በእስያ ለነበሩት አብያተ ክርስቲያናት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የላካቸው መልክታት እያንዳንዳቸውን ማጥናት በየስፍራው የሚገኙ ጉባኤያት ያሉበትን ተግባራዊ ሁኔታ የሚሸፍን ከመሆኑም ባሻገር በየዘመናቱ ቤተክርስቲያን የነበራት እና የሚኖራትን የተለያዩ ገጽታዎችን የሚገልጽ ነው፡፡ ይህንንም በኤፌሶን ለነበረች እና በሰምርኔስ ለነበረች ቤተክርስቲያን የተጻፉትን መልእክታት ስናብራራ በስፋት የተመለከትን ሲሆን አሁንም በጴርጋሞን ለነበረች ቤተክርስቲያን የተላከውን መልእክትም በዚሁ ዓይነት እናጠናለን፡፡
በጴርጋሞን ወዳለው ወደ ቤተክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ በሁለት ወገን የተሳለ ስለታም ሰይፍ ያለው እንዲህ ይላል» (ቁ.12)
«ጴርጋሞን» የተባለችው ከተማ በታናሽ እስያ ውስጥ በምትገኝ «ሚስያ» (ሐ.ሥ.16፡7-8) በተባለች ክፍለ ሀገር ውስጥ የንጉሥ መቀመጫ የነበረች ስትሆን በአሁን ጊዜ «ቤርጋማ» ተብላ የምትጠራ አነስተኛ ከተማ ናት፡፡ በዚህች ከተማ ለነበረች ቤተክርስቲያን ጌታ ኢየሱስ መልእክትን ያስተላልፋል፡፡ ጌታችን ለዚህች ቤተክርስቲያን ራሱን ያስተዋወቀውም «በሁለት ወገን የተሳለ ስለታም ሰይፍ ያለው» በማለት ነው፡፡ በራእ.1፡16 እንደምንመለከተው ባለራእዩ ዮሐንስ ጌታን ሲያየው «ከአፉ በሁለት ወገን የተሳለ ስለታማ ሰይፍ» ሲወጣ አይቷል፡፡ ስለዚህ ይህ የጌታ ሰይፍ ከአፉ የሚወጣ ነው ማለት ነው፤ ይህም ሰይፍ ከጌታ አፍ የሚወጣው የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ ያስረዳል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በኤፌ.6፡17 ላይ «የመዳንን ራስ ቁር የመንፍስንም ሰይፍ ያዙ፤ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው» የሚል ሲሆን በዕብ.4፡12 ላይ ደግሞ «የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል» (ዕብ.4:12) ይላል፡፡ ይህም ጥቅስ ከጌታ አፍ የወጣው በሁለት ወገን የተሳለ ስለታም ሰይፍ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ያስገነዝባል፡፡ ለጴርጋሞን ቤተክርስቲያን በተላከው በዚችው መልእክት ውስጥ በቁ.16 ላይ ይህ የጌታ የአፉ ሰይፍ የተጠቀሰ በመሆኑ ጌታ ራሱን ለቤተክርስቲያኒቱ ያቀረበው ቤተክርስቲያኒቱ ካለችበት ሁኔታ ጋር አብሮ በሚሄድ ማንነቱ መሆኑን እንረዳለን፡፡
“የሰይጣን ዙፋን ባለበት የምትኖርበትን አውቃለሁ፤ ስሜንም ትጠብቃለህ፥ ሰይጣንም በሚኖርበት፥ በእናንተ ዘንድ የተገደለው የታመነው ምስክሬ አንቲጳስ በነበረበት ዘመን እንኳ ሃይማኖቴን አልካድህም።” (ራእ.2:13)
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በጴርጋሞን ቤተክርስቲያን ያሉት አማኞች የሚኖሩበትን ስፍራ ያውቃል፤ ያንን ስፍራም “የሰይጣን ዙፋን ባለበት” ብሎ ይገልጠዋል፤ “የሰይጣን ዙፋን ባለበት” ሲል ሰይጣን በነገሠበትና ገዢ በሆነበት ስፍራ ማለት መሆኑን እንረዳለን፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣንን “የዚህ ዓለም ገዢ” (ዮሐ.12፡31)፣ “የዚህ ዓለም አምላክ” (2ቆሮ.4፡4)፣ በማለት ይጠራዋል፡፡ ይህም ሰይጣን ለጌታ ያልታዘዘውን ዓለም በራሱ መመሪያዎች የሚገዛ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ በ1ዮሐ.5፡19 ላይ “ከእግዚአብሔር እንደ ሆንን ዓለምም በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ እናውቃለን።” ይላል፡፡ ስለሆነም የእግዚአብሔር የሆኑቱ ከዓለም ተጠርተው ከጨለማው ሥልጣን ማለትም ከሰይጣን አገዛዝ ድነው የወጡ ቢሆኑም ዓለሙ ግን በሰይጣን ፈቃድ ሥር እንዳለ እንገነዘባለን፡፡ በተለይም ደግሞ ሰይጣን ለአገዛዙ የሚጠቀመው የዚህ ዓለም መንግሥትን እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ በሉቃ.4፡5-6 ላይ የዓለምን መንግሥታት በተመለከተ “ይህ ሥልጣን ሁሉ ክብራቸውም ለእኔ ተሰጥቷል፤ ለምወደውም እሰጠዋለሁና …” ብሎ በኢየሱስ ፊት ሰይጣን ራሱ የተናገረውን እናነባለን፤ በራእ.13፡2 ላይ ደግሞ የዚህ ዓለም ክፉ መንግሥት ለሆነው ለአውሬው ዙፋኑንና ሥልጣኑን የሰጠው ዘንዶው ወይም ዲያብሎስ እንደሆነ ሲናገር “ያየሁትም አውሬ ነብር ይመስል ነበር፥ እግሮቹም እንደ ድብ እግሮች፥ አፉም እንደ አንበሳ አፍ ነበሩ። ዘንዶውም ኃይሉንና ዙፋኑን ትልቅም ሥልጣን ሰጠው” ይላል (ራእ.13:2)፡፡ በመሆኑም ይህ የሰይጣን አገዛዝና በዓለም ያለው አሠራሩ በጴርጋሞን ባለች ቤተክርስቲያን ውስጥ ገብቶ ስለነበር ጌታ “የሰይጣን ዙፋን ባለበት የምትኖርበትን አውቃለሁ” በማለት በዚያ ላለው አማኝ ሲናገር እንመለከታለን፡፡
ታዲያ እንዲህ ባለ አሳዛኝና አስከፊ ነገር ባለበት ስፍራ እየኖሩ ሳለ በጴርጋሞን ቤተክርስቲያን የነበሩ አማኞች የተመሰገኑበትን ጉዳይ መመልከት በእጅጉ አስደሳች ነው፡፡ በመጀመሪያ “ስሜን ትጠብቃለህ” ተብለዋል፤ ይህም ለፊልድልፍያ አማኞች “ስሜን አልካድክምና” ተብሎ ከተነገረው ጋር የሚመሳሰል ነው (ራእ.3፡8)፡፡ ይህም የሚያሳየው በኢየሱስ ስም መሰብሰብን (ማቴ.20፡18)፣ በኢየሱስ ስም መጸለይን (ዮሐ.14፡14)፣ በኢየሱስ ስም ማመስገንን (ኤፌ.5፡20)፣ ባጠቃላይ የሚያደርጉትን ሁሉ በኢየሱስ ስም ማድረግን (ቆላ.3፡17) ያልተዉና አጽንተው የያዙ መሆናቸውን ነው፡፡ ቀጥሎም “ሰይጣንም በሚኖርበት፥ በእናንተ ዘንድ የተገደለው የታመነው ምስክሬ አንቲጳስ በነበረበት ዘመን እንኳ ሃይማኖቴን አልካድህም።” (ቁ.13) ተብለዋል፡፡ የሰይጣን ዙፋን ባለበት የሚኖሩ እንደመሆናቸው መጠን ሰይጣን የክርስቶስን የታመኑ ምስክሮች እንዲገደሉ የሚያደርግ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ምናልባት በጴርጋሞን ቤተክርስቲያን ውስጥ እንዲህ ያለውን ግድያ ለመፈጸም ሰይጣን ለፈቃዱ የተገዙለትን የአፍ አማኞችን ሊጠቀም ይችል ይሆናል፤ ጌታ ኢየሱስ አንቲጳስን “የታመነው ምስክሬ” ብሎ ሲጠራው ያልታመኑ ሰዎች በጴርጋሞን ቤተክርስቲያን ውስጥ እንደበነሩ ሊያስገነዝበን ይችላል፡፡ እንደዚህ ዓይነቶቹ ሰዎች ከመጣው መከራና ስደት ራሳቸውን የሚያተርፉት አምነንበታል ሲሉ የቆዩትን እውነት በሰው ፊት ሲክዱና የታመኑትን ምስክሮችም አሳልፈው ሲሰጡ ነው፡፡ ይህም ከጌታ የሚያርቃቸውን ያህል ከዓለም ጋር ወዳጅነትን ይፈጥርላቸዋል፡፡ ሆኖም በዚያው ልክ የታመነው ምስክር አንቲጳስ ሲገደል እያዩ እየሰሙ በእምነታቸው የጸኑ አማኞች መኖራቸው ጌታን በእጅጉ የሚያስደስት ነው፡፡ ስለሆነም እነዚህን አማኞች “ሃይማኖቴን አልካድክም” ይላቸዋል፡፡ እዚህ ላይ “ሃይማኖቴን” ሲል “እምነቴን” ማለት ሲሆን ያም እርሱ የገለጠውን እውነት ማመንን የሚያመለክት ነው፡፡ ይህን እምነት በተለይ በመከራ ጊዜ አጽንቶ መያዝ ከፍ ያለ ታማኝነት ነው፡፡
“ዳሩ ግን ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉና እንዲሴስኑ በእስራኤል ልጆች ፊት ማሰናከያን ሊያኖርባቸው ባላቅን ያስተማረ የበለዓምን ትምህርት የሚጠብቁ በዚያ ከአንተ ጋር ስላሉ፥ የምነቅፍብህ ጥቂት ነገር አለኝ። እንዲሁ የኒቆላውያንን ትምህርት እንደ እነዚህ የሚጠብቁ ሰዎች ከአንተ ጋር ደግሞ አሉ።” (ራእ.2:14-15)፡፡
