ቤተክርስቲያን/Aclesia  

ክፍል 7

በሎዶቅያ ወዳለች ቤተክርስቲያን የተላከ መልእክት


በክብር ያለው ክርስቶስ በባሪያው በዮሐንስ በኩል የጊዜውንና የወደፊቱን ነገር የሚናገሩ መልእክታትን ከላከላቸው በእስያ ከነበሩት ከሰባቱ አብያተክርስቲያናት መካከል ሰባተኛዋ በሎዶቅያ የነበረች ቤተክርስቲያን ናት፤ ሎዶቅያ በታናሽ እስያ በነበረች በፍርግያ ክፍለ ሀገር ውስጥ የምትገኝ ታዋቂ ከተማ ነበረች፤ የቀደመ ስሟ ዲዮስፖሊስ (Diospolis) ቢሆንም በኋላ ላይ ግን አንጥያኮስ ቴዎስ (261-253 ከክ.በፊት) የተባለው ንጉሥ በሚስቱ ስም ሎዶቅያ ብሎ ጠርቷታል፡፡ ሎዶቅያ ለቈላስይስ ከተማ የምትቀርብ ሲሆን ወደ 17 ኪ.ሜ. ገደማ ብቻ ርቃ የምትገኝ ነበረች፤ ከተማይቱ በንግድ መስመር ላይ የነበረች ስትሆን ነዋሪዎቿም በሀብት የበለጸጉ ነበሩ፤ በኔሮን ቄሣር ዘመነ መንግሥት በ60 ዓ.ም. በመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት ሙሉ በሙሉ በወደመች ጊዜ ያለ መንግሥት እገዛ ራሳቸው መልሰው ሊገነቧት እንደቻሉ ተመዝግቧል፡፡ ሆኖም በአሁኑ ጊዜ ያለው የከተማይቱ ፍርስራሽ ሲሆን ቦታውም ኤስኪ-ሂሳር (Eski-hissar) በተባለ ስፍራ ይገኛል፡፡

በሎዶቅያ የነበረችው ቤተክርስቲያን የተጀመረችው እንዴት እንደነበር የምናውቀው ነገር ባይኖርም እንደሌሎቹ በእስያ እንዳሉት እንደ ሰባቱ አብያተክርስቲያናት ሁሉ ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን በነበረው የ3 ዓመት አገልግሎት አማካኝነት እንደነበር መገንዘብ ይቻላል (የሐ.ሥ.19፡10)፡፡ ጳውሎስ ወደዚያ ስለመሄድ አለመሄዱ የተመዘገበ ነገር ባይኖርም በሎዶቅያ ያሉት ቅዱሳን በልቡ ውስጥ ስፍራ እንደነበራቸው ሲገልጥ በቈላስይስ መልእክት ውስጥ «ስለእናንተና በሎዶቅያ ስላሉት ፊቴንም በሥጋ ስላላዩት ሁሉ እንዴት ያለ ትልቅ መጋደል እንዳለኝ ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ» በማለት ጽፏል (ቈላ.2፡2)፤ እንዲሁም በዚያ ለነበሩት ቅዱሳን ሰላምታን ሲያቀርብ «በሎዶቅያ ላሉት ወንድሞችና ለንምፉን በቤቱም ላለች ቤተክርስቲያን ሰላምታ አቅርቡልን» ብሏል (ቈላ.4፡15)፡፡ በተጨማሪም በሎዶቅያ ላለች ቤተክርስቲያን መልእክትን ጽፎ ነበር፤ ቈላስይስ እና ሎዶቅያ ተቀራራቢ ከተሞች እንደመሆናቸው መጠን ሐዋርያው ለሁለቱም የላካቸውን መልእክታት እየተቀባበሉ እንዲያነቧቸው ለቈላስይስ ሰዎች ሲጽፍ «ይህች መልእክት በእናንተ ዘንድ ከተነበበች በኋላ በሎዶቅያ ሰዎች ማኅበር ደግሞ እንድትነበብ አድርጉ፤ ከሎዶቅያም የምትገኘውን መልእክት እናንተ ደግሞ አንብቡ» ብሏል (4፡16)፡፡ ይህ ሁሉ የሚያሳየው ሐዋርያው ጳውሎስ በሎዶቅያ ከነበረች ቤተክርስቲያን ጋር የቅርብ ግንኙነት እንደነበረው ነው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፍጥሞ ደሴት በመንፈስ ለነበረው ለባሪያው ለዮሐንስ በተገለጠ ጊዜ መልእክትን ከላከላቸው ከሰባቱ አብያተክርስቲያናት መካከል በሎዶቅያ የነበረች ቤተክርስቲያን ሰባተኛዋና የመጨረሻዋ ቤተክርስቲያን ናት፤ የተላከላት መልእክትም በጊዜው የነበረውን የራሷን ሁኔታ የሚገልጽ ከመሆኑም ባሻገር በቤተክርስቲያን ዘመን መጨረሻ ላይ የሚገኘውን የክርስትናውን ዓለም ገጽታ በጉልህ የሚያሳይ ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍም ወቅታዊውንም ሆነ ትንቢታዊውን መልእክት ጌታ በገለጠልን መጠን ቀጥሎ እናቀርባለን፡፡

«በሎዶቅያ ወዳለው ቤተክርስቲያን እንዲህ ብለህ ጻፍ፤ አሜን የሆነው የታመነውና እውነተኛው ምስክር በእግዚአብሔር ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው እንዲህ ይላል» (ራእ.3፡14)

  1. አሜን የሆነው፣
  2. የታመነውና እውነተኛው ምስክር፣
  3. በእግዚአብሔር ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው የሚሉት ናቸው፡፡ እነዚህም ከሎዶቅያ ቤተክርስቲያን የሥነምግባር ሁኔታ አኳያ የቀረቡ የማንነቱ መገለጫዎች ሲሆኑ ቀጥሎ በየተራ እንመለከታቸዋለን፡፡፣

