለ” ስለሚል መንፈስ ቅዱስ አንድ እንጂ ሰባት አይደለም፡፡ ይሁንና ራሱን በሚገልጥባቸው ሥራዎቹ አንዱ መንፈስ በሰባት መንገድ ተገልጦ ይታያል፡፡ ለምሳሌ በኢሳ.11፡2 ላይ በመሢሑ ላይ ስለሚያርፈው መንፈስ የተነገረው ቃል “የእግዚአብሔር መንፈስ፥ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፥ የምክርና የኃይል መንፈስ፥ የእውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል” ይላል፡፡ በዚህ ጥቅስ ውስጥ የተሰመረባቸው ሰባት ነገሮች የመንፈስ ቅዱስ ማንነትና ሥራ የተገለጠባቸው ናቸው፡፡ ስለሆነም ክርስቶስ “ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስት ያሉት” ሆኖ ሲቀርብ በመለኮታዊ ፍጹምነት ሁሉንም የሚሠራው መንፈስ ቅዱስ የእርሱ መንፈስ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ እንዲሁም ጌታ ኢየሱስ ራሱን “ሰባቱ ከዋክብት ያሉት” በማለት ለሰርዴስ አማኞች ያስተዋውቃል፡፡ ለኤፌሶን ቤተክርስቲያን በላከው መልእክት ውስጥ “በቀኝ እጁ ሰባቱን ከዋክብት የያዘው” ብሎ ራሱን እንደገለጠ እናስታውሳለን (ራእ. 2፡1)፤ በራእ.1፡20 ላይ እንደተገለጸው እነዚህ ከዋክብት የሰባቱ አብያተክርስቲያናት መላእክት ሲሆኑ እነርሱም የሰማይ መላእክት ሳይሆኑ በሰባቱ አብያተክርስቲያናት የነበሩት የክርስቶስ መልእክተኞች መሆናቸውን ቀደም ሲል ማብራራታችን ይታወቃል፡፡ ክርስቶስ “ሰባቱን ከዋክብት በቀኝ እጁ የያዘ” መባሉ የእርሱ መልእክተኞች በእርሱ ኃይል እና ሥልጣን ሥር መሆናቸውን ሲያመለክት፣ “ሰባቱ ከዋክብት ያሉት” ሲል ደግሞ የእርሱ መሆናቸውን ብቻ ትኩረት ሰጥቶ የሚገልጥ ነው፤ ማለትም እርሱ በአብያተክርስቲያናት ያሉት በጌታ የሚገዙ(የሚያተዳደሩ) ወንድሞች፣ ወንጌል ሰባኪዎች፣ እረኞችና እስተማሪዎች ባለቤት መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ይህም እነዚህ አገልግሎቶች በሰው ሐሳብ በተፈጠሩ የሹመት ሥርዓቶች እንዲያዙ በተደረጉባቸው ስፍራዎች ከክርስቶስ እጅ (በሥልጣኑ ሥር ከመሆን) ብቻ ሳይሆን የእርሱ ከመሆንም እየወጡ እንዳሉ ለሚያስተውሉ ሁሉ ትምህርት የሚሰጥ ነው፤ ይህን ያስተዋሉ ሁሉ በአገልግሎቱ በመደቧቸውና ክፍያ በሚያከናውኑላቸው አካላት ባለቤትነት ሥር ከመሆን ወጥተው የክርስቶስ መሆናቸውን በሚያረጋግጥ መልኩ ሊያገለግሉ ይገባቸዋል፡፡

“ሥራህን አውቃለው፤ ሕያው እንደመሆንህ ስም አለህ፤ ሞተህማል”(3፡1)

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ቃል ውስጥ የሚናገረው በሰርዴስ ባለች ቤተክርስቲያን ያሉ አማኞችን ሥራ በተመለከተ ነው፡፡ በእርሱ ፊት የማይታወቅ ነገር የለም፤ በሰርዴስ ቤተክርስቲያን ውስጥ የነበረው አማኝ “ሕያው ነው” የሚል ስም ብቻ ነበረው፡፡ በሥራው ሲታይ ግን የሞተ ነበረ፡፡ የሰርዴስ ቤተክርስቲያን በውጫዊ ቅርጿ ስትታይ እንደ ትያጥሮን ቤተክርስቲያን ለሁሉ የተገለጠ ክፋት አይታይባትም፤ ለሰው ስትታይ የክርስቶስን እውነት የያዘች ትመስላለች፤ ክርስቶስ ግን ወደ ውስጥ ዘልቆ ያያል፤ በሰርዴስ ቤተክርስቲያን ማስመሰል እየተሸፈነ ከእርሱ ተሰውሮ የሚቀር ሥራ የለም፡፡ ሁሉንም ሥራ ያውቃል፡፡ እርሱ በሚያውቀውና በተነገረው መሠረት የሰርዴስ አማኝ በስም ብቻ ሕያው ሆኖ በሥራ ግን የሞተ ነበር፡፡ ይህ አፍኣዊ ክርስትና ደግሞ የጌታን ልብ በእጅጉ የሚያሳዝን ነው፡፡ ጌታ ማየት የሚፈልገው በሥራ የተገለጠ እምነት ነው፡፡ በያዕ.1፡22 ላይ “ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ” ይላል፡፡ ቃሉን በደስታ የሚሰሙ ሰዎች በውጫዊ ሁኔታቸው ከንፈር መምጠጥና ማድነቅ የሚያዘወትሩ፣ በአፍ “ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ!” የሚሉ ለሰው ሲታዩ ሕያው ክርስትና ያላቸው የሚመስሉ ሲሆኑ በተግባር ግን የሞቱ ናቸው፡፡ በሰርዴስ የነበረው አብዛኛው ሁኔታ እንደዚህ ነበር ለማለት ይቻላል፡፡ ጌታችን “ሕያው እንደመሆንህ ስም አለህ ሞተህማል” ሲል ቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ይህ ሁኔታ እንዳለ በስም ሕያው ሆኖ በተግባር ግን የሞተ ነገር እንዳለ የሚያመለክት ነውና፡፡

“ሥራህን በአምላኬ ፊት ፍጹም ሆኖ አላገኘሁትምና የነቃህ ሁን፥ ሊሞቱም ያላቸውን የቀሩትን ነገሮች አጽና” (ራእ.3:2)

በዚህ ቃል ውስጥም ጌታ ኢየሱስ ትኩረት የሰጠው በሰርዴስ ባለች ቤተክርስቲያን ስለነበረው ሥራ ነው፡፡ እዚህ ላይ የተነገረው ሥራም ቀጥሎ ባለው ንባብ “የቀሩት ነገሮች” የተባሉትን የሚያመለክት ነው፡፡ በሰርዴስ ቤተክርስቲያን ብዙዎቹ ነገሮች የሞቱ ሲሆኑ የቀሩት ጥቂት ነገሮች ደግሞ ”ሊሞቱ ያላቸው” ነበሩ፡፡ እነዚህ ነገሮችም በሰርዴስ ውስጥ የተሠሩት የቀሩ ጥቂት መልካም ሥራዎች ናቸው፡፡ “ምንም የተሠራ ሥራ የለም” አላለም፡፡ ነገር ግን “ሥራህን በአምላኬ ፊት ፍጹም ሆኖ አላገኘሁትም” አለ፡፡ ይህም ከልብ ባልሆነ መልኩ፣ የእምነትና የፍቅር ኃይል በሌለበት በዛለና ተስፋ በቆረጠ መንፈስ የሚሠራ ሥራ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ይሁንና ይህም ቢሆን ጨርሶውኑ ከሚጠፋ በእግዚአብሔር ፊት ፍጹም እንዲሆን ለማድረግ መንቃት እንደሚገባ ጌታ ያሳስባል፤ ሊሞቱ ያላቸውን ጥቂት ነገሮች ሕያውነት እንዲኖራቸው ማጽናት እንደሚያስፈልግ ይነግራቸዋል፡፡ በቤተክርስቲያን ደረጃ የሚሠሩ ሥራዎች እየተሠሩ ያሉት በግዴለሽነት ወይም ሥራዎቹ ተሠርተዋል እንዲባሉ ያህል ብቻ ከሆነ ልብን የሚያይ ጌታ አይባርካቸውም፡፡ እርሱ የቤተክርስቲያን ራስ እንደመሆኑ በእያንዳንዷ ጉባኤ በስሙ እየተሠራ ያለውን ሥራ ይቆጣጠራል፤ ሥራውንም የሚመዝነው በሰዎች እይታ ወይም በሰዎች መስፈርት ሳይሆን በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ይታያል? በሚለው መስፈርት ነው፤ ጌታ በሰርዴስ ቤተክርስቲያን ያለውን ጥቂት መልካም ሥራ ሲመለከት “በአምላኬ ፊት ፍጹም ሆኖ አላገኘሁትም” ነው ያለው፡፡ ስለዚህ በመንፈሳዊ ነገር የነቃን ሆነን የቀሩትን ጥቂት መልካም ነገሮች ለማጽናት በእግዚአብሔር ፊት ሲታይ ሥራው ምን ያህል ተቀባይነት አለው የሚለውን ማሰብ ይገባል፡፡

“እንግዲህ እንዴት እንደ ተቀበልህና እንደ ሰማህ አስብ፥ ጠብቀውም ንስሐም ግባ” (ራእ.3:3)