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በጴርጋሞን ባለች ቤተክርስቲያን ውስጥ ከሚነቅፈው ነገር አንዱ “የበለዓምን ትምህርት የሚጠብቁ ሰዎች” በጴርጋሞን ካሉ ቅዱሳን ጋር አብረው መኖራቸው ነው፤ እነዚህ ሰዎች ቸል መባላቸው ጌታን አሳዝኖታል፡፡ ከንባቡ እንደምንረዳው “የበለዓም ትምህርት” የእስራኤል ልጆች ለጣኦት የታረደውን እንዲበሉና እንዲሴስኑ ለማድረግ ማሰናከያን እንዴት ማኖር እንደሚችል ለሞዓብ ንጉሥ ለባላቅ የተሰጠ ትምህርት ነበር፤ በዘኁል. 22 ላይ እንደምናነበው እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባታቸው በፊት በሞዓብ ሜዳ በሰፈሩ ጊዜ “በሬ የለመለመውን ሣር እንደሚጨርስ ይህ ጭፍራ በዙሪያችን ያለውን ሁሉ ይጨርሳል” በሚል ሞዓባውያን ስለፈሩ ንጉሣቸው ባላቅ እስራኤልን ይረግምለት ዘንድ ለበለዓም የምዋርት ዋጋ ልኮለት ነበር (ቁ.17)፡፡ ባላቅ እስራኤልን ይረግምለት ዘንድ በለዓምን በሦስት የተለያዩ ቦታዎች፣ ሦስት ጊዜ፣ ሙከራ ቢያደርግም እግዚአብሔር ጣልቃ ገብቶ ቃልን በበለዓም አፍ በማድረግ እርግማኑን ለውጦ እንዲባርካቸው አድርጎታል፡፡ (ዘኁል.23፡5፤ 24፡10፤ ዘዳግ.23፡4-5፤ ነህ.13፡2)፡፡ ይሁን እንጂ በለዓም በምዋርቱና በአስማቱ እስራኤልን መርገም እንዳልቻለ ባየ ጊዜ ንጉሡ ባላቅ በእስራኤል ፊት እንቅፋትን ወይም ማሰናከያን ሊያኖር የሚያስችለውን ክፉ ትምህርት ወይም ክፉ ምክር እንደሰጠው ከዘኁል.31፡16 እንገነዘባለን፡፡ በዚህ ክፍል ሙሴ በምድያማውያን ላይ በተደረገው የበቀል ጦርነት የእስራኤል ጭፍራዎችና አለቆች ያዳኑአቸውን ሴቶች አስመልክቶ ተቆጥቶ ሲናገር “እነሆ፥ እነዚህ በፌጎር ምክንያት በበለዓም ምክር እግዚአብሔርን ይበድሉ ዘንድ ለእስራኤል ልጆች ዕንቅፋት ሆኑ፤ ስለዚህም በእግዚአብሔር ማኅበር ላይ መቅሠፍት ሆነ።” ብሏል፡፡ ስለዚህ በለዓም የሞዓብና የምድያም ሴቶች ለእስራኤል እንቅፋት እንዲሆኑ የመከረው ምክር ወይም ያስተማረው ትምህርት እንደነበር ይህ ንባብ በግልጽ ያስረዳል፡፡ ይህ በተግባር እንዴት እንደተፈጸመ የምናነበውም በዘኁል.25፡1-9 ባለው ክፍል ነው፡፡ በዚህ ክፍል ሞዓባውያን የእስራኤልን ሕዝብ ወደ አምላኮቻቸው መሥዋዕት እንደጠሩ ሕዝቡም መሥዋዕቱን እንደበሉና ከሞዓብ ልጆች ጋር እንዳመነዘሩ በዚህም ምክንያት በመጣው የእግዚአብሔር ቁጣ 24 ሺህ ያህል ሰው እንደተቀሠፈ እናነባለን፡፡ ጠላት በእርግማን አልሆን ሲለው በማባባል በዘዴና በተንኮል ወደራሱ አቅርቦ እግዚአብሔርን እንዲበድሉ በማድረግ እስራኤልን እንዴት እንዳሳተ እንመለከታለን፡፡ ይህም የበለዓም ትምህርት አስከፊ ውጤት ነው፡፡
በጴርጋሞን በነበረች ቤተክርስቲያን ውስጥ የበለዓምን ትምህርት የሚጠብቁ ሰዎች መኖራቸውን የሚያመለክተው ክርስቲያኖች ነን ካሉ በኋላ ትተንው መጥተናል ያሉትን በውጭ ባለው ዓለም የሚገኘውን የሞዓባውያንን ሥራ ማለትም ጣኦት አምልኮና ሴሰኝነትን የሚፈጽሙ ሰዎች በመካከል እንደነበሩ የሚያሳይ ነው፡፡ በሰምርኔስ በነበረች ቤተክርስቲያን ጠላት በጉልበት ተጠቅሞ እስራትንና ግድያን በአማኞች ላይ በማምጣት ለማጥቃት ሲሞክር የሚታይ ሲሆን በጴርጋሞን ባለች ቤተክርስቲያን ግን በውጭ ባለው ሞዓባዊ ተግባር አንዳንዶችን ሲማርክ እናያለን፡፡ ታዲያ በሰምርኔስ ከነበረው ይልቅ በጴርጋሞን የነበረው የጠላት አሠራር አማኞችን በእጅጉ የሚጎዳ ነው፡፡ ጠላት ብዙ ጊዜ በጉልበት ያልተሳካለትን ዓላማ ተግባብቶና ተስማምቶ ከቤተክርሰቲያን አንዳንዶችን ወደራሱ በማቅረብ በውጭ ባሉ ክፋቶች በመያዝ ሲያሳካ ይታያል፡፡ ስለሆነም የክርስቶስ የሆኑቱ በውጭ ካሉ ዓለማዊ ነገሮች በእጅጉ ሊጠነቀቁ ይገባል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ታማኝነት በሁሉም ስለማይገኝ አንዳንዶች በቤተክርስቲያን እየተመላለሱ ሞዓባዊ ጠባይ ባለው ዓለማዊና ሥጋዊ ሕይወት የሚኖሩ በዚህም ኑሮአቸው ከመፍረድ ይልቅ እንዳልተሳሳቱና ልክ እንደሆኑ አድርገው የሚያስረዱ ሰዎች ይገኛሉ፤ ይህም የበለዓምን ትምህርት መጠበቅ ነው፡፡