1.አሜን የሆነው

አሜን የሚለው ቃል በጸሎትም ሆነ በአምልኮ እንዲሁም ማናቸውም መንፈሳዊ ቃል በሚነገር ጊዜ ከተባለው ነገር ጋር መስማማትን ለማረጋገጥ የሚያገለግል ቃል ሲሆን (1ቆሮ.14፡16) ለአንድ ለተነገረ ቃል አሜን ለማለት በቅድሚያ ያንን ቃል አዎን ብሎ መቀበል ያስፈልጋል፤ ይህም ማለት ያ ቃል እውነት መሆኑን አረጋግጦ ከሙሉ ልብ መስማማትን ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ “አሜን” የሚባለው “አዎን” ለተባለ ነገር ነው፡፡ ሰዎች በሐዋርያት ለተሰበከውም ሆነ በቅዱሳት መጻሕፍት ለተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል አዎን ካሉ በመቀጠል አሜን ይላሉ፡፡ የእግዚአብሔር ቃል እውነትነት ደግሞ የተረጋገጠው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱ በሥጋ የተገለጠው «ጸጋንና እውነትን ተሞልቶ» እንደሆነ (ዮሐ.1፡14) ተጽፏል፡፡ ስለዚህ በክርስቶስ የተገለጠው ቃል ሁሉ ያለምንም ጥርጥርና «አዎን» ማለትም «እውነት» ስለሆነ እኛም በእርሱ «አዎን» ብለን ያለማወላወል ልንመሰክረው፣ ሰዎችም «አሜን» ብለው ሊቀበሉት ያስፈልጋል፤ ይህን በተመለከተ ሐዋርያው ጳውሎስ ሲናገር «ለእናንተ የሚነገረው ቃላችን አዎንና አይደለም አይሆንም፡፡ በእኛ ማለት በእኔና በስልዋኖስ በጢሞቴዎስም በመካከላችሁ የተሰበከ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ አዎንና አይደለም አልነበረም፤ ነገር ግን በእርሱ አዎን ሆኖአል፡፡ እግዚአብሔር ለሰጠው የተስፋ ቃል ሁሉ አዎን ማለት በእርሱ ነውና ስለዚህ ስለ ክብሩ በእኛ የሚነገረው አሜን በእርሱ ደግሞ ነው» ብሏል (2ቆሮ.2፡18-20)፡፡ ስለሆነም ጌታ በሎዶቅያ ላለች ቤተክርስቲያን «አሜን» የሆነው በማለት ራሱን ያስተዋወቀውም እርሱ “አዎን” የሆነው ማለትም የተረጋገጠው፣ የእግዚአብሔር እውነት መገለጫ በመሆኑ ነው፤ ለምሳሌ «እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ» የሚል የተስፋ ቃል በተናገረበት ክፍል ስለራሱ ሲናገር «እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ» ብሏል (ዮሐ.14፡3-6)፡፡ ስለሆነም ይህን «እውነት» የሆነውን ክርስቶስን የሚከተሉ አማኞች በቃልም በሥራም ሁልጊዜ እውነተኞች ሊሆኑ ይገባል፡፡ በእውነትና በውሸት መካከል መወላወል፣ በአንድ ጉዳይ ላይ አዎንና አይደለም እያሉ መቀላቀል ወይም ማምታታት፣ ወይም እውነተኛውን እውነት ለይቶ ለማወቅም ሆነ ለመታዘዝ ቸል ማለት፣ ወይም እውነትን እያወቁ ከሰው ሐሳብ ጋር ለማስማማትና ለማቻቻል መጣር የእውነተኛ አማኞች ጠባይ አይደለም፤ በሎዶቅያ ባለች ቤተክርስቲያን የነበረው ሁኔታ ለብ ባለ ማንነት በተገለጸው መሠረት እውነት በሙሉ ኃይሏ እንድትሠራ አለማድረግ ነበር፡፡ ከዚህ ዓለም የሚገኙ ጊዜያዊና ምድራዊ ነገሮችን ለማትረፍ ሲባል የተገለጠውን የእውነት ቃል በአማኞች ሕይወት በሙላት እንዳይሠራ ወይም በፍጹም ግልጽነት እንዳይነገር ማድረግ ለክርስቶስ ልብ አሳዛኝ ነው፤ ስለሆነም እርሱ ራሱን አሜን የሆነው ብሎ ማስተዋወቅ ተገብቶታል፡፡ በዘመናችንም ቢሆን ያለው ሁኔታ ተመሳሳይ ነው፡፡ የቃሉ እውነት ከምን ጊዜውም በላይ እየተሰበከና እየተጻፈ ቢሆንም አማኞች ግን ለቃሉ እውነት የሚሰጡት ተግባራዊ ምላሽ አናሳና ደካማ ሆኖ ይታያል፡፡ ምናልባት በአምልኮም ሆነ በጸሎት እንዲሁም ቃሉ በሚሰበክበት ጊዜ አሜን የሚለው ቃል እንደዚህ ዘመን አስገረግጦ የተባለበትና በብዛት የተሰማበት ዘመን አይኖርም ይሆናል፤ ነገር ግን ይህ አፍኣዊ እንጂ ተግባራዊ ባለመሆኑ የብዙ አማኞች ሕይወት «የእውቀት መልክ» እና «የአምልኮ መልክ» ይዞ ከመታየት አልፎ ኃይል ያለውና ድል የሚነሣ ሆኖ አልተገኘም፤ ስለዚህ ዛሬም ጌታ ለዚህ ዘመን አማኞች «አሜን የሆነው» እያለ ራሱን በቃሉ ይገልጣል፡፡

2.የታመነውና እውነተኛው ምስክር፣

በዚህ በጸጋው ዘመን ቤተክርስቲያን በምድር ላይ የምትገኝ የእግዚአብሔር ምስክር ናት፡፡ ሆኖም በቃልም ይሁን በተግባር ይህን ተግባሯን በታማኝነትና በእውነተኝነት መፈጸም ተስኗታል፡፡ በሎዶቅያ በነበረች ቤተክርስቲያን ይታይ የነበረውም ሁኔታም የዚህ ዓይነት ነበር፡፡ በመሆኑም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እነርሱ ከነበሩበት ሁኔታ በተቃራኒ ራሱን «የታመነውና እውነተኛው ምስክር» በማድረግ አቅርቦላቸዋል፡፡ ይህም የእርሱ ማንነት እነርሱ በምስክርነት ስፍራቸው ያልተወጡትን ኃላፊነት የሚገልጥ ነው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ እያስተማረ ሳለ «እውነት እውነት እልሃለሁ፤ የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን፤ ምስክራችንንም አትቀበሉትም» በማለት ተናግሯል (የሐ.3፡1)፡፡ በዚህም እርሱ የታመነ ምስክር መሆኑን አረጋግጧል፤ ምክንያቱም «የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውን እንመሰክራለን» ሲል የሚናገረው ራሱን ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አድርጎ ነው፡፡ በምድር ላይ በሥጋ ተገልጦ የታየው እርሱ «በሰማይ የሚኖር የሰው ልጅ ነው» (ዮሐ.3፡13)፤ እርሱ አንድስ እንኳ ያላየውን እግዚአብሔርን በተመለከተ የተረከው በሥጋ ተገልጦ ቢሆንም «በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጅ» ነበር (ዮሐ.1፡18)፡፡ ስለዚህ እርሱ የመሰከረው ሁሉ ከምንጩ የተገኘ ነው፤ እርሱ በመለኮት ዘንድ ባለው ስፍራ ያየውንና የሰማውን በሥጋ ተገልጦ መስክሯልና፡፡ ይህን በተመለከተም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እርሱ እውነተኝነት ሲናገር «እውነተኛ በሆነው በእርሱ አለን፡፡ እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው» ይላል (1ዮሐ.5፡20)፡፡ «ከላይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ ከምድር የሆነው የምድር ነው፤ የምድርንም ይናገራል፡፡ በሰማይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፡፡ ያየውንና የሰማውንም ይህን ይመሰክራል፤ ምስክርንም የተቀበለ እግዚአብሔር እውነተኛ እንደሆነ አተመ» ተብሎም ተጽፏል» (ዮሐ.3፡32)፡፡ ይህም ቃል እርሱ የታመነ ምስክር መሆኑን ያረጋግጣል፤ እርሱ በመለኮቱ ያየውንና የሰማውን በሥጋ ሆኖ መስከረ፤ ይህም ከሁሉም በላይ የታመነ ምስክር ያደርገዋል፡፡

