ቤተክርስቲያን/Aclesia  

ለፍል ፪

በሰምርኔስ ላለች ቤተክርስቲያን የተላከ መልእክት

«በሰምርኔስ ወዳለው ወደ ቤተክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ «ሞቶ የነበረው ሕያውም የሆነው ፊተኛውና መጨረሻው እንዲህ ይላል፡፡» (ራእ. 2፡8)

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰምርኔስ ለነበረች ቤተክርስቲያን ራሱን ያስተዋወቀበትን ይህን አገላለጽ እርሱ ለባለራእዩ ለዮሐንስ በተገለጠ ጊዜ ቀደም ሲል ተናግሮት ነበር፡፡ ዮሐንስ እርሱን በታላቅ ግርማና ክብር ባየው ጊዜ እንደሞተ ሰው ሆኖ ከእግሩ በታች ወድቆ ነበር፡፡ ጌታ ግን ቀኝ እጁን ጫነበትና «አትፍራ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፤ ሞቼም ነበርሁ እነሆም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፤ የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ» ብሎት ነበር (ራእ1፡17-18)፡፡ በዚህም አገላለጽ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምንም እንኳ ሞቶ የነበረ ቢሆንም ከዘላለም እስከዘላለም ሕያው የሆነ ማንነት ያለው እንዲሁም ፊተኛውና መጨረሻ የሆነ ዘላለማዊ አምላክ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ወረድ ብለን እንደምናነበው እስከሞት በሚያደርስ ከፍ ያለ መከራ እና በጥልቅ ድህነት ውስጥ ለነበሩት ለሰምርኔስ አማኞች ይህን የጌታችንን የሚደነቅ ማንነት መስማት ከፍ ያለ መጽናናት የሚፈጥር ነው፡፡ በቊ.9 ላይ እንደምናነበው «መከራህንና ድህነትህን አውቃለሁ፣» እንዲሁም በቊ.1ዐ «ልትቀበለው ያለህን መከራ አትፍራ ... እስከሞት የታመንህ ሁን የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ፡፡» የሚል መልእክትን ሊያስተላልፍላቸው ስለፈለገ ጌታ ኢየሱስ እነርሱ ከነበሩበት ሁኔታ ጋር አብሮ በሚሄድ ማንነቱ ራሱን ገለጠላቸው፤ አዎን እርሱ ሞቶ የነበረ ቢሆንም ከዘላለም እስከዘላለም ሕያው መሆኑ የእርሱ የሆኑት ሁሉ እስከሞት ሊያደርስ በሚችል መከራ ውስጥ እንኳ ቢያልፉ ሕያዋን እንደሚሆኑ የሕይወት አክሊልንም እንደሚቀዳጁ ብርቱ መተማመኛ ይሆንላቸዋል፡፡ በዚህ እምነትም በመከራ እንዲታገሡ፣ እንዲጸኑና እስከ ፍጻሜ እንዲታመኑ ይረዳቸዋል፡፡ ስለሆነም በእነዚህ በከበሩ ቃላት የተነገረውን የክርስቶስ ማንነት በጥልቀት ማየቱ ጠቀሜታው ከፍ ያለ በመሆኑ ቀጥሎ በዝርዝር እንመለከተዋለን፡፡

ሞቶ የነበረው

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእርሱ ወደሆነው በመጣ ጊዜ የገዛ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም ነበር፤ (ዮሐ.1፡11) ከዚያም አልፈው በየጊዜው ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር (ዮሐ.7፡1፣ 7፡25)፤ ሆኖም ጊዜው ሳይደርስ ሊይዙት አልቻሉም (ዮሐ8፡2ዐ)፤ ጊዜው ሲደርስ ግን የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን በሸንጐ ወስነው፣ የሐሰት ምስክር አቁመው፣ ለአሕዛብ አሳልፈው ከሰጡት በኋላ በእንጨት ላይ ሰቅለው ገደሉት (ዮሐ11፡47፤ 19፡17-18)፡፡ እነርሱ ከሕያዋን ምድር ፈጽሞ ሊያስወግዱት፣ «አስወግደው አስወግደው፤ ስቀለው ስቀለው» በማለት በጲላጦስ ፊት ከጮኹ በኋላ በቀራንዮ በመስቀል ላይ ሰቅለው ገደሉት፡፡ ከተቀበረም በኋላ «ሄደው ከጠባቆች ጋር ድንጋዩን አትመው መቃብሩን አስጠበቁ» (ማቴ.27፡66)፡፡ እርሱ ግን የሞተው እነርሱ ስለጠሉትና ማስወገድ ስለፈለጉ አልነበረም፡፡ የእርሱ መሞት ቀደም ሲልም በእግዚአብሔር የተወሰነ ነበር (ሉቃ.22፡22፤ የሐ.ሥ2፡23)፤ ስለሆነም ሞቱን በተመለከተ አስቀድሞ ትንቢት ተነግሮ ነበር (ኢሳ.53፡12፤ ዳን.9፡26)፡፡ እርሱም ራሱ ከመሞቱ አስቀድሞ በተደጋጋሚ ስለመሞቱ ይናገር ነበር እንጂ ለእርሱ ሞቱ ድንገተኛ አልነበረም (ማቴ16፡21)፤ ስለሆነም ጊዜው ሲደርስ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጠ፡፡ «አንዱ ስለሁሉ ሞተ» ተብሎ እንደተጻፈ (2ቆ5፡14) የሞተበት ምክንያትም አይሁድ እርሱን መጥላታቸውና እንዲወገድ መፈለጋቸው ሳይሆን ስለ ሁላችን ምትክ ሆኖ መሞት ስለነበረበት ነው፡፡ እነርሱ ግን ሞቶ መቀበሩን የመጨረሻ አድርገውት ስፍራውን ከመቃብር በታች ያደረጉት፣ ታሪኩንም በሞትና በመቃብር የዘጉት መስሏቸው ነበር፡፡ ሆኖም ኢየሱስን ሞት ይይዘው ዘንድ አልቻለም (የሐ.ሥ2፡24)፡፡ እርሱ ሞቶ የቀረ ሳይሆን «ሞቶ የነበረ» ነው፡፡ በመሆኑም እስከ ሞት በሚያደርስ መከራ ውስጥ ያሉ አማኞች፣ የሚታመኑለት ጌታ እርሱ «ሞቶ የነበረ» መሆኑን ማስተዋል ከሞት ፍርሃት ነጻ የሚያወጣ ነው፡፡