የበለዓም ትምህርት በተለይ የተገለጠው ለጣኦት የተሠዋውን በመብላትና በሴሰኝነት ነው፡፡ ለጣኦት የተሠዋውን መብላት ከአጋንንት ጋር ማኅበረተኛ የሚያደርግ እንደሆነም በ1ቆሮ.10፡10-20 ተገልጧል፡፡ እዚህ ላይ የተጠቀሰው ለጣኦት የተሠዋውን መብላት ቢሆንም ከአጋንንት ጋር ማኅበረተኛ የሚያደርጉ ሌሎች ብዙ ዓለማዊ ተግባሮችም ይኖራሉ ከማያምኑ ጋር አብሮ በማናቸውም ክፋትና ዓመፅ መተባበር የዚህ ክፋት ማኅበር አባል መሆን ነው፡፤ ይህም የበለዓምን ትምህርት የሚጠብቁ ሰዎች መገለጫ ነው፡፡ ሴሰኝነትም እንዲሁ ከቤተክርስቲያን ውጭ ባለው ሞዓባዊ ዓለም የሚገኝ ርኩስ ተግባር ቢሆንም ጠላት ሥጋውያን ክርስቲያኖችን የሚማርክበት ዋነኛ መሣሪያው ነው፡፡ ወንድሞች ከሚባሉት መካከል አንዳንዶች በዚህ ክፉ ዓለም ባለው ሴሰኝነት የሚመላለሱ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ (1ቆሮ.5፡11)፡፡ እነዚህም “የአምላካችንን ጸጋ በሴሰኝነት ይለውጣሉ” የተባሉት ናቸው (ይሁ. 4)፤ ይህ በተቃራኒ ጾታዎች መካከል ያለው ተገቢ ያልሆነ መቀራረብ በቸልታ በሚታለፍባቸው ማኅበራት ሁሉ የሚታይ ውድቀት ነው፡፡ በዓለም ካለው የጠላት አሠራር ጋር በመተባበር ራሳቸውን የክፋት ማኅበረተኛ ያደረጉ ሥጋውያን ክርስቲያኖች ሁሉ በሴሰኝነት መገለጣቸው የማይቀር ነው፡፡ እነዚህም ሰዎች በኅሊናቸው የሚመጣውን ወቀሳ ለመቋቋም ራሳቸውን ያሳመኑበት መንገድ ይኖራቸዋል፤ ምናልባትም የእግዚአብሔርን ጸጋና ምሕረት ለዚህ ክፋታቸው መሸፈኛ ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ እነዚህ “የአምላካችን ጸጋ በሴሰኝነት የለወጡ” ሰዎች የበለዓምን ትምህርት የሚጠብቁ ናቸው፡፡
በጴርጋሞን ባለች ቤተክርስቲያን ላሉ ቅዱሳን በተላለፈው መልእክት ጌታ የነቀፈው ነገር እነዚህ የበለዓምን ትምህርት የሚጠብቁ ሰዎች ከእነርሱ ጋር መኖራቸውን ነው፡፡ “… የበለዓምን ትምህርት የሚጠብቁ በዚያ ከአንተ ጋር ስላሉ፥ የምነቅፍብህ ጥቂት ነገር አለኝ” ብሏቸዋል፤ ስለሆነም ከዓመፅ መራቅ እስከተቻለ ድረስ ከክፉ ሰዎች ጋር አብሮ መሆን ምንም ችግር እንደሌለው በአንዳንዶች የሚታሰበው ሐሳብ በዚህ የጌታ መልእክት አንጻር ተቀባይነት የለውም፡፡ በጸጋና በፍቅር ሰበብ ዓመፀኞችን በቸልታ ዝም በማለት ከእነርሱ ጋር አብረዋቸው እንዲሆኑ ለሚፈቅዱ አማኞች ሁሉ ይህ ግልጽ መልእክት ነው፡፡
በጴርጋሞን ባለች ቤተክርስቲያን ካሉ አማኞች ጋር የነበሩት የበለዓምን ትምህርት የሚጠብቁ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ “የኒቆላውያንን ትምህርት” የሚጠብቁ ሰዎችም ናቸው፡፡ “ኒቆላውያን” ተብለው የተጠሩት ቡድኖች እነማን እንደነበሩ በክርስቲያኖች መካከል የሚሠሩት ክፉ ሥራና የሚያስተምሩት ክፉ ትምህርት ምን እንደነበር በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጠ ነገር የለም፡፡ ሆኖም ሥራቸው በጌታ የተጠላና በአማኞችም ሊጠላ የሚገባው መሆኑን ጌታ ለኤፌሶን ቤተክርስቲያን ባስተላለፈው መልእክት ገልጧል፡፡ እነዚህ ሰዎች በጌታም ሆነ በኤፌሶን ቅዱሳን ለተጠላ ለዚህ ሥራቸው ትምህርት እንዳበጁለት መረዳት ይቻላል፡፡ ሆኖም ትምህርታቸውም ቢሆን እንደ ሥራቸው ሁሉ የተጠላ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ በክፉ ሥራ የተገለጡ ሐሰተኛ ወንድሞች በእልከኝነት ሲሄዱ የሚያደርጉት ነገር ለዚያ ክፉ ሥራቸው ትምህርት ማበጀት ነው፡፡ ትምህርታቸውም እንደ ሥራቸው ሁሉ ክፉ ሲሆን ይህንን ክፉ ትምህርት በአማኞች መካከል አሹልከው ለማስገባት ጥረት ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ሆኖም አማኞች ክፉ ሥራቸውን ብቻ ሳይሆን ክፉ ትምህርታቸውንም ጌታ በሚጠላው መጠን ሊጠሉት ይገባል፡፡ ነገር ግን የኒቆላውያን ሥራ በኤፌሶን ቤተክርስቲያን የተጠላውን ያህል የኒቆላውያን ትምህርት በጴርጋሞን ቤተክርስቲያን አልተጠላም ነበር፡፡ ይህም ጌታ የነቀፈው ነገር ነው፤ ጌታ የሚነቅፈው የሐሰት አማኞችን ክፉ ሥራና ክፉ ትምህርት ብቻ ሳይሆን እነዚህ ክፉ ሰዎች የእርሱ በሆኑት መካከል መገኘታቸውንም ጭምር ነው፡፤ በዚህ መልክ የሚነቅፈው ደግሞ ክፉ ወንድሞች ከእነርሱ ጋር አብረው ሲሆኑ በዝምታና በቸልታ የተመለከቱትን የራሱ የሆኑትን ቅዱሳን ነው፡፡ ስለሆነም የክርስቶስ የሆኑት በክፉ ሥራ፣ በክፉ ትምህርት ቡድን የፈጠሩ ሰዎች በመካከላቸው ሲገኙ እንዲህ ያሉትን ከመካከላቸው ሊያርቁ ወይም እነርሱ ሊለዩአቸው ይገባቸዋል እንጂ በቸልታ ሊያልፉ አይገባቸውም፡፡