እንዲሁም እርሱ እውነተኛ ምስክር ነው፡፡ በጲላጦስ ፊት ቀርቦ ስለማንነቱ በተጠየቀ ጊዜ «እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል» ብሎ ተናግሯል (ዮሐ.18፡37)፡፡ በመሆኑም ቃሉን በሚያስተምርበት ጊዜ «እውነት እውነት እላችኋለሁ» በማለት ምስክርነቱን ያጸና ነበር፡፡ (ዮሐ.5፡19፣25፤ 8፡34፣51፣58፤ 10፡1) ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ በምድር ላይ እውነተኛ ምስክር ሆኗል፡፡

ቤተክርስቲያንም ክርስቶስ በሰማይ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በዚህ ዘመን በምድር ላይ ለእግዚአብሔር የታመነና እውነተኛ ምስክር እንድትሆን ተጠርታለች፤ በሎዶቅያ የነበረችው ቤተክርስቲያን ግን የእግዚአብሔርን እውነት ከዓለማዊ ትምህርቶችና ልማዶች ጋር ለማስማማት ወይም ለማቻቻል ባደረገችው ሙከራ ለብ ባለ ሁኔታ ውስጥ በመግባቷ የታመነና እውነተኛ ምስክር ለመሆን አልቻለችም፡፡ ስለዚህ ይህን ሁኔታዋን በሚገልጥ መልኩ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን «የታመነውና እውነተኛው ምስክር» አድርጎ አቅርቦላታል፤ በዘመናችንም ከዓለማዊው ሥልጣኔ ወይም ከዘመናዊነት ጋር ለመስማማት ሲባል ለዘመናት ጸንቶ የኖረውን “የማይለወጠውን ቅዱሱን የወንጌል እውነት” ቸል ከማለት ጀምሮ በሰው ፊት ለመመስከር እስከማፈር ድረስ በክርስትናው ዓለም ታማኝነትና እውነተኝነት ጠፍቷል፡፡ ኢየሱስ ግን ዛሬም የታመነውና እውነተኛው ምስክር ሆኖ አለ፡፡

3.በእግዚአብሔር ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው፣

ይህን የክርስቶስን ማንነት እግዚአብሔር በፈጣሪነቱ ከፈጠረው ከሚታይና ከማይታይ ፍጥረት አኳያ ስንመለከተው እርሱ ማለትም ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ፍጥረት አስቀድሞ በመጀመሪያ በሕልውና የነበረ መሆኑን ያመለክታል፡፡ «... በሰማይ እና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኲር ነው፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል፤ እርሱም ከሁሉ በፊት ነው፡፡» (ቈላ.1፡15-17) ተብሎ ተጽፏል፡፡ እንዲሁም «በመጀመሪያው ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ፡፡ ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ሁሉ በእርሱ ሆነ፤ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም» ተብሎ የእርሱ ቀዳማዊ ህልውና በግልጽ ተነግሮናል (ዮሐ.1፡1-13)፡፡ እርሱ በመጀመሪያ የነበረ እንደመሆኑ ለፈጠረው ፍጥረት በኲር ሆኗል፡፡ ሆኖም ይህ ፍጥረት ኃጢአት ወደ ዓለም በመግባቱ አማካኝነት አስከፊ ገጽታን ይዞ ነበር፡፡ በኃጢአት የወደቀው ይህ የቀደመው ፍጥረት በእግዚአብሔር ፍርድ የሚጎበኝ እንጂ የሚሻሻል አልሆነም፡፡ ስለዚህ ክርስቶስ ወደ ዓለም ገብቶ በሥጋ ተገልጦ ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ ሆኖ ከሰው ጋር ተቈጠረ፤ ሞት ስለተፈረደበት ስለ ኃጢአተኛው ሰው ማለትም ስለ አሮጌው ፍጥረት ሞተ፡፡ ሆኖም ሞት ይይዘው ዘንድ አልቻለም፤ ከሙታን መካከል ተለይቶ በክብር ተነሣ፡፡ ይህም የአዲሱ የእግዚአብሔር ፍጥረት መጀመሪያ አደረገው፡፡ ስለዚህ «እኛ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም፤ ክርስቶስንም በሥጋ እንደሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም፤ ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፏል፤ እነሆ ሁሉም አዲስ ሆኗል» ይላል (2ቆሮ.5፡16-17)፡፡ ይህም ከእንግዲህ ወዲህ በሥጋ እንደሆነ የማናውቀው ማለትም ከሙታን የተነሣውና በክብር ያለው ክርስቶስ ተከታዮች የሆኑት ሁሉ አዲስ ፍጥረት መሆናቸውን ያሳያል፡፡ በሌላ ስፍራም «እኛ ፍጥረቱ ነንና እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን» የሚል ቃል እናነባለን፡፡ ይህም ፍጥረቱ የሚለው ቃል በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት የሆነውን ሁሉ ያመለክታል፡፡ ክርስቶስም በዚህ በአዲሱ የእግዚአብሔር ፍጥረት መጀመሪያ የነበረ ነው፡፡ የአዲሱ የእግዚአብሔር ፍጥረት መነሻ የክርስቶስ ትንሣኤ ነው፡፡ በእርሱ ያመኑ ሁሉ ደግሞ ከእርሱ ጋር አንድ ሆነዋል፤ ማለትም ከእርሱ ጋር የሞቱ ብቻ ሳይሆኑ ከእርሱ ጋር የተነሡም ናቸው (ሮሜ.6፡3-5፤ ቈላ.3፡1-3)፤ እነርሱ ለያዙት ለዚህ የትንሣኤ ሕይወት ጀማሪው እርሱ ክርስቶስ ነው፤ በቈላ.1፡18 ላይ «... እርሱ በሁሉ ፊተኛ ይሆን ዘንድ መጀመሪያ ከሙታንም በኲር ነው» ይላል፡፡ ከዚህ አኳያ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ፍጥረት መጀመሪያ የነበረ ሆኖ መገለጡ የአዲሱን ፍጥረት ሕያውነት የጀመረ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ታዲያ በሎዶቅያ ባለች ቤተክርስቲያን ውስጥ ሞትን ያሸነፈ አዲስ ሕይወት በተግባር የማይታይ ስለነበር ይልቁኑ በሥጋዊና በዓለማዊ ነገሮች በዚህ በምድር ላይ መመቻቸት ይታይ ስለነበረ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው ሆኖ ተገለጠ፡፡ የአዲሱ ፍጥረት እውነተኛ ጠባያት በማይታይበት የዘመናችን ክርስትናም ቢሆን ክርስቶስ ራሱን የሚገልጠው በዚሁ ማንነቱ ነው፡፡ ብዙ አማኞች በክርስትና ሕይወታቸው ቸልተኛ እንዲሆኑ ካደረጋቸው ነገር የሚወጡት በዚህ የክርስቶስ ማንነት ነው፡፡ «በራድ ወይም ትኲስ እንዳይደለህ ሥራህን አውቃለሁ፤ በራድ ወይም ትኲስ ብትሆንስ መልካም በሆነ ነበር፤ እንዲሁ ለብ ስላልህ በራድ ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው፡፡»(3፡15-16)

