trinity  

አራቱ ወንጌላት

መግቢያ

ወንጌል የሚለው ቃል በቅድሚያ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰበከውን መልካም የምሥራች ያመለክታል(ኢሳ.61፡1፤ ሉቃ.4፡19፤ ማቴ.4፡23፤ 9፡35) በመቀጠልም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚሰበከውን መልካም የምሥራች ያመለክታል (ሮሜ.1፡1-4፤ ሉቃ.2፡10፤ የሐዋ.ሥ.8፡35) ክርስቶስን በተመለከተ የሚሰበከው ወንጌል ከይዘቱ አንጻር በ5 ዓይነት መልኩ ተገልጿል፤ ይኸውም፡-

  1. የጸጋ ወንጌል (የሐዋ.20፡24)
  2. የመዳን ወንጌል (ኤፌ.1፡13)
  3. የሰላም ወንጌል (ኤፌ.6፡15)
  4. የክብር ወንጌል (2ቆሮ.4፡4)
  5. የመንግሥት ወንጌል (ማቴ.4፡23፤ 9፡35፤ 24፡14)

አራቱ ወንጌላት ሲባል ደግሞ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ማንነቱንና ሥራውን የመዘገቡ የመጀመሪያዎቹ አራቱ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ናቸው፡፡ እነርሱም፡-

  1. የማቴዎስ ወንጌል፣
  2. የማርቆስ ወንጌል፣
  3. የሉቃስ ወንጌል፣
  4. የዮሐንስ ወንጌል ናቸው፡፡

እነዚህ አራቱ ወንጌላት ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታሪኮች ትምህርቶችና ታምራት መካከል የተወሰኑትን መርጠው በመጻፍ የእርሱን ማንነት በአራት መንገድ ያቀርቡልናል፡፡ በመሆኑም አራቱ ወንጌላት የጌታችን የሕይወት ታሪክ ሳይሆኑ ስለማንነቱ የሚመሰክሩ መጻሕፍት ናቸው፡፡

1. የማቴዎስ ወንጌል

1.1. ጸሐፊው

ከመጽሐፉ ርእስ እንደምንረዳው የማቴዎስ ወንጌልን የጻፈው ከ12ቱ የክርስቶስ ሐዋርያት መካከል አንዱ የሆነው ቀራጩ ማቴዎስ ነው፡፡ በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ ስለማቴዎስ የምናውቀውን ጥቂት ነገር ቀጥሎ እንመለከታለን፡፡

ማቴዎስ በጌታ ከመጠራቱ በፊት በቅፍርናሆም የቀራጭነት ሥራ ይሠራ ስለነበር የተጠራውም በመቅረጫው ተቀምጦ በነበረ ጊዜ ነው(ማር.2፡1ና14)፤ በዚህ ሥራው ምክንያት “ቀራጩ ማቴዎስ” ተብሎ ተጠርቷል (ማቴ.10፡3)፡፡ የማቴዎስ የመጠራቱ ታሪክ በሚከተሉት ሦስት ጥቅሶች ውስጥ ተመዝግቧል፡፡ (ማቴ.9፡9-13፤ ማር.2፡13-17፤ ሉቃ.5፡27-32)፡፡ ከእነዚህ ክፍሎች ውስጥ በማቴ.9፡9 ላይ “ማቴዎስ” ተብሎ የተጠራው ስሙ በማር.2፡14 እና በሉቃ.5፡27 ላይ “ሌዊ” ተብሎ ተጠርቷል፡፡ በተጨማሪም በማር.2፡14 ላይ የማቴዎስ አባት “እልፍዮስ” የተባለ እንደነበር ተገልጿል፡፡

ቀራጮች ከታዘዘው አብልጠው በመውሰድ(ሉቃ.2፡12-13) እና አንዳንዶችን በሐሰት በመክሰስ (ሉቃ.19፡8) በሚሠሩት ክፉ ሥራ የተነሣ፣ እንደዚሁም በሕዝቡ የሚጠላውን የሮምን መንግሥት የሚያገለግሉ ከመሆናቸው የተነሣ የተናቁ ነበሩ(ማቴ.፡46፤ 18፡17፤ ሉቃ.1፡1)፤ ሆኖም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠሉትና ከተናቁት ወገን የሆነውን ማቴዎስን የራሱ አገልጋይ እንዲሆን ጠራው፡፡ ማቴዎስም በራሱ ቤት(ሉቃ.5፡29) ለጌታ ታላቅ ግብዣ አድርጎለት ከቀራጮችና ከሌሎች ሰዎች ብዙ ሕዝብ በነበረበት የጌታ ደቀመዝሙር መሆኑን በይፋ ገለጠ፡፡ ጌታም ግብዣውን ተቀብሎ በማቴዎስ ቤት ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር በመቀመጡ እርሱ ኃጢአተኞችን ወደ ንስሐ ሊጠራ መምጣቱን አሳየ፡፡