በጴርጋሞን ላለች ቤተክርስቲያን ጌታችን ያስተላለፈው መልእክት በትንቢታዊ ይዘቱ በቤተክርስቲያን ታሪክ ውጥ ከ4ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አንስቶ እስከ 6ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ድረስ በክርስትናው ዓለም የነበረውን ሁኔታ የሚያመለክት እንደሆነ ልንገነዘብ እንችላለን፡፡ በተለይም ቆስጠንጢኖስ የተባለው ቄሣር ከነገሠ በኋላ በ313 ዓ.ም. ክርስቲያኖችን በተመለከተ “ሚላን” በተባለ ቦታ ያወጣውን አዋጅ ተከትሎ የክርስትናው ዓለም ከዓለማዊነትና ከአሕዛብ ተግባራት ጋር የመቀላቀል ወይም የመዋሐድ ሁኔታ በስፋት ታይቶበታል፡፡ አዋጁ አስቀድመው የነበሩት ጨካኝ ነገሥታት ካወጧቸው አዋጆች፣ በተለይም ዲዮቅልጥያኖስ ካወጣው በክርስቲያኖች ላይ ከታወጀው የግፍና የጭካኔ አዋጅ ተቃራኒ ሲሆን ለክርስቲያኖች የሚወግን፣ መብታቸውንና ነጻነታቸውን የሚያስከብርና ከዚያ በፊት የነበረውን ሁኔታ የቀየረ ታሪካዊ አዋጅ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ የዚያኑ ያህል የክርስትናው ዓለም ከዚህ ዓለም መንግሥታት እና በአሕዛቡ ዓለም ከሚፈጸሙ ክፉ ተግባራት ወይም ልማዶች ጋር እንዲዋሐድና እንዲስማማ ያደረገ ሆኗል፡፡ የአዋጁ ይዘትም የታሰሩ ክርስቲያኖች እንዲፈቱ፣ የተወረሱ የክርስቲያኖች ንብረቶች እንዲመለሱላቸው፣ በየስፍራው ለቤተክርስቲያን መሰብሰቢያ የሚሆኑ ሕንጻዎች እንዲሠሩ፣ ባጠቃላይ ክርስቲያኖች የእምነት ነጻነት እንዲኖራቸው፣ እንዲያውም ክርስትና የመንግሥት ሃይማኖት እንዲሆን የሚገልጽ ነበር፡፡ ይህም ብዙ ክርስቲያኖች ወደ ሃይማኖተኝነት እንዲገቡ በር የከፈተ ሲሆን በጊዜው የነበሩትም የክርስትና ሃይማኖት መሪዎች በመንግሥትም ሆነ በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ከበሬታን እንዲያገኙ ያደረገ ነው፡፡
ክርስትናው በንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ አማካኝነት ይህንን ያህል ነጻነትና የከበሬታን ስፍራ ማግኘቱ ምን ክፋት አለበት ተብሎ ሊታሰብ ይችላል፤ ሆኖም ሰይጣን በሰምርኔስ የመከራ ዘመን እስከ ሞት በሚያደርሱ የተለያዩ መከራዎችን በማድረስ ሊያሳካ ያልቻለውን ዓላማ ያሳካው ቆስጠንጢኖስ ለቤተክርስቲያን የሰጠውን ምድራዊ ነጻነት ተጠቅሞ ክርስቲያኖችን ወደ ዓለማዊነት በማስገባት ነበር፡፡ ይህም ለጴርጋሞን ቤተክርስቲያን በተላከው መልእክት የታየ ነው፡፡ በለዓም እስራኤልን በእርግማን ሊያጠፋቸው እንደማይችል ካወቀ በኋላ ንጉሡ ባላቅ እስራኤልን አግባብቶ ከሞዓባውያን ጋር እንዲቀላቀሉና የጣኦቶቻቸውን መሥዋዕት እንዲበሉ ብሎም ከሞዓባውያን ጋር እንዲሴስኑ ያስተማረው ትምህርት የሚፈልገውን ክፉ ውጤት አስገኝቶለት ነበር፤ ይህ የበለዓም ትምህርት በጴርጋሞን ቤተክርስቲያን እንደነበረ ሁሉ በጉሥ ቆስጠንጢኖስ ምድራዊ ነጻነት በሰጣት ቤተክርስቲያን ውስጥም ነበር፡፡ ንጉሡ ራሱ በዚያን ጊዜ የነበረችውን ቤተክርስቲያን በበላይነት ይቆጣጠር ነበር፡፡ እንዲያውም በጊዜው የነበሩት “ጳጳሳት” ለተለያዩ ጉዳዮች ስብሰባ ሲያደርጉ እርሱ ራሱ በስብሰባው ላይ እየተገኘ ንግግር ያደርግና ሁኔታዎችን ይቆጣጠር ነበር፡፡ ይህም በክርስትናው ውስጥ የነበረውን የዚህ ዓለም መንግሥት ጣልቃ ገብነት የሚያሳይ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ምንም እንኳ ክርስትናን ተቀብያለሁ ይበል እንጂ ከእርሱ በፊት እንደነበሩት ቄሣሮች ሁሉ የሮም መንግሥት በመላው ዓለም ሲከተለው የነበረው የጣኦት አምልኮ ሊቀ ካህናት (Pontifex Maximus) ነበር፡፡ ስለዚህ እርሱ እስኪሞት ድረስ በአንድ በኩል ወደ ዓለማዊነት ለገባችው ቤተክርስቲያን ራስ የነበረ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በአሕዛቡ ዓለም ለነበረው የጣኦት አምልኮ ሊቀ ካህናት ነበር፤፡ በተጨማሪም በ313 ዓ.