በዚህ የጌታ ቃል ውስጥ በሎዶቅያ ያለው አማኝ ማንነት በሥራው ሲመዘን ለብ ያለ መሆኑ ተገልጧል፡፡ እንደሚታወቀው ለሰውነት የሚያረካና የሚስማማ አይደለም፡፡ በሎዶቅያ ያለው አማኝ ሕይወትም መልካም ሥራን በአማኞች ላይ ለማየት ለተጠማው ጌታ የሚስማማ አልነበረም፡፡ «በራድ ወይም ትኲስ እንዳይደለህ ሥራህን አውቃለሁ፡፡» ካለ በኋላ ከሁለቱ አንዱን ቢሆን መልካም እንደነበረ ሲገልጽ «በራድ ወይም ትኲስ ብትሆን መልካም በሆነ ነበር» ይላል፡፡ ጌታ የሚፈልገው በሕይወቱ ትኲስ የሆነ አማኝ ቢሆንም ለብ ካለው አማኝ ግን በራድ የሆነው መልካም እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በራድ የሆነው ሰው ቢያንስ ወንጌልን ሰምቶ የመዳንና በመንፈስ የሚቃጠል ትኲስ አማኝ ይሆን ዘንድ ተስፋ አለው፡፡ ለብ ያለው ግን የእግዚአብሔርን እውነት በአንድ በኩል ይዞ በሌላ በኩል ከሰው ሐሳብና ከዓለማዊ ነገሮች ጋር ተስማምቶ ሁሉን አቻችሎ ለመኖር የሚፈልግ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ለሆነ ነገር ያለው ስሜት አነስተኛ ስለሆነ በኃጢአት ላይ ግልጽ ፍርድን በማድረግ ንስሐ ለመግባት፣ የቃሉን እውነት አስረግጦ ለመናገር፣ የዓለምና የሥጋ ከሆነ ነገር በግልጽና በቁርጠኝነት ለመለየት አይፈልግም፤ ከእግዚአብሔር መብት ይልቅ ለሰው ወይም ለሕዝብ መብት ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ ለእግዚአብሔር ነገሮች ግዴለሽ ነው፡፡ በሎዶቅያ ባለች ቤተክርስቲያን የነበረው ለብታ እንደዚህ ያለ ነበር፡፡ አማኝ ነኝ እያሉ በእንዲህ ያለ ለብታ ውስጥ መሆን ግን ለጌታ የማይስማማ በመሆኑ «ከአፌ ልተፋህ ነው» የሚል የፍርድ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶበታል፡፡ ይህም የክርስቶስን ስም በመጥራት፣ በክርስትስና ስምም በመጠራት ነገር ግን እውነትን በአስመሳይነትና በግዴለሽነት ለያዘው የክርስትና ዓለም የሚጠብቀውን የጌታ ፍርድ የሚያሳይ ነው፡፡ ስለሆነም ለጌታ ተስማሚ ካልሆነ የሎዶቅያ ለብታ በግልም ሆነ በማኅበር በእጅጉ ልንጠበቅ ያስፈልጋል፡፡

«ሀብታም ነኝና ባለጠጋ ሆኜአለሁ አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም የምትል ስለሆንህ ጐስቋላና ምስኪን ደሀም ዕውርም የተራቆትህም መሆንህን ስለማታወቅ ባለጠጋ እንድትሆን በእሳት የነጠረውን ወርቅ፣ ተጐናጽፈህ የራቁትነትህ ኃፍረት እንዳይገለጥ ነጭ ልብስን፣ እንድታይም ዓይኖችህን የምትኳለውን ኩል ከእኔ ትገዛ ዘንድ እመክርሃለሁ» (ራእ.3፡17-18)፡፡

በሎዶቅያ ያለው ነገር በሰምርኔስ ካለው ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር ተቃራኒ ነበር፡፡ በሰምርኔስ በነበረች ቤተክርስቲያን ውስጥ አማኙ በመከራና በድህነት ያለ ቢሆንም ጌታ ግን «ባለጠጋ ነህ» ይለዋል (ራእ.2፡9)፡፡ ይህም ባለጠግነት መንፈሳዊ ባለጠግነት ነበር፡፡ በሎዶቅያ ቤተክርስቲያን ግን አማኙ በመንፈሳዊ ነገር ደሀ ሆኖ እያለ የሚታየውን ሥጋዊ ነገር በመቊጠር «ሀብታም ነኝና ባለጠጋ ሆኜአለሁ፤ አንድ ስንኳ አያስፈልገኝም» በሚል ትምክህት ተይዟል፤ ይህን የሚለው በከተማዋ ሀብት ምክንያት ቊሳዊ ነገር ስለተሟላለት የተናገረው ሊሆን ይችላል፡፡ ጌታ ግን “ጐስቋላና ምስኪን ደሀም ዕውርም የተራቆትህ” ይለዋል፡፡ ስለዚህም ጌታ ሦስት ነገሮችን ከእርሱ እንዲገዛ ይመክረዋል፡፡ እነርሱም፡-

  1. ወርቅ
  2. ነጭ ልብስ እና
  3. ኲል ናቸው፡፡

1.ወርቅ

ጌታ የሎዶቅያውን አማኝ «ባለጠጋ እንድትሆን በእሳት የነጠረውን ወርቅ ... ከእኔ ትገዛ ዘንድ እመክርሃለሁ» ይለዋል፡፡ ወርቅ በብሉይ ኪዳን በታቦቱ ላይ የሚገኘው የስርየት መክደኛውና በዚያ ላይ የሚደረጉት ኪሩቤል የሚሠራበት እንደሆነ ይታወቃል (ዘጸ.25.17-18)፡፡ ሊቀ ካህናት በዓመት አንድ ጊዜ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ሲገባ ደም ይዞ ካልገባና በስርየት መክደኛው ላይ ደምን ካልረጨ ይሞታል፡፡ «ደም ሳይፈስ ስርየት የለምና» (ዕብ.9፡22)፡፡ ስለዚህ የኃጢአት ደመወዝ የሆነው ሞት ስለ ኃጢአተኛው በሚሞተው ላይ ሆኖ የኃጢአተኛው ስርየት ይገኛል፤ ይህም የእግዚአብሔር ጽድቅ የሚጠይቀው ነው፤ በመሆኑም ወርቅ የእግዚአብሔር ጽድቅ ምሳሌ ነው፡፡ በመንፈሳዊ ነገር ባለጠጋ መሆን የሚቻለው ይህን ጽድቅ ሲይዙ ብቻ ነው፤ ይህም የእግዚአብሔር ጽድቅ ፍጹም ነው፤ ጌታ ኢየሱስ “በእሳት የነጠረ ወርቅ” በማለት የጠራውም ይህን ያመለክታል፡፡ የራስን መልካም ሥራ አብዝቶ በመናገርና በመመካት የሰው ጽድቅ ቢቈጠር ይህ በእግዚአብሔር ፊት ፍጹም ሊሆን አይችልም፡፡ በጌታ ዘንድ “ጐስቋላና ምስኪን ደሀም” ከመባል አያድንም፡፡ በክርስቶስ ያለውን መንፈሳዊ ባለጠግነትን የሚያስገኘው በእሳት የነጠረ ወርቅ የሆነው የእግዚአብሔር ጽድቅ ብቻ ነው፡፡