በሰርዴስ ባለች ቤተክርስቲያን የነበሩ አማኞች የሞተ ነገር ውስጥ ያሉ ቢሆንም በመጀመሪያ ላይ ግን የእውነትን ቃል ተቀብለውና ሰምተው እንደነበር በዚህ ቃል እንረዳለን፡፡ ይሁንና የእግዚአብሔር ቃል በአእምሮ እውቀት ብቻ የሚያዝ ከሆነ ሕይወት ሊሰጥ አይችልም፤ “…ዳሩ ግን የሰሙት ቃል ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሐደ አልጠቀማቸውም” (ዕብ.4፡2)። በሰርዴስ የነበሩ አማኞች ችግር የእግዚአብሔርን ቃል አለማወቅና አለመቀበል አልነበረም፤ እውቀቱ አለ፤ እውነታውም አሳምኗቸዋል፤ ስለሆነም ላሉበት ውድቀት ምንም ምክንያት የላቸውም፡፡ በመሆኑም የእውነትን ቃል እያወቁ አብዛኛው ነገራቸው የሞተ በመሆኑ እና ጥቂት የቀረ ነገራቸውም ሊሞት ያለው በመሆኑ ተጠያቂነታቸውን ያከብደዋል፤ አውቀው ቸልተኞች ሆነዋልና፡፡ ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እርሱ ይመለሱ ዘንድ ጥሪን ያቀርብላቸዋል፡፡ ራሳቸውን ቆም ብለው በመመልከት ቀደም ሲል የተቀበሉትን የቃሉን እውቀት እንዲያስታውሱ “እንዴት እንደተቀበልህና እንደሰማህ አስብ” ይላቸዋል፤ “አስብ” የሚለው ቃል በመጀመሪያ የተቀበሉትንና የሰሙትን እውነት ፈጽሞ ወደ ጎን ትተው እንደነበር ያሳያል፤ ጌታ ግን ወደ ልባቸው ተመልሰው እንዲያስቡት በግልጽ ይመክራቸዋል፡፡ በዚህም በቻ ሳያበቃ “ጠብቀውም” ይላቸዋል፡፡ ይህም ተግባራዊነቱን የሚመለከት ነው፡፡ ቃሉን መስማትና ማወቅ ያንንም ማስታወስ ብቻውን ጌታን አያረካውም፤ በተግባር መጠበቁንም ይፈልጋል፤ በሌላ ስፍራ “ትእዛዛቱንም ብንጠብቅ በዚህ እንዳወቅነው እናውቃለን፤ አውቄዋለሁ የሚል ትእዛዛቱንም የማይጠብቅ ውሸተኛ ነው፤ እውነትም በእርሱ ውስጥ የለም።” ተብሎ ተጽፏል (1ዮሐ.2፡3-5) ፡፡ በመቀጠል ደግሞ “ንስሐ ግባ” ብሏቸዋል፡፡ ንስሐ ቀደም ሲል በነበረው አለመታዘዝ ላይ መፍረድ በመሆኑ በሰርዴስ የነበሩ አማኞች በቀደመው ውድቀታቸው እንዲጸጸቱና እንዲፈርዱበት የሚያሳስብ ነው፡፡ በእርግጥም አብዛኛው ነገራቸው እንደሞተ አውቀው አስቀድሞ ሰምተውትና ተቀብለውት የነበረውን የእግዚአብሔርን ቃል በማሰብ ወይም በማስታወስ ራሳቸውን ካዩ ንስሐ መግባት እንዳለበቸው ይገነዘባሉ፡፡ ጌታ የሰማነውንና የተቀበልነውን እውነት አስታውሰን ወደ መታዘዝ መምጣታችን የሚያስደስተውን ያህል በቀደመው አለመታዘዛችን ላይ እንድንፈርድበት ይፈልጋል፡፡ እርሱ ጻድቅ እንደመሆኑ ይህን እናደርግ ዘንድ ይጠብቅብቀናል፡፡

“እንግዲያስ ባትነቃ እንደ ሌባ እመጣብሃለሁ በማናቸውም ሰዓት እንድመጣብህ ከቶ” (ቁ.3)

በስም ብቻ ሕያው ነው ሲባል የነበረው ነገር ግን “ሞተህማል” የተባለው አብዛኛው የሰርዴስ ቤተክርስቲያን አማኝ ጌታ በማያምነው ዓለም ላይ የሚፈርደው ፍርድ ይጠብቀዋል፤ ይህንንም “እንግዲያስ ባትነቃ እንደሌባ እመጣብሃለሁ” በሚለው ቃል እንረዳለን፤ ምክንያቱም “እንደ ሌባ” የሚመጣባቸው በሚጠፉትና በጨለማ ላሉት ላይ እንጂ በቅዱሳን ላይ እንዳልሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር “ወንድሞች ሆይ፥ ስለ ዘመናትና ስለ ወራት ምንም እንዲጻፍላችሁ አያስፈልጋችሁም፤ የጌታ ቀን፥ ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ፥ እንዲሁ ይመጣ ዘንድ ራሳችሁ አጥብቃችሁ አውቃችኋልና። ሰላምና ደኅንነት ነው ሲሉ ያን ጊዜ ምጥ እርጕዝን እንደሚይዛት ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል ከቶም አያመልጡም። እናንተ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ቀኑ እንደ ሌባ ይደርስባችሁ ዘንድ በጨለማ አይደላችሁም፥ ሁላችሁ የብርሃን ልጆች የቀንም ልጆች ናችሁና” (1ተሰ.5፡1-5) ይላል፡፡ ስለሆነም የስም አማኞች እንደማያምኑ ሰዎች እንደሚቆጠሩ እንገነዘባለን፡፡ “ስም አለህ ሞተህማል” የተባሉትም ለዚህ ነው፡፡ ሆኖም ጌታ በፍርድ ከመገለጡ በፊት “የነቃህ ሁን፥ ሊሞቱም ያላቸውን የቀሩትን ነገሮች አጽና” የሚል ጥሪዎች አስቀድሞ አቅርቦ ነበር፤ በስም ብቻ ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች በተለይ “የነቃህ ሁን” የሚለውን ማሳሰቢያ ተግባራዊ ሊያደርጉት ይገባል፡፡ ሰዎችን በከንቱ በሚያስመካ አስመሳይነትና አፍኣዊነት ላይ መንቃት ሊሞቱ ያሉትን የቀሩ ነገሮች ለማጽናትን እውነተኛ ንስሐ ለመግባት መነሻ ይሆናቸዋል፤ ሰዎች በአፍኣዊ ክርስትና ላይ ካልነቁ ግን ለንስሐ አይበቁም፡፡ በስም ብቻ ሕያው ነን እያሉ ሰዎች በሚመኩበት አስመሳይነትና ግብዝነት ላይ ሳይነቁ ልክ ነኝ እያሉ በስህተት አሠራርና በሞተ ሥራ በእልከኝነት መቀጠል የንስሐን መንገድ ይዘጋል፤ ስለሆነም ጌታ “እንግዲያስ ባትነቃ እንደሌባ እመጣብሃለሁ” ብሏል፡፡ ስለሆነም በአስመሳዩ ክርስትና ላይ አለመንቃት ቀጥተኛውን ተመጣጣኝ ፍርድ ያገኛል፡፡ ሌባ ሲመጣ ሰዎቹ በማያውቁት ሰዓት በመሆኑ ሊነቁ እንደማይችሉ ሁሉ ጌታም የሚመጣበትን ሰዓት እንዳይታወቅ አድርጎታል፡፡ ይህ የእርሱ የሆኑትን ቅዱሳን የሚያሰጋም የሚያስፈራም አይደለም፤ “በማናቸውም ሰዓት እንድመጣብህ ከቶ አታውቅም” የሚለው የጌታ ቃል የሚስፈራው ለሚመጣላቸው ቅዱሳን ሳይሆን ለሚመጣባቸው አስመሳዮች ነውና፡፡

“ነገር ግን ልብሳቸውን ያላረከሱ በሰርዴስ ጥቂት ሰዎች ከአንተ ጋር አሉ፥ የተገባቸውም ስለ ሆኑ ነጭ ልብስ ለብሰው ከእኔ ጋር ይሄዳሉ።” (ቁ.4)

ጌታ ኢየሱስ በሰርዴስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ያለውን የመልእክቱን ተቀባይ በዚህ ንባብ “ልብሳቸውን ያላረከሱ” ከሚላቸው ጥቂት ሰዎች ጋር አይቆጥረውም፡፡ እነዚህ ልብሳቸውን ያላረከሱ ሰዎች በቁጥር ጥቂት ከሆኑ አብዛኛው የሰርዴስ ቤተክርስቲያን ክፍል “ሕያው እንደመሆንህ ስም አለህ ሞተህማል” የተባለው እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ካላመነው ዓለም ጋር ሊፈረድበት የሚገባው ለዚህ ነው፡፡ ሆኖም አብዛኛው ክፍል የአፍ አማኝ በሆነበት ማኅበር መካከል የጌታ የሆኑ፣ ልብሳቸውን ያላረከሱ ጥቂት ሰዎች መገኘታቸው በእጅጉ ውብና አስደሳች የሆነ ነገር ነው፡፡ “ልብሳቸውን ያላረከሱ” ማለት ምን ማለት ነው? “ልብሳቸውን ያላሳደፉ” ማለት ነው፡፡ እዚህ ላይ የተጠቀሰው ልብስ የሰውነት ማንነታቸው እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ በያዕ.1፡27 “ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው፤ ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ፥ በዓለምም ከሚገኝ እድፍ ሰውነቱን መጠበቅ ነው” ይላል፡፡ ከዚህ ቃል አኳያም አማኝ ሰውነቱን (ልብሱን) በዓለም ከሚገኝ እድፍ መጠበቅ ይገባዋል፡፡ በይሁ.1 ቁ.23 ላይ ደግሞ “አንዳንዶችንም እንኳ እየጠላችሁ በፍርሃት ማሩ” ይላል፤ ስለሆነም ለምስክርነት እንኳ ወደ ዓለማውያን ስንቀርብ “በሥጋ የረከሰውን ልብስ” ተብሎ የተጠቀሰውን ሥጋዊና ዓለማዊ ማንነት እየጠላን መሆን እንዳለበት ያሳስበናል፡፡ በሰርዴስ በነበረች ቤተክርስቲያን ውስጥም ይህን ያደረጉ ጥቂት አማኞች ተገኝተዋል፤ እነርሱም “የተገባችውን” ብድራት ይቀበላሉ፡፡ ይኸውም “ነጭ ልብስ” ተብሎ ተገልጧል፡፡ ነጭ ልብስ እድፍ የማይታይበት ልብስ ነው፡፡ ነጭ ልብስ የለበሰ ሰው በተመልካቹ ሁሉ ፊት ንጹሕ ሆኖ ይታያል፡፡ እነዚህ በምድር ላይ ልብሳቸውን ማለት ማንነታቸውን ያላረከሱ ቅዱሳን በሰማይ በእግዚአብሔር ፊት ንጹሐን ሆነው በክብር የሚታዩ መሆናቸውን የሚመለከት ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ “የተገባቸው ስለሆነ ነጭ ልብስ ለብሰው ከእኔ ጋር ይሄዳሉ” በማለት እነዚህን ሰዎች ከእርሱ ጋር ቈጥሮ ከእርሱ ጋር እንደሚወስዳቸው ተናግሯል፤ እርሱ ለቅዱሳኑ ሲመጣ ራሳቸውን ከዚህ ዓለም ርኵሰት የጠበቁትን ሁሉ ከእርሱ ጋር ቈጥሮ በእርሱ ክብር ሊያከብራቸው ወደ ራሱ ይወስዳቸዋል (ዮሐ.14፡3)፡፡ ስለሆነም በሰርዴስ እንደነበሩት እንደነዚህ ጥቂት ቅሬታዎች ልብሳቸውን ያላረከሱ ሆነን መጠባበቅ አለብን፡፡ “እንግዲህ፥ ወዳጆች ሆይ፥ የዚህ ተስፋ ቃል ካለን፥ በእግዚአብሔር ፍርሃት ቅድስናን ፍጹም እያደረግን ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ፡፡” ተብሎ እንደተጻፈ (በ2ቆሮ.7፡1)፡፡

