ኢየሱስ ለእኔ
... ... መድኅኔ
ያወጣኸኝ ከኵነኔ
ለአእምሮዬ ነህ ሰላሜ
ፍጹም እረፍት ለድካሜ
እንጀራ ነህ ለሕይወቴ
እርካታዬ ለጥማቴ
መሸሸጊያ መመኪያዬ
ከሞት ፍርሃት ማምለጫዬ፡፡
ከመቅበዝበዝ ያረፍኩብህ
ሸክሜን ሁሉ የጣልኩብህ
የማትሰለች እረኛዬ
የማትደክም ጠባቂዬ
አንተን ብዬ አላፈርኩም
ተደግፌህ አልወደቅሁም፡፡
አባት፣ እናት፣ እህት፣ ወንድም
ንጉሥ፣ ጌታ፣ ለዘላለም
ዘይት ይዤ ምጠብቅህ
ጠዋት ማታ ምናፍቅህ
የዘላለም ሽልማቴ
አክሊሌ ነህ መድኃኒቴ፡፡
ውበት የለኝ ውበቴ ነህ
ክብርም የለኝ ክብሬ አንተ ነህ
ደም ግባቴ መዓዛዬ
ጌጤ አንተ ነህ መዋቢያዬ
የጠላቴን ፍላጻውን
እኔን አጥፊ መሣሪያውን
መመከቻ ጋሻዬ ነህ
ጽኑ ግንቤ ኢየሱስ ነህ፡፡
አለቴ ነህ መሠረቴ
ራሴ ነህ ጉልላቴ
ጉልበቴ ነህ ለድካሜ
ፈውሴ አንተ ነህ ለህመሜ፡፡
በጨለማ በሞት ጥላ
ለነበርኩኝ በአውላላ
ፀሐየ ጽድቅ ሆነህልኝ
ጨለማዬን ገፈፍክልኝ
ዛሬማ አንተን ያያል ዓይኔ
ሆነህልኝ ብርሃኔ፡፡
መንገድ፣ ሕይወት፣ ፍጹም እውነት
ወደ እግዚአብሔር ምቀርብበት
መሰላል ነህ ለእኔነቴ
መድረሻዬ ወደ አባቴ
ወዳጄ ነህ አለኝታዬ
የቅርብ አጽናኝ መካሪዬ
ጓዳዬ ነህ የምሥጢሬ
የነፍሴ አባት መምህሬ፡፡
ጻድቅ ሆነህ ያጸደከኝ
ቅዱስ ሆነህ የቀደስከኝ
የማለድከው ስለ እኔ
ኢየሱስ ነህ ሊቀ ካህኔ
የሞት ቀንበር ተጭኖብኝ
የሲኦል ደጅ ሲያስጨንቀኝ
ሞቴን ሞተህ አሳረፍከኝ
ትንሣኤና ሕይወት ሆንከኝ፡፡
ቀና ብዬ ወደ ሰማይ
የእግዚአብሔርን መቅደሱን ሳይ
የዘላለም መሥዋዕቴን
አንተን አየሁ ሊቀካህኔን፡፡
ዓመፃዬ ላይታሰብ
በንጉሡ በእግዚአብሔር ልብ
ዋስ ጠበቃ ሆነህልኝ
በአባትህ ፊት ታየህልኝ፤
አንተ በዚያ በመኖርህ
እኔም ባንተ አረፍኩብህ::
በንጉሥ ቀኝ በዙፋኑ
ትምክህት ሆኖ ለወገኑ
ስፍራ ይዞ ሚጠብቀኝ
ጠበቃዬ የሱስ አለኝ
አለኝ አባት የሚያኮራ
ስለ እኔ የሚራራ
ደግሞም አለኝ ኃያል ንጉሥ
ጥያቄዬን የሚመልስ
ከሰሎሞን የሚበልጠው
እንቆቅልሼን የፈታው
የሱስ ለእኔ ጥበቤ ነው፡፡
በመሆንህ አንተ የእኔ
ሰላም አለኝ በዘመኔ
ስለበዛብኝ ውለታህ
ምስጋናዬ ይፍሰስልህ
ፍጹም ምሉዕ ሆነህልኝ
የእኔ ያልኩትን ጥያለሁኝ
አትጠገብ ጠዋት ማታ
ሁሉንም ነህ የኔ ጌታ
እንዲያው ልበል የሱስ ለእኔ
ሁሉንም ነህ መድኅኔ፡፡