ማቴዎስ ከ12ቱ ሐዋርያት መካከል አንዱ እንደነበረ የ12ቱ ሐዋርያት ስም ዝርዝር ከሚገኝባቸው ከ4ቱም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እንረዳለን (ማቴ.10፡2-4፣ ማር.3፡14-19፤ ሉቃ.6፡13-16፤ የሐ.ሥ.1፡13)፤ ከዚህ ሌላ 12ቱ ሐዋርያት ባንድነት ሳሉ አብሮ እንደነበረ ከመረዳታችን በቀር ስለማቴዎስ ከመጽሐፍ ቀድስ የምናውቀው የለም (የሐዋ.ሥ.2-14፤ 6፡2፤ 9፡27፤ 15፡4)፡፡

1.2. ዋና ሐሳቡ፣

  1. 1. የማቴዎስ ወንጌል ዋነኛ ሐሳብ ኢየሱስ ክርስቶስ የአይሁድ ንጉሥ መሆኑን መግለጽ ነበር፣ ይህንም በሚከተሉት መንገዶች በግልጽ ያሳያል፣
  • ከዚሁ ጋር የተያያዘው ሌላው የመጽሐፉ ሐሳብ የክርስቶስን መንግሥቱን (መንግሥተ ሰማያትን) ማስተዋወቅ ነው፡፡ ይህንንም የሚያቀርበው በሚከተለው መልክ ነው፡፡
  • አከፋፈሉ

    1. ክርስቶስንና መንግሥቱን ማስተዋወቅ (1-10)
    2. ክርስቶስና መንግሥቱ ተቀባይነት አለማግኝትቸው (11-12)
    3. ክርስቶስ ተቀባይነት ካጣ በኋላ ያደረገውና ያስተማረው (13-25)
    4. የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ (26-28)

    1. የማርቆስ ወንጌል

    1.1. ጸሐፊው

    የማርቆስ ወንጌል ጸሐፊ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ “ማርቆስ የተባለው ዮሐንስ” ተብሎ የተጠራው የጌታ አገልጋይ ነው (የሐዋ.ሥ.12፡12፣25 15፡36)፤ ስለሆነም “ማርቆስ” የኋላ ስሙ ሲሆን የቀደመ ስሙ ግን “ዮሐንስ” እንደነበር እንገነዘባለን (የሐዋ.ሥ.13፡5፣13)፡፡ እናቱ “ማርያም” እንደምትባል (የሐዋ.ሥ.12፡2)፣ አጎቱ ደግሞ በርናባስ እንደሆነ (ቈላ.4፡10-11) ታውቋል፡፡