ሕያውም የሆነው

ኢየሱስ ስለ ሰው ልጆች ኃጢአት ሞቶ የነበረ ቢሆንም ሕያው የሆነ ማንነት ያለው ነው፡፡ እርሱ በሥጋ ከመገለጡ በፊት ብቻ ሳይሆን ዓለም ከመፈጠሩ በፊትም ከዘላለም ሕያው ሆኖ የነበረ ነው (ዮሐ.1፡1፤ 17፡5)፤ በኋላ በሥጋ ተገልጦ ቢሞትም ይህ ሞቱ ሕያውነቱን ሊያስቀረው አይችልም አልቻለምም፡፡ ጴጥሮስ በመልእክቱ ሲጽፍ «በሥጋ ሞተ፣ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ» ብሏል (1ጴጥ.3፡18)፡፡ ይህም በሥጋ ባሕርዩ ቢሞትም በመንፈስ ባሕርዩ ሕያው መሆኑን የሚገልጽ ነው፤ ይህም በሦስተኛው ቀን ከሙታን መካከል በመነሣቱ ተረጋግጧል፡፡ መላእክት ክርስቶስ በተነሣ ዕለት ይህን ሲመሰክሩ ወደ መቃብሩ ማልደው ለመጡት «ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም፡፡» ብለዋል (ሉቃ.24፡5፣23)፡፡ ከዚያም በኋላ ለዘላለም ሕያው ሆኖ ይኖራል፤ የእርሱ ሕያውነት ዘላለማዊ ነው፡፡ ይህንንም ቀደም ሲል እንደጠቀስነው እርሱ ራሱ «ሞቼም ነበርሁ፤ እነሆም ከዘላለም እስከዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ» በማለት አረጋግጧል (ምዕ1፡ቊ.18)፡፡ ስለሆነም አማኞች የሚመሰክሩለት ኢየሱስ፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ሕያው የሆነው እርሱ መኾኑን ሁልጊዜም በእምነት ማስተዋል፣ እስከሞት ሊያደርሱ በሚችሉ መከራዎች ጊዜ ታማኝነታችንን ያበረታዋል፡፡

ፊተኛውና መጨረሻው

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ በቤተልሔም መወለዱ የህልውናው ጅማሬ፣ በቀራንዮ በመስቀል ላይ መሞቱም የህልውናው ፍጻሜ አይደለም፡፡ በቈላ.1፡17 ላይ እንደተገለጠው «እርሱ ከሁሉ በፊት ነው»፡፡ እንዲሁም ከመዝ.1ዐ1(1ዐ2)፡25-27 ተጠቅሶ በዕብ.1፡1ዐ ላይ «ጌታ ሆይ፣ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፣ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው፤ እነርሱም ይጠፋሉ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤ ሁሉም እንደልብስ ያረጃሉ፣ እንደመጐናጸፊያም ትጠቀልላቸዋለህ ይለወጡማል፤ አንተ ግን አንተ፣ ነህ ዓመቶችህ ከቶ አያልቁም» ተብሎ ስለ እርሱ እንደተጻፈው እርሱ ሁሉን አሳልፎ የሚኖር የሁሉ ነገር መጨረሻ ነው፡፡ ስለሆነም ስለ ራሱ ሲናገር «ፊተኛውና መጨረሻው» ለማለት ተችሎታል፡፡ ይህም ባሕርይ የዘላለማዊው አምላክ የያህዌህ መለኮታዊ ባሕርይ ነው፡፡ ለምሳሌ በዚሁ በዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ ውስጥ «በዙፋን የተቀመጠው» «ተፈጽሟል፤ አልፋና ኦሜጋ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ» ብሎ የተናገረውን እናነባለን፤ (ራእ.21፡6)፡፡ እንዲሁም በኢሳ.44፡6 ላይ «የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር የሚቤዥም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- እኔ ፊተኛ ነኝ እኔም ኋለኛ ነኝ ከእኔ ሌላም አምላክ የለም» ብሎ ብቸኛው አምላክ ስለ ራሱ ባሕርይ የተናገረው ተጽፎልናል፡፡ ስለሆነም «ፊተኛውና መጨረሻው» መሆኑን ስለ ራሱ የተናገረው ኢየሱስ ምንም እንኳ በቤተልሔም ተወልዶ በቀራንዮ በመስቀል ላይ ሞቶ የነበረ ቢሆንም እርሱ የሰውነት ባሕርይ ብቻ ሳይሆን የመለኮት ባሕርይ ያለው ዘላለማዊ አምላክ መሆኑን በግልጽ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህም እውነታ ስለ ሰውነቱ የተነገሩትን ክፍሎች ብቻ በመጥቀስ አምላክነቱን አጉልተው የሚያስረዱትን እነዚህን ንባቦች ላለማየት በክህደት ጨለማ ውስጥ በሚገኝ ሰው ላይ ማንም ሊቋቋመው በማይችል መልኩ በድምቀት የሚያበራ እውነታ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ስለ ስሙ መከራ በመቀበል በመገፋትና በመነቀፍ በመታሰርና በመሞት ለሚጋደሉ እንደ ሰምርኔስ አማኞች ላሉ ቅዱሳን የተከተሉትና የሚመሰክሩለት ኢየሱስ እርሱ «ፊተኛውና መጨረሻው» መሆኑን በእምነት ማስታወሳቸው ድል ነሺ ለመሆን የሚያበቃቸውን ጽናትና ብርታት የሚያስታጥቃቸው ነው፡፡