በሰርዴስ በነበረች ቤተክርስቲያን ያለውን ሁኔታ በትንቢታዊ ገጽታው ስንመለከተው ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በምዕራብ ቤተክርስቲያን የተነሣውን የተሐድሶ እንቅስቃሴ እና ከዚያ በኋላ የታየውን ውድቀት የሚያመለክት እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ተሐድሶው በተጀመረ ጊዜ ለዘመናት ተረስተውና ተጥለው የነበሩ የእግዚአብሔር እውነቶች ተገልጠው ነበር፡፡ የዚህም ምክንያቱ መጽሐፍ ቅዱስ ብቸኛው የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ከመቀበልና መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ የእምነት መመሪያ ከማድረግ የመጣ ነበር፤ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ ወደተለያዩ ቋንቋዎች እየተተረጐመ፣ የሚያስተምሩ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም አማኞች እንዲያጠኑት በመደረጉ የእግዚአብሔርን እውነት ለዘመናት ከተከማቸው የሰው ሐሳብ፣ የሰው ትምህርትና የሰው ሥርዓት ለመለየት ጥረት በመደረጉ ነው፡፡ ይህ መልካም አገልግሎት ብዙም ሳይቆይ ከዓለማዊ ልማዶችና አሠራሮች ጋር በመደባለቁ በኋላ ላይ ቢሞትም በጅማሬው ላይ ግን የእግዚአብሔርን ቃል መሠረት ያደረገ ነበር፤ ጌታ ለሰርዴስ ቤተክርስቲያን “እንዴት እንደተቀበልህና እንደሰማህ አስብ” ብሎ የተናገረው ቃልም ይህ የተሐድሶ ዘመን ክርስትና አጀማመሩ የእግዚአብሔርን ቃል የተከተለ እንደነበር ለማሳየት የሚያስችለን ቃል ነው፡፡

በዚያ ዘመን ከእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ከተገለጡት እውነቶች መካከል በተለይ ሰው የሚጸድቀው በራሱ የጽድቅ ሥራ ሳይሆን፣ በእምነት በሚገኝ የእግዚአብሔር ጽድቅ መሆኑን የሚናገረው እውነት መሠረታዊና ጐልቶ የሚታየው ነበር፡፡ ይህንን ሁኔታ በመግለጥ በኩል በቤተክርስቲያን ታሪክ ተጠቃሽ የሆነው ጀርመናዊው “ማርቲን ሊተር”(1483-1546) ነበር፡፡ ሉተር በኤርፈርት(Erfurt) ዩኒቨርስቲ የተማረና በፍልስፍና ዶክተር የነበረ ሰው ቢሆንም በዚያው በኤርፈርት ውስጥ በሚገኝ የአውግስጢኖስ ገዳም የኖረ መነኵሴም ነበር፡፡ እልፍኙን ዘግቶ በጾምና በጸሎት ራሱን ስቶ እስኪወድቅ ድረስ በራሱ ላይ ባደረገው መጐሳቆል ጽድቅን ወይም መዳንን ለማግኘት ከልቡ የሚጥር ሰው ነበረ፤ ነገር ግን ከቆይታ በኋላ ጽድቅ በእምነት (Justification by faith) መሆኑን ከመጽሐፍ ቅዱስ ተረዳ፤ ሉተር መጽሐፍ ቅዱስን ለመጀመሪያ ጊዜ ያየው በኤርፈርት (Erfurt) ዩኒቨርሲቲ በመማር ላይ ሳለ በላይብራሪ ውሰጥ ሲሆን የሐናንና የሳሙኤልን ታሪክ የመሳሰሉ አስደሳች ታሪኮች ከማንበብ በቀር በአግባቡ አልተረዳውም ነበር፤ ሆኖም የእግዚአብሔር ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን እውነት ለማወቅ ከፍተኛ ጥማትና ጉጉት ነበረበት፤ በአውግስጢኖስ ገዳም በነበረ ጊዜ ራሱን ከሚገባ በላይ በማጎሳቆል ጽድቅን ለማግኘት እየጣረ ሳለ ገዳሙን ለመጎብኘት ወደዛ መጥቶ የነበረው ጆን ስታውፒትዝ (Jhon Staupitz) የተባለ የጳጳስ ምክትል የነበረ ሰው ሉተርን ባገኘው ጊዜ በራሱ ሥራና ስዕለት በእግዚአብሔር ፊት መቆም እችላለሁ ብሎ ማሰቡ ስህተት መሆኑንና መዳን የሚችለውም በክርስቶስ ደም ላይ ባለ እምነት ምክንያት ወደ እርሱ በሚመጣ የእግዚአብሔር ምሕረት ብቻ መሆኑን ነገረው ከዚያም “ቀዳሚ ተግባርህ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ይሁን” ብሎ መከረውና መጽሐፍ ቅዱስን በስጦታ አበረከተለት፡፡ ይህም ሉተርን በእጅጉ የረዳው ቢሆንም ስለነፍሱ መዳን ግን ገና እርግጠኛ አልነበረም፤ በገዳም ውስጥ መኖር በጀመረ በ2ኛው ዓመት በአደገኛ በሽታ ታሞ በነበረ ጊዜ እንደቀድሞው ሁሉ ፈርቶና ተንቀጥቅጦ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ሊጠይቁት ወደ እርሱ የመጡት አንድ ሽማግሌ መነኵሴ የኃጢአት ይቅርታ ለማግኘት እምነት በቂ መሆኑን ነገሩት፤ ይህም ሉተርን በእምነት ስለመጽደቅ እንዲያስብ የረዳው ሌላ ምክር ነበር፡፡