    ማርቆስ በክርስቶስ ያመነው በጴጥሮስ አገልግሎት አማካኝነት እንደሆነ ለመገንዘብ ይቻላል፣ ምክንያቱም ጴጥሮስ በመልእክቱ “ልጄ ማርቆስ” ብሎ ጠርቶታልና (1ጴጥ.5፡13)፡፡ ሆኖም በወንጌል ሥራ ላይ ተሰማርቶ የምናገኘው ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር ነው፡፡ ጳውሎስና በርናባስ በቀላውዴዎስ ቄሣር ጊዜ በነበረው ረሃብ ምክንያት ከአንጾኪያ ቤተክርስቲያን የተላከ እርዳታ ለኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያን አድርሰው በተመለሱ ጊዜ ማርቆስን ወደ አንጾኪያ ይዘውት በመምጣት በአገልግሎታቸው ከእነርሱ ጋር አብሮ እንዲሆን አድርገዋል፡፡ ከአንጾኪያ በመነሣት ባደረጉት የመጀመሪያው የወንጌል ስብከት ጉዞ እነርሱን እያገለገለ አብሮ የተጓዘ ሲሆን ጉዞውን አቋርጦ የጵንፍልያ ከምትሆንም ጰርጌን ከተባለች ቦታ ከእነርሱ ተለይቶ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ እንደነበረ ተመዝግቧል (የሐ.ሥ.13፡5፣ 13)፡፡ በዚህም ምክንያት ለ2ኛ ጊዜ አብሮአቸው እንዲጓዝ በርናባስ ባሰበ ጊዜ ጳውሎስ አልፈቀደም ነበር፤ ይህም ጉዳይ በጳውሎስና በበርናባስ መካከል መለያየትን የፈጠረ ሲሆን በርናባስ ማርቆስን ይዞ ወደ ቆጵሮስ ሄደ (የሐ.ሥ.15፡36-39)፡፡ ይሁንና ጳውሎስ በመጀመሪያው እስራቱ ጊዜ የቈላስይስንና የፊልሞናን መልእከታት፣ በሁለተኛው እስራቱ ጊዜ ደግሞ 2ኛይቱን የጢሞቴዎስ መልእከት በጻፈ ጊዜ ስለማርቆስ የሰጠው ምስክርነት በኋላ ላይ መለያየቱ እንደተወገደ የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡(ቈላ.4፡10፤ ፊልሞ.24፣ 2ጢሞ.4፡11)፤ ማርቆስ ከቆጵሮስ ሌላ በሮምና በኤፌሶን እንዳገለገለ ከእነዚህ ጥቅሶች የምንረዳ ሲሆን ከ1ጴጥ.5፡13 ደግሞ ከጴጥሮስ ጋር በመሆን በባቢሎን እንዳገለገለ ማወቅ እንችላለን፡፡

    2.2. ዋና ሐሳቡ

    የማርቆስ ወንጌል ዋና ሐሳብ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ የነበረ አገልጋይ መሆኑን ማስተዋወቅ ነው(10፡45)፡፡ በነቢያት መጻሕፍት እንደምናነበው እግዚአብሔር ሊመጣ የነበረውን መሢሕ “ባሪያዬ” ብሎ ይጠራው ነበር(ኢሳ.52፡13፤ ዘካ.3፡8)፤ የማርቆስ ወንጌልም ክርስቶስን በዚህ ገጽታው ያቀርብልናል፡፡ ሆኖም በወንጌሉ መግቢያ ላይ የእግዚአብሔር ልጅነቱን (አምላክነቱን) የሚያቀርብ ሲሆን(1፡1፣11) በወንጌሉ መደምደሚያ ላይ ደግሞ ዐርጎ በእግዚአብሔር ቀኝ መቀመጡን(16፡19) ይገልጻል፡፡ ይህም በፊልጵ.2፡6-16 እንደተገለጸው “የባሪያን መልክ” የያዘው እርሱ አስቀድሞ በእግዚአብሔር መልክ የነ በረ እንደሆነና አገልግሎቱን ሲያጠናቅቅ ያለልክ ከፍ ከፍ መደረጉን የሚያሳይ ነው፡፡ በማርቆስ ወንጌል ውስጥ እንደ አገልጋይ መቅረቡን የምንገነዘበው በሚከተሉት መንገዶች ነው፡፡

    2.3. አከፋፈሉ

    1. የክርስቶስ ማንነቱና ወደ አገልግሎቱ እንዴት እንደገባ (1፡113)
    2. ክርስቶስ ያከናወናቸው አገልግሎቶች(ሥራዎች) (1፡14-10፡52)
      1. በገሊላና በአካባቢው ያገለገለው (1፡14-9፡50)
      2. በይሁዳና በአካባቢው ያገለገለው (10፡1-52)
    3. ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱና ተቀባይነት አለማግኘቱ (11፡1-13፡37)
    4. የክርስቶስ መከራውና ሞቱ (14፡1-5፡47)
    5. የክርስቶስ ትንሣኤውና ዕርገቱ (16፡1-20)

    የሉቃስ ወንጌል ጸሐፊ ከአሕዛብ ወገን የነበረውና ከጳውሎስ ጋር አብሮ ያገለገለው ሉቃስ ነው፡፡ (ቈላ.4፡11፤ እና 14) የሉቃስ ወንጌልንና የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን የጻፈው አንድ ሰው እንደሆነ ሁለቱም መጻሕፍት የተጻፉት “ቴዎፍሎስ” ለተባለ ሰው በመሆኑና (ሉቃ.1፡-4፤ የሐ.ሥ.1፡1) የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የሚጀምረው የሉቃስ ወንጌል ካቆመበት በመሆኑ እንገነዘባለን (ሉቃ.24፡46-50፤ የሐ.ሥ.1፡1-11)፡፡ ስለዚህ የሐዋርያት ሥራም ጸሐፊ ሉቃስ በመሆኑ እርሱ ከነጳውሎስ ጋር ስላገለገለው አገልግሎት ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ በመጠኑም ቢሆን ማወቅ ይቻላል፤ በሐዋ.ሥ. መጽሐፍ ይህን ማወቅ የሚቻለው “እኛ” እያለ በጻፋቸው ሦስት ክፍሎች ነው፡፡