ቊ.9 «መከራህንና ድህነትህን አውቃለሁ፤ ነገር ግን ባለጠጋ ነህ»

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰምርኔስ ያሉት አማኞች በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንደነበሩ ያውቅ ነበር፡፡ «አውቃለሁ» የሚለው ቃል በሰባቱም መልእክታት ውስጥ የምናገኘው ሲሆን ጌታችን የእርሱ የሆኑት ያሉበት ሁኔታ መልካምም ይሁን ክፉ ሥራ ከእርሱ የሚሰወር እንደሌለ ሁሉን በመለኮታዊ እውቀቱ የሚያውቅ መኾኑን የሚያስረዳ ነው፡፡ የሰምርኔስ አማኞች በመከራና በድህነት ውስጥ መሆናቸውን ጌታ ያውቅ ነበር፤ ስለሆነም ካሉበት የመከራና የድህነት ሁኔታ አንጻር ሊያበረታታቸው «መከራህንና ድህነትህን አውቃለሁ» ይላቸዋል፡፡ \

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱን የሚከተሉት ሁሉ መከራን እንደሚቀበሉ በግልጽ ያስተምር ነበር፤ በማቴ.16፡24 «እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ» በማለት የተናገረውን እናነባለን፤ እንዲሁም በሌላ ስፍራ «በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ ነገር ግን አይዞአችሁ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ» ብሏል (ዮሐ.16፡33)፡፡ ስለዚህ የክርስቶስ የሆኑቱ ሁሉ እርሱ በምድር ላይ ሳለ እውነትን በመመስከሩ ይደርስበት የነበረው መከራ ይደርስባቸዋል፤ እርሱ እንደተጠላ ይጠላሉ (ዮሐ.15፡18-2ዐ)፤ እርሱ እንደተሰደበ ይሰደባሉ (2ቆሮ.4፡12፤ 1ጴጥ2፡23፤ ማቴ.12፡24፤ 27፡3ዐ)፤ እርሱ እንደተሰደደ ይሰደዳሉ (ዮሐ.15፡2ዐ፤ 2ጢሞ3፡12)፤ እርሱ ተይዞ እንደታሰረ ይታሰራሉ (ሐ.ሥ4፡1-3፤ 5፡18፤ ዮሐ18፡12)፤ እርሱ እንደተገደለ ይገደላሉ (1ተሰ.2፡14-15፤ ሐ.ሥ.12፡1-2)፡፡ በሰምርኔስ የነበሩ ክርስቲያኖች በእንደ እነዚህ ዓይነት መከራ ውስጥ ነበሩ፤ ይህንን መከራቸውን ማንም ባያውቅላቸውም በመከራ ውስጥ አልፎ በክብር የተቀመጠው ኢየሱስ ያውቅላቸው ነበር፡፡

በሌላ በኩል ድህነታቸውንም ያውቅ ነበር፡፡ እዚህ ላይ የተጠቀሰው ድህነት በሥጋ ያለው ድህነት ነው፡፡ ይህም ከመጀመሪያውም ቢሆን በድህነት ይኖሩ የነበሩና በኋላ በወንጌል አምነው የክርስቶስ የሆኑትን ወይም ደግሞ በክርስቶስ በማመናቸው የተነሣ ከማኅበረሰቡ በሚደርስባቸው ጥላቻ ነቀፋና ስደት ለድህነት የተዳረጉትን አማኞች ሊያመለክት ይችላል፡፡ ይህም የብዙዎች ቅዱሳን መገለጫ ሕይወት ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ በምድር ላይ የኖረው በድህነት ነበር፤ የተወለደው ከደሀ እናት ከመሆኑ ጀምሮ ራሱን የሚያስጠጋበት የሌለው ነበር (ሉቃ2፡24፤ 9፡58)፡፡ በ2ኛቆሮ 8፡9 ላይ እርሱ «ስለ እናንተ ደሀ ሆነ» ተብሏል፡፡ ሐዋርያትም ድሆች ነበሩ (2ቆሮ6፡11)፡፡ በኢየሩሳሌም ቅዱሳን መካከል ድሆች ነበሩ (ሮሜ15፡26)፤ የመቄዶንያ አብያተ ክርስቲያናት በጥልቅ ድህነት ውስጥ ነበሩ (2ቆሮ.8፡2)፡፡ ከዚህ እንደምንረዳው ድህነት በክርስቲያኖች ዘንድ ሊኖር የሚችል ችግር ነው፡፡ ስለሆነም «ድህነት ከእምነት ማነስ የሚመጣ ነው፤ በክርስቶስ ማመንም በሥጋ የሚገኝ ሀብት ባለጠጋ ያደርጋል» የሚለው የአሮጌው ሰው ትምህርት በእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቦች ፊት ሊያፍርና ሊወገድ ይገባዋል፡፡

