አምስቱ ስጦታዎች
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ የዋጃት ቤተክርስቲያን የእርሱ አካል መሆንዋን ማሰብ ነፍስን በመለኮታዊ ሐሴት እና ውስጥን በሚያረሰርስ እርካታ ይሞላል፡፡ አማኝ በዚያች የክርስቶስ አካል ውስጥ ብልት መሆኑን ሲያሰላሰል የሚያገኘው ደስታ እጅግ ከፍ ያለ ከመሆኑም በላይ ማንም ከዚያ የብልትነት ስፍራ ሊያወጣው የማይችል ስለመሆኑ ማሰብም በጣም ያስደንቀዋል፡፡ ራስ ከሆነው ከክርስቶስ ዘንድም የሚያገኘውን መንፈሳዊ መግቦት በደስታ ይቀበላል፡፡
ከተመሠረተች ጀምሮ ከምድር እስከምትወሰድበት ጊዜ ድረስ በዓለም ሁሉ ያሉ አማኞች የሚገኙባት የክርስቶስ አካል የሆነች ቤተክርስቲያን አንዲት ናት፡፡ ያቺ አንድ አካል አሁንም ቢሆን አለች፡፡ በእርስዋም ውስጥ የሚገኝ እያንዳንዱ አማኝ ብልት በመሆኑ በዚያች አካል ውስጥ አንዳች ሥራ ወይም አገልግሎት ይኖረዋል፡፡ ያንንም ሥራ ወይም አገልግሎት የሚያከናውነው ደግሞ ከጌታ በተሰጠው ጸጋ መሠረት ነው፡፡ ስለሆነም የጸጋ ስጦታን በተመለከተ የእግዚአብሔር ቃል የሚያስተምረውን እውነት መረዳት ከጌታ የተቀበለውን አገልግሎት ለመፈጸም ለተነሳሳ አማኝ ሁሉ በእጅጉ ያስፈልገዋል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጸጋ ስጦታዎች የሚያስተምረውን ሁሉ በተገቢው ሁኔታ ማወቅ የብዙ አማኞች ፍላጐት እንደሆነ ይታያል፡፡ ይህም ፍላጐት የተቀደሰ መነሻ እስካለው ድረስ በጸጋ ስጦታዎች ዙሪያ ለሚነሱ ጥያቄዎች ሁሉ የሚያሳርፉ መልሶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ይገኛሉ፤ የጸጋ ስጦታዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሮሜ12፡6-8፤ በ1ቆሮ12፡4-11፤ በ1ቆሮ12፡27-31፤ በኤፌ4፡7-13፤ በ1ጴጥ4፡10-11 ላይ በዝርዝር ተመዝገበው እናገኛለን፡፡ የእግዚአብሔር መንፈስ በቤተክርስቲያን የሚከናወኑ አገልግሎቶች ሁሉ ያለምንም መደነጋገር ይከናወኑ ዘንድ የጸጋ ስጦታዎችን በተመለከተ ሰፊ የቅዱሳት መጻሕፍት ንባባትን ትቶልናል፡፡ ጌታ ቢፈቅድ ወደ ፊት ሁሉንም የምንዳስስ ሲሆን በዚህ ጽሑፋችን ግን ከእነዚህ ንባቦች መካከል በኤፌ4፡7-13 ያለውን መመልከት እንጀምራለን፡፡
«ነገር ግን እንደ ክርሰቶስ ስጦታ መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጠን» (ቊ.7)
ይህ ቃል ለአማኞች በየግል ስለሚሰጥ የጸጋ ስጦታ ይናገራል፡፡ ከዚህ ንባብ በፊት ባሉ ቊጥሮች ስለ አንድ አካል እና ከዚያ አካል ጋር ስለተያያዙ ነገሮች ማለትም ስለ አንድ ተስፋ፣ ስለ አንድ መንፈስ፣ ስለ አንድ ጌታ፣ ስለ አንድ ሃይማኖት (እምነት)፣ ስለአንዲት ጥምቀትና ስለ አንድ አምላክ እናነባለን (ከቊ.4-6)፡፡ ይህም አማኞች እያንዳንዳችን በብልትነት የምንገኝባት የመላዋን ቤተክርስቲያን ገጽታ ያመለክታል፡፡ ከዚያም ሐዋርያው በዚያች አንድ አካል ውስጥ የምንገኝ እያንዳንዳችንን በተመለከተ የጌታ ሐሳብ ምን እንደሆነ ወደ መግለጽ ይመጣል፡፡ በጥቅሉ ስለ አንድ አካል (ስለ መላዋ ቤተክርስቲያን) ከተናገረ በኋላ በመቀጠል ስለእያንዳንዳችን መናገር ይጀምራል፡፡ «ነገር ግን እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጠን» ይላል፡፡ ስለሆነም ቤተክርስቲያን የክርስቶስ አንድ አካል ከመሆንዋ አንጻር እና አንድ ተስፋ፣ አንድ መንፈስ፣ አንድ ጌታ፣ አንድ እምነት፣ አንዲት ጥምቀት፣ አንድ አምላክ የሁሉም አባት ያለን ብንሆንም በየግል ስንታይ ደግሞ እያንዳንዳችን የተለያየ የጸጋ ስጦታ አለን፤ የምንለያየው በሌላ በምንም ሳይሆን ለእያንዳንዳችን በተሰጠን ጸጋ ብቻ ነው፤ ይህን በተመለከተ በሮሜ12፡4 «የብልቶች ሥራ አንድ እንዳይደለ» ስናነብ በዚሁ በኤፌ.4 በቊ.6 ላይ «እንደተሰጠንም ጸጋ ልዩ ልዩ ስጦታ አለን» የሚል እናነባለን፡፡ በ1ቆሮ.12፡4-6 ባለው ክፍል ደግሞ «የጸጋ ስጦታ ልዩ ልዩ ነው፤ መንፈስ ግን አንድ ነው፤ አገልግሎት ልዩ ልዩ ነው፤ ጌታም አንድ ነው፤ አሠራር ልዩ ልዩ ነው፤ ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው» ይላል፡፡ መለያየት በሌለባት በአንዲት የክርስቶስ አካል ውስጥ በእያንዳንዱ አማኝ መካከል የምናየው ልዩነት የእምነት ወይም የትምህርት ወይም የአመለካከት ልዩነት ሳይሆን ከጌታ በተሰጠን የጸጋ ስጦታ ብቻ የሚሆን ልዩነት እንደሆነ እጅግ ውብ ከሆኑት ከእነዚህ የቅዱሳት መጻሕፍት ንባቦች እንማራለን፡፡ ይህ ከስጦታዎች መካከል ብዙዎች እንዲኖራቸው በሚፈልጉት በአንድ የሆነ የጸጋ ስጦታ ተገልጦ ለመታየት ከሚደረገው የዘመናችን ሁኔታ ጋር ሲተያይ እንዴት የተለየ ነው!
የጸጋ ስጦታዎች ለእያንዳንዳችን የተሰጡት በእያንዳንዳችን ፍላጎት መሠረት አይደለም፤ ቃሉ «እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጠን» ይላል፡፡ «እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን» የሚለው ቃልም ለእያንዳንዱ አማኝ የሚሰጠው የጸጋ ስጦታ የሚወሰነው በክርስቶስ ብቻ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ጸጋውን የሚሰጠንም ሆነ በጉባኤ መካከል በዚያ በሰጠን ጸጋ የሚገልጠን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ እኛ እንዲኖረን የምንፈልገውን ወይም በሌላ ሰው ላይ ያየንውንና ለእኛ እንዲሆን የተመኘነውን ስጦታ ጠቅሰን በጸሎት እስከመጠየቅ መድረስ ይህን እውነታ አለመረዳት ወይም በእጅጉ ቸል ማለት ነው፡፡ ጌታ ስጦታዎችን የሚሰጠው በአማኞች ሁኔታ ወይም የግል ፍላጎት ላይ ተመሥርቶ ሳይሆን በራሱ መሻትና ፈቃድ ላይ ብቻ ተመሥርቶ ነው፡፡ ስጦታውም የጸጋ ስጦታ እንደመሆኑ መጠን በእኛ ሁኔታ ላይ ተመሥርቶ ሊሰጠን አይችልም፡፡ በመሆኑም እኛ ማድረግ ያለብን ከመጀመሪያው ጀምሮ ከጌታ ዘንድ የሚቀርብልንን ጥሪ ከእምነት በሚነሣ መታዘዝ እየተቀበልን እንደቃሉ መኖር ብቻ ነው፡፡ ከዚያም በጊዜ ውስጥ እርሱ ራሱ ባስቀመጠን የብልትነት ስፍራችን የተሰጠንን ሥራ እንሠራ ዘንድ የሚያስፈልገውን ጸጋ ይሰጠናል፤ በራሱ ጊዜም በቤተክርስቲያን መካከል በሰጠን ጸጋ ይገልጠናል፡፡ ይህንን ማጤን «ጌታን የማገለግልበትን ጸጋ እንዴት ላውቅ እችላለሁ?» ለሚለው የብዙዎች ጥያቄ መልስ ሊሆን ይችላል፡፡ ጌታ እርሱን የሚያገለግሉበትን ጸጋ እንደሚሰጥ እና በራሱ ጊዜ በዚያ ጸጋ እንደሚገልጥ ማመን የእኔ ጸጋ የትኛው ይሆን? ብሎ ከመጨነቅ ይልቅ ጌታን በታማኝነት ወደመጠበቅ ይወስደናል፡፡ ከሰዎች በሚገኝ ሹመት ለማገልገል ፈቃድ እናገኝ ዘንድ አለቆችን ወይም መሪዎችን ደጅ ከመጥናት ይልቅ ጌታ በራሱ ፈቃድና በራሱ መንገድ እንዲያሰማራን ራሳችንን ለእርሱ እንተዋለን፡፡
ስለዚህ፡- ወደላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ (ቊ.8)
የስጦታዎቹ ባለቤትም ሆነ የስጦታዎቹ ምንጭ ጌታ ኢየሱስ ነው፡፡ ለሰዎች ከሰጣቸው ስጦታዎች አንጻር የእርሱ ማንነት የተገለጠውም ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን የማረከ ድል አድራጊ ጌታ ሆኖ ነው፡፡ ይህም በመዝ.68፡18 ላይ አስቀድሞ ስለመሢሕ የተነገረ ቃል ነበር፡፡ በዚያ ስፍራ «ወደ ላይ ዓረግህ፤ ምርኮን ማረክህ፤ ስጦታንም ለሰዎች ሰጠህ» የሚል ቃል እናነባለን፡፡ ጳውሎስ በኤፌ.4፡8 ላይ የጠቀሰውም ይህንኑ ቃል ነው፤ በዚህ ቃል ውስጥ «ወደ ላይ በወጣ ጊዜ» የሚለው ጌታችን ከሞት ከተነሣ በኋላ በ40ኛው ቀን ወደ ላይ ወደ አባቱ ያረገበትን ጊዜ ያመለክታል፡፡ ይህም የሚታወቀው ከቊ.9-10 ላይ «ወደ ምድር ታችኛው ክፍል ደግሞ ወረደ ማለት ካልሆነ ይህ ወጣ ማለትስ ምን ማለት ነው? ይህ የወረደው ሁሉን ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ ያው ነው» ተብሎ በተጻፈው ቃል ነው፡፡
ጌታ ወደ ላይ በወጣ ጊዜም ምርኮን የማረከ ድል አድራጊ ሆኖ ነበር የወጣው፡፡ ምርኮውም ሌላ ምንም ሳይሆን በጨለማ ሥልጣን ሥር ሆኖ በሞት ፍርሃት ተይዞ በዲያብሎስ እየተገዛ ይኖር የነበረ ሕዝብ ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ሞትን ድል አድርጎ በተነሣ ጊዜ ዲያብሎስ ሰዎችን የሚያስፈራራበት የሞት ኃይል የተሻረ በመሆኑ ብዙ ምርኮን ሊያገኝ ችሏል፡፡ ይህም በኋላ የትንሣኤው ምስክሮች በሰበኩት ወንጌል ብዙዎች ወደ ኢየሱስ በመፍለሳቸው ተረጋግጧል፡፡ እንዲህ ያለው ብዙ ምርኮን የማረከ ድል አድራጊ ደግሞ ለሕዝቡ የሚሰጠው ብዙ ነገር ይኖረዋል፤ በመሆኑም ኢየሱስ ወደ ላይ ከወጣና በአባቱ ቀኝ በክብር ከተቀመጠ በኋላ ለሰዎች ስጦታን ሊሰጥ ችሏል፡፡
«እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፣ ሌሎቹም ነቢያት፣ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ» (ኤፌ.4፡11)፡፡
የቤተክርስቲያን ራስ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ የስጦታዎች ባለቤት እንደመሆኑ መጠን ለሰዎች ስጦታን ይሰጣል፤ እርሱ ለአማኞች በየግላቸው የሚያገለግሉበትን ጸጋ ይሰጣል፤ እንዲሁም ስጦታዎችን ለእያንዳንዱ አማኝ ከመስጠት ባሻገር የጸጋ ስጦታ የሰጣቸውን ሰዎችንም ለቤተክርስቲያን ስጦታ አድርጎ ይሰጣል፡፡ በዚህ በቊ.11 ላይ የተዘረዘሩት አምስቱ ስጦታዎችም ወደ ላይ ያረገውና ራስ የሆነው ክርስቶስ ለቤተክርስቲያን የሰጣቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ሐዋርያት፣ ነቢያት፣ ወንጌል ሰባኪዎች፣ እረኞችና አስተማሪዎች ሲል በፊት በየግላቸው የሐዋርያነት፣ የነቢይነት፣ የወንጌል ሰባኪነት፣ የእረኝነትና የአስተማሪነት ስጦታዎችን ከክርስቶስ የተቀበሉ ሰዎችን ያመለክታል፤ ከዚያ በኋላ ኢየሱስ እነዚህን ሰዎች ራሳቸውን ለቤተክርስቲያን ሰጥቷል፡፡
እነዚህ አምስት ስጦታዎች ለመላይቱ ቤተክርስቲያን የተሰጡት የስጦታዎቹ ባለቤት በሆነው በራሱ በጌታ ኢየሱስ ብቻ መሆኑን በትኩረት ማስተዋል ይገባል፡፡ ይሁንና ይህን ካለማስተዋል የተነሣ እነዚህ ስጦታዎች የቤተክርስቲያን ባለሥልጣናት የሚባሉ ሰዎች የሚሾሟቸው አገልጋዮች ተደርገው በብዙዎች ዘንድ ይታሰባሉ፤ እንደዚሁም እነዚህ አምስት ስጦታዎች ልክ በሌሎች የሥራ መስኮች እንደሚሰማሩ ሰዎች ከተለያዩ የቲዎሎጂ ተቋማት የተመረቁና በሐዋርያነት፣ በነቢይነት፣ በወንጌላዊነት፣ በእረኝነት (በፓስተርነት) እና በአስተማሪነት ሥራ ተቀጥረው በሠራተኝነት የሚያገለግሉ ሰዎችን እንዲያመለክቱም ተደርገዋል፤ ይህም በየስፍራው ከሚገኙ ቅርንጫፍ አጥቢያዎች ለወንጌላዊነትም ሆነ ለፓ¬ስተርነት ሰዎች ከተመለመሉ በኋላ ከበላይ አካላት በወጡ መመዘኛዎች ተወዳድረው ያለፉት ወደ ማሠልጠኛ ተቋማት እንዲገቡ የሚደረጉበት፣ እንዲሁም ከዚያ በኋላ እንደ አንድ የሥራ መስክ (ፊልድ) በወንጌላዊነት ወይም በ¬ስተርነት የሚመረቁበትና በዚያም ባገኙት ዲፕሎማ (ዲግሪ) መሠረት በተለያዩ ወረዳዎች ከተሞችና አጥቢያዎች በማዕርጋቸው ተሹመው የሚመደቡበት አሠራር እነዚህ አምስቱ ስጦታዎች ጌታ ለቤተክርስቲያን የሚሰጣቸው ስጦታዎች መሆናቸውን በተግባር የሚክድ አሠራር ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ እንደማንኛውም የቢሮ ሠራተኛ በአንድ ወቅት ወንጌላዊ የነበረ ሰው በዕድገት በሌላ ጊዜ ፓስተር ወይም ምክትል ¬ፓስተር ወይም ደግሞ እንደ ሁኔታው እየታየ ሐዋርያም ተብሎ እየተሾመ በሥልጣን ከፍ የሚደረግበት ከዚህም ጋር የሚያገኛቸው ጥቅማ ጥቅሞች (ነውረኛ ረቦች) የሚያድጉበት ወይም ደግሞ በተቃራኒው በአንድ ወቅት ፓ¬ስተር የነበረው ተሽሮ በምትኩ ከበላይ አካላት በደብዳቤ ሌላ የሚሾምበት አሠራር በባሕርዩ ፍጹም ዓለማዊ ከመሆኑም ሌላ በሰማይ ያለው የቤተክርስቲያን ራስ እርሱ ራሱ የሚያስፈልጉንን የቃሉን አገልጋዮች እንደሚሰጥ ካለማመን ወይም የእርሱን ስጦታ ወደ ጐን ከመተው የሚመጣ አሠራር ነው፡፡ ነገር ግን በሰማይ ያለው የቤተክርስቲያን ራስ ጌታ ኢየሱስ ዛሬም አካሉ ለምትሆን ቤተክርስቲያን የሚያስፈልጓትን ሰዎች እንደሚሰጣት የሚያምኑ ሁሉ እነዚህ ሰዎች በመካከላቸው በሂደት በጸጋቸው ሲገለጡና ጌታም በድንቅ ሲጠቀምባቸው ያያሉ፡፡
ጌታ ለቤተክርስቲያኑ ስለሚሰጣቸው ስጦታዎች በተለይም ስለ 5ቱ ስጦታዎች በጥቅሉ ይህንን ያህል ካልን አሁን ደግሞ አምስቱን ስጦታዎች እያንዳንዳቸውን በዝርዝር ማየት እንጀምራለን፡፡ አንባቢውም አሁን በተለምዶ እየተሠራበት ካለው ሥርዓት አንጻር ሳይሆን የእግዚአብሔር ቃል ከሚናገረው እውነት አንጻር ብቻ ስለ እነዚህ ስጦታዎች የሚያነበውን ሁሉ በትዕግሥት እየመረመረ እንዲያጠና በፍቅር ይጠየቃል፡፡
1. ሐዋርያት
ሐዋርያ የሚለው ቃል በግሪክ ቋንቋ «አፖስቶሎስ» የሚል ሲሆን ትርጉሙም «የተላከ» ማለት ነው፡፡ የተላከ ሲባልም ላኪውን በመወከል የላኪውን መልእክት ብቻ በትክክል የሚያስተላልፍ መልእክተኛ ማለት ነው፡፡ ቃሉ በግሪክ ቋንቋ ውስጥ ማንኛውንም ዓይነት መልእክተኛ የሚያመለክት ቢሆንም በዋናነትና በመደበኛነት የሚያገለግለው ግን እግዚአብሔር የላካቸውን ብቻ ነው፡፡
የሃይማኖታችን (የእምነታችን) ሐዋርያ
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በተመለከተ «... የሃይማኖታችንን (የእምነታችንን) ሐዋርያና ሊቀካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልከቱ» የሚል ቃል እናነባለን (ዕብ.3፡1)፤ ይህም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ በሰውነቱ ሐዋርያ እንደሆነ የሚናገር ቃል ነው፡፡ በእርግጥም እርሱ ስለራሱ ሲናገር «... እኔንም ታውቁኛላችሁ፤ ከወዴትም እንደሆንሁ ታውቃላችሁ፤ እኔም በራሴ አልመጣሁም፤ ነገር ግን እናንተ የማታውቁት የላከኝ እውነተኛ ነው፤ እኔ ግን ከእርሱ ዘንድ ነኝ፤ እርሱ ልኮኛልና አውቀዋለሁ» በማለት እና «እርሱ ላከኝ እንጂ ከራሴ አልመጣሁምና» በማለት ከአብ ዘንድ የተላከ መሆኑን በግልጽ ተናግሯል (ዮሐ.7፡28፤ 8፡42)፡፡ እርሱ በሰውነቱ የሚናገረውም ሆነ የሚያደርገው ሁሉ ከአብ የሰማውንና አብን ደስ የሚያሰኘውን ብቻ ነበር፤ ይህንንም ሲገልጽ «... ዳሩ ግን የላከኝ እውነተኛ ነው፤ እኔም ከእርሱ የሰማሁትን ይህን ለዓለም እናገራለሁ፤ .... አባቴም እንዳስተማረኝ እነዚህን እናገር ዘንድ እንጂ ከራሴ አንዳች እንዳላደርግ በዚያን ጊዜ ታውቃላችሁ፤....» (ዮሐ.8፡26-30) ብሏል፤ እንደዚሁም በሌላ ስፍራ «እኔ ከራሴ አልተናገርሁምና፤ ነገር ግን የላከኝ አብ የምለውን የምናገረውንም ትእዛዝ ሰጠኝ፤ ትእዛዙም የዘላለም ሕይወት እንደሆነች አውቃለሁ፤ ስለዚህ እኔ የምናገረውን አብ እንደነገረኝ እንዲሁ እናገራለሁ» ብሎ የተናገረውን ቃል እናነባለን (ዮሐ.12፡49-50)፡፡ ስለዚህ ከእነዚህ ሁሉ ቅዱሳን ቃላት ጌታ ኢየሱስ በአባቱ የተላከ፣ ከአባቱ የተቀበለውን መልእክት የተናገረ፣ በሰውነቱ ከራሱ ምንም ያላደረገና ያልተናገረ፣ የላኪውን ፈቃድና መልእክት ብቻ ያስተላለፈ የመጀመሪያው ሐዋርያ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ይህንንም የሐዋርያነቱን ሥራ የሠራው በምድር ላይ በሥጋ ሲመላለስ ሳለ በነበረው የማስተማር ዘመኑ ነው፤ በገሊላ፣ በሰማርያና በይሁዳ እየተመላለሰ ያስተማረው ትምህርት ሁሉ የሐዋርያነቱ መልእክት ነበር፤ በእርሱ የነቢይነት አገልግሎትንም የምናይ ቢሆንም የሐዋርያነት አገልግሎቱ ከዚያ ይልቅ ጐልቶ ይታይ ነበረ፤ ይህም የሐዋርያነቱ አገልግሎት በሰውነቱ የሚከናወን በመሆኑ በብዙ ምልክቶችና ድንቆች የጸና ነበር፡፡ ጴጥሮስ ለእስራኤል ሰዎች ሲናገር «ራሳችሁ እንደምታውቁ የናዝሬቱ ኢየሱስ እግዚአብሔር በመካከላችሁ በእርሱ በኩል ባደረገው ተአምራትና በድንቆች በምልክቶችም ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእናንተ የተገለጠ ሰው ነበረ» ብሎ ስለኢየሱስ መስክሯል (የሐ.ሥ.2፡22)፤ ይህ በእርሱ የተደረገው ምልክት እርሱ ከአብ የተላከ ሐዋርያ መሆኑን አረጋግጦለታል፡፡ የእርሱ የሐዋርያነቱ መልእክቶችና ሥራዎች ሁሉ በ4ቱ ወንጌላት ተመዝግበውልናል፤ በመሆኑም በምድር ላይ ሲመላለስ በፍጹም ሐዋርያነቱ በታማኝነት የአባቱን መልእክት ወደ ሰው ያደረሰውን የእርሱን መልእክት በአግባቡ እንረዳው ዘንድ እንትጋ፡፡
አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከአብ የተላከ ሐዋርያ ሆኖ የተገለጠ ሰው ነበር፤ ነገር ግን እርሱ የመጀመሪያው ሐዋርያ ብቻ ሳይሆን ሐዋርያትን መምረጥና መላክ የሚቻለው ጌታም ነበር፡፡ የእርሱ የሐዋርያነት አገልግሎቱ የሚያበቃበት ጊዜ እንደሚኖር ስለሚያውቅ ከደቀመዛሙርቱ መካከል አሥራ ሁለት ደቀመዛሙርት መርጦ ሐዋርያት አድርጎ ሲሾማቸውና ሲልካቸው እንመለከታለን፡፡ ይህንንም ያደረገው በእነርሱ ጥያቄ ወይም ፍላጎት መሠረት ሳይሆን ወይም የእነርሱን ማንነት እየተመለከተ የተሻሉትን በመምረጥ ሳይሆን ራሱ የወደዳቸውን ወደ ራሱ ጠርቶ በመለየት ነበር፤ ቊጥራቸውንም 12 ያደረገው በራሱ ውሳኔ ነበር፡፡ ይህንንም ማርቆስ ሲጽፍ «ወደ ተራራም ወጣ፤ ራሱም የወደዳቸውን ወደ እርሱ ጠራ፤ ወደ እርሱም ሄዱ፤ ከእርሱም ጋር እንዲኖሩና ለመስበክ እንዲልካቸው ድውዮችንም ሊፈውሱ አጋንንትንም ሊያወጡ ሥልጣን ይሆንላቸው ዘንድ አሥራ ሁለት አደረገ» በማለት ይገልጻል (ማር3፡13-15)፡፡ ጌታ ኢየሱስ ከደቀመዛሙርቱ መካከል እነዚህን 12ቱን ከለየ በኋላ «ሐዋርያት» ብሎ ሰይሟቸው ነበር፤ ይህንንም ሉቃስ በወንጌሉ ሲጽፍ «በእነዚህም ወራት ይጸልይ ዘንድ ወደ ተራራ ወጣ፤ ሌሊቱንም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ አደረ፡፡ በነጋም ጊዜ ደቀመዛሙርቱን ጠራ፤ ከእነርሱም አሥራ ሁለት መረጠ፤ ደግሞም ሐዋርያት ብሎ ሰየማቸው፡፡» ብሏል (ሉቃ6፡12-13)፡፡ «ሐዋርያት» ብሎ የሰየመው እነዚህ 12ቱን ብቻ ነው፡፡ ከእነዚህ ከ12ቱ ሌላ ሌሎችን ሰብዓ እንደሾመ ሉቃስ ይነግረናል (ሉቃ10፡1)፤ ሆኖም ሐዋርያት ብሎ አልሰየማቸውም ነበር፡፡ በመሆኑም ጌታ ኢየሱስ ለአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት የሰጠው ስፍራ ለየት ያለ ሲሆን የሐዋርያነት ሥራውን እንዲሠሩም ለየት ያለ ሥልጣን እንደሰጣቸው እንረዳለን፡፡
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከአብ የተላከ ሐዋርያ ሆኖ የተገለጠ ሰው ነበር፤ ነገር ግን እርሱ የመጀመሪያው ሐዋርያ ብቻ ሳይሆን ሐዋርያትን መምረጥና መላክ የሚቻለው ጌታም ነበር፡፡ የእርሱ የሐዋርያነት አገልግሎቱ የሚያበቃበት ጊዜ እንደሚኖር ስለሚያውቅ ከደቀመዛሙርቱ መካከል አሥራ ሁለት ደቀመዛሙርት መርጦ ሐዋርያት አድርጎ ሲሾማቸውና ሲልካቸው እንመለከታለን፡፡ ይህንንም ያደረገው በእነርሱ ጥያቄ ወይም ፍላጎት መሠረት ሳይሆን ወይም የእነርሱን ማንነት እየተመለከተ የተሻሉትን በመምረጥ ሳይሆን ራሱ የወደዳቸውን ወደ ራሱ ጠርቶ በመለየት ነበር፤ ቊጥራቸውንም 12 ያደረገው በራሱ ውሳኔ ነበር፡፡ ይህንንም ማርቆስ ሲጽፍ «ወደ ተራራም ወጣ፤ ራሱም የወደዳቸውን ወደ እርሱ ጠራ፤ ወደ እርሱም ሄዱ፤ ከእርሱም ጋር እንዲኖሩና ለመስበክ እንዲልካቸው ድውዮችንም ሊፈውሱ አጋንንትንም ሊያወጡ ሥልጣን ይሆንላቸው ዘንድ አሥራ ሁለት አደረገ» በማለት ይገልጻል (ማር3፡13-15)፡፡ ጌታ ኢየሱስ ከደቀመዛሙርቱ መካከል እነዚህን 12ቱን ከለየ በኋላ «ሐዋርያት» ብሎ ሰይሟቸው ነበር፤ ይህንንም ሉቃስ በወንጌሉ ሲጽፍ «በእነዚህም ወራት ይጸልይ ዘንድ ወደ ተራራ ወጣ፤ ሌሊቱንም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ አደረ፡፡ በነጋም ጊዜ ደቀመዛሙርቱን ጠራ፤ ከእነርሱም አሥራ ሁለት መረጠ፤ ደግሞም ሐዋርያት ብሎ ሰየማቸው፡፡» ብሏል (ሉቃ6፡12-13)፡፡ «ሐዋርያት» ብሎ የሰየመው እነዚህ 12ቱን ብቻ ነው፡፡ ከእነዚህ ከ12ቱ ሌላ ሌሎችን ሰብዓ እንደሾመ ሉቃስ ይነግረናል (ሉቃ10፡1)፤ ሆኖም ሐዋርያት ብሎ አልሰየማቸውም ነበር፡፡ በመሆኑም ጌታ ኢየሱስ ለአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት የሰጠው ስፍራ ለየት ያለ ሲሆን የሐዋርያነት ሥራውን እንዲሠሩም ለየት ያለ ሥልጣን እንደሰጣቸው እንረዳለን፡፡
በአራቱ ክፍሎች የተመዘገበው የስም ዝርዝር በቅደም ተከተል አንድ ባይሆንም በዝርዝሩ ውስጥ የተመዘገቡት ሐዋርያት ግን በ4ቱም ክፍሎች ውስጥ እነዚያው ራሳቸው ናቸው፤ «ታዴዎስ የተባለው ልብድዮስ» በሉቃስ ወንጌል «የያዕቆብ ይሁዳ»፣ በሐዋርያት ሥራ ደግሞ «የያዕቆብ ልጅ ይሁዳ» የተባለው ነው፤ አንዳንድ ትርጉሞች ይህን ሐዋርያ በሉቃስ ወንጌልና በሐዋርያት ሥራ ላይ «የያዕቆብ ወንድም ይሁዳ» ይሉታል፡፡ እንዲሁም በማቴዎስና በማርቆስ «ቀነናዊው ስምዖን» የተባለው በሉቃስና በሐዋርያት ሥራ «ቀናተኛ የሚባለው ስምዖን» ብሎ የተገለጠው ነው፡፡