ሆኖም ሉተር ጽድቅ በእምነት ስለመሆኑ የመጽሐፍቅዱስ ማረጋገጫ ያገኘው ከ3 ዓመት የገዳም ቆይታ በኋላ ወደ ዊተምበርግ (Wittemberg) ሄዶ የመጽሐፍቅዱስ አስተማሪ በነበረበት ጊዜ ነበር፡፡ በ1508 በሳክሰኒው በፍሬድሪክ ዘዋይዝ (Frederic the Wise of Saxony) አማካኝነት የፍልስፍና አስተማሪ እንዲሆን ወደ ዊተንበርግ ተወስዶ ጎን ለጎን የቲዎሎጂ ትምህርት በመማር የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ ሆኖ ነበር፤ በዚያም በሮሜ 1፡17 ላይ “ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል” የሚለውን በሚያብራራ ጊዜ ይህ ቃል ቀደም ሲል በእምነት ስለመጽደቅ የተነገረውንና የሚያስበውን እውነት የሚያረጋግጥ መለኮታዊ ቃል መሆኑን ተረዳ፤ በዚህ ቃል ማስረጃነትም በእምነት ስለመጽደቅ የሚናገረውን የመጽሐፍቅዱስ እውነት ደጋግሞ በማስተማር በሥራ መጽደቅ እንደሚቻል ተደርጎ ለዘመናት ሲታሰብ የቆየውን የተለመደ አስተሳሰብ በትምህርቱ መቀየር ጀመረ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሮም ካቶሊክ የኃጢአት ስርየትን በተመለከተ የነበረው አስተሳሰብ ኃጢአትን የሠራ ማንኛውም ሰው እንደሠራው ኃጢአት ዓይነት በሚከፍለው የገንዘብ መጠን መሠረት በፖፑና በጳጳሳቱ ሥልጣን የኃጢአት ስርየትን እንደሚያገኝ የሚገልጽ ነበር፡፡ ይህ የኃጢአት ስርየትን (Indulgences) በገንዘብ የመሸጥ ተግባር ቀደም ሲል ከ1300 ዓ.ም. ጀምሮ በሮም የተጀመረ ሲሆን የክርስቶስ መቃብር የሚገኝባት ኢየሩሳሌም በቱርኮች እጅ ከወደቀች በኋላ ሮምን እንደ ኢየሩሳሌም ቅድስት ሀገር ለማድረግ ሲባል የተደረገ ነበር፤ ሮም የጴጥሮስና የጳውሎስ መቃብር የሚገኝባት የሚል ምክንያትን በመጠቀም በቀላል የገንዘብ ክፍያ የኃጢአት ስርየት የሚገኝባት እንደሆነች በማስተዋወቅ የተጀመረ ብዙ ገንዘብን የማሰባሰቢያ ስልት ነበር፤ ይህም የኃጢአት ስርየት ሽያጭ በመጀመሪያ ላይ በየ100 ዓመቱ በሚከበር በኢዮቤልዩ በዓል ላይ እንዲከናወን ታስቦ የተጀመረ ቢሆንም በኋላ ላይ ግን ጊዜው ስለረዘመባቸው በየ50 ዓመቱ ቀጥሎ በየ33 ዓመቱ ከዚያም በየ25 ዓመቱ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ በዚሁ ልማድ መሠረት በእነሉተር ጊዜም በሲኦል ያለውን የእሳት ቅጣት ለማቅለል ወይም ለማስቀረት በማለት የኃጢአት ስርየት ሽያጭ ይደረግ ነበር፡፡ ዋናው ምክንያት ግን በጊዜው የነበረው ልዮን 10ኛ (1575-1521) የተባለው የሮም ፖፕ በገቢ ማስገኛ ዘዴነቱ ለመጠቀም ያደረገው እንደሆነ ከታሪኩ መረዳት ይቻላል፤ በ1513 ወደ መንበረ ጵጵስና የመጣው ልዮን 10ኛ በመቀማጠል የሚኖርበትን የመንበረ ጵጵስናውን ወጪ ለመሸፈንና በጊዜው በመሠራት ላይ የነበረውን “የቅዱስ ጴጥሮስ ካቴድራል” ግንባታን ለማስፈጸም የሚያስችል ገንዘብ ለማግኘት ብሎ ያደረገው ነበር፤ እንደ ጀርመን ባሉ በሌሎች ሀገሮች የሚኖሩ ሰዎች የኃጢአት ስርየት ሽያጩ እንዳያመልጣቸው በሚል በየሀገሩ እየተዘዋወሩ የፖፑ ፊርማና ማኅተም ያለበትን በተለያዩ ኃጢአቶች መሠረት ዋጋ የተተመነለትን የኃጢአት ስርየት ደብዳቤ የሚሸጡ መልእክተኞች በመላው አውሮፓ ተሰማርተው ነበር፡፡ ይህም ደብዳቤ ለሀብታሞቹ በብራና ለድሆቹ በተራ ወረቀት ተዘጋጅቶ ቀርቦ ነበር፡፡ በጊዜው ማርቲን ሉተር ወደነበረባት ወደ ጀርመኗ ዊተምበርግ (Wittemberg) ለዚሁ ተልእኮ መጥቶ የነበረው ጆን ቴትዝል (Jhon Tetezl) የተባለ መነኵሴ ነበር፡፡ ይህም ሰው በሰረገላ ላይ ተቀምጦ በእጁ ትልቅ ቀይ “መስቀል” ይዞ በብዙ የሃይማኖት ሰዎችና በሙዚቃ ታጅቦ፣ የኃጢአት ስርየት ብዙም ሳይደክሙ አነስተኛ ገንዘብ በመክፈል ብቻ በፖፑ ሥልጣን እንደሚገኝ በመስበክ የተዋጣለት ሰው ሆኖ ነበር፤ ኃጢአትን በአነስተኛ ገንዘብ ማስወገድ ይቻላል የሚለው ይህ የሐሰት ትምህርት የትኛውም ዓይነት ክፋትና ርኵሰት እየባሰ እንዲሄድ በማድረግ ከራሳቸው ከጳጳሳቱና ከመነኰሳቱ ጀምሮ በማኅበረሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ምግባረ ብልሹነት እንዲስፋፋ አድርጎ ነበር፡፡

በዚህ ጊዜ ሉተር ለአጠቃላይ የተሐድሶ እንቅስቃሴ በይፋ መጀመር ተጠቃሽ የሆነውን 95 ርእሶችን (ነጥቦችን) የያዘና የሮም ቤተክርስቲያንን የስህተት ትምህርትና አሠራርን የሚቃወም ጹሑፍ ጽፎ ኦክቶበር 31 ቀን 1517 ዓ.ም በየቤተክርስቲያኑ በራፍ ላይ በምስማር ሰቅሎ የኃጢአት ስርየት ሽያጩን ተቃወመ፡፡ ይህን በተመለከተ የጻፈው ቃልም “የፓፓው የኃጢአት ስርየት ሽያጭ ኃጢአትን ሊያስተሰርይ አይችልም፤ እግዚአብሔር ብቻውን ኃጢአትን ያስተሰርያል፤ በእውነት የሚናዘዙትን በሰው አናዛዥነትና አሳራጊነት የሚደረግ እርዳታ ሳይፈልግ እርሱ ይቅር ይላል፤ ቤተክርስቲያን ራሷ የጫነችውን ቅጣት ልታነሳ ትችላለች፤ ነገር ግን የቤተክርስቲያን ሥልጣን ከሞት በኋላ ሊቀጥል የማይችል በዚህ ዓለም ውስጥ ብቻ ያለ ሥልጣን ነው፤ ‘የኃጢአተኛው ሰው ነፍስ በብዙ ክራውን (crown) ገንዘብ ልትድን ትችላለች’ ለማለት ድፍረት ያለው ይህ ሰው ማን ነው? እያንዳንዱ እውነተኛ ክርስቲያን ያለ ኃጢአት ስርየት ደብዳቤ (Letter of Indulgence) በእግዚአብሔር ጸጋ በክርስቶስ በረከቶች ሁሉ ውስጥ ይሳተፋል” የሚል ነበር፡፡ ይህ ባለ 95 ነጥቦቹ የሉተር ጽሑፍ በጊዜው ለሕዝቡ የተሰራጨ ሲሆን፣ በ14 ቀን ውስጥ በመላው ጀርመን፣ በ4 ሳምንታት ውስጥም በመላው ክርስትና ዓለም እንደተዳረሰ ታሪኩ ያስረዳል፡፡ ጉዳዩም ከዊተንበርግ ጀምሮ በመላው የክርስትና ዓለም ውስጥ አነጋጋሪና ትልቅ መነቃቃትን የፈጠረ ሆኗል፡፡

ማርቲን ሉተር ብዙ መጻሕፍትን የጻፈ ሲሆን ከሁሉም ሥራዎቹ የሚበልጠው ግን መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ጀርመንኛ መተርጎሙ ነው፤ በ1521 ዓ.ም ከጥር እስከ ግንቦት ወር ድረስ ዎርም (Worm) በተባለ ቦታ በሉተር ምክንያት በተደረገ ትልቅ ስብሰባ እርሱንም ሆነ ትምህርቱን ለማጥፋት አዋጅ ታውጆበት ስለነበር ከዊተንበርግ ተወስዶ በዋርትበርግ በሚገኝ አንድ አገረ ገዢ ቤት (Wartburg Castle) ውስጥ ተሰውሮ በተቀመጠ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ጀርመንኛ መተርጎም ጀመረ፤ ከዚያም ወደ ዊተንበርግ በተመለሰ ጊዜ በ1522 ዓ.ም.አዲስ ኪዳንን አሳትሞ አሰራጨ፤ ብሉይ ኪዳንን ደግሞ በ1530 ተርጉሞ ካጠናቀቀ በኋላ በ1534 ዓ.ም. ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ታትሞ ተሰራጨ፤ ሉተር መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ጀርመንኛ የተረጎመ የመጀመሪያው ሰው ባይሆንም የእርሱ ትርጉም ግን በመላው ጀርመን ውስጥ በስፋትና በፍጥነት በመዳረሱ የሃይማኖት መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ማንኛውም ሰው ሊያነበውና ሊመረምረው ችሏል፡፡ ስለሆነም በቋንቋ ምክንያት ተሰውሮ የነበረው የእግዚአብሔር ቃል እውነት ለሁሉም ግልጽ ሆኖ ታየ፡፡ ለተሐድሶ አገልግሎትም ትልቁን አስተዋጽኦ ያደረገውም መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ሕዝቡ ቋንቋ መተርጎሙ ነው፡፡