የሰምርኔስ አማኞች ምንም እንኳ ደሀ ቢሆኑም ድህነታቸውን የሚያውቀው ጌታ «ባለጠጋ ነህ» ይላቸዋል፡፡ ይህም ባለጠግነት በሥጋ ወይም በምድራዊ ነገር ባለጠጋ መሆን አይደለም፤ ምክንያቱም «መከራህንና ድህነትህን አውቃለሁ» በሚለው የጌታ ቃል በድህነት የሚኖሩ መሆናቸውን አይተናልና፤ «ባለጠጋ ነህ» የተባሉት በሥጋ ደሀ እንደሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ባለጠግነታቸው በመንፈሳዊ ነገር መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ በያዕ. 2፡5 ላይ «የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ ስሙ እግዚአብሔር በእምነት ባለጠጎች እንዲሆኑ ለሚወዱትም ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድሆች አልመረጠምን?» ተብሎ የተጻፈው ቃል የድሆቹ ባለጠግነት በእምነት እንደሆነ ያሳያል፡፡ በ2ቆሮ.8፡9 ላይም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አስመልክቶ «ሀብታም ሲሆን እናንተ በእርሱ ድህነት ባለጠጎች ትሆኑ ዘንድ ስለ እናንተ ደሀ ሆነ» ተብሎ የተጻፈው ቃል የሚያስረዳው በእርሱ ድህነት ባለጠጎች የተደረግነው በመንፈሳዊ ነገር መሆኑን እንጂ በምድራዊ ሀብት መሆኑን አይደለም በ1ቆሮ.1፡6 ላይ «ለክርስቶስ መመስከሬ በእናንተ ዘንድ እንደጸና በነገር ሁሉ በቃልም ሁሉ በእውቀትም ሁሉ በእርሱ ባለጠጎች እንድትሆኑ ተደርጋችኋል» ተብሎ እንደተጻፈው የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ክርስቶስን በማመናቸው (በመቀበላቸው) ባለጠጎች የተደረጉት በመንፈሳዊ ነገር ነው፡፡ በዚህ ንባብ ውስጥ «በነገር ሁሉ» የሚለው መንፈሳዊ ነገሮችን ሁሉ የሚመለከት መሆኑን ቀጥሎ «በቃልም ሁሉ በእውቀትም ሁሉ» ተብሎ በተነገረው ንባብ ማወቅ ይቻላል፡፡ ስለሆነም እንደ ሰምርኔስ አማኞች በዚህ ዓለም በድህነት የምንኖር ብንሆንም በእግዚአብሔር ዘንድ በመንፈሳዊ ነገሮች ባለጠጎች የተደረግን መሆናችንን ማስተዋል ይገባል፡፡

«የሰይጣን ማኅበር ናቸው እንጂ አይሁድ ሳይሆኑ አይሁድ ነን የሚሉት የሚሳደቡትን ስድብ አውቃለሁ»

በዚህ ቊጥር ላይ «የሰይጣን ማኅበር» ተብለው የተጠቀሱት ሰዎች በፊልድልፍያ ለነበረች ቤተክርስቲያን በተላከው መልእክት ውስጥም ተጠቅሰው እናገኛቸዋለን (ምዕ.3፡9)፡፡ በዚያም «የሚዋሹ» ተብለዋል፤ ውሸታቸውም በሁለቱም ስፍራ እንደተገለጠው «አይሁድ ሳይሆኑ አይሁድ ነን» ማለታቸው ነው፡፡ እንደሚታወቀው አይሁድ ከሕግ በታች እንጂ ከጸጋ በታች አይደሉም፤ ወደ ክርስትና ከገቡት መካከል በተለይም ከፈሪሳውያን ወገን ያመኑት አንዳንዶቹ ከይሁዳ ወደ አንጾኪያ ወርደው አሕዛብን «እንደ ሙሴ ሥርዓት ካልተገረዛችሁ ትድኑ ዘንድ አትችሉም» እያሉ ያስተምሩ ነበር (ሐ.ሥ.15፡1-5)፤ በገላትያ አማኞች መካከልም የገባው ልዩ ወንጌል ይኸው ነበር (ገላ.1፡6-7፤ 4፡21)፡፡ በሮሜ 2፡25-29 እንደተጻፈው ግን «አይሁዳዊ» የተባለው እንደ ሙሴ ሥርዓት የተገረዘው በግልጥ (በውጫዊ መልኩ) አይሁዳዊ የሆነው ሳይሆን በመንፈስ የተደረገ የልብ መገረዝ ያለው በስውር አይሁዳዊ የሆነው ነው፡፡ ከዚህም አንጻር በሙሴ ሥርዓት በመገረዝ ከሕግ በታች ሊኖሩ የወደዱ ነገር ግን ሕግን የማይጠብቁት ሁሉ እነርሱ አይሁድ ነን ቢሉ እንኳን አይሁድ ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ በገላ.6፡12 «በሥጋ መልካም ሆነው ሊታዩ የሚወዱ ሁሉ እንድትገረዙ ግድ አሉአችሁ፤ ነገር ግን ስለ ክርስቶስ መስቀል እንዳይሰደዱ ብቻ ነው፡፡ በሥጋችሁ እንዲመኩ ልትገረዙ ይወዳሉ እንጂ የተገረዙቱ ራሳቸው እንኳ ሕግን አይጠብቁም» ይላል፡፡ ለሰምርኔስ በተላከው መልእክት የተጠቀሱት «የሰይጣን ማኅበር» የተባሉት እንደ እነዚህ ዓይነት ሰዎች ናቸው፡፡ አይሁዳዊ ነን በማለት ከሕግ በታች ለመኖር የሚወዱ፣ ነገር ግን ሕጉን የማይጠብቁ ናቸው፤ እነዚህም «ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ ላይ ይጭናሉ፤ እነርሱ ግን በጣታቸው ስንኳ ሊነኩት አይወዱም» እንደተባሉት ፈሪሳውያን ናቸው (ማቴ.23፡5)፡፡