በሐ.ሥራ1፡13 ላይ የተዘረዘሩት ሐዋርያት 11ዱ ብቻ መሆናቸውና 12ኛው የሐዋርያነት ስፍራ ክፍት የነበረው ጌታን አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ ስላልተቆጠረ ነው፡፡ የአስቆሮቱ ይሁዳ ከሐዋርያት ጋር ተቆጥሮ ለዚህ አገልግሎት ታድሎ የነበረ ቢሆንም ጌታን አሳልፎ በመስጠቱ ወደ ገዛ ራሱ ስፍራ ይሄድ ዘንድ የሐዋርያነት ስፍራውን ትቶ ሄደ (የሐ.ሥራ1፡17 እና 25)፤ ሆኖም በምትኩ ማትያስ ከአሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋር ተቈጥሮአል (የሐ.ሥራ1፡26)፤ ከዚህ በኋላ በሐዋርያት ሥራ ውስጥም ሆነ ቀጥሎ ባሉት በሌሎች የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ አሥራ ሁለቱን ሐዋርያት የሚጠቅስ ንባብ ሲገኝ ማትያስን በመቊጠር እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አሥራ ሁለቱን ሐዋርያት ከመጀመሪያው ሲመርጣቸውና ሲሾማቸው ዓላማው ከእርሱ ጋር እንዲኖሩና ለመስበክ እንዲልካቸው ነበር (ማር.3፡14)፡፡ ወደ ዓለም ሁሉ ከመላኩ በፊት እርሱ በምድር እያለ የላካቸው ከእስራኤል ወደ ጠፉት በጎች ብቻ ነበር፤ ይህንንም ሲገልጽ አሥራ ሁለቱን ባሰማራቸው ጊዜ ሲያዝዛቸው «በአሕዛብ መንገድ አትሂዱ፤ ወደ ሳምራውያንም ከተማ አትግቡ፤ ይልቅስ ከእስራኤል ቤት ወደሚሆኑት ወደ ጠፉት በጎች ሂዱ» ብሏቸዋል (ማቴ10፡5-6)፡፡ ሄደው የሚሰብኩትም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሲሆን ዋና ይዘቱም «መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች» የሚል ነበር (ማቴ.10፡7፤ ሉቃ.9፡2)፡፡ የላካቸውም ሁለት ሁለት አድርጎ ነበር (ማር.6፡7)፤ በርኩሳን መናፍስትና በበሽታ ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቷቸውም ነበር፡፡ አገልግሎታቸውን የሚፈጽሙትም እንዴት እንደሆነ መመሪያ ከሰጣቸው በኋላ ላካቸው (ማቴ.10፡5-42)፡፡ ሐዋርያትም በታዘዙት መሠረት አገልግሎታቸውን ፈጽመው ወደ እርሱ ከተመለሱ በኋላ ያደረጉትን ሁሉ ለኢየሱስ ነገሩት (ሉቃ.9፡10)፡፡ ጌታ ኢየሱስም ቢሆን ለእስራኤል የመንግሥትን ወንጌል ይሰብክ ነበር፤ ይሁንና እስራኤላውያን እርሱን በመሢሕነት ካለመቀበላቸውም የተነሣ የሰበከውን የመንግሥት ወንጌል አልተቀበሉም ነበር፤ በዚህም ምክንያት እስራኤል ለጊዜው ወደ ጐን ከተተወች በኋላ የእግዚአብሔር የጸጋ በር ለአሕዛብ ተከፈተ፤ የክርስቶስ ሞት እና ትንሣኤም ለዓለም ሁሉ የመዳን መንገድ ሆነ፡፡ ጌታ ከትንሣኤው በኋላ በአንድ ላይ ለነበሩት 11ዱ ሐዋርያት ሊያርግ ሲል ወደ ዓለም ሁሉ ሄደው እንዲሰብኩ ሲልካቸው እንመለከታለን፤ በማቴ.28፡19 ላይ እንደምናነበው «እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋችው ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀመዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆ እኔ እስከዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ» ብሏቸዋል፤ እንደዚሁም በማር.16፡15 «ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ» ብሎ የሰጣቸውን መመሪያ እናነባለን፡፡ ይህም እግዚአብሔር ከአሕዛብ መካከል ለስሙ የሚሆን ወገንን ለመውሰድ የሚያስችለውን መንገድ ይከፍታል፤ ከዚያ በፊት ግን ኢየሱስ ከእነርሱ ሲለይ በምትኩ የሚመጣውን አጽናኝ የሆነውን መንፈስ ቅዱስን መጠበቅ ነበረባቸው፤ ስለሆነም ከመሰማራታቸው በፊት ለሥራቸው ኃይል የሚሆናቸውን መንፈስ ቅዱስን በኢየሩሳለም ሆነው እንዲጠብቁ አዘዛቸው (ሉቃ.2፡49)፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ምስክርነታቸው በእስራኤል ብቻ ሳይሆን እስከምድር ዳር ድረስ እንደሚሆን ሲነግራቸው «...ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ» ብሏቸዋል (የሐ.ሥራ1፡8)፡፡ በዚህም መሠረት ሐዋርያት በመንፈስ ቅዱስ መውረድ ኃይልን ተቀብለው ለእስራኤልና ለአሕዛብ በሰበኩት ወንጌል ከሁለቱ አንድ አዲስ ሰው (አካል) ተፈጠረ ወይም ተመሠረተ (ኤፌ.2፡15)፡፡ ያም አንድ አካል ሌላ ምንም ሳይሆን ቤተክርስቲያን ናት (ኤፌ.1፡23፤ ቈላ.1፡18)፡፡
በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ 12ቱ ሐዋርያት በመጀመሪያ በእስራኤል ምድር በኢየሩሳሌምና በዙሪያዋ ሲያገለግሉ እናገኛቸዋለን፤ በበዓለ ሃምሳ ዕለት ጴጥሮስ ከአሥራ አንዱ ጋር ቆሞ ስለክርስቶስ ሲመሰክር እንደነበር እናያለን (2፡14)፤ ቤተክርስቲያን ከተመሠረተችበት ከዚህ ዕለት ጀምሮ የመጀመሪያዎቹ አማኞች ከሚተጉባቸው ነገሮች ዋናው «የሐዋርያት ትምህርት» ነበር (2፡42)፤ ሐዋርያት በኢየሩሳሌም ሳሉ «የጌታን የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ በታላቅ ኃይል ይመሰክሩ ነበር፤ በሁሉም ላይ ታላቅ ጸጋ ነበረባቸው» (4፡33)፤ አማኞች ከመሬትና ከቤት ሽያጭ የሚያገኙትን ገንዘብ በሐዋርያት እግር አጠገብ ያስቀምጡ ነበር (4፡34፣37፤ 5፡2)፤ በሐዋርያትም እጅ ብዙ ምልክትና ድንቅ በሕዝብ መካከል ይደረግ ነበር (5፡12)፤ ይህም የጌታ ሐዋርያት እንደሆኑ ለሕዝቡ የሚመሰክር ነበር፡፡ በአንድ ላይም ከሚሰጡት የወንጌል ምስክርነት የተነሣ በአንድ ላይ ወደ ወኅኒ ይጣሉ ነበር (5፡18)፤ በኢየሱስ ስም እንዳያስተምሩ ሲታዘዙ ጴጥሮስና ሐዋርያት «ከሰው ሁሉ ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባናል» ይሉ ነበር (4፡19፤ 5፡29)፡፡ ዕለት ዕለትም በመቅደስና በቤታቸው ስለ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ ማስተማርንና መስበክን አይተውም ነበር (5፡42)፡፡ በኢየሩሳሌም ባለች ቤተክርስቲያን ለነበረው የማዕድ አገልግሎት ሰባት ሰዎችን አስመርጠው እንደሾሙም እናነባለን፤ ስለራሳቸውም «እኛ ግን ለጸሎትና ቃሉን ለማገልገል እንተጋለን» ብለዋል (የሐ.ሥራ6፡1-6)፡፡ ይህም ሐዋርያት በመጀመሪያ አካባቢ ቤተክርስቲያንን የማስተዳደሩም ሆነ የጸሎትና የቃሉ አገልግሎት በእነርሱ ላይ እንደ ነበረና በኋላ ግን በጸሎትና በቃሉ አገልግሎት ብቻ ሊተጉ ባሉ ጊዜ ሌላውን አገልግሎት ወደ ሌሎች ወንድሞች እንዳስተላለፉ እናያለን፡፡
ሐዋርያት በኢየሩሳሌም እያሉ ከእነርሱ ቀጥሎ ጌታ በሐዋርያነት የሾመውን በኋላ ጳውሎስ የተባለው ሳውልን በበርናባስ አማካኝነት እንደተዋወቁና እንደተቀበሉት እናነባለን (የሐ.ሥራ9፡27)፡፡ ከዚያም በዚያው በእስራኤል አገር ማለትም በይሁዳ ሁሉና በገሊላ በሰማርያም ስለነበሩ አብያተክርስቲያናት መታነጽና መብዛት ስለምናነብ (9፡31) ሐዋርያት በዚያው በምድረ እስራኤል የሠሩት የሐዋርያነት ሥራ ምን ያህል ሰፊ እንደነበር እንገነዛባለን፡፡ ከሐዋርያት መካከል ጴጥሮስ በየስፍራው ሲዞር በልዳና በሰሮና በኢዮጴም ወንጌልን እየሰበከ ሳለ እግዚአብሔር ለአሕዛብ የመዳን ወንጌል የሚደርስበትን መንገድ አዘጋጀ፤ በቂሣርያ የነበረ ቆርኔሌዎስ የሚሉት አንድ መቶ አለቃ ከዘመዶቹና ከቅርብ ወዳጆቹ ጋር ሆኖ ጴጥሮስ ስለክርስቶስ የመሰከረላቸውን ቃል ሲሰሙ በሁሉም ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ፤ ይህም ልክ በመጀመሪያ የበዓለ ሃምሳ ዕለት እንደወረደው ያለ ሲሆን አሕዛብ ወደ ክርስቶስ አካል በመንፈስ ቅዱስ የተጠመቁበት ጊዜ ነበር (10፡40-48፤ 11፡15-18፤ 15፡7፤ 1ቆሮ12፡13)፡፡ ሐዋርያትና በይሁዳ የነበሩት ወንድሞች አሕዛብ የእግዚአብሔርን ቃል እንደተቀበሉ በሰሙ ጊዜ ጴጥሮስ ወደ አሕዛብ ቃሉ ይደርስ ዘንድ እግዚአብሔር እርሱን የመራው እንዴት እንደነበርና መንፈስ ቅዱስም እንዴት እንደወረደላቸው ሲተርክላቸው እግዚአብሔርን አከበሩ (11፡1-18)፤ ከዚህም በተጨማሪ ሐዋርያት በጳውሎስና በበርናባስ ወንጌል ለአሕዛብ እንዴት እንደደረሰ ከራሳቸው ከጳውሎስና ከበርናባስ ሰምተዋል፤ እንዲያው አሕዛብን «እንደ ሙሴ ሥርዓት ካልተገረዛችሁ ትድኑ ዘንድ አትችሉም» በሚለው የስህተት ትምህርት ምክንያት ሐዋርያት ከሽማግሌዎች ጋር በመሰብሰብ እንደ እግዚአብሔር ቃል ተመካክረው የአሕዛብን ወደ ቤተክርስቲያን መግባት በይፋ የሚያረጋግጥ ውሳኔ ላይ ደርሰዋል፡፡ «እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናል» በሚለው የውሳኔያቸው ቃል የምንረዳው እነርሱ የሚሠሩትም ሆነ የሚወስኑት ሙሉ በሙሉ በመንፈስ ቅዱስ ምሪትና ኃይል እንደሆነ ነው (የሐ.ሥራ15፡1-29)፡፡ ከዚህ በኋላ ውሳኔውን ይዘው ወደ አንጾኪያ የሄዱት ወንድሞች አያሌ ቀን ተቀምጠው እስኪመለሱ ድረስ ሐዋርያት በኢየሩሳሌም እንደነበሩ ለማወቅ እችላለን (15፡33)፡፡ ከዚህ አስቀድሞ ግን ከሐዋርያት መካከል የዮሐንስ ወንድም ያዕቆብ በሄሮድስ ሰይፍ ተገድሏል (12፡2)፤ ጴጥሮስም በወኅኒ ታስሮ የነበረ ቢሆንም ጌታ ከእስር ቤት አወጣው፤ ከዚያም በቤተክርስቲያን ስለ እርሱ ይጸልዩ ለነበሩት ጌታ ከወኅኒ እንዴት እንዳወጣው ከተረከላቸው በኋላ ወጥቶ ወደ ሌላ ስፍራ ሄዶ ነበር (12፡3-17)፤ ይሁንና በሐ.ሥራ15 ላይ በምናነበው አሕዛብን በተመለከተ በነበረው የሐዋርያት ስብሰባ ላይ ተገኝቶ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ሐዋርያት በአንድ ላይ ሆነው ሥራ ሲሠሩ የሚገልጽ ንባብ አናገኝም፡፡
ከዚህ በኋላ እያንዳንዳቸው የተሰማሩባቸውን ስፍራዎችና የሠሩአቸውን ሥራዎች እንዲሁም የእያንዳንዳቸው ፍጻሜ ምን እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ የምናውቀው ነገር የለም፤ ሆኖም የወደፊት ክብራቸውን በሚገባ እናውቃለን፤ ጴጥሮስ ጌታ ኢየሱስን «እነሆ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ፤ እንኪያስ ምን እናገኝ ይሆን?» ብሎ በጠየቀው ጊዜ «እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ እናንተስ የተከተላችሁኝ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ እናንተ ደግሞ በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በአሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ» የሚል የከበረ ተስፋን ተቀብሏል (ማቴ19፡27-28)፤ ይህም ጌታ በሺው ዓመት የክብር መንግሥት ጊዜ ለሐዋርያት የሚሰጠውን የተለየ ዙፋንና ክብር ያመለክታል፡፡ በራእ.21፡14 ላይ የእግዚአብሔር ክብር ላለባት ለቅድስቲቱ ከተማ ለአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ባሏት አሥራ ሁለት መሠረቶች ላይ አሥራ ሁለቱ የበጉ ሐዋርያት ስሞች ተጽፈው እንደ ነበር ይናገራል፤ 12ኛው ስምም በይሁዳ ፈንታ የተተካው የማትያስ ስም እንደሆነ ጥርጥር የለውም፡፡ ይህም በሺው ዓመት መንግሥት ከክርስቶስ ጋር አብራ በምትነግሠውና በምትገዛው ቤተክርስቲያን ውስጥ ያላቸውን የመሠረት (ዋነኛ የሆነ) ስፍራ ያመለክታል፡፡
የጳውሎስ ሐዋርያነት
ጌታ ኢየሱስ ካረገና በክብር በአብ ቀኝ ከተቀመጠ በኋላ ሐዋርያ አድርጎ የሾመው ጳውሎስን ብቻ ነው፡፡ ጳውሎስ የቀድሞ ስሙ ሳውል ይባል የነበረ ሲሆን ክርስቶስን ከማመኑ በፊት ቤተክርስቲያንን ያለልክ የሚያሳድድ ከብንያም ነገድ የሆነ አይሁዳዊ ሕግንም ከሁሉ አስበልጦ የሚያጠብቅ ፈሪሳዊ ነበር (የሐ.ሥራ8፡3፤ 26፡9-11፤ ገላ.1፡13-14፤ ፊልጵ.3፡5-6)፤ ነገር ግን ይህን ያደርግ የነበረው ባለማወቅ ነበር (1ጢሞ.1፡13)፤ እንዲያውም የናዝሬቱን ኢየሱስን ስም የሚቃወም እጅግ ነገር ያደርግ ዘንድ የሚገባው ይመስለው ነበር (የሐ.ሥራ26፡9)፤ በዚያን ጊዜ እርሱ ለእግዚአብሔር ቀናተኛ የነበረ አይሁዳዊ ሰው ነበር (የሐ.ሥራ22፡3)፤ ቤተክርስቲያንን ማሳደዱም ለእግዚአብሔር ካለው ቅንዓት የተነሣ ነበር (ፊልጵ.3፡6፤ የሐ.ሥራ22፡3)፡፡ በዚህ ዓይነት የጌታን ደቀመዛሙርት ለማሳደድ ወደ ደማስቆ በመሄድ ላይ ሳለ በሰማይ የከበረው የናዝሬቱ ኢየሱስ በመንገድ ላይ በክበር ታየው (የሐ.ሥራ9፡1-9)፤ ጌታ ለሳውል በክብር የታየበት ምክንያት ሳውል በእርሱ እንዲያምን ለመጥራት ብቻ ሳይሆን ለአገልግሎት ሊሾመውም ነበር፡፡ ይህንንም ራሱ ሲነግረው «ስለዚህ እኔን ባየህበት ነገር ለአንተም በምታይበት ነገር አገልጋይና ምስክር ትሆን ዘንድ ልሾምህ ታይቼልሃለሁና» ብሎታል (የሐ.ሥራ26፡16)፡፡ ስለሆነም ጳውሎስ ለአገልግሎት የተሾመው በቀጥታ በራሱ በጌታ በኢየሱስ ነው፡፡ በዚህ ነገር ጳውሎስ ጌታን ሲያመሰግን «ለአገልግሎቱ ሾሞኝ ታማኝ አድርጎ ስለቈጠረኝ ኃይል የሰጠኝን ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታችንን አመሰግናለሁ» ብሏል (1ጢሞ.1፡12)፡፡ አገልግሎቱም የሐዋርያነት አገልግሎት ነው፤ ጳውሎስ ጌታ በደማስቆ በታየው ዕለት የተጠራው አማኝ እንዲሆን ብቻ ሳይሆን ሐዋርያ እንዲሆንም ነው፤ እርሱ በሮሜ1፡1 ላይ ስለራሱ ሲጽፍ «ሐዋርያ ሊሆን የተጠራ...» ብሏል፡፡ ስለዚህ ጥሪው ለማመን ብቻ ሳይሆን ለሐዋርያነትም ነበር፡፡ ጌታ ለየት ባለ ሰማያዊ ክብሩ ሊታየው ያስፈለገውም ለሐዋርያነት አገልግሎት ሊሾመው ስለወደደ ነው እንጂ ለማመን ብቻ ቢሆን ኖሮ እንደማንኛውም ሰው ሊያምን የሚችልበት ሌላ ብዙ መንገድ ነበር፡፡ ጌታም የሾመው በዋናነት የአሕዛብ ሐዋርያ አድርጎ ነበር፡፡ ይህንንም ራሱ ሲገልጥ «ለተገረዙት ሐዋርያ እንዲሆን ለጴጥሮስ የሠራለት ለእኔ ደግሞ ለአሕዛብ ሐዋርያ እንድሆን ሠርቷልና» ብሏል (ገላ.2፡8)፤ በሮሜ11፡14 ላይም «እኔ የአሕዛብ ሐዋርያ እንደመሆኔ መጠን...» እያለ ሲጽፍ እናገኛለን፡፡ በክርስቶስ አካል ውስጥ አሕዛብ የመግባታቸው ምስጢርም የተገለጠው ለዚሁ የአሕዛብ ሐዋርያ ለሆነው ለጳውሎስ ነው (ኤፌ.3፡1-9)፡፡ ከመጀመሪያም ቢሆን ጌታ ሲልከው «ሂድ እኔ ወደ አሕዛብ ከዚህ ወደ ሩቅ እልክሃለሁና» ብሎት ነበር (የሐ.ሥራ22፡21)፡፡
ጳውሎስ ለጌታ «የተመረጠ ዕቃ» ነው፡፡ ይህንንም ጌታ ለሐናንያ ሲነግረው «ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነው» ብሏል (የሐ.ሥራ9፡15)፡፡ ስለሆነም ጳውሎስ ለጌታ ልዩ ሐዋርያ ነው ማለት ይቻላል፤ በእርግጥም ጌታ በጳውሎስ በኩል ብቻ የገለጣቸው እስከዚያን ጊዜ ድረስ ተሰውረው የነበሩ ምስጢራት አሉ፤ አሕዛብ በቤተክርስቲያን አብረው የክርስቶስ አካል የመሆናቸው እውነት (ኤፌ.3፡1-12)፣ ጌታ የእርሱ የሆኑትን ሊወስድ ሲመጣ በሕይወት ያሉት አማኞች እርሱን ወደ መምሰል በቅጽበተ-ዓይን እንደሚለወጡ (1ቆሮ15፡52)፣ አሁን በእስራኤል ድንዛዜ የሆነው የአሕዛብ ሙላት እስኪገባ ድረስ እንደሆነና ወደፊት ግን እስራኤል ሁሉ እንደሚድን (ሮሜ11፡25-26) የሚናገሩ ምስጢራት ሁሉ የተገለጡት በጳውሎስ በኩል ነው፡፡ ስለሆነም ጳውሎስ ይህን ሁሉ ምስጢር ለሰዎች ይናገር ዘንድ በእግዚአብሔር ፈቃድ ሐዋርያ የሆነ ሰው ነው፤ እነዚህንም ምስጢራት በጻፋቸው መልእክታት የገለጣቸው በመሆኑ ሁሉንም ልናውቃቸው ችለናል፡፡
ከ12ቱ ሐዋርያት እና ከጳውሎስ ሌላስ?
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አካሉ ለምትሆን ለቤተክርስቲያን ራስ ተደርጎ የተሰጠው ወደ ላይ ካረገና በአባቱ ቀኝ ከተቀመጠ በኋላ ነው፤ ጳውሎስ በኤፌሶን መልእክቱ ይህን ሲገልጥ «ክርስቶስን ከሙታን ሲያስነሣው ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል» ካለ በኋላ «ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዛለት ከሁሉ በላይ ራስ እንዲሆን ለቤተክርስቲያን ሰጠው» ይላል (ኤፌ.1፡21-22)፡፡ ከዚያም ከትንሣኤ በኋላ ባለው በከበረው ሰውነቱ በአባቱ ቀኝ ተቀምጦ ካለበት ለሰዎች ስጦታን እንደሰጠና አንዳንዶችን ሐዋርያት፣ ሌሎችን ነቢያት፣ ሌሎችን ወንጌል ሰባኪዎች፣ ሌሎችን እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ እንደሰጠ ተመልክተናል (ኤፌ.4፡7-11)፡፡ በ1ቆሮ.11፡27-28 ላይም «እናንተ የክርስቶስ አካል ናችሁ፤ እያንዳንዶችሁም ብልቶች ናችሁ» ካለ በኋላ «እግዚአብሔርም በቤተክርስቲያን አንዳንዶቹን አስቀድሞ ሐዋርያትን፣ ሁለተኛም ነቢያትን፣ ሦስተኛም አስተማሪዎችን ... አድርጎአል» ይላል፡፡ ጌታ ለቤተክርስቲያን የሰጣቸውን አገልጋዮች በተመለከተ በሚናገሩት በእነዚህ ክፍሎች «ሐዋርያት» በቅድሚያ ተጠቅሰው እናገኛለን፡፡ ቤተክርስቲያን ከመመሥረቷ በፊት 12ቱ ሐዋርያት የተመረጡና የተሾሙ ቢሆንም ለቤተክርስቲያን ሊሰጡ የሚችሉት ግን እርሷ ከተመሠረተች በኋላ ነው፤ ቤተክርስቲያን የተመሠረተችው ደግሞ ከጌታ ዕርገት በኋላ በበዓለ ሃምሳ ዕለት ነው፡፡ ስለሆነም 12ቱ ሐዋርያትንም ቢሆን ወደ ላይ የወጣውና የቤተክርስቲያን ራስ የሆነው ክርስቶስ ለቤተክርስቲያን ሰጠ ሊባል ይችላል፡፡ እርሱ በምድር እያለ ሐዋርያነታቸው በእስራኤል ዘንድ የተወሰነ እንደነበርና ወደ አሕዛብ ሁሉ እንዲሄዱ ያዘዛቸው ሊያርግ ሲል እንደነበር ቀደም ሲል አይተናል፤ ስለሆነም እነርሱም ቢሆኑ ለቤተክርሰቲያን የተሰጡት ከጌታ ዕርገት በኋላ ነው፤ እዚህ ላይ አሥራ ሁለተኛው ሐዋርያ ማትያስ መሆኑን ማስተዋል ይገባል፡፡ ማትያስ ቀደም ሲል በነበረውና ይሁዳ በተወው የሐዋርያት ስፍራ ገብቶ ከ11ዱ ሐዋርያት ጋር የተቆጠረው ቤተክርስቲያን ከተመሠረተችበት ከበዓለ ሃምሳ በፊት በመሆኑ ለቤተክርስቲናያን የተሰጠው ጌታ በምድር እያለ ከሾማቸው ከ11ዱ ሐዋርያት ጋር 12ኛ ሆኖ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ጳውሎስን በተመለከተ ግን የተሾመውም ሆነ ለቤተክርስቲያን ሐዋርያ ሆኖ የተሰጠው ቤተክርስቲያን ከተመሠረተችና ብዙ ካሳደዳት በኋላ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ስለሆነም በ1ቆሮ.11፡28 እና በኤፌ.4፡11 ላይ የተጠቀሱት ሐዋርያት እነዚሁ 12ቱ ሐዋርያትና ጳውሎስ ናቸው፡፡ እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ነገር በእነዚህ ጥቅሶች ላይ የተጠቀሱት ስጦታዎች ሁሉ በየአጥቢያ ቤተክርስቲያኑ ብቻ ተወሰነው እንዲያገለግሉ ለየአጥቢያ ቤተክርስቲያናቱ የተሰጡ ሳይሆኑ በአጠቃላይ ለመላዋ ቤተክርስቲያን የተሰጡ መሆናቸው ነው፡፡ በዚህም መሠረት ሐዋርያትን ለቤተክርስቲያን ሰጠ ሲባል የክርስቶስ አካል ለሆነችው ለመላዋ ቤተክርስቲያን ሰጠ ማለት ነው እንጂ በዚያን ጊዜም ቢሆን በየአጥቢያ ቤተክርስተያናቱ ሐዋርያት ተሰጥተው ነበር ማለት አይደለም፤ እንደዚሁም ጌታ ተመልሶ እስኪመጣ ድረስ በየስፍራው በሚመሠረቱ አጥቢያ ቤተክርስቲያናት ሐዋርያት ይነሣሉ ማለት አይደለም፤ የመጀመሪያዎቹ ሐዋርያት ሐዋርያነታቸው ለመላው አንዲት የክርስቶስ አካል በመሆኑ ዛሬም ቢሆን የእኛም ሐዋርያት ናቸው፤ እነርሱ በአካል ባይኖሩም ትምህርታቸው የእግዚአብሔር እስትንፋስ በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተካተተ ዛሬም እኛ የሐዋርያነታቸው አገልግሎት ተጠቃሚ ነን፡፡
እነዚህ ሐዋርያት ለቤተክርስቲያን ሐዋርያት ሆነው እንዲሰጡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በዓይን ሊያዩት እና የትንሣኤው የዓይን ምስክር ሊሆኑ ግድ ነበር፤ ይህም ብቻ ሳይሆን ጌታን ካዩትና የትንሣኤው የዓይን ምስክር ከሆኑትም መካከል ሐዋርያ የሚሆኑት ጌታ ሐዋርያ አድርጎ የሾማቸው ብቻ ናቸው፡፡ ይህም ማትያስ እና ጳውሎስ ሐዋርያ ተደርገው ከተመረጡበትና ከተሾሙበት ታሪክ በግልጽ የምንረዳው እውነት ነው፡፡
- 1ኛ) ማትያስ፡- ይሁዳ ትቷት ለሄደው የሐዋርያነት ስፍራ ማትያስ እና ዮሴፍ የተባለው ደቀመዘሙር የተመረጡት ጌታ እስካረገበት ቀን ድረስ ከጌታና ከሐዋርያት ጋር አብረው የነበሩ ስለሆነ ነው፤ ይህንን ጴጥሮስ ሲናገር «ስለዚህ ከዮሐንስ ጥምቀት ጀምሮ ከእኛ ዘንድ እስካረገበት ቀን ድረስ ጌታ ኢየሱስ በእኛ መካከል በገባበትና በወጣበት ዘመን ሁሉ ከእኛ ጋር አብረው ከነበሩት ሰዎች ከእነዚህ አንዱ ከእኛ ጋር የትንሣኤው ምስክር ሊሆን ይገባል» ብሎአል (የሐ.ሥራ1፡22)፡፡ እነዚህ ሰዎች ከመጥምቁ ዮሐንስ ጀምሮ አብረው ስለነበሩ ጌታን ከሞቱ አስቀድሞ በማስተማር ዘመኑ ሁሉ በማየታቸው ላደረገውና ላስተማረው ምስክር መሆን ይችላሉ፤ እንዲሁም ጌታ እስካረገበት ቀን ድረስ አብረው የነበሩ ስለሆኑ የክርስቶስ የትንሣኤው ምስክር መሆን ይችላሉ፤ ይህ የመጀመሪያውና የሐዋርያነቱን ስፍራ ለመያዝ መሟላት የነበረበት ነገር ነው፡፡ ሆኖም የነበረው የሐዋርያነት ስፍራ ይሁዳ ትቶት የሄደው አንድ ስፍራ ብቻ ነበር፤ ለዚያም ስፍራ ከሁለቱ ሰዎች አንዱን መርጦ መሾም የሚችለው ጌታ ብቻ ነው፤ በመሆኑም እነ ጴጥሮስ ሲጸልዩ «የሁሉን ልብ የምታውቅ አንተ ጌታ ሆይ ይሁዳ ወደ ገዛ ራሱ ስፍራ ይሄድ ዘንድ በተዋት በዚህች አገልግሎትና ሐዋርያነት ስፍራን እንዲቀበል የመረጥኸውን ከእነዚህ ከሁለቱ አንዱን ሹመው» ለማለት ችለዋል፡፡ የተጣጣሉትም ዕጣ ለማትያስ በመውደቁ ጌታ የሾመው ማትያስን መሆኑ ስለተረጋገጠ እርሱ ከአሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋር ተቈጠረ (የሐ.ሥራ1፡25-26)፡፡ ዮሴፍ ግን ጌታ ኢየሱስ በምድር ሳለ በገባበትና በወጣበት ዘመን ሁሉ ከሐዋርያት ጋር አብሮ የነበረና የትንሣኤውም የዓይን ምስክር ቢሆንም ሐዋርያ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ይህም በጌታ ሐዋርያ ተደርጎ ባለመሾሙ ነበር፡፡ ስለሆነም ሐዋርያ ለመሆን ጌታን ከማየትና የትንሣኤው የዓይን ምስክር ከመሆን በተጨማሪ በራሱ በጌታ መሾም የግድ ነው፡፡
- 2ኛ) ጳውሎስ፡- ይህ ሐዋርያ በተጠራ ጊዜ በደማስቆ መንገድ ላይ ጌታን አይቶታል፤ በአብ ቀኝ በክብር የተቀመጠው ጌታ ኢየሱስ ለእርሱ ከታየበት ምክንያትም ዋናው እርሱን ሐዋርያ አድርጎ ሊሾመው ነው፤ ይህንንም ጌታ «እኔን ባየህበት ነገር ለአንተም በምታይበት ነገር አገልጋይና ምስክር ትሆን ዘንድ ልሾምህ ታይቼልሃለሁ» ብሎ እንደነገረው ተመልክተናል (የሐ.ሥራ26፡16)፡፡ በኋላም ጳውሎስ በአገልግሎት ዘመኑ የእርሱን ሐዋርያነት ያልተቀበሉ ሰዎች ለሚናገሩበት ተቃውሞ በሰጠው መልስ ላይ ጌታን ማየቱን የሐዋርያነቱ ማስረጃ አድርጎ ሲያቀርብ እንመለከታለን፤ ይህንንም በ1ቆሮ9፡1 ላይ «እኔ ነጻ አይደለሁምን? ሐዋርያስ አይደለሁምን? ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አላየሁትምን?» በማለት ይገልጸዋል፡፡ ለገላትያ ሰዎች በጻፈው መልእክት ውስጥም «በኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታንም ባነሣው በእግዚአብሔር አብ ሐዋርያ የሆነ እንጂ ከሰዎች ወይም በሰው ያልሆነ ጳውሎስ» ብሎ ራሱን ይገልጣል (1፡1)፡፡ የሚሰብከውንም ወንጌል የተቀበለው በቀጥታ ከጌታ እንደሆነ ሲያስረዳ «ወንድሞች ሆይ በእኔ የተሰበከ ወንጌል እንደሰው እንዳይደለ አስታውቃችኋለሁ፤ አየሱስ ክርስቶስ ገልጦልኛል እንጂ እኔ ከሰው አልተቀበልኩትም አልተማርሁትምም» ብሏል (ገላ.1፡11-12)፡፡ ጳውሎስ በቀጥታ ጌታን ያየና በጌታ የተሾመ የሚሰብከውንም በቀጥታ ከጌታ የተቀበለ ከመሆኑም በላይ የትንሣኤው ምስክር መሆንም ችሏል፤ ምክንያቱም እርሱ ጌታን ያየው ከትንሣኤ በኋላ ባለው ማንነቱ ስለሆነ ነው፤ ክርስቶስ ከተነሣ በኋላ ለተለያዩ ሰዎች ለሐዋርያትም ከታየ በኋላ በመጨረሻ ለእርሱ መታየቱን በመግለጽ ይህን ከሐዋርያነቱ ጋር ሲያያይዘው «ከዚያ በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ፡፡ እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ ነኝና የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን ስላሳደድሁ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ የሆንኩ እኔ ነኝ» በማለት ጽፏል (1ቆሮ.15፡7-9)፡፡
>በመሆኑም በመጽሐፍ ቅዱስ ሐዋርያት ተብለው የተጠሩትና ጌታም ሐዋርያት አድርጎ የሾማቸው እነዚሁ ከላይ የተጠቀሱት 12ቱ ሐዋርያትና ጳውሎስ ብቻ ናቸው፡፡
ሌሎች ሐዋርያት እንዳሉ የሚናገሩ ጥቅሶች የሉምን?
