ፊልድልፍያ በእስያ ያለችው የሊድያ ክፍለ ሀገር አንዷ ከተማ ናት፡፡ የጴርጋሞን ንጉሥ በነበረው በአታላስ ፊላድልፈስ (Attalus Philadlphus) ስም «ፊልድልፍያ» ተብላ እንደተሰየመች ከታሪክ መረዳት ይቻላል፤ በተለያዩ ጊዜያት በመሬት መንቀጥቀጥ የተመታች ስትሆን በአሁኑ ጊዜ በስፍራው ላይ አላሼህር የተባለች ከተማ ትገኛለች፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፊልድልፍያ ለነበረች ቤተክርስቲያን ያስተላለፈው መልእክት በዚያ የነበሩትን አማኞች የሚያበረታታ ነገር እንጂ የሚነቅፍ ነገር አልነበረውም፡፡ ስለሆነም ራሱን ለፊልድልፍያ ቤተክርስቲያን ሲያቀርብ ሊናገራቸው ካለው የማበረታቻ ቃል እና ሊሰጣቸው ካለው የተስፋ ቃል አንጻር ባለው ማንነቱ ነው፡፡ በቅድሚያ ራሱን «የዳዊት መክፈቻ ያለው» አድርጎ ያቀርባል፡፡ «መክፈቻ» የሚለው ቃል ሥልጣንን የሚያሳይ ነው፡፡ በራእ.1፡18 ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «የሞትና የሲኦል መክፈቻ» ያለው ሆኖ ቀርቦልናል፡፡ ይህም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሣኤ ኃይል ምክንያት በሞትና በሲኦል ላይ ያለውን ሥልጣን የሚያመለክት ነው፡፡ የዳዊት መክፈቻ ያለው ሲባልም በዳዊት ቤት ላይ ሥልጣን ያለው ማለትን ያሳያል፡፡
«የዳዊት መክፈቻ» የሚለው ይህ ቃል በብሉይ ኪዳን በዳዊት ዙፋን ላይ ከነገሡት መልካም ነገሥታትን አንዱ በሆነው በሕዝቅያስ ቤተመንግሥት ከተሾሙት መካከል የኬልቅያስን ልጅ ኤልያቄምን በተመለከተ ተነግሮ እናገኛለን (ኢሳ.22፡15-25)፤ ከዚያ አስቀድሞ በዳዊት ቤት ላይ አዛዥ የነበረው ሳምናስ የተባለው ሰው ነበረ (ኢሳ.22፡19)፤ ሆኖም ይህ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሆኖ በመገኘቱ «ከአዛዥነት ሥራህ አሳድድሃለሁ፣ ከሹመትህም ትሻራለህ፡፡ በዚያ ቀን ባሪያዬን የኬልቅያስን ልጅ ኤልያቄምን እጠራለሁ፤ መጐናጸፊያህንም አለብሰዋለሁ፤ በመታጠቂያህም አስታጥቀዋለሁ፤ ሹመትህንም በእጁ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፤ በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ለይሁዳም ቤት አባት ይሆናል፡፡ የዳዊትን ቤት መክፈቻ በጫንቃው ላይ አኖራለሁ፤ እርሱም ይከፍታል የሚዘጋ የለም፤ እርሱም ይዘጋል የሚከፍት የለም» በማለት እግዚአብሔር የተናገረውን እናነባለን፤ በዚህም መሠረት በኋላ ላይ የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም የቤቱ አዛዥ ሆኖ እንመለከታለን (ኢሳ.36፡3፤ 37፡2)፡፡ ስለሆነም «የዳዊት መክፈቻ» በዳዊት ቤት ውስጥ ቊልፍ (ወሳኝ) የሆነ ሥልጣንን መያዝ የሚያመለከት ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ «ሕጻን ተወልዶልናልና፤ ወንድ ልጅም ተሰጥቶልናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘላለም አባት የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል፤ ከዛሬ ጀምሮ እስከዘላለም ድረስ በፍርድና በጽድቅ ያጸናውና ይደግፈው ዘንድ በዳዊት ዙፋንና በመንግሥቱ ላይ አለቅነቱ ይበዛል፤ ለሰላሙም ፍጻሜ የለውም» ተብሎ የተነገረለት ነው (ኢሳ.9፡6-7)፡፡ እንዲሁም በአዲስ ኪዳን «እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘላለም ይነግሣል ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም» ተብሎአል (ሉቃ.1፡32-33)፤ እግዚአብሔር ክፉ የነበረውን ሳምናስን ከአዛዥነት ሥራው አስወግዶ በምትኩ የኬልቅያስን ልጅ ኤልያቄምን የዳዊት ቤት አዛዥ እንዳደረገው ሁሉ በክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ የተያዘውን የዚህ ዓለም መንግሥት ሥልጣን አስወግዶ በሚመጣው ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስን በዳዊት ዙፋን ላይ ያነግሠዋል፡፡ ይህም ሥልጣን ለእርሱ ብቻ የተጠበቀ ስለሆነ ጌታ ኢየሱስ ራሱን «የዳዊት መክፈቻ ያለው» ብሎ ገልጿል፡፡
ይህም በቤተክርስቲያን ዘመን በመንፈሳዊ ሁኔታ ሲታይ እርሱ በቤተክርስቲያን ውስጥ ያለውን ሙሉ ሥልጣን ሊያመለክት ይችላል፡፡ መክፈትም መዝጋትም የእርሱ ብቻ ሥልጣን ነው፤ እርሱ የከፈተውን የሚዘጋ የለም፤ እርሱ የዘጋውን የሚከፍት የለም፡፡ ይህም ጌታ ኢየሱስ በቤተክርስቲያን ውስጥ ያለውን ሉዓላዊ ሥልጣን ያመለክታል፤ በፊልድልፍያ በነበረች ቤተክርስቲያን ይህ የእርሱ ብቻ የሆነው ሉዓላዊ ሥልጣን እውቅና አግኝቷል፤ በመሆኑም ወረድ ብለን በቊ.8 ላይ እንደምናነበው «ማንም ሊዘጋው የማይችል» «የተከፈተ በር» ሊሰጣቸው ስለፈለገ ራሱን «የዳዊት መክፈቻ ያለው» በማለት ከፍ ባለ ሥልጣኑ ሊገልጽላቸው መፈለጉን እንገነዘባለን፡፡
