በዚህ ቊጥር ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ለኤፌሶን ቤተክርስቲያን ያቀረበባቸው ሁለት አገላለጾች እናገኛለን፡፡ እነርሱም «በቀኝ እጁ ሰባቱን ከዋክብት የያዘው» የሚለውና «በሰባቱም የወርቅ መቅረዞች መካከል የሚሄደው» የሚሉት ናቸው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ለዮሐንስ በራእይ በታየ ጊዜ በዚህ መልክ መታየቱን በምዕ.1 ቊ.12 እና 16 ላይ እናነባለን፡፡ የሰባቱ የወርቅ መቅረዞችና የሰባቱ ከዋክብት ምስጢርም በራሱ በጌታ የተነገረ ሲሆን ይኸውም በምዕ.1 ቊ. 20 ላይ «በቀኝ እጄ ያየሃቸው የሰባቱ ከዋክብትና የሰባቱ የወርቅ መቅረዞች ምስጢር ይህ ነው፤ ሰባቱ ከዋክብት የሰባቱ አብያተክርስቲያናት መላእክት ናቸው፤ ሰባቱም መቅረዞች ሰባቱ አብያተክርስቲያናት ናቸው» ተብሎ ተጽፎልናል፡፡
በሰባቱ ከዋክብት የተመሰሉት የሰባቱ አብያተክርስቲያናት መላእክት እነማን ናቸው? የሚለውን በጥንቃቄ መረዳት ተገቢ ነው፡፡ እዚህ ላይ «መላእክት» ሲል «የሚያገለግሉ መናፍስት» የሆኑትን የሰማይ መላእክትን የሚያመለክት አይደለም፤ ምክንያቱም «በኤፌሶን ወዳለው ቤተክርስቲያን መልአክ»፣ «በሰምርኔስ ወዳለው ቤተክርስቲያን መልአክ»፣ ... ወዘተ እየተባለ የተጻፉትን መልእክታት ይዘት ስንመለከት በየቤተክርስቲያኑ የሚገኙ አማኞችን የሚመለከቱ ናቸው እንጂ የሰማይ መላእክትን የሚመለከቱ አይደለም፡፡ ስለዚህ እነዚህ የአብያተክርስቲያናት መላእክት በሰባቱም አብያተክርስቲያናት የሚገኙና የሚያገለግሉ የክርስቶስ መልእክተኞች ናቸው፡፡ መላእክት ማለት መልእክተኞች ማለት ስለሆነ እነዚህ በሰባቱ አብያተክርስቲያናት የሚገኙ የክርስቶስ መልእክተኞች በመላእክት ሊመሰሉ እንደቻሉ መገንዘብ እንችላለን፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ «በኤፈሶን ወዳለው ቤተክርስቲያን መልአክ» ሲል አንድን ግለሰብ የሚያሳይም አይደለም፡፡ በአንድ ስፍራ ባለች ቤተክርስቲያን /ጉባኤ/ አንድ ግለሰብ ብቻ መሪ /ገዢ/ የሚሆንበት አሠራር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የለም፡፡ በዚህ ክፍል የተጠቀሰው መልአክ የሚወክለው በኤፌሶን ጉባኤ ውስጥ ያሉትን መሪ ወንድሞች ማለትም በሽማግሌነት በአስተማሪነት በእረኝነትና በወንጌላዊነት የሚያገለግሉ የክርስቶስ መልእክተኞችን የሚያሳይ ሲሆን እነርሱም በጉባኤው የትምህርትም ሆነ የሥነምግባር ሁኔታን የሚመለከት አደራና ኃላፊነት ያለባቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ ጌታ ለጉባኤው የሚሆነውን መልእክት ለእነርሱ ሊያስተላልፍ ችሏል፡፡ ዛሬም ቢሆን በየስፍራው ባሉ ጉባኤዎቹ ጌታ ያስነሣቸውና ጉባኤውን በጌታ የሚገዙ እንዲሁም በጸጋቸው የሚያገለግሉ መሪ ወንድሞች የክርስቶስ መልእክተኞች እንደመሆናቸው ጌታ ለጉባኤው በቃል የላከውን የማበረታቻም ሆነ የእርማት መልእክት የማስተላለፍና በሥራ ላይ እንዲውል የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ እነዚህ ሰባቱ ከዋክብት በጌታ በቀኝ እጁ ተይዘው ታይተዋል፤ ይህም የሚያመለክተው በየጉባኤው /በአብያተ ክርስቲያናት/ ያሉት የክርስቶስ መልእክተኞች በጌታ ሥልጣንና ኃይል ሥር እንደሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን የሚጠብቁትም ሆነ የሚያገለግሉት ከእርሱ ዘንድ በወጣ በቃሉና በመንፈሱ መመሪያ መሠረት ነው፤ ከዚህ ውጪ ሲሆኑ ለመገሠጽም ሆነ ለመፍረድ፣ እንደፈቃዱ ሲሆኑ ደግሞ ለማመስገንና ለማበረታታት ሙሉ ሥልጣን የእርሱ ነው፡፡ ይህ ሥልጣኑ ተገቢ ስፍራ ባልተሰጠባቸው የዘመናችን ጉባኤዎች ዘንድ ይህ በፍርሃት ሊስተዋል ይገባዋል፡፡