እነዚህ ሰዎች በስድብ የተሞሉና በመሳደብ የሚታወቁ ናቸው፡፡ በ2ጴጥ.2፡11 ጀምሮ ስለሚሳደቡ ሰዎች የተጻፈው ቃል «ደፋሮችና ኩሩዎች ሆነው ሥልጣን ያላቸውን ሲሳደቡ አይንቀጠቀጡም፤ ዳሩ ግን መላእክት በኃይልና በብርታት ከእነርሱ ይልቅ ምንም ቢበልጡ በጌታ ፊት በእነርሱ ላይ የስድብን ፍርድ አያመጡም፤ እነዚህ ግን ለመጠመድና ለመጥፋት በፍጥረታቸው እንደተወለዱ አእምሮ እንደሌላቸው እንስሶች ሆነው በማያውቁት ነገር እየተሳደቡ በጥፋታቸው ይጠፋሉ» ይላል፡፡ በሌላ ስፍራም «እንዲሁም እነዚህ ሰዎች ደግሞ እያለሙ ሥጋቸውን ያረክሳሉ፤ ጌትነትንም ይጥላሉ፤ ሥልጣን ያላቸውንም ይሳደባሉ፤ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ግን ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለሙሴ ሥጋ ሲነጋገር ጌታ ይገሥጽህ አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም፤ እነዚህ ግን የማያውቁትን ሁሉ ይሳደባሉ» የሚል ቃል እናባለን (ይሁዳ ቊ.8-1ዐ)፡፡ ስድብ ወደፊት ይመጣ ዘንድ ያለው የአውሬው መታወቂያ ጠባይ ነው፤ በራእ.13፡1 ላይ «በራሶቹ ላይ የስድብ ስም ነበረ» የሚል ስናነብ በቊ.5 ላይ ደግሞ «ታላቅ ነገርና ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጠው፣ በአርባ ሁለት ወርም እንዲሠራ ሥልጣን ተሰጠው፡፡ እግዚአብሔርንም ለመሳደብ ስሙንና ማደሪያውንም በሰማይ የሚያድሩትን ሊሳደብ አፉን ከፈተ» የሚለውን እናነባለን፡፡ አውሬው ደግሞ ወደፊት ይመጣ ዘንድ ያለውና በመጨረሻ ላይ የሚፈረድበት ምዕራባዊው የአሕዛብ መንግሥት ሲሆን ሥልጣኑን የሚቀበለው በቀጥታ ከዘንዶው (ከሰይጣን) መሆኑ ተጽፏል (ራእ.13፡4)፤ ስለሆነም ስድብ ሰይጣን የእርሱ በሆኑት አፍ ላይ የሚያኖረው አስጸያፊ ነገር ነው፡፡ ለሰምርኔስ ቅዱሳን በተነገረው መልእክት ውስጥ የተጠቀሱት ተሳዳቢዎች «የሰይጣን ማኅበር» ካሰኟቸው ነገሮች አንዱ ይኸው ስድብ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡

በዘመናት ሁሉ የአይሁድን ሥርዓተ አምልኮ የሚከተል ከጸጋ በታች ሳይሆን ከሕግ በታች ለመኖር የሚወድ በሃይማኖተኛው የክርስትና ዓለም ውስጥ ያለ ማንኛውም ማኅበር «አይሁድ ሳይሆኑ አይሁድ ነን» በሚሉት ሰዎች ጠባይ ሊገለጥ የሚችል ነው፡፡ እንዲህ ያለው በየዘመናቱ የሚገኝ የሰይጣን ማኅበር ከጸጋ በታች የሚኖሩትን የሚያሳድድ ከመሆኑም ባሻገር የእግዚአብሔር በሆነው ነገር ላይ የስድብን ቃል ለመናገር የሚዳፈር ነው፡፡ ይሁን እንጂ በሁሉ ነገር ላይ የሚፈርደው ጌታ እነዚህ ሰዎች የሚሳደቡትን ስድብ «አውቃለሁ» በማለት ያሉበትን ሁኔታ በፍርድ ዓይኖቹ እየተመለከተው እንደሆነ ከቃሉ እንረዳለን፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በማስተማር ዘመኑ «ብኤል ዜቡል» ብለው የሰደቡት ነበሩ (ማቴ.1ዐ፡25)፡፡ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሳለም በዚያ የሚያልፉት ራሳቸውን እየነቀነቁ ሰድበውት ነበር (ማቴ.27፡39)፡፡ አብረው ከተሰቀሉት ክፉ አድራጊዎችም አንደኛው «አንተ ክርስቶስ አይደለህምን? ራስህንም እኛንም አድን» ብሎ እንደሰደበው ተጽፎአል (ሉቃ.23፡39)፤ ይሁን እንጂ እርሱ «ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም» ነበር(1ጴጥ.2፡23)፡፡ ክርስቲያን «ከሰይጣን» ማኅበር ስድብ ሊደርስበት ይችላል፤ ሆኖም ስድብን በስድብ ፈንታ መመለስ የለበትም (1ጴጥ.3፡9)፡፡ በዙሪያው ያለውን ስድብ ጌታ ስለሚያውቀው ፍርዱን ለእርሱ መተው ይገባዋል፡፡

ቊ.1ዐ፡- ልትቀበለው ያለህን መከራ አትፍራ

ክርስቲያኖች ሁሉ ከመጀመሪያው ስለ ክርስቶስ ስም መከራን ሊቀበሉ እንዳላቸው ሊያውቁ ይገባቸዋል፡፡ በፊልጵ.2፡28-3ዐ ላይ «በአንድም ነገር በተቃዋሚዎች አትደንግጡ፤ ይህም ለእነርሱ የጥፋት ለእናንተ ግን የመዳን ምልክት ነው፡፡ ይህም ከእግዚአብሔር ነው፤ ይህ ስለ ክርስቶስ ተሰጥቶአችኋልና፡፡ ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ ነው እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም፡፡ በእኔ ያያችሁት አሁንም በእኔ እንዳለ የምትሰሙት ያው መጋደል ደርሶባችኋልና» ይላል፡፡ መከራ ሊደርስበት እንደሚችል ቀድሞውኑ የሚያውቅና ተዘጋጅቶ የሚጠብቅ አማኝ መከራው በሚደርስ ጊዜ ካለመደንገጡም በላይ ሊፈራም አይችልም፡፡ «መከራ መቀበል» በዚህ ዓለም ሳለን ከክርስትና ኑሮአችን እንደ አንዱ ሆኖ ተገልጧል፤ በ2ጢሞ4፡5 «አንተ ግን ነገርን ሁሉ በልክ አድርግ፤ መከራን ተቀበል፤ የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ አድርግ፤ አገልግሎትን ፈጽም፡፡» ተብሎ የተጻፈው ቃል ይህንን ያስረዳል፡፡ ስለዚህ ክርስትና በነገር ሁሉ መከናወን የሚገኝበት በዚህች ምድር ላይ በምቾት በሰላም ብቻ የሚኖርበት ሕይወት ሳይሆን መከራ የምንቀበልበትም ሕይወት መሆኑ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ለተረዱት ሁሉ «ልትቀበለው ያለህን መከራ አትፍራ» የሚለው የጌታ ቃል ማበረታቻ ይሆናቸዋል፤ መከራን በፍርሃት ሳይሆን በድፍረት የሚጋፈጡበትን እምነትም ይጨምርላቸዋል፡፡ በተለይም ልንቀበለው ያለውን ጊዜያዊ መከራ ተከትሎ ይመጣ ዘንድ ያለውን ብዙ ክብር በእምነት መመልከት ከቻልን መከራውን ቀላል እንደሆነና ምንም እንዳይደለ ስለምንገነዘብ አንፈራም፡፡ እንዲያውም በሮሜ 8፡18 ላይ እንደተጻፈው «ለእኛ ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ» ለማለት ስንችል፣ በ2ቆሮ.4፡16 ላይ እንደተጻፈው ደግሞ «ስለዚህ አንታክትም ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳን የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል፤ የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና፤ የሚታየው የጊዜው ነውና፤ የማይታየው ግን የዘላለም ነው» ለማለት እንችላለን፡፡