    1. የሐ.ሥ.16፡10-17፡- በዚህ ክፍል ጳውሎስ ሁለተኛውን የወንጌል ስብከት ጉዞ ባደረገ ጊዜ ከጢሮአዳ ጀምሮ እስከ ፊልጵስዩስ ድረስ አብሮ እንደነበረ እንረዳለን፡፡
    2. የሐ.ሥ.20፡5-21፡8፡- በዚህ ክፍል ጳውሎስ ሦስተኛውን የወንጌል ስብከት ጉዞ አጠናቅቆ ከግሪክ ወደ ኢየሩሳሌም በሄደ ጊዜ ሉቃስ አብሮ እንደነበር እናያለን፡፡
    3. የሐ.ሥ.27፡1-28፡16፡- በዚህ ክፍል ደግሞ ጳውሎስ ታስሮ ወደ ሮም በተወሰደ ጊዜ እርሱም አብሮ እስከ ሮም እንደሄደ እንረዳለን፡፡

    ሉቃስ ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው እስራቱ የቈላስይስንና የፊልሞናን መልእክት በሚጽፍ ጊዜ ከእርሱ ጋር አብሮ በሮም ያገለግል ነበር (ቈላ.4፡14፤ ፊልሞ.24)፤ ጳውሎስ ለሁለተኛ ጊዜም ታስሮ ሳለ ብዙዎች ትተውት በሄዱ ጊዜ ከእርሱ ጋር በሮም እስከመጨረሻው ጸንቶ አብሮት የነበረው ሉቃስ ብቻ ነበር(2ጢሞ.4፡9-10)፡፡ ይህ ከአሕዛብ የተጠራ ወንጌላዊ ከአሕዛብ ለተጠራው ቴዎፍሎስ ለተባለው የከበረ ሰው በስሙ የሚጠራውን ወንጌል ጽፎለታል፡፡

    3.2. ዋና ሐሳቡ

    የሉቃስ ወንጌል በዋናነት የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስን ፍጹም ሰው መሆን አጉልቶ የሚያሳይ መጽሐፍ ነው፡፡ ይህንንም በሚከተሉት መንገዶች እንመለከታለን፡፡

    3.3. አከፋፈሉ

    1. የክርስቶስ ጽንሰቱ፣ ልደቱና የሕጻንነቱ ጊዜያት (1፡1-2፡52)
    2. በአገልግሎቱ መጀመሪያ ላይ ያደረጋቸው ነገሮች (መጠመቁና መፈተኑ) (3፡1-4፡13)
    3. በገሊላ የነበረው አገልግሎት (4፡14-9፡50)
    4. ወደ ኢየሩሳሌም ሲወጣ ያደረጋቸው ነገሮች (9፡51-19፡27)
    5. ወደ ኢየሩሳሌም ውስጥ ያደረገውና ያስተማረው (19፡28-21፡38)
    6. የክርስቶስ መከራውና ሞቱ (22፡1-23፡56)
    7. የክርስቶስ ትንሣኤውና ዕርገቱ (24፡1-53)