በሰባቱ የወርቅ መቅረዞች የተመሰሉት ደግሞ ሰባቱ አብያተክርስቲያናት መሆናቸው ተገልጧል፡፡ የወርቅ መቅረዝ በብሉይ ኪዳን በመገናኛው ድንኳን ሁለተኛ ክፍል ማለትም በቅድስት ውስጥ ከሚቀመጡ ሦስት የመቅደስ ዕቃዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ አገልግሎቱም ከማታ እስከ ማለዳ ድረስ መብራት ለማብራት እንዲቻል መብራቱን የሚሸከም ዕቃ ነው፡፡ ቤተክርስቲያንም እውነተኛው የዓለም ብርሃን የሆነውን ክርስቶስን የምታበራ የእግዚአብሔር መቅረዝ ናት፡፡ በፊልጵ.2፡15 ላይ «በእነርሱም መካከል የሕይወትን ቃል እያቀረባችሁ በዓለም እንደብርሃን ትታያላችሁ» ተብሎ እንደተጻፈው ጨለማ በሆነው በዚህ ዓለም የክርስቶስ ብርሃን በአብያተክርስቲያናት መቅረዝነት ያበራል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ክፍል በሰባቱ የወርቅ መቅረዞች መካከል የሚሄደው» ተብሎ ተገልጧል፡፡ የእርሱ ስፍራ ሁልጊዜም የእርሱ በሆኑት መካከል ነው፤ በስሙ በተሰበሰበች በአንዲት ጉባኤ መካከል የሚገኝ መሆኑ በማቴ.18፡20 ላይ ተገልጧል፡፡ ይሁንና እርሱ የሚገኘው በአንዲት አጥቢያ ቤተክርስቲያን በሚሰባሰቡት መካከል ብቻ ሳይሆን በአብያተክርስቲያናት መካከልም እንደሆነና በዚያም ሆኖ ሁሉን እንደሚቆጣጠር በመቅረዞቹ መካከል በመታየቱ እንረዳለን፡፡ ጌታ ኢየሱስ በመቅረዞቹ መካከል የሚቆም ሳይሆን የሚሄድ ሆኖ መገለጡ ደግሞ በእያንዳንዱ አጥቢያ ቤተክርስቲያን እየተሠራ ያለውን መልካምም ይሁን ክፉ ሥራ በሥልጣን እየተዘዋወረ የሚመለከት የአብያተከርስቲያናት ባለቤት መሆኑን ያሳያል፡፡ እያንዳንዷ አጥቢያ ቤተክርስቲያን መቅረዝ እንደመሆኗ የእርሱን ብርሃን ተሸክማለችና በመካከሏ በጨለማ ተሰውሮ ሊቀር የሚችል ክፋት አይኖርም፤ እርሱ ሁሉን ይመለከታል፤ ሁሉንም ይቆጣጠራል፡፡ እንደዚሁም የዚህ ዓለም ጨለማ ውጦ ሊያስቀረው የሚችል መልካም ሥራ ሊኖር አይችልም፤ እርሱ ሁሉንም በጊዜው ይገልጠዋል፡፡
ቊ.2-3 «ሥራህንና ድካምህን ትዕግሥትህንም አውቃለሁ፤ ክፉዎችንም ልትታገሥ እንዳትችል እንዲሁም ሳይሆኑ ሐዋርያት ነን የሚሉቱን መርምረህ ሐሰተኞች ሆነው እንዳገኘሃቸው አውቃለሁ፤ ታግሠህማል፤ ስለ ስሜም ብለህ ጸንተህ አልደከምህም፡፡»
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእርሱ በሆኑት መካከል ምንም እንኳ የሚነቅፈው ነገር ቢኖርም መልእክቱን የሚጀምረው ከሚያመሰግነው መልካም ነገር ነው፡፡ እርሱ አስቀድሞ ማየት የሚፈልገው በመካከላችን ምን መልካም ነገር እንዳለ ነው፡፡ እርሱ በመካከላችን የሚከናወኑትን ሁሉንም ሥራዎች ያውቃል፤ ከእርሱ ሊሰወር የሚችል ወይም እርሱ የማያውቀው መልካምም ሆነ ክፉ ነገር በመካከላችን ሊኖር አይችልም፤ ስለዚህም ለሰባቱም አብያተ ክርስቲያናት መልእክቱን ሲያስተላልፍ «አውቃለሁ» የሚለውን ቃል ይጠቀማል፡፡ ጌታ በኤፌሶን ያለውን አማኝ «ሥራህንና ድካምህን ትዕግሥትህንም አውቃለሁ» ብሎታል፡፡ እነዚህ ሦስት ነገሮች በአጥቢያ ቤተክርስቲያን ዘንድ ሊታዩ የሚገባቸው መልካም ነገሮች ናቸው፤ ሥራን በተመለከተ ሐዋርያው ጳውሎስ ለእነዚሁ ለኤፌሶን ሰዎች ሲጽፍ «እኛ ፍጥረቱ ነንና እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን፡፡» ብሏል /ኤፌ.2፡10/፡፡ ስለሆነም በጌታ በኢየሱስ አምነው የዳኑና በቤተክርስቲያን ውስጥ የክርስቶስ የአካሉ ብልቶች የሆኑ ሁሉ በመልካም ሥራ ሊመላለሱ ይገባል፡፡ «ድካምህን» ሲል ደግሞ የጌታን ሥራ በመሥራት በአገልግሎት መድከምን የሚያሳይ ነው፤ ለምሳሌ በሮሜ.16፡6 ላይ «ስለ እናንተ ብዙ ለደከመች