በሰምርኔስ የነበሩ አማኞች ቀድሞውንም በመከራና በድህነት የነበሩ ቢሆንም ጌታ ወደ እነርሱ በላከው መልእክት የተናገረው ቃል የሚያሳየው መከራው እየቀለለ ወይም እየጠፋ እንደሚሄድ አይደለም፡፡ ይልቁንም «ልትቀበለው ያለህን መከራ አትፍራ» በማለት ገና በቀጣይነት ሊቀበሉት ያለ መከራ እንዳለ በመግለጽ እንዳይፈሩ የሚያበረታታ መልእክት ነው የነገራቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ መከራ ሲደራረብብን «አሁንስ በዛብኝ ወደፊት ምን ልሆን ነው? ጌታ ለምን በዚህ መከራ ውስጥ ሳልፍ ዝም አለኝ?» በማለት በመከራው ከመዳከም አኳያ ለምናነሣቸው ጥያቄዎች በዚህ ቃል የሚያሳርፍ መልስ እናገኛለን፡፡ ጌታ በቀጣይ መከራዎች እንድናልፍ በመፍቀድ በዚያ መከራ ራሱን ማክበር የሚፈልግበት ጊዜም እንዳለ ማወቅ ከምንም በላይ ልብን ያጸናል፡፡

ቊ.1ዐ - «እነሆ እንድትፈተኑ ዲያብሎስ ከእናንተ አንዳንዶቻችሁን በወኅኒ ሊያገባችሁ አለው፤ አሥር ቀንም መከራን ትቀበላላችሁ»

በዚህ ክፍል ዲያብሎስ በሰምርኔስ አማኞች ላይ ሊያደርስ ያሰበውን መከራ ጌታ በዝርዝር ሲነግራቸው እንመለከታለን፡፡ ሆኖም ከመከራው እንደሚያድናቸው የሰጣቸው ተስፋ የለም፡፡ ስለክርስቶስ መከራን የምንቀበለው ለእርሱ ካለን ፍቅርና ታማኝነት በመነሣት እንጂ ከመከራው የመዳን ዋስትናን አስቀድመን ስንይዝ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ እርግጥ ነው በ2ቆሮ.1፡11 ላይ «እርሱም ይህን ከሚያህል ሞት አዳነን ያድነንማል፤ እናንተም ደግሞ ስለእኛ እየጸለያችሁ አብራችሁ ስትረዱን በብዙ ሰዎች በኩል ስለተሰጠን ስለጸጋው ስጦታ ብዙዎች ስለ እኛ ያመሰግኑ ዘንድ ወደፊት ደግሞ እንዲያድን ተስፋ አድርገናል» ተብሎ እንደተጻፈው ከመከራው ያድነናል ብሎ በጌታ ተስፋ ማድረግ መልካም ነው፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ሰምርኔስ አማኞች በመከራ ውስጥ እንድናልፍ ጌታ የሚፈቅድበት አሠራር እንዳለው ማየትም ተገቢ ነው፡፡ በማዳኑም ሆነ በመከራው ውስጥ እንድናልፍ በመፍቀዱ የሚከብረው እርሱ መሆኑን ልብ ልንል ይገባል፡፡

ከእነዚህ የሰምርኔስ አማኞች መካከል አንዳንዶቹን ዲያብሎስ ወደ ወኅኒ እንደሚያስገባቸው ተነግሯል፡፡ በወኅኒ መታሰር በክርስቲያን ላይ ሊደርሱ ከሚችሉ ከባድ መከራዎች አንዱ ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ራሱ በጭፍሮች ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ ታስሮ ነበር፡፡ በዮሐ.18፡12 ላይ «እንግዲህ የሻለቃውና ጭፍሮቹ የአይሁድም ሎሌዎች ኢየሱስን ይዘው አሰሩት» የሚል እናነባለን፡፡ ጴጥሮስና ዮሐንስ ሕዝቡን ስለ ጌታ ኢየሱስ ስላስተማሩ በወኅኒ ታስረው ነበር (የሐ.ሥ.4፡1-3)፡፡ እንዲሁም ሁሉም ሐዋርያት በአገልግሎታቸው የተነሣ በወኅኒ ታስረው ነበር (ሐ.ሥ.5፡18)፡፡ ሄሮድስ ጴጥሮስን ለብቻ በወኅኒ አስሮት ነበር (የሐ.ሥ.12፡4)፤ ጳውሎስና ሲላስ በፊልጵስዩስ ወኅኒ ቤት ታስረው ነበር (የሐ.ሥ.16፡22-24)፤ ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ተይዞ ወደ ቂሣርያ ከተወሰደ በኋላ በዚያ ከ2 ዓመት ያህል በላይ ታስሯል፡፡ እንዲሁም ጳውሎስ ወደ ሮም በተወሰደ ጊዜ ከሚጠብቀው ወታደር ጋር ለብቻው እንዲቀመጥ ቢፈቀድለትም ለ2 ዓመታት ያህል በእስር ላይ ነበር፡፡ ከዚህም ቀጥሎ የመጨረሻውን እስራቱን በተመለከተ በ2ጢሞ.1፡8፤ 2፡8፤ 4፡16 እናነባለን፡፡ ዮሐንስም በፍጥሞ ደሴት ታስሮ ነበር (ራእ.1፡9)፡፡