እንደዚሁም «ቅዱስና እውነተኛ» በማለት ራሱን ይገልጽላቸዋል፡፡ እርሱ ቅዱስ ሆኖ የተወለደ ነው፤ በሉቃ.1፡35 «ካንቺ የሚወለደው ቅዱሱ፣ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል» ተብሎ ተመስክሮለታል፤ እርሱ «ኃጢአት ያላወቀው» ነው (2ቆሮ.5፡21)፤ ይህም በሐሳቡ ውስጥ እንኳ ኃጢአት እንደሌለ ያሳያል፤ እርሱ «ኃጢአትን ያላደረገ» ነው፡፡ «ተንኰል በአፉ አልተገኘበትም» (1ጴጥ.2፡22)፤ ይህም በተግባርም ሆነ በንግግር ስለኃጢአት ሊከሰው የሚችል እንደሌለ የሚገልጽ ነው (ዮሐ.8፡46፤ ሉቃ.23፡4፣14፣22)፤ እንዲሁም «በእርሱ ኃጢአት የለም» (1ዮሐ.3፡5) ይህም ሰው የሆነው ከኃጢአት በቀር በመሆኑ በሰውነቱ ውስጥ የኃጢአተኝነት ባሕርይ ፈጽሞ እንደሌለበት የሚገልጽ ነው (ዕብ.4፡15)፡፡ በአጠቃላይ የእርሱን ቅዱስነት መጽሐፍ ቅዱስ ሲገልጥ «ቅዱስና ያለተንኰል ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ያለ እንደዚህ ያለ ሊቀካህናት ይገባናል፡፡» ይላል (ዕብ.7፡26)፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ እግዚአብሔር በባሕርዩ ቅዱስ እንደመሆኑ እኛም ቅዱሳን መሆን እንደሚገባን፣ የተጠራነውም ለዚሁ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል (1ጴጥ.1፡15፤ ሮሜ.1፡7፤ 1ቆሮ.1፡21)፤ ቅዱሳን የምንሆነው ደግሞ የቅዱሱ የኢየሱስ በመሆናችንና ቃሉን በመጠበቃችን ነው፡፡ ጌታችን ይህንን ሲገልጽ «በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው ... እነርሱ ደግሞ በእውነት የተቀደሱ እንዲሆኑ እኔ ራሴን ስለ እነርሱ እቀድሳለሁ» ብሏል (ዮሐ.17፡17)፤ በፊልድልፍያ ቤተክርስቲያን የነበሩ አማኞች ደግሞ ቃሉን ጠብቀዋል፤ ይህም ቅዱስ የሆነውን የክርስቶስን ባሕርይ እንዲይዙ ያደርጋቸዋልና ይህንኑ ጠባያቸውን ለማበረታታት ጌታ «ቅዱስ የሆነው» ሆኖ ራሱን አቀረበላቸው፡፡ ሆኖም ከቅዱስነቱ ጋር አብሮ የሚሄደው እውነተኛነቱ በመሆኑ «ቅዱስና እውነተኛ» በማለት ራሱን ይገልጻል፡፡ በእርግጥም ኢየሱስ እውነተኛ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ዲያብሎስ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነው፤ በዚህ ተቃራኒ ደግሞ ኢየሱስ እርሱ ራሱ «እውነት» የተባለና እውነትን የሚናገር ነው (ዮሐ.14፡6፤8፡45)፡፡ በሚያስተምርበት ጊዜም በአብዛኛው «እውነት እውነት እላችኋለሁ በማለት እያስረገጠ ይናገር ነበር፡፡» (ማቴ.18፡18፤ ዮሐ.1፡52፤ 5፡25....) ስለዚህ እርሱ እውነተኛ ነው፡፡ ቃሉን የያዙም እንዲሁ እውነተኞች ናቸው፡፡ ምክንያቱም «ቃልህ እውነት ነው» ተብሏልና (መዝ.118፡142፤ ዮሐ.17፡17) የፊልድልፍያ አማኞች ደግሞ ለቃሉ ትኲረት ስለሰጡ የክርስቶስ የእውነተኛነት ባሕርይ ይታይባቸዋል፡፡ በመሆኑም በዚያ ላለው እውነተኛነት እውቅና ለመስጠት ራሱን እውነተኛ አድርጎ ያቀርብላቸዋል፡፡
«ሥራህን አውቃለሁ እነሆ በአንተ ፊት የተከፈተ በር ሰጥቼአለሁ፤ ማንምም ሊዘጋው አይችልም፤ ኃይልህ ምንም ትንሽ ቢሆን ቃሌን ጠብቀሃልና ስሜንም አልካድህምና፡፡»(ቊ.8)
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፊልድልፍያ ያሉ አማኞች ያሉበትን ሁኔታ ያውቃል፤ እነርሱ ቃሉን የሚጠብቁና ስሙን ያልካዱ ናቸው፤ «ሥራህን አውቃለሁ» ሲልም ይህንኑ ቃሉን መጠበቃቸውንና ለስሙ ያላቸውን ታማኝነት አውቃለሁ ለማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሲታዩ ኃይላቸው ትንሽ በመሆኑ ያላቸውን መልካም ነገር ለሌሎች ለማድረስ ያልቻሉበት ሁኔታ እንደነበር እንገነዘባለን፡፡ ሆኖም ጌታ ቃሉን በመጠበቅና ስሙን ባለመካድ ለእርሱ በውስጣዊ ሁኔታቸው ታማኝነትን ስላሳዩ ራሱን ከእነርሱ ጋር ቈጥሮ ማንም ሊዘጋው የማይችል የተከፈተ በርን በመስጠት ሊረዳቸው ፈልጓል፡፡ «የተከፈተ በር» ሲባል በቅድሚያ የቃሉ ደጅ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ለቈላስይስ ሰዎች ከእስር ቤት ሆኖ ሲጽፍላቸው «በዚያን ጊዜም ስለ እርሱ ደግሞ የታሰርሁበትን የክርስቶስን ምስጢር እንድነግር እግዚአብሔር የቃሉን ደጅ ይከፍትልን ዘንድ ስለእኛ ደግሞ ጸልዩ፤ ልናገር እንደሚገባኝ ያህል እገልጠው ዘንድ ጸልዩልኝ» ብሏል (ቈላ.4፡3-4)፡፡ ስለሆነም እዚህ ላይ የቃሉ ደጅ (በር) መከፈት ማለት ልንናገረው የሚገባውን ያህል የቃሉን ምስጢር በጥልቀት መረዳት ማለት መሆኑን እንረዳለን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የቃሉ በር ከተከፈተ በኋላ ያን ቃል የምናገለግልበት የአገልግሎት በር ሊከፈት ይገባል፡፡ ጌታ ለሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠው የተከፈተ በር የቃሉን ፍቺ ብቻ ሳይሆን ሥራ የሞላበት የአገልግሎት በርም ነበር፤ ይህንንም ሲገልጽ «ሥራ የሞላበት ትልቅ በር ተከፍቶልኛልና ተቃዋሚዎችም ብዙ ናቸው» ብሏል (1ቆሮ.16፡9)፡፡ ስለዚህ ለፊልድልፍያ አማኞች “ጌታ የተከፈተ በር ሰጥቼአለሁ” በሚልበት ጊዜ ፍቺውን በጥልቀት የሚረዱበት የቃሉ በር እና ያንንም ተከትሎ ሊኖር የሚገባው ሥራ የሞላበት የአገልግሎት በር መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ በዚህ በኩል ከእነርሱ የሆነ አቅም የለም፤ ቃሉን ለመረዳትም ሆነ ለማስፋፋት ከራሳቸው የሆነ የሰውም ሆነ የማቴሪያል ኃይል የላቸውም፡፡ ስለሆነም ጌታ ማንም ሊዘጋው የማይችል የተከፈተ በር በመስጠት ኃይሉን በድካማቸው ሊገልጥ ወደደ፡፡
