ግጥም    

ክብር ለእርሱ



በበጉ ደም ከተዋጁት
ክብርን ለእርሱ ከሚሰጡት
ከባርነት ነፃ ወጥተው
ልጆች ተብለው ከተጠሩት
በሰማያት በግርማው ቀኝ
ባለው በእርሱ ከሚመኩት
አዲስ ቅኔ አዲስ መዝሙር
ይኸውና ለእርሱ ክብር፡፡

«ለወደደን ላፈቀረን
በደሙ አጥቦ ላከበረን
ለአባቱ ታላቅ መንግሥት
ካህናቱ ላደረገን
ለቀደሰን ላጸደቀን
ወደ አባቱም ላቀረበን
ላስታረቀን ከራሱ ጋር
እንድንኖር በርሱ ፍቅር
የናሱን ደጅ ሰባብሮልን
ሰንሰለቱን ቆራርጦልን
ዲያብሎስን አስጨንቆ
ከእግራችን ሥር ለጣለልን
ለታደገን ከመከራ
እርሱ ብቻ እየሠራ
ሞታችንን ለሞተልን
ነፍሱን ለእኛ ለሰጠልን
በትንሣኤው የሞትን ኃይል
ለዘላለም ላጠፋልን
እርሱ ነግሦ በግርማው ቀኝ
እኛን ንጉሥ ላደረገን
በከበረው የወርቅ ልብስ
አጎናጽፎ ላከበረን
ለሰወረን በእርሱ ጉያ
ክብር ለርሱ ሃሌ ሉያ፡፡

ክብር ይሁን ክብር ለ'ርሱ
በሰማያት በመቅደሱ
ስግደት ይሁን ስግደት ለ'ርሱ
ለዳዊት ልጅ ለንጉሡ
ፍጥረታትም በቋንቋችሁ
ዘምሩለት ለአምላካችሁ
መላእክቱም ስገዱለት
አዲስ ቅኔን አቅርቡለት
ቅዱሳኑም አወድሱት
በአዲስ ዜማ አመስግኑት
በማደሪያው በሰማያት
መሥዋዕቱን አቅርቡለት
በእውነትና በመንፈስም
በልባችሁ ተቀኙለት፡፡


Amharic Bible-|- The Holy Bible [King James Version]