በሰምርኔስ ካሉ ቅዱሳን መካከልም አንዳንዶቹ ወደ ወኅኒ እንደሚገቡ ተነግሯል፡፡ ሆኖም የሚደርስባቸው መከራ በ1ዐ ቀናት ተወስኗል፡፡ 1ዐ የሚለው ቊጥር ሰው ሊሸከመው የሚችለውን ኃላፊነት የሚያመለክት ነው፤ ለምሳሌ በሕጉ ለሰው የተሰጡት ትእዛዛት 1ዐ ናቸው፤ እንዲሁም “ለ1ዐ ቀን መከራ ትቀበላላችሁ” የሚለው መከራው ከሚቻላቸው በላይ አልፎ እንዳይሄድ በእግዚአብሔር የተገደበ መሆኑንና ከተወሰነለትም ቀን በላይ መሄድ እንደማይችል ያስገነዝበናል፡፡

«እስከሞት የታመንህ ሁን የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ»

እግዚአብሔር በየዘመናቱ ሰይጣን መከራ ያደረሰባቸውን ከሞት አድኗቸዋል፡፡ ለምሳሌ ከብሉይ ኪዳን ቅዱሳን መካከል ኢዮብን ብንመለከት ሰይጣን እርሱን በተለያዩ አስከፊ መከራዎች እንዲፈትነው ቢፈቅድለትም ሕይወቱን እንዲያጠፋ ግን አልፈቀደለትም ነበር (ኢዮ.2፡6)፡፡ አናንያ፣ አዛርያ እና ሚሳኤልም ስለ እምነታቸው ወደሚነደው እቶን ውስጥ እንዲጣሉ ቢደረጉም እግዚአብሔር ከዚያ ከሚነደው ከእሳቱ እቶን አድኗቸዋል (ዳን.3፡24-27)፤ ዳንኤልንም ከአንበሶች አፍ አድኖታል (ዳን.6፡19-23)፡፡ በአዲስ ኪዳንም ለሞት ሊያደርስ ከሚችል መከራ ካዳናቸው መካከል ጴጥሮስን ከሄሮድስ እጅ (ሐ.ሥ.12፡11)፣ ጳውሎስንም ከብዙ መከራ አድኗቸዋል (2ጢሞ.4፡17)፡፡ ከሰምርኔስ አማኞች መካከል ወደ ወኅኒ የሚገቡት ግን እስከ ሞት ድረስ የታመኑ እንዲሆኑ ተነግሯቸዋል፡፡ ለእነርሱ የተሰጠው ተስፋ ሊቀበሉት ከላቸው መከራ ማዳን ሳይሆን ከሞት ባሻገር ያለው «የሕይወት አክሊል» ነበር፡፡ እንደሚታወቀው «አክሊል» ያሸነፉ ሰዎች የሚቀዳጁት ሽልማት ነው፡፡ በእምነት ጸንተው እዚህ ምድር ላይ እስከሞት ድረስ ለታመኑ ሁሉ ለዚህ ታማኝነታቸው «የሕይወት አክሊል» ሊቀዳጁ ተገብቶአቸዋል፡፡ በ2ጢሞ.4፡8 ላይ «መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ» በሕይወት ዘመናቸው ለነበራቸው መልካም ገድል ስለተዘጋጀላቸው «የጽድቅ አክሊል» እናነባለን፡፡ በ1ጴጥ.5፡4 ደግሞ እዚህ ምድር ላይ ራሳቸውን አዋርደው ጌታን ሲያገለግሉ ለነበሩት ቅዱሳን ስለሚሰጠው «የክብር አክሊል» እናነባለን፡፡ ስለዚህ የአክሊሉ ዓይነት የተገለጠው አማኞች በምድር ላይ ካለፉበት ሁኔታ ጋር በተያያዘ መሆኑን እናስተውላለን፡፡ ስለሆነም በሰምርኔስ የነበሩ አማኞች እስከ ሞት በሚያደርስ መከራ ውስጥ ስለነበሩ «የሕይወትን አክሊል እሰጥሃለሁ» የሚል ተስፋ ሊሰጣቸው ችሏል፡፡ በተጨማሪም ስለ ሕይወት አክሊል በያዕ.1፡12 ላይ የተነገረው ቃል «በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና» ይላል፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ በምድር ሳለ ሕይወቱ በፈተና ለተሞላና በዚያ ፈተና ለጸና አማኝ የሕይወት አክሊል እንደሚሰጠው እንገነዘባለን፡፡

በሰምርኔስ ለነበረች ቤተክርስቲያን የተላከው መልእክት በትንቢታዊ ገጽታው ከዘመነ ሐዋርያት ቀጥሎ እስከ 4ኛ ክፍለ ዘመን ድረስ በአማኞች ላይ የደረሰውን እጅግ አሠቃቂ መከራ ሊያመለክት ይችላል፡፡ በዚህ ክፍለ ዘመን የነበረው የሮም መንግሥት እጅግ ጨካኝ መንግሥት ነበር፡፡ በዳን.7፡7 ላይ «የምታስፈራና የምታስደነግጥ እጅግም የበረታች ታላላቅም የብረት ጥርሶች የነበሯት አራተኛ አውሬ» ተብሎ የተገለጠው የሮም መንግሥት ሲሆን የቃሉ አገላለጽም የጭካኔውን ከፍተኛነት የሚያስረዳ ነው፡፡