ም. ከታወጀው አዋጅ በኋላ ክርስትና በይፋ ነጻነት እንደተሰጠው ከተረጋገጠ ጊዜ ጀምሮ በጊዜው ላባሩም (Labarum) ተብሎ ይጠራ በነበረው መንግሥታዊ ሰሌዳ ላይ “ኢየሱስ የሰዎች አዳኝ” ከሚለው ጽሑፍ የመነሻ ፊደላት (I.H.S.) እና ከመስቀል ምልክት ጋር በወርቅ የተሠራ የንጉሡ ምስል አብሮ ነበረ፡፡ ይህም የክርስትናንና የአሕዛብን ልማድ የማቀላቀል ሥራ እንደተሠራ የሚያስረዳ ከመሆኑም ሌላ በክርስቲያኖችም ሆነ በአሕዛብ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት የተደረገ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡
በሌላ በኩልም ወደ ዓለማዊነት የገባው የክርስትና ጠባይ እንዲሁ ንጉሡ ያደርግ እንደነበረው በአሕዛቡ ዓለም ከነበረው የጣዖት አምልኮ ጋር መቀላቀል ሲጀምር እንመለከታለን፡፡ ክርስትና በቤተመንግሥት ተቀባይነት ያለውና የተከበረ ሃይማኖት ወደመሆን እንደመጣ የተመለከቱ አሕዛብ በወንጌል እውነት ልባቸው ሳይነካ የዚህ ዓለምን ክብርና ሀብት በመፈለግ ብቻ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እየተጠመቁ በአፍኣዊ መልኩ ክርስቲያን ሆኑ፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ በአሕዛብ ዓለም የሚከበሩ ታላላቅ በዓላት እንዳይማርኳቸውና ወደ ጣኦት አምልኮ እንዳይመልሷቸው በሚል ሰበብ የተለያዩ በዓላትን ማክበር ተጀመረ፤ ውጤቱ ግን የአሕዛቡ ዓለም አምልኮ ወደ ክርስትና እንዲገባ በማድረግ የተቀላቀለ አምልኮ እንዲፈጠር ማድረግ ሆነ፡፡ ለምሳሌ “የጌታ ልደት (Christmass) ተብሎ የሚከበረውን በዓል ብንመለከት በአሕዛቡ ዓለም በእንስት (ሴት) ጾታ የሚመለኩ አማልክት እንደወለዷቸው የሚነገርላቸው ልጆች ልደት በከፍተኛ ድምቀት በየአገሩ ይከበሩ ስለነበር በክርስትናም ከድንግል ማርያም የተወለደውን የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት በማክበር የዚያ ምትክ እንዲሆን ከተደረገ ሕዝቡ ወደነበረበት ጣኦት አምልኮ እንዳይመለስ ያደርጋል በሚል የተጀመረ እንደሆነ ታሪክ ያስረዳል፡፡ በተግባር የሆነው ግን ቀደም ሲል አሕዛብ የአማልክቶቻቸውን ልደት ሲያከብሩ ያደርጉ የነበሩትን የበዓል አከባበር ሥርዓቶች በጌታ ስም ቀይሮ ማድረግ በመሆኑ ጠላት ያቀደውን ክፉ ውጤት የሚያሳካ ሆኗል፡፡ እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ሁሉ የአሕዛብ ልማዶች ከመሪዎች ጀምሮ የክርስትናውን ዓለም አጥለቀለቁ፤ በክርስትና ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጣቸው ነገሮች ማለትም ከዓለም መለየት፣ የቅድስና ሕይወት፣ የአምልኮና የጸሎት ሕይወት፣ ስለእውነት መጋደል፣ … ወዘተ በተፈጠረው ዓለማዊነት የተነሣ ወደ ጎን ተተዉ፡፡ በተቃራኒው ግን እውነተኛ የሆኑ አንዳንድ አማኞች እንደ አንቲጳስ እንዲገደሉ ተላልፈው ይሰጡ ነበር፡፡ ቤተክርስቲያን ለዚህ ዓለም መንግሥት ራሷን አሳልፋ በመስጠት ለታጨችለት ለአንድ ሙሽራዋ የነበራትን ታማኝነት በይፋ ማጉደል ከጀመረች ወዲህ የበለዓምን ትምህርት የሚጠብቁ ሰዎች አመራርና አሠራር የሚገኝባት መሆንዋ ጌታን የሚያሳዝነውና የሚያስቆጣው ጉዳይ ነው፡፡ በጴርጋሞን በነበረች ቤተክርስቲያን ውስጥ የነበረው ይህ ገጽታ እስከ ዛሬም ድረስ በብዙ ክርስቲያኖች ዘንድ የሚታይ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ራስን ለጠላት አሠራር አሳልፎ እየሰጡ የጌታ ነን ማለት በበለዓም ትምህርት ከመበከል የሚመጣ ውድቀት ነው፤ ጌታ ደግሞ ይህንን ቸልታ አያልፈውም፡፡ ራሱ የወሰነውን ፍርድ ይሰጥበታል፡፡ ይህ ከመሆኑ በፊት ግን እንደተለመደው በፍቅር የንስሐ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