በመቀጠል ደግሞ ሌሎች ሐዋርያት እንዳሉ የሚናገረውን የሰው ትምህርት ተቀባይነት ያለው ለማድረግ ሲባል አንዳንዶች የሚጠቅሷቸውን ጥቅሶችን በማንሳት ቃሉ የሚናገረውን እውነት ማጥናቱ አግባብነት ስላለው በመቀጠል እንመለከታቸዋለን፡፡
- ሀ. የሐ.ሥራ14፡4፣14
በዚህ ንባብ ውስጥ እንደምንመለከተው ጳውሎስና በርናባስ አንድ ላይ ከመሥራታቸው የተነሳ በአንድ ላይ ሐዋርያት ተብለው ተጠርተዋል፡፡ በርናባስ በትውልዱ የቆጵሮስ ሰው ቢሆንም በወገኑ ሌዋዊ የሆነ አይሁዳዊ ነበር፤ በኢየሩሳሌም ከነበሩ የመጀመሪያዎቹ አማኞች አንዱ ሲሆን የቀድሞ ስሙ ዮሴፍ ይባል ነበር፡፡ በርናባስ ተብሎ የተሰየመው በሐዋርያት ነው፡፡ የነበረውንም እርሻ ሸጦ ገንዘብን አምጥቶ በሐዋርያት እግር አጠገብ ያኖረ ሰው ነበር (የሐ.ሥ4፡36-37)፡፡ ስለ በርናባስ የምናነበው የመጀመሪያ ነገር ይህን ብቻ ነው፡፡ ይህም በርናባስ ለወንጌል ሥራ የተለየ ሰው እንደ ነበር ያመለክተናል፤ በመሆኑም በአንጾኪያ ቊጥራቸው እጅግ የሚሆን ሰዎች አምነው ወደ ጌታ ዘወር እንዳሉ ወሬው በኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያን እንደተሰማ በርናባስ ለአገልግሎት ወደ አንጾኪያ እንደተላከ እናነባለን፤ እርሱም ሳውልን (ጳውሎስን) ተሰዶ ከሄደበት ከጠርሴስ አምጥቶ ለአንድ ዓመት ያህል አብረው ሕዝብን አስተምረዋል (የሐ.ሥራ11-20-26)፡፡ ቀደም ሲል ሳውልን ጌታ ከታየውና ከጠራው በኋላ ወደ ሐዋርያት ያገባውና ያስተዋወቀው ይኸው በርናባስ ነበር (የሐ.ሥ9፡27)፡፡ በርናባስና ሳውል በአንጾኪያ ወንጌልን ማስተማር ከጀመሩ በኋላ ደግሞ አብረው ሲያገለግሉ እናያለን፡፡ በቀላውዴዎስ ቄሣር ዘመን በዓለም ላይ በነበረው ታላቅ ረሃብ ጊዜ የአንጾኪያ አማኞች በይሁዳ ለሚኖሩት ወንድሞች እርዳታን የላኩት በበርናባስና በሳውል (ጳውሎስ) እጅ ነበር (የሐ.ሥራ11፡27-30)፡፡ ይህን አገልግሎታቸውን ፈጽመው ማርቆስን ይዘው ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ ከተመለሱ በኋላ በዚያ ከነበሩ ነቢያትና መምህራን ጋር ጌታን እያመለኩ ሲጦሙ መንፈስ ቅዱስ «በርናባስና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ» አለ (የሐ.ሥራ11፡25-13፡3)፤ ከዚህ በኋላ ጳውሎስ በቆጵሮስና በታናሽ እስያ ያደረገውን የመጀመሪያ የወንጌል ጉዞ የተጓዘውና ሐዋርያዊ ሥራውን የሠራው ከበርናባስ ጋር ነበር፡፡ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ በዚህ ጉዞ ውስጥ በኢቆንዮን ስለጌታ እጅግ ገልጠው እየተናገሩ ረጅም ወራት መቀመጣቸውን በተናገረበት ክፍል የከተማውን ሕዝብ ሁኔታ ሲናገር «የከተማውም ሕዝብ ተከፍለው እኩሌቶቹ ከአይሁድ እኩሌቶቹ ከሐዋርያት ጋር ሆኑ» ይላል (የሐ.ሥራ14፡4)፤ እንደዚሁም በልስጥራን ጳውሎስና በርናባስን «አማልክት ሰዎችን መስለው ወደእኛ ወርደዋል» መባላቸውንና በዚያ የነበረው የድያ ካህን ከሕዝቡ ጋር ሆኖ ሊሠዋላቸው መውደዱን በሰሙ ጊዜ ልብሳቸውን ቀደው እየጮኹ ማስተዋቸውን ሲተርክ «ሐዋርያትም በርናባስና ጳውሎስ ግን ይህን በሰሙ ጊዜ ልብሳቸውን ቀደው ወደ ሕዝቡ መካከል እየጮኹ ሮጡ» ይላል (14፡14)፡፡ ሆኖም ጳውሎስ ሐዋርያ መሆኑን የሚያስረዱና ብቻውን ሐዋርያ ተብሎ የተጠራባቸው እጅግ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ያሉ ሲሆን በርናባስ ግን ሐዋርያ ተደርጎ እንደተሾመም ሆነ ከጳውሎስ ጋር ሳይሆን ብቻውን ሐዋርያ ተብሎ እንደተጠራ የሚናገር አንድም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የለም፡፡ ደግሞም ጌታ ኢየሱስን በምድር ሳለ አላየውም፤ እንዲሁም ወደ አማኞች (ቤተክርስቲያን) የተቀላቀለው ከበዓለ ሃምሳ በኋላ በመሆኑ እና እንደ ጳውሎስም ከሙታን ተነሥቶ ያረገውን ክርስቶስን ያየ ባለመሆኑ የትንሣኤው የዓይን ምስክር ሊሆን አይችልም፤ ሆኖም ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር በሚሠራ ጊዜ ጳውሎስ እና እርሱ በአንድ ላይ ሐዋርያት ተብለው ሊጠሩ ችለዋል፤ በመሆኑም በዚህ አጠራር ውስጥ ሐዋርያነቱ የጳውሎስ እንጂ የበርናባስ አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡
- ለ. 1ቆሮ4፡6፣9
በዚህ ጥቅስ ላይም ጳውሎስ ራሱን ከአጵሎስ ጋር አድርጎ «እኛ» ብሎ ይጠራል፤ ወረድ ብሎ በቊ.9 ላይ ደግሞ «እግዚአብሔር እኛን ሐዋርያቱን ...» ይላል፤ አጵሎስ ግን ጌታን በዓይኑ አላየም፤ የክርስቶስ የትንሣኤው የዓይን ምስክርም አይደለም፤ ሐዋርያ ተደርጎም በጌታ አልተሾመም፤ ለብቻውም ሐዋርያ ተብሎ የተጠራበትም አንድም ንባብ የለም፡፡ ስለሆነም አጠራሩ የመነጨው እንደ በርናባስ ሁሉ ከሐዋርያው ጋር አብሮ ከመሆኑና ከመሥራቱ የተነሣ እንጂ አጵሎስ በግሉ ሐዋርያ ስለነበረ አይደለም፡፡
- ሐ. 1ተሰ1፡1፣7
በዚህ ክፍል ደግሞ «የክርስቶስ ሐዋርያት እንደመሆናችን ...» የሚል ንባብ ይገኛል፤ ጳውሎስ 1ኛይቱን የተሰሎንቄ መልእክት የጻፈው ከስልዋኖስ (ሲላስ) እና ከጢሞቴዎስ ጋር እንደሆነ በምዕ.1፡1 ላይ እንረዳለን፡፡ ስለሆነም ራሱን ከእነርሱ ጋር አድርጎ ሐዋርያት ብሎ የጠራበት ምክንያት ስልዋኖስና ጢሞቴዎስ ሐዋርያት ስለሆኑ ሳይሆን ከእርሱ ጋር አብረው ስለሠሩ ነው፤ በተሰሎንቄ ከእርሱ ጋር አብረው መሥራታቸውን የሐ.ሥራ17፡1-15ን ስናነብ እንረዳለን፡፡ እነርሱ ግን በየግላቸው ጌታን አላዩም፤ የትንሣኤው የዓይን ምስክርም አይደሉም፤ ሐዋርያት ተደርገውም በራሱ በጌታ አልተሾሙም፤ ለየብቻቸውም ሐዋርያት ተብለው የተጠሩበት አንድም ስፍራ እንኳ የለምና እንደፊተኞቹ ሁሉ ይህም ጥቅስ ስልዋኖስና ጢሞቴዎስ ሐዋርያት ናቸው አይልም፡፡
- መ. ሮሜ16፡7
በዚህኛው ጥቅስ «በሐዋርያት መካከል ስመ ጥሩዎች ለሆኑ ደግሞም ክርስቶስን በማመን ለቀደሙኝ አብረውኝም ለታሰሩ ለዘመዶቼ ለአንዲራኒቆንና ለዩልያን ሰላምታ አቅርቡልኝ» የሚል ንባብ እናገኛለን፡፡ ከዚህ ጥቅስ በመነሣት አንዲራኒቆንና ዩልያን ሐዋርያት ነበሩ ለማለት ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ንባቡ የሚለው «በሐዋርያት መካከል ስመ ጥሩዎች ለሆኑ» ነው እንጂ «ከሐዋርያት መካከል ለነበሩ» ወይም «ሐዋርያት ለነበሩት» አይልም፡፡ አንዲራኒቆንና ዩልያን ጳውሎስን ጌታን በማመን ይቀድሙታል፤ በሐዋርያት መካከልም የታወቁ ነበሩ፤ ከዚህም የተነሣ ንባቡ «በሐዋርያት መካከል (ዘንድ) ስመ ጥሩዎች» ሲል የታወቁ ማለትም ዝነኞች እንደነበሩ የሚያስረዳ ነው እንጂ እነርሱ ሐዋርያት መሆናቸውን የሚገልጽ አይደለም፡፡
ስለሆነም ጌታ እንደሾማቸው ከተመለከትናቸው ውጭ ሐዋርያት እንዳሉ የሚናገር ጥቅስ እንደሌለና ከላይ የተጠቀሱትም የሌሎችን ሐዋርያ መሆን የማያስረዱ መሆናቸውን ልንገነዘብ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህንም ጥቅሶች የሚጠቅሱ ሰዎች ጥቅሶቹን የሚጠቅሱበት ዋነኛ ዓላማ የነስልዋኖስንና የሌሎችን ማንነት ማብራራት የግድ አስፈላጊ ሆኖ ሳይሆን ራሳቸውን በዚህ ሹመት ለማስገባት ቀዳዳ እንዲከፍትላቸው በብርቱ በመሻታቸው መሆኑ ከማንም የተሰወረ ሊሆን አይገባም፡፡
ቤተክርስቲያን በተመሠረተችበት በዚያን ዘመን ራስ የሆነው ጌታ ኢየሱስ ሐዋርያትን ለቤተክርስቲያን የሰጠው የእግዚአብሔር ቤት የሆነችውን የቤተክርስቲያንን መሠረት ለመጣል ነበር፡፡ እነዚህ የመሠረት ሥራ የተሠራባቸው ሐዋርያት ጌታን ያዩና በራሱ በጌታ ቀጥታ የተላኩ ሊሆኑ ይገባቸዋል፡፡ 12ቱን ሐዋርያት በተመለከተ ለሚመሰክሩት ነገር እነርሱን የተለየና የላቀ ተቀባይነት እንዲኖራቸው የሚያደርጋቸው ጌታ ኢየሱስን እና ትንሣኤውን አይተው የሚመሰክሩ መሆናቸው ነው፤ ይህንንም ዮሐንስ ሲናገር «ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያ የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤ ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል፤ እንመሰክርማለን..» ይላል (1ዮሐ.1፡1-2)፤ ጴጥሮስም ስለክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ለአሕዛብ በመሰከረ ጊዜ «እኛም በአይሁድ አገርና በኢየሩሳሌም ባደረገው ነገር ሁሉ ምስክሮች ነን፤ እርሱንም በእንጨት ላይ ሰቅለው ገደሉት፤ እርሱን እግዚአብሔር በሦስተኛው ቀን አስነሣው፤ ይገለጥም ዘንድ ሰጠው፤ ይኸውም ለሕዝብ ሁሉ አይደለም፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር አስቀድሞ የተመረጡ ምስክሮች ለሆነን ለእኛ ነው እንጂ፤ ከሙታንም ከተነሣ በኋላ ከእርሱ ጋር የበላን የጠጣን እኛ ነን፡፡ ለሕዝብም እንድንሰብክና በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ በእግዚአብሔር የተወሰነ እርሱ እንደሆነ እንመሰክር ዘንድ አዘዘን» በማለት የሐዋርያነታቸውን ልዩ ባሕርያት በግልጽ ተናግሯል (የሐ.ሥራ10፡39-42)፡፡ ጳውሎስም ሐዋርያ የሆነበት ምክንያት አስቀድመን በስፋት እንዳብራራነው ያረገውን ጌታ በዓይን ስላየ፣ የትንሣኤው የዓይን ምስክር መሆን ስለቻለና በራሱ በጌታ ሐዋርያ ሊሆን የተጠራና የተሾመ ስለነበር ነው፡፡ ከ12ቱ ሐዋርያትና ከጳውሎስ በኋላ ግን በየስፍራው ወንጌል እየተሰበከ የሚያምኑ ሰዎች በዘመናት ሁሉ የእነርሱን ትምህርት መሠረት አድርገው በዚያው ላይ እንዲታነጹ እንጂ ሌላ ሐዋርያ እንዲኖራቸው ባለማስፈለጉ ጌታ ሌሎች ሐዋርያትን አልሾመም፡፡ በኤፌ.2፡20 ላይ «በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል» ተብሎ የተጻፈው ቃል የሚያረጋግጠውም ይህንኑ እውነት ነው፡፡ በዚህም መሠረት ከአምስቱ ስጦታዎች መካከል ሐዋርያትና ነቢያት የመሠረት ስጦታዎች እንደሆኑ በማያሻማ መልኩ መረዳት ይቻላል፡፡ አንድ ቤት መሠረቱ ከተጣለ በኋላ ቤቱ ወደ ላይ ያድጋል እንጂ ሌላ መሠረት አይጣልም፡፡ የሐዋርያት እና የነቢያት መሠረትም ሌላ ማንም ሳይሆን ራሱ ክርስቶስ ነው፡፡ በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል ሲልም ሐዋርያትና ነቢያት ኢየሱስ ክርስቶስን በተመለከተ ባስተማሩት ትምህርት ላይ መታነጻቸውን ያመለክታል፡፡ የእግዚአብሔር እስትንፋስ የሆኑ መለኮታዊ ቃላትም የተገለጡት የመሠረት ስጦታዎች በሆኑት በሐዋርያትና በነቢያት ነው፡፡
ጳውሎስ በኤፌ.3፡6 ላይ አሕዛብ በአንድ አካል አብረው የመሆናቸውና የመውረሳቸው ምስጢር የተገለጠው ለሐዋርያትና ለነቢያት መሆኑን በሚያስረዳ ጊዜ «... ለቅዱሳን ሐዋርያትና ነቢያት በመንፈስ አሁን እንደተገለጠ በሌሎቹ ትውልዶች ዘንድ አልታወቀም» ይላል፡፡ ከአምስቱ ስጦታዎች መካከልም ሁለቱን ለይተን በቤተክርስቲያን ምሥረታ ወቅት የነበሩ ስጦታዎች ናቸው ለማለት የምንችለው የእግዚአብሔር መንፈስ በዚያው በኤፌሶን መልእክት ውስጥ ሁለቱን ለይቶ በመጥቀስ የሐዋርያትና የነቢያት መሠረት አማኞች የሚታነጹበት እንደሆነና መለኮታዊ ምስጢራትም በእነዚህ ሰዎች እንደተገለጠ ስለነገረን ነው፡፡ ስለሆነም ከ2000 ዓመት በኋላም የእኛ ሐዋርያት እነዚያው የመጀመሪያዎቹ ናቸው እንጂ ሌሎች ሐዋርያት አይደሉም፡፡
እግዚአብሔር ወደ ሰው መግለጥ የሚፈልገውን ምስጢር ሁሉ በሐዋርያት በኩል ገልጦአል፤ ያም እስከ ዮሐንስ ራእይ ባሉት የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ተጽፎ ተጠናቅቋል፤ ስለዚህ እኛ ቀድሞ በእነዚያው ሐዋርያት የተባለውንና የተጻፈውን ትምህርት እና ትእዛዝ በመመሪያነት እንከተላለን እንጂ አዲስ መገለጥን ይዞ የሚመጣ ሐዋርያን አንጠብቅም፡፡ በይሁዳ መልእክት ቊ.17 ላይ «እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ቀድሞ የተነገረውን ቃል አስቡ» የሚል ቃል እናነባለን፡፡ በመቀጠል በቊ.18 ላይ ደግሞ ማሰብ ያለባቸው ያ የሐዋርያት ቃል የትኛው እንደሆነ ሲናገር «እነርሱ፡ በመጨረሻው ዘመን በኃጢአተኝነት እንደ ገዛ ምኞታቸው እየሄዱ ዘባቾች ይሆናሉ ብለዋችኋልና» ይላል፡፡ ይህንንም የተናገረው ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደሆነ ከ2ጴጥ.3፡3 መረዳት ይቻላል፡፡ ስለሆነም ሐዋርያት ሲባል በዚያን ጊዜ እንኳን የሚያመለክተው እነዚያኑ የጌታ ሐዋርያት ነበር፡፡ በእነርሱ በኩል የሚገኘው ትእዛዝ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትእዛዝ ነው፤ ጴጥሮስ የሚጽፍላቸውን ሰዎች ልብ ለማነቃቃት «በቅዱሳን ነቢያት ቀድሞ የተባለውን ቃል በሐዋርያቶቻችሁም ያገኛችኋትን የጌታንና የመድኃኒትን ትእዛዝ እንድታስቡ በሁለቱ እያሳሰብኋችሁ ቅን ልቡናችሁን አነቃቃለሁ» በማለት ጽፏል (2ጴጥ.3፡2)፡፡ በዚህ ጥቅስ ውስጥ “በሐዋርያቶቻችሁ” ሲል ለመልእክቲቱ ተቀባዮች የተለዩ ሐዋርያት ነበሩ ለማለት ሳይሆን ከነዚያው ከመጀመሪያዎቹ የክርስቶስ ሐዋርያት ወደ እነርሱ ሄደው የሰበኩትን ሐዋርያት በተለይ የሚያመለክት ነው፤ ጳውሎስ ለምሳሌ ለቆሮንቶስ ሰዎች ሲጽፍ «የሐዋርያነቴ ማኅተም በጌታ እናንተ ናችሁና ለሌሎች ሐዋርያ ባልሆን ለእናንተስ ምንም ቢሆን ሐዋርያ ነኝ» እንዳለው ያለ ነው (1ቆሮ.9፡2)፡፡ እነዚህ ጴጥሮስ የጠቀሳቸው ሐዋርያት ከእርሱ ጋር የጌታ ሐዋርያት ከነበሩት መካከል እንደሆኑ የምንረዳው «በሐዋርያቶቻችሁም ያገኛችኋትን የጌታን የመድኃኒትን ትእዛዝ እንድታስቡ እያሳሰብኋችሁ» በማለት የጌታችንና የመድኃኒታችንን ትእዛዝ የያዙና ያስተላለፉ መልእክተኞች መሆናቸውን ስለገለጸ ነው፡፡
ሐዋርያት ሳይሆኑ ሐዋርያት ነን የሚሉ
በራእ.2፡2 ላይ «ሐዋርያት ነን የሚሉቱን መርምረህ ሐሰተኞች ሆነው እንዳገኘሃቸው አውቃለሁ» በማለት ጌታ ኢየሱስ በኤፌሶን ወዳለው ቤተክርስቲያን መልአክ የላከውን መልእክት እናነባለን፡፡ ጌታ ኢየሱስ በኤፌሶን ባለች ቤተክርስቲያን ካገኛቸው መልካም ነገሮች መካከል አንዱ ሐዋርያት ነን የሚሉትን መርምሮ ሐሰተኞች መሆናቸውን ማረጋገጡ ነበር፡፡ በዚያ በሐዋርያት ዘመን ከነበሩት የሐሰት አስተማሪዎች መካከል ብዙዎቹ ሐዋርያት ሳያዝዟቸውና ሳይልኳቸው ሐዋርያት አዝዘውናል ወይም ልከውናል በማለት በተለያዩ ከተሞችና መንደሮች በሚገኙ አጥቢያ ጉባኤያት እየዞሩ ተቀባይነት ለማግኘት ይሞክሩ ነበር (የሐ.ሥራ15፡24)፤ ይህ አልሳካ ያላቸው ደግሞ እንደ ክርስቶስ ሐዋርያት ተቀባይነትን ማግኘት ይችሉ ዘንድ በድፍረት «ሐዋርያት ነን» ይሉ ነበር፡፡ ይህንንም በተመለከተ ሐዋርያው ጳውሎስ ሲጽፍ «... እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ፣ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኰለኞች ሠራተኞች ናቸውና፡፡ ይህም ድንቅ አይደለም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና፡፡ እንግዲህ አገልጋዮቹ (የሰይጣን አገልጋዮች) ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ቢለውጡ ታላቅ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜያቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል» (2ቆሮ.11፡13-15) ብሏል፡፡ ከዚህም እንደምንረዳው እነዚህ ሰዎች «ሐዋርያት ነን» የሚሉ ብቻ ሳይሆኑ የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን የሚለውጡ ተንኰለኞች ሠራተኞች ነበሩ፡፡ ያን ጊዜ የክርስቶስ ሐዋርያት በአገልግሎት ላይ ስለነበሩ በየስፍራው ያሉና በተለያዩ አማኞች በኩል ወንጌል የደረሳቸው ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት ሁሉንም በዐይን ስላላዩአቸው ሊታለሉላቸው የሚችሉበት እድል እንዳለ በማሰብ ሐዋርያት ነን እያሉ የሐሰት ትምህርታቸውን ይዘሩ ነበር፡፡ በቆሮንቶስ በነበሩ አማኞች መካከል ብዙ ዓይነት መንፈሳዊ ውድቀት በመኖሩ ለእነዚህ ውሸተኞች ሐዋርያት የሐሰት ትምህርት የተጋለጡ ሰዎች እንደነበሩ ከ2ኛ ቆሮ.11 እንረዳለን፤ ሐዋርያው ጳውሎስ ግን እነዚህን ሰዎች የሰይጣን አገልጋዮች እንደሆኑ በመግለጥ ሥራቸውንም ሰይጣን የብርሃን መልአክ እንዲመስል ራሱን ከመለወጡ ጋር እያነጻጸረ ማንነታቸውን በመግለጥ በክፉ ትምህርታቸው የተታለሉትን ሁሉ በብርቱ ይወቅሳቸዋል፡፡
በቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን ታይቶ የነበረው አጠቃላይ መንፈሳዊ ውድቀት በክርስትናው ዓለም እየታየ ባለበት በዚህ ዘመንም እነዚህ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኰለኞች ሠራተኞች በዙሪያችን ይታያሉ፤ በአንዳንዶች ዘንድ «ከአባቶቻችን ከሐዋርያት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ሐዋርያዊ ሥልጣንን ይዘናል» እየተባለ ሲነገር ከምንሰማው ጀምሮ በግልጽ «ሐዋርያት ነን» ብለው እስከተነሡትና «ሐዋርያው እገሌ» እየተባሉ ለመጠራት እስከደፈሩት ድረስ በውሸተኞች ሐዋርያት የተበከሉ አገልግሎቶች እያየን ነው፡፡ በእጅጉ የሚያሳዝነው ደግሞ እግዚአብሔር የቀባኝ ሐዋርያ ነኝ ብሎ በድፈረት የተነሣውን ሁሉ ሙሉ በሙሉ በመቀበል ወደፈለገው እንዲነዳቸው ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡት የብዙ ሰዎች ጉዳይ ነው፤ «እንደ ገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ» (2ጢሞ.4፡3) እንደተባሉት ሰዎች በሚመቻቸውና የሥጋ አርነት ባለበት መንገድ የሚመራቸውን፣ እነርሱም የሚፈልጉትን መገለጥ ከልቡ አንቅቶ የሚናገርላቸውን ሐዋርያ ሾመው የሚከተሉትና ለትእዛዙም የሚገዙለት ጥቂቶች አይደሉም፤ ሐዋርያ ነኝ ብሎም በድፍረት የተገለጠው ሰው በዚህ የተነሣ የሚያገኘው ነውረኛ ረብ (ጥቅም) እና ክብር ኅሊናውን ስላሳወረው በውሸት ላይ ውሸትን በሐሰት ትምህርት ላይ ሌላ የሐሰት ትምህርትን እየደራረበ ወደ ወደደው ሲወስዳቸው ምንም አይሰማውም፤ ተከታዮቹም አንድ ጊዜ «ሐዋርያ» ብለው ከፍ ያደረጉትን ሰው መመርመር እንደ ድፍረት ቈጥረው በእርሱ ስሜትና ኅሊና እየተመሩ ሲሄዱ ይኖራሉ፡፡ አቤት እንዴት ያለ ድንዛዜ ነው! እንዴትስ ያለ አለማስተዋል ነው! ሐዋርያት ነን የሚሉት በየዕለቱ በሕዝብ ፊትም ሆነ ከዚያ ውጪ የሚሠሩት የተገለጠውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ ሥራና አካሄድ እያዩ ከዚህ ዓመፃ አለመለየትስ እንዴት ያለ ግርዶሽ ነው!
በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ የታነጹ አማኞች ግን እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች ሐዋርያት ነን ብለው ሲነሡ እንደ ኤፌሶን ቤተክርስቲያን መርምረው ሐሰተኞች መሆናቸውን ወዲያውኑ ይረዳሉ፤ የሚመረምሩበት መንገድም በጣም ግልጽ ነው፤ ሐዋርያ የሆነ ሰው ጌታን በዓይን ያየ መሆን አለበት፤ የትንሣኤው የዓይን ምስክር ሊሆን ግድ ነው፤ በራሱ በጌታ ሐዋርያ ተደርጎ የተሾመ ሊሆንም ያስፈልገዋል፡፡ ሐዋርያት ነን የሚሉትም ሆነ የሐዋርያትን ሥልጣን ተቀብለናል የሚሉት ሁሉ ግን ይህ ሁሉ ስለሌላቸው ሐሰተኞች መሆናቸው ወዲያው ይታወቃል፡፡ ከዚያ ይልቅ የቀደሙት ሐዋርያት ያስተማሩት ሁሉ በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ተጽፈው ስለሚገኙና ለእኛ የተሰጠው የእግዚአብሔር መገለጥም ተጽፎ የተጠናቀቀ በመሆኑ ሁልጊዜ በሐዋርያት ትምህርት ልንተጋ ይገባል (የሐ.ሥራ2፡12)፡፡ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተሰብስበን ሐዋርያት የጻፉትን መጻሕፍት በጋራ ስናጠናም ሆነ ጌታ የአስተማሪነት ጸጋ በሰጣቸው ወንድሞች መጽሐፍ ቅዱስን ስንማር በሐዋርያት ትምህርት እየተጋን መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ይህንንም ስናደርግ ሐዋርያው ዮሐንስ እንዳለው ከእነርሱ ከሐዋርያት ጋር ኅብረት እያደረግን ነው (1ዮሐ.1፡3)፡፡
በኤፌ.2፡20 «በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል» ተብሎ ስለተጻፈ እንደ ሐዋርያት ሁሉ ነቢያትም ከአምስቱ ስጦታዎች መካከል የመሠረት ስጦታዎች መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ ነቢያት ሲባልም ትንቢት የሚናገሩ የእግዚአብሔር መልእክተኞች ናቸው፤ ስለሆነም እዚህ ላይ ስጦታዎቹ ራሳቸው ነቢያቱ እንደሆኑ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ለጽሑፋችን መነሻ ባደረግነው በኤፌ.4፡11 ላይም «እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት ሌሎቹም ነቢያት ... እንዲሆኑ ሰጠ» ተብሎ ሲነገር ሰዎቹ ራሳቸው ስጦታ ሆነው እንደተሰጡ የሚያሳይ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ በሮሜ12፡6 ላይ «እንደተሰጠንም ጸጋ ልዩ ልዩ ስጦታ አለን፤ ትንቢት ቢሆን እንደ እምነታችን መጠን ትንቢት እንናገር ...» የሚለውና በ1ቆሮ12፡10 ላይ «ለአንዱም ትንቢትን መናገር ... ይሰጠዋል» የሚለው ነቢያቱ ለቤተክርስቲያን መሰጠታቸውን ሳይሆን ትንቢት የመናገር ስጦታ ከአማኞች መካከል ለአንዳንዶቹ መሰጠቱን ያመለክታል፡፡
በብሉይ ኪዳን ዘመን እግዚአብሔር ማናቸውንም አሳቡን ለሰው ይገልጥ የነበረው በነቢያት በኩል ነበር፡፡ ጌታ ኢየሱስ በሕጻንነቱ ወደ ቤተመቅደስ በተወሰደ ጊዜ የኢየሩሳሌምን ቤዛ ለሚጠባበቁ ስለእርሱ ትናገር የነበረችው ነቢይት ሐና እና «ከነቢይ የሚበልጠው» ተብሎ የተነገረለት (ማቴ.11፡9) መጥምቁ ዮሐንስ ጌታ ከተወለደ በኋላ የነበሩ ነቢያት ቢሆኑም የብሉይ ኪዳን ነቢያት ናቸው፤ ምክንያቱም «ነቢያት ሁሉና ሕጉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናገሩ፤» የቀደሙት የብሉይ ኪዳን ነቢያት ዘመን እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ድረስ መሆኑ በግልጽ ተነግሮናልና ነው (ማቴ.11፡13)፡፡ ሆኖም የእግዚአብሔር ልጅ በሥጋ በተገለጠባቸው ወራትና ዓመታት በምድር ሲመላለስ ሳለ የአባቱን ፈቃድና የልብ ምክር ገልጧል፡፡ እርሱ በዘዳግ.18፡18 ላይ «ከወንድሞቻቸው መካከል እንደ አንተ ያለ ነቢይ አስነሣላቸዋለሁ፤ ቃሌንም በአፉ አደርጋለሁ፤ ያዘዝሁትንም ቃል ሁሉ ይነግራቸዋል፤ በስሜም የሚናገረውን ቃሌን የማይሰማውን ሰው እኔ እበቀልለታለሁ» ተብሎ የተነገረለት ነቢይ ነው (የሐዋ.ሥ.3፡22)፡፡ በመሆኑም በያዘው የነቢይነት ስፍራ ምክንያት «እኔ ከራሴ አልተናገርሁምና ነገር ግን የላከኝ አብ እርሱ የምለውን የምናገረውንም ትእዛዝ ሰጠኝ፡፡ ትእዛዙም የዘላለም ሕይወት እንደሆነች አውቃለሁ፤ ስለዚህ እኔ የምናገረውን አብ እንደነገረኝ እንዲሁ እናገራለሁ» ለማለት ተችሎታል (ዮሐ.12፡49-50)፡፡ ኢየሱስ ነቢይነቱ በሰውነቱ የተገለጠ አገልግሎቱ ቢሆንም እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ ስለሆነ በእርሱ ነቢይነት የተገለጠው ቃል የቀደሙት ነቢያት ከተናገሩት ሁሉ የበለጠና ሁሉን ወደ ፍጻሜ ያመጣ ቃል ነበር፤ መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ሲያስረዳ «ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጐዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን» ይላል (ዕብ.1፡1-2)፡፡
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ በእርሱ የተገለጠውን ቃል ወደ ዓለም ሁሉ የላከው በሐዋርያት በኩል ነበር፡፡ እርሱ «የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፤ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም፡፡ ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል» ብሎ በተናገረው መሠረት ኢየሱስ በምድር ከእነርሱ ጋር ሳለ ያልነገራቸውን መንፈስ ቅዱስ በወረደ (በመጣ) ጊዜ ሁሉን እንደነገራቸው እንገነዘባለን (ዮሐ.16፡12-13)፡፡ ሐዋርያትም ከጌታ ኢየሱስ በቀጥታ የተማሩትንና እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ የገለጠላቸውን የእግዚአብሔር ቃል በአይሁድም በአሕዛብም መካከል ያስተምሩ ነበር፤ ይሁንና ከሐዋርያት ጋር ጐን ለጐን የእግዚአብሔርን አሳብ ይገልጹ ዘንድ ከጌታ የተሰጡ ነቢያትም ነበሩ፤ እነዚህም የአዲስ ኪዳን ነቢያት ናቸው፤ ብዙ ጊዜ ከሐዋርያት ጋር አብረው የሚጠሩት ነቢያት የአዲስ ኪዳን ነቢያት ናቸው እንጂ የብሉይ ኪዳን ነቢያት አይደሉም፡፡ በሐዋርያት ዘመን የአዲስ ኪዳን መገለጥ ገና ባለመጠናቀቁና የአዲስ ኪዳን መጻሕፍትም ገና እየተጻፉ ስለነበር እግዚአብሔር ለሰው ያለውን ፈቃድና አሳብ በእነዚህ ነቢያት በኩል ይናገር ነበር፡፡
በትንቢተ ኢዩኤል ምዕ.2 ቊ.28-29 «ከዚህም በኋላ እንዲህ ይሆናል፤ መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈስሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልምን ያልማሉ፤ ጐበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፤ ደግሞም በዚያ ወራት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎች ላይ መንፈሴን አፈስሳለሁ፡፡» የሚል ትንቢትን እናነባለን፡፡ ይህንንም ጴጥሮስ በበዓለ ሃምሳ ስለ ክርስቶስ በሰበከ ዕለት መንፈስ ቅዱስ መውረዱን በተመለከተ ለማስረዳት ጠቅሶታል (የሐ.ሥ.2፡16-21)፡፡ ይህ ትንቢት እስራኤልን በተመለከተ በቀጥታ የሚፈጸምበት ጊዜ ወደፊት ሲሆን ሐሳቡ ግን በቤተክርስቲያን ጅማሬ ላይ የነበረውን የነቢያት አገልግሎት ጠባይም ለመረዳት ያስችለናል፡፡ በእርግጥም መንፈስ ቅዱስ በበዓለ ሃምሳ ከወረደ በኋላ ወንዶችና ሴቶች የሆኑ የጌታ ባሪያዎች በየስፍራው ትንቢት በመናገር ያገለግሉ ነበር፡፡ ለምሳሌ በኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያን ነቢያት እንደነበሩ «በዚያም ወራት ነቢያት ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ ወረዱ» ከሚለው ቃል እንረዳለን (የሐ.ሥ.11፡27)፤ ከእነርሱም አንዱ አጋቦስ የተባለው ነቢይ ነበር (ቊ.28)፡፡ እነዚህ ነቢያት በርናባስና ጳውሎስ ለአንድ ዓመት ያህል ወዳስተማሩባት ወደ አንጾኪያ መውረዳቸውም በዚያ ያለውን አገልግሎት በተሰጣቸው ጸጋ ለማገዝ እንደሆነ መገንዘብ እንችላለን፡፡ እንደዚሁም በዚያው በአንጾኪያም ነቢያት እንደነበሩ መጽሐፍ ቅዱስ ሲያስረዳ «በአንጾኪያ ባለችው ቤተክርስቲያን ነቢያትና መምህራን ነበሩ» በማለት ይናገራል (የሐ.ሥ.13፡1)፡፡ በቂሣርያም የወንጌላዊው የፊልጶስ ልጆች የሆኑና ትንቢትን የሚናገሩ አራት ደናግል ሴቶች ልጆች ነበሩ (የሐ.ሥ.21፡8-9)፤ በቆሮንቶስም እንዲሁ «ነቢያት» ተብለው የተጠሩ ሰዎች እንደነበሩ ግልጽ ነው (1ቆሮ.14፡29)፡፡
የነቢያት አገልግሎት
የአዲስ ኪዳን ነቢያት የነበራቸው የትንቢት አገልግሎት ሁለት ዓይነት ነበር፡፡ ይኸውም፡-
- 1. የወደፊት ነገሮችን መናገር
እግዚአብሔር ወሳኝ በሆኑ ታላላቅ ጉዳዮች ላይ ወደፊት ምን እንደሚሆን ለነቢያት ሲገልጥላቸው ክስተቱን፣ ቦታውንና፣ ትንቢቱ የሚፈጸምባቸውን ሰዎች በመጥቀስ ትንቢትን ይናገሩ ነበር፤ የዚህ ዓይነቱን ትንቢት በመናገር የታወቀው የአዲስ ኪዳን ነቢይ አጋቦስ ነበር፡፡ በሐ.ሥ.11፡27-28 ላይ «በዚያም ወራት ነቢያት ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ ወረዱ፤ ከእነርሱም አጋቦስ የሚሉት አንድ ሰው ተነሥቶ በዓለም ሁሉ ታላቅ ራብ ሊሆን እንዳለው በመንፈስ አመለከተ፤ ይህም በቀላውዴዎስ ቄሣር ዘመን ሆነ» የሚል ቃልን እናነባለን፡፡ እዚህ ላይ አጋቦስ በመንፈስ ሲያመለክት የምናየው ትንቢት ዓለም አቀፍ ረሃብን የሚመለከት ነበር፤ ይህ በመንፈስ የተገለጠውና ከመሆኑ አስቀድሞ የተነገረው ትንቢት የክርስትናን እውነተኝነት በመላው ዓለም ፊት የሚያረጋግጥ ነበር፤ እግዚአብሔርም እንዲህ ያለውን አለም አቀፍ ጉዳይ ከክርስቲያኖች መካከል ለሆኑት ነቢያቱ መግለጡ እርሱ እውቅና የሚሰጠው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ የተሰበከውንና በሐዋርያትም አማካኝነት በየስፍራው እየተሰበከ የነበረውን የአዲስ ኪዳን እምነት ማለትም ክርስትናን እንደሆነ በዚህች ዓለም ፊት አረጋግጧል፤ ያ በትንቢት የተነገረውም ዓለም አቀፍ ረሃብ ቀላውዴዎስ ቄሣር በተባለው የሮማ ገዢ (ንጉሥ) ዘመን መፈጸሙ የትንቢቱንም ሆነ የተናጋሪውን እውነተኝነት አረጋግጧል፡፡
እንደዚሁም አጋቦስ ያረገው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ልዩ ሐዋርያ አድርጎ ያስነሣውን ሐዋርያው ጳውሎስን የሚመለከት ትንቢትም ተናግሯል፤ ይህን በተመለከተ የተጻፈው ቃልም «... አያሌ ቀንም ተቀምጠን ሳለን ነቢይ የነበረ አጋቦስ የሚሉት አንድ ሰው ከይሁዳ ወረደ፡፡ ወደ እኛም መጣና የጳውሎስን መታጠቂያ ወስዶ የገዛ እጁንና እግሩን አስሮ «እንዲሁ መንፈስ ቅዱስ ይህ መታጠቂያ ያለውን ሰው አይሁድ በኢየሩሳሌም እንደዚህ ያስሩታል በአሕዛብም እጅ አሳልፈው ይሰጡታል ይላል አለ» በማለት ይናገራል (የሐ.ሥ.21፡10-11)፡፡ ጌታ ኢየሱስ ጳውሎስን «ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነው» ብሎ ከመጥራቱም በላይ «ስለ ስሜ ስንት መከራ ሊቀበል እንዲያስፈልገው እኔ አመለክተዋለሁና» በማለት ስለእርሱ ተናግሮአል (የሐዋ.ሥራ9፡15-16)፡፡ ስለሆነም ለጌታ ልዩ የተመረጠ መሣሪያ (ዕቃ) ስለነበረው ስለዚህ ሐዋርያ መታሰር መንፈስ ቅዱስ በነቢዩ በአጋቦስ የተናገረውን ትንቢት ሊገልጥ ቻለ፡፡ እንዲህ ካሉ ዐበይት ጉዳዮች ውጭ የእያንዳንዱን ክርስቲያን የሥራ፣ የትዳር ጉዳይ፣ ወይም የወደፊት ዕድልን የሚመለከት ትንቢት በእግዚአብሔር ስም ተነግሮ አያውቅም፤ በአጠቃላይ ታሪክና ዘመን ስፍራም የማይገድበውን ሥራ ሊሠሩ ጌታ በዓለም ላለች ቤተክርስቲያን የሚያስነሣቸውን የተመረጡ ሰዎችንና ባጠቃላይ ዓለምን ወይም ሕዝቡን የሚመለከት ጉዳይ ካልሆነ በቀር የእያንዳንዱን ግለሰብ የወደፊት ታሪክ ለመናገር እግዚአብሔር ነቢያትን አስነሥቶ አያውቅም፡፡ ስለሆነም ይህንን የሚያደርጉ ሰዎችም ቢሆኑ ራሳቸውን እየመረመሩ ንስሐ በመግባት እግዚአብሔር በቃሉ ወዳስቀመጠው እውነት ሊመለሱ ይገባቸዋል፡፡
- 2. የሚያንጽ ቃልን መናገር
የአዲስ ኪዳን ነቢያት አስፈላጊ በሚሆን ጊዜ አንድ የተለየ ጉዳይን በተመለከተ እግዚአብሔር የሚገልጥላቸውን የወደፊት ነገር የሚናገሩ ከመሆናቸውም ሌላ የሚያንጽ ቃልን በመናገር ያገለግሉ ነበር፡፡ እንዲያውም የነቢያት መደበኛ አገልግሎታቸው ለማነጽ የሚሆን ቃልን ለሰዎች መናገር ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ነቢያት በማኅበር የነበራቸው አገልግሎት የዚህ ዓይነቱ ትንቢት ነበር፡፡ የቆሮንቶስ አማኞች «ፍቅርን ተከታተሉ መንፈሳዊ ስጦታንም ይልቁንም ትንቢት መናገርን በብርቱ ፈልጉ» የተባሉት የሚያንጽና የሚመክር የሚያጽናናም ቃል ማግኘት እንዲችሉ ነው (1ቆሮ.14፡1)፡፡ በልሳን ከመናገር ይልቅ ትንቢት መናገር የበለጠበት ምክንያትም ይኸው ነው፤ «በልሳን የሚናገርስ ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰው አይናገርም፤ የሚያስተውለው የለምና፤ በመንፈስ ግን ምስጢርን ይናገራል፡፡ ትንቢትን የሚናገር ግን ለማነጽና ለመምከር ለማጽናናትም ለሰው ይናገራል፡፡ በልሳን የሚናገር ራሱን ያንጻል፤ ትንቢትን የሚናገር ግን ማኅበሩን ያንጻል፤ ሁላችሁ በልሳኖች ልትናገሩ እወድ ነበር፤ ትንቢትን ልትናገሩ ግን ከዚህ ይልቅ እወዳለሁ፤ ማኅበሩ ይታነጽ ዘንድ ንግግሩን ባይተረጉም በልሳኖች ከሚናገር ይልቅ ትንቢት የሚናገር ይበልጣል፡፡» ተብሎ በተጻፈው መሠረት ነቢያት ማኅበርን የሚያንጽ ቃል የሚናገሩበት አገልግሎት ነበራቸው (1ቆሮ.14፡2-5)፤ በዚህ ዓይነት ወደ ማኅበር የሚመጣው ቃል ከማነጽ ጋር የመምከርና የማጽናናትም ሥራ ይሠራል፡፡
የዚህ ዓይነቱ ትንቢት በመደበኛ ሁኔታ የሚመጣው ለአማኞች ቢሆንም በዚያ ስፍራ ግን ድንገት የማያምን ሰው ቢገኝ እርሱንም የሚጠቅም ሆኖ ይሠራል፡፡ ይህን በተመለከተም «እንግዲህ ማኅበር ሁሉ አብረው ቢሰበሰቡ ሁሉም በልሳኖች ቢናገሩና ያልተማሩ ወይም የማያምኑ ሰዎች ቢገቡ አብደዋል አይሉምን? ሁሉ ትንቢት ቢናገሩ ግን የማያምን ወይም ያልተማረ ሰው ቢገባ በሁሉ ይወቀሳል በሁሉም ይመረመራል በልቡም የተሰወረ ይገለጣል፤ እንዲሁም እግዚአብሔር በእውነት በመካከላቸው ነው ብሎ እየተናገረ በፊቱ ወድቆ ይሰግዳል» ተብሎ የተጻፈው ቃል ያስረዳል (1ቆሮ.14፡23-25)፤ ይህ በማኅበር ከተሰበሰቡ ሰዎች መካከል አንድን የሚያምን ሰው ለይቶ በመጠቆም «እንዲህ ያለ የተሰወረ ነገር በልብህ ውስጥ አለ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር» በማለት የሚነገር ትንቢት አይደለም፤ ነገር ግን ያ ሰው ለጉባኤ ሁሉ የቀረበውን የሚያንጽ ቃል በሚሰማ ጊዜ ግን መንፈስ ቅዱስ በዚያ ቃል የእርሱን ማንነት ገልጦ ለራሱ ያሳየዋል፡፡ ትንቢታዊ ቃሉን የተናገረው ወንድም የተናገረው ቃል በማን ልብ ውስጥ ምን የተሰወረ ነገር እንደተገለጠ ላያውቅ ይችላል፤ ሆኖም በዕብ.4፡12 ላይ «የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፤ የሚሠራም ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፤ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፤ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል» ተብሎ እንደተጻፈ በመንፈስ ቅዱስ ቊጥጥር ሥር ሆኖ የሚነገር የእግዚአብሔር ቃል የተሰወረ ማንነትን ይመረምራል (ዕብ4፡12)፤ ወደ ንስሐም ይመራል፡፡
በሐዋርያት ዘመን በአማኞች መካካል አንዳንድ የስህተት ትምህርትና የምግባር ችግሮች በሚከሰቱበት ወቅት ነቢያት በምክር ቃል አማኞችን ያበረታቱ ነበር፤ የይሁዳና የሲላስ የነቢይነት አገልግሎት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጠው በዚህ ዓይነት ነው፤ በሐ.ሥ.15፡32 ላይ «ይሁዳና ሲላስም ደግሞ ነቢያት ነበሩና ወንድሞችን በብዙ ቃል መክረው አጸኑአቸው» ተብሎ ስለእነርሱ የተጻፈው ቃል እንደሚያስረዳው የይሁዳና የሲላስ የነቢያትነታቸው አገልግሎት ወንድሞችን በብዙ ቃል መክሮ ማጽናት ነበር፡፡ ይህንንም ያደረጉት ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ መጥተው ነው፤ ቀደም ሲል «ካልተገረዛችሁ ትድኑ ዘንድ አትችሉም» በሚለው የሐሰት ትምህርት ምክንያት በአንጾኪያ ቤተክርስቲያን ባሉ አማኞች ዘንድ ተፈጥሮ የነበረው ክርክርና ጥል በኢየሩሳሌም በተደረገው ጉባዔ መፍትሔ ቢያገኝም በነገሩ መንፈሳዊ ሁኔታቸው የተናጋባቸውን አማኞች ለማበረታታትና ለማጽናት የቃል አገልግሎት ያስፈልግ ነበር፤ ስለሆነም በብዙ ቃል መክረው አጸኗቸው፡፡
አማኞች ለመተናነጽ በሚሰበሰቡ ጊዜ ትንቢትን በብርቱ እንዲፈልጉ በታዘዘበት በ1ቆሮ.14 ውስጥ ነቢያቱ እንዴት መናገር እንዳለባቸው የተደነገገ ሥርዓትም ነበር፡፡ በቊ.29 ላይ «ነቢያትም ሁለት ወይም ሦስት ሆነው ይናገሩ፤ ሌሎችም ይለዩአቸው» ይላል፡፡ በዚህም ትንቢትን መናገር ያላቸው ነቢያት ቊጥራቸው ሁለት ወይም ሦስት ተብሎ ተወስኗል፤ ሌሎች ሊለዩአቸው እንደሚገባም ተነግሯል፤ ይህም ማለት የተናገሩበት መንፈስም ሆነ የተናገሩት ቃል ከእግዚአብሔር ስለመሆኑ በእግዚአብሔር ቃል መፈተሽ አለበት ማለት ነው፤ ምክንያቱም ሐሰተኞች ነቢያትም በሕዝቡ መካከል ገብተው ዕድሉን በመጠቀም ሊናገሩ የሚችሉበት አጋጣሚ ስለሚኖር ሌሎች ይለዩአቸው ተባለ፤ ይህም የእውነትንና የስህተትን መንፈስ ለይቶ በማወቅ ከስህተት መንፈስ ለመጠበቅ ለእውነት መንፈስ ለመታዘዝ ያስችላል (1ዮሐ.4፡1-6)፡፡ እንደዚሁም ትንቢታዊ ቃል በሚነገርበት ጊዜ ተራ በመጠበቅ ሁከት በሌለበት መንገድ ሊሆን እንደሚገባም ተደንግጓል፡፡ ከቊ.30ን «በዚያ ለሚቀመጥ ለሌላ ግን አንድ ነገር ቢገለጥለት ፊተኛው ዝም ይበል፡፡ ሁሉ እንዲማሩ ሁሉም እንዲመከሩ ሁላችሁ በእያንዳንዳችሁ ትንቢት ልትናገሩ ትችላላችሁ፡፡ የነቢያት መናፍስት ለነቢያት ይገዛሉ፡፡ እግዚአብሔርስ የሰላም አምላክ ነው እንጂ የሁከት አምላክ አይደለምና» ይላል፡፡ በዚህ ክፍል እንደተገለጠው የእግዚአብሔር ቃል በጉባዔ መካከል ሲገለጥ በመደማመጥና ተራ በመጠበቅ ሊነገር የሚገባ መሆኑን እንገነዘባለን፤ የሚያንጸው ቃል በሚነገርበት ጊዜ አንዱ ሲናገር ሌላው ዝም እያለ ሊሆን ይገባል፡፡ «ሁላችሁ በእያንዳንዳችሁ ትንቢት ልትናገሩ ትችላላችሁ» ሲልም «አንድ በአንድ ትንቢት ልትናገሩ ትችላላችሁ» ለማለት ነው፡፡ ቃሉ የሚያመለክተው በየተራ መናገርን ነው፤ ይህንንም ለመረዳት ከአማርኛው ሌላ የሌሎች ቋንቋዎች መጽሐፍ ቅዱስን መመልከት ይቻላል፡፡ እግዚአብሔር የሰላም አምላክ እንጂ የሁከት አምላክ አለመሆኑም የሚገለጠው በመደማመጥ ትንቢታዊ ቃልን መከፋፈል ሲቻል ነው፡፡
- ሐሰተኞች ነቢያት
የእግዚአብሔርን እውነት ለመበረዝም ሆነ ለማጥፋት እንዲሁም የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለማሳት ጠላት ከሚጠቀምባቸው መሣሪያዎች መካከል ሐሰተኞች ነቢያት ዋነኞቹ ናቸው፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን አክዓብ የተባለው የሰማርያ ንጉሥ በሐሰት ትንቢትን የሚናገሩለት 400 ነቢያት ነበሩት፤ ኤልዛቤልን ያገባውንና በኣልና አስታሮትን የተከተለውን ይህን ክፉ ንጉሥ እግዚአብሔር ለሰይጣን አሳልፎ ሰጥቶት እንደነበርና ሰይጣንም በንጉሡ ነቢያት አፍ ሐሰተኛ መንፈስ ሆኖ እንዳሳሳተው እናነባለን (1ነገሥ.22፡5-36)፡፡ እንደዚሁም በነቢዩ ኤርምያስ ዘመንም የሐሰት ነቢያት ነበሩ፤ እነዚህም እግዚአብሔር ሳይልካቸው በእግዚአብሔር ስም ትንቢትን የሚናገሩ ነበሩ (ኤር.28፡15፤ 29፡21-23)፤ ልክ በዚሁ ዓይነት በአዲስ ኪዳንም በዘመነ ሐዋርያት «ሐሰተኞች ነቢያት በሕዝቡ መካከል ነበሩ» (2ጴጥ.2፡1)፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደዚህ ያሉ ሐሰተኞች ሊመጡ እንደሚችሉ ሲናገር «የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውስጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኩላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ» በማለት አስጠንቅቋል (ማቴ.7፡15)፤ በመሆኑም ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም በወጡ ጊዜ ሐዋርያው ዮሐንስ በመልእክቱ ሲጽፍ «ወዳጆች ሆይ፡- መንፈስን ሁሉ አትመኑ፤ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደሆነ መርምሩ፤ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና» በማለት አስገንዝቧል (1ዮሐ.4፡1)፡፡ በዚያን ጊዜ ከእግዚአብሔር የተላኩ እውነተኞች ነቢያት ስለነበሩ ሐሰተኞቹም በእግዚአብሔር ስም ይመጡ ስለነበር መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደሆነ መመርመር በእጅጉ አስፈላጊ ነበር፤ ስለሆነም አስቀድመን እንዳልነው ነቢያት ትንቢት ሲናገሩ ሌሎች እንዲለዩአቸው ሊደነገግ ቻለ፡፡
- የነቢያት አገልግሎት በዘመናችን
ነቢያት ከሐዋርያት ጋር የነበሩ የመሠረት ስጦታዎች እንደሆኑ በኤፌ.2፡20 ላይ «በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል» የሚለውን በመጥቀስ ማስረዳታችን ይታወሳል፡፡ እውነቱ ይህ ሆኖ እያለ በቤተክርስቲያን ዘመን መጨረሻ ገደማ በምንገኝበት በዚህ ዘመን ነቢያት ነን የሚሉ ብዙ ሰዎች በየስፍራውና በየጊዜው መነሣታቸው አልቀረም፤ ከእግዚአብሔር ቃል የተለየ መገለጥና ራእይ ተቀብያለሁ በማለት በእግዚአብሔር ስም የልባቸውን አሳብ የሚናገሩና ብዙዎችን እያሳቱ የሚገኙ ሐሰተኞች ነቢያት በብዙ ክርስቲያኖች መካከል ይገኛሉ፡፡ በብሉይ ኪዳን የነበሩ የሐሰት ነቢያትን በተመለከተ በኤር.23፡16 ላይ የተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል «የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ትንቢት የሚናገሩላችሁን የነቢያትን ቃል አትስሙ፤ ከንቱነትን ያስተምሯችኋል፤ ከእግዚአብሔር አፍ ሳይሆን ከገዛ ልባቸው የወጣውን ራእይ ይናገራሉ» ይላል (ኤር.23፡16)፡፡ በዙሪያችን ባለው ሃይማኖተኛ ዓለም እንዲህ ያለ አገልግሎት እየታየ በመሆኑ መልእክቱ ለዚህ ዘመን ክርስቲያኖችም በእጅጉ ጠቃሚ ነው፤ በመድረክ ላይ ቆሞ «በዚያ በኩል ያለህ ወይም ያለሽ፣ እንዲህ ያለ ልብስ የለበስክ ወይም የለበስሽ፤ በእንዲህ ያለ አሳብ ውስጥ የምትገኝ ወይም የምትገኚ ... እንዲህ ይልሃል ወይም ይልሻል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር» በማለት የግለሰቦችን ኑሮ የሚመለከቱ መልእክቶችን ማስተላለፍ ከእግዚአብሔር ቃልና ከእግዚአብሔር መንፈስ ያልተገኘ እና ሰው ነቢይ ለመባል ሲፈልግ ከምስኪን ልቡ የሚያወጣውና በድፍረት የሚናገረው መላምት እንደሆነ መገንዘብ ያሻል፡፡ መነሻቸው የሰው ልብ ወይም ወቅታዊ ሁኔታ የሆነላቸውን እነዚህን አሳሳች መልእክቶች እንደ ትንቢት በመቁጠር ከመነዳት መቆጠብ ትልቅ አስተዋይነት ነው፡፡ ዓይን በተጨፈነ ቊጥር በአእምሮ ውስጥ የሚያልፍ ብዙ የተዘበራረቀ አሳብና ትርዒት ሊኖር ይችላል፤ ከዚያ መሐል አንዱን በመገለጥ ያገኘሁት ትንቢት ነው ብሎ በእግዚአብሔር ስም ለመናገር መዳፈር የእግዚአብሔር ነቢይ አያደርግም፤ ሆኖም በዚህ ዓይነት ነቢያት ነን በሚሉ ሰዎች ከሚመሩት የዋሃን መካከል «እግዚአብሔር ይህን ትዳር ቆርጬዋለሁ ብሏል» ተብለው ትዳራቸውን ያፈረሱ፣ «እኔ ለራሴ ስለምፈልግህ ሥራህን እንድትተው፣ ወይም ገዳም እንድትገባ ይልሃል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር» ተብለው ከጥሩ ሥራቸው ወይም ትምህርታቸው እንዲፈናቀሉና ወደማኅበራዊ ቀውስ ውስጥ እንዲገቡ የተደረጉ፣ እንዲሁም «እኔ የምፈውስህ በእጅህ የያዝከውን መድኃኒት ስትጥል ነው ብሎሃል እግዚአብሔር» እየተባሉም በየጠበል ቤቱና በየጸሎት ቤቱ ተንከራተው በመጨረሻም ለኅልፈት የሚዳረጉ ብዙዎች መሆናቸው በእጅጉ የሚያሳዝን ነው፡፡ ሐዋርያው ጴጥሮስ የሐሰተኞች ነቢያትን እና የሐሰተኞች አስተማሪዎችን ጠባዮች በተናገረበት ክፍል «ነገር ግን ሐሰተኞች ነቢያት ደግሞ በሕዝቡ መካከል ነበሩ፤ እንዲሁም በመካከላችሁ ደግሞ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ይሆናሉ፤ እነርሱም የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ክደው የሚፈጥንን ኑፋቄን አሾልከው ያገባሉ፤ ብዙዎችም በመዳራታቸው ይከተሏቸዋል፤ በእነርሱም ጠንቅ የእውነት መንገድ ይሰደባል፤ ገንዘብንም በመመኘት በተፈጠረ ነገር ይረቡባችኋል፤ ፍርዳቸውም ከጥንት ጀምሮ አይዘገይም፤ ጥፋታቸውም አያንቀላፉም» ብሏል (2ጴጥ.2፡1-3)፡፡ ስለሆነም እነዚህ ሰዎች ኑፋቄን አሾልከው በማስገባት፣ በመዳራት፣ ገንዘብን በመመኘት የሚታወቁ ናቸው፤ ስለ እኔ የወደፊት ዕድል ያውቁልኝ ይሆናል ብለው ባለማዋቅ ተጠግተዋቸው የተበዘበዙና የተነወሩ ሰዎች ይህን ሊናገሩ ይችላሉ፤ ስለሆነም ጌታ «ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ» እንዳለው በዘመናችንም ነቢያት ነን የሚሉት ሁሉ እነዚህን መራራ ፍሬዎች የያዙ ስለሆኑ ሐሰተኝነታቸውን አውቀን ልንርቃቸው ይገባል፡፡