2.ነጭ

በዚህ ስፍራ የተገለጠው ነጭ ልብስ ራቊትነትን የሚሸፍን ሆኖ ቀርቧል፡፡ በሎዶቅያ ያለው አማኝ «ተጐናጽፎ የራቁትነቱ ኃፍረት እንዳይገለጥ ነጭ ልብስን ...» እንዲገዛ ተመክሯል፡፡ ይህ አማኝ ከኢየሱስ ሊገዛ የሚችለው ነጭ ልብስም መንፈሳዊ ራቊትነቱን የሚሸፍንበት መንፈሳዊ ልብስ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ሰው በራሱ መልካም ሥራዎች መንፈሳዊ ራቁትነቱን መሸፈን አይችልም፤ አዳምና ሔዋን በኃጢአት በወደቁ ጊዜ ራቁታቸውን እንደሆኑ ሲያውቁ ከበለስ ቅጠሎች ሰፍተው ለራሳቸው ግልድም ያደረጉት ልብስ ራቁትነታቸውን ሊሸፍንላቸው አልቻለም፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሕግ እስከሚሰጥ ድረስ የሰው ልጅ መልካምና ክፉውን ለይቶ በሚያውቀው ኅሊናው ተጠቅሞ ራቁትነቱን ሊሸፍን የሚችል ጽድቅ ሊሠራ አልቻለም፤ እንዲሁም ሕግ ከተሰጠ በኋላም ከሕግ በታች የሆኑት ሁሉ ሕግን በመጠበቅ ሊሠሩት የሚጥሩት ጽድቅ ራቁትነትን አልሸፈነም፤ «ሁላችን እንደ ርኲስ ሰው ሆነናል፤ ጽድቃችንም እንደመርገም ጨርቅ ነው፡፡» ተብሎ ተጽፏልና (ኢሳ.64፡6)፡፡ ስለዚህ መንፈሳዊ ራቁትነታችንን መሸፈን እንችል ዘንድ ከእርሱ ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ የሚገኘው ነጭ ልብስ ያስፈልገናል፡፡ ይህም ነጭ ልብስ ሌላ ምንም ሳይሆን ራሱ ክርስቶስ ነው፡፡ «ነገር ግን ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት» ተብሎ ተጽፏል (ሮሜ.13፡14)፡፡ እርሱ ልክ እንደ ነጭ ልብስ ምንም እድፈት የሌለበትና የሰውን ራቁትነት በእግዚአብሔር ፊት መሸፈን የሚችል እግዚአብሔር የሰጠን ልብስ ነው፡፡ በሎዶቅያ ያለው አማኝ በዚህ ዓለም አሉ የተባሉ የከበሩ አልባሳትን በመልበስ ሥጋውን በሰው ፊት ሸፍኖና አሳምሮ ቢታይም ይህ ልብስ ግን ስላልነበረው ኢየሱስ ከእርሱ እንዲገዛ ይመክረዋል፡፡ የሥጋ ተክለ ሰውነትን በሚጠፋው ልብስ ማሰማመር በብዛት በሚታይበት በዚህ ዘመንም መንፈሳዊ ራቁትነትን ለመሸፈን ይቻል ዘንድ የኢየሱስን ማንነት ተጐናጽፎ መገኘት ያስፈልጋል፡፡ ከእርሱ ዘንድ ያለዋጋ የምንገዛው ነጭ ልብስም ይህ ነው፡፡

3.ኲል

በሎዶቅያ የነበረው አማኝ ቀጥሎ እንዲገዛ የተመከረው ነገር ኩል ነው፤ ጌታ «እንድታይም ዓይኖችህን የምትኳለውን ኩል» ከእኔ ትገዛ ዘንድ እመክርሃለሁ ይለዋል፤ እንደሚታወቀው ኩል የዓይን ቅብዓት ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በአዲስ ኪዳን ጌታ ኢየሱስ የተቀባበት ቅብዓት ሆኖ ተገልጧል (ሉቃ.2፡26፤ የሐ.ሥ.10፡38)፡፡ እንደዚሁም አማኞች የሚቀቡት በዚሁ በእርሱ ቅብዓት እንደሆነ ተነግሮአል (1ዮሐ.2፡20፣27)፡፡ በሎዶቅያ ባለች ቤተክርስቲያን ግን ነገሮችን በመንፈስ ቅዱስ ብርሃን ማየት የለም ነበር፤ ፍጥረታዊ የሆነ የሰው እይታ የበዛበት ሁኔታ ነበር፤ ስለዚህ በዚያ የነበረው አማኝ የልቡ ዓይኖች በርተው እግዚአብሔር ያየውን ያይ ዘንድ ለዓይኖቹ የመንፈስ ቅዱስ ቅብዓት ያስፈልገው ስለነበር ይህን መንፈሳዊ ኩል ከኢየሱስ እንዲገዛ ተመክሯል፡፡ በተለያየ የሰው ዘዴና አመለካከት እንዲሁም በሰው ዕቅድና ጥበብ ላይ የተመሠረተ አገልግሎት በበዛበት በዚህ ዘመንም ነገሮች ሁሉ እግዚአብሔር እንደሚያይ ሳይሆን ሰው እንደሚያይ እየተከናወኑ ነው፡፡ ስለሆነም ለዚህ ዘመን አማኞችም እግዚአብሔር እንደሚያይ ያገለግሉ ዘንድ ይህ ኩል ማለትም የመንፈስቅዱስ ቅብዓት በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡

«እኔ የምወዳቸውን እገሥጻቸዋለሁ እቀጣቸውማለሁ እንግዲህ ቅና ንስሐም ግባ»(ቊ.19)