    4. የዮሐንስ ወንጌል፣

    4.1. ጸሐፊው

    የዮሐንስ ወንጌል ጸሐፊ ከ12ቱ ሐዋርያት መካከል አንዱ የሆነው ዮሐንስ ነው፡፡ በወንጌሉ ውስጥ ራሱን “ጌታ የሚወደው ደቀመዝሙር” ብሎ የሚገልጽ ሲሆን ወንጌሉንም የጻፈው እርሱ መሆኑን ተናግሯል (ዮሐ.21፡20-24)፡፡ እርሱም የዘብዴዎስ ልጅ፣ የያዕቆብ ወንድም መሆኑ ተመዝግቧል (ማቴ.4፡21)፡፡ እናታቸውም ወደ ጌታ መቃብር ከሄዱት ከሦስቱ ሴቶች አንዷ የነበረች፤ “ሰሎሜ” እንደሆነች መረዳት ይቻላል (ማቴ.27፡46ን ከማር.15፡45፤ 16፡1 ጋር አነጻጸር) ዮሐንስ ከወንድሙ ከያዕቆብ ጋር በጌታ የተጠራው ዓሣ በማጥመድ ሥራ ላይ ሳለ ሲሆን ወዲያውኑ ታንኳይቱንና አባታቸውን ትተው ተከተሉት (ማቴ.4፡22)፤ ከወንድሙ ከያዕቆብና ከጴጥሮስ ጋር በመሆን ከሌሎች ተለይተው ከጌታ ጋር የሆነባቸው ጊዜያት ነበሩ (ማር.1፡29-31፤ 5፡35-43፤ 9፡2-8 14፡32-42)፤ በስቅለቱ ዋዜማ በጌታ ደረት ተጠግቶ የነበረው ደቀመዝሙር እርሱ ሲሆን (ዮሐ.13፡23-24)፣ ጌታ በተሰቀለ ጊዜም በስፍራው ተገኝቶ አይቷል፤ የጌታን እናትም ከመስቀሉ ሥር ከጌታ ተረክቦ ወደ ቤቱ ወስዷል (19፡25-27)፡፡ ጌታ ከሙታን በተነሣ ዕለትም ከሴቶቹ በመቀጠል ከጴጥሮስ ጋር ወደ ጌታ መቃብር ሄዶ ትንሣኤውን አረጋግጧል (20፡1-10)፡፡ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ እንደምናነበረው ዮሐንስ ከጴጥሮስ ጋር በመሆን መከራን እየተቀበለ ወንጌልን አገልግሏል (የሐ.ሥ.3፡1-4፡23፤ 8፡14-15)፡፡ በኢየሩሳሌም ጳውሎስና በርናባስ ወደ አሕዛብ ይሄዱ ዘንድ ቀኝ እጃቸውን ከሰጡአቸው አዕማድ መስለው ከሚታዩት ከሦስቱ አንዱ ዮሐንስ ነበር፤ (ገላ.2፡9)፡፡ ከዚህ ሌላ ዮሐንስ ወንጌልን ያገለገለባቸው ስፍራዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያልተገለጹ ሲሆን በራእ.1፡9 ላይ ግን ስለእግዚአብሔር ቃልና ስለ ኢየሱስ ምስክር ፍጥሞ በምትባል ደሴት ታስሮ እንደነበር እንገነዘባለን፡፡

    4.2. ዋና ሐሳቡ

    የዮሐንስ ወንጌል ከቀደሙት ከሦስቱ ወንጌላት በተለየ መልኩ የኢየሱስ ክርስቶስን መለኮታዊ ባሕርይ በተመለከተ በዋናነት በሚገልጽ ወንጌል ነው፡፡ ይህንንም በሚከተለው መልኩ ያስረዳል፡፡

    በተጨማሪም በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ የተመዘገቡት ኢየሱስ ያደረጋቸው ምልክቶች በወንጌሉ ውስጥ የተጻፉበት ዋና ምክንያት ሰዎች “ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ያምኑ ዘንድ አምነውም በስሙ የዘላለም ሕይወት ይሆንላቸው ዘንድ” መሆኑ ተገልጿል (20፡30-31)፡፡ ከዚህም አንጻር የዮሐንስ ወንጌል በኢየሱስ በማመን ስለሚገኘው የዘላለም ሕይወት በስፋት ይናገራል (1፡4፤ 3፡14-16፤ 3፡36፤ 5፡24፣ 39፤ 6፡47፤ 10፡10፣ 28፤ 17፡3)፡፡

    4.3. አከፋፈሉ

    1. ቃል ሥጋ መሆን (1፡1-14)
    2. የመጥምቁ ዮሐንስ ምስክርነት (1፡15-34)
    3. የክርስቶስ የአደባባይ አገልግሎቱ(1፡35-12፡50)
    4. ክርስቶስ ለደቀመዛሙርቱ ብቻ የሰጠው አገልግሎት(13፡1-17፡26)
    5. የክርስቶስ መከራውና ሞቱ (18፡1-19፡42)
    6. የክርስቶስ ትንሣኤውና ከትንሣኤው በኋላ በመታየቱ (20፡1-21፡25)
    
    Amharic Bible-|- The Holy Bible [King James Version]