ለማርያ...» ሲል፣ እንዲሁም በ1ቆሮ.15፡58 ላይ «ድካማችሁ በጌታ ከንቱ እንዳይሆን አውቃችኋልና የምትደላደሉ የማትነቃነቁም የጌታም ሥራ ሁል ጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ» ሲል በአገልግሎት መድከምን የሚያሳይ ነው፤ የኤፌሶን አማኞች በዚህ በኩል ያሳዩትን ድካም ጌታ ተመልክቷል፡፡ እንደዚሁም «ትዕግሥት» ነበራቸው፤ ይህም መከራ ወይም የተለያዩ ፈተናዎች ሲኖሩ እነዚያን ሁሉ ተቋቁሞ መጽናትን የሚያሳይ ነው፡፡ በሮሜ.12፡12 ላይ «በመከራ ታገሡ» የሚል ቃል እናነባለን፡፡ በዕብ.12፡1-2 ላይ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በፊቱ ስላለው ደስታ በመስቀል መታገሡ እንደ አብነት ተጠቅሶ ‹በፊታችን ያለውን ሩጫ› በትዕግሥት እንድንሮጥ ተጽፎልናል፡፡
ጌታ በኤፌሶን ባለች ቤተክርስቲያን ያያቸውን እነዚህን ሦስት መልካም ነገሮች በእኛም ማየት ይፈልጋል፡፡ ሆኖም እርሱ ውስጥን ሁሉ የሚያውቅ ስለሆነ እንደተሰሎንቄ ሰዎች ሥራችን የእምነት ሥራ፣ ድካማችን የእምነት ድካም፣ በትዕግሥት መጽናታችንም የተስፋ መጽናት ሊሆኑ ይገባቸዋል እንጂ በውጫዊ መንገድ የተያዙ መሆን የለባቸውም /1ተሰ.1፡3/፡፡ በኤፌሶን ያለው አማኝ የሚታገሠውንና የማይታገሠውን ለይቶ የሚያውቅ ነው፤ ተገቢ የሆነውን ትዕግሥት ይዞ የተገኘውን ያህል ክፉዎችን ሊታገሥ አይችልም ነበር፤ ሐዋርያት ሳይሆኑ ሐዋርያት ነን ብለው የሚመጡትን መርምሮ ሐሰተኞች ሆነው አግኝቶአቸው ነበር፤ እንዲህ ያሉትን በትዕግሥት መሸከም አግባብ አይደለም፤ ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን የነበረውን አገልግሎት አጠናቅቆ ሲለያቸው ለቤተክርስቲያኒቱ ሽማግሌዎች ከነገራቸው ነገሮች አንዱ «በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኲላዎች እንዲገቡባችሁ ደቀመዛሙርትንም ወደኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ» የሚል ነበር /ሐ.ሥ.20፡28-30/፡፡ ጳውሎስ ከተናገረው ከዚህ ቃልም ቤተክርስቲያን ከሁለት ዓይነት ክፉ ሰዎች ልትጠነቀቅ እንደሚገባ እንረዳለን፤ እነርሱም፡
1. ከውጪ የሚገቡ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኲላዎች፣
2. ከውስጥ ከመካከል የሚነሡ ደቀመዛሙርትንም ወደ ኋላ ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች ናቸው፡፡
በኤፌሶን ቤተክርስቲያን ያሉ አማኞች ሐዋርያት ሳይሆኑ ሐዋርያት ነን ብለው በተኲላ ጠባይ የሐዋርያትን ስም ተላብሰው ከውጭ ወደ ውስጥ ሊገቡ የሞከሩትን መርምረው ሐሰተኞች ሆነው እንዳገኙአቸው ልንገነዘብ እንችላለን፡፡ በ2ቆሮ.11፡13 ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ውሸተኞች ሐዋርያትን በተመለከተ ሲጽፍ «እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኰለኞች ሠራተኞች ናቸውና» ብሏል፡፡ ባሕርያቸውንም ከሰይጣን ባሕርይ ጋር አመሳስሎታል፡፡ እንደ እነዚህ ዓይነት ሰዎችን መታገሥ መንጋውን ለጨካኞች ተኲላ አሳልፎ መስጠት ስለሆነ በጌታ የሚገዙ ወንድሞች አብዝተው ሊጠነቀቁ ያስፈልጋል፤ በዚያን ጊዜ የክርስቶስ ሐዋርያት በሕይወት ስለነበሩ ሐዋርያት ነን ብለው የሚመጡ ሰዎችን ሐሰተኛ መሆናቸውን ለማወቅ የኤፌሶን አማኞች መመርመር አስፈልጓቸው ነበር፡፡ የሐዋርያት ዘመን ካበቃ በኋላ ግን ጌታ ከጳውሎስ ቀጥሎ ሌላ ሐዋርያ ያልላከ በመሆኑ ሐዋርያት ነን ብለው የሚመጡትን ምንም ምርመራ ሳያስፈልግ ሐዋርያ አለመሆናቸውን ማወቅ ይቻላል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች እንደ 12ቱ ሐዋርያትና እንደ ጳውሎስ ጌታን እንዳላዩ የትንሣኤውም ምስክር እንዳልሆኑ ወዲያው ማወቅ የሚቻል በመሆኑ ሐዋርያ አለመሆናቸው ስለሚረጋገጥ ነው፡፡ ይሁንና በዘመናችን ባለው የክርስትናው ዓለም ውስጥ ሐዋርያት ሳይሆኑ ሐዋርያት ነን ማለት፣ «ሐዋርያዊ ሥልጣን ሲወርድ ሲዋረድ ወደ ዘመናችን ደርሷል» ከሚለው አስተሳሰብ ጀምሮ «እኔ ሐዋርያ ነኝ» እስከሚለው የድፍረት ቃል ድረስ በተለያየ ገጽታው ይገኛል፤ እነዚህ ተንኰለኞች ሠራተኞችና ውሸተኞች ሐዋርያት መድረኮችን ይዘው የግል ጥቅምንና ክብርን በግልጽ እየሰበሰቡ ሕዝብን ሲያስቱ እየታወቀ በቸልታ የሚታለፉበት ሁኔታ በስፋት ይታያል፡፡ ይህን መታገሥ ክፉዎችን መታገሥ ነው፡፡ በአፌሶን ቤተክርስቲያን ግን ለእንዲህ ያሉ ሰዎች ምንም ስፍራ አልነበረም፡፡ በዚህ ዘመንም በየስፍራው በጌታ በኢየሱስ ስም የተሰበሰቡ ጉባኤዎች ክፉዎችን እንዳይታገሡ የጌታ ፍላጐት ነው፡፡
በእርግጥ ሐሰተኞችን ለይቶ ማወቅም ሆነ እነርሱን አለመታገሥ ወይም አለመሸከም አድካሚ ሥራ ስለሆነ በራሱ ትዕግሥትን የሚጠይቅ ነው፡፡ የኤፌሶን አማኞች ግን ለዚህም የሚሆን ትዕግሥት ነበራቸው፤ «ታግሠህማል፤ ስለስሜም ብለህ ጸንተህ አልደከምህም» የተባሉትም ለዚህ ነው፡፡ በነገር ሁሉ የጸኑት በሌላ በምንም ምክንያት ሳይሆን ስለስሙ ብለው እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ከራሳቸው ስምና ክብር ወይም ከሌላ የግል ጉዳይ ይልቅ ስለክርስቶስ ስም ይቈረቈሩ ነበር፤ «ጸንተህ አልደከምህም» ተብሎ እንደተመሰከረላቸውም ስለጌታ ስም ብለው ከሐሰተኞች ጋር ተጋፍጠው እነርሱን ላለመሸከም ባደረጉት አድካሚ ጥረት አልደከሙም ወይም አልተሰላቹም፡፡ ስለሆነም ጌታ በዚህ ነገር ደስ ብሎት ያመሰግናቸዋል፡፡
ቊ.4-5 «ዳሩ ግን የምነቅፍብህ ነገር አለኝ የቀደመውን ፍቅርህን ትተሃልና፡፡ እንግዲህ ከወዴት እንደወደቅህ አስብ፤ ንስሐም ግባ የቀደመውንም ሥራህን አድርግ፤ አለዚያ እመጣብሃለሁ ንስሐም ባትገባ መቅረዝህን ከስፍራው እወስዳለሁ»
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በውጪ የሚታየውን መልካም ሥራ በማየት ብቻ ምስጋናና ማበረታቻን ሰጥቶአቸው አላበቃም፡፡ ነገር ግን እርሱ የሁሉን ልብ የሚያውቅ /ሐ.ሥ.1፡25/፣ ኲላሊትንና ልብን የሚመረምር /ራእ.2፡23/ በመሆኑ የውስጥን ሁኔታ ያውቃል፡፡ በኤፌሶን ቤተክርስቲያን በውጪ የሚታየው ነገር መልካም ሆኖ ቢያገኘውም ወደ ውስጥ ሲመለከት ግን የሚነቅፍባቸው ነገር አገኘ፤ የቀደመውን ፍቅራቸውን ትተዋል፡፡ በእርግጥ ምንም ፍቅር የላቸውም አልተባለም፤ ሆኖም የቀደመው ትኲስ ፍቅር አሁን እየቀዘቀዘ ሄዷል፤ ሥራቸውን ድካማቸውንና ትዕግሥታቸውን ለተመለከተ ሁሉ ይህ ላይታየው ይችላል፤ ሆኖም ከሰው እይታ ቢሰወርም ከጌታ ከኢየሱስ እይታ ሊሰወር አልቻለም፡፡ በዘመናችንም በጌታ በኢየሱስ ስም በተሰበሰቡ አጥቢያ ጉባኤዎች ይህ ችግር ይታያል፤ ብዙዎቻችን የእውነት ብርሃን እንደበራልን ወዲያውኑ የምናሳየው መታዘዝ ለጌታ ያለንን ትኲስ ፍቅር የሚገልጥ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ከቆይታ በኋላ በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ ማለፍ ሲመጣ፣ እንዲሁም በዚህች ዓለም በሥጋ ያለን ፍላጐት በእኛና በጌታ መካከል ጣልቃ ሲገባ ያ ለጌታ የነበረን ትኲስ ፍቅር እየቀዘቀዘ ይሄዳል፡፡ በዚህ ቀዝቃዛ ፍቅር ሆነን ብዙ የሚመሰገንና የሚደነቅ መልካም ሥራ ልንሠራ እንችላለን፡፡ ሆኖም ይህ በእውነት የሚወደንን እና ውስጣችንን አጥርቶ የሚያየውን ጌታ ሊያስደስተው አይችልም፤ ትኲስ ፍቅራችንን ሁልጊዜም ለሚፈልገው ጌታ በቀዝቃዛ ፍቅር የምንሠራለት ሥራ፣ የምንደክምለት ድካም የሚኖረንም ትዕግሥት እርሱን አያረካውም፡፡