በሎዶቅያ የነበረው ቤተክርስቲያን አጠቃላይ ሁኔታ ለብ ያለ በመሆኑ «ከአፌ ልተፋህ ነው» የሚል የፍርድ ቃል ቢነገርበትም በዚያ ያሉትን የእርሱን ቅሬታዎች ግን ጌታ ከአፉ ሊተፋቸው አይችልም፡፡ እነዚህ ቅሬታዎች በሎዶቅያ ባለው ለብ ያለ ሁኔታ የተነካኩ ወይም በለብታው ላይ ፈርደው ለጌታ ያልተለዩ በመሆናቸው ምክንያት ከአፉ ባይተፋቸውም የተግሣጽና የቅጣት እርምጃ በመውሰድ ወደ ንስሐ ሊመራቸው ይፈልጋል፡፡ ጌታ ይህን የሚያደርገውም ለእነርሱ ካለው ፍቅር በመነሣት መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ «እኔ የምወዳቸውን እገሥጻቸዋለሁ እቀጣቸውማለሁ» ብሏልና፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በሌላ ክፍል ውስጥ ይህንን ሁኔታ በስፋት ሲገልጽ «እንደ ልጆችም ከእናንተ ጋር፡- ልጄ ሆይ የጌታን ቅጣት አታቅልል፤ በሚገሥጽህም ጊዜ አትድከም፤ ጌታ የሚወደውን ይቀጣዋልና፤ የሚቀበለውንም ልጅ ይገርፈዋል ብሎ የሚነጋገረውን ምክር ረስታችኋል፡፡ ለመቀጣት ታገሡ፤ እግዚአብሔር እንደ ልጆች ያደርግላችኋልና አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማነው? ... ቅጣት ለጊዜው ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፤ ዳሩ ግን በኋላ ለለመዱት የሰላምን ፍሬ እርሱም ጽድቅን ያፈራላቸዋል» (ዕብ.12፡5-11) ይላል፡፡ እውነተኛ አማኝ በአንዳች አለመታዘዝ ውስጥ ቢገኝ እግዚአብሔር እርሱን ወደ ንስሐ ለመመለስና ጽድቅን እንዲያፈራ ለማድረግ ይቀጣዋል እንጂ ያገኘውን የዘላለም ሕይወት አያሳጣውም፡፡ በሎዶቅያ ባለች ቤተክርስቲያን ውስጥ በዚህ መልኩ ጌታ ስለሚወዳቸው የቀጣቸው አማኞች እንደነበሩ እንገነዘባለን፡፡ በቆሮንቶስ ቤተክርስቲያንም ከጌታ እራት ጋር በተያያዘ በደልን የፈጸሙ ሰዎች ተቀጥተዋል፤ ቃሉ ይህንን ሲገልጥ «ስለዚህ በእናንተ ዘንድ የደከሙና የታመሙ ብዙዎች አሉ፤ አያሌዎችም አንቀላፍተዋል» ካለ በኋላ «ራሳችንን ብንመረምር ግን ባልተፈረደብን ነበር፡፡ ነገር ግን በተፈረደብን ጊዜ ከዓለም ጋር እንዳንኰነን በጌታ እንገሠጻለን» ብሏል (1ቆሮ.11፡30-32)፡፡ ይህ ቅጣት ግን ሰዎቹን ወደ ንስሐ እንዳመጣቸው እንገነዘባለን፡፡ ሐዋርያው ሁለተኛውን የቆሮንቶስ መልእክት ሲጽፍላቸው “በመልእክቴ ያሳዘንኋችሁ ብሆን እንኳ አልጸጸትም፤ የተጸጸትሁ ብሆን እንኳ ያ መልእክት ጥቂት ጊዜ ብቻ እንዳሳዘናችሁ አያለሁና፤ አሁን ለንስሐ ስላዘናችሁ ደስ ብሎኛል እንጂ ስላዘናችሁ አይደለም” በማለት ይናገራልና (2ቆሮ.7፡8-9)፤ በዘመናችንም ጌታ «ለመታሰቢያዬ አድርጉት» ብሎ የሰጠው ሥርዓት ብቻ ሳይሆን ሌሎችም የአምልኮና የሥነ ምግባር መርሆዎች ተገቢውን ዋጋ ያላገኙበት ከሥጋዊና ከዓለማዊ አስተሳሰቦችና አሠራሮች ጋር ለማስማማት የሚፈለግበት ሁኔታ ይታያል፤ በዚህ ሁኔታ ውስጥ በቸልታ የሚመላለሱ እውነተኛ አማኞች ካሉ ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ኅብረት ያስተካክሉ ዘንድ ጌታ በተለያየ መንገድ እየገሠጸ ንስሐ ግቡ ይላቸዋል፡፡ ጌታ ኢየሱስ የንስሐን ጥሪ ያስተላለፈው በሎዶቅያ ላሉት ቅሬታዎች ብቻ አይደለም፤ ነቀፋ በተገኘባቸው በኤፌሶን፣ በጴርጋሞን፣ በትያጥሮን፣ በሰርዴስ ለነበሩትም ቅሬታዎችም ነው፡፡ ስለሆነም በክርስትና ዓለም በሚገኙ የተለያዩ ማኅበራት ውስጥ በሚታዩ የተለያዩ ውድቀቶች መካከል የሚገኙ ቅሬታዎችን ጌታ ያስባል፡፡ ምንም እንኳ በዚያ ካሉት ውድቀቶች ወይም ዓመፆች ራሳቸውን ለመጠበቅ የሚጥሩ ቢሆኑም ማኅበረተኛ መሆናቸው ተባባሪ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡ ስለ እውነት ሊደርስባቸው የሚችለውን ነቀፋና ስደት በመፍራት በቃሉ ከተገለጠው የክርስቶስ እውነት ጋር በግልጽ አይቆሙም፤ ስለዚህም ጌታ ንስሐ ግቡ ይላቸዋል፡፡

«እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ እገባለሁ፤ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል» (ራእ.3፡20)፡፡

በሎዶቅያ ባለች ቤተክርስቲያን የነበረው አስከፊ ሁኔታ ጌታን በውስጥ ሳይሆን በውጭ እንዲሆን አድርጎታል፤ ይህም የሎዶቅያን ቤተክርስቲያን በአጠቃላይ ጌታ እንደተለያት የሚያሳይ ነው፡፡ ይሁንና በእርስዋ ውስጥ ላሉ የእርሱን ድምፅ ሊሰሙ ለሚችሉ ለአንዳንድ አማኞች ግን በየግላቸው ከእርሱ ጋር ኅብረት ያደርጉ ዘንድ እንደገና ዕድል ይሰጣል፡፡ «እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፡፡» የሚለው ይህ ቃል በዚህ ክፍል የተነገረው ጌታ ፈጽሞ ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎችን ለመጥራት እንደሚያንኳኳ ሳይሆን በሎዶቅያ ቤተክርስቲያን ውስጥ ለሚገኙና ድምፁን ሊሰሙ የሚችሉ አንዳንድ ሰዎች በራቸውን እንዲከፍቱለት የሚያንኳኳ መሆኑን ለመግለጽ ነው፡፡ የሚያንኳኳውም የእርሱ መልእክተኞች በሆኑት ባሪያዎቹ አማካኝነት በሚያስተላልፈው የቃሉ እውነት በኩል ነው፡፡ ለምሳሌ የቈላስይሱ ኤጳፍራ በሎዶቅያ ስላሉ አማኞች ያስብ እንደነበር እናነባለን፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ሲገልጽ «... ስለእናንተ በሎዶቅያም በኢያራ ከተማም ስላሉቱ እጅግ እንዲቀና እመሰክርለታለሁና፡፡» ብሏል፡፡ ዛሬም ቢሆን በዙሪያችን ባለው ሎዶቅያዊ ክርስትና ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች የምንቀናና ከክርስቶስ ጋር በደጅ ያለን አማኞች ሁሉ እርሱ የእነርሱን በር በእኛ በኩል የሚያንኳኳብን መሣሪያዎች ልንሆን ይገባል፡፡ የማንኳኳቱ ዓላማም መላዋ የሎዶቅያ ቤተክርስቲያን በርዋን እንድትከፍት ለማድረግ አይደለም፤ ይህ በጌታ ዘንድ ተስፋ ያለው ነገር አይደለም፡፡ ምክንያቱም ያን በተመለከተ «ከአፌ ልተፋህ ነው» ብሏል፡፡ ነገር ግን በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ቅሬታዎች በየግላቸው ምላሽ ይሰጡ ዘንድ ያንኳኳል፡፡ «ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ እገባለሁ» ሲል ጌታ የሚጠብቀው በውስጥ ያሉ ድምፁን የሰሙ አማኞች በየግላቸው ደጁን እንዲከፍቱለት እንጂ ቤተክርስቲያኒቱ በጠቅላላ እንድትከፍትለት አለመሆኑን ያሳያል፡፡ ታዲያ በቃሉ አማካኝነት ወደ እርሱ የመጣውን የጌታን ድምፅ ሰምቶ የልቡን ደጅ(በር) ለጌታ የሚከፍት ሁሉ እንዴት የተባረከ ነው! ምክንያቱም ጌታ በሎዶቅያ ያለው ሁኔታ ለእርሱ ዝግ ሆኖ ሳለ ደጁን በሚከፍትለት ሰው ውስጥ በታላቅ ደስታ ይገባልና፡፡ «ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ» ብሎ በገለጸው መሠረት በቃላት ሊገለጽ የማይችል እጅግ ጣዕም ያለው ኅብረት ከእርሱ ጋር ያደርጋል፡፡