ነገር ግን በሐዋርያት ዘመን የነበሩት ነቢያት የሚያገለግሉት የሚያንጽ፣ የሚመክር፣ የሚያጽናና የሚወቅስ ወይም የሚመረምር ቃልን የማምጣት አገልግሎት በዘመናት ሁሉ አስፈላጊ ነው፤ ስለሆነም ይህን አገልግሎት የሚሰጡ ወንድሞች በየአጥቢያ ጉባኤው ይኖራሉ፡፡ «ነቢያት» ሆነው ለቤተክርስቲያን የተሰጡ ስጦታዎች ግን በዚያው በሐዋርያት ዘመን የነበሩት ብቻ እንደሆኑ የመሠረት ስጦታ ከመሆናቸው አንጻር እንረዳለን፤ ስለዚህ በዘመናችን የሚያንጽ ቃልን በጊዜው የሚያመጡ ወንድሞች ነቢያት ተብለው ሊጠሩ አይችሉም፤ በወንጌል ሰባኪነት ወይም በእረኝነትና በአስተማሪነት ከተሰጡን ወይም በሌላ ጸጋ ከሚያገለግሉ ወንድሞች መካከል ትንቢታዊ የሆነ የጊዜው ቃልን የሚያመጡ ወንድሞች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ይህ ግን እነርሱን ነቢያት አያደርጋቸውም፤ ምክንያቱም ነቢያት ለመባል የሚያንጽ ቃልን የሚያመጡ ብቻ ሳይሆኑ ተአምራዊ በሆነ መገለጥ እግዚአብሔር ለሕዝብ ወይም ለዓለም የሚሆን የወደፊት ነገርን የሚመለከት ትንቢት ወይም አዲስ መገለጥን የሚናገሩ መሆን አለባቸው፤ ሆኖም የወደፊት ነገሮችን በተመለከተ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ የተነገሩ ትንቢቶች የተመዘገቡ በመሆናቸው፣ በሐዋርያው ጳውሎስም በኩል የመጨረሻውን ዘመን አስመልክቶ ብዙ ነገር ስለተጻፈ በተለይ ደግሞ በዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ በቤተክርስቲያን ዘመንም ሆነ ከዚያ በኋላ የሚሆነው እስከ ዓለም ፍጻሜ ያለው ነገር በትንቢት የተነገረ በመሆኑ እግዚአብሔር ለሰው የሚገልጠው ነገር ተገልጦ ተጠናቅቋል፡፡ የክርስትናም እውነትነት እነአጋቦስን የመሳሰሉ ነቢያት የተናገሩአቸው ታላላቅ ትንቢቶች በመፈማቸውና ሌሎችም ተአምራትና ድንቆችም በመደረጋቸው ተረጋግጧል፡፡ በእነዚህ ተአምራዊ ትንቢቶችና በሎሎችም ድንቅ ምልክቶች የጸናው ቃልም በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎልናል፤ ስለዚህ ሁሉንም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምናገኘው በመሆኑ፣ በዚያም ያልተገለጠ የቀረ መገለጥ ስለሌለ፣ እግዚአብሔር ከሐዋርያት ዘመን በኋላ ነቢያትን አስነሥቶ አያውቅም፡፡ አሁንም ሆነ ወደፊት እግዚአብሔር ነቢያት አድርጎ የሚያስነሳቸው ሰዎች የሉም፡፡
በመሠረቱ በዚህ ዘመን ያለነው አማኞች በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስ ከወረደ ጊዜ አንሥቶ ባለችው አንዲት ቤተክርስቲያን ውስጥ የምንገኝ በመሆናችን ለእኛም ቢሆን የተሰጡት ነቢያት እነዚያው በሐዋርያት ዘመን የነበሩት ነቢያት ናቸው፤ ሐዋርያው ጳውሎስ «እግዚአብሔር በቤተክርስቲያን አስቀድሞ ሐዋርያትን፣ ሁለተኛም ነቢያትን፣ ሦስተኛም አስተማሪዎችን፣ ቀጥሎም ተአምራት ማድረግን፣ ቀጥሎም የመፈወስ ስጦታ፣ እርዳታንም፣ አገዛዝንም፣ የልዩ ልዩ ዓይነት ልሳኖችንም አድርጓል» በማለት ጽፏል (1ቆሮ.12፡28)፤ በዚህ ንባብ ውስጥ ቤተክርስቲያን የተገለጠችው በዓለም አቀፍና በዘመን አቀፍ ገጽታዋ ወይም በአንድ አካልነቷ መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል፤ እግዚአብሔር በቤተክርስቲያን ካደረጋቸው ከእነዚህ ስጦታዎች መካከል ሐዋርያትና ነቢያት ቤተክርስቲያን በምትመሠረትበት ጊዜ የነበሩ ስጦታዎች መሆናቸውን ደግሞ በኤፌ.2፡20 ላይ «በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል» ከሚለው የእግዚአብሔር ቃል ተምረናል፤ ስለሆነም በ1ጢሞ.3፡15 ላይ «የእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት» የተባለችው ቤተክርስቲያን ተሠርታ በመጠናቀቅ ላይ ባለችበት በዚህ ዘመን በመሠረቱ ላይ እንደነበሩት ሐዋርያትና ነቢያት ሌሎች ሐዋርያትና ነቢያት ይነሣሉ ብሎ መጠበቅ የእግዚአብሔርን አሠራር አለማወቅ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ በሐዋርያትና በነቢያት ይነገር የነበረው ቃል ሁሉ የእግዚአብሔር እስትንፋስ በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኘዋለን፤ ስለዚህ አማኞች ይህንን ተገንዝበው በቀደመውና በመጻሕፍት ላይ በተመዘገበው ትንቢት ብቻ ሊመሩ ይገባቸዋል፤ ጴጥሮስ ይህን በተመለከተ ሲጽፍ «ከእርሱም ይልቅ እጅግ የጸና የትንቢት ቃል አለን፡፡ ምድር እስኪጠባ ድረስ የንጋትም ኮከብ በልባችሁ እስኪወጣ ድረስ ሰው በጨለማ ስፍራ የሚበራን መብራት እንደሚጠነቀቅ ይህን ቃል እየጠነቀቃችሁ መልካም ታደርጋላችሁ፡፡ ይህን በመጀመሪያ እወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም...» ብሏል (2ጴጥ.1፡19-20)፡፡ ስለሆነም የቀደሙት ነቢያት በመጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈው በጸናው የትንቢት ቃል በኩል ዛሬም ስላሉ በዚያው ልንጸና ይገባል እንጂ «የልብን አዋቂ የሆነ መገለጥ ያለው ነቢይ አለ» በተባለ ቊጥር «የወደፊት ዕድሌ ምን እንደሆነ ይነግረኝ ይሆናል» በማለት እንዲሁም «ያለኝ እንዲባረክልኝ ይጸልይልኛል» ብሎ ለየት ያለ ግምት በመስጠት ገንዘብንና ጊዜን ማባከን ተገቢ አይደለም፡፡ በዚህ ዓይነት ባለማወቅና በየዋህነት ሁለንተናዊ ኪሳራ የደረሰባቸውና ነቢይ ነው በተባለው ሁሉ ዘንድ እየተዘዋወሩ በመባከን ዕረፍት ያጡ ብዙ ሰዎች ወደ ጸናው የትንቢት ቃል እንዲመለሱ በጌታ ፍቅር ይመከራሉ፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል በጉባኤ ሆነን ስንሰማም ሆነ በየግላችን መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ ይህንን የጸና የትንቢት ቃል እናገኛለን፡፡ በዚህ ዓይነት እግዚአብሔር በቃሉ በኩል በዚያ ወቅት ያለንበትን ሁኔታ ይናግረናል፡፡ ነቢያቱ ሊነሱ ባይችሉም የቀደሙት ነቢያት የማነጽ የመምከርና የማጽናናት አገልግሎት ግን በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ከወንድሞች በአንዱ በኩል ሊደርሰን እንደሚችል ልናምን ይገባል፡፡
-
3. ወንጌል ሰባኪዎች
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ ለአሥራ አንዱ ሐዋርያት ተገልጦ «ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ» (ማር.16፡15) ብሎ የሰጣቸውን መመሪያ ስንመለከት በዓለም ላለው ፍጥረት ሁሉ የሚያስፈልገውን የወንጌል ሥራ ሰፊነት እንገነዘባለን፡፡ ጌታም በዚህ ሰፊ ሥራ ላይ የሚተጉ ሠራተኞችን ለቤተክርስቲያን ይሰጣል፤ እነዚህም «ወንጌል ሰባኪዎች» ተብለው ተጠርተዋል፡፡ እነዚህ ስጦታዎች ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በተመለከተ የእርሱን አዳኝነት እና በጠቅላላ ማንነቱን ለሰዎች የሚሰብኩ ናቸው፡፡
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ የመጀመሪያው የወንጌል ሰባኪ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በኢሳ.61፡1 ላይ «የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድሆች የምሥራችን እሰብክ ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና፤ ልባቸው የተሰበረውን እጠግን ዘንድ ለተማረኩት ነጻነትን ለታሰሩትም መፈታትን እናገር ዘንድ ልኮኛል» የሚል ቃል እናነባለን፡፡ በሉቃ. 4፡17 ላይ እንደምንመለከተው ጌታችን ኢየሱስ ይህ ቃል እርሱን የሚመለከት መሆኑን ራሱ አስረግጦ የተናገረ ሲሆን ይህ ቃል ሲጠቀስም «የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛል ...» ተብሏል፡፡ ስለሆነም ጌታችን በምድር ላይ በሕዝብ መካከል የመመላለሱ ዋና ዓላማ ወንጌልን ለመስበክ ነበር፡፡ በዚሁ የወንጌል ስብከት ሥራው ጊዜ የእርሱን ማንነት ሊጠይቁ ከመጥምቁ ዮሐንስ ዘንድ ተልከው ለመጡት ደቀመዛሙርት ጌታ የሰጣቸው መልስ «ሄዳችሁ ያያችሁትን፣ የሰማችሁትንም ለዮሐንስ አውሩለት፤ ዕውሮች ያያሉ አንካሶች ይሄዳሉ፤ ለምጻሞች ይነጻሉ፤ ደንቆሮችም ይሰማሉ፤ ሙታንም ይነሣሉ፤ ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል፤ በእኔም የማይሰናከለው ሁሉ ብፁዕ ነው» የሚል ነበር (ማቴ.11፡4-6)፡፡ ስለሆነም የወንጌል ሰባኪነት አገልግሎት ምን እንደሚመስል ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በሰውነቱ በሰጠው አገልግሎት ውስጥ በግልጽ ማየት እንችላለን፡፡ በተለይም ወንጌል በእርግጥም የምሥራች መሆኑን ማስተዋል ይቻላል፤ ከፍ ብለው በተጠቀሱት ክፍሎች ድሆች የተባሉት በኢሳይያስ 61 ላይ ልባቸው የተሰበረ፣ የተማረኩ .... ተብለው የተገለጡት ናቸው፡፡ ለእነዚህ ሰዎች በክርስቶስ የሚገኘውን ሰላምና ዕረፍት እንዲሁም አርነት መስበክ ታላቅ የምሥራች ነው፤ ወንጌል የሚባለው ይኸው ነውና፡፡
ሐዋርያትን «ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ» (ማር.16፡15) ተብሎ በተሰጣቸው መመሪያ መሠረት የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ በዋነኛነት ሠርተዋል፤ ሐዋርያው ጴጥሮስ «ወንድሞች ሆይ አሕዛብ ከአፌ የወንጌልን ቃል ሰምተው ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር በመጀመሪያው ዘመን ከእናንተ እኔን እንደመረጠኝ እናንተ ታውቃላችሁ» ብሎ እንደተናገረ እናነባለን (የሐ.ሥ.15፡7)፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም በኤፌ.3፡7 ላይ «እንደ ኃይሉ ሥራ እንደተሰጠኝም እንደ እግዚአብሔር ጸጋ ስጦታ መጠን የወንጌል አገልጋይ ሆንሁለት» ብሎ ሲጽፍ በ2ጢሞ.1፡11 ደግሞ «እኔ ሰባኪና ሐዋርያ አሕዛብንም አስተማሪ እንድሆን በተሾምሁበት በወንጌል ....» እያለ ሲጽፍ እንመለከታለን፤ እንዲሁም ይኸው ሐዋርያ በሮሜ15፡19 ላይ «ስለዚህ ከኢየሩሳሌም ጀምሬ እስከ እልዋሪቆን ድረስ እየዞርሁ የክርስቶስን ወንጌል ፈጽሜ ሰብኬአለሁ» በማለት ጽፏል፡፡ በመሆኑም የወንጌል ሰባኪነት (የወንጌላዊነት) ሥራ በሐዋርያነት ሥራ ውስጥ የሚገኝ አገልግሎት እንደሆነ በዚህ መረዳት እንችላለን፡፡
ሐዋርያት የወንጌላዊነት ሥራን የሠሩ ቢሆንም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አካሉን ለማነጽ ከሰጣቸው ስጦታዎች መካከል የወንጌል ሰባኪዎች (ወንጌላውያን) ራሳቸውን የቻሉ ስጦታዎች አድርጎ መስጠቱን ማስተዋል ይገባል፡፡ በመሆኑም የወንጌል ሰባኪዎች ከአምስቱ ስጦታዎች አንዱ ሆነው ተገልጠዋል፡፡ በዚህ ዓይነት ሐዋርያት ሳይሆኑ የወንጌላዊነትን ሥራ ብቻ የሠሩ አገልጋዮችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኛለን፡፡ በተለይም በሰማርያ ወንጌልን የሰበከው ፊልጶስ ወንጌላዊ እንደነበር በግልጽ ተጽፎልናል፡፡ በሐ.ሥ.21፡8 ላይ «በነጋውም ወጥተን ወደ ቂሣርያ መጣን ከሰባቱም አንድ በሚሆን በወንጌላዊው ፊልጶስ ቤት ገብተን በእርሱ ዘንድ ተቀመጥን» ይላል፡፡ ይህ ፊልጶስ በሐ.ሥ.6፡5 ከተዘረዘሩት ሰባት የማዕድ አገልጋዮች አንዱ እንደሆነ «ከሰባቱ አንዱ በሚሆን» በሚለው አገላለጽ እንረዳለን፤ ሆኖም «ወንጌላዊው» ተብሎ በመጠራቱ የወንጌላዊነትን ሥራ እንዲሠራ የወንጌል ሰባኪ ሆኖ ለቤተክርስቲያን የተሰጠ እንደነበር ግልጽ ነው፡፡ ይህም የወንጌል ሰባኪነት ሥራው በሰማርያ ከተማ ተገልጧል፡፡ ወደዚያም ወርዶ ክርስቶስን ሰበከላቸው (የሐ.ሥ.8፡5)፡፡ ወንጌል ደግሞ ስለ ክርስቶስ የሚናገር መልካም የምሥራች በመሆኑ «ክርስቶስን ሰበከላቸው» ሲል ወንጌላዊነቱን ያጎላዋል፡፡ እንደዚሁም የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብ ላገኘው ኢትዮጵያዊ ጃንደረባም የሰበከውን ቃል በተመለከተ «ፊልጶስም አፉን ከፈተ፤ ከዚህም መጽሐፍ ጀምሮ ስለ ኢየሱስ ወንጌልን ሰበከለት» ተብሎ ተጽፏል (የሐ.ሥ.8፡35)፡፡ ስለሆነም የፊልጶስ የወንጌል ሰባኪነት አገልግሎት በየዘመናቱ የወንጌል ሰባኪ ሆነው ለሚሰጡ ወንድሞች አብነትና ምሳሌ የሚሆን ነው፡፡ እንዲሁም ከጳውሎስ ጋር አብረው ከሠሩ ወንድሞች መካከል ብዙዎቹ የወንጌል ሰባኪዎች ነበሩ፤ ለምሳሌ ጢሞቴዎስን በተመለከተ ሐዋርያው ጳውሎስ ሲመሰክር «ስለእምነታችሁ እንዲያጸናችሁና እንዲመክራችሁ ወንድማችንን የእግዚአብሔርንም አገልጋይ ከእኛ ጋርም አብሮ በክርስቶስ ወንጌል የሚሠራውን ጢሞቴዎስን ላክነው» በማለት ጽፎ እናገኛለን (1ተሰ.3፡2-3)፡፡ ስለሆነም ሐዋርያት ሳይሆኑ «ወንጌል ሰባኪዎች» ብቻ ሆነው የተሰጡ እንዲህ ያሉ አገልጋዮች በመጀመሪያይቱ ቤተክርስቲያን ውስጥ ነበሩ፡፡
ወንጌል ሰባኪዎች መልካሙን የምሥራች ለማያምኑ ሰዎች የሚሰብኩ ማለትም የክርስቶስን አዳኝነት ላልዳኑ ሰዎች የሚናገሩ አገልጋዮች እንደመሆናቸው መጠን በየዘመናቱ የሚያስፈልጉ ስጦታዎች ናቸው፡፡ ስለሆነም በዘመናችንም ቢሆን ጌታ የሚሰጠን የወንጌል ሰባኪዎች (ወንጌላውያን) አሉ፤ እነርሱም ላመኑ ሰዎች ስለጌታ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስበክ ሊያገለግሉ ቢችሉም ዋነኛው የአገልግሎታቸው ስፍራ ግን በዓለም ላሉ ለማያምኑ ሰዎች መልካሙን የምሥራች መናገር ነው (ሮሜ.10፡14-16)፡፡ ሆኖም በወንጌል ሰባኪነት ለማገልገል አስቀድሞ የተሰበሰበ ሕዝብ ለማግኘት መፈለግ በዘመናችን ባለው የወንጌል አገልግሎት ላይ የሚታይ ዓይነተኛ ችግር ነው፡፡ ይህም ምንም ሳይደክሙና ዋጋ ሳይከፍሉ አስቀድሞ በተዘጋጀ መድረክ ላይ ብቻ ለመስበክ ከሚኖር ተገቢ ያልሆነ ጥማት የሚመጣ ችግር ነው፡፡ በዚህ ዓይነት የወንጌል ሰባኪ ነኝ ማለት ራስን ማሰማራት እንጂ የአገልግሎቱን ጸጋ ከጌታ ተቀብሎ በራሱ በጌታ መሰማራት አይደለም፤ ጌታ በእርግጥ ያሰማራው የወንጌል ሰባኪ የተሰባሰበ ሕዝብ እና የተዘጋጀ መድረክ ሲያገኝ ብቻ ሳይሆን ምንም አማኝ በሌለበት አካባቢም ክርስቶስን ለመስበክ የታመነ ነው፡፡ እንዲያውም በዋናነት የተጠራው ለዚህ እንደሆነ የሚረዳ አገልጋይ ነው፡፡
ወንጌል ሰባኪዎች ወደዚህ አገልግሎት የሚመጡት እንዴት እንደሆነ ስናስብ እነርሱን የሚሰጠውና የሚያሰማራው የቤተክርስቲያን ራስ የሆነው ክርስቶስ መሆኑን ምን ጊዜም መዘንጋት አይገባም፡፡ ወንጌላውያን በአንድ በታወቀም ሆነ ባልታወቀ የቲዎሎጂ ት/ቤት በወንጌላዊነት ሠልጥነው የተመረቁ ሊሆኑ እንደሚገባቸው ፈጽሞ መታሰብ የለበትም፡፡ ወንጌላዊነትን እንደ አንድ የሥራ መደብ ከተለያዩ የቲዎሎጂ ት/ቤቶች መመረቂያ ያደረገው አሠራር ከዘመናዊነት ጋር ብቅ ያለው የሰው ሥርዓት እንጂ ከጌታም ሆነ ከሐዋርያት ያገኘነው ልማድ እንዳልሆነ የታወቀ ነው፤ ሆኖም ከጌታ ዘንድ የወንጌል ሰባኪ እንዲሆኑ ጥሪ ይኑራቸው አይኑራቸው ሳይረጋገጥ አንዳንዶች ከቲዎሎጂ ትምህርት ቤት በወንጌላዊነት ስለተመረቁ ብቻ በዚሁ ሙያ ከተመረቁ ሌሎች ሰዎች ጋር ተወዳድረው የወንጌላዊነት ሥራ የሚቀጠሩበት አሠራር በሃይማኖተኛው የክርስትና ዓለም በስፋት ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ በዚህም አሠራር ሥራ አጥ የሆኑ ሰዎች እንደ አንድ የሥራ መስክ ዕድሉን እየተጠቀሙበት ከመሆኑም ሌላ በየትኛውም ዓለማዊ አሠራር እንደተለመደው ሁሉ አንዳንድ ጊዜ በድምፅ ብልጫ፣ በትውውቅና በዝምድናም የወንጌል ሰባኪዎች እየተባሉ በተወሰነ ደመወዝ የሚቀጠሩበት ሁኔታም ይታያል፡፡ ይህም በዚህች ዓለም ላይ የምሥራቹን ቃል የሚናገሩ የወንጌል ሰባኪዎችን ራሱ ማስነሣትና ማሰማራት ለሚፈልገው በሰማይ በአባቱ ቀኝ ላለው ለጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ ልብ እጅግ አሳዛኝ አሠራር ከመሆኑም በላይ ክርስቶስ በቤተክርስቲያን ላይ ያለውን ሥልጣን መጋፋትም ጭምር ነው፡፡ ስለሆነም አንድ ሰው ጌታ ሳይጠራውና ሳያሰማራው፣ የሚሠራው ሌላ ሥራ ስለሌለው ብቻ፣ የወንጌል ሰባኪ ልሁን ብሎ ሊነሣ አይገባም፡፡ ሌሎች አማኞችም በጸጋው ተገልጦ ሲያገለግል ሳያዩና የጌታ ጥሪ እንዳለው የመንፈስ ቅዱስን ምስክርነት ሳያገኙ «የወንጌላዊነት ሥልጠና ወስዷል» በሚል ብቻ «ይህ ሰው ወንጌላዊ ነው» ሊሉ አይገባም፡፡
ቤተክርስቲያኑን ከላይ ሆኖ የሚያስተዳድረው ትልቁ የበጎች እረኛ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የአካሉን ሙላት ወደ ፍጻሜ ለማምጣት በውጭ ወዳለው ዓለም እየላከ ከማያምኑት መካከል የእርሱ ብልቶች እንዲሆኑ ይጠራባቸው ዘንድ የወንጌል ሰባኪዎችን ያስነሣል፤ ያሰማራልም፡፡ በዚህ መልኩ በእርግጥ ጌታ የሚሰጠን የወንጌል ሰባኪዎች በዚህ ዓለም ሳሉ የሚያስፈልጋቸውን ቀለብ እንዴት ያገኛሉ? የሚል ጥያቄ ምናልባት ሊነሣ ይችላል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ከጻፈው ቃል ለዚህ ጥያቄ የምናገኘው መልስ «... ወንጌልን የሚሰብኩ ከወንጌል ቀለብ እንዲቀበሉ ጌታ ደንግጎአል» የሚል ነው (1ቆሮ.9፡14)፡፡ ጌታችን ይህን አስመልክቶ ሲናገር «... ለሠራተኛ ምግቡ ይገባዋልና» ብሏል (ማቴ.10፡10)፤ እንዲሁም «ወደምትገቡበት ቤት ሁሉ አስቀድማችሁ ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን በሉ፡፡ በዚያም የሰላም ልጅ ቢኖር ሰላማችሁ ያድርበታል፤ አለዚያም ይመለስላችኋል፡፡ በዚያም ቤት ከእነርሱ ጋር ካለው እየበላችሁና እየጠጣችሁ ተቀመጡ ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋልና ከቤት ወደቤት አትተላለፉ፡፡ ወደምትገቡባትም ከተማ ሁሉ ቢቀበሏችሁ ያቀረቡላችሁን ብሉ...» ብሏል (ሉቃ.10፡5-8)፡፡ ከዚህም እንደምንረዳው ጊዜያቸውን በሙሉ ለጌታ ሥራ በመስጠት ወንጌልን ለሚሰብኩ ወንጌላውያን በቤታቸው የተቀበሏቸው ሰዎች ቀለባቸውን እንዲሰጧቸው መደንገጉን ነው፡፡ ይህ አሠራር እኛ ባለንበት በጸጋው ዘመንም ሆነ ወደፊት የመንግሥት ወንጌል በሚሰበክበት ወቅትም ሥራ ላይ የሚውል ነው፡፡ የወንጌል ሰባኪዎችን በቤታቸው የሚቀበሏቸው ሰዎች ከቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ጀምሮ የሚያስፈልጋቸውን ሊሰጡአቸው ይገባል፡፡ ይህንንም ቢያደርጉ ወደ ቤታቸው ከገባው እና በጌታ ስም ከተቀበሉት የወንጌል አገልጋይ ጋር ዋጋቸው አንድ እንደሆነ ጌታ ተናግሯል (ማቴ.10፡40-42፤ ማር.9፡41)፡፡ ሆኖም የወንጌል ሰባኪው «ያቀረቡለትን ለመብላት» ማለትም በእነርሱ አቅም ለመስተናገድ የተዘጋጀ ሊሆን ይገባል፡፡ ይህም ዘመናችን በስፋት ከሚሠራበት የወር ደመወዝን በፔሮል እየፈረሙ በመቀበል በወንጌላዊነት ከማገልገል በእጅጉ ይለያል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን በዘመናችን «እቤቴ ድረስ መጥታችሁ በመኪና ካልወሰዳችሁኝ» ከሚለው ጥያቄ ጀምሮ «ለሥጋ የተመቻቸ ማረፊያና የላመ የጣመ (ውድ) ምግብ ካላቀረባችሁልኝ» እስከሚለው ጥያቄ ድረስ ራሳቸውን ለወንጌል ሥራ ካሰማሩ ሰዎች ብዙ ጊዜ የሚሰማ ሆኗል፡፡ ሆኖም ይህ ጌታ ካስነሣቸውና ካሰማራቸው የወንጌል ሰባኪዎች የሚጠበቅ አይደለም፡፡
ጌታ ያሰማራቸው የወንጌል ሰባኪዎች ምንም እንኳ ከወንጌል ቀለብ እንዲቀበሉ ጌታ መደንገጉን የሚያውቁ ቢሆንም በሚያገለግሏቸው ሰዎች ላይ ለመክበድ ስለማይፈልጉ ለቀለብ የሚያስፈልጋቸውን ለማግኘት በገዛ እጃቸው በመሥራት ይተዳደራሉ፤ ሐዋርያው ጳውሎስ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ እርሱ ድንኳን በመስፋት እየሠራ ራሱንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ይጠቅም ነበር (የሐ.ሥ.18፡1-3)፤ ይህን በተመለከተ ራሱ ጳውሎስ ሲናገር «ከማንም ብር ወይም ወርቅ ወይም ልብስ አልተመኘሁም፤ እነዚህ እጆቼ በሚያስፈልገኝ ነገር ለእኔና ከእኔ ጋር ላሉት እንዳገለገሉ እናንተ ታውቃላችሁ» ብሏል (የሐ.ሥ.20፡33-34)፡፡ እንዲያውም ስለሚያገለግላቸው ሰዎች ገንዘቡንም ራሱንም እስከመስጠት ዋጋ እንደሚከፍል ይናገራል፤ «ወላጆች ለልጆች እንጂ ልጆች ለወላጆች ገንዘብ ሊያከማቹ አይገባቸውምና፤ እኔ ግን ስለ ነፍሳችሁ በብዙ ደስታ ገንዘቤን እከፍላለሁ፤ ራሴንም እንኳ እከፍላለሁ» ብሏል (2ቆሮ.12፡14-15)፡፡ ከዚህም የምንረዳው የወንጌል ሰባኪዎች ወርቅና ብርን እንዲሁም ልብስን የሚያስፈልጋቸውንም እንኳ ቢሆን ከሚያገለግሏቸው ሰዎች ከመጠበቅ ይልቅ ራሳቸው በገዛ እጃቸው እየሠሩ ከራሳቸው አልፈው ስለሚያገለግሏቸው ሰዎች እንኳ ሳይቀር በብዙ ደስታ ገንዘባቸውን የሚከፍሉ ሊሆኑ እንደሚገባ ነው፡፡ ይሁንና ይህን ለማድረግ ጊዜ የማይበቃቸውና ሙሉ ለሙሉ ጊዜያቸው በወንጌል ስብከት ሥራ የተያዘባቸው፣ ለአገልግሎቱ የተሰጡ አገልጋዮች ከሆኑ ግን ከወንጌል ቀለብ እንዲቀበሉ ጌታ ደንግጎአል፤ ብርና ወርቅ ወይም ሌላ የከበረ ነገር ሳይፈልጉ ለኑሮአቸው አስፈላጊ ከሆኑ ነገሮች መካከል ያገኙትን እየተጠቀሙ ጌታን ከልብ የሚያገለግሉ ሊሆኑ ይገባል፡፡ በእርግጥ ጌታ ያሰማራቸው የወንጌል ሰባኪዎች የሚታወቁበት ምልክትም ይኸው ነው፡፡ ከኑሮ አንጻር ወንጌል ሰባኪዎች ሊከተሏቸው የሚገቡት እነዚህ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ መርሆዎችም ማለትም ከወንጌል ቀለብ በመጠቀም ወይም በገዛ እጃቸው ሠርተው በማግኘት ጌታን ማገልገል ለወንጌል ሰባኪዎች ብቻ ሳይሆን በእረኞችና በአስተማሪዎች አገልግሎት ሥራ ላይ የሚውሉ መርሆዎች መሆናቸውን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡
የወንጌል ሰባኪዎች በመካከላችን በተሰጣቸው ጸጋ ሊገለጡ የሚችሉት እንዴት ነው? የሚለው ጥያቄ የብዙዎች እንደሚሆን አያጠራጥርም፤ ወንጌላውያን በሰዎች ምርጫና ምልመላ ወይም በልዩ የወንጌላዊነት ሥልጠና ሳይሆን ጌታ በራሱ መንገድ በሕይወታቸው የጠራቸውና ያሠለጠናቸው ሆነው በመካከላችን የወንጌላዊነትን ሥራ በመሥራት በሚያሳዩት ትጋት ሊገለጡ ይችላሉ፡፡ በዚህም አገልግሎት እየተጉ ሲታዩ የአብያተ ክርስቲያናትን ምስክርነት እያገኙ ይሄዳሉ፡፡ ወደዚህ ሁኔታ የሚደርሱት በግል ከጌታ ጋር ካላቸው የጠበቀ ኅብረት ተነሥተው ቅዱሳት መጻሕፍትን በጸሎት ሆነው፣ ጊዜ ሰጥተው፣ በማጥናት በእግዚአብሔር ቃል ተሞልተው፣ በነፍሳት ፍቅር ተይዘው፣ ክርስቶስን መስበክ ሲጀምሩና በዚህም አገልግሎት እያደጉና እየተጉ ሲሄዱ ነው፡፡ ይህ ጸጋቸው በየስፍራው ሥራ ላይ ሲውል ያዩ አብያተ ክርስቲያናት የሚሰጡት ምስክርነት ይበልጥ በዚህ ጸጋ የሚያገለግሉትን ይገልጣቸዋል፤ ለምሳሌ የልግስና ስጦታን ለመረከብ ወደ ቆሮንቶስ ከተላኩት ሦስት ወንድሞች አንዱ «ስለወንጌል ስብከት በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የተመሰገነ ወንድም» ተብሏል (2ቆሮ.8፡18)፡፡