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለእነርሱ የተከፈተ በር ለመስጠት ያስቻሉት በእነርሱ ዘንድ ያገኛቸው ሁለት መልካም ነገሮች ቃሉን መጠበቃቸውና ስሙን አለመካዳቸው ናቸው፡፡ በሰርዴስ ቤተክርስቲያን ቃሉን በደስታ መስማትና መቀበል ቢኖርም ቃሉን መጠበቅ ግን አልነበረም፤ ስለሆነም “ሕያው እንደመሆንህ ስም አለህ ሞተህማል” ተባሉ፡፡ በፊልድልፍያ ግን «ቃሌን ጠብቀሃል» ስለተባለ በዚያ ስም ብቻ ሳይሆን ሕያውነት ያለው በተግባር የተገለጠ እውነተኛ ክርስትና መኖሩን እንረዳለን፡፡ ጌታን እወደዋለሁ የሚል ማንም ቢኖር ይህ እውነት መሆኑን ሊያረጋግጥ የሚችለው ቃሉን በመጠበቅ ነው፡፡ ጌታችን ራሱ ሲናገር «የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን፤ በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን፡፡» ብሏል (ዮሐ.14፡23-24)፡፡ ቃሉን መጠበቅ «ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ» በሚል ብቻ ከሚገለጥ አፍኣዊነት በተቃራኒ የሚታይ ተግባራዊ ክርስትና ነው፡፡ በዘመናችን በዝቶ በሚታየው ሃይማኖተኝነት ውስጥ ግን እንደ ፈሪሳውያን ቃሉን እየተናገሩ አለማድረግ (ማቴ.23፡3) የብዙ ክርስቲያኖች መገለጫ ሆኗል፡፡ እንዲህ ባለው አፍኣዊነትና አስመሳይነት መካከል እንደ ፊልድልፍያ አማኞች ቃሉን የሚጠብቁ ልንሆን ይገባናል፡፡ በዮሐ.17፡17 ቀደም ሲል እንደጠቀስነው ቃሉን መጠበቅ በቅድስና ለመኖር የሚያስችል ነው፤ ይህም በክርስቶስ ያለ ባሕርይ ነው፡፡ በየግላችን ብቻ ሳይሆን በቤተክርስቲያንም ቅድስና ሊኖር ይገባል፤ «አቤቱ እስከ ረጅም ዘመን ድረስ ለቤትህ ቅድስና ይገባል» የሚለው ቃል በዚህ በጸጋው ዘመን ባለው የእግዚአብሔር ቤት ማለት በቤተክርስቲያንም ውስጥ ተግባራዊ ሊሆን የሚገባው ነው (መዝ.92፡5)፡፡ በተለይም በክርስትናው ዓለም ብዙ ውድቀት ሲታይ ራስን ከክፋትና ከክፉ ሰዎች ለይቶ በግልም ሆነ በማኅበር ለጌታ የተቀደሱ (የተለዩ) መሆን ይገባል፡፡ ይህም በፊልድልፍያ ቤተክርስቲያን በግልጽ ይታያል፤ ይህም የሚገኘው ለቃሉ በተሰጠው ትኲረትና ቃልን በተግባር በመጠበቅ ነው፡፡
በመቀጠልም የፊልድልፍያ አማኞች ስሙን አለመካዳቸው በጌታ ዘንድ እውቅና የተሰጠው ወይም የተመሰገነው ሁለተኛው ገጽታቸው ነበር፡፡ “ስሙን አለመካድ” ማለት በቤተክርስቲያን ያለውን የእርሱን የባለቤትነት ሥልጣን አለመግፋትን የሚያሳይ ነው፡፡ ከመጀመሪያውኑ ወንጌል ሊሰበክ የሚገባው በእርሱ ስም መሆን አለበት፤ ይህንንም ራሱ ሲናገር «ክርስቶስ መከራ ይቀበላል፤ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል፤ በስሙም ንስሐና የኃጢአት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ ይሰበካል ተብሎ እንዲህ ተጽፏል» ብሏል (ሉቃ.24፡46-47)፡፡ ከዚያም በተሰበከላቸው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ያመኑ ሰዎች በስፍራቸው በቤተክርስቲያንነት በሚሰበሰቡ ጊዜ ሊሰበሰቡ የሚገባቸው በእርሱ ስም ነው፡፡ እርሱ በመካከላቸው ሊገኝ የሚችለውም በስሙ ሲሰበሰቡ ነው፤ ይህንንም እውነታ ያስተማረው ራሱ ጌታ ኢየሱስ ሲሆን «ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ እኔ በመካከላቸው እሆናለሁና» በማለት በግልጽ ተናግሯል (ማቴ.18፡20)፡፡ በመቀጠልም በግልም ሆነ በማኅበር አማኞች ወደ እግዚአብሔር በጸሎትም ሆነ በአምልኮ ሲቀርቡ ተቀባይነትን ያገኙ ዘንድ በኢየሱስ ስም ሊቀርቡ እንደሚገባቸው ተነግሮናል፤ በዮሐ.14፡13-14 ላይ «እኔ ወደ አብ እሄደለሁ፤ አብ ስለ ወልድ እንዲከበር በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ፤ ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ» በማለት ጌታ የተናገረውን ቃል እናገኛለን፡፡ በኤፌ.5፡20 ላይ ደግሞ «ሁልጊዜ ስለ ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምላካችንንና አባታችንን ስለሁሉ አመስግኑ» የሚል ቃል እናነባለን፡፡ በአጠቃላይ የክርስቶስ የሆኑት ሁሉ እርሱ በአካል ወደ ሰማይ ዐርጎ በእግዚአብሔር ቀኝ ባለበት በዚህ ዘመን በምድር ላይ የሚያደርጉትን ሁሉ በእርሱ ስም ሊያደርጉት ይገባል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ይህንኑ እውነት ጠቅለል ባለ መልኩ ሲገልጽ «እግዚአብሔር አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት» ይላል (ቈላ.3፡17)፡፡ በፊልድልፍያ ቤተክርስቲያን ያሉ አማኞች ይህን በታማኝነት የሚያደርጉ ስለነበር «ስሜን አልካድህምና» ተብሎ ተመስክሮላቸዋል፡፡ ስለሆነም ከክርስቶስ ስም ይልቅ ሌሎች ብዙ ስሞች ከሚሰበኩበት፣ መሰባሰቢያ ወይም ወደ እግዚአብሔር መቅረቢያ ከተደረጉበት ሥርዓት ተለይተን እንደ ፊልድልፍያ ቤተክርስቲያን የምናደርገውን ሁሉ በኢየሱስ ስም ልናደርግ ይገባል፡፡