ብዙ መልካም ነገሮች በተገኙባት በኤፌሶን ቤተክርስቲያን የቀደመ ፍቅር አለመኖሩ ንስሐ ሊገባበት የሚያስፈልገው ውድቀት ነበረ፡፡ ስለዚህም ጌታ የንስሐ ጥሪን ለኤፌሶን አማኞች አስተላልፏል፡፡ «ንስሐ» የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የማያምኑ ሰዎች ወንጌል ተሰብኮላቸው ወደ ጌታ ዘወር ሲሉ ያለእርሱ በኖሩበት ባለፈው ዘመን ተጸጽተውና ኃጢአተኛ መሆናቸውን ተናዝዘው መመለሳቸውን የሚያመለክትባቸው በርካታ ክፍሎች ቢኖሩም በዚህ በምናጠናው ክፍል በቊ.5 ላይ የተጠቀሰው ግን አማኞች በአንዳች ጥፋት ሲወድቁ ከውድቀታቸው የሚነሡበት መንገድ ሆኖ ነው፡፡ የቀደመ ፍቅሩን የተወው የኤፌሶን አማኝ ከውድቀቱ ለመነሣት ሦስት እርምጃዎችን በየደረጃው እንዲወስድ ተነግሮታል፡፡
1. ከወዴት እንደወደቅህ አስብ፡-
«የቀደመ ፍቅር ማጣት» «ውድቀት» መሆኑን የኤፌሶን አማኝ እንዲያስተውለው ይህ ቃል ያሳስባል፡፡ ብዙ ሰዎች አማኝ ለሌላ ሰው ሊሰማና ሊታይ በሚችል ክፉ ተግባር ተገልጦ ካልታየ በቀር ይህ ውድቀት መሆኑን ላይረዱ ይችላሉ፤ ጌታ ግን በልባችን የወደቅንበትን ስፍራ ስለሚያይ «ከወዴት እንደወደቅህ አስብ» ይላል፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን ችግሩን ማግኘት የመፍትሔው የመጀመሪያ ደረጃ ነው ማለት ይቻላል፤ ስለዚህ በመንፈስ ጠንክሮ በጽናት ለመቆም ከወዴት እንደወደቁ ማሰብ በመጀመሪያ ሊወሰድ የሚገባው እርምጃ ነው፡፡
2. ንስሐም ግባ፡-
ይህ ደግሞ ከወዴት እንደወደቅን ለይተን ካወቅን በኋላ በዚያ ውድቀት ላይ የማያወላውል ግልጽ ፍርድን ልንፈርድበት እንደሚገባ የሚያመለክት ቃል ነው፡፡ «ንስሐ» መጸጸትንና መናዘዝን ጨምሮ ከመጥፎ ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ መለየትን የሚያጠቃልል እርምጃ ነው፤ እንዲሁም ወደ ጌታ ሐሳብና ፈቃድ ሙሉ ለሙሉ መመለስ ነው፡፡ የኤፌሶን አማኞች የቀደመ ፍቅራቸውን መተዋቸው የወደቁበት ስፍራ መሆኑን ከተረዱ በኋላ በዚህ ነገር ላይ ፈርደው ወደቀደመው ፍቅር ለመመለስ ቢወስኑ «ንስሐ ገቡ» ይባላል፡፡ የቀደመ ፍቅርን ማጣት ውድቀት መሆኑና ንስሐ ሊገባበት /ሊፈረድበት/ የሚገባ ጌታን ያሳዘነ ውስጣዊ ነውር እንደሆነ በብዙዎቻችን ዘንድ የማይስተዋል በመሆኑ በዚህ ነገር ንስሐ ሲገባበት ይታይም፤ ይሁንና በውስጣችን ያለው የቀዘቀዘ ፍቅር ልቡን የሚያቈስለው ጌታ ኢየሱስ ግን በዚህ ነገር ላይ «ንስሐ ግባ» የሚል መልእክት ያስተላልፋል፡፡
3. የቀደመውን ሥራህን አድርግ፡-
ይህ መልእክት ንስሐው እውነተኛ ንስሐ መሆኑ በተግባር የሚረጋገጥበትን መንገድ የሚያመለክት ነው፡፡ እዚህ ላይ የቀደመ ሥራ የተባለው አማኞች በቀደመው ፍቅር ሳሉ በዚያ ፍቅር አነሳሽነት ይሠሩት የነበረውን ሥራ የሚያመለክት ነው፤ የቀደመ ፍቅራቸውን በተዉበት ጊዜ የሚሠሩት ሥራ ምንም እንኳ መልካም እና ውጤታማ ቢሆንም የሚፈለገው ትኲስ ፍቅር በሌለበት የተሠራ በመሆኑ ጌታን የሚያረካና የሚያሳርፍ ሥራ ስላልሆነ «የቀደመውን ሥራህን አድርግ» የሚል መልእክት ለማስተላለፍ ተገብቶታል፡፡ በቀደመ ፍቅር የሚሠራው ሥራ በቀዘቀዘው ፍቅር ሆኖ ከሚሠራው ሥራ ምን ያህል ሊበልጥ እንደሚችል ለማንም ግልጽ ነው፡፡ የቀደመውን ፍቅር በመተዉ ምክንያት ጥፋተኝነት ተሰምቶት በመጸጸት ደረጃ ንስሐ የገባ ሰው ይህ ንስሐው በቀደመው ሥራ ተገልጦ እውነተኝነቱን ማረጋገጥ አለበት፡፡ ነገሮችን አለባብሶ ማለፍ በተለመደበት በዚህ ዘመን ይህ እውነት ሁላችንንም ምንኛ ይጋፈጠን ይሆን!