በሎዶቅያ ለነበረች ቤተክርስቲያን የተነገረው መልእክት በትንቢታዊ ገጽታው በቤተክርስቲያን ዘመን መጨረሻ ላይ ያለውን የክርስትናውን ዓለም አጠቃላይ ሁኔታ የሚያመለክት ነው፡፡ በተለይም ከ20ኛው ምዕተ ዓመት መጀመሪያ አንስቶ ለዘመናት ተለያይተው የኖሩ የክርስትና ሃይማኖት ድርጅቶችን አንድ ለማድረግ በሚል በሚከናወነው የኢኩሜኒዝም እንቅስቃሴ ውስጥ ይህ ገጽታ በስፋት የሚታይ ነው፡፡ ይህም እንቅስቃሴ በእግዚአብሔር ቃል ለተነገሩት መለኮታዊ እውነቶች ትኲረት የማይሰጥ ብቻ ሳይሆን እውነትን በመሠዋት ጭምር አንድነትን ለመመሥረት ጥረት የሚያደርግ መሆኑ ሎዶቅያዊ ገጽታን እንዲይዝ አድርጎታል፡፡

ዘመናዊው የኢኩሜኒዝም እንቅስቃሴ የተጀመረው በ1910 ዓ.ም. በስኮትላንድ ዋና ከተማ በኤድንበርግ (Edinburgh) በተደረገው የዓለም የሚሽነሪ ኮንፍረንስ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በዚህ ኮንፈረንስ አማካኝነት በ3 ነገሮች ማለትም በወንጌል ስርጭት፣ በአገልግሎት ሰጪነትና በአስተምህሮ ጉዳዮች አንድነት ለመፍጠርና አብሮ ለመሥራት ታቅዶ ነበር፡፡ በ1948 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ) በተመሠረተው የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤትም በእነዚህ ሦስት ዘርፎች የተጀመረውን የኢኩሜኒዝም እንቅስቃሴ በዋናነት ቀጥሎበታል፡፡ ይህ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት በአሁኑ ጊዜ በብዙ አገሮች የሚገኙ የክርስትና እምነት ድርጅቶችን በአባልነት የያዘ ነው፡፡ ሆኖም እስከአሁን ድረስ በአስተምህሮ እውነተኛ አንድነት ማምጣት ያልቻለ ሲሆን ከአንድነት ይልቅ የቃሉን እውነት አቻችሎ የማለፍ ነገር ይታይበታል፤ ይህም በኢኩሚኔዝም እንቅስቃሴ አስተባባሪዎችና አራማጆች ዘንድ ከመጀመሪያው ጀምሮ የነበረ ሲሆን አንድነቱ የተፈለገው በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አንድ ከመሆን ይልቅ በአገልግሎት ሰጪነት ማለት በኢንዱስትሪ፣ በማኅበራዊ፣ በፖለቲካዊ እና በሌሎች ዓለም አቀፍ ጉዳዮች የክርስትናው ዓለም በአንድነት የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ነበር፡፡ እንዲያውም በ1925 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) የስዊድን ዋና ከተማ በሆነችው በስቶክሆልም (Stockholm) በተደረገው ዓለም አቀፍ የክርስቲያኖች ኮንፈረንስ ላይ «አገልግሎት ሰጪነት አንድ ያደርጋል፤ አስተምህሮ ግን ይከፋፍላል» በሚል ርእስ በክርስትና ትምህርት አንድ ከመሆን ይልቅ በዓለማችን ባሉ የተለያዩ አገሮች ውስጥ በሚደረጉ እንቅስቀሴዎች ውስጥ ከላይ በተጠቀሱት የተለያዩ ዘርፎች አገልግሎት በመስጠት ረገድ አንድ ለመሆን የሚያስችል ዕቅድ ታቅዶ ነበር፡፡ እስከ አሁን ድረስም በዓለም ባሉ አብያተክርስቲያናትም የሚታየው ይኸው ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ዘንድ በክርስቶስ ኢየሱስ የተገለጠውን እውነት ቸል በማለት በማኅበራዊ ፖለቲካዊና ኤኮኖሚያዊ ነገር ውስጥ በመግባት የሚደረግ እንቅስቃሴ የዘመናችንን ክርስትና በመንፈሳዊ ነገሮች ለብ እንዲል ያደረገ ዋነኛ ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህም በሎዶቅያ የነበረች ቤተክርስቲያን ዋነኛ መገለጫ ነበር፡፡

ክርስቶስ ያስተማረው እውነት እስከ ዛሬ ሳይለወጥ ያለና ወደፊትም የሚኖረውን ያህል እርሱ የመሠረታት ቤተክርስቲያኑ አንዲት መሆኗ የማይለወጥ ሐቅ ነው፡፡ «አካልም አንድ እንደሆነ ብዙም ብልቶች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ብልቶች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደሆኑ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው ይላል» (1ቆሮ.12፡12)፡፡ በሌላ ስፍራም «በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ» ይለናል (አፌ.4፡4)፡፡ ስለዚህ በክርስቶስ ራስነት የምትመራው የእርሱ አካል የሆነችዋ ቤተክርስቲያን ምን ጊዜም አንዲት ናት፡፡ አማኞች በምድራዊ ነገራችን በነገድ በቋንቋ የተለያየን ልንሆን እንችላለን፡፡ በቤተክርስቱያን ግን አንድ አካል ሆነናል፡፡ አንድ አካል ብዙ ብልቶች እንዳሉት ሁሉ በብልቶች ሥራ ማለትም በአገልግሎትና በጸጋ ስጦታ ልዩ ልዩ ልንሆን እንችላለን፤ ልዩነት የሚኖረን በጸጋ ስጦታ እንጂ በትምህርትና በእምነት አይደለም፤ ስለሆነም በቤተክርስቲያን «አንድነት በልዩነት» ሊኖር የሚችለው ከጸጋ ስጦታ አንጻር ብቻ ነው፡፡ በትምህርትና በእምነት ግን አንድ ልንሆን ይገባል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የትምህርትና የእምነት ልዩነት ባለበት በክርስትና ውስጥ «አንድነት በልዩነት» የሚል አስተሳሰብን ተግባራዊ ማድረግ ውኃውን ለብ ማድረግ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለክርስቶስ የሚስማማው ባለመሆኑ «ከአፌ ልተፋህ ነው» በማለት ያስጠነቅቃል፡፡ በየግላቸው የጌታ የሆኑ ቅሬታዎችን ደግሞ በንስሐ እየጠራ ወደ ራሱ ያቀርባቸዋል፤ ወደ ውስጣቸው ገብቶ ኅብረት ለማድረግም ከደጅ ቆሞ ያንኳኳል፡፡