«እነሆ አይሁድ ሳይሆኑ አይሁድ ነን ከሚሉ ነገር ግን ከሚዋሹ ከሰይጣን ማኅበር አንዳንዶችን እሰጥሃለሁ፤ እነሆ መጥተው በእግሮችህ ፊት ይሰግዱ ዘንድ እኔም እንደወደድሁህ ያውቁ ዘንድ አደርጋቸዋለሁ» (ቊ.9)
በዚህ ንባብ ውስጥ ቀደም ሲል በሰምርኔስ ለነበረች ቤተክርስቲያን የተላከውን መልእክት ስናጠና የተመለከትናቸውን «የሰይጣን ማኅበር» የተባሉትን እናገኛለን፡፡ የዚህ የሰይጣን ማኅበር ዋነኛ መገለጫ ሆኖ የተጠቀሰው ውሸት ነው፤ «የሚዋሹ» ተብለዋልና፤ ውሸት (ሐሰት) ደግሞ የሰይጣን ዋነኛ ባሕርዩ ከመሆኑም ሌላ የውሸት መነሻ፣ ምንጩም እርሱው ነው፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለዚህ ጉዳይ ለአይሁድ ሲናገር «እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ፤ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ፤ እርሱ ከመጀመሪያው ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለሌለ በእውነት አልቆመም፤ ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፤ ሐሰተኛም የሐሰትም አባት ነውና፡፡» ብሏል (ዮሐ.8፡44-45)፡፡ ስለሆነም እነዚህ «የሚዋሹ» የተባሉት ሰዎች «የሰይጣን ማኅበር» ተብለው መጠራታቸው አግባብ ነው፡፡ ውሸታቸውም ያልሆኑትን ነን ማለታቸው እንደሆነ ከንባቡ መረዳት ይቻላል፤ «አይሁድ ሳይሆኑ አይሁድ ነን የሚሉ» ተብለዋልና፡፡ እነዚህ ሰዎች ከአይሁድም ሆነ ከአሕዛብ ወደ ክርስትና ከገቡ በኋላ እንደገና ራሳቸውን ከጸጋ በታች ከመሆን አውጥተው ከሕግ በታች ለማድረግ ወደ አይሁዳዊነት ያፈገፈጉ ሰዎች ናቸው፡፡
ለምሳሌ የዕብራውያን ክርስቲያኖች ከመጀመሪያውኑ አይሁድ ነበሩ፤ ሆኖም ክርስቲያን ከሆኑ በኋላ እንደገና ወደ አይሁድ ሥርዓት ሲመለሱ ታይተው ነበር (ዕብ.10፡33-39)፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የገላትያ አማኞች ከአሕዛብ ወደ ክርስትና የገቡ ነበሩ፤ ሆኖም ተገርዘው ሕግን እንዲጠብቁ በሐሰት አስተማሪዎች በተሰበከላቸው ልዩ ወንጌል ምክንያት ወደ አይሁዳዊነት ሲወድቁ ታይተዋል (ገላ.1፡6-7)፡፡ እንዲህ ያሉትን አማኞች እንደገና ወደ ጸጋው ወንጌል ለመመለስ ብዙ ጥረት የተደረጉ ቢሆንም ሳይመለሱ የቀሩት ግን «ሐሰተኛ ወንድሞች» ሆነው ቀጥለዋል፡፡ እነርሱም የአባታቸውን የሰይጣንን ባሕርይ በመላበስ «ተንኰለኞች ሠራተኞችና ውሸተኞች ሐዋርያት» ሆነዋል (2ቆሮ.11፡13-15)፤ በገላ.6፡13 ላይ «በሥጋችሁ እንዲመኩ ልትገረዙ ይወዳሉ እንጂ የተገረዙት ራሳቸው እንኳ ሕግን አይጠብቁም» ተብሎ እንደተጻፈው በተግባር የማያደርጉትን በቃል ብቻ የሚሰብኩ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ናቸው፤ ጳውሎስ በሮሜ.2፡21-23 እንደገለጸውም አትስረቅ ብለው እየሰበኩ የሚሰርቁ፣ አታመንዝር ብለው እየሰበኩ የሚያመነዝሩ፣ ጣዖትን እየተጸየፉ ቤተመቅደስን የሚዘርፉ፣ በአጠቃላይ በሕግ እየተመኩ ሕግን የሚተላለፉ ናቸው፤ በእርግጥም «የሚዋሹ» ናቸው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ እነዚህ ሰዎች አይሁድ ነን ይላሉ እንጂ በተግባር ሲታዩ አይሁድ አይደሉም፤ ስለ እውነተኛ (ልባዊ) አይሁዳዊነት መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር «በግልጥ አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ አይደለምና፤ በግልጥ በሥጋ የሚደረግ መገረዝም መገረዝ አይደለምና፡፡ ዳሩ ግን በስውር አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ ነው፡፡ መገረዝም በመንፈስ የሚደረግ የልብ መገረዝ ነው እንጂ በመጽሐፍ አይደለም፤ የእርሱ ምስጋና ከእግዚአብሔር ነው እንጂ ከሰው አይደለም፡፡»ይላል (ሮሜ.2፡28-29) ስለዚህ እውነተኛ አይሁዳዊ ልቡ በመንፈስ የተገረዘለትና ከዚህም የተነሣ በሕጉ የተገለጠውን መልካም ነገር ይዞ የተገኘ እንጂ በአፍአዊ ቅርጹ ብቻ በሥጋ ተገርዞ በሕግ እየተመካ በተግባር ግን ሕጉን የማይጠብቀው አይደለም፡፡ በፊልድልፍያ ቤተክርስቲያን (ማኅበር) ውስጥ ግን «ቃሌን ጠብቀሃል» ብሎ ጌታ እንደተናገረው ቃሉ በተግባር ይጠበቃል፤ ስለሆነም እውነተኝነት በተግባር የሚገለጥበት ሁኔታ አለ፤ በመሆኑም ጌታ ቅዱስና እውነተኛ ሆኖ ራሱን አቅርቦላቸዋል፡፡ አይሁድ ሳይሆኑ አይሁድ ነን በሚሉት ሐሰተኞች ዘንድ ግን «የእውነት መልክ» (ሮሜ.2፡20) እንጂ እውነተኝነት የለም፡፡ «የአምልኮ መልክ» እንጂ ኃይል ያለው እውነተኛ አምልኮ የለም (2ጢሞ.3፡5)፡፡