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በኤፌሶን ቤተክርስቲያን ውስጥ እየተሠራ ያለው መልካም ሥራና የሚታየው ምስክርነት የቀደመው ፍቅር በሌለበት እንዲቀጥል አልፈለገም፤ ስለዚህ ይህ ሁኔታ ንስሐ ካልተገባበትና ወደ ቀደመ
ፍቅር ካልተመለሱ ጌታ ኢየሱስ በቤተክርስቲያን ላይ ባለው ሥልጣን መሠረት የራሱን ፍርድ እንደሚፈርድ ይነግራቸዋል፡፡ «አለዚያ እመጣብሃለሁ ንስሐም ባትገባ መቅረዝህን ከስፍራው እወስዳለሁ» ይላቸዋል፡፡ ሰባቱ የወርቅ መቅረዞች ሰባቱ አብያተክርስቲያናትን የሚያመለክቱ መሆናቸውን አስቀድመን ተመልክተናል፡፡ ስለዚህ መቅረዝህን ከስፍራው እወስዳለሁ ሲል በኤፌሶን ከተማ እንደ አጥቢያ ቤተክርስቲያን መቀጠልህ ያቆማል ማለት ነው፡፡ መቅረዝ መብራትን የሚይዝ ዕቃ እንደሆነ ሁሉ አጥቢያ ቤተክርስቲያንም የክርስቶስን ብርሃን ይዛ የምታበራ ናት፤ ይሁንና የቀደመው ትኲስ ፍቅር በቀዘቀዘበት ሁኔታ በስሙ የሚጠራ ማናቸውም ምስክርነት እንዲቀጥል ጌታ አይፈልግም፡፡ ለኤፌሶን ቤተክርስቲያን ራሱን ሲገልጥ «በሰባቱ የወርቅ መቅረዞች መካከል የሚሄደው» ሆኖ መቅረቡ በመቅረዞቹ ህልውና ላይ መወሰን የሚቻለው መሆኑን የኤፌሶን አማኞች እንዲያስተውሉ ነው፤ በመቅረዞቹ መካከል የሚሄድ ሆኖ ራሱን ያቀረበላቸው ንስሐ ካልገቡ በኤፌሶን ያለው መቅረዝ /የጉባኤ ምሰክርነት/ እንደሚወሰድ ሊነግራቸው ስላሰበ ነበር፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚፈልገውን ትኲስ ፍቅር ሲያጣ የሚወስነው ውሳኔ እስከዚህ ድረስ እንደሆነ ማየት በስሙ ዙሪያ ተሰብስበው ሥራውን ለሚሠሩ፣ ለሚደክሙና በትዕግሥት ለሚጸኑት ሁሉ እንዴት አስፈሪ ነው! ስለሆነም ይህ ከወዴት እንደወደቁ ለማሰብ፣ ንስሐ ለመግባትና የቀደመውን ሥራ ለመሥራትም የሚያነቃቃቸውና የሚያበረታቸው ሊሆን ይገባል፡፡
ቊ.6፡- «ነገር ግን ይህ አለህ፤ እኔ ደግሞ የምጠላውን የኒቆላውያንን ሥራ ጠልተሃልና»
በኤፌሶን ያለች ቤተክርስቲያን ያለችበት ውድቀት አሳሳቢ ቢሆንም መልካም ነገሮችዋ ግን በጌታ ዘንድ ዋጋ የተሰጣቸው ነበሩ፡፡ ጌታ በዚህች ቤተክርስቲያን ያለውን አማኝ ውድቀቱን በግልጽ ከነገረው በኋላ «ነገር ግን ይህ አለህ» በማለት መልካም ነገሩን ወደማበረታታት ይመለሳል፡፡ ይህ የኢየሱስ አቀራረብ እርሱ የሚረካበትን ነገር ለማድረግ በፍጥነት ምላሽ እንሰጥ ዘንድ ልብን የሚያሸንፍ ነው፤ በኤፌሶን ያሉ አማኞች ጌታ የሚጠላውን የኒቆላውያንን ሥራ ይጠሉ ነበር፡፡ ጌታ ያበረታታቸውም በዚህ ነው፡፡ በዚህ ስፍራ ላይ የኒቆላውያን ሥራ የተገለጠ ሲሆን በቊ.15 ላይ ደግሞ የኒቆላውያን ትምህርት ተጠቅሷል፡፡ «ኒቆላውያን» የሚባሉት ሰዎች እነማን እንደነበሩ ሥራቸውም ሆነ ትምህርታቸው ምን እንደነበረ የተነገረን ነገር የለም፤ ይሁንና በጌታ የተጠላ ሥራ እንደነበራቸው በግልጽ ተቀምጦልናል፡፡ በእርግጥ ሰዎቹ በኤፌሶን ቤተክርስቲያንና በጴርጋሞን ቤተክርስቲያን ውስጥ ሥራቸውንና ትምህርታቸውን ለማስረፅ የሞከሩ የሐሰት ወንድሞች እንደነበሩ ከንባቡ ይዘት እንረዳለን፡፡ ሥራቸውም በጌታ የተጠላ በመሆኑ ክፉ ሥራ የነበራቸው ክፉ ሰዎች እንደነበሩ መገንዘብ እንችላለን፡፡ በኤፌሶን ባለች ቤተክርስቲያን ያሉ አማኞች ጌታ የሚጣላውን የእነዚህን ሰዎች ክፉ ሥራ በመጥላታቸው ተመስግነዋል፤ የጌታን ፈቃድና ሥልጣኑን የሚጋፋ ልቡንም በእጅጉ የሚያሳዝን ሥራ ሲሠራ ቸልተኛ ወይም ለዘብተኛ መሆን ተገቢ አይደለም፤ እርሱ የሚጠላውን መጥላት ተገቢ ነው፡፡ በአማኞች መካከል ሠርገው ከሚገቡና ተመሳስለው ከሚኖሩ ነገር ግን ጌታ የሚጠላውን ሥራ ከሚሠሩ ሰዎች ጋር ተስማምቶ ለመኖር ሲባል ነገሮችን እያቻቻሉ ማለፍ እውነተኛ የሆነውንና ሕዝቡን በጽድቅ የሚመራውን እርሱን በእጅጉ ያሳዝነዋል፡፡ ስለዚህ በየአጥቢያ ጉባኤዎች ሁሉ እርሱ የሚጠላውን ሥራ የሚጠላ ስሜት ሊኖር ይገባል፡፡
ቊ.7 «መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ»
ይህ ቃል ለሰባቱ አብያተክርስቲያናት በተላኩት በሰባቱም መልእክታት ውስጥ የሚገኝ ቃል ነው፤ ጆሮ ያለው ክርስቲያን ለራሱ አጥቢያ ቤተክርስቲያን የተላከውን መልእክት ብቻ ሳይሆን ለሌሎቹም አብያተክርስቲያናት የተላኩትን መልእክታት መስማት አለበት፤ ይህም በሌሎች አብያተክርስቲያናት ውስጥ የተመሰገኑትን መልካም ነገሮች እርሱም አጽንቶ እንዲይዛቸው፣ የተነቀፉትን ነገሮች ደግሞ እንዲርቃቸው ይረዳዋል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ሳለም «የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ» እያለ ይናገር ነበር /ማቴ.11፡15፤ 13፡9፡43/፤ ካረገም በኋላ በላካቸው በእነዚህ መልእክታት «ጆሮ ያለው ይስማ» ይላል፡፡ «ጆሮ ያለው» ሲል በሥጋ ያለውን ጆሮ ሳይሆን የልብን ወይም የውስጥን ጆሮ የሚያመለክት ሲሆን ከልብ አስተውለን በተግባር መታዘዝ እንዳለብን የሚያስገነዝብ ቃል ነው፡፡ ይህም በየግላችን ለጌታ የምንሰጠው ምላሽ ነው፡፡ «ጆሮ ያለው» ሲል በነጠላ የተነገረ መሆኑን ልብ ልንል ይገባል፡፡ አንዳንድ ጊዜ አብዛኛው በተሳሳተ አካሄድ ሲሄድ ታዲያ ለጌታ ማን ቀረለት እንል ይሆናል፡፡ ጌታ የሚፈልገው ጆሮ ያለውን ማለትም ከጌታ የተነገረውን በትክክል የሚሰማና የሚታዘዝ ሰውን ነው፡፡ መልእክቱንም የላከው ለእንዲህ ያሉ ሰዎች ነው፡፡ በዘመናችን መንፈስ ለአብያተክርስቲያናት የሚለውን ለመስማት የብዙዎች ጆሮ ያልተከፈተ ቢሆንም ጆሮ ያለው ግን ሰምቶ ይጠቀምባቸዋል፡፡
ቊ.7 «ድል ለነሣW በእግዚአብሔር ገነት ካለው ከሕይወት ዛፍ እንዲበላ እሰጠዋለሁ፡፡»
ይህ በኤፌሶን ባለች ቤተክርስቲያን ላለው ድል ነሺ የተሰጠ ተስፋ ነው፡፡እርሱም በእግዚአብሔር ገነት ካለው የሕይወት ዛፍ እንዲበላ ነው፡፡
በዘፍጥ.2፡8-9 ያለውን ክፍል ስንመለከት እግዚአብሔር አምላክ በምሥራቅ ኤድን ገነትን እንደተከለና የፈጠረውንም ሰው በዚያ እንዳኖረው እናነባለን፡፡ በገነትም መካከል የሕይወትን ዛፍ፣ መልካምንና ክፉን የሚያስታውቀውን ዛፍ አበቀለ፡፡ ሆኖም ሰው እንዳይበላ የተከለከለውን መልካምና ክፉን የሚያስታውቀውን ዛፍ በመብላቱ ከገነት እንዲወጣ ተደረገ፤ ሰው መልካምና ክፉን ወደማወቅ ከመጣ በኋላ በዚያ የኃጢአተኝነት ባሕርዩ ሆኖ የሕይወትን ዛፍ ይበላ ዘንድ እጁን እንዳይዘረጋ እግዚአብሔር በምሕረቱ ከገነት አስወጣው፡፡
«ገነት» የሚለው ቃል ሰው በእግዚአብሔር ደስ ተሰኝቶ በሕይወት ለዘላለም የሚኖርበትን ስፍራ ያመለክታል፤ በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት እንደተነገረው ደግሞ «ገነት» ጌታ በሰማይ በክብር የሚገኝበትን ስፍራ የሚያመለክት ነው፤ ጌታ «ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትሆናለህ» ብሎ በመስቀል ላይ ከእርሱ ጐን ተሰቅሎ «በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ» ላለው ክፉ አድራጊ የተናገረው ቃል ይህንኑ ያረጋግጣል /ሉቃ.23፡43/፤ ጳውሎስም ስለራሱ ሲናገር «እንዲህ ያለው ሰው ... እስከ ሦስተኛው ሰማይ ተነጠቀ ... ወደገነት ተነጠቀ» በማለት ጽፏል /2ቆሮ.12፡2-4/፡፡ ስለዚህ የክርስቶስ ለሆኑት ድል ነሺዎች የተዘጋጀው የእግዚአብሐር ገነት በሰማይ ይኸው ራሱ ኢየሱስ ያለበት ስፍራ ነው፡፡ በዚያም ያለው የሕይወት ዛፍ ሌላ ማንም ሳይሆን ራሱ ኢየሱስ ነው፤ በኤፌሶን ቤተክርስቲያን የቀደመ ፍቅር እንዲቀዘቅዝ ምክንያት የሆኑትን ነገሮች ማለትም በመከራ ውስጥ ለማለፍ አለመፈለግ፣ እንደ ዴማስ በዚህች ዓለም የሚመችና ደስ የሚያሰኝ ነገር መፈለግ፣ ከጌታ ነገር ይልቅ የራስን ነገር ማስቀደም ... ወዘተ እነዚህን ድል ነስቶ በቀደመው ትኲስ ፍቅር ጌታን የሚከተል ሁሉ በዚህ ዓለም ሰው ለራሱ ከሚያበጃት ገነት የሚገኘው ደስታና ጥቅም ቢቀርበትም በሰማይ በእግዚአብሔር