«እንግዲህ ንስሐ ግባ አለዚያ ፈጥኜ እመጣብሃለሁ» (ራእ2፡16)
ጌታችን በጴርጋሞን ቤተክርስቲያን ውስጥ እየወቀሰው ያለውና የንስሐ ጥሪን ያስተላለፈለት ሰው የበለዓምን ትምህርትና የኒቆላውያንን ትምህርት የሚጠብቁትን ሰዎች ቸል ያለውን አማኝ ነው፡፡ ጌታ የሚጠላውን ክፋት ቸል ማለት ንስሐ ሊገባበት የሚያስፈልግ ጥፋት መሆኑን በዚህ እንገነዘባለን፤ ብዙዎች ስለንስሐ ሲያስቡ ራሳቸው በፈጸሙት ኃጢአት ላይ መፍረድንና ያንን መናዘዝ ብቻ አድርገው ይረዳሉ፤ ሆኖም አብረውን ያሉ ክፉ ሰዎችን ቸል ማለትና አብረውን እንዲቀጥሉ መፍቀድም ከዓመፃቸው ተባባሪ የሚያደርግ ከመሆኑ የተነሳ ንስሐ ሊገባበት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ጌታ «ፈጥኜ እመጣብሃለሁ» በማለት የእርሱ የሆነውን፣ ነገር ግን ክፉዎችን ቸል ያለውን አማኝ በፍርድ ቃል ይናገረዋል፡፡ «ፈጥኜ እመጣብሃለሁ» የሚለው ቃል አመጣጡ በፍርድ መሆኑንና ለሚመጣበት ለዚያ አማኝም አስፈሪ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡ በሌላ በኩል ግን የበለዓምን ትምህርትና የኒቆላውያንን ትምህርት የሚጠብቁ ሰዎችን በተመለከተ የንስሐ ጥሪ ሲያስተላልፍላቸው አናይም፡፡ ይልቁኑ «በአፌ ሰይፍ እዋጋቸዋለሁ» ይላቸዋል፡፡ ስለዚህ እነርሱ ከእርሱ ጋር ኅብረት ሊያደርጉ በማይችሉበት የክፋት ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎች መሆናቸውን እንገነዘባለን፤ ጌታ እነዚህን ሰዎች «እዋጋቸዋለሁ» በማለት በጠላት ክልል ውስጥ እንዳሉ ኃይሎች ከመቁጠር በቀር ሌላ ምንም አላለም፡፡ ስለዚህ ጌታ እየተዋጋቸው ያሉ የበለዓም ትምህርት አራማጆችን ንስሐ እንዲገቡ መጠበቅ ስለ ሰዎቹ ከሚኖር ውሱን እውቀት አለዚያም ከቸልተኝነት የሚመጣ ስህተት ነው እንጂ ሰዎቹ ወደ ንስሐ እንዲመጡ ከሚኖር ፍላጎት የሚመጣ መልካምነት አይደለም፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህን ክፉ ሰዎች የሚዋጋበትን የዕቃ ጦር «የአፌ ሰይፍ» ተብሏል፡፡ በኤፌ6፡18 እና በዕብ4፡12 ላይ የምናነበው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍልም የእግዚአብሔር ቃል «ሰይፍ» ተብሎ እንደተጠራ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ የእርሱ በሆነች ጉባኤ ውስጥ ሾልከው የሚገቡና ክፉ ትምህርቶችን የሚጠብቁ ሰዎችን የሚዋጋው በቃሉ አማካኝነት ነው፡፡ በምድር ላይ በአማኞች ውስጥ በሚኖረው በመንፈስ ቅዱስ በኩል ከቃሉ የሚገኙ እውነቶች እየተጠቀሱ በክፉ ትምህርታቸው የሚገለጠውና በእግዚአብሔር እውቀት ላይ የሚነሳው ከፍ ያለው ነገራቸው ሁሉ ይፈርሳል (2ቆሮ10፡5)፡፡ የእግዚአብሔር ቃል በአግባቡ ካልተጠና ግን ሥጋዊነት ጎልቶ ስለሚወጣ የበለዓም ትምህርት አመቺ ሁኔታን ያገኝና ብዙዎችን ይቆጣጠራል፡፡ ይህም ሥጋዊነት እንደ አንቲጳስ ያሉ ቅዱሳን በእግዚአብሔር ቃል የሚያደርጉትን የእምነት ገድል ሊቋቋመው ስለማይችል በእጁ ያለውን ሥጋዊውን ሰይፍ በመጠቀም እየገደላቸው የእውነትን ምስክርነት ሊያጠፋ ይሞክራል፡፡ ይሁንና ጌታ በቃሉ ሰይፍነት በሚያደርገው ውጊያ ምን ጊዜም አሸናፊ ስለሚሆን እውነትን ማዳፈንም ሆነ ማጥፋት አልተቻለም፤ አይቻልምም፡፡
«መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ» (ቁ.)