ከጀርመን ውጪም ቢሆን በሌሎች የአውሮፓ አገሮች “ጽድቅ በእምነት” መሆኑን ከመጽሐፍ ቅዱስ በመረዳት የተሐድሶ ሥራን የሠሩ ሰዎች ነበሩ፡፡ ከእነዚህም መካከል የስዊትዘርላንዱ ኡልሪክ ዝዊንግል (Ulric Zwingle) (1484-1531) ተጠቃሽ ነው፤ ዝዊንግል ባስል (Basle) በተባች በሰሜን ስዊትዘርላንድ ባለች ከተማ የቲዎሎጂ ትምህርት በመማር ላይ እያለ የሮም ካቶሊክ ቤተክርስቲያንን ስህተት በግልጽ እየተናገረ ያስተምር ከነበረው ቶማስ ዊቴንባክ (Thomas Wittenbach) ከተባለው ሰው የቲዎሎጂ ትምህርት ተምሯል፡፡ እርሱና ሌሎች የትምህርት ባልጀሮቹ የክርስቶስ ሞት ብቻ የነፍሳቸው ቤዛ መሆኑን ተረድተው ነበር፡፡ ከዚያም ከ1506 ዓ.ም. ጀምሮ ግላሪስ (Glaris) በተባች ቦታ እያገለገለ ለ10 ዓመታት በቆየበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት በማጥናት ለወደፊቱ የተሐድሶ ሥራው ራሱን አዘጋጀ፤ በ1514 ዓ.ም. የጳውሎስን መልእክታትን በራሱ የእጅ ጽሑፍ ገልብጧል፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በየመድረኩ መጽሐፍ ቅዱስን በመስበክ ብዙ ተቀባይነት አገኘ፡፡ ከዚያም ከ1516-1518 ድረስም የኃጢአት ስርየት ይገኝበታል ተብሎ በካቶሊኮች በሚታመንበትና የኃጢአት ስርየትን ለማግኘት ከተለያዩ የአውሮፓ ክፍሎች ብዙዎች በሚጎርፉበት ኤይንዚደልን (Einsiedeln) በተባለ ስፍራ የሚገኝ የቪግሮ ኤረሚታና (Vigro Eremitana) ገዳም ውስጥ ለ3 ዓመታት ያህል ወንጌልን አገልግሏል፡፡ ዝዊንግል ከገዳሙ ኃላፊ ጀምሮ ሁሉም መጽሐፍቅዱስ እንዲያነቡ በማድረግ ሰዎች ለሥዕል ከመስገድ ክርስቶስን ወደ ማመን፣ ከሰው ልማድና ሥርዓት ንጹሕ ወደ ሆነው የወንጌል አስተምህሮ እንዲመጡ ጥረት አድርጓል፤ ሲሰብክም “የኃጢአትን ስርየት በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራና ምልጃ፣ ለማግኘት ፈልጉ እንጂ ከቡርክት ማርያም አትጠይቁ” ይል ነበር፡፡ ወደዚያ ስፍራ ከተለያየ አቅጣጫ በየክብረ በዓሉ ለሚመጡት ሁሉ “ክርስቶስ ብቻውን ያድናል፤ እርሱ በየትም ስፍራ ያድናል” ይላቸው ነበር፡፡ ይሁንና የሮም ፖፕ ልዮን 10ኛ እርሱን ከመቃወም ይልቅ በማባበልና በጥቅም ሸንግሎ መያዝን መርጦ ነበር፡፡ ከዚያም ከ1519 ዓ.ም. ጀምሮ ዙሪክ (Zurich) ወደተባለችው ታዋቂ ከተማ ተዛውሮ በአንድ ካቴድራል ውስጥ የወንጌል ስብከት ሥራውን ቀጠለ፤ ከዚያ በኋላም ዊተንበርግ ለሉተር የተሐድሶ እንቅስቃሴ ማዕከል እንደነበረች ሁሉ ዙሪክም ለዝዊንግል የተሐድሶ እንቅስቃሴ ማዕከል ነበረች፡፡

ለማርቲን ሉተር የተሐድሶ እንቅስቃሴ መነሻ የሆነው የዚያን ጊዜው የኃጢአት ስርየት ደብዳቤ ሽያጭ (Sales of Indulgence) ወደ ስዊትዘርላንድም መጥቶ ነበር፤ ይህን የሽያጭ ተልእኮ ከፖፕ ልዮን 10ኛ ተቀብሎ ወደ ስዊትዘርላንድ ሄዶ የነበረ ሳምሶን የተባለ በሚላን የሚገኘው የፍራንሲስካን መነኩሴ ነበር፡፡ ዝዊንግል ገና በኤይንዚደልን ከተማ እያለ ይህ መነኩሴ ወደዚያ ስፍራ በመጣ ጊዜ በጽናት ስለተቃወመው ብዙም አልተሳካለትም ነበር፡፡ ከዚያ በኋላም ቢሆን መነኩሴው በተለያዩ ከተሞች እየተዘዋወረ ብዙ ገንዘብ ካሰባሰበ በኋላ ወደ ዙሪክ ከተማ ሊገባ ሲል ተቀባይነት አላገኘም ነበር፡፡ በጊዜው ዝዊንግል (Zwingle) የዙሪክ ፓስተር ተደርጎ ተመድቦ ስለነበር በክርስቶስ ኢየሱስ መሥዋዕትነት ስለሚገኘውና እግዚአብሔር ብቻ ስለሚሰጠው የኃጢአት ስርየት እያስተማረ በማነሳሳት ሕዝቡ የፖፑን የኃጢአት ይቅርታ እንዲቃወም አደረገ፤ ከዚያም መነኩሴው የሕዝቡን ቁጣ ሲመለከት ወደ ዙሪክ ከተማ ሳይገባ በ3 ፈረሶች በሚሳብ ሰረገላው በፍጥነት ወደ ጣሊያን ተመልሷል፡፡ ከዚያም የሀገረ ስብከቱ ጳጳስና ሌሎች ኃላፊዎች ለጊዜው ዝዊንግል ያደረገውን ቢደግፉም ለእነርሱ ለራሳቸው የመዳንን ወንጌል በግልጽ በመሰከረላቸው ጊዜ ግን አጥብቀው ተቃወሙት፤ በመጨረሻም በ1520 ከተመደበበት የፓስተርነት ሥራው ለቆ የፓፓውን ሥርዓት ፊት ለፊት መቃወም ቀጠለ፡፡

ዝዊንግል በዙሪክ ሳለ አብረው ከሚሠሩት ሌሎች ባልደረቦቹ ጋር በመሆን ከሠራቸው ሥራዎቹ ሁሉ ትልቁ ሥራ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ጀርመንኛ ቋንቋ መተርጎሙ ነው፤ ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳንን በሙሉ የያዘው ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ከ1524-1529 ባለው ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቀ ሲሆን ይህም ማርቲን ሉተር ሙሉውን የጀርመንኛ መጽሐፍ ቅዱስ ከማሳተሙ 5 ዓመት ቀድሞ የሆነ ነው፡፡ ይህም ሥራ ለተሐድሶ እንቅስቃሴ ዋነኛ መሳሪያ ሆኗል፡፡

በስዊትዘርላንድ ውስጥ በተለይም በጄኔቫ ሆኖ የተሐድሶ እንቅስቃሴ በማድረግ የሚታወቀው ሌላው ሰው ደግሞ የፈረንሳዩ ጆን ካልቪን (John Calvin) (1509-1564) ነው፡፡ ካልቪን አክራሪ የካቶሊክ ተከታይ በነበረ ጊዜ በሃይማኖቱ ውስጥ ጳጳሳት፣ አባቶች፣ ሊቃውንት፣ የሚባሉትን ሳይሆን ነቢያትንና ሐዋርያትን እንዲሰማና መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያነብ ለመጀመሪያ ጊዜ የመከረው ከጄምስ ሊፌቭሬ (James Lefevre) ቀጥሎ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ፈረንሳይኛ ቋንቋ በመተርጎሙ የሚታወቀው ፒተር ሮበርት ኦሊቬንታን (Peter Robert Oliventan) የተባለው ሰው ነበር፡፡ ካልቪን ከብዙ ተቃውሞና ክርክር በኋላ ከ1523-1527 ድረስ በውስጡ በቆየ፣ ከ3 ዓመት በላይ በሆነ ትግል እውነታውን ተረድቶ የተለወጠ ሰው ነው፡፡ ከዚያም የግሪክና የዕብራይስጥ ቋንቋ ተምሮ መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ ካጠና በኋላ ራሱን ከካቶሊክ ለይቶ በፓሪስና የሕግ ትምህርት በተማረባት በቦርሄስ (Borges) ከተሞች የተረዳውን እውነት በኅቡዕ መስበክ ጀመረ፡፡ ካልቪን ምንም እንኳ ፓሪስን የአገልግሎቱ ማዕከል ለማድረግ አስቦ የነበረ ቢሆንም በደረሰበት ስደት ምክንያት ከፈረንሳይ ሊወጣ ችሏል፡፡ የእርሱ የቅርብ ባልንጀራ የነበረው ኒኮላስ ኮፕ (Nicolas Cop) “የሁሉም ቅዱሳን ቀን” ተብሎ በሚከበር አንድ ትልቅ ክብረ በዓል ላይ ንግግር እንዲያደርግ ባገኘው መድረክ ካልቪን ጽፎ የሰጠውን ስለ ክርስቶስ ብቻ እንጂ ስለ ቅዱሳን ምንም የማይናገረውን ጽሑፍ በማቅረቡ ምክንያት በተነሣው ማዕበል ኮፕ ከመያዙ በፊት ወደ አገሩ ወደ ባስል ተወስዶ ሲሄድ ካልቪን ደግሞ በዚያው በፈረንሳይ ውስጥ አንጉለም (Angouleme) በተባለች ቦታ ካኖን ሉዊስ ዱ ቲሌት (Canon Louis Du Tillet) በተባለ ሰው ቤት ውስጥ ጥቂት ጊዜ ተቀምጦ በኋላ ወደ ባስል መጥቶ በ1535 ዓ.ም “የክርስትና እምነት ተቋም (Institutes of the Christian Religion)” የተባለውን የመጀመሪያውን መጽሐፍ ጽፎ ለማሳተም ችሏል፡፡ ከዚያም በ1536 ወደ ጄኔቫ (Geneva) ከሄደ በኋላ በፈረንሳይም ሆነ በስዊትዘርላን (Switzerland) የተሐድሶውን አገልግሎት ጀምሮ ከነበረው ከዊሊያም ፋሬል (William Farel) (1489-1565) ጋር ተገናኘ፡፡ ፋሬል ካልቪንን በጄኔቫ ተቀምጦ የጌታን ሥራ አብረው እንዲሠሩ ጠየቀው፡፡ ከብዙ ማመንታት በኋላ ቢሆንም በፋሬል ብርቱ የሆኑ ምክሮች ተሸንፎ በጄኔቫ ተቀምጦ የተሐድሶውን አገልግሎት አብረው ማከናወን ቀጠሉ፡፡ ሁለቱም የፓፓው ሥርዓት ዋነኛ ተቃዋሚዎች ብቻ ሳይሆኑ እጅግ ጥብቅ በሆኑ የዲሲፒሊን ሕጎች የሚያምኑ ነበሩ፤ ከሚሰብኩት ቃል በተጨማሪ ለመታዘዝ ከባድ የሆኑ ሕግና ደንቦችን ተግባራዊ ለማድረግ ሲሞክሩ ሕዝቡ ተቃወማቸው፤ እንዲያውም ከአገልግሎት እንዲታገዱ ተደረጉ፤ ከዚያም በ1538 ሁለቱም ከጄኔቫ ወጡ፤ ፋሬስ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ ወደኖረባትና ወዳገለገለባት ወደ ኔዮፍካቴል (Neuofchatel) ሲሄድ ካልቪን ደግሞ ወደ ባስል (Basle) ከዚያም ወደ ፈረንሳይ ስትራስበርግ (Strasburg) ሄደ፤ በስትራስበርግም ወደ 15 ሺ የሚደርሱ የፈረንሳይ ሰዎችን በአገልግሎቱ ለመማረክ ችሏል፡፡ በዚህ የተሳካ አገልግሎት በስትራስበርግ ለ3 ዓመት ከቆየ በኋላ በጄኔቫ ሰዎች እንደገና ተጠርቶ በ1541 ወደ ጄኔቫ ተመለሰ፡፡ ከዚያም በፊት በነበሩት በ3 ዓመታት ውስጥ በጄኔቫ ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካና ማኅበራዊ ቀውስ ስለነበርና ሕዝቡም በመሪዎች ይበደል ነበር፤ ይህም እነ ካልቪንን ከጄኔቫ በማስወጣታቸው የመጣ የእግዚአብሔር ቅጣት አድርገው ስለወሰዱት ሕዝቡ ካልቪንን እንደገና ሊመልሱት ቻሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ካልቪን በ1564 ዓ.ም. እስከሚሞትበት ጊዜ ድረስ ቀሪ ዘመኑን ያሳለፈው በጄኔቫ ነበር፡፡