ክርስቲያኖች ሕያው የሆነውን አንድ አምላክ እግዚአብሔርን የሚያመልኩና ለአሕዛብ አማልክት የማይሰግዱ በመሆናቸው እንዲሁም የኢየሱስ ክርስቶስን ጌትነት በመመስከራቸው በአሕዛቡ ዓለም በከፍተኛ ደረጃ ይጠሉ ነበር፤ በአገር ላይ አንድ አደጋ በደረሰ ቊጥር የአደጋው ምክንያት ክርስቲያኖች ተደርገው ይወሰዱ ነበር፤ ከዚህም የተነሣ እጅግ አሠቃቂ የሆኑ ስደቶችና መከራዎች ይደርስባቸው ነበር፤ በሮም ግዛት ውስጥ ከኔሮን ቄሣር ጀምሮ እስከ ዲዮቅልጥያኖስ ድረስ ባሉት ዘመናት ውስጥ በጌታ ከተወሰኑት አሥር የመከራ ቀናት ጋር ሊነጻጸር በሚችል መልኩ በክርስቲያኖች ላይ እጅግ አሠቃቂ የሆኑ አሥር ዋና ዋና የመከራና የስደት ዘመናት ተመዝግበዋል፡፡ እነርሱም፡

  1. በነሮ(በኔሮን) ዘመን፣
  2. በዶሚትያን (በድምጥያኖስ) ዘመን፣
  3. በትራጃን ዘመን፣
  4. በማርቆስ ኡሬሊየስ ዘመን፣
  5. በሴቬሩስ ዘመን
  6. በማክሲሚን ዘመን፣
  7. በዴኪየስ (በዳክዮስ) ዘመን፣
  8. በቬሌሪያን ዘመን፣
  9. በኡሬሊያን ዘመን፣
  10. በዲዮክሌትያን(በዲዮቅልጥያኖስ) ዘመን የነበሩት የመከራ ዓመታት ናቸው፡፡

ይሁንና በክርስትና የተገለጠውን እውነት ይህ ሁሉ መከራ ሊያጠፋው አልቻለም፤ ጌታችን ኢየሱስ በአማኞች ላይ መከራ እንዲደርስ ቢፈቅድም መከራው ግን እርሱ ከወሰነው ጊዜ በላይ አልፎ እንዲሄድ አይፈቅድለትም፡፡ ቀደም ሲል እንደተመለከተነውም ለአስር ቀን መከራ ትቀበላላችሁ ብሎ ለሰምርኔስ አማኞች ጌታ የተናገረውም ይህን ያሳየናል፤ ስለሆነም ጨካኞቹ ነገሥታት በእግዚአብሔር ፍርድ እየሞቱ መከራው ጌታ በወሰነው ጊዜ ሊያቆም ችሏል፡፡

የዚያን ጊዜ መከራ ጌታ በወሰነለት ጊዜ ያቁም እንጂ ዲያብሎስ በየዘመናቱ ክፉ ሰዎችን በመጠቀም የክርስቶስ የሆኑቱን ማሳደዱንና እስከሞት የሚያደርሱ አሠቃቂ መከራዎችን ማምጣቱ አልቀረም፤ ሆኖም አማኞች እንደነዚህ ቅዱሳን ለጌታ እስከሞት ድረስ የታመኑ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ይህም ከሆነ ጌታ በሰጠው የተረጋገጠ ተስፋ መሠረት የሕይወት አክሊልን ይቀበላሉ፡፡

«መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ፤ ድል የነሳው በሁለተኛው ሞት አይጐዳም»

መንፈስ በሰምርኔስ ለነበረች ቤተክርስቲያን ያስተላለፈው መልእክት በዚያ ዘመንም ሆነ ጌታ ተመልሶ እስከሚመጣ ድረስ በምድር ላይ የስፍራው ለሚኖሩት አብያተ ክርስቲያናት የተላለፈ መልእክት መሆኑን በውስጥ ጆሮአችን በማስተዋል እንድንሰማ በዚህ የማስገንዘቢያ ቃል ተነግሮናል፡፡ ስለሆነም በበረከትና በሰላም መኖርን ብቻ ሳይሆን ስለ ክርስቶስ እስከሞት የሚያደርስ መከራ መቀበል ሊኖር እንደሚችልም መንፈስ የሚለውን ልንሰማ ይገባል፡፡ ይህንን ተረድተው ለጌታ እስከሞት የታመኑት ሁሉ ከፊት ለፊታቸው የተጋፈጣቸውን መከራ በጽናት ተጋፍጠው ድል መንሳት ችለዋል፤ ሞት ሲፈረድበት ድል የነሣው አማኝ ደግሞ «በሁለተኛው ሞት አይጐዳም» የሚል የተባረከ ቃል ኪዳን ተገብቶለታል፡፡ «ሁለተኛው ሞት» ሁለተኛ የተባለው በሥጋ የሚደርሰው ሞት አንደኛ ሆኖ ተቈጥሮ ነው፤ በራእ.21፡14 መሠረት ሁለተኛው ሞት የእሳት ባሕር ነው፤ ስለሆነም እስከ ሞት ታማኝ በመሆን ድል የነሳው አማኝ በዚህ ዓለም በሥጋ በደረሰበት ሞት ቢጐዳም በሁለተኛው ሞት ግን እንደማይጐዳ ማለትም ጒዳቱ ፈጽሞ ሊያገኘው እንደማይችል ተረጋገጠለት፡፡ ይህ እስከሞት ሊያደርስ የሚችል መከራን ለሚጋፈጡ አማኞች ሁሉ ብርቱ ጽናትን ያጎናጽፋቸዋል፡፡

ክፍል ሦስት >>>>

Amharic Bible-|- The Holy Bible [King James Version]