እነዚህ «የሚዋሹ»፣ «የሰይጣን ማኅበር» የተባሉ ሰዎች በፊልድልፍያ ያሉትን እውነተኛ አማኞች የሚጠሉና የሚቃወሙ እንደሆነ ግልጽ ነው፤ እንዲያውም እነርሱ የሚጠሏቸውን ያህል ጌታም የሚጠላቸው ይመስላቸው ይሆናል፡፡ ነገር ግን ጌታ ለፊልድልፍያው አማኝ «መጥተውም በእግሮችህ ፊት እንዲሰግዱ አደርጋቸዋለሁ፤ እኔም እንደወደድሁህ ያውቁ ዘንድ አደርጋቸዋለሁ» በማለት ወደፊት እርሱን ከፍ አድርጎ «የሰይጣን ማኅበር» የተባሉትን ግን እንደሚያዋርዳቸው ነግሮታል፤ «በእግሮችህ ፊት እንዲሰግዱ አደርጋቸዋለሁ» የሚለው ቃል «በሰማይና በምድር ከምድር በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ ...» ተብሎ እንደተጻፈ ሁሉም ለጌታ በሚገዛበት ጊዜ እነዚህ የሰይጣን ማኅበረተኞች የጌታ በሆኑት ፊት ለጌታ እንዲሰግዱ ሲደረጉ የሚፈጸም ነው፤ ይህም ከእምነት የሚመጣ ፈቅደው የሚያደርጉት ሳይሆን በሁኔታው አስገዳጅነት ተሸንፈው የሚያደርጉት ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩም «እኔም እንደወደድሁህ ያውቁ ዘንድ አደርጋቸዋለሁ» ማለት እነርሱ ይህን አውቀው ወደ ጌታ ዘወር እንደሚሉ የሚያሳይ ሳይሆን እግዚአብሔር የጽድቅ ፍርዱን ያሳያቸው ዘንድ ብቻ የሚያደርገው መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡
ዛሬም በፊልድልፍያ ቤተክርስቲያን ጠባይ ቃሉን በመጠበቅና ስሙን ባለመካድ ሊኖሩ የሚወዱትን አማኞች አይሁዳዊ ጠባይን የተላበሱ በተግባራቸውም የተነሣም የሰይጣን ማኅበር ሊባሉ የሚችሉ ሰዎች በእጅጉ ሊጠሏቸው ይችላል፡፡ የተለያዩ ተቃውሞዎችና ስደቶችም ሊደርስባቸው ይችላል፡፡ ሆኖም ሁሉን በእግሮቹ ሥር የሚያስገዛው ጌታ የእርሱ የሆኑትን ሲያከብር የሰይጣን የሆነውን ሁሉ እንዴት እንደሚያዋርደው በተነገረው የተስፋ ቃል በእጅጉ ሊበረታቱ ይገባል፡፡
«የትዕግሥቴን ቃል ስለጠበቅህ እኔ ደግሞ በምድር የሚኖሩትን ይፈትናቸው ዘንድ በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ካለው ከፈተናው ሰአት እጠብቅሃለሁ፡፡ እነሆ ቶሎ ብዬ እመጣለሁ ማንም አክሊልህን እንዳይወስድብህ ያለህን አጽንተህ ያዝ» (ቊ.10-11)
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሳቸውን ከእርሱ ጋር ቆጥረው የትዕግሥቱን ቃል ለጠበቁት የፊልድልፍያ አማኞች የሰጣቸውን የከበረ የተስፋ ቃል በዚህ ንባብ ውስጥ እናያለን፡፡ እርሱ «ትዕግሥቴ» ብሎ የሚጠራው ነገር የአማኞችም ትዕግሥት ሊሆን ይገባዋል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ «ጌታም ወደ እግዚአብሔር ፍቅር ወደ ክርስቶስም ትዕግሥት ልባችንን ያቅናው» ይላል (2ተሰ.3፡5)፡፡ የክርስቶስ ትዕግሥት እርሱ ወደፊት ሊይዘው ያለውን የከበረ መንግሥቱን በተስፋ እንዲጠብቅ ያደረገውን የእርሱን የተባረከ ስሜት ያሳየናል፡፡ ጌታ ኢየሱስ በሥጋ ሲገለጥ ጌታ አምላክ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን እንደሚሰጠው፣ በያዕቆብ ቤት ላይ ለዘላለም እንደሚነግሥ ለመንግሥቱ መጨረሻ እንደሌለው ተነግሮለታል (ሉቃ.1፡32-33)፤ እንደዚሁም መሢሕ መሆኑ ተመስክሮለታል፤ ነገር ግን መንግሥቱን ሳይረከብ (ሳይነግሥ) መሢሑ ተገደለ፡፡ አባቱም «ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ» አለው (የሐ.ሥ.2፡35)፤ ስለሆነም አሁን በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ «ጠላቶቹ የእግሩ መረገጫ እስከሚሆኑ ድረስ ወደ ፊት ይጠብቃል» (ዕብ.10፡13)፡፡ በትዕግሥት የሚጠብቀውም ወደፊት የእርሱ ከሆኑት ጋር የሚነግሥበትን የከበረ መንግሥት ነው፤ “የክርስቶስ ትዕግሥት” የተባለውም ነው፡፡ እኛም ከእርሱ ጋር እንደምንነግሥ ተስፋ ተገብቶልናል (2ጢሞ.2፡11)፤ ስለዚህ ከእርሱ ጋር በትዕግሥት መጠባበቅ አለብን (ሮሜ.8፡25)፡፡ የፊልድልፍያው አማኝ «የትዕግሥቱን ቃል ስለጠበቅህ» የተባለው ከክርስቶስ ጋር የምንይዘውን የወደፊቱን የከበረ ስፍራ ለመያዝ ከእርሱ ጋር በትዕግሥት መጠባበቅ እንደሚገባ የተነገሩትን ቃላት የጠበቀ ወይም ያከበረ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡
በትዕግሥት የጠበቀውን ተስፋ ያገኝ ዘንድ የሚያስችለውን ማረጋገጫ ጌታ ሲሰጠውም «በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ካለው ከፈተናው ሰዓት እጠብቅሃለሁ» ይለዋል፡፡ እዚህ ላይ ጌታ አማኙን የሚጠብቀው «ከፈተናው» ብቻ ሳይሆን «ከፈተናው» ሰዓት መሆኑን ልብ ልንል ይገባል፡፡ ይህም ቃል የክርስቶስ አካል የሆነችውና እውነተኛ አማኞችን ብቻ የያዘችው አንዲቱ ቤተክርስቲያን ወደ ፈተናው ሰዓት እንደማትገባ፣ ከዚያ በፊት ጌታ እንደሚወስዳት የሚያረጋግጥ ነው፡፡
«የፈተናው ሰዓት» የተባለውም ወደፊት በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ያለው የመከራና የፍርድ ዘመን ነው (ዳን.12፡1፤ ማቴ.24፡21)፡፡ እርሱም በትንቢተ ዳንኤል ላይ የተገለጠው ሰባኛው ሱባኤ ነው (ዳን.9፡24-27)፤ በዚህም ጊዜ ውስጥ የክርስቶስ ተቃዋሚው በተአምራትና በምልክቶች በሐሰተኛ ድንቆችም ብዙዎችን ያስታል (2ተሰ.2፡10፤ ራእ.13፡11-18)፤ በዚህም የተነሣ በቅድሚያ “የምጥ ጣር መጀመሪያ” የተባሉት ፍርዶች (ማቴ.24፡8)፣ በመቀጠልም ”ታላቁ መከራ” (ማቴ.24፡21) የተባለው ፍርድ በዓለም ሁሉ ላይ ይመጣል፡፡ እነዚህ ሁሉ ፍርዶች በቤተክርስቲያን ላይ አይደርሱም፤ ምክንያቱም የፈተናው ሰዓት የሚመጣው “በምድር የሚኖሩትን ይፈትናቸው ዘንድ” እንደሆነ ጌታ ተናግሯልና፤ “በምድር የሚኖሩትን” የሚለው ይህ አገላለጽ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ በተደጋጋሚ እናገኘዋለን (ራእ.6፡10፤ 11፡10፤ 13፡14፤ 17፡8)፤ በሁሉም ስፍራ የሚያመለክተው በገጸ-ምድር ላይ በነዋሪነት ያሉ ለማለት ሳይሆን በምድራዊ ሐሳብና በምድራዊ ተስፋ የሚኖሩ ለማለት ነው፡፡ የፈተናው ሰዓት የሚመለከታቸው በአሁኑ ዘመን ሐሳባቸውም ሆነ ተስፋቸው ምድራዊ የሆኑትን ነው፤ ቤተክርስቲያንን በተመለከተ ግን «ከሰማያዊ ጥሪ ተካፋዮች» መሆናችን ተገልጧል (ዕብ.3፡1)፤ ስለዚህ እኛ በዚህ ዘመን በሰማያዊ ሐሳብና በሰማያዊ ተስፋ እንኖራለን፡፡ «እኛ አገራችን በሰማይ ነውና» ተብሎ እንደተጻፈ በምድር ብንኖርም ሰማያዊ አገርን እንናፍቃለን (ፊልጵ.3፡20)፡፡ ስለሆነም ጌታ ለቅዱሳኑ እስከ አየር ሲመጣ ያን ጊዜ በደመና እንነጠቃለን፤ የእርሱን ክቡር ሥጋ እንዲመስል በተለወጠ በከበረ ሰውነት ወደ አገራችን ወደ ሰማይ እንገባለን፡፡ የፈተናው ሰአት የሚጀምረው ከዚያ በኋላ ነው፡፡ በፊልድልፍያ ሕይወት እየኖሩ የኢየሱስን የትዕግሥት ቃል የሚጠብቁ ሁሉ ዕድል ፈንታቸው ከፈተናው ሰዓት በፊት ከእርሱ ጋር ሊኖሩ ወደ ሰማይ መወሰድ መሆኑን በማመን ሁልጊዜ የሚፍለቀለቅ ደስታ ልባቸውን ሊሞላው ይገባል፡፡ የክርስቶስ የሆኑት ሁሉ የፈተናው ሰአት ሊያሰጋቸው አይችልም፡፡ የምታገሠውስ እስከ መቼ ነው? በሚል ሊሰላቹ አይገባም፤ ምክንያቱም ለእኛ የዘገየ ቢመስለን እንኳ «ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም» (2ጴጥ.3፡9)፡፡
ስለዚህ ጌታ ለፊልድልፍያው አማኝ «እነሆ ቶሎ ብዬ እመጣለሁ» ብሎታል፡፡ በመሆኑም መታሰብ ያለበት ጉዳይ ከሚመጣው ቊጣ ማለት ከፈተናው ሰዓት ስለመዳን ሳይሆን በሰማይ ከጌታ ልንቀበለው ስለሚገባን ብድራት (ዋጋ) ብቻ ሊሆን ይገባል፡፡ ምክንያቱም መዳናችን አንድ ጊዜ ተረጋግጧልና፤ ያን በተመለከተ ምንም ጥያቄ ሊኖረን አይችልም፡፡ ከዳንን በኋላ ግን ከእርሱ ልንቀበለው ያለውን አክሊል አስመልክቶ ግን ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል፤ ለዚህም ነው ጌታ «ማንም አክሊልህን እንዳይወስድብህ ያለህን አጽንተህ ያዝ» ያለው፤ «አክሊል» በክርስቶስ ሞት ያገኘነውንና በጸጋ የተሰጠን ለዘላለም ሕይወት (መዳናችንን) የሚመለከት አይደለም፡፡ ነገር ግን የዳኑና የዘላለም ሕይወት ያገኙ ሰዎች በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት ቀርበው የሚቀበሉትን ሽልማት ወይም የመልካም ሥራ ዋጋ የሚያመለክት ነው (2ቆሮ.5፡10)፡፡ ጌታ ኢየሱስ ስለዚህ ጉዳይ ሲናገር «እነሆ በቶሎ እመጣለሁ፤ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ» ብሏል፡፡ ስለዚህ ጌታ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ዋጋ የሚከፍልበት ጊዜ ወደ ፊት ሲመጣ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ያን ጊዜ ጌታ ለእያንዳንዱ አማኝ የሚያስረክበው የመልካም ሥራ ዋጋ (አክሊል) የጽድቅ አክሊል (2ጢሞ.4፡8)፣ የክብር አክሊል (1ጴጥ.5፡4)፣ የሕይወት አክለል (ያዕ.1፡12፤ ራእ.2፡11) ተብሎ ተጠርቷል፡፡ ጌታ እንደ ፊልድልፍያ አማኞች ላሉት ሁሉ እነዚህን አክሊሎች በቶሎ በሚመጣበት ጊዜ ሊሰጣቸው ተዘጋጅቷል፡፡ ሆኖም በአንዳች ስንፍና ምክንያት እነዚህ ብርቱ የነበሩ አማኞች የነበራቸውን መልካም ነገር አጽንተው(አጥብቀው) ካልያዙ ማለት የሚዳከሙና የሚተዉት ከሆነ አክሊላቸውን ሊያጡ ይችላሉ፡፡ ይህ እንዳይሆን «ያለህን አጽንተህ ያዝ» ተባለ፤ እንዲያውም ባላቸው(በያዙት) ነገር ላይ ሊጨምሩ ይገባቸዋል፡፡ «ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ ድካማችሁ በጌታ ከንቱ እንዳይሆን አውቃችኋልና የምትደላደሉ፣ የማትነቃነቁም፣ የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ፡፡» ተብሏልና (1ቆሮ.15፡58)፡፡ የጌታ ሥራ በበዛላቸው መጠን አክሊላቸውም ይበዛልና፡፡
በፊልድልፍያ ላለች ቤተክርስቲያን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተላለፈው መልእክት በትንቢታዊ ገጽታው በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ እስከ ጌታ መምጣት ድረስ በሚቆየው የክርስትና ዓለም መካከል የሚገኙትን ለጌታ የታመኑትን ቅዱሳን ያመለክታል፡፡ በትያጥሮን ለነበረች ቤተክርስቲያንና በሰርዴስ ለነበረች ቤተክርስቲያን በተላኩ መልእክታት ውስጥ የጌታ መምጣት የተነገረ በመሆኑ የእነዚህ ቤተክርስቲያናት አስከፊ ገጽታ በክርስትናው ዓለም እስከ ጌታ መምጣት የሚቀጥል መሆኑን ቀደም ሲል መመልከታችን ይታወሳል፡፡ አሁን ደግሞ በእነዚህ ሁኔታዎች መካከል መታየት ጀምሮ ተገልጦ እስከ ጌታ መምጣት የሚቀጥለውን የፊልድልፍያ ቤተክርስቲያንን ብሩህ ገጽታ እንመለከታለን፡፡