በትያጥሮን ቤተክርስቲያን ገጽታ የተመለከትነውንና ቤተክርስቲያን በታሪኳ ውስጥ ያሳለፈችውን የጨለማ ዘመን ሰብሮ የወጣው የእነዚህ የተሐድሶ አገልጋዮች ሥራ በመነሻው ላይ የእግዚአብሔር ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት ያደረገ ነበር፤ በተለይም በመዳን ትምህርት ላይ በቃሉ የተገለጠው እውነት ብዙዎችን ለዘላለም ሕይወት አብቅቶ ነበር፤ ሆኖም ብዙም ሳይቆይ በራሳቸው በተሐድሶ መሪዎችም ሆነ በተከታዮቻቸው ዘንድ የነበረው መንፈሳዊነት እየሞተ ሄዶ አገልግሎታቸው ሁሉ በሰው ሥርዓትና ደንብ እንዲሁም በዓለማዊ አሠራር ተጽዕኖ ሥር ሲወድቅ እንመለከታለን፡፡

በማርቲን ሉተር ዘመን በጀርመን የነበረው “የቅድስቲቷ ሮም” (Holy Roman Empire) ንጉሠ ነገሥት (1500-1558) ቻርለስ 5ኛ (Charles v) ነበር፡፡ እርሱም በ1521 ዓ.ም. ዎርም (Worm) በተባለች በጀርመን ደቡባዊ ምዕራብ በምትገኝ ከተማ በጠራው ትልቅ ስብሰባ ሉተር ተገኝቶ እንዲጠየቅ ተደርጎ ነበር፤ በዚህ ጊዜ ሉተር ወደ ስብሰባው ሲሄድና ከስብሰባው ሲመለስ በሰላም መጓዝ እንዲችል የጥበቃ መብት (safe sonduct) እንዲሰጠው የሉተር የቅርብ ባልደረባ በነበረው በሳክሰኒው አገረ ገዢ በፍሬደሪክ ዘዋይዝ (Frederick the wise) አማካኝነት ንጉሠ ነገሥቱ ተጠይቆ ስለተፈቀደለት በስብሰባው ላይ መገኘት ችሏል፡፡ በስብሰባውም ላይ ሉተር ያስተማረውን ትምህርትና የጻፋቸውን ወደ 20 የሚደርሱ መጻሕፍት እንዲተው ተጠይቆ ነበር፡፡ ሆኖም ሉተር ላመነበት ነገር በጽናት በመቆሙ ካስተማረውና ከጻፈው ነገር ወደ ኋላ እንደማይል ስላረጋገጠ የካቶሊክ ቤተክርስቲያንን ከነሉተር እንቅስቃሴ ለመታደግ በሚል እነርሱን ለማጥፋት በሚል እነርሱን ለማጥፋት የሚያስችል አዋጅ ንጉሠ ነገሥቱ በዎርም ጉባኤ ላይ ተነበበ፡፡ ሆኖም ንጉሡ ከፈረንሳዩ ፍራንሲስ 1ኛ (Francis I) (1494-1547) በነበረው ጦርነት ቱርኮች በአውሮፓ ግዛቶች ላይ ሊያደርሱት በሚችሉት ጉዳት ዙሪያ ተወጥሮ ስለነበር ለነሉተር የተሐድሶ እንቅስቃሴ ትኩረት ሳይሰጥ ብዙ ዓመታት አለፉ፡፡

በዚህ ጊዜ በመጠቀምሉተርና ከእርሱ ጋር አብረው ይሠሩ የነበሩት እነሜላንክተን (Melancthon) በስብከቶቻቸውና በጽሑፎቻቸው ሕዝቡን ብቻ ሳይሆን ብዙ አገረ ገዢዎችንም መማረክ ችለዋል፡፡ ሆኖም የፖለቲካ ሰዎች የሆኑት እነዚህ አገረ ገዢዎች አሁን በተቀበሉት እምነት ምክንያት ሊደርስባቸው የሚችለውን ጥቃት ለመካከል መሰባሰብ ጀመሩ፡፡ እንዲህ ዓይነቱን የዚህህን ዓለም መርሆ ተከተለ እንቅስቃሴ መፍቀድና መተባበር በሉተርም ሆነ በሌሎች የተሐድሶው አገልጋዮች የታየ መንፈሳዊ ውድቀት ነበር፡፡ “ሕያው እንደመሆንህ ስም አለህ ሞተህማል” ተብሎ በሰርዴስ ለነበረች ቤተክርስቲያን የተነገረው ቃል በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ መፈጸም የጀመረውም መንፈሳዊው የተሐድሶ እንቅስቃሴ በዚህ ዓለም ገዢዎች እጅ መግባ ከጀመረበት ከዚህ ወቅት ጀምሮ ነበር፡፡ በዎርም ጉባኤ (Worm) በነሉተር ላይ የታወጀውን አዋጅ ለማስፈጸም እንዲቻል በ1526 በስፓየርስ በተደረገው ጉባኤ (Spires) አዋጁ በፍጥነት ተግባራዊ እንዲሆን ጥረት ተደርጎ ነበር ነገር ግን ሉተርን በመደገፍ የተሐድሶውን እንቅስቃሴ የተቀላቀሉት በጀርመን የነበሩት የተለያዩ አገረገዢዎች ተሰባስበው የጋራ አቋም ከያዙ በኋላ እግዚአብሔር በእነርሱ ዘመን ከተጻፈው ቃሉ ውስጥ የገለጠውን “ጽድቅ በእምነት ነው” ለሚለው ትምህርት እንደሚቆሙና ይህ እውነት እንዲጠፋ እንደማይፈቅዱ የሚገልጽ ጽሑፍ አቅርበው ነበር፡፡ ሆኖም ቱርኮች ድል እያደረጉ በሀንጋሪና በሌሎች አገሮች መዝመታቸውን የሚገልጽ ድንገተኛ ወሬ በመምጣቱ የስፓየርሱ ስብሰባ ዓላማውን ሳያሳካ ተቋረጠ፤ ከዚያም ከ3 ዓመት በኋላ በ1529 ንጉሠ ነገሥቱ ስብሰባው በድጋሚ እንዲጠራ አደረገ፡፡ በዚያው በስፓየርስ በተደረገው በዚህ በ2ኛው ስብሰባ ላይ በተሰባሰቡት በፓፓው ሥርዓት ተከታዮች መካከል ንጉሡ በየግዛቱ የተስፋፋውን የእነሉተርን እንቅስቃሴ በ1526ቱ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት በኃይል ለመግታት የሚያስችለው በዎርም ጉባኤ የታወጀው አዋጅ ተግባራዊ እንዲሆን አወጀ፡፡ ሆኖም የተሐድሶው ተከታይ የሆኑት አገረ ገዢዎች በቂ ምክንያቶቹን በማቅረብ አዋጁ ተግባራዊ እንዳይሆን በጽናት ተከራከሩ፡፡ ይሁን እንጂ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለጉባኤው ውሳኔ እንዲገዙ በተጠየቁ ጊዜ እነዚህ ተሐድሶዎቹ ተቃወሙ (The Reformers Protested)፡፡ ይህ የሆነው እ.ኤ.አ. ሚያዝያ 19 ቀን 1529 ዓ.ም. ሲሆን ተቃውሞአቸው በፓፓው ሥርዓት ተከታዮች ተቀባይነት ስላገኘ በማግሥቱ በይበልጥ በዝርዝር የተጻፈ ተቃውሞአቸውን የያዘ ጽሑፍ ለንጉሠ ነገሥቱ አቀረቡ፡፡ ባቀረቡት የተቃውሞ ጽሑፍ ላይ የፈረሙት እነዚህ ሀገረ ገዢዎችም የሳክሰኒው ጆን (John, Elector of Saxony)፣ የሄሱ ፊሊፕ (Philip, Landgrave of Hesse)፣ የብራንደርበርጉ ጆርጅ (George of Brandenbrg)፣ የሉነንበርግ የሆኑት ኧርነስትና ፍራንሲስ (Ernest and Francis of Lunenberg)፣ የአሃልቱ ዎልፍጌንግ (Wolfgang of Ahalt) እና የ14 ንጉሣዊ ከተሞች ምክትል አገረ ገዢዎች ነበሩ፡፡ እነዚህና ሌሎችም የተሐድሶ እንቅስቃሴ ተከታዮችና አራማጆች የነበሩት ሰዎች ፕሮቴስታንቶች(ተቃዋሚዎች) እየተባሉ መጠራት የጀመሩት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው፤ በጊዜው በፓፓዊው ሥርዓት በሚመራው የክርስትና ዓለም የነበረውን ክፉ ትምህርትና የስህተት አሠራር ተቃውመዋልና፡፡ ይሁንና ተቃውሞውን ያቀረቡት እነዚህ ሰዎች ከላይ እንደተገለጸው በመንፈሳዊ አገልግሎት ላይ የነበሩ ሰዎች ሳይሆኑ የተሐድሶውን ሐሳብ የተቀበሉ የፖለቲካ ሰዎች ናቸው፡፡ ተቃውሞውን ሲያቀርቡ ሉተር ራሱ እንኳ ከእነርሱ ጋር አብሮ አልነበረም፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል መሠረት አድርጎ የተጀመረው የተሐድሶ እንቅስቃሴ በዚህ መልኩ በዚህ ዓለም ባለሥልጣናት እጅ ሲገባ በስም ብቻ ካልሆነ በቀር በመንፈሳዊ ነገሩ ሞተ፡፡ ማርቲን ሉተር ቀደም ሲልም ቢሆን በሳክሰኑ ኢሌክተር በፍሬድሪክ ዘዋይዝ ጥበቃ ሥር ለመሆን የተስማማ ከመሆኑም ሌላ ሕዝቡን የሚወክሉት አገረ ገዢዎች (አለቆች) ለተሐድሶ እንቅስቃሴ አስፈላጊ እንደሆኑ አድርጎ ያምን ነበር፡፡ ከፍሬድሪክ ቀጥሎ የሳክሰኒ ኢሌክተር የነበረው ወንድሙ ጆን የተሐድሶ እንቅስቃሴው ዋነኛ አራማጅ ሲሆን ሉተርና ባልንጀራው ሜላንክተን የቤተክርስቲያን አስተዳደርን አምልኮን፣ እና ሌሎች ተግባራትን እንዲሁም የካህናት ደሞዝን የሚመለከት አዲስ ሕግ (Constitution) እንዲያዘጋጁ በማድረግ በግዛቱ በሳክሰኒ ያሉ አብያተክርስቲያናት እንዲመሩበት አደረገ፤ ተሐድሶውን የሚያራምዱ የሌሎች የጀርመን ግዛቶች አገረ ገዢዎችም ይህንኑ ልምድ በመውሰድ ተግባራዊ አደረጉት፤ ይህንንም ተከትሎ በእነርሱ ግዛቶች ውስጥ ያሉት አብያተ ክርስቲያናት ከሮም ቤተክርስቲያን ተገነጠሉ፡፡ በእግዚአብሔር ቃል ብቻ ሲመራ የነበረው የተሐድሶ እንቅስቃሴም በፖለቲካው ተጽዕኖ ምክንያት በሰው ሥርዓት የሚመሩ የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናትን በዚህ መልኩ ፈጠረ፡፡ የታደሱ በሚባሉት በእነዚህ አብያተክርስቲያናት ሁሉ ስለክርስቶስ፣ ስለመንፈስ ቅዱስ ይነገራል፣ መጽሐፍ ቅዱስም በመመሪያነቱ ሲታመንበት ይታያል፡፡ ሆኖም በተግባር ሲታይ እነዚህ ነገሮች ሁሉ ትክክለኛ ስፍራቸው አልተሰጣቸውም፤ ሁሉም ነገር በሰው አሠራር ሥር በመሆኑ መንፈሳዊው ነገር የሞተና እየሞተ ያለ ሆኖ ይታያል፡፡