ገነት ካለው ከሕይወት ዛፍ እንዲበላ ይደረጋል፤ ማለትም በክርስቶስ ያለውን፣ ጣዕሙ ሁልጊዜም የማይጠፋውንና እርሱ ባለበት በዚያ በእግዚአብሔር ቀኝ የሚገኘውን መለኮታዊ ደስታና ዕረፍት ለዘላለም ያገኛል፡፡ ይህም ለእኛ እጅግ የሚያበረታታ ተስፋ ነው፡፡ እስከመስቀል ሞት ድረስ በወደደን ጌታ እና በእኛ መካከል ጣልቃ በመግባት ለእርሱ ያለንን ትኲስ ፍቅር ለማቀዝቀዝና ለእርሱ የነበረንን የተቀደሰ ቅንዓት ለማደብዘዝ የሚሞክሩ የዓለም ነገሮች የሥጋ መሻቶች በዙሪያችን በበዙበት በዚህ ዘመን ድል ነሺዎች ሆነን በቀድሞው ፍቅራችን መጽናት ይገባናል፡፡
ከቤተክርስቲያን ታሪክ አኳያ ሲታይ በኤፌሶን ቤተክርስቲያን የነበረው ሁኔታ በዘመነ ሐዋርያት የነበረችው ጥንታዊት ቤተክርስቲያን ያሳለፈችውን እና የነበረችበትን ሁኔታ የሚያመለክት ነው፤ በዚያን ጊዜ የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን የሚለውጡ ተንኰለኞች እንደነበሩ ቀደም ሲል አይተናል /2ቆሮ.11፡13/፡፡ ሐዋርያት ሳይልኳቸው «ካልተገረዛችሁ ትድኑ ዘንድ አትችሉም» ብለው የሚሰብኩ የሐሰት አስተማሪዎች ነበሩ /ሐ.ሥ.15፡1/፤ እንደዚሁም የተለያዩ ኑፋቄዎችን አሾልከው የሚያገቡ ሐሰተኞች ነቢያትና ሐሰተኞች አስተማሪዎች ነበሩ /2ጴጥ.2፡1/፤ በዚህ ሁሉ ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች እነዚህን ሁሉ ተጋፍጠው ሳይሰለቹ መርምረው በመለየት ሐሰተኞች መሆናቸውን ሲያውቁ ስለጌታ ስም ከእነርሱ ለመለየት ጽኑአንና ቁርጠኞች ነበሩ /1ዮሐ.1፡1-6/፡፡ ይህም ጽናታቸው በዘመናችንም ቢሆን የሐሰት አሠራሮች በቸልታ መታየት እንደሌለባቸውና በግዴለሽነት ተሸክመን በመኖር የጌታን ልብ ማሳዘን እንደሌለብን፣ በምትኩ ግን ስለስሙ በመቈርቈር ከሐሰተኞች መለየት እንዳለብን የሚያስተምረን ነው፡፡
በሐዋርያት ዘመን በነበረችው ቤተክርስቲያን በተለይም ያ ክፍለ ዘመን በሚያበቃበት በጳውሎስና በጴጥሮስ እንዲሁም በዮሐንስ የአገልግሎት ዘመን መጨረሻ ገደማ የቀደመው ፍቅር የቀዘቀዘበት ሁኔታ ይታይ ነበር፡፡ በእስያ አገር ባሉ ክርስቲያኖች ዘንድ የነበረው ትኲስ መንፈሳዊ ስሜት በርዶ እንደነበረ በጳውሎስ ላይ መከራ በደረሰ ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ በማለታቸው ይታወቃል፤ ይህንንም ራሱ ሲገልጽ «በእስያ ያሉቱ ሁሉ ከእኔ ፈቀቅ እንዳሉ ታውቃለህ» ብሎ ለጢሞቴዎስ ጽፎለታል /2ጢሞ.1፡15/፤ ዴማስንም በተመለከተ ሲጽፍ «ዴማስ የአሁኑን ዓለም ወዶ ትቶኛልና ወደተሰሎንቄም ሄዷል» ብሏል /2ጢሞ.4፡10/፡፡ እንዲሁም በእስራቱ ወቅት ሁሉም እንደተውት ሲናገር «በፊተኛው ሙግቴ አንድ እንኳ አልደረሰልኝም፤ ሁሉም ተውኝ እንጂ፤ ይህንም አይቊጠርባቸው» ብሏል /2ጢሞ.4፡16/፡፡ እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የሚገኙት በ2ኛ የጢሞቴዎስ መልእክት ሲሆን ይህቺም መልእክት የተጻፈችው ጳውሎስ ስለ ጌታ ስም የሚሠዋበት ጊዜ ከመድረሱ ጥቂት አስቀድሞ በእስር ላይ ሳለ ነበር፡፡ እንደዚሁም 2ኛ ጴጥሮስንና የዮሐንስ መልእክትን እንዲሁም የዮሐንስ ራእይን ስናነብ ክርስትናው ሲጀምር በሁሉም አማኞች ዘንድ የነበረው መንፈሳዊ ቅንዓት፣ ታማኝነትና ታዛዥነት፣ ለእውነት መቆም፣ በመከራ ውስጥ ጨክኖ ማለፍ ባጠቃላይ በሁለንተናዊ መሰጠት የሚገለጥ ለጌታ የነበራቸው ትኲስ ፍቅር ቀንሶና ቀዝቅዞ ነበር፤ ሐሰተኞች እና የሐሰት አሠራሮች ሾልከው ይገቡ ነበር፤ ብዙዎችም ሐሰተኞችን በመዳራታቸው መከተል ጀምረው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በውጪ የሚታየው ምስክርነትና የሚሠራው መልካም ሥራ እንደተጠበቀ ቀጥሏል፤ ነገር ግን የቀደመ ፍቅር ባለመኖሩ የልብ ዝለትና ተስፋ መቁረጥ ባደከመው ስሜት የሚከናወን ሥራ ጌታን የማያረካው በመሆኑ እርሱ በእጅጉ የሚነቅፈው ነው፡፡