በቤተክርስቲያን ታሪክ በክርስትና ላይ የበላይነት ይዞ በታየው የኤልዛቤል ትምህርትና ከዚያም ቀጥሎ ጎልቶ በታየው ሕይወት የሌለው የስም ክርስትና ላይ የነቁ አማኞች የእውነትን ቃል በትክክል በማጥናትና ለጌታ በመለየት የታመነ ምስክርነት መስጠት እንደጀመሩ ከ19ኛው ክፍለዘመን መጀመሪያ አንስቶ ያለውን የቤተክርስቲያን ታሪክ በማየት መገንዘብ እንችላለን፡፡ እንደሚታወቀው ጽድቅ በእምነት ብቻ እንደሆነ የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በ16ኛው ክፍለ ዘመን በነበረው የተሐድሶ እንቅስቃሴ አማካኝነት ቀደም ብሎ ተገልጦ እንደነበር ተመልክተናል፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ ሥራ የተጠናቀቀውን መዳን ከሚገልጸው ከዚህ መሠረታዊ እውነት ቀጥሎ ያሉት እውነቶች ግን ገና ወደ ብርሃን አልወጡም ነበር፡፡ ሆኖም የእግዚአብሔር መንፈስ በየትኛውም ክፍለ ዘመን እንደሚሠራው ሁሉ በ19ኛው ምዕተ ዓመት መጀመሪያ አንስቶ ባሉት ዓመታት ውስጥም በተለያዩ ስፍራዎች የክርስትና እምነት ድርጅቶች (ዲኖሚኔሽንስ) ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ክርስቲያኖችን ለቅዱሳት መጻሕፍት እውቀት ከፍተኛ ፍላጐት እንዲኖራቸው በማድረግ ልባቸውን የማንቃት ሥራን ይሠራ ነበር፡፡
በዚያ ወቅት በብሉይ ኪዳን በነቢያት መጻሕፍት ተነግረው ፍጻሜ ያላገኙ ትንቢቶችን በተመለከተ እርግጡን ለማወቅ ጥናቶች መደረግ ጀመሩ፡፡ በተለይም የእስራኤልን መመለስና የሺህ ዓመት መንግሥትን የሚመለከቱ መጻሕፍት እየታተሙ ተሰራጩ፡፡ ከዚህም ሌላ ቤተክርስቲያን በሰማይ ባለው በአንዱ ራስ በክርስቶስ የምትመራ የክርስቶስ አካል የመሆኗ እውነት ትኲረት ተሰጥቶት በአግባቡ እየተጠና በአማኞች መካከል መገለጥ ጀመረ፡፡ ስለሆነም ቤተክርስቲያን በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ ባለ ተዋረድን በተከተለ በሰው አደረጃጀት መመራቷ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እንዳልሆነ ታወቀ፤ እንደዚሁም አንድ ጊዜ በክርስቶስ አምኖ የዳነ ሰው ለዘላለም ተቀባይነትን ያገኘና ወደ ፍርድ የማይመጣ የመሆኑም እውነት በዘመናት ውስጥ ተዳፍኖ ከኖረ በኋላ በይፋ መታወቅ የጀመረው ያን ጊዜ ነበር፡፡ ይሁንና እነዚህን እውነቶች እየተረዱ በያሉበት ስፍራ ይመሰክሩ የነበሩት ቅዱሳን ከነበሩባቸው የእምነት ድርጅቶች እየተገፉ መውጣት ጀመሩ፤ ወዴት እንደሚሄዱ ሳያውቁ ቢወጡም ከወጡ በኋላ እንዴት መሰብሰብ እንዳለባቸው ማጥናት ጀመሩ፡፡ መሰብሰብ የጀመሩትም በየቤታቸው ሲሆን በዚያም ለጸሎትና ለቅዱሳት መጻሕፍት ጥናት እየተሰባሰቡ ሳለ ጌታ በእነርሱ ላይ ሌሎችን ይጨምር ነበር፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላም ቤተክርስቲያን መሰብሰብ ያለባት በዙሪያቸው እንዳለው ሥርዓት በሃይማኖት ስም ሳይሆን በኢየሱሰ ስም መሆኑን ከመጽሐፍ ቅዱስ ስለተረዱ (ማቴ.18፡20) በዚሁ መሠረት በኢየሱስ ስም መሰባሰባቸውን ቀጠሉ፤ ይህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለፊልድልፍያ ቤተክርስቲያን «ስሜን አልካድህምና» በማለት የገለጠውና ለስሙ የተሰጠውን ክብር ከሚገልጹት ነገሮች አንዱ ነው፡፡
እነዚህ አማኞች ከቃሉ የተገለጠላቸውን እውነት በስፋት ከማዳረስ አንጻር የተለያዩ ትራክቶችን፣ የተወሰነ ጊዜ ጠብቀው የሚታተሙ ጽሑፎችንና መጻሕፍትን እያሳተሙ ማሰራጨታቸው ከፍተኛ ውጤት አስገኝቷል፡፡ መንፈስ ቅዱስ የብዙዎችን ልብ ወደ እውነት ለመምራት የተሰራጩትን መንፈሳዊ ጽሑፎች ተጠቅሞቦት ነበር፤ እነዚህን ጽሑፎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እያነጻጸሩ በማንበብ እውነቱን የተረዱና የተቀበሉ ብዙ ሰዎች የነበሩባቸውን የእምነት ድርጅቶች (Denominations) እየተዉ ለጌታ ተለዩ፡፡ በዚህ ምክንያት ጌታ በእነዚህ አማኞች ላይ ከዚህ በፊት ሲወዱአቸው ሲያከብሯቸው ከነበሩ ከቅርብ ወገኖቻቸው ጭምር እጅግ ብዙ ስደትና መከራ ደርሶባቸዋል፡፡ እንዲሁም እነዚህ አማኞች ከየትኛውም ቤተ እምነት (ዲኖሚኔሽን) እንዳልሆኑ ሲታወቅ በየቤተ እምነቱ ካሉ መሪዎችና ከተከታዮቻቸው ከፍተኛ ተቃውሞ ደረሰባቸው፤ ነገር ግን ሁል ጊዜም እንደሚሆነው ሁሉ የሚሰብኩት እውነት የበለጠ እንዲደመጥና ብዙዎችም ወደ ራሱ እንዲሳቡ ለማድረግ ጌታ የተነሣውን ተቃውሞና ስደት ለበጎ ተጠቀመበት፡፡ ምክንያቱም ተቃውሞው በጨመረ ቊጥር ብዙ ክርስቲያኖች በተለያዩ የሃይማኖት ስሞች ከሚሰበሰቡባቸው ስፍራዎች እየተለዩ በጌታ በኢየሱስ ስም ወደመሰብሰብ ይመጡ ነበር፡፡
እነዚህ ወደ ጌታ ስም የተሰበሰቡ አማኞች ግልጽ የሆነ ድርጅት ስላልሆኑ፣ ሥርዓተ ክህነትና የእምነት መግለጫ ስለሌላቸውና ፕሬዝዳንት ወይም አንድ የተሾመ አገልጋይ ስለሌላቸው አገልግሎታቸው ወዲያውኑ ያቆማል ብለው ያሰቡ ብዙዎች ነበሩ፡፡ ሆኖም ጌታ «ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡት በዚያ እኔ በመካከላቸው እሆናለሁና» ብሎ ለተሰጠው የተስፋ ቃል የታመነ ስለሆነ በመካከላቸው በመገኘት እርሱ አጸናቸው፡፡ እነርሱም በስሙ ተሰባስበው የጌታን ገበታ በመካከላቸው በመዘርጋት እንደ መጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች እንጀራውን ይቈርሱ ነበር (የሐ.