በዝዊንግልና በካልቪን አማካኝነት በስዊትዘላንድ በተካሄደው የተሐድሶ እንቅስቃሴም ቢሆን ከዚህ የተለየ ታሪክ የለውም፡፡ ኡልሪክ ዝዊንግል (Ulric Zwingle) ከሉተር በባሰ መልኩ የፖለቲካ ሰዎች የሆኑትን አገረ ገዢዎችን ተጠቅሞ ከካቶሊኮች የሚመጣውን ጥቃት በመከላከል ተሐድሶውን በማስፋፋት ያምን ነበር፤ በ1527 ዓ.ም. በየአገሩ ያሉ የተሐድሶ ግዛቶች የጋራ ጥምረት (Confederation) እንዲፈጥሩ ሐሳብ አቀረበ፤ በዚህ መሠረት ኮንስታንስ (Constance) የተባለው ግዛት በቅድሚያ ፈቃደኝነቱን ገለጠ፡፡ በመቀጠል የበርኔ (Berne)፣ የሴንት ጎል (St.Gaul)፣ የሙልሃውሰን (Mulhausen)፣ የባስል (Basle)፣ የስካፍሃውዘን (Schaffhausen)፣ እና የስትራስበርግ (Strasbourg) ግዛቶች የተባለውን ጥምረት ፈጠሩ፡፡ ይህ እንደተሰማ ሉሰርን (Lucern)፣ ዙግ (Zug)፣ ስዌይዝ (Schwetiz)፣ ኡሪ (Uri) እና ኡንተርዋልደን (Unterwalden) በተባሉ 5 የስዊትዘላንድ ካቶሊካዊ ግዛቶች ከፍተኛ ቁጣ የተቀሰቀሰ ሲሁን “እንዲህ ዓይነቱ ኑፋቄ በእሳትና በሰይፍ ሊወገድ ይገባል” በሚል በ5ቱ ግዛቶች ውስጥ አዲስ የሃይማኖት ቡድን ሊመሠርቱ የሚጥሩ ላይ ሞት ታወጀ፤ ከዚህም ጄምስ ኬይሰር (James Keyser) የተባለ በዙሪክ ወንጌልን የሚያገለግል ሰው ኦበርኪርክ (Oberkirk) ወደተባለ ስፍራ ለእሁድ አገልግሎት በመሄድ ላይ ሳለ በመንገድ ላይ በድንገት በ6 ሰዎች ተይዞ ወደ ፍርድ ቤት ከተወሰደ በኋላ በእሳት ተቃጥሎ እንዲሞት ተፈረደበት፤ እርሱም የጌታ ጸጋ አበርትቶት እምነቱን እየመሰከረ በሰማዕትነት አለፈ፡፡ ይሁን እነጂ በዙሪክ ፕሮቴስታንቶች ዘንድ ይህ ሁኔታ ከፍተኛ ቁጣን የፈጠረ ሲሆን እነርሱም በተራቸው በ5ቱ የካቶሊክ ግዛቶች ላይ ጦርነት አወጁ፤ ዝዊንግል ራሱ ወደ ጦርነት ከዘመቱት መካከል አንዱ ሲሆን “በእግዚአብሔር ብቻ ማመን ቢገባንም ትክክለኛ ምክንያት በሚኖረን ጊዜ ግን እንደ ኢያሱና ጌዴዎን ስለአገራችንና ሰለ አምላካችን ልንዋጋ እንችላለን” እያለ ቅስቀሳ ያደርግ ነበር፡፡ እርሱ የወንጌል አገልጋይ ሆኖ ሳለ እንዲህ ያለ ሥጋዊና ፖለቲካዊ ሥራ መሥራቱ በጥሩ ሁኔታ የተጀመረው መንፈሳዊ አገልግሎቱ እየሞተ መሄዱን ያሳያል፡፡ ሆኖም በ1531 ዓ.ም. ካፕል (Cappel) በተባለች አንድ ስፍራ በካቶሊኮቹና በፕሮቴስታንቶቹ መካከል በተደረገው ጦርነት ሲዋጉ ዝዊንግልና ሌሎች 25 የተሐድሶው አገልጋዮች ተገድለዋል፡፡