ስለዚህ በሎዶቅያ ባለች ቤተክርስቲያን እንደነበረው ሁሉ በዓለማዊና በሥጋ ነገሮች ተበርዞ በጌታ ፊት ለብ ባለ ክርስትና ውስጥ የምትገኝ አንባቢ ሆይ ለአንተ በግልህ በተለያዩ ጊዜያት የተሰሙትን የማንኳኳት ድምፆች ቸል አትበላቸው፡፡ አንተ በግልህ ቃሉን ስታጠናም ሆነ የክርስቶስ መልእክተኞች እውነቱን ሲመሰክሩልህ፣ ይህንንም ጽሑፍ እያነበብክ ሳለህም ቢሆን ክርስቶስ ድምፁን እያሰማህ ወደ ውስጥህ ሊገባ ሲያንኳኳ ትከፍትለት ዘንድ ወደ ኋላ አትበል፤ ፈጽሞ አታመንታ፤ ጊዜ የለህምና፡፡ እርሱ ክርስቶስ በሎዶቅያዊው የክርስትና ሥርዓት ተገፍቶ በውጭ ቢሆንም አንተን ግን በግልህ ይፈልግሃል፤ ከአንተ ጋር እራት መብላት ይፈልጋል፡፡ ለዚህ የፍቅር ጥያቄው አዎንታዊ ምላሸ ለመስጠት አትዘግይ፡፡

«እኔ ደግሞ ድል እንደነሣሁ ከአባቴም ጋር ከዙፋኑ ላይ እንደተቀመጠሁ ድል ለነሣው ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ ዘንድ እሰጠዋለሁ» (3፡21)፡፡

በሎዶቅያ ያለው ሁኔታ በምድራዊ ነገር ተመቻችቶና ተደላድሎ መቀመጥን የሚያሳይ ነው፡፡ ይህም «ሀብታም ነኝና ባለጠጋ ሆኜአለሁ አንድ ስንኳ አያስፈልገኝም» በሚለው አገላለጽ ውስጥ የሚታይ ነው፡፡ ሆኖም ይህን ዓለማዊና ምድራዊ ነገር ድል የነሣ የሎዶቅያ አማኝ በክርስቶስ ዙፋን ላይ ከክርስቶስ ጋር እንደሚቀመጥ ቃል ተገብቶለታል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን የተስፋ ቃል ሲሰጥ ጉዳዩን ያነጻጸረው እርሱ ሁሉን ድል ከነሣ በኋላ በአባቱ ዙፋን ከመቀመጡ ጋር ነው፡፡ እርሱ «በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ ነገር ግን አይዟአችሁ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ» ብሎ እንደተናገረው ዓለምን ድል የነሣ ጌታ ነው (ዮሐ.16፡33)፡፡ እንደዚሁም እርሱ «ለሞት ያውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ» ቢሆንም ሞትን በትንሣኤው ድል አድርጎታል (ዕብ.2፡14)፤ እኛም በእርሱ በኩል ድል መንሣትን ልናገኝ እንችላለን፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ሲገልጥ «ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ? የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው፤ የኃጢአትም ኃይል ሕግ ነው፡፡ ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን» ይላል፡፡ ስለዚህ በዘመናችን በስፋት የሚታየውንና ክርስትናን ከዓለማዊነት ጋር አስማምቶ ለመያዝ የሚደረገውን ሎዶቅያዊ አሠራር በክርስቶስ ኢየሱስ ድል ልንነሣ ይገባል፡፡ ይህም ከሆነ እርሱ ከአባቱ ጋር በአባቱ ዙፋን እንደተቀመጠ እኛ ደግሞ ወደ ፊት ይመጣ ዘንድ ባለው በእርሱ በክርስቶስ ዙፋን ላይ እንቀመጣለን፡፡

ጌታ ኢየሱስ አሁን በከበረው ሰውነቱ ያለበት ስፍራ በእግዚአብሔር ቀኝ እንደሆነ በተደጋጋሚ ተነግሮናል (ማር.16፡20፤ የሐ.ሥ.2፡33-36፤ ዕብ.8፡1፤ 1ጴጥ.3፡22)፡፡ ይህም እርሱ የተቀመጠበት ስፍራ በድል ነሽነቱ ለእርሱ የተሰጠው በሰማይ ያለ የአባቱ ዙፋን ነው፡፡ ወደ ፊት ደግሞ በሺው ዓመት ጊዜ በምድር ላይ ሲነግሥ እርሱ እንደ ሰው ልጅነቱ በክብር የሚቀመጥበት የክብሩ ዙፋን አለው፡፡ «የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል፡፡» ይላል (ማቴ.25፡31)፡፡ በዚያን ጊዜም የእርሱ የሆኑቱ ድል ነሺዎች ከእርሱ ጋር እንደሚነግሡ ተጽፏል (2ጢሞ.2፡11፤ ራእ.5፡10)፡፡ ስለሆነም ከእርሱ ጋር በዙፋኑ ላይ ይቀመጣሉ፡፡ ጌታችን ይህን ተስፋ ለ12ቱ ሐዋርያት በተናገረው ቃል ሲያረጋግጥ «እውነት እላችኋለሁ እናንተስ የተከተላችሁኝ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ እናንተ ደግሞ በአስራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በአስራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ፡፡» ብሏል (ማቴ.19፡28)፡፡ ስለሆነም ዛሬ በዚህች ምድር ላይ ስንሆን ከእርሱ ጋር ከሰፈሩ ውጭ ሆነን መከራ እየተቀበልን ብንኖር በሚመጣው ዓለም ደግሞ ከእርሱ ጋር በዙፋኑ ላይ ተቀምጠን ከእርሱ ጋር እንነግሣለን (2ጢሞ.2፡11)፡፡ በሎዶቅያዊው ክርስትና መካከል የሚገኙ ድል ነሺዎች ሁሉ በዚህ የታመነ የተስፋ ቃል ሊበረታቱ ይገባል፡፡

«መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ» (ራእ.3፡22)

በሎዶቅያ በነበረች ቤተክርስቲያን ውስጥ ለነበሩት ሁሉ የተነገረው ቃል በሌሎቹ አብያተክርስቲያናትም ለሚገኙት የተላከ መሆኑን በዚህ ቃል እንረዳለን፡፡ ይህ ቃል ለሰባቱም አብያተክርስቲያናት በተላኩት መልእክታት ውስጥ የሚገኝ እንደመሆኑ ለእያንዳንዱ ቤተክርስቲያን የተላለፈውን መልእክት ሁሉም እንዲጠቀሙበት ያስፈልግ ነበር፡፡ በእኛ ዘመን ያሉ አብያተክርስቲያናት ደግሞ የመጨረሻዎቹ አራቱ ማለት የትያጥሮን፣ የሰርዴስ፣ የፊልድልፍያና የሎዶቅያ ዓይነት እንደሆኑ ለእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት የተላኩትን መልእክቶች በትንቢታዊ ገጽታቸው ስናጠና ተገንዝበናል፡፡ ስለዚህ ለሎዶቅያዊው ክርስትና የተነገረውን የማስጠንቀቂያና የተግሣጽ ቃል እንዲሁም ለቅሬታዎቹ የተነገረውን የንስሐ ጥሪና የተስፋ ቃል በክርስትናው ዓለም የሚገኙ ጆሮ ያላቸው አማኞች ሁሉ ሊሰሙት ይገባል፡፡ ይህም መስማት ለማወቅ ያህል ከመስማት አልፎ በተግባር በመታዘዝ የሚገለጥ መስማት ሊሆን ይገባል፡፡




Amharic Bible-|- The Holy Bible [King James Version]