በሰው ሥርዓት ሳይሆን በቀጥታ በራሱ በጌታ በኢየሱስ አሠራር በመካከላችን የሚገለጡት የወንጌል ሰባኪዎች «ወንጌላዊ እከሌ» ተብለው እንዲጠሩ የሚፈልጉ አይደሉም፡፡ ይሁን እንጂ «ወንጌላዊ» የሚለውን ቃል ከግለሰብ የመጠሪያ ስም በፊት በማድረግ እንደ ማዕረግ ስም መጠቀም በብዙዎች ዘንድ የተለመደ ሆኖ ይታያል፡፡ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ «ወንጌላዊ» የሚለውን ቃል ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ስጦታዎች የሚገልጹ ቃላትን በማዕረግ ስምነት መጠቀምን ፈጽሞ አያስተምርም፤ ይህ ሊመጣ የሚችለው ግን ሥጋ በወንጌል አገልግሎት ስም ከብሮ ለመጠራት ሲፈልግ እንደሆነ ማሰብ ይቻላል፤ አንዳንድ ጊዜ ከሰባቱ አንዱ ፊልጶስ «ወንጌላዊው» ተብሎ በሐዋ.ሥ.21፡8 ላይ መጠራቱን በተሳሳተ መንገድ በመጠቀም «ወንጌላዊ እከሌ» ተብሎ መጠራት እንደሚቻል ሲነገር ይሰማል፤ ይሁን እንጂ በዚህ ጥቅስ ላይ ፊልጶስ «ወንጌላዊው» ተብሎ መጠራቱ የሚያገለግልበትን የጸጋ ስጦታ ለመግለጽ ነው እንጂ በማዕርግ ስም ለመጥራት አይደለም፤ እንዲያውም ፊልጶስ በዚህ ክፍል የተጠራው «ወንጌላዊው ፊልጶስ» ተብሎ እንጂ «ወንጌላዊ ፊልጶስ» እንዳልሆነ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ በሌሎች ቋንቋዎች በተጻፈ መጽሐፍ ቅዱስ ስም አቀማመጡ እንዲሁ ነው፤ ለምሳሌ ብዙ ሰዎች ሊያነቡት የሚችሉትን የእንግሊዘኛ መጽሐፍ ቅዱስን ብናነጻጽር እንኳ “Philip the Evangelist” ይላል እንጂ “Evangelist Philip” አይልም፡፡ በሁለቱ አነጋገሮች መካከል ጉልህ ልዩነት አለ፤ «ወንጌላዊው ፊልጶስ» ሲባል ፊልጶስን በሚሠራው የወንጌላዊነት ሥራ ለይቶ ለመጠቆም (ለመግለጽ) መፈለግን ሲያስረዳ «ወንጌላዊ ፊልጶስ» ሲባል ግን «ወንጌላዊ» የሚለውን ቃል በማዕርግ ስምነት መገልገልን ይገልጻል፤ ልብ ብሎ ለሚያስተውል ሁሉ ይህ ግልጽ ይሆንለታል፡፡ ወንጌላዊ የሚለውን ቃል በማዕርግ ስምነት መጠቀም ተገቢ ቢሆን ኖሮ ፊልጶስ በተጠራባቸው ቦታዎች ሁሉ ከስሙ በፊት «ወንጌላዊ» የሚል ቃል ይኖር ነበር፤ ሆኖም በሐዋ.ሥ.8 ውስጥ የፊልጶስ ስም 14 ጊዜ ያህል ሲጠራ አንድም ጊዜ ወንጌላዊ ፊልጶስ አልተባለም (ቊ.5፣ 6፣ 12፣ 13፣ 26፣ 29፣ 30፣ 31፣ 34፣ 35፣ 37፣ 38፣ 39፣ 40)፡፡ ስለሆነም አንድን ሰው በወንጌል ሰባኪነት አገልግሎቱ ለመግለጽ ስንፈልግ «እገሌ የትኛው?» ተብሎ ቢጠየቅ «ወንጌላዊው ነዋ! ወንጌላዊው እከሌ» ብለን ከመናገር በቀር ሁል ጊዜም ስንጠራው ወይም ስናስተዋውቀው ወይም ስሙን ስንጽፍ «ወንጌላዊ እከሌ» ካልን ወይም ያ ወንድም ራሱን ለእኛ ሲያስተዋውቅ «ወንጌላዊ እከሌ» እባላለሁ ካለ ይህ አጠቃቀም ወንጌላዊ የሚለውን ቃል የማዕረግ ስም ማድረግ ነው፡፡ ይህም ዛሬ በዘመናችን በስፋት የሚታይ ሲሆን ማዕረግና ክብር ከሚጠማው የሥጋ ፍላጐት የሚነሳና ከእግዚአብሔር ቃል ውጪ የሆነ ልማድ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያሉትን ጌታ ነጻ አውጥቷቸው ምንም ዓይነት የማዕረግ ስም ሳይፈልጉ ዝቅ ብለው ሲያገለግሉ ማየት የዘወትር ምኞታችን ነው፡፡
ቀደም ሲል እንደገለጽነው የወንጌል ሰባኪዎች በዋናነት ለማያምኑ ሰዎች ቀጥሎም ላመኑ ሰዎች ስለክርስቶስ መስበክ የአገልግሎታቸው ዓላማ ነው፡፡ ጊዜያቸውን በሙሉ ለዚሁ አገልግሎት የሰጡም ቢሆኑ የራሳቸውን ሥራ እየሠሩ የሚያገለግሉ ወንጌላውያን ትኲረት ሊሰጡበትና ሊጠነቀቁበት የሚገባው ነገር የአገልግሎታቸውን ዓላማ እንዳይስቱ ነው፤ ሐዋርያው ጳውሎስ «ስለ እርሱም (ስለክርስቶስ) የምንናገረው ብዙ ነገር አለን....» እንዳለው (ዕብ.5፡11) ወንጌላውያን ስለ ጌታ ኢየሱስ የሚናገሩት ብዙ ነገር እያለ ስለራሳቸው ወይም ስለሌሎች ሰዎች የሚናገሩ መሆን የለባቸውም፤ በ2ቆሮ.4፡5 «ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታ እንደሆነ እንጂ ራሳችንን አንሰብክምና ስለ ኢየሱስም ራሳችንን ለእናንተ ባሪያዎች እናደርጋለን» የሚል ቃል እናነባለን፡፡ አንድ እውነተኛ የወንጌል ሰባኪ ሊከተለው የሚገባ መርህ ይህ ነው፡፡ ሆኖም የራስ ነገር ጎልቶ እንዲታይ በሚፈለግበት ጊዜ ለማያምኑ ሰዎች በተዘጋጁ ታላላቅ የወንጌል ስርጭት መድረኮችም ይሁን ለአማኞች ወንጌል በሚሰበኩባቸው ጉባኤያት «በዚህ አገር ይህን ሠርቼ፣ ይህን ሰብኬ፤ በዚህ ቦታ አንድ ወንድም አነጋግሮኝ፣ አንዲት እኅት ጸልይልኝ ብላኝ ... እንዲህ ሆኖ ... እንዲያ ተብሎ....» የሚሉ ገጠመኞችን በመደርደር ስለራስ መተረክ የበዛበት አገልገሎት በስፋት ይታያል፡፡ እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ ጠቃሚ ያልሆኑ አስቂኝ ቀልዶችና ተረቶች ጊዜውን ሲያጣብቡት ማየት የተለመደ ነው፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ወንጌል እሰብካለሁ በማለት በተረከቡት መድረክ «አሁን በመገለጥ የሚታየኝ ነገር አለ» እያሉ ከዚያ አስቀድሞ በነበረው በዚሁ ዓይነት ነገር የተሰላቸውን ሕዝብ እንደገና ወደማሰላቸትና ብሎም ወደማሰናከል የሚወስዱ የሐሰተኛ መገለጥ አገልግሎቶች ሃይማኖተኛውን የክርስትና ዓለም ሞልተውት ይታያሉ፡፡ ተነግሮ የማያልቀው የክርስቶስ ማንነት እያለ ራስን በሕዝብ ፊት ሊያሳውቁና ሊያስከብሩ የሚችሉ እንዲህ ያሉ ነገሮችን በማንሣት ጊዜ መውሰድ ክርስቶስን መስበክ ሳይሆን ራስን መስበክ ነው፡፡ እውነተኛ የወንጌል ሰባኪዎች ከዚህ መራቅ አለባቸው፡፡
የአዲስ ኪዳንም ይሁን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ዋነኛ ትኲረት ክርስቶስ መሆኑ ይታወቃል (ዮሐ.5፡39፣46)፤ ወንጌል መስበክም ማለት ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ማንነት መመስከር ነው (ሮሜ.1፡4)፡፡ ስለሆነም የወንጌል ሰባኪዎች የስብከታቸው ዋና ይዘት ስለ ክርስቶስ ሆኖ፣ ይህም ከብሉይ ኪዳንና ከአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በማስረጃነት በተጠቀሱ የእግዚአብሔር ቃላት የተሞላ ሊሆን ይገባዋል፡፡ የሰሚዎችን ልብ ሊነካ የሚችለውና መንፈስ ቅዱስ የማያምነውን ሊጠራበት የሚችለው ስብከት ይህ ነው፡፡ በሐ.ሥ.2 ውስጥ የምናየውን በበዓለ ሃምሳ ዕለት የተሰበከውን የጴጥሮስን ስብከት ስንመለከት ዋና ርእሰ ጉዳዩ የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ እንዲሁም በአባቱ ቀኝ በክብር መቀመጡ፣ «ጌታ» እና «ክርስቶስ» መደረጉ ሲሆን ለዚሁ ማስረጃ የሚሆኑ ሦስት የተለያዩ ንባቦች ከቅዱሳት መጻሕፍት ተጠቅሰው ነበር፡፡ በውጤቱም የሰሚዎች ልብ ሲነካ እናያለን (ቊ.37)፡፡ እንዲሁም በሐ.ሥ.13፡16-41 የምናነበውን የጳውሎስን ስብከት ስንመለከት ከቅዱሳት መጻሕፍት በተወሰዱ ታሪኮችና ጥቅሶች የተመሠረተና የተሞላ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ስለ ክርስቶስ በመስበክ ጊዜውን ሁሉ መጨረስ ለሚፈልጉ ሁሉ እነዚህ ስብከቶች አብነት ሊሆኗቸው ይችላሉ፡፡ የወንጌል ሰባኪዎች የሐዋርያትን አብነት በመከተል ስለሰው ወይም ስለ ራስ ከመስበክ ተለይተው የእግዚአብሔር ቃል ስለክርስቶስ የሚናገራቸውን ማንነቶቹን በመስበክ ሊጠመዱ ይገባቸዋል፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ሲጽፍለት «አንተ ግን ነገርን ሁሉ በልክ አድርግ፤ መከራን ተቀበል፤ የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ አድርግ፤ አገልግሎትህን ፈጽም» ብሎታል (2ጢሞ.4፡5)፡፡ ይህ ቃል የወንጌል ሰባኪነት ጸጋው ኖሯቸው የሰነፉትን ወይም የተዳከሙትን ሰዎች የሚያበረታታና የሚያነቃቃ ቃል ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ወንጌል ሰባኪዎች ብዙ ሥራዎችን በመጀመር ራሳቸውን በአላስፈላጊ ውጥረት ውስጥ ስለሚከቱ ከጌታ የተሰጣቸውን የወንጌል ሰባኪነት አደራ ሳይወጡ ይቀራሉ፡፡ ከተያዙባቸው ሥራዎች መካከል አንዳንዶቹ የቱንም ያህል አስፈላጊ ቢሆኑም ከጌታ ሥራ ይልቅ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚችሉ አይደሉም፤ ስለዚህ ነገርን ሁሉ በልክ እያደረጉ ወንጌልን ለመስበክ ቅድሚያ መስጠት ጥሪው ካላቸው ሁሉ የሚጠበቅ ነው፤ እውነተኛ የወንጌል ሰባኪዎች የጌታ ሥራ እየተበደለ በራሳቸው ነገር እንዲያዙ የሚያደርግ ልብ የላቸውምና፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ወንጌልን ከመስበክ አኳያ ስለ ክርስቶስ በሚደርስ መከራ ምክንያት ተሰላችተው መዳከም በአንዳንድ ወንጌላውያን ዘንድ ይታያል፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ጊዜ መከራው ከአቅም በላይ እስኪሆን ድረስ ያለልክ ሊከብድ ይችላል (2ቆሮ.1፡8)፡፡ ሆኖም ጌታ በመከራ ውስጥ አሳልፎ በእኛ ሊሠራ ያለውን እንደሚሠራ ማመን ያስፈልጋል፤ እርሱ ሳይፈቅድ ሊሆን የሚችል ነገር የለም፤ እርሱ የራሳችንን ጠጉር ቆጥሮአል፤ መልእክተኞቹ ለሆኑት ሁሉ እርሱ ዋጋ ሰጥቷል (ማቴ.10፡28-30) እስከሞት መታመንን የሚጠይቅ ከሆነም ጌታ ለዚሁ የሚሆን ጸጋንና እምነትን ይሰጣል፡፡ ይህንን ተረድቶ በወንጌል ሰባኪነት ሥራ በመበርታትና በመትጋት ፈንታ ወደ ኋላ ማፈግፈግ ወይም ተስፋ ቆርጦ «ሁለተኛ አላገለግልም» ማለት ከጌታ በተቀበሉት መክሊት አለማትረፍ ነው፡፡ የወንጌል ሰባኪ የሆነ ሰው ገና ከጌታ ዘንድ ጥሪ እንዳለው ሲያውቅና ሲያምን ስለስሙ መከራ መቀበል እንዳለ ሊያውቅ ይገባል፡፡ ይህንንም አውቆ መከራ እየተቀበለ የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ እንዲያደርግ አገልግሎቱንም እንዲፈጸም የእግዚአብሔር ቃል ያበረታታዋል!
በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ የምናምን ሁላችን ስለክርስቶስ የመመስከር ኃላፊነት በእርግጥ አለብን፤ ይሁንና በወንጌል ሰባኪነት ለቤተክርስቲያን የተሰጡ ወንድሞች በዚሁ ጸጋ ተገልጠው ቢሠሩ ለክርስቶስ አካል ብልቶች ሆነው የሚገጠሙትን ነፍሳት ወደ ጌታ ለማምጣት ብዙ ሊሠሩ ይችላሉ፡፡ ቃሉም ወደማያምኑት መካከል በፍጥነት እየሮጠ በዓለም በሚጣለው የወንጌል መረብ ብዙ ነፍሳት ሊጠመዱ ይችላሉ፡፡ ይህ ይሆን ዘንድ ጌታ እንዲህ ያሉ የወንጌል ሠራተኞችን እንዲያስነሣ በጸሎት ልንለምነው ይገባል፡፡ እርሱ በምድር ሳለ ብዙ ሕዝብ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ባየ ጊዜ አዘነላቸውና ለደቀመዛሙርቱ «መከሩስ ብዙ ነው ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፡፡ እንግዲህ የመከሩን ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞችን እንዲልክ ለምኑት» ብሎ ነበር (ማቴ.9፡36-38)፡፡ በዘመናችንም በተመሳሳይ ሁኔታ ባለማወቅ የጠፋና በሰው ሥርዓተ ሃይማኖት የተያዘ፣ ተጨንቆና ተጥሎ ያለ፣ የተወደደውንና የከበረውን የክርስቶስን ማንነት መስማት የሚያስፈልገው ብዙ ሕዝብ በዙሪያችን አለ፡፡ ጌታ ኢየሱስ ዛሬም ለዚህ ሕዝብ ያዝናል፡፡ የክርስቶስ ልብ ያለንና ይህ የሚሰማን ሁላችን ጌታ እውነተኛ የመከር ሠራተኞችን እንዲያስነሳ ልንጸልይ ይገባል፡፡
-
4. እረኞች
ወንጌል ሰባኪዎች በማያምኑት መካከል በሚያቀርቡት የወንጌል ቃል ልባቸው ተነክቶ ወደ ክርስቶስ የመጡት ነፍሳት የሚያስፈልጋቸው ቀጣይ አገልግሎት ደግሞ የእረኝነት አገልግሎት ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ የእርሱ የሆኑት ሁሉ በእረኝነት አገልግሎት እንዲጠበቁ፣ እንዲመገቡና እንዲሰማሩ ይፈልጋል፡፡ ስለሆነም ይህን የሚያገለግሉ እረኞችን ለቤተክርስቲያን በየጊዜው ይሰጣል፤ ከዚህ ቀጥሎ እነዚህን ጌታ ኢየሱስ የሚሰጠንን እረኞች በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረንን እውነት እንመለከታለን፡፡
- የነቢያት መልካም እረኛ
የእረኝነትን አገልግሎት ምንነት ለመረዳት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መልካም እረኝነት የተጻፈልንን መረዳቱ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ በዮሐ.10፡1-16 ራሱ ኢየሱስ ስለ መልካም እረኝነቱ ያስተማረው ቃል በስፋት ተጽፎልናል፡፡ «እውነት እውነት እላችኋለሁ ወደ በጎች በረት በበሩ የማይገባ በሌላ መንገድ ግን የሚወጣ እርሱ ሌባ ወንበዴም ነው፤ በበሩ የሚገባ ግን የበጎች እረኛ ነው» (ቊ.1)፤ በዚህ ምሳሌ የእውነተኛ እረኛ ባሕርይ ከሌባው እና ከወንበዴው ባሕርይ ተለይቶ በበሩ የሚገባ ሆኖ ቀርቦልናል፡፡ እረኛው በበረቱ ላሉት ለእነዚያ በጎች በእርግጥ እረኛቸው እርሱ እስከሆነ ድረስ ወደ በረቱ ተሰውሮ በድብቅ ለመግባት የሚፈልግበት ምንም ዓይነት ሁኔታ የለም፤ ማንም ሰው እያየው በግልጽ በታወቀው በር ይገባል፡፡ ስለሆነም በበር መግባት ፍጹም ግልጽነትንና እውነተኝነትን ያሳያል፡፡ ጌታ ኢየሱስም «እኔ በግልጥ ለዓለም ተናገርሁ፤ አይሁድ ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኩራብና በመቅደስ እኔ ሁልጊዜ አስተማርሁ፤ በስውር ምንም አልተናገርሁም» ለማለት የተቻለው እውነተኛ እረኛ ነው (ዮሐ.18፡2)፡፡ ይህም የሚያሳየው አገልግሎቱ ሁሉ ማንም የሚያየውና የሚሰማው ለሁሉ የተገለጠ እንደነበረ ነው፡፡ በበሩ የሚገባ የእውነተኛ እረኛ ጠባይ እንዲህ ነው፡፡ በቤተክርስቲያንም ጌታ የሚያስነሣቸው እረኞች አገልግሎታቸው በብርሃን የሆነና ለማንም የተገለጠ አገልግሎት ሊሆን ይገባል፡፡ አንዳንድ ጊዜ የልብ አሳብንና የወደፊት ዓላማን በመሰወር በሕዝብ መካከል በመግባት ነፍሳትን መማረክ እንደሚቻል የሚያስቡ ቢኖሩ ይህ የሌቦቹና የወንበዴዎቹ ባሕርይ እንጂ የእውነተኛው እረኛ ባሕርይ አለመሆኑን ከዚህ ሊማሩ ይገባል፡፡ ጌታ ኢየሱስ በድብቅ ወይም «አዩኝ አላዩኝ» በሚል መሹለክለክ የሚፈጸም የእረኝነት አገልግሎትን ይጸየፋል፤ ምክንያቱም ይህ በበሩ መግባት መውጣት ሳይሆን በሌላ በርና በሌላ መንገድ መግባት መውጣት በመሆኑ ነው፤ ይህም የሌባውና የወንበዴው አገልግሎት ነው፡፡ ወንጌል ለተመሰከረላቸውና ልባቸው ለተነካ ነፍሳት የሚሰጥ የእረኝነት አገልግሎት በብርሃን ወይም በግልጽ ሊሆን ይገባል፤ የሚነገራቸው እውነትም ተድበስብሶ ወይም ተሸቃቅጦ ሊነገራቸው አይገባም፤ በፍጹም ግልጥነት የእግዚአብሔርን እውነት ማወቅ ይኖርባቸዋል፤ በዚህ ዓይነት ነፍሳትን በየግላቸው የሚያገለግሉ እረኞች በበሩ የሚገቡና የሚወጡ እረኞች ናቸው፡፡
«ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል፤ በጎቹ ድምፁን ይሰሙታል፤ የራሱንም በጎች በየስማቸው ጠርቶ ይወስዳቸዋል» (ቊ.3)፡፡ በዚህ ክፍል እረኛው ከበጎቹ ጋር ባለው የቅርብ ግንኙነት የተነሣ በጎቹን በየስማቸው እንደሚያውቃቸው እንረዳለን፡፡ ጌታ ኢየሱስም «የእርሱ የሆኑትን ያውቃል» (2ጢሞ.2፡14)፤ በዚሁ በዮሐ.10፡15 ላይ እንደምናነበው እርሱ ራሱ «መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ አብም እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው የራሴን በጎች አውቃለሁ፤ የራሴም በጎች ያውቁኛል» ብሎ ተናግሯል፡፡ ስለሆነም በእረኝነት አገልግሎት ውስጥ እረኞች የሚያገለግሏቸውን አማኞች በሚገባ ሊያውቋቸው ይገባል፡፡ ከስማቸው ጀምሮ አጠቃላይ ያሉበትን ሁኔታ በቅርበት አውቀው አስፈላጊውን መንፈሳዊ አገልግሎት ሊሰጧቸው ይገባል፡፡
«የራሱንም ሁሉ ካወጣቸው በኋላ በፊታቸው ይሄዳል፡፡ በጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል፤ ከሌላው ግን ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉትም፤ የሌሎችን ድምፅ አያውቁምና» (ዮሐ.4-5)፤ በዚህ ንባብ እረኛው የበጎቹ ባለቤት ሆኖ ይታያል፤ ስለሆነም በጌታ በኢየሱስ ላመኑ ሁሉ ባለቤት የሆነው «ትልቁ የበጎች እረኛ» ራሱ ኢየሱስ ነው (ዕብ.13፡20)፤ እርሱ ለቤተክርስቲያን የሰጣቸው እረኞች ግን የሚጠብቁት የእርሱን በጎች በመሆኑ የበጎቹ ባለቤት አለመሆናቸው ሊታወቅ ይገባል፡፡ ይሁን እንጂ ከእርሱ በአደራ የተሰጧቸውን በጎች ለማገልገል የእርሱን ምሳሌነት ሊከተሉ ይገባል፡፡ ስለሆነም እረኛው በጎቹን ለመምራት በፊታቸው እንደሚሄድ ሁሉ የክርስቶስን በጎች የሚያገለግሉ እረኞችም ቀጣዩን የክርስትና ሕይወት ጉዞ ለማሳየት ሁልጊዜም በፊታቸው ሊሄዱ ይገባል፡፡ ይህም ማለት ነፍሳት በክርስቶስ አምነው ከዳኑ በኋላ እንዴት እንደሚጸልዩ፣ እንዴት እንደሚያመልኩ፣ ክፉውን እንዴት እንደሚያሸንፉ፣ በፈተና እንዴት እንደሚጸኑ በእግዚአብሔር ቃል ከማስረዳት በተጨማሪ በተግባርም በሕይወት እየኖሩ በመልካም ምሳሌነት ጭምር በፊታቸው ሊወጡና ሊገቡ ይገባል ማለት ነው፡፡ እንደዚሁም እረኛው ለበጎቹ የሚሆን ምግብ ወደሚገኝበት የማሰማሪያ ቦታና ወደ ዕረፍት ውኃ እንደሚመራቸው ሁሉ እነዚህም አገልጋዮች ነፍሳትን የእግዚአብሔርን ቃል ተመግበው የነፍስ ዕረፍት ወደሚያገኙበት መንፈሳዊ መሰማሪያ ሁልጊዜም ሊመሯቸው ይገባል፡፡ ይህም ከሆነ የክርስቶስ በጎች ያንኑ የተቀደሰ ፈለግ ተከትለው ይጓዛሉ ማለት ነው፡፡
እረኞች በዮሐንስ 10 ከተነገረው የኢየሱስ መልካም እረኝነት ሊማሩ የሚገባቸው ሌላው ነገር ደግሞ ስለሚጠብቋቸው የክርስቶስ በጎች ራስን እስከመስጠት የሚደርስ ታማኝነትን ነው፤ ክርስቶስ ኢየሱስ ነፍሱን ስለ በጎቹ የሚያኖር መልካም እረኛ መሆኑን ሲገልጥ፡- «መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል፡፡ እረኛ ያልሆነው በጎቹም የእርሱ ያልሆኑ ሞያተኛ ግን ተኩላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኩላም ይነጥቃቸዋል፤ በጎቹንም ይበትናቸዋል፡፡ ሞያተኛ ስለሆነ ለበጎቹም ስለማይገደው ሞያተኛው ይሸሻል፡፡ መልካም እረኛ እኔ ነኝ አብም እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው የራሴን በጎች አውቃለሁ፤ የራሴም በጎች ያውቁኛል፤ ነፍሴንም ስለ በጎች አኖራለሁ» (ቊ.11-15) ብሏል፡፡ በዚህ ክፍል ጌታ ኢየሱስ መልካሙን እረኛ ከሞያተኛው እረኛ በተቃራኒ መልኩ በማነጻጸር የመልካሙን እረኛ ታማኝነትና እውነተኛነት ገልጧል፡፡ ሞያተኛው እረኛ ተኩላ በሚመጣ ጊዜ በጎቹን ትቶ የሚሸሽ ሲሆን መልካሙ እረኛ ግን ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል፤ ሞያተኛው እረኛ በጎቹን ትቶ የሚሸሸው ለበጎቹ ስለማይገደው እንደሆነ ሁሉ መልካሙ እረኛ ደግሞ ነፍሱን ስለበጎቹ የሚያኖረው ለበጎቹ ግድ ስለሚለው ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ነፍሱን ስለ እነርሱ እስከማኖር ድረስ የእርሱ የሆኑትን ሁሉ የወደደ መልካም እረኛ ነው፡፡ እርሱ ለቤተክርስቲያን የሰጣቸው እረኞችም ይህን ባሕርይ ሊይዙ ይገባቸዋል፡፡ ለሚያገለግሏቸው የክርስቶስ በጎች ግድ የሚላቸው፣ ፍቅር ያላቸውና በቅርበት ሆነው በየግላቸው ያሉበትን መንፈሳዊ ሁኔታ የሚከታተሉ፣ ክፉው ሰይጣንና የእርሱ መልእክተኞች እነዚያን ነፍሳት ለመንጠቅ በሚተጉበት ወቅት ስለ እነርሱ ራሳቸውን አሳልፈው በመስጠት የሚጋፈጡ½ የሚደርስባቸውን ፈተናም ሆነ የተለያየ ችግር አብረው የሚካፈሉ መሆን እንዳለባቸው ከመልካሙ እረኛ ከኢየሱስ ሊማሩ ይገባል፡፡
ትልቁ እረኛ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ገና ወደ በረቱ ያልገቡ ሌሎች በጎችንም በተመለከተ የሚያደርገውን የእረኝነት ሥራ በተመለከተ ሲናገር «ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል፡፡ ድምፄንም ይሰማሉ አንድም መንጋ ይሆናሉ እረኛውም አንድ» ብሏል (ቊ.16)፡፡ በመጀመሪያ ወደ ክርስቶስ የመጡት አማኞች ከአይሁድ ወገን በመሆናቸው በበረቱ ውስጥ አስቀድመው የገቡት በጎች አይሁድ የነበሩ ናቸው፤ ስለሆነም በዚህ ክፍል ሌሎች በጎች ብሎ የጠራቸው ከአሕዛብ በእርሱ የሚያምኑ መሆናቸውን እንረዳለን፡፡ በዚህም አባባሉ በወንጌል ሥራ አማካኝነት የቤተክርስቲያን ዘመን እስኪጠናቀቅ ድረስ ስለሚጨመሩ በጎች (ነፍሳት) ተናግሯል፡፡ ይህም ከአሕዛብ መካከል ያሉትን በጎች ወደ በረቱ ማምጣት በመልካም እረኝነቱ በልቡ ያለው የእርሱ ዕቅድ ነው፡፡ ስለሆነም ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በወንጌል ስብከት ልባቸው ተነክቶ በኢየሱስ የሚያምኑት ሁሉ የእርሱ በጎች እየሆኑ በእርሱ እረኝነት እንዲጠበቁ ወደ በረቱ እየገቡ ይገኛሉ፡፡ ይህም የሚያመለክተን የእረኝነት አገልግሎት በቤተክርስቲያን ዘመን ሁሉ ጌታ ለሚጠራቸው ነፍሳት በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን ነው፡፡ አንዱ እረኛ እርሱ በዘመናት ሁሉ የሚጠራቸውን በጎቹን የሚያስጠብቀው በየጊዜው በጸጋ በሚሰጠን የታመኑ እረኞች ነውና፡፡
- እረኞች ለክርስቶስ ሊኖራቸው የሚገባ ፍቅር
በእረኝነት አገልግሎት ውስጥ ራሱን ለክርስቶስ በጎች አሳልፎ እስከ መስጠት የሚደርስ ፍቅር ሊኖረን እንደሚገባ ተመልክተናል፤ ይህም የእውነተኞች እረኞች ዓይነተኛ ምልክት ነው፡፡ እረኞች ሆነው ለቤተክርስቲያን የተሰጡ ወንድሞችን ወደዚህ እውነተኛ አገልግሎት ሊያደርሳቸው የሚችለውና የእረኝነት አገልግሎታቸው ዋነኛ መንስኤ ሊሆን የሚችለው የእረኞች አለቃ የሆነውን ክርስቶስን መውደድ ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በጎቹን በአደራ ከሚሰጣቸው እረኞች የሚፈልገው የመጀመሪያ ነገር ቢኖር እረኞቹ ለእርሱ ያላቸው ፍቅር ነው፡፡ ይህም ለጴጥሮስ የእረኝነት አገልግሎትን በአደራ በሰጠበት ወቅት ተገልጧል፡፡ በዮሐ.21፡15-17 ያለውን ክፍል በምናነብ ጊዜ ጌታ ለ3 ጊዜያት ያህል «የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ ትወደኛለህን?» እያለ ጴጥሮስን የጠየቀውን ጥያቄ ስንመለከት ይህን በሚገባ እንረዳለን፤ ጴጥሮስ ቀደም ሲል «ሁሉ ቢሰናከሉ እኔ ከቶ አልሰናከልም፤... ከአንተ ጋር የምሞት እንኳ ቢሆን ከቶ አልክድህም» በማለት በራሱ ቢተማመንም (ማር14፡2931) ይህን ቃሉን ባለመጠበቅ ውድቀትን አሳይቶ ስለነበር «ትወደኛለህን?» ለሚለው የጌታ ጥያቄ የሰጠው መልስ «ጌታ ሆይ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ» የሚል ነበር፡፡ በዚህን ጊዜ ጴጥሮስ በጌታ የሚታመንና የሚደገፍ ሆኖ ስለነበር በጎቹን ከጌታ በአደራ ለመቀበል ቻለ፡፡ ጌታም አደራውን ሲሰጠው «ግልገሎቼን አሰማራ፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ፣ በጎቼን አሰማራ» ሲለው እናያለን፡፡ በዚህም መልካሙ እረኛ ኢየሱስ የእረኝነት አገልግሎትን እርሱን ለሚወዱ እና በእርሱ ለሚደገፉ ራሱ ለሚያስነሣቸው እረኞች አሳልፎ እንደሰጠ ለመረዳት እንችላለን፡፡ ስለሆነም እረኞች የሚያገለግሏቸው በጎች ከትልቁ እረኛ ከኢየሱስ በአደራ የተረከቧቸው እንደሆኑ ምንጊዜም መዘንጋት የለባቸውም፤ እነርሱም በመንፈሳዊ ዕድገታቸው የተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሊሆኑ እንደሚችሉ «ግልገሎቼ»፣ «ጠቦቶቼ» እና «በጎቼ» ከሚሉት አገላለጾች እንረዳለን፤ ጌታችን በዚህ መልክ የበጎቹን የዕድገት ደረጃ በ3 ከፍሎ ማስቀመጡም የእረኝነት አገልግሎት፣ የሚገለገሉት ነፍሳት ያሉበትን መንፈሳዊ ዕድገት ማገናዘብ የሚገባው መሆኑን ያስተምረናል፡፡ ይህም የሚያመለክተው በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ገና ግልገል ለሆኑትና የስሜታዊነቱን ወራት ማለትም ጠቦትነቱን አልፈው በመንፈሳዊ ነገር ለጎለመሱት በጎች የሚያስፈልገው አገልግሎት «ማሰማራት» መሆኑን ነው፡፡ አዲስ አማኞች እስኪጠነክሩ ድረስ እንደ አቅማቸው አንድ ሰው ስለ እግዚአብሔር ቃላት መጀመሪያ ያለውን የሕፃንነት ትምህርት በሚማርበት መስክ ላይ ሊሰማሩ ይገባቸዋል፡፡ ከዚያ በኋላ የማሰማራቱ አገልግሎት የሚቀጥል ቢሆንም በእግዚአብሔር ቃል እያደጉ ሄደው በራሳቸው አንዳንድ እውነቶችን መመርመር በሚጀምሩ ጊዜ ከመለኮታዊው እውነት እንዳይስቱና በክፉ ትምህርቶች እንዳይደናገሩ በይበልጥ «የመጠበቅ አገልግሎት» ሊደረግላቸው ይገባል፤ ይህ የጠቦትነት ጊዜ ስለሆነ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ የሚገባበት ወቅት ነው፡፡ ከዚያም ሁሉን ለይተው በእግዚአብሔር እውነቶች ሁሉ ካረፉ በኋላም ቢሆን የእረኝነት አገልግሎት ያስፈልጋቸዋል፤ ያም የማሰማራቱ አገልግሎት ነው፤ በመንፈሳዊ ነገር የጎለመሱት እነዚህ አማኞች በለመለመው መስክ የማይሰማሩ ከሆነ የሥጋ ፈቃድና ዓለማዊነት ሊበረቱባቸው ይችላሉ፡፡ ስለሆነም ከእነዚህ አደጋዎች እንዲጠበቁ የእግዚአብሔርን ቃል በሚመገቡበት መንፈሳዊ መስክ ላይ ሁልጊዜም ሊሰማሩ ይገባል፤ ይህም እረኞች እነዚህ «በቃ አድገዋል ምንም አያስፈልጋቸውም» ብለው አንዳንድ በጎችን መተው እንደሌለባቸው ሁልጊዜም ሊያሰማሯቸው እንደሚገባ ያሳያል፡፡ ይሁን እንጂ በሁሉም የዕድገት ደረጃ ላይ የሚገኙት በጎች የክርስቶስ እንጂ የእረኞቹ አይደሉም፡፡ በመሆኑም ለበጎቹ የሚሆን ተገቢ አገልግሎት ለመስጠት እረኞች ለበጎቹ ባለቤት ለክርስቶስ ያላቸው ፍቅር እጅግ ወሳኝ ነው፤ እንዲያውም ለበጎቹ ከሚኖራቸው ፍቅር አስቀድሞ ለእርሱ ለበጎቹ ባለቤት የሚኖራቸው ፍቅር የአገልግሎታቸው መነሻ ሊሆን ይገባል፡፡