በጄኔቫ የነበረውን ተሐድሶ በማካሄድ ይበልጥ የሚታወቀው ጆን ካልቪንም ቢሆን ከመንፈሳዊ አገልግሎቱ በተጨማሪ የሲቪልና የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን የሚመለከቱ አስተሳሰቦች ነበሩት፡፡ አስቀድሞ እንደገለጽነው በጊዜው ህዝቡ ሊሸከሙት እስከማይችሉት ያደረሳቸውን ጥብቅ የዲሲፕሊን መመሪያዎች ከዊሊያም ፋሬል ጋር በመሆን ተግባራዊ ለማድረግ ከመሞከሩም ሌላ በጥፋተኞች ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ሊሰጥ የሚችል የቤተክርስቲያን ፍርድ ቤት (Consistory) እስከማቋቋም ደርሷል፡፡ ካልቪን በእምነት ጉዳይ ጥፋተኞች የተባሉትም እስከሞት በሚደርስ ቅጣት እንዲቀጡ ያደርግ ነበር፡፡ ለምሳሌ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስን ሦስትነት (Trinity) በመካድ ከፍ ያለ የሐሰት ትምህርትን ያስተምር ለነበረው ሰርቪተስ (Servetus) ለተባለው ሰው በእሳት ተቃጥሎ መገደል ዋናውን አስተዋጽኦ ያደረገው ካልቪን እንደሆነ ታሪክ ያስረዳል፤ እንዲያውም “ሰርቬተስ ወደ ጄኔቫ ከመጣ በሕይወት አይመለስም” ብሎ እንደተናገረ ተመዝግቧል፡፡ እንዲሁም የካልቪንና የእርሱ ተከታዮች የሆኑት የሲቪል መሪዎች የቤተክርስቲያን ፍርድ ቤቱን አሠራርና ሥልጣን የተቃወመውን ዣክ ግሩየት (Jacques Gruet) የተባለውን ሰውም በአንድ ሰሌዳ ላይ የተቃውሞ ጽሑፍ ጽፈሃል በሚል ተወንጅሎ በማስጨነቅ (በtorture) እያስፈራሩ ብዙ ካሠቃዩት በኋላ በሰይፍ እንዲገደል አድርገዋል፡፡ ካልቪንም ሆነ ተከታዮቹ በአክራሪ አመለካከታቸው እንደ ዘፈንና ዳንስ፣ ስካርና ዝሙት የመሳሰሉ አለማዊ ሥራዎችን ማስቀረት የሚፈልጉት በሚሰብኩት የእግዚአብሔር ቃል ብቻ ሳይሆን በሕግና በሥርዓት በተደነገገው ቅጣትም ጭምር ነበር፡፡ እንደዚሁም የብሉይ ኪዳን ቅጣት ሕጎች በክርስትና ዘመንም ቢሆን ተግባራዊ መሆን እንደሚገባቸው በካልቪን ዘንድ ይታመን ነበር፡፡ ለምሳሌ በዘጸ.22፡18ና በዘሌ.20፡27 የተጻፈውን ሕግ በመጥቀስ በ1545 ዓ.ም. በጄኔቫ ውስጥ በጥንቆላ ተግባር ተገኝታችኋል በሚል 23 ሰዎችን በእሳት ተቃጥለው እንዲሞቱ ተደርጓል፡፡ ይህ አሠራር “በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ…” የሚለው የክርስቶስ ትምህርት የተካደበትና የተጣሰበት አሠራር ነው /ማቴ. 5፡44-45/፡፡ ያዕቆብና ዮሐንስ በአንድ ወቅት ክርስቶስን ባልተቀበሉት ሳምራውያን ላይ “ኤልያስ ደግሞ እንዳደረገ እሳት ከሰማይ ወርዶ ያጥፋቸው እንል ዘንድ ትወዳለህን?” ብለው ኢየሱስን ሲጠይቁት ዘወር ብሎ በመገሠጽ “ምን ዓይነት መንፈስ እንደሆነላችሁ አታውቁም፤ የሰው ልጅ የሰውን ነፍስ ሊያድን እንጂ ሊያጠፋ አልመጣም” እንዳላቸው ተጽፏል (ሉቃ. 9፡51-56)፡፡ የነካልቪን አገልግሎትም በጄኔቫ ከነበረው ፖለቲካዊና ዓለማዊ ሥርዓት ጋር አንድ ሆኖ ሲንቀሳቀስ በፍቅር የተሞላውን የክርስቶስ ትምህርትና መንፈስ ሙሉ በሙሉ አጥፍቶታል፡፡ ምንም እንኳ በእነርሱ የተሐድሶ አገልግሎት ክርስቶስን በማመን ብቻ የሚገኘው ሕይወት ተሰብኮ ብዙዎች ቀደም ሲል ከነበሩበት ጨለማ ነጻ የወጡ ቢሆንም እየቆየ ሲሄድ ግን አገልግሎታቸው ከአለማዊ አሠራር ጋር በመዋሐዱ ምክንያት ስም ብቻ እንጂ ሕይወት የሌለው ሆነ፤ በእርግጥም “ሕያው እንደመሆንህ ስም አለህ ሞተህማል” መባል የሚገባው ነበር፡፡

በማርቲን ሉተር፣ በኡልሪክ ዝዊንግልና በጆን ካልቪን እንዲሁም ከእነርሱ ጋር አብረው በሠሩት የተሐድሶ አገልጋዮች በ16ኛው ክ/ዘመን የተካሄደው የወንጌል ሥራ በጅማሬው ላይ ለመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከፍተኛ ትኩረት የሰጠና መጽሐፍ ቅዱስን ለክርስትና ትምህርት ብቸኛ ማስረጃ አድርጎ የተቀበለ በመሆኑ ለዘመናት በጨለማ ተውጦ የነበረውን የመዳን ወንጌል ወደ ብርሃን ለማውጣት ችሏል፡፡ ነገር ግን በታሪካቸው እንደተመለከትነው ብዙም ሳይቆይ አገልግሎቱ እየሞተ ሄዷል፡፡ ስለሆነም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ሁኔታ ያሉትን ሁሉ በሰርዴስ ለነበረች ቤተክርስቲያን እንዳለው ሁሉ “እንዴት እንደ ተቀበልህና እንደ ሰማህ አስብ፥ ጠብቀውም ንስሐም ግባ” እያለ ይመክራቸዋል፡፡ ስለዚህ ለሰርዴስ ቤተክርስቲያን የተጻፈው መልእክት በትንቢታዊ ገጽታው በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ መፈጸም ከጀመረበት ከ16ኛው ክ/ዘመን ጀምሮ ጌታ እስኪመጣ ድረስ በሚቀጥለውና ልክ እንደ ሰርዴስ ቤተክርስቲያን በስም ብቻ ሕያው ሆኖ ከዓለማዊነት ጋር በመዋሐዱ ምክንያት ሙት በሆነው የዘመናችን ክርስትና ውስጥ ለሚገኙ አማኞች “የነቃህ ሁን” የሚል ግልጽ መልእክትን የሚያስተላልፍ ነው፡፡

“እንዲሁ በነጭ ልብስ ይጐናጸፋል፥ ስሙንም ከሕይወት መጽሐፍ አልደመስስም፥ በአባቴና በመላእክቱም ፊት ለስሙ እመሰክርለታለሁ።” (ቁ.5)

እዚህ ላይ “ድል የነሣው” የተባሉት ቀደም ሲል “ልብሳቸውን ያላረከሱ” የተባሉት ጥቂት ሰዎች (ስሞች) እንደሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ከዓለማዊነት ጋር ተቀላቅሎ በሚገኘው በሰርዴስ ቤተክርስቲያን አብዛኛው ክፍል ሁኔታ ውስጥ በዓለም ከሚገኝ እድፍ ራሳቸውን ጠብቀው ለመገኘት የቻሉ አማኞች በእርግጥም በዚያ ያለውን ፈታኝ ነገር ድል የነሱ ናቸው፤ ከ16ኛው ክ/ዘመን የተሐድሶ እንቅስቃሴ በኋላም ከዓለማዊነት ጋር በመስማማት በስም ብቻ ሕያው ነኝ ከማለትና በአፍ “ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ!” ከማለት በቀር እውነተኛው ክርስቲያናዊ ሕይወት በሌለበት ወይም በተግባር በሞተበት በፕሮቴስታንቲዝም ሥርዓት ውስጥ አፍአዊውን ክርስትና ድል ነስተው ለጌታ የተረፉ ጥቂት ቅሬታዎች መኖራቸው እርግጥ ነው፡፡ እነዚህም “በነጭ ልብስ ይጎናጸፋል” ተብሎ የተነገረላቸው የከበረ የተስፋ ቃል ባለቤት ናቸው፡፡ ንጹሕና ክቡር የሆነውን የክርስቶስ ማንነት ተጎናጽፈው (በክብር ተላብሰው) በእግዚአብሔር ፊት ያለ ዕረፍት ይቀርባሉ፡፡ እነዚህ ቅሬታዎች “ሕያው” የሚባሉት በስም ብቻ ሳይሆን በእውነትም ሕያው ናቸው፤ ስለሆነም ጌታ “ስሙን ከሕይወት መጽሐፍ አልደመስስም” ብሏቸዋል፡፡ አንድ ጊዜ በእርሱ በእውነት አምነው ሕይወት ያገኙት ከማይጠፋው ዘር የተወለዱ የማይጠፋ ሕይወት ባለቤት ናቸውና (1ጴጥ. 1፡23፤ 2ጢሞ.2፡9)፤ “ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ!” በሚሉት የአፍ ወይም የስም አማኞች ላይ “ከቶ አላውቃችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች ከእኔ ራቁ” ብሎ የሚመሰክርባቸው ጌታ (ማቴ.7፡21-23) ለእነዚህ እውነተኛ አማኞች ደግሞ “በአባቴና በመላእክቱ ፊት ለስሙ እመሰክርለታለሁ” የሚል የከበረ ተስፋን ጨምሮ ሰጥቷል፡፡ በማቴ.10፡32 ላይ “ስለዚህ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ” ብሎ ጌታ መናገሩን እንመለከታለን፡፡ በሉቃ. 12፡8 ላይ ደግሞ “እላችሁማለሁ፥ በሰው ፊት የሚመሰክርልኝ ሁሉ፥ የሰው ልጅ ደግሞ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ይመሰክርለታል” ብሎ የተናገረውን ቃል እናነባለን፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ በሰማያዊ አባቱ ፊትና በሰማያዊ ፍጥረታት በመላእክት ፊት የእውነተኛ አማኞች ምስክር ነው፡፡ እውነተኛ አማኞች በግላቸውም በሆነ በሰው ፊት እውነተኞች ናቸው፤ በዚህ ዓለም ያለውን የሰውን ሥርዓት ፈርተውም ሆነ አቻችለው ስለ ክርስቶስ መመስከር ያለባቸውን እውነት አይሸሽጉም፡፡ በሰርዴስ እንዳለው የስም ክርስትና ከዚህ ዓለም ጋር ተመሳስለውና ተስማምተው አይኖሩም፡፡ ስለዚህ ጌታም በአባቱና በመላእክቱ ፊት በሰማያት ይመሰክርላቸዋል፡፡ “በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምን በነፍሱ ምስክር አለው” (1ዮሐ.5:10)

“መንፈስ ለአብያተክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ” (ቁ.6)

ይህ ቃል በተለይ ለድል ነሺዎቹ የተነገረ ቃል እንደመሆኑ መጠን በየአብያተክርስተያናቱ ለሚገኙ ድል ነሺዎች ተስፋቸውን የሚያጸና ማረጋገጫ ነው፡፡ በየአብያተክርስቲያናቱ ራሳቸውን ከዚህ ዓለም አሠራር ጠብቀው በስም ብቻ ሳይሆን በእውነት ሕያው የሆኑ ቅሬታዎች ለሰርዴስ ድል ነሺዎች የተሰጡት ተስፋዎች ባለቤት ይሆናሉ፡፡

ለታሪካዊ ገለጻው የተጠቀምንባቸው ዋቢዎች
• Miller’s Church History, by Andrew Miller, Vol. II Vol. III
• Wikipedia, the free encyclopedia

ክፍል ስድስት>>>>

Amharic Bible-|- The Holy Bible [King James Version]