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጴርጋሞን ላለች ቤተክርስቲያን ያስተላለፈው መልእክት እንደ ሌሎቹ መልእክታት ሁሉ “መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን” የያዘ መልእክት ነው፡፡ ይህም በጴርጋሞን ውስጥ የተመሰገነው ነገር ማለትም «የጌታን ስም መጠበቅ፣ የኢየሱስን እምነት አለመካድ» በሌሎቹ አብያተ ክርስቲያናትም ሊገኝ የሚገባው መሆኑን ያሳየናል፤ እንዲሁም በጴርጋሞን ቤተክርስቲያን የተነቀፈውን የበለዓምን ትምህርት እና የኒቆላውያንን ትምህርት የሚጠብቁ ሰዎች የጌታ ከሆኑት ጋር አብረው የመገኘታቸው ነገር በሁሉም አብያተክርስቲያናት ዘንድ መኖር እንደሌለበት የሚያሳይ ነው፡፡ ለአንዲቷ አጥቢያ ቤተክርስቲያን የተላለፈው መልእክት ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለሌሎቹም በመሆኑ ሁሉም አብያተክርስቲያናት ለጴርጋሞን ቤተክርስቲያን የተላከውን መልእክትም ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡ የተመሰገኑትን መልካም ነገሮች ማለትም በጌታ ስም መጸለይን፣ በጌታ ስም መሰብሰብን፣ እንዲሁም የጌታ በሆነ እምነት መጽናትን፣ አጥብቀው እንዲይዙና በውጭ ያለውን የአሕዛብ ልማድና ዓለማዊነትን እንዲሁም ጌታ የሚጠላውን ማናቸውንም ሥጋዊ ነገር የሚያስተምሩና የሚከተሉ ሰዎችን ቸል እንዳይሏቸው መንፈስ ለጴርጋሞን ቤተክርስቲያን ባስተላለፈው መልእክት በኩል ያሳስባቸዋል፡፡ የልብ ጆሮ ያላቸውና ጌታን ከልብ እያዳመጡ የሚመላለሱ ሁሉ ይህን በተግባር ያውሉታል፡፡
“ድል ለነሣው ከተሰወረ መና እሰጠዋለሁ፥ ነጭ ድንጋይንም እሰጠዋለሁ፥ በድንጋዩም ላይ ከተቀበለው በቀር አንድ ስንኳ የሚያውቀው የሌለ አዲስ ስም ተጽፎአል።” (ራእ.2፡17)
በዚህ ቃል ውስጥ ጌታችን ክርስቶስ በጴርጋሞን ቤተክርስቲያን ላለው ድል ነሺ የተሰጠውን ተስፋ እንመለከታለን፡፡ በተስፋው ቃል ውስጥ ድል ለነሳው ከጌታ የሚሰጡ ሁለት ነገሮች ናቸው፤ እነርሱም “የተሰወረ መና” እና “ነጭ ድንጋይ” ናቸው፤ እነዚህ ሁለት ነገሮች የሚያመለክቱትን መንፈሳዊ ሐሳብ መመልከቱ ጠቃሚ ነው፤ «የተሰወረውን መና» የሚለው ቃል በብሉይ ኪዳን በመገናኛው ድንኳን ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ በሚቀመጠው በታቦቱ ውስጥ በወርቅ መሶብ ተደርጎ ይቀመጥ የነበረውን መና ያስታውሰናል (ዕብ9፡4)፤ ይህም መና በምድረ በዳ ይጓዙ ለነበሩት እስራኤላውያን ከሰማይ ከወረደው መና ውስጥ ተወስዶ በቅድስተ ቅዱሳን እንዲቀመጥ የተደረገ መሆኑን ከዘጸ.16፡31-34 እንገነዘባለን፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በምድር ላይ ሳለ «እኔ ከሰማይ የወረደ የሕይወት እንጀራ ነኝ» ብሎ ባስተማረበት ትምህርት ራሱን በዚህ መና ምሳሌነት ገልጿል (ዮሐ.6፡31-58)፡፡ ባሁኑ ጊዜ ደግሞ እርሱ ወደ ቅድስት ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ የገባና በዚያ ተሰውሮ የተቀመጠ መና ነው፡፡ ወደፊትም ከዚያ ከተሰወረበት ቅድስተ ቅዱሳን በክብር ይገለጣል፤ በመሆኑም ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉ የሚያስተምረውን የለዓምን ትምህርት ባለመቀበል፣ ለጣዖት የተሠዋውን ያልበሉት ከዚያ የራቁ የጴርጋሞን ድል ነሺዎች ይህ የከበረው የተሰወረ መና እንደሚሰጣቸው ተስፋ ተገብቶላቸዋል፡፡ ስለሆነም ጌታችን «ድል ለነሳው ከተሰወረው መና እሰጠዋለሁ» ሲል እርሱ በክብር ዐርጎ አሁን በሚገኝበት በእግዚአብሔር ቀኝ የሚኖርበትን ክብር እና በዚያም ያለውን የእርሱን ማንነት በመረዳትና በማሰላሰል እንዲደሰትበት እሰጠዋለሁ ማለት መሆኑን እንረዳለን፡፡ በመቀጠልም «ነጭ ድንጋይ» እንደሚሰጠው ይናገራል፡፡ በዚያ ነጭ ድንጋይ ላይ «ከተቀበለው በቀር አንድ ስንኳ የሚያውቀው የሌለ አዲስ ስም» እንደተጻፈበት ተገልጿል፡፡ ነጩን ድንጋይ ለየት የሚያደርገው የተጻፈበት አዲስ ስም ነው፤ በማናቸውም ውድድር ወይም ትግል ድል ያደረገ ሰው አንዳች የማዕረግ ስም የተጻፈበት ነጭ ድንጋይ ከታላላቆች ዘንድ በሽልማት መልክ ቢቀበል ለእርሱ ታላቅ ክብርና ማዕረግን ያስገኝለታል፤ ጌታ ግን በጴርጋሞን ቤተክርስቲያን ድል ለነሳው አማኝ እሰጠዋለሁ ያለው ነጭ ድንጋይ በላዩ ላይ የተጻፈውን አዲስ ስም ተቀባዩ ብቻ በግል እንዲያውቀው አድርጎ የጻፈበት ድንጋይ ነው፡፡ ይህም ምሳሌያዊ አገላለጽ ድል ነሺ አማኞች ጌታ በየግላቸው የሚገባቸውን አዲስ ክብር እንደሚያጎናጽፋቸው በእርሱና በእያንዳንዱ አማኝ ዘንድ ብቻ ሊታወቅ የሚችል ልዩ ጣዕም ወዳለው ኅብረት እንደሚያስገባቸው የሚያመለክት ነው፡፡ ስለሆነም አማኞች በጴርጋሞን ቤተክርስቲያን ለነበሩት ድል ነሺዎች የተሰጣቸውን እነዚህን ተስፋዎች ለማግኘት ከክርስትና ጋር እየተደባለቀ ያለውን ዓለማዊነት ድል ሊነሱ ይገባቸዋል፡፡
ክፍል አራት>>>>