- የእረኞች አገልግሎት
ከ5ቱ ስጦታዎች መካከል አንዱ የሆነው የእረኞች ስጦታ እንደሌሎች አራቱ ስጦታዎች ሁሉ ለመላይቱ ቤተክርስቲያን የሚሰጥ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ስጦታው የሚገለጠውና ሥራ ላይ የሚውለው በየአጥቢያ ቤተክርስቲያናቱ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በተለያዩ ከተሞችና መንደሮች በሚኖሩ አብያተ ክርስቲያናት ብዙ እረኞች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ሆኖም እያንዳንዷን ቤተክርስቲያን በመልካም ያስተዳድሩ ዘንድ ጌታ በየአጥቢያው የሚያስነሣቸው ወንድሞችም የእረኝነት ሥራን ይሠራሉ፡፡ እነዚህም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ «ሽማግሌዎች» ወይም «በጌታ የሚገዙ» ተብለው የተገለጡት ናቸው፡፡ የእነርሱ የእረኝነት ሥራ ባሉበት አጥቢያ ቤተክርስቲያን ያሉትን ሁሉንም የእግዚአብሔርን መንጋ (አማኞች) በመልካም ማስተዳደር ነው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ደግሞ እንደ መንጋው ብዛት ጌታ በአንድ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ውስጥ በተጨማሪ የሚያስነሣቸው እረኞች ይኖራሉ፤ እነዚህ እረኞች ጉባኤውን የሚያስተዳድሩ ላይሆኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን በተሰጣቸው የእረኝነት ጸጋ የተወሰኑ አማኞችን በግል የመከታተልና የመጠበቅ እንደዚሁም የመመገብ አገልግሎት ይኖራቸዋል፡፡ ሌሎች አማኞች ጸጋቸውን አይተው እንዲያገለግሉ ሊያበረታቷቸው ከሚችሉ በቀር እረኞች ሆነው እንዲያገለግሉ የሚመድባቸውም ሆነ የሚያሰማራቸው ለሥራቸውም ፕሮግራም የሚያወጣላቸው ማንም ሰው ሊኖር አይገባም፡፡ ጠቅለል ባለ አነጋገር ሽማግሌዎች ሁሉ እረኞች ሲሆኑ እረኞች ሁሉ ግን ሽማግሌዎች አለመሆናቸው ሊታወቅ ይገባል፡፡ ይሁን እንጂ በየአጥቢያ ቤተክርስቲያናቱ በመልካም በሚያስተዳድሩ ማለትም የሽማግሌነትን ሥራ በሚሠሩ ወንድሞች አገልግሎት ውስጥ የእረኝነት አገልግሎትን ስለምናገኘው የእረኝነት አገልግሎት ምን ምን እንደሆነ ስለ ሽማግሌዎች አገልግሎት ከተነገሩ ክፍሎች እናጠናለን፡፡
- 1ኛ. መንጋውን መጠበቅ
በሐዋ.ሥ.20፡28-30 ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ቤተክርስቲያን ሽማግሌዎች የተናገረውን የእረኝነት ሥራ እናነባለን፡፡ «በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፡፡ ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፣ ደቀመዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ» ብሏቸዋል፡፡ በዚህ ክፍል «ጳጳሳት» የተባሉት ሰዎች ከፍ ብሎ በቊ.17 ላይ ደግሞ «ሽማግሌዎች» ተብለው ተጠርተዋል፤ እነርሱም በእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ያለውን መንጋ እንዲጠብቁ መንፈስ ቅዱስ የሚሾማቸው ናቸው፡፡ መንጋውን የሚጠብቁትም ከውጪ ወደ ውስጥ ከሚገቡ ጨካኞች ተኩላዎች እና በውስጥ ደግሞ ከአማኞች መካከል ተነሥተው ደቀመዛሙርትን ወደ ኋላ ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን ከሚናገሩ ሰዎች ነው፡፡ ሁለቱም ዓይነት ሰዎች ለክርስቶስ መንጋ ጠንቅ ናቸው፡፡ ሥራቸውን የሚሠሩት ደግሞ በተኩላው ባሕርይ ተመሳስሎ በመቅረብ የሐሰትና የክህደት ትምህርትን በመዝራት ወይም የእግዚአብሔርን ቃል በማጣመም ነው (2ጴጥ.3፡16)፡፡ በ2ቆሮ.11፡13-15 ላይ ተንኰለኞች ሠራተኞች የተባሉትም በዚህ የተነሣ ነው፡፡ ሽማግሌዎች ይህንን ተንኰላቸውን አውቀው ከውጪ ሾልከው ከገቡትም ሆነ በውስጥ ተመሳስለው ከተቀመጡት ተንኰለኞች ሠራተኞች እና ከሚያሰራጩት ክፉና ሐሰተኛ ትምህርት መንጋውን ሊጠብቁ ይገባል፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት የክርስቶስንና የሐዋርያትን ትምህርት በማስተማር ነው፡፡ ሽማግሌዎች ይህን አገልግሎት በአጥቢያ ቤተክርስቲያን ደረጃ የሚያከናውኑ ሲሆኑ አጥቢያ ቤተክርስቲያኑን የማስተዳደር ኃላፊነት የሌላቸው ነገር ግን የእረኝነት ጸጋ የተሰጣቸው ሌሎች ወንድሞችም በተሰጣቸው ጸጋ ይህንኑ ሥራ ይሠራሉ፡፡ ስለዚህ አንዱ የእረኞች አገልግሎት በቅርበት የሚያገለግሏቸውን ነፍሳት ከውጭ ከሚገቡ ጨካኞች ተኩላዎችና በውስጥ ሊነሱ ከሚችሉ ጠማማ ነገርን ከሚናገሩ ሰዎች መጠበቅ ነው፤ በ1ጴጥ.5፡2 ላይም «በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ» ተብሎ ለሽማግሌዎች የተመከረው ቃልም ይህንኑ የሚገልጽ ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስም «ጠቦቶቼን ጠብቅ» ብሎ ለጴጥሮስ የነገረውን ስናስብ ገና ብዙ ነገሮችን ማስተዋል የሚጠበቅባቸውና በመንፈሳዊ ነገር ያልጎለመሱ፣ በጠቦትነት ደረጃ ያሉና በስሜታዊነትም ለሚመላለሱ አማኞች «የመጠበቅ አገልግሎት» በይበልጥ አስፈላጊ መሆኑን እንረዳለን፡፡
- 2ኛ. መንጋውን መጐብኘት
በ1ጴጥ.5፡2 ላይ የእግዚአብሔርን መንጋ በእረኝነት ለሚጠብቁ ሽማግሌዎች ከተሰጠው ምክር አንዱ «እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፣ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት» ይላል፡፡ ይህ በጥቅሉ ለሽማግሌዎች በአጥቢያ ቤተክርስቲያን ደረጃ ያላቸውን ኃላፊነት የሚያሳይ ሲሆን መመሪያው ግን የእረኞችን ሁሉ አገልግሎት ያሳያል፡፡ የክርስቶስ መንጋ ከሚያስፈልገው አገልግሎት አንዱ መጐብኘት ነው፡፡ አንድ እረኛ በጎቹን በሚጎበኝበት ጊዜ እነዚያ በጎች ያሉበትን የኑሮ፣ የጤና የአመጋገብና... የሌላም ሁኔታ ያያል፤ በዚያ የጎደላቸው ነገር ካለ የሚሟላበትን መንገድ ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ ጉብኝቱ ለመንጋው ሲባል እንጂ ለእረኛው ሲባል አይደለም፡፡ እረኞች ይህንን ተረድተው የሚያገለግሏቸውን የክርስቶስን መንጎች በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ ያውቁ ዘንድ በየጊዜው ጉብኝት ሊያደርጉላቸው ይገባል፡፡ ይሁን እንጂ ጉብኝቱ የሚከናወነው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ መሆን የለበትም፡፡ እረኞች የጉብኝት ሥራ በሚሠሩበት ጊዜ ወደውና ፈቅደው በደስታ ሊያደርጉት እንደሚገባ እንጂ በኃይል የተጫነባቸው ይመስል በግድ መሆን እንደሌለበት የሚገልጽ ነው፡፡ እንደዚሁም በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት መሆን የለበትም፤ እረኞች ከሚጎበኟቸው አማኞች ሊያገኙት የሚችሉትን ሥጋዊ ጥቅም እያሰቡ ሊጎበኙ የሚዞሩ መሆን እንደሌለባቸው በዚህ ቃል ተመክረዋል፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ ጥቅም «መጥፎ ረብ» ተብሏል፡፡ ስለዚህ እረኞች በሌላ በምንም ዓይነት ጥቅም ተነድተው ሳይሆን በቃሉ እንደተነገረው በበጎ ፈቃድ ላይ ብቻ ተመሥርተው፣ አደራውን የሰጣቸው የክርስቶስ ፍቅር ብቻ ግድ ብሏቸው ለመንጋው የተቀደሰ ጉብኝት ሊያደርጉ ይገባል፡፡
- 2ኛ. መንጋውን መጐብኘት
ጌታ ኢየሱስ ስለ እውነተኛ እረኛ በተናገረበት ክፍል «... የራሱንም ሁሉ ካወጣቸው በኋላ በፊታቸው ይሄዳል» የሚለውን ቃል ተመልክተናል፤ እረኞች የክርስቶስን መንጋ በመልካም ምሳሌነት እየመሩ የክርስትና ሕይወትን የጉዞ አቅጣጫ ሊያሳዩ እንደሚገባም አይተናል፡፡ በእርግጥም መልካም ምሳሌነት ሁል ጊዜም ቢሆን በእረኞች ላይ ሊታይ የሚገባው ነገር ነው፤ በ1ጴጥ.5፡3 ላይ ከሌሎቹ ምክሮች ቀጥሎ ለሽማግሌዎች የተሰጠው አንዱ ምክር «ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ» የሚል ነው፡፡ እረኞች የክርስቶስ ለሆኑት አማኞች የሚያስተምሯቸውን ቃል እንዲታዘዙ በኃይለ ቃል ወይም በማስጨነቅ መናገርና በግድ እንዲታዘዙ ማድረግ ተገቢ እንዳልሆነና ውጤትም እንደሌለው ከዚህ ንባብ እንረዳለን፡፡ ተገቢ የሆነውና ውጤት የሚያስገኘው አገልግሎት ግን በተግባር ለመንጋው ምሳሌ ሆኖ መገኘት ነው፡፡ በ1ጢሞ.4፡12 ላይ «... ለሚያምኑት ምሳሌ ሁን እንጂ...» የተባለውም ለዚህ ነው፡፡
- የእረኞች አገልግሎት በዘመናችን
በዘመናችን የክርስቶስ መንጋ ከፍ ባለ ግራ መጋባት ወዲያና ወዲህ እየተቅበዘበዘ ሲባዝን ይታያል፡፡ ይህ ደግሞ ለክርስቶስ ልብ በእጅጉ የሚያሳዝን ነው፤ እርሱ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተጥለውና ተጨንቀው ለነበሩ ሕዝቦች እንዳዘነላቸው የተጻፈው ቃል ይህን የእርሱን ስሜት እንድናውቅ ያስችለናል (ማቴ.9፡36)፡፡ ስለሆነም ይህን የሚቅበዘበዝ ሕዝብ የሚጠብቁና የሚያሰማሩ እረኞችን ጌታ በዘመናችንም ቢሆን ይሰጣል፤ እነዚህ በእርግጥ ጌታ የሰጠን እረኞች ለእርሱ ባላቸው ፍቅር ነፍሳትን በታማኝነትና በቅርበት የሚያገለግሉ እረኞች ናቸው፡፡ በአንድ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ብዙ እረኞች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በዚህ ዘመን በዙሪያችን ባለው የክርስትና ዓለም ያለውን አሠራር ስንመለከት ግን ከዚህ በተቃረነ መልኩ በአንድ አጥቢያ «አንድን ሰው ብቻ» ፓ¬ስተር የሚያደርግ ወይም በአንዳንድ ቦታ እንደሚታየው «ረዳት ¬ፓስተሮችን» ጨምሮ የሚሾም የሰው ሥርዓት ይታያል፡፡ ይህም የቤተክርስቲያን ሥልጣን ተደርጎ ሲቆጠርና ከፓ¬ስተሩና ከረዳት ፓ¬ስተሩ ውጪም በዚያው አጥቢያ ሌሎች ¬ፓስተሮች (እረኞች) ሊኖሩና ሊያገለግሉ እንደማይችሉ ተደርጎ ሲወሰድ ይታያል፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ የሰው ሐሳብ ተለይተን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ስንመለስ እረኝነት «ዋና ¬ፓስተርም» ሆነ «ምክትል (ረዳት) ፓስተር» እየተባለ በሰው የሚሰጥ የሥልጣን ሹመት ሳይሆን ከጌታ የምንቀበለው የጸጋ ስጦታ መሆኑን እንረዳለን፤ እንደዚሁም ጌታ በአንዲት አጥቢያ ቤተክርስቲያን ውስጥ እንደሚያስፈልገው መጠን ከአንድ በላይ ፓ¬ስተሮችን (እረኞችን) ሊሰጥ እንደሚችል እንገነዘባለን፡፡ እነዚህ ጌታ የሚሰጠን እረኞችም የሚጠብቋቸውን፣ የሚያሰማሯቸውንና የሚጎበኟቸውን በጎች ራሱ ጌታ ይሰጣቸዋል፤ ይህንንም እርሱ በየጊዜው በተለያየ መንገድ ወደ እነርሱ በማምጣትና በማገናኘት የሚያከናውነው ይሆናል፡፡ በዚህ መልክ ጌታ ወደ እነርሱ ያቀረባቸውን ነፍሳት እረኞች በታማኝነትና በትጋት ሊያገለግሏቸው ይገባል፡፡
ጌታችን ለቤተክርስቲያን የሰጣቸው እረኞች በሰው ሥርዓት መሾምንና «¬ፓስተር» ተብለው መጠራትን የሚፈልጉ አይደሉም፤ በዚህ ባለንበት ዘመን በክርስትናው ዓለም ያለውን የእረኝነት አገልግሎት ስንቃኝ ግን በብዛት የተለመደው አሠራር በአንድ ጉባኤ ላይ አንድን ሰው «¬ፓስተር» ብሎ በመሾም የሚታየው አሠራር ነው፡፡ አንዲትን አጥቢያ ቤተክርስቲያን (ጉባኤ) በመልካም የሚያስተዳድሯት እረኞች መንፈስ ቅዱስ የሚያስነሣቸውና የሽማግሌነትን ሥራ የሚሠሩ ወይም በጌታ የሚገዙ ወንድሞች ናቸው እንጂ አንድ እረኛ (¬ፓስተር) አይደለም፡፡ በዘመናችን በድርጅታውያን አብያተ ክርስቲያናት የሚታየው የአንድ ሰው አስተዳደር ግን የሰው ሥርዓት ነው እንጂ ከእግዚአብሔር ቃል የተገኘ አይደለም፡፡ እንደዚሁም ጌታ ለቤተክርስቲያን የሚሰጣቸው እረኞች ራሱ በጊዜው በእረኝነት አገልግሎት እያተጋ በየአጥቢያ ቤተክርስቲያኑ የሚገልጣቸው እንጂ ከአንድ ሥልጠና ወይም ከአንድ የቲዎሎጂ ት/ቤት የተመረቁ ስለሆኑ ብቻ በሰው የሚሾሙ አይደሉም፡፡ ፓ¬ስተርነት (እረኝነት) ዲግሪ ወይም ዲፕሎማ የሚቀበሉበት አንድ ምድራዊ ሙያ ሳይሆን ጌታ መንጋውን ለማስጠበቅና ለማስመሰግ ለቤተክርስቲያኑ የሚሰጠው ስጦታ ነው፤ ስለሆነም በዚህ ዓለም ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንደተመረቁበት የትምህርት ዓይነት «ዶክተር እከሌ» ወይም «ኢንጂነር እከሌ» .... እየተባሉ በሙያዊ የማዕረግ ስም እንደሚጠሩበት ልማድ «¬ፓስተር እከሌ» ተብሎ የመጥራትም ሆነ የመጠራት ልማድ መኖር የለበትም፡፡ በመሠረቱ «ፓስተር» የሚለው ቃል የላቲን ቃል ሲሆን በእንግሊዘኛና በሌሎች ቋንቋዎች ሁሉ የተለመደ ቃል ሆኗል፤ ትርጉሙ ግን ሌላ ምንም ሳይሆን «እረኛ» ማለት ነው፡፡ ሆኖም በአገራችን በሰው የሚሾሙት ወይም ራሳቸውን የሚሾሙት ግለሰቦች «¬ፓስተር» እንጂ «እረኛ» ተብለው ሲጠሩ አይሰማም፤ የዚህን ምክንያት በጥንቃቄ የመረመረ ሰው «እረኛ» ብሎ በአማርኛ ከመጥራትም ሆነ ከመጠራት ይልቅ «ፓ¬ስተር» ብሎ መጥራትም ሆነ «¬ፓስተር» ተብሎ መጠራት ለሥጋ ይበልጥ ደስ ስለሚያሰኝ መሆኑ ሊሰወረው አይችልም፡፡ ሆኖም በጥቅሉ «¬ፓስተር» የሚለው የላቲን ቃልም ሆነ «እረኛ» የሚለው የአማርኛ ቃል ከመጠሪያ ስም በፊት እየገባ የሚነገር የማዕረግ ስም (ቅጽል) አለመሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ይህ አጠቃቀም በዓለም ካለው የሰው ሥርዓት ወይም «መምህር መምህር» ተብለው መጠራት ከሚወዱት ከፈሪሳውያን ልማድ የተወረሰ ጠባይ እንጂ (ማቴ.23፡7) ከመጽሐፍ ቅዱስ የተገኘ ባለመሆኑ ልንርቀው ይገባል፡፡
እረኞች በአንድ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ሥር በገንዘብ ተቀጥረው የሚያገለግሉም አይደሉም፡፡ እንዲህ ያለው አሠራር በዘመናችን በብዙ ስፍራ የተለመደ ቢሆንም ከመጽሐፍ ቅዱስ የተገኘ ግን አይደለም፡፡ በእርግጥ የእረኝነት አገልግሎቱ የእረኞቹን ሙሉ ጊዜ የሚወስድ ከሆነ እንደማንኛውም የወንጌል አገልጋይ የወንጌል ቀለብን ከሚያገለግሏቸው አማኞች መቀበል በእግዚአብሔር ቃል የሚገኝ አሠራር ነው፡፡ ሆኖም እረኞች በዓለማውያን መሥሪያ ቤቶች እንደሚሠሩ ሠራተኞች በደመወዝ ተቀጥረው የሚያገለግሉ ከሆነ ግን የሞያተኛ እረኞችን ባሕርይ ይይዛሉ፤ ስለሆነም ከዚህ ዓለማዊ አሠራር መለየት ያስፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ቃል ከሚያገለግሏቸው አማኞች የወንጌል ቀለብን እየተቀበሉ ጊዜያቸውን ለእረኝነት አገልግሎት የሰጡ ወንድሞችም ቢሆኑ ስለሚቀበሉት ቀለብ ብለው የክርስቶስን እውነት ለመንጋው ከመግለጥ ወደ ኋላ ማለት የለባቸውም፤ የመንጋውን መንፈሳዊ ዕድገት ሳይሆን ከመንጋው የሚገኘውን ረብ (ጥቅም) አይተው ጌታ ሳያሰማራቸው እረኞች ነን ብለው ለማገልገል የተነሡ ሰዎች ግን ስለሚያገኙት ጥቅም እንጂ ስለ እግዚአብሔር እውነት ግድ የላቸውም፡፡ ስለሆነም ለሰው ደስ የሚያሰኘውን እንጂ ለጌታ ደስ የሚያሰኘውን አያዩም፡፡ በዘመናችን እጅግ ብዙ በጎች እንዲህ ያለውን ነውረኛ ረብ በሚያጋብሱ ሰዎች አላግባብ ሲሸለቱ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ «ስጡ ይሰጣችኋል» የሚለው የተቀደሰ መርህ ተጣምሞ እየተተረጐመላቸው «ለተቀባውና ለባለራእዩ ወይም ለነፍስ አባታችሁ ስትሰጡ እግዚአብሔር ለእናንተ ይሰጣል» የተባሉና በእጅጉ የተበዘበዙ ብዙ የዋሃንን በዙሪያችን ስንመለከት የሞያተኞች እረኞችን የተንኰል አሠራር በእግዚአብሔር ቃል ገልጦ ለማሳየትና ለየዋሃኑ ለማሳወቅ ያለን ፍላጎት እየጨመረ ይሄዳል፡፡ የሚገርመው ደግሞ እጅግ በተገለጠ ማጭበርበር እየተበዘበዙ ያሉት ምስኪኖች እውነቱን ቢረዱም እንኳ ከዚያ የዓመፅ አሠራር ሊለዩ አለመቻላቸው ነው፤ ስለሆነም እግዚአብሔር የእነዚህን የዋሃን ዓይኖች እንዲከፍት በቃልና በጸሎት ልንተጋ ያስፈልጋል፡፡
እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተጥለውና ተጨንቀው ያሉትንና በሞያተኛ እረኞች እየተታለሉ በየስፍራው የሚቅበዘበዙትን የክርስቶስን በጎች በየግል እየቀረቡ የሚያስፈልጋቸውን አገልግሎት የሚሰጡ እረኞች በየዘመናቱ የሚያስፈልጉ በመሆናቸው በዘመናችንም ጌታ ያስነሣቸው እውነተኛ እረኞች በየስፍራው እንዳሉት የታመነ ነው፤ እንዲህ ያሉት እረኞች በዙሪያቸው ባለው የሃይማኖተኛ ዓለም አሠራር ሳይደናገሩ ከክርስቶስ የተቀበሉትን አደራ በትጋት ሊወጡ ይገባል፡፡ በብዙ መደነጋገርና በብዙ ጥያቄ ውስጥ የሚገኙ ብዙ የዋሃን የክርስቶስ በጎች እንዲህ ያለው አገልግሎት በእጅጉ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ጌታ በዚህ አገልግሎት የተገለጡ እውነተኛ እረኞችን አብዝቶ እንዲሰጠንም የዘወትር ጸሎታችን ሊሆን ይገባል፡፡
5. አስተማሪዎች
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አካሉ ለሆነች ቤተክርስቲያን ከሚሰጣቸው ስጦታዎች መካከል «አስተማሪዎች» አንደኛዎቹ ናቸው፡፡ አስተማሪዎች በኤፌ.4፡11 ላይ ከተዘረዘሩት ስጦታዎች አምስተኛ ሆነው የተጠቀሱ ቢሆንም «ከእረኞች» ጋር ተያይዘው ተገልጠዋል፤ በዚህ ክፍል «እረኞችና አስተማሪዎች» የሚለው አገላለጽ ይህንኑ የሚያስረዳ ነው፡፡ በወንጌል ሰባኪዎች አገልገሎት ወደ ጌታ የመጡት ነፍሳት በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እያደጉ እንዲሄዱ፣ እንዲታነጹ፣ እንዲጸኑ፣ የእረኞችና የአስተማሪዎች አገልግሎት በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ ሁለቱ ስጦታዎች ምንም እንኳ የተለያዩ ቢሆኑም ሁልጊዜም ባይሆን በአብዛኛው በአንድ ሰው ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ነፍሳትን በእረኝነት አገልግሎት ለመጠበቅ የአስተማሪነት ስጦታ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡ ይሁንና እረኞች ነፍሳትን በመጠበቅና በመመገብ ላይ የሚያተኩሩ ሲሆኑ አስተማሪዎች የእግዚአብሔርን እውነት በመግለጥና በማስረዳት ላይ የሚያተኩሩ ስለሆኑ ስጦታዎቹ ሁለት የተለያዩ ስጦታዎች ናቸው፡፡ ስለሆነም ሁለቱንም በተመለከተ የእግዚአብሔር ቃል የሚያስተምረንን እውነት ለይተን ማጥናት ይገባናል፡፡
በ1ቆሮ.12፡28 ላይ «እግዚአብሔርም በቤተክርስቲያን አንዳንዶቹን አስቀድሞ ሐዋርያትን፣ ሁለተኛም ነቢያትን፣ ሦስተኛም አስተማሪዎችን... አደረገ፡፡» የሚል ቃል እናነባለን፤ ከዚህም ቃል አስተማሪዎች እንደ ሌሎቹ ስጦታዎች ሁሉ እግዚአብሔር በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገልጣቸው ወይም የሚያስነሣቸው መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ የእግዚአብሔርን እውነት ማስተማር በብዙዎች ሊታሰብ እንደሚችለው ከአእምሮ ብስለት፤ ከእውቀት ብዛት ወይም የተለያዩ ሥልጠናዎችንና ሴሚናሮችን ከመውሰድ ሊገኝ የሚችል አይደለም፡፡ በዘመናችን በቴዎሎጂ ት/ቤት ስለተማሩ ብቻ በአስተማሪነት ሥራ ተቀጥረው የተለያዩ ሥልጠናዎችን እንዲሰጡ የተመደቡ ሰዎችን በየስፍራው እናያለን፡፡ ከእነዚህ መካከል እግዚአብሔር ከመጀመሪያው ጸጋውን ስለሰጣቸው የሚያገለግሉ አንዳንዶች እንዳሉ የማይካድ ቢሆንም ይህ አሠራር ግን አስተማሪዎችን ለቤተክርስቲያን የሚሰጠውና በመካከላችንም የሚገልጣቸው እግዚአብሔር እንደ ሆነ ከሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር ተቃራኒ ነው፡፡ በእውነት የሚኖሩ ክርስቲያኖች ግን እግዚአብሔር በመካከላቸው አስተማሪዎችን እንደሚያስነሣና እንደሚሰጣቸው ይተማመኑበታል፡፡
አስተማሪዎች ሆነው ለቤተክርስቲያን የተሰጡ ወንድሞች የአገልግሎታቸውን ባሕርይ በአዲስ ኪዳን ዘመን የመጀመሪያው መምህር (አስተማሪ) ከሆነው ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ሊማሩ ይችላሉ፡፡ እርሱ «የእስራኤል መምህር» በነበረው በኒቆዲሞስ «መምህር ሆይ፡- እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን» ተብሎ የተመሰከረለት መምህር ነው (ዮሐ.3፡2)፡፡ ኢየሱስ በምድር ላይ ያስተምር በነበረ ጊዜ በደቀመዛሙርቱም ሆነ በሌሎች ሰዎች «መምህር ሆይ» እየተባለ ይጠራ ነበር፡፡ እርሱ በእርግጥም ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጣ መምህር ሰለሆነ መምህር ተብሎ መጠራቱ አግባብነት ነበረው፡፡ ይህንንም ራሱ ለደቀመዛሙርቱ አረጋግጦ ሲናገር «... እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ፤ እንዲሁ ነኝና መልካም ትላላችሁ» ብሏል (ዮሐ.13፡13)፤ በመልካም አስተማሪነቱም የእግዚአብሔርን እውነት በቤተመቅደስ (ዮሐ.7፡14፤ ማቴ.26፡55)፣ በምኲራብ (ማር.1፡21፤ 6፡2)፣ በተራራ ላይ (ማቴ.5፡1-2)፣ በባሕር ዳር (ማር.4፡1) ለሕዝቡና ለደቀመዛሙርቱ ያስተምር ነበር፤ በትምህርቱም የሚሰሙት ሁሉ ይገረሙ ነበር (ማቴ.7፡28፤ 22፡33)፤ ሲገረሙም «እነዚህን ነገሮች ይህ ከወዴት አገኛቸው፣ ለዚህ ሰው የተሰጠችው ጥበብ ምንድር ናት?.....» ይሉ ነበረ (ማር.6፡2)፡፡ በሚከተሉት ደቀመዛሙርቱም ሆነ በማያምኑት አይሁድ ሁሉ ዘንድ ይህን ያህል የተደነቀው እውነተኛው መምህር ጌታ ኢየሱስ በቤተክርስቲያን እግዚአብሔር ለሚያስነሳቸው አስተማሪያዎች ድንቅ አብነት (ምሳሌ) ነው፡፡
ቤተክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ መውረድ ከተመሠረተች በኋላ ሐዋርያት የመስበክ ብቻ ሳይሆን የማስተማር አገልግሎትንም ይሰጡ ነበር፤ በሐ.ሥ.5፡42 ላይ «ዕለት ዕለትም በመቅደስና በቤታቸው ስለ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ማስተማርንና መስበክን አይተውም ነበር» ተብሎ የተጻፈው ቃል ይህንን ይገልጻል፤ ስለሆነም በሐዋርያት አገልገሎት ውስጥ የወንጌል ሰባኪነትን ጸጋ እንደምናገኝ ሁሉ የአስተማሪነትን ጸጋም እናገኛለን፡፡ ይሁንና እግዚአብሔር አስተማሪዎችን በየአብያተክርስያናቱ በማስነሣት እነርሱ ራሳቸውን የቻሉ የተለዩ ስጦታዎች እንደሆነ አረጋግጧል፤ በአንጾኪያ ቤተክርስቲያን መምህራን መኖራቸው ይህን እንድናስተውል ያደርገናል፤ ይህን በተመለከተ የተጻፈው ቃልም «በአንጾኪያ ባለችው ቤተክርስቲያን ውስጥ ነቢያትና መምህራን ነበሩ፤ እነርሱም በርናባስ፣ ኔጌር የተባለው ስምዖን፣ የቀሬናው ሉክዮስም፣ የአራተኛው ገዥ የሄሮድስ ባለሟል ምናሔ፣ ሳውልም ነበሩ» የሚል ነው (የሐ.ሥ.13፡1)፤ በዚህ ቃል ውስጥም የትኞቹ ነቢያት የትኞቹ መምህራን እንደሆኑ ተለይተው ባይነገሩንም በርናባስና ሳውል የአስተማሪነት ስጦታ እንዳላቸው በሌሎች ንባቦች እንረዳለን፡፡ ለምሳሌ በሐ.ሥ.11፡26 ላይ «በቤተክርስቲያንም አንድ ዓመት ሙሉ ተሰበሰቡ፤ ብዙ ሕዝብንም አስተማሩ» ተብሎ ስለ በርናባስና ሳውል የተጻፈው ቃል በይበልጥ ላመኑ ሰዎች ለመታነጽና ለመጽናት ለማደግም የሚሆን የእግዚአብሔር ቃል ሲያስተምሩ እንደ ነበር የሚያሳይ ነው፡፡ እንደዚሁም በሐ.ሥ.15፡35 ላይ «ጳውሎስና በርናባስም ከሌሎች ከብዙ ሰዎች ጋር ደግሞ የጌታን ቃል እያስተማሩና ወንጌልን እየሰበኩ በአንጾኪያ ይቀመጡ ነበር» ሲል እነዚህ ሁለቱ አገልጋዮች በአንጾኪያ አብረው በነበሩ ጊዜ የነበራቸው አገልግሎት ወንጌልን ለማያምኑት መስበክ ብቻ ሳይሆን ላመኑትም የጌታን ቃል ማስተማር እንደነበር ያስገነዝባል፡፡ በተለይም ጳውሎስ ሐዋርያም ስለሆነ ወንጌል ወዳልደረሰበት ቦታ ሄዶ በሚሰብከው ወንጌል የሚያምኑትን ሰዎች የጌታ ደቀመዛሙርት ሆነው እንዲለዩ በማድረግ የተወሰነ ጊዜ እዚያው አብሮአቸው በመኖር የእግዚአብሔርን ቃል ያስተምራቸው ነበር፤ ለምሳሌ በቆሮንቶስ «በመካከላቸው የእግዚአብሔርን ቃል እያስተማረ ዓመት ከስድስት ወር የተቀመጠ ሲሆን በኤፌሶን ደግሞ ደቀመዛሙርትን ለይቶ ጢራኖስ በሚሉት ት/ቤት ዕለት ዕለት እየተነጋገረ ሁለት ዓመት ያህል ተቀምጧል (የሐ.ሥ.18፡11፤ 19፡9)፡፡ ለማያምኑ ሰዎችም ቢሆን በተለይም ለአይሁድ በማስረዳትና መጻሕፍትን በመተርጐም ይመሰክርላቸው ነበር (የሐ.ሥ.17፡2፤ 18፡4፤ 19፡8፤ 28፡23-31)፡፡ ይህም የአስተማሪነት ሥራ ባሕርይ ነው፡፡ ከዚህም የምንረዳው አስተማሪዎች በውስጥ ያሉትን አማኞች ለማጠንከርና ለማጽናት የሚያስችል አገልግሎት እየሰጡ ከዚህ ጐን ለጐን ደግሞ በውጭ ያሉ በጥያቄ የተሞሉ ኢአማንያንን ለማስረዳትና ለማሳመን የሚያስችል አገልግሎትን የሚሰጡ መሆናቸውን ነው፡፡
የአስተማሪነትን ጸጋ በአጵሎስ ውስጥም እናገኛለን፡፡ እርሱ ገና ሙሉውን የክርስትና እውነት ሳይረዳ በመጥምቁ ዮሐንስ ትምህርት ብቻ ይህ ጸጋው መታየት ጀምሮ ነበር፤ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እርሱ «በመጻሕፍት እውቀት የበረታ ነበረ፤ እርሱ የጌታን መንገድ የተማረ ነበረ፤ የዮሐንስንም ጥምቀት ብቻ አውቆ በመንፈስ ሲቃጠል ስለ ኢየሱስ ይናገርና በትክክል ያስተምር ነበር» (የሐ.ሥ.18፡25)፤ ይህንን ጸጋውን የተመለከቱት አቂላና ጵርስቅላም ወስደው የእግዚአብሔርን መንገድ ከፊት ይልቅ ገለጡለት(የሐ.ሥ.18፡26)፡፡ አስተማሪዎች ሙሉውን የቅዱሳት መጻሕፍት እውቀት ሊይዙ ቢገባቸውም ጸጋው የሚሰጣቸው ግን ከዚያ በፊት እንደሆነ በዚህ መረዳት ይቻላል፤ የተሰጣቸውን ጸጋ በብቃት እንዲያገለግሉበትም ከእነርሱ አስቀድመው የእግዚአብሔርን እውነት ከሚያውቁ አማኞች ዝቅ ብለው መማር እንዳለባቸውም ከአጵሎስ ሕይወት እንማራለን፡፡ አጵሎስ ወደ ቆሮንቶስ ሄዶ በአስተማሪነት ጸጋው ያመኑትንም ሆነ ያላመኑትን አይሁድን ያገለግል ነበር፡፡ «በደረሰም ጊዜ አምነው የነበሩትን በጸጋ ይጠቅማቸው ነበር፡፡ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ ከመጻሕፍት እየገለጠ ለአይሁድ በሁሉ ፊት በጽኑ ያስረዳቸው ነበርና» ተብሎ ስለ እርሱ የተጻፈው ቃል አጵሎስ በቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን የነበረውን የአስተማሪነት አገልግሎት ያመለክታል (የሐ.ሥ.18፡27-28)፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም «እኔ ተከልኩ፤ አጵሎስ አጠጣ» ብሎ በጻፈው ቃል የአጵሎስ አገልግሎት በይበልጥ አስቀድሞ በጳውሎስ ስብከት ያመኑትን አማኞች እንዲጸኑና እንዲጠነክሩ የሚረዳ መሆኑን አመልክቷል፤ የማስተማር አገልግሎት ተተክሎ የበቀለውንና የጸደቀውን ተክል እንደማጠጣት ነውና፡፡ ስለሆነም በጌታ አምነው የጸደቁ አማኞች የአስተማሪዎች አገልግሎት ያስፈልጋቸዋል፡፡
እንደዚሁም ጢሞቴዎስ የወንጌል ሰባኪነት ጸጋ ያለውን ያህል (2ጢሞ.4፡5) የአስተማሪነት ጸጋም እንደነበረው ለእርሱ ከተጻፉለት ሁለት መልእክታት መረዳት እንችላለን፡፡ እርሱ ከሕጻንነቱ ጀምሮ ቅዱሳት መጻሕፍትን ያውቅ ነበር (2ጢሞ.3፡15) ከጳውሎስም ጋር አብሮ ያገለገለ በመሆኑ የጳውሎስን ትምህርት የተከተለ ሰው ነው (2ጢሞ.3፡10)፤ ስለሆነም ጳውሎስን «ስለዚህ ወንድሞችን ብታሳስብ በተከተልከው በመልካም ትምህርት የምትመገብ መልካም አገልጋይ ትሆናለህ» በማለት ይጽፍለታል (1ጢሞ.4፡6)፤ እንዲሁም «ይህን እዘዝና አስተምር፤... እስክመጣ ድረስ ለማንበብና ለመምከር ለማስተማርም ተጠንቀቅ ... ለራስህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ» (1ጢሞ.4፡11-16)፤ «እነዚህን አስተምርና ምከር» (1ጢሞ.6፡3)፣ “… ፈጽመህ እየታገስህና እያስተማርህ ዝለፍ ገሥጽ ምከርም” (2ጢሞ.4፡2) ብሎ ጽፎለታል፡፡ እነዚህ ሁሉ ንባቦች ጢሞቴዎስ ከሌሎች የጸጋ ስጦታዎች ጋር የአስተማሪነት ጸጋ የተሰጠውና እርሱም ራሱ ለቤተክርስቲያን አስተማሪ ሆኖ የተሰጠ መሆኑን እንገነዘባለን፤ በተመሳሳይ መንገድ በቀርጤስ ሲያገለግል የነበረው ቲቶም የአስተማሪነትን ሥራ ይሠራ እንደነበር ከተጻፈለት መልእክት እንረዳለን፤ በቲቶ.2፡1 ላይ «አንተ ግን ሕይወት ለሚገኝበት ትምህርት የሚገባውን ተናገር» ተብሎ የተጻፈለት ቃል እና በቁ.8 ላይ «በትምህርትህም ደኅንነት ጭምትነትን ጤናማና የማይነቀፍ ንግግርን ግለጥ» የሚለው ቃል ቲቶ እንደ ጢሞቴዎስ ሁሉ ከሌሎች ጸጋዎች ጋር አስተማሪነት በዋናነት እንደተሰጠው የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡ በጢሞቴዎስና በቲቶ አገልግሎት ውስጥ የምናየው ይህ የአስተማሪነት ጸጋ በተለይ የአገልግሎቱን ተግባራዊ ገጽታ ለአስተማሪዎች ሁሉ የሚያሳይ ነው፡፡ በየአጥቢያ ቤተክርስቲያኑም በሐዋርያት ወይም እነርሱ ባዘዟቸው ሰዎች ይሾሙ የነበሩት ሽማግሌዎች ወይም በጌታ የሚገዙ ወንድሞች ለማስተማር የሚበቁ መሆን እንዳለባቸው ተነግሯል (1ጢሞ.3፡2፤ ቲቶ.1፡9)፡፡ «መልካም የሚያስተዳድሩ ሽማግሌዎች ይልቁንም በመስበክና በማስተማር የሚደክሙት እጥፍ ክብር ይገባቸዋል» የሚለው ቃል ሽማግሌዎች ከአስተዳደር አገልግሎታቸው ጋር የመስበክና የማስተማር ሥራ ሊሠሩ እንደሚችሉ የሚያመለክት ነው (1ጢሞ.5፡17)፡፡ ይሁንና ሽማግሌዎች ያልሆኑ አስተማሪዎችን እግዚአብሔር በየአጥቢያ ቤተክርስቲያኑ በዘመናት ሁሉ ያስነሣል፤ እነርሱንም አስተማሪዎች አድርጎ የሚሰጠው ለመላይቱ ቤተክርስቲያን በመሆኑ አገልግሎታቸው በአንዲት አጥቢያ ቤተክርስቲያን ብቻ የሚገደብ አይደለም፤ እግዚአብሔር በመንፈሱ እንደመራቸው በየስፍራው እየተዘዋወሩ በቅዱሳት መጻሕፍት የተገለጠውን መለኮታዊ ትምህርት በማስተማር ያገለግላሉ፡፡
አስተማሪዎች የሚያስተምሩት ትምህርት በክርስቶስና በሐዋርያቱ የተገለጠውን የእግዚአብሔርን እውነት ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመጣበትን ዓላማ ሲገልጥ «እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ፤ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ» ብሏል (ዮሐ.18፡37)፤ የሚናገረውንም እውነት «ከእግዚአብሔር የሰማሁት እውነት» በማለት ገልጦታል (ዮሐ.8፡40)፡፡ እርሱ በምድር ላይ እያስተማረ ሳለ አይሁድ ያልተቀበሉት፣ ነገር ግን ከእግዚአብሔር የሆነ ትምህርት ነበረው፡፡ ይህን ትምህርቱን በተመለከተ ሲናገርም «ትምህርቴስ ከላከኝ ነው እንጂ ከእኔ አይደለም፤ ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድ ቢኖር እርሱ ይህ ትምህርት ከእግዚአብሔር ቢሆን ወይም እኔ ከራሴ የምናገር ብሆን ያውቃል» ብሏል (ዮሐ.7፡16-17)፡፡ ይህም ቃል ጌታችን «ትምህርቴ» «ይህ ትምህርት» ብሎ የጠራው፣ ከሌሎች ትምህርቶች የተለየ ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጣና አንድ እውነተኛ ትምህርት እንዳለ ያስገነዝባል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ያስተማራቸው ዋና ዋና ትምህርቶችም ስለአባቱና ስለራሱ፣ ስለመንፈስ ቅዱስም ማንነት ያስተማረው ትምህርት፣ በተራራ ያስተማረው የእርሱ ደቀመዛሙርት የሚለዩበት የሥነምግባር ትምህርት (ማቴ.5-7)፣ በባሕር ዳር ስለመንግሥተ ሰማያት ምስጢር በምሳሌ ያስተማረው ትምህርት (ማቴ.13)፣ ስለዳግም ምጽአት ለደቀመዛሙርቱ ያስተማረው ትምህርት (ማቴ.24-25)፣ እንዲሁም የዘላለም ሕይወትን፣ ዳግም ልደትን፣ አምልኮን፣ ጸሎትን አገልግሎትን ... ወዘተ የሚመለከቱ የተለያዩ ትምህርቶችን አስተምሯል፡፡ ለቤተክርስቲያን የተሰጡ አስተማሪዎች ይህን የክርስቶስን ትምህርት ሊያስተምሩ ይገባቸዋል፡፡ በ2ዮሐ.9 ላይ «ለሚወጣ ሁሉ በክርስቶስም ትምህርት ለማይኖር ሰው አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት ለሚኖር አብና ወልድ አሉት፡፡» የሚል ቃል እናነባለን፡፡ በዚህ ክፍል የቤተክርስቲያን አስተምህሮ «የክርስቶስ ትምህርት» ተብሎ የተጠራ ሲሆን ክርስቲያኖች የሚያምኑትና አስተማሪዎችም የሚያስተምሩት ትምህርት ክርስቶስ ያስተማረው ትምህርት ሊሆን እንደሚገባ ያሳያል፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣበትን ዓላማ ፈጽሞ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት የገለጠው እውነት ነበረ፡፡ ኢየሱስ ይህን አስመልክቶ ሲናገር «ከእናንተ ጋር ስኖር ይህን ነግሬአችኋለሁ፤ አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱሰ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል፤ እኔም የነገርኳችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል» ብሏል (ዮሐ.14፡25-26)፤ እንዲሁም «የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፤ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም፡፡ ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፡፡» በማለት አስቀድሞ ተናግሯል (ዮሐ.16፡12)፡፡ ስለዚህ ሐዋርያት ክርስቶስ ያስተማራቸው ትምህርት እንዳለ ሆኖ እርሱ ያልነገራቸውን ቀሪ እውነት ወይም ትምህርት ደግሞ መንፈስ ቅዱስ እንዳስተማራቸው በእነዚህ ጥቅሶች እንረዳለን፤ እነርሱም ከጌታ ኢየሱስና ከመንፈስ ቅዱስ ያገኙትን (የተቀበሉትን) ሙሉውን የእግዚአብሔር እውነት አስተምረዋል፤ ትምህርታቸውም «የሐዋርያት ትምህርት» ተብሎ የተጠራ ሲሆን በሐዋርያት ሥራና በመልእክታት ውስጥ በስፋት የተገለጠ ትምህርት ነው፡፡ የመጀመሪያዎቹ አማኞች ከሚተጉባቸው ነገሮች አንዱና የመጀመሪያው የሐዋርያት ትምህርት እንደ ነበር በሐ.ሥ.2፡42 ላይ እናነባለን፡፡ ከሐዋርያት ትምህርት ቀጥሎ እነዚህ አማኞች ይተጉ እንደነበር የተገለጠው በኅብረት ነው፡፡ ሁሉም አማኞች በሐዋርያት ትምህርት ያምኑ ስለነበር ኅብረት ሊኖራቸው ችሏል፡፡ እውነተኛ ኅብረት ወይም የመንፈስ አንድነት ሊኖር የሚችለው አማኞች ሁሉ የሚያምኑት ትምህርት የክርስቶስና የሐዋርያት ትምህርት ብቻ ሲሆን ነው፡፡ በተለያየ ዘመን በቤተክርስቲያን ጌታ የሚያስነሣቸው አስተማሪዎችም ሊያስተምሩት የሚገባው ትምህርት ክርስቶስና ሐዋርያት ያስተማሩትን ትምህርት ብቻ ሊሆን ይገባል፡፡ ሐዋርያት ጌታንም እነርሱንም ባልተቀበሉት አይሁድ ዘንድ የሚታወቅ በጊዜው ከነበረው የፈሪሳውያንና የሰዱቃውያን ሃይማኖታዊ ትምህርት የተለየ ትምህርት ነበራቸው፤ ይህም ትምህርት በጌታ በኢየሱስ ስም የሚያስተምሩት ሲሆን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ፣ ስለ በደላችን እንደ ሞተ እኛን ስለማጽደቅም ከሙታን እንደተነሣ በእግዚአብሔር ቀኝ እንደተቀመጠ፣ ወደፊትም በሕያዋንና በሙታን ላይ የሚፈርደው እርሱ እንደሆነ እንዲሁም ሌሎችን እውነቶች ያካተተ ትምህርት ነው፡፡ ይህን ትምህርት ሲያስተምሩ «በዚህ ስም እንዳታስተምሩ አጥብቀን አላዘዝናችሁምን? ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞልታችኋል» በማለት የአይሁድ ሸንጎ ይቃወማቸው ነበር (የሐ.ሥ. 5፡27)፡፡ ስለሆነም «በትምህርታችሁ» ተብሎ ሊገለጽ የቻለ በጊዜው ሐዋርያት ብቻ የሚያስተምሩት ትምህርት እንደነበር ከዚህ እንረዳለን፡፡ አስተማሪዎች በየስፍራው ሊያስተምሩት የሚገባው ትምህርትም ያንኑ የሐዋርያትን ትምህርት ሊሆን ይገባል፡፡
የክርስትናው ዓለም በተለያየ ትምህርት ተከፋፍሎ በሚታይበት ዘመን ሁሉ እውነተኛ አስተማሪዎች የክርስቶስንና የሐዋርያትን ትምህርት በማስተማር ያገለግላሉ፡፡ በክርስትናው ዓለም መከፋፈል የመጣውም የሐዋርያትን ትምህርት ከመከተል ይልቅ የተለያዩ የሐሰት አስተማሪዎች በሚፈጥሩት የሐሰት ትምህርት በመወሰድ ነው፡፡ እውነተኛ ትምህርት የመኖሩን ያህል ከሰይጣን የሆኑ የሐሰት ትምህርቶች መኖራቸውን ልንዘነጋ አይገባም፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እነዚህ የሐሰት ትምህርቶች «ልዩ ወንጌል» (ገላ.1፡6)፣ «ልዩ ትምህርት (1ጢሞ.1፡3፤ 6፡3)፣ እንግዳ ትምህርት» (ዕብ.13፡9)፣ «የአጋንንት ትምህርት» (1ጢሞ.4፡2) .... ተብለው ተገልጸዋል፡፡ በሐዋርያት ዘመን «የበለዓም ትምህርት» (ራእ.2፡14)፣ «የኒቆላውያን ትምህርት» (ራእ.2፡15) ተብለው የተገለጡ ክፉ ትምህርቶች ነበሩ፡፡ እነዚህን ትምህርቶች የሚያስተምሩትም «ሐሰተኞች አስተማሪዎች» የተባሉ ሲሆን ክፉ ሥራቸውን በተመለከተ «እነርሱም የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ክደው የሚፈጥንን ጥፋት በራሳቸው ላይ እያሰቡ የሚያጠፋ ኑፋቄን አሾልከው ያገባሉ፤» ተብሎ ተጽፏል (2ጴጥ.2፡1)፡፡ ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ እስከ ዘመናችን ድረስ እነዚህ የሐሰት አስተማሪዎችና ክፉ ትምህርታቸው በዙሪያችን አሉ፡፡ በተለይም በእኛ ዘመን ብዙዎች ለሥልጣንና ለገንዘብ ጥቅም ሲሉ የፈጠሯቸው ብዙ ክፉ ትምህርቶች የሚያጠፉ ኑፋቄዎች ሆነው ብዙዎችን ሲያጠፉ ይታያል፡፡ በመሆኑም እውነተኛ አስተማሪዎች ከምን ጊዜውም ይልቅ ያስፈልጉናል፡፡ የሐሰተኛ ትምህርት ባሕርይው ከእውነተኛው ትምህርት ጋር ተደባልቆና ተመሳስሎ መቅረብ በመሆኑ ብዙ አማኞች የእውነትንና የሐሰትን ትምህርቶች ለይተው ለማወቅ ይቸገራሉ፡፡ ስለሆነም የእውነት ትምህርትን ከሐሰት ለይተው በአግባቡ የሚያስተምሩ ከጌታ የተሰጡ አስተማሪዎች ያስፈልጋሉ፡፡
የክርስቶስንና የሐዋርያትን ትምህርት የምናገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙት ቅዱሳት መጻሕፍት ነው፡፡ ስለሆነም አስተማሪዎች በተሰጣቸው ጸጋ ሲያገለግሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተገኘ ትምህርትን ብቻ ሊያቀርቡ ይገባል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበት አንዱ ዓላማም ለትምህርት መሆኑን ከራሱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንረዳለን፡፡ በሮሜ.15፡4 «በመጽናትና መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ ይሆንልን ዘንድ አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፏልና» የሚል ቃል እናነባለን፡፡ በ2ጢሞ.3፡16 ላይ ደግሞ «የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል» ተብሎ ተጽፏል፡፡ ስለዚህ አስተማሪዎች ለትምህርታቸው የሚጠቅሱት ማስረጃና ማስተማሪያ “መጽሐፍ ቅዱስ” ሊሆን ይገባል፡፡ በተከፋፈለው የክርስትና ዓለም አንዱ ከሌላው የሚለይበትን እምነት የሚገልጹ ትምህርቶችን የያዙ የእምነት መግለጫዎች በበዙበት በዚህ ዘመን ከእግዚአብሔር የተሰጠንን ቅዱሱን መጽሐፍ የእምነት ትምህርታችን ብቸኛ ማስረጃ አድርጎ መጠቀም እጅግ የተባረከ መንገድ ነው፡፡ ከቅዱሳት መጻሕፍት አንዳንድ ክፍሎችን በመውሰድ በትክክል የሚናገሩትን እውነት ሳይሆን አጣምሞ በመተርጐም የተዘጋጁ የእምነት መግለጫዎች የእምነት መመሪያ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ከጌታ ዘንድ የተሰጠ እውነተኛ አስተማሪ መጽሐፍ ቅዱስን እንጂ እነዚህን የእምነት መግለጫዎችንም ሆነ ሌሎች ድርሰቶችን በማስረጃነት አይጠቀምም፤ እንዲያውም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚቃረኑ መጻሕፍት የያዙትን በእግዚአብሔር እውቀት ላይ የሚነሣ የሰው ሐሳብ በተረዳው የእውነት ቃል እያፈረሰ ያገለግላል (2ቆሮ.10፡5)፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የክርስቶስንና የሐዋርያትን ትምህርት የያዘ መጽሐፍ በመሆኑ ከዚህ መጽሐፍ ብቻ የተገኙ ትምህርቶችን የሚያስተምር አስተማሪ ለተጠሙት ሁሉ ውኃውን ከምንጩ እየቀዳ የሚያጠጣ ሰውን ይመስላል፡፡ በተለያዩ የሰው አሳቦች አመለካከቶች ያልተበከሉ ትምህርቶችን ማስተላለፍ የሚቻለው መጽሐፍ ቅዱስን ብቸኛ መመሪያ በማድረግ ነው፡፡ አስተማሪዎች መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ቃል የያዘ መጽሐፍ መሆኑን አምነው የሚናገረውን ቃል በትክክል ከተረዱትና በሚገባ ካወቁት በኋላ ሊያስተላልፉ ይገባቸዋል፤ ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ሲጽፍለት «የእውነትን ቃል በቅንነት (በትክክል) የሚናገር የማያሳፍርም ሠራተኛ ሆነህ የተፈተነውን ራስህን ለእግዚአብሔር ልታቀርብ ትጋ፡፡» ብሎአል (2ጢሞ.2፡15)፡፡ ስለሆነም አስተማሪ የእውነትን ቃል በቅንነት ማለትም በትክክል ወይም በአግባቡ ለይቶ ለመናገር ይችል ዘንድ በግሉ ከጸሎት ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በማስተዋል ሊያጠና ይገባዋል፡፡ በዙሪያችን ብዙ ክፉና ሐሰተኛ የሆኑ ትምህርቶች በበዙበት በዚህ ዘመን ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቦች በማይናገሩት ሐሳብ ላይ እየተጠቀሱ ስለሆነና ብዙ አማኞችም ትክክለኛውን እውነት ለይቶ የሚነግራቸው እውነተኛ አስተማሪ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ አስተማሪዎች የእውነትን ቃል ለይተው በመረዳት ለይተው መናገር ይገባቸዋል፡፡ በዚህም የሚተጉ ከሆነ የማያሳፍር ሠራተኛ ሆነው ጌታን ማገልገል ይችላሉ፡፡
አስተማሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ለማስተማር ሰው እንዲያሰማራቸው ወይም እንዲመድባቸው የሚያስተምሩትን የትምህርት ርእስም በፕሮግራም አውጪዎች እንዲወሰንላቸው መጠበቅ የለባቸውም፡፡ በተሰጣቸው ጸጋ መሠረት ለሚያገለግሏቸው ሰዎች በጊዜው አስፈላጊ የሆነውን ትምህርት የእግዚአብሔር መንፈስ እንደመራቸው መርጠው ከተገልጋዮቹ ጋር በተስማሙበት ጊዜና ቦታ ተገኝተው የማስተማር አገልግሎታቸውን ሊሰጡ ይገባቸዋል፡፡ የሚያስተምሯቸው አማኞች የጌታ ደቀመዛሙርት እንደሆኑ እንጂ የእነርሱ ደቀመዛሙርት አለመሆናቸውንም ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ ስለሆነም አስተማሪዎች በሰርተፊኬት ወይም በዲፕሎማ ለማስመረቅ ብለው የሚያስተምሩ መሆን የለባቸውም፡፡ የማስተማር አገልግሎት ዋነኛ ግቡ የሚማሩት (የሚገለገሉት) ሰዎች የእግዚአብሔርን እውነት በይበልጥ ያውቁና ይረዱ ዘንድ በልባቸውም የነበሩ ጥያቄዎች ተመልሰውላቸው በጌታ ያርፉ ዘንድ ከስህተትና ከሐሰት እንዲሁም ከክፉ ትምህርቶችም ይጠበቁ ዘንድ ማስቻል ነው፡፡ ይህን ውጤት ማስገኘት የሚችል የማስተማር አገልግሎት ለዚህ ዘመን አማኞች በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡ እንደ አንድ የሙያ ትምህርት በኮርስ መልክ ተምሮ የወረቀት ማስረጃዎችን መቀበል በሕይወት ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም፤ እንደዚህ ዓይነት የማስተማር አገልግሎት የተኰረጀው ከዓለማዊ አሠራር ነው እንጂ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰደ አይደለም፡፡
የጌታ ደቀመዛሙርት ለሆኑም ሆነ ላልሆኑ ሰዎች የሚቀርቡ ትምህርቶች የሚገለገሉት ሰዎች በወቅቱ የሚያስፈልጋቸውን ርእስ ወይም ያልተረዱትን እውነት የሚገልጽ ቢሆን መልካም ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን በተለያዩ አርእስት እየከፋፈሉ በሚገለገሉ ሰዎች የመቀበል አቅም መሠረት ለመረዳት በሚያስችልና በቀላሉ በሚገባ መልክ ማስተማር አስተማሪዎች ሊያገለግሉ የሚችሉበት አንዱ መንገድ ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን የነበረውን የማስተማር አገልግሎት ሲገልጽ «ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ንስሐንና በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ለአይሁድና ለግሪክ ሰዎች እየመሰከርኩ በጉባኤም በየቤታችሁም አወራሁላችሁና አስተማርኋችሁ እንጂ ከሚጠቅማችሁ ነገር አንዳች ስንኳ አላስቀረሁባችሁም» ብሏል (የሐ.ሥ.20፡20)፡፡ ለአይሁድና ለግሪክ ሰዎች፣ ማለትም ለማያምኑ ሰዎች የሚያስፈልጉትን ሁለት ትምህርቶች፣ ንስሐንና በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ያስተምር እንደነበር ከንባቡ እንረዳለን፡፡ እንዲሁም በዕብ.5፡11-14 ላይ የእግዚአብሔርን እውነት የሚናገሩ ትምህርቶች «ወተት» እና «ጠንካራ» ምግብ ተብለው በደረጃ ለሁለት ተከፍለዋል፡፡ በዚህ ክፍል ወተት የተባለው «አንድ ሰው ስለ እግዚአብሔር ቃላት መጀመሪያ ያለው የሕጻንነት ትምህርት» ሲሆን (ቁ12)፣ «ጠንካራ ምግብ» የተባለው ደግሞ «መልካሙንና ክፉውን ለመለየት በሥራቸው የለመደ ልቡና ላላቸው ለፍጹማን ሰዎች» የሚሰጥ ትምህርት ነው (ቁ.14)፡፡ ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን በተለያዩ ርእሶች እየመደቡ በየደረጃው ማስተማር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ልምድ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ይህ ግን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን በተለይ በአንድ የትምህርት ዓይነት ባለሙያ ለማድረግ ከማሠልጠን በእጅጉ የተለየ ነው፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ለአማኞች ሁሉ የሚያስፈልግ የሕይወት ትምህርት ነው እንጂ ለሚያገለግሉ ብቻ ወይም ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ የሚሰጥ የሙያ ትምህርት አይደለምና፡፡
አስተማሪዎች ምንም እንኳ የጠለቀው የእግዚአብሔር ቃል እውቀት ቢኖራቸውም በዚህ እውቀታቸው መመካትና መታበይ የለባቸውም፡፡ የሚታበዩ ከሆነ ግን እንደ ማንኛውም የዓለም እውቀት ስለ እግዚአብሔር ያውቃሉ እንጂ እግዚአብሔርን ያውቃሉ ማለት አይቻልም፤ ሰው እግዚአብሔርን እያወቀ በሄደ ቁጥር የራሱን ታናሽነት እያየ ስለሚሄድ የበለጠ ትሑት እየሆነ ይሄዳል እንጂ አይታበይም፡፡ አስተማሪዎች ከጌታ ከኢየሱስ ፍጹም ትህትናን ይማራሉ (ማቴ.11፡28)፡፡ ይህም ትህትና ከጌታ የተሰጡ የእውነተኛ አስተማሪዎች ምልክት ነው፡፡ እነዚህ እውነተኛ አስተማሪዎች «መምህር» ወይም «ሊቃውንት» ተብለው መጠራትን የሚጸየፉ ናቸው፤ ምክንያቱም ጌታ ኢየሱስ ሲያስተምር «.. .. እናንተ ግን መምህር ተብላችሁ አትጠሩ መምህራችሁ አንድ ስለሆነ እናንተም ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ.. .. .. ሊቃችሁ አንድ እርሱም ክርስቶስ ነውና ሊቃውንት ተብላችሁ አትጠሩ» ብሎ ለተናገረው ቃል ይታዘዛሉና (ማቴ.23፡8-10)፡፡