ሥ.2፡42)፡፡ የዚያ ጉባኤ ባለቤትም ራሱ ጌታ ኢየሱስ መሆኑ በተግባር ተረጋግጦ ነበር፡፡ የጌታም ሥራ እየበዛ ሄደ፡፡ እንደዚሁም በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ቃሉ ለሚያስተምረው እውነት በቊርጠኝነት መታዘዝ ትልቅ ትኲረት ተሰጥቶት ነበር፤ ጌታ የተከፈተ የቃሉን ደጅ(በር) ስለሰጣቸው የእግዚአብሔርን ምስጢር እርሱንም ክርስቶስን ለማወቅ የሚጥሩ በመሆናቸው በመካከላቸው ለቃሉ ስፍራ ተሰጥቷል፤ ከዚህም ጋር በግልም ሆነ በጉባኤ የቃሉ ተግባራዊነት በግልጽ ይታያል፤ በመካከልም ዓመፃ በሚከሠት ጊዜ የእግዚአብሔርን ቤት ቅድስና የመጠበቅ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻር በእያንዳንዱ ዓመፅ ላይ እንዲፈረድበት ይደረጋል፡፡ ዓለማዊነትና ሥጋዊነት በአማኞች መካከል ዕድል እንዳያገኝ ቃሉን ማወቅ ብቻ ሳይሆን ቃሉን መጠበቅ መገለጫቸው ነው፡፡ «ጌታን በንጹሕ ልብ የሚጠሩ» እነዚህ አማኞች ለጌታ ለክብር የሚሆን የተቀደሰም ለጌታውም የሚጠቅም ለበጎም ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ዕቃ ይሆኑ ዘንድ ራሳቸውን ከውርደት ዕቃዎች ያነጹ ናቸው፤ በአንድነትም ሆነው «ጽድቅን፣ እምነትን፣ ፍቅርን፣ ሰላምን» አጥብቀው ይከተላሉ (2ጢሞ.2፡21-22)፡፡ ፊደላዊ ከሆኑ የሃይማኖት ሥርዓቶችም ተለይተው እግዚአብሔርን በመንፈስና በእውነት ያመልካሉ፤ እነዚህ አማኞች በተለያየ የዓለም ክፍል የሚገኙ ከነገድ ከቋንቋ ለጌታ የተለዩ እና በስሙ የተሰባሰቡ ወገኖች ናቸው፡፡
«ድል የነሳው በአምላኬ መቅደስ ዓምድ እንዲሆን አደርገዋለሁ፤ ወደፊትም ከዚያ ከቶ አይወጣም፤ የአምላኬን ስምና የአምላኬን ከተማ ስም ማለት ከሰማይ ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን አዲሱቱን ኢየሩሳሌምን፣ አዲሱንም ስሜን በእርሱ ላይ እጽፋለሁ፡፡» (ቊ.12)በፊልድልፍያ ያለው አማኝ «ድል የነሣው» ተብሎ ሲገለጽ በትያጥሮንና በሰርዴስ በነበሩ አብያተክርስቲያናት የታዩትን ክፋቶች ድል ማድረጉን የሚያሳይ ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ «አይሁድ ሳይሆኑ አይሁድ ነን የሚሉ ነገር ግን የሚዋሹ» ተብለው የተጠቀሱት ሰዎች የሚታይባቸውን አስመሳይነት ወይም አፍአዊነት የፊልድልፍያው አማኝ በእውነተኝነት ድል የነሣ መሆኑን እንደሚገልጽ መገንዘብ ይቻላል፡፡
ጌታ ኢየሱስ ለፊልድልፍያ ድል ነሺዎች በሰጠው የተስፋ ቃል ውስጥ «አምላኬ» የሚለውን ቃል በተደጋጋሚ ሲናገር እናያለን፡፡ በዮሐ.20፡17 «ነገር ግን ወደ ወንደሞቼ ሄደሽ እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደአምላካችሁ ዐርጋሁ ብለሽ ንገሪያቸው» በማለት ጌታ ከትንሣኤው በኋላ ለማርያም መግደላዊት የተናገረውን ቃል እናነባለን፡፡ «ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ» ሲል የእርሱ የሆኑትን ከራሱ ጋር መቊጠሩን «ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ» ሲል ደግሞ ራሱን የእርሱ ከሆኑት ጋር መቊጠሩን የሚያሳይ ነው፤ ይህም «ወንድሞቼ» በማለት የእርሱ የሆኑትን በመጥራቱ የሚታይ ነው፡፡ ስለሆነም በፊልድልፍያ ለነበሩት አማኞች በሰውነቱ በያዘው ስፍራ በመካከላቸው ሆኖ በባለቤትነት ሲናገር እናያለን፡፡
ጌታ ኢየሱስ ለድል ነሺዎቹ የሰጠው ይህ የተስፋ ቃል በሁለት ተከፍሎ ሊታይ ይችላል፡፡ የመጀመሪያው አማኙን በአምላኩ መቅደስ ዓምድ እንደሚያደርገው የሚገልጽ ነው፡፡ ዓምድ ምሰሶ ማለት ሲሆን ከመሠረት ቀጥሎ የሚገኝ አንድን ቤት የሚሸከም ነገር ነው፡፡ ስለሆነም ጠንካራነትን ወይም ብርታትን ያሳያል፡፡ ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ የፊልድልፍያ አማኞችን ብርቱ የሆነ እምነትና በተግባር የሚታይ ክርስቲያናዊ ሕይወት ለዘላለም እውቅና እንደሰጠው የሚያመለክት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በድል ነሺው ላይ ሦስት ስሞችን እንደሚጽፍ የሰጠው የተስፋ ቃል ነው፡፡ እነዚህም ሦስት ስሞች «የአምላኬ ስም»፣ «የአምላኬ ከተማ ስም» «አዲሱ ስሜ» በማለት ገልጿቸዋል፡፡ በድል ነሺዎች ላይ ስም መጻፉ እነርሱ ከባለ ስሙ ጋር ያላቸውን ሕያው ግንኙነት (መተሳሰር) የሚያመለክት ነው፡፡ ኢየሱስ የአምላኩን ስም በድል ነሺዎቹ ላይ ሲጽፍ እነዚያ አማኞች የአንዱ ሕያው አምላክ ሕዝብ መሆናቸውን ያሳያል፤ የአምላኬ ከተማ በማለት የጠራትን ከተማ «ከሰማይ ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደው አዲሲቱ ኢየሩሳሌም» ብሎ ጠቅሷታል፤ እርስዋም የበጉ ሚስት የተባለችው ቤተክርስቲያን መሆንዋን እናውቃለን (ራእ.21፡9)፡፡ ኢየሱስ በድል ነሺው ላይ የእርስዋን ስም መጻፉ ድል ነሺውን ወደፊት ከእርሱ ጋር ልትነግሥ ከእርሱ ጋር በክብር በምትገለጠው (ከሰማይ ከምትወርደው) ቤተክርስቲያን ውስጥ እንደቈጠረው ይገልጻል፡፡ “አዲሱ ስሜ” የሚለው ደግሞ ወደ ፊት ጌታ የሚይዘውን አዲስ ስፍራ የሚያሳይ ሲሆን ይህ አዲስ ስም በድል ነሺው ላይ መጻፉም አማኙ ወደፊት ከእርሱ ጋር የሚኖረውን አዲስ የክብር ግንኙነት የሚያመለክት ነው፡፡ ለፊልድልፍያ አማኞች የተሰጠው ይህ ተስፋም ቃሉን ለጠበቁትና ስሙን ላልካዱት በዘመናት ሁሉ ላሉ ድል ነሺ አማኞች የተሰጠ ተስፋ ነው፡፡
ክፍል ሰባት >>>>